በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ (1:1)
ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው። ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። (1: 7-8)
To share the word of God to Christ's body in Ethiopian language, Amharic.
በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ (1:1)
ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው። ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። (1: 7-8)
በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ፥ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ የቅዱሳን ልብ በአንተ ስራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ፥ በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። (1: 5-7)
አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፥ (1: 11-13)
በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥ (1:3)
ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል። (1:15)
ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል (2: 11-13)
መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ይህን በሙሉ ሥልጣን ተናገርና ምከር ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ። (2: 14-15)
ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤
ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። (3: 4-7)
እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። (1:7)
በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤ መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ። (1: 13-14)
እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። (2: 1-2)
የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ። (2:7)
ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ (2:11)
የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። (2: 15)
እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። (2: 21)
ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። (1:22)
የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። (3:5)
በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። (3:12)
በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። (4:1-2)
ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፥ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ። ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። (4: 17-18)
የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ (1:5)
ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ፤ (1: 12)
የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ። (1: 14)
ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ (1: 15)
ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን (1: 17)
አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ፤ (2: 5-6)
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ (6:6)
ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። (6:10)
አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። (6:11)
የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ። ሙሴም። ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ይህን ታላቅ ራእይ ልይ አለ። (3: 2-3)
እኔም እጄን እዘረጋለሁ፥ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብፅን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል። (3:20)
ፈርዖንም። ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም አለ። (5: 2)
እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። (6: 3-4)
ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። (6: 7)
ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ ከከባዱም ሥራ የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም። (6:9)
ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። (1:12)
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። (1: 13-14)
እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። (1: 21-22)
ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። (1:27)
በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። (2: 9-15)
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። (1: 3-4)
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል። (1:5)
መግቢያ (መግቢያው የተወሰደው ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም ላይ ነው)
የመልእክቱ ጸሐፊ ጳውሎስ ሲሆን የተጻፈውም ከሮም እስር ቤት በ60 ዓ.ም ነው:: የተጻፈውም የአንባቢውን አድማስ በማስፋት የእግዚአብሔርን የዘላለም ዕቅድና የጸጋውን ስፋት ጥልቀት ለማሳወቅና በዘመን ፍጻሜ ሁሉን በአንድነት አጠቃሎ በክርስቶስ ሥልጣን ሥር ማዋል ነው::
በመልእክቱ ላይ የተካተቱት ዋና ዋና ሃሳቦች:-
ይህች ቤተክርስቲያን ለ3 ዓመት በጳውሎስ ተገልግላለች (ሐዋ 20: 31) ከቆላስያስ መጽሐፍ ጋር ብዙ መልክቱ ይመሳሰላል (ሁለቱንም ከሮም እስር ቤት ነበር የጻፋቸው):: የክርስቶስ ስም የከበረበት ስፍራ ነው አጋንንት እየሱስን አውቃለሁ ጳውሎስንም አውቃለሁ ብሎ ሰዎችን የደበደበበት ቦታ ነው:: ብዙ ድንቅና ተአምራትም ሆኖል ብዙ ጠንቋዮችም ንስሀ ገብተዋል:: እንዲሁም የጳውሎስ ጨርቅ ድውያንን የፈወሰበት አጋንንትንም ያወጣበት ስፍራ ነው (ሐዋ 19ን ይመልከቱ) ስለዚህ ደብዳቤው በደንብ አብሯቸው ለኖሩት ቅዱሳን ቢያስፈልግ በስም መጥራት የሚችልበት ጉባኤ ነው የተጻፈው:: ጽሁፉም በመንፈሳዊ ጥልቀት ነው የተጻፈው:: መንፈስ ቅዱስ አስተማሪ ነውና ያስተምረናል::
ወደ ኤፌሶን 1: 1-2
1፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤ 2 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ከሰላምታው ስንጀምር በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ብሎ ነው የሚጀምረው:: ይህ ማለት እኔ እራሴን የሾምኩኝ አይደለሁም ፈቃዱ ሆኖ ሐዋርያ ያደረገኝ መልክቱን የሰጠኝ ጌታ ነው እያለ ነው:. እግዚአብሔር ሲልክ ስራ ይሰራል እራሱን የሾመ ግን ክብር ለጌታ ለማምጣት ይከብደዋል ስለዚህ ጌታ ባሰማራን ላይ ሆነን እናገልግል::
በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን:- ቅዱሳን ብሎ ነው የሚጠራቸው ይህ ስም እንዲሁ አልመጣም ከቀደሰን ከጌታ እንጂ እኛም ይህንን ስም ተቋድሰናል ከቀደሰን ከልጁ የተነሳ ተቀባይነትን አግኝተናል:: እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤ ይላል ልክ በውሃ ውስጥ ላሉ አሳዎች እንደማለት ነው ከውሃው ሲወጣ አሳ እንደሚሞት እኛም በክርስቶስ መሆናችን ነው በህይወት ያኖረንና ጌታን እናመስግን:: በህይወት ለመኖር በክርስቶስ ውስጥ ላላችሁ ለእናንተ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን እያላቸው ነው:: ዛሬም ለእያንዳንዳችን ይሁንልን:: አሜን!
