2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች

መግቢያ

የዚህ መጽሐፍ ዓላማ

  1. ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ዘመን አስተምሯቸው ነበርና:-
    1. መጨረሻው ዘመን አሁን ነው በማለት ደምድመዋው ነበር ከመከራቸው የተነሳ
    2. ከስራቸው በመልቀቅ ስራ የማይሰሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ
  2. የጻፈውም ጳውሎስ ሲሆን በአገልግሎቱ አብረውት ወደዛ ሄደውም የነበሩትን ስልዋኖስንና ጢሞቴዎስን ይጠቅሳል
  3. ይህች ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው በሐዋርያት ሥራ 17 መሰረት በሁለተኛው የጳውሎስ የወንጌል ጉዞ ላይ ነበር::  ስትመሰረትም ብዙ ተቃዋሚዎች ነበሯት ሌላ ንጉስ አለ ብሎ የሮምን ሕግ ጥሷል በሚል ክስ ተነስቶ ነበር::  የቤተክርስቲያኒቷም ምዕመናን በብዛት አሕዛብ ናቸው::
ምዕራፍ 1 ንባብ

ምዕራፍ 1

ፍቅራችንና እምነታችን ይጨምር

2ኛ ተሰሎንቄ 1:1-4
1፤ ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤2፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን።3፤ ወንድሞች ሆይ፥ እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ ስለሚበዛ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን፤4፤ ስለዚህ በምትታገሱበት በስደታችሁና በመከራችሁ ሁሉ ከመጽናታችሁና ከእምነታችሁ የተነሣ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን።

ትልቁ የዝች ቤተክርስቲያን በመከራ ውስጥ የመጽናትን ሚስጥር ብንመረምር ፍቅራቸው፤ መጽናታቸውና እምነታቸው ነበረ:: እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ ስለሚበዛ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን፤ የሚገርመው ነገር እምነት የሚያድግ ነው ምክንያቱም ትላንትናን በመከራ ያሻገረን ዛሬም ያሻግረናል ብለው በማለት እምነታቸው እያደገ ሄዷል:: ሌላው የርስ በርስ ፍቅራቸው ደግሞ እየበዛ ነው የሄደው::  በመጽናታቸው ምክንያት ምስጋና በዝቷል ለእግዚአብሔር:: ይህም በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን ይላቸዋል::  በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ በመቆማችሁ ተመክተናል ለሌሎችም ምሳሌ ሆናችኃል እያለ ነው::

ዛሬ በህይወታችን ምን የሚታይና የሚያስመሰግን ነገር ይኖር ይሆን?  ዕለት ዕለት ፍቅራችንና እምነታችን እያደገ መሄድ አለበት እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።  ስለዚህ እምነታችን በስራም መገለጥ አለበት ልክ እንደ ተሰሎንቄ ሰዎች እርስ በርሳቸው መዋደዳቸው ሚስጥሩ በስራ የተገለጠ እምነት የመኖሩ ጉዳይ ነው::  ወንድማችን ተቸግሮ ብናይ የሚረዳ ፍቅር ሊኖረን ይገባል::   እንደዚህ እምነታችን ሊያድግ ይገባዋል ማለት ነው:: በምንም ነገር ውስጥ ብናልፍ እንኳን እረኛችን ከእኛ ጋር ነውና እንጽና እርሱ የታመነ ነውና ያሻግረናል::  አሜን!


ብድራትን እንቀበላለን

2ኛ ተሰሎንቄ 1:5-8

5፤ ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቈጠሩ ዘንድ፥ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው።6-7፤ ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።8፤ እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤
መቼም በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ብሎ እንቅጩን ነግሮናል ጌታ ስለዚህ እንደው አንዳች እንደደረሰብን አድርገን እራሳችንን አናስጨንቅ የሚረዳንን ጸጋ እንጠይቅ::  እዚህጋ ጳውሎስ ከአሳዳጅነት ልምዱ ነው የሚነግራቸው እርሱን እየመሰላችሁ ከተከተላችሁት መሰደድ አይቀሬ ነው ምክንያቱም የጸኑትን መንቀል ያልጸኑትንም ይነቅላልና::  እርሱ ሲያሳድድ የነበረው ከመለወጡ በፊት እንደነዚህ አይነት ምስክርነት ያላቸውን ነበርና::  ስለዚህ እዚህጋ እያለ ያለው የህይወት ፍሬ ቢታይባችሁ ነው መከራው የበዛው በርቱ ጌታ ይመጣል::  ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ የሚሆነው:-

