መግቢያ:-
ይህ በአለአንድ ምዕራፍ ደብዳቤ የተፃፈው በይሁዳ ነው:: ይህ ሰው የጌታ የእየሱስ ወንድም ነው እራሱን ግን የሚጠራው የያዕቆብ ወንድም ብሎ ነው:: ከወንድምነቱ ይልቅ እራሱን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ብሎ ነው የሚጠራው:: የፃፈበትንም ምክንያት ሲናገር እማኞች ሳይሆኑ አማኝ መስለው የሐሰት ትምህርት ከሚያስተምሩ እንዲጠበቁ ለማስጠንቀቅ የተፃፈ ነው:: እግዚአብሔር ለመዳን አንድ ጊዜ በተሰጠው እምነት እንዲፀኑ ይመክራል::
ይሁዳ 1: 1-2
1፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤
2፤ ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ።
ምንም እንኳን የጌታ ወንድም ቢሆንም እራሱን ባሪያ ብሎ በትህትና መጥራቱ ደስ ይላል:: በማቴዎስ 13:55፤ ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን?
ጌታ እየሱስም ስለቤተሰብ ሲናገር በማርቆስ 3:34፤ በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና፦ “እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። 35፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም፡” አለ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከማድረግ ጋር ነው ያገናኘው:: ይሁዳም ይህንኑ ነው ያደረገው::
የፃፈውም በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር አብ ተወደናል:: እንዲሁም መወደድ ብቻ ሳይሆን ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀናል::
ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ።
ይሁዳ 1: 3-4
3፤ ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።
4፤ ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።
የይሁዳን መልእክት ያስቀየረው መንፈስ ቅዱስ ነው እርሱ መፃፍ የፈለገው ስለተቀበልነው ደህንነት ሆኖ ሳለ ጌታ ደግሞ የፈለገው በሃይማኖት ስለመጋደል ነው እንዲፅፍ ግድ ያለው::
ለምንድነው ስለ ተሰጠን ሃይማኖት መጋደል ያለብን? ይህ እምነት ወይም ሃይማኖት አንድ ጊዜ ተሰቶናል መጋደልን ምን አመጣው? ጌታ የሚያውቀውና የሚያየው ነገር ስላለ ነው እንዲፃፍልን ያደረገው::
በመፅሃፉ መግቢያ እንደነገረን በጌታም ተወደንና ለክርስቶስ እንደሚገባ ሆነን ተጠብቀናል :: የሚጠበቅ ነገር ዋጋ አለው:: አንድ ዳይመንድ የሚሸጥበት ሱቅ ብንሄድ በካሜራ እንዲሁም ሴኩሪቲ ሲስተሙ ከተነካ ከፖሊስ ጋር የተገናኘ ነው ግን ምስኪን ሱቅ ስንሄድ እንደዛ አይደለም:: የሚጠበቀው ውስጡ ካለው ሃብት የተነሳ ነውና እኛም ውስጥ ክርስቶስ ስላለ አብ ልጁን በእኛ ውስጥ እያየ ወዶን ያስጠብቀናል ለመምጣቱ የተዘጋጀን እንድንሆንና በጠላት እንዳንዘረፍ ያስጠብቀናል:: ዋጋችን ከፍ ያለ ነው!!
