የሐዋርያት ሥራ

የሐዋርያት ሥራ የሚያሳየው እንዴት መንፈስ ቅዱስ እየሱስን እየገለጠውና እያገነነው እንደሆነ ነው:: ቤተክርስትያን በእግዚአብሔር ኃይል እንደተመሰረተችም እናያለን::  ሰው እያየና እየሰማ የእግዚአብሔር መንፈስ በሰው ላይ ወረደ::  ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ድምጽ ከሰማይ መጣ የነበሩበትንም ቤት ሞላው::  

 2: 4፤ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። 6፤ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ።

በቃሉም እንደሚል:- 1: 3፤ ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።

ስለ ትንሳኤው ከእነርሱ በላይ ምስክር ማን መሆን ይችላል?

2: 32፤ ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ 

2: 24፤ እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።

ደግሞም ትእዛዝን ሰጣቸው:- 

1: 4፤ ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን፦ ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ 5፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፡ አለ።

ይህንንም ቃል ፈጸመው:- 

2: 33፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።

ዛሬም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው እቅድ መንፈሱን በልግስና ማፍሰስ ነው :-

 2: 17፤ እግዚአብሔር ይላል፦ በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ 

አሜን ስራው የእርሱ የሚሰራውም እርሱ ክብርም ለእርሱ ይሁን!!!  አሜን!!!

Introduction
የሐዋርያት ሥራ 1: 1-8
የሐዋርያት ሥራ 1: 9-11
የሐዋርያት ሥራ 1: 12-26
የሐዋርያት ሥራ 2: 1-4
የሐዋርያት ሥራ 2: 5-13
የሐዋርያት ሥራ 2: 14-21
የሐዋርያት ሥራ 2: 22-32
የሐዋርያት ሥራ 2: 33-42
የሐዋርያት ሥራ 2: 43-47
የሐዋርያት ሥራ 3: 1-10
የሐዋርያት ሥራ 3: 11-18
የሐዋርያት ሥራ 3: 19-26
የሐዋርያት ሥራ 4: 1-14
የሐዋርያት ሥራ 4: 15-22
የሐዋርያት ሥራ 4: 23-31
የሐዋርያት ሥራ 4: 32-37
የሐዋርያት ሥራ 5: 1-11
የሐዋርያት ሥራ 5: 12-16
የሐዋርያት ሥራ 5: 17-27
የሐዋርያት ሥራ 5: 28
የሐዋርያት ሥራ 5: 29-42
የሐዋርያት ሥራ 6: 1-7
የሐዋርያት ሥራ 6: 8-15
የሐዋርያት ሥራ 7: 1-60
የሐዋርያት ሥራ 8: 1-8
የሐዋርያት ሥራ 8: 9-25
የሐዋርያት ሥራ 8: 26-40
የሐዋርያት ሥራ 9: 1-9
የሐዋርያት ሥራ 9: 10
የሐዋርያት ሥራ 9: 11-19
የሐዋርያት ሥራ 9: 20-26
የሐዋርያት ሥራ 9: 27-31
የሐዋርያት ሥራ 9: 32-43
የሐዋርያት ሥራ 10: 1-7

የሐዋርያት ሥራ 10: 9-17፤ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ። 17፤ ጴጥሮስም ስላየው ራእይ፦ ምን ይሆን? ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤

እግዚአብሔር እንደዚህ ነገሮችን እያቀናበረ የሚመራ ጌታ ነው::  ዛሬም ይችላልና ምራኝ እንበለው ሲናገረንም የምንሰማበትን ጸጋ ይስጠን::  የመንግስቱን ስራ በእኛም ይስራ::  አሜን

የሐዋርያት ሥራ 10: 38

38፤ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን 

በመንፈስ ቅዱስ 

በኃይልም ቀባው፥ 

እርሱም 

መልካም እያደረገ 

ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ 

እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤

እርሱ ተቀብቶ አገለገለ እኛንም ዛሬ ሲልከን ሁሉን አስታጥቆ ነውና ስራችን እርሱ የጀመረውን መቀጠል ነው::  ማንም ከማንም አይበልጥም እርሱ አባት ነውና ለማንም ሳያዳላ በተጠማ ሁሉ ላይ ኩመንፈሱ ያፈሳል:: መልካም ለማድረግ ምንም ችሎታ የለንም ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ይቻላል:.  ሌላው ለዳያቢሎስ የተገዙትን መፈወስና መፍታት ነው ስራው ይህንን የሚያደርገው እርሱ እራሱ ነው በእኛ ውስጥ::  እስከ አለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎን የለ ታድያ ለምን አይወስደንም ጎሉ ከእኛ ጋር ብቻ መሆን ከሆነ አይደል እንዴ? ነገር ግን ስራ አለን እርሱ በእኛ ሆኖ የሚሰራው::  የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ብሎ የተወሰነ ሰው የለም ሁሉ ድንኳኑን እየሰፋ ሙሉ ጊዜ ያገለግላል አለበለዚያማ ጎዶሎ ጊዜ ልንሰጠው  ነው እርሱ  ሙሉ ዋጋ ከፍሎልን የምን የተሸራረፈ ነገር መስጠት ነ?!!

ተነስተን የጠላታችንን ደጅ እንውረስ!  ጠላትን ከምንሰማ ጌታችንን እንስማ ውጡ ውረሱ እያለን ነው::  ተባረኩ! 

የሐዋርያት ሥራ 11: 15፤ ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው።

የአህዛብ ታሪክ የተቀየረበት ሐዋርያቱንም አሀ! ያስባለ ክፍል::  እንደእኔ ከሆነ መቼም ክርስቶስ ለእስራኤሎች የመጣና ርዝራዡ የደረሰኝ ነበር የሚመስለኝ:- እርሱ ግን እራሱን የዳዊት ልጅ ሳይሆን ይል የነበረው የሰው ልጅ ነበር::  በዘላለም እቅዱ ውስጥ እንዳለን ገና አዳም ሲወድቅ እመጣለሁ ብሎ ቃል እንደገባ ለሰው ልጅ ሁሉ መጣ::  አስቦ ወለደን!  እርሱ ፈልጎን መጣ!  ይህ ጌታ እኮ በሲና ተራራ ላይ የተገለጠው ነው ማንም እንዳይቀርብ ብሎ ያለ የቀረበ ሁሉ እንስሳም ቢሆን ይሞት ነበረ::  ሊቀ ካህናቱ እንኳን በአመት አንድ ጊዜ ሲገባ ጎትቶ ማውጫ እግሩ ላይ አስሮ  ነበር::  እንግዲህ ይሄ ጌታ ነው በእኛ ውስጥ ሊኖር የመጣው !!! አይደንቅም!  ማንም የማይለውጠው እውነት!  እግዚአብሔር በሰው ውስጥ መኖሩ!  የቀደሙት ነብያትን የሚጠቀምባቸው እየመጣና እየሄደ ነበር እንጂ አብሮ ኖሮ አይደለም::  ሙሴን እንኳን ከውጪ ነው ያናግረው የነበረው::  ዛሬ የሆነውን ቢያዩ መቼም ይደነግጣሉ እላለሁ ::   የሆነልን ግርም ይላል!  ስሙ ይባረክ ከእኛ ጋር ለሚኖረው ለዚህ ለከበረ ጌታ ክብር ይሁን::  አብሮን ሊኖር ለመጣው ጆሮአችንን ልባችንን እንስጠ እርሱ ሁሌ ይናገራል ይመራል::  ከእስትንፋሳችን ይልቅ ቅርብ ነው::  አሜን

የሐዋርያት ሥራ 12

5፤ ጴጥሮስም በወኅኒ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር።

የጸሎቱም መልስ:- 

የሐዋርያት ሥራ 12

7፤ እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና፦ ፈጥነህ ተነሣ፡ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ።

በሮች ሁሉ አውቀው እየተከፈቱ ከሰማይ ለመጣው መልስ ምላሽን ሰጡ::  እየጸለዮ ያሉት ወገኖች ግን ለዚህ ፈጣን መልስ የተዘጋጁ አይመስሉም::

የሐዋርያት ሥራ 12

15፤ እነርሱም፦ አብደሻል፡ አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም፦ መልአኩ ነው፡ አሉ።

የሚገርመው:-

እርሱ ሳይሆን መልአኩ ነው::  መልአክ በር ያንኳኳል እንዴ?  ዘው ብሎ  ይገባል እንጂ::  ለማንኛውም ጴጥሮስ ተፈቷል ሰንሰለቱም ከእጁ ወድቆ መልስ ሊሆን በደጅ ላይ ዘገየ::  መጸለይ ብቻ ሳይሆን መቀበልንም እንለማመድ

ጌታ እየሱስ እንደተናገረው:-

የማርቆስ ወንጌል 11

23፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር፡ ቢል ይሆንለታል።

ጸሎት ከእግዚአብሔር ዘንድ መልስን ያመጣል:: መጸለይን ብቻ ሳይሆን መቀበልን በእምነት እንለማመድ!!

የሐዋርያት ሥራ 12

24፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር።

ይህ የሆነው ግድያው ማሳደዱ እያለ ነው::  ገዳዩ በትል ተመቶ እንቅፋት ከመሆን ተወገደ ወንጌልን የሚጋፋ አይበጀውም “ሳኦል ሆይ ለምን ታሳድደኛለህ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል” እንደተባለው ሄሮድስ ላይ ደርሶ እናየዋለን::  እኛን የነካ እርሱን ነክቷል ግን እራሳችንን ጌታ እንደሚያየን እናያለን?!  አንዳንዴ  ጉዲፈቻ የሆንን ነው  የምንመስለው አባት እያለን አልተዋችሁም እያለን ደርሶ የጠላትን ሽንገላ እየሰማን ስንት ጊዜ ይሆን ጌታን ያማነው?  እግዚአብሔር ማስተዋል ይስጠንና እንደተወደዱ ልጆች እንመላለስ ወንጌላችንም መውረሱን ይቀጥል::

የሐዋርያት ሥራ 13

10፤ አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን?

እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በየቦታው አሉ::  መልካም ልብ ይዘው ሰዎች ወንጌልን እንዳይቀበሉ ሰይጣን የሰለጠነባቸው ለማሳት የሚጠቀምባቸው ወይም የዘራነውን ወንጌል የሚያጣጥሉ::  በጌታ በእየሱስ ስም አሁን የጌታን ወንጌል እንሰብካለንና ሊሰሙ ካሉ ሰዎች ዙሪያ ልቀቁ::  መንገዳችሁ ከመንገዳችን አይገናኝ!  ወንጌልን ሊሰሙ የሚፈልጉ ሁሉ መንገዳቸው ከመንገዳችን ይገናኝ!  ጌታ ሆይ ነፍሳትን ወደ ቤትህ ሰብስብ የመከሩ ጌታ ሆይ እኛንም ቀብተህ ላከን::  አሜን!

