የማርቆስ ወንጌል

የመጽሐፉ መግቢያ:- ይህ የወንጌል መጽሐፍ ከአራቱ መጽሐፍት አነስ ያሉ ምዕራፎችን የያዘና በተለይም ከአይሁድ ውጪ ያሉ አንባቢዎችንም ታሳቢ ያደረገ መጽሐፍ ነው::  ደራሲው ክፍሉ እንደሚለው ማርቆስ የተባለው በሌላ ስሙም ዮሐንስ የሚባል ነው የፃፈው:: ሐዋ 12:12 ላይ ጼጥሮስ ከእስር እንዳመለጠ ቅዱሳን ተሰብስበው ወደሚፀልዮበት ወደ እርሱ ቤት እንደመጣ ይነግረናል:: ማርቆስ ከጳውሎስም ከጴጥሮስም ጋር ያገለገለ ሰው ነው:: እንዲያውም ይህ መጽሐፍ በጴጥሮስ ስር ሆኖ ነው የፃፈው ይባላል::
ምዕራፍ 1

የማርቆስ ወንጌል 1: 1-8

1፤ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ። 2እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ። የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር። ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል። እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።

ማርቆስ ጌታ እየሱስን የእግዚአብሔር ልጅ ብሎ ይጠራዋል እንደዛውም ነው! አሜን!

በምድረ በዳ ስለሚጮኽ ሰው ድምፅ ይነግረናል ይህም ሰው ከጌታ በፊት የተላከና መንገዱን የሚጠርግ ነበር:: እርሱም ፍፁም ከብሉይ ስርአት ውጪ ነበር የሚሰብክና የማያደርገው:: ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ አይሁድ ለኃጢአት የሚያውቁት መስዋትን ማቅረብ ነበር:: እርሱ ግን ንስሀ ግቡና ተጠመቁ ነበር የሚላቸው ለመቀበል አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳን የዮሐንስን አወላለድና ህይወቱን ስለሚያውቁ ብዙዎች መተው ይጠመቁና ለሚመጣው ጌታ ይዘጋጁ ነበር:: በብሉይ ኪዳን አምልኮ እኮ የሚካሄደው በቤተ መቅደስ ነበር:: የሐጥያትም ስርየት ደም ሳይፈስ ስርየት እንደሌለ እያወቁ ግን ይሰሙትና የሚላቸውን ያደርጉ ነበር:: ዛሬም በህይወታችን ጌታ የላከንን በማድረግ ለተፈጠርንለት ስራ እንትጋ አንታክት:: ዮሐንስ ህይወት ከተለመደው ለየት ያለ ነው የግመል ጠጉር ይለብስና ወገቡንም በጠፍር ይታጠቅ ነበር:: አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር። ምንም አይነት ትስስር የለውም ነበር ከዓለም ጋር ምኑንም ይዘው ሊያስፈራሩት የማይችሉት ነበር:: ስለዚህም ይፈሩት ነበር::

ስለእየሱስም ሲናገር እያጎላ ይናገር ነበር እንጂ በምንም አይነት ክብርን ለራሱ አይወስድም ነበር:: ስለ ኢየሱስ ይል የነበረውም ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል:: እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር። ዛሬ ለዚህ ቃል እኛ ምስክሮች ነን::


ኢየሱስ ተጠመቀ

የማርቆስ ወንጌል 1: 9-13
9፤ በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። 10፤ ወዲያውም ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና፦ 11፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል፡ የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ። 12፤ ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው። 13፤ በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ ከአራዊትም ጋር ነበረ፥ መላእክቱም አገለገሉት። ጌታ ኢየሱስ ሲጠመቅ ሰማያትም ሲቀደዱ ታየ የኢሲይያስም ፀሎት ተመለሰ ኢሳይያስ 64: 1፤ ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! የሚለው:: አብም ስለእርሱ በድምፅ ከሰማያት ተናገረ:- የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል፡ የሚል:: እግዚአብሔር አብ በልጁ ደስ ተሰኝቷል ምክንያቱም የሰውን ልጅ ለመታደግ ታዞ ወደምድር መቷልና:: መንፈስም ወደምድረ በዳ እንደወሰደው እናያለን:: ከፍታ ላይ ነው ኢየሱስ ስለእርሱ አብ መስክሮለት ደስ ብሎት እያለ ፈተና መጣ:: ጠላት ደስታንና ከፍታን ሲያይ ሊጥል ይመጣል የተዘጋጀንና የነቃን በቃሉ የተመሰረትን ልንሆን ይገባል:: በፈተና ውስጥ ሆኖ ከአራዊት ጋር እንጂ ሰው እንኳን አብሮት አልነበረም መላእክት ግን አገለገሉት:: ይህ ሁሉ እኔን ለመታደግ ነው ያደረገው:: ስሙ ይባረክ!


የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች

የማርቆስ ወንጌል 1 : 14-15
14-15፤ ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፦ ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሐ ግቡ፡ በወንጌልም እመኑ፡ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።

ዮሐንስ ተላልፎ ከተሰጠ በኃላ እንደገደሉት እናውቃለን:: አገልግሎቱን ጨርሶ ሄደ እየሱስም አገልግሎቱን ቀጠለ:: እየሱስ ምን ሰበከ ወይም ምን ላይ አተኮረ ብለን ስንል የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከ እንደነበረ እናያለን እኛም በዚህ መሰረት ነው ወንጌልን ማድረስ ያለብን:-

  1. ዘመኑ ተፈጸመ – የዘመኑን መፈፀም ሁሉም ሰው በደንብ ያወቀበት ጊዜ ላይ ነን በዚህ ረገድ ምንም ጥያቄ የለም::
  2. የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች፤ ወደእኛ አምላካችን ከምን ጊዜውም በላይ ቀርቧል ብለን ስንል ልጁን ከመላክ በላይ መቅረብ ምን አለ?
  3. ንስሐ ግቡ፡ ትልቁ መልእክት ንስሀ ግቡ እንታረቅ እያለ ያለው እራሱ የተበደለው እግዚአብሔር መሆኑ ይገርማል
  4. በወንጌልም እመኑ :- በልጁ ሞትና ትንሳኤ እመኑ ብሎ በሩን ከፍቶ እየጠበቀ ነው መምጣቱንም ያዘገየው ሰዎች ሁሉ ይድኑና ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ ነው የታገሰውና መምጣቱን እያዘገየ ያለው::

እየሱስ ዛሬ ይህንን አገልግሎት ለእኛ ሰቶንና ሾሞን ሄዶ መንፈስ ቅዱስን ልኮልናል:: ከዚህ ውጪ ምንም መስበክ የለብንም:: ዘመኑ ተፈፀመ የሚባልበት ዘመን ላይ ነን እናም መንግስቱን እንስበክ:: ማራናታ!


ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ

የማርቆስ ወንጌል 1: 16-20
16፤ በገሊላ ባሕርም አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። 17 ኢየሱስም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው።  18 ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። 19 ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ደግሞ በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አየ። 20 ወዲያውም ጠራቸው አባታቸውንም ዘብዴዎስን ከሞያተኞቹ ጋር በታንኳ ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ። 

ጌታ እየሱስ ደቀመዝሙሮችን ሲጠራ እናያለን የተጠሩትንም አንድ የስራ ኃላፊነት ነበር የሰጣቸው ሰውን አጥማጅ መሆን የሚል:: የተጠሩትም: – ወንድማማቾቹን ስምዖንና እንድርያስን እንዲሁም ሌሎቹ ወንድማማቾች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ:: እነዚህ ሶስቱ መሪዎች የሆኑና ክብሩንም ያሳያቸው ናቸው:: የሚገርመው ሲጠራቸው ብድግ ብለው ሁሉን ትተው ተከተሉት እንጂ ጥያቄ እንኳን አልጠየቁም:: እኛስ ዛሬ ለጌታ ጥሪ ምላሻችን እንዴት ይሆን? እኛም ዛሬ ለክርስቶስ ሰውን የምናጠምድና ከጌታ ጋር ታረቁ ልንልየተጠራን ነን! ከኃላው እንከተለው:: ጌታ ፀጋውን ያብዛልን!



እየሱስ የእግዚአብሔር ቅዱሱ

የማርቆስ ወንጌል 1: 21-28
21፤ ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ። 22 እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ። 23 በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤  24 እርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ። 25 ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። 26 ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ። 27 ሁሉም። ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። 28 ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ። 

ወድያውም ጊዜ ሳያጠድፋ ወደ ምኩራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ የሚያስተምር የነበረውም እንደ ባለ ስልጣን ነበርና ሰሚዎቹ ተገረሙ ይለናል:: እየሱስ በስልጣን ቢያስተምር የማይደንቀው ምክንያት ቃሉን የሰጠው ለሙሴና ለነብያቱ እርሱ ነበረና ነው:: በዛም የነበረ እርኩስ መንፈስ እየሱስን ማን እንደሆንክ አውቃለሁ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ እርሱም አስወጣው:: በዛም የነበሩት ይህ ምንድነው መናፍስት የሚታዘዙለት ብለው አደነቁ:: አላወቁም እንጂ በመካከላቸው የቆመው የጌቶች ጌታና የነገስታት ንጉስ ነው:: የእየሱስ ዝና በየስፍራው ሁሉ ወጣ ይላል በዛ በአንድ ሰው ነፃ መውጣት:: ስለዚህ ዛሬም ይህ ጌታ በእስራት ያሉትን በእኛ ውስጥ ሆኖ ሰርቶ ነፃ ማውጣት ይፈልጋል:: የልጅነት ስልጣን ተሰቶናል እኛም ይህንን ስልጣን ልንለማመድ ይገባል ስሙን ሰቶናል በስሙ ደግሞ አጋንንት ይወጣል:: እየሱስ ከስም ሁሉ በላይ ስም አለው ስሙም በላይ በሰማይ በምድር ከምድር በታች ያሉ ሁሉ ይንበረከካል:: እርሱ ሁሌም ይሰራል:: አባቴ ሁሌ ይሰራል እኔም እሰራለሁ ብሎናልና በእኛም ውስጥ መንፈሱን ልኳል ይሰራል::


ብዙዎችን ፈወሰ አጋንንትንም አወጣ

የማርቆስ ወንጌል 1:29-34
29፤ ወዲያውም ከምኵራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገባ። 30 የስምዖንም አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ነገሩት። 31 ቀርቦም እጅዋን ይዞ አስነሣት ንዳዱም ወዲያው ለቀቃትና አገለገለቻቸው። 32 ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ 33 ከተማይቱም ሁላ በደጅ ተሰብስባ ነበር። 34 በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፥ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፥ አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም። 

የስምዖን አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ለእየሱስ ነገሩት ይላል ክፍሉ ነገሩት የሚለው አሳብ እኮ ዛሬ እኛ ፀሎት የምንለው ነው:: ፀሎት ማለት ደግሞ መናገርና ተማምኖ እንደሰማን አውቀን መጠበቅ ነው:. እነዚህ ሰዎች ነገሩት እሱም ወደ እርስዋ ሄዶ እጅዋን ይዞ አስነሳት ንዳዱም ለቀቃት:: ዛሬ የምንፀልየውን ፀሎት እንደሰማን አምነን ማመስገን እንጂ የማናምን መሆን የለብንም እንደተሰማን ማወቅ አለብን ጌታ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎን የለም እንዴ? የምናምን እንሁን እንጂ የማናምን አማኝ አንሁን::

ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ:: ለምን ብለን ያልን እንደሆነ ሲፈውስና አጋንንትን ሲያወጣ አይተዋል ደግሞም ሰምተዋል:: ለእኛም ያደርግልናል ብለው አምነው በሽተኞችን ይዘው መጡ:: እምነታቸው የመጣው ከመስማትና ከማየት ነው:: ተአምራት ሲደረግ ማየት እንኳን ባንችል ከቃሉ ዛሬ እይኸው እየሰማን ነው እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል እንጂ እምነትን ከየትም አናመጣም ቃሉ ወደ እኛ መጥቶ በእምነት መዋሀድ አለበት:: እርሱም በሽተኞችን ፈወሰ አጋንንትንም አወጣ:: ዛሬም ይሰራል ይህ ጌታ ይፈውሳል አጋንንትንም በእኛ ሆኖ ያወጣል:: ማንንም አንጠብቅ እንጣራ ይሰማል ከሰው ሰው አይለይም ጌታ ቅርብ ነው በነገር ሁሉ ይሰማናል ይረዳናል::


ማለዳም ተነሥቶ ጸለየ

የማርቆስ ወንጌል 1: 35-39
35፤ ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ። 36 ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩትም ገሥግሠው ተከተሉት፥ 37 ባገኙትም ጊዜ። ሁሉ ይፈልጉሃል አሉት። 38 እርሱም። በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና አላቸው። 39 በምኵራባቸውም እየሰበከ አጋንንትንም እያወጣ ወደ ገሊላ ሁሉ መጣ። 

ከእየሱስ የምንማረው ነገር በዚህ ክፍል ላይ ጸሎትን ነው:: ማለዳ ተነስቶ ማንም ወደማይረብሸው ቦታ ሄዶ ይጸልይ ነበር:: ሐዋርያት ግን መተው ሁሉ ይፈልጉሀል አሉት እንጂ ከአንተ ጋር በጸሎት እንትጋ ሲሉ አናይም ብቻ ናና ተአምርን አድርግ እንጂ ነው ጥያቄያቸው ተአምራት የሚሆነው እኛ ከጌታ ጋር ጊዜ ስናሳልፍ ነው ደግሞም ተአምራትን ለማድረግ አይደለም ፊቱን የምንፈልገው ፍቅሩ ግድ ብሎን እንጂ! ሁሉ የፈለጉት ምክንያት ጌትነቱ ገብቷቸው ሊከተሉት ሳይሆን የጎደላቸውን እንዲሞላላቸው ብቻ ነበረ ነገር ግን እኛ ዛሬ የምንፈልገው ለምን ይሆን? የህይወታችን ጌታና ንጉስ መሆኑን አውቀን በፊቱ ልንገዛ መሆን አለበት ወደ እርሱ የምንመጣው:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!!


እየሱስ ለምጻሙን አንፃ

የማርቆስ ወንጌል 1:40-45
40፤ ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ ተንበረከከና፦ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፥ ብሎ ለመነው። 41 ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው። 42 በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀውና ነጻ። 43 በብርቱም ተናግሮ ወዲያው አወጣው፤ 44 ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ አለው። 45 እርሱ ግን ሲወጣ ብዙ ሊሰብክና ነገሩን ሊያወራ ጀመረ፥ ስለዚህም ኢየሱስ ተገልጦ ወደ ከተማ መግባት ወደ ፊት ተሳነው፥ ነገር ግን በውጭ በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ከየስፍራውም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

ይህ ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ መጀመሪያ ያደረገው ነገር መንበርከክና አምልኮን መስጠት ነበር፦ ከዛም ጥያቄውን ማቅረብ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፥ ብሎ እርግጠኛ የሆነበትን ነገር ጠየቀ ብትወድ ችግር የለብህም ትችላለህ በአንተ ዘንድ ጥያቄ የለም ብሎ ለመነው። ጌታ ኢየሱስም አዘነለት ይላል በጣም ይገርማል በዛች ቅፅበት ህይወቱን ሁሉ ማየትና ያለበትን ነገር ተረዳው እናም እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው። ጌታ ያውቀናል ያሳለፍነውንና ያለንበትን ነገር ደግሞም የሚራራ እንጂ የሚጨክን ጌታ አይደለም ጌታችን:: ተናገረው ለምፁም ሰምቶ ለቆ ሄደ እንዴት ድንቅ አምላክ ነው የምናመልከው? ስሙ ይባረክ! ምንም አይነት ህመም ቢሆን ጌታ ይፈውሳል!

ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ የተባለው ሰው ወጥቶ ወሬውን በሰፊው አወራ ውጤቱም እየሱስ ወደ ከተማዋ መግባትም እንዳይችልና በምድረ በዳ እንዲያገለግል አደረገው:: ስውየው የተባለው ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ ነበረ። የተባልነውን ቢገባንም ባይገባንም እናድርግ::


ምዕራፍ 2

እየሱስ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን አለው

የማርቆስ ወንጌል 2: 1-12
1፤ ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ። በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር። አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት። ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ።  ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም። ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል?  ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው አሰቡ።  ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው። በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ? ሽባውን። ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? 10 ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤ 11 ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። 12 ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፥ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና። እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ። 

እየሱስ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው ሲያስተምር እዚህ ክፍል ላይ እናያለን:: ይህንን ሽባ ሰው ያለው ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ነው:: ይህን በማለቱ ግን በዛ ስፍራ የነበሩ ጻፎች በልባቸው ያሰቡትን አውቆ ነበር መልስን የሰጠው በጊዜው የእግዚአብሔር ቤት አገልጋዮች ናቸው ግን እየሱስ ለሚለው ነገር እንግዳ ናቸው ወይ ጠይቀው አልተማሩ ወይ አንብበው ተዘጋጅተው አልጠበቁ:: መጽሐፍት ሁሉ ስለእኔ ይናገራሉ ብሎ ያውቃልና ጌታ:; ዛሬ ስናገለግለው ከሁሉ በላይ የሆነውን ጌታን እንወቅ እርሱንም በቃሉ ውስጥ እናገኘዋለን::

የሚገርመው ግን ሰውየው የተፈወሰው ጣርያውን ነድለው ባወረዱት ወዳጆቹ እምነት ነው:: እየሱስም ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ:: ሃሌሉያ! የጌታ ነገር ሁሉ ያጠነጠነው ሰዎችን ነፃ ማውጣት ላይ ነው:: እኛም ዛሬ የቤተክርስቲያንን ህግ ለመታዘዝ የእግዚአብሔርን ቃል እንዳንጠመዝዝ እንጠንቀቅ የጌታ አይን ባለበት ላይ እርሱም ሰው ላይ ይሁን አይናችን:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!


ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም

የማርቆስ ወንጌል 2: 13-17
13፤ ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። 14 ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው። 15 በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ ይከተሉትም ነበር። 16 ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ። ከቀራ ጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው? አሉ። 17 ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው። 

እዚህ ክፍል ላይ አምስተኛው ደቀ መዝሙር ማቲዎስ በሌላ ስሙ ሌዊ ሲጠራ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ ሲከተለው እናያለን:: እርሱም ቀራጭ ነበረና በቤቱ በመአድ ሲቀመጡ የተሰበሰቡት ሁሉ እርሱን የሚመስሉ ሐጥያተኞች ስለነበሩ ሀይማኖተኞቹን አስቆጣ:: ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።  እንደዛማ ባይሆን የት ነበርን ዛሬ? እያንዳንዳችን ሐጥያተኞችና ሞት የሚገባን ነበርን በቸርነቱ ይቅር ብሎ ቀድሶ የራሱ ባያደርገን ኖሮ:: ስለዚህ ዛሬ ብዙ ይቅር የተባልን ነንና ጌታን በብዙ እንወዳለን ደግሞም ሰዎችን ታግሰን ወደ ጌታ እናመጣለን በማንም አንፈርድም የባስን ስለነበርን::


የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው

የማርቆስ ወንጌል 2: 18-28
18፤ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም፦ የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት። 19 ኢየሱስም አላቸው። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም። 20 ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ። 21 በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። 22 በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ። 23 በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። 24 ፈሪሳውያንም። እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት። 25 እርሱም። ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ 26 ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። 27 ደግሞ። ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ 28 እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።

ሰዎች እየሱስን ስለምን እንደዚህና እንደዚያ ያደርጋሉ ወይም አያደርጉም ተብሎ ስለ ደቀመዝሙርቱ ጥያቄ ሲቀርብለት እናያለን:: አንዱ ጥያቄ አይጾሙም ሲሆን ሌላው ደግሞ ህግን አይጠብቁም በሰንበት እህል ቀጥፈው በሉ ነበር:: ያልገባቸው ጉዳይ እየሱስ ስርነቀል ለውጥ ሊያደርግ መምጣቱን ነው:: እኛም እንኳን የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች ሆነን በአንዳንዱ ጉዳይ ስናነክስ እንታያለን:: በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ ለማድረግ ስንጥር እንታያለን:: እኛ በክርስቶስ አዲስ ነን አዲስ ኪዳንን የተቀበልን እንደሆንን እንወቅ እንጂ ዳግመኛ ወደ ተተወ ኪዳን አናመዝንና በስራ ለመጽደቅ ጽድቃችንንም ለማቆም አንጣር::

ሰንበት ለእኛ እንጂ እኛ ለሰንበት አይደለንምና እኛ ወደ እረፍት የገባን ሰዎች ነን:: የሰውን ህግ ከመጠበቅ ይልቅ ጌታን ለማወቅና እርሱን ለመታዘዝ እንትጋ:: ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው ልንፈራ የሚገባን ጌታን ብቻ ነው::


ምዕራፍ 3

እጁ የሰለለችውንም ሰው ፈወሰ

የማርቆስ ወንጌል 3: 1-6
1፤ ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፥ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ ሊከሱትም፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። 
እጁ የሰለለችውንም ሰው። ተነሥተህ ወደ መካከል ና አለው። በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ። ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፥ ሰውየውንም። እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እጁም ዳነች። ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ከሄሮድስ ወገን ጋር ተማከሩበት። 

ሰንበት ለሰው እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም ብሏችው ነበር ወደ ምኩራብ የገባው ነገር ግን እዛም ምን ሊያደርግ እንደሆነ ይጠባበቁት ነበር :: እርሱም ጠየቃቸው በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ እርሱም የሰውየውን እጅ ፈወሰው:: በፈውሱ በመደሰትና ነፃ ስለወጣው ሰው ስለማመስገን ፋንታ እንዴት እንደሚያጠፉት ነበር የተማከሩት:: ዛሬም ልባችንን ልንጠብቅና ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይለን ዘንድ እናመሰግን ዘንድ ነው የሚገባው:: እየሱስ አይኑ ሁሉ በሰዎች ላይ ነው እኛም ዛሬ ህግና ስርአት ባህልና ዘር ከሚል መጠላለፍ ወተን የጌታን አሳብ እናገልግል እርሱም በአምሳሉ የፈጠረውን ሰውን ነፃ ማእጣት:: ከዚህ ክፍል ላይ ስለእየሱስ ባህሪ የተማርኩት ታጋሽነቱን (ለተቃዋሚዎቹ) ርህራሄውን (ለታመመው ሰው) ነው::


ብዙ ሕዝብ ተሰበሰቡ

የማርቆስ ወንጌል 3: 7-12
7፤ ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገው ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ 10 ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። 11 ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ።  12 እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው። 

እዚህ ክፍል ላይ ከተለያየ ስፍራ ሰዎች ተሰብስበዋል ከአካባቢው አገር ሳይቀር ዝናው ወቶ ነበር:: አብዛኛው የመጣው ችግሩ እንዲፈታለት ሌላው ደግሞ ዝናውን ሰምቶ ለማየት ነው:: እርሱም ሁልጊዜ ሁለት ነገሮችን ያደርጋል በመጀመሪያ ያስተምራል ከዛም ይፈውሳቸዋል:: አጋንንትም ሲያዩት ወድቀው እየሰገዱ ይወጣሉ እርሱም እንዳይገልጡት ያዛቸዋል ምክንያቱም አጋንንት አይደለም እርሱን መግለጥ ያለበት እርሱ በራሱ ጊዜ ለሚፈልጋቸው ይገልጥ ነበርና:: የአጋንንት ምስክርነት አያስፈልገውም:: እዚህ ክፍል ላይ ያየሁት የእየሱስ ባህሪ አለመሰልቸቱን አይቻለሁ ስቃያቸውን አይቶ ችላ አይልም ነበር::


የሐዋርያት ሹመት

የማርቆስ ወንጌል 3: 13-19
13፤ ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። 14 ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ 15 ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤16 ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ 17 የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ 18 እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ 19 አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን። 

ጌታ እየሱስ ወደ ተራራ የሚሄደው ለመጸለይ ጊዜ ከአባቱ ጋር ለማሳለፍ ነው:: እዚህ ጋር ስንመለክት እጸሎት ስፍራው ላይ አገልጋዮችን መርጦ ይዞ ሲሄድ እናያለን:: የተጠሩትን አገልጋዮች የስራ ድርሻቸው እንይ:-

  1. ከእርሱም ጋር እንዲኖሩ – የአገልግሎት መጀመሪያ ከእርሱ ጋር መኖር ነው
  2. ለመስበክ እንዲልካቸው – ከእርሱ ጋር ስንኖር ስለ እርሱና ስለ መንግስቱ መስበክ እንችላለን:: ያየነውንና የሰማነውን እንሰብካለን
  3. ድውዮችንም ሊፈውሱ – ጌታ ሁልጊዜ ለተጨነቁት ሲራራና ሲፈውስ እናያለን ይህም ህዝቡን ነፃ የማውጣት ስራ በቤቱ እንዲሰራና ህዝቡ እረፍትን እንዲያገኝ ይፈልጋል::
  4. አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ – ያለ ስልጣን አጋንንት አይወጣም
  5. አሥራ ሁለት አደረገ – ስንት መሆን እንዳለባቸው ወስኗል

ዛሬም ከእርሱ ጋር ለመኖርና ጊዜያችንን በፀሎት ለማሳለፍ እንነሳሳ ደግሞም እናዘውትር:: ዛሬ በቤተክርስቲያን የሚያገለግሉትን በቁጥር ፀጋን ሞልቶ የሚሰጥ ጌታ እራሱ ነው:: እዚህ ክፍልላይ ያየሁት የጌታ ባህርይ መፀለይን ማዘውተሩን ነው::


በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ አይሰረይለትም

የማርቆስ ወንጌል 3: 20-30
20፤ ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። 21 ዘመዶቹም ሰምተው። አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ። 22 ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም። ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። 23 እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው። ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? 24 መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ 25 ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። 26 ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። 27 ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። 28 እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ 29 በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም። 30 ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና። 

ሐዋርያት እንጀራ መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ይሰበሰብ ነበር ሁሉ እየሱስን ይፈልጉ ነበርና ከመከራቸው ለመላቀቅ:: ዛሬም እየሱስ ይፈለጋል ብዙ ሰው በእንቆቅልሽ ውስጥ ነው ያለው:: ይህንን ሁሉ ድንቅ ሲያደርግ ሲያዩት አዲስ ነገር ነውና በብሉይ ኪዳን በተለይ ሐጥያትን ማስተሰረይ ይህ የሚሆነው በአጋንንት አለቃ ነው ብለው ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ተሳደቡ::

ስለዚህም ጌታ እየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም ብሎ አላቸው:: የሚገርመው ቤተሰቦቹ ሳይቀሩ አብዷል አሉ ምክንያቱም ከኢየሩሳሌም የመጡ ጻፎች ነበሩና በዛ ስፍራ እየሱስ በሚያደርገው ነገር ደስተኞች እንደማይሆኑና ሊያጠፉት እንደሚነሳሱ በደንብ ነቅተዋል:: በእኛም ህብረተሰብ ትልቁን ቅጣት የሚቀጡት የመቀበርያ ስፍራ አታገኝምና ከእድር እናስወጣለን አይደል ትልልቁን ሰው አስሮ የያዘው? እንደዚሁ በእስራኤት ያልተገደለው የትኛው ነብይ ነው? ሁሉንም ገድለዋል አሁን ደግሞ ልጁን:; እነሱ ግን ለእግዚአብሔር የቀኑ ነው የሚመስላቸው ዛሬም በዘመናችን የክርስቶስን ተከታዮች በማሳደድ ላይ ያሉ አሉ ከጥንትም ያለ ደግሞም የሚኖር ነው ይህንን የሚያደርገው የዚህ ዓለም ግዢ እንደሆነ የታወቀ ነው:: ይህንን ገዢ ሐይለኛ ተብሎ የተገለፀውን አስረን የያዘውን ሁሉ መበዝበዝ በስሙ ማለትም በእየሱስ ስም ለእኛ ተሰቶናልና የያዘውን ሁሉ እናስጥላለን:: በስሙ ውስጥ ሐይል አለ:: አሜን!