እርሱ እንደዚህ እያስጠበቀን ነውና እኛም እንተባበር:: የህይወታችን ዋጋ ከፍ ያለ ነውና እንጋደል:: መጋደል የአንድ ጊዜ ትዕይንት አይደለም ቀጣይነት ያለው ነው:: ባላጋራችን ዲያቢሎስ በዙሪያችንን ይዞራል ያለ እረፍት ስለዚህ የነቃን ስር የሰደድን እንሁን:: በቆላስይስ 2:7፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ።
እንደሚገባ በቃሉ የማይኖሩ ቃሉንም እንደወደዱ የሚያጣምሙ ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተው እንዳያታልሉን እንጠንቀቅ:: በስተመጨረሻ አላውቃችሁም የሚባሉ ናቸውና ደህንነታችንን ዕለት ዕለት እንጠብቅ::
ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ:: ይህንን በብዙ መልኩ እያየን ነው በስጋ የማደርገው ኃጥያት ምንም አይደለም የጸጋ ዘመን ነው እያሉ የከበረውን የሚያስጥሉ አሉና ቅድስና ለእግዚአብሔር ልንል ይገባል ይህ ስጋችን የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ነውና በቅድስና መጠበቅ አለበት:: ይህነው መጋደል ፋራ አመነፈስሽው ሊያስብል ቢችልም ጸጋውን እንዳናጣጥል እንጠንቀቅ:: በማይመች አካሄድ እንዳንጠላለፍ እንጠንቀቅ::
ደግሞም እኛም አምላክ ነን የሚሉ እያደረጉ ያሉት ነገር ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን መካድ ነው። እርሱ ብቻ አምላክ ነውና ከምንሰማው እየተጠነቀቅን መጋደላችንን እንቀጥል::
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ይሁዳ 1:5፤ ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ።
በእምነት ተጋደሉ የሚለውን ለማጉላት እግዚአብሔር የማያምኑትን እንዴት እንዳጠፋ እንድናስተውል ይነግረናል:: ከግብፅ ህዝቡን ለምንና እንዴት አዳነ? በዘጸአት 3:9፤ አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። 10፤ አሁንም ና፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ።” ብሎ ሙሴን ላከ:: ሲያወጣቸውም በኃይልና በተዘረጋች ክንድ ነበረ:: ሊያወጣቸውም የመጣበት ምክንያት ቃሉን ለመጠበቅ ነው ለአብርሃም ቃል ገብቶ ነበረና:: ምን የሚል ቃል? ትውልድህ ባሪያ ይሆናል ግን አወጣቸዋለሁ ሌላኛው ተስፋ ደግሞ በአንተ የምድርን ህዝብ ሁሉ እባርካለሁ የሚል መሲሁን የሚያመጣበት መንገድ ነበረና ነው::
እግዚአብሔርም እንደተናገረው ሲያደርግ ህዝቡ ግን አመጹበት በእርሱ ላይ መደገፍና መታመን አልቻሉም:: አንዴ ወደ ግብጽ እንመለስ ብለው አለቃ ሲሾሙ አንዴ መቀበርያ ስለሌለ በእዚህ እንድንሞት ነው ያመጣኸን ሲሉ ሌላ ጊዜ መና ሰለቸኝ እያሉ ቅዱሱን መንፈስ አስመረሩት:: በዚህም የተነሳ የተስፋይቱን ምድር አያዮም ብሎ አለ:: በዘኍልቍ 14:22፤ በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ 23፤ ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤ እንዳለው እንዲሁ ዛሬ የምናምን እንሁን::
እነዚህ ሰዎች ወደ ተስፋይቱ ምድር ያልገቡት በራሳቸው ችግር ነው እንጂ እግዚአብሔር ስላልፈለጋቸው ወይም አሳቡን ለውጦ አይደለም:: እዚህም ስፍራ ላይ ሀሰተኞች ሾልከው ገብተው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ እንዲሁም ብቻውን ጌታ የሆነውን እየሱስን ይክዳሉ:: እንግዲህ የተሰጠንን ይህንን መዳን ችላ ብንልና ባንጋደል እኛው ነን ከህይወት የምንጎድለው:: እግዚአብሔር እጁን ከፍቶ ከኃጥያታችን በልጁ ደም አንጽቶ አድኖን ልጆቹ አድርጎናልና የጊዜውን ነገር እየናቅን በጌታ ስር ሰደን ቃሉን በልባችን እየሸሸግንና እየታዘዝን እንመላለስ:: ሌሎችንም እናንቃ!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ይሁዳ 1: 6-7
6፤ መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል። 7፤ እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።
ይሁዳ የሚሰጠን ሌላኛው ምሳሌ ደግሞ መኖሪያቸውንም ስለተዉት መላእክት ነው:: እነዚህ መልአክት መሆን የሌለባቸውን ሆነዋል ወይም ማድረግ የሌለባቸውን አድርገዋል ስለዚህም ምክንያት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።
በዘፍጥረት 6:2፤ የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። ስለነዚህ ይሆን ክፍሉ የሚያወራው? ምክንያቱም የሚቀጥለው ቁጥር ከዝሙትጋር ግንኙነት እንዳለው ያስረዳ “እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና” ብሎ ስለሰዶምና ጎሞራ ያወራል:: በዚህ ምክንያት ይሆን የውሃ ጥፋት የመጣውና ኖህንና ቤተሰቡን ብቻ ያስቀረው፤ እግዚአብሔርም ሰውን በመፍጠሩ የተፀፀተው እዚህ ጋር ነው::
የሚቀጥለው ምሳሌ ወይም ሌላው በእግዚአብሔር የተቀጡት ይሁዳ እንደሚለን ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል ይላል:: ሰው በብዛት ስለተቀበለው ወይንም ደግሞ እየበዛ ስለመጣ ይህ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እንዳንለዝብና እንዳናመቻምቸው ሐጥያት ነው እግዚአብሔርም የፈረደው በእሳት በማጥፋት ነው ዛሬም ውሳኔው አይለወጥም::
ይህ የሚያሳየው እግዚአብሔር መለየታችንን መቀደሳችንን ቃሉን መጠበቃችንን ይፈልጋልና ጠላትና ዓለም በፊታችን የሚያመጡትን እየናቅን በጸጋው እንቁም መጋደላችንንም እናብዛ:: እርሱ ክርስቶስ ብቻውን ጌታ እንደሆነ ሁሉ ይወቅ እንጂ አሁን በዘመኑም እንደሚባለው እኛ አምላክ አይደለንም ፍጥረት ነን እርሱ ብቻውን ከፍ ያለ ሁሉን የፈጠረ የሁሉ መገኛ ጌታና ንጉስ ነው:: አሜን!
