መግቢያ
የዚህ መጽሐፍ ዓላማ
ጳውሎስ ከዚህ ከተማ ሲያሳዱት ነው ከተማውን ለቆ የወጣው አገልግሎቱም ለሶስት ሳምንት ነበር ሐዋ 17:2:: በጣም አጭር ጊዜ ስለነበረ ያገለገላቸው ያሉበትን ለማወቅ ነበር የጻፈው በሐዋርያት ሥራ 16:40 እስከ 17:10 ማየት ይቻላል:: ጳውሎስ አብረውት ያገለገሉትንም ወንድሞች ስም በደብዳቤው ላይ አስገብቷቸዋል::
ምዕራፍ 1
ወንጌላችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንጂ በቃል ብቻ አይደለም
1ኛ ተሰሎንቄ 1:1-5
1፤ ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። 2-3፤ በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥ የእምነታችሁን ስራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤4፤ በእግዚአብሔር የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ተመረጣችሁ አውቀናልና።5፤ ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።
እዚህ ጋር ጳውሎስ እንዴት ስለእነሱ እንደሚያመሰግኑ እየነገራቸው ነው:: በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥
1. የእምነታችሁን ስራ
2. የፍቅራችሁንም ድካም
3. በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤
በእግዚአብሔር የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ተመረጣችሁ አውቀናልና።
ወንጌላችን:-
በኃይልና
በመንፈስ ቅዱስ
በብዙ መረዳትም እንጂ
በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ። እነጳውሎስ ማገልገል የቻሉት ጥቂት ጊዜ ቢሆንም እንኳን በመካከላቸው መንፈስ ቅዱስ መረዳትን ሰቷቸው ነበርና ወንጌልን እንደሚገባ ይዘው ነበር:: ዛሬም እኛ የሚያስፈልገን ከወይኑ ግንድ ጋር መጣበቅና ህያው የሆነውን ወንጌል መኖር ነው:: ወንጌል የሚሰራ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም በድንቅና ተአምራትም የተሞላ ነው:: አሜን!
ጌታን መምሰል
1ኛ ተሰሎንቄ 1:6-10
6፤ ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤7፤ ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው።8፤ ከእናንተ ወጥቶ የጌታ ቃል በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አልተሰማምና፥ ነገር ግን ምንም እንድንናገር እስከማያስፈልግ ድረስ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል።9-10፤ እነርሱ ራሳቸው ወደ እናንተ መግባታችን እንዴት እንደነበረ ስለ እኛ ይናገራሉና፤ ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥ ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።
ወንጌልን በብዙ መከራ እንደገናም ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀበሉት:: የተቀላቀለ ስሜት ያለው ነው የሚመስለው አይደል? መከራና ደስታ? የእግዚአብሔር መንፈስ ያስችላል ጸጋንም ይሰጣል:: ዛሬም ይህ መንፈስ በደስታ ይሙላን! አሜን!
ጳውሎስ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ ይላል እዚህጋ እንደምናየው ይመሰክርላቸዋል እኛንና ጌታን መስላችኃል ለሌሎችም ምሳሌ ሆናችኃል ይላቸዋል:: እኛስ ጌታን እንመስል ይሆን? በስፍራው ሁሉ ምንም መናገር እስከማያስፈልገን ድረስ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል:: በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ እምነታችን ለሰው ሁሉ ይታያልና ለጌታም ክብርን ያመጣልና ጌታን እንምሰል::
ወደ እናንተ የገባነው እንዴት እንደነበረ ታውቃላችሁ ከብዙ እንግልትና ድብደባ ሸሽተው ነበር የመጡት በሌላ አነጋገር ደካማ በሚመስል ጌታ ግን ሲሰራ በድካማቸው የተፈጠረው:-
1. ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥
2. ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥
3. ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።
እኛም ዛሬ ይህንን ህያው ጌታ እናገለግላለን፥ የእርሱን ከሰማይ መገለጥ እንጠባበቃለን፥ ወደ ጣዖትም አንመለከት እኛ የህያው እግዚአብሔር ልጆች ነን:: አሜን!