ወደ ኤፌሶን 1: 3
3፤ በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።
እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ግድ ይላል:-
እግዚአብሔር አብን ስለባረከን በረከት እናመስግነው:: ምስጋና ይገባዋልና!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1
4፤ ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።
አንድ ነገር እናስተውል እዚህ ክፍል ላይ:- እኛ እግዚአብሔርን አልመረጥነውም፤ አላሰብነውም እንዲያውም ያለነውም ከፍርድ በታች እንደሆነ እንኳን አላስተዋልንም እግዚአብሔር አብ እራሱ በክርስቶስ መረጠን:: ክብር ለስሙ ይሁን!
ማን መረጠን የሚለው ከተመለሰልን መቼ ተመረጥን የሚለውን እንይ:: እኛ ሳንፈጠር ብቻ ሳይሆን ዓለም ሳይፈጠር ነው የተመረጥነው:: ለምን መረጠን?
ይህ የእኛ ማንነት ይሆን ዘንድ ነው ጌታ ወደ ምድር የመጣው ይህንን ሁሉ ማንነት የምናገኘው በክርስቶስ ውስጥ ነው እንጂ አንዱም የእኛ አይደለም:: ቅዱስ ነውር የሌለበት ፍቅር የሆነ እየሱስ ነው:: እግዚአብሔር ቅዱስና ያለነውር ናችሁ ሲል አረ እኔ አይደለሁም እያልን አጉል ትህትና ውስጥ እንገባና ቃሉን እንቃወማለን:: ቃሉ እንደሚል ሁሉ ሐጥያትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል አይቀየርም ክብሩ የጎደለን ነበርን በክርስቶስ ውስጥ ስንሆን ግን ቃሉ እንደሚለን ነን:: እራሳችንን እያየን ቃሉን የምንቃወም እንዳንሆን በእየሱስ ውስጥ እራሳችንን እንይ ስለዚህ መሆን ያለበት በልጅህ መርጠህ ቅዱስና ያለነውር በፍቅር እንድሆን አድርገኸኛልና ተመስገን ማለትና እንደቃሉ መኖር ነው የሚጠበቅብን:: ጌታን እናመስግን በልጁ ስለመረጠን፤ ስለቀደሰንና ያለነውር በፍቅር እንድንሆን ስላደረገን::
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1: 5
5፤ በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።
ለእግዚአብሔር ልጆች ነን እርሱ ጥርጥር የለውም ግን እንዴት ልጅ ሆንን የሚለውን ግን እንየው እስኪ:: እዚህ ክፍል ላይ እንደምናየው በእየሱስ ክርስቶስ ሥራ ነው ልጆች የሆነው እንጂ በራሳችን አይደለም ይህንን አስረግጠን እንወቅ! በመስቀል ምጥ ተወለድን! ሃሌሉያ!
ይህ የልጅነት መንገድ እንዳለ እንኳን የማናውቅ በጨለማ የምንደናበር ነበርን ነገር ግን እግዚአብሔር አብ በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ይህንን ህይወት እንድናይ አደረገን:: በበጎ ፈቃዱ የምትለውን አስምሩበት እንጂ ከሌሎች የተሻልን ሆነን ወይም እውነትን በራሳችን አውቀን የመጣን አይደለንም! ወደደንና የራሱ አደረገን!