የሐዋርያት ሥራ 13

17፤ የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። 18፤ በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው።

ጳውሎስንና በርናባስን ለዮልኝ ብሎ መንፈስ ቅዱስ ለይቶ ላካቸው::  በዚህ ስፍራ ላይ እንዳየነው ወደ ተላኩበት ሄደው ወንጌልን መስበክ ቀጠሉ ::  

እስራኤልን ከግብጽ ሲያወጣ አንዳቸውንም ተማምኖ አይደለም :: እነዚህ ሰዎች በባርነት የደቀቁ ግብጾቹ እንደፈለጉ የሚያደርጏቸው ነበሩ::  ግብጾቹ ደግሞ በጊዜያቸው ኃያላን ምርጥ ጦር ያላቸው ነበሩ ይህም እግዚአብሔርን አልገደደውም ህዝቡን ከፍ ባለው ክንዱ አወጣቸው::  ብቻውን ተዋጋላቸውና ከመከራቸው ገላገላቸው:: በበረሃም ለአርባ ዓመት ይህንን ሁሉ ሚሊዮን ህዝብ መገባቸው::  እንደው ስለለመድነው ነው እንጂ ቃሉን ይህ እኮ ትንግርት ነው::  ተጏድሎበት አያውቅ በየዓለቱ ምግባቸውን ይሰጣቸው ነበር::

ዛሬ ስለነገ አታስቡ ስንባል አንሰማም ዛሬን ሳንኖር ስለነገ እንዳሰብን አለን::  አትጨነቁ ተባልን ፤ እኔ አስብላችኃለሁ ፤  ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም እያለን ስንቶቻችን እሺ ታውቅልኛለህ ብለን እርፍ ብለን ነገራችንን ከምስጋና ጋር ሳንጨነቅ የምናሳስበው ይሆን?  እርሱ እኮ ሚሊዮኖችን በምድረበዳ ለአመታት መግቧል አቅርቦት በሌለበት ውስጥ እንኳን አልጎደለበትም::  የእኛ ጌታ እንዲሰራ ሁኔታዎችም መሟላት አያስፈልጋቸድም ምክንያቱም የሌለውን እንዳለ አድርጎ ይጠራዋል::  

እንታመን በዚህ ጌታ ግብጾች በእስራኤል ላይ የተጠበቡት በማድከም ነው ቃሉ ከሰሚዎቹ ጋር ሊዋሀድ አልቻለም ነበር::  ዛሬም  ይሄ ውጊያ ይሰራልና ከጠላት መጠበብ እናምልጥ አንተ ታውቅልኛለህ በማለት እንጽናና ዛሬን እየኖርን የተሰጠንን ተልኮ እንፈጽም እርሱን ወንጌልን መስበክ የጠፉትን መፈለግ ይብዛልን:: ከፍቅርም በቀር እዳ እንዳይኖርብን እንትጋ::  የእግዚአብሔር ጸጋ ይርዳን!!  አሜን

የሐዋርያት ሥራ 13

46፤ ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው፦ የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን።

እኛም የታሰብን ነበርን በእግዚአብሔር ዓይን እንጂ ለእስራኤል የመጣው በረከት ርዝራዥ የደረሰን አይምሰለን::  ጌታ እየሱስ እራሱን የሰው ልጅ ብሎ ይጠራ ነበረ እነርሱ የዳዊት ልጅ ሲሉት::  ልክ ነው ከዳዊት ዘር ነው የመጣው ነገር ግን የሰውን ልጅ ሁሉ ሊታደግ መቷል::  በቅድሚያ ለአይሁድ ከዛም ለአህዛብ ሁሉ ነው ወንጌል::  የታዘዙትም በእየሩሳሌም በይሁዳ በሰማርያ ከዛም በዓለም ዙርያ ምስክሮቼ ሁኑ ነው::

አባት አለን አስቦ የወለደን ይህንንም ሲያስረዳ ዓለም ሳይፈጠር እኔና እናንተ ታስበናል::

ወደ ኤፌሶን 1

4፤ ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።

ጌታ የሰራት ቀን ይህች ናት በእርስዋ ደስ ይበለን ሃሴትም እናድርግ::  እርሱ መልካም አባት ነውና  እንገዛለት በእሽታም መንፈስ እንሞላና የተላክነውን ወንጌልን ማድረስ እንቀጥል የደከሙትን እናበርታ የተቸገሩትን  እንርዳ የታመሙትን እንጠይቅ የታሰሩትን እንጎብኝና የእግዚአብሔርን ፍቅር በዚህ ሁሉ ውስጥ እናሳይ::

ተባረኩ!

የሐዋርያት ሥራ 14

3፤ ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ።

ለጸጋው ቃል እየመሰከረ በምልክትና በድንቅ እያጀበ በጎነቱን የሚያሳይ ጌታ ዛሬም ይሰራል አልተለወጠም::  በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስና በርናባስ ለረጅም ወራት የቆዩት አልጋ በአልጋ ሆኖ አልነበረም አገልግሎት ፈተናን አስነስተውባቸው ነበር ነገር ግን የጌታ መገኘትና ማጀቡ በዛላቸውና ነው::  

የዛን ዘመን ውጊያ ከአሁኑ ጋር ሲተያይ ይለያያል::  ሊገድለን የሚነሳ የለም አሁን ግን በይሉኝታ ተብትቦ እንዲሁም በስራና በጉዳያችን ላይ እንድናተኩር በማድረግ ተቀይሯል::  ይህንን የሰላ የጠላት ውጊያ ጌታ ይስበረው ከላያችንና ወንጌልን መስበክ የጠፉትን መፈለግ ይሁንልን::

አብዛኛዎቻችን ድንቅና ተአምራት በእኛም እንዲሰራ እንፈልጋለን::  መፈለግ ጥሩ ነው የሚመጣው ግን በጣብያው ላይ ነው የሚገለጠ::  እርሱ የጸጋውን ቃል ሊያጸና ይመጣልና አምነን እንሰማራ:: 

ተባረኩ!

የማቴዎስ ወንጌል 24

36፤ ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። 37፤ የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና።

የመጨረሻው ዘመን ላይ ስለመሆናችን መቼም የሚጠራጠር የለም::  የሚገርመው የመጨረሻው መጨረሻ ላይ ነን::  ይህ የምንሰማው የአንድ አይነት ጾታ ጋብቻም ሆነ በየቦታው የእወቁልን ልፈፋቸው እየጨመረ የሚመጣ ነው ቃሉ እንደሚለው::  የኖኅ ዘመን እንደዛ ነበረና ሰው አምላኩን የረሳበት መብላት መጠጣትና መጋባት ነበረ ስራው::  እግዚአብሔርየሚያመልክና ፊቱን የሚፈልግ አልነበረም::  

ኖኅ ግን በእምነት መርከብን ሰራ መሳቅያ መላገጫ ነበረ ሲሰራው ነገር ግን መርከቡ ከተዘጋ በኃላ ጎርፉም ሲመጣ ልክ ማን እንደነበረ ታየ::  ዛሬም በህይወታችንና በአቅዋማችን የሚሳለቁ ይኖራሉ እኛ ግን ከሞት የተነሳውን ጌታ በህይወታችን ሾመን በመርከቡ ላይ ተሳፍረናል::  እኛ የእኛ አይደለንም የእርሱ ነን:: እንበርታ መምጣቱንም ወንጌልን በመስበክ እናስቸኩል!

ስለዚህ ጻድቁ ጽድቁን ማድረጉን ይቀጥል ኃጥአንም ኅጥያትን:: 

ማራናታ!  ጌታየሱስ ቶሎ ና!!

የሐዋርያት ሥራ 14

19፤ አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ፤ ሕዝቡንም አባብለው ጳውሎስን ወገሩ የሞተም መስሎአቸው ከከተማ ወደ ውጭ ጐተቱት። 20፤ ደቀ መዛሙርት ግን ከበውት ሳሉ፥ ተነስቶ ወደ ከተማ ገባ። በነገውም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ወጣ።

እነዚሁ ሰዎች አማልክት በመካከላችን ናቸው ብለው ለጳውሎስና ለበርናባስ መስዋት እንሰዋ እንዳላሉ ወድያው ደግሞ እስከሞት ድረስ ይወገር ዘንድ ፈቀዱ ወይም ተባበሩ::  ጌታንም ኦሳእና ሲሉት ውለው በስንተኛው ቀን አስወግደው ስቀለው ብለዋል::  ዓለም በክፉ የተሞላ ነው::  ደብዳቢዎቹ ሞቷል ብለው ረክተው እንደሄዱ ብድግ ብሎ ወደ ከተማ ገባ ይላል መንቀሳቅስ እንኳን መቻሉ የሚገርም ነው እርሱ ግን በማግስቱ ረጅም መንገድ ሄደ ወደሚቀጥለው ከተማ ጌታውን ለማስተዋወቅ:: 

አንዳንዶቻችን ግን ይህንን ተናገሩን በክፉ አዩን ብለን የጌታን ስራ ትተን እንቀመጣለን እስኪ ጳውሎስ ያንን ቢያደርግ አስቡት?  ከዚህስ በላይ ይቅርብኝ ቢል?  እርሱ ግን በተአምራት ተፈውሶ ምናልባትም ከሞት አስነስቶት ነው አገልግሎቱን የቀጠለው::  

ምን ላይ ነን?  እራሳችንን እንይ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንኑር :: ከፍቅርም በቀር ሌላ እዳ እንዳይኖርብን የተነገረን ነን::  ጌታ ይመጣል ለእያንዳንዱም እንደስራው ይከፍለዋል::

ተባረኩ!

የሐዋርያት ሥራ 15

8፤ ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ 9፤ ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም።

እግዚአብሔር በእኛና በእስራኤላውያን መካከል አለየም ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን እርቀንም ለነበርነው ሰላምን ሰበከን ይላል ቃሉ::  ከመጀመርያም እቅዱ የሰውን ልጅ ወደ ክብሩ መመለስ ነበረና::  አንድ ነገር ማስታወስ ያለብን ቢኖር ጠላት ሁልጊዜ ማንነትን ነው ጥያቄ ውስጥ የሚከተው::  ለሄዋን ያላት ሞትን አትሞቱም እንደ እግዚአብሔር መሆን ነው የሚቀርባችሁ ብሎ እግዚአብሔርን እንድትጠራጠር አደረጋት ከዛ በኃላ እርስዋን መጣል ቀላል ነበር::  የሆነው ምንድነው?

