ምዕራፍ 1
እግዚአብሔር የታመነ ነው
1ኛ የቆሮንቶስ 1: 1-9
ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቅዱሳንን እንዲህ ብሎ ነው የሚጠራቸው:
1. በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥
2. የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤
እኛም የዚህ አካል ነን ተቀድሰናል – መቀደስ ማለት አንድ ጊዜ የተሰጠን ነው ክርስቶስ ወደኛ ህይወት ሲገባ እንጂ ሰርተን የምናመጣው አይደለም:: ከእርሱ ተካፍለናልና ይህንን የተቀደሰ የህይወት መንገድ እንጠብጥብ:: እራሳችንን እንቀድስ ብለን ስንጥር የመስቀሉን ስራ ዋጋ እንዳናሳጣው:: ስለዚህም እርኩሰትን እጸየፋለሁ እኔ ተቀድሻለሁኝና ማለትና የዓለምን ከንቱ ነገር ሁሉ እንቃለሁ ብለን ዕለት ዕለትም ይህንን በህይወታችን እየገለጥን እንጉዋዝ::
በክርስቶስ ኢየሱስ ስላመናችሁ በተሰጣችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ሁልጊዜ ስለ እናንተ አምላክን አመሰግናለሁ፤
ይህም ማለት:-
1. በነገር ሁሉ
2. በቃልም ሁሉ
3. በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና::ይህንን ሁሉ ጸጋ ተቀብለናል ይህንንም ሁሉ ነገር በእኛ ላይ አፍስሶአል::
ስለዚህ በዚህ ሁሉ ባለጠግነት ለምን ተሞላን? ብለን ስንል: የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ የምንጠብቀው ሙሽራ አለን ስለዚህ በዛን ቀን
የቱ ቀን?!እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል።
ምን ያደርገናል?
ያጸናችኋል!!!! አሜን አረ ጎበዝ እጃችንን ዘርግተን እርሱን እንጋብዝ እርሱ እራሱ ያጸናናል:: ስሙ ይባረክ!
ምክንያቱም ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።
አሜን!!!!! ባንታመን እንኩዋን እርሱ ለዘለዓለሙ የታመነ ጌታ ነው:: በጌታችን እንኩራ እራሱን ተማምኖ ጠርቶናልና ብቃታችንም እርሱ እራሱ ነው:: “አልበቃም” የሚልን ዘር እንዴት ቢደፍር ነው ጠላት በእኛ ላይ የሚዘራው??? እርሱ የታመነና ብቁ ነው:: አሜን!! አንድን ነገር እናውጅ እኔ በክርስቶስ ሙሉ ነኝ እንበልና ቃሉን ከራሳችን እናዋህድ::
ቀናችሁ ይባረክ!!
የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን
1ኛ ቆሮንቶስ 1:10-17
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። ይለናል ጳውሎስ: ለምን ብለን ያልን እንደሆነ የሚለያይ መንግስት አይጸናምና:
ስለዚህ ከመካከላችን ክርክር አስወግደን እኔ የክርስቶስ ነኝ ፤ አንተም የክርስቶስ ነህ ፤ አንቺም የክርስቶስ ነሽ ብለን በአንድ ሀሳብ ተስማምተን ትልቁን የእግዚአብሔርን ስራ እያየን እናገልግል እንጂ ወደፊት የምንለያይ መሆን የለብንም:: የተጠራንለት ጥሪ የከበረ ነው እርሱም:ሞትና ትንሳዔውን መመስከር ነው::
ወንጌልን ልሰብክ እንጂየክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም።
ወደ ሮሜ 116፤ በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና።
እንበርታ! ይህንን ወንጌል ለሁሉ እናድርስ እዳ አለብንና!
የተባረከ ቀን ይሁንልን!!
የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን
1ኛ ቆሮንቶስ 1: 18 – 31
የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። አሜን የእግዚአብሔር ኃይል ለማወቅ ጥበበኛ መሆን አላስፈለገም እንዲያውም ሞኝ ሆኖ በስብከት ማመን ብቻ ነው የተጠበቀብን:: አይገርምም?
የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና።
መቼም አውቃለሁ ያለ ጠቢብ ዛሬ በእኛ ሲስቅ አይደንቀንም ምክንይቱም በጥበብ እርሱን ማወቅ አይቻልምና:: ወገኖች ገብቶናል የመጠራታችን ሚስጥርና ጥልቀት?
ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ::
ዛሬም ጆሮ ለሚሱጠን ሁሉ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው::
ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው። አሜን!!!!
ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። ነገር ግን፡— የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ፡ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።
በክርስቶስ የሆነልን ምንድነው ብለን ብንል:-
1. ጥበብ – እርሱን እናውቅ ዘንድ
2. ጽድቅ – ተሰጠን በፊቱ መሆን የምንችልበት ወይም ደሞ ጻድቃን ተባልን የእርሱ ለኛ ተቆጥሮ
3. ቅድስና – እርሱ እራሱ ቀደሰን
4. ቤዛነት – እርሱ ስለ እኛ ሞተና ከኃጢአትና ከጨለማው አሰራር ዋጀን::
እናስተውል በራሳችን አንዳች ነገር እንዳልሆነ ስለዚህ ቃሉ እንደሚለን ትምክህታችን በርሱ ላይ ብቻ ይሁን::
ትምክህታችን እርሱ እንደሆነ ሲገባን ነገራችንን ሁሉ ወደ ፊቱ እንጥላለን እንጂ በአንዳች አንጨነቅም:: ስለዚህ አሁን የሚያስጨንቀንን ወደ ፊቱ አምጥተን እንጣል ባንጥል ደግሞ ምንም ማድረግ እንደማንችል እንወቅ ለውጥ የለም ደግሞም አይመጣም:: ሊረዳን እጅግ ፈጣን ወደ ሆነው ጌታ እንምጣና እንረፍ በጠላት ሽንገላ ስር አንሁን::
መልካም የተባረከ ቀን!!
ምዕራፍ 2
እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኃይል ይሁን
1ኛ ቆሮንቶስ 2: 1-5
እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።
1ኛ ቆሮንቶስ 1: 18፤ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።
1ኛ ጴጥሮስ 1: 3-5፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።
ወገኖቼ የዳነው በእግዚአብሔር ኃይል ነው: የምንጠበቀውም በእርሱ ኃይል ነው:: ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል ነው:: ስለዚህ ኃይልን በመግለጥ ማገልገልን እንለማመድ እርሱ ነውና የሚሰራው::
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና።
እኛም ዛሬ እንቁረጥ አልችልምን ትተን በእርሱ እችላለሁ ብለን እንውጣና የጌታን ክብር እንይ ይህ ስራ ለሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ብቻ የተሰጠ አይደለም:: የግማሽ ጊዜ አገልጋይ ብሎ ነገርም የለም ጌታ በግማሽ ስላልሞተ ግማሽ ብሎ ነገር የለም:: ሁላችንም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነንና እንበርታና የተሰጠንን ስራ በእርሱ ኃይል እንስራ:: እርሱም ክርስቶስን መግለጥ ነው:: የምንገልጠውም በጥበብ ቃል ሳይሆን በመንፈስና ኃይልን በመግለጥ መሆን አለበት:: ጌታ ማስተዋልን ይስጠን:: አሜን!
የተባረከ ቀን ይሁንልን::
እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን
1ኛ ቆሮንቶስ 2: 6-17
እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን። አሜን! እንዴት በድፍረት ይህንን ማለት እንደምንችል ላሳያችሁ:
እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።
መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በምኑ በኩል? በመንፈሱ በኩል የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ይገልጥልናል:: የጀመርነው የህይወት ጎዳና መንፈሳዊ ነው:: ስለዚህም
መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።
በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።
ጳውሎስ ደግሞ ደግሞ ስለመንፈስ ነው የሚነግረን ለምን ብለን ስንል?
ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።
ወደፊት ፍጥረታዊ ሰዎች መሆን አይገባንም:: እናስብበት:: ሐዋርያትን ኃይል እስክትቀበሉ ድረስ በእየሩሳሌም ጠብቁ የተባሉበት ምክንያት ይኽው ነው:: ዛሬም ጊዜ ሰቶናልና ኃይልን እንቀበል: ጊዜ በፊቱ እንውሰድ አለበለዚያ ቅጠል ብቻ ሆነን ፍሬ ፈልጎ ሲመጣ እንዳናፍር እንጠንቀቅ:: በእግዚአብሔር መንፈስ ተሞሉ ነፃ ስጦታ ነውና::
የጌታ ፀጋ ይብዛልን!
ምዕራፍ 3
እንደ ሰው ልማድ መመላለስ
1ኛ ቆሮንቶስ 3: 1-3
ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?
ሥጋውያን ማለት ምን ማለት ነው?1. ቅናት2. ክርክር ያለበት እንደሆነ ጳውሎስ በግልጽ አስቀምጦታል:: ይህ ለምን ይገኝበታል ሥጋዊ ሰው ላይ ያልን እንደሆነ መልሱ ግልጽ ነው አልሞተም!! በገላትያ 5: 20 ላይ ሁለቱም የስጋ ፍሬ ተብለው ይጠቀሳሉ:: በቅለን ስናበቃ ይህ ፍሬ ከሆነ በእኛ ላይ አንዥርጎ የሚገፕው ምን ይባላል?
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም።ምን እናድርግ ታድያ?!መንፈሳውያን እንሁን!እንዴት?
1ኛ ጴጥሮስ 21፤ እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ 2-3፤ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።
ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ጊዜ እናጥፋ እርሱ እራሱ ያሳድገናል: ጫካውን ይመነጥራል: ይቀድሳል እናም ይለውጠናል እራሳችንን ለመለወጥ መጣር ግን ልክ አትክልትን እንደ መግረዝ ነው አብዝቶ ያፈራል:: ወይም ደግሞ ዱቄት ወንዝ እንደወረደችው ነው እራስዋን ልታቦካ:: እራሳችንን ግን ለሚሰራው ቃል ስንሰጥ እንዴት እንደተቀየርን ሳናውቅ ለውጥ በህይወታችን ይመጣል:: እንጸልይ:ጌታ ሆይ እራሴን መለወጥ አልችልም ቃልህን ሰጥተኸኛል እንዲቀይረኝ እራሴን በፊትህ አመጣለሁ እርዳኝ:: ቃልህ ህያው ነው መንፈስም ነው:: ዕለት ዕለት ቃልህን እንዳነብ ጸጋን ስጠኝ:: አሜን!
