መግቢያ
ይህ ወንጌል የተፃፈው ለአህዛብ ሲሆን በተለይም ለቴዎፍሎስ ነበረ:: ፀሃፊውም እራሱ እስራኤላዊ አይደለም:: በዚህ ወንጌል ውስጥ ብቻ የሚገኙ ታሪኮች አሉ:: ለምሳሌ የመልአክት ዝማሬ እረኞች ባሉበት ስፍራ መገለጡ ጌታ እየሱስ ሲወለድ: ርኅሩኁ ሳምራዊ ምሳሌ: የጠፋው ልጅ ታሪክ እናም የእየሱስ በልጅነቱ ወደ ቤተመቅደስ መሄዱ::
ይህ ወንጌል የተፃፈው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን ነው:: በማለት እርሱ የዓይን እማኝ እንዳልሆነ ይገልጣል:: የተፃፈውም በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ነው የፃፍኩት ብሎ ይላል::
ሉቃስ 1:1-4፤ የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ።
ጌታ ሆይ ተመስገን ይህንን ቃልህን እንደዚህ በጥንቃቄ የተፃፈውን እንድንማረውና ገንዘባችን እንድናደርገው እርዳን::
ሉቃስ 1:5፤ በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። 6፤ ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።7፤ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር።
እንግዲህ ሉቃስ ቃል እንደገባው ከመጀመርያ ጀምሮ ነው ስለተማረው ቃል እርግጡን እንዲያውቅ ለቴዎፍሎስ እየፃፈ ያለው እግዚአብሔር እኛን እያየ ነበረና ይኸው ዛሬ እኛጋር ደርሷል::
የጀመረውም ከዘካርያስና ከኤልሳቤጥ ነበረ በዚህ ውስጥም ስለ ሄሮድስም አንስቷል ይህ ገዢ ነው ህፃናትን የጨፈጨፈው እየሱስን ለመግደል አስቦ:: እርሱ የመሰለው ስልጣኑን የሚቀማው እየሱስ ግን በዚህኛው ዓለም ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዓለም ገዢ ነው:: እርሱ የነገስታት ንጉስና የጌቶችም ጌታ ነው::
እነዚህ ባልና ሚስት ሁለቱም ከካህናት ዘር እንደሆኑ ይገልፃል ደግሞም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ ይላል:: ልጅ የሌላቸውና እድሜያቸውም መግፋቱን ልጅ ማግኛው ዘመን ማለፉን ያመላክታል:: ፃድቅ ነበሩ የሚለው አሳብ እንዴት ይገርማል :: ነገር ግን እንደነ አብረሃም በእምነት እንጂ በአዲስ ኪዳን እንዳለው ፃድቅነት አይደለም ምክንያቱም ሁሉም ኃጥያትን አድርገዋል የእግዚአብሔር ክብር ጎሏቸዋል ይላልና ቃሉ:: በብሉይ ኪዳን የኃጥያት ስርየት በእንስሳት ደም ማግኘት ይቻል ነበር ነገር ግን ዘላቂ አልነበረምና የእግዚአብሔር በግ እየሱስ መጣልንና አፀደቀን ልጅም አደረገን:: አሜን!
አባት ሆይ ተመስገን በደምህ ዋጅተህ ልጅ ስላደረከን:: ጌታ ሆይ አንተን የሚይዝህ ነገር የለም ከዚህ አለመቻል ውስጥ ዮሃንስ ተወልዷልና ዛሬም በህይወታችን ትሰራለህ የሚያቆምህ ምንም ነገር የለም ተመስገን! እታመንሃለሁ ጌታዬ!
ሉቃስ 1:8፤ እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል፥ . . . ሉቃስ 1:11፤ የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። . . . ሉቃስ 1:13፤ መልአኩም እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፡ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።
በብሉይ ኪዳን ጥቂት ሰዎች ናቸው ጻድቅ ተብለው የተጠሩ ከነዛ መካከል ዘካርያስ አንዱ ሆነ:: ይህ ሰው ካህን ነውና በተራው ገብቶ እግዚአብሔርን ያገለግላል ምንም እንኳን መሃንነት በህብረተሰቡ ዘንድ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ቢሆንም::
የእግዚአብሔር የጉብኝት ሰዕት ሲደርስ ግን መልአኩን ልኮ የምስራች ነገረው:: ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ! በዚች አንድ ቀን ጉብኝት ወደ ዘካርያስ ቤት እየመጣ ያለውን ብናይ:-
– ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥
– በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል
– በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የሚለው አሳብ ይገርማል ጌታ እየሱስ ስለእርሱ ሲመሰክር “እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ ብሎ ነበረ::
– ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል የሚለው ይገርማል:: ህፃን ነው ገና በሆድ ግን መንፈሱ አገኘውና አላማውን እንዲተገብር ረዳው:: የጌታ አሰራር!
ዘካርያስ ግን እስከአሁን ልጅ ስጠኝ ብሎ እየለመነ አይመስልም ጸሎቱን ከሁኔታዎች የተነሳ የተወው ይመስላል:: ጌታ ግን ለመመለስ መጣ ምንም እንኳን ዘካርያስ ዝግጁ ባይሆንምና ይህን በምን አውቃለሁ ብሎ ምልክትን ቢጠይቅም:: ምልክት ትፈልጋለህ እንግዲያውስ ዲዳ ሆነህ ቆይ እስኪፈፀም:: ለካስ እራሱ ነው ምልክት የጠየቀው?!
አባት ሆይ በፀሎት በፊትህ የቀረብኩትን ሁሉ ሰምተኸኛል ዛሬ ያልተመለሱ ቢኖሩም ይመለሳሉ አንተ ታላቅ ነህና ተመስገን! ተስፋ ባለመቁረጥ በቤትህ እንዳገለግልህ ጸጋህን ለእኔና ለወገኖቼም አብዛልን:: ዛሬ የቆየ ጥያቄ የሚመለስበት ቀን ይሁን:: አሜን!
ሉቃስ 1:14፤ ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።
በመልአኩ ለዮሃንስ የተሰጠው ተስፋና የሚመጣበት ዓላማ ወይም አገልግሎቱ በደንብ ለዘካርያስ ተነግሮታል::
ለቤተሰቡ:- ደስታና ተድላም ይሆንልሃል እንዲሁም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል::
የእስራኤል ህዝብ ለመሲሁ መምጣት የተዘጋጀ አይደለምና ለማዘጋጀት የተላከ ከአወላለዱ ጀምሮ ማን ይሆን በሚያስብል ተአምራት የመጣ ልጅ ነው::
በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ – ተስፋ ነው:: ጌታ እየሱስም መስክሮለታል::
የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ – ትእዛዝ
ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ – የሚፈጸም ተስፋ ነው
ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል – አገልግሎቱ
እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ – መንገድን የመጥረግ አገልግሎት:: ህዝቡን እያጠመቀ እኔ እርሱ አይደለሁም እያለ እየመሰከረ ለሚመጣው ጌታ አዘጋጀ:: ደቀ መዛሙርቱንም የጌታ ሆኑ በስተመጨረሻ::
የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች – አገልግሎት ሲሆን ከአሮጌው ኪዳን ወደ አዲስ እንዲመጡና እንደልጅ ሆነው እንዲቀርቡ እንዲያደርግ:: ባጭሩ ለውጥን እንዲቀበሉ
የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ – የማንቃት አገልግሎቱ
በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል – ይህ አገልግሎት መንገድን ለእየሱስ ለሚጠርገው የተሰጠ ነው:: በትንቢትም ኤልያስ ከመሲሁ ፊት ይመጣል ብለው ይጠብቁ ነበር ግን ሲስቱ እናያለን:: ይህ ህፃን ገና በእናቱ ሆድ እያለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል በኤልያስም መንፈስና ኃይል ያገለግላል:: ታላላቆች ግን አላወቁም::
የእኔ አገልግሎት ምንድነው? ብለን ቆም ብልእን ልንጠይቅና ለተጠራንለት ዓላማ ልንቆም ያስፈልጋል:: በክርስቶስ አስቦ ወለደን እንደሚል ምን ይሆን ለእያንዳንዳችን ያሰበው?
አባት ሆይ ለእኔም እንዲሁ የሰጠኸኝ አገልግሎት አለና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተስማምቼ እንዳገለግልህና መክሊቴንም እንዳተርፍበት እርዳኝ:: አሜን!
ሉቃስ 1:18 25
ዘካርያስም መልአኩን፦ “እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” አለው።
በእጣ ክፍሉ በታማኝነት በሚያገለግልበት ቦታና ሰዓት የምስራች ለዘካርያስ መጣለት:: ምንም እንኳን በእድሜው ያረጀ ቢሆንም እግዚአብሔር ሲናገር ማመን አልቻለምና ምልክትን ጠየቀ:: መልአኩም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም፡” አለው። አገልግሎም ሲወጣ ህዝቡ ራዕይ እንዳየ አስተዋሉ::
የእግዚአብሔር ቃል የሚፈፀም ነውና የተናገረንን አምነን እንጠባበቅ:: ለእርሱ የሚሳነው የለምና በሙሉ ልባችን እንመነው::
ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና፦ “ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል፡” ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች። እርጉዝ ነኝ ብላ ማውራት አላስፈለጋትም ጊዜው ሲደርስ ሆድዋ እራሱ ይናገር ነበረና እራስዋን ሸሸገች!
አባት ሆይ ተመስገን የሰጠኸንን ቃል የምትፈጽም ጌታ ነህና የተናገርከንንም ሁሉ እንወርሳለን:: አሜን!
እንደተናገረው ለሚያደርግ አምላክ ክብር ይሁን! አሜን!
ሉቃስ 1: 26-33
27፤ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።
መልአኩ ገብርኤል ያመጣላት መልእክት
እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥
ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ – ይህ ስም የተቀባ ስም ዛሬም እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ስም:: በላይ በሰማይ በምድር ከምድርም በታች ሁሉ ይንበረከክለታል::
እርሱ ታላቅ ይሆናል – አሜን ታላቅ ነው
የልዑል ልጅም ይባላል – የምወደው ልጄ ይህ እርሱን ስሙት ብሎ አብ መስክሮለታል::
ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል – ቃል እንደገባው 2 ሳሙኤል 7:16፤ ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፥ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል።
በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፥
ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።
አሜን የጌታ መንግስት ለዘላለም የጸና ነው:: ለዚህ ቃሉን ተናግሮ ለሚፈጽም ጌታ ክብር ይሁን:: ዛሬም በስራ ላይ ነው:: ሁሉም ነገር እንዳለው ይሆናልና በዙሪያችን ባለውነገር አንሸበር የመጨረሻው ውሳኔ የጌታ ነው:: ሃሌሉያ!
ሉቃስ 1: 34-38
34፤ ማርያምም መልአኩን፦ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለችው።
የተፈጥሮን ነገር ሁሉ ያላሟላ ስለሆነ መልእክቱ ግራ ገብቷት መጠየቅዋ ትክክል ነበረ:: ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ የተባለች ብትሆንም እርስዋም አዳኝ ያስፈልጋታልና እንዴት ከስዋ የመጣ ያድናል የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል:: መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። አሜን! እርሱ በድንግልና የተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ ነው:: ቃል ስጋ ሆነ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ!
በዚሁ ሌላ መልካም ዜና ነገራት:- ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው አላት የሁለቱ ልጆች ግንኙነትና ተልእኮ ባይገባትም እንኳን በጉብኝቱ ደስ ብሏታል::
ወንድ የማታውቀው አርግዛ እንድትወልድ እንዲሁም ያረጀችው ልጅ እንድታቅፍ የሚያደርግ ጌታ ስሙ ይባረክ:: ሳይንሱን ሁሉ የገለባበጠው ጌታ ይባረክ:: ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። አሜን!
በዚህ ውስጥ ማርያምም፦ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፡” አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ። ከጌታ ጋር ተስማማች ምንም እንኳን በባህሉ ከትዳር ውጪ አርግዞ መገኘት ዋጋ ቢያስከፍልም እርሱ ብሏል ብላ ቆመች:: እርሱም የሚሳነው የለምና ቃሉን ይፈጽማል::
ለተናገረን ነገር እኛ በእምነት እንቁም ሌላውን ሁሉ ኤልሻዳዮ ጌታ ይወጣዋል::
አባት ሆይ ተመስገን ቃልህ ከእኛ ጋር ይዋሃድና ይጥቀመን:: እንደተናገርከንም መታዘዝ ይሁንልን ምሕረትህ ዛሬ በእኛ ላይ ትገለጥ:: አሜን!
ሉቃስ 1: 39-45
41፤ ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥
ማርያም ኤልሳቤጥን ልትጠይቅ መጣች:: እግዚአብሔር ለዘካርያስ በነገረው መሰረት ይኸው ህፃኑ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ:: ቃል ስጋ ሆንዋል በማህፀንም እያለ ይሰራል::
እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።
ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት። እግዚአብሔር እንደተናገረው እንደቃሉ ነውና የተስፋ ቃላችንን ሁሉ እንወርሳለን ምክንያቱም የተናገረው የታመነ ነው:: አሜን!
ሉቃስ 1: 46-56
46፤ ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ 47፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤
ማርያም እንደቃልህ ይሁንልኝ ብላ ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዘችና ቃል የሆነው እየሱስ በእርስዋ ውስጥ ተፀነሰ:: ኤልሳቤጥም በመንፈስ ተሞልታ ትንቢትን እንደተናገረች ሁሉ ማርያምም ቃል እየጠቀሰች በመንፈስዋ ሃሴት እያደረገች ጌታን ማክበርና መባረክ ይዛለች:: የእየሱስ እናት መሆን እንዴት የሚገርም መመረጥ ነው? ነገር ግን እርስዋም የእግዚአብሔር ክብር ይጎድላታልና አዳኝ አስፈልጏታል::
እርስዋም:- ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ብላለች አሜን እርሱ ቅዱስነው:: እናውቃለን ብለው የታበዮትን አዋረዳቸው ለትሁታን ግን ፀጋን ሰጠ!
አምላካችንን እናመስግን እናድንቅ እናወዳድሰው ስለሚገባው ይህ ንጉስ እኛን ፍለጋ ሲመጣ ይህንን ሁሉ ነገር ሰርቶ ነውና ይክበርልን:: አሜን! እኛም እንደማርያም ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች እንበል::
ሉቃስ 1: 57-66
57፤ የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች። 58፤ ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው።
የጌታን መልእክት እንዴት ይሆናል ብሎ እንዳላለ ዘካርያስ እንደተባለው አባት ሆነ:: ይህንንም በዓይኑ አይቶ ሙሉ ለሙሉ እስኪታዘዝ ድረስ ዲዳ ነበረ:: እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም፡” አለው። የእግዚአብሔር ቃል የሚፈጸም ነው:: አሜን!
ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ጎረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ደስ አላቸው። ምሕረቱን በእያንዳንዳችን ቤት ላይ ያግንነው::
ስም ሊያወጡለት የፈለጉት የአባቱን ስም ነበረ ነገር ግን እናትምአባትም ተቃወሙና ስሙ ዮሐንስ ነው ሲሉ እነርሱም፦ “ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም፡” አሉአት። የእግዚአብሔር ነገር ሰው ባሰመረለትና በተለመደው መንገድ አይሰራምና መቀበል ግድ ነበረ:: አይሆንም ባይሉ ግን ስሙን ይቀይሩት ነበረ ማለት ነው::
አባት ሆይ ያልከው እንደሚፈፀም አውቀን በሰጠን የተስፋ ቃል እንድንታመንና እንድንጠብቅ እርዳን:: አሜን!
ሉቃስ 1: 65-71
67፤ አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ፦
68፤ “የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤
እዚህ ምዕራፍ ላይ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ትንቢትን ስትናገር አይተናል እንዲሁም ማርያም አሁን ደግሞ ዘካርያስ:: እርሱም የጀመረው እግዚአብሔርን በመባረክ ነው:: አሁን ያሉት ዮሃንስ ሊገረዝ ባለበት ስርዓት ላይ ቢሆንም እንኳን አባትየው በመንፈስ ተነድቶ ስለመሲሁ እየተናገረ ነው:: ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና እያለ:: አሜን የሰውን ልጅ ያሰበው ጌታ ይባረክ::
ሲቀጥልም ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥
በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል:: ይህ የመዳን ቀንድ የሆነው መሲሁ እየሱስ ‘ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው ብሎ መንፈስ ቅዱስ መሰከረለት:: አሜን ከሚጠሉን ከሰይጣንና ከአጋንንቶች እጅና መንጋጋ ነው:: ጨለማችንን አብርቶ ፤ በደላችንንም ይቅር ብሎ ፤ በጽድቁ አጽድቆ ፤ በቤቱ ተክሎን ፤ ከዓለም ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ብሎ አባት ሆኖን፤ በእጁም መዳፍ ቀርጾ ማንም ከእጄ አያወጣችሁም ብሎን ፤ አይዞአችሁ ዓለምን አሸንፌአለሁ ብሎን ፤ በእኛ ውስጥ ለመኖር መጣ:: ምን አይነት ህይወት ነው?!