ምዕራፍ 2
የወንጌል አደራ
1ኛ ተሰሎንቄ 2:1-9
1፤ ወንድሞች ሆይ፥ ራሳችሁ ወደ እናንተ መግባታችን ከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና።2፤ ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን።3፤ ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኵሰት ወይም ከተንኰል አልነበረምና፤4፤ ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም።5፤ እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም 6፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።7፤ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤8፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።9፤ ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን።
በፊልጲስዮስ መከራ ቢቀበሉም ቢንገላቱም እንኳን ከረጅም የመንገድ ጉዞ በኃላ ወደ ተሰሎንቄ መተው እንደገና ተስፋ ሳይቆርጡ ምን ይመጣብን ይሆን ሳይሉ ቁስላቸውም ሳይደርቅ ወንጌልን ለመስበክ ደፈሩ:: በሚገርም ሁኔታ ፍሬን አፍርተው ከዚህም ስፍራ ተባረሩ::
ተስፋ ባለመቁረጥ ወንጌልን የሚሰብኩበት ምክንያት:-
1. እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ – የሚያጸናንና አብሮን የሚሰራ አለ የታመንን ሆነን እንገኝለታለን በፊቱ::
2. ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም – የእነሱ ግብ ጌታን ደስ ማሰኘት ብቻ ነው ሰውንማ ቢሆን ማስደሰት የሚፈልጉት ቀላል ነበር እኮ አለመስበክ ወይንም መሸቃቀጥ ለሁሉ የሚመች ማድረግ ነበር::
ወንጌልን ማገልገል የሚያካትተው ነገር:-
- የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ – ያለ ስስት ሁሉን ሰተን ማገልገል ይጠይቃል ጌታ እኮ ዙፋኑን ጥሎየባርያን መልክ ይዞ ነው ያገለገለው::
- ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና – በፍቅር ነው ሁሉንም መስጠት የሚቻለው
እንዲያውም በማንም እንዳይከብዱ እየሰሩ ራሳቸውንም ይችሉ ነበር::
ከዚህ የምንረዳው ጌታ የታመንን ሆነን ተቆጥረናልና ስናገለግል በፍቅር፥ እኛነታችንን በማካፈልና ባለመታከት መሆን አለበት::
ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ተጠርተናል
1ኛ ተሰሎንቄ 2:10-20
10፤ በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ 11-12፤ ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና። 13፤ ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።14፤ እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና። 15፤ እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥16፤ ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል።17፤ እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤18፤ ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን።19፤ ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? 20፤ እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።
በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ
- ቅድስናና
- ጽድቅ
- ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተም እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ ይላል ጌታን ከአወቅን በብርሃን እንመላለስ እንዲህ ነው መመላለስ ያለብን:: በኑሮ ልንገልጠው ይገባል::
ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና። እኛ እኮ የተጠራነው ወደ መንግስቱና ወደ ክብሩ ነውና እንደሚገባ እንመላለስ::
እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥
በእውነት እንዳለ
በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ
እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ
እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት
እኛስ ዛሬ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚሰራ ቃል ተቀብለን ልንመላለስበት ይገባል::
ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና:: ወንጌል ወደኛ እንዳይደርስ ምን ያህል አይሁዶች እንደተከላከሉና እንዴት ያለ ዋጋ እየተከፈለ እኛጋ እንደደረሰ እናስተውል::
ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና። እኛም ላገለገሉን ክብር ያገለገልናቸው ደግሞ ለኛ ክብራችን ናቸው የምናገኘው ሽልማት በመምጣቱ ፊት ይህ ነው::
ምዕራፍ 3
በመከራ ስለመጽናት
1ኛ ተሰሎንቄ 3: 1-4
1፤ ስለዚህ ወደ ፊት እንታገሥ ዘንድ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ።2፤ ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤3፤ በዚህ መከራ ማንም እንዳይናውጥ፥ ለዚህ እንደ ተመረጥን ራሳችሁ ታውቃላችሁና።4፤ በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንቀበል ዘንድ እንዳለን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፥ ይህንም ታውቃላችሁ።
ጳውሎስ ልንታገስ ባልተቻለን ጊዜ የእግዚአብሔርን አገልጋይ ጢሞቲዎስን ላክን:: ያሉበትን የእምነት ይዘት ያውቁ ዘንድ አንድ ሰው ንስሀ ገብቶ ብቻ መለቀቅ የለበትም ክትትል ያስፈልገዋል:: ህፃን ተወልዷል በቃ ብለን ትተነው ብንሄድ ምን እንደሚፈጠር ማሰብ አይከብድም:: እንዲሁ ጳውሎስ ቢችል እራሱ ይጎበኛል አብያተ ክርስትያናን አለዚያም አንዳቸውን ይልካል ያሉበትን አውቆ በርቱ አልያም ይህንን አስተካክሉ ለማለት::
ጢሞቴዎስን የላከው ስለ እምነታቸው:-
- እንዲያጸናችሁ – መከራ በዝቶባችኃልና እንደምናስባችሁ እንድታውቁ ደግሞም እኛም እራሳችን በዛው መከራ ውስጥ እንዳለን እንድታውቁ እንጂ በእናንተ ላይ ብቻ የመጣ መአት አድርጋችሁ አትውሰዱ ስለዚህም በርቱ:: ጌታ እየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር አጽናኝ እንደሆነ ይናገራል:: እርሱ እራሱ ህዝቡን ያጽናናል::
- እንዲመክራችሁ – መምከር የጌታ ስራ ነው እየሱስ ድንቅ መካር ነውና ደግሞም የምክር መንፈስን ይሰጣል ያጸናን ዘንድ::
በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ብሎ ጌታ እንቅጩን ነግሮናል:: ቃሉ ሲዘራ ምን አይነት መሬት ላይ እንደወደቀ እኮ ይፈተናል በቃሉ ደስ ብሏቸው ለጊዜው ፈተና ግን ሲመጣ የማንጸና መሆን የለብንም:: ስር ሰደን እንመላለስ ምንም አይነት ፈተና ወደ እኛ ቢመጣ እረኛችን አይተወንም! እንበርታ::
ለጌታ መኖር
1ኛ ተሰሎንቄ 3:5-8
5፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ፦ ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል፡ ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ።6፤ አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ የምስራች ብሎ በነገረን ጊዜ፥ እኛም እናያችሁ ዘንድ እንደምንናፍቅ ታዩን ዘንድ እየናፈቃችሁ ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስቡን በነገረን ጊዜ፥7፤ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤8፤ እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና።
እዚህ ጋር ጳውሎስን ያሳሰበው ነገር ከእምነት ተንሸራተው ይሆን ልፋታችንስ ከንቱ ሆኖ ይሆንን? ነበር ስጋቱ ለምን ብለን ብንል እምነትን ሊፈትን ቢሆንለትም ወደኃላ ሊመልስ ፈታኝ ይመጣል ከተሰማው ቃል የተነሳ:: ጠላት እኮ ሌላ ምንም ግብ የለውም ቃሉን ከማስጣል በስተቀር ምክንያቱም ቃሉ ከእኛ ጋር በእምነት ሲዋሀድ ነው የሚሰራው አለበለዚያ ካላሳደገን ቃሉን ተነጥቀናል ማለት ነው:: ፈታኝ ሁልጊዜ ይመጣል ከቃሉ በኃላ ስለዚህ የሙጥኝ ብለን ህያው ቃሉን በልባችንም እናሰላስለው የእግዚአብሔር ቃል የሚሰራ ህይወትም የሆነ መንፈስም ነውና:: እነዚህ ሰዎች በፍቅርና በእምነት ጸንተው ነበረ:: መጽናታቸውም እንዴት ጳውሎስን ደስ እንዳሰኘውና እንዳጽናናው እናያለን:: ምክንያቱም እርሱ ህይወቱን ለጌታ ሰቶ ለራሱ መኖር ያቆመ ሰው ነበር በሚሄድበት ሁሉ ግድ የሚለው የአብያተ ክርስትያናት ጉዳይ ነው:: በህይወት የመኖሬ ትርጉም የጌታ ስራ መሰራቱና እናንተ ስር መስደዳችሁ ነው ይላቸዋል::