ዛሬም ጌታን ለማገልገል እንነሳ እኔን ላከኝ እንበለው:: ቅዱሱንም መንፈስ እናክብር::


የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ

የማርቆስ ወንጌል 3: 31-35
31፤ እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። 32 ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና። እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። 33 መልሶም። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። 34 በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና። እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። 35 የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።

ቤተሰቦቹ ልከው ሲያስጠሩት እናያለን እዚህ ክፍል ላይ:: ከላይም ደግሞ እንዳየነው ዘመዶቹ አብዷል ብለው ነበርና ስላልሰማቸው እንደገና እናቱና ወንድሞቹ ደግሞ እየሞከሩ ነው ሊያስቆሙት:: እሱም ያንን ስለሚያውቅ አልወጣም ነገር ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእርሱ ቤተሰብ እንደሆነ መሰከረ:: በሌላ ስፍራም ቃሉ እንደሚለን በማቴ 7: 21፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። እንዲሁም ደግሞ በ1ኛ ዮሐንስ 2: 17፤ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። በአባታችንም ጸሎት ሲያስተምረን ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን የሚል ነው::

ዛሬ የማንንም ፈቃድ ሳይሆን የጌታን ፈቃድ እንፈጽም እርሱንም ደስ እናሰኝ:: ከጌታ የተማርነው ይህንን ነው መከራው እያስፈራው ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ ግን የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን ብሎ እራሱን ስለ እኛ እንደሰጠ እናውቃለንና ፈቃዱን ከመታዘዝ ወደኃላ እንዳላለ እኛም አንልም:: የጌታ ጸጋ ያግዘን!

ያየሁት የጌታ ባህሪይ በዚህ ክፍል ላይ ቆራጥነትን ነው::


መልካም መሬት

የማርቆስ ወንጌል 4: 1-20
1፤ ደግሞም በባሕር ዳር ሊያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በታንኳ ገብቶ በባሕር ላይ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕር ዳር በምድር ላይ ነበሩ። በምሳሌም ብዙ ያስተምራቸው ነበር፥ በትምህርቱም አላቸው። ስሙ። – እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤  ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ። 10 ብቻውንም በሆነ ጊዜ፥ በዙሪያው የነበሩት ከአሥራ ሁለቱ ጋር ስለ ምሳሌው ጠየቁት። 11 12 እንዲህም አላቸው። ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን፥ አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፥ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፥ እንዳይመለሱ ኃጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል። 13 አላቸውም። ይህን ምሳሌ አታውቁምን? እንዴትስ ምሳሌዎቹን ሁሉ ታውቃላችሁ? 14 ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው:: 15 በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል። 16 እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ 17 ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። 18 በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ 19 የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። 20 በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።

ይህ ምሳሌ ስለ ቃል አቀባበላችን በሰፊው የሚነግረን ስፍራ ነው ሰው በህይወቱ እንዴት አደገ ወይም ለምን አላደገም የሚለውን በደንብ ይመልሳል:: አራት አይነት የቃል አቀባበል አለና መንገድ ዳር፥ ጭንጫ፥ በእሾክ መካከልና መልካም መሬት ናቸው:: ቃሉ ነው ህይወታችንን የሚያሳድገእንይ የሚቀይረው እንጂ ሌላ ማጂክየለውም በህይወት ለመለወጥና ለማደግ::

  1. መንገድ ዳር – ህይወቱ በጣም በቀላሉ በጠላት የሚጠቃ ነው ሲጀምር መንገድ ዳር ምን ያደርጋል በጌታ አልረካም ማለት ነው የተሻለ ሌላ አለ ወይም ደግሞ ለዚህ ህይወቴን አላንበረክክም የሚል ማንነት ነው
  2. ጭንጫ – እነዚህ ሰዎች አስመሳዮች ናቸው የጌታንም የዓለምን ይፈልጋሉና
  3. በእሾክ መካከል – ይሞክራሉ ይጥራሉ ግን ይሸነፋሉ:: ምክንያቱም የጌታ ፍቅር አልገባቸውምና በዓለም ፍቅር ተይዘዋል ስለዚህም ድካምን ለመሸፈን ግድ የለም ይህንን ባደርግ ወይም ምን አለበት ይህንን ባደርግ ያበዛሉ:: አንዳንዴም ወገባቸውን ገትረው ብንዘፍን ምን ችግር አለው? ብለው ዓለምን በግልፅ ወደ ቤተክርስቲያን ሊጋብዙ ይጥራሉ:: የክርስቶስ ፍቅር ሲገባን ግን ሁሉን ትተን እንከተላለን::
  4. መልካም መሬት – የሚያፈራ መሬት ነው እድገቱ የተጠበቀ ነው:: ቃሉ ይመጣል ያብባል ፍሬውም በህይወት ይታያል ይህ ህይወት ከትክክለኛ መለወጥ በኃላ የሚመጣ ነው:; ሰው በክርስቶስ ፍቅር ሲሸነፍ ምልክቱ መለወጥ መጀመሩና ያለ ምንም ማስመስል እርሱን ወደ መምሰል መምጣቱ ነው::

አናስመስል ይልቁንስ ወደ ጌታ መተን ይህንን መሬት እመስላለሁና ለውጠኝ ውጤትን ያመጣል ምክንይቱም ጌታ ፀሎትን ይሰማልና:; የጌታ ፀጋ ይርዳን! አሜን!


በብርሃን እንመላለስ

የማርቆስ ወንጌል 4: 21-25
21፤ እንዲህም አላቸው፦ መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? 22 እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም። 23 የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። 24 አላቸውም። ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል። 25 ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 

መብራትን ስናስብ ለራሱ የተፈጠረ አይደለም ለሌላ መጠቀሚያ እንጂ በርቶ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሌላውን እንዲረዳ ካልተቀመጠ ምንም ዋጋ የለውም:: እንደዚሁም የእኛ ህይወት ለዓለም ብርሀን እንደሆነ እናውቃለን:: ቃሉ እንደሚል ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ የተጠራነውም በውስጣችን የበራውን ብርሃን ክርስቶስን ልናብለጨልጭ ነው እንጂ እርሱ ካላበራና ካልታየ የእኛ በምድር መቆየት እምኑ ላይ ነው? ብርሃኑን በእኛ ውስጥ ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና ተነስተን በከፍታ ላይ ማብራት አለንብ:: ህይወታችን የሚኮንን ጨለማን የሚገልጥና የሚያሳይ ከጨለማ ጋር የማይተባበር ወደ ብርሃን የሚጋብዝ ተደርጎ ተፈጥሯል:: እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ እኛ አዲስ ፍጥረት ነን አሮጌው ሁሉ አልፏል:: አሜን ሃሌሉያ!

ዛሬ የምንሰማው ምንድነው? ከየትስ እየሰማን ነው? የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። አለ እየሱስ። ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ ብሎም አክሏል ምክንያቱም በቃሉ ላይ በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ ሌላውን አይሰሙም ይላል መስማት ያለብን ከከበረው ቃሉ መከተልም ያለብን እረኛችንን ነው:: በእኛ ተማምኖ ሌላውን አይሰሙም ይላል እንጠንቀቅ መስማት ያለብንን እንለይ ሁሉንም አግበስብሰን እንዳንቸገር መገኘት በሌለብን ስፍራ አንገኝ መለየት ካለብን ትስስር እንለይ እርሱን ከሚመስሉ ጋር ህብረትን እናድርግ ቃሉን እናጥና በጸሎትም እንትጋ:: ከቅዱሳን ጋር አብዝትን እንተያይ ዘመኑ ሲያልቅ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ ቃሉ ይነግረናልና አብዝተን ህብረትን እንፈልግ በዛ ውስጥ መታነጽ አለና:: ቃሉ በእኛ ዘንድ ሲኖር እየበዛ ይሄዳል አለበለዚያ ያው ያለውም ይለቀምና ይሟጠጣል ሁልጊዜ በቃሉ ካልተሞላን:: ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል። እንበርታ ጌታ መልካም ነውና:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የቃሉ ዘር በራሱ ያድጋል

የማርቆስ ወንጌል 4: 26-29
26፤ እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ 27፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። 28፤ ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። 29፤ ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።

የእግዚአብሔርን መንግስት በገበሬ ይመስለዋል:: ገበሬውም ዘርን ይዘራል ለሊትና ቀን ሳይል ማደግ ይጀምራል:: ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ሲሆን መሬቱ ደግሞ ቤተክርስቲያን ናት:: ሲደርስ ደግሞ የሚያጭዱት መላእክት ናቸው:: የሚገርመው ዘሩ አውቆ ማደጉ ነው:: በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ይህ የሚሆነው ያለውሀና የፀሓይ ብርሀን እንዳይደለ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን እጅ እናያለን በዚህ ረቂቅ ስራው ውስጥ:: ስለዚህ እዚህ ጋር መጠየቅ የምፈልገው ዘሩም ሆነ ምድሩ የማን ነው ነው? ሁሉም የጌታ ነው ስለዚህ ቤተክርስቲያን አትሸነፍም ታድጋለች ደግሞም ታፈራለች:: አትጠወልግም!አትረግፍም! ጌታ ሁልጊዜ ይሰራል! የቤተክርስቲያን ራስ እየሱስ ነው:: በቃሉ እንሞላ! ቃሉ በእኛ ውስጥ ያድጋል:: ቃሉ ለእኛ የጦር እቃችን ነውና:: ጳውሎስ ተከለ አጵሎስ አጠጣ የሚያሳድግ ግን እግዚአብሔር ነው::


የእግዚአብሔር መንግስት ሰናፍጭ ቅንጣት ናት

የማርቆስ ወንጌል 4: 30-34
30፤ እርሱም አለ፦ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? 31 እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥  32 የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች።  33 መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፥  34 ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር። 

ሰናፍጭ ከዘር ሁሉ ትንሽ ነች ነገርግን ስታድግ ሁሉን ትበልጣለች:: የእግዚአብሔርም መንግስት ሁልጊዜ ሲጀመር ከትንሽ ይሆንና አገሩን ይሞላል:: እየሱስ የመረጠው አስራ ሁለት ሐዋርያትን ነበር ዛሬ ከሁሉም ወገንና ቋንቋ በዓለም ሁሉ ወንጌል እየተዳረስ ይገኛል:: ለዚህም ነው ጅማሬህ ታናሽ ቢሆን ፍጻሜህ ትልቅ ይሆናል ይለናል::


ስንጠፋ አይገድህምን?

የማርቆስ ወንጌል 4: 35-41
35፤ በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ፦ ወደ ማዶ እንሻገር፡ አላቸው። 36 ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። 37 ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር።  38 እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። 39 ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። 40 እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። 41 እጅግም ፈሩና። እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።

ወደ ማዶ እንሻገር ብሎ ተናግሮ የተጀመረው መንገድ እክል አጋጠመው ይኸውም ማዕበል ነበር:: በጌታ ውስጥ ያለው አሳብ እንሻገር ብሏል መሻገር ግድ ነው የሚያቆም ነገር የለም ነው ነገር ግን የሚያጨናግፍ ነገር ተፈጠረ:: ስንጠፋ አይገድህምን? ብለው እስኪሉ ድረስ ጀልባዋ ላይ የገባውን ውሀ በማፍሰስና በመቅዘፍ ላይ ተጠምደው ነበረ:: ዛሬ ምን ላይ አጥምዶን ይሆን ጠላት ከትልቁ ተልእኮ ላይ አይናችንን አስነስቶትስ ይሆን? መጠየቅ ጥሩ ነው ዙሪያችንን እንይ እስኪ እኛ መንፈሳውያን ሰዎች ነንና የጊዜውን ፀልየን መቀበል አለብን:: ጌታ ከተኛበት ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው ይላል:: ሃሌሉያ! ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? ብሎ ነበር ያላቸው:: የተጠየቁትን እናስተውል እምነት የላችሁምን? እንሻገር አይደለም ያልኩት ታድያ ቃሌን የሚያጥፍ ማነው? ባለማመናችሁ እናንተ ናችሁ ያልታዘዛችሁት:: አለመታዘዛችንን ሳናስተውል ሳንታዘዝ ስንቱን አጋጣሚ አልፈነው ይሆን? ዛሬ ስለተፃፈ ምን ነካቸው ሐዋርያት እንል ይሆናል ነገር ግን ዛሬም ጠላት ለማዘናጋት በዙሪያችን እንደሚዞር አውቀን እንንቃበትና ጌታ ያለን ቃል ላይ እንቁም::


ምዕራፍ 5

ሌጌዎን ያለበትን ሰው ፈወሰ

የማርቆስ ወንጌል 5: 1-20
1፤ ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር መጡ። ከታንኳይቱም በወጣ ጊዜ፥ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ከመቃብር ወጥቶ ወዲያው ተገናኘው፤ እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፥ በሰንሰለትም ስንኳ ማንም ሊያስረው በዚያን ጊዜ አይችልም ነበር፤ ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና ዳሩ ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፥ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም፤ ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን በመቃብርና በተራራ ሆኖ ይጮኽ ነበር ሰውነቱንም በድንጋይ ይቧጭር ነበር። ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፥ በታላቅ ድምፅም እየጮኸ። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤ አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ ብሎት ነበርና። ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው አለው፥ 10 ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው። 11 በዚያም በተራራ ጥግ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበርና። 12 ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን ብለው ለመኑት። 13 ኢየሱስም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ገቡ፥ ሁለት ሺህም የሚያህል መንጋ ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና በባሕር ሰጠሙ። ፍ1 ሌጌዎን ማለት ጭፍራ ማለት ነው። 14 እረኞቹም ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩ፤ ነገሩም ምን እንደ ሆነ ለማየት መጡ። 15 ወደ ኢየሱስም መጡ፥ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ። 16 ያዩት ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ እሪያዎቹ ተረኩላቸው። 17 ከአገራቸውም እንዲሄድላቸው ይለምኑት ጀመር። 18 ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው። 19 ኢየሱስም አልፈቀደለትም፥ ነገር ግን። ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው። 20 ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ። 

በብዙ ጉልበትና ኃይል እንኳን ለማሰር ያስቸገረው ሰው እየሱስን ሲያይ በእግሩ ስር ወድቆ አታሰቃየን ብሎ ሲለምን እናያለን:: ሰይጣን ሁልጊዜ ስራው ክፉ ነው ማሰቃየትንም ይወዳል የኛ ጌታ ደግሞ ነፃ ማውጣት ነው ስራው ይህንን ሁሉ ጊዜ የተሰቃየውን ሰው ሊረዳ ነበር ወደ መቃብሩ ስፍራ የመጣው:: በእርሱ ነፃ መውጣት ሰዎች ሲደሰቱ ሳይሆን እንዲያውም ሂድልን ነበር ያሉት:: በዓይናቸው ፊት የማይቻለው ተችሎ እያዩ ግን ማስተዋልን አልቻሉም ነበር:: ለጌታ ግድ የሚለው የሰው ከስቃይ መገላገል ነውና::

አጋንንት የወጣለት ሰው ከጌታ ጋር መሆን ፈልጎ ነበር ጌታ ግን ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው። የጌታ ምህረት ነው ይህንን ሰው ደህና ያደረገው:. ሰውየውም ሄዶ ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ:: ይህ ሰው ወንጌላዊ ነው የሆነው የተደረገለትን በመስበክ:, እኛም የበዛልንን ምህረት እንመስክር ብዙ ተደርጎልናልና::


የደምዋ ምንጭ ደረቀ

የማርቆስ ወንጌል 5: 21-34
21፤ ኢየሱስም ደግሞ በታንኳይቱ ወደ ማዶ ከተሻገረ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ በባሕርም አጠገብ ነበረ። 22 ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና። 
23 ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው። 
24 ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። 
25 ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ 
26 ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ 
27 የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች። 
28 ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና። 
29 ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። 
30 ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ። ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ። 
31 ደቀ መዛሙርቱም። ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ። ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት። 
32 ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። 
33 ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። 
34 እርሱም። ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት።

ብዙ ሕዝብም ተከተሉት እያጋፉትም ወደ ኢያኢሮስ የሚሉት ከምኵራብ አለቆች አንዱ ወደሆነው ሰው ቤት ልጁን ለመፈወስ በጉዞ ላይ ነበረ:: በመንገዱም ላይ አንዲት ሴት የልብሱን ጫፍ ነካች:: እርሱም ቆመ በመነካቱ ሳይሆን ኃይል ከእርሱ እንደወጣ ስላወቀ ነው:: ሐዋርያቱ ግን ማን ነካኝ ትላለህ እንዴ ይህ ሁሉ ህዝብ እያጋፋህ? አልገባቸውም ነበር እርሱ የሚለው ነገር ስለዚህም ልትደበቅ እንዳልተቻላት አውቃ የሚለውም ገብቷት ነበረና በእግሩ ስር ወድቃ የሆነውን ሁሉ ነገረችው::

ገና ስትመጣ ዓላማ ነበራት የልብሱን ጫፍ የነካሁ እንደሆነ እድናለሁኝ እና መንካት አለብኝ ብላ ነው የመጣችው:: ያላትን ሁሉ በጤናዋ ምክንያት ያጣች ግን በህመም የምትሰቃይ ሰው ናትና ወደ እርሱ ስትመጣ ሌላ አማራጯን ሁሉ ጨርሳ ነው:: ስለዚህም እንደምንም ብላ ተንጠራርታ ነካችው ወድያውም መዳንዋን የደምዋንም መቆም አወቀች:: ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል! የሚገርመው ነገር መዳንዋን ያወቀች ብትሆንም እንኳን ጌታ:- ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት ከእርስዋ ጋር ተስማማ:: ሰውን ከስቃይ መገላገል ይወዳልና ጌታ ከስቃይሽ ተፈወሺ አላት:: ያለፈችበትን የሚረዳ ጌታ እርሱ እጅግ የሚምር የሚራራ ነውና:: ስሙ የተባረከ ይሁን! እምነታችንን በጌታ ላይ እናድርግ ሌላው አልተፈወሰምናእኔስ ምን አገኛለሁ አንበል አንዳንዱ ዝም ብሎ የሚያጋፋ ነውና በእምነት ወደ እርሱ እንቅረብ አያሳፍረንም:: ዛሬም ጌታ ይፈውሳል! ዛሬም በስራ ላይ ነው! አሜን!


እመን ብቻ እንጂ አትፍራ

የማርቆስ ወንጌል 5: 35-43
35፤ እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት፦ ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት። 36 ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ። እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። 37 ከጴጥሮስም ከያዕቆብም ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። 38 ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤትም መጥቶ ሰዎች ሲንጫጩና ሲያለቅሱ ዋይታም ሲያበዙ አየ፤ 39 ገብቶም። ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው። 40 በጣምም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናትም ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ። 41 የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። 42 ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ። 43 ይህንም ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አዞአቸው። የምትበላውን ስጡአት አላቸው።

መቼም የእየሱስ ነገር ይገርማል ሰውን ከሞት አስነስቶ እያለ ለማንም አትንገሩ ማለቱ ነው:: ግን ይህንን ለማድረግ ይቻላል? ልጅትዋ እኮ እራስዋ ምልክት ናት ከሞት የተነሳችው ነው ቅፅል ስምዋ የሚሆነው:: እንዴት ከሞት ተነሳሽ ስትባል መናገርዋ አይቀርም::


እየሱስ ወደ ምኩራብ አለቃው ቤት እየሄደ ሳለ አታድክመው ልጅህ አርፋለች የሚል መልእክት ተነገረው:. አይይ አይዞህ እንግዲህ እኔስ ከእእንተ ጋር ልሄድና ልፈውስልህ ነበር ግን ቀድማ ሞተች ብሎ አልተለየውም:: እመን ብቻ እንጂ አትፍራ ነበር ያለው! ግን አሁን ልጅህ ሞታለች ለተባለው ሰው አትፍራ ምን አይነት መልእክት ነው? በትክክል መልክቱን የሰማ አይመስልም እየሱስ ግን አትፍራ የሚለው ቃል ህያው ነውና የኢያኢሮስን ልብ ደግፎ ያዘለት:: ወደ ስፍራውም ሲደርስ ጫጫታና ዋይታ ለቅሶ ነበረ የገጠማቸው ስለዚህም እየሱስ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው። በጣምም ሳቁበት። ዛሬም እየሱስ በእኛ ውስጥ ይሳቅበታል ስንት ጊዜ አይተን የለም? ሲመራን እሺ ብለን ስንመራ ሞኝ ተብለናል ግን ማን ሞኝ እንደሆነ ጊዜ ገልጧል:: የሳቁበትን ሁሉ አስወጥቶ እነዛኑ ክብሩ ሲገለጥ ያዩትን ሐዋርያትና የብላቴናይቱን እናትና አባት ይዞ በሩን ዘጋ:: ምክንያቱም አለማመንን በሙሉ አወጣ ከስፍራው ወላጆችዋ እንደሆነ የፈለገህን በለን ልጃችን እንድትነሳ እናምናለን የሚሉ ናቸውና:: አለማመንን ዛሬ አስወጥተን በራችንን እንዝጋ:: እየሱስም:- የብላቴናይቱን እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ ይላል ቃሉ:: የሳቁት ሱዎች ምን ብለው ይሆን ከእፍረት ሌላ? ጌታ ዛሬም ይሰራል ምንም የሚሳነው ነገር የለም:: ብቻ እንመን ነውጌታ የሚለን:: ስለምንሰማውም ነገር እንጠንቀቅ! እምነት የሚመጣውም ሆነ የሚጣለውም ከመስማት ነውና:: እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል:: እምነት ተሰፍሮ የሚሰጥ ሳይሆን ከቃሉ ውስጥ የሚወለድ ነውና ህያው ቃሉን ዕለት ዕለት እንብላ:: ለሚያምን ሁሉ ይቻላል:: ያለ እምነት እግዚአብሔር ደስ ማሰኘት አይቻልምና የምናምን አማኞች እንሁን:: የጌታ ጸጋ ይሙላብን! አሜን!