አባት ሆይ ተመስገን ክብርህን ጥለህ የባርያን መልክ ይዘህ ተዋርደህ ለእኛ የመጣህ ጌታ እናመሰግንሃለን:: እኛነታችን ሁሉ የአንተ ነውና ክበርበት! አሜን
ሉቃስ 1: 72-75
72-73፤ እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤ 74-75፤ “በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን።
ዘካርያስ ትንቢቱን ሲቀጥል ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ አለ እንዲህ ያለውን:-
ዘፍጥረት 22:16 – 18፤ እንዲህም አለው፦ “እግዚአብሔር፦ ‘በራሴ ማልሁ፡’ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና፣ በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና።”
አብርሃም ቃሉን ሰምቶ አንድ ልጁን መስዋእት ለማድረግ ስላልሳሳ በራሱ ምሎ እራሱ መጣና ተቤዥን:: በአብርሃም የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ እንደሚል ይኸው እኛ ከአህዛብ ወገን የሆንን ለዚህ ቃል መፈጸም የቆምን ምልክቶች ነን:: አሜን!
በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ሃሌሉያ! ! ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን:: አሜን!
ሉቃስ 1: 76-80
78፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ 79፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል።”
ስለዮሃንስ ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ “እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ ነው የመጣበት አገልግሎት:: እራሱም መስክሯል እኔ እርሱአይደለሁም በማለት:: መንገድን መጥረግና የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ መግለጥ ነበረ :: ጌታ የሰጠን ስራ ምን ይሆን? የተሰጠንማ ስራ አለን:: ይህንኑ ጌታ ይግለጥልን::
ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው:: አሜን! የአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ጉብኝት አገኘን:: ይህ ብርሃን በራልን ጨለማችንም በራ!
ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። አሜን! በሞት ጥላ ተቀምጠን ነበረ ያለ መፍትሄ ምንም መውጫ የሌለበት:: በኢየሱስ ግን አመለጥን ውደ ህይወት ተሻገርን! ጨለማችንንም አበራው! እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናው ምሕረቱንና ርህራሄውን ያበዛልን ጌታ ይባረክ!
አባት ሆይ ተመስገን መፍትሄ የሌለውን ፍፃሜያችንን ለውጠህ አባ አባት የምንልበትን መንፈስ ሰጥተህ በቤትህ አለመለምከን:: በአብ ቀኝ ተቀመጥን!
ሉቃስ 2: 1-7
7፤ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።
በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ትእዛዝ ወጣ ይህ ትእዛዝ ከነገስታት የወጣ ይምሰል እንጂ ወራቱን ጠብቆ ትእዛዝ ያወጣው አምላካችን ነው:: ትእዛዙም የወጣው ትንቢቱ እንዲፈፀም እየሱስ በቤተልሔም ይወለድ ዘንድ ነውና ዮሴፍም ለመቆጠር እጮኛውን ይዞ ወደ ቤተልሐም መጣ:: ትንቢቱም በሚክያስ 5:2፤ አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። የሚለው ነው:: በዝችው ከተማ ነበረ ዳዊትም የተቀባው::
የትንቢቱ ትእዛዝ ሲፈፀም እንደመቃብሩ ሁሉ የከበሬታን ቦታ ማዘጋጀት ይችል ነበረ ነገር ግን የነገስታት ንጉስና የጌቶቹ ጌታ ስፍራ ጠፍቶ በከብቶች በረት በግርግም ተወለደ:: እውነትም እንዴት ነው እራሱን አዋርዶ የመጣልን?! እየሱስ ተወለደ ዓለም ሁሉ አላወቀም:: ዓለሙን ሁሉ በቃል የፈጠረው ጌታ መወለዱን ከጥቂቶች በቀር አብዛኛው አላወቀም:: እርሱም እውቅና ስጡኝ አላለም:: ትሁት ጌታ! ተመስገን! የእኛም ህይወት ከዚህ ግርግም የማይለይ ቁሻሻ ነበረ እርሱ ሲገባ ግን በደሙ አነፃንና ፃድቅ ቅዱሳን ተባል! ሃሌሉያ!
አባት ሆይ የዝቅታን ዝቅታ ስለእኛ አየህ:: ተመስገን ስለተወለድክና ስለመጣህልን እናመሰግንሃለን! ልጆችህ ስላደረከን ከፍ በል! ይህንን የመጣህበትን የማዳን ወንጌል ይዘን እንድንወጣና እንድንመሰክር እርዳን በጸጋህንም ሙላን:: አሜን
ሉቃስ 2: 8-20
10፤ መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤
11፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።
12፤ ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።”
እየሱስ ለህዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እረኞች ተነገራቸው:: ይህም የምስራች መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል የሚል ነበረ:: ይህ ለሊት ምን አይነት የተለየ ለሊት ነው? አምላክ ሰው ሆኖ የተወለደበት ለሊት:: ዓለሙ ሁሉ በእንቅልፍ ላይ ነው እነዚህ እረኞች በማንም አጀንዳ ላይ የማያሰፍራቸው ይህንን ክብር ያዮ ዘንድ ተመረጡ:: የመልአኩን መልአክት ሰሙ አብረውም ያሉትን መልአክትን ዝማሬ አደመጡ:-
“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ።”
እነዚህ እረኞች ሰምተው ብቻ ዝም አላሉም መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ፡” ተባባሉና ታዘዙ:: ዛሬም ወድያው መታዘዝ ይሁንልን ጌታ በሚያሳየንና በሚያዘን ነገር ላይ:: ጸጋህን ስጠን!
በፍጥነትም መጡ ህፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙት:: ከቤተሰቡ በተጨማሪ እነዚህ እረኞች ናቸው ያወቁት ስለመሲሁ:: ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። የተቀበልነውን ነገር እምነታችንን እንዳይጎዳ በልባችን እንጠብቅ::
እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ። እኛም ዛሬ ይህንን መሲህ እኛን ያሰበውን እናመስግን::
ሉቃስ 2: 21 – 28
21፤ ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ።
ገና ሳይፀነስ መልአኩ እንደተባለው ስሙን ኢየሱስ ብለው ጠሩት:: ማርያም እንደቃልህ ብላ ተስማምታ ነበረና የዘካርያስ እጣ አልደረሰባትም:: ታዘዘች ይኸው እግዚአብሔርም እንደተናገረ ወንድ ልጅን እርሱም የዓለምን መድኃኒት አቀፈች::
እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበርና ሲያመጡት ተቀብሎ አቀፈው:: ይህ ሰውን ከምድር አፈር ያበጀ ጌታ ሰውእጅ ገባ:: ምን አይነት ዝቅታ ነው በሰው እጅ መታቀፍ በሰው እጅ መብላት መጠጣት መታቀፍ እንደማንኛውም ልጅ ቋንቋ መማር መዳህ መውደቅ መነሳት ሁሉን አድርጏል:: ስናስበው ግን ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ውስጥ የሚኖር ጌታ: በሲና ተራራ ሲገለጥ የቀረበ ሰው ወይም እንሰሳ ሁሉ ይሞት ነበረ: ዮሃንስ እንኳን በደንብ የሚያውቀው መቆም አልቻለም በፊቱ:: እንግዲህ ይህንን ጌታ ነው ተቀብሎ ያቀፈው:: ክብሩን ሁሉ ጥሎ እራሱን አዋርዶ መጣ:: ኃጥያት ባይኖርበትም እንደህጉ ለእርሱም መስዋእት ቀረበ::
ስምኦን ጌታውን ጠበቀ በመንፈስ እንደተረዳውም ተቀብሎም አቀፈው:: የተሰጠን የተስፋ ቃል የሚወረስ ነው:: አምላካችን የተናገረውን የሚፈጽም ነው:: አሜን!
አባት ሆይ ክብርህን ትተህ እኔን ፍለጋ ተዋርደህ ስለመጣህልኝ አመሰግናለሁኝ:: እገዛልሃለሁኝ: አመልክሃለሁኝ! አሜን!
ሉቃስ 2:29-35
30-31፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ 32፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።”
ስምእኦን የምጠብቀውን አይቻለሁና አሰናብተኝ እያለ ነው:: የሚገርመው ይህ ሰው የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበርና ጌታን ባመጡትበት ቀን በመንፈስ ተመርቶ ወደ መቅደስ መጣ:: መጥቶም የሚጠባበቀውን ጌታ አቀፈ::ብዙዎች እናውቃለን ያሉ በመካከላቸው የተገኘውን ጌታ አላወቁትም::
እንደስምኦን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የበረታ ህብረት ሊኖረን ይገባል እርሱ መቼም አያደላ በፊቱ እንሁን እንጂ ይመራል ይናገራል:: ጌታ እየሱስ እንዳለን ከእኔ ወስዶ ለእናንተ ይነግራል ስለወደፊቱም ያሳውቃችኃል ብሏል:: እንጠማው መንፈስ ቅዱስን ያለ እርሱ አንዳች ማድረግ አይቻልም::
ስምኦን ስለጌታ ያለውን እናስተውል ያዘጋጀኸውን ማዳንህን እንዲሁም ለአሕዛብ ሁሉ የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። ይሄ ቃል ኪዳን የተገባው ለአብርሃም ነበረ በአንተ የምድር ነገዶች ሁሉ ይባረካሉ ተብሎ ነበረ:: ይህ የሚባርክ ጌታ ለአህዛብ ሁሉ መጣ ወይም ለሰው ልጆች! በደህንነት ስራው ውስጥ አህዛብን ሁሉ ያሰበ ጌታ ይባረክ! ዛሬ በፊቱ ይህ ብርሃን በርቶልን ቆመናልና ክብር ምስጋና ይብዛለት!
አባት ሆይ ከአንተ ጋር ህብረት ማድረግ በመንፈስ መመላለስ የጊዜውንና የውደፊቱን እቅድህን ከአንተ በመስማት የነቃን አድርገን በምትሰራበትም ጊዜ ገንዘቦችህ አድርገን:: አሜን!
ሉቃስ 2: 36-40
38፤ በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።
40፤ ሕፃኑም አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።
ነብይት ሃና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። አርጅታም እንኳን ከአገልግሎት አልታጣችም በዚህም ላይ ጨምራ በጾምና በጸሎት ሌሊትና ቀን ትተጋ ነበረ:: ይገርማል!! ጌታ ግን አይቷት ነበረና ወደ ቤተመቅደሱ ባመጡት በዚያው ሰዓት የምትጠባበቀውን ጌታ አገኘችው:: ይገርማል በዚያች ሰዓት ተገኘች! እርስዋም የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።
እኛም ዛሬ ጌታ ሊመጣ በደጅ ባለበት ሰዓት ላይ ነንና በትጋት እንጠባበቅ ስምኦንም ሃናም ያደረጉት ይህንኑ ነው ደግሞም አላፈሩም አገኙት:: ሌላው ስለእርሱ ትናገር ነበረ ይላል:: ወንጌልን ልንናገር የተጠራን ነንና ስለጌታችንና አምላካችን ማዳን በነፃ ስለሆነው ወንጌል እንናገር::
ሕፃኑም አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። አሜን! ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ በእኛም ላይ ይሁን ጥበብን ይሙላብን ያበርታን ያጠንክረንለተጠራንለትጥሪ ያስታጥቀን::
አባት ሆይ ልትመጣ በደጅ ነህና ተዘጋጅተን በመክሊታችንም አትርፈን ዘይታችንም ሞልቶ እንድንገኝ እርዳን:: አሜን!
ሉቃስ 2: 41-52
49፤ እርሱም፦ “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው።
50፤ እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም።
የአንድ ቀን መንገድ ከሄዱ በኃላ ነበረ ዮሴፍና ማርያም ብላቴናው ኢየሱስ ከፋሲካው በዓል አብሯቸው እንዳልተመለሰ ያስተዋሉትና ፍለጋ የተመለሱት:: ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም፦ “ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን፡” አለችው። እርሱ ግን “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” ሲላቸው እነርሱ ግን አላስተዋሉም:: በዓመት አንድ ጊዜ ወንድ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መታየት ስላለበት ይህንኑ ለመፈጸም መገኘታቸውን ብቻ ነው ያሰቡት:: ሊፈልጉት የሄዱት ጌታ በመካከላቸው እየተመላለሰ እንዳለ ባወቁ!
እየመለሰላቸው ያለው አባቴ እግዚአብሔር ነው የምገኘውም በቤቱ ነው እያላቸው ነው:: በ12 ዓመቱ የአባቱን ቤት ስራ እየሰራ ነበረ:: ከቤተሰቡ ስር እንኳን ወደኃላ ቢቀርም ብዙም አልተሰማውም:: እኛም ጉዳያችን ሁሉ ስለቤቱ ስራ መሆን አለበት:: ልጆቻችንንም ወደቤቱ እንዲመጡና እንዲተከሉ እናድርግ ደግሞም እንጸልይ::
አባት ሆይግድ የሚለን የአንተ ቤት ስራ ይሁን የምትናገረንንም እንድናስተውል እርዳን:: ልጆቻችንም በቤትህ ይለምልሙ እራስህንም ግለጥላቸው:: በኢየሱስ ስም አሜን!
ሉቃስ 3: 1-20
2፤ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ።
አንድ ሊቀ ካህናት መኖር ሲገባው ሁለት ናቸው ሐናና ቀያፋ:: በትክክለኛው በእግዚአብሔር የሚ ታወቀው ቀያፋ ነበረ ህዝብ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለህዝቡ ይሙት ብሎ ትንቢትን የተናገረ ነው:: ታሪክ እንደሚነግረን ግን ሮማዎች እንዲወርድ አስገድደውት ነው::
የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ ይላል:: መጥምቁ ዮሐንስ ትልቅ አገልግሎት ይዞ የመጣ ነው:: ይህንንም እንዲፈጽም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቷል:: መንገዱን ለጌታ የሚያስተካክል ሰው ነበረ:: ከፍ ያሉትን ቃሉን እናውቃለን ከእኛ ሌላ ማን አለ የሚሉትን ዝቅ በሉ ዝቅ ያሉትን ቀራጭ የነበሩትን ለእናንተም ነው ጌታ የመጣው ተጠባበቁ:: ህይወታቸው የተበለሻሸውንም እንደነ መቅደላዊት ማርያም ያሉትን ጠብቁ መፍትሄ እየመጣ ነው ያለ ድምጽ ነው:: ድምጹም:- “ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፡” አሜን! እኛም አህዛቦች ይኸው ማዳንህን አየን! ተመስገን!
ሁሉን አንድ ሊያደርግ የመጣ ጌታ አይሁድ የለ አህዛብ ወይም ወንድ የለ ሴት ደግሞም ጨዋ የለ ባርያ! ሁሉም በክርስቶስ አንድ ነው:: የጥሉን ግድግዳ ሁሉ አፈረሰው::
ማነህ ሲባል ዮሐንስ:- ዮሐንስ መልሶ፦ “እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፡” አላቸው።
አባት ሆይ አንተ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት አጠመከን:: ዮሐንስ የተላከበትን ስራውን በፍጹም ታዘዘና አገለገለህ:: እኛም የተጠራልነትን ስራህን እንድናገለግል እርዳን ጸጋ ይጨመርልን:: አሜን!
ሉቃስ 3: 21-38
21፤ ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥ 22፤ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።
ኢየሱስ ስለኃጥያት መጠመቅ አልነበረበትም እርሱ ግን ታዘዘና ተጠመቀ ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ:: በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።
የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል ተባለ:: ይህንን ጌታ ልበሱት ተብለን ለበስነው አሁንም በአብ ፊት መታያችን እርሱ ነው:: አንድ ጊዜ አባቱንደስ አሰኝቷልና በእኛም ላይ ሲያየው ደስ ይለዋል:: እንጂ በአንዳች በስራችን ተቀባይነትን ያገኘን አይደለንም::
ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ አልነበረም:: እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው:: መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ከመጣ በኃላ አገልግሌቱን ጀመረ:: እኛም መንፈስ ቅዱስ እጅግ ያስፈልገናል ያለ እርሱ አንዳች ማድረግ አንችልም:: ኃይልን እስክትቀበሉ በእየሩሳሌም ቆዮ የተባሉትም ለዚሁ ነው ከመጣ በኃላ አገልግሎታቸውና ህይወታቸው እንዴት እንደተቀየረ እናውቃለን::
አባት ሆይ በመንፈስ ቅዱስ ኃይላችንን አድስ አንተን ደስ ማሰኘትና ማገልገል ይሁንልን:: አሜን!
ሉቃስ 4: 1-2
1፤ ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ 2፤ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ።
በዮሃንስ እጅ ዝቅ ብሎ ከተጠመቀ በኃላ መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ:: እንዲሁም በሐዋ. ሥራ 10:38፤ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ ይላል::
በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ ሲወጣ የሆነው ነገር አልጋ ባልጋ አልነበረም:: የጠበቀው አርባውንም ቀን መፈተን ነው:: ቃሉም እንደሚል አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። ጌታ ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልም ተሞልቶ እያለ ጠላት አልተኛም ስለዚህ በምናልፍበት በማንኛውም ፈተና ጌታ መፈተኑን እያየን እንበርታ:: በነገር ሁሉ የተፈተንና የሚራራ አምላክ ነው ያለን::
በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ። ጠላታችን ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ ያለ እረፍት ይዞራል ነገር ግን ጌታ ከእኛ ጋር ነውና አሸናፊዎች ነን:: ጠላት እንደሆነ መሞከሩን አይተውም እኛም መታመናችንን አንተውም:: በፈተና የሚጸና ብጹእ ነው እንደሚል እንጽና ጌታም መውጫውን ይሰጠናል አንደናገጥ አንርበትበት ከእኛ ጋር ያለውን እንወቅ::
ሉቃስ 4:3-4
3፤ ዲያብሎስም፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ፦ ‘እንጀራ ሁን፡’ ብለህ እዘዝ፡” አለው። 4፤ ኢየሱስም፦ “ ‘ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም፡’ ተብሎ ተጽፎአል፡” ብሎ መለሰለት።
አርባውን ቀን ሁሉ በዲያቢሎስ ሲፈተን የቆየው ጌታ በነዚህ ቀናት ምንም አልበላምና ተራበ:: ሁሉን የፈጠረ ጌታ ተራበ?! ይህንን ክፍተት ያወቀ ጠላት ቃል ይዞ ብቅ አለ:: ሄዋን ጋር ተሳክቶለት ነበረና ይህንኑ ልምዱን ይዞ መጣ:: ይዞ የመጣው ቃል ጌታ እየሱስ ተጠምቆ ሲወጣ ድምጽ ከሰማይ መቶ ነበረና እሱኑ ይዞ መርዝ ቀላቅሎ መጣ::
የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ፦ ‘እንጀራ ሁን፡’ ብለህ እዘዝ፡” አለው። መርዙ ልጅ ከሆንክ ላይ ነው:: እንደሆነማ ተመሰከረ! የሌላውን ማረጋገጫ ያላስፈለገው ጌታ ግን በኤፌሶን 6 ላይ እንደተማርነው ቃሉ የመንፈስ ሰይፍ ነውና አውጥቶ ተጠቀመበት:: ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም፡’ ተብሎ ተጽፎአል፡” ብሎ መለሰለት። አሜን!