ዛሬም እኛ በቃሉ ስር ሰደን በእምነትና በፍቅር እየኖርን ጌታን ደስ እናሰኝ ምርኮንም እንሰብስብለት የሚያሳስበንም ነገር የአካሉ ጉዳይ ሊሆን ይገባል:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን! አሜን
ለጌታ ቀን የተዘጋጀን እንሁን
1ኛ ተሰሎንቄ 3:9-13
9-10፤ ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላበት ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እየጸለይን በአምላካችን ፊት ከእናንተ የተነሣ ስለምንደሰተው ደስታ ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር በእናንተ ምክንያት ምን ያህል ምስጋና እናስረክብ ዘንድ እንችላለን?11፤ አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅና፤12-13፤ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።
ጳውሎስ ሊያያቸው የሚፈልገው ማድረግ ካለብኝ ነገር የጎደለ ይኖር ይሆንን? ነው ሁልጊዜ በጭንቅላቱ የሚመላለሰው ያለውን ሁሉ እናም የሚያውቀውን ሁሉ ሊያሳውቃቸው ነው:: ምን አይነት ትጋት ነው? ጸንተው ቆመዋል ተብሎ ሲሰማ ደግሞ ምስጋናውን ያበዛል ለጌታ::
ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት
- በቅድስና
- ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥
- እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።
ልባችንን የሚያጸናው እርሱ ነውና እርሱን እንታመን እርሱም የታመነ ነው:: ዕለት ዕለት ፍቅራችን ያብዛ ይጨምርም::
ምዕራፍ 4
መቀደስ
1ኛ ተሰሎንቄ 4:1-3
1፤ እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን።2፤ በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና።3፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤
እዚህጋ ጳውሎስ ያስተማራቸውን ሲደግምላቸው እናያለን:: እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንዴት እንድትመላለሱ ከፊት ይልቅ አብዙት እንጂ ደርሰናል ይበቃናል አትበሉ:: ይህንን ጨምሩ ወይም አስተካክሉ ሲል አናይም ያስተማራቸውን ትምህርቶች በደንብ ጠንቅቀው እየኖሩበት ነው ግን አሁንም ያስተማርናችሁን ያዙ ብሎ በመደጋገም ይነግራቸዋል:: በዚህ ዘመን ሰው ስህተት የሚገባው እኮ አጭር መንገድ ወይም የተሻለ ትምህርት እያለ ነው እዚህጋ የሚያሳየን ግን የያዛችሁትን እውነት አብዝታችሁ ጠብቁ ነው የሚለው:: ለዚህም ነው በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና አይለወጥም አንድ ጊዜ የሰበኩት እውነት ማሻሻያ የለውም እኔ ከጌታ ተምሬዋለሁና ስለዚህ ማንም የተለየ ወንጌል ቢሰብክ የተረገመ ይሁን የሚለው ቃሉ::
ማደግ ከፈለግን በግልጽ ፈቃዱ ምን እንደሆነ ለእያንዳንዳችን በማያሻማ መልኩ እዚህ ክፍል ላይ ተጠቅሷል:: የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ መቀደስ ስንል ሁለት አይነት ነው:: አንደኛው እየሱስ ክርስቶስን ወደ ህይወታችን በጋበዝን ጊዜ ሁሉን ክደን ለጌታ ተለየን ወይም ተቀደስን:: ይህ ቅድስና የጸና የማይዋዥቅ ነው:: ዕብራውያን 10: 10፤ በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። እንዲሁም ወደ ኤፌሶን 4: 24፤ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።
ሁለተኛው እና ጳውሎስ የሚያነሳው እዚህጋ በስጋችን መቀደስን ያሳያል :: በዚህ ዓለም እስከኖርን ድረስ ልንኖረውና ወደውጪ ወቶ ደግሞ መገለጥና መታየት አለበት:: ይሄኛው ቅድስና የመዋዥቅን ነገር እንዳያሳይ ሁልጊዜ በአእምሯችን መታደስ በመለወጥ ደህንነታችንን ዕለት ዕለት እንኖረዋለን:: 1ኛ ቆሮንቶስ 6: 18፤ ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።
ለጌታ እንቀደስ!
