የዮሐንስ ራእይ

መግቢያ

በዚህ መጽሐፍ ብዙ አሳብ አለ ከዚህ መካከልም እንደገባን የምናየው:-

1.  ስለ እየሱስ መገለጥ

2.  የእግዚአብሔርን ፍርድ

3.  ለባርያዎቹ የክርስቶስን ክብር ለማሳየት

4. ወደፊት ሊሆን ያለውን

5.  ስለሐሰተኛው ክርስቶስ እና ሌላም

ጥልቅ መጽሐፍ ነው ምክንያቱም ትንቢት ስለሆነ በዚህ ውስጥ ግን እግዚአብሔር ቃሉን ይግለጥና መረዳትን ይስጠን ይህንን እየሱስን የበለጠ በክብሩ እንወቀው: የማይገባንም ክፍል ቢኖር ስንሄድ ሙሉ እውቀት ይኖረናልና:: በመልእክቶችና በወንጌል መጽሐፍት ውስጥ እየሱስን የምናውቀው ዝቅ ብሎ በትህትና እንደመጣ ስናይ በዚህ ክፍል ደግሞ ያለውን ክብርና ግርማ እንዲሁም ወደ ምድር ሲመጣ ጥሎት የመጣውን ክብሩን ያሳያል::

ይህ ጌታ ታላቅ ነው ደግሞም መንፈስ ነው!  ጌታ ያስተምረን!

የዮሐንስ ራእይ 1: 1-3

1፤ ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ 2፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ። 3፤ ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።

በሰማይ ያለውን ክብሩን እናይ ዘንድ እግዚአብሔር አብ  ነው ይህንን ራዕይ እንዲገለጥ ያደረገው ስለ ለእየሱስ ፤ እየሱስም መልአኩን ልኮ ለዮሐንስ ፤ ዮሐንስም ለእኛ አደረሰን:: የሐዋርያት ሥራ 1: 9፤ ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው ይለናል ቃሉ::  ከዛስ ምን ተፈጠረ? እየሱስን የምናውቀው ዝቅ ብሎ የመጣ ትሁት፤    ስለእኛ ዝም ብሎ የተንገላታ ፤  የተመታ፤  የተሰቀለ ጌታ ነው::  ምንም እንኳን ጌታ ክብሩን ቢነግረንም ብዙም አልገባንም ለዚህ ነው ከደመናው ባሻገር ያለውን እንድናይና እንዴት እንደከበረ ደግሞም እንደሚመጣ ሙሉ መረጃ ሊሰጠን ወደደ::  ስፍራን ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ ብሎን ነበረ የት ነው ይህ ስፍራ የተዘጋጀው ካልን መልሱን እዚህ ክፍል ላይ ይሰጠናል:: እንዴት ድንቅ ነው ይሄ ጌታ?!

ዮሐንስም  ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ።  ዛሬም ቃሉን ልናውቅና ምስክሮቹ እንድንሆንና የእርሱን በጎነት እንድንናገር ተጠርተናል እንናገር እንመስክር!

ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።  ዘመኑ ያኔ ደርሷል ከተባለ ዛሬማ በደጅ ነው ጌታ እናክብረው በህይወታችን! እንበርታ!

የዮሐንስ ራእይ 1: 4-5፤ 

ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

እዝች ክፍል ላይ ስላሴን ቁልጭ አድርጎ  ያሳየናል በዚህ ሰላምታ ውስጥ::  ራዕይ በብዛት የተጠቀሰው ከብሉይ ኪዳን ነው አንዳንዶች እንደሚሉት 70%  የሚሆነው::  እግዚአብሔር አዲስ ኪዳን ላይ አይደለም የራዕይን መጽሐፍ ያሰበው ገና ድሮ በቃሉ ውስጥ በነብያቱ ተናግሯል::  

ሰላምታውም :- 

1. ከአብ : ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥  ኦሪት ዘጸአት 3

14፤ እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ፡ አለው።

2. ከመንፈስ ቅዱስ:   በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ 

ትንቢተ ኢሳይያስ 11

2፤ የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።

ይህንን ቃል ስንተነትነው ሰባቱ የመንፈስ ቅዱስ መገለጫዎች ናቸው:- 

2.1 የእግዚአብሔር መንፈስ

2.2 የጥበብ መንፈስ

2.3 የማስተዋል መንፈስ፥ 

2.4 የምክር መንፈስ

2.5 የኃይል መንፈስ፥ 

2.6 የእውቀት መንፈስ

2.7  እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ

ይህ መንፈስ በእኛ ላይ ይምጣ ዘይታችንም የሞላ የሚሆነው እንደዛ ነው ዕለት ዕለት በእርሱ ስንሞላ:: ይሙላን በማንነቱ::

3. ከወልድ: ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ 

አባቱን እስከሞት እንደታዘዘና እንደታመነው እናውቃለን:: 

እኔን ባታምኑ አብን በስራው እመኑት እያለ መስክሯል::

ከሙታን በኩር ሆኖ ደሙን እያንጠባጠበ ወደ አብ ገብቷል ከሁሉ በፊት ነው:: እርሱ ነገሥታት ገዥ ነው ሁሉን ከእግሩ ስር ያስገዛለታል::

አሜን እንዴት ያለ መልእክት ነው አምላካችን የላከልን::  ልናገነውና ልናመልከው ይገባል::  እርሱ ትልቅ ሆኖ ሳለ አስቦን  ይህንን  መልእክት ላከልን:: እኔንም ታሳቢ አድርጎ የተፃፈ ነው ብዬ እላለሁ::  እያንዳንዳችን እንደዚህ እናስብ:: ለሚናገረን መልእክት ጆሯችን የተከፈተ ይሁን::

የዮሐንስ ራእይ 1:6

ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥  6፤ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።

ቃሉን እናስተውል ለወደደን ነው እንጂ ለሚወደን አይልም::  በኃላፊ ነው የተገለጠው የቱጋ ነው ታድያ የወደደን?!  በመስቀል ላይ በመሞት ነው አንድ ጊዜ የወደደን በሮሜ 5:8 እንደሚለን:- ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። አይገርምም ገና ኃጥያተኞች ሳለን የሚወደድነገርም ሳይኖረን ነው የወደደን ስለዚህ ነው ዮሃንስም ልጆች ሆይ ሐጥያትን ብታደርጉ ጠበቃ አላችሁ የሚለን::  ጠበቃ አለን ብለን ደግሞ በኃጥያት እንዳንመላለስ በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም። ይለናል::  እራሳችንን ማየት ያለብን በመስቀሉ ውስጥ ነው ተወደናል!!

የሚገርመው ሐጥያታችንን ያጠበው ከወደደን በኃላ ነው::  መውደዱ ነው ወደ መስቀል የወሰደውና ደሙን እንዲያፈስ ያስገደደው::  በዛም ደም እኛ ታጠብን የሰማይ ሰራዊትም ሲጠይቁ  እናያለን እነዚህ እነማን ናቸው ብለው መልሱ ልብሳቸውን በበጉ ደም ያነፁ ነው!!  ሃሌሉያ!!! ታጥበናል ከሐጥያታችን::

አጥቦ አንጽቶ ብቻ አይደለም የተወን መንግስትን ሊያወርሰን እንጂ:: የመሰረተው መንግስት የካህናት መንግስት ነው:: 1ኛ ጴጥሮስ 2: 9፤ እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤

የንጉስ ካህናት ሆነናል!!! አሜን ታድያ ለዚህ ጌታ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።

ቀናችንን ስንውል ምስጋናን እየሰዋን እናመስግነው እናወድሰው ስለመወደዳችንና የካህንነትን ማዕረግ በእርሱ ስራ ስለተቀበልን:: ካህን ስራው መቀደስ ነውና ስሙን እየቀደስ  በቤቱ እናገልግለው ይህንን እድል አግኝተናል ማንም ከእኛ አይወስደውም ድሮውንም ስራችንን አይቶ ሳይሆን መጥፋታችንን አውቆ ነውና የሞተልን::  የዓለምን ሁሉ ኃጥያት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ ታድጎናል!!!  ሃሌሉያ!

የዮሐንስ ራእይ 1: 7-8

7፤ እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን። የዮሐንስ 8፤ ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፦ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ፡ ይላል።

እነሆ ስንባል ምን ብለን ቀና ማለታችን አይቀርም አንዳች ለማየት እንዲሁ ባለ ጉጉት ነው ጌታን መጠበቅ ያለብን እርሱ ይመጣል:: በዳንኤል 7: 13-14 እንዳለው እንዲሁም በማቲዎስ 24: 42 ላይ መቼ እንደሚመጣ አናውቅምና የተዘጋጀን እንሁን:: ደመና እንደተቀበለው ደመና በእርግጥ ደመና ሲሆን ሌላው ፍቺው ደግሞ የእግዚአብሔር ህዝብ ማለት ነው በዕብ 11:1 እንደሚናገረው በምዕራፍ 10 ያሉትን የእምነት አርበኞች ደመና ብሎ ይጠራቸዋል:: ከደመና ጋር ይመጣል ቅዱሱ በሐውዋርያት ስራ 1:9::

 በፊት የመጣው ዝቅ ብሎ ተዋርዶ የባርያን መልክ ይዞ ሲሆን ሲመለስ ግን በኃይል ነው የሚመጣው::  እራሱም ጌታ በማርቆስ ወንጌል 14: 62፤ ኢየሱስም አለ፦ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ። በብሉይ ኪዳንም ለሙሴም ሲገለ በሲና ተራራ እንዲሁም ወደ መገናኛው ድንኳን ሲጣ ደመናው ነበረ::  እርሱ በደመና ላይ ይራመዳል ደመና የሚታዘዝ አይደለም በውስጡ ይታለፋል እንጂ የማይጨበጥ ነገር ነው:: ለእርሱ ግን ግዑዙ ሁሉ ይታዘዛል::

ዓይንም ሁሉ ያዩታል ይላል ሲመጣ ጌታ መጣ ብሎ አዋጅ ነጋሪ የለም በዜናም አይደለም የሚሰማው ሁላችን በህይወት ካለን በዛው ቅጽበት እናየዋለን::  በማቴዎስ 24:26፤ እንግዲህ፦ ‘እነሆ፥ በበረሀ ነው’ ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በእልፍኝ ነው’ ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤27፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤

እኛ ብቻ ሳንሆን የወጉትም ያዩታል::  የወጉት ሲባል በስጋ  የወጉትን ብቻ ሳይሆን እርሱን አውቀው የዓለም ነገር በልጦባቸው ትተውት የሄዱት ልቡን የወጉት ሁሉ  ያዩታል::  ምን ይሉ ይሆን? ለምናውቃቸው ወደኃላ ለተመለሱት እንፀልይ ልብን ያሳዝናል ከእርሱ መለየታቸው:: 

ለምን ይሆን የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ የሚለው? ስላላወቁትና ስላልተቀበሉት ነው ::  ከዚህ ዋይታ ያወጣን ጌታ ይመስገን::  ማራናታ!

ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፦ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ፡ ይላል። ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ያለ እርሱ አልሆነም::  እርሱ አልፋ የሁሉ መጀመሪያ መነሻ እንዲሁም ዖሜጋ የሁሉ መደምደምያ ነው::  ክብር ይሁንለት!!

የዮሐንስ ራእይ 1: 9-11

9፤ እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ። 10፤ በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥

በፍጥሞ ደሴት በእስር ላይ ነበረ ዮሃንስ የታሰረውም ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር  በመሆኑ ምክንያት ነበር::   እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ይላል::  መከራ የለም አላለንም በተለይ ዮሃንስ በሚጽፍበት ዘመን የሮም አገዛዝ ሁሉንም አካባቢ ተቆጣጥሮ የነበረበትና ተገዳዳሪ ወይም ሌላ መንግስት የማይታሰብበት ጊዜ ነው::  ይህ መንግስት ጊዜያዊ ነው የእግዚአብሔር መንፍስት ግን ዘላለማዊ ነው::  እርሱ እራሱ መከራ እየተቀበለ ያለ ሰው ነው በዝች ደሴት ማምለጥ ስለማይችሉ ነው እስረኞቹን እዚህ አምጥተው የሚጥሏቸው::  የመልእክቱ ተቀባዮችም ቢሆኑ ይኽው የመንግስት ጡጫ የሚያገኛቸው ስለሆኑ እኔ ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር አብሬ መከራውን የምካፈል ብሎ ብቻ አልዘጋም ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንግስት የምካፈል ብሎ ይጨምራል::  ጊዜያዊዉ መንግስት ያልፋል የማያልፍን መንግስት እኛም ተካፋይ የሆንበትን እንወርሳለን:: የሮም መንግስት ቢያስረውን እግዚአብሔርን ወደ ዮሃንስ ከመምጣት አላገደውም::  እግዚአብሔር አይከለከልም የምናመልከው ጌታ ትልቅ ነው:: በምንም ነገር ውስጥ እንለፍ እርሱ ከእኛ ጋር ነውና በድል እንወጣለን::

በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ ይላል ሰዎቹ ያሰሩት ከዛ እንዳይወጣ እርሱ ግን በመንፈስ ሆኖ በንጉሱ ፊት ከሁሉ በላይ በሆነውም መንግስት ፊት ነበረ::  የዓለም ነገር በእግዚአብሔር ተሸናፊ ነው ምን ቢከበን ጊዜያዊ ነው እንበርታ::  በመንፈስ ሆኖ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥ ይላል::  ይህንን ድምጽ በሲና ተራራ ሲሰሙት እስራኤሎች ያሉት አንድ ነገር ነው እግዚአብሔር አይናገረን ሙሴ አንተ ተናገረን የሚለውን ሁሉ ንገረን እናደርጋለን ነበር::  እንደ ታላቅ የመለከት ድምፅ የሆነበት የጌታ የእየሱስ ክርስቶስ ንግግር ነበረ::  ሃሌሉያ!!  በመንፈስ ተሆኖ የሚሰማ ድምጽ:: በመንፈስ እንመላለስ ፤ በመንፈስ እንጸልይ::

ይህም ድምጽ የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ፡ አለኝ። የታሰረው እንዳያገለግል ነበረ ግን እያገለገለ ነው ዮሃንስ::  እግዚአብሔር ይጠበባል መንግስቱ በምንም አይቆምም!!! ሃሌሉያ! ዛሬም እናገለግለዋለን! 

የዮሐንስ ራእይ 1: 12-16

13፤ በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፥ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። 

14፤ ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፥ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤

15፤ እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፥ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ነበረ።

16፤ በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፥ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ።

ዮሃንስ እየሱስን በደንብ ያውቀዋል ግን በዚህ መልኩ አልነበረምና ወደቀ::  ልክ ዳንኤል እንዳለው እርሱም እየሱስን የሰው ልጅ የሚመስል ብሎ ይጠራዋል::  አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ ብሎ ስለራሱ ያወጀ ጌታ! ስሙ ይባረክ::  

በመቅረዞቹም መካከል ነበረ ጌታ የነበረው ይህ መቅረዝ የሚያስታውሰን የቀደመውን ሙሴ የሰራውን የመገናኛ ድንኳን ነው ምንም ሳትሳሳት እንዳየኸው ስራ የተባለው በሰማይ ስላየው ነው መቅረዙን::    መቅረዙ በራሱ ብርሃን አይሰጥም ከዘይቱ እንጂ ዘይት ካልተጨመረ አይበርም የእኛም ህይወት ያለ መንፈስ ቅዱድ መብራት አይችልም ዕለት ዕለት ተሞሉ ተብለናል እየሱስን እየመሰልን እያብለጨለጭን እንድንመላለስ:: 

እየሱስ በብዙ መከራ አልፎ ከብሮ እያየ ነው በመከራና ስደት ውስጥ ያለው ዮሃንስ::  ያንን ሁሉ ያለበትን የሚያስረሳ ነው በራዕይ እያየ ያለው እርሱም የጌታን ክብር::  ሁሉ ይታለፋል እንዲህ የከበረ ጌታ በሰማይ በክብሩ ሆኖ አይኑን በእኛ ላይ አድርጏል:: ዓለም አታሸንፍም ድሉ የተረጋገጠ ነው ጌታን እናገለግላለን!!

ዮሃንስ በተቻለው መጠን ካለው እውቀቱ ጋር በማዛመድ ግልፅ የሆነ መረጃ ሊሰጠን ጥሯል::  እየሱስ በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር ይላል እንደዚሁም  በዳንኤልም መጽሃፍ እንደሚልው ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ ይላል ይህ ቅድስናውንና በዳንኤልም ላይ እንደምናየው ዳንኤል 7: 22፤ በዘመናት የሸመገለው እስኪመጣ ድረስ፥ ይላል እርሱ በዙፋኑ ላይ የጸና ጌታ ነው::

ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ ይህ የሚያሳየው ፍርድን ነው እግሩም የጋለ ናስ በምንም ውስጥ የሚራመድ ጌታ የከበረ ጌታ ነው:: ድምጹም የሚያስፈራ እንደብዙውሃ ድምጽ::

በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፥ በፊቱ ያየናል በመካከላችንም ይመላለሳል:: ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ እርሱ ሲናገር ይቆራርጣል እኛንም በቃሉ ይሰራናል ጠላትንም በቃሉ ያጠፋል:: የእግዚአብሔር ቃል ለእኛም መዋጊያችን ነው በኤፌ 6 ላይ እንደምናየው:: ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። ማን ያየዋል?

ጌታ ሆይ አንተ ትልቅ ነህ ተባረክ::

የዮሐንስ ራእይ 1: 17

17፤ ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ፥ እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥   18፤ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።

ዮሃንስ እየሱስን ባየ ጊዜ መቆምም አልቻለም ወደ ደረቱ ተጠግቶ የሚጠይቀው ዮሃንስ እንደሞተ ሰው ሆኖ ወደቀ ልክ እንደእርሱ ዳንኤልም መቆም አልቻለም ነበረ::

ሕዝቅኤል 1:28፤ በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።

ዳንኤል 8:17፤ እኔም ወደ ቆምሁበት ቀረበ፤ በመጣም ጊዜ ፈርቼ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ ራእዩ ለፍጻሜ ዘመን እንደ ሆነ አስተውል፡” አለኝ።

 ጳውሎስ እንዳለው ነው ክርስቶስን በስጋ ታውቁት ከነበረ አሁን እንደዛ አትወቁት  ክቡር  ንጉስ ነው::  ዮሃንስ በወደቀበት ቀኝ እጁንም ጫነበት፥ እንዲህም አለው፦ አትፍራ፤ ብሎ አበረታው::  መፍራትም የሌለበትን  ምክንያት እየሱስ ሲያብራራ:

1.  ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥   በኢሳያስ 44:6  ላይ ይህንኑ ቃል ጌታ ስለራሱ ተናግሯል::  እርሱ ከሁሉ በፊት የነበረና የሚኖር እኔ እኔ ነኝ የሚል የህይወት ሁሉ መገኛ ጌታ ነው! 

2.  ሞቼም ነበርሁ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥  ጌታ አንድ ጊዜ የሞትን ጽዋ ጠጥቶ እዳችንን ሁሉ ከፍሎ በትንሳኤ ተነስቷል ደግሞ  መሞት አያስፈልገውም  ስለዚህ ለዘላለም ህያው ነው::

3. የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።  የመጨረሻ ሰውን የሚያስፈራራው ነገር ቢኖር ሞት ነው እሱም ተሸንፏል::  ሰይጣን እንደፈለገየሚያደርገው ነገር የለም ገደብ አለው::  ለእኛ ለምናምነው የታመነ ጌታ ነው ታድያ ምን ያስፈራል ጌታ ለእኛ ነው እንታመነው::  ይህንን ትልቅ ጌታ እንወድሰው!  ሃሌሉያ ይገባዋል!!

ዋው ጌታዬ ሆይ ክብርና ምስጋና ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል:: አሜን

የዮሐንስ ራእይ 1: 19-20

19፤ እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ።  

20፤ በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፥ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

ዮሃንስ ጌታን እንደዚህ በክብሩ አይቶ ከወደቀበት አይዞህ ተብሎ ተበረታቶ ተነስቶ ሳለ ጌታ ጻፍ ይለዋል:: ጻፍ ትእዛዝ ነው እኛም የህይወታችንን ታሪክ ብንጽፍ ለምስጋና ይሆናል አቤነዘር ለማለትም ይጠቅማል የምናልፍበትን ሁሉ ለበጎ አድርጎ እየለወጠ እዚህ ያደረሰን ጌታ ብዙ የሚነገርለት ነገር አለ በህይወታችን::  ስሙ ይባረክ:: የሚጽፈውም ያየኸውን አሁንም ያለውን:- በቤተክርስቲያናቱ (ከምዕራፍ 2-5) ውስጥ በዛ ሰዓት እየሆነ ስላለው እንዲሁም ደግሞ  ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ነው።   

እነዚህ በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፥ አለው መላእክት ሲባል አንዳንዶች መላእክ ማለት ክንፍ ያለው መላእክት ማለቱ ላይሆን ይችላል እረኛን ወይም የቤተክርስቲያን ሽማግሌን ማለቱ ይሆናል ይላሉ ምክንያቱም በምዕራፍ 2 ሲጀምር የደብዳቤው ተቀባይ  በኤፌሶን ወዳለው መልአክ ነው የሚለው::  አብራርቶ ነግሮንም ሚስጥር አለው ይገርማል::  እነዚህን ከዋክብት በቀኝ እጁ ይዟል ከእጁ ማንም አያወጣውም ዋስትና ያለው ቦታ ናቸው:: 

የወርቅ መቅረዞቹ ደግሞ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።  የሚገርመው 1:13 ላይ ጌታ በመቅረዞችር መካከል ነበረ::  እነዚህ መቅረዞች ቤተክርስቲያንን የሚወክሉ ናቸው ስለዚህ ጌታ በመካከላቸው ነው ያለው::  ዛሬም በመካከላችን የሚመላለስ ጌታ አለ::  እሩቅ አይደለም መንግስትህ ትምጣ ብላችሁ ጸልዮ ብሎ ያስተማረን ጌታ መንግስቱ በመካከላችን ናት::  እንዴት ያለ መታደል ነው በእርሱ ፊት መሆን?!  ተባረክ ጌታ ሆይ!!  ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን::

የዮሐንስ ራእይ 2: 1-7

1፤ በኤፌሶን ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል፦

2፤ ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ፦ ሐዋርያት ነን፡ የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤

3፤ ታግሠህማል፥ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም። 

4፤ ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና።

ይህ መልእክት የተላከው ቀጥታ ከእየሱስ ወደ ኤፌሶን ቤተክርስቲያን ነው:: ኤፌሶን ማለት ትልቅ የመገበያያ ከተማ ነበረች የዳያናም ቤተመቅደስ ያለባት ልክ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚበረታታበትና የጠላት አምልኮ የሰለጠነበት ከተማ ነው::  በዚህ መካከል ነው እንግዲህ ይህች ቤተክርስቲያን ያለችው::  ጳውሎስ ለሶስት ዓመት ቁጭ ብሎ አገልግሏቸዋል ከእርሱም ጋር አጵሎስ ና ጢሞቲዎስ እንዲሁም ዮሃንስም አቂላና ጵርስቅላም አገልግለዋል::   ብዙዎች የደከሙበት ነው::  

ጌታ የሚወደው ነገር አለ

1.  ስራህን አውቃለሁ:- ምክንያቱም በመቅረዞቹ መካከል እየተመላለሰ ነውና እርሱ እሩቅ አይደለም ዛሬም ስራችንን ያውቃል ማንም ሊነግረው አያስፈልግም::  እርሱን በመፍራትና በማክበር እንመላለስ መንጋውምየጌታ እኛም የጌታ::

2. ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤  በመከራ ውስጥ ከውጪ ውጊያ ቢኖርም ታግሰው በትጋት ለጌት ስራ እየደከሙ እንዳለም ያውቃል::  እንዴት ነው ዛሬ የጌታን ስራ እየደከምን/እየሰራን ያለነው ? እርሱ ያያል::

3. ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ፦ ሐዋርያት ነን፡ የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ በሐዋ 20:29 ላይ ጳውሎስ  ሽማግሌዎችን ከቤተክርስቲያንዋ ጠርቶ ሲመክር ነግሯቸው ነበር ምን አይነት ሰዎች እንደሚነሱ ጌታም ከዛው ነው የቀጠለው::  እነዚህን ስህተተኞች አስወግደዋል:: ዛሬም አለማዊ ምኞትን አስወግደን የተባረከውን የጌታችንን መምጣት በጸጋው እንጠባበቅ::

የወቀሰባቸው ነገር

1.  ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና።

ብዙ  የምነቅፍብህ ነገር አለኝ ብሎ ፍቅርህን ትተሀል ነው::  ብዙ እንደተባለ እናስተውል ፍቅር በብዙ ተወክሏል ምክንያቱም የጌታ አገልግሎት ሁሉ መሆን ያለበት በፍቅር ስለሆነ::  ፍቅር ከሌለ እንደሚንሿሿ ጸናጽል ነን:,  ጌታን ወደን ከዛም ሰውን ሁሉ እንድንወድ ተጠርተናልና::  ፍቅራችን ይብዛ!!