በጠላት ኃይል ሁሉ ላይ ስልጣን ተሰቶናል የሚጎዳንም የለም:: ጠላት የቀረለት ሽንገላ ነውና ለዚህ ሽንገላው አንንበርከክ እናሳደው ከአሸናፊዎች በላይ ነንና በአይምሯችን መታደስ እንለወጥ ቃሉ ይለውጠው አስተሳሰባችንን:: መልክት ጌታ ሲናገር ጠላትም እየሰማ እንደሆነ እንወቅ:: እንንቃ ጠላት ዙሪያችንን የሚዞር ምንም ማድረግ የማይችል ነው እድል ካልሰጠነው:: ስለዚህ በቃሉ እውነት እንሞላ እንደቃሉም እናስብ:: የተቀበልነውን የተስፋ ቃል አጥብቀን እንያዝ እንዳያስጥለን:: የምንዋጋበትን የእግዚአብሔርን ቃል እንያዝ በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ በጌታና በኃይሉ ችሎት እንበርታ!
ሉቃስ 4: 5-8
7፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል፡” አለው። 8፤ ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ፡’ ተብሎ ተጽፎአል፡” አለው።
አርባ ቀን ሙሉ ሲፈትነው የቆየው ዲያቢሎስ መቼም ኢችን ሶስት ሽንገላ ብቻ አይደለም ወደእርሱ ይዞ የመጣው ብዬ አስባለሁ:: ልጅ ከሆንክ የሚለው ወጥመዱ መክሸፉን ሲያይ ስገድልኝና ክብርን ሁሉ ልስጥህ ብሎ መጣ::
የሚገርመኝ ነገር የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል፥ ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ ማለቱ ነው:: ማን ሰጠውና? አዳምም አይደል? አሁን መቀምያው እንደሆነ አላወቀ! ለመስቀል ሞት በመታዘዝ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስምን ሰቶን እናንበረክከዋለን ዛሬ:: በትንሳኤው ጉልበት ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ የሞትና የሲኦልን ቁልፍ ይዟል:: ለዲያብሎስ የቀረ ስልጣን የለም ሁሉንም ተቀምቷል ያለው ሽንገላ ብቻ ነውና በቃሉ እውነት ተሞልተን ስራውን እናፍርስበት::
ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?! መርዙ ቀላል አይደለም የሚመጣበት መንገድ ረሃብን እንዲሁም ብልጽግናንና ክብርን አስታኮ መጣ:: ድፍረቱ ለፈጠረው ጌታ ይህንን ሁሉ ክብር ስገድልኝ እንጂ እሰጥሃለሁ ይላል :: በዙሪያችንም ስናይ ማን ለእርሱ ሰግዶ በሰላም ተቀመጠ? ፍፃሜያቸውን አይተናል:: የእኛ ጌታ ግን እውነተኛ እረኛ የዓለምን ክብር ሳይሆን እራሱን ሰጠን ወደንና ፈቅደን ደስም ብሎን እንሰግድለታለን::
ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ፡’ ተብሎ ተጽፎአል፡” አለው። አሜን! ሊሰገድለትና ሊመለክ የሚገባው ለእርሱ ብቻ ለፈጠረን በደሙም ለዋጀን ለእውነተኛው ጌታ ብቻ ነው:: አሜን!!
አባት ሆይ እኔም ትውልዴም አንተን ብቻ እናመልካለን ለአንተም ብቻ እንሰግዳለን! አሜን!
ሉቃስ 4:9-13
ሉቃስ 4:12፤ ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎአል፡” አለው።
ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህንን ሁሉ ክብር ለምወደው እሰጣለሁ ሲል ትንሽ ስቅጥጥ አይለውም ሲዋሽ:: ምን መውደድ አለው መግደልና ማጥፋት እንጂ! ይሄኛው ፈተናው ስለከሸፈበት ወደ ታች ራስህን ወርውር በሚለው ፈተና ተገለጠ::
ጠላት ያለውን ሁሉ ወርድሯል ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ አይችልም ምክንያቱም ፍጥረት ነው ያልቅበታል:: ይዞ የሚመጣውም ፈተና እስከአሁን የተጠቀመበትን ነው:: ብትወድቅ መልአክቱን ስለአንተ ያዝልሃል ሲለው ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎአል፡” አለው። በቃሉ መለሰለት እንጂ ጌታችን በሌላ መልኩ ሲጋበዝ አናየውም ጀግና ጀግና መጫወት የለብንም:: ቃሉና ስሙ በቂ መዋግያ ነው::
በ1 ዮሐንስ 2:15-16፤ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። የጌታን መፈተን በዚህ ቃል ውስጥ እስኪ እንየው ያልተፃፈልን አቅጣጫ የለምና:-
የሥጋ ምኞት የሚለውን ምሳሌው ድንጋዮን ዳቦ አድርግ ያለበት አይነት ነው::
የዓይን አምሮት – (ሄዋንንም የጣለበት) ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህንን ሁሉ ክብር እሰጥሃለሁ ያለው ነው::
ስለ ገንዘብም መመካት – ትምክህት/ትዕቢት ብዙ መገለጫ አለው እኛ ግን የተባልነው ትሁት እንድንሆን ነው በፈተና ከመውደቅ ይጠብቀናልና:: የሚመካ በጌታ ይመካ!
ስለዚህ በምናልፍበት ነገር አናድንቅ ለሁሉ ነውና ፈተና:: በ1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።
ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። በያዕቆብ 4:7፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል:: ተመልሶ አይመጣም አልተባልንም ይሸሻል ወይም ለጊዜው ተለየ እንጂ:: እግዚአብሔር ማንንም አይፈትንም ዲያቢሎስ ነው የሚፈትነን በቃሉ ተሞልተን ጸንተን እንቃወም:: ነገራችንን ከሰው ጋር አናያይዝ ከኃላ ያለውን እንንቃበትና እንምታው!
ሉቃስ 4: 1-13 (ክለሳ)
1፤ ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥
ይህንን ክፍል ትንሽ ደቆስ አድርገን እንጭመቀው ብዬ ነው እንደገና ያጠናሁት:: ምክንያቱም በተለያየ ፈተና እናልፋለንና ጠላት ምን ላይ እንደሚያተኩርና እኛስ ምን ማድረግ አለብን እንድናስተውል ነው::
ከሶስቱ ፈተናዎች ሁለቱ ልጅ ከሆንክ ነው የሚሉት:: ለምን ልጅነትን ይመታል? እሱን ከወሰደብን ሌላ የምንቆምበት መሰረት ያሳጣናልና ነው:: አንቺን ብሎ ክርስትያን ሲለን እውነትም ብለን ስብር እንልና ምህረትና ጸጋ እንዳለ እንረሳለን:: ያኔ ለእርሱ ይመቸዋል ከቅዱሳንና ከቤተክርስትያን ያርቀናል ከዛማ ካልነቃን ከባድ ነገር ውስጥ ይከተናል:: ብንደክም ለጌታ ብንበረታ ለጌታ:: ለፈተናው መመለስ ያለብን እየሱስ ነው በእኔ ውስጥ ክርስትያን ድሮውንም በራሴ አልጸደኩ:: እንዲያውም ጠላቴ በድካሜ ጸጋውን ይሰጠኛል በትከሻውም የሚሸከመኝ እረኛ አለኝ ሮጬ ወደ እርሱ እሄዳለሁ ይረዳኛል ብለን መመለስና መበርታት ይገባናል:: በክርስቶስ ምን እንደሆንን ከቃሉ ጠንቅቀን እንወቅ::
ምን እናድርግ:-
ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዮ ተብለናል:: ፈተና የለም አላለንም አሸንፌያለሁ ብሎናል:: እራሱም እየሱስ በመጨረሻዋ ሰዓት ብቻውን ተጋ እንጂ ሐዋርያቱማ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሏቸው ነበረና ጌታ ስለእነርሱም ማለደ:: ስለእራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለቅዱሳንም መማለድን አንርሳ:: ፈተናው መጥቶ ሲመታን በአለቱ ላይ ቤታችንን ሰርተናልና ሰባብሮ ይዞን አይሄድም::
እንዳንረታ በክርስትና ዋናው ሃብታችን መንፈስ ቅዱስ ነው:: ጌታ እየሱስ በመንፈስ ተሞልቶ ነው አርባውንም ቀን እየተፈተነ በርትቶ ለአንዱም የሰይጣን ፈተና ሳይወድቅ እኛን ተቤዥቶ ያለው:: ዛሬ የሚራራልን ሊቀ ካህናት ቢፈተንም ያልተረታ አለልን:: ስለዚህ ዕለት ዕለት በመንፈስ ተሞሉ እንደሚል ጠይቀን እንሞላ:: እርሱ እንደሆነ በልግስና ሳይሰፍር መንፈሱን ይሰጠናል:: ስሙ ይባረክ!
ሌላው ጌታ እየሱስ ከዲያቢሎስ ጋር አታካራ አልገባም :: ይመልስ የነበረው የተጻፈው ቃል ነበረ:: ስለዚህ ዛሬም መዋጊያችን በሁለት በኩል የተሳለው የመንፈስ ሰይፍ ነው:: ቃሉን እንብላ እናሰላስለው ከእርሱም ፈቀቅ አንበል በጸሎትም እንትጋ::
ሉቃስ 4: 14-21
17-19፤ የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥
ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። ከአርባ ቀን ጾም በኃላ ኢየሱስ የበረታው በመንፈስ ኃይል ነበረ:: የጌታ ዝና እየወጣ ሄደ በምኩራብም ያስተምር ጀመረ:: በዚህም ጊዜ ነው የኢሳያስን መጽሐፍ የሰጡትና አንብቦ ሳያብራራ የተቀመጠው:: ምን ማብራራት ያስፈልጋል በፊታቸው ቆሞ እየፈጸመው?! ማስተዋል ይስጠን ከጌታ ጋር እንዳንተላለፍ::
ክፍሉም የሚለው: የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ አሜን ይህ መንፈስ በእኛም ላይ ነው:: ምን ለማድረግ?
– ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤
– ለታሰሩትም መፈታትን
– ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥
– የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ
– የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል፡:
የተላከበትን ዓላማ ቁልጭ አድርጎ ነገራቸው:: እኛም የተላክነው ለዚሁ ነው:: እኛም የተላክነው ለድሆች: ለታሰሩ: ለዕውሮችና ለተጠቁት ነው:: ወንጌል ስለእየሱስ ነው ይህንን ሁሉ የሚያደርግና የሚሰራ እራሱ በመንፈሱ ነው:: እንዲሁም የተወደደችውንም የጌታን ዓመት ሰበከ ይህም ማለት እዮበልዮ ነው በዕዳ ሁሉ የተያዙት በየ50 ዓመቱ ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ነውና የጌታ ዓመት ሲላቸው በደንብ ይገባቸዋል:: ማንም ዕዳ አይኖርበትም ብሎ አወጀ እኛም ነፃ ሆንን የሚከሰን እስከማይኖር ድረስ – ማንም በክርስቶስ ቢሆን ኩነኔ የለበትም:: ይህንን እንድንሰብክ ተጠርተናል:: ማለትም የእግዚአብሔር በግ እየሱስ ተገልጧል የዕዳው ጽህፈት ተደምስሷል ሞትና ሲዖልም ድል ተነስተዋል አርነት ታውጇል ብለን እናውጃለን:: አሜን!
አባት ሆይ ስራችንን ችላ እንዳንል እርዳን! አሜን
ሉቃስ 4: 22-30
22፤ ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።
ወንጌል ምን እንደህነና ለማን እንደሆነ ከትንቢቱ ነገራቸው:: ወንጌል ለድሆች: ለታሰሩት: ለዕውሮችና ለተጠቁት ነው:: ይህንን መስፈርት ስላሟላን ይህንን ጌታ አወቅን እንጂ አንዳች በእኛ ባልሆነ መንገድ ዳንን:: ይህንንም ወንጌል ልናደርስ አደራ ተሰጠን:: እንዲሁም የተወደደችውን የጌታን ዓመት ይኸውም የመምጣቱንና የመመለሱን ዜና እንድንናገር ተጠርተናል::ማራናታ!
ከልጅነቱ ጀምሮ ወዳደገበት ወደ ገሊላ መጥቶ ሲያስተምር ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ማለትን ጀመሩ ከአፉ ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሳ እየተደነቁ:: መተላለፍ ሆነባቸው ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር የዮሴፍ ልጅ መስሏቸው:: ስለዚህም ይለይላችሁ ብሎ የኤልያስን ወደ ሰረፕታዋ መበለት መላክና ስለንዕማን ለምጽ ነገራቸው::
ብዙ መበለቶች በእስራኤል ቢኖሩም እንኳን የተላከው ወደ አህዛቢቷ ሴት ነበረ:: በእስራኤልም ብዙ ለምጻሞች እያሉ ከሩቅ መጥቶ ንዕማን ተፈወሰ:: ስለዚህ የእግዚአብሔርን ማዳን ካልተቀበላችሁ አሁንም ይኸው ነው የሚሆነው እያላቸው ነው:: በቅድሚያ ለጠፋው ለእስራኤል ነበር ወንጌል አልሰማም ሲሉ ወደ አህዛብ ደረሰ:: ይኸው ዛሬ የከበረውን ቃል እየተመገብን ከመንፈሱም እየጠጣን አለን:: እስራኤል ግን እስከዛሬ ጠፍታለች:: አቤቱ ለዚህ ህዝብ ወንጌል ይድረስ ደንዳናውን ልባቸውንም ፈስው:: አሜን!
ይህ ንግግሩ አስቆጥቷቸው ከከፍታ ላይ ሊጥሉት ወሰዱት እርሱ ግን ጊዜው አልደረሰምና በመካከላቸው አልፎ ሄደ:: ሰው በዚህ እንኳን እንዴት አያስተውልም?! በሌላ ስፍራ ካለማመናቸው የተነሳ ብዙ ማድረግ አልቻለም ነበር:: ነብይ በአገሩ አይከበርም::
አባት ሆይ እኛን የበረሃ ወይራ የነበርነውን አሰብከን በወይኑም ግንድ ላይ አደረከን ተመስገን:: ወንጌልን ይዘን እንሮጥ ዘንድ ልጆችህን እርዳን:: አሜን!
ሉቃስ 4: 31-37
32፤ ቃሉ በሥልጣን ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ።
ባደገበት ከተማ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን ብለው ሳይሰሙት ቀሩ:: ወደ ቅፍረናሆም ወርዶ ሲያስተምር ቃሉን በስልጣን ያስተምር ነበረና በትምህርቱ ተገረሙ::
እያስተማረም አጋንንት ያደረበት ሰው “ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ፡” አለ። ኢየሱስም፦ “ዝም በል ከእርሱም ውጣ” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ።
ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ:: አጋንንት በደንብ አውቀውታል የእግዚአብሔር ህዝብ ግን አላወቀም:: የጠላትን ምስክርነት አንፈልግም የልጅነት ስልጣን የተሰጠንና ከአሸናፊዎችም በላይ መሆናችንን ቃሉ መስክሮልናልና ሌላ ምስክር አያስፈልገንም:: ዛሬም ይህንን የተሸነፈ አጋንንት በስሙ ስልጣን እያወጣን ሰዎችን ለጌታ እንማርክ:: እርሱም ይወጣል!
ከዚህ ተአምር በኃላ ዝናው በዙሪያው ባለች አገር ወደ ስፍራው ሁሉ ስለ እርሱ ወጣ። ይህ እንዲሆን ቅናቴ ነው – የኢየሱስ ዝና ይውጥና ሰዎች ወደ እርሱ ይሰብሰቡ! እኛን ሳይሆን እርሱ ይታይ! መዳን ይታወጅ! ለታሰሩትና ለታወሩት ወንጌል ይድረስ:: አሜን! አንብበንና ሰምተን እንድንሄድ ሳይሆን እንጸልይ የመከሩ ጌታ የመከሩን ሰራተኞች እንዲጨምርና እኛንም እንዲልከን::
አባት ሆይ እኔንም ላከኝ ወደ መከሩ ሰውን አጥማጅ አድርገኝ:: አሜን
ሉቃስ 4: 38-41
40፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ እርሱም በእያንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው።
በእያንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። እንዴት ደስ ይላል ባለመለየት ሁሉንም ፈወሰሰ:: ጌታ ኢየሱስ ዛሬም ይፈውሳል:: በመገረፉ ቁስል እኛ ተፈወስን:: መፈወሳችንም ደስ ያሰኘዋል የልጆችም እንጀራ ነው ብሎ ጠርቶታልና በአባታችን ቤት መብል አንከለከልም:: አጋንንትም በስሙ ይወጣል!