የተባረከ ቀን ይሁንልን!
እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር
1ኛ ቆሮንቶስ 3: 4-8
እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ።
የሚያሳድግ እግዚአብሔር ነው!!!! በብዙ አገልጋዮች ተገልግለናል ጌታ እራሱ ግን እረኛችን ነው:: የሚከታተልና ግድ የሚለው ነው እርሱ የተለያዮ አገልጋዮችን ልኮ እርሻው ላይ ያሰራል: እርሻው ግን የጌታ ነው:: በዋጋ ገዝቶ የራሱ አድርጎናልና ቸልታ አይታሰብም አባቴ ይሰራል እኔም እሰራለሁ ያለን ጌታ መንፈስ ነው አይደክምም! አይታክትም! አይኖቹ ሁልጊዜ በእርሻው ላይ ናቸው::
እንግዲህ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ነው ማለት ነው ጉዳዮ ስለዚህ ወደፊቱ እንቅረብ ሳይፈርድ እየራራ የሚያሳድግ አባት አለን:: ሲደክመን የሚሸከም የሚያባብል ጌታ:: እርሱ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ ከሆነ በእርሱ ደስ ይበለንና እርሱን ወደ መምሰል እንሂድ:: እራሳችንን መቀየር እንደማንችል ግን እንገንዘብ:: እርሱ ድሮ ጥለነው የመጣነው የድካም መንገድ ነው አሁን በመረቀልን በዚህ በአዲስ መንገድ ላይ ነው ያለነው::
የጸሎት ርዕሰጌታ ሆይ እነሆ በፊትህ ነኝ እኔ የአንተ ነኝና ስራኝ: አሳድገኝም እንደቃልህ የምትልከውንም ሰራተኛ ልከህ አስተምረኝ እርሻህንም አሳምር: : በእየሱስ ስም አሜን!
የተባረከ ቀን ይሁንልን!
ማነን?!
1ኛ ቆሮንቶስ 3: 9
የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና።
ሕንፃ ወይም እርሻ በራሱ ምንም አያደርግም ካልተሰራበት:: አይደል? ስለዚህ ወደ ሕንፃችን ወይም ደግሞ ወደ እርሻችን የጋበዝነው እየሱስ በስራ ላይ ነው:: ገዝቶን በማሰማመር ላይ ይገኛል ታድያ እንደወደደ አድርጎ እኮ መስራት በዋጋ የገዛው የባለቤቱ ውሳኔ ነው:: አይደለም እንዴ?! ለዚህም ነው ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነን የሚለው ቃሉ::
ሕንፃው ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ብዙ ነገር ሊፈጠር ይችላል ግን ማሰብ ያለብን ሕንፃው እራሱን መቀየር እንደማይችል ነው ስለዚህም መላላጥ ትተን ለተፈጠርንለት አገልግሎት እንዋል:: ለሆስፒታልነት የተገነባን ሕንፃ የገበያ ስፍራ ብናደርገው አስቡት እስኪ የሚባክነውን ሪሶርስ? ማነን?! ሲጠራን ገና ምን እንደሚሰራብን ወስኖአል እኮ መጠየቅ እና ማወቅ ያለብን ማነኝ ነው::
እውነት ማነህ? ማነሽ?
መቼም ጊዜውን የሚያባክን አይደለም የኛ ጌታ እርግጠኛ ነኝ ማንነት አለን ወደ ቤቱ እስከጠራን ድረስ:: ዳር ቆመን የምንታዘብ መሆን የለብንም እንግባ ወደ መሀል የአንተን ስራ ማንም አይሰራልህም ያንቺንም እንደዛው:: ስራችን ቁጭ ብሎ እኛኑ ይጠብቃል:: በጌታ ልብ ሰው እንደመደበ ነው የሚያውቀው ምክንይቱም የመስሪያውን ሪሶርስ ሁሉ በጠየቅን ጊዜ ለማቅረብ ሰማይ እየጠበቀ ነው:: በጸጋ ላይ ጸጋን ደሊቨር ለማድረግ:: የመንግስቱ ስራ የሚሰራው በጸጋ ነው::
የዮሐንስ ወንጌል 1: 16፤ እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና::
የጸሎት ርዕሰማንነቴን አሳውቀኝ ምንድነው በእኔስ መስራት የምትፈልገው?
የጌታ ክብር በእያንዳንዳችሁ ሲገለጥ ለማየት እቸኩላለሁ::
የጌታ ሰላምና ጸጋ ይብዛልን! አሜን!
የእያንዳንዳችን ሥራ ይገለጣል
1ኛ ቆሮንቶስ 3:10-15
ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል
እግዚአብሔር አይዘበትበትም እርሱ ትልቅ ነው እንጠንቀቅ:: ስራችንን በግብር ይውጣ ወይም ደግሞ ሲመቸን ብቻ አልያም ደግሞ ሲመስለን እንዳንሰራ ብቻ አንድ ቀን:-
በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።በእሳት ውስጥ አልፎ ወይ ያሸልመናል ወይ ደግሞ መዳናችን በጭንቅ ይሆናል
ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል።
ስለዚህ ወገኖቼ እንዴት በቤቱ ልንመላለስ እንደሚገባን እናስተውል::
እንዴት እናገልግል?
1. (በተሰጠን ጸጋ) የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። 2. (በጥንቃቄ) እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። 3. ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
አልረፈደም ለማገልገል ወደ እርሻው ባለቤት ቀርቦ ስራ ስጠኝ ማለት ነው:: እርሱ ያሰማራናል ወደምናፈራበት እርሻ ይልከናል ስለዚህ እንጸልይ::
የጌታ ጸጋ ይትረፍረፍላችሁ! አሜን!
የእግዚአብሔር መንፈስ መኖርያ
1ኛ ቆሮንቶስ 3: 16፤
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?
‘ቤት’ ከመሆን ወደ ‘ቤተ መቅደስ’ ወደ መሆን ምን ቀየረን? እየሱስን የህይወታችን አዳኝና ጌታ ባደረግነው ጊዜ ያን ጊዜ በደሙ ዋጅቶ ቀደሰን እናም አብሮን ይኖር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ መጣ:: እኔ ብሄድ ይሻላል አጽናኙ ይመጣል ብሎ ነግሮን ነበር ለእርሱም መጠንቀቅ አለብን ዓለም ባያውቀው እንኩዋን እኛ በደንብ እናውቀዋለን:: እኔ መንፈስ ቅዱስን አልተሞላሁም ብላችሁ እንዳታስቡ ተሞልታችሁዋል ቃሉ እንደሚል ለቤዛነት እንደታተምን ይነግረናል::
ስለዚህ በዋጋ የገዛን መኖርያዎቹ ያደረገን እርሱ እራሱ ነው:: ቤተ መቅደሱ ነኝ ብለን አፋችንን ሞልተን ለመናገር ያበቃን እርሱ ነው:: የሆነውን ሆነናል የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ:: ይህ ቤተ መቅደስ ደግሞ ቅዱስ ነው የተቀደሰውም በበጉ በእየሱስ ደም ነው:: አሜን!
በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ መሸጥና መለወጥ አይታሰብም ቤቴ የፀሎት ቤት ይባላል ብሎ የቤቱ ቅናት እንደሚበላው ጌታ አሳይቶናል:: ታድያ ዛሬ ቤቱን በምን ሞልተነዋል? በጸሎት: በቃል: በዝማሬና በመንፈሳዊ ቅኔ? ወይስ በምን? ኮተቱን ሁሉ ሰብስባችሁ አውጡ:: ጌታን ብቻ እናስብ ወደኛጋ ለመኖር የመጣውን እንግዳ እንከባከብ: እናስተናግደው: አንዝጋው እናውራው እርሱ ይህንን ይወዳልና:: አስቡት እስኪ እንግዳ ቤታችሁ መቶ ባታናግሩት ምን ይሰማዋል ምናልባትም ተነስቶ ይወጣል መንፈስ ቅዱስ ግን ታግሶ እየጠበቀን ነው:: አረ እናስተውል ትልቁ እንግዳ በቤት ነው!!!!!! ግድ መንበርከክ የለብንም ከርሱ ጋር ለማውራት እርሱ አባታችን እኮ ነው::
የጸሎት ርዕሰ1. ንስሀ እንግባ እንደሚገባ ባላስተናገድነው2. ጸጋን እንጠይቅ እርሱን መፈለግ በልባችን እንዲገኝ3. ሁልጊዜ እናውጅ መቅደሱ እንደሆንን
የጌታ ጸጋ ይብዛልን:: አሜን!!