ጎበዝ ደህንነት የመገለጥ ጉዳይ ነው:: እርሱ እንደወደደ ነው በልጁ ሥራ የዋጀን እዚህ ጋር መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ታድያ ይህንን ደህንነት እንዴት ልኑርበት ሲሆን መልሱም እንደመጣንበት አመጣጥ ማለትም በመገለጥ መጥተናል በመገለጥ እንመላለስ! ብልጣብልጥነቱን እንተውና እርሱ በሚሰጠን መገለጥ እንከተለው:: ክርስትና ዕለት ዕለት መገለጥ ከሌለው በራሳችን ስለምንመራ ተሸናፊዎች ነው የሚያደርገን:: በፊቱ በጸሎት እየተጋን ቃሉንም እየበላን በመገለጥ እውነት ውስጥ እንኑር:: እርሱ በየቀኑ አዲስ ነው መቼ አረጀና በትላንቱ እንኑር ወይም የራሳችንን መብራት እናብራ? እርሱ በእኛ ውስጥ እንዳለ እኛም በእርሱ ውስጥ እንደሆንን ብናየው ያ የድል ሁሉ ቁንጮ ነው::
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1:6
6፤ በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ።
እግዚአብሔር ወደ መንግስቱ ያፈለሰን በጸጋ ነው ይህም ጸጋ ከመብዛቱ የተነሳ መገረምና ማመስገን ብቻ ነው የቀረልን:: የጸጋውን ክብር እናመስግን ወደ መንግስቱ ፈልሰንበታልና:; ለዚህም ነው በጸጋ እንጂ በሥራችን አይደለም የጸደቅነው የምንለው:: በውድ ልጁ እንዲያው ይህንን ጸጋ ሰጠን! ሃሌሉያ!
አንዳችንም ምህረት የተገባን አይደለንም በጸጋው ግን ይቅር ብሎ አንጽቶ የራሱ አደረገንና በእኛ ተደሰተ:: ቃሉ እንደሚል አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፤ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል። አሜን!
ይህንን እናስተውል እግዚአብሔርን ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። በእምነት እንቀበል ወደ እርሱም በእምነት እንቅረብ በጸጋው በልጁ ተቀብሎናልና:: ይህ የማይሻር እውነት ነው!
የምስጋና ርዕስ:- የተዋጀንበትን በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠንን የጸጋውን ክብር እናመስግን!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1: 7
በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት።
እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን በውድ ልጁ ደም ተዋጀን:: እራሱ ጌታም እንዳለን የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። ብሎ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። መዳናችን ጊዜያዊ አይደለም የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። ተዋጅተናል ብለን ስንል የዋጀ አካል አለ ማለት ነው እርሱም አፉን ያልከፈተው እንደበግ ተነድቶ ደሙን ያፈሰሰው እየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው:: የእርሱም ዓላማ ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ሃሌሉያ!
ቤዛነታችንን አገኘን በእየሱስ ደም ይኸውም የበደላችን ስርየት። ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በእየሱስ መግባት ቻልን:: ይህ ስፍራ በዓመት አንድ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ስለራሱና ስለሌሎች የኃጥያት ማስተሰሪያ መስዋዕት ይዞ እየፈራና እየቸረ እግሩ ታስሮ ቢሞት እንኳን ጎትተው ለማውጣት እንዲችሉ ታስሮ ይገባል:: አዲሱ ሊቀ ካህን ግን ስለራሱ የኃጥያት መስዋእት ማቅረብ ያላስፈለገው ንጹና ቅዱስ ሲሆን ደሙን ስለእኛ እያንጠባጠበ ወደ አባቱ ገብቶ አስታረቀን ስለዚህም ዛሬ አባ አባት ሆይ ብለን ዘው ብለን ወደ ቅድስት መግባት ቻልን!