አባት ሆይ ስምህ ይባረክ! ረውስን ለህዝብህ ሰተሃልና ዛሬም በህመም የሚሰቃዮ በኢየሱስ ስም ይፈወሱ:: አሜን!
ሉቃስ 4:42-44
43፤ እርሱ ግን፦ “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል፡” አላቸው።
በጸባም ጊዜ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ምክንያቱም ፈውስንና የአጋንንትን መታዘዝ አይተው ነበረና ወደ እርሱም መጡ፥ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ወደዱ። እዚህ ኑር አስተምረን ፈውሰን የትም አትሂድ ነው አባባላቸው::
እርሱግን በየስፍራው ሁሉ የመንግስትን ወንጌል እየሰበከ ዞረ:: ዛሬም በስፍራ ሁሉ መሰበክ አለበት ጌታ ሊመጣ በደጅ ነውና ከወገን ከቋንቋ ሁሉ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ዘወር እንዲሉ:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን ይህንን ወንጌል ይዘን እንድንሮጥ::
ሉቃስ 5: 1-3
3፤ ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር።
ጌታ ጴጥሮስን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው:: ለመነው የሚለው ነገር ልቤን ነካው የለመነውም ሊያገለግልበት ነው ውስጡ ከገባ በኃላ:: እኛም ውስጥ የገባው ጌታ በሮሜ 12:1፤ እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። ተብለናልና ለጌታ ያለ ስስት እራሳችንን እናቅርብ! ጌታ ሆይ ጸጋህ ያግዘን!
ሉቃስ 5 : 4-7
4: ነገሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን፦ “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ፡” አለው።
ለሊቱን ሙሉ ባለሙያ የሆኑት ዓሳ አጥማጆች ምንም እንዳልያዙ ቢነግሩትም እርሱ ግን ጣሉት አላቸው:: በቃሉ ሰማይና ምድርን የፈጠረው ጌታ ዛሬ ቢደግምስ መፍጠሩን? እነሆም በቃሉ መሰረት መረቡን መተው ሞሉት:: ዛሬም ጌታ ይህንን ማድረግ ይችላልና ሁኔታን አይተን አንመላለስ የጌታን ፊት እንጂ! እርሱ ተአምራትን ያደርጋል እውቀታችንን አንደገፍ::
ሉቃስ 5: 8-11
8 ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ፡” አለው። 9 ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፥
ሲፈልጉ አድረው ያጡትን ዓሳ በቃሉ መረባቸውን በሞላ ጊዜ ጴጥሮስ ማለት የቻለው “ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ፡” አለው። አሁን ስለ ኃጥያት ምን አመጣው? የፈለገውን አገኘ ግን የእግዚአብሔርን ልግስና የማይገባኝ ነኝ እኔ ኃጥያተኛ ነኝ ከእኔ ራቅ አለ:: የጌታ መገኘት ማንነቱን አሳየው:: ጌታም አትፍራ ሰውን አጥማጅ አደርግሃለሁ ብሎ ወደ አገልግሎት ጠራው:: የኃጥያተኞች ወዳጅ የተባለው ጌታ ማንንም ሳይለይ አጥቦ አንጽቶ ይጠቀምብናል:: ሃሌሉያ!!
ሉቃስ 5: 12-16
12 ከከተማዎችም በአንዲቱ ሳለ፥ እነሆ፥ ለምጽ የሞላበት ሰው ነበረ፤ ኢየሱስንም አይቶ በፊቱ ወደቀና፦ “ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ፥ ልታነጻኝ ትችላለህ፡” ብሎ ለመነው። 13 እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፦ “እወዳለሁ፥ ንጻ፡” አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ለቀቀው።
በብሉይ ኪዳን ለምፃምን መንካት ያረክሳል ስለዚህ ማንም አይቀርበውም የተገለለ ነው:: የዚህ ሰው ጥያቄ ግን ይገርማል ምን ቢያይና ቢተማመን ነው አንፃኝ ብሎ የጠየቀው?! ጌታ ግን ሳይሸሸው እንዲያውም ዳሶ እወዳለሁ ንፃ ብሎ ፈወሰውና ራስህን ለካህን አሳይ አለው:: ዋዉ ጌታ መታሰባችንን ይወዳል ስሙ ይባረክ!
ምንም እንኳን አትናገር ቢለውም ዝናው ወጣ ብዙ ሕዝብም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ይሰበሰቡ ነበር:: ዝናው በወጣ ጊዜ ግን እርሱ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ብሎ ይጸልይ ነበር ይላል:: እኛስ? ያውም ጌታ ስራውን ሲሰራ መቼም እኛ አይደለን የምንፈውስ ወዴት ይሆን የምንሮጠው? ወደ እግሮቹ ይሁንልን! ከፊቱ አንታጣ! እርሱ ዛሬም ይሰራል:: ጌታዬ ሆይ ክብርህን ወደ ራሳችንም ይሁን ወደ ሌላ ስጋ ለባሽ በመውሰድ እንዳንበድልህ እርዳን!
ሉቃስ 5:17 አንድ ቀንም ያስተምር ነበር፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮችም ሁሉ ከኢየሩሳሌምም መጥተው የነበሩ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ይቀመጡ ነበር፤ እርሱም እንዲፈውስ የጌታ ኃይል ሆነለት።
እነዚህ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ሲያስተምር ሰምተው ስህተት ለማግኘትና እርሱን ለመክሰስና ነገር ን ለመፈለግ ነው የሚከታተሉት እንጂ ለመማር ወይም የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራ ለማየት አይደለም:: ያም ሆነ ይህመምጣታቸው ጥሩ ነው ቢያንስ ኒቆዲሞስን ወደጥያቄ አምጥቶታልና::
ለጌታ እየሱስ እንዲፈውስ የጌታ ኃይል ሆነለት ይላል:: ምን እንዲያደርግ? እንዲፈውስ!!! መፈወሳችንን የሚወድ ጌታ ስሙ ይባረክ!! ዛሬም ይሄ ኃይል ይገለጥ በእያንዳንዳችን ምክንያቱም ብዙዎች ፈውስ ያስፈልጋቸዋልና:: ያቺ ሴት ስትፈወስ ኃይል ከእኔ ወጣ አለ ብዙዎች እያጋፉት እርስዋ ግን ተንጠራርታ የልብሱን ጫፍ በእምነት ነካችና ፈውስ ሆነላት::
አባት ሆይ ይህ ኃይል በእኛም ህይወት ይስራ:: አሜን
ሉቃስ 5:18 – 26
20 እምነታቸውንም አይቶ፦ “አንተ ሰው፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ፡” አለው።
ይህንን ሰው ወደጌታ ይዘው የመጡ ሰዎች የሚገርሙና የመጡበትን ዓላማ ሳይፈጽሙ የማይመለሱ ናቸው:: በእነርሱ እምነት ይህ ሰው ተፈወሰ:: እኛም ዛሬ በእምነት ወድፊቱ የምናቀርበው ልመና ይመለሳል:: በሌላው አንፃር ይህንን ንግግሩን ያልወደዱለት ነበሩ:: ያለ አንዱ እግዚአብሔር በቀር ማን ኃጥያትን ማስተሰረየት ይችላል ብለው አሰቡ:: ጌታም በምድር ላይ ኃጢአት ሊያስተሰርይ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፡” ብሎ፥ ሽባውን፦ “አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ፡” አለው። ወድያውም እንደተባለው አደረገ ፈውሱንም ተቀበለ:: ሊቀ ካህናቱም ይሁን ማን ይህንን ማድረግ አይችሉም የታረደው በግ ግን ኃጥያትን ይቅር ማለና መፈወስ ይችላል:: አሜን!
ከዚህም የተነሳ ሁሉንም መገረም ያዛቸው፥ እግዚአብሔርንም አመስግነው፦ “ዛሬስ ድንቅ ነገር አየን፡” እያሉ ፍርሃት ሞላባቸው።
ሉቃስ 5: 27-32
31 ኢየሱስም መልሶ አላቸው፦ “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ 32 ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።”
ወንጌል ዛሬም ይኸው ነው! ለሕመምተኞችና ለኃጢአተኞች ነው ኢየሱስ የመጣው ሊፈርድባቸው ሳይሆን ሊያድናቸው ነው:: ማኅበረሰቡ ከሚለው ባህላችን ከሚለው የምድር ቀመሮች ከሚያወሩት ሁሉ ወተን ሰውን በሰውነቱ አይተን የእግዚአብሔርም ክብር እንደጎደለው አውቀን ክርስቶስን ባለማዳላት እንስበክ:: ከጌታ ጋር ታረቁ እንበል:: እንደባህሉ ቢሆንማ ማቴዎስ ደቀ መዝሙር ባልሆነም ነበር:: ጌታ ይርዳን!
ሉቃስ 5: 33-39
35 ነገር ግን ወራት ይመጣል፥ ሙሽራውም ከእነርሱ ሲወሰድ ያንጊዜ፥ በዚያ ወራት ይጦማሉ።” 36: ደግሞም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “የአዲስ ልብስ እራፊ ባረጀ ልብስ ላይ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱን ይቀደዋል ደግሞም አዲስ እራፊ ለአሮጌው አይስማማውም።
ጥያቄያቸው “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ ምን ብዙ ይጦማሉ ጸሎትስ ስለ ምን ያደርጋሉ፥ ደግሞም የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ስለ ምን እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ ይጠጣሉም?” ነበር:: እነርሱ የሚጾሙትና የሚጸልዮት አንዱ ምክንያት መሲሁ እንዲገለጥ ነበረ እርሱ በመካከላቸው ቆሟል:: ጊዜውን ያልዋጀ ነበረ (የልማድ):: ጊዜያችንን እንድንዋጅ ጌታ ይርዳን ከጌታ ተረድተን የጊዜውን ማድረግና በሚያስፈልግ ጊዜ ጾምን ማወጅ:: በተመደው አካሄድ ከመሄድ በአዲሱ በመረቀልን መንገድ የጌታን ፈቃድ እያወቁ ከአዲስ አሰራሩ ጋር ተዋህዶ በመንፈስ እየተመላለሱ መጾምና መጸለይ ይሁንልን::
ሉቃስ 6:1-5
5 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፡” አላቸውም።
ስለጾም አነሱ መለሰላቸው ጌታ የሚፈልገው ጾም ምን አይነት እንደሆነም አያውቁም:: ኢሳ 58:1-9 ያለውን አይነት ውጤት ያለው ጾም እንጂ ልማድን አይደለም የሚፈልገው::
እዚህም ክፍል ላይ ሰንበትን አልጠበቁም በእርሻው መካከል ሲያልፉ እሸት ቀጥፈው በልተዋል ነው ክሱ:: የሰንበት ጌታ እንደሆነ አውጆ ክሱ ተቀባይነት አላገኘም ከዚህ የባሰ ዳዊት አድርጏል ብሎ ሻረው ቃሉን ማንበብና ማወቅ ይለያያል ያወቀ ይኖርበታል:: አቤት ትኩረታቸው ሁሉ ልምድ ላይ ነው:: እኛም ሳናስብ በልምድ ተይዘን ዋናውን የተጠራልለትን ሰውን መውደድና ወደ ጌታ ማምጣት አስትቶን እንዳይሆን ጌታ ሆይ እርዳንና ሰፊ ልብን ስጠን!
በሆሴዕ 6:6 ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና:: አሜን!
አባት ሆይ በልምና በባህል ተጠርዤ እንዳልገኝ እርዳኝ የመረጥከውን አይነት ህይወት እንድመላለስና ቃልህንና ኃይልህን እንዳልስት እርዳኝ::
ሉቃስ 6: 6-11
9 ኢየሱስም፦ “እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል?” አላቸው።
ጥያቄውን እንኳን ያስተዋሉ አይመስለኝም:: እነሱን የያዛቸው ነገር ሰንበት ተደፈረ ነው:: የሰንበት ጌታ እንደሆነ ከሳምንት በፊት ነግሯቸው ነበር እነርሱ ጋር ግን ቃሉ ጠብ አላለምና እንደወጥመድ ሊጠቀሙበት ተነስተዋል:: ጌታ መሆን የማይገባው ጌታ ሆኖ ፈውስን ሊከለክል ነበረ:: ጌታ ግን ወደ ምኩራብም ሲመጣም ያንን እጁ የሰለለችን ሰው አይቶት እጎበኘዋለሁ ብሏልና አሳቡን አላስቀየሩትም በሰንበት በጎ አደረገ! ፍቅሩ ብዙ የሆነ ጌታ ስሙ ይባረክ!
ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን፦ “እጅህን ዘርጋ፡” አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች። አሜን! ሰውን በማዳንና በመፈወስ ደስ የሚለው ጌታ ዛሬም አልተለወጠም በዚሁ አሳብ ላይ ነውና ወደፊቱ እንምጣና እንፈወስ ሌሎችንም እናምጣና የጌታችንን ማዳን እናሳይ! ሃሌሉያ!
ሉቃስ 6: 12-16
12 በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ።
ሙሉ ለሊት መጸለይ?! እንዴት ደስ የሚል ነገር ነው? ከእኛም የሚጠበቅ ነው ምክንያቱም ጸጋን በልግስና ይሰጣልና:: በራሳችን በተለያየ ዘዴ ለተወሰነ ሰዓት ለጸሎት መትጋት ይቻል ይሆናል በጸጋ ግን ሲሆን ቀላል ነው:: እንደፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናልና ይህንን በፊቱ የምንተጋበትን ጸጋ ያፍስስልን! አሜን!
ጌታለሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሮ በማግስቱ ያደረገው ነገር ደቀመዛሙርትን መርጦ መጥራት ነበረ:: እነዚህ በዚህ ሁሉ ጸሎት ውስጥ የተመረጡ ናቸው ወንጌልን ለዓለም ያደረሱት:: ለመንግስቱ ስራ እንበርታ!
ሉቃስ 6:17-19
19 ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር።
ወደ ጌታ ኢየሱስ ይመጡ የነበረው ሊሰሙትና ሊፈወሱ ነበር:: ኃይልም ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና :: ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ::
ለሐዋርያት ያላቸው ከመሄዱ በፊት ኃይልን እስክትቀበሉ ድረስ በእየሩሳሌም ጠብቁ ነበረ:: ይህ ኃይል ዛሬም ያስፈልገናልና ለመቀበል በፊቱ እንገኝ:
አባት ሆይ ኃይልህን ሙላንና በእኛ ተጠቀም:: አሜን!
ሉቃስ 6:20-26
22 ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። 23 እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና።
የእግዚአብሔር ነገር ተቃራኒ ነው ለድሃው ጽድቅን ይሰጣል:: ስለስሙ ስንጠላ ብጹዓን ናችሁ ይለናል ዋጋችሁም በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም ይለናል እንጂ ተክዙ አላለንም:: በስሜ የሚያፍርብኝን አፍርበታለሁ የማያፍረውን ደግሞ እመሰክርለታለሁ ብሎናልና በህይወታችን እርሱን እናሳይ ደግሞም እንመስክር:: ጥላቻ ከመጣም እንደሰት:: አንድ በህብረታችን ውስጥ የነበሩ አባት ወግ ደርሶኝ ከእድር ተባርሬአለሁና አመስግኑልኝ ያሉትን አልረሳውም:: የገባው እንደዚህ ይላል::
ሉቃስ 6: 27
27 “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥
ጆሮ ያለው ይስማ:-
ከሰማን ጌታ ይናገራል ዙሩን እያከረረው ነው ያለው:: ጠላቶቻችሁን ውደዱ?! እንዴት ይቻላል?! ጠላት የተባለው በምክንያትም አይደለም እንዴ? ጠላት እንዳለን ጌታም ያውቃል ግን ደግሞ ብቃትን ሰቶናልና የጌታ መልስ ለዚህ ጥያቄ በአዲሱ ሰው ይቻላል ነው በመንፈስ ተመላለሱ የሚል ነው::
ደቀመዝሙር መሆናችን የሚታወቀው በፍቅራችን ነው የምንወደው ለይተን አይደለም የወዳጅና የጠላት የሚል ግሩኘ የለንም ሁሉ ወዳጅ ነው በጌታ ዲክሽነሪ:: ማስተዋል ይሁንልን እንደቃሉ እንድንመላለስ:: በክርስቶስም የተፈጠርነው መልካምን ለማድረግ ነውና ሰውን ሳንለይ መልካም እናድርግ::
ሉቃስ 6:28 የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ።
የሚረግሙንን መመረቅ? ቢያንስ መመረቁ ቀርቶ ዝም ብለን እንለፍ የሚለው ትንሽ ይሻላል የሰጡትን ሰፍሮ መመለስ ለሚያውቀው አእምሮ:: ነገር ግን በአእምሮ አንመራም የምንመራው በመንፈስ የምናመልከው በመንፈስ ነውና ልባችንን ወደ ጌታ እናንሳ:: ይህ የምንኖርበት አዲስ የህይወት መንገድና ዘይቤ ነው እንጂ ስንፈልግ ኦን ስንፈልግ ኦፍ የምናደርገው አይደለም:: እኛስ የክርስቶስ ልብ አለን:: ሰው በደህናው ክፉ አይሆንምና ክርስቶስን እንዲያውቁ እየባረክን እንጸልይላቸው ለክፉ ንግግራቸውም እግዚአብሔር ይባርካችሁ እንበል:: ጠላት አንዳች እንዳያገኝ በድል መመላለስ እንዲሆንልን እራሳችንን በቃሉ እንፈትሽ!