የተደረገልንን እንይ:-

1. መንፈስ ቅዱስንም በመስጠት መሰከረ – ማደርያው

2. ልባችንን በእምነት አነጻው – ቀደሰን

እንዴት ደስ ይላል!!  ልባችንን ስናምነው አነጻውና የራሱ ማደርያ አደረገው መንፈሱን በልባችን አፈሰሰው!!!!  ልብን የሚያውቅ ጌታ ቆሻሻውን፤ የከረፋውን፤ ክፉ አሳብ ማብቀያውን ከስሩ ነቅሎ አውጥቶ ጠራርጎ አሳመረውና ቀደሰውና በመንፈሱ ሞላን::  ልባችን የህይወት መውጫ ነው::  ከልባችን ጉዳይ አለውና ልባችንን ይፈልገዋል::  እኛ የራሳችን አይደለንም የእርሱ ነኝ በዋጋ ተገዝተናልና የሙሴ ህግ ቀንበር ነበርና አላስፈለገንም በእኛ ላይ አልተጫነም::  መዳናችን የከበረ ነው!!

ተመስገን ጌታዬ!!!

አሜን

የሐዋርያት ሥራ 15

24፤ ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው፦ ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል፡ ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን፥

28-29፤ ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።

በአንድ እግር የእግዚአብሔር መንጋ እንዲያነክስ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ሕግንና ጸጋን ማቀላቀል ነው::  ሕግ ለእኛ አልተሰጠም ለእስራኤሎች እንጂ እርሱም ደግሞ እንዲፈጽሙት አይደለም እንደማይችሉትማ  ያውቃል ግን የቅድስናውን ልክ ለማሳየት ነበረ የተሰጠው ሁሉ ሐጥያትን አድርገዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል እንደሚለው ነው::

ዛሬ አናንክስ የእግዚአብሔር ጸጋ ክርስቶስን ለመምሰል እንድንችል በጣም በቂ ነው ያልተጫነብንን እየጫንን ክርስትና ከባድ ነው አንበል::  ለውጣችን በመንፈስ ቅዱስ ስለሚሰራ መንገር እስከማንችል ድረስ ይሆናል ግን አስር ጊዜ የተዘራውን ቃል ቆፍረን እያወጣል እንዳይበቅልና እንዳይለውጠን አናድርግ::  አሰራሩን እንመን::  በቃሉና በጸሎት በፊቱ እንገኝ ለውጥ የማይቀር ይሆናል::  የመንፈስ ፍሬ በህይወታችን ይታያል አለበለዚያ ማስመሰል ይሆንና ፍሬ ፈልጎ ሲመጣ ቅጠል ብቻ ሆነን እንገኛለን:: 

አድርጉ የተባልነው:

ለጣዖት ከተሠዋ፥  አጋንንትን እያመለኩ እያየን በመካከላቸው ተገኝተን ተካፋይ አለመሆን

ከደምም፥ ከታነቀም፥  ራቁ ነው  ምክንያቱም እንስሳ ሲታረድ ደሙ መፍሰስ እንጂ ለአገልግሎት መዋል የለበትም በደም ውስጥ ህይወት አለና  ደሙም ያልፈሰሰውን የታነቀን እንሰሳ ለምግብ አለመጠቀም ነው:: 

ዝሙት ይሸሻል እንጂ አውጣኝ ተብሎ እዛው መቀመጥ አይደለም::

እነዚህን ከውጪ መቆጣጠር የምንችላቸውን እናስወግድና በጸጋው ላይ እንኑር::

ክርስትና ቀላል ነው በእርሱ እጅ ቁጭ ብሎ መሰራት ነው::  ምክንያቱም ተፈጸመ ብሏል::

ተባረኩ

የሐዋርያት ሥራ 15

36፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን፦ ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፥ እንዴት እንዳሉም እንወቅ፡ አለው።

የሐዋርያት ሥራ 15

41፤ አብያተ ክርስትያናትንም እያጸና በሶርያና በኪልቅያ ይዞር ነበር።

ጳውሎስ በልቡ የሚከብድበትንይ ቅድሚያ የሚሰጠው ስለአብያተ ክርስትያን ነው::  እዚህ ክፍል ላይ እንደምናየው ያለ እረፍት ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው እየሄደ እያገለገለ እያለ እንደገና  መጎብኘትን ፈለገ::  ለማጽናት ያሉበትን ለማወቅ የጎደሉበትም ነገር ካለ  ለመሙላትና ለማስተማር ለማጽናትም ነው::   እኛም ማንንም ሳንጠብቅ የደከሙትን ማበረታታት የበረቱትን ቀጥሉበት በማለት የጌታ ዓይን ባለበት የእኛምዓይኖች ሊሆኑ ይገባል::  ይህ ለሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሚተው አይደለም እንደዛማ ከሆነ እኛ የግማሽ ጊዜ አገልጋይ ልንባል ነው እየሱስ ግን ሙሉ ህይወቱን ሰቶን ከሞት ታድጎን ልጁ አድርጎናልና ሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንደሆንን እንወቅ:: ሁሉ ካህን ነው የካህናት መንግስት ነው የመሰረተው ለአባቱ ካህናት እንድንሆን አበቃን::  ወደኃላ የለም ባለን ጊዜ ገንዘብ እውቀትና ጸጋ በነጻየተሰጠንን በነጻ እንሰጣለን::  ዓይናችን ወንድምና እህቶቻችን ላይ ይሁን ::  እኔ ብቻ ልደግ አንበል::  እስኪ ዛሬ አንድን የምታውቁትን ሰው ወደ ልባችሁ እንዲያመጣ ጸልዩና ሲያመጣላችሁ ደውላችሁ ወይም በአካልም ከተገናኛችሁ እሰየው ጸልዩለትና ጌታ እንደሚወዳቸው ተናገሩና አሳውቁኝ::  የጌታን ፈቃድና ድምጽ መለማመድ እንጀምር::  እርሱ አሁንም ማን ይላክልናል እያለ ነስ ሁሉ ወደገዛ መንገዱ እየሄደ ስለሆነ እኛ እስኪ ቆም ብለን እኔን ላከኝ እንበለው::  እርሱ ሁሌ ይናገራልና እንስማው::

ተባረኩ!!

የሐዋርያት ሥራ 16

6፤ በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤

የሐዋርያት ሥራ 16

9፤ ራእይም ለጳውሎስ በሌሊት ታየው፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው፦ ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን፡ እያለ ቆሞ ሲለምነው ነበር።

መንፈስ ቅዱስ ወዴት መሄድ እንዳለብን በግልጽ የሚናገር ጌታ ነው::  ወደ እስያ ከልክሎ ወደ መቄዶንያ ላካቸው::  እስያ ወንጌል አያስፈልግም እያለ አይደለም ግን ጊዜው አይደለም ወይም የተሻለ እሳብ ስላለው ብቻ ነው::  

እኛም ዛሬ ያልተላክንበት ሄደን ጊዜያችንን ብቻ ሳይሆን የእርሱንም ጊዜ እንዳናባክን እግዚአብሔር ይርዳን::  እግዚአብሔር ወደሚመራን እንሂድ እንጂ ደስ ወዳለን መሆን የለበትም::  የጌታ ዓይኖች ወዴት ነው እያዩ ያሉት?  የእኛም ያንን ማየትና መታዘዝ ይሁንልን:: እርዳታችንን የሚፈልግ ማን ይርዳኝ ፤ ወዴት ልድረስ፤  የሚል አለና እንንቃ በጌታ ቤት ያለ ስራ እንድንቀመጥ ፈቃዱ አይደለም::  በሚሰጠን ጸጋ እናገልግል አለበለዚያ ጸጋ ምን ያደርግልናል?! 

አባት ሆይ በፊትህ ነኝና እኔን ላከኝ ለኔም ለእናንተም ጸሎቴ ነው:: ጌታ ይርዳን!

የሐዋርያት ሥራ 16

14፤ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።

ሊድያ እዚህ ክፍል ላይ እንደሚናገረው እግዚአብሔርን የምታመልክ ናት ግን ክርስቶስን አላወቀችም ነበረ::  ብዙዎች ዛሬ ለእግዚአብሔር የሚቀኑ እናመልካለን የሚሉ ክርስቶስን በግል የማያውቁ አሉ::  እግዚአብሔር ግን ልባቸውን ለምንናገረው ቃል ካልከፈተ ማስተዋል አይችሉምና ጸሎታችን ውስጥ ማስገባት አለብን::  ልባቸውን ክፈት ብለን ላልዳኑት ቤተሰቦቻችን ብንፀልይ ሌላ የመከሩ ሰራተኛ ሊመሰክርላቸው ይችላልና እንፀልይ::  የጻድቅ ሰው ፀሎት በስራዋ እጅግ ኃይልን ታደርጋለች:: እንደፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናልና::

የሐዋርያት ሥራ 16

17፤ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው፡ ብላ ትጮኽ ነበር።  18፤ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ፡ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።

አሜን ዛሮም በስሙ አጋንንት ይወጣል::  አጋንንትን አውጡ ተብለን የተሾምን ነን::  እንዳዘዘው በዚያው ሰዓት ወጣ!!!  ስሙ ይባረክ ይህ የተቀባ ስም ለእኛ ተሰቶናል::

ይህች የሟርተኝነት መንፈስ ያለባት ሴት ምን አጠፋች?  እየተናገረች ያለችው ጥሩ ነገር ነው::  የመዳንን መንገድ የሚናገሩ የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው፡  ልክ ናት ነገር ግን ከአጋንንት ምስክርነትን ጌታ አይፈልግም አብሬ የምሰራ ነኝ እያለ እያስመሰለ ወደጸሎት ሲሄዱ ብዙ ቀን አወካቸው::  ማንነቱ ገብቶት ነበረና ጳውሎስ ግን ይህንን መንፈስ አስወጣው::  

መንፈሳችን የነቃ ይሁን የእግዚአብሔርን መንፈስና የአጋንንትን መንፈስ እንለይ::  ትክክለኛ የሚመስልን ቃል የተነበየ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለምና በዚች ሴት ውስጥ የተናገረው መንፈስ ትክክል ነበረ::  መንፈስን እንመርምር በሰዎች ላይም ያለውን የህይወት ፍሬ እያየን ህብረት እናድርግ::  

ከእንደዚህ አይነት ከረቀቀ የጠላት አሰራር ጌታ እኛንም ቤተክርስቲያንንም እንዲታደግ እና እንዲያነቃ እንጸልይ::

የሐዋርያት ሥራ 16

24፤ እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው። 25፤ በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር።  26፤ ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ።