የዮሐንስ ራእይ 2: 5-7

5፤ እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ። 

6፤ ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና።

7፤ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ።

ቃሉን እንደመስታወት ነውና በቃሉ ውስጥ ተነክቼ በፊቱ መምጣት ሲገባኝ እንደገና ሌላ መልእክትን ላከልኝ ሊምረኝ የወደደ ጌታ::  የተለየ ፍቺ ካለ እታረማለሁ::  

ያ የድሮው ፍቅር የት ሄደ እኔን ብቻም አይመስለኝም ሁላችንንም ነው ጌታ የሚጠይቀው ዛሬ ለማንበብ ያህል ማንበብ የለብንም ንስሀ እንግባ ፍቅሩን በልባችን የሚያድስ እርሱ ነው::  መፈለግንም ማድረግንም በእኛ የሚሰራ እርሱ ነውና::  አይለፈን ይህ አጋጣሚ እንጠቀምበት::  ሁሉ ሰላም ቢመስል ብንዘምር ብናገለግል ነፍሳችንን እንኳን ለመቃጠል አሳልፈን ብንሰጥ ምንም ጥቅም የለውም ፍቅር ከሌለ::  ይህ በአንድ ጊዜ የሚሆን አይደለም ቀስ በቀስ ስፍራችንን ለቀን ይሆናልና እንመለስ:: የሚዘረዝረው መልካም ነገር ስለ ኤፌሶን ቤተክርስቲያን የሚገርም ነው ግን ምን ያደርጋል?  ፍቅር ቀዝቅዟልና ዋጋ የለውም::  እርሱ የሚጠላውን ጠልተዋል ግን ፍቅር ጎደለ::

እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ።  ንስሀ መግባት ያስፈልጋል በወደቅንበት ነገር ደግሞ ደጋግሞ መናገር የለበትም ሊረዳን የሚፈልግ ጌታ እያሰበን ነው::  ፍቅር ብዙ ወይም ዋናው የተጠራንበት የታዘዝነውም ነገር ነውና::  የማቴዎስ 22: 37፤ ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። 38፤ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።39፤ ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ፡ የምትለው ናት። ጌታ አዲስ ነገር አይደለም እየጠየቀ ያለው የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ ነው እያለ ያለው አመድ  የለበሰ የተዳፈነውን እናራግፍ ዛሬ::

እንግዲህ ምን ያህል እንደራቅን እንይና በፊቱ ወድቀን እርዳን እንበለው ሁሉ በፍቅር ማሰሪያ መታሰር አለበት::  በፍጹም ፍቅር ከተመላለስን በፊቱ መሆንን አንጠግብም ሁሌ እርሱን የምንራብና የምንጠማ እንሆናለን አለበለዚያ ያለህን እወስደዋለሁ እያለን ነው:: ይህ ምን ማለት ነው ህልውናው የሌለበት ወይም ከሚመላለስበት ከመቅረዙ መካከል  መነሳት ማለት ነው በጣም ያስፈራል:: ምን ይጠቅመናል እሱ የሌለበት ህይወት ማባከን ነው::

በቃሉና በጸሎት በመትጋት ከቅዱሳን ጋር ህብረትን ለማድረግ በመጏጏት እንዲሁም ስለ እየሱስ በመመስከር የመጀመርያ ፍቅራችን መመለሱን ማወቅ እንችላለን:: 

መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ።

ጆሮአችን ሰምቶ ልባችን ተለውጦ እንገኝ::  ሽልማቱም ከህይወት ዛፍ መብላትና ለዘላለም ከእርሱ ጋር መኖር::  አዳምና ሔዋን እንዳይደርሱበት ያስጠበቀውን የህወት ዛፍ የሚናገር ይመስለኛል::  ፍቅራችንን እናድስ!!

የዮሐንስ ራእይ 28-11

9፤ መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፥ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ የሰይጣንም ማኅበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ፦ አይሁድ ነን፡ የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ።

10፤ ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።

ይህ መልክት የተፃፈው ለሰምርኔስም ቤተ ክርስቲያን ነው::  መልክቱን የላከው  

ሞቶ ከነበረው ሕያውም ከሆነው ፊተኛውና መጨረሻው ከሆነው ከእየሱስ ነው::  ሞትን ሞቼ ነበር አሁን ግን ህያው ነኝ ያለበት ምክንያት ሞት ነው እያሳደዳቸው ያለው ለዚህ ነው በመዝጊያውም ላይ ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም። እያለ የሚያመለክታቸው::  ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ሲያልፉ መቼም ጌታ ለምን ተወን አይመልስም አያተርፈንም እያሉ ጥያቄ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም ነገር ግን እዚህ መልክት ላይ መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፥ ያላየሁት አይምሰልህ ሞትን ድል የነሳሁኝ ነኝ ምንም ቢመጣ ጸንተህ ቁም ነው መልእክቱ::  ድህነት ውስጥ ቢሆኑም ጌታ የሚላቸው ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ ነው የእኛና የጌታ አስተያየት ይገርማል::  እንዲሁም 

የሚደርስባቸውን ስድብ አውቃለሁ እያላቸው ነው። ስድቡ አይሁድ ካልሆኑ ነገር ግን ነን ከሚሉ ነው::  

የመልክቱ ዋና ጭብጥ በርቱ ነው !ሊመጣ ያለ ልትቀበለው ያለህን መከራ አለና አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። ማለትም በወህኒ መጣል ብቻ ሳይሆን ሞትም እንዳለ ሊያሳያቸውና እንዲጸኑ ነው የጻፈው:: ቃሉ እንደሚል  2ኛ ጢሞቴዎስ 3: 12፤ በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ይህ ሞት በዘመናችን ብዙም የለም ግን ዓለም ልታሸፍተን ትፈልጋለች ከጌታ ስር እኛ የተጠራነው እሱን ልንመስል ነውና እንምሰለው:: በምንም ነገር ውስጥ ብናልፍ ጌታ ያያል ችላ አይለንም ድል የነሳ ጌታ አለን!  በምናልፍበት ነገር ሁሉ እንጽና::  እርሱ ድል ነስቷል!!  ሃሌሉያ!

የዮሐንስ ራእይ 2: 12-17

13፤ የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም። 14፤ ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ።

15፤ እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ።

ጰርጋሞን ቤተክርስትያን የምትገኘው በግሪክና በቱርክ መካከል ነው::  ይች ከተማ ጌታ እንደገለጸው የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ነው ያለው::  በጣኦት አምልኮ የተበከለ ወይም ባህላቸውየሆነ ነው::  እነዚህ ክርስትያኖች በለአም እስራኤልን እንዳሳተና 24ሺው እንዳለቀበት ዘመን ያለ ቁጣን የሚያመጣ ነው:: እንዲሁም ደግሞ የኒቆላውያንን ትምህርት የሚከተሉም ነበሩባት ቤተክርስቲያንዋ::   ጌታ እንደመልእክቱ ፀኃፊ እራሱን የጠራው በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል፦ ነው ያለው ይህ ውጊያና ቁጣም እንዳለበት ያሳያል:: አንዳንዱ ስለክርቶስ ህይወቱን ያጣል ሌላው ደግሞ ተመሳስሎ ለመኖር ያመቻምቻል::  ጌታ ሁሉንም ያያል!

ከዓለም ጋር ወዳጅነትን እንድመሰርት ጌታ አይፈልግም እራሳችንን ከዓለም እንለይ እንደሱ እንደሚሆኑት አንሆንም እኛ የምንወደውና የምንኖርለት ጌታ አለን:: ስለዚህ ንስሀ ግቡና ተመለሱ ነው የተባሉት::  ዛሬም መልክቱ ይኼው ነው::  ህይወታችንን እንይና እናስተካክል::

ይህንን ላደረገው ከህይወት መና ይበላል ያለው የህይወት መና እራሱ ጌታ ነው:;  ነጭም ድንጋይ በላዮ የተፃፈበት ይቀበላል ይላል ይህ የሮማውያን የዘመኑ ሽልማት ነው በጊዜው ያለውን የሚገባቸውን ምሳሌ ነው የሚነግራቸው::  ሽልማት በሰማይ አለ ለእያንዳንዳችን  ተዘጋጅቷል እንበርታ!  

ጆሮ ያለውይስማ!

የዮሐንስ ራእይ 2: 18-19

18፤ በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻስናካፍል

19፤ ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።

ትያጥሮን ቤተክርስቲያን ሊድያ ሐዋ 16:14 የመጣችበት ከተማ ነው:: ይህች ከተማ በንግድ የታወቀች ናት::  የተለያዩ ነገሮችን ያመርታሉ ወደ ፊልጲስዮስና ሌሎችም ስፍራ ይነግዳሉ::  ሊድያ ሀር ሻጭ ነበረች::  

ስለ መልእክቱ ላኪ መግለጫ ስናይ:-

– እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት – ይህ የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚያሳይ ነው::

– በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት – ምንም የሚያቆመው የለም::

– የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፦ እስከአሁን እራሱን የሰው ልጅ እያለ ይጠራ ነበር እዚህ ጋር ግን የእግዚአብሔር ልጅ ብሎ ነው እራሱን የጠራው::  ክብሩን ያሳያል! ይህንን ሁሉ ለምን መግለጽ አስፈለገው ብለን ስንል በመልክቱ  ውስጥ ማንነቱን ማሳየት ያለበት መልክት ስላለ ነው::  በመካከላቸው እርሱን እንዳይከተሉ የሚያደርግ ሰው ስላለ::

ይህች ቤተክርስትያን የተመሰገነችበት ብዙ ነገር አለ

ሥራህንና 

ፍቅርህን 

እምነትህንም 

አገልግሎትህንም 

ትዕግሥትህንም 

ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።

ይህ ሁሉ መልካም ነገር ያላትን ቤተክርስቲያን እንትወቀስ ያደረጋት ምን ይሆን?

ስለበዛልን ነገር ሁሉ ጌታን እናመስግን::  ህብረት ቢሆን ፍቅር ቢሆን ይኸው ቃሉን ማንበብ ቢሆን::  የኤፌሶን ቤተክርስቲያን የተወቀሰችው በፍቅርዋ መቀነስ ብቻ ነው እነዚህ ደግሞ ብዙ የበዛላቸው ናቸው::  ጌታ ይመጣልና እንዘጋጅ::

የዮሐንስ ራእይ 2: 20-29

20፤ ዳሩ ግን፦ ነቢይ ነኝ፡ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤

የትያጥሮን  ቤተክርስቲያን ቅዱሳን በብዙ የተጉ ከፊት ይልቅ ስራው የበዛላቸው ነበሩና ጌታም ያላቸው 

ራእይ 2: 24፤ ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፥

25፤ ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ።

ዳሩ ግን ይህች ነብይ ግን በዚሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙዎችን እያሳተች በእግዚአብሔር ላይ አመጽን ታለማምዳለች::   ልክ ኤልዛቤል በእስራኤል ላይ አመጽን እንዳመጣችውና ኤልያስ ዝናብ እንዳይዘንብ ለ3 ዓመት ሰማይ ተዘጋ::  አገሩ ሁሉ ከእርስዋ የተነሳ ተቀጣ:: በአካብ ዘመን የእግዚአብሔር አገልጋዮች ለእስዋ አማልክት አገልጋዮች ሆኑ እስራኤል አመነዘረች::

ይህችም ሴት ይህንኑ ነው ያደረገችው የጠለቀ የአጋንንት ስራ ውስጥ ገብታ የምትተነብየውም በዚሁ በክፉ መንፈስ ነበረ::  የሐዋርያት ሥራ 15

28-29፤ ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።

ቃሉ እንደሚለው እኛና መንፈስ ቅዱስ ይህንን ወስነናል ብሏል ይህ ትእዛዝ ነው ለእኛ::  ከቃሉ ውጪ የሆነ ትንቢት ይቅርብን በዙሪያችንም ያሉትን እንመርምር  ትንቢት ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለምና::  የጌታ ፍርድ በዝች ሴት ላይ በአልጋ እጥላታለሁ የሚከተሏትንም ንስሀ ካልገቡ በታላቅ መከራ ውስጥ ይገባሉ::  ማየት ያለብን ነገር ጌታ ታግሷታል ንስሀ እንድትገባ እርስዋ ግን አሻፈረኝ አለች ስለዚህ እራሱን የእግዚአብሔር ልጅብሎ የጠራው ለዚች ቤተክርስቲያን ሲጽፍ ምክንያቱ ስልጣኔን የሚጋፋ አለ ማለቱ ነው::  ክብር ሁሉ የሚገባው ጌታ ነው::  

ያላችሁን ጠብቁ ሲል ይህ ለዛሬ ለእኛም ነው::  ሰው ይሰለችና  መጸለዮንም በቃል መሞላቱንም ችላ ይልና ህይወቱ ለብ ወደማለት እየሄደ መሆኑን አይገነዘብም ለብ ካልን ልተፋህ ነው እንደሚከተል እንወቅ መቅረዛችን ከሚወሰድ እንትጋ:: 

ሁልጊዜ እንትጋ የጌታ ነገር አያርጅብን::  ህብረትን ከቅዱሳን ጋር እናድርግ እርስ በእርሳችንም እንበረታታ::

ድል ለሚነሳው ሽልማት አለ ይላል ጌታ!

ጆሮ ያለው ይስማ!

ማራናታ

የዮሐንስ ራእይ 3: 1

1፤ በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል፦ ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል።

ለሰርዴስ  ቤተክርስቲያን መልክቱን ሲልክ ጌታ እራሱን የጠራበት ስም:- ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት ብሎ ነው::  አጠራሩ መልእክቱን ይወስነዋል ለምን ስለ መንፈስ ቅዱስና ስለ ቤተክርስቲያኑ አነሳ? በሌሎቹም ቤተክርስቲያኖች እራሱን በተለያየ ማዕረግ ነው የሚጠራው ሽልማቱም ይለያያል::  

ይህን ያለበት ምክንያት ስንመለከት ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል። ህያው ሆኖ መሞት ስም ብቻ?!  ምን አይነት አገላለጽ ነው?  ስራህን አውቃለሁ ከኔ የተሰወረ አይደለም እያላቸው ያለው ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ነው::  እያየን ነው ጌታ::

እዚህ ቤተክርስቲያን ያሉት ቅዱሳን ያሉ ይመስላሉ እንጂ የያዙት ስም ብቻ ነው ድሮ ብርቱ ሆነው ሊሆን ይችላል ዛሬ ግን ሙት ሆነዋል:: ፕሮግራሞች ይደረጉ ይሆናል ግን ጌታ ሲያይ ሞተሀል እያለ ስለሆነ የሚያስፈልጋቸው የመንፈስ ቅዱስ ጉብኝት ነው::  

ትላንትና የኖርነው ኑሮ ለዛሬ ዋስትና አይደለም ዛሬ ተግተን መገኘት አለብን አለዛ የሞተ ተብሎ ነው የሚጠራው በጌታ ፊት:: ይህች ቤተክርስቲያን የስህተት ትምህርት ወይም መከራ የለባትም በርቱ አይዟችሁ ሲባሉ አናይም ጠላትም አይዋጋቸውም ስላልተዋጉት:: ከሞቱ የሚፈለገው እርሱ ነው ለምን ይዋጋቸዋል ያሉ መስለው መጥፋታቸውን ስላወቀ ትቷቸዋል ጠላትም::  ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ!!!

መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

አቤቱ እርዳን መዳናችንን ዕለት ዕለት እንድንፈጽም!  አሜን

የዮሐንስ ራእይ 3

2፤ ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና።

3፤ እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።

ጌታ ያለንበትን ሁኔታ ያውቃልና ለሚናገረን ነገር ልብ እንስጥ::  ይህንን ራዕይ ጌታ እንድንማርበት በቃሉ ሲሰጠን ከዚህ አይነት ስህተት እንድንጠበቅና እንድንነቃ ነው::  የትኛውም ቤተክርስቲያን ወይም አማኝ በነዚህ መልክቶች እራሱን መመርመር ይችላል::  ሆስፒታል ስንድ ሃኪም ኤክስሬ ወይም ደም እንድንሰጥና ያለውን ችግር  ለማወቅ እንደሚጥር ጌታም ይህንን ቃል እራሳችንን እንድንመረምርበት ሰቶናልና በቃሉ እውነት ተረድተን ህይወታችንን እናስተካክል::

ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ 

እንዴት ያስደነግጣል?! እንዴት ነው ፍጹም የሚኮነው?! ወደቀደመው ነገር በመመለስ እዚህ ጋር ጌታ የሚያስታውሳቸው እንዴት ወደጌታ እንደመጡ ነው::  ወደነው እሺ ብለን ፈልገነው መተን ታድያ ዛሬ ምን ነካን ነው መልክቱ:: የነቃህ ሁን ይላልና ቃሉ እንንቃ እኛ ህያዋን ነን::  ከዚህ ዓለምም አይደለንምና ለጌታ እንገዛ:: 

ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና።  ፈጽሞ ከህይወት መንገድ አትውጣ እንደ ሌባ እመጣለሁና ጊዜ አለኝ ብለህ አትዘናጋ አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ!  ተመለስ ነው መልእክቱ መመለስ ያለብን ነገር ይኖር ይሆን?

ማንም ቢደክም  ጌታ ወድያው ለመፍረድ አይደለም የሚነሳው የሚለን ንስሀ ግቡና ተመለሱ ነው::  ዛሬ ቀን ሳለ እራሳችንን እንመርምር::

እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ ነው መልእክቱ ሊረዳን ይፈልጋል:: 

የማቴዎስ ወንጌል 25

13፤ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።

እንንቃ!!  

የዮሐንስ ራእይ 3

2፤ ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና።

3፤ እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።

ጌታ ያለንበትን ሁኔታ ያውቃልና ለሚናገረን ነገር ልብ እንስጥ::  ይህንን ራዕይ ጌታ እንድንማርበት በቃሉ ሲሰጠን ከዚህ አይነት ስህተት እንድንጠበቅና እንድንነቃ ነው::  የትኛውም ቤተክርስቲያን ወይም አማኝ በነዚህ መልክቶች እራሱን መመርመር ይችላል::  ሆስፒታል ስንድ ሃኪም ኤክስሬ ወይም ደም እንድንሰጥና ያለውን ችግር  ለማወቅ እንደሚጥር ጌታም ይህንን ቃል እራሳችንን እንድንመረምርበት ሰቶናልና በቃሉ እውነት ተረድተን ህይወታችንን እናስተካክል::

ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ 

እንዴት ያስደነግጣል?! እንዴት ነው ፍጹም የሚኮነው?! ወደቀደመው ነገር በመመለስ እዚህ ጋር ጌታ የሚያስታውሳቸው እንዴት ወደጌታ እንደመጡ ነው::  ወደነው እሺ ብለን ፈልገነው መተን ታድያ ዛሬ ምን ነካን ነው መልክቱ:: የነቃህ ሁን ይላልና ቃሉ እንንቃ እኛ ህያዋን ነን::  ከዚህ ዓለምም አይደለንምና ለጌታ እንገዛ:: 

ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና።  ፈጽሞ ከህይወት መንገድ አትውጣ እንደ ሌባ እመጣለሁና ጊዜ አለኝ ብለህ አትዘናጋ አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ!  ተመለስ ነው መልእክቱ መመለስ ያለብን ነገር ይኖር ይሆን?

ማንም ቢደክም  ጌታ ወድያው ለመፍረድ አይደለም የሚነሳው የሚለን ንስሀ ግቡና ተመለሱ ነው::  ዛሬ ቀን ሳለ እራሳችንን እንመርምር::

እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ ነው መልእክቱ ሊረዳን ይፈልጋል:: 

የማቴዎስ ወንጌል 25

13፤ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።

እንንቃ!!  

የዮሐንስ ራእይ 3: 4-6

4፤ ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።

5፤ ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ።

በሰርዴስ ቤተክርስቲያን ያልረከሱና ስም ብቻ ያልሆኑ በቅድስና የሚመላለሱ ጥቂት ቅዱሳን  አሉ::  ለእነርሱ ልብሳቸውን ላላረከሱት የሚላቸው የተገባቸውም ስለ ሆኑ!  ዋዉ የተገባቸው!  ምንድነው የሚገባቸው? 

