ተቀባይነትን አግኝተናል

- የእግዚአብሔር ልጆች ነን– ገና እንሆናለን አይደለም ቃሉ የሚለን የእኛ ድርሻ ጌታ እየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መቀበልና በስሙ ማመን ሲሆን የጌታ ድርሻ ደግሞ ተቀብሎ ልጅ ማድረግ ነው:: በዮሐንስ ወንጌል 1: 12፤ ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው:: ይለናል ቃሉ ስለዚህ ልጅ ነን:: እስኪ እንደዚህ እናስበው:- ልጃችሁ ዛሬም ነገም እየመጣ ‘አባዬ/እማዬ ልጅህ/ሽ ነኝ?’ ቢል ምን መልስ እንሰጣለን? ምናልባት የመጀመርያ ሰሞን ቀልድ መስሎን እንደነገሩ እንመልስ ይሆናል ሲደጋገም ግን ችግር እንዳለ ይገባናል:: በሌላው በኩል ደግሞ ልጄ አይደለህም ብሎ ልጅን ያህል ነገር ክዶ ማባረር እኮ አይቻልም DNA የሚባል ነገር ስላለ አልያም የራሳችንን DNA መውሰድ አለብን ከልጃችን ውስጥ አይደል? ግን ይህ ደግሞ አይቻልምና አንድ ጊዜ ልጅ ሆኖ ከተወለዱ በኃላ መሻር አይቻልም ማለት ነው:: የመጀመሪያው ላይ እንመለስና አስረግጠን ለልጃችን ልጅ መሆኑን እንነግረዋለን ደግሞም ማን ልጅ አይደለህም የሚልን ጥርጣሬ በልጃችን እንደሚጨምር ማወቃችን አይቀርም:: ያን ጊዜ ልጃችንን በደንብ አስታጥቀን እንልከዋለን መመለስ ያለበትን:: እንዲሁ እግዚአብሔር ቃሉን ሰቶናል ልጅ ነህ ብሎ ምን እንፈልጋለን ታድያ እዛ ጥርጣሬ የሚዘራብን ጠላታችን ላይ ቃሉን እንናገር እንጂ:: በእግዚአብሔር በኩል ያየነው እንደሆነ አስተማማኝ ነው አይክደንም አንድ ጊዜ በመስቀሉ ከእርሱ ተውልደን ስልጣን ተሰጥቶናል:: በጠላት ላይ መሳቅ እንጂ ልጅህ አድርገኝ እንደገና ብሎ መዘመር አያስፈልግም:: እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ በጌታ ዘንድ የለምና:: አንድ ጊዜ ልጅ ሆኛለሁ::
- የጌታ ወዳጆች ነን :- በዮሐንስ ወንጌል 15: 15፤ ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና። ብሎናል አይገርምም?
- ጸድቀናል :- ወደ ሮሜ 4-20 – 5: 1፤ ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም።ስለዚህ ደግሞ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። ነገር ግን። ተቈጠረለት የሚለው ቃል ስለ እርሱ ብቻ የተጻፈ አይደለም፥ ስለ እኛም ነው እንጂ፤ ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው።እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤ የጸደቅነው በእምነት ነው እምነታችንም እኛን ለማጽደቅ ከሞት በተነሳው በእየሱስ በማመናችን ነው ልክ እንደ አብረሃም:: እንጂ በራሳችን የምንታመንበት አንዳች ነገር የለም:: ተስርቶ አልቋል እመኑ ስንባል እሺ ካለቀማ ምን እጨምራለሁ ብሎ በእርሱ እርፍ ማለት ነው::
- አንድ መንፈስ ነን:- 1ኛ ቆሮንቶስ 6: 17፤ ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከእርሱ ጋር አንድ ስለመሆን ጌታ እየሱስ የጸለየውን እንመልከት:: በዮሐንስ 17: 20-23፤ ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ስለዚህ ክርስቶስ ብእኛ እየኖረ ካለ እንግዲህ ከራሱ ጋር አንድ አድርጎናልና ጠላት በእኛ ላይ አይሰለጥንም ገና በምድር ሳለ ከሁለት ሺህ ዓመታት በኃላ ስለምንመጣውም ጸልዮልናል:: ከእርሱ ጋር አንድ ሆነን የመንግስቱን ስራ እንሰራለን::
- በዋጋ ተገዝቻለሁ:- 1ኛ ቆሮንቶስ 6: 19-20፤ ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። ይህ ስጋ የጌታ ነው ሊቀደስ ይገባል እንደወደድን የምንወጣና የምንገባ አይደለንም የራሳችን ስላልሆንን እርሱን የምናከብር ነን::
