ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች

መግቢያ

የዚህ መጽሐፍ ዓላማ:

ይህ መጽሐፍ ጳውሎስ ከእስር ቤት ሆኖ ከጻፋቸው አራቱ መልእክቶች ውስጥ አንዱ ነው:: (ሌሎቹ መጽሐፍት ኤፌሶን፤ ቆላስያስ እና ፊልሞና ናቸው) ይህ ቤተክርስቲያን በአውሮፓ የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ነው:: በሐዋርያት 15:40-19:22 በጳውሎስ ሁለተኛው የወንጌል ጉዞ ላይ በህልሙ (በሐዋ 16:9) ወደ መቄዶንያ መተህ እርዳን የሚለውን ራዕይ ካየ በኃላ ነው የመጣው:: ፊልጲስዮስ በመቄዶንያ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ወይም በአሁንዋ ሰሜናዊ ግሪክ ውስጥ ያለች ግዛት ናት:: የመጽሐፉ ጸሐፊ እራሱ ጳውሎስ ነው::

በዚህ መልዕክቱ:-

  1. ስለሰጡት ስጦታ ሊያመሰግናቸው (ከነሱ ከተለየ በኃላ ስጦታ በተደጋጋሚ የላኩለት ከዚህ ቤተክርስቲያን ብቻ ነው (2ቆሮ 11:9 እና ፊል 4:10-20)
  2. ሊያበረታታቸው
  3. ሁልጊዜ በጌታ ደስ እንዲላቸው (ምንም እንኳን ከእስር ቤት የጻፈው መልዕክት ቢሆንም 16 ጊዜ ስለደስታ ጽፏል)

ምዕራፍ 1

ምዕራፍ 1 ንባብ
ሰላምታ

ወደ ፊልጵስዩስ 1:1-2
1፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤
2፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ጳውሎስ እራሱንና አብሮት የሚያገለግለውን ጢሞቴዎስን የኢየሱስ ባርያ ብሎ ይጀምራል ጽሁፉን:: እየሱስ ጌታዬ ነው በሰራሁት ስራ ሁሉ ጌታዬን ለማስደሰት ነው እያለ ይህንን እንደመረጃ እየሰጠ ያለውነው::

የተጻፈላቸውም የቤተክርስቲያንዋ አገልጋዮችና እንዲሁም ምዕመኑ በሱ አጠራር ቅዱሳን ብሎ ይጠራቸዋል ዛሬም ለኛ ቢጽፍ እንደዚህ አድርጎ ነው የሚጠርን ደግሞም ቅዱሳን ነን በጌታ ከመዋጀታችን የተነሳ::

የመግቢያው ሰላምታ እንደሰላምታ ብቻ አይደለም ባርኮትም አለበት ከአባታችን እንዲሁም ከእየሱስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን:: አሜን! ማንም በክርስቶስ ካልሆነ በስተቀር ይህንን ሰላም መለማመድ አይቻልምና እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይነት አይደለም አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ ነው:: ዛሬም ሰላሙና ጸጋው ይብዛልን ይትረፍረፍልን::


መልካሙን ስራ ክርስቶስ ይፈጽመዋል

ወደ ፊልጵስዩስ 1: 3-8
3-5፤ ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ።
6፤ በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤
7፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል።
8፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና።

የዝች ቤተክርስቲያን ሰዎች ከጳውሎስ ጋር ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ነው አብረውት የወንጌል ሰራተኛ የሆኑት እርሱም በጣም ነው የሚወዳቸውና ስለእነሱ ሲጸልይም በደስታ አምላኩን ያመሰግናል:: ጳውሎስ ወዳጅነቱን በግልጽ ነው የሚያሳየው ደብዳቤው የግል እንጂ ለቤተክርስቲያን የተጻፈ መልእክት እንኳን አይመስልም:: ባደረጉለት ስጦታ ምክንያት ህይወቱን ይደግፉ ነበርና መቼም ድንኳን በመስፋት ብዙውን ጊዜ ከሚያውል ለማገልገል እንዲችል አስችለውታል ምክንያቱም አብራችሁኝ አገለገላችሁ ብሎ እውቅና እየሰጣቸው ነው:: ጸጋ የተለያየ ነውና በተሰጠን ጸጋ እንገለጥ ያን ጊዜ ወንጌል በኃይል ይሄዳል የግድ ሁሉም ሰው መስበክ የለበትም ልግስናም ጸጋ ነውና ለመንግስቱ ያስፈልጋል:: የተሰጠን ጸጋ ምንድነው? እናገልግልበት::

እግዚአብሔር ታማኝ ነውና በእናንተ የተጀመረው ስራ ይቀጥላል፥ ይሰፋል ምክንያቱም እሱ የታመነ ጌታ ስለሆነ የስራውም ባለቤት እርሱ ስለሆነ ይህ የማይቀር ሀቅ ነው:: በእርግጥ የእኛ መተባበር ያስፈልጋል የእግዚአብሔር ግን መምራትና መርዳት አስፈላጊ ነው እርሱንም ያደርገዋል እያለን ነው ለእኛም::

በእስራቱ ሳያፍሩና ሳይረሱት ስለእርሱ በማሰብ አብረውት ቆመዋል ከዚህ ሁሉ በላይ ግን እንደዚህ ያቆመው ጸጋ እንደሆነ ጳውሎስ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው ለእናንተም ይህ ጸጋ ያቆማችኃል እያላቸው ነው:: ምንም አይነት ነገር ቢመጣ እርሱ በጸጋው ያቆማችኃል እኔ ምስክር ነኝ እያለ ነው:: ዛሬም በምናልፍበት ሁሉ በጸጋው ሊረዳን የታመነ ነው የእኛ ጌታ ከጳውሎስ ጋር እንደነበረ ዛሬም ከእኛ ጋር በስራ ላይ ነው::

ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች ከመውደዱ የተነሳ ሁልጊዜ መቼ ነው የማያቸው በሚል ጉጉት ውስጥ ነበር ግን የወንጌል ስራ ስለበለጠበት ሳያያቸው ቆየ:: ሊያያቸው እንዴት እንደሚናፍቅ ግን እግዚአብሔር ነው ምስክሬ ይላቸዋል እንዲህ ያለ መነፋፈቅንና መተሳሰብን ጌታ በዘመናችን ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥም ያድርግ ይህ ፍቅር ይፍሰስልን:: አሜን!