ነጭ ልብስ መልበስና  ከእርሱ  ጋር መሄድ።  ይህ ነጭ ልብስ እራሱ እየሱስ ነው አዲሱን ሰው ልበሱ ተብለን የለም?  እንዲሁም ደግሞ በራዕይ መጽሐፍ ላይ እነዚህ ነጫጭ የለበሱ እነማን ናቸው ከተባሉት ውስጥ ናቸው ::  እኛም ነጩን ልብስ ለብሰን እንገኝ እርሱ በእኛ ይክበር ይንገስ::  

ሌላው ደግሞ የሚላቸው ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በስማችን የሚያውቀን እረኛ ስማችንን በህይወት መጽሐፍ  ጽፎታል አቤት እንዴት ያለ መወደድ ነው?! እኔ በስም ታውቄ ስሜ በበጉ መጽሐፍ ላይ ተጽፏል!  ምን እላለሁ አሁንም እገዛልሀለሁኝ አባት ሆይ::

በዚህም ብቻ አያበቃል የሚገባላቸው ቃል በመጨረሻ  በነጩ ዙፋን ፍርድ ጊዜ እየሱስን አውቃለሁ  እርሱ ነው ጽድቄ ብለን ስንመልስ አብ ወደ እየሱስ ነው የሚያየው እየሱስም እንዳላቸው በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ አለ::  የእርሱ ምስክርነት አውቃታለሁ የሚለው እዚህ ምድር ላይ በእርሱ ሳናፍር ከመሰከርን እርሱም በሰማይ ይመሰክርልናል:: የተቀሩት ሞታችኃል የተባሉት የህይወትን መንገድ ትተው በምናለበት ብዙ ነገር እየቀላቀሉ ስለመጡ ነው:: ዛሬም ጸንተን ቆመን ለስሙ እንመሰክራለን::

ዛሬ ቀን ሳለ ህይወታችን እየሱስን ያሳይ ምስክርነት ወንጌልን መመስከር (ዋና ስራችን ነው) ብቻ ሳይሆን የህይወትም ምስክርነት ሊኖረን ይገባል::  እርሱን በመፍራትና በቅድስና ስንኖር እንዳንተ/እንዳንቺ መኖር እፈልጋለሁ ይላሉ ሰዎች ፍሬ ያለውህይወት እንኑርእርሱንም እናስከብረው::

ጌታ ከሞተ ህይወት ይታደገን ህያው የሆነ የሚታይ ህይወትን በመንፈስ ቅደስ ያድርግልን::

የዮሐንስ ራእይ 3: 7-9

7፤ በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል፦

8፤ ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና።

እራሱን የጠራበትን ማዕረግ ስናይ የዳዊት መክፈቻ ያለው፤  ከዳዊት ዘር ንጉስ አይጠፋም የተባለውን ትንቢት የፈጸመ

የሚከፍት፥  ይህ ንጉስ ከከፈተ ከፈተ ነው

የሚዘጋም የሌለ፤  እርሱ ከፍቷልና ማን ይችላል መዝጋት

የሚዘጋ፥   ከዘጋም ዘጋ ነው

የሚከፍትም የሌለ፤  ይህ ንጉስ ከዘጋ ዘጋ ነው

ቅዱስና እውነተኛ የሆነው:- እርሱ ቅዱስና እውነተኛ መሲህ ነው

ለምን ጌታ ስለ ቁልፍ እንዲሁም ቅዱስና እውነተኛ የሚለውን ማዕረግ እዚህ ስፍራ ላይ ተጠቀመ?  እስከ አሁን ያሉትን ማዕረጎች ስናይ በመጀመርያ ዮሃንስ ካየው ማንነቱ ነው የተጠቀሰው ይህ ግን በምዕራፍ አንድ ላይ አልተጠቀሰም:: የተከፈተ በር ስለሰጣቸው ነው ስለ ቁልፍ የሚናገረው ደግሞም አይሁድ ሳይሆኑ ነን የሚሉ ውሸታሞች ብዙ ነገር ሊልኑባቸው ስለጣሩ ነው::  ማለትም ስታችኃል እኛ ነን የመጀመሪያዎቹ የእግዚአብሔር ህዝብ::  ነገር ግን ጌታ መሲህ እንደሆነ እራሱን እውነተኛና ቅዱስ ብሎ ይጠራል::  በተጨማሪም የሞትና የሲኦልን ቁልፍ የያዘ እርሱ እንጂ እነዚህ ሰዎች የሚሉት አይደለም የሚሆነው::  እንዴት ደስ ይላል ማንም በእኛ ህይወት ላይ አይወስንም የሚወደን ጌታ እንጂ!!!  ስሙ ይባረክ!  ስራህን አውቃለሁ የምትለው በሁሉ ቤተክርስቲያን የተጠቀሰ ነው ዛሬም ስራችንን ያውቃል:  ይመረምራል ለእርሱ ታማኝ እንሁን!

የዮሐንስ ራእይ 3: 12

12፤ ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።

የፊላደልፍያ ቅዱሳን በመከራ ውስጥ እያለፉ በመሆናቸው ጌታ ምንም ሲወቅሳቸው አናይም ነገር ግን ያላችሁን እስክመጣ ጠብቁ ነው የተባሉት::  ሰው ይሰላችና ካለበት ነገር ሳያስበው እየተንሸራተተ ስለሚሄድ ነው ያለህን ጠብቅ የሚለን ጌታ::  

ይህንን ሁሉ አልፎ ድል ለነሳ ሽልማቱ ጌታ የሚገባላቸው ቃል :-

1.  በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤  ዓምድ የሌለው ቤት የለም ያለ ዓምድም ቤት አይቆምም ቃል እየገባላቸው ያለው እርግጠኛ ሁኑ የዓምዱን ያህል በቤቴ መሆናችሁ አይቀርምና::  ከዚያም ከቶ ማንም አያወጣም::  ፈተናቸው ከአይሁድ ነበረና እኛ የምንላችሁን ካላደረጋችሁ አትድኑም ወይም የእግዚአብሔር መሆን  አትችሉም የሚሉ ስለነበሩ የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ ከሆነው ነው የስራው ባለቤት:: ዛሬም ጌታ እንድንጸና እንዲሁም የምንወርሰውን እንወቅ::

2.  የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።  ይህንን ስም ማንም አያውቀውም ግን ይህንን ስም በእኛ ላይ ይጽፈዋል:: 

ተስፋችን ህያው ነውና እንጽና ያለንንም ተግተን እንጠብቅ::  ጌታ ይመጣል::

የዮሐንስ ራእይ 3: 14-16

14፤ በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦

15፤ በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር።

16፤ እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።

ለሎዶቅያ ላይ የተገለጠበት ማዕረግ:- 

1. አሜን የሆነው፥ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ሁሉ የተገለጠበት ጌታ በእርሱ ዘንድ አሜን ነው::

2. የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥  እየሱስ ነው እውነተኛና የታመነ ምስክር ስለ አባቱም የተረከልን አባቱንም በእርሱ ውስጥ አሳየን::  የአብንም ስራ በእርሱ ውስጥ አየን:: የእየሱስ ምስክርነግ እውነተኛ ነው:: 

3. በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው:: የዮሐንስ 1: 1፤ በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።  ጌታ እየሱስ ፍጥረት አይደለም ሁሉ ሲፈጠር ቭን ያለእርሱ የተፈጠረ የለም:: እርሱ አልፋና ኦሜጋ ነው::

እንግዲህ እንዲህ ባለው እውነተኛና የታመነ ምስክር ፊት የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ምን ትመስላለች? በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር።

እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።

እንዴት ከባድ ነገር ውስጥ ነው ያሉት?! ለብ ያለ ውሃ ማን ይፈልጋል? ለጌታ የሚያቀርቡለት ህይወትና አምልኮ ምንም የሚጋብዝ አይደለም::  ለብ ያለ ነው:: ለመዋጥ አይቻልም መትፋት እንጂ!  የሚገርመው ልተፋህ ነው ብሎ ያስጠነቅቃል ምን አይነት ፍቅር ነው? ማንም እንዲጠፋበት የማይፈልግ ጌታ::  ይህች ቤተክርስቲያን ከመንፈስ ቅዱስ እሳት ወጥተዋል ግን አላስተዋሉም ያለ መንፈስ ቅዱስ መመላለስ ወደ ለብታ ነው የሚያመጣው::

ለእኛም ዛሬ የሚቀርልን ነገር ይህ ርሁሩህ ጌታ ህይወታችንን እንድናይ ይፈልጋል::  እንደው እንደነገሩ ነው ጸሎታችን? አምልኳችን?  ለነፍሳትን ግድ ይለናል? ወይስ የሌሎች ስራ ነው?  ቸልታ ማለት ለብታ ነው::  በመንፈስ ቅዱስ እየተቀጣጠልን ነው ወይስ የራሳችንን እስት እያቀጣጠልን?  እርሱ አንዳች ጎሎት በሰው አይደገፍም:: በአካሉ ውስጥ ምን እያደረግን ነው?  ጌታ ስራህን አውቃለሁ እንዳለ ስራችንን ያውቃል::  በመንፈስ እንቀጣጠል::

የዮሐንስ ራእይ 3: 17-18

17፤ ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም፡ የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥

18፤ ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።

የጌታ እይታና የሰው እይታ ልዩነቱን እናያለን::  

ይህች ቤተክርስቲያን የምትለው:- 

ሀብታም ነኝ

ባለጠጋ ሆኜአለሁ 

አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም፡ ነው

በጌታ እይታ ደግሞ

ጐስቋላ

ምስኪንም 

ድሀም 

ዕውርም 

የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥

የሆነችውን ያላወቀች ቤተክርስቲያን ናት ዛሬ ጣታችንን ወደዝች ቤተክርስቲያን እንጠቁም እንጂ መልክቱ ለአንባቢው ሁሉ ነው::  ምንድነው ያላወቅነው ነገር?! ድሀ ሆነን ሳለ ሀብታም ነን የምንልበት ጉዳይ በምድራዊው ነው እራሳችንን የምንለካው?  ወይስ በማያልፈው በጌታ ቃልና በመንፈሱ ነው እራሳችንን የምንመረምረው?  ጸጋውን ይስጠንና እራሳችንን እንይ ምክሩንም እንስማ::

ይህወታችንን እንደቀልድ የምንይዘው ጉዳይ አይደለም::  እነሱን የመከረው ለኛም ይጠቅማል::  መፍትሄ ሳይሰጥ ችግር ብቻ ገልጦ አይሄድም የእኛ ጌታ አላማው መርዳት ስለሆነ:: ማነው ከእኛ መካከል እርቃኑን ወቶ የሚሄድ?  አሳቡ እንኳን ይዘገንናል እንኳን ተፈጽሞ ማየት ታድያ እንዲሁ ቶሎ እርምጃ መውሰድ አለብን እራቁትነታችንን ካሳየን በመንፈስ::

ምክሩም:- ባለ ጠጋ እንድትሆን (የምድሩን እንርሳውና):- 

በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ 

እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።

ልብሱንም እንድንለብስ ነጩ ልብስ ተሰቶናል እንደወርቅ የሚፈተነውን እምነታችንን እንድናንነሳ ይፈልጋል አይናችንንም እንድንኳል::  ይህ ሁሉ ግዛ የሚለንን ኑና በነጻ ግዙ ብሎ ያወጀውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በልግስና ሳይሰስት የሚሰጠውን እንቀበል::  በራሳችን አንዳች ማድረግ አንችልምና ዕለት ዕለት መንፈስ ይሙላብን:,  

አሜን!

የዮሐንስ ራእይ 3: 19-22

19፤ እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ።

20፤ እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።

እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ። ለብ ላለችው ቤተክርስቲያን የሰጣት ተግሳጽ ምክሬን ስሚ ደሀ ነሽ ተራቁተሻል ነው ከዛም ሲበዛ በደጅ መሆን ነው::  ለሰው ከእርሱ መለየት የባሰ ቅጣት ይኖር ይሆን?!  እኔ የለም ባይ ነኝ!  ጌታ ወቷል እኮ ከመካከላቸው ግን አላስተዋሉም::  ፕሮግራም እየቀጠለ ነውግን ተመላኪውየለም:: ማስተዋል ይሁንልን::

አንድ እንኳን አያስፈልገኝም የምትለው ሎዶቅያ ጌታዋን ውጪ አድርጋ ነው::  ምን አላት ታድያ?!   በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ የሚጠቀሰው ለአዲስ ሰው ሆንዋል ጌታ ግን ለቤተክርስቲያን በስሙ ለተጠሩት ነው የተጠቀመው::  የሚፈልገው ህብረት ነው::  እራት መብላት ከእኛ ጋር ጊዜን ማሳለፍ ነው የሚፈልገው::  ቁርስ እበላለሁ ቢሆን ወደ ጉዳያችን ወደ ስራ ለመሄድ ልባችን የተነሳ ይሆንና ብዙ ጊዜ ላንሰጥ እንችላለን እራት ግን የምንቸኩልበት ጊዜ አይደለም ቁጭ ብለን ከእርሱ ጋር ጊዜ እንድናሳልፍ የተመቸውን ጊዜ ነው የመረጠው::

የጌታ ፍቅርይገርማል በደጅ ቢሆንም ለመግባት ያንኳኳል እንጂ መብታችንን ጥሶ ልግባ አይልም::  መገዛት በውድ እንጂ በግድ አይደለም::  እንደዚህም ሆኖ መልእክት ከመላክ አልቦዘነም::  አረ አስተውሉ እያለነው::  እራሳችንን ብንመረምር ባልተፈረደብንም ነበር ይላል ቃሉ::  ክርስትና ከክርስቶስ ጋር ህብረት ነው::  ከእርሱ ጋር ህብረትን ስናደርግ ከቅዱሳንም ጋር ህብረትን እያደረግን ጸጋን እንከፋፈላለን::  

የምናገኘው ሽልማት:-

21፤ እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።  አሜን

ጆሮ ያለው ይስማ!!

የዮሐንስ ራእይ 4: 1-7

2፤ ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤

4፤ በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።

በዝች አጭር ባለ11 ቁጥር ምዕራፍ ውስጥ ስለዚህ ታላቅ ዙፋን 12 ጊዜ ተጠቅሷል::  እንድናውቅ የተፈለገው በሰማይ ስላለው የዙፋኑ ክፍል ንው::  የተከፈተ በር ውስጥ ነው የገባው ዙፋኑ  ወዳለበት::  ስለዙፋኑና እንስሳቱ ጥልቅ የሆነ ነገር በአእምሮ ለመሳልና ለመረዳት የሚከብድ ነው ደስ የሚለው ስንሄድ እናየዋለን ዛሬ ግን ምን እንወቅ? 

በዙፋኑ  ላይ አምላካችን አለ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ምን አይነት ቤት ሰርቶ እየጠበቀን ይሆን? ዓይን ያላየው  ጆሮም ያልሰማው አይደልየተባልነስ ስፍራ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ትሆናላችሁ ብሎናል::  እንዴት አስውቦ እንደሚሰራው ማሰብ ነው::  ሁን ሲለው ሁሉ ይፈጠራልና::

ሌላው 24 ዙፋኖችና የተቀመጡባቸውም አሉ ነጭ የለበሱና የወርቅ ዘውድ የጫኑ ማንነታቸው ካልተገለጸ ልገምት አልነሳም ስሄድ አያቸዋለሁ::  እንግዲህ ይህንን ጌታ እንዴት እናምልከው?  ምን አይነት መስዋትስ ይቀበላል?  እራሱ በሰራው ስፍራ ከብሮ ያለው ጌታ ከእኛ የሚፈልገው የተሰበረ መንፈስና የልብ ትህትናን እንዲሁም ቃሉን ማክበርን ነው::

ትንቢተ ኢሳይያስ 66

1፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው?

2፤ እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።

ይህንን ጌታ ልናመልክ ተጠርተናል!  እናመልክሃለን አምላካችን ሆይ አንተ ትልቅ ነህ ተባረክ!!  በዙፋንህ ከብረህ ላለኸው ለአንተ ክብር ይሁን! አሜን!

የዮሐንስ ራእይ 4: 8-11

8፤ አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም፥ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፤ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። 

9፤ እንስሶቹም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘላለምም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ፥

10-11፤ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፦ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፦ ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል፡ እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ። 

በቀንና በለሊት ሳያቋርጡ  ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም፥ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፤ እያሉ ያመልኩታል።  አምላካችን አምልኮ አይጎድልበትም!  ሁሌም ይመለካል::  

አምላካችን:-

 – የነበረው

–  ያለ 

– የሚመጣ፥ 

–  ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፤ እንደሆነ እንወቅ::  

እንስሶቹ እንዲህ ብለው ሲያመልኩት 24ቱ ሽማግሌዎችም ተቀላቀሉና አክሊላቸውን በዙፋኑ ፊት አድርገውና በዙፋኑም ፊት ወድቀው እየሰገዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው፦ 

– ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ 

– አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና 

– ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና 

– ተፈጥረውማልና 

ስለዚህ:- 

ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል፡ እያሉ ሰገዱ። 

አሜን ይህ የዘላለም ጌታ ድሮም ዛሬም ወደፊትምያለ ጌታ አምልኮ ስግደት ሊቀበልይገባዋል::  እርሱ ሁሉን ፈጥሯል ሁሉ ደግሞ ያልፋል ዘላለማዊዉ ኑሮ በላይ በሰማይ ነው የዚህ ምድር ነገር ግን ቀሪ ነው::  ልባችንንም አይናችንንም በዚህ ጌታ ላይ አድርገን በፊቱ በመገዛት እንመላለስ እናምልከው እናወድሰው ስለሚገባው:: እውቅና ለሚገባው እውቅናን እንስጠው::

ሃሌሉያ!

የዮሐንስ ራእይ 4: 8-11

ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም፥ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፤ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። 

ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ፦ ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል፡

ይህንን አምልኮ ስናይ እዛ መካከል አሁን መገፕት ያሰኛል::  ይህ ጌታ ቅዱስ ነው ብቻ ብለው አይደለም እያመለኩት ያሉት ቅድስና ከኃይል ጋር  ያለውና ሁሉን የሚገዛ እያሉ ነው የሚሉት::  መቼ መቼ ነው የሚያመልኩት? ያልን እንደሆነ በቀንና በለሊት አይቋረጥም ::  ኢሳያስም ይህንኑ ነው የሚነግረን አንዱ ለአንዱ ቅዱስ ነው እያለ ይነግራል::  አይገርምም!!  ዛሬውኑ ማምለክን ካልተለማመድን እንዴት ልንሆን ነው ሰማይ ስንሄድ?!  ይህንን ሁሉን የሚገዛ አምላክ ሳናቋርጥ ልናመልከው ይገባዋል!!  እርሱ አምልኮ የተገባው ነው!!

ደግሞም ሁሉን የፈጠረ አላመልክም የሚለውንም የፈጠረውና እንደፈቃዱ ያደረገው እርሱ ነው::  በምድር ገዛን ያሉ ሁሉ ጊዜያዊ ሲሆኑ የእኛ ጌታ ግን ለዘላለም ይገዛል:: ስለዚህ ሽማግሌዎቹም:-

አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና 

ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና 

ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል፡

አሜን!

ስለዚህ ዓለምና ሞላዋ በውስጥዋም ያለው ሁሉ የጌታ ነውና ፍጥረት ሁሉ ሊያመልከው ይገባል::  አንድም ፍጥረት በፈቃዱ አልመጣም ፈጣሪው እግዚአብሔር ፈጠረው እንጂ!  አምላካችን ትልቅ ነው::

የተፈጠርነው እርሱን ለማምለክ ነው በሰማይም የሚጠብቀን ይህ አምልኮ ነው ሌላው የአገልግሎት ዘርፍ ሁሉ ይታጠፋል::  እናምልከው ስለሚገባው!

የዮሐንስ ራእይ 5: 1-2

1፤ በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ።  2፤ ብርቱም መልአክ፦ መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ።

ይህ መጽሐፍ ምንድነው? በአብ እጅ በሰባት ማኅተም የታተመ? ልክ እንደ ዮሃንስ ሁሉ ህዝቅኤልም አይቷል  የተጻፈበትንም ነግሮናል:: በሕዝቅ 2: 10፤ በፊቴም ዘረጋው፥ በውስጥና በውጭም ተጽፎበት ነበር፤ ልቅሶና ኀዘን ዋይታም ተጽፎበት ነበር።  የሚገርመው በፊትም በኃላም ነው የተጻፈበት::

ይህ መጽሐፍ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ይዘጋ ተብሎ ተዘግቷል:: በዳንኤል 12: 

4፤ ዳንኤል ሆይ፥ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል።

ብርቱም መልአክ፦ መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ።

ብርቱ የሆነው መልአክም መፍታት አይችልም:: አዋጅን ግን አወጀ ማኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን? ብሎ::  እኛን ሊታደግ ከዚህ ፍርድ ሊያወጣ ማንም አልቻለም::  ማንም መብትም ብቃት የለውም::  መዳናችን እንደው እንደቀልድ የምንይዘው አይደለም የከበረ መሆኑን እንረዳ::

ስለዚህ የከበረ ደህንነት ጌታን እናክብረው::

የዮሐንስ ራእይ 5: 3-5

3፤ በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም።

4፤ መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ።

5፤ ከሽማግሌዎቹም አንዱ፦ አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል፡ አለኝ።

በሰማይም በምድርም ከምድርም በታች ይህንን መጽሐፍ ሊፈታ አይደለም ሊመለከተው እንኳን ማንም አልቻለም::  ማህተሞቹን ሊፈታ የተገባው ማን ነው? ብሎ ነው መልአኩም እየጠየቀ ያለው::  ብርቱ ጉልበተኛ ወይም ባለስልጣን አይደለም ጥያቄው የተገባው ማን ነው::  ይህንን ለማድረግ የሚችል ባለመብት ማነው ነው ጥያቄው::

ማንም ባልተገፕ ጊዜ ዮሃንስ አለቀሰ ይህ የሚያሳየው በሰማይ ሁሉም እንዴት  ባለ ጭንቀት ውስጥ እንደነበሩና  ዮሃንስም ራዕይ ብቻ ሳይሆን እያየ ያለው እየተካሄደ ያለ ሴረሞኒው ላይ እንደተገኘ ነው::  በእግዚአብሔር ቀን በመንፈስ ነበርኩ እንዳለው ማለት ነው::  እርሱም እየተካሄደ ባለው ስርአት ውስጥ ተካፋይ ነበረ::

ማንም አልተገኘም ማህተሞቹን ለመፍታት የተገባው::  ከሽማግሌዎቹም አንዱ፦ አታልቅስ፤ እነሆ፥

1. ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም 2. የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል፡ አለኝ።  ሃሌሉያ!!!!!

ሃሌሉያ!!!!!  ሃሌሉያ!!!!!  ሃሌሉያ!!!!!

ድል የነሳው ጌታ እንዴት የተገባውሆነ ብለን ብንል:- ያዕቆብ ልጆቹን ሲባርክ ይሁዳን (የይሁዳ አንበሳ ያስባለውን እናገኛለን)

ኦሪት ዘፍጥረት 49

8፤ ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ።9፤ ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከአደንህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፤ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል?

10፤ በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል።

የዳዊት ስር :-

ትንቢተ ኢሳይያስ 11

1፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል። 10፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል።

የሐዋርያት ሥራ 13

22፤ እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም፦ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፡ አለ። 23፤ ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።

እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለደህንነታችን እየሰራ ነበረ እንጂ የይድረስ ይድረስ ወይም አጋጣሚ የሚባል ነገር የለም ገና በዘፍጥረት 3 ላይ እመጣለሁ እንዳለ ይህ የተገባው ጌታ ትንቢቱንና የሰጠውን ቃል ፈጽሞ በመካከላችን መቶ ድል በመንሳት ታደገን! ስሙ ይባረክ!!

የዮሐንስ ራእይ 5: 6-8
6፤ በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፥ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።
7፤ መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው።
8፤ መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።

ከሽማግሌዎቹ አንዱ ለዮሃንስ አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል፡ አለው:: ይህንንም የይሁዳ አንበሳ ሲመለከት ያየው አንበሳ ሳይሆን እንደታረደ በግ ሆኖ ነው ያየው::

ይህም በግ ለየት ያለ አቋም ነው ያለው:- – ሰባትም ቀንዶችና

  • ሰባት ዓይኖች ነበሩት

እነዚህ ዓይኖች ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። ተመሳሳይ ነገር እናያለን በዘካርያስ 4: 10፤ የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? እነዚህ ሰባቱ ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፤ እነዚህም በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸው።

በግ ስናይ መሸነፍን እንዳናስብ እንደአንበሳ ሆኖ ባይሰባብር እንደበግ ሆኖ መስዋአት ሆኖ ድል ነስቷል:: ስሙ ይባረክ:: ስለዚህም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው እጅ መጽሐፉን ወሰደ ማኅተሞቹንም ፈታ:: ሃሌሉያ!!!