ቅዱስ ነን
1ኛ ቆሮንቶስ 3: 17፤
ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።
ባለፉት ቁጥሮች ላይ ማነን ብለን ከዛም ደግሞ የእግዚአብሔር ህንፃ ወይም እርሻ እንደሆንን አይተን ነበር:: እንደዚሁም ደግሞ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆንና እርሱ እንደሚኖርብን ተነጋግረናል:: ታድያ እርሱ የሚኖርበትን ቤተ መቅደሱን ማፍረስ ጥሩ ነው? ምን በወጣኝና!እንደምትሉኝ እርግጠኛ ነኝ:: እንደዚህ ነው ጉዳዩ: ሰውን ሁሉ በክርስቶስ እንወቅ ይለናል ጳውሎስ ያን ጊዜ በምናየው ሁሉ ላይ መፍረድን እናቆምና ወደ መማለድ እንሄዳለን:: በነገር ሁሉ ከእኛ አፍ መውጣት ያለበት የሚያንጽና በጨው የተቀመመ መሆን አለበት ምክንያቱም የምናናግረው ሰው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና:: እንዴት ቅዱሳንን ትሪት እንደምናደርግ እናስተውል::
ሌላው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ መሆኑን እናያለን:: ቅዱስ ነኝ ለማለት አፋችን መተሳሰሩና መክበዱን አስተውላችሁታል? የደፈርን ያህል ነው የሚሰማን:: ለምን?! ይህ የጠላት ሽንገላ ነው ቃሉን አናሻሽለውም ናችሁ ካለ አሜን ነው መልሱ:: የቁጫጭዋ ታሪክ መጣብኝ ድልድዩን ከዝሆን ጋር ስትሻገር ነቀነቅነው አይደል እንዳለችው ነው:: ትሁት ሊያደርገን ነው የሚገባው እንጂ ሊያስታብየን አይደለም:: እርሱ ነው የቀደሰን የእኛ ቅድስናማ ከምን ጋር እንደተወዳደረ እናውቃለን::የምተውላችሁ ነገር 1. ቅዱሳንን በፍቅር ተቀበሉ: አትሙ: ከትቻላችሁ ተሸከሙ:: 2. እኔ ቅዱስ የሆንኩ የእግዚአብሔር መቅደስ ነኝ ብለን እናውጅ::
የተባረከ ቀን ይሁንልን:: አሜን!
ሞኝነት ይመረጣል
1ኛ ቆሮንቶስ 3: 18-19
ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና።
በስብከት ሞኝነት አምነን ከሞት ወደ ህይወት መጣን ታድያ አሁን የምን ብልጣ ብልጥ ለመሆን መጣር ነው የያዝነው? በዛው እኔ አላውቅም አንተ ታውቅልኛለህ ብንል በእርሱ ላይ ብንታመን አይሻለንም? ቃሉም በእኛ ዘንድ ክቡር መሆን አለበት እንደሚለንም ነን:: የዝችን አለም አስተሳሰብ ሎጅክ የሚሰጥ ነገር ስንፈልግ የሚፈጥረውን: ታሪክ የሚቀይረውን የእግዚአብሔርን ቃል ቸል እንዳንል ያስፈራል:: ጉባኤ እግዚአብሔር ቢጠራና ሕዝቤን እንዴት ላሻግረው ባህሩን ቢለን ምናልባትም ሎጅካሉ አስተሳሰባችን አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ነው ስለለመደ ታናል ስራ ወይም እንደዚህ አድርግ እንደዛ አድርግ እንለው ይሆናል እንጂ መቼም ንፋስን አንፍስ አንለውም ቀይ ባህርን ለመክፈል:: ንፋሱም ሲነፍስ ብናይ አረ ይህንን ውሳኔ አስተካክል እያልን እንቅፋት እንሆንበት ነበር በአስተሳሰባችን ካልተቀየርን በስተቀር ስራውን አናይም:: ልክ የአንድ ስልክ ቻርጀር ለሌላው እንደማይሰራ እኛም ኮባተብል አንሆንም በመንግስቱ ስራ ውስጥ:: አካሄዳችን ሁሉ ሎጅክን የተንተራሰሰ ነው ከዚህ መውጣት አለብን::
የገባው ደግሞ እነዚህ አጥንቶች በህይወት ይኖራሉ? ሲባል አንተ ታውቃለህ ብሎ አብሮ ሰራተኛ ሆኖ ድንቅን ያያል:: ከሎጅክ እንውጣ በእጃችን ያደረገው በትር ባህር ይከፍላል:: በእጅህ ምን አለ? ነው ሁልጊዜ ጥያቄው ጥቂት ዘይትም ቢሆን እሱ በቂ ነው በጌታ እጅ ሲገባ የሚለንን በሞኝነት ስናደርግ ድንቅ ይሆናል::
ዛሬ የምለምናችሁ ነገር ዘመናችሁን አትፍጁ በመጏተት ስለዚህ ዛሬ እጅ ወደ ላይ: እንማረክና ድንቅ በህይወታችን እንይ::
እናንተም የክርስቶስ ናችሁ
1ኛ ቆሮንቶስ 3: 21-23
ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።
የእግዚአብሔር ሀሳብ ዓለምን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው:: ስለዚህም በክርስቶስ ውስጥ ያለው ሁሉ የእኛ ነው:: እራሳችንን ከመንግስቱ ወይም ከአካሉ ውጪ አንየው:: እኛ በክርስቶስ ውስጥ ነው ያለነው:: ትምክህታችንም መሆን ያለበት ባስጠለለን ጌታ ላይ ነው:: ከእርሱ ውጪ ትምክህት ከእኛ የራቀ ይሁን በጥበባችን አልዳንን ወይም እርሱን ወደማወቅ በምርምር አልደረስን ብሞኝነት አመነው ገባን ትልቁ የእግዚአብሔር ሚስጥር እየሱስ:: ስለዚህ መከፋፈልን ትተን በክርስቶስ አንድ አካል እንደሆንንና አካሉም በህብረት ዝንፍ ሳይል አንዱ አንዱን እየረዳ እንዲሁም ሁሉም የራሱን ሚና እየተጫወተ እንደሚኖር እንዲሁ ይሁንልን::እኛ የክርስቶስ እንጂ የራሳችን አይደለንም እርሱ በእኛ ይኖራል:: አሜን ይኑር: ይክበር: ከፍ ከፍ ይበልና ይታይልን የልቡ ሀሳብ በሰማይ ያለው በእኛም ውስጥ ይሁን::የተባረከ ቀን ይሁንልን:: አሜን!
ምዕራፍ 4
በአንዳች አትፍረዱ
1ኛ ቆሮንቶስ 4:1-5
እኛ የክርስቶስ እንደሆንን በትናንትናው ቃል ተነጋግረናል ታድያ ማን በማን ላይ መፍረድ ይችላል? ቢፈርድስ ምን ሊመጣ ይችላል? ህብረትን ከማፍረስና የጌታን ስራ ከማዘግየት ሌላ::
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ በራሴ ላይ ምንም አላውቅምና፥ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ እኔን የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። እርሱ ሲፈርድ ግን:-
1. በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ 2. የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ 3. በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል።
ይህ ማለት ግን የጌታ ቤት ስራ ሲበደልና ሲጠፋ ዝም ማለት አይደለም በፍቅር ሳንፈርድ ማቅናት አለብን ለአንድ ግብ:: ግቡም የጌታ ስራ እንዲሮጥ:: እንዴት ማድረግ እንችላለን ካልን:-
1. ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ 2. አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። 3. ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ተብለናል!
እንደ አካል ከተቀባበልን በመፍረድ መጠፋፋቱ ይቀርና በንጹ ልብ እንተናነፃለን:: ልናገለግል የተነሳነው ጌታን ነው ተጠሪነታችንም ለእርሱ ነው:: በቅንነት እንሰራለን ምስጋናን ከጌታ በመጨረሻ እንቀበላለን:: ስራው የጌታ እኛም የጌታ!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን:: አሜን!
አልታበይ
1ኛ ቆሮንቶስ 4:6-7
ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ፡— ከተጻፈው አትለፍ፡ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ።
መታበይ እመውደቅ አፋፍ ላይ ሲደረስ ያለ ምልክት ነው ስለዚህም አውቀናል ብለን ከተፃፈው አንለፍ:: ድንቅና ተአምራት ቢደረጉ እንኳን ከእኛ እንዳልሆነ ተረድተን ሙሉውን እውቅና ላደረገው እንስጥ:: እንጂ ይህን ለማሳየት ከበሮ አናስመታ:: ማስመታቱ ቢያስፈልግ ኖሮ እንደ ጳውሎስ የሚያስመታ የለም ነበር የሚለን ግን በወንድማችን ላይ አንታበይ በእኛ የሰራው ጌታ ነው እያለን ነው:: የሁሉ አይን ወደ ጌታ እንዲሆን እናድርግ:: ምክንያቱም:-
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?
የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ:: እርሱ ለትሁታን ጸጋን ይሰጣል::ዛሬ ልባችንን በፊቱ እንፈትሽ እንሻላለን የምንላቸውን ነገሮች ሁሉ እንይና ከጌታ በተሰጠን ጸጋ እንዳደረግን አውቀን ጌታን እናክብር ከጸጋው ወድቀን እንዳንገኝ::መልካም ቀን!
እራስን መካድ
1ኛ ቆሮንቶስ 4: 8-21
በዚህ ክፍል ላይ ሐዋርያው በቃን፤ ጠግበናል፤ ነግሰናል፤ ማንም ምንም አያስፈልገንም ላሉት የቆሮንቶስ ሰዎች የእነሱንና የሐዋርያት ህይወት እያነፃፀረ ያሳያቸዋል:: ለምሳሌ:-
እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን እናንተ ግን ኃይለኞች ናችሁ፤ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ እኛ ግን የተዋረድን ነን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።
ወደ ጉዳዩ ሲገባ ዋናው ሊጽፍ ያነሳሳው ነገር ወቅሶ ጉድለታቸውን ብቻ አሳይቶ ሊዘጋው አይደለም:-
እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም።
የመልክቱ ዋና የሚከተለው ነው:-
እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ።
ከላይ በንጽጽር እንዳስቀመጠው ህይወቱ ጌታን በማክበር እንጂ በትእቢት አልነበረም የሚመላለስ የነበረው::
ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን:: እራስን መካድ እዚህጋ ነው ያለው::
እኛም ዛሬ በጉዟችን ዝቅ ብለን ጌታን እየመሰልን እራሳችንን እየካድን ልንመላለስ ይገባል::
ተባረኩ
ምዕራፍ 5
ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና
1ኛ ቆሮንቶስ 5: 1-13
በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። 2፤ እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። 3-4፤ እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ 5፤ መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው። 6፤ መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? I7፤ እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ 8፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም። 9፤ ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ። 10፤ በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን አላልሁም፤ ይህስ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር። 11፤ አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። 12፤ በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? 13፤ በውጭ ባሉቱ ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።
ሐዋርያው የቀደመውን ምዕራፍ ሲዘጋው
1ኛ ቆሮንቶስ 4: 20-21 የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን?