በምሪት ተመርቶ መቶ መደብደብና ወደ ወህኒ መጣልን ምን ይሉታል?!  ቀጥታ ወደ ጥርጣሬ የሚከት ነገር ነው ቅዥት ነበር ማለት ነው?  አያስብልም? ስንት ጊዜ ጠላት እንደዚህ እያለ ጊዜያችንን በልቶብን ይሆን?  አልጋ በአልጋ ነው አልተባልንም መንገዱ ጌታን ስንከተል የተሰጠን ማረጋገጫ አሸንፌአለሁ አይዟችሁ ነው!!  ጌታ ድል ነስቷል::

ልብሳቸውን ገፈው እንዲደበድቧቸው ገዢዎቹ አዘዙ::  ይህንም አደረጉ እናም ወደ ውስጠኛው እስር ቤት ጥለው እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው ይላል ቃሉ::  መቼም ከዚህ በኃላ መሆን የነበረበት እንዴት እዚህ ደረስን? ብሎ ነገሩን ሁሉ ማብላላት ነበር አይደል?!  እነርሱ ግን አምልኮን ጀመሩ::  ስለተደበደብኩኝና ስለቆሰልኩ አምልኮን አልቀንስም አሉ::  እስረኞቹ ሁሉ እየሰሙ አምልኮን ቀጠሉ ምን ይሉናልም አላሉ ::  እስረኞቹ መቼም እዚህ እንዲታሰሩ ያደረጋቸውን እንዴት ይቀጥላሉሳይሉ አይቀርም ቅጣት እኮ እንድንተው ለማስገደድ አይደልእነሱ ግን አብዝተው ቀጠሉ::   የላካቸውን እንዲሁም እየተዋጋቸው ያለውን ጠንቅቀው ያውቁ ነበርና::  አሳሪ ባለስልጣን ነኝ ባይ አስሮ ሲሄድ ጌታ ደግሞ  ፈታ ብላችሁ አምልኩ ብሎ የነሱን ብቻ ሳይሆን እስር ቤቱንም ክፍት አደረገው የኔ ጌታ ሰንሰለቶች ሁሉ ወደቁ::  አምልኮውን የሰሙ ታሳሪዎች ውጤቱንም አዩ:: ሰንሰለቶች ስራቸውን አቆሙ እነዚህን የእግዚአብሔርን ልጆች አናስርም ብለው አመጹ::  ሃሌሉያ!

በምናልፍበት ነገር ያንኑ ነገር አንስተን ብንዘበዝብ መፍትሄ የለውም ሁሉን ወደሚችል ጌታ ዓይናችንን እናንሳና እናምልከው::  እርሱ እጁን ልኮ ካለንበት ጎትቶ ያወጣናልና!!! አሜን!

ስሙ ይባረክ!

የሐዋርያት ሥራ 16: 27-32

27፤ የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። 28፤ ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፦ ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፡ ብሎ ጮኸ። 30፤ ወደ ውጭም አውጥቶ፦ ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? ኣላቸው። 31፤ እነርሱም፦ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፡ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ፡ አሉት።

የወህኒው ጠባቂ የነቃው በምድሩ መናወጥ ይሆናል እንጂ ዝማሬና አምልኮውን አልሰማም::  ያሰራቸው ሁሉ ተፈተው የእስር ቤቱ በር ሁሉ ተከፍቶ ሲያይ እስረኛም አልቀረ ያሰኛል::  ነገር ግን እስረኞቹ እግዚአብሔርን መፍራትና ድንጋጤ ውስጥ ነበሩና አልተነቃነቁም::  ወደዚህ ናና እርዳን ያለው ሰው ይህ ሰው ይሆንን? በዚህ ሰው ጥሪ መተው ከስራቸው ጠላት ሊያጠፋው ነበረ እግዚአብሔር ግን  ጳውሎስን ተጠቅሞ እራስህን አታጥፋ አለው::  ምን ላድርግ እንድድን?  የሚገርም ጥያቄና ጌታም የሚፈልገው ይህንን ነበረ:: መልሱም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፡ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ፡ አሉት።  ሰዎች አምነው ይድኑ ዘንድ እኛን ልኳል ጌታ በምንሰራበትም ይሁን በምንውልበት ለጌታ ምስክሮች እንሁን::  ይህ ሰው አሳሪ ይመስላል የታሰረው መፈታት ያለበት ግን እርሱ ነበረና እርሱንና ቤተሰቡን ጌታ አሰበ:: የፊልጵስዮስ ቤተክርስቲያን አባላት መካከል ሊድያ እና ይህ የእስር ቤት ጠባቂ ከነቤተሠቡ ይገኙበታል::  ሲጽፍላቸውም በመልእክቱ እንዴት እንዳልተጠየፉት ይናገራል ምክንያቱም ተደብድቦ ሞተ ብለው ጥለውት ከነበረበት ከተማ ነበር  በማግስቱ ወደዝች እንደገና ደብድባ  ከነቁስሉ በድንጨት ተጠርቆ የታሰረበት ከተማ የመጣው:: ይገርማል!  እኛ ምን ሆንን? እንደዚህ ነበር ወንጌል እኛጋ የደረሰው ዛሬ ግን ግፋ ቢል ግልምጫን ፈርተን ምን ይሉን እያልን ወንጌልን ከመናገር ተቆጥበናል::  ሰዎች በእስራት ላይ ናቸውና መፍትዎችም እኛ ነንና እንነሳና ጌታን ለፍጥረት ሁሉ እንስበክ::

ምስክሮች እንሆን ዘንድ ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!  እርሱ ቅርብ ነውና አብሮን ይሰራል::

የሐዋርያት ሥራ 16: 32-40

32፤ ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው።

33፤ በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤

በዛችው ለሊት መዳን ከነመላ ው ቤተሰብ ሆነለት ደግሞም ተጠመቁ::  በነጋታው ልቀቁዋቸው የሚለው ትዕዛዝ ሲመጣ ጳውሎስና ሲላስ ስራቸውን ጨርሰዋል::  የሚባክን ጊዜ የለም !  እኛስጋ ?  እግዚአብሔር ይርዳንና የጌታን ሰዓት እንዳናባክን በእርሱ በሚሰራው ታምነን እንሰማራ:;  ዛሬ ሌላውን እናስብ ከራሳችን እንውጣ የእኛን ጌታ ይሰራዋል በዝች ምድር ላይ መጻተኞች እንደሆንን ቃሉ ይነግረናልና::  ጠላት ሁልጊዜ ስለራሳችን ሊያሳየን ነው የሚፈልግው ንስር ሆነን በነፃነት ልንኖር ሲገባን ጥሬ ለቃሚ ዶሮ አድርጎናል::  ፈጽሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው በመንፈስ ቅዱስ እንድንመራና ክንፎቻችንን ዘርግተን ንፋሱ ወደሚወስደን ልንበር የተጠራን ነን::

አባት ሆይ ኃይልን ስጠንና ምስክሮችህ እንሁን! አሜን

የሐዋርያት ሥራ 17

10፤ ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ ፤

11፤ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።

የጳውሎስ አገልግሎት ፍሬ እያፈራ ጢሞትዮስን የመሰለ ረዳት እግዚአብሔር ሰቶት ፊሊጲስዮስ ፤ ተሰሎንቄ ፤እና ቤሪያ የሚገኙት አብያተ ክርስትያናት ተመስርተዋል ምንም እንኳን ከሁሉ ቦታ እያባረሩት ቢሆንም መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርትያናትን አጽንቷቸዋል::

የቤሪያ ቅዱሳን ግን የሚገርሙት እንደዚህ ይሆንን ቃሉ ብለው መረመሩ::  ጌታ እየሱስ እንደተናገረው መጽሐፍት ሁሉ ስለእኔ ይናገራሉ እንዳለው ከቃሉ እውነትነቱን አመሳከሩ እንጂ በስሜት ወደ መነዳትና መልክቱን ያመጡትን ወደ መጉዳት አልሄዱም:: ልባቸው ለወንጌል የተዘጋጀውን ወደእኛ ያምጣ::  እንደሊድያና እንደ ቤሪያ ሰዎች:: 

ብዙ አይነት ሰው ሊገጥመን ስለሚችል ስንመሰክር እንታገስ አንዲት ጠጠር አስቀጠን ሊሆን ይችላል በአንድ ሰው ህይወት ውስጥ የምንሄደው ሌላው መቶ ደግሞ ሌላውን ይሰራል::  ተስፋ አንቁረጥ በእግዚአብሔር ፊት እንጸልይ ነፍሳትን እንዲሰጠንና እንዲያወርሰን::  ክርስትና ቤተክርስቲያን ስንመጣ ብቻ የምንኖረው ሳይሆን በስራ ስፍራም እቤትም የትም የምንገኝበት ቦታ ሁሉ ላይ መሆን አለበት::  ጌታን እናብለጭልጨው የስራ ስፍራችን የተሰማራንበት  መስካችን ይሁን ጌታን ለማሳየት:: 

ጸጋው እንደሚረዳን አምናለሁኝ እንታዘዝ እርሱ ያስደንቀናል::

ተባረኩ!

የሐዋርያት ሥራ 17

16፤ ጳውሎስም በአቴና ሲጠብቃቸው ሳለ፥ በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት።

አንድ ጥያቄ እራሴን ጠየኩኝ አሁን ጳውሎስን ያበሳጨው ያበሳጨኛል?  ወይስ ተለማመድኩት? ምንም አይደለምወይም ምን ቸገረኝ ይሆን::  እርሱ ግን ጣዖትን ሲያይ ተበሳጨበት መንፈሱ::  አዲስ አበባ እንብርቷ ላይ እሬቻ ሲመለክ አንዳንዱ የሰላም አምላክ ነው ሌላው የምስጋና በዓል ነው እያለ ያሽሞነሙነዋል::  ይሄ ጣዖት ነውና ሊያበሳጨን ልንቃወመው ይገባል እንጂ ስናልፍ ቡናቸውን እንኳን መጠጣት የለብንም::  ሐዋርያት የተውልን አንዱ መመሪያ ለአህዛብ ለጣዖት የተሰዋ አትንኩ ነው:: እግዚአብሔር ከምድራችን ላይ ይስበረው::  በእየሱስ ስም ተመልሶ በዛች ምድር አይመለክ!  እርሱን ማምለክ ከጀመሩ ጀምሮ ምድሪቱ በደምና በረሀብ እየታመሰች ነውና አጥብቀን ጠልተነው ልንቃወም ይገባል ይህ አራጅ መንፈስ ነው እየተመለከ ያለው::  

እኛ እርኩስን አንነካም ለእግዚአብሔር እራሳችንን እንቀድሳለን የምናውቀውንም ወገን ሁሉ በዚህ ሀሳብ እናንቃ ሌላ ረዳት አምላክ የለም አምላካችንስ አንድ አምላክ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ በውስጥዋም ያሉትን ሁሉ ያለ ረዳት የፈጠረ ነውና ስሙ ይባረክ!