ፍቅራችን በእውቀትና በማተዋል ይብዛ

ወደ ፊልጵስዩስ 1: 9-11
9-11፤ ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።

1. ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሆን ዘንድ ከክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶብን መገኘት አለብን:: እናስተውል ከእኛ አይደለም የጽድቁ ፍሬ የሚመጣው ከጠራን ከራሱ ነው:: ነገር ግን ገና የራሳችንን ጽድቅ ለማቆም የምንነሳ ከሆነ አስቸጋሪ ነው ወደ እረፍቱ መግባታችን ታድያ ምኑ ላይ ነው? ውላችን እኛ ልንሞት እርሱ በእኛ ሊኖርም አይደል? እንደዛ ካላሰብን የምንፈልገውን መለወጥ አናየውም ጥረት ግረት ሆኖ ይቀራል:: ክርስትና ግን እረፍት ነው ደግሞም ክብርና ምስጋናን ከእኛ ህይወት የተነሳ የምናመጣ ነን:: ደስ አይልም? በተቃራኒውምእንዳለ ልብ እንበል::

2. ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ እኛ የመድኃኒታችንን ከሰማይ መገለጥ የምንጠባበቅ ነን:: ስንጠባበቅ ግን ኑሮ እናቆማለን ማለት አይደለም ነገርን ፈትነን የሚሻለውን ማለትም:- እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ይለናል ቃሉ:: ይህንንም የምናደርገው ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅተን ቅኖችና እለነውር ሆነን እንጠብቅ::

3. ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። ፍቅር በእውቀት እየጨመረ የሚመጣ ነው:: ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ ጌታ ይፈልጋል:: ይህ እንዲበዛ ነው ጳውሎስ እጸልያለሁኝ ያለን እኛም እንጸልይ ይህ ከመታወቅ የሚያልፍ ፍቅር በህይወታችን ውስጥ ይገኝ ዘንድና ማስተዋልም እንዲሆንልን::


በሁሉ ምክንያት ክርስቶስ ይሰበክ

ወደ ፊልጵስዩስ 1:12-20


12፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።
13፤ ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥
14፤ በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ።
15፤ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤
16፤ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥
17፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ:: 18፤ ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።
19፤ ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
20፤ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል።

ወንድማችን ጳውሎስ ወንጌልን ሲሰብክ የደረሰበት ብዙ ድብደባ ብሎም እስራት ነው:: መታሰሩም ወንጀል ሰርቶ ሳይሆን በእምነቱ እንደሆነ ታውቋል:: ይህም ወሬ አሳሪዎቹም ሳይቀሩ አውቀዋል ምናልባትም ወንጌልን ሰምተዋል:: በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በእኔ ላይ የመጣውን መከራ እዩ ሳይሆን እያለ ያለው አይዟችሁ መታሰሬ አያሳዝናችሁ በርቱ ወንጌልን ስበኩ እያለ ነው:: እንዲያውም አንዳንድ ወንድሞች እስራትን ንቀው ከፊት ይልቅ ወንጌልን እየሰሩ ነው ይላል ምክንያቱም እርሱ ስለ እስራቱ ሳይሆን የሚያወራው ስለወንጌል መሰበክ ስለሆነ በወገኖች ላይ ያሳደረው ነገር ወንጌል መሮጥ አለበት የሚልና ብያዝ እንኳን ግፋ ቢል መታሰር ነው እንደእርሱ ሳልያዝ ልስራ የሚል መንፈስ ነው:: ሌሎች ደግሞ በማሾፍ የሞተ ተነሳ ይላል ብለው አንዳንዶችም መከራውን ሊያበዙና ወደፊት ስለዚህ ጌታ ሁለተኛ እንዳይናገር ተስፋ ለማስቆረጥ ስለ እየሱስ ይናገራሉ:: በዚህ ሁሉ ግን ይላል እየሱስ ብቻ ይሰበክ በዚህ ደስ ብሎኛል ይላል::

በህይወት ይሁን በሞት በስጋዬ ጌታ ይክበር ባይ ነው ምክንያቱም አላፍርም በጸሎታችሁና በመንፈሱ ተረድቼ እቆማለሁ ይህ ተስፋዬ ናፍቆቴም ነውና ብሎ ስለ ዘላለም ህይወቱ እንጂ ከስር ስለመፈታቱ አያወራም ሁልጊዜ ወደጌታ ያሳያል ያበረታል:: እኛም ዛሬ አይናችንን በርሱ ላይ አድርገን ወንጌልን እንስበክና እንኑረው::


ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ነው

ወደ ፊልጵስዩስ 1:21
21፤ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።

ዘራፍ!! እያለ ድፍረት ለማግኘት እራሱን እያነቃቃ አይደለም ጳውሎስ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነው ሲለን ውስጡ የሞላውን እውነት ነው የሚነግረን ያለው:: ያስጨነቀው መሞቱ አይደለም ለኔ መሞት ጥቅም ነው ነው ያለው ብኖር እጠቅማችኃለሁ ስለዚህ ስጋዬ በግርፋትና በመከራ ይለፍ እንጂ ነፍሴን መንካት ማንም አይችልም በሚል ልበ ሙሉነት ነው እየተናገረ ያለው:: ለሌላው አካል ወይም እስር ቤት ላስገቡት ቦታም አልሰጣቸው ከእስርም ያስመልጣል ከሞትም ያስነሳል የኔ ጌታ ሁሉ በእጁ ነው እያለ ነው:: ከዚህ በፊት ደብድበው ሞቷል ብለው ጥለውት አልሄዱም? እርሱ ግን ተነስቶ መስበኩን ቀጠለ አይደል? ጌታውን ጠንቅቆ ያውቃል እኛም እንወቀው:: የሚያኖረን ከክርስቶስ የተቀበልነው ጸጋ እንጂ የሰው ቸርነት ወይም የስጋችን ብርታት አይደለም::

ህይወታችን እራሱ ክርስቶስ ነው በእርሱ ውስጥ ነን ካልን እዚህ እንሁን ወይም በሰማይ ምንድነው ለውጡ? በመጀመርያ ግን በእርሱ ውስጥ ነኝ የሚለው ሀሳብ በውስጣችን ሊዘልቅና አይምሯችን በዚህ እውነት ሊሞላ ይገባዋል:: ሞት እኮ መውጊያውን ተነጥቋል ዛሬ መጣሁ እያለ አያስፈራራንም ከሞትም ጋር ህብረትም ወዳጅነትም የለንም:: ለእኛ ሞት ማለት በር ብቻ ነው ወደ ዘለዓለሙ መዝለቂያ እንዲያውም ሊያስፈራን ሳይሆን ስራችንን ስንጨርስ በል አሰናብተኝና ወደቤት ልምጣ የምንልበት ማለፊያ በር ብቻ ነው:: የመጨረሻ የተባለውን ትንፋሽ በዚች ምድር ላይ ስንወስድ ወድያው የመጀመሪያውን በሰማይ እንጀምርና ጌታንም በክብሩ እናየዋለን:: ግን ዛሬ ነፍስና ስጋችንን የሚያላቅቀው ነገር ሞት አይደል?! ዛሬም ጠላት መጣሁብህ እያለ ባዶ እጁን የቀረበትን የሽንፈት መሳሪያውን እንደድል ሲጠቀምበት ዝም አልነው:: ይብቃ እኛ የክርስቶስ ነን!! ማንም ከቶ አያስፈራራንም ብንኖር ለጌታ ብንሞት ለጌታ! ሃሌሉያ!!!


ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ

ወደ ፊልጵስዩስ 1: 22-30

22 ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። 23 በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ 24 ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። 25 -26 ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ። 27 ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። 28 በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ 29 ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤
30 በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።

አሁን እንደው ጳውሎስ ልኑር ወይስ ልሙት የቱን ልምረጥ እያለ ሲቸገር ይገርማል:: ማንም በዚህ ጥያቄ ሲፈተን አይቼ አላውቅም ልኑር ህይወቴን አቅና የሚል እንጂ እኔንም ጨምሮ ሊያውም ከአንዱ የድብደባ መድረክ ወደሌላው የሚሄደው ጳውሎስ የቱን መምረጥ እንዳለበት ሲቸገር ይደንቃል:: ልክ እንደው ሁለት የሚያጉዋጉዋ ነገር በፊቱ ያለ ይመስላል:: አንድም እየተደበደቡ መኖር አልያም መሞት እና ወደ ጌታ መሄድ:: እሱ እንዳስቀመጠው ግን ለኔ መሞቱና ወደ እረፍት መግባቱ ይሻላል ደግሞም በጣም እናፍቃለሁና ከጌታዬ ጋር መኖርን ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ብቆይ ደግሞ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ ብሎ መቆየቱን መርጧል:: ከራሱ ይልቅ ለሌላ ለመኖር ወሰነ እኛስ ምን እንወስን ይሆን? እራሳችንን ስናይ ግን አንዳች ጎደለን ብለን ወይም ይህ ነገር አልተሳካም ብለን ወደ ጌታ በሄድን ወይም እርሱ በመጣ እምንል ነን:: ምን አይነት የወንጌል መልእክት እንደያዝን አይገባኝም ጌታ ይርዳን ለክርስቶስ አካል እንኑር ብለን ለመኖር ከየት እንደምንጀምርም ግራ ይገባል:: ወንጌል ግን ለጌታ መኖር ነው::

ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ ብሎ ይላል እንዴት ነው እንደሚገባ የምንኖረው?

1. በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ – የያዝነው የወንጌል ስራ እንደ አካል በህብረት የሚሰራ ነውና በመዋደድና በመደጋገፍ ልንሰራ ይገባል:: ዮሐንስ 13:35. እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።

2. በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ – 1ኛ ቆሮንቶስ 12
13፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። እናስታውስ ያው አንዱ መንፈስ በሁላችን አለልዩነት አለ::

እንደዚህ ስንመላለስ የጠላት ፉከራና ቀረርቶ አያስፈራንም ምክንያቱም የመዳን ምልክት እንጂ ለእኛ የጥፋት አይደለም:: ክርስቶስን ስንከተል ከወንጌል የተንሳ መከራ ይመጣል ግን አያጠፋንም እናሸንፋለን::


ምዕራፍ 2

ምዕራፍ 1 ንባብ

በክርስቶስ ያለ ምክርን እንፈጽም

ወደ ፊሊጲስዮስ 2: 1-4

1 በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤
2 በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤
3 ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤
4 እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።

I. በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ ምን አይነት ምክር ነው? ጳውሎስ ደስታዬን ፈጽሙልኝ ያሰኘው-

  1. የፍቅር መጽናናት
  2. የመንፈስ ኅብረት
  3. ምሕረትና ርኅራኄ

እነዚህ ፍቅር፤ ኅብረት፤ ምህረትና ርህራሄ በክርስቶስ ውስጥ ያየናቸው ባህሪያት ናቸው ስለዚህ እነዚህ ባህርያት በመንፈስ ቅዱስ በኩል ዛሬ በእኛ ይገለጣሉ:: በፍቅር ተመላለሰ ደግሞም ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም የተባለለትን ትልቅ መስዋዕትነት ከፈል:: ከአባቱም ጋር ህብረት ነበረው ለሊቱን ሁሉ ሲጸልይ ያድራል:: ምህረትና ርኅራሄውም በደንብ ታይቷል:- ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? እኔም አልፈርድብሽም ሂጂ ሲል በሌላ ቦታ ደግሞ እረኛ እንደሌላቸው ተበትነው ሲያይ አዝኖ:: ለታመሙት ራርቶ የሚፈውስ ከሚያለቅሱት ጋር የሚያለቅስ ሩህሩህ ጌታ:: ብዙ ማለት ይቻላል ስለ እየሱስ ይህ በርሱ የተጀመረው ህይወት አሁንም በእኛ ይቀጥል::

II. በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ ምን ብናደርግ ነው በአንድ ሀሳብ ልንስማማ የምችለው?

  1. አንድ ፍቅር – ክርስቶስን ብቻ ማየት እንዴት እንደወደደን
  2. አንድም ልብ – ክርስቶስ እንዲከብር ብቻ ማሰብ
  3. አንድም አሳብ – እርሱን በሀሳባችን ሁሉ መቀደስ ያኔ እርሱን ብቻ ለማክበር እንስማማለን
  4. በትሕትና – ሰውን ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ ማወቅና ከኔ ይሻላል ማለት
  5. ለሌላው በማሰብ – በሌላው ውስጥም ጌታ ይሰራል ብሎ መቀበልና መርዳት ወደ ተጠሩበት ነገር እንዲደርሱ

በዚህ ሁሉ ውስጥ ዝቅ ማለትና በትህትና መመላለስ አለብን እኔ አውቃለሁን ትተን ከኔ ይሻላል ወገኔ እንበል:: ያለ ሌላው አገልግሎት እኔ የምሮጠው ሙሉ እንድማይሆን ማወቅ:: እግዚአብሔር ለትሁታን ጸጋን ይሰጣልና::


የክርስቶስ አሳብ በእኛ ይገኝ

ወደ ፊልጵስዩስ 2:5-6
5፤ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። 6፤ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥

በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን:: ምን አሳብ በእኛ ዘንድ ይሁን? የቱ አሳብ ይግዛን? እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ የሚለው አሳብ::

ምን ማለት ፈልጎ ነው ለመሆኑ እንደ መቀማት አልቆጠረውም ሲለን:: እስኪ ትቶ የመጣውን ምንም ያልመሰለውን ክብሩን እንይ::

  • የሰማይ ሰራዊት ሳያቋርጡ ቅዱስ ቅዱስ የሚሉት፥
  • ከፍ ባለና በረጅም ዙፋኑ ላይ የተቀመጠ፥
  • በደመናት ላይ የሚራመድ፤
  • ሰማይና ምድርን በውስጧም ያሉትን ሁሉ በቃሉ ትእዛዝ የፈጠረ፥
  • ሰማይን በስንዝር የሚለካ፥
  • ውሆችን በእጁ የሰፈረ፥
  • የምድርንም አፈር በመስፈርያ ሰብስቦ የያዘ፥
  • አስተማሪና አማካሪ የሌለው፥
  • ምድርን በቃሉ ያጸና፥
  • በሚደነቅ ብርሃን ውስጥ የሚኖር፥
  • የአማልክት አምላክ፥
  • የጌቶችም ጌታ፥
  • ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥
  • በፍርድ የማያደላ፥
  • መማለጃም የማይቀበል፥
  • አይደክምም አይታክትም፥
  • ማስተዋሉም አይመረመርም፥
  • ሰውን ከአፈር በእጁ የሰራ የህወትንም እስትንፋስ የጨመረበት፥
  • ለዘመኑ ቁጥር የሌለው፥
  • እንደ እርሱ አይነት አምላክ የለም:: ሃሌሉያ! አሜን! ብዙ ማለት ይቻላል ስለጌታችን ስሙ ይባረክና ይህን ሁሉ ጥሎ እኔን ብሎ መጣ?!