1.  መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ 

2.  መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።

3.  እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤


ለእኛ ዕረፍትን ይሰጠናል የአባቴ ብሩካን ወደ እረፍታችሁ ግቡ ብሎ ስለዚህ:- ይህ ቀን በእርግጥ እንዲመጣ አውቀን እንጽና::  መቼም እየደረሰብን ያለው ፈተና እዚህጋ ከምናነበው ለየት ያለ የዘመነ ነው::  እናስተውል ሁሉ ያልፋልና ጸንተን ጌታን እንጠብቅ:: ጌታ በእርግጥ ይመጣል!!የበደሉንም ሆኑ ያልተቀበሉትን ጌታ ይበቀላል ከዚህ ጥፋት ከእግዚአብሔርም ቁጣ አምልጠናልና ጌታን እናመስግን::

ማራናታ!!


ስሙ በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ

2ኛ ተሰሎንቄ 1:9-12

9-10፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።11-12፤ ስለዚህም ደግሞ እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥ አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ የእምነትንም ሥራ በኃይል ይፈጽም ዘንድ ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን።

በመስቀል ላይ ዋጋ እየከፈለ ሳለ አሻግሮ ፍሬውን እኔን/አንተን/አንቺን ያይ ነበር ጊዜው ደርሶ ሊወስደን ሲመጣ ደግሞ ይገረምብናል:: ደስ አይልም ፍሬውን አይቶ ማመን አቅቶት ሲገረም በእኛ? ወይ ያ ቀን ምን አይነት ቀን ነው ጌታ እየተገረመ የሚያስተናግደንና የሚደነቅብን? አረ በደስታ እጠብቀዋለሁ ቅዱሳን ከሚለው ማኅበር የቀላቀለኝን ጌታ:: ዛሬ በዙሪያዬ ያለው ሰልፍ ምንድነው? ከዛ ክብር ጋር ሲወዳደር?! ምንም እንዳልሆነ እንቀዋለሁ::

ዛሬም እላለሁ ማራናታ!

በሌላው በኩል ደግሞ:- እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።
ዛሬ ቀን ሳለ ለዚህ ጥሪ መልስ የማይሰጥ በዘላለም ጥፋት ይቀጣል። ለዘላለም ከጌታ መለየት ጥርስ ማፋጨትና መቆጨት ነው የሚሆነው:: እኛ የክርስቶስ ወንጌል የገባን ወንጌሉን ለማድረስ እንሩጥ:: በምድር የመቆየታችን ትልቁ ዓላማ እንደነዚህ ያሉትን እንድንታደግ ነውና ጸጋው ይረዳናል ወጥተን የጠላትን ደጅ ወርሰን የጌታን አዳኝነት እናውጅ:: ጌታ የሟቹን ሞት አይወድምና ሁሉም እንዲድኑ ይፈልጋል::

እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ (እናስተውል በጸጋው ነው)

  1. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር
  2. እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥
  3. አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ ስለ እናንተ ሁልጊዜ ይህንን እንጸልያለን ይላል:-

እኛም ይህንን ለራሳችንም ለቅዱሳንም ሁሉ እንጸልይ:-

  1. የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ በእኛ እንዲሞላ
  2. የእምነትንም ሥራ በኃይል ይፈጽም ዘንድ – በእኛ መስራት የጀመረውን እንዲፈጽም::

አሜን ይሙላን የጀመረውንም ይፈጽም!!