ስለሚበድሉአችሁም ጸልዮ ሲለን ጌታ ከዚህ በላይ ኖሮ ነው:: ለገረፉት ለተፉበት ለሰቀሉት የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ጸልዮ አሳይቶን ነው:: ማንም ጸጋ ቢጎድለው በልግስና የሚሰጠውን ጌታን ይጠይቅ እንደሚል ቃልህ ጌታዬ ሆይ ሁሉን እየወደድን የምንጸልይበትን ጸጋ ስጠን በመንፈስ ቅዱስ በልባችን የፈሰሰውን ፍቅር አያሳፍርምና ግለጠው:: አሜን!
ሉቃስ 6:29 “ጕንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ስጠው፥ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን ደግሞ አትከልክለው።
ይሄ መቼም በእርግጥ መምታት ብቻ አይደለም ለምሳሌ:- ጌታ ኢየሱስን “ጋኔን አለበት፡ አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ?” እንዲሁም “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” ሁሉ ይሉት ነበረ:: እርሱ ለዚህ ስድባቸው ሲመልስና ለእራሱ ሲከራከር አናይም:: በዘመናችን ዱላን ብዙም ላንቀምስ እንችላለን ስድብና ማሽሟጠጥ ግን አይቀሩም:: ይሉኝን (ይሉኝታን) አውጥተን ጥለን ፍቅርን ተሞልተን በመልካም ልብ ሳንፈርድ ቁጣም ሳይሞላን እንመላለስ:: ለሁሉ ፍቅርን እንስጥ:: የጌታ ጸጋ በዛ ውስጥ ይገለጣል::
እርሱ ህይወቱን እንደሰጠን እያሰብን ማካፈልንና መስጠትን እንድንለማመደው ጌታ ይርዳን:: ሌሎችን በመባረክ ደስ ይበለን:: ህይወትን እንኑሩው እንጂ ማንበብ ብቻ አይሁንብን::
ጌታ ሆይ እንድንዘረጋ ወደምትፈልገው ሁሉ እንዘረጋ ዘንድ ጸጋህን ስጠን በውስጣችንም ያለው ፍቅር ወጥቶ ይውደድ – እኛ የምንሰጠው የለንምና! ተባረክ:: አሜን!
ሉቃስ 6: 30-31
30 ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፥ ገንዘብህንም የሚወስድ እንዲመልስ አትጠይቀው። 31 “ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።
ሰውን በለመስጠት ለመባረክ የሚያስፈልገን ከገንዘቡ በላይ ፍቅር ነው:: ፍቅር ካለ መስጠት ይቀላልና የተቸገሩትን ለማሰብ የክርስቶስ ፍቅር ይሙላን::
ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ ማድረግ የሚለው እራሳችንን እንድናይ የሚያደርገን ሚዛን ነው:: ይህንን ምክር ወርቃማው ህግ ብለው ይጠሩታል:: እንዲድረግብን የማንፈልገውን አናድርግ:: በማስተዋል እንመላለስ ለሌሎችም እንቅፋት እንዳንሆን::
አባት ሆይ በልግስና ያለ ስስትእንድንሰጥናሌሎችን ልክ አንተ እንደወደድካቸው መውደድ እንድችል እርዳኝ:: አሜን!
ሉቃስ 6: 32-33
32 የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። 33 “መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና።
የአዲሱ ኪዳን ህይወት ከብሉይ ይለያል:: ጥሩ ተብለው የሚባሉትን ሁሉ የሚቀይር ነው:: የሚወዱንን መውደድ ወይም መልካም ላደረጉልን መልካም መመለስ ጥሩ ነው ምን ክፋት አለው? እንል ይሆናል:: ነገር ግን በውስጣችን እየኖረ ያለው ፍቅር የሆነ ጌታ ለዚህ አይደለም የመጣሁት እያለ ነው:: ይህንንማ ሰው ሁሉ ማድረግ ይችላል:: የእኔ ደቀ መዝሙር ግን በፍቅሩ ይታወቃል ስለተደረገለት ወይንም ወሮታን ለመመለስ አይደለም የሚወደው ነገር ግን እግዚአብሔር ሰውን በወደደበት መውደድ እየወደደ ምላሽን ሳይጠበቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማገልገል ነው:: እግዚአብሔር ይርዳን የሰው ልጆችን ሁሉ ሳንለይ እንድንወድድና መጥፋታቸው ግድ ብሎን የምስራቹን እንድንመሰክር:: ከፍቅርም በቀር ሌላ እዳ አይኑርብን:: ያለዛ ግን እንደሚሿሿ ፀናፅል ነን ከድምጽ ውጪ ምንም ፍሬ የሌለው ማለት ነው:: ጆሮ ያለው ይስማ! ሁሉን በጸጋው ለሚያደርገው እረኛ እራሳችንን እናቅርብ!
ሉቃስ 6: 34-36
35 “ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና። 36 አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።”
ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ ያስባለው ነገር እየሱስን እየመሰሉ መመላለሱ ነው:: አምላካችን ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና ከእኛም ይህ አባታችንን መምሰል ይጠበቅብናል:: ጠላትን እንደ ክርስቶስ በመውደድ ፤ እንዲሁም በክርስቶስ የተፈጠርነው መልካም ለማድረግ ነውና መልካምን እያደረግንና ምንም ተስፋ ሳናደርግ ማበደርን እየተለማመድንጌታን እናሳይ:: አባታችን ርኅሩኅ እንደ ሆነ እኛም ርኅሩኆች እንሁን። ልክ እንደ አባታችን የሰው ልጅ ሁሉ ያሳዝነን የምንራራም እንሁን:: ጌታ ማስተዋልን ይስጠን!
ሉቃስ 6:37 “አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ።
የእግዚአብሔርን ርኅራኄ የቀመስንና ያስተዋልን እኛ እንጂ ዓለም አይደለችም:: ርኅራኄውን እንደቀመሰ ሰው ስንመላለስ በሌሎች ላይ እንዳንፈርድ ፤ እንዳንኮንንና ይቅርታን እንዳንነፍግ:: ይልቁንም ሰፊ ልብ ይዘን ሌሎችን ማቀፍና የቀመስነውን ጌታ መስለን መማረክ ይሁንልን::
ጌታ ይቅር በሉ ሲለን ሳያልፍበት ቀርቶ አይደለም:: ማንም በማይቀርበው ብርሃን ይኖራል የተባለው ጌታ ሲመቱት ፤ ሲገርፉት ፤ ሲተፉበትና ሲሰቅሉት ይቅር አላቸው:: ከማን እንማር ታድያ ይቅርታችን በአጭር የቀረ አይሁን እንደተቀበልን በልግስና እንስጥ:: ጌታ ይርዳን! ቃሉን እንኑርበት እንጂ አንብበን አንለፈው እራሳችንን እንይበት በዚህ መስታወት::
አባት ሆይ እንዳን ከፍቅር በቀር ሌላ ዕዳ አይኑርባችሁ ስትለን በሌላ ዕዳ ውስጥ ተይዘን እንዳንገኝ ዓይኖቻችንን ክፈትልን:: አሜን!
ሉቃስ 6:37 “አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ።
የእግዚአብሔርን ርኅራኄ የቀመስንና ያስተዋልን እኛ እንጂ ዓለም አይደለችም:: ርኅራኄውን እንደቀመሰ ሰው ስንመላለስ በሌሎች ላይ እንዳንፈርድ ፤ እንዳንኮንንና ይቅርታን እንዳንነፍግ:: ይልቁንም ሰፊ ልብ ይዘን ሌሎችን ማቀፍና የቀመስነውን ጌታ መስለን መማረክ ይሁንልን::
ጌታ ይቅር በሉ ሲለን ሳያልፍበት ቀርቶ አይደለም:: ማንም በማይቀርበው ብርሃን ይኖራል የተባለው ጌታ ሲመቱት ፤ ሲገርፉት ፤ ሲተፉበትና ሲሰቅሉት ይቅር አላቸው:: ከማን እንማር ታድያ ይቅርታችን በአጭር የቀረ አይሁን እንደተቀበልን በልግስና እንስጥ:: ጌታ ይርዳን! ቃሉን እንኑርበት እንጂ አንብበን አንለፈው እራሳችንን እንይበት በዚህ መስታወት::
አባት ሆይ እንዳን ከፍቅር በቀር ሌላ ዕዳ አይኑርባችሁ ስትለን በሌላ ዕዳ ውስጥ ተይዘን እንዳንገኝ ዓይኖቻችንን ክፈትልን:: አሜን!
ሉቃስ 6:38 ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።”
ከላይ ያነበብነው አታድርጉ የተባልነውን ነው:- አትፍረዱ፤ አትኮንኑና ይቅር በሉ:: ቀላል ይመስላል ስናነበው ስናልፍበት ግን እንዴት እንሆን? ይህንን ሁሉ ነገር የምናደርገው ለራሳችን ስንል ነው ሲደርስብን አንወደውም ያመናል ሲፈረድብን ስንኮነን ስንቀምሰው መራራ ነውና እናስወግደው::
አሁንም ስጡ እየተባልን ነው:: የምንሰጠው ስለሚሰጠን ሳይሆን ርኁሩኅ የሆነውን አባታችንን እንድንመስል ብለን ነው:: እርሱ ለኃጥያተኛም ለፃድቁም እኩል ፀሐይን ያወጣልና:: ስንሰጥም በልግስና ደስ እያለን እንስጥ:: እርሱ ታማኝ ነውና በሰጠነው መስፈርያ ይሰፍርልናል:: መስጠት ይዋሃደን ዘንድ ጌታ ይርዳን:: ሰውን በችግሩ መድረስ እንድንችል ጌታ ዓይናችንን ይክፈትልን ጸጋውንም ያብዛልን::
ሉቃስ 6: 39-40
39 ምሳሌም አላቸው፦ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን? 40 ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል።
የሚመራን ማን እንደሆነ ውሳኔው የእኛ ነው እውር እንዳንከተል በቃሉ እውነት መርምረን የህይወትንም ፍሬ እያየን መሆን አለበት::
እረኛችን ግን ሲያስተምረንና ሲቀርጸን እርሱን እንድንመስል ነው:: ይኸው ነው የተወሰነው በሮሜ 8:29 . . . አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና:: በኃላም ስንገለጥ እርሱን እንመስላለን:: እውር ያስተማረው ጥሩ እውር ይሆናል ከጌታም የተማረ ጌታን እየመሰለ ይመጣል:: እርሱን የምንመስለው እንዴት ነው? በፍቅራችን፤ በትህትና፤ በርኅራኄና በመንፈሳዊ ፍሬዎች ሁሉ በማሸብርቅ ነው:: እነዚህን የሚቃወም የዓለምም ህግ የለም:: እግዚአብሔር ትልቅ ነው!!
ሉቃስ 6: 41-42
41 “በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?
ሌሎችን መርዳትን አይደለም ጌታ እየተቃወመ ያለው ነገር ግን እራስህንም መርምር በሌላው ከምታየው የበለጠ በአንተ እንዳይገኝ ነው:: ዳዊት አንዲት በግ የነበረችው ታረደችበት የሚለውን ታሪክ ሲሰማ ቡራ ከረዮ አለ እርሱ መሆኑን ባለማወቁ:: ማለት የነበረበት:- እኔም ወድቄያለሁና ንስሃ ልግባና ከዚህ ሰው ጋር ከዛ በኃላ እነጋገራለሁ ማለት ነበረበት:: ያችም ስታመነዝር የተገኘች ሴት ከሳሾችዋ በሙሉ ባለ ምሰሶ ሆነው ተገኙ:: እራሳችንን ብንመረምር ባልተፈረደብን ነበር:: ሌሎችን እዮ የተባልነው በክርስቶስ ውስጥ ነውና እያንዳንዱን ቅዱሳን ስንመለከት ክርስቶስን እንይና ከእኛ እንደሚበልጡ እንረዳ ድሮስ እንዴት ከእየሱስ እንወዳደር? ትህትናን ለብሰን በእውነት ገብቶን እንመላለስ::
ሉቃስ 6: 43-45
43 “ክፉ ፍሬ የሚያደርግ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያደርግ ክፉ ዛፍ የለም።
ዛፍ ስም የሚወጣለት በፍሬው ነው:: የብርትኳን ዛፍ ወይም የማንጎ ዛፍ ያስባለው ከሚያፈራው ፍሬ የተነሳ ነው:: እንግዲህ እናስተውል አፍሩ የተባልነው የመንፈስ ፍሬ ነው:: ሐዋርያቱ ምንም ያልተማሩ ነበሩና ከእየሱስ ጋር እንደነበሩ አወቋቸው:: ውሎ አዳራችን ከእየሱስ ጋር ከሆነ እየሱስን እንመስላለን:: የህይወት ቃል አለህ ወዴት እንሄዳለን ብለዋልና:: ይህ ቃል መንፈስ ነው እውነትም ነውና መልካም መሬት ሆነን እንቀበለው እርሱም ያፈራል::
በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል። የተሞላነው ምንድነው? ቃሉን? ዕለት ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ ተባልን አለዚያ ዓለም ክፍተቱን ተጠቅማ መራራውን እውቀት ትሞላናለችና:: ክርስቶስን ወደ መምሰል አንመጣም:: ቃሉን ስናሰላስል እንዋል እርሱ ነው በአእምሯችን መታደስ የሚለውጠን:: የእግዚአብሔር እርሻ ነንና ልባችን በቃሉ ይሞላና የምንናገረው ቃል ሰውን የሚያንጽ የጥበብ ቃል ይሁን:: ቃሉ በሙላት ይኑርባችሁ ተብለናልና ለቃሉ ጊዜና ክብር ይኑረን!
ሉቃስ 6: 46-49
46 “ስለ ምን፦ ‘ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥’ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም?
ጥያቄውን መመለስ የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው:: ለምን በአፋችን ብቻ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ማለት እንዳይሆንብን ህይወታችንን በቃሉ ላይ መስርተን እንኑርበት:: ጌታ ሶስት ነገሮችን እየነገረን ነው:-
1. ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ – እራስን መካድ: ማስገዛትና ጌታን መከተል
2. ቃሌንም የሚሰማ – ደቀ መዝሙር መሆን
3. የሚያደርገው፥ – መታዘዝ
በዚህ መልኩ የሚከተል ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ ብሎ:- ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። እምነታችንን የሚፈትን መከራ መምጣቱ አይቀርም ያኔ እንጸናለን ወይንስ ትተን እንሄዳለን?
ይህንን ያላደረገው ደግሞ ያለ መሰረት (እናስምርበት) ቤቱን የሰራ ነው አይጸናም:: ክርስትና ክርስቶስን መምሰል እንጂ በአፍ ብቻ መከተል አይደለም በቃሉ ላይ እንደግ እንመስረትበትም::
ከ12 አንዱ ሲክደው ምንም ምልክትን አላሳየም ሌሎቹ አላወቁበትም ጌታ እንጂ:: እነሱኑ ነበር የሚመስለው ጠላት አሳብ አስገባበት እርሱም አስተናገደው:: ከውጪ ጥሩ ክርስትያን መምሰልና ሰውን ማታለል ይቻላል በጌታ ፊት ግን ሁሉ የተራቆተ ነው:: በመጨረሻው ጌታ ጌታ ሆይ ሲሉት አላውቃቸውም ከሚባሉት ውስጥ በስምህ አጋንንት አላወጣንም እንደዛና እንደዚህ አላደረግንም የሚሉ አሉበት:: እራሳችንን በቃሉ ብርሃን እንመርምር አገልግለን የተጣልን እንዳንሆን::
ሉቃስ 7: 1-7
7 ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል።
ቃል የገባው ይህንን ይላል! ጌታ እየሱስን ስለቃል በደንብ አድርጎ ሰበከው:: ይህ ሰው የተመሰከረለት ጥሩ ሰው ነው ህዝቡን የሚወድና ምኩራብም የሚሰራ በኢየሱስ ፊት ግን ለመቆም ወይም ወደ ቤቱ እንዲገባ እራሱን የተገባው አድርጎ አልቆጠረምና መልክተኞችን ላከ:: መሲሁን ከሚጠባበቁት ይልቅ ይህ ምንም የማያውቅ አህዛብ ጌታን በግርማው ተቀበለው::
ዛሬም የሚያስፈልገን ይህ ህያው ቃል ነው ለቃሉ ክብር ይኑረን:: ቃሉ በከበረበት ጌታም ይገኛል::
ሉቃስ 7: 8-10
9 ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ፦ “እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም፡” አላቸው። 10 የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ባሪያውን ባለ ጤና ሆኖ አገኙት።
ይህ ሰው መልካም እንደሆነ መስክረውለታል ከስራውም ማየት ይቻላል ለልጁ አይደለም እንደዚህ የተጋው:: ኢየሱስንና በአካባቢው ላሉት ሁሉ የባለስልጣን ቃል ምን ማለት እንደሆነ ሰበካቸው:: ይህንን ሁሉ የሚመላለሰው በመልክተኛ ነው ፊቱ ለመቆምማ አልደፈረም:: የጌታ ቃል ስልጣኑ ይግባን!! ሁሉን ወደመኖር ያመጣው በቃሉ ነው:: አሁንም የምንኖርባትን ትልቁን ዓለም ያጸናት ጥሩ በሆነ መሰረት ላይ መስርቶ ሳይሆን በቃሉ ነው ደግፎ የያዘው! ሃሌሉያ!