የተደረገልንን ስናስብ ምስጋና ይገባዋልና ጌታን እናመስግን:: አንድ ጊዜ ዋጋ ከፍሎ ተዋጅተናልና ወደ ባርነት ተመልሰን ይህንን ቅዱስ ካህን ለራሳችን ደግመን አንስቀለው እርሱን በመፍራት በቅድስና እንመላለስ::
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1: 8
8፤ ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን።
እግዚአብሔር ከእኛ የከለከለው ነገር የለም በሰማያዊው ስፍራ ባርኮናል በዚህም በምድር ደግሞ አብዝቶ ባለው ሁሉ ጸጋ ባርኮናል::
የጸሎት ርእስ: ጸጋህን በጥበብና በአእምሮዬ ሞልተሀልና ተመስገን በራሴ ጥበብ አልደገፍም!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1: 9-10
9፤ በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ 10፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።
የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናል:: ለማን? ምንድነው ይህ ምሥጢር? የሚሉትን ጥያቄዎች እንመልስ::
ለማን? ጌታ እየሱስ ወዳጆች ብያችኃለሁ አለን ወዳጅ ሚስጥር ያውቃልና የዘመኑን ፍጻሜ ሚስጥር አስታወቀን:: እርሱ እራሱ ወደ ልቡ አስጠግቶ አሳወቀን:: ይገርማል! እንደው እንደቀላል አንየው የአገር ሚስጥር በጥቂቶች እጅ ነው እኛ ግን የዓለም ፍጻሜ ሚስጥር አወቅን:: የእኛ ጌታ እንደቃሉ ነው:: እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። የሰማይን እውቀት ሰጠን::
ምንድነው ይህ ሚስጥር? በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ በዘመን ፍጻሜ በሰማይ ይሁን በምድር ያለው ሁሉ በክርስቶስ የመጠቅለሉ እቅድ ነው::
ይህንን ያህል ሚስጥር እናውቅ ዘንድ የተደረገበት ምክንያት ምንድነው? ወይም ድርሻችን ምንድነው? ከላይ እያየን እንደመጣነው ይህንን መዳን የጀመረው ጌታ ከፍጻሜው ማድረስ ይፈልጋል ይህንንም ለማድረግ መንፈስ ቅዱስ ስራውን ተረክቧል ስለዚህ እራሳችንን ለዚህ ጌታ እንልቀቅ በአፍ ሳይሆን በተግባር መሆን አለበት:: እርሱ ሊልቅ እኛ ደግሞ ልናንስ ይገባል:: ዝግ ብለን ከእርሱ እየሰማን እንመላለስ ያስደንቀናል:: በእያንዳንዳችን ውስጥ ሊሰራ ያስቀመጠው ጸጋ አለና በዚህ መክሊት እናትርፍ:: ሁላችን ካህናት ነን የመንግስቱ ስራ ለጥቂቶች አይደለም ለሁላችንም ነውና ዛሬ እራሳችንን በፊቱ አቅርበን እነሆኝ ላከኝ እንበለውና የዘመን ፍጻሜ በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡና እቅዱ በእኛም ይስራ::
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1 11-12
11፤ እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። 12፤ ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።
ከላይ ቁጥር 3 ላይ እንዳየነው በሰማያዊ ስፍራ እንደተባረክን ይነግረናል እዚህ ክፍል ላይ ደግሞ አንዱን የተባረክንበትን በረከት እናያለን እርሱም ርስት መቀበላችን ነው በሰማይ:: ለዚህ ርስት እንዴት በቃን ብንል? እራሱ እግዚአብሔር ምክርን መክሮ በዛ ምክር መሰረት ልጁን ልኮ ስለዋጀን ነው ለዚህ ርስት የበቃነው:: ምክርን መክሮ ብቻ ቢያበቃ እዚህም ባልተገኘን ነበር ነገር ግን እንደ ፈቃዱ አስቀድሞ የወሰነው ውሳኔ በክርስቶስ ለሚመጡ ርስትን ይወርሳሉ ብሎ ነበረና አወረሰን:: ሃሌሉያ! ስለዚህ እኔና እናንተ በዚህ ውሳኔው መሰረት የርስት ባለቤት ልንሆን በቃን ማለት ነው! ደግሞም በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። ሃሌሉያ!
ርስትን ተቀበልን ብለን ግን ቁጭ ልንል የተጠራን አይደለንም ሌሎችንም ለማፍለስ እንጂ! እነዛ ለምጻሞች ያገኙትን ካላካፈልን ይህ ግፍ ነው ብለው የምድርን ረሀብ ለማስታገስ ህዝባቸውን ጋብዘዋል ዛሬም ላለው የነፍስ ጩኸትና ረሀብ መልስ እንስጥ ወደዚህ ኑና ጥገቡ እንበል:: ሰው ለብሶ አምሮበት ሲሄድ ጥያቄ የሌለበት ይመስላል ሁሉ ግን በሞት ፍርሀት የሚመላለስ ነውና ወንጌልን እናድርስ እኛ እጅ ነው መፍትሄ ያለው ርስቱ ሰፊ ነውና ሰውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ታረቁ ብለን ወደ እረፍት እናፍልስ!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1: 13-14
13፤ እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ 14፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።
ርስትን የተቀበላችሁና ለርስቱ የተለያችሁ እናንተ ደግሞ እንዴት ወደዚህ እንደደረሳችሁ አስቡ:-
መንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል። በዘመናት መጨረሻ ሁሉን በክርስቶስ መጠቅለል እንደሆነ እቅዱ አይተናል ይህንንም ስራ የሚሰራው ኃላፊነቱን የተቀበለው መንፈስ ቅዱስ ነው ሁሉን ዋጅቶ ሲጨርስም ለእግዚአብሔር ክብር ይሆናል:: እዚህ ስራ ላይ ለመስራት ተጋብዘናልና እንስራ ለክብሩ ምስጋና ይሆናልና:: አሜን! ብቃታችንን አልፈለገም የዓለም ምናምንቴ እንደመረጠ አንርሳ ስለዚህ የእርሱን ምሪት ተከትለን በስራው እንደነቅ!
