መግቢያ
የዚህ መጽሐፍ ዓላማ
የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ጳውሎስ ነው
1. ክርስትናንና አይሁዳዊነትን እየቀላቀሉ ስለነበር
2. ከእምነት በምን አይነት ፍጥንት እንደራቁ ስለተገነዘበ
3. ፀጋን/ጽድቅን ከስራ ጋር በመቀላቀላቸው
4. መዳን በፀጋ መሆኑን ሊያሳያቸው
ምዕራፍ 1
እኔን የጠራ ጌታ ነው
ወደ ገላትያ 1: 1-2፤
በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤
እዚህ ጋር ጳውሎስ ሊያሳያቸው የፈለገው ማን እንደላከው ነው:: በእግዚአብሔር ነው ሐዋርያ የሆንኩት እርሱ ነው የጠራና የላከኝ እያላችው ነው:: ለምን ብለን ስንል ባለው ስልጣን መሰረት የሚናገረውን ሁሉ ከዚህ በኃላ ከእግዚአብሔር የተላከ መልእክት አድርገው እንዲወስዱት እንጂ ይህ የጳውሎስ ሀሳብ ነው እንዳይሉ ነው::
እርሱ ብቻም አይደለም አብረውትም የሚያገለግሉ ወንድሞች ሁሉ ያመኑበትን ነገር እየጻፈላቸው እንደሆነ እየነገራቸው ነው:: ስለዚህ ብትቀበሉ ይሻላል መልክታችንን ብሎ ነው የሚላቸው::
ከዚህ የማየው ነገር;- እኔን የጠራ ጌታ እንደሆነና ዋጋ የክፈለና የራሱ ያደረገኝን ጌታን አገልግለውና ለእርሱም የምገዛ፤ ደስ የማሰኘው ልጅ መሆን ነው የእኔ ድርሻ:: ስሙ ይባረክ:: አሜን!
ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ
ወደ ገላትያ 1:3-5
ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
1. ”ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ”
እኔ እኮ ብዙ አተኩር የነበረው በመዳኔ ላይ ከሲኦል ማምለጤን ነው ለካስ ከዛ በፊት ያመለጥኩት ከዝች ክፉ ዓለምም ነው:: ለዚህም ነው ለካ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። የሚለው! በሌላ ስፍራም በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ለዚህ አለቃ ነበር ስታዘዝ የኖርኩት አሁን ግን በእኔ ላይ አይሰለጥንም ከእርሱ አገዛዝ ድኛለሁ አለቃዬ አዳኜ ነው:: አሜን!!
2. ”እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ”
እየሱስ እንደማን ፈቃድ ነው ራሱን የሰጠው? እንደ አባታችን ፈቃድ እርሱ ነበር ያቀደው መዳናችንን እናም ሳይሳሳ አንድ ልጁን የሰጠኝ::
ሰጠኝ ብዬ ስል እንደው ቀለል አለብኝ የሰጠኝ እኮ እየሱስ ህይወቱን ነው እርሱም በመስቀል ሞት ለመሞት! ለመሰቃየት! ትንሽ ጻድቅነት ቢኖረኝ እንኳን እሺ ግን እልም ያልኩኝ ሐጥያተኛ ለሆንኩት ለእኔ?! ዋዉ! ቃሉ እኮ በትክክል ቁጭ አድርጎታል በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ የሚለው! አዎ ሙታን ነበርኩ ዛሬ ግን ያ ሁሉ ነገር አልፎ አዲስ ፍጥረት ሆኛለሁ በህይወት አለሁ ከወይኑ ግንድ ላይ ተጣብቄ:: ሃሌሉያ!
3. ”ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” ሌላ ምን ይባላል ውለታው ብዙ ነው:: ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን። አሜን!!
በክርስቶስ ጸጋ ተጠርተናል
ወደ ገላትያ 1: 6፤
በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤
1. በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ
በቃሉ እንደሚለው ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። በሌላም ስፍራ ላይ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥ ክብር የጎደለኝ ነበርኩ በዚህ ጸጋ ግን ተጠራሁኝ፤ ጸደኩኝ ፤ የእግዚአብሔርም ወገን ሆንኩኝ ይህንንም ጸጋ ተቀበልኩኝ:: ይህም ጸጋ ዓለማዊ ምኞትን ሁሉ ገሸሽ አድርጌ የተባረከውን ጌታዬን እንድጠብቅ ያደርገኛል::
2. ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤
ይህ ልዩ ወንጌል ምንድነው ከእየሱስ ጸጋ ውጪ የሆነ ነው ማለት ነው:: ይቅርብኝ ልዩ ወንጌል! እኔ የያዝኩት እውነት በአዳም ሐጥያትና ሞት ገባ በእየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ በጸጋ መዳን ወደ ህይወት መሻገር ሆነ አሜን! በትምህርት ንፋስ አልፍገመገምም፤ እቆማለሁ በህይወት፤ በእውነቱና በመንገዴ በእየሱስ ላይ የምሰራው የለም ለእኔ የሰንበት እረፍት ነው የቀረልኝ ፤ ወደ እረፍቴ ገብቻለሁ እኔ አይደለሁም ለማሸነፍ የምጥረው ድል አድርጎ እራሱ ሰርቶ ሰቶኛል ቆሜ ድሌን አጣጥማለሁ:: ክብር ለጌታዬ ጸጋውን ለሰጠኝ ይሁን ከከፍታዬ አልወርድም::ሃሌሉያ!! አሜን!
ወንጌል አንድ ነው
ወደ ገላትያ 1:7-10
እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ።
ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።
አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።
ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።
የተቀበልነው ወንጌል አንድ ነው እርሱም በጸጋ መዳናችን ነው:: በስራ አይደለም ደግሞም የምንጨምርበት ነገር የለም ተጠናቋል:: ስለተሻገርን መዳን ቀሎ አይታየን አንዳንዴ ለሰዎች ስትመሰክሩ ነው ከባድነቱ የሚታየው ሰው እንዴት ይሄ መዳን አይታየውም አትሉም? የዚህ ዓለም ገዢ አይምሮን ያሳውራል ያንን ሁሉ አልፈን መተን ደግሞ አሁን መወናበድ የለብንም የዳነው በጸጋ ነው የምንጨምርበት ከእንትና የተሻልኩ ነኝ የምንልበት ምንም ማማሀኛ የለም የማይገባን ነበርን ከትልቅ ምህረቱ የተነሳ ቀድሶ ወደ ራሱ አስጠጋን::
ከዚህ እውነት ውጪ ሰዎችን ለማሳመንም ሆነ ለአስተሳሰባችን እንዲመች አድርገን ቃሉን አናጣምም ቃሉ እዚህ ጋር የሚለው እንደዚህ አይነቱ የተረገመ ይሁን ነው::
ስለዚህ ከሰው ይልቅ አምላካችንንና አባታችንን ደስ ማሰኘት ይሻላል:: የምወደው ልጄ ይህ ነው በእርሱ ደስ የሚለኝ ብሎ አንድ ጊዜ በልጁ ደስ ተሰኝቷል:: የሐጥያት ዋጋ ሙሉው ተከፍሏል እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ልጁን መልበስ ነው:: እርሱ ውስጥ ወስዶ በአብ ቀኝ የሰወረንም ለዚሁ ነው ስራ አበቃ እዳ ሁሉ ተከፈለ ብሎ ደስ አለው አብ ቤተሰቡ ሁሉ ትሰብስቦ ሲያይ በልጁ ውስጥ አለቀ! ሌላ ስራ አያስፈልግም አትናወጡ ቅዱሳን!