ይሁዳ 1: 8-10
8፤ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ። 9፤ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ “ጌታ ይገሥጽህ፥” አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም። 10፤ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ።
እነዚህ ሰዎች ህልም ውስጥ ናቸው የራሳቸውን የምናብ ዓለም ፈጥረው ከእውነታ ርቀዋል:: ስለዚህም ስጋቸውን እያረከሱ በቤተክርስቲያንም የተሾሙትን ይሳደባሉ:: ለእርምት እንኳን ስፍራ የላቸውም ሁሉን ይንቃሉ እነርሱ ብቻ ያሉት ነው ትክክል የሚመስላቸው:: አሁን ያለው የቤተክርስቲያን ችግር ይህ ነው ሀይ ባይ ማጣት እና ድፍረት የተሞላበት ሆንዋል:: ስልጣንንም አያከብሩም ብሎ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ጋር እያወዳደረ ይናገራል:: ሚካኤል ግን ሰይጣንን እንኳን አልተሳደበም:: የወደቀውን የተጣለውን ከስልጣኑ የተነሳውን እግዚአብሔርን የተቃወመውን:: ያለው አንድ ነገር ነው “ጌታ ይገሥጽህ፥” ::
ዛሬም እኛ ሰይጣንን በራሳችን አይደለም የምንዋጋው በእየሱስ ስም ነው:: ለእግዚአብሔር ተገዙ ሰይጣንን ተቃወሙት ከእናንተ ይሸሻል ነው የተባልነው:: ራሳችንን ማስገዛት እንለማመድ:: ስድብንም በስድብ አንመልስ እንመርቅ ፤ ባለስልጣንንም እናክብር::
ከባድ አባባል ነው አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች መባል:: እንሰሳ ነው አእምሮ የሌለው ሰው ግን በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሆኖ ሳለ እራሱን ያዋርዳል:: መንፈሳዊ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ ነገር ግን ፍጥረታዊ ናቸው:: ስለዚህም በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋ ይላል:: ማስተዋል ይሁንልን:: ዝቅ ብለን ሌላው ከእኔ ይሻላል እያልን በትህትናና በፍቅር እንመላለስ:: መታወቅም ያለብን በፍቅራችን ነው:: እግዚአብሔርን ስንፈራና ስንወድ ከዚህ እንጠበቃለን::
አባት ሆይ ሀይ ባይ ያጡትንና ማንንም አንሰማም ያሉትን ወገኖች ዛሬ ታስብ ዘንድ ከእንቅልፍ እንደሚነቁ ይነቁና ለአንተ ይገዙ ዘንድ እጸልያለሁኝ:: በእየሱስ ስም አሜን!
ጸጋው በእውነት ይብዛልን!