ለዚህ በግ የቀረበው አምልኮ:- ሁሉም በፊቱ ወደቁ አራቱ እንሰሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ከዛም በእያንዳንዳቸው እጅ በበገና የታጀበ የቅዱሳን ጸሎት ነው ያቀረቡለት:: እንዴት ደስ ይላል?! ዛሬ በሚቀርበው እጣን ውስጥ የእያንዳንዳችን ጸሎት በፊቱ ይቀርባል:: ሃሌሉያ! በፊቱ ተቀባይነት አለን ጸሎታችንም ይሰማል:: ጌታ አይንቀውም እንደእጣን በፊቱ ይቀርባል::

ድል ለነሳው ለታረደው በግ አምልኮና ክብር ይብዛለት! አሜን

የዮሐንስ ራእይ 5: 9-14


9-10፤ መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ፡ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።
11፤ አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፥
12፤ በታላቅም ድምፅ አሉ፦ የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል።
13፤ በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ፦ በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን፡ ሲሉ ሰማሁ።
14፤ አራቱም እንስሶች፦ አሜን አሉ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።

የብርቱው መልአክ ጥያቄ ማነው የተገባው ማኅተሙን ሊፈታ ነበረ መልሱንም በአዲስን ቅኔ ዘሙሩ :-

መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥
ለምን ተገባው?

  • ታርደሃልና፥ ጌታ ስለታረደ ይገባዋል
  • በደምህም ለእግዚአብሔር
    ከነገድ ሁሉ
    ከቋንቋም ሁሉ
    ከወገንም ሁሉ
    ከሕዝብም ሁሉ – የአብርሃም በረከት ለህዝብ ሁሉ ደረሰ በዘፍ 12:1-3 እንደተናገረው:: ስለዚህ ጌታ በመታረድ የእዳ ጽህፈታችንን አስወግዶ ሙታን የነበርነውን ከእርሱ ጋር አስነስቶ ህያዋን አደረገን:: በፈቃዱም ዋጅቶን ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት አደረገን ይህም ብቻ አይደለም በምድርም ላይ እንነግሳለን፡ ይላል ዝማሬው አይገርምም?! እልፍ አእላፋትም ዘመሩት:: ጌታ ያደረገልን ይገርማል ስሙ ይባረክ::

አምልኮው ቀጠለ:-

በታላቅም ድምፅ አሉ፦
የታረደው በግ
ኃይልና
ባለ ጠግነት
ጥበብም
ብርታትም
ክብርም
ምስጋናም
በረከትም ሊቀበል ይገባዋል።
አሜን!

አምልኮው የመሰለኝ በሰማይ ብቻ ነበረ የሚገርመው ነገር ግን ቃሉ የሚለን ፍጥረት ሁሉ
በሰማይና
በምድርም
ከምድርም በታች
በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ
በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ፦

ይህ ሁሉ ፍጥረት ምን አለ? በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን፡ ሲሉ ሰማሁ። አሜን ይሁንልህ ጌታዬ!


አራቱም እንስሶች፦ አሜን አሉ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ

እንዴት ደስ ይላል ክብርና አምልኮ ሁሉ ለታረደው በግ ይሁን:: አሜን!!!!
ዛሬ አምልኳችንን ወደፊቱ እናምጣ የታረደው በግ የተገባው ነውና::

የዮሐንስ ራእይ 6

1፤ በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ፦ መጥተህ እይ፡ ሲል ሰማሁ።

2፤ አየሁም፥ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት።

በጉ ማኅተሞቹን መፍታት ሲጀምር የመጀመሪያው አምባላይ ፈረስ ወጣ ይላል በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት።

ይህ መልክተኛ ድል እየነሳና ድል ለመንሳት ስልጣን ተሰቶት ነው የወጣው:: በዘካርያስ 1: 7-11 እና  6:1-8 ላይ ተደግሞ እናየዋለን::

ትንቢተ ዘካርያስ 6

5፤ መልአኩም መልሶ፦ እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙበት ስፍራ የሚወጡ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ናቸው።

ስለነፋሳት ስናስብ ፍርድን የሚያሳዮ ናቸው ለምሳሌ 

ትንቢተ ኤርምያስ 49

36፤ ከአራቱም ከሰማይ ማዕዘናት አራቱን ነፋሳት በኤላም ላይ አመጣለሁ፥ ወደ እነዚያም ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከኤላም የተሰደዱ ሰዎች የማይደርሱበት ሕዝብ አይገኝም።

 እንዲሁም 

ትንቢተ ዳንኤል 11

4፤ እርሱም በተነሣ ጊዜ መንግሥቱ ይሰበራል፤ እስከ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ይከፋፈላል። ለዘሩ ግን አይከፋፈልም፥ እንደ ገዛበትም አገዛዝ አይሆንም፤ መንግሥቱ ይነቀላልና፤ ከእነዚህም ለሌሎች ይሆናልና።

ፍርድ ተጀምሯል እግዚአብሔር በጽድቅ ይፈርዳል::

የዮሐንስ ራእይ 6

3፤ ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ፡ ሲል ሰማሁ።

በጉ እነዚህ ማኅተሞች በተፈቱ ቁጥር የሚሆን ነገር አለ::  

የመጀመሪያው ሲፈታ ቀስት የያዘ ፈረሰኛ ወጣ አክሊል ተሰቶት ድል እንዲነሳ ወጣ::

ሁለተኛው ሲፈታ:-   ዳማ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፥ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።

ሶስተኛው ሲፈታ:-እነሆም፥ ጕራቻ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። የምግብም ዋጋ እንዲወደድ የሚያደርግ ነው ከዘይትና ከወይን ውጪ::

አራተኛውም ሲፈታ:- ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።

ይህ ንን የፍርድ ቃል በሕዝቅኤል 14

21፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ይልቁንስ ሰውንና እንስሳን ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ ፍርዶቼን፥ ሰይፍንና ራብን ክፉዎችንም አውሬዎች ቸነፈርንም፥ ስሰድድባት!

አምላካችን እንደዚሁ አይፈርድም ምክንያት ሲኖር እንጂ::  በዘሌዋውያን (26: 18-33) 26: 18፤ እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ።

ፍርድ አለ በክርስቶስ ግን ሆነን ማምለጥና ማስመለጥ አለ የጻድቅ ሰው ጸሎት በስራዋ እጅግ ኃይልን ታደርጋለችና እንበርታ::  እነዚህ አራት ፈረሰኞች እየሰሩ ይሆናል ማየት ያለብን በክርስቶስ ያገኘነውን መዋጀት ነው::  ከምድር  ወደ ሰማይ ቤታችን መሄዳችን አይቅርም::

የዮሐንስ ራእይ 6: 9-17

9፤ አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ።

12፤ ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፥ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፥ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፥

17፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።

በመጀመሪያው የአራቱ ማኅተሞች መፈታት አራት ፈረሰኞችን የተለያየ ፍርድ አስይዞ ሲልክ አምስተኛው ግን ለየት ይላል::  ይኸውም በክርስቶስ ላይ ባለ እምነታቸው  የተነሳ የተገደሉ ቅዱሳንን ነፍስ እናያለን::  እነርሱም በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? ይላሉ::  ጊዜው ገና እንደሆነና እነርሱ ግን ነጭ ልብስ ለብሰው እንዲያርፉ ተደረጉ::  አምላካችን የተሸነፈ ይመስላል ከሞት ልጆቹን ማስጣል ያቃተው ነገር ግን ከፍርድ አያመልጡም የገደልዋቸው:;  እስጢፋኖስን ሊቀበለው ሲነሳ እናያለን ገዳዮቹን ከማባረር ይልቅ::  የጌታ አሰራር ከአእምሮ በላይ ነው:: 

ወደ ስድስተኛው ማኅተም ስንሄድ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፥ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፥ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፥ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፥

ይህንን ቃል የሚመስል ፍርድ በኢሳ 13:1-22 እናገኘዋለን እንዲሁን በኢዮኤል 2:10, 30-31 የምድር ፍጻሜ ላይሆን ይችላል የመንግስት/ የአገር መውደቅ ሊሆን ይችላል:: ኢሳያስ ያየው የባቢሎንን መውደቅ ነበር:: ብርሃንን አያዩም ይሞታሉ ታላላቆቻቸውም ደግሞ ከዋክብት እንደሚወድቁት ይወድቃሉ:: በመሸነፍ ውስጥ የት ልግባ ይላሉ ሹማምንቶቹ ምክንያቱም እግዚአብሔር እየፈረደ ነውና ወዴትም ማምለጥ አይቻልም:: ማንም በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ቢሉም የሚያድን የለም:: አምላካችን ይፈርዳል::

የዮሐንስ ራእይ 7: 1-8

2፤ የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፥ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ፦

3፤ የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ፡ አላቸው።

በዚህ ክፍል ላይ የሚያስገርም ነገር እናያለን እርሱም ንፋሳት ሲያዙ::  እንዴት ንፋስ ይያዛል? !  በምዕራፍ 6 ላይ ያለው መከራ ሁሉ ሲወጣ አይተናል:.  እዚህ ምዕራፍ ላይ ደግሞ ሲዘገዩ::  ምክንያቱም እግዚአብሔር ህዝቡን ሊያትም ፈለገ::  ይህ ሁሉ የጌታን መምጣት የሚያሳይ ነው::  የጌታን መምጣት ወንጌልን በማስፋፋት እንድናፋጥን ተነግሮናልና በሄድንበት ሁሉ ሰዎችን የምናጠምድ እንሁን::

ሌላው በሆል ፉድ እስቶር ውስጥ አንድ ነገር አየሁኝ የእጅ እስካነር ችፕስ ያላቸው ሰዎች እጃቸው ላይ አሉ ማለት ነው ይህ ችፕስ እየተሰጠ ነው ማለት ነው ካርድ ወደፊት አያስፈልግም ማለት ነው::  አይናችን እያየ ቃሉ እየተፈጸመ ነውና ጨርቄን ማቄን የምንልበት ጊዜ አይመስለኝም::  በጌታ ጸንተን በንቃት  ማድረግ ያለብንን እያደረግን እንበርታ::  

እዚህ ክፍል ላይ 144 ሺ ያህል እንደታተሙ እናያለን ምዕራፉን ደግሞ ወረድ ብለን ቁጥር 8 ላይ ማንም የማይቆጥራቸው ይላል::  ስለዚህ በመጨረሻው ዘመን ወደ ጌታ ዘወር የሚሉ አይሁዶች ይሆኑ?  እኛ አሁን በመንፈስ ቅዱስ ታትመናል ይላል ቃሉ:;  አጥፊው በግብጽ ያልፍ የነበረው ደሙን ሲያይ እንደሆነ እንዲሁ ዛሬ የክርስቶስ ደም ማምለጫ ነው ለህዝቡ:: 

ጌታ በደጅ ነው:: ማራናታ!!

የዮሐንስ ራእይ 7: 9

9፤ ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤

ዮሃንስ ያየው ይገርማል  እያንዳንዳችን እዚህ ሰልፍ ውስጥ አለንበትና ጌታን እናመስግን::   

ያየው እስኪ እንመልከት

1.  የሰውን ብዛት ማንም  ሊቆጥራቸው የማይችል :-  የጌታ ዘር ብዙ ነው ገንይም እንበዛለን ሰዎችን ከሲኦል እንናጠቃለን::

2.  ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ :- ለዚህ ነው ወንጌል በምድር ሁሉ መሰበክ ያለበት ሁሉ እንዲደርሰውና ወደ ጌታ ዘወር እንዲል::  ይህንን ቃል ኪዳን ጌታ ከአብርሃም ጋር ነበር የገባው በዘፍ 12:1-3  በእርሱ በኩል ሁሉን እንደሚደርስ ይኸው ዛሬ የዛ ቃል ኪዳን ተካፋዮች ሆነን  በቤቱ አለን::  ስሙ ይባረክ!!

3. ነጭ ልብስ ለብሰው :- ይህንን ያለበሰን እራሱ ጌታ ነው ::  ጽድቃችን እየሱስ ተባረክ!

4. የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው:- ጌታ እየሱስም ወደ እየሩሳሌም በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ በዮሐንስ 12: 13፤ የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና፦ ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፡ እያሉ ጮኹ።

ይህንኑ በሰማይ ሲደገም እናያለን!  ጌታችን ድል ነስቶ በዙፋኑ ላይ ነውና ጌታን እናመስግን::

ማራናታ!

የዮሐንስ ራእይ 7: 10

10፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ አሉ፦ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው። 

እነዚህ ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል ሰዎች በበጉና በዙፋኑ ፊት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ማምለክ ነው የቀጠሉት::  በሰማይ የሚቀርልን ነገር ማምለክና በጌታ መደነቅ ነው::  መንፈሳዊዉን ዓለም እንደሚገባ ተረድተናል ለማለት ይከብደኛል::  ብዙ የምናውቀው እዛው ስንደርስ ይመስለኛል::  አሁን በድንግዝግዝ ነው የምናውቀው ስንደርስ ግን ሁሉ ግልጽ ይሆናል::  ማንም አያስገድድም ጌታን እንድናመልክ የምናየው ነገር ነው ዝም ብለን እንዳንቆም የሚያደርገን::  የክብሩ ታላቅነትና  የእኛን ታናሽነት ስናይ ነፍስም አይቀርልን መወደዳችን እየገረመን እናመልካለን!!!

በአምልኳቸው ውስጥ እንዴት እዚህ ስፍራ ላይ እንደተገኙ ይገልፃሉ:- 

ከሁሉም በፊት ደስ የሚለው በታላቅም ድምፅ እየጮሁ ነበረ የሆነላቸውን ለበጉ ለእየሱስ የሚገልጡት፦ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው።  ማዳን የማን ነው? የአምላካችንና የበጉ ነው::  ማንም ተገብቶት አይደለም በዛ ስፍራ የተገኘው ስላዳነን ብቻ ነው እርሱ ተንገላቶ ከጨለማው ኃይል ስር ፈልቅቆ አውጥቶ ነው ለዚህ ድል ያበቃን::  ሃሌሉያ!!

ስለዚህም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉና ለአምላካችን ክብር ይሁን!!  የተከፈለው ዋጋና ፍቅሩ ገብቶን  እናመስግን እናምልከው እንገዛለት::  እርሱ ክብር የተገባው ነውና!! 

ደግሞም ዛሬ ወደዛ ቁጥር ላይ የሚጨመሩ ከሲኦል የሚያመልጡ ሰዎችን እንደሊድያ ልባቸውን እየከፈተ ይስጠንና የአባታችንን ቤት እንሙላው ሰዎች ከጨለማው አገዛዝ ያምልጡ የበጉ የእየሱስ ልፋት ዛሬም ማዳንን ያድርግ:: ሃሌሉያ!!

የዮሐንስ ራእይ 7: 11-12

11፤ መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ፦

12፤ አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን፡ አሉ። 

መልአክቱም በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤  ማንም ሊቆጥራቸው ያልቻለው ነጭ ልብስ የለበሱት ማዳን የአምላካችንና የበጉ ነው ብለው ሲያመልኩ ግን ቆመው ማየት አልቻሉም:: 

ስለዚህም 

1. በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥  በዚህ ክቡር ጌታ ፊት እንዴት ይቆማል ? 

2. ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ፦ በግምባራቸው መደፋት ብቻ አይደለም በዛው ስግደትን ቀጠሉ መነሳት እንደገናም መውደቅ መነሳት መውደቅ ሆነ::

3. አሜን፥ ብለው ከሰው ጋር ከተስማሙ በኃላ የራሳቸውን አምልኮ ቀጠሉ:-

በረከትና 

ክብር 

ጥበብም 

ምስጋናም 

ውዳሴም 

ኃይልም 

ብርታትም 

ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን፡ አሉ። 

እኛም ዛሬ አሜን እንላለን ለዚህ ጌታ!!

የታደገን በግ ስሙ ይባረክ!

የዮሐንስ ራእይ 7: 13-14

13፤ ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ፦ እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ።

14፤ እኔም፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ፡ አልሁት። አለኝም፦ እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።

ምዕራፉ የሚጀምረው የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ፡ በሚለው መልአክ ነው እነዚህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሊመጣ ካለው ፍርድ እግዚአብሔር ያሰባቸው ናቸው እርሱ ህዝቡን አይተውምና::  ደግሞም ከሌላው ጋር አብረው እንዳይገኙ ምልክት ተደረገባቸውና ከታላቁ መከራ የመጡ ተባሉ::

በ ትንቢተ ዳንኤል 12: 1፤ በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።

ከሽማግሌዎቹ አንዱ እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? ብሎ የጠየቀው ጠፍቶት አይደለም ለዮሃንስ የሚነግረው ነገር ስላለ እንጂ::  

እነማን ናቸው? ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ሌላ ማንነት የላቸውም ማንነታቸው የእየሱስ ደም በመፍሰሱ ጽድቅን ማለትም ነጩን የማይገባቸውን የለበሱ ናቸው::  ከዚህ አገር ከዚህ ዘር ተብሎ ማንነት ያልተሰጣቸው::  ሃሌሉያ!  የምታወቀው በእርሱ ውስጥ ነው::

ከወዴትስ መጡ? 

እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥

ጌታ እየሱስም ይህንኑ ነግሮናል  በማቴዎስ 24: 21፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።

ዓለምም ምኞትዋም ያልፋሉ ዓይናችን በጌታ ላይ ይሁን ሁሉ አልፎ ይህንን በዓይናችን የምናይበት ዘመን ይመጣልና:: በሰማይ ተገኝተን ጌታን የምናመልክበት ጊዜ ይመጣል:: ቃል እንደተገባው ምልክት ተደረገባቸውና ከያሉበት እየተለቀሙ በዙፋኑና በበጉ ፊት ዘንባባን ይዘው ማምለክ ቀጠሉ:: በመንፈስ ቅዱስ ዕለት ዕለት ተሞሉ እንደሚል ለመምጣቱ በሚያዘጋጀን ጌታ እየተዘጋጀን መምጣቱን በጉጉት እንጠብቅ:: አሜን! ጌታ ይመጣል አይዘገይምም! ማራናታ!

የዮሐንስ ራእይ 7: 15-17

15፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል።

16፤ ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ 

17፤ በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል። 

በታማኝነት ጌታን ለተከተሉት በደሙ አጥቦ ላነጻቸው ምንድነው የሚጠብቃቸው? 

1.  በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥  ምን አይነት ክብር ነው በእርሱ ዙፋን ፊት መገኘት? በዚህ ምድር እንኳን ፕሬዝደንቱን ጨበጥኩት ስንት ዓመት የሚወራ ነገር ነው አይደለም በዋይት ሀውስ እንድትኖር የአሜሪካ ህግ ፈቅዷል ብንባል::  ይህ ዙፋን የከበረ ነው::

2.  ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥  ይህንን አሳብ ስናየው የካህን ስራ ነው ቀንም ለሊትም በቤተ መቅደስ መገኘት::  እኛንም ለመንግስቱና ለአባቱ ካህናት ስላደረገን ቀንና ለሊት በመቅደሱ ተገኝተን እናመልከዋለን::

3. በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። ምን አይነት መታደል ነው ይህ ጌታ በእኛ ላይ ያድርብናል::  አሜን!

4. ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥  መቼምየምድር ርሀብ በምግብ ይታገሳል ክብሩን መጠማት ግን ማን ያረካዋል?  ስለዚህ ከክብሩ እንጥእግባለን::

5.  ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥  ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ እኔ የምሰጠውን ውሃ የሚጠጣ አይጠማም እንዳለን እርካታችን እርሱው ነውና ደግመን እስከማንጠማ ድረስ ያጠግበናል በፊቱ ሆነን::

6. ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ የዓለም ውርጅብኙ ሁሉ ቀጥ ይላል ጠላት በዚህ በዚያ የሚያጣድፈን ሁሉ ይቆማል እረፍት በሰማይ ቀርቶልናል::

7. በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥  እርሱ እራሱ እረኛ ይሆነናል ቅጥረኛ ያልሆነ እረኛ እርሱ ብቻ ነውና::

8. ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ ጌታ የህይወት ምንጭ ነው የህይወት ህግ ነው ዛሬም በእኛ ውስጥ የሚሰራው:: እርሱ ህይወት እንዲሆንልንና እንዲበዛልን መጣ:: ይህ ምንጭ ክውስጣችን ይፈልቃል መገኛው ከእርሱ ነውና አይቋረጥም አሜን::

9. እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል። ክርስትና መቼም በእንባ የታጀበ ነው ምድር ሰልፍነውና ነገር ግን በሰማይ ለቅሶ የለም:: ሃሌሉያ! ለባርያዎቹ ጌታ ያዘጋጀው ህይወት ይህ ነው:. ስሙ ይባረክ የምናልፍበት ሁሉ ጊዜያዊ ነው ሁሉ ያልፋልና ያለንን ህይወት ጠብቀን እንመላለስሰ እኛ እረኛ ያለን ዓላማ ያለን፤ መድረሻ ያለን ነንና::

ይህ ሁሉ ህዝብ ወደቤቱ ከመከራው በፊት ተሰበሰበ!! ጌታ ለቃሉ ታማኝ ነው::

የዮሐንስ ራእይ 8: 1-2

1፤ ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኵል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ።

2፤ በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው።

በሰማይ ዝምታ የሆነበት ምክንያት በትንቢተ ዕንባቆም 2: 20፤ እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድርም ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል።

እንዲሁም በትንቢተ ዘካርያስ 2

13፤ እግዚአብሔር ከተቀደሰ ማደሪያው ነቅቶአልና ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ፥ በፊቱ ዝም በል።

እግዚአብሔር ሊፈርድ ሲነሳ ዝምታ ይሆናል ማን ምን ማለት ይችላል? 