የሐዋርያት ሥራ 17

24፤ ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ 25፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።

30፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤

ጳውሎስ የጀመረው ስብከቱን ከዛው በዙሪያው ካለው ነገር ወይም ሁኔታ ተነስቶ ነው::  ለማይታወቅ አምላክ ብላችሁ የምታመልኩት ላሳውቃችሁ በሚል ነው የጀመረው ጥበብን ለመስበክ መንፈስ ቅዱስ ይሰጠናልና በእርሱ ላይ እንደገፍ::  ይህ ያላወቁት አምላክ ግን ሁሉን የፈጠረ  ህይወትን የሚሰጥ ነው::  ሌሎች አማልክት ግን በሰው የሚገለገሉ ሰው የሚሸከማቸው ናቸው::  የእኛ አምላክ ግን አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።  ሰውም በሰራው ህንፃ አይኖርም በእኛ ውስጥ እንጂ::  

የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰው ሁሉ ወደ ንስሃ እንዲመጣ ነው::  ጌታም ሲመጣ የሰበከው እኛም የተባልነው  የእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ ነውና ተልዕኮአችንን እንፈጽም::  ጌታ ይመጣል አይዘገይም በዚች ምድር ሊፈርድ ይመጣል:: ሁሉም እንዲድኑ ነው ፈቃዱ በዚህም የእግዚአብሔር መንፈስ ረዳታችን ነው::  የሰዎች መጥፋት ግድ ይበለንና ለመድረስ እንሂድ::

ተባረኩ!

የሐዋርያት ሥራ 18

1፤ ከዚህም በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ።

9-10፤ ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን፦ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና፡ አለው።

እዚህ ክፍል ላይ የምናየው የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ስትመሰረት ነው::  በዚች ከተማ ብዙ ህዝብ አለኝ ማንም አይነካህም ስራ አለው ጌታ ስለዚህም ጳውሎስ ለ18 ወራት አገለገላቸው::  አይሁድም አንሰማም ስላሉት የልብሱን ትብያ አራግፎ ደማችሁ በእናንተ ላይ ነው ብሎ ወደ አህዛብ ፊቱን አዞረ:: 

በዚሁ ስፍራ ነበረ ድንኳን ሰፊዎች እንደእርሱ የሆኑትን አቂላና ጵርስቅላን  ያገኘው እነርሱም ጌታን ለማገልገል እራሳቸውን የሚሰጡ ባልና ሚስት ናቸው::

እግዚአብሔር ሰዎችን በህይወታችን ላይ ያመጣል  ይሰጠንማል::  እነዚህ ባልና ሚስቶች አብረውት መጏዝን ጀመሩ::  በዙሪያችን ስለሰጠን ሰዎች ጌታን እናመስግን::  ሰው ትልቅ ስጦታ ነውና መንግስቱን አብረን እንወርሳለን በዚህም በምድር  ጌታን በሰጠን ጸጋ እናገለግላለን::   ጌታ ከእኛ ጋር ነው እንበርታ::  በተሰጠንም መክሊት እናገልግልና እናትርፍ::

ተባረኩ!

የሐዋርያት ሥራ 17

31፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።

መቼም ለዓለም ይህ እውነት የማይገባ ነው::  እነዚህ ፈላስፎች በዝች ትንሽዬ ጭንቅላታቸው ቢያወጡ ቢያወርዱ የትኛውንም ቀመር ቢቀምሩ የማይደርሱበት እውነት ቢኖር ትንሳኤ ነው::  የሙታን ትንሳኤ እንዳለ ሲነግራቸው ግማሹ አሹፎ ሄደ::  የሰው ልጅ ክቡር መሆኑን እንኳን አላወቁም:: 

እኛ ግን ትንሳኤን የምንጠባበቅ ነን::  ከክርስቶስ ጋር የሞትና በትንሳኤውም አብረን የተነሳን  ነን::  ድሉ ተጠናቋል!!  ትንሳኤ ሆነልን!!!

በዚህ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ቆመን ዘመናችንን ለዚህ ሊፈርድ ለሚመጣው ጌታ እንዋጅለትና  እርሱ እንደወደደ  በእኛ ይስራ!  ክብሩንም ይግለጥ!  እኛ የምናመልከው ህያው ጌታ ነውና የሚሰማ የሚመልስ የሚናገር ነው::  ስሙ ይባረክ እንኳንም የራሱ አደደገን::

በእኛ ውስጥ ስላስቀመጠው ማንነቱና ስለሰጠን ድል ጌታን እናመስግን::  አሮጌው ማንነት አልፏል ሁሉ አዲስ ሆንዋል!!!

አሜን

መልካም አዲስ ዓመት!

የሐዋርያት ሥራ 18

12፤ ጋልዮስም በአካይያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ፥ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፥ ወደ ፍርድ ወንበርም አምጥተው፦

15፤ ስለ ቃልና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን፥ ራሳችሁ ተጠንቀቁ እኔ በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድምና፡ አላቸው።

ጳውሎስን ለመክሰስ በአንድ ልብ ሆነው ተነሱና ወደ ፍርድ ወንበር አመጡት::  ጋልዮስ ግን ነገሩን አፈረሰባቸው::  ጠላት ጳውሎስን ለማዘግየትም ይሁን ለመበቀል እነዚህን ሰዎች አስነስቶ ነበር ነገር ግን አምላኩ እግዚአብሔር ፍርድ እንዲሰጥ ብቻ ሳይሆን ነገሩንም ዋጋ ማሳጣት ይችላልና ብቻ እኛ በጌታ ላይ ይሁን ዓይናችን::  እርሱ የሚሰራውን ያውቃልና ውጊያው የእግዚአብሔር ነው::  ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ሲከሱት እንዴት ዋጋ ያጣል ከሰማይ ካልሆነ በቀር?

ዛሬም የጠላትየሰላው ምክርና ክስ አይሰራም የወንድሞች ከሳሽተጣለ እንደሚል ቃሉ አሁንም በእኛ ላይ አይሰምርለትም::  ስለእኛ የሚማልድ አለ በሰማይ!

ስሙ ይባረክ!

የሐዋርያት ሥራ 18

22፤ ወደ ቂሣርያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ።.  23፤ ጥቂት ቀንም ቆይቶ ወጣ፥ ደቀ መዛሙርትንም ሁሉ እያጸና በገላትያ አገርና በፍርግያ በተራ አለፈ።

ጳውሎስ ቅዱሳንን እያጸና ያልፋል ምክንያቱም አንዳች የጏደለ ካለ ለመሙላት ይላል በሌላ ስፍራ::  እንዲሁም የማውቀውን  ሁሉ አሳወኳችሁ ተጋሁ ይላል::  ትጋቱ የሚገርም ነው::  እግዚአብሔር ለእኛም ይህንን ትጋት ይስጠን! 

ቅዱሳንን ማየትና አንዱም የአንዱን ሸክም መሸከምን ያብዛልን

የሐዋርያት ሥራ 18

24፤ በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።

26፤ እርሱም በምኵራብ ገልጦ ይናገር ጀመር። ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፥ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።  27፤ እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈቀደ ጊዜ፥ ወንድሞቹ አጸናኑት፥ ይቀበሉትም ዘንድ ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤

ጳውሎስ ጵርስቅላና አቂላን ደቀመዝሙር አደረገ እነርሱ ደግሞ አጵሎስን አገለገሉ::  የተጠራነው ደቀመዝሙርትን እንድናፈራ ነው::  ይህ ሰው በጸጋ እጅግ  ጠቀማቸው እንደሚል በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለው ጸጋ የክርስቶስን አካል ለማገልገል አስፈላጊ ነው::  ጸጋ አልተሰጠኝም የሚል የለምና ለሁላችንም አከፋፍሏል:: የኤፌሶን ቅዱሳን በደንብ የተገለገሉና የተለወጡ ናቸው::  የኤፌሶንንም መልክት ስናየው ጥልቀት ያለው መንፈሳዊ መልእክት  ነው::  ሰው በክርስቶድ ስር መስደድ አለበት የሆነልንን ስናውቅ የጊዜውን እንንቀዋለን::  ስለዚህ ስር እንስደድ  ቃሉን መስማትና መታዘዝ ቃሉንም ማመንዥግ ይብዛልን::

የጸሎት ርእስ:  በሰጠን ጸጋ እንድናገለግል

እንዲሁም ስር ሰደን እንድናድግ የቃሉንም ደጅ እንዲከፍትልን::

የሐዋርያት ሥራ 19

1፤ አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ።

2፤ ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም፦ አልተቀበልንም፡ መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም፡ አሉት።

6፤ ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ።

ያለ መንፈስ ቅዱስ ክርስትና ከባድ ነው::  ዮሐንስም ያለው እኔ በውሃ አጠምቃችኃለሁ ከኔ በኃላ የሚመጣው ግን በእሳት ያጠምቃችኃል::  እነዚህ ሰዎች የዳኑ ናቸው ለዚህ ነው  አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ የሚለው ቃሉ ነገር ግን ስለ መንፈስ ቅዱስ አያውቁም ነበር ምናልባትም አጵሎስ ያገለገላቸው  ሊሆኑ ይችላሉ::  በፊተኛው ምዕራፍ እንዳለው አጵሎስ (18: 25፤ እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር።)

መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን ባመን ስጋ ለባሽ  ሁሉ ላይ ይወርዳል የሚመጣው ሊሰራን ሊያበጃጀንና ለመንግስቱ ስራ ሊሾመን ነው::  ጌታ እየሱስም እኔ ብሄድ ይሻላል  ደግሞም እርስር በመጣ ጊዜ ያከብረኛል ብሎ ነግሮናል:: ዕለት ዕለት በመንፈስ ተሞሉ ተብለናልና እንጸልይ ለሙላቱ!