ምዕራፍ 6

ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ

የማርቆስ ወንጌል 6: 1-6
1፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና። እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው?  ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። 

እየሱስ ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ ይለናል ቃሉ:: የታዘብኩት ጉዳይ ቢኖር ጌታ እየሱስ ቢነቅፍ ወይም ቢቆጣ ከእምነት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ነው:: ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና::

ወዳደገበት አካባቢ መቶ በሰንበት በምኵራብ ያስተምር ነበር ነገር ግን ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና ስለ ማንነቱ መነጋገር ጀመሩ:: እነሱ የዚህ ቤተሰብ ልጅ አይደለምን ብለው የፈረጁት እየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው! አሜን! ሃሌሉያ! ስለተሰጠችው ጥበብ አድንቀው ሳይጠቀሙበት ተሰናክለው ቀሩ ምክንያቱም ማንነቱን አላወቁምና:: ዛሬም የምናጋፋ እንዳንሆን ጌታን በግላችን እንወቀው፤ ክርስትና የግል ነውና::

ስለዚህም እየሱስ በዚያም ስፍራ በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። ለካስ ጌታንም አላሰራ የሚል ሁኔታ አለ?! እርሱም አለማመን ነው! እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው:: እዚህ ቦታ ግን የሰሙትን ቃል እንዳያምኑት ሌላ ቃል በሰሚዎቹ መካከል ተነገረ ይኸውም እናውቀው የለም እንዴ ይህንን ሰው? ደሞ ከየት አመጣው ብለው ሲሉ የተዘራውን መልካም ዘር ሁሉ ተለቀመ ከሰሚዎቹም አልተዋሀደም:: ስለዚህ ከምንሰማው እንጠበቅ ከማመን ሊያሰናክለን ከሚችል ሁሉ እንራቅና የህይወት እንጀራ የሆነውን ሰው ያለ እርሱ መኖር አይቻለውም የተባለለትን የቃሉን ምግብ እንመኝና ለመንፈሳችን እንመግብ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው

የማርቆስ ወንጌል 6: 7-13
7፤ አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ። 10 በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። 11 ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። 12 ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ 13 ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።

ጌታ እየሱስ በመጀመሪያ ሐዋርያትን ሲጠራቸው ከእርሱ ጋር እንዲኖሩና ወንጌልን እንዲሰብኩ አጋንንትንም እንዲያወጡ ነበር:: አሁንም ጊዜው ደረሰና ወደ እርሻው ብቻቸውን ሁለት ሁለት አድርጎ ሲልካቸው እናያለን:: ሁለት ሁለት የመሆናቸውም ምክንያት እንዲደጋገፉና እንዲበረታቱም ነው:: ሲልካቸውም በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰቶ አስታጥቆ ነው የላካቸው እነሱም ሲመለሱ ያመጡት መረጃ ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ እና ብዙ አጋንንትንም እንዳወጡ ነበር፥ ይህም ብቻ አይደለም ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው ነው የሚለው ቃሉ:: ዛሬም ጌታ አልተለወጠም፥ ይሰራል፥ ሲልከንም ስልጣንን ሰቶ ነው ስራው የእርሱ ነውና በእኛ ላይ የተጠራውን ስሙን ያከብራል:: ማገልገል ብለን ስንል ደግሞ ጌታ ልኮናልና እርሱ የሚያስፈልገንን ሁሉ ያሟላል:: እግዚአብሔር የላከውን መልክተኛ አለመቀበል ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል ነበር ያላቸው:: የእግዚአብሔርን የምህረት ጊዜ ሰዎች እንዲቀበሉት እንምከር:: የእግዚአብሔርን መንግስት እንስበክ ንስሀ ግቡ እያልን በአጋንንት እስራት ውስጥ ያሉትን ነፃ ማውጣትና ህመምተኞችን መፈወስ የእኛ ስራ ነው:: የጌቲ ጸጋ ይብዛልን!


የመጥምቁ የዮሐንስ መገደል

የማርቆስ ወንጌል 6: 14-29
14፤ ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል፡ አለ። 15 ሌሎችም። ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም። ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ። 
16 ሄሮድስ ግን ሰምቶ። እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ።
17 ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ 
18 ዮሐንስ ሄሮድስን። የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና። 
19 ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤ 
20 ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ 
21 በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና 
22 የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን። የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ 
23 የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት። 
24 ወጥታም ለእናትዋ። ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች።
25 ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። 
26 ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። 
27 ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ 
28 ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። 
29 ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት። 

መጥምቁ ዮሐንስን ስንመለከት ከዓለም እራሱን ያራቀና በምንም መንገድ በዓለም ነገር የማይጠላለፍ ሰው ነው:: ኑሮውን በምድረ በዳ ምግቡን የበረሀ አንበጣና ማር ልብሱ የግመል ፀጉር ያደረገነበረ ታድያ ምን ቀርቶት ከዓለም ጋር ህብረት ያድርግ? ስለዚህም የሚያየውን ሐጥያት ሐጥያት ነው ለማለት የጨከነ ሰው ነውና ይኸው ጉዳይ ነበር ከንጉሡ ሄሮድስ ጋር ያጣላው:: ንጉሡ ሄሮድስም ይፈራው ነበር ጻድቅ መሆኑን ስለሚያውቅ ሊያስገድለውም አልፈለገም የተናገረውን ቃሉን ማጠፍ ስለማይችል ብቻ ነበር እንዲገደል ያደረገው:: ይህ ሰው የተገደለው ሐጥያታቸውን ለመሸፈን ሲባል ብቻ ነው::

በዛው በጽድቅ መንፈስ እየሱስ ሲመጣ አልተመቻቸውም ምክንያቱም ይህ የጽድቅ መንፈስ ይወቅሳልና እንጂ ዮሃንስስ አልተነሳም:: የእግዚአብሔር መንፈስ አንዱ ስራው ስለሐጥያት መውቀስ ነውና ሰዎች በሐጥያት ሲመላለሱ ስለሚወቀሱ ቅዱሳንን መሸሽ ይጀምራሉ:: እኛ ግን ታረቁ የምንል ነንና በየዋህነት መንፈስ ሰዎችን እናቅና:: እግዚአብሔር እጅግ የሚምር የሚራራና ማንም እንዲጠፋ የማይፈልግ ጌታ ነውና ብርሃናችን ሁልጊዜ የበራና ለዚህ ጨለማ ዓለም ብርሃን መሆንን እንቀጥል:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው

የማርቆስ ወንጌል 6: 30-44
30፤ ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። 31 እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። 32 በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ። 33 ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ። 34 ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። 35 በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤ 36 የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው አሉት። 37 እርሱ ግን መልሶ። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት። 38 እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ አላቸው። ባወቁም ጊዜ። አምስት፥ ሁለትም ዓሣ አሉት። 39 ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው። 40 መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ። 41 አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ 42 ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ 43 ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ። 44 እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ። 

ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት በዚህ ጊዜ ነው በሉ ወደ ምድረ በዳ እንውረድ የሚላቸው ምክንያቱም እንዲያርፉ:: ግን ምድረ በዳ የእረፍት ቦታ ነው? እስኪ ከየት እንደመጡ እንየው :- ከአገልግሎት ድል በድል ሆነው ትንሽም ብትሆን ልባቸው አበጥ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ እየሱስ አብሯቸው ሳይኖር ትልልቅ ነገሮችን አድርገው ተደንቀው እያሉ ነው የምድረ በዳ ጥሪ የመጣው:: ነገሩ እንዲያርፉ፤ እንዲበሉ፤ እራሳቸውን ተረጋግተው እንዲያዩ ደግሞም ለነገው አገልግሎት አቅም እንዲኖራቸው ብሎ ነው:: ቁጭ ብሎ ድልን ማውራት ለፈተናና ሽንፈት ያጋልጣል::

ወደ ምድረ በዳ ሲሄዱ ሰዎች በዛ ጠበቁዋቸው ድካም ቢኖርም እንኳን ለማረፍ ቢሆንም የሄዱት እየሱስ ማገልገልን ቀጠለ:: አስተምሮ ሲጨርስም የሚበሉትን ስጡአቸው ብሎ እርፍ:: እምድረ በዳ ላይ ምግብ ከወዴት ይመጣል እራሱ አይደል እንዴ እረፍት ያስፈልጋችኃል ብሎ የወሰዳቸው እንደገና ስራና አሳብ ውስጥ ገቡ ህዝቡ ብዙ ነው ለዚህ ሁሉ የሚሆን ምግብ ከየት ደግሞስ በምን ያህል ገዝተን ተሸክመን ልናመጣ ነው? ብዙ ነገር ነው ጭንቅላታቸው ውስጥ የሚመላለሰው:: እየሱስም ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው አጣርተው አምስት እንጀራና ሁለት አሳ ብለው መለሱ:: ከአምስት ሺህ በላይ የሆነ ህዝብ ለመመገብ አስቀመጧቸው ያላቸው ግን አምስት እንጀራና ሁለት አሳ ብቻ ነው:: አመስግኖ ቆራርሶ ሰጣቸው እያንዳንዳቸው ቁራሽ እንጀራና አሳ ደረሳቸው እንጂ የተቆለለ ምግብ ወይም በትሪው ላይ ተቆልሎ መሸከም እቅቷቸው ነበር አይልም:: ስለዚህ የሆነው ነገር የመጀመሪያውን ቁራሽ ሲሰጡ የሚቀጥለው ይመጣል:: እምነታቸው ነው የታየው ኢቺ ቁራሽ ናት ይህንን ሁሉ ህዝብ የምትመግበው ብሎ መቀበል:: ሐዋርያት ከአገልግሎት መተው ብዙ ነገር አወቅን ብለው እያሉ ነው እንግዲህ ከዚህ በፊት አይተውት የማያውቁት ትምህርት ሊያስተምራቸው የፈለገው:: ግን አምነው ቁራሽዋን ይዘው ለማደል ተነሱ:: ተአምራቱ በእጃቸው ላይ በዛ ያ ሁሉ ህዝብ ተመግቦ የተረፈው አስራ ሁለት መሶብ ነበረ:: ተአምር!

በእጃችን ላይ ያለውን ነገር ይዘን እንቅረብና እንመን እርሱ የሚሰራውን ያውቃል ያትረፈርፈዋል::


ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር

የማርቆስ ወንጌል 6: 45-56
45፤ ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። 46 ካሰናበታቸውም በኋላ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 47 በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ። 48 ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር። 49 እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥ 50 ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው። 
51 ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤ 52 ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር። 53 ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ። 54 ከታንኳይቱም ሲወጡ ወዲያው አውቀውት 55 በዚያች አገር ሁሉ ዙሪያ ሮጡና እርሱ እንዳለ ወደ ሰሙበት ስፍራ ሕመምተኞችን በአልጋ ላይ ያመጡ ጀመር። 56 በገባበትም ስፍራ ሁሉ፥ መንደርም ከተማም ገጠርም ቢሆን፥ በገበያ ድውዮችን ያኖሩ ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

ሐዋርያቱን አሰናብቶ እርሱ ግን እንደለመደው ለጸሎት ወደ ተራራ በምሽት ወጣ:: ለምን አብረው እንዳልጸለዩ አይገባኝም ጻድቅ በምቹ ጊዜ ይጸልያል ይላልና ቃሉ:: በእርግጥ እንዲሄዱ ግድ አላቸው እራሱ ጌታ በመሄዳቸው ግን አትርፈዋል ብዬ ለማለት ይከብደኛል ከማዕበል ጋር ነው ሲታገሉ የነበሩትና::

ሲጨነቁ አይቶ በባህሩ ላይ እየተራመደ መጣ ከማዕበሉ የበለጠ ያስፈራቸው ግን ይህ ምትሀት ብለው የጠሩት ነገር ነው ከውሀው ብንተርፍ ይህ ነገር ይገድለንማል ሳይሉ አይቀሩም:: የጌታን ስም መጥራትና መቃወም የሚለው አሳብ ውልም ያለባቸው አይመስሉም ብቻ ባለ በሌለ ኃይላቸው ከማዕበል ጋር መታገል ይዘዋል:: ልክ እንደታሪክ አንብበን ካለፍነው አንማርበትም ነገር ግን ይሄ የብዙዎቻችን ችግር ነው ብዬ አምናለሁ ከነገሮች ጋር መታገል:: ይልቅስ ወደ ዙፋኑ እናምጣው አምላካችን መፍትሄ አለው መንገድ በሌለበት ውስጥ መንገድን ያወጣል:: ጌታም አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸውና ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ::

ለምን እንዲሄዱ ግድ አላቸው? ይህ ችግር እንደሚመጣ ያውቅ የለም እንዴ? ያልን እንደሆነ ከሰአታት በፊት የሆነውን በአእምሯቸውም አልመዘገቡት በቁራሽ እንጀራና አሳ ስንትና ስንት እንደመገቡ ከዛም ስንት መሶብ እንደተነሳ ተአምራት በፊታቸው ተደርጎ ነበር:: መቼም ይህንን ስናይ ምን ነካቸው እነዚህ ሰዎች ብለን እንፈርዳለን የእኛም ታሪክ ዛሬ ቢጻፍ እመኑኝ ከዚህ ላይሻል ይችላል:: ለዚህ ነው መንፈስ ቅዱስ የተሰጠን የተማርነውን እንዲያሳስበን፤ ወደ እውነትም ሊመራን፤ ሊያበረታን፤ ከእኛ ጋር የሚኖር ረዳት፤ ለቤዛነት የታተምንበት ጌታ ዛሬ ኃይላችን ነው:: ማንም እንዳይመካ ሁሉን በእኛ ውስጥ እያደረገ ያለው እርሱ ነውና አሁንም ከመደንንዘዝ ያውጣንና ወደ ማስተዋል ይምራን!

በዚህ ሁሉ ውስጥ መቼም የጌታ ትዕግስት ይደንቃል ልቡን ሰፊ አድርጎ ነው የሚያገለግላቸው:: እኛም ልባችንን አስፍተን እናገልግል:: ወደ ጌታ የመጡትና የዳሰሱት ሁሉ ተፈወሱ:: ጌታ ዛሬም ይፈውሳል::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 7

ወግን ለመጠበቅ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መሻር

የማርቆስ ወንጌል 7: 1-23
1፤ ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡትም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንድ በርኵስ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ። ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፥ ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፥ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ። ፈሪሳውያንም ጻፎችም። ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች። ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። እንዲህም አላቸው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። 10 ሙሴ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና። 11 እናንተ ግን ትላላችሁ። ሰው አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው ቢል፥ 12 ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤ 13 ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። 14 ደግሞም ሕዝቡን ጠርቶ። ሁላችሁ እኔን ስሙ አስተውሉም። 
15 ከሰው የሚወጡት ሰውን የሚያረክሱ ናቸው እንጂ ከሰው ውጭ የሚገባውስ ሊያረክሰው የሚችል ምንም የለም። 16 የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ አላቸው። 17 ከሕዝቡ ዘንድ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ምሳሌውን ጠየቁት። 18 እርሱም። እናንተ ደግሞ እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ሊያረክሰው ምንም እንዳይችል አትመለከቱምን? 19 ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና፤ መብልን ሁሉ እያጠራ አላቸው።20 እርሱም አለ። ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው። 21 ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ 22 ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤ 23 ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል። 

ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። እነማን ናቸው ይህንን ጥያቄ የጠየቁት ስንል? ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና ጻፎች ናቸው:: እንከን ማውጣት ክህሎታቸው ነው ሁልጊዜ በምን እንደሚያጠምዱት ስለሚፈልጉ እግዚአብሔር ትኩረት ያልሰጠውን፤ በነሱ አይን ግን ትልቅ ስፍራ የተሰጠውን የእጅ መታጠብ ስርአት አካብድው ጊዜውን ያጠፉበታል:: ይህንን ሳነብ ጌታ እዚህ ግባ የማይለው ነገር እኔ ግን ሙጭጭ ብዬ የያዝኩት ምን ይሆን ብዬ አሰብኩኝ፤ ዋናውን ጉዳይ ወደጎን እንዳደርግ የሚያደርገኝ ነገር ካለ መንፈስ ቅዱስ ፈትሸኝና ልወቀው ነው ጸሎቴ:: አንባቢም እራሱን ቢያይ አይከፋም::

ለጥያቄያቸው የጌታ መልስ መቼም እሱ ባይልም እንኳን ስለ እዳሪ አታስቡ ይልቅስ ከልባችሁ የሚወጣው እንዳያረክሳችሁ ተጠንቀቁ ልብና ሆድ ከአንድ አይመገቡም ነበር መልሱ:: ጎሽ ጥሩ አደረጋችሁ ወይም የኔዎቹ ልክ አይደሉም ነበር የጠበቁት መልስ እርሱ ግን ትንቢትን በመጥቀስ ከዚህ በፊት ተነገራችሁ አሁንም እዛው ላይ ናችሁ? ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ።  የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። እንዲህም አላቸው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል።  ተብለው በትእዛዝ ሰጪው እየተነገራቸው እያለ እሱን ተወውና እጅ መታጠብ አስፈላጊ ነው ይላሉ:: የህዝቡንም ትኩረት ወደ ተራ ጌታ ወዳልስጠው ነገር በመምራት ደርሶ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ እየመሰላቸው ነው:: ስንቱ ይሆን ሚዛን በማያነሳ ነገር ላይ ጊዜውን የሚፈጅ ዛሬ በእኛ ዘመን? ጌታ ይርዳን!

ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥  ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤  ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል። ህይወታችንን በቃሉ እንጠብና እንቀድስ:: በእኛ ህይወት ውስጥ እንዲመጥን አድርገን ቃሉን አንጠምዝዝ ይልቁንስ ህይወታችንን ወደ ጸጋ ዙፋኑ አቅርበን በሚያስፈልገን ጸጋ ተሞልተን የልቡን አሳብ እናገልግል::


ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት

የማርቆስ ወንጌል 7: 24-30
24፤ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። ወደ ቤትም ገብቶ ማንም እንዳያውቅበት ወደደ ሊሰወርም አልተቻለውም፤ 25 ወዲያው ግን ታናሺቱ ልጅዋ ርኵስ መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ተደፋች 26 ሴቲቱም ግሪክ፥ ትውልድዋም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች፤ ከልጅዋ ጋኔን ያወጣላት ዘንድ ለመነችው። 27 ኢየሱስ ግን። ልጆቹ በፊት ይጠግቡ ዘንድ ተዪ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምና አላት። 28 እርስዋም መልሳ። አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው። 29 እርሱም። ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት። 30 ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። 

ይህች አህዛብ ሴት የጨነቃት እናት ናት ልጅዋን አጋንንት ይዞ ያሰቃየባት ናት:: የትኛውም የምድር አካል ሊረዳት አይችልም ከጌታ በቀር:: ጌታጋርም ስትሄድ ለአንቺ አይደለም የመጣሁት ልጆች ይጥገቡ ዘንድ ተዪ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምና አላት:: አይሰጥሽም የተባለችው ፈውስን በምን መልክ እንደሚጠራው ስናይ እንጀራ ይለዋል:: እንጀራን በአባታችን ቤት መብላት ለእኛ ነው ፈውስም እንጀራችን ነው አንከለከልም:: ቡችላ ብሎ ቢጠራትም ከእንብርክክዋ ሳትነሳ ክብርን እየሰጠችው ጌታ ሆይ፥ ብላ እየጠራችው ቡችሎችም እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው። የሙጥኝ ዛሬ አለቅህም ልጄን ሳትፈውስ ተሰቃይተናል የሚረዳንም የለም እናም ብዙ ብዙ ነገር ነው በውስጥዋ እየተመላለሰ ያለው::

እየሱስም ያለ መልስ እንደማትሄድ ቆርጣ አምና መምጣትዋን አይቶ እምነትን ማለፍ ስለማይችል ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት። ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። ባይፃፍም ቅሉ ምስጋናና እልልታ በዛ ቤት እንደሚበዛ እርግጠኛ ነኝ:: ትልቅ እረፍትን በቤትዋ አደረገ ካመንን ለእርሱ መስራት ቀላል ነው::


ሁሉን ደኅና አድርጎአል

የማርቆስ ወንጌል 7: 31-37
31፤ ደግሞም ከጢሮስ አገር ወጥቶ በሲዶና አልፎ አሥር ከተማ በሚባል አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። 32 ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፥ 33 እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት። ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ 34 ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና። ኤፍታህ አለው፥ እርሱም ተከፈት ማለት ነው። 35 ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ። 36 ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት። 37 ያለ መጠንም ተገረሙና። ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ።

የዚህን ከተማ ስም ማር 5:1-20 ባለው ታሪክ ላይ እናውቀዋለን:: ሌጊዎን ይዘው በመቃብር ስፍራ ሲያሰቃዩት የነበረው ሰው ከተፈወሰ በኃላ የተደረገለትን የሚሰብክበት ስፍራ ነው:: እሱን በፈወሰው ጊዜ ግን እሪያዎቻቸው ስላለቁባቸው ሰዎቹ ወደ ከተማችን አትገባም ብለው ጌታን ከዛው መልሰውት ነበር ዛሬ ግን በሽተኞቻቸውን ወደ እርሱ አመጡ እርሱም ፈወሰላቸው::

ጌታ ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ሲፈውስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም በሌሎችም ወንጌላት ላይ ተፅፏል ሁሉንም አጋንንት ነበር የያዛቸው የዚህኛው ላይ ገስጾ ሲያወጣ አናይም:: ህዝቡም እጁንም ይጭንበት ዘንድ ነበር የለመኑት ነገር ግን ከዛ በላይ ነበር ያስፈለገው:-

  1. ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ መለየት ያስፈልገው ነበር ከተጽእኖና ከማንኛውም ልምምድ
  2. ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ
  3. እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ ማየት የተሳነውንም በዚህ ሁኔታ ፈውሶ ያውቃል
  4. ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና :- ጸሎት ያስፈልጋል ፈውስን ለማግኘት እንጂ እጅ ብቻ ስለተጫነ ላይመጣ ይችላል
  5. ኤፍታህ አለው፥ ቃልን አወጀ ይፈታ ዘንድ::

ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ።  ያለ መጠንም ተገርመው ያሉት አባባል ደስ ይላል:- ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ሃሌሉያ የእኛ ጌታ ሁሉን ደህና ያደርጋል በጥያቄያችን ላይ መልስ አለው:: ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ ዛሬም ያደርጋል ይሄ ጌታ ህያው ነው።

ፈውስን ስናስብ ከጌታ ምሪት የሚያስፈልገው ነው አንድ አይነትን በሽታ በተለያየ መልኩ ሲፈውስ እናያለን ስለዚህ ምሪት እንቀበል እርሱ እንጂ እኛ ፈዋሾች አይደለንም የሚለንን እናድርግ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 8

አዝንላቸዋለሁ አለ እየሱስ

የማርቆስ ወንጌል 8: 1-13
1፤ በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም። በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት። እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው፥ እነርሱም። ሰባት አሉት። ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፥ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ለሕዝቡም አቀረቡ። ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ። በሉም ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ። የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ። 10 አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ። 11 ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር። 12 በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ። 13 ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ። 

ጌታ ለህዝቡ አዝንላቸዋለሁና የሚበሉትን ስጧቸው አለበለዚያ በመንገድ ይደክማሉ ብሎ ለህዝቡ እንደ እረኛ ሲቆረቆር እራሴን በዛ ውስጥ እያሰብኩኝ ደስ አለኝ ጌታዬ ያስብልኛል:: እንደተለመደው ሐዋርያት የትናንቱን ተአምር እንዴት ህዝቡን እንደመገበ ጠፍቷቸው በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት:: ወቸ ጉድ ምድረ በዳ ቢሆንስ በአይን መፍትሄው ባይታይስ ለጌታ ምን ተስኖት? እኛም የያዝነው ይህንኑ ነው የትላንቱን እየረሱ ጥሬ መሆን አቤኔዘር እንበል እንጂ?! እርሱም የመለሱለትን ልክ እንዳልሰማ ምን አለ እጃችሁ ላይ አለ? ሰባት አሳ ጥቂትም አሳ አሉት:: እንደልማዱ በሉ አምጡ ብሎ ባርኮ ሰጣቸው:: ህዝቡም በሉ ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ። የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ። አሰናበታቸውም ይልና ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ ይላል:: አሁንም ረጋ ብለው የሆነውን ነገር ለማገናዘብ ጊዜ አልነበራቸውም አንድ ምዕራፍ ተዘጋ እጃቸውን እያራገፉ ወደሚቀጥለው ሩጫ:: እኛም እዛው ላይ ነን ያለነው ተረጋግተን እንመላለስ ትላንትን ያለፍነው በእርሱ ነው:: የምናልፍበትን የሚያውቅ ነውና እንታመን ያዝንልናልና:: ምድረ በዳውን አይተን ከየት ነው መፍትሄ የሚመጣው ብለን ተስፋ የቆረጥንበት ጊዜ ነበረ ግን ጌታ ደርሶ አሻገረን:: አይጥፋብን የትናንቱ እናመስግን::

ጌታ የሚገርመው እጅግ ታጋሽ መሆኑ እንጂ ሰው ቢሆን እነዚህን መልሶ ሌላ ሐዋርያትን ይመለምል ነበር:: ግን ዛሬን ሳይሆን የነገውን ማንነታችንን እያየ እኛንም ታግሶ በመንፈሱ ያነቃናል:: ሃሌሉያ! እጅግ የሚምርና የሚራራ ጌታና አባት አለን::

ወደ ማዶም ሲሻገር የባሰ ያለማመን ነበር የገጠመው ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር።  ቢያውቁት ግን ባከበሩት ነበረ:: በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ። ትልቁ ምልክት የእግዚአብሔርን ልጅ ከማየት በላይ ምን ሊኖር ይችል ይሆን? መተላለፍ!! ጸጋው ይብዛልን! አሜን!


ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው

የማርቆስ ወንጌል 8: 14-21
14፤ እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። 15 እርሱም። ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው። 16 እርስ በርሳቸውም። እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ። 17 ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? 18 ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? 19 አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም። አሥራ ሁለት አሉት። 20 ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም። ሰባት አሉት። 21 ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው። 

ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው:: የእግዚአብሔር ቃል ስለ ሰጎን በኢዮብ 39: 17፤ እግዚአብሔር ጥበብን ከእርስዋ ከልክሎአልና፥ ማስተዋልንም አልሰጣትምና። ይላል እዚህም ክፍል ላይ የምናየው ሐዋርያት ማስተዋል አተው ፊታቸው የተደረገው ተአምር በአእምሯቸው ሳይመዘግቡት ከእነሱም ሳይዋሀድ ቀርቷልና ሊጠቀሙበት አልቻሉም:: ለዚህም ነው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 2: 14፤ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። ስለዚህ ቃሉን ለመረዳት መንፈሳዊ መሆን አለብን:: ትዝ ይለናል እኮ ምን እንዳደረገ ዘርዝረን መናገር እንችላለን አንዳችም ሳይቀር አምስቱን እንጀራ አምስት ሺህ ተመግበው አሥራ ሁለት መሶብ ቍርስራሽ እንደተነሳ። እንዲሁም  ሰባቱን እንጀራ አራት ሺህ ተመግበው ሰባት መሶብ ቍርስራሽ እንደተነሳ አይጠፋንም መዘንጋት አይደለም ችግሩ ችግሩ መዋሀዱ ላይ ነው። እዚህ ክፍል ላይ አንድ እንጀራ ነበራቸው እኮ ይህ አንድ እንጀራ ለተፈለገው ቁጥር መብዛት ይችል ነበር ግን አላስተዋሉም ልባቸው ደንዝዞ ነበረና:: ታድያ በእምነት ካልተዋሀደ ምንም አይጠቅምምና ምን እናድርግ? አለበለዚያ በቀላሉ ጠላት መቶ ይለቅመውና ስራውን ያቃልላል:: በኢያሱ 1: 8፤ የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ይህ ነው የሚያስፈልገው ደግመን ደጋግመን ማንበብና ለሌሎችም ማካፈል ያኔ በልባችን ላይ ይጻፋል::

ሌላው ተጠንቀቁ፥ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው ይላል ቃሉ:: ከምን? ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ይህም ማለት ከዓለም ነገርና የራስን ጽድቅ ከማቆም መጠንቀቅ እንዳአለብን ነው የሚነግረን:: እኛ ጽድቃችን እየሱስ ነውና በእርሱ የምንመካ ነን ይህ አይጥፋብን:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


አጥርቶም አየ

የማርቆስ ወንጌል 8: 22-26
22፤ ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት። 23 ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፥ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት። አንዳች ታያለህን ብሎ ጠየቀው። 24 አሻቅቦም። ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ። 25 ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየና ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ። 26 ወደ ቤቱም ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው። 

ለየት ያለ ተአምራት ነው በዚህ ስፍራ የተደረገው:: ይኸውም በመጀመሪያ ከከተማ ይዞት ወጣ ሌላው ደግሞ አንዳች ታያለህን ብሎ መጠየቁ:: ስለ ቤተ ሳይዳ በሌላ ስፍራ የተናገረው ካላነበብን ይህንን ታሪክ ለመረዳት ይከብደናል:: በማቴዎስ 11: 21፤ ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ንስሀ አለመግባታቸው ወይም ከጌታ ያለመተባበራቸው ምክንያት አለማመን ነው:: ከተማዋ ሁሉ ባለማመን ተሞልታ ህዝቡም ሁሉ በአለማመኑ ስለፀና ይህንን ሰው እንዴት ይፈውሰው? ምክንያቱም በማርቆስ 6: 5፤ በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። 6፤ ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። ያለ እምነት ፈውስ ሊመጣ አይችልምና:: ሰውየውን ለመርዳት ነው ምን ታያለህ ያለው እንጂ ጸሎቴ ተሰምቶ ይሆን ከሚል ጥርጣሬ አይደለም:: እምነት ማጣት ተአምራትን ስለሚያቆም እንጂ:: ደግሞ ጸለየ ሰውየውም አጥርቶ አየ ከዛም ወደ ቤቱ ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው:: ለምን ይሆን ለማንም አንዳች አትናገር ያለው? እምነቱን ሸርሽረው ፈውሱን እንዳያስጥሉት ነው:: እኛም ከምንሰማው እንጠንቀቅ ደግሞም ድንቅና ተአምራትን አማኞች እንሁን:: ጌታ ዛሬም ይሰራል:: ማስተዋል ይስጠን!


ማን ትሉኛላችሁ?

የማርቆስ ወንጌል 8: 27-33
27፤ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም፦ ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። 28 እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት።29 እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም። አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። 30 ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። 31 የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር። 32 ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። 33 እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለው። 

እየሱስ ሰዎች ማን እንደሆንኩ ይላሉ ብሎ ጠየቃቸው የሚባለውን ነገሩት:: እርሱም እናንተስ? ብሎ ጠየቃቸው:- ጴጥሮስም አንተ ክርስቶስ ነህ አለው:: አሜን! ለእኛስ ይሄ ጌታ ማነው? እዳችንን በመስቀል የከፈለ፤ ሳንወደው የወደደን፤ በደሙ ያጠበን፤ የቀደሰን፤ ለመንግስቱ ካህናት ያደረገን፤ ብሎም ልጆቼ ያለንና በመንፈሱ የሞላን ጌታችን፤ አዳኛችን፤ ንጉሳችን ነው! አሜን!

ትንሽም ቆይቶ የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር:: በዚህ ጊዜ ወንድማችን ጴጥሮስ አይሁንብህ ብሎ ሊመክረው ተነሳ:: ክፉ ከመመኘቱ ሊያወጣውና የወዳጅነቱን ሊነግረው ቢመስልም ቅሉ ነገሩ ግን ወዲህ ነው:: ይህንን አሳብ ወደ ጴጥሮስ የላከው ሰይጣን ስለሆነ ነው ጌታም በጴጥሮስ የተጠቀመውን ጠላት የገሰጸው:: የእርሱን አሳብ አንስተውም እንደሚል ቃሉ እንዳንስት የሚያስፈልገን የቃሉ መነጽር ነውና በቃሉ ውስጥ አሳባችንን እንየው ደግሞም እንፈትሽ:: እዚሁ በዚሁ ከአንድ ጥግ ወደሌላው ሲወነጨፍ የምናየው የሰውን ድክመት በቃሉና በመንፈሱ ማሸነፍ እንችላለን:: ለምን ይመስላችኃል ጠላት ቃሉን የሚለቅመው? እንዳናመልጥበት፤ እንዳንጸናበት፤ የእርሱን ሽንገላ እንዳንመክትበት ብሎ ነው ቃሉ በልባችን ከእኛ ጋር ከተዋሃደ በፍጹም አያታልለንምና:: ጴጥሮስ አይኑን ማድረግ የነበረበት ትንሳኤው ላይ ነበር ሞቼ እቀራለሁ አላለምና:: አይናችንና አትኩሮታችን በእርሱ ላይ ይሁን:: በቃሉና በጸሎት ስር እንስደድ ጌታ ጸጋውን ያብዛልን:: አሜን!


ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ

የማርቆስ ወንጌል 8: 34-38
34፤ ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 35 ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። 36 ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? 37 ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? 38 በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።

ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር፥

  1. ራሱን ይካድ – የመጀመሪያ ነገር በክርስትና ራስን መካድ ነው ምክንያቱን ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።
  2. መስቀሉንም ተሸክሞ – ብዙ ጊዜ የመከራ ምሳሌ ይመስለናል ነገር ግን መቁረጥን ወደኃላ አልማፈግፈግንና ታማኝነትን ያሳያል:: ከጨከንን በጌታ አናፍርም የመጣውን ሁሉ እንቀበላለን እንጂ አናፈገፍግም::
  3. ይከተለኝ – መከተል መቼም የምንከተለውን ሰው አሳብ ብቻ ማስተናገድ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው:: ስለዚህም ነፍሳችንን ልናድን የምንዋትር አይደለንም እርሱን ለማክበርና ለመታዘዝ የምንተጋ እንጂ:: አለበለዚያ ለነፍሳችን ቤዛ የምንሰጠው እራሳችንን ክደን በመከተል ለእሱ ላዳነን ነው::
    የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!

እየሱስ በፊታቸው ተለወጠ

የማርቆስ ወንጌል 9: 1-13
1፤ እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ፡ አላቸው። ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፥ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም። የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። 10 ቃሉንም ይዘው። ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። 11 እነርሱም። ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። 12 እርሱም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናናል፤ ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም። 13 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ደግሞ መጥቶአል፥ ስለ እርሱም እንደ ተጸፈ የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት አላቸው። 

የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ ብሎ ባለው መሰረት ከስድት ቀን በኃላ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው:: ብዙ ጊዜ እነዚህን ሶስት ሐዋርያት ለይቶ ይወስዳል በመጨረሻም መሪ የነበሩት እነዚሁ ናቸው ከፊታቸው ላለው ኃላፊነት እያዘጋጃቸው ነበረ ባይገባቸውም እንኳን:: ጌታ ጊዜን አያባክንም ለመረጠን ስራ እያዘጋጀን ነውና መክሊታችንን እንዳንቀብር እንመንዝረው:: እዚህ ጋር እንደምናየው የመንግስቱ ክብርና ሞገስ ሲገለጥ እንዳልተዘጋጁ ያስታውቃል የሚሉትን አያውቁም ነበረና:: እርሱ ግን ቃሉን ጠብቋል ክብሩን አሳይቷቸዋል:: እኛም እስራው ላይ እንቁም እርሱ እራሱ ይመራናል ያስተምረናል ወደ እርሱ ካልቀረብን ግን የተሰጠንን የመንግስቱን ስራ መስራት አንችልም::

የእግዚአብሔር መንግስት ሲገለጥ

  1. ፍርሃት ይሆናል :- እግዚአብሔርን መፍራት ይወድቃል:: እዮብ ይህንና ያንን እጠይቀዋለሁ ይገለጥ ሲል ከርሞ አንድም ጥያቄ መጠየቅ ትዝ አላለውም::
  2. እራስንም መርሳት ይመጣል:- ለእኛ በዚህ መሆን መልካም ነው ብሎ ሲያበቃ ዳስ እንስራ ብሎ ያለበት ዝርዝር ውስጥ እርሱ የለም:: እርሱን ደስ ለማሰኘት እንጂ እራሳችንን የምንረሳ ነው የምንሆነው::
  3. የእግዚአብሔር ድምጽ መስማት አለ:- እግዚአብሔር አብ ስለ ልጁ ሲመሰክር ሰሙ:: ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም። የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።

ዛሬም እርሱን እንስማ ከቃሉ እናገኘዋለን የሚለንን በጸሎት ወደ ፊቱ እንቅረብ በመገዛትም ወደ አደባባዮቹ እርሱም ህያው ነውና ያበራልናል ደግሞም ይገኝልናል:: አሜን!

ክብሩን ዛሬ እንጠማ እንፈልግ እንበረታታ የፈለጉት ሁሉ አግኝተውታልና ፊታችን አያፍርም ያለ ክብሩም አንዳች ማድረግ አይቻልም:: ሃሌሉያ! አሜን!
ሶስቱን ሐዋርያት ብቻቸውን እንደወሰዳቸው ከእያንዳንዳችን ጋር ጉዳይ አለውና ፊቱን በመፈለግ እንትጋ::

ከተራራውም ሲወርዱ አንድ ትእዛዝ ሰጣቸው የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ እነሱም ቃሉንም ይዘው ግራ ገብቷቸው ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ከዛም ትዝ ያላቸው ነገር ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት እንግዲህ የምናውቀው ይመጣል የሚባለው ኤልያስ ነው ብለው:: እርሱ ሲያስተምራቸው የከረመውን ረስተውታል እንደሚሞትና እንደሚነሳ አይሁንብህ ሁሉ ብለው ሲያበቁ ውስጣቸው አልተቀመጠምና ምንም አልገባቸውም:: እንገረም ይሆናል በነሱ ነገር እስኪ አንድ ነገር ልጠይቅ ስንት ጊዜ የጌታን እርዳታ አይተን ሌላ ችግር ሲመጣ አዲስ ሆነን አናውቅም? እኛም ያው ነን መንፈስ ቅዱስ ይርዳን እንጂ ቃሉን በቀንም በለሊትም እናመንዥግ አለበለዚያ እውቀት ብቻ እንጂ መገለጥ ሆኖና የህይወት መመሪያ ሆኖ በልባችን አይመዘገብም:: እንደነገሩ አይሁን የጌታን ቃል ስናነብና ስንሰማ ጌታ አጠገባችን ሆኖ እንደሚናገረን አክብረን በልባችን እየተንቀጠቀጥን እንስማ::

ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም ብሎ አለ እየሱስ እርሱ ስለእኛ ነው ክብሩን ትቶ ባዶ ሆኖ የባርያን መልክ ይዞ የመጣው:: ክብር ከዘላለም እስከ ዘላለም ለስሙ ይሁን:: ለዚህ ስለ እኔ ለተናቀውና መከራን ለተቀበለው ጌታ እኖራለሁ አከብረውማለሁ ዘመኔም ይገባሀል አባት ሆይ:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


እየሱስ:- ወደ እኔ አምጡት አለ

የማርቆስ ወንጌል 9: 14-29
14፤ ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ሲከብቡአቸው ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አየ። 15 ወዲያውም ሕዝቡ ሁሉ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፥ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። 16 ጻፎችንም። ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። 17 ከሕዝቡ አንዱ መልሶ። መምህር ሆይ፥ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ 18 በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፥ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፥ አልቻሉምም አለው። 19 እርሱም መልሶ። የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው። 20 ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። 21 አባቱንም። ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ 22 ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው። 23 ኢየሱስም። ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። 24 ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ። አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ። 25 ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና። አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፥ ከእርሱ ውጣ እንግዲህም አትግባበት አለው። 26 ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም። ሞተ እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። 27 ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው ቆመም። 28 ወደ ቤትም ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ። እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው? ብለው ብቻውን ጠየቁት። 29 ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም አላቸው። 

በዚህ ክፍል ላይ የተጨነቀ አባት የታመመ ልጁን አምጥቶ ደቀ መዛሙርቱ ሊረዱት አልቻሉም:: እየሱስ ክብሩን ለተወሰኑት ሐዋርያት አሳይቶ ሲመለስ የጠበቀው ይህ ነበር:: ከቻልክ እርዳን የሚል ተስፋ የቆረጠ ሰው ጥያቄ ትላንትና ልኳቸው አጋንንት በስምህ ተገዛልን ብለው የነገሩት ሐዋርያት ሊረዱዋቸው አልቻሉም ምናልባትም እርሱም ሐዋርያቱም ይፈውሳሉን ሰምቶ የመጣ መሆን አለበት ለዚህም ተስፋ ቢቆርጥ አይደንቅም:: እየሱስ ግን መልሶ ብትችልስ? ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ብሎ አለው:: እርሱማ ይችላል እኔ ነኝ አምኜ መቀበል ያለብኝ:: እየሱስ ሰውን ሲነቅፍ የነበረው እምነት ሲያጡ ነው:: አንዳንዱ ጸሐይ ትቁም ብሎ አምኖ ጸልዮ አቁሞ የለም እንዴ ብዙ ነገርን ሊያዛባ የሚችል ያልገባው በሌላ ስፍራ የሚኖር ይሄኔ ጸሐይ ሳትጠልቅ ቆየች ብሎ ይል ይሆናል ለሌላው ደግሞ ምነው ጠዋቱ ጨለመ ይላል ዓለም ሁሉ የሚያየው ጸሎትና ውጤት እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ ነው እርሱ ይችላል እኛ እንታመን::

የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው። ትልቁ እምነትን የሚሰርቅ ነገር ቢኖር በእኛ ልክ እግዚአብሔርን ማየት ነው:: የተባልነው በራሳችሁ አንዳች ማድረግ አትችሉም ነውና ወደ እኔ አምጡት እንዳላቸው ሁሉን ነገር ወደ እርሱ እናምጣ እንዴት እንደሚሰራ የሚያውቀው እርሱ ነው ብቻ እንመን:: በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ ብሏልና እየሰማን እንታዘዝ እርሱ ሁልጊዜ ይሰራል:: የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ እምነትን በምድር ያገኝ ይሆንን? ብሎ ጌታን ያሳሰበው ጉዳይ ነውና ከጭንቅላታችን ጭላንጭል እውቀት እንውጣና በጌታ ላይ እንታመንና ክብሩን እንይ:: ስንተጋ በጾምና በጸሎት ወደ እርሱ እየቀረብን ነውና እርሱም ወደ እኛ ይቀርባል ታድያ ጨለማ በብርሃን ፊት እንዴት መቆም ይችላል:: ብርሃኑ ግድ ይወርሳል ጨለማችንን ያበራ ጌታ በእኛ ውስጥ ከዚህ ከሸክላ ውስጥ የከበረውን ማንነቱን ያሳያል ታምነን እንሰማራ ምንም አይነት አጋንንት በፊታችን አይቆምም! አይችልማ ሃሌሉያ! ከዛ በኃላ ጻፎች ሲከራከሩ አልታዩም ምክንያቱም ወንጌል በእውነት ከኖርነው የሚታይ ነውና ምን ክርክር ያስፈልጋል በተግባር እየታየ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም

የማርቆስ ወንጌል 9: 30-37
30-31፤ ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ያስተምር ስለ ነበር ማንም ያውቅ ዘንድ አልወደደም፤ ለእነርሱም፦ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ይገድሉትማል፥ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል፡ ይላቸው ነበር። 32 እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም፥ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። 
33 ወደ ቅፍርናሆምም መጣ። በቤትም ሆኖ። በመንገድ እርስ በርሳችሁ ምን ተነጋገራችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። 
34 እነርሱ ግን በመንገድ። ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? ተባብለው ነበርና ዝም አሉ። 
35 ተቀምጦም አሥራ ሁለቱን ጠርቶ። ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው። 
36 ሕፃንም ይዞ በመካከላቸው አቆመው አቅፎም። 
37 እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው።

እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም ዋናውን ነገር ማስተዋል አልቻሉምና ይስቱ ነበረ:: የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ይገድሉትማል፥ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል፡ ይላቸው ነበር። ልብ ብለው ቢሰሙት ጥሩ ነበረ ምክንያቱም እሞታለሁ ብቻ ሳይሆን እነሳለሁ ነበር እያላቸው ያለው:: ኢቺ ብቻ ገብታቸው ቢሆን ኖሮ ሳይበታተኑ እየተጉ በጠበቁት ነበር:: በእርግጥ የሞተ ሲነሳ ያዩት ሶስቱ ሐዋርያት ሙሴን ነበር በክብሩ መገለጥ ጊዜ ኤልያስስ ተወሰደ እንጂ አልሞተም ለነገሩ ብዙም ልብ አላሉትም ከመደንገጣቸው በቀር እናም አሁን ከሙታን መካከል እነሳለሁ ሲል እንደነገሩ ሰምተውታል ግን ሆኖ ስለማያውቅ ችላ ብለውታል ለዚህም ነው ከሞተ በኃላ ሁሉም ወደ ጉዳዩና ህይወቱ የተመለሰው ከትንሳኤው በኃላ አብሯቸው ባይሆን አይጸኑም ነበር:: እጅግ የሚምርና የሚራራ ጌታ ራራላቸውና ወደ አገልግሎታቸው አበርትቶ መለሳቸው:: ዛሬስ እንዴት ባለ ልብ ይሆን ቃሉን የምንሰማው? እናስተውል ጌታ በብዙ መንገድ ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም ነውና የሚለው በማስተዋሉ ይሙላን::

እርሱ ስለሞትና ትንሳኤው ሲያስተምራቸው የእነሱን ልብ የያዘው አሳብ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? ነበር! ስለዚህም ጌታ ትልቅ ለመሆን ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው ይሄ መቼም ለሰው የሚመች አይደለም ግን ዝቅ ማለትን መማር አለብን:: ጌታ እኮ ሁሉን ትቶ ነው የባሪያን መልክ ይዞ የመጣውና ደግሞም የመስቀል ሞት የታዘዘው በዚህም ምክንያት ከልክ በላይ ከፍ ከፍ አደረገው እግዚአብሔር አብ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ሰጠው:: አሜን! ሃሌሉያ! ስለዚህ ዝቅ ብለን ሌሎችን እናገልግል የተወልን ፍለጋው ይህ ነውና::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነው

የማርቆስ ወንጌል 9: 38-41
38፤ ዮሐንስ መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ስለማይከተለንም ከለከልነው፡ አለው። 39 ኢየሱስ ግን አለ። በስሜ ተአምር ሠርቶ በቶሎ በእኔ ላይ ክፉ መናገር የሚችል ማንም የለምና አትከልክሉት፤ 
40 የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነውና። 
41 የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ። 

በክርስቶስ አንድ አካል መሆናችን ካልገባን እንደ ዮሐንስ ህግ አስከባሪ አጋፋሪዎች መሆናችን ነው:: የሚሆኑትን ነገሮች ለክርስቶስ ነው ወይ ከማለት ይልቅ ከቤተክርስቲያናችን ህግ ውጪ ነው የሚል አባባል ሲቀድም ብዙ ታዝበናል መቼም:: መንግስቱን የሚያስፋፋ ከሆነ እንዲያውም በርታ ምን እንርዳህ ነው መባል ያልበት:: በኦርቶዶክስ ተሀድሶ ህብረት ውስጥ እያለሁ እነዚህን በብዙ ሰምቻለሁ ከአስራ ሁለቱ ነገድ ውጪ እንዴት ሆኖ ዘራፍ የሚሉ ብዙ ነበሩ የተወሰኑት ደግሞ ይህ ከእግዚአብሔር ነው ብለው ደግፈውናል:: በእኔ በኩል ሳንሱር አድርጌ ካላሳለፍኩት እንዴት ሆኖ? አንበል በቅድሚያ እንመርምር አለበለዚያ ዝም ማለት ይሻላል:: ከእግዚአብሔር ከሆነ ይዘልቃል ካልሆነ ደግሞ ይከስማል:: ከቻልን እንጸልይ በጉዳዮ::

የጌታ መልስ ግን በስሜ ተአምር ሠርቶ በቶሎ በእኔ ላይ ክፉ መናገር የሚችል ማንም የለምና አትከልክሉት፤  ቃሉ እንደሚል ለውሳኔ አንቸኩል ሁሉን በፍቅር መነጽር እንይ ደግሞም አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል ይላል:: በሌላም ስፍራ ላይ እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። እንጠንቀቅ ለአስተያየታችን:: ስለዚህ የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነውና በህብረት የመንግስቱን ስራ እንስራ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእኔ የሚያምኑትን አታሰናክሉ