ምዕራፍ 2

ምዕራፍ 2 ንባብ

እውነትንና ፍቅርን እንከታተል

2ኛ ተሰሎንቄ 2:1-12


1-2፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል፡ ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን።3፤ ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና።4፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው።5፤ ገና ከእናንተ ጋር ሳለሁ፥ ይህን እንዳልኋችሁ ትዝ አይላችሁምን?6፤ በገዛ ራሱ ጊዜም ይገለጥ ዘንድ፥ የሚከለክለውን አሁን ታውቃላችሁ። 7፤ የዓመፅ ምሥጢር አሁን ይሠራልና፤ ብቻ ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ አሁን የሚከለክል አለ።8፤ በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል፤9-10፤ ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው።11-12፤ ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።

እየሱስ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ሁለት ነገሮች መሆን አለባቸው:-

  1. ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና።
  2. እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው።

ስለዚህ እነዚህ ምልክቶች ከመሆናቸው በፊት አይመጣምና አንናወጥ ደግሞም አንዘናጋ:: ብዙ ዓመት በፊታችን እንዳለ እናቅድ አንድ ቀንም እንደቀረው የተዘጋጀን እንሁን:: ጌታችን ሲመጣ በአፉ እስትንፋስ የሚያጠፋው እንደሆነም እንገንዘብ አሁንም እየሰራ ያለ ግን እንደወደደ እንዳይገለጥ እየተከለከለ ነው:: ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት:-

  • በተአምራት ሁሉና
  • በምልክቶች
  • በሐሰተኞች ድንቆችም
  • በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። ውስጣቸው ለክፋት የተከፈተ ነው:: የሚያምኑትንም እንኳን የሚያስት ነውና ስር ሰደን በቃሉ እንኑር:: ማንም እንዲጠፋ እግዚአብሔር አይፈልግም::

ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል። ሰው እውነትን በገፋ መጠን ለስህተት አሰራር በራሱ ሀሳብ ተስቦ ባርያ ይሆናል ስለዚህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ እንደሚል ቃሉ ውስጣችንን በዚህ እንሙላና እውነትንና ፍቅርን እንከታተል::


ጸንታችሁ ቁሙ


2ኛ ተሰሎንቄ 2:13-17


13፤ እኛ ግን፥ በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፥ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤14፤ ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ።15፤ እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ።16-17፤ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የወደደን በጸጋም የዘላለምን መጽናናት በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ።

እነዚህ ሰዎች ምስጋናን ለእግዚአብሔር እንዲበዛ አድርገዋል:: እኛ ግን፥ በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፥ ለምንድነው ለማመስገን ግድ የሚላቸው?

እግዚአብሔር :-
– በመንፈስ መቀደስ
– እውነትንም በማመን
– ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤
– በወንጌልም ጠርቷችኃልና
እናንተም ጸንታችኃልና ስለዚህ እናመሰግናለን ይላቸዋል::

ስለዚህ በዚህ መዳን እንዴት እንኑር:-
እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥

  1. ጸንታችሁ ቁሙ፥ ባለመናወጥ
  2. በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ እንድትጸኑ::

ይህንን ያወቅነውን እውነት ይዘን ለሚደርስብን ስደት ማን ይረዳናል ብለን ብንል:-
ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የወደደን፥ በጸጋም የዘላለምን መጽናናት፥ በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ። አሜን!

በነገር ሁሉ የሚረዳ ጌታ አለን በእርሱ ላይ እንደገፍ ሊረዳን የታመነ ነው:: በውጣ ውረዱ ሁሉ ያጸናናል ይታደገንማል በራሱ አሰራር:: ማጽናትና ማጽናናት ብቻ ሳይሆን በዚህ ዓለም ስንኖር በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ይደግፈናል::


ምዕራፍ 3

ምዕራፍ 3 ንባብ

ጌታ የታመነ ነው

2ኛ ተሰሎንቄ 3:1-5


1-2፤ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጌታ ቃል እንዲሮጥ በእናንተም ዘንድ ደግሞ እንደሚሆን እንዲከበር፥ እምነትም ለሁሉ ስለማይሆን ከዓመፀኞችና ከክፉዎች ሰዎች እንድንድን ስለ እኛ ጸልዩ።3፤ ነገር ግን የሚያጸናችሁ ከክፉውም የሚጠብቃችሁ ጌታ የታመነ ነው።4፤ የምናዛችሁንም አሁን እንድታደርጉ ወደ ፊትም ደግሞ እንድታደርጉ ስለ እናንተ በጌታ ታምነናል።5፤ ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው።