- የክርስቶስ አካል ነኝ:- 1ኛ ቆሮንቶስ 12: 27፤ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። እያንዳንዳችን በክርስቶስ ውስጥ አካል ነን:: አንዳችንም ያለስራ መቀመጥ የለብንም ምክንያቱም የተፈጠርንለት ስራ እኛኑ ይጠብቃልና:: ማንነታችንን አውቀን ለስራ እንሰማራ እርሱ በድማችን ያወቀን እረኛ ነው::
- ቤዛነትን አገኘሁ:- ወደ ኤፌሶን 1: 3፤ በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።4፤ ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።5፤ በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።6፤ በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ።7፤ በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።8፤ ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። ለተጨማሪ ለማጥናት ይህንን ሊንክ ተጠቅመው ይመልከቱት https://ye-jesus.com/2021/08/17/የኤፌሶን-መልእክት/ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን በውድ ልጁ ደም ተዋጀን:: እራሱ ጌታም እንዳለን የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። ብሎ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። መዳናችን ጊዜያዊ አይደለም የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። ተዋጅተናል ብለን ስንል የዋጀ አካል አለ ማለት ነው እርሱም አፉን ያልከፈተው እንደበግ ተነድቶ ደሙን ያፈሰሰው እየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው:: የእርሱም ዓላማ ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ሃሌሉያ!
- ወደ መንግስቱ አፈለሰኝ:- ወደ ቆላስይስ 1: 13-14፤ እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ይህ ክፍል ገና የሚተገበር ሳይሆን ያለቀ እንደሆነ እንረዳለን:: አንድ ጊዜ ፈልሰናል:: ስለዚህ እንደወደድን በኃጥያት እየተመላለስን እንኑር?! ይህን ካሰብን በክርስቶስ የሚገኝ ደህንነት ምን እንደሆነ አልገባንም ማለት ነው:: ቀድሶን የእኔ ናችሁ ማደሪያዬ ቤቴ ናችሁ ብሎን እንዴት ብለን በኃጥያት እንመላለሳለን?! ይህ ከእኛ ይራቅ! ወደመንግስቱ እንደፈለሰ ሰው እንመላለስ::
- በእርሱ ተሞልቻለሁ:- ወደ ቆላስይስ 2: 9፤ በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።10፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ይህ የማይሻር እውነት ነው:: እርሱ በእኛ ውስጥለመኖር ሲመጣ ማንነቱን ሁሉ ነው ይዞ የመጣው ይኼውም ድል መንሳቱን! በእርሱ ተሞልተናል:: ነፍሳችንን ርንስበካት!
- ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት የመቅረብ መብት አለኝ :-ወደ ዕብራውያን 4: 14፤ እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ።15፤ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም።16፤ እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።አሜን! እንግዲህ አጥቦ አሳምሮ በውስጣችን እየኖረ ነው ያለው:: እየሱስ በምድር ሲመላለስ ለሊቱን ሙሉ ይጸልይ ነበረ እኛም ዛሬ በጸጋው በርትተን ወደ ጸጋ ዙፋኑ ለመቅረብ ድፍረት አለን አሜን:: የምንለምነው ይሰማል ደግሞም በጸጋ ላይ ጸጋን ይሰጠናል!
ስለዚህ ይህንን ሁሉ ቃልሰምተን ችላ አንበል ይህ የእግዚአብሔር ቃል ስለእኛ ማንነትነው የሚያወራው:: እኔ በዚህ ቃል ላይ የተባለውን ነኝ እያልን ነፍሳችንን እንስበክ ለውጡን ታዩታላችሁ በይህወታችሁ:: እኔ ለዘመናት የቆየ የማይግሬን ራስ ምታት ለቆኝ ከሄደ 20 ዓመትን አስቆጠረ:: ተጠቅሜበታለሁና የክርስቶስን አካል ይጠቅማል ብዬ ስላመንኩኝ አካፍያለሁ::