ከዚህም በኃላ ሰባት መላእክት መለከት ይዘው እናያለን::  ከዚህ በፊት ስለነዚህ መላእክት አልተጠቀሰም::  ፍርድ ሲተላለፍ መለከቱን የሚነፉ መላእክት ተዘጋጅተው እየጠበቁት ነው::  ከእግዚአብሔር ፍርድ ማን ያመልጣል ዝም ሲል ከኃጥያት ጋር የተስማማ ወይንም ደግሞ ምንም የማይመስለው ይመስል ህሆናል ነገር ግን ፈራጅ በሰማይ አለ::  ፍርድም ከቤቱ የሚጀምር ፃድቅ አምላክ ነው::  መንገዳችንን እርሱን በመፍራትና በማክበር እንጠብጥብ::

የዮሐንስ ራእይ 8: 3-5

3፤ ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።

4፤ የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።

5፤ መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ።

ሰባቱ መላእክት በተጠንቀቅ ቆመው መለከቱን ለመንፋት እየተጠባበቁ ነው::  በዚህ መሀል ነው ሌላ መልአክ የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ የቆመው፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው ይላል የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።  አሜን!  ጸሎትን የሚሰማ ጌታ በላይ በሰማይ አለ:: ፀሎቱና እጣኑ በፊቱ ሲወጣ ለፀሎት መልስ ይሰጣል::  መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ ምክንያቱም መልሱን ሲሰጥ በመገኘት ነውና በሲና ተራራ ይኸው ነበረ::   ፀሎታችንን ሰምቶ ችላ የሚል ጌታ አይደለም::

ኦሪት ዘጸአት 19

16፤ እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ።

የሚገርመው ነገር በሚካሄደው ስርአት መካከል የህዝቡን ፀሎት ለመስማትና ለመመለስ ጊዜ የሚሰጠን ጌታ ስሙ ይባረክ::  የቅዱሳን ፀሎት  ይመለሳል በእግዚአብሔር ጊዜ እርሱ ሰምቶ የሚመልስ::

የዮሐንስ ራእይ 8:  6-7

6፤ ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ።

7፤ ፊተኛውም መልአክ ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ።

ሰባቱን ማኅተም በጉ በፈታ ጊዜ ብዙ ፍርድ ሆንዋል አሁን ደግሞ እነዚህ ሰባት መለከቶች ምን አይነት ፍርድ እንደሚያመጡ እናያለን::  መልአክቱም ተዘጋጅተዋል::

የፊተኛው መልአክ ነፋ፤ 

ደምም የተቀላቀለበት በረዶና 

እሳት ሆነ፥ 

ወደ ምድርም ተጣለ፤ 

የምድርም ሲሶው ተቃጠለ 

የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ 

የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ።

ይህንን የሚመስል ፍርድ በግብጽ ላይ አይተናል በዘጸአት 9: 22-26 እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በግብፅ አገር በሰው በእንስሳም በእርሻም ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብፅ አገር ሁሉ በረዶ ይሆን ዘንድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፡ አለው።

የእግዚአብሔር  ፍርድ የማይቀር ነው ከዚህ ሁሉ ፍርድ በፊት ጌታ ህዝቡን ምልክት አድርጎ ከጉዳት እየከለለ ነው:;  ግብጽ ስትመታ እስራኤላውያን ያሉበት ግን ምንም አልተፈጠረም ::

ኦሪት ዘጸአት 9: 26፤ የእስራኤል ልጆች ተቀምጠው በነበሩባት በጌሤም አገር ብቻ በረዶ አልወረደም።

ምድር  በብዙ  መከራ  ውስጥ  ታልፋለች ጌታ ግን ህዝቡን ይጠብቃል ብናልፍም የምንሄደው ወደ ጌታ ነው የሚያስፈራን ነገር የለም የተማመነውና የተደገፍነው ጌታ ድንቅ ነው:: ወደ እጄ የገቡትን ማንም አይነጥቅም ብሎናል::

ዓይኖቻችንን በጌታ ላይ እናድርግ!

የዮሐንስ ራእይ 8: 8-9

8፤ ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ

9፤ በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ።

እነዚህ ሰባት መላእክት መለከቱን ሲነፉ የሚፈጠር ፍርድ አለ::  ሁለተኛው ሲነፋ የሆነው ታላቅ ተራራ ላይ ነበረ ፍርዱ በኤርምያስ 51: 25፤ አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊ ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እጄንም እዘረጋብሃለሁ፥ ከድንጋዮችም ላይ አንከባልልሃለሁ፥ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ።

ተራራ በመንግስት ይመሰላል እንጂ በገሀድ የሚታየው ተራራ አይደለም::  እንዲሁም በዳንኤል መጽሐፍ 2:35 ላይ እጅ ያልነካት ድንጋይ ተንከባላ ምስሉን ከሰበረችና ካደቀቀች በኃላ ታላቅ ተራራ ሆነች::  ተራራ መንግስትን ይወክላል::  የሚፈረድበት መንግስት/አገር አለ::  ይህ  አገር ፍርድን ሲያገኝ አብሮት የሚጎዳው ብዙ ነው::  የእግዚአብሔር ፍርድ ከባድ ነው ከእርሱ ፍርድ ማን ያመልጣል:: በተሰሎንቄ ላይ የእግዚአብሔር ቃል ክፉ እንዳይገለጥ የሚከለክል በእኛ ውስጥ አለ እኛ ከሄድን በኃላ ክፉም በመሉ ኃይሉ ይሰራል እግዚአብሔር ፍርድን ያመጣል:: 

ታማኙ ጌታ ያስመልጠናል! ስለሚጠፉት ግን ግድ ይበለን ዛሬ ቅን ሳለ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ እንድናደርስ ጌታ መንቃትን ይስጠን::

ይህንን ሁሉ ውርጅብኝ ዓለም ስታስተናግድ እግዚአብሔር ህዝቡን ግን በምዕራፍ 7 በፊቱ አምጥቶ አከማቸ ከመከራውም ታደገን::  መልአኩ የአምላካችንን ባሪያዎች ምልክት እስክናደርግ ምንም ጉዳት አይጀምር እንዳለ ከውርጅብኙ በፊት ህዝቡን በዙፋኑ ፊት ያቆመው ጌታ ስሙ ይባረክ::

የዮሐንስ ራእይ 8: 10-11

10፤ ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፥ በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል።

11፤ የውኃውም ሲሶ መራራ ሆነ መራራም ስለተደረገ በውኃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ።

የምድር ፍርድ እንደቀጠለ ነው ይህ ሶስተኛው ፍርድ መልአኩ መለከቱን በነፋ ጊዜ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፥  የወደቀው ኮከብ ነው ስሙ እሬቶ ይባላል እንዲያጠፋ የመጣውም በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ።  እንዴት ውሃዎችን ብቻ መጦ ወደቀ ስለዚህ ኮከብ ይባል እንጂ ሌላ ትርጉም አለው::  ያጠቃው ክፍል ወንዞችን (ብዙ ናቸው) እንዲሁም የውሃ ምንጮችን ነው (ይህም ብዙ ቁጥር ነው)::  

በሌላ ክፍል ላይ ስናይ በትንቢተ ኤርምያስ 9: 15፤ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህን ሕዝብ እሬትን አበላዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣዋለሁ።

እንደዚሁም 

ትንቢተ ኤርምያስ 23: 15፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኵሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና እሬትን አበላቸዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ።

ውሃውን የመታው በእሬት ነው ከላይ በኤርምያስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው:: ይህ ፍርድ ደግሞ የመጣበት ምክንያት እዚህ ቃሉ ላይ  እንደተቀመጠው ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኵሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና ነው ምክንያቱ::  ዛሬም ቤተክርስቲያን ውስጥ የምናየው የነብያት ውጥንቅጥ ካልተመለሱ እግዚአብሔር ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም አለበለዚያ ግን በጊዜው  ፍርድን ያገኛል:: ስለዚህ ፍርዱ አመጹን የሚመጥን ነው የሚሆነው::  ቅድስናውንና ፍቅሩን ታላቅነቱን ማሳየት ሲገባ ባላሳዩበት ይህ ፍርድ ይወጣል::  እንደዚሁም አምላክ ባልሆነው በአጋንንት መንፈስ የሚጠነቁሉና ህዝቡን ከእግዚአብሔር መንገድ ያጠፉንም ይመለክከታል:: ስቃዮም መራራ ይሆናል አምላካችን አይዘበትበትም::

ዛሬ ጊዜ ሳለ ወደንስሀ ሰዎች እንዲመጡ እንፀልይና እንናገርም::  ይህ ያነበብነው የማይቀር  ነገር ነው::  ጌታ ዓይኖቻችንን ይክፈት በድፍረትም የምንሰብክበትን ፀጋ ይስጠን::

የዮሐንስ ራእይ 8: 12-13

12፤ አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት።

13፤ አየሁም፥ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ፦ ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፡ ሲል ሰማሁ።

አራተኛው መልአክ ሲነፋ የተፈጠረው የፀሓይ የጨረቃና የከዋክብት መመታት የገሃዱን ዓለም የብርሃናቱን ነገር አይደለም የሚናገረው ነገር ግን ታላላቅ መንግስታት ላይፍርድ መሆኑን ነው::  ይህም ሲሶው ነው እየተመታ ያለው ሙሉ ለሙሉ ፍርድን ገና አላገኙም::

የሚገርመው ይህ ሁሉ ውርጅብኝ መቼም በአንድ ጀምበር የተደረገ ባይሆንም ዓለም እየተቀበለች ነው የእግዚአብሔርን ፍርድ::  ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ ንስሩ የሚያውጀው ያስደነግጣል የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፡ ሲል ሰማሁ።  ዓለም እየተፈረደባት ነው ሞትን ናና ውደቅብኝ ተብሎ የሚለመንበት ጊዜ::  

ዛሬ ከጌታ ጋር ያለንን ኅብረታችንን አጥብቀን እንያዝ የሚያስመልጠን እርሱ ብቻ ነው የሚመጣውን ስለሚያውቅ ነው የእግዚአብሔር በግ ሆኖ መስዋዕት የሆነው:: የሌላውም መዳን ያስጨንቀን እንፀልይ ለቤተሰቦቻችን ለጏደኞቻችን ለጎረቤቶቻችን አብረውን ለሚሰሩት እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤት ሆነው ለጠፉት ወገኖች እናሳስብ:: ጌታ ፀጋውን ያብዛልን:: በፊቱ ስንቆም እነዚህን ይዤ መጣሁ የምንል ፍሬያችን ደስ የሚያሰኘውና አገልግሎታችንም በእሳት ውስጥ የሚያልፍ ተቃጥሎ የሚጠፋ ገለባ ይዘን እንዳንገኝ እንበርታ በጸጋው::

የዮሐንስ ራእይ 9: 1-2

1፤ አምስተኛውም መልአክ ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፥ የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው።

2፤ የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ ፀሐይና አየርም በጕድጓዱ ጢስ ጨለሙ።

ይህ እንግዲህ ወየው በምድር ለሚኖሩት ተብሎ አዋጅ ከተነገረ በኃላ ከሶስቱ የከፉ ፍርዶች ውስጥ የመጀመርያው መሆኑ ነው::  አምስተኛው መልአክ መለከቱን ሲነፋ ዮሃንስ ያየው ነገር ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀ  ኮከብ ነው::  ኮከብ ሲል መቼም በገሀዱ ዓለም ያለው ኮከብ አይደለም ይህ የሚያሳየው ስልጣን ያለው ስው ወይም መንግስት እንደሆነ ነው::  

ሉሲፈርም የንጋት ኮከብ ነበረ መጀመርያ ሲፈጠር:: በኢሳይያስ 14: 12፤ አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ!  ስለዚህ ይህ ፍርድ ስልጣን የነበረውን የሚያዋርድ ነው የሰይጣን ወይም ደግሞ ነገስታትና አገራቸውን ይመለከታል::

ጌታ እየሱስም አጋንንት እንኳን በስምህ ተገዛልን ብለው ሲሉት  በሉቃስ 10: 18፤ እንዲህም አላቸው፦ ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ።  

ይህም በኮከብ በተሰጠውመክፈቻ – 

–  የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ 

–  ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ 

–  ፀሐይና አየርም በጕድጓዱ ጢስ ጨለሙ።  ይህንን ፍርድ በሰዶምና ገሞራ ላይ እናያለን:: አብረሃም በዘፍጥረት 19: 28፤ ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ በዚያች አገር ወዳለውም ምድር ሁሉ ተመለከተ፤ እነሆም የአገሪቱ ጢስ እንደ እቶን ጢስ ሲነሣ አየ። ይህ ፍርድ ነው ምድርን የሚጠብቃት::

ደህንነታችን ምን ያህል የከበረ እንደሆነ እንገንዘብና ለሌሎችም የሚያስሮጠን ጸጋ በእኛ ላይ ይገለጥ ጊዜ የለም ጌታ በደጅ ነው ሰዎችን ለአባታችን መንግስት እንሰብስብ እርሱም ልባቸውን እንደ ሊድያ እየከፈተ ይስጠን:: አሜን!

የዮሐንስ ራእይ 9: 3-4

3፤ ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፥ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው።

4፤ የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተባለላቸው።

ከእስፈሪው አንዱ የሆነው መለከት የጥልቁን ቁልፍ ይከፍት ዘንድ ነው የተሰጠው::  መቼም በጥልቁ ውስጥ ምን/ማን እንዳለ እናውቃለን::  በምሳሌያዊ ንግግር አንበጣ ይባል እንጂ እየወጣ ያለው የሰይጣን ሰራዊት ነው በአንበጣ አምሳል::  አንበጣን እግዚአብሔር ለመቅጣት ሁሌ ይጠቀምበታል እዚህም ላይ ያለው ምሳሌ ይኸው ነው::  የወጣው ሰራዊት አንበጣ ብቻ ሳይሆን ጊንጥም መሆኑ ነው::  እውነትም በምድር ላሉ ወየው!  አጋንንት አይራራም ማሰቃየት ነው ስራው::

የተሰጣቸውም ትዕዛዝ ማንን መንካትና ማንን አለመንካት እንዳለባቸው ይጨምራል::  ከሁሉ በፊት አንድ መልአክ ይህ ፍርድ ከመጀመሩ በፊት የአምላካችንን ባሪያዎች ምልክት እናድርግ ብሎ ነበረና እነሱን እንዲሁም 

በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተባለላቸው።

ስለዚህ የቀረው ማነው እግዚአብሔርን የማይከተሉ ሰዎች ናቸው የሚጠቁት ማለት ነው::  እግዚአብሔርን ስላላወቁ እንዲያውቁና እንዲድኑ ነው በዚህ ውስጥ አለበለዚያ ግን አንድጊዜ ወደ ሞት ከተሻገሩ ወድያ እድል የለም::  ለዘላለም የሚጠብቃቸውን ትንሽዋን ነው እንዲቀምሱት እግዚአብሔር እያደረገ ያለው::

ወንጌልን ለሰዎች መንገር  ምርጫ አይደለም ግዴታችን አድርገን እንቁጠረው የሚጠብቃቸውን ስናይ እንዘንላቸው ቢገፉንም እንታገስ::  ጌታ በጸጋ ሁሉ ይሙላን::

የዮሐንስ ራእይ 9: 5-12

5፤ አምስትም ወር ሊሣቅዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፤ እነርሱም የሚሣቅዩት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚሣቅይ ነው።

6፤ በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ አያገኙትምም፥ ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል።

ወየው በምድር ለሚኖሩት የተባለለት አንዱ ቅጣት እንግዲህ ሞት የሌለበት ለተወሰነ ጊዜ እንዲያሰቃዮ የሰው ልጆችን መብት የተሰጣቸውን አጋንንት ነው::  እነዚህ በአንበጣና በጊንጥ የተመሰሉት መናፍስት ንጉስ አላቸው ይላል በምሳሌ 30: 27፤ አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም ሁላቸው ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ ይላል::  ይህ የሚያሳየን ምሳሌያዊ መሆኑን ነው ::

ሞት ከስራው የታገደበት ከባድ  የስቃይ ጊዜ ሰዎች የሚጠብቃቸውን አውቀው ንስሃ እንዲገቡ የመጨረሻ እድል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች እየሰጠ ያለበት ነው::  ከተፈቀደላቸው በላይ ማድረግ አይችሉም::  ብዙ ምሳሌያዊ ነገርን እናያለን ለምሳሌ ለጦርነት እንደተዘጋጁ ፈረሶች – ወደ ዘመቻ የወጡ ናቸው::

ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፥ እንደ አንበሳ ግን አይደሉም::

እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው በጅራታቸውም መውጊያ አለ፥ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጐዱ ሥልጣን አላቸው። እንደ ጊንጥ የሚያደርጋቸው ስራቸው ነው መውጋታቸው::

ፊተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል።  ይህ ሁሉ የሚጠብቃቸው ሰዎች ዛሬ በአጠገባችን ይኖራሉና ወንጌልን ከመናገር ዝም አንበል::  ለሰዎችን መዳን ከመጸለይ አንቦዝን::  ጌታ በደጅ ነው !   

እስከዛሬ ከዓለም ጅማሬ ጀምሮ ያለውን ሁሉ ያደረገ ይህንንም ሲሆን የምናየው እውነት ነውና ወገባችንን ታጥቀን ትኩረታችንን ሁሉ በመንግስቱ ላይ እናድርግ::  ለመታዘዝና ለመላክ እሺ እንበል ተራራ አይሁንብን በጸጋ ነውና የሚሰራው::

ራእይ 9: 13-15

13፤ ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ፥

14፤ መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ፦ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው፡” አለው።

15፤ የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ።

ስድስተኛው መለከት በተነፋ ጊዜ ድምጽን በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራው መሠዊያ ቀንዶች ሰማሁ ይላል ዮሃንስ::  ይህ ድምጽ የመጣው ከመሰውያው ነው የቅዱሳን ጸሎት ይሆናል::  በብሉይ ኪዳን መሰዋትንና እጣኑን የሚያቀርቡበት ስፍራ ነውና::

ሌላው የተከናወነው ነገር በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት እንዲፈቱ ትእዛዝ ተሰጠ::  የዚህ ዓለም ገዢ የተባለው ዲያቢሎስ ብዙ ስልጣን ያላቸውን መልአክት አስከትሎ ነው የወደቀው::  ውጊያችንም ከነዚህ የጨለማው ስልጣናት ጋር ነው::  ሁሉም ግን እንደወደዱ እንዲሰሩ የተለቀቁ አልነበሩም ::  እዚህ ጋር እንደምናየው ገና እየተፈቱ ያሉ እናያለን::

ሲፈቱም የተሰጣቸው  ስራ የዓለምን ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ ይላል::  ከዚህ በፊት የወጡት በአንበጣና በጊንጥ የተመሰሉት መግደል አልተፈቀደላቸውም ነበር::  እነዚህ ግን ስራቸው መንደል ነው::  

እግዚዖ ያስብላል የሰው ልጅ የሚጠብቀው ነገር ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ወደ መዳን ሊመራቸው  እንደሆነ ያስተውሉ ይሆን?  ጌታ ሆይ ቤተሰቦቻችንን ሁሉ አሳልፈህ ስጠን ወደ መዳን ይምጡ::  እንዲሁም የምናውቃቸውንም የማናውቃቸውንም ጨምረህ ስጠን ርንደሊድያ ልባቸውን ከፍተህ ስጠን:;  በእየሱስ ስም አሜን!

ራእይ 9: 16-21

16፤ የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ፥ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ።

20፤ በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤

21፤ ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም።

የዚህ ስድስተኛው መለከት የሰው ልጅን ሲሶ የሚያጠፋ ነው ከተባለ መቼም ብዙ መሆን አለበት አጥፊው ወይም ኃይለኛ::  እንደምናየው የማይቆጠር ጭፍራ ነው እልፍ ጊዜ እልፍ፥ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ ይላል ዮሃንስ::  የቀረው ሁለቱ እጅ ነው ሌላውን ያጠፋው ማለት ይከብዳል ምክንያቱም ይህ ጭፍራ ለየት ባለ መንገድ ነው የተገለጠው::

ያጠፉ የነበረውም ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ። ታድያ የትኛው ሰው ነው ይህንን ማድረግ የሚችል::  በዚህም ላይ ፈረሶቹ 

እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፥

የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ 

ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፥ 

ራስም አላቸው በእርሱም ይጐዳሉ።

ይህ መንፈሳዊ ውጊያ ነው መናፍስት ተለቀው የሚሰሩበይ ጊዜ ነው::  እግዚአብሔርግን ዓላማው ምንድነው? ሰውን ማሰቃየት? በፍጹም አይደለም::  አላማው  ንስሀ እንዲገቡና እንዲድኑ ነው::

ይህንን ሁሉ ያደረገው ጣኦትን ከማምለክ ወደእርሱ ዞር እንዲሉ ነበረ:: በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤

እንዲሁም ከክፉ ስራቸው እንዲመለሱና ንስሃ እንዲገቡ ነበረ::  ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም።

የንስሃ መንፈስ በህዝቡ ላይ ይፍሰስ ያለንበት ዘመን ነፍሰ ገዳይ የበዛበት ዝሙት የበዛበት ሌብነትም የበዛበት ነው::  ጌታ ይርዳን!

ራእይ 10:  1-4

1፤ ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፥

2፤ የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥ እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።

3፤ በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ።

ይህ ብርቱ  መልአክ ተብሎ የተጠቀሰው በጣ ከጌታ እየሱስ  ጋር የሚመሳሰል ነገር አለው ምናልባትም ጌታ ይሆን? 

– ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ 

– በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፥ 

– ፊቱም እንደ ፀሐይ 

– እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፥ 

– የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። 

– ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ 

–  ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥ 

–  እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ  ይላልና ነው የተመሳሰለብኝ:: 

መጽሐፍን የወሰደ እንዲሁም የይሁዳ አንበሳ የሆነ በፍጥረት ሁሉላይ ባለስልጣን ( በምድርም በባህርም ላይ እግሩን ያኖረ) እግሮቹም እንደእሳት የሆኑ ፊቱም እንደ ፀሀይ የሚያበራ ብዙው መግለጫ እርሱን ይመስላል:::  ማንም ይሁን ማን ስልጣን ያለው እንደሆነ ግን ግልጽ ነው::

ይህብርቱ መልአክ ትንሽ መጽሐፍ ይዟል ግን ምንም ነገር ስለመጽሐፍዋ የተነገረ ነገር የለም::  ይኸው መልአክ ጮኸ  በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ። ነገር ግን ዮሃንስ የተናገሩትን ሊጽፍ ሲል አትጻፍ ተባለ::  በጊዜው ሁሉ ይገለጣል እውቀታችንም ሙሉ ይሆናል::

ይህ ሁሉ ዝግጅት ጌታ ሊገለጥ የዓለምም ፍጻሜ  ሊሆን ነውናየተዘጋጀን እንሁን!

ራእይ 10: 5-11

5፤ በባሕርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ዘረጋ፥

6፤ ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘላለምም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ፦ “ወደ ፊት አይዘገይም፥

7፤ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥ ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል፡” አለ።

ወደ ፊት አይዘገይም፥  የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል  ብሎ ነው የማለው ይህ ምስጢር ምን ይሆን ? ሚስጢር እስኪገለጥ የሚጠበቅ ነው:: 

ዮሃንስ መጽሐፉን ወስዶ ከበላ በኃላ አፉ ላይ እንደማር ጣፈጠው በሆዱ ግን መራራ ሆነ ይላል::  ከዛም በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደ ገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል” ተባለልኝ። ይላል የበላውን ቃል ትንቢት መናገር ሊኖርበት ነው::

ጌታ ይመጣል እዚህ ላይ የምናነበው ሁሉ ይፈጸማል::  ተግተን መገኘት ይሁንልን::

ራእይ 11: 1-2

1፤ በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ፦ “ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ።

2፤ በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።

ዮሃንስ መለኪያ ተሰቶት ለካ የተባለው:- 

– የእግዚአብሔርን መቅደስና 

– መሠዊያውን 

– በዚያም የሚሰግዱትን 

መቅደሱና መሰውያውን መለካት ይቻላል ግን ሰውን እንዴት ይቻላል?  ዘካርያስም መቅደሱን ሲለካ አይቷል ነገር ግን ያኔ ሲለካ ምናልባትም ዘሩባቤል ሊያድሰው ስለነበረ ነው ቢባል አሁን ለምን ይለካል?