የጸሎት ርዕስ ይሰጣል ጳውሎስ የጌታ ቃል እንዲሮጥ እንዲሁም ደግሞ በእናንተም ዘንድ እንደተከበረው በሌላም ስፍራ እንዲከበር:: የጸሎት ርዕሱ ስለራሱ አይደለም ስለጌታ መንግስት እንጂ ይሄ ነው ጳውሎስን በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ እንዲጸና ያደረገው እራሱን አለማየቱ እንጂ እኮ ተስፋ ቆርጦ በቃኝ ይል ነበር:: ከክፉ ሰዎች ሰይጣንም እየነዳ ከሚያመጣብን እንድንጠበቅ ጸልዮ ይላል:: ጌታም እኮ ይህንን ብሎናል ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ:: አይደል ለራሳችንም ለቅዱሳንም መጠበቅ እንጸልይ::
ጌታ የታመነ ነው

  1. ያጸናናል – እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ እንደሚል ጌታ የታመነ ነው ማንም ያላየውን አይቶ ጣልቃ ይገባል ስለዚህ ሁልጊዜ አይናችን በእርሱ ላይ ይሁን በሚያጸናን ላይ::
  2. ይጠብቀናል– ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። ብሎ ጌታ ስለእኛ ማልዷል:: እርሱ ሊጠብቀን የታመነ ነው::

የተሰሎንቄ ሰዎች ልብ የሚጣልባቸው ነበሩ አሁንም ሆነ ወደፊት የምንላችሁን ትታዘዛላችሁ ይላቸዋል እኛም ዛሬ የምንሰማና የምንታዘዝ እንሁን::

ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና እንደሚል:- ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው። ለሰው ከባድ የሆኑ ነገሮች ቢኖሩ ያለምክንያት መውደድና የበዛ ትዕግስት ናቸው:: እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪልክ ዓለምን ምንኛ እንደወደደ እንገንዘብ:: ክርስቶስ በመስቀል እንዴት እንደታገሰ እናስብ:: እኛ አንችልም ይህ ግን በውስጣችን ያለው የጌታ መንፈስ ፍሬ ነውና እርሱ ራሱ በእኛ ውስጥ ይፈጥረዋል:: አሜን ልባችንን ያቅና::


የእግዚአብሔር ቤት ስርዓት አለው

2ኛ ተሰሎንቄ 3:6-18
6፤ ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።7፤ እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ ራሳችሁ ታውቃላችሁና፤ በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዓት አልሄድንምና፤8፤ ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፥ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም።9፤ ይህም እኛን ልትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁ ዘንድ ነበር እንጂ፥ ያለ ሥልጣን ስለ ሆንን አይደለም:: 10፤ ደግሞ ከእናንተ ጋር ሳለን፦ ሊሠራ የማይወድ አይብላ፡ ብለን አዘናችሁ ነበርና።11፤ ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና።12፤ እንደነዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን እንመክራቸውማለን።13፤ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ።14፤ በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ተመልከቱት፥ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ።15፤ ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት።16፤ የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።17፤ በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው፤ የመልእክቴ ሁሉ ማስረጃ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ።18፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

የእግዚአብሔር ቤት ለሁሉ ነገር ስርዓት አለው እንዴት ህይወታችንን መምራት እንዳለብን ቃሉ ይመክረናል:: ቃሉን ካላወቅን ግን ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል እንደሚለው እንዳይሆንብን ቃሉ በሙላት በእኛ ዘንድ ይገኝ:: ይህንን የእግዚአብሔርን ቤት ስርዓት ከማይከተሉ ጋር እንዴት እንኑር ብለን ያልን እንደሆነ መለየትና አለመተባበር ብቻ ነው የሚያዘን:: መለየትን ወይም ደግሞ አለመተባበርን ስናስብ ጠላትነት ማለት እንዳልሆነ እንገንዘብ:: ስንለይ ይህ ሰው ተምሮና ተስተካክሎ እንዲመለስ ነውና በፍቅርና በየዋህነት ገስጸን እናቅና::

የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። አሜን

ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን!



Published by Betty & Abera

We’re dedicated to share God’s goodness and mercy through His word!

2 thoughts on “2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች

Leave a comment