የማርቆስ ወንጌል 9: 42-50
42፤ በእኔም ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር። 43 44 እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመሄድ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል። 
45 46 እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመጣል አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። 
47 48 ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነመ እሳት ከመጣል አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል። 
49 ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል። 
50 ጨው መልካም ነው፤ ጨው ግን አልጫ ቢሆን በምን ታጣፍጡታላችሁ? በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።

ጌታ በደሙ ዋጅቶ ወደ ቤቱ ያመጣቸውን ታናናሾች ከማሰናከል እንድንቆጠብ ነው ጌታ የሚያሳስበው:: ማሰናከል በብዙ መንገድ ይገለጣል:- ክርስቶስን የማያከብር ኑሮ፥ በስህተት ትምህርት፥ ቅድስናን ባለመጠበቅ እና ሌላ ብዙ ማሰናከያ ማንሳት ይቻላል መዳናችንን በፍርሃት እንፈጽም:: ይህን የሚያደርግ ሞት ነው የሚገባው እያለ ነው ጌታ ስለዚህ ህይወታችንን እንመርምር እንቅፋት እንዳንሆን በቤቱ:: ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ሰውን የምናሰናክለው ለስጋችን ጥቅም ነው እንጂ መቼም ለጌታ አይደለም ማሰብ ያለብን ሁሉን ጥለን እንሄዳለን ታድያ ለዘላለሙ ህይወት ብንተጋ አይሻልም:: ላለማሰናከል ያለህን ሁሉ ስጥ ነው እያለን ያለው ወደ ሲኦል ከመጣል ሁሉን በቅን ልብ አገልግለን ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባትን ምርጫችን እናድርግ::

ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ እኛ በመንፈስ ቅዱስ እሳት ተሞልተን ለእግዚአብሔር የተለየንና የተቀደስን ነን:: መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል እንደሚል የአፋችን ፍሬ የሆነው መስዋት በጨው የተቀመመና ጌታን ደስ የሚያሰኝ ይሁን:: መቼም በአዲስ ኪዳን የእንስሳ መስዋዕት አናቀርብም የአፋችንን ፍሬ እንጂ:: ስለዚህ ከዚህ አንደበት መውጣት ያለበት ቃል የሚያንጽና የሚያጽናና ከልብ የሆነ እውነተኛ ቃል መሆን አለበት:: ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን ይላል ቃሉ። ስለዚህም ነው በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ የተባልነው፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ እንደሚል ሰው ለራሱ መኖር ካቆመ ጌታን ለማገልገልና ደስ ለማሰኘት የሚያግደን ስለማይኖር ከሌላው ጋር ተስማምተን እንሰራለን::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 10

ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው

የማርቆስ ወንጌል 10: 1-12
1፤ ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ ደግሞም ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ እንደ ልማዱም ደግሞ ያስተምራቸው ነበር። ፈሪሳውያንም ቀርበው። ሰው ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። 
እርሱ ግን መልሶ። ሙሴ ምን አዘዛችሁ? አላቸው። 
እነርሱም። ሙሴስ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ አሉ። 
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ። 
ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ 
ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ 
ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። 
እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። 
10 በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር ጠየቁት። 
11 እርሱም። ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤ 
12 እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።

ሊፈትኑት ፈልገው ነው ስለፍቺ የጠየቁት ህግ ሰጪውን ከማን ጋር እየተነጋገሩ እንዳሉም አያውቁምና:: እነሱ ለእግዚአብሔር የቀኑ መስሏቸው እሱኑ ሊያስደስቱት የሚፈልጉትን ገፉት! ስለፍቺ የሰጣቸው መልስ እርሱ ስለትዳር ያሰበው ገና ከፍጥረት መጀመሪያ እንደሆነ ነገራቸው:-

  1. ከፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ ተሳስቶ የማያውቀው እግዚአብሔር እንደዚህ ፈጥሮናልና ይህ ዘመን አመጣሽ ችግር በዚህ ቃል ይፈታል ወንድ ወንድ ነው ሴትም ሴት ናት አለቀ:: ጠላት ሁሌ እግዚአብሔር አቅዶ ያደረገውን ነገር ለመምታት ይፈልጋል ግን አይሆንም ህብረተሰቡ እንኳን ቢቀበላቸው ሰዎች እራሳቸውን መቀበል ስለማይችሉ እራስን ወደ ማጥፋት ይሄዳሉ ይህም የጠላት ግብ ነው ሰውን መግደል ጌታ ግን ነፃ ሊያወጣን መጣ:: ሃሌሉያ!
  2. በጋብቻ ሲተሳሰሩ ባል አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ለዚህም ነው የባል ቤተሰብ ከትዳር መካከል መውጣት ያለበት እርሱ ነው ቤተሰቡን ትቶ ከሚስቱ ጋር መተባበር ያለበት:: ይህ የብዙ ትዳር መፍረሻ ምክንያት ነው የባል ቤተሰብ ልጃቸው እንደተጎዳ ነው የሚያስቡት አይተው የማያውቁት አይነት መታዘዝና ሚስቱን መስማቱን ሲያዩ የተበደለና እየተጫነችው አለቃ የሆነችበት ስለሚመስላቸው ጣልቃ መግባት ይፈልጋሉ ግን እንደዛ አይደለም ቤተሰብ ከልጆች ትዳር መውጣት አለበት ይህ የእግዚአብሔርም አቋም ነው::
  3. ሁለቱም አንድ ስጋ ይሆናሉ:- ህብረታቸው አንድ የመሆን ነው:: ትዳርን የመሰረተ እራሱ ስለሆነ ነው በመጀመሪያ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ተአምራትን ያደረገው በየትኛውም ትዳር ውስጥ ጌታ አለ ያንን ህብረት የመሰረተው እርሱ ነውና በመካከላቸው ተገኝቶ ቃል ኪዳናቸውን ያከብራል::
  4. ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም:- በእግዚአብሔር ፊት አንድ እንደሆኑ ነው የሚያውቀው:: ልክ አንድ ሰው ተነስቶ ሰውነቴ ለሁለት ይከፈልልኝ ብሎ እንደመጠየቅ ነው:: ይህ እብደት ነው የሚባለው ፍቺም እንደዛው ነው ካለ ዝሙት በቀር::
  5. እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው:- በመካከላቸው ተገኝቶ አጽድቆ አጣምሮ ከሁለት ሰው አንድ ሰርቷልና መለያየት የጌታን ህግ መተላለፍ ነው እንጂ እንደቀላል ተነስተን እነ እከሌ አድርገውታልና ምን ችግር አለው ብሎ ነገር አይሰራም ይህ የልብ እልህ እንደሆነ ቃሉ ይነግረናል ከሞትን ለጌታ ሁሉ ሰላም ይሆናልና እንሙት በፊት::
  6. ትዳሩን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ስለዚህ ትዳራችንን እንንከባከብ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊት ጸድቋልና:: ባል ሚስቱን ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደደ ይውደዳት እንዲሁም ሚስት ለባልዋ ትገዛ እርሱ ራስ ነውና:: በሌላ ስፍራም ላይ ቃሉ የሚለን:- ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንደህፃናት እንሁን

የማርቆስ ወንጌል 10: 13-16
13፤ እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። 14 ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና። ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። 
15 እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው። 
16 አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው። 

የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ ጌታችን:: ህፃናትን ስናስብ ሁሉን ያምናሉ ለምሳሌ:- በኃላ ስመጣ ክንፍ ይዤ እመጣና ትበራለህ ቢባል ችግር የለበትም ልጅ ሲያስብ የሚውለው የት ድረስ እንደሚበር እንጂ ልወድቅ እችላለሁኝ ብሎ እንኳን ለቅጽበት አይጠራጠርም ወላጁን አምኖ በጉጉት ይጠብቃል:: ጥርጣሬ የለም አምኖ ቁጭ ነው የሚለው:: እኛስ?! ብልጥ ነን አይደል እግዚአብሔር ላይ ከመደገፍ ይልቅ የአውሮፕላን ትኬት ብትገዛልኝ በረርኩ ማለት ነው ብለን ቁጭ! ቃሉን ለኛ እንዲመች ቀይረን እንሰማለን ምክንያቱም ለአእምሮ የማይመች ብለን እንፈርጃለን የእግዚአብሔርን ድምጽ:: አይይ ይሄ አስተሳሰባችን በጌታ ቃል ይሞላ እናም ቃሉን ህያው እንደሆነ እንቀበል ምክንያቱም ጌታ ያለን ይህ የምናገረው ቃል ህያው ነው መንፈስም ነው ብሎናልና! እ ን መ ን!!!
ሌላው የልጅ ባህሪ አሁን አጥፍቶ ተቀቶ እያለቀሰ ወደ ስራችን ይገባል የሚቀየምን ልብ የለውም ይቅር ይላል እኛም በይቅርታ ካልተመላለስን ፀሎታችን እንኳን አይሰማም ጉንጭ ማልፋት ብቻ ነው የሚሆነው ከወንድምህ ጋር አንዳች ካለህ መስዋዕቱን አስቀምጥና በፊት ታረቅ ነው የሚለን ቃሉ:: ስለዚህ እንደልጅ በፊቱ እንመላለስ እንመነው የሚለንን ሳንጠራጠር እንቀበል::

አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው:- ሳነበው ገና ደስ አለኝ የጌታ ልጅ ነኝ ዛሬም እቅፍ አድርጎ ይባርከኛል እንደሁልጊዜው ስሙ ይባረክ:: ሁልጊዜ የሚባርክ የሚንከባከብ እረኛ ነእጥሎን ወዴትም አይሄድም እርሱ አስቀድሞ ወደደን እርሱ ወደ መንግስቱ ዋጋችንን ከፍሎ ተቤዠን! ስሙ ይባረክ! ልጆቹን ይወዳል ይባርካል ጌታ! ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል

የማርቆስ ወንጌል 10 17-31
17፤ እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። 18 ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። 
19 ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። 
20 እርሱም መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው። 
21 ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው። 
22 ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ። 
23 ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው። 
24 ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ። ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። 
25 ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው። 
26 እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው። እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ። 
27 ኢየሱስም ተመለከታቸውና። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ። 
28 ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ይለው ጀመር። 
29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ 
30 አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። 
31 ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ። 

ይህ ሰው ለእየሱስ ሰገደና ቸር መምህር ሆይ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀ:: ይህ ሰው በትክክል ከልጅነቱ ጀምሮ ነው ትዕዛዛትን የፈጸመው እናም የጎደለኝ ይኖር ይሆን ወይ ብሎ ነው ጌታን እየጠየቀ ያለው:: ጌታም ወደደውይላል ቃሉ:: ሐብትህን ለደሀ ሰተህ ተከተለኝ ሲለው እርሱን ማድረግ አልቻለም ከበደው ምክንያቱም ገንዘብን ወዷልና:: ገንዘብን መውደድ ደግሞ የሐጥያት ሁሉ ስር ነውና ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻልም አንዱን መተው ለሌላው መገዛት ግድ ነው ከሁሉ ነገር ይልቅ እንደአምላክ የተቆጠረ ገንዘብ ነው:: ጌታም ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው አለ:: ምን በሚሉ? በገንዘብ ለ ሚ ታ መ ኑ! አንታመንበት መታመኛችን ጌታ ብቻ ይሁን! ንስሀ ልንገባ ይገባል ራሳችንን ብንመረምር አይፈረድብንም እንደሚል ቃሉ ፈትሸኝ በደምህም እጠበኝ እንበለው::

ግን እኮ ይህ ሰው የሳተው የትዕዛዝ ሁሉ መጀመሪያ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ የሚለውን ነው:: በአንዱ የወደቀ በሁሉ ወድቋል:: ስለዚህ ምክንያት ነው ጌታ እየሱስ የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ሁሉ ሐጥያት ሊሸከምና ሊቤዠን የመጣው:: ክብር ለስሙ ይሁን ሁሉ ሐጥያትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል የሚለው እውነት ነው ምክንያቱም አንድ የሚችል ቢገኝ ኖሮ እየሱስ ባልመጣ ነበር ሁሉላችንም ከሐጥያት ቀንበር በታች ነበርን ጌታ ባይመጣልን ኖሮ ሌላ መፍትሄ የለንም ነበር::

ማን ሊድን ይችላል ብለው ግራ ሲገባቸው ኢየሱስ ተመለከታቸውና። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ። አሜን እርሱ በጸጋው ይረዳናል በገንዘብ ላይ አለቃው ሆነን እንድንሰለጥንበትና እንድናሰራው እንጂ በራሳችን አንዳክር ለሚረዳው መንፈሱ እራሳችንን እናስገዛ:: ምንም የከሰርነው ነገር የለም ጌታን ተከትለን ዓለምን ንቀን ሁሉ አለን! ጌታም እንዳለን በዚህ ዘመን ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። አሜን መቶ እጥፍ ነው የተሰጠን:: ይህንን ካለን በኃላ ደግሞ ለጥንቃቄ ይሆን ዘንድ ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ አለ ሁልጊዜ አቋማችን አንድ ይሁን ለእርሱ መገዛት ሌላው ሁሉ ይጨመራል::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እየሱስ ስለሞትና ትንሳኤውን ተናገረ

የማርቆስ ወንጌል 10: 32-34
32፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፥ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም አሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር፦ 33፤ እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፥ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፥ 34፤ ይዘብቱበትማል፡ ይተፉበትማል፡ ይገርፉትማል፡ ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፡ አላቸው::

የሞትና የትንሳኤውን ነገር ደግሞ ደጋግሞ ነው የነገራቸው እነርሱ ግን ብዙም አያስተውሉም ነበረ:: ጌታ እየሱስ ስለእኛ የሚሆንበትን ሲናገር እንደሚዘብቱበት፡ እንደሚተፉበት፡ እንደሚገርፉት፡ እንደሚገድሉት፥ ነገር ግን በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ፡ ተናገረ:: አምላክ የሆነው እየሱስ በራዕይ ላይ ዮሃንስ ባየው ጊዜ እንደሞተ ሰው ነበረ የሆነው ትላንትና ደረቱ ጋር ጠጋ ብሎ እንዳላወራው ዛሬ ግን በፊቱ መቆም እንኳን አይቻልም:: ይህንን ጌታ ነው እንግዲህ የዛቱበት የተፉበት የገረፉት የተዘባበቱበት ብሎም የገደሉት:: ትልቅ ሆኖ ሳለ ህይወት ሰጪ ሆኖ ሳለ አሰቃዩት ምን አይነት ፍቅር ነው:: ክብሩን ሁሉ ትቶ ለዚህ አንድ ጉዳይ ወደ ምድር መጣ ህይወቱን ሰጠ በግ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንዲል እርሱም ዝም አለ:: ወደ እየሩሳሌም ለህይወቱ ሳይሰስት ሲያቀና ይገርማል ይህ የሆነው ለእያንዳንዳችን ነውና ክብር ይገባዋል! አሜን!


ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን

የማርቆስ ወንጌል 10: 35-45
35፤ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው፦ መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን፡ አሉት። 36 እርሱም። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው። 
37 እነርሱም። በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት። 
38 ኢየሱስ ግን። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አላቸው። 
39 እነርሱም። እንችላለን አሉት። ኢየሱስም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 
40 በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው። 
41 አሥሩም ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ይቈጡ ጀመር። 
42 ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። 
43 በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ 
44 ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ 
45 እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። 

ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው እየሱስ ለወንድማማቾቹ እነሱም የተለመነውን ሁሉ ሲያደርግስላዮት አሁን ደግሞ ልሞት ነው እያለ ነው ሳንጠይቀው ከምንቀር ብለው ልባቸውን ሞላ አድርገው በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት:: ግን የውስጥ ጥያቄያቸው ምንድነው? ታላቅ መሆን ነው ምክንያቱም በመልሱ ውስጥ ጠቅሶታል ጌታችን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ ነበረ መልሱ:: እየሱስ ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣምና አለ:: እርሱ ዝቅ ብሎ ሊያገለግል ከመጣ ተከታዮቹም ይህንን እንዲያደርጉ እና ያንን ያገልጋይነትን ልብ እንድንይዝ ነው የሚፈልገው:: ዛሬም እኔ ይህንን አደረኩ ያንን አደረኩ ከማለት እርሱ ይህንና ያንን አደረገ ማለትን እንማር:: እርሱን ከፍ እናድርግና እናክብር::

የሚገርመው የምትለምኑትን አታውቁም ነበር የጌታ የመጀመሪያ መልስ። ሲቀጥልም እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አላቸው። ጽዋ? ምን ችግር አለው አሉ:: ጥምቀት? እንዴ ዮሃንስ ሲያጠምቅ አይተን የለም እንዴ? እንችላለን አሉ እርሱ ግን ስቃዩን ጽዋ ሞቱን ደግሞ ጥምቀት እያለ እንደሆነ አላስተዋሉም ነበር:: ለዚህ ነው ጥምቀት ከእርሱ ጋር ሞተን እንደመነሳት የሚታይ ስርዓት የሆነው:: እናም በዚህ ጸሎት መሰረት ያዕቆብ የመጀመሪያው መስዋዕት ሆነ የምንለምነውን እንወቅ:: ጴጥሮስ ግን ተረፈ መትረፍ ከማይችልበት ጥብቅ ጥበቃ ውስጥ ወጥቶ ጌታን አገለገለ:: የሚገርመው ሐዋርያት በአስራ ሁለቱ ነገዶች ላይ የሚፈርዱ ነበሩ እንጂ በቀኝና ወይም በግራ የሚቀመጡ አይደሉም ደግሞም የሚቀመጡት የተዘጋጀላቸው ሰዎች ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው። ቃሉን ስለማያውቁ ወይም ስላላስተዋሉ ይስቱ ነበረ:: ቃሉን እንወቅና እንደቃሉ እንጸልይ ጌታም ይሰማናል::


ኢየሱስም ምን ላደርግልህ ትወዳለህ አለው?

የማርቆስ ወንጌል 10: 46-52
46፤ ወደ ኢያሪኮም መጡ። ከደቀ መዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጣ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስ እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር። 47 የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ። የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ይጮኽ ጀመር። 
48 ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። 
49 ኢየሱስም ቆመና። ጥሩት አለ። ዕውሩንም። አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል ብለው ጠሩት። 
50 እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ። 
51 ኢየሱስም መልሶ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? አለው። ዕውሩም። መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ አለው። 
52 ኢየሱስም። ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው።

ብዙዎች ዝም እንዲል የገሰጹት ማየት የተሳነው በርጤሜዎስ ግን የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። ያለበትን የሚያውቀው እርሱ ነው እንዴት አብዝቶ አይጮህ ጠዋት ማታ እርዳታ የሚጠይቅ ምናልባትም ሰው የሰለቸው ሰው ነው:: ታድያ እንዴት አብዝቶ አይጮህ? እኛም በጉዳዮቻችን ስንጸልይ አብዝተን እንጩህ ይሰማናልና::

ኢየሱስም ቆመና። ጥሩት አለ። ዕውሩንም ዝም በል ብለው የገሰጹት ሁሉ አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል ብለው አሉት:: መጽናት ጥሩ ነው ጸንተን ባለመናወጥ ፊቱን እንፈልግ:: እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ።  ኢየሱስም ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? አለው። እርሱም ምንም ጊዜ ሳይወስድና ሳያቅማማ መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ አለው። ለጌታ የሚሳነው ነገር የለም ስንጸልይ በእኛ ልክ አይሁን የእርሱን ታላቅነት አይተን እንጂ:: ኢየሱስም። ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም:: የመንግስተ ሰማያት መገበያያ እምነት ነው በእምነት ነው የምንቀበለው:: ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው። አይኑን አልነካው አልዳሰሰው ወይም ጭቃ አልቀባው ሄደህ ታጠብ አላለው እምነትህ አዳነህ ሲለው አጥርቶ አየ ደግሞም መጸለይ አላስፈለገውም:: የጌታ አሰራር ግሩም ነው ሁልጊዜ አንድ እንዲሆን አንፈልግ እርሱ ሉአላዊ አምላክ ነውና ብቻ ከእርሱ ጋር እንስማማ የሚለንንም እንስማ ያስደንቀናል ስሙ ይባረክ! ሃሌሉያ! የተፈወሰው ሰው እራሱ ተከተለው ሰው ከእስራቱ ሲፈታ የተደረገለትን ሲያውቅ ጌታውን ይከተላል::

ዛሬ በምን ላይ ነው የጌታን ፊት የምትፈልጉት? ይሰማል በርቱና ጸልዮ ፊታችሁም አያፍርም:: እርሱየታመነ ጌታ ነውና!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 11

ሆሣዕና በአርያም

የማርቆስ ወንጌል 11: 1-11
1፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወዳሉቱ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወዲያውም ወደ እርስዋ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። 
ማንም። ስለ ምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፥ ወዲያውም ደግሞ ወደዚህ ይሰደዋል አላቸው። 
ሄዱም ውርንጫውንም በመንገድ መተላለፊያ በደጅ ውጭ ታስሮ አገኙት፥ ፈቱትም። 
በዚያም ከቆሙት አንዳንዶቹ። ውርንጫውን የምትፈቱት ምን ልታደርጉት ነው አሉአቸው። 
እነርሱም ኢየሱስ እንዳዘዘ አሉአቸው፤ ተዉአቸውም። 
ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡት፥ ልብሳቸውንም በላዩ ጣሉ፥ ተቀመጠበትም። 
ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር። 
የሚቀድሙትም የሚከተሉትም። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ 
10 በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። 
11 ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቅደስ ገባ፤ ዘወር ብሎም ሁሉን ከተመለከተ በኋላ፥ ጊዜው መሽቶ ስለ ነበረ ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። 

ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቅደስ ገባ፤ ዘካርያስ 9: 9፤ አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። እንደተባለው ትንቢት ተፈጸመ እንደገናም በሐጌ 2 ላይ እንዳለው ትንቢት ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምክንያቱም እራሱ ንጉሱ በትህትና በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ገብቷልና ነው:: ሃሌሉያ! እንደዚሁም ደግሞ በመዝሙረ ዳዊት 118: 25፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና። 26፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ። የሚለውን ቃል ሆሳእና እያሉ እያስተጋቡ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ያነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።  በቁጥር 27፤ እግዚአብሔር አምላክ ነው፥ ለእኛም በራልን፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ፡ የበዓሉን መሥዋዕት በገመድ እሰሩት። እንደሚል ይህ የእግዚአብሔር በግ እየሱስ ለእያንዳችን መስዋዕት ይሆን ዘንድ እራሱን አሳልፎ ለመስጠት አዘጋጀ:: ዋዉ ምን አይነት ፍቅር ነው?! እናመሰግንሀለን አባት ሆይ!

የሚገርመው ሌላው ታሪክ የአህያይቱ ውርንጫ ነገር ነው የት እንደሚያገኙአት ነግሮ ላካቸው ሄደው ያላቸው ቦታጋ አገኙአት ባለቤቱም አልከለከለም ፈቀደላቸው:: ጌታ ቀድሞ ተናግሮታል ማለት ነው ሳይከራከር ፈቀደላቸው:: ስንት ጊዜ ይሆን ከእርሱ ዘንድ ሰምተን የተባበርንና የታዘዝነው? እግዚአብሔር በብዙ ጎዳና ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም የሚለው እንዳይፈጸምብን ወደፊቱ እንምጣና በፊቱ እንገኝ ሲሰራም አብረነው ሰራተኞች እንሁን:: የውርጫዋ ባለቤት የዋህ ሆኖ የመጣውን ንጉስ የምታስቀምጥ እንሰሳ አበረከተ:: እኛስ ምን ተጠይቀን ይሆን? ዛሬ ለጌታ የሚያስፈልገውን ወደ ፊቱ እናምጣ::
ሌላው አህያዋ ማንም ተቀምጦባት አያውቅም ይላል መቼም ብዙ ስለ እንሰሳ ባላውቅም ፈረስ እንደሚሰለጥነው መሰልጠን አለበት ብዬ አስባለሁ ነገር ግን ምንም ያልሰለጠነ ውርንጫ ላይ ቢሆንም የተቀመጠው አላስቸገረውም ለዚህ ጌታ ፍጥረት ሁሉ ይታዘዘዋል:: ሊታደገው የመጣለት የአዳም ዘር ግን አልታዘዘም ጌታውንም አላወቀም ስለዚህ በኢሳይያስ 53 እንደሚለው በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ብሎ ጌታ የጠየቀው ተፈጸመ:: ዛሬ ልባችንን እልኸኛ አናድርግ የሚናገረንን እንስማና እንታዘዝ:: ንጉሳችን ጻድቅና አዳኝ ፤ ትሑትም ነው ታድጎናልና ለእርሱ ክብር እንኑር!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!!