እስራኤሎች ይህንን ቢሉ አይደንቅም ብዙ የአምላካቸው አሻራ አለና በዙሪያቸው:: ሙት ከሆነው አብረሃም የተገኙ: ቀይባህርና ዮርዳኖስ የተከፈለላቸው: እያሪኮ በመዞር ብቻ የፈረሰላቸው: ያልገነቡትን ከተማ የወረሱ: ብዙ ነገስታትን ድል የነሱ ብዙ ብዙ መጥቀስ ይቻላል:: እነሱ ተለማምደውታልና ብዙም አልታያቸው:: እኛስ እንዳንለምደውና ታላቅነቱ እንዳይደበዝዝብን!
ጌታ ኢየሱስም ተገርሞበት እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አለ:: ምን አይነት እምነት? ትልቅ! ጌታ እየሱስ ምንም አላለም ነገር ግን መልክተኞቹ ሲመለሉ ባርያውን ድኖ አገኙት!!!! ሃሌሉያ ክብር ይሁንለት!! ጆሮ ያለው ይስማ!! ቃሉ ህያው ነው በሁለት በኩልም የተሳለ ነው!! ይሰራል ሳይሰራም አይመለስም! ቃል! ቃል! ቃል!
ሉቃስ 7: 11-15
13 ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና፦ “አታልቅሽ፡” አላት። 14 ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፥ የተሸከሙትም ቆሙ፤ አለውም፦ “አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ።” 15 የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፥ ለእናቱም ሰጣት።
ናይን ወደምትባለው ከተማ በአጋጣሚ አልመጣም ቀኑን የትና እንዴት እንደሚውል የሚያውቅ ጌታ:: ቀጥታ እርሰዋን ሊረዳት መጣ ስለታሪክዋ የነገረው የለም ግን አያትና አዘነላት አንድ ልጅዋን አታለችና::
ጸሎትን ከጌታ እንማር እርሱ ነገሮችን ያዛል :: ከየት እንዳመጣነው የማይገባኝ ድምፃችንን ሁሉ ለውጠን የለቅሶ ዘይቤ አስይዘን እንጸልያለን ወይም ደግሞ እርሱ መረጃ የጎደለው ይመስል እንወተውታለን:: ማንም ምንም ሳይነግረው አውቆ አዘነላትና ልጅዋን በሰውኛ ሬሳ የሆነውን እርሱ ግን አናገረው አንተ ጎበዝ ብሎ ጠርቶ ተነሳ አለው እርሱም ተነስቶ ተቀመጠ ለእናቱም ሁለተኛ ሰጣት ድሮውንስ ልጅ የሚሰጥ እርሱ አይደለምን?! በአላዛርም ይህንኑ ነው ያደረገው::
የሞተም ይሰማዋል! እኛም ስንጸልይ ጉዳዮን አድሬስ እናድርግ እንጂ አንዘብዝብ:: ስትጸልዮ እንደአህዛብ አትሁኑ ተብለናል:: እግዚአብሔር መንፈስ ነው! እንወቀው ሰምቶ የሚመልስ ነው የለመነውን እንደተቀበልን ብንቆጥር ለእኛ ይሆናል:: የጌታን የሚያዝን ልብ ይስጠን ሌሎች ሲያዝኑ አብሮ የሚያዝንና የሚጸልይ ማንነትን ያብዛልን::
ሉቃስ 7: 16-17
16 ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸውና፦ “ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል፥” ደግሞ፦ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐበኘ፡” እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። 17 ይህም ዝና ስለ እርሱ በይሁዳ ሁሉ በዙሪያውም ባለች አገር ሁሉ ወጣ።
ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸው ይላል ቃሉ:: ለምን?! እንደዚህ አይነት ነብይ በህይወት ዘመናቸው ያላዮና የነብያትን አገልግሎት በዝና እንጂ በተግባር ያላዮ ትውልድ ናቸው: ይህንን ያደረጉት ነብያት እነኤልያስና ኤልሳዕ ነበሩ:: ኢየሱስ ግን ከነብያትም የሚበልጥ የእግዚአብሔር ልጅ የሚጠብቁት መሲህ መሆኑን አልተረዱም:: መሲሑ ሲመጣ የሚያደርገውን ተአምራት እያደረገ ነውና:: እነርሱ ግን ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል፥” ደግሞ፦ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐበኘ፡” አሉ:: ይህንን ያሉት ከሮም አገዛዝ ያወጣናል ብለው ነበረ እንጂ የእግዚአብሔር እቅድ ዓለምን ሁሉ ለማዳንና የሰይጣንን መንግስት ለመጣል እንደሆነ በጥልቀቱ አልተረዱትም::
ተአምራት ሲደረግ የጌታ ስም ይገናል ዝናውም ይወጣል ብዙዎችንም ወደ እግዚአብሔር መንግስት ያመጣል:: እነዚህ ጸጋዎች በቤተክርስቲያን እንዲገለጡ እንጸልይ:: ብዙዎች እያነከሱ በቤቱ እየተመላለሱ ነው ያሉት:: የዚህች ሴት መጎብኘት ደስ አይልም? አንድ ልጅዋን መልሶ ሰጣት! አሜን! ይህንን ክብሩን ያሳየን::
ሉቃስ 7: 18-20
20 ሰዎቹም ወደ እርሱ መጥተው፦ “መጥምቁ ዮሐንስ፦ ‘የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ?’ ብሎ ወደ አንተ ላከን፡” አሉት።
ይህንን ጥያቄ ከመጥምቁ ዮሃንስ መስማት ያስገርማል:: ምክንያቱም ሲያጠምቀው መንፈስ ቅዱስ በእርግብ መልክ መጥቶ ሲቀመጥበት በአይኖቹ አይቶ እንደዚሁም ከአብ ዘንድ ድምጽን ሰምቶ ነበረና ነው:: በእርግጠኝነትም ይህ የእግዚአብሔር በግ እያለም አውጆለት ሲያበቃ ይህንን መጠየቁ ነው ያስገረመኝ::
አንዳንዴ ግራ ሲገባኝ እነዮሃንስም ያንን ሁሉ ምልክት ተሰቷቸው ጥያቄ ጠይቀዋል ብዬ እጽናናለሁ:: ስለዚህ እኛ ብቻ አይደለንም ግራ የሚገባን ከሴቶች ሁሉ ከተወለዱት ይበልጣል የተባለውም ወሳኙ ነብይ ጠይቋል:: ደስ የሚለው ጌታ አይታዘበን ወይንም አይቆጣን በነገር ሁሉ የተፈተነው ካህን ይረዳናል:: በድካማችን ኃይሉ ይገለጣል ደግሞም ጸጋን ይሰጠናል:: አሜን!! ሃሌሉያ!
ሉቃስ 7: 21-23
ዮሃንስ ለላከው ጥያቄ በቃል ወይም በንግግር አልመለሰም ያላቸው ያያችሁትን የሰማችሁትንም አውሩለት ነበረ:: ወንጌል የሚታይና የሚሰማ ነው:: በኢሳያስም መጽሐፍ በትንቢት እንደተነገረው:-
ዕውሮች ያያሉ፥
አንካሶችም ይሄዳሉ፥
ለምጻሞችም ይነጻሉ፥
ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፥
ሙታንም ይነሣሉ፥
ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤
ይህ መሲሁ ሲመጣ የሚሰራው ነውና ስራው እየተሰራ ነው:: ዮሃንስን የገረመው ለምን እስከአሁን ቆየህ ነፃ አውጣን ነበረ:: ለምን በእስር ቤትስ እቆያለሁ ቶሎ መንግስትህን መስርት ነው ጥያቄው:: ኢየሱስ የመጣው የሰማይን መንግስት ለመመስረት ነው:: የሐዋርያቱም ጥያቄ ሊያርግ ሲል ይኸው ነበረ::
ስለዚህ ብዙዎች በዚህ ይሰናከላሉ ምክንያቱም የሚፈልጉት የእስራኤልን መንግስት እንጂ የማይታየውን የእግዚአብሔርን መንግስት አይደለም:: ንጉስ አንግስልን አሉት በሳሙኤልም ዘመን ጌታም እኔን ነው የናቁት አለ:: እነርሱ የፈለጉት እንደ አህዛብ ያለ በፊታችን የሚሄድ ንጉስ ነበረ:: እግዚአብሔር ግን በቀን በደመና በለሊትም በእሳት አምድ እየመራቸው ነበረ:: ንጉሳችን እግዚአብሔር ነው!
ዛሬም ኢየሱስ በእኛ ውስጥ እየኖረ ስለሆነ እነዚህ ተአምራት ይቀጥላሉ:: ኃይሉን እንጠማ!!!
ሉቃስ 7: 24-28
ዮሃንስ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል እንደሚበልጥ ጌታ መሰከረ ምክንያቱም ሌሎቹ ነብያት ይመጣል ብለው አንዳንዶችንም ከሩቅ ተሳለሙት ሲል ዮሃንስ ግን ይኸው ብሎ ማወጅና ይመጣል የተባለውን መሲህ ማየት ሆነለት::
የብሉይ ኪዳን አገልጋይ ሆኖ ሳለ ኢየሱስን ማየት ብቻም ሳይሆን ስለእርሱ ሲመሰከር በጆሮው የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰማ መንፈስ ቅዱስም ሲወርድ አየ! ዮሃንስ ማለት በመልአክ መልክት ይመጣል ተብሎ የመጣ ፥ በበረሃ የኖረ ፥ ከሰው የማይነካካ የሚበላውና የሚለብሰው ሁሉ የተለየ ፥ እራሱን ሙሉ በሙሉ ለተላከለት አገልግሎት የሰጠ ነው:: ይህ ሁሉ ቢሆንም ቅሉ በክርስቶስ የጸደቀ ግን ይበልጠዋል:: ምክንያቱም እርሱን ለብሰን፥ በደሙ ታጥበን ፥ እርሱን በልባችን ሾመን ፥ በእርሱ ተሞልተናልና ነው:: አሜን! መዳናችን እጅግ ክቡር ነውና ይህንን ሁሉ ሳናደርግ ድነናልና ይህንን ህይወት አንለማመደው በየዓለቱ እንደነቅ!
ሉቃስ 7: 29-30
ዮሃንስ የጌታን መንገድ ሊያቀና ከፊቱ የተላከ ነበረ:: ህዝቡን ወደ ንስሃ የሚያመጣ ከፍ ያለውን የትቢት ልብ ዝቅ የሚያደርግ አልበቃም ብሎም ዝቅ ያለውን ከፍ አድርጎ ልብን ሁሉ አደላድሎ የሚጠብቅ ነብይ:: ነገር ግን ህዝቡ ሁሉ ቀራጮች እንኳን ሳይቀሩ መተው ተጠምቀው ሲጠብቁት አውቀናል የሚሉት ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ አልተጠመቁምና የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው ጣሉ። እንዴት ከባድ ንግግር ነው? ! የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው መጣል? የጌታ ምክር በይወታችን ይጽና! እግዚአብሔር ፈቃድ አለው ምንድነው ፈቃዱ በህይወታችን? እርሱን እንወቅና ፈቃዱን እንፈጽም እንጂ ሞኞች አንሁን::
ይህ ሰው ተራ ሰው እንዳልሆነ ያውቃሉ ብዙም ጊዜ አንተ እርሱ ነህን ብለው ጠይቀውታል እርሱም እኔ እርሱ አይደለሁም መንገድን የማዘጋጅ ነኝ ብሏል ልብ አላሉምና አለፋቸው:: ጌታም ሲመጣ አልተዘጋጁምና አልተጠቀሙበትም:: ጥምቀት በብሉይ ኪዳን አይታወቅም ግን ዮሃንስ አጠመቀ በኤልያስም መንፈስ ተገለጦ እንደ ትንቢቱ አገለገለ::
ሉቃስ 7: 31-35
32 በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ እንዲህ ይላሉ፦ ‘እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም’።
ይህንን ምሳሌ ሲናገር ጌታ የመጥምቁን የዮሐንስና የራሱን አገልግሎት ለማለት ነው:- ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም’። ዮሃንስ ንስሃ ግቡ እናንተ የእፉኝት ልጆች ይላቸው ነበረ:: አኗኗሩ ሁሉ የተለየ ሲሆንባቸው ጋኔን አለበት አሉት::
በሌላ አንፃር እግዚአብሔር ጌታ የሱስን ላከ የምስራቹን ይዞ መጣ:- እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም:: የተገፉትንና የተጣሉትን ሁሉ ወደ መንግስቱ የሚያስገባ የኃጥያተኞች ወዳጅ የሆነ የእግዚአብሔር በግ:: ለእርሱም ምላሽ አልሰጡምና፤ እግዚአብሔር በምንም አይወቀስም:: ጥበብም ለልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች አላቸው:: ጥበብ በብዙ ተጣርታለች ምክሩን ያልጣሉት ግን የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነውን እየሱስን አወቁ:: እኛም አወቅን! ተመስገን ጌታ ሆይ!
ሉቃስ 7: 36-39
36 ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ።
ልመናን የማያልፍ ጌታ በዚህ ፈሪሳዊ ቤት ለመስተናገድ መጣ:: ይህ ሰው የጋበዘው ነብይ መስሎት ነው ምክንያቱም ነብይ ቢሆን ኖሮ ይህችን ሴት ባወቃት ነበር አለ:: ከነብይነትም አወረደው:: እርሱ ግን በቤቱ ጋብዞ በሰው ላይ ይፈርዳል የሚገርመው ነገርና ያላወቀው ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ በቤቱ ተቀምጦ ነበር:: ዛሬስ እኛ እንዴት ነን በጉባኤ መካከል በእህት ወንድሞቻችን መካከል ከፍቅርና እርስ በእርስ ከመቀባበል ባለፈ የፍርድ ልብ እንዳንይዝ እናስወግድ ወይም ስህተትን ካየን እንጸልይላቸው:
እርስዋ ግን ሰውየው ያሰበውን ሳታውቅ በቤቱ ገብታ ሳትጋበዝ ይሉኝታም ሳይዛት አገልግሎትዋን ቀጠለች አካሉን ለቀብር ማዘጋጀት ይህንን ወግ ጌታ አያገኝምና::
ያደረገችውም:-
– ሽቱ አምጥታ
– በእግሩ አጠገብ በመሆን እራስዋን ዝቅ አድርጋ:
– ከፍቅርዋ የተነሳ እያለቀሰች
– በእንባዋ እግሩን እያራሰች
– በራስ ጠጕርዋም እያበሰች እራስዋን አዋርዳ
– እግሩንም በመሳም ፍቅርዋን እየገለጠች
– ሽቱ ቀባችው::
አገልግሎታችን ምንድነው? ማንም አይሰራልንምና ተነስተን እናገልግል የጌታ ውለታ የበዛብን ነን!
ሉቃስ 7: 40-50
47 ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።”
ይሉኝታ ሳይዛት ሰው ሁሉ ለመብላት ተሰብስቦ ባለበት እርስዋ ግን አሳብዋንም ዓይንማንም በጌታ ላይ አድርጋ ለማምለክ ተገኝታለች:: አካባቢውን ሁሉ በዚህ ውድ ሽቶ አውዳ አመለከችው::
ስምዖን ግን ጌታን በልቡ እያማ ነው ማንነትዋን ነብይ ቢሆን ኖሮ ያውቅ ነበረ እያለ ባለበት ጌታ የልቡን አሳብ አውቆ መመለስ ጀመረ:: ለምን እንደዚህ እየሆነች እንዳለች ገለጸለት:: እርሱ ምንም አላደረገለትም እርስዋ ግን ብዙ ተትቶላታልና ብዙ ወደደች ፍቅርዋንም በተግባር ገለጸች:: እርስዋንም፦ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል፡” ብሎ ገበናዋን ሳይገልጥ ይቅር አለላት:: በነገር ሁሉ የተፈተነና ምንም ኃጥያት ያልተገኘበት ሊቀ ካህን ዛሬም ይራራል ይቅርም ይላል::ስምዓን ቤት ስትገባ ስብር ብላ እንደነበረችው አይደለም ስትወጣ ቀና ብላ ወጣች እዳዋ ሁሉ ተከፍሎ::
እኛንም ቀና ያደረገን አባ አባ እንድንል ያደረገን በከበረ ደሙ አንጽቶናን ለመንግስቱ ዋጅቶ ነውና ስሙ ይባረክ! የሚያጸድቅ እርሱ የሚኮንን ማነው?!
ሉቃስ 8: 1-3
1 ከዚህም በኋላ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር፤
በብዙ መንገድ እግዚአብሔር ተናግሮ ነበረ አሁን ግን ልጁ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ ዞረ:: አሜን!! የሚናገረው የምስራች ነው! ምንድነው ይህ የምስራች?! እውቀት ደብቀኸናልና የእባቡ ምክር ይሻላል አንፈልግህም ብላችሁ ጥላችሁት ወደ መከራ ከገባችሁበት የምርጫሁ መከራና ጨለማ ሊያወጣችሁና ሊታረቃችሁ ፈጣሪያችሁ መጥቷል ይመስለኛል በቀላል ቋንቋ:: ዛሬም ዝናው በምድር ነገዶች ሁሉ ዘንድ ይሰማል::
ጌታ ሲወለድ መልአኩ ለእረኞቹ ያላቸው ታላቅ የምስራች እነግራችኋለሁ ነበረ:: ዛሬም ይህ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የምስራች ይሰበካል!! የምስራች አለን! የእግዚአብሔር በግ ተገልጧል እንታረቅም ይላል ብለን የምንሰብክ አምባሳደሮች ነን!!