የሐዋርያት ሥራ 19: 11-20

20፤ እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።

ይህ ቃል የመጣው የጳውሎስ የልብስ ቁራጭ ከፈወሰና አጋንንትን ስላስወጣ ነው::  የካህኑ የአስቄዋ 7 ልጆችም አጋንንት ሊያወጡ ሲሞክሩ በርትቶ እንደደበደባቸው በኤፌሶን ከተማ ሁሉ ተሰማ ስለዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ::

18. አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። 

19፤ ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ።

ይሄ ነው ማደግና ማሸነፍ::  አንድ ሰው እንኳን በዚህ ስም ማሾፍ ወይም ማቃለል አይችልም::  እነዚህ 7 ልጆች እኮ የካህን ልጆች ናቸው ካህናት ለመሆን የታጩ ነገር ግን አሮጌውን ፕሮ አዲድኪዳን ነውና በአሮጌው ማንነት አዲሱን ኪዳን መውረስና ስሙን መጠቀም አልቻሉም:: ምን ብንደክም በህይወታችን አጋንንት ቭን የማን እንደሆንን ጠንቅቆ ያውቃል::  የታደገን ጌታ ስሙ ይባረክ!

ዛሬ ለወንጌል እንውጣ ይህ የከበረ ስም ተስቶናል::  ቃሉ በኃይል ያድጋል ያሸንፍማል እኛ ብቻ ታዘን እኔን ላከኝ ርንበል ይህንን ወንጌል ሳናፍር ለፍጥረት ሁሉ እንስበክ!!!

የሐዋርያት ሥራ 19: 21-41

26፤ ይህም ጳውሎስ፦ በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም፡ ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል።

ይህንን የተናገረው እነዚህን አማልክት በመስራት ትርፍ የሚያገኘው ሰው ነው::  ግን ጳውሎስ ሰውን አሳተ እንዴ?!  እንዲያውም ወደ ህይወት መንገድ መራቸው እንጂ::  ሰው ነገሮችን ከራሱ ጋር ነው የሚያያይዘው ወንጌልን ሰብከን ተቃውሞ ቢገጥመን አንዳንዱ ለእግዚአብሔር ቀንቶ ሳይሆን በሆነ ሌላ ምክንያት ይሆናል እኛ ግን ከሞት የተነሳውን የሁሉ ራስ የሆነውን እየሱስን  እንሰብካለን::

ጳውሎስን ለማሰናከልና ካሰበበት መንገድ ጠላት እንደለመደው እስር ቤት ሊያስገባው ወይም በህይወቱ ላይ አደጋ ሊጥል ነበረ እግዚአብሔር ግን ስብስቡ ምንም በኃይል የተደራጀ ቢሆንም በተነው::  ባርያው መድረስ ያለበት ቦታ አለና::  ጠላት ምንያህል ቢጠበብ እግዚአብሔር ካሰበልን ነገር አንጏድልም እንደርሳለን ብቻ ዓይናችን በእርሱ ላይ ይተከል::

ስራችንን በጸጋው በትጋት እንስራ ማንንም አንለፍ ህይወት የማያስፈልግው የለምና!

የሐዋርያት ሥራ 20: 1-12

7፤ ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ።

9፤ አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት።

10፤ ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም፦ ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ፡ አላቸው።

12፤ ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ።

ይህ የጳውሎስ የመጨረሻ  ጉብኝ  ነውና  ያለውን  ሁሉ  እውቀት  ሳያስቀር  እየመከረ  ቤተክርስቲያንን  ሁሉ እያጸና ያለበት ጊዜ ነው::   ነገ መንገድ  አለ በፊቴ  ልተኛ  ልረፍ  አይደለም  የሚያስበው  የጌታን  ነገር  እንጂ!!  እስኪነጋ  ድረስ  አገለገለ::  

በዚህ  ምክንያት ነገሩ ሲረዝም ይህ ብላቴና ከእንቅልፍ የተነሳ ወደቀ::  ሲደርሱም ብላቴናው  ሞቶ ነው ያገኙት  ነገር ግን በላዩ ላይ  ወደቀና  ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ፡ አላቸው።  ይህን በጌታ እየሱስ አገልግሎትም አይተናል አይደል? ተኝታለች ሲላቸው  ሳቁበት ልምድ ያላቸው  ነገር ግን እናትና አባትዋን እንዲሁም ሐዋርያትን ይዞ ገባና ተነሺ ሲላት ተነሳች ብላቴናዋ::   ሌላው ደግሞ በኤልሳዕም አገልግሎት የሞተው የሱናማይቱ ልጅ  ከሞት  ተነስቷል ልክ ጳውሎስ እንዳደረገው በላዩ ላይ ወድቆ ነበረ::   ጌታ ህያው ነው! የህይወትም ምንጭ ነው::

ዛሬም ጌታ  አልተለወጠም  የእኛ ማንነት ሳይሆን የስሙ ስልጣን ይሰራል::  ሞቶ ያገኙት ብላቴና  በህይወት ኖረ!!  

ከጳውሎስ የምንማረው ነገር በጌታ ላይ ዓይናችንን  አድርገን  የመንግስቱን ስራ ጊዜ ሳለ በትጋት መወጣት ነው::  በተሰጠን ጸጋ ማገልገል  ይሁንልን::

የሐዋርያት ሥራ 20: 17-21

17፤ ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤

18-19፤ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤

20-21፤ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።

ጳውሎስ እነዚህን ሽማግሌዎች ጠርቶ እራሱንና አገልግሎቱን እየገምእገመ ነው::  ወደ ኤፌሶን መሄድ ስለማይችል ወደ እርሱ ሽማግሌዎችን ጠርቶ እያናገረ ነው::  በአገልግሎቱ አያፍርምና  በሁሉ ፊት እንዴት እንዳገለገለ ይገልጻል:: ያገለገለውም:-

1.    በትሕትና 

2.   በእንባ 

3.   ለጌታ እየተገዛሁ (ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና )

4.   ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ

5.   በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ

6.   ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።

ምን አይነት አገልግሎት ነው?!  በመጨረሻው ኤፌሶንን ጥሎ እንዲወጣ ያደረገው የአህዛብ ግፊት ቢሆንም ግን አይሁድም ያሴሩበት ነበር ነገር ግን ለጌታ ተገዛሁ ይላል::  እንደዚህ በአገልግሎት መጨረሻ አገልግሎታችንን  መመዘን እንችል ይሆን?  ወይስ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ ያለ የእኛን ህይወት እያሞቀና እያደመቀ ብቻ የሚኖር ነው ለእኛ?  ዛሬ ህይወታችንን እንመርምር ምንድነው ለጌታ የምንሰጠው?  እርሱ የሰጠን እራሱን ነው::  

ሌሎችን የሚጠቅም መንግስቱንም በሚያሰፋ አሳብና ልብ ጌታ ይሙላን::  ትህትናን ከኔ ተማሩ እንደተባልን ጳውሎስም በትህትና እንዳገለገለ እንዲሁ ማገልገል ይሁንልን::  በምድርያለነው እርሱን ለማገልገል ነው!!!

በቤትም በቤተክርስቲያንም መትጋት ይሁንልን::  ወንጌል ቋንቋችን ይሁን!

የሐዋርያት ሥራ 20: 22-27

24፤ ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።

26፤ ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ።

እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ  ነኝ?! የጳውሎስ አባባል አስደነገጠኝና እራሴን አንቺስ ብዬ ብጠይቅ  መልስ ስላጣሁ ጸለይኩኝ ይህንን ለማለት እንዲያበቃኝ ቃሉ ግን ውስጤን አናጋው:: እኔም አንድ ቀን እንደዚህ ማለት እችል ይሆን?!  

አይደንቅም ጳውሎስ ይህንን ሲል ለሊቱን ሙሉ አስተምሮና  መክሮ ሲጨርስ በዛው ሳይተኛ መንገዱን ወደሌላ አገልግሎት ያቀናል::  ተደብድቦ እያቃሰተ ያመልካል ያችም ለሊት ሳታልፍ አንድ ቤተሰብ ሙሉ ተሰብኮ ተጠምቋል::   ስንቱን ክፍል በእግሩ አዳርሶ ሰብኳን::  በየስፍራውም ሲደርስ  የሚጠብቀው ድብደባና ህይወቱን ማሳደድና ሴራ ነው::  እርሱ ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እፈጽም ዘንድ ነፍሴ በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ አለ!!!  እኔስ ብለን እንጠይቅ? የተሰጠንን አደራ እንዴት እያደረግን ነው?!  እንጠየቅበታለን የሰው አደራ እንኳን እንዴት ከባድ ነው እንኳንስ የጌታ?!

የማቴዎስ ወንጌል 10

39፤ ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል። ብሎን የለ ጌታ?  

ሀብታችንን በላይ በሰማይ እናከማች  ተኮፍሰው ወንጌልን የሚንቁትን አትፍሩ ምክንያቱም ነገ የሚጠብቃቸውን እናውቃለንና እንመስክር ቀን ሳለ የጌታን ስራ እንስራ ሁሉ በጸጋውያገልግል  ምን ለውጥ መጣለሁ አንበል  ይህ የጠላት ሽንገላ ነው  የሚሰራው ጌታ መንፈስ ቅዱስ ነው እራሳችንን እንስጠው ያስደንቀናል::  ጊዜያችንን እንዋጅ በፊቱ እንበርከክ ቃሉንም እናመንዥግ!!  እንበርታ እያንዳችን የክርስቶስ አካል ነንና የማይሰራ የሰውነት ክፍል ካሌ ሌላውን ሁሉ እንደሚያውክ የሌላውን ስራ ከመመኘት የተሰጠንን ቅልጥፍ አድርገን በታማኝነት እንስራ::

የሐዋርያት ሥራ 20: 28-38

29-30፤ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ። 

32፤ አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።

የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ለሶስት ዓመታት በጳውሎስ ተገልግላለች::  ይህ ክፍል የሚያሳየን መሪዎቹን አስጠርቶ የመጨረሻውን የስንብት ምክር እየሰጣቸው ነው::  ምንም እንኳን ይህንን ሁሉ ጊዜ ቢያገለግላቸውም ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንደሚመጡ እያስጠነቀቃቸው ነው::  ሲመጡም  ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ናቸው::  ስለዚህ ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ ይላቸዋል::  ቤቱን ጌታ ይጠብቃል ምንም እንኳን በአሁኑ ዘመን ነገሮች ውጥንቅጣቸው የወጣ ቢመስልም እርሱ ግን አለ በዙፋኑ የሚፈሩትንና  በእውነት  የሚፈልጉትን ያውቃቸዋል::  አይሸነፍም! ያለ ፊት መጨሚደድ ተዘጋጅታ  የምትጠብቀውን  ሙሽራ  ያዘጋጃል!