ይሁዳ 1: 11፤ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።
ይህንን ክፍል ይሁዳ ሲጀምረው ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ ነው የሚለው እንዴት እንጋደል ስንል እነዚህን የሚጠቅሳቸውን ሰዎች ባለመምሰል ነው:: እነዚህም ሶስት ሰዎች:- ቃየል፤ በለዓምና ቆሬ ናቸው::
- ከቃየል ብንጀምር መስዋትን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቦ ተቀባይነትን አላገኘም ምክንያቱ ግን እንደወንድሙ እንደ አቤል የደም መስዋአት ስላልሆነ ብቻ አይደለም በዕብራውያን 11:4፤ አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። በእምነት ስላቀረበ ነው:: እንዲሁም በ1 ዮሐንስ 3:12፤ ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው። ስለዚህ ወዮላቸው እግዚአብሔር አልተቀበላቸውምና በቁጣና በቅምያ ተሞልተዋል በእጃቸው ማንንም ባይገድሉም እንኳን ቃሉ እንደሚል ወንድሙን የማይወድ ነፍሰ ገዳይ ነው:: በቃየል መንገድ እራሳችንን እንዳናገኘው እኛ የክርስቶስ እንጂ የራሳችን አይደለንም:: በፍቅርና በእምነት እህቶችንና ወንድሞችንም በማክበርና እርስ በእርስም በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛን ሆነን እንመላለስ። ከንቱ ከሆነው ነገር ፈቀቅ እንበልና የራሳችንን መንገድ እንጠብጥብ:: የኃይማኖት መልክ ያለን ኃይሉን ግን የካድን እንዳንሆን ዕለት ዕለት በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን እንፈልግ እርሱ ይመራናል ይረዳንማል::
- ሁለተኛው እንዳንከተለው የተተወልን ምሳሌ በለዓም ነው:: በለዓም ማነው? ነብይ ነው:: ነገር ግን ገንዘብ አጏጉቶት እስራኤልን ሊረግም ወጣ:: ሶስት ጊዜ ሞከረ ከአፉ የሚወጣውና የሚያየው ራዕይ እስራኤልን መባረክ ብቻ ሆነ:: እግዚአብሔር ያልረገመውን መርገም አይቻልም:: ከውጪ ለሚሆነው ጌታ እንደዚህ ይጠብቃል:: እስራኤን ተዘልሎ ተቀምጧል በለዓም እንደዚህ ሊረግማቸው መከራውን እየበላ እንዳለ የሚያውቁት ነገር የለም:: ጠባቂያችን አይተኛም አያንቀላፋም! በዘኍልቍ 22:18፤ በለዓምም መልሶ የባላቅን ባሪያዎች፦ ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እንደሚል ቃሉን አልተላለፍም እያለ ግን ለመርገም ይነሳል:: ይህ ሁሉ ለገንዘብ:: በአህያ እንኳን ተናግሮት እያለ ይህ ሰው ብዙ ጥረት ከማድረግ ወደ ኃላ አላለም:: በመጨረሻም ክፉ ምክርን መከረ ይህንን ህዝብ መርገም አልቻልኩም ግን በዝሙት ቢወድቅ እግዚአብሔር እራሱ ይዋጋዋል የሚል:: ደግሞም በለዓም እንደመከረው እግዚአብሔርን አስቆጡት በዚህ ሐጥያት ምክንያት ሃያ አራት ሺ ሰው አለቀ::በዘኍልቍ 25:2፤ ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ወደ አምላኮቻቸውም ሰገዱ። 3፤ እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ።በዘኍልቍ 31:16፤ እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ። አለ ሙሴ::
- ሶስተኛው ምሳሌ እንዳትመስሉት የተባልነው ቆሬ ነው:: ቆሬ በሙሴ ላይ ተነሳና ጉባኤን ሰበሰበ ሙሴ የሚሉትን በሰማ ጊዜ በግንባሩ ወደቀ ምክንያቱም የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ቁጣ አውቆ ነበረና:: በዘኍልቍ 16:3፤ በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው፦ ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ። 4፤ ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወደቀ፤ ሙሴ የፈራው አልቀረም መሬት ተከፍታ ዋጠቻቸው:: የመቃወም ህይወት በእግዚአብሔር ቤት መኖር የለበትም:: ሁሉም እያገለገለ ያለው አንድን ጌታ ነውና መፎካከር የለብንም:: በቤተክርስቲያንም የተሾሙትን እንፀልይላቸው:: ባልተሰጠንም ጸጋ ገብተን የሌሎችን ስራ ለመስራት አንሞክር የስራው ባለቤት ጌታ ነውና እርሱን ደስ ለማሰኘት እንድንችል እርሱን እንስማው እርሱ እራሱ ያሰማራል:: የእግዚአብሔር መንግስት ስራ ባለቤት አለው::
ከምን እንሽሽ ታድያ?