የምስጋና ርዕስ: በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ የሚለውን እያሰብን እንዲሁም ርስታችንን እያሰብን ጌታን እናመስግን:: ለዚህ ያበቃን አምላካችን ነውና!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1:15-16
15፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ፥ 16፤ ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤
ከላይ እንዳየነው በእርሱ ማመን መንፈስ ቅዱስን ወደ እኛ የሚጋብዝ ነው:: እርሱ በእኛ ውስጥ ሲገባ ደግሞ የእርሱ የሆነው ሁሉ የእኛ ይሆንና የመንፈስ ፍሬ ይባላል:: ስለዚህም ነው በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመናችሁ እንዲሁም እርሱ ያዘዘንን ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ የሚላቸው:: ደቀመዝሙርቱ መሆናችን በምንድነው የሚታወቀው? በፍቅር! ስለዚህ ይህ የእርሱ ማንነት በውስጣችን መገለጥ ይጀምራል ማለት ነው:: እግዚአብሔር ፍቅር ነው እንጂ ፍቅር አለው አይልምና ቃሉ:: ህግንም በሁለት ጠቀለለው አምላክህን ውደድና ባልንጀራህን ውደድ! ይህንን የሚቃወም የምድር ህግ እንኳን የለም:: ህግን ፈጽሙ አልተባልንም ህብረት ይኑራችሁ ከጌታ ጋር እንጂ ያንጊዜ በእርሱ ውስጥ ያለው ሁሉ በእኛ ውስጥ የማይነጥፍ ምንጭ ሆኖ እየፈለቀ ይታያል:: የቤተክርስቲያን አደራው የተሰጠው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ እንወቅ::
ይህ መጽሐፍ በመግቢያው ላይ እንደተገለጠው ለስህተት ትምህርት መልስ ወይም ሌላ እቅድ ኖሮት የተጻፈ አይደለም ወደሚቀጥለው መንፈሳዊ ከፍታ ለማሳደግ እንጂ ምንም የሚወቅሳቸውም ነገር የለም በመልእክቱ:: ስለዚህ ጳውሎስ ይህንን ፍቅርና ትጋት ሲያይ ሌላም ከፍታ አለ ብሎ የበሰሉ ስለሆኑ አጥንትን ወደ መቆርጠም እያስገባቸው ነው:: ይህንንም ያደርግ የነበረው ስለእነሱ በመጸለይ ነው:: የሚጸልየውም ስላላቸው ፍቅር ማመስገን ነበረ::
የጸሎት ርእስ:- ስለቤተሰባችን እንዲሁም በዙሪያችን ስላሉ ቅዱሳን ሁሉ እግዚአብሔርን እናመስግን በሚቀጥለው ጥናታችን ደግሞ ዝርዝር የጸሎት ርእሶች ላይ እንጸልያለን:: እስኪ በጌታ ፊት የምታመሰግኑለትን የአንድ ሰው ስም ንገሩኝና እኔም አብሬ ላመስግን?
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
ወደ ኤፌሶን 1: 17
17፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ።
የሚገርመው ከላይ በቁጥር 8 ላይ ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን ብሎ ካለን በኃላ ደግሞ እዚህ ክፍል ላይ እንደገና መልሶ ጸሎት እንጸልይ ይለናል:: ሁለቱ ሀሳብ የሚጋጭ ይመስላል ነገር ግን እያለን ያለው መንፈስ ቅዱስን ሲሰጠን ሁሉንም ሰቶናል (መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆነ አንዘንጋ) ነገር ግን እንደምንጭ የእኛ ሆኖ መፍለቅ ስላለበት ነው ጸልዮ የሚለን እንጂ አዲስን ነገር ሊያስተዋውቀን አይደለም:: በዛ ላይ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ተባርከናል አካውንታችን ሙሉ ነው ያስቀረብን ነገር የለም:: ነገር ግን ባንክ ገንዘብ አለኝ ሀብታም ነኝ ብንል አውጥተን ካልተጠቀምንበት ምን ይሰራል? አለኝ ማለት ብቻ?! ስለዚህ እንዳለን ማወቅ ከዛም እርምጃ መውሰድ አለብን ለመጠቀም ያን ጊዜ አገልግሎት ላይ ይውላል:: አሁንም ማወቅ ያለብን በእርሱ ሙሉ ነን ግን በአእምሯችን መታደስ ተለውጠን ይህንን እውነት የራሳችን አድርገን ልናዋህደው ይገባል:: አለበለዚያ አይጠቅመንም!