ብሎ ስለሰማው ነገር መውቀስ ይጀምራል በአህዛብ መካከል እንኳን የማይታይ ሐጥያት በእግዚአብሔር ቤት እንዳለ ይጠቅስና ፍርድን እንደፈረደበት ይናገራል::
ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም።
ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ።
ሁላችንም አንድ ቀን በፊቱ እንቀርባለን አገልግሎታችንም በእሳት ውስጥ ያልፋል በውጤቱም መሰረት ሽልማት አለ:: ስለዚህ ፋሲካችንን ክርስቶስን ደስ ለማሰኘት እንኑር::
መልካም ቀን!
ምዕራፍ 6
ወንድም ወንድሙን አይክሰስ
1ኛ ቆሮንቶስ 6: 1-11
የወንድሞች ከሳሽ ተብሎ የተባለው ሰይጣን እያለ እኛ ወንድማችንንልንከስ አይገባም ሲሆን መታገስና በየዋህነት መንፈስ ማቅናት እንጂ::
ማን ነበርን የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ የማንችል ነበርን
አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን?
አሁንስ ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።
ታድያ መካሰስን ምን አመጣው?!
በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን?
እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? እንግዲህ ጉድለታችን ምንድነው?! አለመሞት ነው: ብንሞት ኖሮ ክርክርና መካሰስ በእኛ ዘንድ አይገኝም ነበር:: በእኛ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም ይሰደባል?! ይህ እንዳይሆን ያለፈውን የማያስፈልገውን የህይወታችንን ዘመን ረስተን አዲሱን ማንነታችንን እናጎልብት አላውቃችሁም ከምንባል ዛሬ ከጌታ ጋር ጊዜ እናጥፋና (በተለይ በዚህ በኮቪድ 19 ዝግ ላይ) እንቀየር አላውቃችሁም ማለት እኮ እኔን አትመስሉም ማለቱ ነው::
የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነን
1ኛ ቆሮንቶስ 6:12-20
ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።
ስጋችን ከርሱ የተቀበልነው እንደሆነ አስተውለናል? የተቀበልነውን እንደገና ደግሞ ዋጀቶ የራሱ አደረገን:: ቤተ መቅደሱ ስለሆንን እንዴት እናክብረው ታድያ በስጋችን?
ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።
ይህ ማለት ደግሞ:-
ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና።
ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። እግዚአብሔርም ጌታንም አስነሣ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል። ስለዚህ ዛሬ እንንቃ ከእርሱ ጋር እንተባበር አንድ መንፈስ ነንና:: ቃሉ እንደሚለን ነን ምንም ማሻሻያ አናድርግ አንድ መንፈስ ነን ብለን ስንል እርሱ በእኛ እየኖረ ነው ማለት ነው::ጌትን በዚህ እናመስግን አንድ መንፈስ ከእርሱ ጋር ያደረገንን::ጌታ መልካም ነውና ከመልካምነቱ ያጥግበን:: አሜን!
ምዕራፍ 7
ጋብቻ
1ኛ ቆሮንቶስ 7: 1 -16
በዚህ ክፍል ላይ የቆሮንቶስ ሰዎች ስለትዳር የጠየቁትን ጥያቄ የሚመልስበት ነው::
የሚዳስሳቸውም ሀሳቦች:-
1. ለእያንዳንዱ ለራሱ ትዳር ይኑረው
2. ላላገቡና ለመበለቶች
3. ያላመነ ላገቡ
ከላይ ላሉት ሀሳቦች መመሪያን ይሰጣል
በትዳር ላይ ላሉ:-
ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት።
ሀ) ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥
ለ) እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋሐ) ሚስትም ባልም በገዛ ሥጋቸው ላይ ሥልጣን የላቸውም የርስ በርስ ነው እንጂ
መ) ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤
ሠ) ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ።
ረ) ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፥ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፥ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፥ እኔ ግን አላዝም፥ ጌታ እንጂ።
ላላገቡ
ሀ) ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፡— እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤
ለ) ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ።
ያላመነ ላገቡ
ሀ) ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፥ አይተዋት፤
ለ) ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፥ አትተወው።
ሐ) ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው።
መ) የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል።
ሠ) አንቺ ሴት፥ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ አንተ ሰው፥ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?
በዋጋ ተገዝታችኋል
1ኛ ቆሮንቶስ 7: 17-24
ከዚህ በፊት ባለው ክፍል እንዳየነው ስለ ጋብቻ መክሯል:: አሁን ደግሞ ስለ ቅዱሳን ስራ ይናገራል:: ከመዳንችሁ በፊት በማኽበረሰቡ ውስጥ የነበረውን ባህል ቀጥሉ ይላል ለምሳሌ
1. ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ 2. ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ። መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ከንቱ ነው፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ። 3. ባሪያ ሆነህ ተጠርተህ እንደ ሆነ አይገድህም፤ አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል። 4. ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ ነው።
ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር።
ለእኛ ዛሬ የሚቀርልን ነገር ቢኖር በጌታ የሆነ ሰው በዓለም ያለው ስራው ምንም ሊለያየን አይገባም ሁሉን በፍቅር እና በአክብሮት እንቀበል ምክንያቱም ሁላችንም እኩል ነው ዋጋችን እሱም የከበረው የእየሱስ ክርስቶስ ህይወት ነው ዋጋችን:: ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ነን:: በዋጋ ተገዝታችኋል!!
ምክርን እመክራለሁ
1ኛ ቆሮንቶስ 7: 25-40
ምዕራፉን ስንጀምር እንዳየነው እዚህም ቦታ ላይ ለጥያቄያቸው መልስ እየሰጠ ነው:: እዚህጋ እንደሚናገረው እኔ እመክራለሁ ይለናል::
ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ። እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤
1. ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። 2. በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ 3. በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ። 4. ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር። 5. ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።
6. ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት። እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት::
ይህን የሚመክርበትን ምክንያት: –
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኗል፤ የዚች ዓለም መልክም አላፊ ነውና።
ያገባንም ያላገባንም የጌታን መምጣት እንጠባበቅ:: ማራናታ!
ምዕራፍ 8
ከአንዱ በቀር ማንም አምላክ የለም
1ኛ ቆሮንቶስ 8: 1-13
እንግዲህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።
መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።
ከአምላካችን ሌላ አምላክ የለም ስለዚህ በእኛ ባህል ውስጥ ወርንና ቀናትን እያስታከከ በብዙዎቻችን ቤት ወይም ጎረቤት ሲሰዋና ሲበላ እያየን ወይም እየተካፈልን አድገናል ዛሬ ግን ምን እናድርግ? እንዴት እንመላለስ ነው ጥያቄው:: ቃሉስ ምን ይላል?
መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም።
መብላት አለብን ለጣዖት የተሰዋ?
ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል።
አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤት በማዕድ ስትቀመጥ አንድ ሰው ቢያይህ፥ ደካማ ሰው ቢሆን ለጣዖት የተሠዋውን ለመብላት ሕሊናው አይታነጽበትምን? በአንተ እውቀትም ይህ ደካማ ይጠፋል፥ እርሱም ክርስቶስ የሞተለት ወንድም ነው። እንዲህም ወንድሞችን እየበደላችሁ ደካማም የሆነውን ሕሊናቸውን እያቆሰላችሁ ክርስቶስን ትበድላላችሁ።
ዳሩ ግን ይህ መብታችሁ ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ። ነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም፤ አንዳንዶች ግን ጣዖትን እስከ አሁን ድረስ ስለ ለመዱ፡— ለጣዖት የተሠዋ ነው፡ ብለው ይበላሉና ሕሊናቸው ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል።
ስለዚህ ጌታን ከምንበድል ሌላውን በማደናቀፍ ባንበላስ?!
ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ ማንም ግን እግዚአብሔርን ቢወድ እርሱ በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው።
ምዕራፍ 9
ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ
1ኛ ቆሮንቶስ 9:1-27
ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።
በዚህ ምዕራፍ ላይ ጳውሎስ የሚዳስሰው ስለ እርሱ መጠራትና ሐዋርያ መሆን ነው:: ሐዋርያ ለመሆኑም የሚሰጣቸው ማስረጃ እንደሚከተለው ነው
እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ።
ከቤተክርስቲያን እሱና በርናባስ ነበሩ ጥቅም የማይቀበሉት ግን መብታቸው ሆኖ ሳለ በራሳቸው እየሰሩ ይተዳደሩ ነበር:: ይህም ነገር እርሱ ሐዋርያ ባይሆን ነው ወደሚል ድምዳሜና እኔ የእከሌ እኔ ደግሞ የእከሌ የሚል ክፍፍል ውስጥ ያስገባቸው::
እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና።
ስለዚህ አገልጋዮች መንፈሳዊውን ዘርተው መኖሪያቸውን ከቤተክርስቲያን ማግኘት መብታቸው ነው ማለት ነው::
እኛ መንፈሳዊን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር እኛ ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? ስለዚህ ስለሚያገለግሉን ወገኖች እግዚአብሔር ይመስገን እንባርካቸው ደግሞም እንፀልይላቸው::
በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤
አሜን ነፋስን እንደሚጎሽም አይደለም የእኛ ነገር ስለዚህ እንበርታ ፥ ሩጫችንን እንሩጥ ፥ ነፍሳትን ለጌታ እንማርክና የማይጠፋውን አክሊል እንቀበል::ዛሬም ስለምድራችን እንፀልይ እግዚአብሔር ስለደሀው እንዲነሳ::
ምዕራፍ 10
ከዓለቱ ከክርስቶስ ጠጥተናል
1ኛ ቆሮንቶስ 10:1-12
ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤
ደመናው ለእስራኤላውያን ምን ነበር የሆነላቸው ብለን ብንል:- 1. በቀን የደመና አምድ ከፀሐይ ሊከልላቸው2. በለሊት የእሳት አምድ ጨለማውን አብርቶ ሊመራቸው3. በእስራኤልና በግብጽ መካከል ገብቶ ሊለይና ሊጠብቃቸውይህ ሁሉ እንክብካቤ ነበረ በዙሪያቸው እነሱ ግን:
ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ።
የ ቆሮንቶስ ሰዎች ዙሪያቸውን ጣኦትን በሚያመልኩ ወገኖቻቸው መካከል የሚኖሩ ናቸው:: ጣኦት ማምለክ ባህልም ነው አሁን አዲስ ሐይማኖት መጣና እንዴት ያቁሙት? አለማምለክ ከጤነኝነት ከማያስመድብ ማህበረሰብ ውስጥ እየኖሩ ያሉበት ነገር ዋጋ ያስከትላል መነጋገርያም ያደርጋል:: ጳውሎስ ግን የሚላቸው ነገር ለእስራኤልም አልበጀም ጣኦትን ማምለክ ከእያሱና ከካሌብ በስተቀር ሁሉም ምድረበዳ ቀሩ እግዚአብሔርግን ልክ እንደናንተው ተንከባከባቸው ጣኦትን ሲያመልኩ ግን:-
እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና። እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን።
ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።
ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።
ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ። እንግዲህ እንደተወደዱ ልጆች እንመላለስ::
ከፈተናው ጋር መውጫውን ያደርግላችኋል
1ኛ ቆሮንቶስ 10: 13፤
ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።
ማነው ግን እየፈተነን ያለው?! ያ ክፉ ነው እንጂ እግዚአብሔርማ አይፈትነንም:
የያዕቆብ መልእክት 1:13፤ ማንም ሲፈተን፡— በእግዚአብሔር እፈተናለሁ፡ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።
ለምን አይፈትነንም ብለን ስንል እርሱ እራሱን የሰጠ እውነተኛ እረኛችን ነውና::
ዮሐንስ 10: 14-15፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።
ስለዚህ እላችኋለሁ እያንዳንዱ ፈተና መውጫ አለው እንደጠላት ሀሳብማ ቢሆን ባልወጣን ነበር ቃሉ እንደሚል ከምንችለው በላይ እንድንፈተን አይፈቅድም! ሃሌሉያ!! አሜን!
ጸሎታችን መሆን ያለበት መውጫ እንዳደረክልኝ እርግጠኛ ነኝ አሳየኝ መውጫውን መሆን አለበት እንጂ ከጨለማው ዓለም የምንሰማውን የአለቀልህ ዜና አናስተጋባ:: በዚህ ቃል ልባችንን እናጽናና እግዚአብሔር የታመነ ነው:: በአይምሮአችን መታደስ እንለወጥና ቃሉ እንደሚለን እንኑር:: ቃሉን ከራሳችን ጋር እናዋህደው::
ታድያ ሁሉ ፈተና መውጫ አለው እያልሽ ነው ብትሉኝ አፌን ሞልቼ አዎን እላለሁ::
ስለአገራችን እንፀልይ ሰላምና እረፍት እንዲሆን እንዲሁም እርሱን መፍራት በምድራችን ላይ ይሁን::
ጌታን እናስቀናውን?
1ኛ ቆሮንቶስ 10: 14-22
የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን?
ምዕራፉን ሲጀምር ጀምሮ እስከዚህ ድረስ ደግሞ ደጋግሞ የሚነግራቸው ነገር ስለ ጣዖት አምልኮ ነው:: በተለይ እዚህ ጋር ጠበቅ አድርጎ ሽሹ ነው እያለ ያለው::
ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ።
ለምን ይሸሻል ጣዖትን ማምለክ? ምክንያቱም የነፍስ ትስስር አለበት ለጣዖት የተሰዋን መብላት በክርስትናው የጌታን እራት እንደመብላት ነው:: በጨለማው ዓለም ምን ኮፒ የማይደረግ አለ? ኦርጅናል የለው!
ስለዚህ በተቃራኒው ለአጋንንት የተሰዋውን ስንመገብ የአጋንንት ማኅበረተኞች እንሆናለን ማለት ነው
የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?
ይሄንን ስጋና ደሙን ስንወስድ ከእኛ ጋር ህብረት እንደሚያደርግ ግልጽ ነው መቼም:: ስለዚህ ከእርሱ ጋር አንድ ስጋ እንሆናለን ቃሉ እንደሚለን::
አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው እላለሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም።
ከዚህ በኃላ መቼም ይህንን ነገር በቀላሉ እንደማታዩት አምናለሁ ሌሎችንም ለማቅናት ቃሉን ማወቅ መልካም ነው::ጌታ አይናችንን ይክፈት! አሜን!
ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉ
1ኛ ቆሮንቶስ 10: 23 – 33
እኛ ግን ጌታን ልናመልክና ደስ ልናሰኝ ከዓለም ተለይተናል::
እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።
እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ፥ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ።
ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም።
1. በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤
2. ከማያምኑ ሰዎች አንዱም ቢጠራችሁ ልትሄዱም ብትወዱ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ።
3. ማንም ግን፡— ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው፡ ቢላችሁ ከዚያ ካስታወቃችሁና ከሕሊና የተነሣ አትብሉ፤
በዚህ ሁሉ ውስጥ ሁሉ የተፈቀደልን ነን ብለን የማያንጽና የማይጠቅም ነገር አናደርግም ነገር ግን የክርስትና መሰረቱ ፍቅር ነውና እውነትን በፍቅር ይዘን እሩጫችንን በትዕግስት እንሩጥ:: ለማንም ማሰናከያ ሳንሆን ሁሉን ደግሞ ለእግዚአብሔር ክብር እያደረግን እንመላለስ:: ዓይናችን በጌታ ላይ ይሁን እሱንም ደስ ለማሰኘት እንኑር::
ምዕራፍ 11
ክርስቶስን እንምሰል
1ኛ ቆሮንቶስ 11: 1
እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።
እንዴት ያለ ልበ ሙሉነት ነው? እኔስ እየመሰልኩት ነው? እራሴን መጠየቅ አለብኝእስኪ ክርስቶስ እንዴት ተመላለሰ ብዬ ልጀምር:-
1. ለራሱ አልኖረም2. የሱ መብል የላከውን ፈቃድ ማድረግ ነበር3. ሳይመቸው እንኳን የአንተ ፈቃድ እንጂ የእኔ አይሁን የሚል ነበር4. ክብሩን ሁሉ ትቶ ዝቅ አለ5. የበደሉትን ይቅር አለ6. ትተውት የሄዱትን ሐዋርያት እንኳን ሳይወቅስ ሰላም ለእናንተ ይሁን አለከጠቀስኩት በላይ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል ስለ እየሱስ::
እኔ ታድያ እንዲህ እንደ ጳውሎስ ለማለት እችላለሁ?
ከሰማይ የተሰጠኝ ብቃት አለ
እንዴት ቢባል የሚያስፈልገኝ ጸጋ ሁሉ ተሰቶኛል እርሱን ለመምሰል:: በደጅ ሆኖ ማንኩዋኩዋቱን ሰምቼ ወደ ህይወቴ በጋበዝኩት ጊዜ ከእኔ ጋር ለመኖር መቷል:: ስለዚህ እኔ አሁን የምኖረው ኑሮ ለሞተልኝ: ለዋጀኝ ጌታ ነው ብዬ ዕለት ዕለትም መስቀሉን ተሸክሜ እከተለዋለሁ:: ደግሞም ወደ ህይወቴ ሲገባ አዲስ ፍጥረት ሆኛለሁ አሮጌው ሁሉ አልፏል:: ከህግ እርግማን ተዋጅቻለሁ: የእዳውም ጽህፈት ከፊቴ ተወግዷል:: የእግዚአብሔር መንፈስ ባለበት በዛ አርነት አለ:: አሜን በነፃነት እመላለሳለሁ ልጅ ነኝና ከሰማይም ልጁን ለመምስእል የሚያስፈልገው ሁሉ የተሰጠኝ ነኝ:: በመጨረሻም:-
1ኛ ዮሐንስ 32፤ ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን። አሜን!!
ምክር
1ኛ ቆሮንቶስ 11: 2-16
ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።
ያስተማራቸውን ወግ ቤተክርስቲያንዋ በደንብ እንደያዘች ጠቅሶ ያመሰግናቸዋል:: ይህንን የሚለው ከፃፉለት ደብዳቤ ላይ ነው:: እርሱ ወደ ሌላ ስፍራ ለአገልግሎት ሲሄድ ጥያቄ ተነሳ እንዴትም ማድረግ እንዳለባቸው እየጠየቁት ነው በደብዳቤያቸው ላይ:: ጥያቄውም ስለ ባህላቸው ነው:: ሙሉ በሙሉ እንተወው ወይስ ምን እናድርግ የሚል አይነት:: የጳውሎስ መልስ:-
1. ሴት እንድትሸፋፈን
2. ወንድ ደግሞ እንዳይሸፋፈን ይነግራቸዋል:: ለምሳሌ:- አሁን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሰዎች ብንመለከት ሴት ትሸፋፈናለች ገና ለገና ወደ ጌታ መጥቻለሁ ብላ ፀጉሯን ለቃ መሄድ ከማህበረተሰቡ ተጽዕኖ የተነሳ አትችልም እስዋም አይመቻትም እነዚህም የቆሮንቶስ ሰዎች ባህላቸው ይህን ይመስላል:: ይህ ግን በሌላ ስፍራ ህግ እንዳልሆነ ጳውሎስ ይነግረናል::
ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም።
እኛ ዛሬ ይህ ጥያቄ የለብንም ነገር ግን አንዳንድ ቦታ ላይ ተተግብሮ አይተን ጥያቄ ቢፈጥርብን መልሱ ህግ አይደለም የሚለው ነው:: እውቀትን ከማጣት የተነሳ በማይረባ ክርክር የጌታን ቤት ስራ አናዘግይ:: ሁልጊዜ ልናስብ የሚገባን ጌታን ደስ ስለማሰኘትና መንግስቱን ለማስፋት ይሁን::
የጌታ እራት

1ኛ ቆሮንቶስ 11: 17-34
ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤
ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም፡— እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡ አለ። እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ፡— ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡ አለ።
የጌታን እራት ለምን እንወስዳለን?