በለሲቱን ረገመ

የማርቆስ ወንጌል 11: 12-14
12 በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። 
13 ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 
14 መልሶም። ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ። 

የበለስ ወራት አይደለም ለምን ፍሬ ፈልጎ መጣ? እርሱ አምላክም ነው ፍሬ እንደማይኖረው ሙሉ እውቀት የለውም? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጤ ናጡኝና ምን ይሆን የዚህ ትምህርት ሚስጥር ብዬ ጸለይኩኝ መቼም ለመናገር ያህል አይናገርምና መልክትማ አለው::

የበለስ ዛፉ አላናገረውም ነገር ግን ጌታችን “መልሶም” ይላል ልክ ንግግር ውስጥ እንደነበረ:: ምን እያለ ነበር ዛፉ? የበለስ ወራት ባይሆንም ቅሉ ደርሻለሁ ፍሬ አለኝ የሚል የውሸት መረጃ እያሳየ ነበረ:: እኛም ዛሬ ብዙ የወሸት መረጃ የሚሰጡንን ጉዳዮች ጭራ ይዘን በዙሪያችን እንሸበራለን ስለጤና ቢሆን ስለስራ ቢሆን ስለቤተሰብ ስለአገር ሌላም ሌላም ጉዳይ:: ዓለማትን ሁሉ በቃሉ የፈጠረ በቃሉ ደግሞ ማድረቅም ይችላል እኛም በስሙ እንድናደርቅ ስልጣን ተሰቶናል::

ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም እየሰሙ ነው የተናገረው የመለሰ ወይም የጠየቀም የለም እንደነገሩ አለፉት እንጂ ከዚህ ውስጥ የፈጣሪነቱን አንደምታ እንደሚያዩ አላወቁም:: ስለምንናገረው ነገር ማስተዋል ይስጠን ስንት ጊዜ ይሆን በሀይለ ቃል ሰውን የሚጎዳ የእርግማን ቃል የተናገርነው? እናስተውል ምን ከአንደበታችን እንደሚወጣ:: የአንደበትህን ፍሬ ትበላለህ ይላልና ቃሉ ስለዚህ ትዳራችንን ፤ ልጆቻችንን፤ አካላችንን ፤ ቤተሰባችንን ፤ አብረውን የሚያገለግሉትን ፤ አገራችንን ሁሉ እንባርክ! የምትባርክ ነፍስ ደግሞ ትባረካለች:: ዛፍዋ ደግማ ፍሬ እንዳትሰጥ በተነገራት መሰረት ዝቅ ብለን ስናነብ እንደደረቀች እናያለን::

ይህንን ምሳሌ ወደ ህይወታችን ስናመጣው ደግሞ ጌታ ከህይወታችን ፍሬ ይፈልጋል ወራትን ጠብቆ አይደለም ፍሬ መገኘት ያለበት በህይወታችን ምክንያቱም ፍሬ ልናፈራ ተሹመናልና ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም ፍሬ የማፍራቱ ጉዳይ:: ዕለት ዕለትም እርሱን ወደ መምሰል ማደግ አለብን:: ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ገበሬው አብ ይቆርጠዋል፤ ይደርቃል ወደ እሳትም ይጣላልና ፍሬ ይኑረን በወይኑ ግንድ ላይ ሆነን ማፍራት አለብን:: ጆሮ ያለው ይስማ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች

የማርቆስ ወንጌል 11: 15-19
15፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ወደ መቅደስም ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ 16 ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም። 
17 አስተማራቸውም። ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። 
18 የካህናት አለቆችም ጻፎችም ሰምተው፥ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ይገረሙ ስለ ነበር ይፈሩት ነበርና እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ፈለጉ። 
19 ማታ ማታም ከከተማ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር። 

ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ብሎ ያለበት ምክንያት መስዋዕት ለማቅረብ የሚመጡት ሰዎች የሚገበዩት ከዛው ከቤተመቅደሱ ስለሆነ ከቀን ወደ ቀን ቅልጥ ያለ የገበያ ስፍራ ሆኗልና ነው:: ቤቱ ካለመከበሩም የተነሳ መተላለፊያ ሆኖ ነበር የሲናን ተራራ የረሱ ይመስላል ማንም ወደ ተራራው ቢጠጋ ይሞታል የሚለውን:: እግዚአብሔር በአብዛኛው እስራኤላዊ ዘንድ ችላ የተባለበት ጊዜ ነው ብል ማጋነን አይሆንም:: ይህንን ወደራሳችን እናምጣው እስኪ:- ዛሬ ቤቱ እኔ ነኝ ህንፃው አይደለም በውስጤ ምን አለ? ጸሎት? ምስጋና? ቃሉ? አምልኮ ወይንስ እርሱን ደስ የማያሰኝ ነገር ልቤን ሞልቶት ይሆን? በአእምሯችን መታደስ ልንለወጥ ይገባል ይህንንም የሚያደርገው ህያው የሆነው ቃሉ ነው:: ቃሉን በልባችን እንሸሽግ እናሰላስለው ያን ጊዜ አላስፈላጊውን ቁሻሻ ሁሉ ከእኛ እያስወጣ በሌላ መገለጥ እያስደመመ ወደ ጌታ ያስጠጋናል:: ሃሌሉያ! በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ ነው የሚለን ቃሉ ስለዚህ እዚህ ላይ እናተኩር አስተሳሰባችን መረን ሲለቅ ዝም አንበለው እናግደውና የሚያስበውን እንስጠው አለበለዚያ ግን የጌታ ማደሪያ እንዴት እንሆናለን? ማስተዋል ይስጠን!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእግዚአብሔር እመኑ

የማርቆስ ወንጌል 11: 20-26
20፤ ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት። 21 ጴጥሮስም ትዝ ብሎት። መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው። 
22 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። በእግዚአብሔር እመኑ። 
23 እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። 
24 ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። 
25 ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። 
26 እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። 

ጴጥሮስ ማለዳ ሲያልፉ በአንድ ቀን መድረቋን አስተውሎ ለጌታ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው:: ታድያ ከአፉ ቃል ወቶ ላይተገበር ይችላል? በፍጹም! ጌታም አልደነቀውም ትላንትናም ቆሞ እስክትደርቅ አልጠበቀም ወይም ደግሞ ሲያልፉ አያችሁ እንደደረቀች አላለም የተናገረው እንደሚሆን ያውቃልና:: ይልቁንስ እኛ እናስተውል ለምነን እዛው ቆመን ደረቀ አልደረቀ ቅጠሉ ጠወለገ? እያልን ጸሎታችንን ሲሰራ ለማየት እንሞክራለን ግን አለማመን ነው:: ከለመንን ተሰምተናል ከተናገርንም ቃላችን ይተገበራል ብለን ማመንና ማመስገን አለብን::

በእግዚአብሔር እመኑ አለ ጌታ እንዴት እንመን?

  1. ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን – መቼም ሁላችንም ማንም የሚለው ዝርዝር ውስጥ እንገባለን:: ያለው፥ የፀለየው ወይም የተናገረው እንዲደረግለት ቅድሚያ ሁኔታ አለው እያለን ነው እሱም:-
  2. በልቡ ሳይጠራጠር፥ ለዚህ ነው በእግዚአብሔር እመኑ ያለው ጌታ
  3. ይህን ተራራ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ምንድነው ተራራችን ዛሬ እንዲነቀል በእምነት ያለጥርጣሬ እንጸልይ
  4. የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ማመን ያስፈልጋል ለመጸለይ ብቻ ሳይሆን ከጸለይንም በኃላ ለመቀበልና ፀንተን ለመጠበቅ
  5. ይሆንላችሁማል። አሜን!

ጸሎት የሚከለክል ነገር ጌታ የነገረን በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም ይቅርታን ካላገኘን ደግሞ ጸሎታችን አይሰማም:: ስለዚህ በይቅርታ እንመላለስ:: ለየትኛው ክብራችን ሰስተን ነው ዝቅ ብለን ይቅርታ የማንጠይቀው ወይም ይቅር የማንለው?! እኛ እኮ የራሳችን አይደለንም የጌታ እንጂ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ?

የማርቆስ ወንጌል 11: 27-33
27፤ ደግሞም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እርሱም በመቅደስ ሲመላለስ፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ 28 እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ እነዚህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። 
29 ኢየሱስም። እኔም አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም መልሱልኝ፥ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ። 
30 የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ አላቸው። 
31 እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ነው ብንል። እንግዲያውስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ 
32 ነገር ግን። ከሰው ነው እንበልን? አሉ፤ ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና ሕዝቡን ፈሩ። 
33 ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።

የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? ብለው የሚገርም ጥያቄ ጠየቁት ስልጣን ሰጪውን! ይገርማል! ግን ሊከተሉት እንዳልሆነ እውን ነው የሚከሱበትን ነገር እንዲያገኙ እንጂ! ዮሃንስ ከአወላለዱ ጀምሮ በተአምራት ነበረ ይህ ህፃን ማን ይሆን ብለው እስኪጠይቁ ነበር እዚህ ጋር ግን አገልግሎቱ ከሰማይ ነበረ ወይ ሲባሉ አዎን ለማለትም እንዳልፈለጉ እናያለን:: ከሰማይ ነው ካሉ ደግሞ ዮሃንስ ታድያ ስለእኔ የመሰከረውን ለምን አልተቀበላችሁም ይመጣባቸዋልና መልሳቸው መሀል ላይ ነበር አናውቅም::

እነዚህ ሰዎች ያላስተዋሉት ነገር ቢኖር እየሱስ ፈጣሪ መሆኑንና ደስ ሊያሰኙት የሚፈልጉት ጌታ በትህትና በመካከላቸው መገለጡን ነው:: ለጌታ ቀናን ብለው ስንቶች የእግዚአብሔርን መልክተኞች አደናቅፈው ይሆን? እንጠንቀቅ ካልገባን ዝምታን እንምረጥ እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር ስንጣላ እራሳችንን እንዳናገኝ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 12

ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ

የማርቆስ ወንጌል 12: 1-12
1፤ በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ 
ይዘውም ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። 
ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት አዋርደውም ሰደዱት። 
ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፥ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ አንዳንዱንም ገደሉ። 
የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ። 
እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለው፥ ርስቱም ለኛ ይሆናል ተባባሉ። 
ይዘውም ገደሉት፥ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት። 
እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል ገበሬዎቹንም ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። 
10 
11 ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው። የሚለውን ይህን መጽሐፍ አላነበባችሁምን? 
12 ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ። 

ጌታችን የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ገበሬዎቹ ግን ታማኝ ሆነው አልተገኙም መልክተኞችን ሲልክ ይደበድባሉ ይገድላሉም:; ይህ ምሳሌ ስለእስራኤል ነው ከባርነት አውጥቶ በከንዕን ተከላቸው ምድራቸውን ባረከ ምድረ በዳ ቢሆንም እንኳን ፍሬ እንዲሰጣቸው አደረገ:: ንጉስ አንግስልን ሲሉግም ንጉስ አነገሰላቸው ወደ ጦርነትም ሲወጡ ተዋጋላቸው ከአብርሃም ጋር ስለገባው ቃሉ አብርሀም በሌለበት እንኳን በታማኝነት ፈጸመው:: ይህን ሁሉ ያደረገው በስተመጨረሻ በእነርሱ በኩል መጥቶ ዓለምን ለመዋጀት ነበረ ስሙ ይባረክ:: ልክ ምሳሌው ላይ እንዳለው ያልተደበደበና ያልሞተ መልክተኛ ወይም ነብይ የቱ ነው? ሁሉንም ገደሉ እንዲያውም ልጁ ወራሽ ነውና እንግደለው እንዳሉት ገበሬዎች ይህንኑ ነው ያደረጉበት:: ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ። 

ስለዚህም እናውቃለን ያሉት ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው። አሜን! በእስራኤሎች ተቆጥቶ እስከመቼ እታገሳለሁ? ለሙሴም ይህንን ህዝብ አጠፋለሁ ብሎ ነበር ግን ታገሰና በእነርሱ በኩል ሰው ሆኖ የባርያን መልክ ይዞ መጣልን መጥቶም የሁላችንንም ሐጥያት ለመሸከም እራሱን አቀረበ ይህ የእግዚአብሔር በግ እየሱስ! ስሙ ይባረክ ስለተደረገልን ምን እንላለን ምስጋናን እንሰዋለን እንገዛለትማለን እንጂ!


የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ

የማርቆስ ወንጌል 12: 13-17
13፤ በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ። 14 መጥተውም። መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ? አሉት። 
15 እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ። ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ አላቸው። 
16 እነርሱም አመጡለት። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤ እነርሱም። የቄሣር ናት አሉት። 
17 ኢየሱስም መልሶ። የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በእርሱም ተደነቁ። 

በንግግርም ሊያጠምዱት ስለ ግብር እንዲጠይቁት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ:: ግቡን ልብ ብላሁ አስተውሉ! በንግግርም ሊያጠምዱት ነው የመጡት እነማን ናቸው ያልን እንደሆነ ከሄሮድስ ወገንና እንደገናም ደግሞ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ ሰዎች ናቸው:: አንዳች ምክንያት አግኝተው ሊያስወግዱት ነው የሚፈልጉት::

የሚገርመው የሚናገረውን እየሰሙት አይደለም የላከውን በማንገላታትና በማስወገድ በነሱ ቤት ለእግዚአብሔር መወገናቸው ነው ነገር ግን ጌታ ታግሶ አስተማራቸው የጥበቡን ጥልቀት:: እርሱ እኮ ስለሰው ሊነገረው አይገባም ሁሉን ያውቃል ግን ሊገባቸው አልቻለም:: የቄሳር ምስል ያለበትን ለቄሳር የእግዚአብሔር ምስል ያለበትን ደግሞ ለእግዚአብሔር እያላቸው ነው:: እኛ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረናልና ለፈጠረን ጌታ እንገዛለን:: ሃሌሉያ! ከምናገኘው የተወሰነውን እንደቀረጥ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ለሞተውና ለተነሳው ጌታ እንኖራለን እያንዳንዳችን ይህን እንበል በእኔ የሚኖረው እራሱ እየሱስ ነው እኔ አልኖርም ብለን እንሹመው ሊገዛን ይገባዋልና በዋጋ ተገዝተናል:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም

የማርቆስ ወንጌል 12: 18-27
18፤ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም፡ አሉት፦ 19 መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። 
20 ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤ 
21 ሁለተኛውም አገባት፥ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 
22 ሰባቱም አገቡአት፥ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። 
23 ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች? 
24 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? 
25 ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም። 
26 ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር። እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? 
27 የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ። 

ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም፡ አሉት፦ መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። ደግሞም ሰባቱ አገብዋት ግን ልጅ ሳያስቀሩ ሁሉም ሞቱ በስተመጨረሻ በትንሳኤ ታድያ የማን ሚስት ልትሆን ነው:: ለምን ይህንን ይጠይቃሉ መጀመሪያውኑ የሙታን ትንሳኤ የለም ብለው ካመኑ ወይስ በትንሳኤ እንደዚህ አይነት ታሪክ ያለው ሁሉ ሲጣላ ቀውጢ የሆነ ትንሳኤ ይሆናልና ትንሳኤ ይቅር ብለው ሊያግባቡ? ወይስ እምነታችን ትክክል ነው ብለው ሊያስፈርሙት? ይገርማል የእኛ ጌታ ግን የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር። እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ብሎ ነው እራሱን የሚጠራው:: ሃሌሉያ! በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ከሞት ህግ አርነት ወተን በህይወት እንድንኖር ክርስቶስ እራሱን ቀድሷል:: እንዲሁም በራእይ 1: 17፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ 18፤ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። እኛም ከእርሱ ጋር ተነስተናል!

መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? እጅግ ትስታላችሁ አላቸው ጌታ ስለ ህያውነቱ እያወቁ እንዳላረጀ በዘመናት መካከል እያዩ ቃሉንም ሲመረምሩ እየዋሉ እነሱ ግን ስተዋል:: የሙታን ትንሳኤ ጊዜ ስጋችን ለእርሱ አሰራር እንደሚመቸው አድርጎ ከመቅጽበት ይቀይረዋል የስጋ ምኞት የለም እንደመላእክት በቅድስናው ፊት መኖር ነው የሚጠብቀን:: ላለመሳት የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑር በህይወታችን እናጥና ቃሉን እናሰላስለው ከእኛ ጋር እንዲዋሀድም እናመንዥገው እንጂ የማይጠቅመን እንዳይሆንበጠላት ተለቅሞ:: ጌታ ህያው ነው! ፀሎቴ:- ጌታዬ ሆይ የቃልህን ደጆች ክፈትንል እንድናስተውልም እርዳን ነው:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በፍጹም ልብህ፤ ነፍስህ፤ አሳብህና ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ

የማርቆስ ወንጌል 12: 28-34
28፤ ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ፦ ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው። 29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ 
30 አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። 
31 ሁለተኛይቱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። 
32 ጻፊውም። መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ 
33 በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው። 
34 ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ። አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። 

ለሰዱቃውያን ደህና አድርጎ እንደመለሰ የተመለከተው ይህ ከጻፎችም አንዱ ስለመጀመሪያይቱ ትዕዛዝ ጠየቀው ጠፍቶት ወይም ለማወቅ ፈልጎ እንዳይመስለን እንደተለመደው ለማጥመድ እንጂ:: ህግ ሰጪውም ሲመልስም:- እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም

  1. በፍጹም ልብህ – በልባችን ላይ ጌታን እናንግሰው እርሱ የህይወት መውጫ ነውና በሙሉ ልባችን እንውደደው
  2. በፍጹምም ነፍስህ – ማንነታችን እኔነት እወዳለሁ እጠላለሁ የሚለው ማንነታችን ሊወደው ይገባል
  3. በፍጹምም አሳብህ – የምናወጣውና የምናወርደው በአሳባችን እርሱ መሆን አለበት
  4. በፍጹምም ኃይልህ – በጉልበታችን በገንዘባችን በትምህርታችንና በእውቀታችን ሁሉ ልንወደው ይገባል::

ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። እግዚአብሔር ቀናተኛ ነውና ለማንም እንድንሆን አይፈልግም:: ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት ብሎ አላበቃም የጠየቀው የመጀምሪያይቱን ብቻ ቢሆንም እንኳን ሁለተኛይቱንም ነገረው:: ሁለተኛውም:- ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል ናት:: እየሱስ ደቀመዝሙርቴ እንደሆናችሁ በፍቅራችሁ ታወቁ ነው ያለን ደግሞም ከፍቅር በቀር ሌላ እዳ አይኑርባችሁ ነውና የተባልነው በፍጹም ልብ አሳብ ነፍስና ጉልበት ጌታችንን እንውደድ የሰውንም ልጅ ሁሉ እንደራሳችን እንውደድ::

ሰውየው መልሱን ሰምቶ ልክ ብለሀል መውደድ ከመታዘዝ ይበልጣል ብሎ አለ እንጂ እምነቱን በስራ አልገለጠም ግን እሩቅ አይደለም አለ እየሱስ ልክ እንደዚህ ሰው ያሉ ሰዎች በዙሪያችን አሉና እንጸልይላቸው እምነታቸው በስራ እንዲገለጥና በመገለጥ መረዳት ወደ አምላካቸው እንዲጠጉ ምክንያቱም የአእምሮ እውቀት አያድንም መገለጥ እንጂ::

ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!


እየሱስ መሲህ ነው

የማርቆስ ወንጌል 12: 35-44
35፤ ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ፦ ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው፡ እንዴት ይላሉ? 36 ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። 
37 ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። 
38 39 ሲያስተምርም እንዲህ አለ። ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ 
40 የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ። 
41 ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ 
42 አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። 
43 ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ። እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ 
44 ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው።

ዳዊት በመንፈስ ተረድቶ መሲህ ከእርሱ ዘር የሚመጣ ቢሆንም እንኳን ጌታዬ ብሎ ነው የሚጠራው ደግሞም ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። ስለዚህ ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብሎ ነው የሚጠይቃቸው በሌላ አባባል እኔ መሲህ ነኝ ምንም እንኳን ከዳዊት ዘር ብገኝም እያለ ነው ያስተዋለ የለም እንጂ! መሲሁ ሲመጣ ማድረግ ያለበትን ድንቅና ተአምር ያውቃሉ ለዚህም ነው ዮሃንስ ወደ እርሱ ልኮ ምንም እንኳን የተላከው እርሱ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ ያየ ቢሆንም ግን አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ ብሎ መልእክተኛ ላከበት እየሱስም የምታዩትን ንገሩት ነበር ያለው::

ከዛም ዞር ብሎ ስለመባ መታዘብ ያዘ እንደዛች መበለት ጥቂት የሰጠ የለም እንደእርስዋም የተደነቀ የለም:: ምን ያህል እንደምንሰጥ አይገደውም ግን በደስታና በልግስና ስንሰጥ ጌታ ደስ ይለዋል:: የልግስናና የመታዘዝን መንፈስ ይሙላብን! አሜን!


ምዕራፍ 13

እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል

የማርቆስ ወንጌል 13: 1-13
1፤ እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ፡ አለው። ኢየሱስም መልሶ። እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው። 
በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም። 
ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። 
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። 
ብዙዎች። እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። 
ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። 
ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። 
እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። 
10 አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። 
11 ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። 
12 ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ 
13 በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 

ሐዋርያው ስለቤተ መቅደሱን ውበት ሲያሳየው እየሱስ ግን ይፈርሳል አለው በሚፈርስ ነገር አትደነቅ የፈረሰው ወደ 70 ዖ.ም. አካባቢ ላይ ነበር:: እኛም አይናችንን ማድረግ ያለብን በክብሩ ላይ መሆን አለበት የሚያስገርመን የሚያስደንቀን እርሱ ይሁን:: ደግሞም ዛሬ ቤተመቅደሱ እኛም አይደለን? እኛኑ በመንፈሱ አሳምሮ ይሰራናል:;

ሌላው የጠየቁት ነገር ስለመጨረሻው ዘመን ነበረ መቼ እንደሚሆን:: እርሱ ግን ሲመልስ ቀኑን አልቀጠረም ግን የምጥ መጀመሪያ ምልክቶችን ነገራቸው መቼም ባለንበት ዘመን ሁሉንም አይተናል ብንል ማጋነን አይሆንም:; እየሱስ ግን ትኩረት እንዲያደርጉ የሚፈልገው አንድ ጉዳይ ላይ ነው ይሄውም ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ነው ያለው:: የሚያስት እንደሚመጣ ከተነገረን እንዳንስት ምን እናድርግ? የእግዚአብሔርን ቃልና ኃይሉን አታውቁምና ትስታላችሁ ስለሚል ቃሉን እንወቅ እንዳንስት!

ስለስሙ እንግልት ሲደርስብን እራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው መልስ የሚሰጠው በሐዋርያቱ ህይወት እንዳየነው:: በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ስለዚህ በሙላት እርሱን እያሳየን እንመላለስ በምድር የሚያፍርብኝን በሰማይ ሰራዊትና በአባቴ ፊት አፍርበታለሁ ያለንን እናስብና እንበርታ! እንጽና ያለንበት ጊዜ የመጨረሻ ዘመን ነውና:: ማራናታ!

አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል ስላለን ወገባችንን ታጥቀን ወንጌልን እናድርስ::


የመጨረሻው ዘመን

የማርቆስ ወንጌል 13: 14-27
14፤ ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥ 15 በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥ 
16 በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። 
17 በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። 
18 ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 
19 በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። 
20 ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። 
21 በዚያን ጊዜም ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም። እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ 
22 ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። 
23 እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። 
24 በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ 
25 ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። 
26 በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 
27 በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። 

ያለንበት የመጨረሻ ዘመን መሆኑ አያጠያይቅም ጌታ ሊመጣ በደጅ ያለበት ጊዜ ጠላትም ጊዜ እንደሌለው አውቆ በብዙ ቁጣ ጥፋትን እያደረገ ሰዎችን በብዛት እያጠፋ ያለበት ጊዜ ላይ ነው ያለው:: የመጨረሻው መጨረሻ ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ስታዩ ነው ተብለናል:: ይህም በተቀደሰው ቤተመቅደስ እስራኤሎች በሚያቆሙት ውስጥ መጥቶ እኔ እግዚአብሔር ነኝ አምልኩኝ ሲል ማለት ነው:: እስራኤላውያን ቤተመቅደሱን አዘጋጅተው ጨርሰዋል መትከል ብቻ ነው የሚቀራቸው ያኔ በአይናችን ፊት የመጨረሻውን ለማየት እየታደምን እንደሆነ አውቀን የተመረጡትን እንኳን ለማሳት የሚችል መሆኑ የተነገረለት አሳች ይገለጣልና እንጠንቀቅ:: በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና ስለሚል ለሚጠፉት የሚራራ ልብ ጌታ ይስጠን።  እኛ ግን በዚህ ነገር የምንጨነቅ አይደለንም ምክንያቱም እኛ እስካለን ድረስ ጠላት በግልጽም አይሰራም ደግሞም በእኛ ውስጥ ያለው ይበልጣል:: እኛ ማተኮር ያለብን ሰዎችን ወደ ፍቅሩ መንግስት ማፍለስ ላይ ነው::

በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል! ሃሌሉያ! ማራናታ ጌታ ሆይ ቶሎ ና! በዚያን ጊዜም ጌታ መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።  አሜን! የዝችም ምድር ነገር ሰው እንደዚህ የሚዋደቅላት ያበቃላታል ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ።  አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይኖራል እራሱ በጉ የሚያበራበት! ከአባታችን ጋር ያለ እንባ ያለ ህመም ያለ መከራ በደስታ የምንኖርበት ዘመን ይመጣልናል:, አሜን!