ምሳሌያውት ሊሆንም ይችላል::  እግዚአብሔር ሁሉን እንደሚከታተልና እንደሚያይ ያሳየኛል:: ህዝቡንና ቤቱን ችልይ አይልም እኛ ነን ቤቶቹ በአዲሱ ኪዳን::

በውጪ ያለውን አደባባይ ጌታ ትቶታል ለክቶ ማወቅም አልፈለገም  ምናልባትም በክርስቶስ ሁሉን አንድ አድርጎአልና በአደባባይ የሚቆም የለም ሁሉ ካህን ሆኖ ገብቷል ወደ ቅድስትና ቅድስተ ቅዱሳኑ::  

ሀሰተኛው ክርስቶስ 7 ዓመት ሲገዛ ሶስት አመት ተኩሉን (42 ወር) በፀባይ ከዛም የሚቀጥለውን ደግሞ በማስገደድ ነውና እርሱ መቶ ወደ መቅደሱ የሚገባበት ጊዜ አለ ያኔም ይረግጡታልየተቀደሰውን:: ይህንን ከማየትና ምስክር ከመሆን ያውጣንና ህዝቡን ሲሰበስብ አብረን መሰብሰብ ይሁንልን::

ራእይ 11: 3-6

3፤ ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።”

4፤ እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።

5፤ ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። 

6፤ እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው።

እነዚህ ሁለት ምስክሮች እንደነኤልያስና ሙሴ  ነው የተገለጡት::  ብዙ ሰዎች ኤልያስና ሔኖክ ናቸው ስላልሞቱ መተው ነው ይላሉ ግን ይህንን ለማለት የሚያስረግጥ ነገር ባይኖርም በተለየና በማይቋረጥ ኃይል መገለጣቸውን እናያለን::

– እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ 

– ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። 

– ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥ 

– ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ 

– በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው።

ይህንን ሁሉ ሊያደርጉ የቻሉት የኃይላቸው ምንጭ እራሱ መንፈስ ቅዱዝ ሆኖ ነው:: እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።  ይህንኑ መልእክት በዘካርያስም ላይ እናገኛለን ለእያሱና ለዘሩባቤል::  በተጨማሪም በኃይልና በብርታት አይደለም በመንፈሴ ነው እያለ  ያበረታቸው ነበረ::  

በዚህም ስፍራ እነዚህ ሁለት ምስክሮት 1.260 ቀናት ማለትም  ለሶስትና ተኩል ዓመታት ይህንን ምስክርነት ይቀጥላሉ::

ምስክርነቱም እኮ ማቅ ለብሰው ነው የሚለው ይህ ማቅ መልበስ የሚያሳየስ ንስሃን ነው::  በዚህ ሁሉ ጥፋትና መቅሰፍት ውስጥ እግዚአብሔር ንስሃ ግቡ አምልጡ ነው መልእክቱ::

አምላካችን እንዴት ያለ ፍቅር ነው ማንም እንዲጠፋ እእይፈልግም ስሙ ለዘላለም የተባረከ ይሁን:. ልቡ በነፍሳት መዳን ላይ ነውና የእኛም በዛ ላይ ያተኩር::  መጥፋታቸድ እየታየንና እየራራንላቸው እንፀልይ ደግሞም እንመስክር::  ጌታ መንፈስ ቅዱስና አብ ስለእየሱስ ለመመስከር ከፍኛ ጋር አሉ:: 

አሜን!

ራእይ 11: 7-14

7፤ ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል ያሸንፋቸውማል ይገድላቸውማል።

8፤ በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብፅ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።

እነዚህ ሁለት ምስክሮች የተገደሉት ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኃላነው::  እግዚአብሔር በታላቅ ኃይል አስጠብቋቸዋል ምክንያቱም በምድር ያለው ኃይል ባይችል ነው ከጥልቁ አውሬው ሊዋጋቸው የተገለጠው ::  

እነዚህን ምስክሮች ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። ከዚህም የተነሳ ብዙዎች አኤልያስ ነው አንዱ ሁለተኛው ደግሞ ሙሴ ወይም ሄኖክ ብለው የሚገምቱት:: ማንም ይሁን ማን የእግዚአብሔር አላማ ምንድነው? አላማው ወደ እንኡ ኑ ነው:,  የሰው ልጅ ሁሉ ንስሃ እንዲገባና እንዳድን ነው ጥሪው የታተሙትን ካሰብን ብዙ ናቸው ቁጥሩ ሌላ ትርጉም ከሌለው መተ አርባ አራት ሺ ነበረ::

በድናቸውም እንዳይቀበር አቆዩት ስለከተማዋም በአራት በመንፈሳዊ ምሳሌ ተጠቅሳለች:-

1. በታላቂቱ ከተማ – እራስዋን ከፍ ያደረገች

2.  ሰዶምና – ቅድስና የሌለበት

3.  ግብፅ- ባርነት ያለበት

4.  ጌታቸው የተሰቀለባት ናት – የመጨረሻ ክህደት ያለበት::

ህዝብ ሁሉ ደስ አለው ሲሞቱ በኃጥያታቸው የሚወቅስ የለም አስረሽ ምችው ሆነ ይህለነሱ ደስታ ነው እግዚአብሔር ግን እንዴት ከሚመጣው ላድን ብሎ እየተጠበበ ነው::  ስለዚህም የህይወትን መንፈስ ሰደደና ከሞት አስነሳቸው እሬሳቸስ ለቀናት በሜዳ ላይ የተጣለውን የልጆቹን::  ዓለም እጢዋ ዱብ እስኪል ድረስ ደነገጠች ስጦታ መቀያየሩ እንኳን ደስ አለን ሁሉ ቀረ::   

ከሞት መነሳት ብቻ ሳይሆን በሰማይም፦ “ወደዚህ ውጡ፡” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ።  ሃሌሉያ!! ከዚህ በላይ ምን አይነት ምስክርነት ነው ጌታ መስጠት የሚችለው?!  ስሙ ይባረክ ማንም እንዳይሞት የሚፈልግ ጌታ ስሙ ይባረክ!!

በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ ከከተማይቱም አሥረኛው እጅ ወደቀ፥ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፥ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፥ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ።  ክብር ይገባዋል!  እንደገና በምድር ለሚኖሩ ወየው ምክንያቱም ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል።

ጌታ የሚድኑትን ነፍሳት በእኛ ላይ ይጨምርና  ብዙዎችን ያስመልጥ::  አሜን!

ራእይ 11:15-19

15፤ ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም፦ “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል፡” የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ።

16፤ በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር እየሰገዱ፡

17፤ እንዲህ አሉ፦ “ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤

18፤ አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።”

19፤ በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።

ሁሉም ጌታን ማመስገንና ማምለክ ላይ ነው::  እርሱ ሊመለክ ይገባዋልና:: አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።”  

ጊዜው ደረሰ!

ይህንን ጌታ አብረን እያመለክን እንዋል!

ራእይ 12: 1-2

1፤ ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።

2፤ እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች።

ታላቅ ምልክት በሰማይ ሆነ ይህም ስለአንዲት ሴት ነውእርስዋም እስራኤል ናት:: ይህች ሴት ልዮ መገለጫ አላት:-

– ፀሐይን ተጐናጽፋ 

– ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች

– አስራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት – 12 ሐዋርያት

– ፀንሳ ነበር፥ 

– ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች። የሚወለደውም የሰይጣንን መንግስት የሚገለባብጠው ህዝቡንም ነፃ የሚያወጣው እየሱስ ነው::  ይህ ክፍል ወደኃላ ወስዶ እንዴት ባለ መወለድ እንደመጣ ሊያሳየን ወደደ አልጋ ባልጋ አልነበረም ማለት ነው አመጣጡ::  ስሙ ይባረክ እንኳን መቶ ታደገን::

ራእይ 12: 3-5

3፤ ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥

ራእይ 12:4፤ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ።

ራእይ 12:5፤ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።

ከላይ እንዳየነው ይህች ሴት እስራኤል ናት::  ዮሃንሰም ሲነግረን ታላቅ ምልክት ሆነ ነው ያለው ምሳሌያዊነቱን ለማሳየት::  ወደ ዮሴፍ ህልም ስንመጣ ፀሐይን ጨረቃንና ከዋክብቱን ይነግረናል እነማን እንደሆኑ:: ለእርሱ በግብጽ ምድር ገዢ ሆኖ የእስራኤን ሁሉ መሰረት የሆነው ያዕቆብ መቶ እንደሚሰግድለት ነው ያየው ያዕቆብ ደግሞ እስራኤል ነው::  ዘፍጥረት 37:9፤ ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ፦ “እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፤ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።”

እስራ ሁለተኛው እንግዲህ የእርሱ ትውልድ መሆኑ ነው::

ሌላው ደግሞ ሁለተኛው ምልክት ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥ ይላል::  ይህ ዘንዶ ስልጣን ወይም ንግስና ያለው ነው ምክንያቱም ዘውድ አለውና የዚህ ዓለም ገዢ ዲያብሎስ እንደሆነ አንዘንጋው:;  ቀይ የሚለውም በደም የተነክከረና ጨካኝ መሆኑን ያሳያል::

እንዲሁም ይህ ዘንዶ በጅራቱ የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። የተከተሉትንና ከእርሱ ጋር የተጣሉትን ሲሶ መላእክት ያሳያል::  ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። ይህንን በትክክል አድርጏል እየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ህፃናትን ሁሉ ሳይራራ አርዷል ግን እግዚአብሔር ከሰማይ ተጠበበናወደ ግብጽ እየሱስን አሸሸው::  ግን ሞክሯል የተወለደውን መድኃኒት ለማጥፋት::

ክብር ለአምላካችን ይሁን ዛሬም ይሞክራል እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር ለመወዳደር ነገር ግን የወደቀና የተጣለ ዘንዶ ነው::  ድል ለነሳው ክብር ይሁን!!!! አሜን

ራእይ 12: 6-9

6፤ ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች።

7፤ በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥

8፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።

9፤ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።

ሴቲቱ በዘንዶው መከራ ስለበዛባት ትሰደዳለች እስዋም እስራኤል ናት::  የምትሰደድበትም ስፍራ ተዘጋጅቶላታል  ልክ እየሱስ ስፍራን ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እንዳለው ምሳሌ በምድርም ለዚህ ህዝብ መሸሸጊያ ስፍራ ተዘጋጅቷል::  በዚህ መሀል መልአክቱ ከዘንዶው ጋር ውጊያ ያደርጋሉ ደግሞም ይረቱታል::  ከውጊያውም በኃላ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም ለዲያቢሎስና ለሰራዊቱ::  ሃሌሉያ!!  ተጣሉ!!

ስራው ማሳት በእግዚአብሔር ላይ ሰውን ማሳመፅ የሆነው ተረታ::  ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። አሜን ተጣለ!!  ድሉ ይቀጥላል!

ራእይ 12: 10-12

10፤ ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።

11፤ እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም።

12፤ ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”

ይህንን አዋጅ ያወጀው ወንድሞች ብሎ ነው የጠራን ጌታ እየሱስ መሆን አለበት ያወጀው መልአክት  ወንድሞቻችን ብለው የሚጠሩን አይመስለኝም::  ዋናው መልእክት በአሁኑ ሰዕት የተከናወነው:- 

– የአምላካችን ማዳንና 

– ኃይል 

– መንግሥትም 

– የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ 

– ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።  ሃሌሉያ!!  ጠላታችን እረፍት የሚነሳን ተጣለ::

የተጣለውም በምንድነው ብንል:-

– ከበጉ ደም የተነሣ  – የእየሱስ እንደበግ መታረድ ነው ያነፃን:: 

ኤፌሶን 1:7፤ በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። አሜን! 

– ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ – የፈለገውን ውሸት ቢያመጣ በህይወታችን ስልየነው ልንክደው አንችልምና እንመሰክራለን የሆነልንንና ያደረገውን::

ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም። ከተወደድንበት ፍቅር የተነሳ እንወደዋለን ህይወታ ችንም የእርሱ ነው:: ፊልጵስዩስ 1:21፤ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።

ይህንን ሁሉ ኪሳራ ስላስተናገደ ለማጥፋት ወቷል የዳንን እኛ ለሌሎች መቆምንይ ሌሎችን ማስመለጥ ይሁንልን::

ራእይ 12: 13-17

13፤ ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።

17፤ ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።

ጥቂት ዘመን እንደቀረው አውቆ ጠላት በታላቅ ቁጣ ወቶ ሴቲቱን ማለትም እስራኤልን አሳደደ::  እስራኤል በተለይም የዳኑትን ማሳደዱ አይደንቅም ምክንያቱም ውጤቱን ያውቀዋልና::  አሁን ዓለማዊነት በጣም ተጠናውቷቸዋል ምንም የኃይማኖተኝነት ምልክት የሌላቸው በዝተዋል::  ስለዚህ እነዚህ የዳኑ ጅውሾች ውጊያው ይበዛባቸዋል ይህንን ለመግፈፍና መሲሁ መቶ ነበር ወደሚለውሀሳብ ለማምጣት::  ጌታም እንዳለው በማቴዎስ 23:39፤ እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም። ይህንን እየጠበቀ ነው::

እስራኤልን በክንፍ ሲያወጣ አይተናል  በዘጸአት 19:4፤ ‘በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም እንደዚሁ ያወጣቸዋል ምክንያቱም በስተመጨረሻ የሚመጣው እዛ ነውና::  ጠላት ያንን ነው ማጥፋትና መከላከል የያዘው::  ግን ተሸንፏል::

ዘንዶው እርስዋን ትቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።

ውጊያው የነበረና የሚቀጥል ነው ድሉም የአምላካችን ነው::  ድሉ የታወቀ ውጊያ ውስጥ ነን::  እናስተውል ጠላት እንዳያታልለን እንሸነፋለን ብለን ወደማሰብ እንዳያመጣን ድሉ ተጠናቋል!  ሃሌሉያ ድል ለነሳው ክብር ይሁንለት::

ድል ለነሳው ክብር ይሁን

ራእይ 13:1-2

1፤ አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ።

2፤ ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው።

ከባህር ሲወጣ አየሁት የሚለው አውሬና ዘንዶው (በምእራፍ 12) ያየነው በጣም ይመሳሰላሉ ግን አንድ አይደሉም::  በዳንኤል 7 ላይም እንደተገለፀው ይህ አውሬ በምድር የሚገለጠው የክርስቶስ ተቃዋሚ ብሎ ዮሃንስ ይጠራዋል:: 

1 ዮሐንስ 2:18፤ ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ይላል ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን። መገለጡ አይቀርም::

ያየሁትም አውሬ 

–  ነብር ይመስል ነበር፥ የግሪክን ኢንፓየር ይመለከታል

–  እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ የፐርዥያን ኢንፓየር

– አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። የባቢሎንን ኢንፓየር

–  ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው። 

ይህ የሚያሳየው በምድር የተነሱትን ነገስታትና የአገዛዞችን  አይነት ነው::  ከነዚህ ሁሉ የከፋ ግን እየመጣ እንደሆነ ነው  የሚያሳየው ደግሞም  ትልቅም ስልጣን ዘንዶው ሰጠው::  ስልጣንም ብቻ አይደለም ኃይሉንና ዙፋኑን ሁሉ ጨምሮ ሰጠው:: ለምን?  ጊዜው እንዳለቀ አውቆ ሊያጠፋ ስለሆነ ነው::

ይመጣል የተባለው ይመጣል ስለዚህ ስራችንን በጊዜ እንስራ አንዘናጋ ጌታ ጸጋን ይስጠን::

ራእይ 13: 3-6

3፤ ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥

4፤ ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፦ “አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል?” እያሉ ሰገዱለት።

5፤ ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው።

6፤ እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ።

ይህ አውሬ እየሱስን ለመምሰል ሲጥር እናያለን ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ይላል የታረደው በግ እየስ ብቻ ነው::

ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥ መዳኑ ሲታወቅ ብዙ ክብር  አመጣለት::  ምድር ሁሉ ወደ ሞት ጎዳና እየነጎደ ነው ያለው የእነዛን የሁለቱንምስክሮች ነገር ረሳና አውሬውን መከተሉን ቀጠሉ ሞቱን ሳያዩ::

ለዘንዶውም ሰገዱለትለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፦ “አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል?” እያሉ ሰገዱለት? 

ለዚህ አጥፊ ዘንዶ ሰገዱ ለአውሬው ስልጣን ስለሰጠው::  ስግደት ግን የሚገባው የእኛ ጌታ ብቻ ነው ይህ አውሬ ህልሙ ሁሉ ይሄው ነበረ ግን ይህንንም ቢያገኝ ጊዜያዊ ነው:: ማን ይዋጋዋል አውሬውን ብለው በሚያደርገው ነገር ተገርመዋል::

አውሬው ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። የተሰጠው የሚሳደብበት አፍ መሆኑ ይገርማል::  መሳደብ ሲባል በእግዚአብሔር ላይ መነሳቱን ያሳያል::  አምላክእኔ ነኝ ሲል ስድብና ድፍረት ነው:: አውሬውም  በእግዚአብሔር ስምና በማደሪያው በሰማይም በሚያድሩት ላይ ሊሳደብ አፉን ከፈተ:: ይህ ጊዜያዊ ድል የትም አያደርሰውም::  ጌታ በዚህ አይናወጥ ወይም አይሸነፍ እርሱ በዙፋኑ ከብሮ ይኖራል::  አሜን!

ራእይ 13: 7-18

7፤ ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።

8፤ ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።

17፤ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ።

በዚህ ምዕራፍ ላይ እንደምናየው ሀሰተኛው ክርስቶስ በምድር ተገልጦ ስራውን ጀምሯል:: ዓለምን ሁሉ እያሰገደ ነው የሚገርመው በዚህ ውስጥ ስማቸው በህይወት መጽሐፍ የተፃፈ አልሰገዱም ድል እንዲያደርጋቸውም ስልጣን ተሰቶታል::  ድል የሚያደርጋቸው ግን እምነታቸውን በማስተው ሳይሆን በመግደል ነው::  ስልጣኑም በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ነው ስለዚህ የቀረ አገር ወይም ስፍራ የለም ሁሉ ተከትሎ እያመለከው ነው።  ምናልባትም ፖለቲካ ይመስል ይሆናል ነገር ግን ይህ ለጠላት የሚቀርብ አምልኮ ነው:: 

ኢኮኖሚውን ይቆጣጠራል ማንም ስሙን ወይም ቁጥሩን ካልተቀበለ በስተቀር መግዛትም መሸጥም አይቻልም::  ጥበቡንም በዚህ ይገልጣል::  ቅዱሳን ያላቸው ምርጫ እንቢ ሲሉ መገደል ብቻ ነው:;  እነዚህ ቅዱሳን እነማንናቸው? ሁለት አይነት አመለካከት አለ አንዱ ቤተክርስቲያን ከሄደች በኃላ የዳኑ ናቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ ቤተክርስትያን አልተወሰደችም እርስዋ ናት የምትሰደደው ነው የሚሉት::  በተለያየ ቦታ እንዳየነው ግን ጌታ ድሉን በሰማይ ብቻውን እያከበረ አይደለም::  ምዕራፍ 4 ጀምሮ ቅዱሳንን  እናያለን 24ቱን ሽማግሌዎች ጨምሮ::  እንዲሁም 7:9 ላይም እናያለን:: 

እኔም ይሁንልኝ ብዬ የምለው ቀድሞ መሄዱን ነው::  ለምን በምድር ይተወናል?  በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ?  በቤተክርስቲያን ላይ ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው ዛሬ እንደወደደ እንዳይሰራ የሚያደርገው::  ስለዚህ ቅዱሳን ብንወሰድ ነው እንደዚህ በግልፅ ለመገለጥ የበቃው::  በዛም ሆነ በዚህ ለሁለቱም ግምቶች ተዘጋጅቶ መጠበቁ ወሳኝ ነው:: 

እዚህ ክፍል ላይ ሌላ አውሬ እናያለን ከመጀመርያው የሚለየው የመጀመሪያድ ከውሃ ነው የወጣው ይሄ ደግሞ ከምድር::  ስራውም የመጀመሪያው አውሬ እንዲመለክ ማስገደድ ነው:: በኃይል ነው የሚሰራው ራእይ 13:13፤ እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል።  ልክ የነብይነት ስራ የሚሰራ ነው የሚመስለው::  እርሱ ነው ሰውን ሁሉ የሚያስተው:: 

ሰይጣንና መንግስቱ ተሸንፏል ድል ሁሌም ለጌታና ለአካሉ ነው::

ራእይ 14: 1-5

1፤ አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።

2፤ እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ።

3፤ በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም።

እነዚህ 144 ሺህ በመጀመርያ የተጠቀሱት  ምዕራፍ 7 ላይ ነበረ ከመቅሰፍቱ በፊት ታተሙ::  በጉ ከነዚህ ሰዎች ጋር በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ በእነርሱም ላይ ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው ተፅፎ ነበረ::  የሌላውን ምልክት አይደለም የተቀበሉት የጌታቸውን እንጂ::  አውሬውም ገደላቸው አሁን ግን ከንጉሳቸው ጋር መጡ::  ልክ እንደቀጠረን በሐዋርያት ስራ ላይ እንዲሁ እንደሄደ ይመጣል እንደሚል ቃሉን ጠብቆ በዛው ተራራ ላይ መጣ::  አሁን ግን የመጣው ሊፈርድ ነው::

አምልኮንና ዝማሬንም ቀጠሉ ከእነርሱ በቀር ማንም ያልቻለውን  በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤  ስለ አዘማመራቸውና ድምፃቸው ዮሃንስ እንደዚህ ይላል:-  እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ::

እነዚህ ሰዎች ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው።በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም። ምን አይነት ህይወት ነው? በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ አልፈው ለጌታ የኖሩ ናቸው::

ጌታ ይወስደናል! ማራናታ!