1. ገንዘብን ከመውደድ:- ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ስር ነው:: ጌታም ያለን ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም ነው:: ጌታን በሙሉ ኃይላችን እንውደድ::
2. ከዝሙት መሸሽ – ቆማችሁ ተቃወሙት አይደለም የተባልነው ሽሹት ነው:: እግዚአብሔር ዝሙትን ይጠላል ምክንያቱም በስጋችን ላይ የምንፈፅመውና ከውስጥ የሚወጣ ደግሞም ሁለንተናን የሚበክል ነው:: ይህ ስጋችን የጌታ መቅደስ ነው:: እርሱ ራሱ ይቀድሰን!
3. የመቃወም ህይወት በእግዚአብሔር ቤት መኖር የለበትም
በቃሉና በጸሎት እንትጋ እራሳችንንም እንመርምር ሌሎችንም እያነቃን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠን መዳን እንጋደል:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን በማስተዋል እንድንመላለስ::
ይሁዳ 1: 12 – 13
12፤ እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥ 13፤ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው።
አሁንም ማሰብ ያለብን ይሁዳ የተነሳበትን አሳብ ነው:: እርሱም ስለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ ያለውን:: ስንጋደል ይህንን ለመጠበቅ በመካከላችን እነዚህን ሰዎች የሚመስሉ ካሉ እንድንጠበቅ ነው::
እነዚህ ሰዎች እራሳቸውን የሚወዱ ናቸውና በድሮ የቅዱሳን ልምድ ውስጥ የሆነውን በህብረት እንጀራን የመቁረስ ጊዜ ላይ ሲገኙ የራሳቸውን ምግብ ይዘው የማያካፍሉ እራሳቸውን የሚወዱ ሌላው ምግብ ቢኖረው ባይኖረው ግድ የማይላቸው እኔ ብቻ የሚሉ በሁሉ መታየትን የሚሹ ለታይታ የሚመላለሱ ውሃ የሌለው ደመና ናቸው:: ደመና ከመጣ ዝናብ መዝነብና ምድርን ማጠጣት ነበረበት እነርሱ ግን ምንም አይነት ፍሬ የሌላቸው ናቸው:: ጳውሎስም በ1 ቆሮንቶስ 11:21፤ በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና፥ አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል። 22፤ የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን አንዳችም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? አላመሰግናችሁም። ይላቸዋል ተመሳሳይ ችግር ነው የምናየው::
እነዚህ ሰዎች ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥ ፍሬ በሚፈራበት ወቅት እንኳን ፍሬ የሌላቸው ለማንም ምንም የማይሰጡና የደረቁ ናቸው:: እግዚአብሔር ከዚህስ ይጠብቅ! ውሃ ዳር እንደሚታይ አረፋ ደርሶ ስራ የሰራ ይመስላል ግን ምንም ያላደረገ በማእበል ብቻ ተገፍቶ የተፈጠረ አረፋ ማለት ናቸው:: እነዚህም ሰዎች ዝም ብለው ግርግር ይፈጥራሉ እንጂ ፍሬ ያለው ነገር የሌላቸው ናቸው:: መጨረሻቸውም ንስሃ ካልገቡ ጥፋት ነው:: የሚጠብቃቸውም ጨለማ ነው::
ስለዚህ እራሳችንን እየመረመርን ለራሳችን እንደምናስበውና እንደምንወደው ሌሎችንም እንድንወድና ስለሌሎችም እንድናስብ ግድ ይለናል:: ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ! ጌታ ፍሬ ልናፈራ ሾሞናል!