ታድያ እኔ ምኔን ልጣል? የቱን የሚያጏጏውን ክብሬን፤ ውበቴን፤ ሀብቴን? አረ ምኔን ምን አለኝ ይህን ትቼ ነው የመጣሁት የምለው?! እራቁቴንም አይደል የመጣሁት? ስሄድስ ይህ የእኔ ነው ይዤው ልሂድ የማልል ደካማ ፍጡር:: ምኔ ነው ያስመካኝ? የቱ ነው እንደው ዝቅ እንዳልል ሁሉን ትቼ እንዳልከተለው የሆንኩበት?! ምንም የሌለኝ ደካማ መሆኔን ብቻ ነው ያየሁት እንዲያውም በተቃራኒው ትምክህቴን አስትቶ ሊያሸማቅቀኝ የሚገባው ምንም ልሰጠው አለመቻሌ ነው መሆን ያለበት:: የመሰጠቴን ደረጃ ከፍ አድርጎ እኔ ለአንተ በፈቃዴ የተገዛሁ ባርያ ነኝ ልለው ሲገባ እርሱ ግን ከፍቅሩ የተነሳ ደስ የሚለው የምትሰጭኝ የለም እንዲያውም ከነድካምሽ ነይ ብሎ እጁን ዘርግቶ አንቺ ልጄ ነሽ አለኝ!!!!! እሱ ከሆነልኝ ነገር ጋር ሳስተያየው እኔ የደመደምኩት:- ልከተለው፤ ልገዛለት፤ ባለኝ ሙሉ ኃይል ሁሉ ላከብረው፤ በትህትናም ልመላለስ ይገባል ብዬ እላለሁ::

እዘምራለሁ ለክብሩ ሌላማ ምን አለ?

ምን ይከፈልሀል ጌታ ሆይ ምን ይከፈልሀል

ብቻ ተመስገን እንልሀለን ምስጋና ይገባሀል!!!


ምን አለኝና ምኔን ልክፈልህ
እንደው ዝቅ ብዬ ልዘምርልህ
በህያዋን ጉባኤ መካከል
እንዳንተ ያለ የለም ከፍ በል!!!

ሃሌሉያ! አሜን! አሜን! አሜን! አሜን!


እየሱስ ራሱን ባዶ አድርጎ፥ አዋርዶ የባርያን መልክ ያዘ


ወደ ፊልጵስዩስ 2:7-8
7፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ 8፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።

ለመስቀል ሞት ታዘዘ ብለን እንደተለመደ አባባል እንላለን ምናልባትም ከልጅነት ጀምሮ እየሰማን ስላደግንም ሊሆንም ይችላል ብቻ ብዙ አይደንቀንም:: ከሲኦል አምልጠናል የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል ብለን እመስቀሉ ውጤቶች ላይ ነው የምናተኩረው:: ከላይ (በቁጥር 5 እና 6) እርሱ ትቶ የመጣውን ለማየት ሞክረናል:: ፈጣሪ ሆኖ ሳለ በአንድ ስፍራ በአንድ አካል ውስጥ ተገለጠ:: ይህንንም ሁሉ ያደረገው ስለወደደን ነው:: የመስቀል ሞት ግን ምን ይመስላል? እንዴትስ እራሱን ባዶ አደረገ? ምን ማለት ነው የባርያንስ መልክ መያዝ ማለት?

አማካሪ የማያስፈልገው ጠቢብ:- በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።

ምድርን በቃሉ ብቻ የፈጠረው ጌታ:- ለቤተሰቦቹ መታዘዝና መስራት ነበረበት፥

ምንም ሐጥያት የሌለው ቅዱሱ ሊቀድሰን የመጣው:- በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ::

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከአፈር በእጁ እንዳልተሰራው:- ሰው ግን ጌታውን ሰቀለ (በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?)

ሰማይ ዙፋኔ ምድር የእግሬ መርገጫ ያለ ጌታ:- በምድር ሲኖር ቤት አልነበረውም

ያለማቋረጥ የሰማይ ሰራዊት የሚያመልኩት ንጉስ:- እግር ሊያጥብ ዝቅ አለ

የሲናን ተራራ በመገኘቱ ያጨሰው፤ ማንም ቢቀርብ ተራራውን ሰውም ይሁን እንሰሳ ይሞት እንዳልነበረ:- ተፉበት፤ ማነው የመታህ? እያሉ አሾፉበት

እልፍ አእላፍ መላእክት የሚያገለግሉት ጌታ:- የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም አለ

በአንድ ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ:: ይህ እንዲደገም ማድረግ የሚችለው ጌታ:- ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።

ይሄ ነው እንግዲህ በጥቂቱ የሆነው ታድያ ከዚህ በላይ ባዶ መሆን ምንድነው? የባርያን መልክ መያዝ ከዚስ በላይ አለ? እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። የሰውን ልጅ ነፃ በማውጣት ፍሬውን ዛሬ በእያንዳንዳችን ላይ ለማየት ነው ይህን ሁሉ የታገሰው:: ከኔ ተማሩ ሲለን በህይወቱ ኖሮ አሳይቶናል ጌታችን ስለዚህ መታዘዝንና ትህትናን አስተማረን ይህ በእርሱ ውስጥ ያለው አስተሳሰብ በእኔም ውስጥ ይገዛል:: ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ ብሎናል:: በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር ይላል ቃሉ:: እርሱ ግን ፈጽሞ አባቱን ታዞ ስራችንን ሰርቶ ወደ አባቱ ሄደ:: እንዴት እንመላለስ ታድያ?

የተከፈለብኝ ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው!! የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የወደደኝና እራሱን ባዶ አድርጎ የባርያንም መልክ ይዞ መቶ ወደራሱ ሊመልሰኝ የተንገላታልኝ የጌታዬ ነኝ:: አሜን!!


ከስም ሁሉ በላይ ስምን ተቀበለ

ወደ ፊልጵስዩስ 2: 9-11
9፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፥ 10፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ 11፤ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።

በምን ምክንያት ነው አየሱስ ያለ ልክ ከፍ ከፍ ያለው? እራሱን ባዶ አድርጎና አዋርዶ እንዲሁም የባርያን መልክ ይዞ መጥቶ ለሞት ያውም ለመስቀል ሞት ስለታዘዘ ነው:: ከፍ ከፍ ብሎ ብቻ አልቀረም የከፍታው ልክ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስምን አሰጠው:: ይህ ስም አለ እግዚአብሔር አብ በሰማይ፤ በምድርና ከምድር በታች ያሉ ስም ያለው ሁሉ ለዚህ ስም ይንበርከኩ ብሎ አዋጅን አወጀ:: ይህንን አዋጅ የማይታዘዝ ማን ይሆን? ሁሉ ፍጥረት አይደል? ስለዚህ ሁሉ ይገዛል ለዚህ ህግ:: ስም እስካለው ድረስ ሁሉም ለዚህ ለእየሱስ ስም መንበርከኩ ግድ ነው:: ዛሬ የለም ብለው የሚሉት ሁሉ የማያምኑበትም ወደዱም ጠሉም ይንበረከካሉ ለዚህ የተቀባ ስም::

በዚህ ስም ምን የማድረግ ስልጣን አለው?