ለመጸለይ ሲጋብዘን ወንድማችን እንዴት ጌታን እንደገለጠው እንይ:- የክብር አባት! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ፤ አሜን! እርሱ የክብር አባት ነው የተከበረ ቃሉን የማያጥፍ እውነተኛ! ሃሌሉያ! ጌታም ጸሎት ሲያስተምረን እንደዚሁ ነበረ መግቢያው ክብሩንና ማንነቱን ነበረ ያሳየን እርሱ አባታችን ነው:: አሜን!
ይህ የከበረ አባት እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ ነው ጸሎቱ:: ይህ ጸሎት ስጠኝ ሳይሆን የሰጠኸኝን አሳውቀኝ ነው:: በክርስቶስ ሙሉ ነን! ስለዚህ በፊቱ ይህንን ጸሎት እንጸልይ እንዲያውም ጽፈን እቤታችን ውስጥ ሁልጊዜ የምናየው ቦታ እንለጥፈው እርሱን ማወቅ የአንድ ቀን ጉዳይ አይደለም:: ለራሳችንም ለሌሎችም መጸለይ ያለብን ጸሎት ነው:: ይህንን ስንጸልይ በህይወታችን የሚሆኑ ነገሮች በሚቀጥለው ጥናት እናያለን::
ወደ ኤፌሶን 1: 18-19፤
ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤
ከላይ በቁጥር 17 እንዳየነው የጳውሎስ ጸሎት የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁነበረ:: ለምን ይህንን ጸሎት መጸለይ አስፈለገ? የልባችን ዓይኖች እንዲበሩ:: ልብ ዓይን አለው እንዴ? እንድናስተውል ማለቱ ነው ምሳሌያዊዉ ንግግር:: እግዚአብሔር ማስተዋልን ካልሰጠን ከየትም አናገኝምና:: የኤፌሶን ቅዱሳን ግን ይህንን አያውቁም? እኛ እንደምናውቀው እነርሱም ያውቃሉ:: አንድ ምሳሌ ልጠቀምና መኪና ሞተር እንዳለው በሞተሩ ኃይል እንደሚሄድ አብዛኞቻችን እናውቃለን:: መካኒክስ ምን ያህል ያውቃል? እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ልዮነቱ የሚመጣው መካኒኩ መውጫ መግቢያውን ዘርዝሮ ሲያውቅየእኔ እውቀት ግን ቁንጽል ነው:: ልክ እንዲሁ የጠለቀ እውቀት እንዲኖረን ነው ጳውሎስ የፈለገው:: እስኪ የልባችን ዓይኖች ሲበሩ ምን እንደሚሆን እንመልከት:-
አንድ ጥያቄ ልጠይቅ ይህንን ኃያል ጌታ ይዘን የሚያስፈራን ምንድነው? ምንም! እርሱ ኃያል ነው ሊረዳንም ዝግጁ ነው:: እስራኤሎች ለሊት እሳቱን ሰማይ ላይ እፍስሶ በቀን ደግሞ ደመናውን ዘርግቶ ከሚያቆማቸው ምድራዊ ኃይል ሁሉ እየተዋጋ ርስታቸውን አወረሳቸው ዛሬም ከዚህ በበለጠ እኛ ውስጥ ሆኖ ተሸክሞናል እርስታችን መድረስ አያጠራጥረንም:: እንደርሳለን እንዲያውም ከጠላታችንን ላይ ምርኮን ቀምተን:: አሜን!
ወደ ኤፌሶን 1
20-21፤ ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ 22፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። 23፤ እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።
አቤት እንዴት ደስ የሚል ቃል ነው ድል የነሳውን እየሱስን እንዴት አብ ከፍ እንዳደረገው ነው የሚገልጸው:: ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው :- አሜን እየሱስ ከሙታን ተነስቷል! ሞቶ የቀረ ጌታ አይደለም የምናመልከው:: ሃሌሉያ!