ጳውሎስ ሲያገለግል በማንም ላይ ሸክም አልነበረም  እንደአሁኑ ዘመን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ተብሎ ቁጭ አላለም ድንኳን እየሰፋ እርሱንና ተርፎት አብረውት ያሉትንም ያኖር ነበረ::  ስለዚህም “አትመኝ!”  እንዳለ ቃሉ ከማንም ብርና ወርቅ አልተመኘሁም ይላል::  ያለኝ ይበቃኛልን እንማር ያለንንም ከሌሎች ጋር በመከፋፈል የተቸገሩትንም በመርዳት እንመላለስ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው፡ እንዳለ፡ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ ይላል::  እንደዚህ ምሳሌ የሚሆኑንን በቤቱ ያስነሳልን እኛም ምሳሌ መሆን እንድንችል ጌታ ይርዳን::

የሐዋርያት ሥራ 21:1-16

13፤ ጳውሎስ ግን መልሶ፦ እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም፡ አለ።

ጳውሎስ ብዙ ጊዜ መልክት መቶለታል ምን እንደሚጠብቀው ወደ እየሩሳሌም ከሄደ ነገር ግን አትሂድ አልተባለም::  ነብይ አጋቦስ በመታጠቅያው ታስሮ የሚጠብቀውን አሳይቶታል የጳውሎስ መልስ ግን እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ነው ነበር ያለው::  

በመጀመሪያም  ገና ሐናንያ ሲጸልይለት የነገረው ነገር

የሐዋርያት ሥራ 9

15፤ ጌታም አለው፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ 16፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና።

ሁለቱን በሚገባ ፈጽሟል የቀረው በነገስታት ፊት ስሙን መሸከም ነው ለዚህም ሳያቅማማ እየሄደ ነው::  በሚያልፍበት መንገድ ሁሉንም እየተሰናበተ የመጣውም ደግሞ እንደማያያቸው ስለሚያውቅ ነው::  እስከ መጨረሻ መጽናትን እንማራለን ከህይወቱ::  ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ዝግጁ ነበረ::  ህይወቴ በእኔ ዘንድ አርከብርም ባይነው::  እግዚአብሔር  ያየልንን  እንይ እርሱ ይወርሰናል እርሱ በእያንዳንዳችን ላይ ዓላማ አለው ለዛ ዓላማ እንኑር::  ከጌታ የምንሰስተው ምንም የለም እኛም እራሳችን የእኛ አይደለንም የእርሱ እንጂ በዋጋ ተገዝተናል::  እግዚአብሔር ፈርተው ለክብሩ የሚቆሙ ነብያትን ያብዛልን::   እሩጫችንን በትግስት እንሩጥ!

የሐዋርያት ሥራ 21: 17-26

19፤ ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው።

21፤ ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል።

ጳውሎስ እየሩሳሌም ሲመጣ ወገኖች ተቀበሉት ከያዕቆብም ጋር ተገናኘ አገልግሎቱንም ተረከላቸው ጌታንም አመሰገኑ::  ነገር ግን በውሸት እየተከሰሰ እንደሆነ ነገሩትና መፍትሄ ያሉትንም መከሩት:: የመንጻትን ህግ እንዲፈጽምና ህጉን እየጠበቀ መሆኑን እንዲያሳይ ነበር ምክሩ::  ጳውሎስም ተስማማ::  ለምን ይሆን የተስማማው?

የጳውሎስ ትምህርት የብሉይ ህግ መጠበቅ ከጸጋ መውደቅ ነውእያለ አስተምሮ ሲያበቃ እዚህ ጋር አመቻምች ነው የሚሉት?  አይደለም እርሱ ሁልጊዜ የሚናገርበትን መንገድ ለማግኘት ነው ጥረቱ ብዬ ነውየማስበው እንጂ የዚህ የመንጻት ስርአት ምንም እንደማያደርገት ስርአት ብቻ እንደሆነ ጠንቅቆ  ያውቃል::  ስለትን መሳል አያስፈልገንም በጌታ ፊት እንድንሰማ እርሱ እራሱ እንደሚሰማን ነግሮናልና::  ከህግ በላይ ከጸጋ በታች ነንና አለበለዚያ ከክርስቶስ ጸጋ ወድቀናል::  ቅድስና የክርስትና ስር መሰረቱ ሳይሆን ፍሬው ነው::  እርሱን እየመሰልን በመለወጥ በቃሉና በመንፈሱ የሚመጡ እንጂ በውጭ በምናደርገው ስርአት የሚመጣ አይደለም::  ጌታ እንዳናመቻምች ይርዳን!  በጌታና በቃሉ እንዳናፍር በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቆራጥ ወታደር እንሁን!

የሐዋርያት ሥራ 21: 27-40

30፤ ከተማውም ሁሉ ታወከ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፥ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ::

31፤ ሊገድሉትም ሲፈልጉ፦ ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች፡ የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤

32፤ እርሱም ያን ጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወረደባቸው፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ።

ጳውሎስ ህጉን እንደሚጠብቅ ሰው ወደቤተ መቅደስ ቢሆንም አልሰራም::  በእስያ የሚያውቁት ሰዎች እንዲያዝና እንዲደበደብ አደረጉ ሻለቃው መቶ እስኪያስቆም ድረስ::  እግዚአብሔር ከሞት አዳነው ምክንይቱም ስራውን አልጨረሰም ነበር እሱም በነገስታት ፊት መቆም::  ለነገስታቱም ወንጌል ያስፈልጋልና::  ሻለቃው ባይደርስ ኖሮ ህዝቡ በጣም ተናደው ነበረና ምናልባትም ለእግዚአብሔር የቀኑ መስሏቸዋልና ይገድሉት ነበር::  ማዳን የአምላካችን ነው::  የተጠራልነትን ስራ እስክንጨርስ ጌታ ይጠብቀናል እራሳችንን ዝቅ አድርገን አንይ የእግዚአብሔርን አጀንዳ የተሸከምን በእርሱም ጸጋ የምንፈጽም ነን::

ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወንጌልን ማገልገል የሚፈልገው ጳውሎስ ሻለቃውን አስፈቀደ ለመናገር::  ይህ ህዝብ ወገኑ ነው እኔ ልጥፋ እስኪል ድረስ የሚወደው ህዝብ ነው::  ትልቁን ስራ ሰርተዋል እራሳቸውን ለጌታ  አስገዝተው መሲሁን እየጠበቁ ነበርና::  ተላለፉ እንጂ!  ስለዚህ ለዚህ ህዝብ ቅናት አለው  ወንጌልን ሰብኮ መጋረጃቸው እንዲነሳና እየሱስን እንዲያዩ::  እኛም ዛሬ በዚህ ቅናት ልንወጣ ይገባል::  የደከመውን ማበርታት፤  የጠፉትን መፈለግ ፤ በጨለማ ያሉትንም ወደ ብርሃን መተው ጌታን እንዲያገኙ ተጠርተናል::  ሁሉም በተሰማራበት ተግቶ ማገልገል አለበት::  ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!

የሐዋርያት ሥራ 22: 1-30

13፤ እርሱም ወደ እኔ መጥቶ በአጠገቤም ቆሞ፦ ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ፡ አለኝ። እኔም ያን ጊዜውን ወደ እርሱ አየሁ።  14፤ እርሱም አለኝ፦ የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል።  15፤ ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና።

በዚህ ምዕራፍ ላይ ጳውሎስ ለህዝቡ የህይወት ምስክርነቱን እየሰጠ ነው::  ሊታገሱት ቢያቅታቸውም ቅሉ እርሱ ግን ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ መጠቀሙ አይቀርም:: እንዴት ወደዚህ እምነት እንደመጣ ማን እንደነበረ ነገራቸው::  እንደነሱ አሳዳጅ እንደነበረ በእስጢፋኖስ ሞትም እንደተባበረና ብዙዎችንም እንዳሳሰረ  ነገር ግን ከማሳደድ እንዲመለስ ያደረገው እራሱ እየሱስ እንደሆነ መሰከረ::  ሐናንያ የነገረው ነገር ግን በጣም ይገርማል:-

– የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና 

–  ጻድቁን ታይ ዘንድ 

– ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል

ምን አይነት መመረጥ ነው?! ይህ ግን ለጳውሎስ ብቻ አይደለም በክርስቶስ ላመንን ሁሉ ነው::  ትህትና መስሎን እኔ ትል የማልረባና የተለያዩ ቃላትን እንጠቀማለን ይህ ስህተት ነው::  ንጉሱ መረጠን ደግሜ እላለሁ መረጠን ለራሱ!

1. ፈቃዱን እንድናውቅ ነው:- ፈቃድ ለማወቅ ጠጋ ማለና ልብን መስጠት ያስፈልጋል

2.  ጌታን እንድናይ ነው:-  ማን ይሆን ጌታን ያላየ በገሀዱ አይን ማለቴ አይደለም በመንፈስ እናም መገኘቱን ያላረጋገጠ? እርሱ የቅርብ አምላክ ነው

3. ድምጹን ለመስማት:-  በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ አላለም? ግድ ነው የመስማት ብቃቱ  ተሰቶናል

ጌታ አንዱን ከሌላው አይለይም ለጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ለእኛም የተሰጠ ነው መርጦናል::  እራሴን እንደጌታ ምርጥ መቁጠር አለብኝ! 

እኔን የሚያሳድድ ጌታን እንዳሳደደ ነው የሚሰድበኝም እንዲሁ::  ግን እራሳችንን እንደዚህ እንቀበላለን? ቃሉ ግን የሚነግረን ይህንን ነው!  ተቀባይነትን ያገኘን ምርጦች ነን::   ስለዚህ በሰው ሁሉ ፊት ምስክር እንሁን::

የሐዋርያት ሥራ 23: – 1-11

1፤ ጳውሎስም ሸንጎውን ትኵር ብሎ ተመልክቶ፦ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ፡ አለ።

11፤ በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፦ ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ፡ አለው።

ጳውሎስ ለምን ታሰረ?! ምን አጠፋ?

ጳውሎስ ጌታውን በትጋት ህይወቱን ሳይሰስት ወደ አህዛብ አዙሮ አገለገለ::  እግሩ እስኪነቃ ድረስ ከአገር ወደ አገር እያስተማረ ዞረ ::  መንገዱ ሁሉ ቀላል አልነበረም ከመከራ ውደ መከራ ነበር::  ከአንድ ስፍራ መዋረድ ወደሚቀጥለው  መዋረድ ምንም ሳያንገራግርናሳያጉረመርም አገልግሏል::  እኔን ምሰሉ እኔ ክርስቶስን እመስላለሁ እያለ ስለሁሉመዳን ሮጠ::

እኔ እርሱን ብሆን የምለው ይህን ሁሉ አገልግዬ አንድ ጊዜ እንኳን እረፍት አይኖረኝም? አልበዛም? ታያለህ ግን? ምን እስክሆን ነው የምትጠብቀው? አንተም ዝም አልከኝ?  እናሌላም ሌላም ልብ የሚኮረኩርና ቁጣዬን የምገልጽበትን መንገድ እፈልግና ማገልገልም እተው ነበር::  ጳውሎስ ግን ያገኘውን አጋጣሚሁሉ ለራሱ ሳይራራ ወደ ስብከት መድረክነት ይቀይረዋል:: መሞት ማለት ለጌታ ይህነው!!!!  እንሙት!!!!