ራእይ 14: 6-13

6፤ በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤

7፤ በታላቅ ድምፅም፦ “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት፡” አለ።

12፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው።

13፤ ከሰማይም፦ “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው።” መንፈስ፦ “አዎን፥ ‘ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል’ ብለህ ጻፍ፡” የሚል ድምፅ ሰማሁ።

እዚህ ስፍራ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚያስታውቁ መልአክትን እናያለን::  

የመጀመርያው ወንጌልን ለዓለም ሁሉ የሚሰብክ ሲሆን  የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት ይላል:: 

ሁለተኛው የባቢሎንን መውደቅ እያወጀ ተከተለው::  ስለባቢሎን ገና ብዙ እናያለን በሚመጡት ምዕራፎች::

ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው፥ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ፦ “ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥ እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል።

ለቅዱሳኑ የተባለው ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው። “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው።” መንፈስ፦ “አዎን፥ ‘ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል’

በዚህ ሁሉ ውስጥ እራሱን ያለ ምስክር የማይሰጥ ጌታ ልጆች አሉት ::  በመጨረሻው ዘመን አውሬው ጊዜ እንደሌለው አውቆ የእግዚአብሔርን ህዝብ መግደል ነው ስራው ጌታም ብፁዓን ብሎ ይጠራቸዋል::  

ራእይ 14:  14-20

14፤ አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው።

18፤ በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን፦ “ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቍረጥ፡” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ::

እዚህም ቦታ ላይ የሰውን ልጅ የሚመስልና በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል  ያደረገ ካለ እየሱስ ማን ሊሆን ይችላል?  በነጭ ደመና ላይ ተቀምጦ በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው። ይህንንም ማጭፍ የሚጠቀመው የደረሰውን መከር ለመሰብሰብ ነው:: “የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፥ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና፡” ብሎ አንድ ሙልአክ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።  ከመድረስም አልፎ ጠውልጏል ነው የሚለው ጌታን ይህን ያህል ነው የታገሰው ሰዎች እንዲድኑ ብሎ:: በወንጌል መጽሐፍ ላይ አንተ ስንዴ ዘራህ እንክርዳዱ ከየት መጣ እናስወግደው ወይ ብለው ቢሉት ተውት አብሮ ይብቀል እንዳለ አብሮ በቅሎ ዛሬ ግን ስንዴው ወደ ጎተራው እየተሰበሰበ ነው በራሱ በጌታ::  በማቴዎስ 13:30፤ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን፦ እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ፡’ አለ።” ማቴ 13: 24-43 ጌታ ስለ ሙጨረሻው ዘመን በደንብ ነግሮናል::

እንደገናም ደግሞ  እዚህ ስፍራ ላይ የወይን ዘለላዎች ቁረጥ ይላል::  ቅዱሳን በወይን ግንዱ ላይእንደተተከሉ ቃሉ ይናገራል ይህም ጊዜ ህዝቡን ወደ ቤቲቱ ጌታ እየሰበሰበ ነው::  በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን፦ “ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቍረጥ፡” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ::

ይህንን ምዕራፍ ስናይ ለምዕራፍ 13 መልስ ነው::  አውሬው ፈፅሞ ያሸነፈና ነገርር ሁሉ የተጠናቀቀ ይመስላል ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቁጣ መገለጥ ስናይ ህዝቡን ሰብስቦ ሲያበቃ በቁጥር 20፤ የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ። ውጊያው ከእየሱስ ጋር ይሆናል ይህም አርማጌዶንን የሚገልፅ ይመስላል ምክንያቱም ምዕራፉን ስንጀምር በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ተገልጧል::

ድል ለአምላካችንና ለእኛም ለህዝቡ ነው!!!!  ክብር ይሁንለት!

ራእይ 15:1-4

1፤ ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በእነርሱ ስለሚፈጸም ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት ታዩ።

2፤ በእሳትም የተቀላቀለውን የብርጭቆ ባሕር የሚመስለውን አየሁ፥ በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቍጥር ላይ ድል ነሥተው የነበሩት የእግዚአብሔርን በገና ይዘው በብርጭቆ ባሕር ላይ ሲቆሙ አየሁ።

3-4፤ “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ 

የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ 

መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ 

ጌታ ሆይ፥ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? 

አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፥ 

የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ፡” እያሉ የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ።

ዮሃንስ ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፤  ሲል ምን ይሆን ያሰኛል ያየው ግን የእግዚአብሔር ን ቍጣና  በእነርሱ ስለሚፈጸም ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት ነበረ።   ይህንኑ ቃል በዘሌዋውያን 26:21፤ “ ‘በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ ባትሰሙኝም፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ።  ይህንኑ ነው በምድር ላይ እያደረገ ያለው እንደተናገረው::

እነዚህ ሰባት መቅሰፍቶች በማይታዘዙት ላይ የመጡ ናቸው:: ለታዘዙትና አውሬውን ድል ነስተው ለመጡት  ደግሞ:- የእግዚአብሔርን በገና ይዘው በብርጭቆ ባሕር ላይ ሲቆሙ አየሁ።  እነዚህ ቅዱሳን ምንም እንኳን አውሬው ድል  እንዲነሳቸው ስልጣን ቢሰጠውም የእርሱን ቁጥር ግን አልተቀበሉም:- በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቍጥር ላይ ድል ነስተው የመጡ ናቸው::

እነዚህ ድል የነሱ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ ይላል::  ለምን ሁለቱ በአንድ ላይ ተጠቀሰ? ምክንያቱም ህግን ፈጽሞ በፍቅር አቅፎናልና ነው ብሉይም አዲስም ኪዳንን አዋህዷል ጌታ::  የሚገርመው  በገናን ይዘው ማምለክ ቀጠሉ የከፈሉት የህይወት ዋጋ በሞት ማለፋቸው ትዝም ሳይላቸው አንተ ይገባሃል እያሉ አምልኳቸውን ቀጠሉ!!!  ሰይጣን ከመጀመሪያውም የአምልኮ መሪ ነበረ ዛሬ ደግሞ የገደላቸው ቅዱሳን የእርሱን ስፍራ ይዘው አመለኩት:- አምልኮ የሚገባውን::  በገና ይዘው ያየነው በምዕራፍ 5 ላይ እንሰሶቹና ሃያ አራቱን ሽማግሌዎች ነበር አሁን ግን ይህ ሰራዊት ያመልካል::  በዝማሬያቸውም ጌታን የአህዛብ ንጉስ እንዲሁም የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ እያሉ ነው የሚዘምሩት::  እኛም አህዛብ የሆንን አምነንና ጽድቁን አጣጥመን እያመለክነው ነው ደግሞም እናመልካልእን::  ሃሌሉያ!!!

ራእይ 15: 5- ራእይ 16:7

5፤ ከዚህም በኋላ አየሁ፥ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፥

6፤ ሰባቱንም መቅሠፍት የያዙ ሰባቱ መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፤ ከተልባ እግርም የተሠራ ጥሩ የጌጥ ልብስ ለበሱ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጠቁ።

8፤ ከእግዚአብሔርም ክብርና ከኃይሉ ጢስ በመቅደሱ ሞላበት፥ የሰባቱ መላእክት ሰባቱ መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ አንድ እንኳ ወደ መቅደሱ ይገባ ዘንድ አልቻለም።

ራእይ 16:1፤ ለሰባቱም መላእክት፦ “ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ፡” የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ።

በላይ በሰማይ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ ይላል ዮሃንስ:.  ሙሴ እንደምታየው ስራ የተባለው ይህንን እያየ ነበረ::  ሰባቱንም መቅሠፍት የያዙ ሰባቱ መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፤ የእግዚአብሔር መታገስ ሁሉ እንዲድኑና ንስሃ እንዲገቡ ነው እንጂ ፍርድማ ይቀጥላል::

ልክ በሙሴ ዘመንና ሰለሞንም ቤተ መቅደሱን ሲያስመርቅ ከእግዚአብሔር ክብር የተነሳ ማንም ሙንቀሳቀስ እንዳልቻለ ሁሉ እዚህም ጋር የምናየው ይህንኑ ነው መልአክቱም መግባት አልቻሉም::  ከእግዚአብሔርም ክብርና ከኃይሉ ጢስ በመቅደሱ ሞላበት፥ የሰባቱ መላእክት ሰባቱ መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ አንድ እንኳ ወደ መቅደሱ ይገባ ዘንድ አልቻለም።

እነዚህ ሰባት መልአክት ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ ተባሉ::  እነርሱም አፈሰሱ ሰዎች ግን እግዚአብሔርን ይሳደቡ ጀመር እንጂ ንስሃ አልገቡም:,  የእግዚአብሔር አላማ ጠላት ላይ መፍረድና ሰዎችን ደግሞ ለማዳን ነበረ::

ይህ ሁሉ ቁጣ በምድር ላይ እየመጣ ያለው መልአክቱ እንደሚሉት:-

እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤

የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና::  ከመሰዊያውም እንዲህ ብሎ ሲናገር ሰማሁ፦ “አዎን፥ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው።

እርሱ እውነተኛ እንጂ ፍርደ ገምድል አይደለም:: ስለተገደሉት ቅዱሳን በቀል ነው::  እረፍት እንዲያደርጉ ተነግሯቸው ነበረ መቼ ነው የምትፈርድልን ሲሉት::  ፍርዱን አየን!

ራእይ 16: 8-21

8፤ አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት።

10፤ አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች ከስቃይም የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፥

15፤ “እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።”

16፤ በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ አስከተቱአቸው።

17፤ ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ፦ “ተፈጽሞአል፡” የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ።

ሰባቱ መቅሰፍቶች በዚህ ምዕራፍ ላይ በምድር ሲፈሱ እናያለን::  ከነዚህም መካከል:- 

ፀሃይ እንድታቃጥል ተሰጣት ይህ ማለት የኦዞን መቀደድ እያሉ የሚሉት ይሆን ወይስ ከዛም የከፋ ይመጣል? ለበረከት የተሰጠን ፀሃይ ለጥፋት ልትሆን ነው::  

ጨለማም በምድር ላይ እንዲሆን ልክ ግብፅ ላይ እንደመጣው መቅሰፍት :  

የኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ ማለትም ለጦርነቱ ለመክተት ለምድር ነገስታት  የተዘጋጀ ነው::  አሁንም ወንዙ እየደረቀ ነው:: መጨረሻው ላይ እንዳለን እናስተውል::

ይህ ሁሉ ግን ሲኦልን ቅመሱትና ንስሃ ግቡ ወደ እኔ ተመለሱ እያለ ባለበት የሰው ልጅ ግን የቀናው መሳደብ ነበረ:: ስለዚህ ጌታ ተፈጸመ አለ ትዕግስት አበቃ ልብስህን ጠብቅ እንደሌባ እመጣለሁ አለ::

በእንቁራሪት የተመሰለ አሳች መንፈስ ነገስታትን ሁሉ ወደ አርማጌደን አሰለፈ መንግስታት ከእግዚአብሔር ጋር ሊዋጉ::  ውጤቱ የታወቀ ነው::  በጉም በጽዮን ተራራ ላይ ተገጧል ድል ይነሳል::  ማንም አይቶት የማያውቅ የመሬት መናወጥ ሆነ ደሴቶችም ሸሹ ተራሮችም አልተገኙም ይህ የእግዚአብሔር ቀን ነው!  ድል ለነሳው ክብር ይሁን! 

ጌታ ይመጣል!  ልብሳችንን ለብሰን ተዘጋጅተን ሳንዘናጋ እንጠብቅ!

ራእይ 17: 1-18

1፤ ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፦ “ና በብዙም ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤

ራእይ 17:6፤ ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ።

8፤ ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ። 9፤ “ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፥ 10፤ ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።

14፤ እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።”

ሰባቱን የእግዚአብሔርን ቁጣ የያዙ መልአክት በምዕራፍ 16 እድወጡና ቁጣውም በምድር እንዳፈሰሰው አይተናል::  ግን እነማን ተቀጡ የሚለውንም ትንሽ ነግሮናል:- 

ራእይ 16:6፤ የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና።” ይላል::  ይህ ምዕራፍ ጠለቅ ብሎ ከነምክንያቱ ይመልስልናል:: የምትቀጣውም በብዙም ውኃዎች ላይ የተቀመጠችው ታላቂቱ ጋለሞታ ናት::

ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።”  አለኝም፦ “ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፥ ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው::  ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት እንደሚል ቅጣትዋን ትቀበላለች:: በዓለም ሁሉ የተንሰራፋ ግድያ ነው የተፈጸመው በእግዚአብሔር ምርጦች ላይ ስለዚህ ፍርድ ግድ ነው:: እነዚህ ነገስታት ለጠላት የተገዙ እርሱ እንደወደደ የሚዘውራቸው ናቸው::

እነዚህ ህዝቦችና ነገስታት ፍጥረት መሆናቸውን ረስተው ከፈጣሪ ጋር ለመዋጋት አሰቡ::  ሁሉ ተሰብስበው በጉን ሲዋጉ በጉ በድል አድራጊነት ይወጣል::  ይህ ብቻ አይደለም  ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።” እርሱ ባገኘው ድል የዳኑትም ድል ይነሳሉ ይላል::  ምን አይነት ጌታ ነው? ስሙ ይባረክ! ጌታ ሁሌም ድል ይነሳል! 

ድል ለነሳው ክብር ይሁን::

ራእይ 18: 1-24

1፤ ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች።

2፤ በብርቱም ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፥ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤

4፤ ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ “ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤

5፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።

በዚብ ምዕራፍ ላይ የምናየው የባቢሎንን መቀጣትና መጥፋት ነው::  በምዕራፍ 17ም ላይ ይህንኑ አይትእናል ታድያ ሁለት ባቢሎን አለ ወይስ በመንፈሳዊውና በኢኮኖሚው ነው ሁለት የሆኑት?  ይህችኛዋ እየደቀቀች ያለችው በሃብትዋ ነው:: 

እግዚአብሔርም  ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ይላል::  በዚህ ዘመንም ህዝብ አለው አምላካችን ጠላት በብዙ ኃይሉ እየሰራና ቅዱሳንን እየገደለ ባለበት ጊዜ::

የመጨረሻው ሰዓት ነውና ሁሉ የጠላት አሰራር እየተደመሰሰ ያለበት ጊዜ ነው::  ማን ከበጉ ጋር ተዋግቶ ያሸንፋል?  ቅጣቱን ሁሉ ይቀበላል በጠላት እጅ ላለፉት ጌታ ይይልይቸው ሌሎችምአሉና እስኪመጡ አረፍ በሉ ነበረ::  ይኸድ አሁን ዘመን መቶ ለልጆቹ እየተበቀለና ክቡር መሆኑን እያሳየ ነው::  ባቢሎን ወደቀች!

ጌታ ይከብራል ይነግስማል::  አሜን!

ራእይ 19: 1- 1-4

1-2፤ ከዚህ በኋላ በሰማይ፦ “ሃሌ ሉያ፤ በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት፥ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፥ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው፡” ብሎ ሲናገር እንደ ብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምፅ ያለ ድምፅን ሰማሁ።

3፤ ደግመውም አሉ፦ “ሃሌ ሉያ፤ ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።”

4፤ ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር፦ “አሜን፥ ሃሌ ሉያ፡” እያሉ ሰገዱለት።

እዚህ ስፍራ ላይ እግዚአብሔርን እያመለኩበት ያለው ምክንያት በባቢሎን መቀጣት ምክንያት ነው::  

1.  የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፥ 

በምዕራፍ 6:10-11፤ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” አሉ። 11፤ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው። ልክ እንደተናገረው ቁጥሩ ሲፈጸም ፍርዱን አደረገ::  

እንዲሁም ደግሞ  በራእይ 18:24፤ በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።”

2.  ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና 

የእግዚአብሔር ፍርድ ጽድቅን የተሞላ ነው::  በራእይ 16:5፤ የውኃውም መልአክ እንዲህ ብሎ ሲናገር ሰማሁ፦ “ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፥ ቅዱስ ሆይ፥ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤

3.  ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው፡”

ይህንን በሰሙ ጊዜ ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር፦ “አሜን፥ ሃሌ ሉያ፡” እያሉ ሰገዱለት።

ዛሬም እኛ ሃሌ ሉያ እያልን ለዚህ ፃድቅ ለሆነ ፈራጅ እያመለክን እንሰግድለታለን::  የምናየውን ሁሉ ውጥንቅጥ ፀጥ አድርጎ የሰላሙን መንግስት በሰማይ ለዘረጋው ወደ እርሱም ለሚወስደን ጌታ ክብር ይሁንለት::  እናመልከዋለን፦ እንባርከዋለን ደግሞም እንገዛለታለን፦ እንታዘዘውማለን:: አሜን!!!

ራእይ 19: 5-10

5፤ ድምፅም እንዲህ ሲል ከዙፋኑ ወጣ፦ “ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፥ አምላካችንን አመስግኑ፡”

6፤ እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምፅ፥ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ “ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና።

7፤ የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ።

8፤ ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ተሰጥቶአታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና።”

9፤ እርሱም፦ “ ‘ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው፡’ ብለህ ጻፍ፡” አለኝ። ደግሞም፦ “ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው፡” አለኝ።

10፤ ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና፡” አለኝ።

በብዙዎች እየተመለከ ነው የእኛ ጌታ ድምፃቸው ይገርማል ቃሉ እንደሚል  እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምፅ፥ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ::  ይህ ህዝብ እኮ አስር ሺ ወይም አንድ ሚልየን ብቻ አይደለም በጣም ብዙ ነው በጌታ ፀድቆ ለአምልኮ የሚቆመው ወደ ሰርጉም የታደመው::ሃሌሉያ እንዴት የሚናፈቅ ቀን ነው በአንድ ድምፅና ቋንቋ ጌታን እንደዚህ ድብልቅ በሚያደርግ አምልኮ ስፍራውን ሁሉ መሙላት?  “ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፥ አምላካችንን አመስግኑ፡” እንደሚል እናመስግነው የበጉ ሰርግ ደርሷልና ሙሽራይቱም እራስዋን አዘጋጅታለች::

ከእርስዋ መዘጋጀት በላይ እርሱ እንዴት እንዳዘጋጃት እንይ:-

ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ተሰጥቶአታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና።” ይህንን የጽድቅ ስራ የሰራው ማነው እራሱ ነው በመስቀል ላይ ስሙ ይባረክ::  እርሱ እራሱ ነው ቤተክርስቲያኑን ያዘጋጀው አስጊጦና አዲስን የፅድቅ ልብስ አልብሶ::  ሃሌሉያ ጌታ ሊመሰገን ይገባዋል::

ደግሞም “ ‘ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው፡’ ብለህ ጻፍ፡” አለኝ። ደግሞም፦ “ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው፡” ብፁአን ተብለን ተጠራን እርሱ በሰራው ፅድቅ::

መለአኩ እንዳለው የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ አለው ስግደት ለመለአክት አይገባም ለበጉ እንጂ!  የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና፡” አለኝ። የእየሱስ መንፈስ ስለእርሱ ይመሰክራል ክብርንም ለእርሱ ያመጣል እንጂ ፍጥረት እንዲቀበል አምልኮን አያደርግም:.  ስለዚህ ከእኛ ጋር መልአክት ጌታን ያመልካሉ::

 “ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና። አሜን!!!

ራእይ 19: 11-15

11፤ ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም።

12፤ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤

13፤ በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።

15፤ አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ “እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤” እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል።

ሰማይ ተከፍቶ ዮሃንስ ያየው ማንን ነው?  እየሱስን ነው እርሱም በፈረሱ ላይ ተቀምጧል:-

1.  የታመነና 

2.  እውነተኛ ይባላል፥ 

3.  በጽድቅም ይፈርዳል 

4.  ይዋጋልም

5.  ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ 

6.  በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ 

7.  ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤

8.  በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ 

9.  ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።

ይህ እውነተኛና የታመነው በጽድቅም የሚፈርደው ጌታ ይዋጋል::  እየሄደ ያለው ወደ ጦርነት ቢሆንም ቅሉ እንደጦረኛ የታጠቀው መሳሪያ የለውም:: ታድያ በምን ይዋጋል?  መልሱ በቃሉ ነው::  አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል::  የጌታ ስም ማነው ብንል? ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።  

ልብሱ በደምየተረጨ እንደሆነ ይነግረናል የማን ደም ይሆን ገና ጦርነቱ አልተጀመረ? የራሱ ይሆን? የሚገርመው አስከትቶ የመጣውን ጦር ስናይ:- በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። እነሱም መሳሪያ አልያዙም::  ምን አይነት ዘመቻ ነው?  በጉ ብቻውን በቂ ነው ተከታዮቹ መዋጋትም አያስፈልገንም ድሉን ከእርሱ ጋር ማጣጣም እንጂ!!  በነበልባል አይኖቹ እያየ ፍርድን እዛው ይሰጣል እርሱ የታገሰው ሰዎች እንዲድኑ ነበረ::

በራሱ ላይ ብዙ ዘውድን የጫነውጌታ ድል የሚነሳና ፃድቅ ጌታ ነውክብር ይሁንለት!!

ራእይ 19: 16-21

16፤ በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት፦ “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ፡” የሚል ስም አለው።

:9፤ በፈረሱም የተቀመጠውን ጭፍራዎቹንም ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ጭፍራዎቻቸውም ተከማችተው አየሁ።

20፤ አውሬውም ተያዘ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ።

21፤ የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ።

የፍጥረት ድፍረት ይገርማል ከእየሱስ ጋር ለመዋጋት ማሰባቸው!!  እርሱ ግን ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተዋጋ ተገደሉም::  በቁጥር 12፤ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ በዚህ ክፍል ደግሞ ጌታችን በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት፦ “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ፡” የሚል ስም አለው።  ይህንን ስም ስም ነው ብለው ሌሎች ላያውቁት ይችላሉ እኛ ግን ህዝቦቹ ይህንን ስም እናውቃለን እርሱ የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ ነው::

ሃሌሉያ!!!!!

ንጉሳችን ታላቁን ፍርድ እዚህ ስፍራ ላይ ሲያደርግ  እናያለን::  የዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ፈጣሪ  የሆነው አውሬውም ተያዘ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ።  የዚህ ሁሉ ሰው መጥፋት ምክንያት ይህ አውሬ ነው:: ጌታችንም ይህንን ጠላት ከነህይወቱ ወደ እሳት ይጥለዋል ልንፈራው ሳይሆን ፍርዱን እንደሚያገኝ አውቀን በድፍረት እንመላለስ::  ጠላት ተሸንፏል የነገስታት ንጉስ ነግሷል:::

አሜን ክብር ይሁንለት!!!

ራእይ 20: 1-3

1፤ የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ።

2፤ የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፥

3፤ ሺህ ዓመትም አሰረው፥ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል።

የሚገርመው ነገር አንድ መልአክ ነው እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣንን የያዘውና ያሰረው ብዙ ግርግር አላስፈለገም::  ስለያዘው መልአክም ምንም መግለጫና ስልጣኑን ነገር ሲነገር አናይም ስልጣን ያለው ወይም ታላቅ መልአክ አይደለም የመጣው::  ጊዜው ሲደርስ እንደዚህ በቀላል ይያዛል ለእግዚአብሔር አቻ ወይም እኩያ አይደለም ሰይጣን ፍጥረት ነው ስለተለቀቀ እንጂ ዓለምን ያመሰው ይህንን ያህል የወደደውን ለማድረግ ስልጣን ስላለው አይደለም::  ከአዳም የወሰደው ስልጣን ሁሉ ተወስዶበታል በሁለተኛው አዳም:: መልአኩም ያደረገበትን ስናይ:- 

–  ሺህ ዓመትም አሰረው፥ 

–  ወደ ጥልቅም ጣለው 

–  አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ 

–  ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል።

ይህንን ሁሉ ያደረገበት አንድ መልአክ ነው::  ጊዜው ሲደርስ ባይፈታው እራሱን እንኳን ነፃ የማያወጣ ተራ ፍጥረት ነው::  የሚደረግበት ነገር ደስ ይላል መታሰር ወደ ጥልቅ መጣል::  እርሱ የሚያውቀው ማሳት ነው ይሄውም  አቅም ከእርሱ ተወሰደበት::  ተዘግቶበት ማኅተምም ተደረገ መልሶ እንዳያስት::  ሽንገላው ከሄዋን አንስቶ እስከዛሬ የሰውን ልጅ አሰቃይቷል ከእግዚአብሔርም ጋር አጣልቷልና ይህ የተደረገበት ይገባዋል::

እዚህ ስፍራ እባቡ ሲታሰር እርሱ እየሾመ ና የላካቸው ከውሃ የወጣው አውሬና ህዝብን ሁሉ ተአምራት እያደረገ ያሳተስ ነብይ በህይወት የነበሩ ናቸውና ከነህይወታቸው ወደ እሳት ባህር ጌታ እንደጣላቸው ቅጣታቸውንም እንዳገኙ በምዕራፍ 19 አይተናል::

ይህ ሁሉ ዝግጅት ጌታ በምድር አንድሺ አመት ስለሚነግስ ነው::  ጠላት ምንም እድል የሌለው የተሸነፈ ኪሳራን የተቀዳጀ ፍጥረት ነው:: የእኛ ጌታ ግን በዙፋኑ ላይ ከብሮ ነገሮችን ሁሉ ባቀደው መሰረት እየተገበረ ያለ ንጉስ ነው::  ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም ከፍ ይበል::   በምድርም ከህዝቡ ጋር ይነግሳል::  አሜን!!