1. ለመታሰብያዬ አድርጉት ስላለን
2. እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እንድንናገር
3. ህብረት እንድናደርግ (ሐዋርያት ስራ 2:42-47)
4. የሚያስተሳስረን ስለሆነ (1 ቆሮንቶስ 10:15-17)
የሚጎዳንስ እንዴት ነው?
1. ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት
2. ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥
3. የረሀብ ማስታገሻ አይደለም – ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ።
ፍርዱስ ምንድነው በአግባቡ ባለመውሰዳችን?
ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል
እንግዲህ እንዴት እንዘጋጅ የጌታን እራት ለመውሰድ?
1. ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤
2. ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤
3. ስለዚህ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ
ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን።
ይህ ማለት ፈርተን አንውሰድ ማለት ነው አረ እይደለም ለመውሰድ እንበረታታ ከጌታ እና ከቅዱሳን ጋር ህብረት ማድረግ መልካም ነውና::
ምዕራፍ 12
የመንፈስ ቅዱስ አሰራር
1ኛ ቆሮንቶስ 12: 1-6
ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።
1. የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤
2. አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤
3. አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
ለመንግስቱ ስራ ጌታ በተለያየ መንገድ ልጆቹን ይጠቀምብናል:: ከላይ እንደተመለከትነው የጸጋም ስጦታ፤ አገልግሎትና አሰራር የተለያዩ ናቸው ያንን ውበት ያመጣው ጌታ ግን አንድ እግዚአብሔር ነው:: በአካሌ ውስጥ የተለያዩ ብልቶች የተለያየ ስራ ይሰራሉ የሚያገለግሉት ግን እኔን ነው:: እንዲሁ በክርስቶስ አካል ውስጥ የተለያየ አሰራር ቢገለጥ እየተገለገለ ያለው ጌታ እየሱስ ነው እኛ አንድ አካል ነን አንዱ ስራውን በትክክል ካልሰራ ሌላው አካል ሁሉ ይታወካል:: ስለዚህ በእያንዳንዳችን ውስጥ እንደሚሰራው አሰራሩ እንታዘዝ::በአንዱ ውስጥ እንደዚህ በሌላው ደግሞ እንደዛ የሚሰራ ጌታ ነው ካልን ዘንዳ ታድያ ለምን ጸጋን እናወዳድራለን? በእኔ ላይ ጸጋ የለም ወይንም ብዙ ለውጥ አላመጣምን ምን አመጣው?! ያ መርዘኛ አስተሳሰባችንን በክሎት እኮ ነው እንጂ ያለ ስራ የሚቀመጥ ስራ ፈት ልጅ ጌታ የለውም!!!! ወደ እርሱ በመጣን ቀን እንደዚህ በአንተ/በአንቺ እሰራለሁ ብሎ መቷል:: እናስተናግደው!!
ምንም ይሰራ ምን የሚሰራው ጌታ ነው:: ተመኙ ብንባል የምንመኛቸውን አገልግሎቶች መገመት ቀላል ነው ግን ውስጣችን ያለውን ጸጋ አክብሮ መገለጥ ደግሞ ታላቅ ጥበብ ነው:: የማንንም ጸጋ ሳታወዳድሩ እኔን ላከኝ እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ ምክንያቱም ጌታን ከጌታ ጋር ማወዳደር ነውና ጸጋን ከጸጋጋር ማወዳደር:: ጌታ ማስተዋልን ይስጠን!
መንፈስ ቅዱስን መግለጥ
1ኛ ቆሮንቶስ 12: 7
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል።
እዚህጋ ቃሉ እንደሚለን ለእያንዳንዱ (አስምሩልኝ ለእያንዳንዱ ላይ) መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለጥቅም ይሰጠዋል:: መቼም የሚያስተን ሰው ካልፈለግን በስተቀር በግልጽ ነው የተነገረን እያንዳንዳችን ለጥቅማችን ሲባል የተሰጠን ስጦታ አለ ማለት ነው:: የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ልክ እንደ ክሪስማስ ትሪ ውሰዱት መቶ ያስውባል ስለዚህ ከመንፈስ ፍሬ በጣም ይለያል:: አንዳንዴ ሰዎች ድንቅና ተአምራት እየተሰራባቸው ህይወታቸውን ቀርበን ስናይ ያስበረግጋል ምክንያቱ ፀጋ ለመቀበል መዳን ብቻ ይበቃል ለጥቅማችን መቶ ሊረዳን ማለት ነው::
ለመንፈስ ቅዱስ በጣም መጠንቀቅ እንዳለብን ቃሉ ይነግረናል:: እርሱ እያንዳንዳችንን ሊያንፅ መቷል:: መሳሪያ ሳንታጠቅ አይደለም ወደ ውጊያ የገባነው ታጥቀናል ስሙ ይባረክ:: እርሱ እሩቅ ሆኖ የምንጠራው ጌታ ወይም ሌሎች ሲፀልዩልን የሚሰማ ከመሰለን ተሳስተናል እርሱ የቅርብ ጌታ ነው:: በፊቱም ተሰሚነት አለን:: አሜን!
ዛሬ እጆቻችንን ዘርግተን እናመስግነው ወደኛ ሊረዳንና ለጥቅማችን የተሰጠንን ጌታ::
የመንፈስ ቅዱ ስጦታዎች
1ኛ ቆሮንቶስ 12: 8- 11
መንፈስ ቅዱስ ለማነጽና ለጥቅማችን እንደተሰጠንና የጸጋ ስጦታዎችን ማወዳደር ልክ እንዳልሆነ አይተናል:: ሌላው ቀርቶ በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር እየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው ማለት እንኳን አይቻልም:: ከዚህ በታች ስጦታዎቹን እንያቸው:-
1. ጥበብን መናገር
2. እውቀትን መናገር
3. እምነት፥
4. የመፈወስ ስጦታ፥
5. ተአምራትን ማድረግ፥
6. ትንቢትን መናገር፥
7. መናፍስትን መለየት፥
8. በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥
9. በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም
ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።
ይሄ ሁሉ የተሰጠው የአካሉን ወይም የቤተክርስቲያንን ደህንነት ለመጠበቅ ነው::
የክርስቶስ አካል ናችሁ
1ኛ ቆሮንቶስ 12: 12-27
እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።
አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።
አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና።
ስለዚህ አንዱ ብልት ሌላውን አታስፈልገኝም ቢለው ወይም ደግሞ እኔ ይህንን ነኝና የአካል ክፍል አይደለሁም፡ ቢል ይህን በማለት የአካል ክፍል መሆን ይቀራልን? አካል ሁሉ አንድ አይነት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። ስለዚህ ማየት ያለብን አካሉን እንጂ አንድ ብልትን መሆን የለበትም::
ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። ከዚህ ክፍል የሚቀርልን- ከአንዱ መንፈስ ጠጥተናል በአንድም አካል ውስጥ እግዚአብሔር አገጣጥሞናልና ሌላው አያስፈልገኝም ወይም እኔ በቂ ነኝ ብሎ ነገር የለም የሚለውን ነው:: አንዱ የሰውነታችን ክፍል ተለይቶ ቢወጣ የወጣ ጊዜ ሞቷል መበስበስ ነው ውጤቱ እዚህም ጋ የምናየው ይህንኑ ነው:: ክርስትና ከአካሉ ውጪ የለም ለመሞት ካልሆነ በቀር:: ጌታ ማስተዋልን ይስጠን!
ስጦታዎችን ለቤተክርስቲያን ሰጠ
1ኛ ቆሮንቶስ 12: 28-31
ከዚህ በፊት የተለያዩ ስጦታዎችን እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን እንደሰጠ አይተን ነበር:: የሚከተሉትም ስጦታዎችን በተጨማሪ ተሰተዋል:-
1. ሐዋርያትን፥
2. ነቢያትን፥
3. አስተማሪዎችን፥
4. ተአምራት ማድረግን፥
5. የመፈወስን ስጦታ፥
6. እርዳታንም፥
7. አገዛዝንም፥
8. የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል
ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን? ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ።
ምንም እንኳን መጀመሪያ ይህንን ቀጥሎም ይህንን ስጦታ ሰጠ ቢለንም አንዱን ስጦታ ከሌላው ማወዳደር ልክ እንዳልሆነ አይተን ነበር:: እርሱ እንደወደደ ስጦታን በእኛ ውስጥ ያስቀምጣል መስራት የምንችለውን በጥሩ ሁኔታ የምንወጣውን ስለሚያውቅ የሚሰጠን ስጦታ ቅዱሳንን የሚጠቅም አካሉንም የሚያንጽ ነው::
እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ ስለማይለዋወጥ ቤተክርስቲያንም ገና ስላልተነጠቀች ዛሬም እነዚህ ስጦታዎች በሙሉ በስራ ላይ ናቸው:: አካሉን ለማገልገል ተሰተዋል:: ስለዚህ የተሰጠንን ስጦታ ጠንቅቀን እንወቅ ነው ምክሬ::
የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ
1ኛ ቆሮንቶስ 12: 31-13:1-3
ያለፈውን ምዕራፍ ሐዋርያው የዘጋው የሚበልጥ መንገድ ላሳያችሁ ብሎ ነው:: ምንድነው የሚበልጠው መንገድ?
ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ።
1. በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር
2. ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥
3. ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ
4. ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥
5. ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥሰው እነዚህን ካደረገ መቼም የምንለው መልአክ የሆነ ሰው ብለን እንመድባለን:: ልክ ነው ይህ ሁሉ ጥሩ ነው ነገር ግን ፍቅር ከሌለበት ሐዋርያው እንደሚለን
ፍቅር ግን ከሌለኝ
1. እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ።
2. ከንቱ ነኝ።
3. ምንም አይጠቅመኝም።
ይሄ ሁሉ ስራ ዜሮ ገባ ማለት ነው:: ጌታም ያለን እኮ ደቀመዝሬ መሆናችሁ የሚታወቀው በፍቅር ነው ብሎናል::
እግዚአብሔር ፍቅር ነው እንጂ ፍቅር አለው አልተባልንም:: ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው:: የተቀበልነውም መንፈስ የፍቅር መንፈስ ነው::በፍቅር እንመላለስ! ክፋትን ሁሉ እናስወግድ!