ይሁዳ 1:16-18
16፤ እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል። 17፤ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤ 18፤ እነርሱ፦ “በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ፥” ብለዋችኋልና።
እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ነገር የጣሉ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው የሚሄዱ ዘባቾች ናቸው:: እግዚአብሔር ማጉረምረምን ይጠላል ይህ የሚመጣው ደግሞ ከእርሱ ጋር ህብረት ማድረግ ሲቀርና መንፈስ ቅዱስን መተው ሲመጣ ነው:: እርሱ አእምሮን በሚያልፍ ሰላም ይጠብቀናል ተላልፈንም አንሰጥም አለበለዚያ የራሳችን መሪ እንሆንና በእርሱ ላይ መደገፉን እንተዋለን:: ቃሉ እንደሚል እነዚህ ሰዎች ማታለልና ሰውን መደለል እንዲሁም ሰውን አይተው አድልዎ ያደርጋሉ እንደነዚህ ያሉ እንደሚመጡ ቀድሞ ተነግሮናል:: ዛሬ ብዙ ዘባቾችን እያየን ነው:: ጌታ ይጠብቅ ለወጥመዳቸው እንዳንወድቅ::
የእግዚአብሔር ቃል ችግርን ብቻ ነግሮን አይተወንም መፍትሄም ይሰጠናል:: እናንተ ግን ይለናል ይሁዳ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ሊነግረን:- ቃሉ አስቀድሞ ነግሮናልና እንደቃሉ እንኑር:: ከእርሱ ጋር ህብረትን እናድርግ በጌታ ላይ እንደገፍ! እንደምኞታችን ሳይሆን እንደእርሱ ፈቃድ እንመላለስ:: እኛ የራሳችን አይደለንምና::
ይሁዳ 1:19-23
19፤ እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው። 20፤ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ 21፤ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።
አንድ ጊዜ ስለተሰጠን መዳን እንድንጋደል እየመከረን ነው ቃሉ:: እነዚህ ለማሳሳት ወደ እግዚአብሔር ቤት ሾልከው የሚገቡትን ጥሉ አዋርዱ አይደለም እያለን ያለው:: ነገር ግን የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ስጋውያን ናቸው::
እናንተ ግን
– በመንፈስ ተመላለሱ፥ ስጋውያን አንሁን
– ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፥ በቃልም በፀሎትም ከቅዱሳን ጋር ፀጋን በመከፋፈል
– በመንፈስ ቅዱስም ጸልዮ፥ እራስን ማነፅ ነውና
– ምሕረት እየተጠባበቃችሁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።
– ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥
– አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥
– በኃጥያት የወደቁትን በፍርሃት ማሩ
ነው የተባልነው::
በራሳችን ፍቅር ሌላውን ብንወድ ያልቅብንና እንሰለቻለን የተባልነው ግን በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ ወይም በፍቅሩ ውስጥ ሁኑ ሌላውን ጌታ እንደሚወድ ውደዱ ነው የተባልነው:: ይህ ፍቅር ለማንም አያዳላም ሁሉን ይወዳልና አብረን እንፍሰስ ጌታ በእኛ ውስጥ ሌላውን ወዶ መንገዳቸውን ያቅና!
በመንፈስ ቅዱስም መፀለይን ችላ እንዳንለው:: አብዝተን በመንፈስ እንፀልይ!
የእግዚአብሔር ጸጋ ይብዛልን!
ይሁዳ 1: 24-25
24፤ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው፥ 25፤ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።
የእግዚአብሔር ቸርነቱ እንዴት ይደንቃል? እንዳንሰናከል ይጠብቀናልና በሌላ ስፍራ በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ እንደሚለው እንጠበቃለን ስሙ ይባረክ:: እግዚአብሔር ማንንም በክፉ አይፈትንም ሲጀምርም ተወዳድረን አሪፍ ስለሆንን አይደለም ወደ ጉያው የመጣነው ነገር ግን እርሱ የዓለምን ምናምንቴ መረጦ ታድያ ምናችን ይፈተናል ይጠብቀን እንጂ በራሳችንም አልዳንን በጸጋው ነው እውቀታችን እንዳንል ደህንነት መገለጥ ነው ጴጥሮስን እንዳለው አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ሲለው ስጋና ደም ሳይሆን የአባቴ መንፈስ ነው የገለጠልህ እንዳለው ነው:: ምንም የምንመካበት የሌለን ነን:: እንጠበቅ እንጂ በእርሱ!
በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው፥
እናስተውል በክብሩ ፊት!!!! ሃ ሌ ሉ ያ! በክብሩ ፊት ሳንሸማቀቅ እየሱስን ጽድቃችን ለብሰን በደስታ ነውር የሌለን አድርጎ ሊያቆመን ለሚችለው ክብር ይሁን!! ምን አይነት መታደል ነው?! ሰው በራሱ አይበረታም የሚያበረታና የሚረዳ እራሱ ጌታ ነውና ክብር ይሁንለት:: ምን እንላለን ምን አይነት ፍቅር ነው ለእኛ ያለው ከማለት በቀር!! የጌታ ስም ይባረክ!!
በዚህ የይሁዳ መጽሐፍ ጥናት በዚህ ተጠናቀቀ የሚገርመው አንድ ምዕራፍ ቢሆንም ግን ብዙ አሳብ የታጨቀበት ነው መዳናችንን በጌታ ላይ በመታመን እንፈጽም ፤ ፍሬንም እናፍራ፤ ወደ ጥፋት የሚሮጡትንም ቅዱሳን እንታደግ፤ በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ እንኑር::
ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።
አሜን!!!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