ሲያስነሳው ምን ሆነ? ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ተቀበለ:: ዛሬም ስሙን ስንጠራው ይህ ሁሉ የሰይጣን ሰራዊት ይንበረከካል:: ከእኛ የተነሳ ሳይሆን ከከበረው ስሙ የተነሳ! ያልተሸነፈ ሰይጣን የለም ሁሉም ተሸንፈዋል! እጁን ያልሰጠ የለም ሁሉንም ስልጣናቸውን ገፎ እያዞረ አሳያቸው::
በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ እኛም ከእርሱ ጋር ተቀምጠናል:: ስራውን ጨርሶ ቁጭ ባለበት እኛንም በዛው አስቀመጠን! ስራው አልቋል! ተፈጸመ ብሏል! የእግዚአብሔር የብርታቱ ጉልበት የታየው እየሱስን ከሙታን ሲያስነሳው ነው:: ዛሬም ጉልበቱ ይታያል:: ደግሞም ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።
ወደ ኤፌሶን 2
1-2፤ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። 3፤ በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።
በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር ጌታን ወይም ሰይጣንን ነው የምናመልከው በመካከል ሌላ የለም:: ሰው ሲፈጠር አምላክን የሚፈልግ ማንነት በውስጡ አለና ግድ ይላል ወደ አንዱ ጎራ መሆን:: ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን ምክንያቱም ለአዳምና ለሄዋን የተነገራቸው ከዛፉ ፍሬ ከበሉ ሞትን እንደሚሞቱ ነበር እነሱ ግን ባለመታዘዝ በሉ:: ነገር ግን እግዚአብሔር ሞት ብሎ የጠራው የሰውን ከእርሱ መለየት ነበር እንጂ እነሱማ በስጋቸው በህይወት ኖረው ልጆችን ሁሉ አፍርተዋል:: ስለዚህም በሮሜ 5 ላይ እንደሚለው በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። ስለዚህ አለመታዘዝ ከእርሱ ለይቶ የሰይጣን አደረገን እንደወደደም አዘዘን ዛሬ በዓለም ያሉት ይህንኑ ነው እያደረጉ ያሉት:: ለዚህ ነው ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ ይህንን ሁሉ የሰይጣን ስራ አፍርሶ ድል ነስቶ የምናሸንፍበትን ይህንን የተቀባ ስምና ሰቶን መንፈስ ቅዱስንም አፍስሶ በአብ ቀኝ እኛንም በውስጡ ይዞ ቁጭ አለ:: ሃሌሉያ!
የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን አሁንስ? ወደ ህይወታችን አዳኝና እረኛ ተመልሰናልና የስጋችንን ፈቃድ ሳይሆን የእሱን ፈቃድ እያደረግን ነው የምንኖረው:: ሞኝነት አይምሰለን የእርሱን ነገር ማስቀደም እመኑኝ አናፍርም! እርሱ ታማኝ ነው! በምክሩ እንራመድ!
ወደ ኤፌሶን 2: 4-5
4፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ 5፤ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥
የሚገርመው እግዚአብሔር አብ ልጁን የላከው ሌላ ምንም ምርጫ የለም ምን ይሻላል ከሚል ወይም ሰው ፍጥረቴ ነው የማዳን ግዴታ አለብኝ ብሎ ከግዴታው አይደለም የመጣልን:: ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ እንጂ ግዴታው አይደለም ሰው የወደቀው በራሱ ነው:: ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆችና በበደላችን ደግሞ ሙታን ነበርን:: አዳምና ሄዋን አልታዘዙም መታዘዝ ከመስዋእት ይበልጣል:: ይህንን የሞተ ማንነት ለማሻሻል ምንም ብናደርግ የሚፈጠር ነገር የለም የኃጥያተኝነት ማንነታችን አይሻርም ነበር ጌታ ባይመጣልን:: እርሱን በማወ ግን ህይወት ሆነልን:: ምሕረቱንና ፍቅሩን በእኛ ላይ ላበዛው ጌታ ክብር ይሁን::
በዮሐንስ 17: 3፤ እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። የዘላለም ህይወት እርሱን ማወቅና ከቁጣ መዳን ነው:: አሜን! ምንም እንኳን ከእግዚአብሔር ተለይተን የሞትንና የቁጣ ልጅ ብንሆንም ከትልቅ ፍቅሩ የተነሳ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና:: በምን ድናችኃል? በጸጋ!!!! ህይወት የሰጠን የተቋረጠውንም ግንኙነት የቀጠለው እራሱ የተበደለው አምላክ ነው:: ከእግዚአብሔር መለየት ሞት ነው::