በዚህ ስፍራ የሚለውን ስንመለከት:- እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ፡  እኛም መልካም ህሊና በእግዚአብሔር ፊት ሊኖረን ይገባል::  ይህም ማለት ሁልጊዜ መንግስቱን ያስቀደመ ስለሌላው ግድ የሚለው ማንንት ያስፈልገናል::  እንዴት እራሱ ጌታ አይገለጥለትና አያጸናው በእየሩሳሌም ስለእኔ መስክረሀል አለው::  ከዚህ የሚበልጥ ሽልማት ምን አለ?!  የተጠራነው ስለዚህ መልካም ጌታ ልንመሰክር ነውና በጎነቱን ማዳኑንም ለዓለም እንመስክር::

የሐዋርያት ሥራ 23- የሐዋርያት ሥራ 25

20፤ እርሱም፦ አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል። 

21፤ እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ፡ አለው።

ሻለቃው የአይሁድን የምክር ሚስጥር ስለሰማ ወደ አገረ ገዢው ፊሊክስ ወሰደው::  ከሳሾቹም ተከራከሩ ግን አሳማኝ አልነበረም እግዚአብሔር ነገራቸውን ስላቀለለው አልተቀበላቸውም ግን በእስር ቤት ተወው::  ጉቦንም ፈልጎ ብዙ ጊዜ እያመላለስ አነጋገረው (ለሁለት ዓመት) ጳውሎስ ግን ወንጌልን ብቻ ነበር የሚሰብከው::  ስልጣኑንም ሲለቅ ለፊስጦስ በዛው እንደታሰረ ተወው አይሁድን ደስ ለማሰኘት::  ጳውሎስ ምን አይነት ቆራጥነት ነው ያለው?  ገንዘብ ሰጥቼ ከዚህ አምልጬ ልሩጥ አላለም::  በዚህ ሁኔታ ውስጥብንሆን ምን እናደርግ ይሆን ወይም ለወዳጃችን ምን እንመክር ይሆን ወይስ መዋጮ መሰብሰብ እንጀምር ይሆን እሱን ለማስፈታት?  ጳውሎስ የተጠራው  ግን እነዚህ ባለስልጣናት ሁሉ ወንጌልን እንዲሰብክ ነውና ጥሪውን አውቆ በእስር ላይ ሆኖ ያለምንም ማንገራገር ወንጌሉን ይሰብካል:: 

ፊስጦስም እንደገና ክሱን ሰማ ምንም አላገኘበትምና ጳውሎስ ወደ ቄሳር ይግባኝ ጠየቀ::  ከዛም ደግሞ ወደ ንጉስ አግሪጳና በርኔቄ ቀረበ ወንጀል ስላላገኙበትከአንዱ ወደ አንዱ ያስተላልፉታል በዚህ ውስጥ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ እየተከናወነ እንደሆነ ማን አስተዋለ?  ከተላከው ከጳውሎስ በቀር!   እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለውን አጀንዳ ይፈጽም ቢገባንም ባይገባንም እረኛችን ይመራናል:: ስለእኛ ሌሎችን ያስነሳል ልክ እንደጳውሎስ የእህት ልጅና ሻለቃው:: በጌታ እንታመን!

የሐዋርያት ሥራ 26: 1-32

17-18፤ የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ። 19፤ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም።

ጳውሎስ በንጉሱና በአገረ ገዢው ፊት ስለ እምነቱ ሲገልጽ:- ፈሪሳዊ እንደነበረ ይህንንም ስም የሚጠሩትን አሳዳጅ እንደነበረ ነገር ግን በደማስቆ መንገድ ጌታ ሲገናኘው አቅጣጫው እንደተቀየረና ከሰማይ ለታየው ራእይ እምቢ እንዳላለ ገለጸ::  የተሰጠውም አገልግሎት እዚህ ጋር እንደገለጸው

– የኃጢአትንም ስርየት 

– በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ 

– ከጨለማ ወደ ብርሃን 

– ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ 

– እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ 

– ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ 

ይህንን ትእዛዝ ለእኛም እግዚአብሔር ሰቶናል::  እግዚአብሔር ይርዳን ይህንን እውነት እንግለጥ::  ጳውሎስ ይህንን በመንገዱ ሁሉ ፈጸመው አገለገለ::  እሩጫዬንም ጨረስኩኝ አለ ጊዜን ሳያባክን አገለገለ::

የሐዋርያት ሥራ 27: 1-44

23፤ የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፥

24፤ እርሱም፦ ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል፡ አለኝ።

25፤ ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ፥ አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁና።

ይህ መርከብ 276 ሰዎችን ያሳፈረ ነበር የጳውሎስን ምክር እንቢ ብለው ለታላቅ መከራ ተጋለጡ::  አውራቂስም የእግዚአብሔርን አጀንዳ ሊቃወም ጳውሎስን በመንገድ ሊያስቀር ቢወጣም አይችልም ኃይል የእግዚአብሔር ነውና::  አይደለም ጳውሎስ ሁሉም ከእርሱ የተነሳ ተጠበቁ ምክንያቱም በቄሳር ፊት መቆም አለበትና: :  ወታደሮቹ እንኳን እስረኞቹን እንግደል ብለው ቢማከሩም በአንዱ መቶ አለቃ ምክራቸውን መታው::  የጠላት ምክር ዛሬ በጌታ በእየሱ ስ ም  ከዙሪያችን ይመታ!

እግዚአብሔርን የሚያውቅ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁ ይላል::  ጌታ የተናገረን ምንድነው እንደዛው ይሆናል የፈለገው ነገር ቢፈጠርም አይለወጥምና በጌታ ልባችን ይጽና::

የሐዋርያት ሥራ 28: 1-10

2፤ አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን።

3፤ ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው።

5፤ እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤

ከዛ ሁሉ እንግልት በኃላ በሰላም እያንዳንዱ ነፍስ ደሴትዋ ላይ ደረሰ::  ቸርነትንም ከህዝቡ አገኙ እግዚአብሔር ሲረዳ ሞገስን ይሰጣልና::  የተሳፈሩበት መርከብ ግን ምልክቱም የለ ተሰባበረ ቃሉን የሰጠ ጌታ ግን ታማኝ ነውና የእርሱ የሆንኩት ብሎ ተማምኖ የተናገረውን ቃል አጸናው::  

የማዕበሉ ነገር አለቀ ሲባል እባብ አገኘችውና ነደፈችው::  የደሴቲቱ  ሰዎች እግዚአብሔር ቀጣው ብለው አብጦ እስኪሞት ሲጠብቁ እርሱ ግን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም ይላል::  መንደፍን ግን ነድፋዋለች ይህንን ሰው ግን መግደል በእባብ መርዝ እንኳን አልተሳካም::  የደሴቲቱ ሰዎች ኃጥያተኛ ነው እንዳላሉ አሁን ደግሞ አለመሞቱን ሲያዩ አምላክ ነው አሉት::  ወይ ዓለም?!  ጠላት በብዙ መንገድ ይዋጋል በመከራ መጣል ሲያቅተው አንዳንዴም በኩራት እንድንኮፈስ ይጥራል እኛ ግን ትህትናን ከጌታ እንማር ክብር ለሚገባው ክብር ይሁን::

ጳውሎስ እስረኛው ከስራ ውጪ አልነበረም በሽተኞችን ፈወሰ ይላል ቃሉ ፈውሱን ሲያዩ መቼም ጌታን ወደማወቅ ይመጣሉ ብዬ አምናለሁ::  በጊዜውም አለጊዜውም ጌታን መመስከር ያስፈልጋል::

በህይወታችን ላይ ምንም እርሱ ያልፈቀደው አይመጣም ከመንገዳችንም አያቆመንም የምናመልከው እርሱ ጌታና ሁሉን ቻይ ነው::  አሜን!

የሐዋርያት ሥራ 28: 11-31

23፤ ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር።

28፤ ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል።

31፤ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።

የሚገርመው ነገር ምን ያህል ወንጌል እንደተሰራ ነው እነጳውሎስ በሚሄዱበት  መንገድ ሁሉ ወንድሞችን ያገኛሉ ይህም ጳውሎስን አጽናናው::  የአገልግሎቱን ፍሬ እያየ ነውና ተጽናና የምናፈራው ፍሬ የትም አይሄድም::

በዚህ ስፍራ የአይሁድን  ታላላቆች ጠርቶ ከጠዋት የጀመረ እስከማታ ድረስ  የመጣበትን የክስ ሂደና  እርሱ እየሱስ መሲህ መሆኑን አስተማረ ግማሹ ሲቀበል ግማሹ ተቃወመ በዚህም ይሁን በዛ  ወንጌል ተሰበክ::  

በመጨረሻም ያላቸው ይገርማል:- ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል።  አሜን እንኳን ወንጌል ለአህዛብም እንዲሆን ጌታ ፈቀደ::  እኛም ሰምተን ድነናልና በቤቱ መጻተኛ  አይደለንም ቤተኛ ነን::  እጁን ዘርግቶ የተቀበለን አምላክ ይባረክ::

በሮሜ የሁለት ዓመት እስር ቆይታው ጳውሎስ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር ይላል ቃሉ::  እዚህ እስር ላይ እያለ ነው የኤፌሶንን ፤ ፊሊጲስዩስን የጻፈውና በጌታ ደስ ይበላችሁ የሚለው እርሱ እስር ላይ ሆኖ!    እስር ላይ ቢሆንም የሚያሳስበው የቤተክርስቲያን ነገር ነበረ::  እኛ እዚህ ጋር ብንሆን እውነት ያለማጉረምረም በፊታችን ያለውን የመንግስት ስራ እየሰራን ጊዜ እንደሌለው ሰው አተኩረን እንሰራ ይሆን?! ባለንበት በማንኛውም የህይወት ውጣ ውረድ ሁሉ እግዚአብሔርን እንፈልግ  እርሱን እንግለጥና ሌሎችን እናገልግል ዓለም ያልፋል ሁሉም ይቀራል ዓይናችንን በጌታ ላይ እናድርግና በህይወታችን ላይ ያለውን አጀንዳ እንፈጽም:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን ማስተዋልንም ይስጠን:: የምንሰስተው ህይወት የለንምየምንኖረው ኑሮ የእኛ አይደለምየእርሱ ነውና!

Published by Betty & Abera

We’re dedicated to share God’s goodness and mercy through His word!

Leave a comment