ራእይ 20: 4-6

4፤ ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ።

ራእይ 20:5፤ የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም። ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው።

ራእይ 20:6፤ በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።

ህይወታቸውን በጌታ ምክንያት ያጡት ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ይነሳሉ::  እነዚህ ሰዎች ቢኖሩ 80 ወይም ግፋ ቢል 120 ዓመት ነበረ ህይወታቸውን ጠላት ባያጠፋው ኖሮ ጌታ ግን የተሻለ እድል ሰጣቸውና ለአንድ ሺ ዓመት ከእርሱ ጋር ይኖራሉ::  መነሳት ብቻ አይደለም በ2:26-27፤ ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፥ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፥ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ እንደቃሉ ስልጣንም ይሰጣቸዋል::

ሌሎቹ ሙታን ግን በዚህ ጊዜ አይነሱም:: 

ይህ ፊተኛው ትንሳኤ በእየሱስ ምክንያት ያለፉት የሚነሱበት ነው ካህናትም ይሆናሉ ይላል ምክንያቱም ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉት ናቸውና::

እስከመጨረሻው መፅናት ይሁንልን::

ራእይ 20: 7-10

7፤ ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፥

8፤ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው።

9፤ ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው።

10፤ ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።

የሺ ዓመቱ መንግስት የሚመራው በጌታ እየሱሰ ነው::  ሰይጣንም ታስሯል ሰው ሁሉ በነፃነት ያለ ተፅኖ ጌታውን እያመለከ በሰላም የሚኖርበት ዘመን ነው::  ልክ ሰይጣን ሲፈታ የባከነውን ጊዜ ማካካስ የፈለገ ይመስላል::  ከምኔው የሚከተለው ሰራዊት መለመለ::  በምድር ላይ የነበራት ሰዎች እኮ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው ህይወታቸውን ሳይሰስቱ በሞት ያከበሩት ነበሩ::  ትውልዳቸው ምንም እንኳን በዚህ እግዚአብሔርን በማወቅ ቢያድግም ወደ ክፉ የሚገፋው ጠላት ባይኖርም እንኳን ይኸው ከጠላት ጋር ለመግጠም ጊዜም አልወሰደበትም:: ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው ይላል። እንዴት እንደዚህ ሊሆን ቻለ? የሰው ክፋት ውስጡ ነው ማለት ነው:: ይግርማል!

ይህም በጠላት የሚመራ ሰራዊት የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው። እግዚአብሔር ላይ መፍረድ አይቻልም ምን ማድርእግ ይቻላል ይህ ሁሉ ህዝብ እንደገና በጠላት ተታለለ::  በደሙ አጥቦ መንፈሱን ሰቶ ቤተክርስቲያንን ነበረ በምድር ላይ እንድትኖር የፈቀደው ታድያ ከመቼው የሰው ልጅ ጌታውን ጥሎ ከጠላቱ ጋር አበረ?!

ፍርዱ በሰዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ባሳታቸውም ላይ ነበረ::  ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።

የጠላት ፍፃሜ በእሳት ባህር መኖር ነው ፍርዱንም ያገኛል::  አምላካችን ለዘላለም ይነግሳል!  ክብር ይሁንለት!

ራእይ 20:11፤ ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም።

ይህ ዙፋን ታላቅ የተባለበት ምክንያት ከዚህ የሚበልጥ ስልጣን እንደሌለ ለማሳየት ሲሆን ነጭ መሆኑ ደግሞ ንፁህነቱንና ቅድስናውን ያሳያል::  የእኛ ጌታ በጽድቅ ይዳኛል ዳኝነቱም እንከን የለውም::  ለምን ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም?  ከሱ ፊትስ ወዴት ተሸሽቶ መደበቅ ይቻላል? 

ዙፋን የተዘረጋው በክርስቶስ ለምናምነው አይደለም ለማያምኑት ነው የእኛ ኃጥያት አንድ ጊዜ በክርስቶስ ላይ ሆነ::  በልጁ የሚያምን አይፈረድበትም ያላመነው ግን ይፈረድበታል::  ይህ ማለት ግን ያለምንም ኢንቨንተሪ ወደ መንግስቱ ይገባል ማለት አይደለም እንዴት እንዳገለገልን ጌታ ይመዝናል ስራችንን::  በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን ለሽልማት::  ለሰባቱ አብያተ ክርስትያናት በተፃፈው ክፍል ላይ ድል ለነሳ የተለያየ ሽልማት እንዳለ እናያለን::  ይህንን ደግሞ ጳውሎስ በአንደኛም በሁለተኛውም የቆሮንቶስ መልክቱ ነግሮናል::  እንዴት ነው ይህንን ጌታ እያገለገልን ያለነው?  ዛሬ እድሉ እያለን ምን እየሰራን ነው?

1 ቆሮንቶስ 3:12፤ ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ 13፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።

14፤ ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤

15፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል።

2 ቆሮንቶስ 5:10፤ መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና።

ጌታ ማስተዋልን ይስጠን ፀጋውንም ያብዛልን! 

ራእይ 20: 12-15

12፤ ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።

13፤ ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ።

14፤ ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።

15፤ በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።

የገረመኝ ነገር ሞት በእርሱ ዘንድ ያለውን ሙታን ሰጠ ማለቱ ነው:: ሞትም ስፍራ አለው ማለት ነው ሙታንን የሚያስቀምጥበት?  ሲኦል እሺ ይስጥ ባህርም እሺ የሞት ግን እንደዚህ መሆኑ ገርሞኛል:: 

የነጩ ዙፋን ፍርድ ክርክር የለውም ስሙ በህይወት መጽሐፍ ያልተገኘ ሁሉ ይፈረድበታል::  በክርስቶስ ላለነው ፍርድ የለብንም በአባትና በመልአክቱ ፊት እመሰክራለሁኝ እንዳለን የምንፈራው ምን እሆን ይሆን ብሎ የሚያስብለን ነገር የለም::  የፍርድ ቀን እንዳለ ጌታምነግሮን የለም? በማቴዎስ 11:22፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።

ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ሞት ማለት ከህይወት መለየት ብቻ ሳይሆን እራሱን የያዘ ማንነት ያለው ነው ማለት ነው::  ሲኦል ማለት እራሱ እሳት ያለበት ቦታ አይደለም ማለት ነው?  እንደገና ወደ እሳት ባህር የሚጣለው::  ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።

ስሙ በህይወት መጽሐፍ ላይ ያልተገኘው ሁሉ ወደ እሳት ባህር ነው የሚጣለው::  አይዘገንንም?  ዛሬ ቀን ሳለ ለጌታ ሰዎችን እንድንዋጅ ለክብሩ በወንጌል እንድንደርስ ጌታ ይርዳን::  ምርኮ ለጌታ በእኛ ውስጥ ይምጣለት::  መናጠቅ ይሁን ዛሬ!

ጌታ ሆይ የሰዎችን ልብ እንደ ሊድያ ልብ ከፍተህ ስጠን!  እየሱስ በፍጥረት ሁሉ ዘንድ ይሰበክ ሲኦል ይክሰር ዛሬ

አሜን!

ራእይ 21: 1-8

1፤ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም።

2፤ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።

3፤ ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ “እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤

4፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና፡” ብሎ ሲናገር ሰማሁ። 

7፤ ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።

የአዲስ ሰማይንና አዲስ ምድር መጠቀስ ብዙ ነገርን ይለውጣል::  አዲስ ሲባል ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ የተዘጋጀ የሚያምርም ነው የምትወርደውም ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው::  አዲስ የሚሆነው ምድሩና ሰማዩ ብቻ ሳይሆን አሰራሩም አዲስ ነው::  እራሱ ጌታ ይገኛል:-

እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥  በሙሴ ዘመን ነው ድንኳን የነበረው እግዚአብሔር ብቻውንእንጂ በሰፈሩ መካከል አልነበረም በእሳትና በደመና ይመራቸው ነበር::  የሚነጋገረውም ከሙሴ ጋር ብቻ ነበር::  ይህ ግን ተቀየረና ሁላችንንም ህዝቡ አደረገን::

እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤

ከእኛ ጋር መሆኑ የሚታወቀው:- 

– እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ 

– ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ 

– ኀዘንም ቢሆን ወይም 

– ጩኸት ወይም 

– ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ 

– የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና፡

– መገኘት የማይገባውም አይገኝም:-የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።

ይህንን ሁሉ የሚያስቀር አዲስ አሰራር ጌታ ያመጣል:: መንግስተ  ሰማይን ልዩ የሚያደርገው በወርቅ መሰራቱ ወይም የሳሩና የአትክልቱ ማማር ሳይሆን የእግዚአብሔር መገኘት ነው:: የተሰጠንም የተስፋ ቃል ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። አሮጌው አልፏል!  ይህንን ሁሉ የሚያወርሰን በልጁ ስለዋጀን እንጂ የተገባን ሆነን አይደለም::  ስሙ ይባረክ! 

ራእይ 21: 9-27

10-11፤ በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤

22፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም።

23፤ ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር።

24፤ አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤

25፤ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥

27፤ ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።

ስፍራን ላዘጋጅ እሄዳለሁ እንዳለን አዘጋጅቶ እርሱ ባለበት እንድንገኝ  ይወስደናል::  ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም አሁን ማሰብ ከምንችለው በላይ ልዮ ቦታ ነው ነገር ግን የምንደነቀው በስፍራው ማማር ሳይሆን በእግዚአብሔር ክብር ነው:: ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር። ምን አይነት ስፍራ ነው? ክብሩ የሚያበራበት?!  በጉ መብራት የሆነበት ስፍራ!  የተፈጥሮው መብራቶችም አያስፈልጉም በዚያ ቀንና ለሊት የለም::  ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም። መኖርያችን እርሱ ነው!! በምንም ነገር ላይ ጥገኛ አንሆንም::

ይህ ስፍራ ሁሉ አዲስ የሆነበት ነው:: ድካም የለም ለሊት የተሰጠን ስጋችን እንንዲያርፍ ነው ያኔ ግን ለአሰራሩ እንዲመች አድርጎ ይለውጠናል ከመቅጽበት ያንን የማይሞተውን እንለብሳለን::  ሃሌሉያ!!!

በምድር ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች በግራም ይገዛሉ እዛ ስንሄድ በሮቹ ከአንድ ወጥ እንቁ የተሰሩ እንዲሁም ከወርቅ የተሰራ ነው:: ወርቁና እንቁውን የሚያስንቅ የእግዚአብሔር ክብር ግን ገና ያስደንቀናል::

በዛም መገኘት የሚችሉት ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተፃፉት  በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።  ይህንን ቀን እናፍቃለሁ!!

 በክብሩ እየሰከሩ ማምለክ ብቻ ያለበት ስፍራ ማንም ማንንም የማያይበት የሁሉ አይኖች በጌታቸው ላይ የሚሆንበት ሰይጣንና ሰራዊቱ የሌሉበት በሰላምና በእረፍት  የተሞላ ስፍራ:.  ለቅሶ ህመም ችግር የሌለበት ስፍራ ለምርጦቹ ያዘጋጀው ስፍራ::  ዋው ምን እንላለን ጌታ ሆይ ተመስገን አሁን  የምናልፍበትን ውጣ ውረድ ሁሉ የሚያስረሳ ተስፋ ስለሰጠኸን ተባረክ::

ስምህም ይወደስ!!

ራእይ 22: 1-2

1፤ በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ።

ራእይ 22:2፤ በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ።

ዮሃንስ መቼም በተቻለ መጠን በምድርኛ ቋንቋ አዲሲቱን ስፍራ ሊገልጥልን ሞክሯል:: ከዙፋኑ መካከል የህይወት ውሃ ይወጣል::  ይህም ውሃ የህይወትን ዛፍ ያጠጣል የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ::  ይህ የህይወት ዛፍ ነበረ የመባረራችን ምንጭ አሁን ግን ለመፈወሻነት የሚውል ሆነ::  አዳምና ሄዋን ከተባረሩ በኃላ እንዳይደርሱበት ይጠበቅ ነበር ከዚህ በኃላ ግን አይጠበቅም::  ምንም እንኳን የሰዓት  ኮንሰፕት ባይኖርም ፍሬውን ግን ይህ ዛፍ በየወሩ ይሰጣል::  የሚያፈራውም አስራ ሁለት ነው::  በዛ ስፍራ የሚሆነው የሰው ቁጥር ግን ከመቆጠር የሚበልጥ ነው:: ምናልባትም አገልግሎቱ ሌላ ይሆን ይሆናል::  ቅጠሉ ለመፈወሻ ይሆናል እዚህ ስፍራ ደግሞ ህመም የለም ስቃይ የለም::  ስንሄድ እንረዳዋለን::  ሁሉ የሚደንቅ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ::

እንኳን እርሱ አባት ሆነን!

ራእይ 22: 3-4

3፤ ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፥ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፥ ፊቱንም ያያሉ፥

4፤ ስሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል።

አዲሲቱ እየሩሳሌም ውስጥ መርገም ከቶ የለም::  መርገሙማ በምድርበክርስቶስ ደም ታጥቦ ቀረልን ይህች ስፍራ ከዛ የነፃች ናት::  አዲሱን ልብስ ለብሰን በእርሱ ስራ ተውበን የምንኖርበት ስፍራ ነው::  

ይህ ስፍራ የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል ሌላ መቅደስም የለም ሌላ ብርሃንም አያስፈልግም ጨለማና መከራ ስቃይ እንባ በዚህ ስፍራ የላቸውም::  እርሱ በዙፋኑ ላይ ነው ይመለካል ይከበራል!

ሽልማታችን የሚሆነው፥ ፊቱንም እያየንማምለካችን ነው:: አቤት እንዴት ያለ ቀን ነው ያ ቀን?!  የናፈቅነውን ጌታ ፊት ለፊት እያዩ በመደነቅ ማምለክ!!  አሜን ሃሌሉያ!

በዚህ ብቻ አያበቃም ስሙም በግምባሮቻችን ይሆናል።  አሜን ስሙን በግንባራችን ለሚፅፈው ክብር ይሁን::  ያለህን ጠብቅ በቶሎ እመጣለሁ ነው ጌታ የሚለውና ዕለት ዕለት በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት እርሱን እንጠባበቅ:: ሽልማታችንን እናገኛለን::  በፊቱ ከመሆን የሚበልጥ ምን ይኖር ይሆር ይሆን?!

ላሰበን ጌታ ክብር ይሁን!!! የሚጠብቀን የከበረ ህይወት ነውና ዛሬ የከበበንን እያራገፍን ወደፊት እንግፋ የዝች ምድር ነገር ማብቅያ አለው ለዘላለም አይደለም::

ራእይ 22:5፤ 

ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፥ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ።

ይህ የምንወርሰው ስፍራ እንዴት ያለ ነው? 

*  መርገም የሌለበት – የምድር ኩነኔ የለም

*  የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል – ፍጹም የሆነ አስተዳደር ይሆናል

*  ባሪያዎቹም ያመልኩታል፥  አምልኮ ይበዛል

*  ፊቱንም ያያሉ፥ ፊቱን እያየን እንለመልማለን 

*  ስሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል – የርሱ መሆናችን ይታወቃል

*  ለሊት የሌለበት – ጨለማውን ገፎ አስወግዶታል::

*  አምላካችን የሚያበራበት – እርሱ እራሱ ያበራልና አርቲፊሻል ወይም የተፈጥሮም ብርሃናት አያስፈልጉም::

*  ለዘላለም የምንነግስበት – ለመንግስቱ ፍፃሜ የለውምና ልጆቹ አብረን እንነግሳለን::

አቤት እንዴት ድንቅ ነው?! አሰራሩ ሁሉ ከአእምሮ በላይ ነውና ጌታን እንባርክ:: በፊቱ የከበርንበት መክበር የምድርን ነገር ሁሉ የሚያስረሳና ወደ አምልኮ የሚወስድ ነው::  ዕለት ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ እንዳለን ዛሬም አባት ሆይ ሙላን ወደ ፀጋ ዙፋንህም እንቀርባለን ፀጋን እንቀበል ዘንድ በፀጋህ ሁሉ ሙላን::  ስትጠራን የተዘጋጀን እንሁን ከራሳችን አልፈን ሌላውን የምናዘጋጅ አድርገን::  አሜን!

ራእይ 22: 6-7

6፤ እርሱም፦ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ።”

7፤ “እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው፡” አለኝ።

በዚህ መጽሐፍ የተፃፈው ሁሉ የታመነና  እውነተኛ ነው::ይህም የትንቢት መንፈስ መልአኩን ልኮ ለእኛ እንዲፃፍና እንዲደርስ አደረገ::  ይህንን መልክት የላከልን በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር  እንድናውቅ ነው::

 ምንም እንኳን መልአኩ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር  እንደሆነ ቢናገርም ክብደት ለመስጠት እራሱ ጌታ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው፡ ብሎ አለ:: 

ዛሬም መልክቱ ያው ነው ቶሎ እመጣለሁ ቃሌን እያደረጋችሁ ጠብቁኝ ነው::  ጌታ ይመጣል!  ማራናታ!!

ራእይ 22:  8-13

10፤ ለእኔም፦ “ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።

11፤ ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ፡” አለ።

12፤ “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።

13፤ አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።

ራዕዩን አይቶ ሲጨርስ ዮሃንስ በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ። እርሱም፦ “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፡” አለኝ።

መልአክት ከእኛ ጋር አብረው የሚያገለግሉ ናቸው::  አምልኮ ከሰውም ከመልአክም የሚገባው አምላካችን ብቻ ነው::  ጌታ ደግሞ ደጋግሞ የነገረን ነገር እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።

እንደ ስራችን የሚከፍለን እራሳችንን ያዳንን ስለሆንን ሳይሆን በእርሱ ምን ያህል ታምነን ኖርንና አገለገልንን ነው ጥያቄው:: በእርሱ ተደግፈን መመላለስ ይሁንልን:: ጌታ እንድንፅናናበት የሚፈልገው መምጣቱን ነው::  ጠላትም ሊያስጥለን የሚፈልገው ይህንኑ ተስፋ ነው::  ጌታ  ካልመጣ ምንድነው ተስፋችን? እርሱ ግን እንዳለን ይመጣል::  ምክንያቱም አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ ብሏልና:: ጽድቅን በማድረግ እንቀጥል የዓለም ሐጥያት እያንገሸገሸ ከኃጥያት ኃጥያት በማማረጥ ላይ ነን ጊዜው እየከፋ ነው የሚሄደውና ዓይናችንን በጌታና በመምጣቱ ላይ እናድርግ::  እንዳለን ይመጣል!  እንዲያውም ጊዜው ቀርቧል:: ማራናታ! 

ራእይ 22:14-16

14፤ “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። 

15፤ ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።

16፤ “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።”

አዳምና ሄዋን ወደ ህይወት ዛፍ እንዳይደርሱ እግዚአብሔር በኪሩብ አስጠበቀው::  በክርስቶስ ለዳነው በበጉ ደም ለታጠብነው ብጹአን ለተባልነው ደግሞ ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንድንገባ ተፈቀደልን::  በራሳችን ጽድቅ ሳይሆን በበጉ ስራ ኃጥያታችንም በደሙ ተወግዶ መድረስ ቻልን::

እኛ ወደ ህይወት ዛፍና ወደ አዲሲቱ እየሩሳሌም ስንገባ በውጭ ደግሞ የሚቀሩ አሉ::  ዛሬ በዓለም ሳለን ውሸቱ ሌብነቱ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው በእነርሱ ዓይን ቃሉን ለምናውቅ ደግሞ በውጭ እንደሚቀሩ እናውቃለንና ሳንዘናጋ ይህንን የምስራች ወንጌል እንመስክር::

የራዕይን መጽሐፍ በዝችበአንድ አረፍተ ነገር  አፀናው ከእሱ እንደሆነም አረጋገጠልን:- እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ::  ስለመሲህነቱም:- በኢሳይያስ 11:1፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል። እንደሚል ቃሉ ይህ መሲህ ስራውንጨርሶ ስፍራም አዘጋጅቶሊወስደን እየተዘጋጀ ነው::

የንጋት ኮከብ:- በዘኍልቍ 24:17፤ አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል:: ጊዜው ደርሶ ተገልጧል ጌታችን::

ስሙ ይባረክ!!

ራእይ 22:17-22

17፤ መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ “ና፡” ይላሉ። የሚሰማም፦ “ና፡” ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።

20፤ ይህን የሚመሰክር፦ “አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ፡” ይላል።  አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና።

በመንፈስ ቅዱስ ታግዘን እያንዳንዳችን ደግሞም እንደክርስቶስ አካልና ሙሽራ *ና *  እንላለን ::  እርሱ ይምጣልን!

የሚሰማም፦ “ና፡” ይበል። ያልዳነው ጌታን የማያውቀው ሁሉ ይህንን ጥሪ ይጣራ የህይወን ራስ እየሱስን ወደ ልቡም ወደ ምድርም  ይጥራ::  ጌታን የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ::  ይህ የህይወት ራስ እየሱስ ወደ እርሱ ለሚመጡት ሁሉ የህይወትን ውሃ ማንንም ሳይሙርጥና ሳያዳላ ይሰጣል:: ስሙ ይባረክ!

ጌታችን ሆይ ና ብለን ስንጣራ መልሱ፦ “አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ፡” ይላል።  አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና። ማራናታ

ይህንን መጽሐፍ እንዳየነው ብዙ ነገር እንደሚካሄድ አየንበት::  የጌታን ክብርና ግርማ በሰማይም ያለውን አምልኮና ዝግጅት አይተናል::  የእኛ ስራ በጌታ ፀጋ ተደግፈን ዛሬ እንደሚመጣ እየተጠባበቅንና እንዲመጣም እየተጣራን መኖር ፤  ምን ያህል እንደተወደድን አውቀን ጠላታችንን ፀንተን መቃወም፤  ስፍራንም እንዳዘጋጀልን አውቀን ሃሴት ማድረግ ፤  ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ መስበክ ነው ወደዚህ ጌታ ካልመጡ የሚጠብቃቸው የእሳት ባህር ነውና::  

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።

የራዕይን መጽሐፍ በዚህ አጠናቀናል::

ማራናታ!

Published by Betty & Abera

We’re dedicated to share God’s goodness and mercy through His word!

One thought on “የዮሐንስ ራእይ

Leave a comment