ከዝሙት መራቅ
1ኛ ተሰሎንቄ 4: 4-7
4-5፤ ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤
6፤ አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል። 7፤ ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።
እኛ ከዓለም የተለየን ለእግዚአብሔር የምንኖር ነንና በቅድስና እንጂ እግዚአብሔር እንደማያውቁ መመላለስ የለብንም:: እነርሱ በአምልኮ ስፍራዎቻቸው እንኳን ዝሙትን ለማድረግ አይከለክሉም እንዲያውም ይበረታታሉ እኛ ግን ለጌታ ተቀድሰናልና አንድ ሴት ለአንድ ወንድ እንዲሁም አንድም ወንድ ለአንድ ሴት በትዳር ትስስር ውስጥ ብቻ የሚፈጸም አልጋውም ንጹ ተብሎ የተመሰከረለት በእግዚአብሔር የተመሰረተ ሕብረት ነው:: ዝሙትን እንጥላ ደግሞም እንሽሽ!
ጌታ የማይመቸው አንዱ ነገር ማታለል ነው:: እርሱ እውነት ነውና እውነትን ይወዳል እኛም እውነትን እንከታተል:: ስናታልል እግዚአብሔር ለእውነት ይቆምና ተበዳይን ይክሳል ያጠቃነው ሰው ሲለመልም እናያለን ማለት ነው::
እናስተውል ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። ለክብሩ እንቀደስ:: አሜን!
የጌታን ምክር እንስማ
1ኛ ተሰሎንቄ 4:8-12
8፤ እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ።
9፤ እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤
10-12፤ እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን።
ይህንን ምክር የማይሰማ ጳውሎስን አይደለም የገፋው መንፈስ ቅዱስን እንጂ ስለዚህ ቃሉን በሙሉ ክብሩ ልንወስደው ይገባል::
መዋደድን ከእግዚአብሔር ተምራችኃል ይላቸዋል:: ምን አይነት ፍቅር ነው ከእግዚአብሔር የምንማረው ፍቅር? ሲበደል ይቅር የሚል፥ ሲራብ የሚያበላ እንጂ እሳት ሙቅና ሂድ የማይል፥ ሲረግም የሚመርቅ እንዲህ አይነት ነው ከሱ የምንማረው ፍቅር:: የወደደ ደግሞ በብዙ ይጠነቀቃል ለወገኖች እንጂ አታላይ አይሆንም ለዚህ ነው በመካከላቸው ያለው ፍቅር በተግባርም የተገለጠ የሆነው:: ይህም ፍቅራቸው ደግሞ በሌላ ስፍራ ሁሉ ተሰምቷል:
ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥
በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥
የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን።
ማን ስራ ፈት ሆኖ እራሱንና ቤተሰቡን የማይረዳ መሆን ይፈልጋል? መልሱ ማንም ነው:: ሳንሰራ ስራ ፈት ሆነን ወንጌልን እንስበክ ብንል እንዳንተ መሆን አልፈልግም ነው ሰው የሚለው:: በተቻላችሁ መጠን እራሳችሁን ቻሉ ሌላውን እርዱ ያኔ የሚታይ ፍቅር ሲኖር ወንጌልም ሰሚ ያገኛል እያላቸው ነው:: በውጭ ባሉት ዘንድ በአግባብ እንመላለስ::
በጌታ እንጽናና
1ኛ ተሰሎንቄ 4:13-18
13፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን።
14፤ ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። 15፤ በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ 16፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ 17፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። 18፤ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።
ጌታ ከሙታን ተነስቷልና በእርሱ አምነው ያንቀላፉትም ይነሳሉ:: እኛ ተስፋ የሌለን አይደለንም በእርግጥ ልብን ያሳዝናል የምንወደውን ሰው በሞት መነጠቅ ግን እንደማያምን ለዘላለም እንደማናያቸው አድርገን ማየት የለብንም:: እኔ በራሴ ወደጌታ የሄዱ በጣም የምወዳቸው ሰዎች አሉኝ የምጽናናው ግን ሌላ አገር እንዳሉና አንድ ቀን ሄጄ እንደማያቸው ነው:: እንጽናና በዚህ ቃል! መንፈስ ቅዱስንም አናማርር!