ወንጌል የሚገለጥ ነው
ወደ ገላትያ 1: 11-12
ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።
1. ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤
እኔ ከሰው ተቀብዬ አይደለም ወንጌልን የሰበኩት ከራሱ ከጠሪው ነው የተማርኩትናም የሰበኩት እያለ ነው:: መለኮታዊ ነው ጥሪዬ ድምጹን ሰምቼ፤ አይኔም ከክብሩ የተነሳ ታውሮ፤ ሰዎችን ያሳደድኩ መስሎኝ ፈጣሪዬን ሳሳድድ የነበርኩትን ራርቶ በህይወት አኖረኝና ይህንን ወንጌል ሰጠኝ እያለን ነው:: ዛሬም ጥሪ አለ፤ ዛሬም መላክ አለ፤ ዛሬም መገለጥ አለ:: ጌታ በስራ ላይ ነው::
2. ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም::
ይሄ ቃል በጣም ዋጋ አለው ለእኔ ምክንያቱም ጳውሎስ ወንጌልን የተማረው ከራሱ ከእየሱስ ነው:: ወንጌል ሁልጊዜ አዲስ ነው፤ የሚሰራ ነው በሐዋርያት ብቻ ብሎ ነገር የለም:: ዛሬም ለእኔ ወንጌሉን ያበራልኝ በመንፈሱ ነው:: ጸጋ ቢሆን ዛሬ ይሰጣል፤ ቃሉን መግለጥ ቢሆን ዛሬ ይሰጣል ምክንያቱም እየሱስ በስራ ላይ ነው ሙሽራይቱን ያስውባል፤ አካሉንም አገልጋዮችን ልኮ ይገነባል:: ጳውሎስ እንዴት እንደተጠራ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል በሐዋርያት ስራ ላይ
”ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።”
ዛሬም ወንጌል አልተለወጠም ይህንን የከበረ ቃል ይዘን እንወጣለን:: አሜን
ወንጌል በአሳዳጁ ሲሰበክ
ወደ ገላትያ 1: 13-24
ከዚህ በፊት እንዳየነው ጳውሎስ ከጌታ እንደተቀበለና እንደተማረ አይተናል:: እስኪ እንየው የእርሱ ትኩረት የነበረውን ከደማስቆ መንገድ በፊት:-
1. በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤
2. የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥
3. ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።
ከደማስቆ መንገድ በኃላ ደግሞ:-
1. በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ ለየኝ በጸጋውም ጠራኝ
2. እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥
3. ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥
4. ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም።
5. ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።
6. ነገር ግን፡— ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል፡ ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።
ይህን ሁሉ ነገር የሚነግራቸው መግቢያው ላይ ለጠቀሰው ሀሳብ ማጠናከሪያ ነው:: ሐዋርያ መሆኑን በፊት ከተጠሩት ሐዋርያት እንኳን ሁለቱን ብቻ እንዳገኘ እነሱንም ያገኘው ወድያው እንዳልሆንና ለተገለጠለግ እውነት ወድያው ምላሽ ሰቶ እንዳገለገለ ነው የሚያስረግጠው ስለዚህ እኔ የነገርኳችሁ ወይም ያስተማርኳችሁ ወንጌል እውነት ነውና ጽኑ እያለ ለማጠናከሪያ ነው የሚነግራቸው የህይወቱን ታሪክ::
ከዚህ የህይወት ጉዞ ያየሁት:-
1. በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ እንደለየኝ በጸጋውም እንደጠራኝ
2. ከስጋና ደም ጋር ሳልማከር መታዘዝን
3. ለእግዚአብሔር ስም መመስገን ምክንያት መሆንን እንዳለብኝ አይቻለሁኝ::
ጌታሆይ ተመስገን ስለመረጥከኝ ደግሞም እርዳኝ እንድታዘዝ የመታዘዝን መንፈስ በእኔ ውስጥ አድርግ:: በእርምጃዬም ሁሉ ለአንተ ምስጋና ይምጣ እንጂ ስምህ ከእኔ የተነሳ አይሰደብ:: በእየሱስ ስም! አሜን!
ምዕራፍ 2
በሐሰተኞች አለመነዳት
ወደ ገላትያ 2: 1-10
ከዚህ በፊት እንዳየነው ጳውሎስ መልእክቱ ለገላትያ ሰዎች ወንጌል ብቻውን ነው የሚያድነው እንጂ ካልተገረዛችሁና የሙሴን ህግ ካልጠበቃችሁ የሚሉትን አትስሙ ነው የሚለው እዚህም ክፍል ላይ ምክንያቱን እንይ::
ከ14 ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤ (መጀመሪያ ሄዶ የነበረው ከዳነ ከ3 ዓመት በኃላ እንደነበር አይተናል)
እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤
ለምን አህዛብ የሆነውን ቲቶን ይዞ ሄደ? ስለመገረዝ አንድ እልባት ለመስጠት ፈልጎ ነው:: ታሪኩን በሐዋርያት ስራ 15 ላይ እናገኘዋለን:: መሪዎቹ አላስገደዱትም እንዲገረዝ:: አትሳቱ አያስፈልግም እያላቸው ነው::
ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ።
ጳውሎስ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር ሾልከው የገቡ ሐሰተኛ ወንድሞች ይህንን እንዳደረጉ::ስለዚህ መሪዎች የሆኑትም እጃቸውን ሰጡኝ ቀጥል ብለው እንጂ አልተቃወሙኝም እያለ ነው::
ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ።
የሰጡት ትዕዛዝ አንድ ነው የሙሴን ህግ መጠበቅ ወይም መገረዝ ሳይሆን እነዚህ ከውጪ የሚደረጉ ነገሮች ናቸውና የውስጥ የሆነውን የፍቅርን አገልግሎት እሱም ደሆችን ማሰብ::
ለእኛም ይህ ነው የጌታ ትዕዛዝ በሄድንበት ሁሉ ደሀን እናስብ እናም አርነታችንን አናስነጥቅ::
ለእውነት እንቁም
ወደ ገላትያ 2: 11-14
ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና። አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን፡— አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት።
እዚህጋ የምንመለከተው ጴጥሮስ አንጾኪያ ያለችውን ቤተክርስቲያን ሊጎበኝ መቶ እያለ ስለተፈጠረው ነገር ነው የሚነግረን:: ጴጥሮስ ከእየሩሳሌም ወገኖች ሳይመጡ በፊት ከአህዛብ ጋር ይበላ ነበር ሰዎቹ ከመጡ በኃላ ግን ማስመሰል ጀመረ እንደማይበላና የሙሴን ህግ እንደሚጠብቅ:: በዚህ ጊዜ ነበር ጳውሎስ ትናንት ሌላ ዛሬ ሌላ ሲሆንበት በሁሉ ፊት የወቀሰው:: የጥልን ግድግዳ አፍርሷል ብለን ታድያ እንዴት መስበክ ይቻላል? እየሱስ እኮ ቀርበው ላሉትም ሰላምን ርቀን ላለነውም ሰላምን ነው የሰበከውና አንድ ጊዜ የጥልን ግድግዳ አፍርሶ ሁለቱን አንድ አድርጏል በሰማይና በምድርም ያለውን ከአባቱ ጋር አስታርቋል:: ሊወቀስ ይገባው ነበር ጴጥሮስ እንደመሪ ይህንን ሲያይ እንደዚህ እነዚያን ሲያይ እንደዛ መሆን አልነበረበትም ባይ ነው ጳውሎስ:: እንደዚህ ደግሞ መኖር ከፈለክ አህዛብም እንደራሳቸው ህግ ይኑርዋ የእኛን ህግ አንጫንባቸው ነው የሚለው ይሄ ግን ቤተክርስቲያንን ወጥ የክርስቶስ አካል አያደርጋትም ስለዚህ ወደ አንዱ እንምጣ ሁሉ አንድ ነው መለያየት የለም::
ስለዚህ የተማርኩት ነገር ለገባኝ እውነት በየትኛውም አጋጣሚ ጸንቶ መኖር እናም ህያው የወንጌል ምስክር መሆን አለብኝ::
በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ጸድቀናል
ወደ ገላትያ 2: 15-16
እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤ ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።
1. እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤
የሚገርመው ነገር ከአይሁድ ውጪ ያለውን ሰው ሁሉ አይሁዶች ሐጥያተኛ ብለው ነው የሚጠሩት:: ለዚህም ነው እዚህጋ ጳውሎስ ትምክህት ቢያስፈልግ አለኝ አይሁድ ነኝ እንጂ አህዛብ አይደለሁም ይልና ሲቀጥል ያፈርሰዋል ምንም እንደማይጠቅም::
2. ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥
የምንጸድቀው በአንድና አንድ ነገር በማመን ብቻ ነው እርሱም በክርስቶስ እንጂ የህግንማ ስራ እኛም ትተነዋል የሙሴን ህግማ በመጠበቅ የሚዳን ቢሆንማ እኮ የሚጠብቅ ነበረ ግን ህግ ከመክሰስ ያለፈ የማጽደቅን ስራ አይሰራም:: እየተከታተለ ስራውን ይሰራ ነበር በትጋት እሱም መክሰሱን ያለ ርህራሄ እዚህ ጋር ልለፍ ቀላል ነገር ነው የተሰራውወይም ትላንትና በርትቶ ነበር ብሎ እንኳን ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባው ነገር የለም ስለዚህ እግዚአብሔር እርሱን አሮጌ አድርጎ አዲስን መንገድ ከፈተልን ሁሉን እኩል አድርጎ በጸጋ የሰውን ልጅ ሁሉ አጸደቀ:: አሜን!
3. እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።
ስለዚህ ያመነው በጽድቅ ስራ ሳይሆን በክርስቶድ ነው ያንን መንገድ በደንብ ሄጄበታለሁ አድካሚ ነው የሚሻለው አሁን ያስተዋወኳችሁን እውነት መያዝ ነው እሱም በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ መዳን::
ጌታ ይርዳን በጸጋ ጀምረን የህግ ምሁራን እንዳንሆን አይናችንና ልባችን ሁልጊዜ በጸጋው ላይ ይሁን አንቀላቅል ለዚህ ነው ዕለት ዕለት እራሳችንን መስበክና ማንቃት ያለብን ድንገት እህግ ሰፈር እንዳንገኝ አስተሳሰባችንን ሁሉ እንለውጥ ከተመካንም በእየሱስ ስራ ላይ ብቻ ይሁን::
ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖራለሁ
ወደ ገላትያ 2: 17-19
ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና። እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና።
በክርስቶስ የጸደቅን እኛ በጸጋ ድነናል ብለን ስንል እኮ ሐጥያትን ለማድረግ ላይሰንስ አግኝተናል ለማለት አይደለም:: እንዲያውም የህይወት አኗኗራችን ደረጃው ጨምሯል እያልን ነው:: እኛ የጽድቅ አገልጋዮች ነን:: ቃሉ በሌላ ስፍራም እንደሚል ”ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።” በክርስቶስ ያገኘነው ማንነት ይሄ ነው የጽድቅ ዘር በእኛ አለ::
ስለዚህ ህግ እየተከታተለ አይከሰኝም የእኔ ደረጃ ከፍ ብሏል ከጸጋ እንጂ ከህግ በታች አይደለሁም:: እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ምኞት ሁሉ የምክድበትን ጸጋ በእኔ አስቀምጧልና ብቃት አለኝ ጸጋው በዝቶልኛል የዓለም ነገር ለኔ ሞኝነት እንዲሆን አድርጏል ጸጋው::
ስለዚህ እኔ ህያው ሆኜ ለእግዚአብሔር እኖራለሁ እንጂ ለህግማ ሞቻለሁ:: የሞተ ይነሳል እንዴ?! አረ በፍጹም! ለህግ አልነሳም ያለሁበት ተመችቶኛል ከፍታ በጌታ ጸጋ! አሜን!
ከወጣሁበት ከፍታዬ አልወርድም! የጌታ ስም ይባረክ በእኔ ውስጥ ጽድቅን ጨምሮ ከህግ የበላይ ላደረገኝ!
ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል
ወደ ገላትያ 2:20-21
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።
እየሱስ አንድ ነገር አለ ዕለት ዕለት መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ ለኔ ሊሆን አይገባውም ሲል እዚህጋ ጳውሎስም ያጠናክረዋል አሁን እየተካሄደ እንዳለ አድርጎ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ ይላል:: መቼ? አሁን ወይም ሁልጊዜ::
መስቀል ማለት የምንገኝበት ሁኔታ/ኮንድሽን ማለት ነው እርሱም ለዓለም፤ ለራሳችንና ለሐጥያት ሞተናል:: ሕያው ሆነን የምንኖረው እኛ ሳንሆን ህይወቱን የለወጠን እየሱስ ነው በእኛ የሚኖረው:: አሜን!
ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እንደሚል ቃሉ መውደድና መስጠት አብረው የሚሄዱ ናቸው ወደደንና እራሱን ስለእኛ ሰጠ:: ስለዚህ ለታደገኝ ጌታ ብኖርለትና ህይወቴን ኑርበት ብዬ ፍቅሬን እኔስ በመስጠት ብገልጠው?! ይገባዋል!
እርሱ ስለእኔ እንደበግ በሸላቾቹ ፊት ዝም ብሏል ሲበዛበት ይህች ጽዋ ትለፍ አለ ግን የእኔ ሳይሆን ያንተ ፈቃድ ይሁን ብሎ ስለእኔ ራሱን ሰጠ መድህኔ:: ታድያ ብኖርለት ምን ይገርማል? እኖራለሁኝ ለእርሱ ክብር ዓለምን፤ ሐጥያትን እራሴንም ክጄዋለሁ እኔ አሁን የምኖረው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ብቻ ነው። አሜን!
የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ እንዲህ ሊታደገኝ ተንገላቶ እያለ እየሱስ እናም ሕግን አላቆመውም ምክንያቱም አልችልም ሕግን ጠብቄ መጽደቅ የከፈለውንም የመስቀል ዋጋ ከንቱ አላደርግም:: ላዳነኝ በድንቅ አሰራሩ ለጠራኝ ጌታ ክብር ይሁን::
ምዕራፍ 3
ለእውነት እንታዘዝ
ወደ ገላትያ 3:1-5
የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጸማላችሁን? በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን? እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው?