  1. እንድንበት ዘንድ:- (ሐዋ 4:12፤ መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።)
  2. ምልክትና ድንቅ ያደርጋል:- (የሐዋ 3:6: ጴጥሮስ ግን፦ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ፡ አለው።)
  3. አጋንንት ይወጣሉ (ማር 16: 17)
  4. በስሙ ስንለምን ይደረጋል (ዮሐ 14:13-14)

በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነው

ወደ ፊልጵስዩስ 2:12-13
12፤ ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ 13፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።

በእናንተ ዘንድ ብሆንም ባልሆንም ታማኝ ሁኑ ይላቸዋል እኛም ዛሬ ሰው አየን አላየን ብለን አንቀያየር ሁልጊዜ ጌታ ያየናልና በታማኝነት እንመላለስ:: መዳን አንድ ጊዜ ተሰቶናል ዕብ ምዕራፍ 4 ላይ እንዳለው የምንኖረው ለመግባት አይደለም ምንም ጥረት ማድረግም አያስፈልገንም ያመንን ጊዜ ያን ጊዜ መዳንን በማግኘት ወደ እረፍቱ ገብተናል ደግሞም አገራችን በሰማይ ነው እንላለን:: ግን መስራት እንዳለብን ደግሞ መዳንን ፈጽሙ ይለናል:: ለምን? ብለን ብንል የኛ አገልግሎት የጌታ አምባሳደር ሆነን የመንግስታችንን አቋም በማንጸባረቅ መኖር ነው ሁሉ ትዕዛዝ ከመምሪያው ይተላለፋል የሚያስፈልገንንም ሁሉ እራሱ መንግስታችን ያሟላል::

እንዴት የራሳችንን መዳን እንፈጽም ታድያ? በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ምክንያቱም ለመዳናችን ያደረግነው አስተዋጾ የለምና ሁሉን ጌታችን እየሱስ በመስቀል ላይ ተንገላቶ ተፈጸመ ብሎ ፈጽሞታልና ልንታበይ ወይም ልንመካ በራሳችን አያስፈልግም::

ከላይ እንዳየነው ደህነታችን ከኛ ስራን አይጠይቅም እየሱስ እንዳደረገው አይተናል:: መኖሩም ቢሆን ስራ አይፈልግም እንዴት? የተባልኩኝ እንደሆነ:- ምክንያቱም ስለ በጎ ፈቃዱ

1, መፈለግንም (ሲለን):- ከላይ ፊሊ 2:1 ላይ እንደተብራራው (የፍቅር መጽናናት፥ የመንፈስ ኅብረት፥ ምሕረትና ርኅራኄ) በክርስቶስ ውስጥ ያለው አሳብ በእኛም እንዲሆን ነው::

2. ማድረግንም (ሲለን):- አንድ ፍቅር – አንድም ልብ – አንድም አሳብ -በትሕትና – ለሌላው በማሰብ በመደረግ ይገለጣል ማለት ነው:: ምክንያቱም:-

በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና!!!!

እስኪ ከእኛ ይሁን ከሰው ልጆች እየሱስን አይዞህ እንኳን ያለው አለ? በመስቀል ላይ ሲንገላታ?! ማንም የለም እንዲያው የተሰጠንን ደህንነት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንፈጽም::

ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።


ጌታን በህወታችን እናሳይ

ወደ ፊልጵስዩስ 2 :14-18
14-15፤ በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ 16፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። 17፤ ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ 18፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ::

በዚህ በጨለማ በሆነ በመጥፎና ጠማማ ትውልድ መካከል እንዴት እንመላለስ? እነሱን በመምሰል ወይስ ጌታን በማሳየት? እስኪ እንየው
1. ያለ ነቀፋ – እንዳንነቀፍ ፈጽመን የእግዚአብሔርን ቃል እንኑረው እርሱ አይደለም ለዝች ምድር በቅድስናውም ፊት ያለ ነቀፋ አቅርቦናል እርሱን እንግለጥ

2. የዋሆችም – የዋህነትን የምንማረው ከራሱ ከጌታችን ነው እርሱ እንዳለን እኔ የዋህ ነኝ ከእኔ ተማሩ ብሎናል:: በሌላ ስፍራም ያዕ 3: 13፤ ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። እንደእርግብ የዋህ እንሁን ተልኳችንም ነው::

3. ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ – ነውራችንን ሁሉ አስወግዶ መገለጫችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆኗል ብቃትን ሰቶናል የእርሱ ማንነት በእኛ ውስጥ ነግሷል

4. ሳታንጐራጉሩ – ማንጎራጎር እስራኤልን በምድረበዳ አስቀርቷል እንጠንቀቅ እኛ መሆን ያለብን በሁሉ አመስጋኞች መሆን ነው ቃሉ እንደሚለን::

5. ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ – ይህ አመጸኛ ትውልድ ክፉ ማድረጉ፤ ማስጨነቁ፤ ፍርድ ማጣመሙ የማይቀር ነው እኛ ግን ይህ ሁሉ ቢደርስብንም እንኳ ለክፉ ክፉ በማድረግ ሳይሆን በፍቅር ማሸነፍ ያለብን የፍቅር ልጆች ነን

6. እንደ ብርሀን መታየት – በምትጠፋው ዓለም ላይ እኛ ብርሀንና ጨው እንደሆንን አውቀን ለሌላው እናብራ እንጂ ከጨለማው ጋር አንተባበር:: ህይወታችን መመስከሩ ብቻ አይበቃም ነገር ግን ቃሉን እንስበክ ወደ መንግስቱ ሰዎችን ከጥፋት እንሰብስብለት ለጌታ:: ኑሯችን ጌታን ካሳየ ያኔ ቃላችንን ሰዎች ያከብሩታል:: ለዝች ዓለም በጣም እናስፈልጋታለን ጌታ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነውና የራሳችንን ብርሀን እናብራ በጣም አስፈልጋታለሁ::

አገልግሎት እዚህ ጋር ጳውሎስ እንደሚለው የአክሊል መቀበያ እንዲሁም በጌታ ፊት የምናሳየው ትምክህታችን እንጂ ከዚህ ከምድር ምንም አይነት ወሮታን አንጠብቅ:: በስተመጨረሻ አገልግሎታችን በእሳት ይፈተናል:: በሌላው ደስታ ደስ ይበለን እንጂ ውስጣችን አይቆጣ::


ከራስ ይልቅ የክርስቶስን ማስቀደም

ወደ ፊልጵስዩስ 2 :19-30
19 ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። 
20 እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤ 
21 ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። 
22 ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደ ሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ። 
23 እንግዲህ እንዴት እንደምሆን ባየሁ ጊዜ፥ እርሱን ቶሎ እንድልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ 
24 ራሴ ደግሞ ግን ፈጥኜ እንድመጣ በጌታ ታምኜአለሁ። 
25 ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤ 
26 ሁላችሁን ይናፍቃልና፥ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል። 
27 በእውነት ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፥ ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይጨመርብኝ ለእኔ ደግሞ እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም። 
28 እንግዲህ እንደ ገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በብዙ ፍጥነት እልከዋለሁ። 
29 እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፥ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ 
30 በእኔ ዘንድ ካላችሁ አገልግሎት እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን እንዲፈጽም፥ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና።