ምዕራፍ 5
የብርሃን ልጆች ነን
1ኛ ተሰሎንቄ 5: 1-11
1፤ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ 2፤ የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። 3፤ ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም። 4፤ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥
5፤ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤ 6፤ እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ። 7፤ የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፥ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤ 8፤ እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤ 9፤ እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።. 10፤ የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ።. 11፤ ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው።
ለምን ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም ይላል? ማወቅ የለብንም እንዴ? አያስፈልገንም ምክንያቱም ሁልጊዜ የተዘጋጀን መሆን ስላለብን:: ጳውሎስ ብቻ አይደለም ይህንን ያለው እራሱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስም ብሏል:-
የማቴዎስ ወንጌል 24: 36፤ ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።
የሐዋርያት ሥራ 1: 7፤ እርሱም አለ፦ አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤
ሌላው ምክንያት ማወቅ የማያስፈልገን በብርሃን ውስጥ እየኖርን ነንና ማንም ስራው ትክክል ቢሆን ወደ ብርሃን እንደሚያመጣ ለማስፈተሽ እንዲሁ ኑሯችን በብርሃናት አባት በጌታ ፊት እየኖርን ስለሆነ ነው እንጂ እኛ በጨለማ የምንደናበርና የምንሄድበትን የማናውቅ አይደለንም:: እንደሌባ የሚሆንባቸው አመጣጡ በጨለማ ለሚመላለሱት ነው:: ለእኛ ግን ቀኑንና ወራቱን አወቅን አላወቅን ለውጥ የለውም የምንኖረው እኮ አሁን ከእርሱጋር ነው:: አሜን!
እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን እንዴት እንመላለስ ወይም ሊያሳስበን የሚገባው ነገር ምንድነው?!
- በመጠን እየኖርን በዚህ ላይ ደግሞ
- የእምነትንና
- የፍቅርን ጥሩር
- የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንልበስ
- እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።. እኛ የምንሸበር አይደለንም ምክንያቱም ቁጣ የለብንም አንድ ጊዜ የራሱ ልጆች አድርጎናል::
- የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ።. (ሞተንም ወደ እርሱ ብንሄድ ወይም በህወት እየኖርን ቢመጣና በደመና ብንቀበለው ለእኛ ለውጥ የለውም ከእርሱ ጋር እየኖርን ነውና ስለዚህ በዚህም ሆነ በዛ በዛች ቀን በደስታ እንገኛለን)
- ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው። የተሰጠን አገልግሎት መተናነጽ ነው::
እምነት፥ ፍቅር እና ተስፋ ጸንተው ይኖራሉ!