የገላትያ ሰዎች እየሱስ በፊታቸው እንደተሰቀለ ያህል ነበር ወንጌል የገባቸው የነበረው ሐሰተኛ አስተማሪዎች ገብተው ዓይናቸውን ከመስቀሉ ላይ እስኪያስነሷቸው ድረስ:: ይህ ሲሆን ግን አላስተዋሉም ለእውነት መታዘዝ ማቆማቸውን:: በህግ ሳይሆን በእምነት ነበር የመንፈስ ቅዱስን ስራ ሁሉ ያዩትና የተለማመዱት የነበረው:: ዛሬ ታድያ ምን ተፈጠረ በመንፈስ ጀምራችሁ በስጋ የምትፈጽሙት እያለ ነው አወዳደቃቸውን የሚያሳያቸው::
ወደኛ ስንመለስ ይህ ሁሉ ለትምህርታችን ነውና እንዴት እንገኛለን? በእምነት ወይስ በስጋ አስተሳሰብ? እዚህጋ የህግን ስራ የስጋ ነገር እንደሆነ ጳውሎስ እያቀያየረ ይጠቀምበታል:: ለስጋውያን መንፈሳዊ ነገር ሞኝነት ነው ለእኛ ግን መንፈሳውያን ለሆንን ህይወት ነው:: ስንቶቹን አገልጋዮችን በዚህ ምክንያት አተን ይሆን? መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን የሚሰራው በእምነት እንጂ በስራ አይደለምና እንንቃ:: ስለዚህ የመስቀሉን ስራ በማመንና ዓይናችንን በርሱ ላይ በማድረግ ይበቃናል:: ደህንነታችን አይቅለልብን የእየሱስን ህይወት አስከፍሏልና በእምነት እንጏዝ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!
በእምነት መጽደቅ
ወደ ገላትያ 3: 6-9
እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።
እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፡— በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ፡ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።
የሚገርመው አብርሐም የብሉይ ኪዳን ሰው ሆኖ ሳለ ወንጌል ደርሶት አምኖ ነበር:: አይገርምም?! እየሱስ እኮ ገና አልመጣም፤ አላየውም፤ አልተጻፈለት እንደኛ ግን በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እኛ ግን ዛሬ በዛ ኪዳን ውስጥ እያለን ሌላ ያስመኘናል እሱም የህግ ባርነት!
አይሁድ እኛ የአብርሃም ልጆች ነን ብለው ሲሉ የነበረው ለእየሱስ ይህን ማለታቸው ነው:: ለማንም አልተገዛንም ብለው የሚመኩት:: ግን የህይወትን ራስ አብርሐም ከሩቅ አይቶ ያመነውን ጌታ ማየት አልቻሉም አጠገባቸው ሲመላለስ አላወቁትም ስለዚህም አሳልፈው ሰጡት::
ለእኛ ግን ለምናምን የአብርሃም በረከት በክርስቶስ ደረሰን እናም ”በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ፡” የተባለው ደረሰንና ዛሬ እየኖርንበት ነው::
ስለዚህ አሁን ቃሉ እንደሚል ”እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። ” ይለናል እኛም አሜን እንላለን!
ጻድቅ በእምነት ይኖራል
ወደ ገላትያ 3:10-12
ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግም ከእምነት አይደለም፡ ነገር ግን፡— የሚያደርገው ይኖርበታል፡ ተብሎአል።
ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ ሲባል አታነክሱ እያለ ነው ጳውሎስ ከእምነት ወይም ከህግ አንዱን ምረጡ እንጂ ሁሉቱንም ይዞ መሄድ አይቻልም ብሎ ሲያበቃ ፍጻሜውንም ያሳየናል:: ህግን ከተከትልን በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ኑሮአችን ከእርግማን በታች መሆን ነው ማለት ነው:: በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ማንም መፈጸም ስላልቻለ አይደል እንዴ ጌታ የመጣው?! ስለዚህ ፊታችንን ወደ እምነት እናዙር ጠላት አብዝቶ ፊታችንን ወደ ሚከለክልበት አቅጣጫ ማለት ነው:: ከእምነት ስንርቅ ለጠላት ቀላል ኢላማው ነን የማያልቅ የቤት ስራ ሲያሰራን ይኖራል ያልበቃን እንደሆንን ሁልጊዜ በማሳየት:: ዛሬም ነገም እየተመላለስን ማሳረም ነው ማለት ነው ስራችን ፈተናው ‘open book’ ሆኖ ሁሉም ይለፍ በክርስቶስ በኩል ተብሎ እያለ እኛ ግን ጊዜና ጉልበት ለማያስፈልግ ነገር እያባከንን እንዳንገኝ ብቻ:: እንንቃ!!!!
ጎበዝ እንንቃ የተባልነው እኮ ጻድቅ በእምነት ይኖራል እንጂ በስራ አይደለም:: መቼም ይህን ብዬ ስል እንደው እንደፈለግን በሐጥያት እንመላለስ ማለቴ እንዳልሆነ ይሰመርበት እንደዛማ ከሆነ ጭርሱን በደህንነት ሰፈርም አላለፍን ማለት ነው ክርስቶስን መምሰል ግድ ይላል:: በአእምሯችን መታደስ እንለወጥ እንጂ የሆነ ነገር achieve ለማድረግ አንጣር እንረጋጋ እዳችን ተሰርዟል ነጻ ነን ማመን ነው የሚጠበቅብን:: እግዚአብሔር መዳንን ቀላል ስላደረገው የዚህ ዓለም ጥበበኞች ከበዳቸው:: እኛ ግን መዳን በእምነት እንደሆነ ገብቶናል:: አናሻሽለውም አሜን እንጂ! እየሱስ ከህግ እርግማን ዋጅቶናል!! አሜን!
ከሕግ እርግማን ክርስቶስ ዋጀን
ወደ ገላትያ 3: 13-14
በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።
ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ እርሱ ራሱን የሰጠው እና የተንገላታው እኛ ከዚህ የሕግ እርግማን ነፃ እንድንሆን ነው:: እርሱ ሐጥያትን የማያውቅ ንፁ ሆኖ ሳለ በእንጨት ላይ በተሰቀለ ጊዜ ግን እርሱም እርግማን ሆኖ ከእኛ ጋር ተካፍሎ ነፃ አወጣን:: ሃሌሉያ! አሜን!
ሕግ የመጣው የእግዚአብሔርን የቅድስና ልክና ከእኛ የሚጠበቀውን ሊያሳየንና አዳኝ እንደሚያስፈልገን ለማሳየት ነው:: ከዚህ በፊት እንዳልኩት ሕግ የተሾመበት ስራው እየተከታተለ ስህተትን ማሳየት ነው እሱንም በትጋት ሰርቷል::
ሕግ የመጣው በሙሴ ነው የመጣውም ለእስራኤላውያን እንጂ ለኔ ለአሕዛብዋ አይደለም:: እኔ ግን እንደአሕዛብ የእግዚአብሔርን የቅድስና ልክ (standard) መድረስ ስላልቻልኩ ከቁጣ በታች ተዘግቶብኝ ነበር:: አብርሐም የኖረው ከሕግ በፊት ነበር:: ስለዚህም አብርሐም ወንጌል ተሰበከለት እርሱም ተቀበለና ጽድቅ ሆኖ የተቆጠረለት:: የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ እኔም ይህንን የመዳን ወንጌል ስቀበል በእምነት የአብርሀም በረከት በእየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ለአሕዛብዋ ደረሰልኝ:: መድረስ ያልቻልኩትን ያንን የቅድስና ከፍታ በእየሱስ በማመን የእርሱ ጽድቅ ለኔ ተቆጥሮ ይህንን ሰማያዊ መንግስት ተቀላቀልኩኝ:: ዛሬ በስራዬ እንደማላስደስተው ያወኩኝ በጸጋው የዳንኩኝ ልጅ ነኝ:: አሜን!
በተስፋ ቃል እግዚአብሔር ርስት ሰጥቶአል
ወደ ገላትያ 3: 15-20
ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፡— ለዘሮቹም፡ አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፡— ለዘርህም፡ ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም። ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
ሕግ ምንድር ነው? መልሱ:-
ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ:: ስለዚህ ሕግ መዳረሻ ነው ማለት ነው ዘሩ እስኪመጣ::
ይህ ዘር ማነው?
ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፡— ለዘሮቹም፡ አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፡— ለዘርህም፡ ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። አሜን ሕግ ስራው ጨርሶ ተሰናብቷል የተጠበቀው ስለመጣ እርሱም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መካከለኛው አምላክ ብቻ ሳይሆን እንደ እኛው ሰው ሆኖ የኖረው:: ስለዚህም ቃሉ እንደሚል መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም ለሰው ብቻ አይደለም ወይም ለእግዚአብሔር ነገር ግን ሁለቱንም ያማከለ መካከለኛ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል አለ፤ ሁለቱን ያስታረቀ፤ የጥልን ግድግዳ ያፈረሰ፤ ዛሬም የሚማልድ ሊቀ ካህን አለን በሰማይ:: አሜን!
ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።
ስለዚህ ርስታችንን የምንወርሰው በሕግ ሳይሆን በተስፋ ቃል ነው ያም የተስፋ ቃል ለአብርሃም ተስቷል ለእኛም ለምናምን ዛሬ ወደ እኛ በክርስቶስ በዘሩ በኩል ደርሶልናል::
ከሞግዚት በታች አይደለንም
ወደ ገላትያ 3:21-25
እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል። እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር። እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤ እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም።
እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማል? አረ በፍጹም:: የጽድቅ መንገዱ እኔ አይደለሁም ስራዬ መክሰስ ብቻ ነው ይልቁንስ ከሐጥያት በታች ከመዘጋት ማምለጫው መንገድ መቶልናል::
በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤ እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። መሆንም አያስፈልግም ወላጃችን ክርስቶስ መቶልናልና ሞግዚት አያስፈልገንም::
በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ
ወደ ገላትያ 3: 26-29
በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።
ማመን ብቻ ነው ከኔ የተጠየቀው ልክ አብረሐም እንዳደረገው አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት:: እኔም በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን ልጅ መሆን ተሰቶኛል:: ስለዚህም የተስፋው ቃል ወራሽ ነኝ::
ከላይ እንዳየነው የሕግ ነገር የሚያዋጣ አይደለም ደግሞም የራስ ስራ እዚህ ግባ አይባልም በቅዱሱ በእግዚአብሔር ፊት:: ስለዚህ መፍትሄ ብሎ የሰጠኝን ይህንን በክርስቶስ በማመን ልጁ መሆንን በሙሉ ልቤ ተቀብዬ ፍሬ እያፈራሁ እኖራለሁ:: ሞግዚት ከእንግዲህ ወዲህ አያስፈልገኝም:
በሞትና ትንሳኤው አምኛለሁ በመሆኑም እርሱን ለብሻለሁ:: ለዚህ ነው ሰውን ሁሉ በክርስቶስ አውቃለሁ የሚለው ቃሉ ክርስቶስን ገልጠን ከስር ያለውን ማንነት አንይ እራሳችንንም አናሳይ ደግሞስ ምን ለማግኘት ወይም ማንን ደስ ለማሰኘት? ጠላትን ወይስ ጌታን? የእኛ ማንነት በእርሱ ውስጥ ተሸሽጏል ይህ የሆንው እኮ እኔ በራሴ ማድረግ ስላልቻልኩ አይደል? በክርስቶስ እየሱስ ሁሉ አንድ ነው የሚለን እኮ ይህንን ጻድቅ የሆነ ጌታ ስለለበስነው ነው:: – አይሁዳዊ ወይም የግሪክ – ባሪያ ወይም ጨዋ – ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና:: ሰውን ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ እንወቅ:: ልዩነት ሁሉ ጠፍቷል ሁሉ አንድ ነው::
እንግዲያስ በክርስቶስ ከሆንን የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ ይለናል ቃሉ እኛም አሜን እንላለን::
ምዕራፍ 4
የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ባሪያ አይደለሁም
ወደ ገላትያ 4:1-7
ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥ 2፤ ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። 3፤ እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤ 4፤ ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 5፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። 6፤ ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። 7፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።
በእኛ ላይ ጠባቂና መጋቢ ሞግዚታችን ሕግ ነበር:: ነገር ግን የሰው ልጅን ለማዳን እግዚአብሔር ቀጠሮን ቀጥሮ ስለነበረ ያም ጊዜ እስኪደርስ ድረስ የሰው ዘር ሁሉ ባሪያ ሆኖ ነበር::
ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ምን አደረገ?
ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤
ለምን ላከልን?
እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ እና
ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ።
ሕግን አሰናበተው እንዳይገዛን ልጅ ናችሁ ብሎ ሻረው ከእኛ ላይ::
ልጆችስ ከሆንን በኃላ?
እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። አሜን! በእኔ ውስጥ አባ አባት ብሎ የሚጮህ መንፈስ ተልኮ በስራ ላይ አለ:: የተላከው መንፈስ ልጅ መሆኔን ይመሰክርልኛል እኔ ውስጥ ሆኖ የማንንም ማረጋገጫ አልፈልግም!
ስለዚህ?!
ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነኝ እንጂ ባሪያ አይደለሁም፤
ልጅ መሆኔ የሚሰጠኝ ጥቅም ምንድነው ቢባል:-
ልጅም ከሆንኩ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነኝ። አሜን! ልጅ መሆኔ እውን ነውና መውረስ ደግሞ በመወለድ የሚመጣ ጥቅሜ ነው ::
በእግዚአብሔር ታውቄያለሁ
ወደ ገላትያ 4: 8-9
8፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ 9፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?
እውነት ነው የቀደመው ህይወት እርሱን ሳናውቅ ተመላለስን አምላክም ላልሆነው ፍጡር ሁሉ ሰገድን ለዚህም ዓለም ገዢ ተገዛንለት እንደውደደም ባርያ አድርጎን ህይወታችንን መራው::
አሁን ግን ያ ባርነት አብቅቶ ከእኛ ላይ ተገርስሶ ወደ ህይወታችን እረኛና ፈጣሪ መተናል እርሱን አውቀንማል ከዚህም ሁሉ በላይ በእርሱ ታውቀናል:: እውነተኛው እረኛ አውቆኝ በስሜ ይጠራኛል መሰማሪያንም ይሰጠኛል:: አሜን!
ታድያ የምን ባርነት?!
ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት እመለሳለሁ?
ከነፃነት ወደኃላ ወደ ባርነት?
አረ ይቅርብኝ ተመችቶኛል ይሄ ነፃነት::
አልያዝም በባርነት!
እኔ በእግዚአብሔር ልጅ በእየሱስ መስቀል በዋጋ ተገዝቻለሁ ልጁ እንድሆን ስለዚህ ባርያ መሆንም ከሞግዚትም በታች መተዳደር ይቅርብኝ::
ክርስቶስ በእኛ ሊሳል ይገባል
ወደ ገላትያ 4:10-20
10፤ ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። 11፤ ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ። 12፤ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና፡— እንደ እኔ ሁኑ፡ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም። 13፤ በመጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ፥ 14፤ በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። 15፤ እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ::
16፤ እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን? 17፤ በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ። 18፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው። 19፤ ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል። 20፤ ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ::
የገላትያ ሰዎች ልባቸው መሆን በሚገባው ቦታ ላይ አልነበረም :: ጳውሎስ እንደሚለው ልባቸው ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ መጠበቅ ላይ ነበር:: እያደረጉ የነበረው ሰንበትን ማክበር፤ ወራቶችን እየጠበቁ እንደ ሕጉ መስዋትን ማቅረብና ባዕላትን መጠበቅ ነበር ይህ ሁሉ ግን ሊመጣ ላለው ለእየሱስ ምልክቶችና መዳረሻ እንጂ ዋናው አልነበርም:: ስለዚህም ነው ጳውሎስ የደከመለትንና የሮጠለትን የክርስቶስን ወንጌል እርሱም በፊታቸው ተስሎ የነበረውን ክርስቶስን እንዲያዩና ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ነው አሁንም ክርስቶስ በፊታችሁ ይሳል የሚለው::
በመጀመሪያ ሲቀበሉት የነበራቸው ፍቅር ያላቸውን ሁሉ ያለ ስስት የሚያሰጥና እንደ ክርስቶስ መልእክተኛ ነበር የተቀበሉትና ወንጌል የገባቸው አሁን ግን ዋናውን ቁጭ አድርገው ወደ ሞግዚት መሄድ አማራቸው::
እኛስ እንዴት ነን ምን ላይ ነው ልባችን ያለው? ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷል ደግሞም የሰንበት እረፍት ቀርቶልናል ስለዚህ ልባችንን በክርስቶስ ላይ አድርገን እንደጀመርን እንጨርስ:: ለብ ባለ ህይወት አንመላለስ ልክ መጀመርያ እንደጀመርነው በጋለ ህይወት ጌታን በማመን በእርሱ ጽድቅ ተደግፈን እንመላለስ:: ጸጋን ሁሉ ሊሰጠንና ሊረዳን ከእኛ ጋር ነው አዳኛችን እየሱስ! አሜን!