ጢሞቴዎስ በጳውሎስ ፊት እንዴት ያለ ተቀባይነት እንዳለው በዚህ ክፍል ላይ እናያለን ምክንያቱ ደግሞ

  1. የራሱን ሳይሆን የክርስቶስን የሚፈልግ ነው ልክ እንደ ጳውሎስ:: በዚህ ሰዓት እስር ቤት እያለ ጢሞቴዎስን መላክ ከባድ ነው በብዙ የሚረዳውን እስር ቤትም የሚያስፈልገውን ሁሉ የሚያቀብለውን በልቡም መልእክት ሲመጣ የሚልከውን መጽናናት ሲያስፈልገ ሁሌ አጠገቡ የሚገኘውን በዚህ ወሳኝ ሰዓት መላክ ምን አይነት መሰጠት ነው? እኔ ይቅርብኝ ሄደህ እነሱን አገልግለሀቸው አይተሀቸው ተመክለስ ብሎ መላክ?!
  2. ስለ ኑሮአቸው በቅንነት የሚጨነቅ ነው:- ይህ ነገር በጳውሎስ ውስጥ ነበረ ወደ ጢሞቴዎስም ተላልፏል:: በቅንነት የጌታን ነገር ለማየት በቅን መጨነቅ አላቸው ሁሉቱም:: እንደ አካልም እንዲህ ልናስብ ይገባል ስለሌላው በቅንነት ልንጨነቅ በተለይ ክርስቶስ በህይወታቸው እስኪሳል::
  3. ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ።  ተፈትኖ ጸንቶ መገኘትን እናያለን በህይወቱ:: ወንጌልን ስናገለግል ከውስጥም ከወንድሞች ከውጭም ካልዳኑት ፈተና አለ ግን መዘጋጀትና ጌታ እንዳለን ተግተን መጸለይ ነው:: በፊቱ ስንሆን ማምለጫውን ከፊታችንም ምን እንደመጣ ይነግረናል ደግሞም ያግዘናል::

ይህ ዘመን ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም የሚለው በግላጭ የታየበት ነው ማለት እንችላለን:: የእግዚአብሔር ጸጋ ይብዛልን::

ጳውሎስ ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤ እርሱ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና።

ሌላው የሚገርም አገልጋይ አፍሮዲጡ ነው:: ሲገልጸውም ወንድም፥ ሠራተኛ ወታደር፥ በነብሱ የሚወራረድ ይለዋል:: እንዴት እንደሚያስፈልገው ቢያውቅም ግድ የለም እናንተም ናፍቃችሁታል እሱም እንደዛው ስለዚህ እልከዋለሁ ሲል ይገርማል:: ይህ ሰው እራሱን መጨረሻ ነው የሚያደርገው ያ በክርስቶስ ውስጥ የነበረው አሳብ ለሌሎች መኖር በሱ ላይ ይታያል:: ተቀበሉት እንዲህ አይነቶቹንም የእግዚአብሔር ባሪያዎችን አክብሩ ይለናል::

እኔም እግዚአብሔር መምሰል እራሴን ማስለመድ እንዳለብኝና ሌሎችን ማስቀደም ስለቅዱሳን ኑሮ ማሰብና መማለድ እንዳለብኝ ተምሬያለሁ:: ደግሞም እግዚአብሔር እንዴት ስለእኛ እንደሚጠነቀቅ አይቻለሁ አፍሮዲጡ ታሞ እንዴት ከሞት እንደተረፈ እናያለን ወንጌልን ስናገለግል የፈተናው ዘርፈ ብዙ ነው ግን እንታገስ ሁሉ ያልፋል ጌታ ብቻ ይክበር:: አሜን!


ምዕራፍ 3


ተጠበቁ! ከምን እንጠበቅ?

ወደ ፊልጵስዩስ 3:1-2
1፤ በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው።. 2፤ ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።

ወንድማችን ጳውሎስ ከእስር ቤት በጌታ ደስ ይበላችሁ ይለናል:: በጌታ ደስ መሰኘት የሚመጣው ከሁኔታ ሳይሆን በውስጣችን ካለው መንፈስ ነው:: ደስታ የመንፈስ ፈሬ ነው ስለዚህ ሁልጊዜ በውስጣችን የሚገኝ በነገሮች ያልተደገፈ የጌታ ስጦታ ነውና በራሱ በጌታ ደስ ይበለን:: ዛሬ በምንም ነገር ውስጥ እያለፍን ቢሆን አሁን ቆም ብለን በዚህ ደስታ ውስጥ ለመሆን እንውስን ደግሞም እንጽና ምን እንዳይመጣ ነው? ሁሉን የሚቆጣጠረው እኮ አባታችን ነው:: ሃሌሉያ! አሜን!

ከዚህ በፊት የነገርኳችሁ ቢሆንም እንኳ ደግሜ ልንገራችሁ ይላል:: የተደገመ ነገር ላይ አትኩሮት ማድረግ ጥሩ ነው:: ሊደግምላቸውም የፈለገው ነገር ስለ መጠበቅ ነው:: ከምንድነው ተጠበቁ የሚላቸው?

  1. ከውሾች ተጠበቁ፥ መቼም ውሻ ሲለን እንስሳውን እንዳልሆነ ግልጽ ነው:: ምሳሌው ከአህዛብ አስተሳሰብ ለማለት ነው:: አህዛብ ሐጥያተኛና ከእግዚአብሔር የራቁ እንደሆኑ የታወቀ ነው ስለዚህም እስራኤላውያን በውሻ መስለው መጥራታቸው ይህንን ያመላክታል:: ጌታችንም በማቴ 15: 26፤ እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም፡ አለ። ስለዚህ መጠበቅ ያለብን ከአህዛብ አስተሳሰብ ነው እኛ ህይወታችንን ለጌታ የሰጠን ነን ለራሳችን አንኖርም ለሞተልን እንጂ እነሱ እንደወደዱ ሲሆኑ ከነርሱ ጋር አብረን እነሱ የሚያደርጉትን ሁሉ አናደርግም ይህ እስራት እንዳይመስለን መቀደስ እንጂ ውስጣችንም እሺ አይለንም:: የተከፈለልን ዋጋ ብዙ ነውና ወስደን አንቀላቅለውም::
  2. ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ በየጊዜው የተለያዩ አገልጋዮች ይነሳሉ እኛ ግን ማየትና መመዘን ያለብን በፍሬያቸውና በአኗኗራቸው መሆን አለበት:: የዋህ ልብ ክርስቶስን የሚመስል ማንነት እንጂ ክፋትን ካየን አለመተባበር እንዳለብን እንወቅ::
  3. ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ:- መገረዝም ሁለት አይነት ነው ማለት ነው:: አንዱ የስጋ ብቻ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንፈስ ነው:: መጀመርያ መገረዝ የተሰጠው አብረሀም ነበር ግን አላጸደቀውም:: የጸደቀው በእምነት እንጂ:: የስጋው መገረዝ በራሱ ምንም አያደርግም በእምነት በክርስቶስ ያገኘነው ግን አዲስ ፍጥረት አድርጎናል:: በገላትያ 5: 6፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።

ማን ነን?