ማራናታ
የቤቱ ስርዓት
1ኛ ተሰሎንቄ 5: 12-14
12-13፤ ወንድሞች ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ።
14፤ ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።
በጌታ ቤት የሚያገለግሉትን አገልጋዮች ማወቅና ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን:: ግን እውነት እንነጋገርና በዚህ ዘመን የቤተክርስቲያን መሪዎች ይከበራሉ? እንደኔ እንደኔ የተመታ አገልግሎት ነው ባይ ነኝ ምክንይቱም ሁሉ ለራሱ መሪ ሆኖ እየተመላለሰ ያለበት ዘመን ነውና የአገልግሎቱንም ውጤት ስናየው እንደዛው የተመታ ሆኗል:: መሪ የሌለው ሰራዊት እንዴት ድል ያደርጋል?! ለጠላት ጥቃት በቀላሉ የተጋለጠ እንጂ ድልን ማሰብ ሞኝነት ይመስለኛል:: በሌላው ጎን ስናየው ደግሞ አንዳንድ መሪዎች ያላቸውን ሁሉ ሰተው ለማገልገል የሚፈሩም ያሉ ይመስለኛል:: ያላቸውን ሁሉ አውጥተው ካገለገሉ ምዕመናቸው አይመለስም አኩርፎ ይቀራል ወይም ሌላ ቤተክርስቲያን ይሄዳል እዛም አይጠቅም ወይ አያሰራ አይነት እንቅፋት ይሆናል:: ይሄንን ለማስተካከል ቀላል ያልሆነ ቁርጠኝነት ይጠይቃል ደግሞም እያንዳንዳችንን ይመለከታል:: ለምን ግን በፍቅር ከመጠን ይልቅ አክብሩዋቸው ተባልን?!
- የሚደክሙትን :- እውነተኛ አገልጋይ ጌታን በእኛ ለማየት ይደክማል፥ ያለውንም ሁሉ ሰቶ ያገለግላል፥ በምላሹ ምንም ባለመጠበቅ በነፃ የተሰጠውን በነፃ በመስጠት ይደክማልና::
- በጌታም የሚገዙአችሁን:- መሪዎችን ጌታ ይሾማል (በእርግጥ እራሳቸውንም የሚሾሙ ይኖራሉና) ፍሬያቸውን እያየን፥ ለቤቱ የሚያደርጉትን ድካም እያየን እንገዛ ከጌታ ተሹመዋልና::
- የሚገሥጹአችሁንም:- እውነትን በፍቅር በመያዝ ለሚገስጹን ጆሮ እንስጥ:: አጥፍተን ለምን ተገሰጽን ብለን አናፈንግጥ ትክክለኛ ተግሳጽ ያቀናልና::
እርስ በእርሳችን እንደ አካል ለመኖር እንዴት እንመላለስ?
- ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው:- ከላይ እንዳየነው መገሰጽም የአገልግሎት አካል ነው ግን ለተወሰኑ ሰዎች ግን የተተወ አይደልም የሁላችንም ኃላፊነት ነው:: ስርዓት ከሌለ በቅጡ የቤቱን ስራ በአንድ ወጥ መስራት ያስቸግራልና::
- ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው
- ለደካሞች ትጉላቸው፤
- ሰውን ሁሉ ታገሱ
- በሰላም ሁኑ
ጌታ በስራ ላይ እንዳለ እንወቅ፤ እናስተውል፤ እንፍራው፤ አንዳፈር ልክ እንደው እንደወደድን አንመላለስ እርሱን ደስ ለማሰኘት ከሆነ እንግድያስ እንደቃሉ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳናችንን እንፈጽም:: ጌታ ወደቤቱ የጠራው የተለያየ አይነት ሰው ነውና ሁሉንም በፍቅር፤ አንዳች የምማረው አለ በማለት ዝቅ ባለ ልብ እየተቀባበልን ልንመላለስ ይገባል::
የጌታ ጸጋና ማስተዋል ይብዛልን!