የተስፋ ቃል ልጆች ነን
ወደ ገላትያ 4:21-31
21፤ እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ። 22፤ አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። 23፤ ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። 24፤ ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። 25፤ ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። 26፤ ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት። 27፤ አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል። 28፤ እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። 30፤ ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። 31፤ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።
እንደምሳሌ አድርጎ ጳውሎስ ሊያሳየን የሚፈልገው ቁም ነገር የተስፋ ቃልን ነው:: ይስሐቅ እግዚአብሔር እንደተናገረው የዓለም መድኃኒት የእየሱስ ክርስቶስ መምጫ ግንድ ሆነ:: ዘርህ በእርሱ ይጠራል ብሏልና እንዳለው በይስሐቅ በኩል ይህ ተስፋችን መጣልን:: እኛም ተስፋችንን መጀመሪያ ላይ በዘፍጥረት ከሴቲቱ እንደሚመጣ የነገረንን ፈጸመው:: ስለዚህ እግዚአብሔር የዘገየ ቢመስለንም እንኳን ይመጣል ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም::
ምዕራፍ 5
በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን
ወደ ገላትያ 5:1-5
1፤ በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። 2፤ እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፡— ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። 3፤ ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት፤ ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። 4፤ በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። 5፤ እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና።
ባርነትን እንቢ ብለን ነፃነትን እንምረጥ አለበለዚያ ግን ቃሉ እንደሚለን ሁሉንም ሕግ መጠበቅ ግድ ይላል:: የተወሰነውን ወይም ደግሞ አቅሜ የፈቀደውን ካደረኩኝ በቂ ነው ብሎ ነገር የለም ሕግ ካሉ ሁሉንም አንዷን ማጉደል አይቻልም:: ታድያ የቱ ይሻላል በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት ያወጣንን መቀበል ወይስ እንደማይሆንልን እያወቅን በሕግ ጎዳና መሄድ? እኔስ በክርስቶስ ያገኘሁት ነፃነት ይሻለኛል አለመቻሌን ጠንቅቄ አውቂአለሁ::
ደግሞም በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። ወየው አረ ወደ ጸጋው እንመለስ? ጸጋው ብቻውን በቂ ነው::ስለዚህ እላለሁ እኔ ግን በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለሁ። እርሱ ብቻ ነው ያለኝ ተስፋ::
በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት
ወደ ገላትያ 5:6-8
6፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። 7፤ በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? 8፤ ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም።
በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ እሱ ላይ ተቀጥላ አያስፈልገንም:: መገረዝም አለመገረዝም የስጋ ነገር ነውና ለመንፈሳዊዉ ህይወት አይጠቅምም:: እምነት እምነት ስንል ያለ ፍቅር መሆን የለበትም ስለዚህ እሩጫችንን እንሩጥ በፍቅር እንጂ ለእውነት ባለመታዘዝ አይሁን:: ይህ ማባበል ለጥፋት ነውና ወደ ስጋ ማየቱ አያዋጣም አልተቻለንም በስጋ እሱን ደስ ማሰኘር እናም እውነትን በፍቅር እንያዝ እሱም እኛ በመንፈስ ከእምነት ከሆነ የጽድቅን ተስፋ እየተጠባበቅን በክርስቶስ ኢየሱስ በሚሰራው እምነት በፍቅር እንቆማለን::
አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ
ወደ ገላትያ 5:9-15
9፤ ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። 10፤ የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። 11፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። 12፤ የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። 13፤ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። 14፤ ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፡— ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፡ የሚል ነው። 15፤ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
የመስቀል እንቅፋት ምንድነው? ሕጉ ነው እንቅፋት የነበረው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል:: አሜን! እርሾን እናስወግድ አለዚያ ግን እህሉን ሁሉ ነው የሚያቦካው ማለትም መገረዝን ብቻ እንፈጽምና ሌላውን ግን ማድረግ የለብንም የሚባል ነገር የለም አንዱን ስናስገባ ፈጽመን ከጸጋው እንወድቃለን ነገራችን ሁሉ ተበላሸ ማለት ነው:: ስለዚህ አሁን አርነት ወተናል ግን ይሄ አርነት ለሥጋ ምክንያትን እንድንሰጥ አይደለም ወይም ደግሞ ወደኃላ ተመልሰን ሕግን እንድናቆለፓፕስ አይደለም ለጠራን ጌታ በፍቅር ተገዝተን ሰውን ሁሉ ወደን በቅድስና እንድንመላለስ ነው:: አንዱ የሌላውን ሸክም ይሸከም ዘንድ ነው ይህም የሚያሳየን እንደው ደርሶ እንድንኮፈስ ሳይሆን የለየልን ሐጥያተኞች በጸጋ እንጂ በስራ ያልዳንን መሆናችንን ስለምናውቅ ወገኖች ላይ የሚፈርድ ሳይሆን የሚራራና የሚሸከም በፍቅር የሚቀበል ከማንም አልበልጥም የሚል ማንነትን እናጎለብታለን:: ብንነካከስና ብንበላላ የምንጠፋፋው እኛው ነን ይህ ደግሞ የጠላታችን ትልቁ ግብ ነው እኛ የተጠራነው እርስ በርስ ተደጋግፈን እንድንመላለስ ነው:: አካል ማለት ይኸው ነው: :
በመንፈስ ተመላለሱ
ወደ ገላትያ 5:16-18
16፤ ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። 17፤ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። 18፤ በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም።
በመንፈስ ተመላለሱማለት በሌላ አባባል የስጋን ምኞት አትፈጽሙም ማለት ነው:: መመላለስን ስናስብ የሚደጋገም ነገር ማለት ነው ለምሳሌ መተንፈስን ስናይ እስከአሁን ተንፍሻለሁ ይበቃኛል ብንል ምን እንደሚሆን ይታወቃል አይደል ስለዚህ ወደ መተንፈሳችን እንመለሳለን:: ሁልጊዜ አንዱ አንዱን ለማሸነፍ ይጥራል ፥ ይቀዋወማል ስለዚህ በመንፈስ መመላለስ ሁልጊዜ የምንኖርበት ሁኔታ መሆን ነው ያለበት እንጂ ወጣ ካልን ከጸጋው መውደቅ ነውና ዕለት ዕለት በመንፈስ መመራትን እንፈልግ ልጆች ነንና::
እንዴት እናሸንፍ ታድያ? በመንፈስ በመመራት ማሸነፍ እንችላለን ያኔ አድርግ አታድርግ አይሆንም ነገራችን መንፈስ ብቃትን ይሰጠናል አለዚያ ግን በመንፈስ የጀመርነውን ጉዞ በስጋ እንዳንጨርስ ያሰጋል:: የምንወደውን ማድረግ አንችልም እኛ የፍቅር ባሪያ ነን ህይወታችንን ለጌታ የሰጠን ነን:: በመንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው ይላልና ቃሉ:: የጠራን የታመነ ነው! አሜን!