በዚያ ዘመን የነበሩ አገልጋዮች ሴቶችን ከእቁብ አያስገቡም ነበር ጌታ ግን ሁሉ ያለው የሁሉ ፈጣሪ በገንዘባቸውም እንዲያገለግሉት ፈቀደ እንዲሁም ከ12 ጋር አብረው ነበሩ:: “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፡” ያላት ብዙ ወዳለች የተባለችው የሽቶዋ ባለቤት መቅደላዊት ማርያምም አንድዋ አገልጋይ ነበረች:: በገላትያ 3:28 አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። አሜን አንድ ነን በሁሉም ጌታ ይጠቀማል! እናገልግለው!
ሉቃስ 8: 4-15
10 እርሱም እንዲህ አለ፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው።” 11 “ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው።
ጌታ በዚህ ስፍራ ላይ ስለዘሪው ሲያስተምርና ፍቺውንም ለሐዋርያቱ ሲነግራቸው እናያለን:: ዘሩ ቃሉ ነው የሚዘራውም በተለያየ አይነት ልብ ላይ ነው:: የሰውን የልብ አይነት ማወቅ ለእኛ አልተሰጠንም የተሰጠን መዝራት ነውና እንዝራ:: የሚያበቅል መንፈስ ቅዱስ ነው! ተስፋ ሳንቆርጥ ሳንሰለች እንዝራ! ሰይጣንም ይልቀመው: በፈተና የሚከዱም ይሁኑ: በዓለም ነገር የተጠላለፉም ይሁኑ መቶ እጥፍም የሚያፈሩ ይሁኑ እኛ ልባቸውን ስለማናውቅ አምነን እየጸለይን እንዝራ::
የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ስለተሰጠን እንጂ እኛም ይህንን ሚስጥር ማወቅ አንችልም ነበረ::
ሉቃስ 8:16 “መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ።
በህይወታችን ላይ የነበረውን ጨለማ ገፎ በብርሃኑ ሞላው :: በዓለም ስንመላለስ የዓለም ብርሃን የተባልነውም ለዚሁ ነውና ይህንን ጨለማ ዓለም ሳንሸማቀቅ እናብራው:: ባይመስለንም እንኳን የሰው ልጅ ክርስቶስን ካላወቀ እርዳታ የሚያስፈልገው ምስኪን የሚጠፋ ፍጥረት እንደሆነ አውቀን በብርሃኑ ወደ ብርሃን እንምራው:: እንጂ ብርሃናችንን ደብቀን አብረን በጨለማ አንመላለስ:: ክፉን በክፉ አንመልስ: የሚጠሉንን እንውደድ: ለሚያሳድዱን እንጸልይ እና ሌላም ሌላም በውስጣችን የበራው ብርሃን ህይወትን በዓለም ቀመር እንዳንኖረው ግድ ይለናልና አዲሱ ሰው ክርስቶስ ህይወቱን በእኛ ይኑር:: አሜን!
ሉቃስ 8: 17-18
18 እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
ተሰውሮ የሚቀር ነገር የለም ሁሉ በግልጥ ይታያል አንድ ቀን ስለዚህ ማንም አገልግሎ የተጣለ እንዳይሆን ይጠንቀቅ!
መስማት ለሰው አቅጣጫን የሚያስይዝ ነውና እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ እየተባልን ነው:: ጌታም ጆሮ ያለው ይስማ ይላል ደጋግሞ:: በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ ተብለናልና ልባችንን መልካም መሬት አድርገን እንስማ! ከላይም እንዳለው ቃል የሰው ልብ የተለያየ ነው ቃሉን ሲሰማ መልካም መሬት ላይ ካላረፈ ቃሉ አያፈራም:: ለዚህም ነው በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህንን ዓለም አትምሰሉ የተባልነው መለወጥና መታደስ የሚመጣው በቃሉ ነው:: አለበለዚያ አለን ብለን የምናስበውም ይወሰዳል:: ለጊዜው ተቀብያለብ ብለን ብናስብም:: የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ይህንኑ ብላ ነበረ ጌታ ግን በራእይ 3:17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም፡ የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ ልተፋህ ነው ይላቸዋል::
ጌታ አስተውሎ መስማትን ይስጠን!
ሉቃስ 8: 19-21
21 እርሱም መልሶ፦ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው፡” አላቸው።
ይህንን ማለቱ መቼም ቤተሰቡን መናቁ ወይም ችላ ማለቱ አይደለም:: ከላይ ጀምሮ ሲያስተምር የነበረውን ቃሌን በማስተዋል ስሙ ኑሩትን በቤተሰብ ምሳሌ አጠናቀቀው:: የእግዚአብሔር ቤተሰብ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ገለጸልን ይኸውም ቃሉን መስማትና ማድረግን እንደሚጠይቅ አሳወቀን:: ቃሌ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚወደኝ እርሱ ነው ይልና ወደ እኛ እንደሚመጣና መኖርያም እንደሚያደርግ ይገልፃል እንዲሁም ጸሎታችን እንደሚሰማ ይናገር የለም በሌላ ስፍራም? ቃሉን ሰምተን ስንኖርበት እናተርፋለን!
ቃሉ በልባችን እርሻ ተዘርቶ ይብቀልና ይውረሰን:: ቃሉን እንዴት እንደምንሰማም እንጠንቀቅ በአውቃለሁ ሳይሆን ሁልጊዜ በትህትና ሊሆን ይገባል:: በቃሉ ይሰራናል ስንኖረውም የማን ወዳጅና ቤተሰብ እንደሆንን ያሳውቃል:: ጌታ ይርዳን ላይ ላዮን ሳይሆን ጠለቅ ብለን እንድንመላለስና ልጁን እንድንመስለው:: አሜን!
ሉቃስ 8: 22-25
25 እርሱም፦ “እምነታችሁ የት ነው?” አላቸው። ፈርተውም ተደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም፦ “እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ የሚያዝ ለእርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” አሉ።
እንሻገር ብሏቸው መንገድ ጀምረው ሳይጨርሱ ማዕበል መንገዳቸውን ያዘውና ያስጨንቃቸው ጀመር:: እነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ በውሃ ላይ ልምድ ያላቸው ናቸው ታድያ ለምን እንደዚህ ደነገጡ ያልን እንደሆነ ምክንያቱ ይህ ዓውሎ ንፋስ አጥፊ እንደሆነና መውጫም የሌለው ገዳይ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው:: ከልምዳቸው ይልቅ አጠገባቸው ያለውን ጌታ ቢያዮ ይሻል ነበር::
ለሊቱን ሲጸልይ የሚያድረው ጌታ ቢተኛ አይደንቅም ጀልባዋ በውሃ እየተሞላች እርሱም በውሃው ውስጥ እንቅልፉን ቀጠለ:: ጠፋን ብለው ሲቀሰቅሱት እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ተዉም፥ ጸጥታም ሆነ። ፍጹም አምላክ ፍጥረትን ሁሉ የሚያዝ ፍጹም ሰው ደክሞት የሚተኛ ነበረና::
ከዚህ በኃላ እምነታችሁ የት ነው? ብሎ ጠየቃቸው በማዕበሉ ላይ ወይንስ በእኔ ላይ ነው? ነው ጥያቄው:: ዛሬ የት ነው እምነታችን ጌታ ያሻግራል! ሲቀሰቅሱትም ተነሳና ረዳቸው እኛም ዛሬ ስንጠራው በዙፋኑ ያለ የሚሰማ ሊቀ ካህናት አለን:: የገረመኝ ማዕበሉን ፈርተው ቀሰቀቁሱት ገስጾ ጸጥ ሲያደርገውም ፈርተውም ተደነቁ ይላል:: ደግሞም ይህ ማነው? አስባላቸው ይሄኛው ፍርሃታቸው ለየት ያለ ነው በጀልባ አብሯቸው የሚጏዘውን ገና በደንብ አላወቁትም ነበር:: እርሱ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ መሲህ ነው! የተከተልነውማ ጌታ የጌቶችም ጌታ ነው:: አሜን!
በእየሱስ ስም ያቆመን ማዕበል ሁሉ ከፊታችን ጸጥ ይበል! ጸሎታችንንም የምንቀበልበት ቀን ይሁን! ዓይናችንም በእርሱ ላይ ይጽና ሁሉን ጸጥ ያደርግና በሰላም ያሻግረናልና! ሃሌሉያ!!!
ሉቃስ 8:26-35
35 የሆነውን ነገር ሊያዩ ወጥተውም ወደ ኢየሱስ መጡ፥ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ።
ይህንን ሰው ሊረዳው የመጣለት እየሱስ ብቻ ነው:: ሰዎች የሚችሉትን ረዱት ይኸውም በብረት አስሮ ማስቀመጥ ነው እንጂ ከዛ ያለፈ አልቻሉም:: እየሱስ የመጣበት አንዱ አላማ የተጠቁትን ነፃ ማውጣት ነበረና በማዕበል ሊቋቋመው ቢነሳም እንኳን አላቆመውም:: አልፎ መጥቶ ነፃ አወጣው:: አጋንንቱ የሚወስደው ወደ መቃብር ስፍራ ነው ከሙታን መካከል እራቁቱን ሊያኖረው:: አዳምና ሄዋን በኃጥያት ሲወድቁ እራቁታቸውን መሆናችውን አወቁ እንደዛ ሊያዋርዳቸው ነበረ ተሳካለት:: እየሱስ መቶ ታደገንና ወደ ክብራችን መለሰን::
ጠላት ሞትን እንጂ ህይወትን አይሰጥም ህይወትን የሚሰጠው እየሱስ ነው:: ህይወት እንዲበዛልን መጣ! ዛሬም ስሙ ከስም ሁሉ በላይ ነው! ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ትናንትናም ዛሬም እስከዘላለም ድረስ ያው ነው:: ሰውን ለመርዳት እንደእየሱስ ግድ ይበለን:: እርዳታ የሚያስፈልገውን ሰው ሁሉ ወደ እርሱ እናምጣ:: ዛሬም ነፃ ያወጣል ይረዳልና! አምላካችን በስራ ላይነው! አሜን!
ሉቃስ 8: 36-39
39 “ወደ ቤትህ ተመለስ፥ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረግልህ ንገር፡” ብሎ አሰናበተው። ኢየሱስም እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት በከተማው ሁሉ እየሰበከ ሄደ።
ይህ ሰው የሚታወቀው ታላቅ ነገር የተደረገለት ተብሎ ነው:: ይህ ሰውከእየሱስ ጋር መኖር ፈልጎ ነበር ምናልባትም እነዚያ አስጨናቂ መናፍስት ይመለሳሉ ብሎ ይሁን ወይንም ውለታው በዝቶብኛል ብሎ ይሆናል ጌታ ግን አልፈቀደም:: የእግዚአብሔር አሰራር ግን ለየት ስለሚል ወደ ቤትህ ሂድ አለው:: የከተማው ሰው ሁሉ ወተው ሂድልን ብለው ለመኑት ጸሎታቸውንም ሰማና ሄደላቸው:: ነገር ግን ወንጌላዊ ወደ ከተማቸው ማስገባቱን አላወቁም:: ሰውየውም በከተማው ሁሉ እየሰበከ ሄደ ይላል:: ይህንን ሰው ለመርዳት ተሻግሮ የመጣውጌታ ፍሬ እፍርቶ ተመለሰ የከሰረ ቢመስልም ሂድልን ሲሉት:: በመንፈስ ግን የተሰራ ስራ አለ:: ሂድልን ሲሉት ሰውየውንም ይዞባቸው በሄደ ነበር ስለሚወዳቸው ግን እሱን ሰጣቸው በእርሱ ተጠቅሞ ይረዳቸዋልና::
ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች አህዛብ ናቸው ተብሎ ቢታሰብም የሰማርያ ህዝብ ያችን ሴት ሰምተው ከእነርሱ ጋር እንዲቆይ ለመኑትና ከተማው ሁሉ ተከተለው በተቃራኒው:: የዛሬ ምኞቴ ለአገራችንም ይኸው ነው እርሱን መከተልና መፈለግ ይሁንልን:: የእግዚአብሔር ፍቅር በምድራችን ይስራ!! አሜን!!
ሉቃስ 8:40-42
42 አሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንዲት ሴት ልጅ ነበረችውና፤ እርስዋም ለሞት ቀርባ ነበረች። ሲሄድም ሕዝቡ ያጨናንቁት ነበር።
በአጋንንት የተያዘውን ሰው ነፃ አውጥቶ የከተማውም ሰው ሁሉ ሂድልን ብለውት እየተመለሰ ነበር:: በተቃራኒው በዚህኛው የባህሩ በኩል ደግሞ ብዙ ህዝብ በጉጉት እየጠበቁት ነበር ከነዚህም አንዱ ይህ የምኩራብ አለቃ ነበረ:: እርሱም እየሱስ እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲመጣና የታመመችውን ልጁን እንዲፈውስለት ለመነው:: እርግጠኛ መሆን የሚቻለው በዛ ያለው ሰው ሁሉ ያውቀዋል እንዴት እግሩ ስር ወደቀ? እየሱስን የሚያሳድዱት የእርሱ ቢጤዎች ናቸው ይሄ እንዴት ተለየ?
ቸሩ ጌታ ለምን እንደ መቶ አለቃው አላመንክም ከዚሁ ቃል ብናገር ትድናለች አላለውም ይህችን ብላቴና እቤቱ ሄዶ ለመፈወስ ተስማምቶ መንገድ ጀመረ:: ያለንበት ድረስ መቶ የሚገናኘን ጌታ አይፈርድብንም ጸጋን ሰጥቶ ያቆመናል እርሱ እንደሰው አይደለምና በደረስንበት እምነት እንመላለስ:: የሚረዳንና የሚያዝንልን ሊቀ ካህናት አለን!! ሊቀ ካህኔ እየሱስ እኔን ልትረዳ ስለምትፈጥን ተመስገን!! እንደሰው ስላይደለህ ተመስገን!! ስለምትረዳኝም ተመስገን!!
ሉቃስ 8: 43-48
46 ኢየሱስ ግን፦ “አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና፡” አለ።
ሰው ሁሉ እያጨናነቁትና እያጋፋት ባለበት ውስጥ የዳሰሰኝ ማነው? ሲል ሐዋርያቱም ተገረሙ:: መዳሰሱንና በእምነት መነካቱን የሚያውቅ ጌታ ግን ማነው አለ:: አስራ ሁለት ዓመት የተሰቃየችበትን በቅጽበት ዳሰሳ የተገላገለችው ሴት እየተንቀጠቀጠች ተናዘዘች:: ፈውስዋንም አረጋገጠች:: የምናጋፋ ሳይሆን አስተውለን በእምነት የምንነካ ያድርገን:: ነገርዋን ለማንም ሳትነግር ከልብዋ ጋር ተማክራ በእምነት መጥታ ዳስሳው ፈውስዋን አገኘች:: እምነትን የማያልፍ ጌታ በዛ ሁሉ ፍትግጊያ ውስጥ ዳሰሳን ሰማ:: በፊቱ የምንለምነውን የሚሰማ ተራ ያዙ ቢዚ ነኝ የማይል ጌታ ስሙ ይባረክ!
እርሱም፦ “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፡” አላት። እንዴት ልብ ያረካል ንግግሩ ልጄ ሆይ ብሎ ጠርቶ ፈውሷን በአደባባይ አወጀው! ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትም ሆነ ከእጁ መቀበል አንችልም:: እምነትም የሚመጣው ህያው የሆነውን ቃል በመስማት ነው:: ይህች ሴት ብዙ ስለእየሱስ ሰምታለች ማለት ነው መጥታ የዳሰሰችው:: ባህሉ ባይፈቅድላትም የነካችው እንደሚረክስ ብታውቅም ቅሉ መጣች:: እየሱስ ይቀድሳል እንጂ በምንም አይረክስም!!
ቅዱስ አባት ሆይ የጸሎታችንን ለሆሳስ እንኳን ታዳምጥና ትመልሳለህና ክብር ይሁንልህ!!!
ሉቃስ 8: 49-56
50 ኢየሱስ ግን ሰምቶ፦ “አትፍራ፤ እመን ብቻ ትድንማለች፡” ብሎ መለሰለት።
ልጅህ ሞታለች የሚል መርዶ ለደረሰው አባት አትፍራ!! እመን ብቻ ትድንማለች እንዴት ይባላል? አባትየውማ የመጣው በህይወት እያለች ከመቼው ያንን ባህር ተሻግሮ ተመልሶ ብሎ በጉጉት ጠብቆ ሲያገኘው በእግሩ ወድቆ የለመነው ይህ እንዳይሆን ነበረ:: ነገር ግን የፈራው ደረሰ ጌታም ጊዜውን ወሰደ ሌላም ሴት ለመርዳት ቆየ:: የመጣበትን ሳያደርግ የማይመለስ ጌታ የጉብኝት ጊዜዋ ከዚህ በላይ እንዲቆይ አልፈለገምና አሰባት የደምዋም ምንጭ ደረቀ! ሃሌሉያ!!