ምክር
1ኛ ተሰሎንቄ 5: 15-28
15፤ ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።
16፤ ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤. 17-18፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።
19፤ መንፈስን አታጥፉ፤ 20-21፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤
22፤ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ።
23፤ የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። 24፤ የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል። 25፤ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ። 26፤ ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። 27፤ ይህ መልእክት ለቅዱሳን ወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አምላችኋለሁ። 28፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።
እንደ ክርስቶስ ተከታዮች ጳውሎስ ይህን ይመክረናል:-
- ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።በሌላ ስፍራ ላይ በተለይ ለቅዱሳን ይላልና እርስ በእርሳችን እንረዳዳ:: ግራህን ለሚመታህ ቀኝህን ስጠው ብሎ አስተምሮናል ጌታ እየሱስ::
- ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ:- ደስታን የምናውቀው ለሆነልን መልካም ነገር የምንገልጽበት ስሜት ነው በሚል ነው እዚህ ክፍል ላይ ግን ትዕዛዝ ነው ምንም ይሁን ምን የከበበን በጌታ ነው ደስታችን መሆን ያለበት በሚያልፍበት ነገርና ሁኔታማ ቢሆን ኖሮ እንጉርጉሮ አውጡ ነበር ማለት የነበረበት ጳውሎስ ግን ደስ ይበላችሁ ይለናን:: መቼ ደስ ይበለን? ሁልጊዜ:: አሜን!
- ሳታቋርጡ ጸልዩ:- ጸሎት ለእኛ ስንበረከክ የምናስበው ሳይሆን የኑሮ ዘይቤያችን ነው ልክ እንደመተንፈስ:: ጌታ ሲያገለግል ይውልና ለሊቱን ሲጸልይ ያድራል ከሱ ይህንን ተምረናል::
- በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። በሁሉ አመስግኑ? ከባድ አይመስልም? ከባድ ነው ግን ያስጨነቀንንና የፈራነውን እያሰብን ወደ ጌታ ቀና ስንል ከማመስገን ሌላ ምን የሚቀርልን አለ? ሁሉ በእርሱ ፊት ኢምንት ነው:: በምንም ውስጥ እያለፍን እያለን እስኪ ማመስገን እንጀምር የእግዚአብሔር ጸጋ ያስረሳናል ደግሞም ብቃት ይሰጠናል:: እሳቱ አያቃጥልም ውሀውም አያሰጥምም ከጌታ ጋር ስንሆን የሚቀየረው ውሀው ወይም እሳቱ ሳይሆን እኛ ነን:: እሳቱ ሌላውን ሲያቃጥል ለእኛ ደግሞ የአምልኮ ቦታ ይሆናል:: ብናማርርና ብናጉረመርምስ? ነገሩን ጥሩ አድርጎ ጠላት እያጠበቀ ወደባሰ መከራ ነው የምንገባው ብናመሰግን ግን የምንጠቀመው እኛው ነን:: እናመስግን አምላካችን ትልቅ ስለሆነ::
- መንፈስን አታጥፉ፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ:- ትንቢትን በእግዚአብሔር ቃል እናበጥር እንጂ ትንቢትን አናርቅ ምክንያቱም እንድንጽናናበትና እንታነጽበት ዘንድ ተሰቶናልና እንጠቀምበት::
- ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ። የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። ደስ አይልም እኛን የሚቀድሰው እርሱ እራሱ ነው የኛ ድርሻ ራሳችንን ወደ እርሱ ማቅረብ ነው:: ለዚህም ነው ስለመምጫው ቀን መጨነቅ የሌለብን ቀድሶ እርሱ ያቆመናልና ምክንያቱም የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል ይለናል:: እኛ የብርሃን ልጆች ነን ከክፉ ጋር ህብረት የለንም:: ስለዚህ ሁለንተናችን (መንፈሳችን፤ ነፍሳችንና ስጋችን) ይቀደሳል ማለት ነው በስጋዬ እንደፈለኩኝ ልኑር ብሎ ነገር የለም::
- ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ። ጌታ እንደረዳን እርስ በርስ እንሸካከም በተለይም ስለአገልጋዮች እንድንጸልይ ያስፈልጋል እየተጠየቅንም ነውና እንጸልይ::

ጌታ ይባርክሽ።
LikeLike