የፍቅር ባህሪያት
1ኛ ቆሮንቶስ 13:4-7
ፍቅር :-
1. ይታገሣል፥
2. ቸርነትንም ያደርጋል፤
3. አይቀናም፤
4. አይመካም፥
5. አይታበይም፤
6. የማይገባውን አያደርግም፥
7. የራሱንም አይፈልግም፥
8. አይበሳጭም፥
9. በደልን አይቆጥርም፤
10. ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለዓመፃ ደስ አይለውም፤
11. ሁሉን ይታገሣል፥
12. ሁሉን ያምናል፥
13. ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥
14. በሁሉ ይጸናል።
እስኪ ራሳችንን በእነዚህ ባህርያት ውስጥ እንየው:: ካላገኘናቸው ውስጣችን እንጸልይ:: ፍቅር ከሁሉ የሚበልጥ ነውና:: እራስን መካድና መስቀሉን ተሸክሞ መመላለስ ጌታን ብቻ ማሰብ እርሱንም በሙሉ ሀይላችን መውደድ ባልንጀራችንንም እንደራሳችን መውደድ ያስፈልጋል::
ፍቅር አይወድቅም/ይበልጣል
1ኛ ቆሮንቶስ 13: 8-13
ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ የሚበልጠው ፍቅር ነው
ለምን አይወድቅም ለምንስ የሚበልጥ ነው? ብለን ስንል ፤ ይህ ዓለም ያልፍና ወደ ማያልፈው ሙሉ እውቀት ወዳለበት ወደ ዘላለም ቤታችን መግባት ስላለ በዛኛው ዓለም
ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።
ፍጹም ወደሆነው አገር ስንገባ በድንግዝግዝ መኖር ይቀራል:: ሃሌሉያ! እንዴት የሚናፈቅ አገር ነው የወረስነው?
ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ።
እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። ፍቅር ይበልጣል ደግሞም አይወድቅም!! ጌታን መምሰል እራሳችንን እናስለምድ ፤ በፍቅር እንመላለስ ፤ ከፍቅር በቀር እዳ እንዳይኖርባችሁ ተብለናልና:: ይህን ለማድረግ በአእምሯችን መታደስ እንለወጥ ፤ ቃሉ ህይወትም ነው መንፈስም ነው ፤ የሚሰራ ነውና የማይገባን ያስወግዳልና ቃሉን በመንፈስ ከእኛ ጋር ይዋሀድ አለበለዚያ አይጠቅመንም:: በቃሉና በፀሎት እንትጋ::
ምዕራፍ 14
ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ
1ኛ ቆሮንቶስ 14: 1-6
ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ።
ትንቢትን ልትናገሩ ግን ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ፤ ማኅበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጐም በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።
ለምን ያልን እንደሆነ:-
1. ለማነጽ
2. ለመምከር
3. ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል
4. ማኅበሩን ያንጻል
በልሳን መናገርስ ጥቅሙ ምንድነው?
1. በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና፥ በመንፈስ ግን ምሥጢርን ይናገራል፤
2. በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል
ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር፥ አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ?
ስለዚህ እራሳችንን ለማነጽ በልሳን እንናገር ጉባኤን ለማነጽ ደግሞ ትንቢትን እንናገር::
የጸጋ ስጦታዎችን እንድንጠቀም አበረታታችኅለሁ ለጥቅማችን ተሰጥተውናልና:: እርስ በርሳችን እንተናነጽ፥ እንጽናና ፥ እንበረታታ::
የእየሱስ መንፈስ የትንቢት መንፈስ ነው:: አሜን!
መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ ፈልጉ
1ኛ ቆሮንቶስ 14:12-25
መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ 1. ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ2. በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ
እዚህጋ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ መተርጎምም እንድትችሉ ጸልዩ እያለ ነው ሐዋርያው የሚነግረን::
እስኪ በልሳን መፀለይን እንይ
1. መንፈሴ ይጸልያል
2. አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው።
3. ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥
4. እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ፡— አብደዋል፡ አይሉምን?
ትንቢትስ?
1. ትንቢት ለሚያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለማያምኑ አይደለም።
2. በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።
3. ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረ ይገለጣል፥ እንዲሁም፡— እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።
እንግዲህ: በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ
እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም።
ስለዚህ ወገኖቼ የጸጋ ስጦታን በብርቱ እንፈልግ በተለይም ትንቢትን መናገር ምክንያቱም ብዙዎችን ያንጻል ያጽናናልም:: አገልግሎት ግን በፍቅር መሆን እንዳለበት እንወቅ:: ጥያቄው ስንቶችን አጽናናህ ሳይሆን ስንቶችን ወደድክ ነው:: በስምህ አጋንንት አላወጣንም እንደዚህና እንደዚያ አላደረግንም? የሚሉ በመጨረሻ እንዳሉ ቃሉ ይነግረናል:: ጸጋው ሚዛን አይደፋም በስተመጨረሻ በእሳት የሚያልፈው አገልግሎታችን የመንፈስ ፍሬ ነውና ፍቅርን እንከታተል ትዕግስትን እናክልእራስን መግዛት እና ሌሎችንም የመንፈስን ፍሬ እናፍራ::
መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ ፈልጉ
1ኛ ቆሮንቶስ 14:12-25
መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ
1. ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ
2. በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ
እዚህጋ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ መተርጎምም እንድትችሉ ጸልዩ እያለ ነው ሐዋርያው የሚነግረን::
እስኪ በልሳን መፀለይን እንይ
1. መንፈሴ ይጸልያል
2. አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው።
3. ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥
4. እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ፡— አብደዋል፡ አይሉምን?
ትንቢትስ?
1. ትንቢት ለሚያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለማያምኑ አይደለም።
2. በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ።
3. ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረ ይገለጣል፥ እንዲሁም፡— እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።
እንግዲህ: በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ
እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም።
ስለዚህ ወገኖቼ የጸጋ ስጦታን በብርቱ እንፈልግ በተለይም ትንቢትን መናገር ምክንያቱም ብዙዎችን ያንጻል ያጽናናልም:: ስናገለግልም በፍቅር መሆን እንዳለበት እንወቅ::
ስንቶቻችን ግን ትንቢትን መናገር እንለማመዳለን? ይሄ ጸጋ ሊገለጥ ይገባዋል:: እንጸልይ ጸጋውም ካላቸው ጋር እንማከር ምናልባት በውስጣችን እያለ ለመጠቀም አላወቅንበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ::
ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን
1ኛ ቆሮንቶስ 14: 26-40
ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።
አምላካችን የስርዓት አምላክ ነው ወጥ የሆነ ስራ እንጂ የተዘበራረቀ ነገር የለውም:: ስለዚህ ቤቱ በስርዓት ለማነጽ እንዲሆን ይፈልጋል::
በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን።
ከዚህ የምንረዳው በጉባኤ ስንሰበሰብ ለእያንዳችን (አስምሩልኝ እያንዳንዱ ላይ) የሚሰጥ ነገር አለ ማለት ነው አሰራሩ ሲገለጥ ውበቱ ይታያል:: ተለማምደናል? ወይስ ችላ ብለናል? እርሱ ታማኝ ነው ሰቶናል ስለዚህ ረጋ ብለን እናስተውልና እንደተሰጠን ጸጋ እንገለጥ::
በልሳን የሚናገር ቢኖር 1. ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ 2. አንዱም ይተርጉም፤ 3. የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር።
ነቢያትም 1. ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ 2. በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል3. ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ። 4. የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ፤
እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።
ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤ ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ።
ወገኖቼ አበረታታችኅለሁ የጸጋን ስጦታ እንድትለማመዱ ትርፋማ ያደርጋልና ደግሞም እየበዛ ይሄዳል::
ምዕራፍ 15
የክርስቶስ ወንጌል
1ኛ ቆሮንቶስ 15:1-4
እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን፡ ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፡-
መጽሐፍ እንደሚል፡ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል፡ በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ሃሌሉያ!!!! ሃሌሉያ!!!! ሃሌሉያ!!!!አሜን!
በዚህም ምክንያት ይህ የምስራች ወደ እኛ ወንጌል ሆኖ ደረሰልን:: በዚህም ወንጌል የሆነልንን እንይ:-
ወንድሞች ሆይ፥ 1. የሰበክሁላችሁን 2. ደግሞም የተቀበላችሁትን 3. በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን4. በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤
በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ።
ይሄ ወንጌል በሌላ አባባል ሞትና ትንሳኤው:- ተስበክን፤ ተቀበልነው፤ ቆምንበት እናም ዳንበት:: አሜን!
በወንጌል ተለወጥን፥ ወደ ፍቅሩም መንግስት ፈለስን፥ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ተጠራን፥ በሰማይም ዕርስት ይጠብቀናል እኛ አገራችን በሰማይ ነው:: ድነናል ይህንን ማንም እንዲያረጋግጥልን እስከማያስፈልግን ድረስ በቃሉ ዛሬ አንበነዋል ስለዚህ ሳትናወጡም ቁሙ! የዚህ ወንጌል አገልጋይ መሆን እንዴት ትልቅ ክብር ነው::እንግዲህ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? ማንም!
የትንሳዔ ምስክሮች
1ኛ ቆሮንቶስ 15: 5-11
የክርስቶስ ትንሳዔ በምስክር የጸና ነው ከዚህ በታች እንደምናየው ከተነሳ በኃላ ለብዙዎች ታይቷል::
1. ለኬፋም ታየ
2. በኃላም ለአሥራ ሁለቱ፤
3. ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤
4. ለያዕቆብ
5. ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤
6. ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።
እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።
እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ። አሜን አምነናል!