አርፋለች ለተባለው መልክት ትድናለች ብሎ ማለት ይገርማል:: ጊዜ በእርሱ ላይ ተጽዕኖ የለውም ከጊዜ ውጪ ይኖራል የእኛ ጌታ:: የዘገየብን የመሰለን ይመጣል ጌታ አይቀርም:: በኢያኢሮስ ቤትም ሲደርሱ ልምድ ያላቸው ነበሩና ይህ የህይወት ንጉስ አልሞተችም ሲላቸው ሳቁበት በኃላ ለማፈር:: አብርሃምም ይህንኑ ሆንዋል ምን ትሰጠኛለህ ያለልጅ እሄዳለሁ አለ ጌታም ሙት ከሆነው ማህጸን ውስጥ ይስሃቅን ሰጥቶ አሳቀው:: ጌታ በስራ ላይ ነው:: ወላጅዎችዋንና ከተወሰኑት ሐዋርያትን ብቻ ይዞ ገባ ክብሩን ለማየት ጥቂቶች ተመረጡ:: ጌታም እጅዋን ይዞ፦ “አንቺ ብላቴና፥ ተነሺ፡” ብሎ ጮኸ።ነፍስዋም ተመለሰች፥ ፈጥናም ቆመች፥ ወላጆችዋም ተገረሙ ይላል:: ከሞት ትነሳለች ብለው ጠብቀው ይሆን?! እንጃ!! ብቻ ግን ልጃቸው ተነሳች! ምስጋና ይድረሰው! የሞተብን፥ የተውነውና የረሳነው ነገር ሁሉ ህይወት ያግኝ! በእየሱስ ስም አሜን!
ሉቃስ 9: 1-6
1 አሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤2 የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው፥
እግዚአብሔር አብርሃምን ሲጠራው የምድር ነገዶችን ሁሉ በአንተ እባርካለሁ ብሎት ነበር:: ከአብርሃም ይስሃቅ ከዛም ያዕቆብ ከእርሱም 12 ነገዶች ወጡ:: ይኸው እዚህ ቃል ላይ እዛው ተስፋ ላይ ሲመለስ እናያለን አሳቡን የማይቀይር ጌታ መልሶ 12ቱን ነገዶች አስነሳና ላካቸው:: ሲልካቸውም በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው:: መንግስት የእርሱ ብቻ ነው የሰይጣን መንግስት መሸነፍና መልቀቅ መፍረስም አለበት:: ይኸው ተስፋ በእኛ ቀጥሏል ሊቀ ካህናችን እየሱስ እየማለደልን በአብ ቀኝ ነውና ዛሬም ድል የእኛ ነው:: እግዚአብሔር ዛሬም በጤና እንድንሆን ፈቃዱ ነው:: በመጀመርያ የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲሰብኩ ላካቸው ይህ ዋናው የተላኩበት አገልግሎታቸው ነው ከዛም ደዌን መፈወስ እኛንም ልኮናል:: አሜን!
ሉቃስ 9: 7-9
7 አንዳንድ ሰዎች፡— “ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፥” 8 ሌሎችም፡— “ኤልያስ ተገለጠ፥” ሌሎችም፡— “ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፡” ይሉ ስለ ነበሩ፡ አመነታ።
ሄሮድስን ግራ ይግባው እንጂ ዝናው እየተሰማ ያለው ዮሃንስ ከሙታን ተነስቶ አይደለም፥ ኤልያስም አይደለም ወይንም ከቀደሙት ነቢያት አንዱም አይደለም! እነርሱን አስቀድሞ የላከ ጌታ እንጂ የጫማውን ጠፍር እንኳን ለመፍታት የማይበቁ መሆናቸውን ያወቁ ባርያዎቹ ናቸው እነዚህ::
እግዚአብሔር ለአዳምና ለሄዋን ገና በኃጥያት ሲወድቁ ቃል የገባውን ለአብርሃምም እንደነገረው የዓለምን ሁሉ ነገዶች ሊታደግ የመጣው እራሱ ፈጣሪ የሆነው ታዳጊው አምላካችን ነው:: የእግዚአብሔር በግ ንጹህ በግ ስለኃጥያታችን ተላልፎ የሚሰጥ በግ ነው እየሱስ! እራሱን ያለስስት በእኔ እግር ገብቶ የተገኘ ወዳጅ! ድንቅና ተአምራትን እያደረገ የተገለጠ ጌታ ሁሉን የፈወሰ የሞቱትን ያስነሳ ዛሬም ያልተቀየረ የሚሰራ ጌታ ነው! አሜን
ሉቃስ 9:10 ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። ከእርሱ ጋርም ወስዶአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ ምድረ በዳ ለብቻው ፈቀቅ አለ።
ጌታ እየሱስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጥቶ ላካቸው:: ከተማሪነት አልፈው ወደ ማገልገል መጡ:: ለማገልገል ሲወጡ ስንቅ ሳይሆን የያዙት ኃይልና ሥልጣን ነበረ የተቀበሉት:: ከአገልግሎትም መልስ የሆነውን ሁሉ ነገሩት:: እርሱ ግን ወደ ምድረ በዳ ይዟቸው ሄደ::
ለምን ወደ ምድረበዳ ወሰዳቸው? አገልግሎቱን አገልግለው የመጡት እርሱ በሰጣቸው ኃይልና ሥልጣን ነው በራሳቸው አይደለምና በፊቱ እርፍ ብለው ኃይላቸው እንዲያድሱና እንደገና በኃይል መውጣት ይሆንላቸው ዘንድ ነው:: አገልግለን የተጣልን እንዳንሆን እራሳችንን በእግሩ ስር ማድረግን እንማር:: እየሱስም ሲጠመቅ አብ ከመሰከረለትና መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ካረፈ በኃላ የሄደው ወደ ምድረበዳ ነው ለብቻው ከአባቱ ጋር ለመቆየት:: እኛም ይህንን ወደ ጸጋ ዙፋኑ መቅረብን ልናዘወትር ይገባል::
ይህንኑ ሐዋርያት ሲተገብሩት እናያለን እኛ ለቃሉና ለጸሎት እንተጋለን ሲሉ እንዲሁም በግልጥነት እንድንናገር ስጠን ሲሉትና በኃይል ሲሞላቸው እናያለን:: እንትጋ!
ሉቃስ 9:11 ሕዝቡም አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፥ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው።
ወደ ምድረበዳ ሐዋርያቱን ለማሳረፍ ይዞ ቢወጣም ህዝቡ ግን ተከተሉት:: መልካሙ ጌታ አልመለሳቸውም እንደልማዱ ስለ መንግስቱ ይነግራቸው ነበረ:: በመጀመርያ ቃሉን ያስተምርና መንግስቱን ይገልጥ ነበር በቃሉ:: ዛሬም መንግስቱን በቃሉ ውስጥ ያስተምራል:: ቃሉን ካስተማረ እምነትም ከቃሉ ከተፈጠረ በኃላ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው። ከእምነታቸው የተነሳ የሰራበት ከእምነትም መጉደል የተነሳ ምንም ማድረግ ያልቻለበት አጋጣሚ አለ::
ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም! እምነት ከመስማት የምንሰማውም የእግዚአብሔርን ቃል ነው:: ከቃሉ ውጪ እምነት ከየትም አይመጣምና! ለቃሉ ጊዜ ይኑረን በእግሮቹ ስር ቁጭ ብለን እንደማርያም እንማር! ቃሉን ላከ ፈወሳቸው ከመከራቸውም አዳናቸው እንደሚል ጌታ ቃሉን ይልካል ካለንበትም ያወጣናል ይፈውሰንማል! አሜን
ሉቃስ 9: 12-17
16 አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛርሙርቱ ሰጠ።
እንደሐዋርያቱ ምክር ቢሆን ስለመሸ ባሰናበታቸው ነበረ:: እርሱ ግን ጥቂቱን ባርኮ አጠገባቸውና ተረፈ! የእኛ ምክር ይኸው ነው የእርሱ ግን ተፈጥሮን ሁሉ ያልፋልና እረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ ያለን ለዚሁ ነው::
ዛሬ እጃችን ላይ ምን አለ? ያለውን እናቅርብለት በትንሽዬዋ አይምሯችን አስበን አውጥተን አውርደን አይሁን:: ያለንን በእምነት ወደ እርሱ ይዘን እንቅረብ አንዳንዴ ከምናልፍበት ነገር የተነሳ አምላካችን ማን እንደሆነ ይጠፋናል መሰለኝ:: እርሱ ሁሉን የፈጠረ ነው፥ በሁሉ ላይ ስልጣን ያለው፥ መንደርደርያና መነሻ አያስፈልገውም የሌለውን እንዳለ አድርጎ የሚጠራ ጌታ ነው! እንታመንበት ከስጋችን ሳንማከር ወደ እርሱ እንቅረብ እርሱም እንደታላቅነቱ መጠን ይሰራል::
ሉቃስ 9: 18-20
20 “እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፡— “ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ፡” አለ።
እየሱስ ጠፍቶት አይደለም ሌሎች ስለእኔ ምን ይላሉ ብሎ የጠየቃቸው ለሚቀጥለው ጥያቄ መንደርደርያ እንዲሆን እንጂ:: ለእናንተ ማን ነኝ?! ዛሬም ይህንን ጥያቄ መመለስ አለብን:: ጴጥሮስም አንተማ ከእግዚአብሔር የተቀባህ መሲህ ነህ አለው::
ለእኔ? የእግዚአብሔር በግ ነህ! ስለዚህ ኩነኔ የለብኝም! በሞትህም ሞቴ ተሻረ – አዳኜና ማምለጫዬ ነህ:: ዕዳዬን የከፈልክ! ቅድስናዬ ጽድቄ የዕዳው ጽህፈት የተሻረልኝ!! የእግዚአብሔር ወገን አደረከኝ! ከቁጣህም አዳንከኝ! ወዳጅ ሆንኩኝ! እየሱስ ጌታዬና አምላኬ ነህ እገዛልሃለሁ!
ሉቃስ 9:21—22 እርሱ ግን፡— “የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊጣል ሊገደልም በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባዋል፡” ብሎ ለማንም ይህን እንዳይናገሩ አስጠንቅቆ አዘዘ።
ማንነቱን ሲጠይቃቸው ከእግዚአብሔር የተቀባህ ብሎ ጴጥሮስ በመንፈስ ተረድቶ መለሰ:: ጌታም ከዚህም የበለጠ ስለእኔ እወቁ ብሎ በእርሱ ላይ የሚሆነውን ገለጸላቸው::
የሚደርስበትን ሲዘረዝር:-
መከራ እንደሚቀበል
በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊጣል – ግንበኞች የጣሉት የማዕዘን ራስ እየሱስ
ሊገደልም – ስለእኛ በደል ሙሉ ዋጋ ሊከፍል
በሦስተኛውም ቀን – የሞትንና የሲዖልን ቁልፍ ተቀብሎና መቃብሩን ፈንቅሎ ሊነሳ!!
ሊከብርና ሊገንን ይገባዋል!! አሜን!
እነሱ የሚፈልጉትና የሚጠብቁት የምድር ንጉስ ከሮም አገዛዝ ነፃ የሚያወጣ እርሱ የሚለው እሞታለሁ:: በመጨረሻ ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል መንግስትን ለእስራኤል መቼ ትመልሳለህ ነበረ ጥያቄያቸው:: መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ እንጂ ይህንን ጥልቅ እውነት የተረዱት ከዛ በፊት ምንም አልገባቸውም::
ዛሬም በመረዳት እንመላለስ የዳነው በስራ ሳይሆን በእርሱ መስዋትነት ነውና የምንመካበትም የለንምና ዝቅ ብለን በትህትና ጌታን እናገልግል ከማንም አንሻልም:: ይህንንም የመዳን እውነት ለፍጥረት እንንገር::
ሉቃስ 9:23 ለሁሉም እንዲህ አላቸው፡— “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።
የሚደርስበትን መከራ ነግሯቸው ሲያበቃ እነሱንም እንደሚጠብቃቸው ነገራቸው:: እነርሱ እያዘኑ ያሉትና ልባቸው የከበደው ስለእርሱ ነበር ለካስ እነርሱም መስቀል መሸከም ይጠብቃቸዋል::
በዘመኑ መስቀል ተሸክሞ መሄድ እንጂ መመለስ የለምና የሚናገረው በዘመኑ የሮም አገዛዝ የሚፈጸም ቅጣት ስለሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል:: የሚሰቀሉበትን መስቀል የመሸከም ግዴታ የሟቹ ነው:: ራስን ካልካዱ በስተቀር ወደዚህ ህይወት ማን ይገባል?! ይህ መሸከም የሚቀጥል ነው በየዕለቱም ነው:: እኛ የራሳችን አይደለንም በዋጋ ተገዝተናል!
ሉቃስ 9:24-27
25 ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?
መስቀል ተሸክማችሁ ተከተሉኝ ያለውን ችላ ማለትና ለዓለም ትርፍ መሮጥም ሆነ በኃጥያት ማግበስበስ በምድር እንዲመቸን ሊያደርግ ይችል ይሆናል ነገር ግን ነፍሳችን የሚያስፈልጋትን አዳኝ ባታውቅ ምን ይጠቅማል?! የተከማቸው ኃብት ከስጋም ሆነ ከነፍስ መሞት አያስጥልም::
ዉደ ነፍሳችን እረኛ ዞር እንድንልና እንድናውቀው የረዳን ጌታ ይባረክ! መዳን ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅብን በቃሉ አለማፈርም ነው:: በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል ይላልና በጌታና በቃሉ እንዳናፍር ጌታ ይርዳን!
አባት ሆይ ዕለት ዕለት መስቀላችንን ተሸክመን እንድንከተልህ እንዲሁም በአንተ ላይ ዓይናችንን እንድናደርግና በሙሉ ልባችን እንድንከተልህ ጸጋህን አብዛልን!
ሉቃስ 9: 28-29
29 ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።
እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ ያለው ጌታ ማንነቱን በመጠኑ ሊያሳያቸው ወደ ተራራ ወሰዳቸው:: ደግሞም ጌታ እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ እንዳለው ክብሩን አሳያቸው::
አብሯቸው ቢበላና ቢጠጣ ቢመላለስም እርሱ ግን የተፈራውና የተከበረው ጌታና አምላካችን ነው:: ስለዚህም ያየነውንና ከገናና ክብሩ የሰማነውን የዳሰስነውን እናወራለን እንመሰክራለን ብለው ጻፉልን:: ሃሌሉያ!
በዚያ ተራራ ላይ እየጸለየ ፊቱ ተለወጠ ይህንንም በሙሴ እናያለን አርባ ቀንና ለሊት ከጌታ ጋር ቆይቶ ሲወርድ ፊትህን ሸፍን እስኪሉት ደረሰ:: የእየሱስ ግን የፊቱ መለወጥ ብቻ ሳይሆን ልብሱም ተብለጨለጨ ወይም አጣቢ ሊያነፃው እስከማይችል የምድር ያልሆነ መዋብ ሆነባቸው:: ይህ ጌታ ዛሬ ከእኛ ጋር ነው የምናጋፋ ሳይሆን ክብሩን የምናይ ያድርገን:: አሜን!!!
ሉቃስ 9: 30-31
30 እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤
ጌታ ክብሩን ሊያሳይ ይዟቸው በወጣበት ሁለት ሰዎች ማለትም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር:: የእነዚህ ሰዎች ተጽዕኖ በእስራኤሎች ላይ ቀላል አይደለም:: ለምን እነዚህ ታዩ? ለምን አዳም፤ ዳዊት ወይም ደግሞ አብርሃም አልታዩም?
በጥቂቱ ለመጥቀስ ሙሴ ህግን ወክሎ ኤልያስ ደግሞ ነብያትን ወክሎ ቆመዋል:: ቃል እንደገባው አምላክ ሰው ሆኖ አዩ:: ይህ ተአምር ነው!!! በሙሴ ዘመን እስራኤላውያን እግዚአብሔር አይናገረን እንሞታለን አሉ:: ዛሬ እንደዛ የተንቀጠቀጡለት ጌታ በመካከላቸው ቆሞ አላወቁትም:: ክብሩ ሰማያትን ሸፍኗል!! ይህ ትልቅ ጌታ ተላልፎ በሰው እጅ ለመሞት መጣ?!!! እንዴት ጥልቅ ነው ደህንነታችን:: ከእነርሱም ጋር የተነጋገረው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር። ይደንቃል! የተዋጀሁት በእንሰሳ ደም ሳይሆን ክብሩን ጥሎ በመጣውና እጅግ በወደደኝ ቅዱስና ኃያል አምላክ ነው! መዳኔ ውድ ነውና ተመስገን!!
ሉቃስ 9: 32-33
33 ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን፡— “አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ፡” አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር።
ጴጥሮስ የሚለውንም አያውቅም ነበረና ሶስት ዳስ ማቆም ፈለገ:: በእውኑ ኢየሱስ ከሙሴና ከኤልያስ መደዳ ነውን? ጌታም አልወቀሰውም ታገሰው:: የእኛ አምላክ በላይ በሰማይ በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ጌታ ነው የሰው እጅ በሰራው ዳስ አይኖርም::
የእግዚአብሔር ዓላማ ምንድነው ይህንን ክብር ሲያሳያቸው? ክብሩን አይተው ምስክር ይሆኑ ዘንድ ነው:: ሶስቱን ብቻ መርጦ ነው ይዞ ወደ ተራራው የወጣው:: እነርሱም እንቅልፍ የከብዶባቸው ያለ ቢሆንም ግን ነቅተው ክብሩን አዩ:: የሚነጋገሩትንም ሰሙ ስለሚመጣው መከራውና በእየሩሳሌም ስለሚፈጸመው የሰው ልጆችን ነፃ የማውጣት ተልዕኮና ስለኢየሱስ ተላልፎ መሰጠት ነበር::
ክብሩን እንዳናይ ከሚከለክል ድካም ጌታ ያውጣንና ክብሩን እንይ:: ሐዋርያቱ አብረውት በጸሎት ተግተው ቢሆን ኖሮ ይህ ባልሆነ ነበር:: ዛሬም በጸሎት እንድንተጋና ክብሩን እንድናይ ጸጋው ይብዛልን:: አሜን!