የሥጋ ሥራ
ወደ ገላትያ 5:19-21
19፤ የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥20፤ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥21፤ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
እውነት ነው ከላይ ያሉትን የሚያደርጉ በመንፈስ የሚመላለሱ አይደሉምና የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም:: በመንፈስ መመላለስ በቃሉ መታነጽን ይጨምራል ምክንያቱም ቃሉ ጌታ እየሱስ እንዳለው መንፈስ ነው፥ ህይወትም ነው::
ማን ወይም እንዴት ልንወርስ ነው ታድያ የሚል ጥያቄ ውስጥ እንደምንገባ እርግጠኛ ነኝ:: ነገሩ እንደዚህ ነው በራሳችን አንዳች ማድረግ የማንችል ነን እናም ወደ ቃሉ ስንመጣ ቃሉ ይረዳናል በእምነት ከእኛ ጋር ሲዋሀድ:: እነዚህ ሕግን የሚሰብኩ ሰባክያን እራሳችሁን ቀይሩ ለሚሉት ስብከት መልስ ነው እነዚህን ሁሉ ስራዎች በህይወታችን እዚም እዛም እናያቸዋለን:: የምንኖርበት እና የምንታወቅበት ባህሪ መሆን የለበትም ሁልጊዜ ራስ ወደሆነው ወደ እየሱስ ማደግ አለብን:: እናም እራሳችንን ከዚህ ሁሉ ስራ ነፃ ካወጣን በኃላ ነው ስራ ተሰራ ጌታን ደስ አሰኘሁት የምንለውና ራሳችንን የምናታልለው:: ማንም በስጋ ጌታን ደስ ማሰኘት አይችልም:: ይሄንን ማሰብ ማለት መቼም የማንወጣው አዙሪት ውስጥ መግባት ነውና እጃችንን እንስጥና ለሚለውጠን ጌታ እንገዛ:: ደስ የሚለው ይህንን ሁሉ ስትጨርሱና ስትችሉ ኑ አላለንም ይህ ልብን ያሳርፋል ያለን እናንት ሸክማችሁ የከብደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኃለሁ ነው:: ስሙ ይባረክ የኔ ጌታ!
የመንፈስ ፍሬ
ወደ ገላትያ 5: 22-26
22፤ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፣23፤ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።24፤ የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።25፤ በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።26፤ እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።
እናስተውል እዚህጋ የመንፈስ ፍሬ እንጂ የመንፈስ ፍሬዎች አይልም:: ፍሬውን የሚያፈራውም ፍሬውም አንድ ነው እርሱም በእኛ ውስጥ የሚሰራው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው:: እነዚህ ባህሪያቶቹ ናቸው በእኛ ውስጥ ሲኖር የሚገልጠው:: ለዚህ ነው የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ የሚለው:: እኛ መስቀሉን ተሸክመን የምንከተል ሰዎች ነን ለክፉና ለዚህ ዓለም የሞትንበትን ደረሰኝ ይዘን የምንዞር:: ዓለምንም መውደድ ከእግዚአብሔር ጋር ጥል እንደሆነ የገባን ነን::
ደግሞ ደጋግሞ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ጳውሎስ ይነግረናል:- በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ:: ሚስጥሩ ያለው ከመንፈሱ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ላይ ነው:- በመንፈስ ብንኖር ወይም ብንመላለስ ስጋ ምኞቱንና መሻቱን አይፈጽምም ማለት ነው:: ደግሞም እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ የምንመካም አንሆንም:: በእኛ ውስጥ የሚታየው የእኛ ያልሆነው የእርሱ ፍሬ ይሆናል ማለት ነው:: እኛማ ይህንን ፍሬ ከየት እናመጣዋለን የእኛ ፍሬማ የስጋ እንጂ የመንፈስ አይደለም ምንም ብንጥር አናመጣውም ብናመጣው እንኳን ጊዜያዊ ነው:: ጎበዝ ጥረት ግረት እኮ ቀረ ስሙ ይባረክ ላሳረፈን ጌታ የእኔ ጽድቅ ለእናንተ ይሁን ብሎ ለቀየረንና የመንፈስ ፍሬ ተካፋይ ላደረገን:: ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን! አሜን!
ምዕራፍ 6
አንዱም የአንዱን ሸክም ይሸከም
ወደ ገላትያ 6: 1-2
1፤ ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።2፤ ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።
ከላይ እንዳየነው የመንፈስ ፍሬ በእኛ ውስጥ አለና ይሄ የዋህነትና ፍቅር አገልግሎት ላይ እንድናውላቸው ነው ክፍሉ የሚነግረን:: ምን አይነት አገልግሎት ብለን ካልን በበደል ውስጥ የሚገኝን ሰው ማቅናት:: ማቅናት ብልን ስንል ሀሜትን አስወግደን፥ መፍረድን አስወግደን ፥ እኔም እንዳንተው መሆን የምችል የሀጥያት ብቃት ያለኝ ግን በጸጋ የዳንኩኝ ነኝና ብለን በማሰብ እንጂ እኔ ካንተ እሻላለሁ በሚል አስተሳሰብ መሆን የለበትም:: የእኛ ስራማ የተገለጠ ነው አይደል? ስለዚህ በዚህ በተቀበልነው ማንነት ሌላውን እንደግፍ:: አካሉን እናንጽ ማፍረስ ቀላል ነው መገንባት ግን ትዕግስትንና ፍቅርን ይጠይቃል:: ሌላውን ስንረዳ እንዳንፈተን ማንነታችንን ጠንቅቀን ማወቅ ነው ብቃታችን እርሱ እንደሆነ መገንዘብ አለብን::
የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ እንደሚል ቃሉ ሕጉ ምንድነው ብለን ስንል የሌላውን ሸክም መሸከም ነው:: እርሱ የእኛን በደል ተሸክሟል ምሳሌያችን እርሱ ነው:: ከፍቅር በቀር እዳ እንዳይኖርባችሁ ተብለናል ለምንሰጠው ፍቅር ምላሹ ጥላቻ ቢሆን እንኳን እንደ የድል እዳ ይቆጠርልናል ማለት ነው:: ለምንሰጠው ፍቅር በምላሹ ፍቅር ላናገኝ የምንችልበት አጋጣሚው ሰፊ ነውና በዚህ ደስ ሊለን እንጂ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም:: አንዳችን የሌላችንን ሸክም እንሸከም እንደአካል ምክንያቱም ብቃትን ይሰጠናልና:: ስሙ ይባረክ ይሄ ጌታ! አሜን!
እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን
ወደ ገላትያ 6: 3-5
3፤ አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና።4፤ ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤5፤ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።
ስለመንፈስ ፍሬና ስለሚሰጠን ብቃት አይተን ነበር ከዛም በኃላ ደግሞ ሌሎችን በበደል ውስጥ የሚመላለሱትን በየዋህነት ማቅናት እንዳለብን አይተናል:: እንደዚህ ስናደርግ አንዳችን የሌላችንን ሸክም ስንተጋገዝ እንደው ምናልባት በእኛ ውስጥ ለምን ብዬ የሚል ልብ እንዳይገኝ:: ምንም ሳንሆን ምንም የሆንን መስሎን እንዳንታበይ ብቻ እናስታውስ ይህ የምንመካበት ፍሬ የመንፈስ ቅዱስ ነውና ሊያገለግልም ነውና በእኛ ውስጥ ያለው ስለዚህ ሌላውን ለማገልገልና ሸክምን ለመካፈል አንዘግይ ፈጥነን እራሳችንን ያለስስት እናቅርብ::
ይህንንም ስናደርግ የራሳችንን ስራ እንፈትን እንጂ በግብር ውጣ የምንመላለስ መሆን የለብንም:: ሁልጊዜም ሸክምን ለሌላው ብቻ አናምጣ እኛም ውስጥ ብቃት አለና እራሳችንንም እንርዳ ስለዚህ ነው ቃሉ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ የሚለው:: እርስ በእርሳችን ሸክማችንን ካልተሸካከምን እንግዲህ የራሳችንን ሸክም ለብቻችን ልንሸከም ነው ማለት ነው:: ክርስትና ግን የመሸካከም ህይወት ነው በአንድ ወቅት መድከም በሌላ ጊዜ ደግሞ መበርታት አለና የዚህ ዓለም ገዢ ሌት ተቀን እንደሚዋጋን እንወቅ እኛ ካለንበት ነገር ሌላው በቀላል ምክር ሊያወጣን እንደሚችል እንገንዘብ:: ክርስትና የህብረትም የግልም ህይወት ነው::
እርስ በርስ ሸክምን እንሸከም እንረዳዳ የአካል አሰራር እንደዛ ነውና::
የዘራነውን እናጭዳለን
ወደ ገላትያ 6: 6-10
6፤ ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል።7፤ አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤8፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።9፤ ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።10፤ እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።
በብሉይ ኪዳን ለካህናቱ ከሁሉም ነገር ላይ አስራትን ያወጡ ነበር ይህ ግን ለእኛ ለአሕዛብ አዲስ ነገር ነው:: ስለዚህም ነው ጳውሎስ ያንን ስርአት ስለማናውቅ ቃሉን ለሚያገለግሉን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ጋር መልካም ነገር ሁሉ እናካፍል የሚለው::
እግዚአብሔር አይዘበትበትም ሁሉንም ያውቃልና እንደዘራነው እንደዛው እንቀበላለን:: ስለዚህ መልካምን ነገር ሁሉ በማካፈል እንታወቅ::
በሁለት አይነት መንገድ ዘር ይዘራል እርሱም በሥጋ ወይም ደግሞ በመንፈስ የሚገርመው ነገር ሶስተኛ አለመኖሩና ሁለቱም ማጨዳቸው ነው:: የሚታጨደውም በሥጋ ከተዘራ መበስበስ በመንፈስ ከተዘራ ከመንፈስ የዘላለምን ህይወት ያታጨዳል ማለት ነው:: መቼም ማንም ውጤቱን እንደዚህ እያየ የሥጋን ዘር ለመዝራት ይወጣል ብዬ አላምንም:: በመንፈስ ግን እንዴት እንዝራ ብለን መጠየቃችን አይቀርም:: ስለዚህ ዘሩን በሚገባው መሬት ላይ እንዝራ ሥጋዊ ውጤት ለማምጣት ሳይሆን ደስ ያለው በልግስና ይስጥ ስለሚል በልግስና ለወንጌል ስራ እንዝራ::
በተለይም ለቅዱሳን አብዝተን ልንተጋገዝና ልንረዳዳ ይገባል:: ጌታ ሁሉን ሰቶናልና እኛም እየሰጠን መንግስቱን እናገለግላለን::
ከክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ
ወደ ገላትያ 6: 11-14
11፤ እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ።12፤ በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው።13፤ በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም።14፤ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።
እዚህ ጋር የምናየው ሰዎች ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ እና በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ እየወደዱ የመስቀሉን ስራ ያጣምማሉ:: ለሚመጣው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ወይም ባህላቸውን ለማክበር ያህል እንጂ ስለ ህዝቡ ወይም ስለ ወንጌል ግድ ብሏቸው አይደለም እነሱ እራሳቸው የማይፈጽሙትን ሕግ በሰው ላይ ለመጫን የሚነሱት:: ስለዚህ በዙሪያችን ያሉትን የመስቀሉን ስራ የሚያዋድቁትን ሰዎች ከመስማትና ከመሳት ይልቅ ቃሉ ምን ይላል ብለን ወደ ቃሉ መሮጥ ይበልጣል::
ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት
እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። አሜን!
እውነት ግን ሌላ ትምክህት ከየት ይገኛል? ሁሉ ነገር ጊዜያዊና እንከን የሞላበት የማያሻግርም ነው::
ለእኔ ግን ትምክህቴ ሌሎች ገለል የሚያደርጉት እኔግን በስንት ምጥ የተወለድኩበት የጌታዬ መስቀል ነው:: ሃሌሉያ አሜን!
አዲስ ፍጥረት መሆን
ወደ ገላትያ 6:15-18
15፤ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።16፤ በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።17፤ እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ።18፤ ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና:: እውነታው ይሄ ነው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት፤ ለርስቱ የተለየን፤ የንጉስ ካህናት፤ ቅዱስ ህዝብ፤ እርሱን እያብለጨለጭን የምንኖር፤ ልጆች እንጂ ገና በሞግዚት ባርነት ስር ያልሆነ ትውልድ፤ ስጋን ከክፉ መሻቱ ጋር የሰቀለ ትውልድ፤ በመንፈስ ፍሬ የተሞላ እንዲሁም የራሱን መንገድ የሚጠበጥብ ትውልድ ነን::
አሮጌው ማንነት ተንኮታኩቶ ላይነሳ ወድቋል፤ ዓለምን መውደድ ተጠራርጎ ወቷል በፊቴ የተሳለውን ክርስቶስን እያየሁ ወደፊት መንጎድ ብቻ ከጌታዬ ጋር:: ሃሌሉያ!!! ይህን ሁሉ የሰጠን በመስቀል ላይ ራሱን ያንገላታው እየሱስ ነው:: ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁንለት! አሜን!!
በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን
በየትኛው ሥርዓት?
አዲስ ፍጥረት በመሆኑ ሥርዓት ውስጥ እግዚአብሔር ሰላምንና ምህረትን ሰቷል:: እርሱ የሰላም አለቃ ነውና አይምሮን ሁሉ የሚያልፍ እንዲሁም ዓለም የማይሰጠውን ሰላም በውስጣችን አፈሰሰው:: እንግዲህ ምን ይባላል? ከማመስገን ሌላ?
እዚህ ጋር ጳውሎስ በማጠቃለያው እውነቱ ይሄ ነው ትከተሉት እንደሆን ተከተሉት እኔ በእርሱ ሰላምና ምህረት ውስጥ ያለሁኝ ባርያው ነኝ አታድክሙኝ እያላቸው ነው::
እኛም የክርስቶን ማህተም ተሸክመናል ማለትም በወዶ ገብ ለዘላለም የእርሱ ሆነናል ማለት ነው:: ለዘላለም እገዛልሀለሁ ጌታዬ::
ወገኖቼ ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን። አሜን!!!

ጌታ ይባርካችሁ
LikeLike
እጅግ ጠቅሞኛል አመሠግናለሁ በርቱ ልሏቹ እወዳለሁ
LikeLike
Be blessed
LikeLike
The word of God is amazing!
LikeLike
እጅግ ጌታ ይባርካችሁ በመልዕክታችሁ ተባርካለሁ
LikeLike