ሐዋርያው እዚህ ጋር የቀደመውን ህይወቱን ያነሳል ሐዋርያ ልባል የማይገባኝ የቤተክርስቲያን አሳዳጅ ቅዱሳንንም የማስር ነበርኩኝ ይለናል:: ይሄ ሁሉ ግን ወደ ጌታ ለመምጣትና ከሁሉ በላይ ለማገልገል አላገደውም ምክንያቱም አሮጌው ሁሉ አልፏል ሁሉም አዲስ ሆኗል:: ባለፈው ነገራችን እየተወቀስን ያለን ካለን እርሱ አልፏል አሁን ምህረትን ያገኘን ነን:: ይልቁንስ በጠላት ሽንገላ የተሰጠንን ጸጋ እንዳናባክን እንጠንቀቅ:: እኛ ተሻግረናል ሌሎችን የማሻገር አገልግሎት ተሰቶናልና ተነስተን የጠላትን መንደር እናሸብር!! ሃሌሉያ!
ተነስቷል የሚለውን ዝማሬ እጋብዛችኃለሁ::
ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአል
1ኛ ቆሮንቶስ 15: 12-23
ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን፡ ከእናንተ አንዳንዶቹ፡— ትንሣኤ ሙታን የለም፥ እንዴት ይላሉ? ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ
1. ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤
2. ደግሞም፡— ክርስቶስን አስነሥቶታል፤ ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤
3. ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም።
4. ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤
5. ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ።
6. እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ።
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።
አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። አሜን!
1. ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና።
2. ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።
ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው::ወገኖቼ ተስፋ እንደሌላቸው እንዳንሆን ትንሳኤ የሚጠብቀን ነን:: ክርስቶስ ከሙታን በመነሳቱ እኛንም ያስነሳናል ደግሞም የህያው ጌታ አገልጋዮች ነን:: ትንሳኤንና ድልን እናውጃለን:: አሜን!
አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም ይሽራል
1ኛ ቆሮንቶስ 15:24 – 34
በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። አሜን!
ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።
የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤
ስለዚህም እንላለን ሞት ሆይ መውጊያህ የታል?
ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፡— ሁሉ ተገዝቶአል፡ ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። መቼም ሁሉን የሚያስገዛው አይገዛም እርሱም እግዚአብሔር አብ ነው::
ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።
እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው?
አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 34፤ በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ።
ሁሉን ከእግሩ በታች ይረግጣል የኛ እረኛ:: እርሱ ከሁሉም በላይ ነው ዛሬ ከበበን ብለን እውይ የምንለው እርሱ ጋር ሲደርስ እንደ እርጥብ ጠፍር የሚወድቅ ነው:: አሜን!
እየሱስ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው
1ኛ ቆሮንቶስ 15: 35-45
ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል።
ይሄንን ጥያቄ በሁለት እንክፈለው:: የመጀመሪያው እራሱ ትንሳኤ እንዴት ይኖራል የሚሉ ሰዎች ጥያቄ ነው ሰው ከሞተ ሞተ የሚሉ ናቸዉ የመለሰላቸውን እንይ::
አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል።
ሞኝ ብሎ ነው አወቅን የሚሉትን የሚጠራው በአእምሯችን ከተመራን የእግዚአብሔርን ነገር ማወቅ እንደማንችል እኔና እናንተ በደንብ ጠንቅቀን እናውቃለን:: ስለዚህ ፍጥረትን በመመልከት እንኳን ይህን ጥያቄ መመለስ እንደሚቻል ነው ያስቀመጠው:: የእንስት ስጋ እንኳን ይለያያል የዓሳ ከበሬ የበሬው ከበግ እና ለእግዚአብሔር የተለየ አድርጎ ማስነሳት እንዴት ይሳነዋል እያለ ያስረዳል ሐዋርያው:: በሌሎችም በብዙ ማስረጃ::
ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ የመጉዋጋት ጥያቄ ነው:: ምን እንደምንመስል ነው:: መልሱ እንይ:-
ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው። የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ።
ስለዚህ ወገኖቼ ይህንን እናስተውል አሁን በድካም እየዘራን ነው በኃይል እንነሳለን:: እንዲሁ ደግሞ፡— ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ፡ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። እየሱስ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ እንደሆነ እናስተውል ከእርሱም ጋር አብረን የምንሰራ እንደሆንም አንዘንጋ:: አሜን
የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም
1ኛ ቆሮንቶስ 15: 46-58
አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፡— ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።
የማይበሰብሰውን የምንወርስ እኛ እንደምንለወጥ ቃሉ ይነግረናል ይሄ የለበስነው ስጋ የማይበሰብስ ሆኖ ይለወጣል እንጂ በዚህ ድካም በሞላበት ስጋችን መንግስተ ሰማያትን አንወርስም:: ወይም ደግሞ መለከቱ ሲነፋ በህይወት ከሆንን ከመቅጽበት የማይበሰብሰውን እንለብስና እንለወጣለን:: ሃሌሉያ!!
ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፡— ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ፡ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤
አሜን ሞት መዋጥ ብቻ ነው የሚያውቀው ያኔ ግን ይዋጣል፥ የሚወጋበት ሕግ ይወሰዳል ሐጥያትም አይኖርም ፥ ስለዚህ ሞት አይቀማም ፥ አያስጨንቅም ፥ ድልም አይነሳም ፥ ይሸነፋል ደግሞ ላያገግም ለመጨረሻ ጊዜ ይሰናበታል:: ሃሌሉያ!! አሜን! ያ ቀን እንዴት ያለ ቀን ነው ሞትን የምንቀብርበት?! እስከዛሬ ወግተሀል በቃህ!! የሚባልበት ኦ ያ ቀን! የማይበሰብሰውን አካል የምንወርስበት ምን አይነት ቀን! ጌታ ሆይ ተመስገን ፈጽመህ የምትበቀልበት ቀን አለና አመሰግንሀለሁ! አሜን!
ድል መንሳት ተሰቶናል
1ኛ ቆሮንቶስ 15:57-58
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን!
ያለንን ነገር ጠንቅቀን ማወቅ አለብን እርሱም እዚህጋ እንደተጻፈው ድል መንሳት ነው:: የሰጠን ማነው? እራሱ እግዚአብሄር ነው:: ግን ድል ዝም ብሎ ተነስቶ የሚሰጥ ጉዳይ ነው እንዴ? አረ አይደለም ድሉ የመጣው ውጊያ ተደርጎ ነው: : እየሱስ ስሙ ይባረክና እዳችንን ሁሉ በመስቀል ተሸክሞ ሞቶ ከሙታንም ድል ነስቶ ድለተነሳ ነው ይሄ ድል የመጣው:: ይሄስ ድል ለኔ እንደሆነ በምን አውቃለሁ? ብንል አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ:: አትዮጵያ ጣልያንን ስታሸንፍ ነበርን እንዴ? ዛሬ ግን ለማንም ባርያ አልሆንም እያልን እራሳችንን እዛ ድል ውስጥ አድርገን እንቆጥር የለም እንዴ? ታድያ እኛ እኮ ዛሬ የሰማያዊዉ መንግስት አካል ነን:: ልንፎክርና እራሳችንን እዛ ውስጥ ማየት ግድ ይላል እርሱአባታችን እኛም ደግሞ ልጆች ነን::እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል እየሰማንአለን አሁን እምነታችንም እየጨመረ ነው:: ስለዚህ አዋጅን እናውጃለን:-
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን!
ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን 1. አውቃችኋልና 2. የምትደላደሉ፥ 3. የማትነቃነቁም፥ 4. የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።
ምንም ሳንሰራ በማመን ብቻ የተሰጠንን ድል እያጣጣምን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ እንሂድ እያለን ነው:: ስለዚህ ድላችንን አውቀናል፥ እንጸናለን፥ አንነቃነቅም የጌታም ስራ ይበዛልናል:: ጠላት በየጊዜው መቶ መሰረታችንን እንድንቆፍር አያድርገን:: ኢትዮጵያዊ አይደለሽም ብሎ ለሚከራከራችሁ ማስረጃችሁ ምንድነው? ማስረጃው ከመብዛቱ የተነሳ መሳቅ አይቀናንም ብላችሁ ነው? እንዲሁ ርግጥ ያለእን ማንነታችንን በክርስቶስ እንያዝ ድላችንንም እናውጅ::
ምዕራፍ 16
የመጨረሻ ምክር
1ኛ ቆሮንቶስ 16:1-24
በመዝጊያው በዚህ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚመክረን
1. ንቁ
2. በሃይማኖት ቁሙ፥
3. ጎልምሱ
4. ጠንክሩ እናም
5. ሁሉ በፍቅር ይሁን በእናንተ ዘንድ ይለናል:::
ስለዚህ ወገኖች የእኛ ስርና መሰረት በፍቅር የጸና ይሁን በፍቅርም ላይ እንደግ ፥ እንጠንክር::
ሌላው የሚመክረው ነገር ለቅዱሳን ገንዘብን ስለ ማዋጣት፥ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።
ይህንን እኛም ልንከተለውና ቅዱሳን ችግር ሲገጥማቸው መርዳትን እናብዛ::
በማጠቃለያ እንዲህ ይላል:-
ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን።
ጌታችን ሆይ፥ ና። አሜን ቶሎ ና! ማራናታ!
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። አሜን!

May God of all the garaces and powers bless you abundantly in Jesus Name!
LikeLike
በብዙ ተባረክ ለመረዳት ቀለል ያለና ጠቃም ነዉ
LikeLike
ጥሩ ማብራሪያ እና ቀለል ያለ አገላለፅ ስለሆና ለጥናትና ለመረዳት እጅግ በጣም ጥሩ ነው ጌታ ይባርካችሁ
LikeLike
1 ቆሮንቶስ ለማ ነዉ የተፃፈው
LikeLike
ተባረክ!!በጣም አስተማሪ ነው ።
LikeLike