በጸጋ ድነናል የምንኖረውም በእርሱ ጸጋ ነው ግን ይህ ማለት እንደወደድን በኃጥያት ለመመላለስ ፈቃድ አይደለም:: እንዲያውም ምን ያህል እንደተወደድንና እንደቀደሰን ስናውቅ ለእርሱ ክብር እንኖራለን::
ወደ ኤፌሶን 2: 6-7
6-7፤ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።
ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ ያለን አልበቃ ብሎት በዛ ላይ ሌላ በረከት ጨመረልን ይኸውም:- ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። አስነሳን ካልን መሞት አለ ማለት ነው:: ከእርሱ ጋር ሞትን ተቀበርን አሁን ደግሞ ቃሉ እንደሚል ተነሳንና ከእርሱ ጋር አስቀመጠን:: አሁንም የመዳናችንን ቀንድ እየሱስን እንመልከት ምክንያቱም ያስነሳን ከእርሱ ጋር ነውና:: እርሱ ባያደርግልን ኖሮ እዚህ ጋር የምናወራውን አንዱንም የማድረግ ብቃት ያልኑበርን ነበርን::
ስለዚህ መዳናችን ምን ያህል ዋጋ ያስከፈለ ብቻ ሳይሆን ምኅረትንም እንደጠየቀ እናያለን:: እዚሁክፍል ላይ እንደሚለው በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ ይላል:: ምንድነው የሚያሳየው ለእኛ ያለውን ቸርነት! ሃሌሉያ! ቸርነት ተደርጎልናል:: እንደገናም ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው:: እኛን ከእየሱስጋር ያስነሳን!
ከስስቱ የተነሳ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን:: በየት? በሰማያዊ ስፍራ! እንዴት እንደወደደን እዩ! በዚህ ቃል መሰረት እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጠናል (እኔ አይደለሁም ያልኩት ቃሉ ነው) ስለዚህ እንደቃሉ እናስብ እንደቃሉም እንኑር! በአጉል ትህትና እኔን ብሎ ደግሞ በሰማያዊ ስፍራ ተቀማጭ የምንል ብንኖር ቃሉን እንቃወማለን ድሮውንም ጌታ ነው ከምኅረቱ የተነሳ ለዚህ ያበቃን:: እንመን! እንደቃሉ እንቁም! እኔ በአብ ቀኝ በክርስቶስ ውስጥ ነኝ እንበል! ይህ እውነት ነው አርነትም ያወጣናል:: ሃሌሉያ!
ወደ ኤፌሶን 2: 8-9
8፤ ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ 9፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።
ጸጋው ያዳነን በእምነት ነው ባናምን ኖሮ (አሁን በዓለም ላይ ያልተቀበሉት እንዳሉ ሁሉ) መዳን አይሆንልንም ነበር:: ይህንን ጸጋ ስንቀበለው አምነን ህይወት ሆነልን:: እናስተውል ጸጋው ተገልጦ በእምነት ባያድነን ኖሮ በምንም መንገድ መዳን የምንችል አይደለንም:: በመጀመሪያ በጸጋ መዳናችንን ማወቅ አለብን ይህንን አምኖ መቀበላችን ለብዙ የእምነታችን አቋም መሰረት ነው:: የዳነው በራሳችን ጥረት አይደለም እርሱን በማመን ብቻ ነው:: ይህ ጸጋ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ይላል ቃሉ:: ይህንን ስጦታ እጃችንን ዘርግተን ተቀበልን! ጌታም ተቀበለንና አጸደቀን! ያለዚህ ስጦታ ተስፋም አልነበረንም:: በቲቶ 2:11፤ ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይላል ሰዎችን ሁሉ ነው የሚያድነው ይህ ጸጋ:: ግን ይህ ጸጋ በስጦታ የተጠቀለለው በእየሱስ መስቀል እንደሆነ እናስብ የተንገላታውንና ዋጋ የከፈለውን እናስብ::
ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም በጸጋ እንጂ! በስራ ምንም ማምጣት እንደማንችል አውቀናል ስለዚህ በመዳናችን ላይ ለመጨመር አንታገል እራሱ ቃሉ ያለ ትግል ውስጣችን ሲያድግ ያሳድገናል:: ክርስትና መገለጥ ነውና:: እርሱን በማወቅና በመገለጥ መንፈስ ይሙላን::