ተኝታችሁ እንዳላገኛችሁ ትጉ

የማርቆስ ወንጌል 13:28-37
28፤ ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ 29 እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። 
30 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 
31 ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። 
32 ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። 
33 ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። 
34 ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። 
35 እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና 
36 ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። 
37 ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።

ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ። ነው ጌታ ያለን ድንገት ስመጣ ተኝታችሁ እንዳላገኛችሁ እያለን ነው:: እኛ የምንፈልገው በዚህ ዓመተ ምኅረት እመጣለሁኝ ብሎ ቀጠሮ ቢሰጠን ደስ ይለናል ጌታ ግን ያለው ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። አብ ብቻ ነው የሚያውቀው ስለዚህ ከእናንተ የሚጠበቀው ነቅቶ መጠበቅ ነው ብሎናል:: ስንጠብቀውም ማድረግ ያለብንንም ነግሮናል:- ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና

  1. ተጠንቀቁ፤
  2. ትጉ፤
  3. ጸልዩ 

አንድ ምልክት የተወልን ቢኖር ስለ በለስ ነው:: ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ አለን በለስ በማን ይመሰላል እዚህ ምሳሌ ላይ? በእስራኤል ነው! መንግስት ከሆነች ይኸው ብዙ አስርት አመታት ተቆጥረዋል ሰሞኑንም ዜና ከሰማን እስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት ላይ ናቸው ብዙ አገር እስራኤልን በመቃወምም ላይ ነው ታድያ ይህ ሁሉ የመምጣቱን ነገር ከመቼውም በላይ እንደቀረበ እያሳየን ነው የጌታን መምጣት የምንለካበት ቴርሞ እስታቱ እስራኤል ናት:: ስለዚህ መምጣቱ በደጅ ነውና አብዝተን እንተያይ በጸሎት እንትጋ እንዲሁም በጸጋው እንታመን::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 14

መልካም ሥራ ሠርታልኛለች

የማርቆስ ወንጌል 14: 1-9
1፤ ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና። 
እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። 
አንዳንዶችም። ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው? 
ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። 
ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። 
ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። 
የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። 
እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል። 

ኢየሱስ እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች አለ ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ሰብራ በራሱ ላይ ስታፈስስ።  ለምን ያልን እንደሆነ  የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው።  ይህ ነበረ ግብዋ መቼም ይሞታል ብላ አይደለም እጅግ ስለወደደችው ያልተለመደ ስጦታ ነው የሰጠችው የትም ቦታ ላይ አናይም እንደዚህ ያለ ስጦታ ምናልባት ሳትሰብር ብትሰጠው እሺ የተለመደ ይሆናል ይህ ግን ለየት ያለ ተግባር ነው እርሱ ግን ያውቅ ነበር ለምን እንደተደረገ:: ከመቀበሩ በፊት ይህን ወግ አያገኝም ነበረና ነው:: ይህች ሴት የተቻላትን አደረገች እንዲሁም መልካም አደረገችልኝ ነው ያለው ጌታ እኛስ ታድያ የተቻለንን ለመንግስቱ እያደረግን ነው? እራሳችንን እንጠይቅ::

የሚገርመው አንዳንዶችም ማለትም ይሁዳ ሌባ ነበረና ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው የሚባክነው ብሎ ነበረ:: ሽቶው ግምቱ ከሦስት መቶ ዲናር የሚበልጥ ዋጋ ያወጣ ስለነበር ለምን ተሽጦ ለድሆች አልተሰጠም ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት ይላል ቃሉ:: ሁልጊዜ ነቀፋ ትክክል ነው ማለት አይደለም ሰው ከራሱ ተነስቶ እንደው ደርሶ ጥሩ መከራከሪያ ጭምብል ለብሶ ሊነቅፍ ይችላል ማሰብ ያለብን ጌታ ምን ይላል ነው ሁልጊዜ በቃሉ እራሳችንን እንፈትሽ እንጂ ወደ እኛ ለተወረወረው ትችት ሁሉ መልስ ለመስጠት ጊዜ አናጥፋ እራሱ ጌታ ይከራከርልን “ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ” ብሎ እንዳለው አሜን! እዚህ ጋር የተማርኩት ሌላው ነገር ጊዜው የሆነና ያልሆነ ነገር አለ የጊዜው ነገር ምንድነው እንድናደርግ ጌታ የሚፈልገው? እርሱ እራሱ ይምራን እኛ እያለን ሌላ ፍለጋ አይሂድ እንታዘዝ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው መከረ

የማርቆስ ወንጌል 14: 10-21
10 ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። 
11 ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። 
12 ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። 
13 ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው። ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ 
14 ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። 
15 እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ 
16 በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። 
17 በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። 
18 ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። 
19 እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም። እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። 
20 እርሱም መልሶ። ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። 
21 የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው። 

እየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ለምን ይሆን የወሰነው በእርሱ ዘንድ መቀመጥ ይቀይራል እንጂ! ይሁዳ ግን ቀስ በቀስ ነው ጠላትን ወደ ህይወቱ የጋበዘው መጀመሪያ መስረቅን ተለማመደ ከዛም ሰለጠነበት በዚሁ ምዕራፍ እንዳየነው ሽንጡን ገትሮ ለድሆች ይሁን ይህ ሽቱ ሲል ነበር በጭንብል ውስጥ ተከልሎ ግን ለድሀ አስቦ አልነበረም ለመስረቅ እንጂ! ታድያ አንድ መስኮት ክፍት ከሆነ ሌባ በዛች መስኮት ገብቶ ሁሉንም ክፍል ማዳረስ እንደሚችል ሁሉ ሌብነትን ያለማመደው አሳልፎ መስጠትም ቀላል እንደሆነ መከረው እርሱም ተነዳ ስለዚህም አሳልፎ ለመስጠት ተደራደረ:: ይህ የሚያስተምረን ህይወታችንን በቀንና በለሊት የሚውጠውን ፈልጎ እንደ አንበሳ በዙሪያችን ያጏራልና ነቅተን፤ ስር ሰደን፤ ጌታን እያከበርንና ጸጋን እየጠየቅን እንመላለስ ምክንያቱም በመንፈስ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም የሚሆነው የእኛ ነገር::

ሌላው ስለዚህ ቤቱን ለመጨረሻው የጌታ እራት በፋሲካ ስላዘጋጀው ሰው እንመለከታለን:: ደቀ መዛሙርቱ መተው መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል አሉት። እርሱም ወድያው በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ አሳያቸው፤ እነርሱም በዚያም አሰናድተው ጠበቁት ጌታም ማምሻው ላይ መጣ። ሰውየው ተዘጋጅቶ ነበረ ጌታ በህልም ይናገረው ወይ በመላእክ ይናገረው ባይገለጥም እንኳን ይህ ሰው ግን ሰምቶ ተዘጋጅቶ ነው የጠበቀው:: እኛም ዛሬ በብዙ መንገድ ጌታ ልመጣ ነው እያለን እየተናገረን ነውና ተዘጋጅተን እንጠብቀው ይመጣል፤ አይዘገይም፤ በእርግጥ ይመጣል! አሜን

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ሥጋውንና ደሙን ባርኮ ሰጣቸው

የማርቆስ ወንጌል 14: 22-26
22፤ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፡ አለ። 23 ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። 
24 እርሱም። ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። 
25 እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው። 
26 መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። 

እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፡ አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ።  እርሱ እራሱ በፈቃዱ ህይወቱን ሰጠን አመስግኖ:: ይህ ማለት ሥጋው ለሥጋችን ደህንነት ደሙ ደግሞ ለሐጥያታችን ስርየት ነው:: ስለዚህ ጉዳይ ጳውሎስ ሲጽፍ ለመታሰቢያው አድርጉት ይለናል:: 1ኛ ቆሮ 11: 24፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም፦ እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡ አለ። 25፤ እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ፦ ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡ አለ።

መታሰቢያ ብለን ስንል ስለሁኔታው እያሰቡ ማመስገን ነው ማለት ነው:: ምን ተፈጠረ በዛ ምሽት የሚለውን በአይነ ህሊናችን እንዳሰው እስኪ የዓለም ሁሉ ፈጣሪ በፍጥረቱ ለመገደል ተላልፎ የሚሰጥበት ቀን! ነፃ ሊያወጣውና ወደክብሩ ሊመልሰው የመጣውን የዋሁን ጌታ ባርያ ካደረገውና በግዞት ካስቀመጠው ጋር ተባብሮ ነፃነት ይቅርብን ብሎ ያወጀበት የመግደል ስርአት! እርሱ ግን ስለበደላችን ደቀቀ ስለ መተላለፋችንም ቆሰለ የደህንነታችንም ተግሳፅ በእርሱ ላይ አረፈ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን:: የሚያደርጉትን አያውቁም እያለ እየማለደልን ስለ እኛ መከራውን በላ ሳያጉረመርም እራሱን ስለእኛ አሳልፎ ሰጠ! ከህያዋንም ምድር ተወገደ! ይህ ሁሉ በፈቃዱ ሆነ ነፍሱንም ስለእኛ አኖረ! ሃሌሉያ! የጌታን እራት ስንወስድ ይህንን እናስብ እርሱ እራሱን ስለእኛ መስጠቱን እያየን በዚህ ውስጥ እያሰብነው ለስጋችን ፈውስን ለሐጥያትም ስርየትን እንዳገኘን እያሰብን ህብረትን እናድርግ ከወደደን ጌታ ጋር! እኛም እራሳችንን እንስጠው:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ

የማርቆስ ወንጌል 14: 27-31
27፤ ኢየሱስም አላቸው፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ፡ የሚል ተጽፎአልና። 28 ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። 
29 ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። 
30 ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። 
31 እርሱም ቃሉን አበርትቶ። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። 

ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ ብሎ ቀጠሮ እየሰጣቸው ነው እነርሱ ግን አላስተዋሉም የሆነውን እናውቃለን:: መነሳቱንም እየነገራቸው ነበር ግን ምንም አልገባቸውም:: የትንቢትን ቃል ጠቅሶ እረኛው ይመታል መንጋውም ይበተናል በኔ ትሰናከላላችሁ እያለ ነበር ግን አልሰሙም:: እኛም እንደዚሁ ነው አንዳንዴ የምንመላለሰው የሚሰማኝ ከመከራ ስጋት ያርፋል ይል የለም ቃሉ? እንስማውና እርፍ እንበል እርሱ ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም የሚለእ እንዳይሆንብን እናስተውል:: ቃሉን የምንሰማ ብቻ ሳንሆን እናመንዥገው እስኪዋሀደን ድረስ:: ሰምተውት ቢሆን ኖሮ የኤማኦስ መንገደኞች አይኖሩም ነበር ፤ ፈርተው አይንቀጠቀጡም ነበር፤ ሰውን ማጥመድ ትተው ወደ አሳ ማጥመዳቸው አይመለሱም ነበር፤ ቶማስም ካላየሁ አላምንም አይልም ነበር:: ጌታ እኮ በግልጽ እየተናገረ ነው ስለመነሳቱ ማን ቢሰማ?! ማስተዋልን ጌታ ይስጠን!

ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው እራሱን ከሌሎቹ የተሻለ አድርጎ ነበር ያቀረበው ጌታም የሚሆነውን ነገረው እንዲያውም ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። የሆነውን እናውቃለን:: በጸጋ መቆም ይቻላል በኃይልና በብርታት ግን አይሆንም በመንፈሱ እንጂ! የሚረዳንን ጸጋ ለመቀበል ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ እርሱም በልግስና ይሰጠናል አለበለዚያ ግን በቀላሉ ጠላት ወጥመድ ውስጥ ገብተን እንወድቃለን:: ምን አለፋን የሚረዳ ጸጋ ካለ በእርሱ ላይ እንታመን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩ

የማርቆስ ወንጌል 14: 32-42
32፤ ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ፡ አላቸው። 33 ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና። 
34 ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። 
35 ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና። 
36 አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። 
37 መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? 
38 ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። 
39 ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። 
40 ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም። 
41 ሦስተኛም መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። 
42 ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። 

እንደልማዱ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረ ይላል ቃሉ:: ይህ እኔን ለመውለድ የተጀመረ ምጥ ነው:: ብዙ ነገር አሰብኩኝ ጭንቀቱን ሳየው ምናለ በተደበቀ ወይ አገሩን ጥሎ በሄደ ሁሉ ብዬ በሰውኛ አሰብኩኝ ግን ወግጂ እንደሚለኝ እንደጴጥሮስ አልጠፋኝም ግን ይጨንቃል ያለፈበት ይህ ሁሉ ስለእኔ? ዋው ጌታዬ ሆይ ምን እላለሁ አመሰግናለሁ!! መልሶም አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ብሎ ጸለየና ደግሞ መለስ አድርጎ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። ደግሞም ተመልሶ ይህንኑ ጸሎት ጸለየ:; አቤት ጭንቀቱ?! በዚህ ጭንቅ ውስጥ ፈቃድህ ይሁን ማለት መቻል ትልቅ ነገር ነው::  ይህን ሁሉ ጭንቅ ስላየ ነው የሚራራልን ሊቀ ካህናት አለን የሚለው ሳይፈርድ ይረዳናል::

ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና መለስ ብሎ ሲያያቸው ሐዋርያቱ ግን ተኝተው ነበር:: በምድር ወድቆ ያምጣል፤ ይጨነቃል፤ ቢቻልህ ሰዓቲቱ ትለፍ እያለ ይጸልያል አይዞህ እንኳን ሊሉት አልቻሉም:: ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን?  አለው:: ለምን ብንል እርሱ ነው እስከሞት ድረስ እንኳን ቢሆን እልለይህም ያለው ስለዚህም ቃሉ ፈተና ማምጣቱ እንደማይቀርለት ጌታ አውቆ ነው ትጋ የሚለው ግን እንቅልፍ ላይ ነበረ:: ማንም ሳያጽናናው ብቻውን አምጦ ሰዓቱ ደረስ እንግዲህ እንሂድ አላቸው:: ስለእኔ ይህ ጌታ በሐጥያተኞች እጅ አልፎ ተሰጠ! ጌታዬ ሆይ! ዋጅተኸኛልና እንደዚህ ተሰቃይተህ ስምህ ከዘላለም እስከዘላለም የተባረከ ይሁን! አሜን!

ለአንተ የምኖርበትን ጸጋ ስጠኝ!


እየሱስ ተላልፎ ተሰጠ

የማርቆስ ወንጌል 14:43-52
43፤ ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ። 44 አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 
45 መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤ 
46 እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። 
47 በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ። 
48 ኢየሱስም መልሶ። ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? 
49 በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው። 
50 ሁሉም ትተውት ሸሹ። 
51 ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥ 
52 ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ። 

እየሱስ ተዘጋጅቶ እየጠበቀው ነበር ይሁዳን ልክ እንደው እንደናፈቀ ሰው መምህር ሆይ ብሎ ሲስመውና በዛም ምልክት የተሰጣቸው ጠባቂዎች ሲይዙት እናያለን:: አሁን ደቀ መዛሙርቱ ነቁ ከመንቃትም ባለፈ ለምመምህራቸው ለመዋጋት ተነሱ:: እየሱስ ግን ይህንን አይነት ኃይል አይደለም የፈለገው እርሱ ዝም ብሎ በሸላቾቹ ፊት መሆን እንጂ ቢፈልግማ በአንድ አፍታ አንዱ መልአክ ፀጥ ጭጭ ሊያደርጋቸው ይችላል እርሱ ቢናገር ወደ አፈርነት ሰው ከመቅፅበት አይለወጥም ብላችሁ ነው? ብቻ ጌታ ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ እራሱን ሰጣቸውና ወሰዱት:: መሞት እንኳን ቢሆን ከአንተ ጋር እሞታለሁ ያለ ሁሉ ጥሎት ሸሸ:: በህይወት ላይ ይህ ሊያጋጥም ይችላል ጌታ ህን ታማኝ ነውና የትም ጥሎን አይሄድም በእርሱ እንታመን:: ድሮውንም እግዚአብሔር ልምዱ ቃል ኪዳን ሲያደርግ ብቻውን ነው ከአብርሃም ጋር ያለውን ብናይ አብርሀም እንቅልፍ ላይ ነበረ እግዚአብሔር በመስዋእቱ መካከል ሲያልፍ እንዲሁም እየሱስ የአዲስ ኪዳንን ብቻውን ተወጣ ሰው ሁሉ ፊቱን አዙሮበት:: አቤት ፍቅር!

ሰይፍ የእግዚአብሔርን መንግስት አትሰራም በመንፈስ ነው ስራው የሚሰራው:: ለዚህም ነው ጌታ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ የቀጠለው:: የሆነልን መንፈስ የፍቅር መንፈስ ነው ሁሉን መውደድ ነው የተሰጠን ትዕዛዝ ስለዚህ ምላሳችንንም እንደሰይፍ እንዳንጠቀምበት እንሰብስብ የሰውን ጆሮና ልብ አናቁስልበት ከቻልን በጨው የተቀመመ ንግግር ይኑረን አለበለዚያ ግን ዝም ማለት መልካም ነው ጌታ ይርዳን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ

የማርቆስ ወንጌል 14: 53-72
53፤ ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። 54 ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። 
55 የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤ 
56 ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም። 
57 
58 ሰዎችም ተነሥተው። እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት። 
59 ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። 
60 ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ። አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። 
61 እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። 
62 ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። 
63 ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? 
64 ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ። ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት። 
65 አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። 
66 ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥ 
67 ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና። አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። 
68 እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። 
69 ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት። ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። 
70 እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን። የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት። 
71 እርሱ ግን። ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። 
72 ጴጥሮስንም ኢየሱስ። ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

እየሱስን ብዙዎች በሐሰት ይከሱት ጀመረ ነገር ግን ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። እየሱስም ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ።  ያኔ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ብሎ ሲል ሁሉም በአንድ ድምጽ ይሙት አሉ:: አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።  ይህን ሁሉ የታገሰው እኔን ብሎ ነው:: ሃሌሉያ!

በዚህ ግርግር ውስጥ ቃሉን ለመጠበቅ የሚጥር ጴጥሮስ ነበረ:: በአንዲት አገልጋይ ፊት የምትይውን አላውቅም እያለ ቆየ እርስዋም እየተከታተለች ከእርሱ ወጉን ነው ማለትዋን ቀጠለች ጴጥሮስም መካዱን:: የሚገርመው እየካደ መሆኑን ያስተዋለው ዶሮ ሲጮህ ነው ጌታ እንዳለው ሶስት ጊዜ ካደው ዶሮ ሁለቴ ሳይጮህ:: ደስ የሚለው ግን ተጸጽቶ ማልቀሱ ነው:: ሁልጊዜ ድካሙ ነው የሚታየው ነገር ግን ከእርሱ በስተቀር አስሩ ሐዋርያት በዛም አልነበሩ እርሱ ብቻ ነበር እዛ ድረስ የተከተለው:: ዛሬም ለእያንዳንዳችን የሚያስፈልገን ጸጋ ነው ለመጽናት ስለዚህ ጸጋን እንጠይቅ::

እኛ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ እንዳለ ጌታ የምናይ ነን ጌታ በደመና ከመላእክቱ ጋር ይመጣል ሊወስደን ለሙሽራው ሰርግ ተዘጋጅተን ብርሃናችን በርቶ እንጠብቅ::


ምዕራፍ 15

የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እየሱስን ሰጡት

የማርቆስ ወንጌል 15: 1-15
1፤ ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም። አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። አንተ አልህ ብሎ መለሰለት።
የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም። 
ጲላጦስም ደግሞ። አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል ብሎ ጠየቀው። 
ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም። 
በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር። 
በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። 
ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር። 
ጲላጦስም። የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤ 
10 የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። 
11 የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው። 
12 ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ። እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው። 
13 እነርሱም ዳግመኛ። ስቀለው እያሉ ጮኹ። 
14 ጲላጦስም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን። ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ። 
15 ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። 

በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ግን እየሱስ ከዚህ በፊት በአጠገባቸው ተሰውሮ ሄዶ ያውቃል ጊዜው አልደረሰም ነበረና:: ጊዜው ሲደርስ ግን ለመስቀል ሞት አሳልፎ እራሱን በፈቃዱ ሰጠ:: በጌታ ተወደናልና ጌታን እናመስግን!

የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እየሱስን እንደሰጡት ጲላጦስ ገብቶት ነበር:: ሊፈታው ምን ቢፈልግም ህዝቡን አንድ ጊዜ አሳምጸውት ነበረና የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ።  የመጀመሪያው ነጻ ውጪ በርባን ነበረ:: ወንጀለኛው ተለቆ ጻድቁ በእርሱና በብዙዎች ፈንታ ለሞት ተላልፎ ተሰጠ:: እኛም በርባኖች ነበርን በማንኛውም ጊዜ ለፍርድ በእግዚአብሔር ፊት ብንቀርብ ሞት የሚፈረድብን ነበርን ነገር ግን እግዚአብሔር ፍርዱን ሁሉ በልጁ ላይ አድርጎት እኛ በነፃ ተለቀቅን! እንደቀላል እንዳናየው ከዘላለም ሞትና ስቃይ ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት አፍልሶናልና:: ይህንን የተደረገልንን ለሌሎች ማካፈል የበራልንን ብርሃን ልናበራና መንገድ ነኝ ያለውን እየሱስን ልናሳይ የህይወት አላማ አድርጎ ሰቶናል::

ሌላው እነዚህ የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው ነው የሰጡት:: በገላትያ 5 ላይ እንደምናየው ቅንዓት አንዱ የስጋ ፍሬ ነው እኛ ውስጥም መገኘት የለበትም:: እኛ መንፈሳውያን ሰዎች ነን ጌታ ስለዋጀን የስጋን ምኞት የማንፈፅም ነን:: በቃሉ ላይ እንደሚል ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። ስለዚህ ነው እኛ በመንፈስ ነን የምንለው:: መንፈስ ነን አላልኩም እኛ ስጋ፤ ነፍስና መንፈስ ያለን ፍጥረቶች ነን:: የምንመግበውን እንምረጥ! ስለመንፈሳዊ ነገር እናስብ በላይ መዝገባችን ባለበት ልባችንና አስተሳሰባችን ይሁን:: በማንኛውም ሰዓት አእምሮአችን ያስባል ማሰብ አቁሞ አያውቅም ስለዚህ የሚያስበውን ነገር እንስጠውና እንግራው እንደው እንደፈቀደ እንዳይጋልብ ቃሉን ዕለት ዕለት እንመግበው እምነታችንም ያድጋል ቃሉን ስናውቅ ደግሞ የቃሉን ባለቤት ወደማወቅ ያመጣናል:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ወታደሮች ተዘባበቱበት

የማርቆስ ወንጌል 15: 16-20
16፤ ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። 17 ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ 
18 የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ 
19 ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። 
20 ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። 

የሮማ ወታደሮች ጭፍራውን ሁሉ ወይንም በጊቢው ያሉትን ወታደሮች ሁሉ ጠርተው ቀይ ልብስ አለበሱትና ማሾፍ ጀመሩ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ማሾፉም ወደ መምታት ተቀይሮ የከፋውን ነገር አደረጉ ይኼውም ንጉስ ክሆነ አክሊል ያስፈልገዋል ብለው የእሾህ አክሊል ጎንጉነው ደፉበት፤  በዛም አላቆሙም እሾኩ ወደ ጭንቅላቱ ውስጥ እንዲገባ  በመቃ መቱት እርሱም አልበቃም ተፉበትም፥ መትፋቱ ይህ የመጀመሪያ አይደለም ለጌታችን ከዚህ በፊትም የያዙት ተፍተውበታል ግን ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ነው:: በኢሳይያስ 50: 6፤ ጀርባዬን ለገራፊዎች ጕንጬንም ለጠጕር ነጪዎች ሰጠሁ፥ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም። ትንቢቱ ተፈፀመ:: ምንም አይነት የጭንቀት ህመም ይሁን ከራስ ጋር የተያያዘ ህመም እርሱ እራሱ ላይ ቆስሎ ወስዶታልና እኛ መታመም የለብንም በመገረፉ ቁስል ተፈውሰናል:: አሜን!

ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ይህንን ሁሉ የሚያደርገው እኔን ለመታደግ ነው:: እንጂ በመካከላቸው አልፎ መሄድ መሰወር ይችል ነበር ግን ይህንን ሁሉ በዝምታ ተቀበለ:: ኦ ሃሌሉያ! በአምላኬ ተወድጃለሁና ጌታዬን ለዘላለም አመሰግናለሁ:: ለእርሱም ምስክር እሆናለሁ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የእየሱስ መሰቀል

የማርቆስ ወንጌል 15: 21-32
21፤ አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። 22 ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። 
23 ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። 
24 ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። 
25 በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። 
26 የክሱ ጽሕፈትም። የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር። 
27 ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። 
28 መጽሐፍም። ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ። 
29 የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ 
30 ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። 
31 እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ። ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ 
32 አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር። 

የእግዚአብሔር ጊዜ ሆነና እየሱስ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ ቢልም ከእርሱ አላለፈም ነገር ግን ተላልፎ በሐጥያተኞች እጅ ገባ:: ተፉበት፤ ገረፉት፤ ተሳለቁበት፤ ልብሱን በእጣ ተከፋፈሉ፤ የእሾክን አክሊል አደረጉለት ፤ አሾፉበት፤ ሌሎችን ያዳንክ እራስህን አድን፤ ከመስቀል ውረድ አሉት፤ እራሳቸውን እየነቀነቁ አሾፉ፤ ሌላም ሌላም ግን ትንቢትን ሁሉ እየፈጸሙ እንደሆነ አልገባቸውም ያደረጉት ሁሉ ከ700 ዓመት በፊት በኢሳያስ ትንቢት ውስጥ ተጽፎ ይገኝ ነበር:: ከመገረፉና ከመድከሙ የተነሳ መስቀሉን እንኳን መሸከም አልቻለም ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆን የኛ ጌታ ዝም ብሎ ታገሰ የሚሰጡትንም ባህላዊ የህመም ማስታገሻ አልተጠቀመም እንቢ ነው ያለው እያንዳንዷን ህመም ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ ተሰቃየ አፉንም አልከፈተም:: ሃሌሉያ! እንዴት ያለ ፍቅር ነው? እውነትም:- ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለም ነፍሱን ስለሌሎች አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ:: ለዚህ ለዋጀን ለእግዚአብሔር በግ ክብር ይሁን:: አሜን!

እስኪ ዛሬ ይህንን ጌታ እናስበውና ስላደረገልንም ድንቅ የመስቀል ስራ እናወድሰው:: በምስጋና ብቻ እንዋል እርሱ ወዳጅ ነው:: ወዳጅ ደግሞ አብዝቶ አብሮነትን እንደሚፈልግ ሁሉ ዛሬም ጌታ ከእኛ ጋር ማሳለፍን ይወዳልና እድል እንስጠው እናዳምጠው ስሙንም እንቀድስ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ሰጠ

የማርቆስ ወንጌል 15: 33-41
33፤ ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 34 በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው። 
35 በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ። 
36 አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ። ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው። 
37 ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ። 
38 የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። 
39 በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። 
40 41 ሴቶችም ደግሞ በሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ መግደላዊት ማርያም የታናሹ ያዕቆብና የዮሳም እናት ማርያም ሰሎሜም ነበሩ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የወጡ ሌሎች ብዙዎች ሴቶች ነበሩ። 

ከስድስት ሰዓታት የመስቀል ላይ ስቃይ በኃላ ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ።  በዚህም ሰዓት ፀሐይ ብርሃንዋን ከለከለች ምድርም በጨለማ ተዋጠች:: በዘመኑ የነበረው የሰው ልጅን ያስተውል ይሆን? ያለ ሰዓቱ ጨለማ ሲሆን? እርግጠኛ ነኝ ያስተውላሉ ግን በምን ምክንያት እንደሆነ የሚያውቅ አንድ ሰው እንኳን አለ ለማለት ያስቸግራል በኢሳያስ ላይ እንደሚለው:- በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ማንም አላስተዋለም::

በዛ ሁሉ ስቃይ ውስጥ አልፎ በድብደባ፤ በረሀብ እንዲሁም እንቅልፍ በማጣት ተዳክሞ እያለ በዙሪያው ያሉትን ያስገረመ ነገር ሆነ ይሄውም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? አለ:: እግዚአብሔርም ተወው ፊቱንም አዞረበት የመጣበትን ስራውን እስኪጨርስ ድረስ:: በታላቅ ድምፅ መጮህ አይደለም አይኑንም ማንቀሳቀስ የሚያቅት ከባድ ህመም፤ ስቃይና ድካም ላይ ነው ያሉት ብለው ነው የሚያስቡት ለዚህም ነው ሞታቸውን ለማፍጠን ጭናቸውን የሚሰብሩት:: እነዚህ ወታደሮች ብዙዎችን አይተዋል ሁሉም በሰመመን ውስጥ ገብተው ነው የሚሞቱት እንጂ ይህን ያህል ሀይል እንደማይኖር እርግጠኛ ናቸው:: እርሱ ግን ጮሆ ነፍሱን በፈቃዱ አስረከበ:: ለዚህም ነው በፊቱ ቆሞ የነበረው የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። ሃሌሉያ! የእግዚአብሔር ልጅ ነው! ይህን ሁሉ የሆነው ስለእኔ ነውና ጌታን አመሰግናለሁ::

የቤተመቅደሱን መጋረጃ ምን ነካው? ከስራው ማን አሰናበተው? ከዚህ በኃላ በእኔና በህዝቤ መካከል አትለይም ብሎ ከላይ ወደታች ቀደደው ስለዚህም በእየሱስ ስጋ በኩል ወደፊቱ ለመግባት ድፍረትን አግኝተናል ደሙ ከሐጥያት ሁሉ አንፅቶናል:: በእኛና በእርሱ መካከል የሚለይ ነገር የለም እርሱ በእኛ፤ እኛም በእርሱ ውስጥ ነን:: ሃሌሉያ::


የእየሱስ መቀበር

የማርቆስ ወንጌል 15: 42-47
42፤ አሁንም በመሸ ጊዜ የሰንበት ዋዜማ የሆነ የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ የከበረ አማካሪ የሆነ የአርማትያስ ዮሴፍ መጣ፥ 43 እርሱም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር፤ ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። 
44 ጲላጦስም አሁኑን እንዴት ሞተ ብሎ ተደነቀ፥ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ቆይቶአልን? ብሎ ጠየቀው፤ 
45 ከመቶ አለቃውም ተረድቶ በድኑን ለዮሴፍ ሰጠው። 
46 በፍታም ገዝቶ አውርዶም በበፍታ ከፈነው ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው፥ በመቃብሩ ደጃፍም ድንጋይ አንከባለለ። 
47 መግደላዊትም ማርያም የዮሳም እናት ማርያም ወዴት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።

ከአርማትያስ የሆነው ዮሴፍ የሚባል ሰው የእየሱስን ስጋ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ገብቶ ጠየቀ:: ደፍሮ የምትለውን ቃል እዩልኝ ምክንያቱም ዓለም ሁሉፊቱን ከእየሱስ ባዞረ ጊዜ ዋጋ ቢያስከፍለኝም ያስከፍለኝ የመጣም ይምጣ ብሎ ነው የጠየቀው እናም የተፈቀደለት:: ጲላጦስ ግን በዚህ ፍጥነት እንዴት ሞተ ነበር ያስገረመው ይህ የሚያሳየው በራሱ ነው ነፍሱን የሰጠው ጌታችን:: ማንም ነፍሴን ከኔ አይወስዳትም በፈቃዴ ግን አኖራለሁ ብሎም የለ?

ሌላው ስለዮሴፍ ያየሁት ነገር የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር ይላል ከስራቸውም ጋር አይተባበርም ነበር:: የሚገርም አቋም ነው መንግስቱን መጠበቅ ይህንንም በማድረጉ መቃብሬን ከባለ ጸጎች ጋር አደረግህ የሚለው ትንቢት በእርሱ ተፈፀመ:: ለራሴና ለአንባብያን የምጠይቀው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየተጠባበቅን ነው? ጌታ በደጅ ነው መንግስቱን አገልግለን እንለፍ በእጃችንም ያለውን መክሊት እናትርፍበት::

በዚህ ክፍል ላይ የምናያቸው ሴቶች አሉ:: እነዚህ ሴቶች የጌታ ወዳጆች ናቸው ትጋታቸውም ይገርማል ከማለዳ ጀምሮ እስከመጨረሻዋ እረፍቱ ድረስ ይከተሉና የሚደረገውን ሁሉ ያዩ ነበር:: አንድ እንኳን ሐዋርያ ሊገኝ ባልቻለበት ሁኔታ እነሱ ግን አልተለዩትም:: እነሳለሁ የሚለውን መልእክት ስላላስተዋሉ በዛ እንኳን መጽናናት እስከማይችሉ ድረስ ነው የነበሩት:: የእነሱ ዓላማ ያረፈበትን አይተው ተመልሰው መተው ፍቅራቸን ሽቱና ዘይት በመቀባት ለመግለጽ እንጂ የትንሳኤው የመጀመሪያ ምስክር የመሆን አልነበረም:: ሽቶውንማ መቅደላዊት ማርያም ከአንድ ቀን በፊት አድርጋለች:: ተናግሮም ነበር ለመቃብሬ እያዘጋጀችኝ ነው ብሏቸው ነበር ግን ማን ቢሰማ? ወገኖቼ ጌታ ይናገራል ማስተዋልን ይስጠን ስንቱ ሽው ብሎ ሳንገነዘበው አልፎብን ይሆን?! ጌታ ይርዳን!

ጌታ እየሱስ ስለእኛ ሞትን ቀመሰ ተቀበረ እንዴት ያለ አእምሮን የሚያልፍ ፍቅር ነው:: ታድያ እንደዚህ ከወደደን እንዴት ቅርብ ሆኖ ሊረዳን እንዳለ፤ ፀሎታችንን ሊሰማና ሊመልስ እንደሚችል አይጥፋብን እኛ በጣም የተወደድን ልጆች ነን! ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ብሌናል:: ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 16

ኢየሱስ ተነሥቶአል በዚህ የለም

የማርቆስ ወንጌል 16: 1-6
1፤ ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ። 
እርስ በርሳቸውም። ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር፤ 
ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ።
ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። 
እርሱ ግን። አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። 

የእየሱስን መቃብር እስከ መጨረሻ አይተው የሄዱት ሽቱ አምጥተው ሊቀቡት ነው:: ያሳሰባቸው ግን አንድ ነገር አለ እሱም ድንጋዩ ነበር እየተነጋገሩም የመጡት እሱኑ ነበር:: ነገር ግን ስንት ጊዜ ነው ጌታ እነሳለሁ ብሎ የነገራቸው?! ማስተዋልን ይስጠን! እርሱ በህይወት አለ እነርሱ ግን እንደሞተ ነው የሚያውቁት ገንዘባቸውን ጊዜያቸውን እያባከኑ ነው በእርግጥ ፍቅራቸው በጣም ደስ ይላል:: እርሱ ግን ወደገሊላ እቀድማችኃለሁ እንዳለ ይመጣ ነበር:: ቢሞትም እንኳን ብዙዎች ሲተውት እነሱ በታማኝነት መጡ:: የበለጠን ዜና ተቀበሉ:: ከእውቀት ያለፈ ነው ጌታችን የሚለንን ብቻ እንስማው እናም እንዴት ብለን አንጠይቅ አሜን እንጂ:: ሁላችንም ታሪክ አለን ትላንትን እንዴት እንዳሳለፈን ዛሬም ያው ነው አይጥፋብን ያደረገልን ተአምራት:: ቀና ብለው ሲያዩ ድንጋዩ ተንከባሏል!!! ሃሌሉያ! ያስጨነቀን ነገር ሁሉ ዛሬ በእየሱስ ስም ይንከባለል:: አሜን!

ከዛም ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ።  የእግዚአብሔር መልአክ በዛ እየጠበቃቸው ነበር ኃዘናቸውን የሚያስረሳ ዜና ሊነግራቸውና የመጀመሪያዎቹ የትንሳኤ ምስክሮች ሊሆኑ:: መልአኩም:- አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ።  መቃብሩ ባዶ ነው ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል እርሱ ብቻም አይደለም የተነሳው በእርሱ ያመንን እኛም ተነስተናል!! አሜን! ዮሃንስ እንደጻፈው በራእይ ላይ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። አሜን! የምናመልከው ጌታ ሁሉን የተቆጣጠረ ነው:: ለነሱ እነሳለሁ ብሎ እየደጋገመ ነግሯቸው እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ለእኛ ደግሞ እመጣለሁ እንዳለ ነውና ጌታ ይመጣል እንዘጋጅ!!

ማራናታ!!


የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል በእጃቸው ላከው

የማርቆስ ወንጌል 16: 6-8
እርሱ ግን። አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ።  ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም። ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው።  መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም አንዳች አልነገሩም። እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው። 

የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው:: አሜን! ወንጌል ዘመን ተሻጋሪ ነው ዛሬም አልተለወጠም! ዛሬም ይሰራል አሁንም የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች እንዲድኑና ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት እንዲፈልሱ ነው:: ለዚህ ወንጌልም ባለአደራ ሆነን በእጃችን ተቀብለናል:: ጌታ ይርዳን መድረስ ያለብንን ሰዎች ሁሉ እንድንደርስ::

እነዚህ ሴቶች የመጡት አስክሬን ፍለጋ ነው የጠበቃቸው ባዶ መቃብር ከመላእክ ጋር ታድያ እንዴት አይደነግጡ? ጭራሽ በዚህ የለም ሲላቸው ስንት አሳብ በአእምሯቸው ውስጥ እንደተመላለሰ መገመት ይቻላል የት ወሰዱት? ለምን ያንገላቱታል? ሌላም ሌላም እንጂ ተነስቷል የሚለው አሳብ ውልም አላለላቸውን:: ሲነግራቸው ነበር እንደሚነሳ ግን አላስተዋሉም::

መልአኩም መልክት ላካቸው ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩ ካለ በኃላ ለጴጥሮስም ይላል ጴጥሮስ ደቀመዝሙር ውስጥ አይጠቃለልም እንዴ? ምናልባትም ሶስት ጊዜ ስለካደው በፀፀት ላይ ይሆን? ብቻ ጌታ የሚያውቀው አለና ነው ይህንን ያስገባው:: ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው።  ይህንን ሁሉም ስተውታል ደግሞ ደግሞ የነገራቸው ጉዳይ ነእ ተነስቶ ሲመጣ ቀጠሯቸው በገሊላ ነበር ግን አንዳቸውም ትዝ አላላቸውም ስለዚህ ነው ሌላ መልክተኛ ያስፈለገው:: መቼም እህቶቻችን የመጡት ለምድር ሚሽን ነበር እርሱ ግን የምስራቹ አብሳሪ አድርጎ ሚሽናቸውን ቀየረው ሽቷቸውንም ይዘው ወደ ሚሽናቸው ወጡ::

ነገር ግን የገጠማቸው ያልጠበቁት ስለነበረ አእምሯቸው ማገናዘብም የከበደው ይመስላል በቃሉም እንደሚነግረን መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ እንጂ ሃሌሉያ ጌታ ተነስቷል ብለው አይደለም ከዛ የወጡት:, ጠብቀው ግን ቢሆን ኖሮ እንዴት ያለ የአምልኮ ጊዜ ይሆንላቸው ነበር ብዬ አስባለሁ:: ጌታ ምን ብሎናል? በጣቢያው ላይ ያለንን በልባችን ይዘን እንጠብቀው ጌታ አይዘገይም:: ሄደውም መልክቱን ሲናገሩ በአጭሩ ተናገሩ ነው የሚለው ምናልባትም ልክ እንሆን ያየነው እውነት ነው እያሉ ይሆናል ግን እራሱ ሲመጣ ሌላ ምን ምስክር ያስፈልጋል ያኔ ሁሉም ሞትን ድል ነስቶ መነሳቱን አወቁ::

ጌታ ሊመጣ በደጅ ነውና አይናችንን በእርሱ ላይ እናድርግ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እየሱስ አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ

የማርቆስ ወንጌል 16: 9-14
9፤ ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ። 10 እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ 
11 እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። 
12 ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤ 
13 እነርሱም ሄደው ለሌሎቹ አወሩ፤ እነዚያንም ደግሞ አላመኑአቸውም። 
14 ኋላም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፥ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። 

እንደው እውነት እንነጋገርና እኛ ብንሆን ከሞት የተነሳነው መጀመሪያ ለማን እንገለጥ ነበር? አልሞትኩም በህይወት አለሁ! እያልኩኝ ለጲላጦስ፤ ለሔሮድስ ወይም ለሊቀ ካህናቱ አይመስላችሁም? እየሱስ ግን የታየው ለተከታዮቹ ብቻ ነበረ ለዛውም ሰባት አጋንንት ላወጣላት በአገልግሎቱ እጅግ በተጠቀመች ሴት ብዙ ስለተተወላት ብዙ ለወደደች ከፍቅርዋም የተነሳ ያልተለመደ የሽቶ ብልቃጥን በመስበር ስጋውን ለመቃብር ላዘጋጀች ምስኪን ሴት:: እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ 
እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። ይገርማል! እነሳለሁ ብሎ ስንቴ አስተምሯል አሁን ደግሞ የመነሳቱ ዜና ሲመጣ ሊያምኑ አልፈለጉም:: ኃዘናቸውን ትተው በደስታ ተሞልተው መጠበቅ ሲገባ አላደረጉትም:: ጠላትና ስጋችን የሚለንን ትተን ቃሉ የሚለንን እንያዝ::

ሁለቱ የኤማኦስም መንገደኞችም ታየን ብለው ነገሩአቸው እነሱንም አላመኑም:: እየሱስ ግን ከተበተኑበት አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ እያደረጋቸው ነው:: በስተመጨረሻም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፥ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። 

ነቀፈ?! እንዴት አይነቅፍ ሲነግራቸው ከርሞ አላስተዋሉም መልእክተኛም ቢልክባቸው አላመኑ ታድያ ይገርማል ቢወቀሱ? እየሱስ የሚወቅሰን በአንድ ነገር ነው እርሱም አለማመንን:: ያለ እምነት እግዚአብሔር ደስ ማሰኘት አይቻልምና እንዲሁም ጻድቅበእምነት በህይወት ይኖራል እንደሚል የምናምን አማኝ እንሁን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን ማስተዋልንም ይስጠን!


የተሰጠን አደራ

የማርቆስ ወንጌል 16: 15-16
15፤ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፡ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። 16 ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። 

ከትንሳኤው በኃላ ጌታ እየሱስ በመካከላቸው ተገኝቶ አደራን ሰጣቸው:: ይህንን ቃል ለምናምንም ሁሉ ነው ይህ አደራ እንጂ ለሐዋርያቱ ብቻ አይደለም::

  1. ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፡ – እንግዲህ በመጀመሪያ የተሰጠን አገልግሎት እኛ ነን ወደ አልዳኑት የምንሄደው:: የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ባይሄዱ ኖሮ እኛጋር ወንጌል ባልደረሰ ነበር::
  2. ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። የምንሰብከው ለፍጥረት ሁሉ እንጂ ለኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም:: ጌታ ሁሉንም የሰው ልጅ ነው በልጁ መጠቅለል የሚፈልገው:: ሳንመርጥ ለሰው ልጅ ሁሉ ወንጌልን እንንገር:: እግዚአብሔር እንታረቅ በደልንም አላድብም ይላል ብለን መልክቱን እናድርስ::
  3. (በስብከታችሁ) ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። መጠመቅ በአደባባይ በጌታ በእየሱስ አዳኝነት አምኛለሁ ብሎ በአደባባይ ማወጅ ነው እንጂ ጌታ ሲደመር መጠመቅ መዳን ነው ብለን እንዳናስብ መዳን በበጉ በእየሱስ በማመን የሚመጣ ነፃ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው:: ለምሳሌ ቆርኖሊዮስን በሐዋ 11:1-18 ስናይ ሳይጠመቁ በፊት መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረዷልና መዳናቸውን እናውቃለን:: ሌላው ደግሞ ከጌታ ጋር የተሰቀለው ወንበዴ ዛሬ በመንግስትህ አስበኝ ብሎ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ ተብሎ ድኗልና:: ካልተጠመቅን መንግስተ ሰማያት አንገባም አይደለም ምልክት ነውና እንጠመቃለን::

በጸሎት እየተጋን ጌታ የተሰጠንን ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን የመስበክ ተልዕኮ እየተወጣን ሰዎችን ከፍርድ እንታደግ እንዳለንም በመሄድ እናድርስ:: እንደተፈረደባቸው አያውቁም እኛ ግን እናውቃለንና ሙጭጭ ብለን ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት እንዲፈልሱ እንርዳቸው:: ይህ ተልዕኮ የተሰጠ ለሁላችንም ነው እንጂ ለተወሰኑ ሰዎች አይደለም::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የአማኝ ምልክቶች

የማርቆስ ወንጌል 16: 17-20
17፤ ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ 18 የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ። 
19 ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። 
20 እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።

ጌታ እየሱስ ሂዱና ወንጌልን ስበኩ ብሎ ሲልከን ባዶ እጃችንን አይደለም:: አብሮን እንደሚሰራ ነግሮን ነው በእኛ ብቃትና ችሎታ የሚሆን ነገር የለም ሁሉ በእርሱ ነው:: እርሱ ደግሞ እውነተኛ ነውና ስናምነው እነዚህ ምልክቶች ይከተሉናል፤

  1. በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በስሙ ነው የሚወጣው ምክንያቱም ስሙ ከስም ሁሉ በላይ ከፍ ያለ እንዲሆን አብ አድርጏልና ሁሉ ይንበረከካል:: ከእኛ ጋር ስሙን የሚያያይዘው ነገር የለም የበር ቁልፍ ቢሰጠን ማን እንደሆንን አይቶ ነው እንዴ በሩ የሚከፈተው? በፍፁም የቁልፉ ትክክለኝነት ብቻ ነው የሚያስፈልገው:: ስሙም እንደዚሁ ነው በራሱ ይሰራል አምነን መሰማራት ብቻ ነው ከእኛ የሚጠበቀው:: አጋንንት ይህንን ስም ስንጠራ ለቆ ይሄዳል::
  2. በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ ይህ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላታችን ልዩ ምልክት ነው:: መንፈስ በማይነገር መቃተት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በእኛ ውስጥ ይጸልያልና አበረታታችኃለሁ ሁልጊዜ በልሳን መጸለይን አዘውትሩ:: በአማርኛ ስንጸልይ ወድያው ጸሎታችን ያልቃል በልሳን ግን ከሆነ ሙሉ ቀን መጸለይ ይቻላል::
  3. እባቦችን ይይዛሉ፥ መቼም እየዞርን እባብን ከነነፍሱ የመያዝ ራዕይ አይደለም ይሄ ነገር ግን ጠላት የሚያመጣውን ውጊያ ሁሉ ማየትና ማሸነፍን ያሳየናል
  4. የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እኔ መርዝ ብጠጣ አልሞትም ብሎ መጠጣት ሳይሆን ሳናውቅ ጠላት ሊያጠቃን ቢመጣ ጥበቃ አለን:: እርሱ ሊሰርቅና ሊገድል አይደል የሚመጣው?
  5. እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ:- እየሱስ ደዌያችንን ተቀብሏል ህመማችንንም ወስዷልና በእምነት እጃችንን ስንጭን የህመም ኃይል ይሰበራል::

ኢየሱስም ይህንን ሁሉ ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።  አሜን ሊቀ ካህናችን እየሱስ በሰማይ አለ:: ሐዋርያትም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር። እነሱ እንደወጡ እኛም ወተን እንስራ ጌታም ከእኛ ጋር አብሮ በመስራት ቃሉን ያጸናልና:: ሃሌሉያ! ጌታ አልተለወጠም!!!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!!
የማርቆስን ጥናት እዚህ ላይ ጨርሰናል::


Published by Betty & Abera

We’re dedicated to share God’s goodness and mercy through His word!

Leave a comment