ወደ ፊልጵስዩስ 3: 3
እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና። 
ስለማንነታችን እስኪ ትንሽ እንይ:-

  1. በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ:- የእኛ እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚመለከውም በእውነትና በመንፈስ እንደሆነ ጌታ እየሱስ ነግሮናል::
  2. በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ :- እየተከሰስን ወይም ደግሞ አንዳችን ለውጥ ለማምጣት በጽድቃችን ላይ ለመጨመር አይደለም:: የክርስቶስ ደም ከሞተ ህሊና ሁሉ ታድጎን በእርሱ እየተመካን በሆነልን ነገር ላይ አንዳች እስከማንጨምር ድረስ በተጠናቀቀ ድል ላይ ልባችንን ሞልተን እንደልጅ እንመላለሳለን ይህንን ትምክህት የሰጠን የታረደልን እየሱስ ስሙ ይባረክ! አሜን!
  3. በሥጋም የማንታመን :- የስጋን ትምክህት አሽቀንጥረን የጣልን ነን:: በስጋ በመመላለስ መጽደቅ የሚቻል ቢሆን ኖሮ እየሱስ ለምን ይህንን ሁሉ ዋጋ ከፈለ?
  4. እኛ የተገረዝን ነን:- በቁ 2 ከላይ እንዳየነው ከሀሰተኛ መገረዝ ስለመጠበቅ ይነግረናል:: እውነተኛ አለ ማለት ነው እርሱም እኛ በመንፈስ ተገርዘናል በስጋ ሳይሆን በቆላስይስ 2: 11፤ የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። እኛ በእጅ አይደለም የተገረዝነው በእጅ የተገረዙት ልባቸው ሳይገረዝ ቀረ የእኛ ልብ ግን በጌታ ተገረዘ:: በዚህ ዘመን የመገረዝ ጉዳይ አሳሳቢ አይደለም በመንፈስ የመቀደሱ ጉዳይ ላይ ግን ለመቀበል ችግር አለ:: የተቀደስኩት መቀደስ በቂ አይደለም ልጨምርበት የሚለው ሀሳብ በዛ ዘመን ተገረዙ ከሚሉት አይለዩም ባይ ነኝ:: የክርስቶስ ስራ አልተጠናቀቀም እንጨምርበት እንደሆነ ያስተዋልን አልመሰለኝም እርሱ ተፈጸመ ብሎ ሳለ:: ሁልጊዜ የሆነ ደረጃ ላይ ለመድረስ መጣር ነው የያዝነው የተደረገልን አልበቃ ብሎናል በአንድ ጊዜ መንፈሳችን እንደተለወጠ አኮ አይደለም ነፍሳችን የምትለወጠው እንደተወለደ ልጅ እየተማረች የእግዚአብሔርን እውቀት በማወቅ ታድጋለች:: ማስታወስ ያለብን በአብ ቀኝ ወስዶ ስራ አለቀ ቁጭ በሉ ብሎናል:: ይህ ማለት ግን ለሐጥያት ፈቃድ እንደመስጠት የሚቆጥሩት አሉ አሳቡ እራሱ ከየት መጣ የሞተ ይነሳል እንዴ እኛ ለዓለም ሞተን ለክርስቶስ የምንኖር ነን:: ጸጋ ይብዛልን!

ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ

ወደ ፊልጵስዩስ 3: 4-11
4፤ እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። 
ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። 
– አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤  10 11 እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። 

መመካት ቢኖርብኝ ብዙ የምመካበት ነገር አለኝ ይላል ጳውሎስ ባለው እስታንዳርድ በማሕበረሰቡ ዘንድ ፐ! የተባለ ነበር ጳውሎስ ሁሉንም መስፈርት አሟልቶ የሚኖር ነበር :: በሰው ፊት አልፏል በእግዚአብሔር ፊት ግን ከንቱ ነበር:: እውነት የሆነውን ባየ ጊዜ ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ:: ይህንን ሁሉ ዘመኑን የለፋበትን በማኅበረሰቡም ዘንድ ትልቅ ተቀባይነትንና የከበሬታ ወንበር የሚያሰጠውን ሲተው ሞኝ ያሰኛል:: ለእግዚአብሔር ቀንቶ ሲያሳድዳቸው የነበሩትን ተቀላቅሎ ምን ነካው የሚያስብል ነገር ነው በህይወቱ የሆነው:: ሁሉን ለክርስቶስ ስል ትቼዋለሁ ይላል ስደትና መከራ የሚያመጣበትን መንገድ መረጠ::

በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ለጳውሎስ ይህንን ሁሉ ቢያጣም በምድር ለሱ ቦታ ያለው ጉዳይ ጌታውን ማወቁ ነው:: ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥

ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥

በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ ያንን ሁሉ ዘመን የፈጀሁበት የራሴን ጽድቅ ላቆም ነበር ግን ትክክለኛው በእምነት የሆነው እንጂ እኔ ስጠብቅ የኖርኩት ህግ አይደለም::

በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤  እግዚአብሔር አብ ሊያየን የሚፈልገው በክርስቶስ ውስጥ ነው:: የእርሱ ጽድቅ ተቆጥሮልን የራስን ጽድቅ ማቆም ትተን በእርሱ ውስጥ መገኘት::

እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በሮሜ 6: 5፤ ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤

በመከራውም እንድካፈል፥ ክርስቶስን ተከትለን ጠላት መከራ አያመጣም ማለት ዘበት ነው ቢመጣም ግን እንጸናለን::

ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።  ከፈለጉ ህይወቴን ይውሰዱ እንጂ እኔስ እስከመጨረሻ እርሱን እመስላለሁ የሚል አቋም አለው::

እኛም ዛሬ አንዳችም ጽድቅ ማቆም የማንችል መሆናችንን አውቀን በእርሱ ውስጥ እንዳለን አውቀን መንገዳችንን እርሱን በማሳየት እንኑር::


እንዴት ሩጫችንን እንሩጥ

ወደ ፊልጵስዩስ 3:12-13
12፤ አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። 13፤ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥

አሁን እንደያዝኩት አልቆጥርም የሚለን ደህንነቱን አይደለም ሰው ከእግዚአብሔር አንድ ጊዜ ከተወለደ አይጠፋም አምላኬ አይደለም ብሎ እስካልካደ:: እዚህ ጋር ጳውሎስ የሚለው ስለ አገልግሎቱ አልረካሁም እርሱ ለእኔ ብዙ ዋጋ ከፍሏልና ገና እንደሚገባ አላገለገልኩም ለማለት ነው:: እሱ እንደዚህ ካለ እኛ ምን እንበል? ደህንነት አንድ ጊዜ ተቀብለን የሚቆም አይደለም ጌታን ማገልገልና እምነታችንን እግዚአብሔርን በመምሰል እየኖርን ማሳየት አለብን:: በሌላም ስፍራ ፀንተን ሐይማኖታችንን እንጠብቅ ይለናል::

ጳውሎስ ሩጫውን ሲሮጥ እንዴት እንደሆነ ይነግረናል:- 1. እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ:- ማን እንደኔ እዩ እስኪ የደረስኩትን ቦታና የሰው ብዛት እያለ ጉራውን አይቸበችብም ገና አልያዝኩም እያለ ነው:: ዝቅ ብሎም ሐዋርያት ጋር ሄዶ እንዴት ነው ወንድሞች አገልግሎቴ ብሎ የጠየቀ ሰው ነው እነርሱ ግን መቀበል አቅቷቸው ገፍተውት ነበር መለወጡን ተጠራጥረው:: ስለራሱ ክብር ሳይሆን ስለጌታው ብቻ ነበር የሚታየውና የሚያስበው:: አንድ ብቻ ነው ተልዕኮውና ግቡ እርሱም ጌታን ማገልገል! እኛም በግል ጉዳይ ከመከራከር ወተን ጌታን ብቻ ማክበርና ማገልገል ላይ ልባችንን ማድረግ አለብን::

2. በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ :- በእርሱ ውስጥ የሚሰራው ጌታ እንደሆነ ስለገባው የኃላውን እየረሳ ሁልጊዜ ወደፊት ነው የሚያየው ልዘክርም ቢል ጌታን ብቻ ነው የሚያሳየው:: እኛንም ጌታ ይርዳን!

3. በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ ሁልጊዜ ወደፊት ማሰብ ነገ ጌታ ምን ሰርቶ ያስደንቀኝ ይሆን፥ ማነው የሚድነው፥ የት ነው የሚልከኝ ብለን ወደፊት እንደጳውሎስ እናስብ እንጂ ባለፈው ድል ወይም ደግሞ ሽንፈት ላይ አይሁን አይናችን:: ከሰዎችም ጋር ያለንን ነገር በክርስቶስ ውስጥ እናድርግ ሰዎችን ከክርስቶስ ውጪ አንያቸው::


በደረስንበት በዚያ እንመላለስ

ወደ ፊልጵስዩስ 3: 14-16
14፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። 15፤ እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ 16፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ።

በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ እፈጥናለሁ ይለናል:: እኛ ከፍ ላለ ነገር ተጠርተናል በእግዚአብሔር:: እሩጫ ውስጥ እንዳለ ሰው ነው እራሱን የሚቆጥረው ግን ይህ የሩጫ ውድድር ለየት ያለ ነው ምክንያቱም ከጎናችን ካለው ጋር አይደለም የምንወዳደረው የተነገረን ውድድሩን ጨርሱ ነው:: እኛ ሰውን ኮፒ አናደርግም ነገር ግን በተሰጠን ጸጋ ክርስቶስን ማክበር ነው ጎላችን:: የግድ ዳዊት ጦረኛ ለመምሰል የሳዖልን ልብስ መልበስ የለበትም ጌታ ያለማመደው በወንጭፍ ነውና ድሉም በዛው ነው የሚገኘው:: የተሰጠንን መክሊት እናትርፍበትና ለአክሊል እንብቃ ያልሰጠውን የሚጠብቅ ፍርደ ገምድል ጌታ አይደለም ያለን:: ጳውሎስ በመጨረሻ ሩጫዬን ጨርሻለሁ ብሎ የህይወቱን ምዕራፍ ዘግቷል:: የጀመርነውን ሩጫ ሮጠን እንድንጨርስ ጌታ ይርዳን::

ሌላው የሚገርም አባባል በዚህ ክፍል ላይ:- ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ:: ምን የሆንን?! ፍጹማን! አይገርምም ፍጽምና ተሰቶናል:: ምን እንድናስብ ነው ወንድማችን የሚነግረን? በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል ይለናል:: የጠራን ጌታ ነው የሚያሰማርንም እርሱ ነው ግድ እንደነ እንትና መመላለስ የለብንም:: ስለበጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም እርሱ አይደል በእኛ የሚሰራው? ስለዚህ ሁሉን ከእርሱ ጋር እንጨርስ:: በምንም አይነት ሌላው የሄደበትን አንፈልግ ኦርጅናል የሆነ አሰራር አለው ለእያንዳንዳችን ስለዚህ የራሳችንን መንገድ እንጠብጥብ በሌላው እየገባን እንቅፋት አንሁን ሌሎችም እንቅፋት እንዲሆኑብን አንፍቀድ::


ጌታን ምሰሉ

ወደ ፊልጵስዩስ 3:17-19
17፤ ወንድሞች ሆይ፥ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፥ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ። 18፤ ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። 19፤ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው።

ጳውሎስ ደስ የሚለኝ አንዱ ነገሩ እየሱስን እንደሚመስል እርግጠኛ መሆኑና እኔን ምሰሉ ብሎ በድፍረት ማለቱ ነው:: ማንን እንመስላለን? ልንመስል የተጠራነው እየሱስን እንጂ ቤተክርስቲያናችንን ወይም ክርስቶስን የማይመስሉ መሪዎችን አይደለም ሁልጊዜ አይናችን በጌታ ላይ ይሁን:: እርሱን የሚመስሉትን ተመልከቱ ምሰሉዋቸው ደግሞም ለሌሎች ምሳሌ ሁኑ ነው የሚለን:: ምክንያቱም ብዙዎች ለመስቀሉ ጠላቶች ሆነው ነው የሚመላለሱት::

ለመስቀሉ ጠላት መሆን ምን ማለት ነው? ጳውሎስ እንዲያውም አለቅሳለሁኝ ስለነሱ ምክንያቱም መጨረሻቸው ጥፋት ስለሆነ ይላል:: ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው:: ጠላት መሆን ማለት ይህ ነው! የሚያስቡት ሁሉ ለራሳቸው እንጂ እነ ጳውሎስና ጢሞቲዎስ እንደሚያስቡት ስለክርስቶስና ስለአካሉ አይደለም:: ሁሉን ትቶ እኛን ብሎ የመጣውን ጌታ ነው ማክበር ያለብን:: የመስቀሉ ጠላቶች አሳባቸው ሁሉ ምድራዊ ነው እኛ ግን ከዚህ ምድር አይደለንም ስጋን ከክፉ መሻቱ ጋር ሰቅለናል:: (በሮሜ 8:5-8) እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ:: ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። አለቀ! ጌታን በስጋ ደስ ማሰኘት አይቻልም!

ስለዚህ ዛሬ እንዴት እንመላለስ? ጌታን በመምሰል የምድሩን ሳይሆን የሰማዩን እያሰብን እንመላለስ፥ እርሱን የሚመስሉትን እየደገፍን፥ በታማኝነት እንመላለስ::


እኛ አገራችን በሰማይ ነው

ወደ ፊልጵስዩስ 3: 20-21
20፤ እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ 21፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።

አገራችን በሰማይ ነው ብለን ስንል ጌታ እራሱን ባዶ አድርጎ፥ ተዋርዶ፥ የባርያን መልክ ይዞ የመስቀል ሞት ሞቶ እዳችንን ከፍሎ ነው ወደዚህ ክብር ያመጣን:: ስለዚህ እኛም በትክክል የዚህ አገር ዜጋ መሆናችንን ለማሳወቅ እታች እላይ ማለት የለብንም እኛው እራሳችን ካልገባን በቀር:: ምሳሌ ልስጣችሁ:- ኢትዮጵያዊ ለመሆኔ ማስረጃዬ ምንድነው? አንድ ሰው አይደለሽም ቢለኝ ያዙኝ ልቀቁኝ እላለሁ እንዴ? ተወው ብዬ እሄዳለሁ እንጂ የዛ ሰው ማመንና አለማመን ማንነቴን እንደማይቀይረው ስለማውቅ ዝም ብዬ እሄዳለሁ ምክንያቱም ውስጤ ተዋህዷል፥ እርግጠኛም ነኝ:: ልክ እንደዚሁ ኖርማል መሆን ነው ያለበት ወደዚህ እረፍትና አገር የመግባቴ ጉዳይ እንጂ እወቁልኝ ብዬ የምለፍፈው አይሆንም ከኔ ጋር ሲዋሀድ::

እኛ ተስፋ የሌለን አይደለንም ተስፋችን፥ መድኃኒታችን ጌታ እየሱስ ይመጣል እርሱን የምንጠባበቅ ነን:: ስፍራ ላዘጋችላችሁ እሄዳለሁ ብሎ ቃል ገብቶልናል:: እመጣለሁ ብሎን አሳቤን ቀየርኩኝ የማይል እውነተኛና ታማኝ ጌታ ነው! ሃሌሉያ!

ሲመጣ ተዘጋጅተን እንጠብቅ ይህንን ዓለም በመናቅ እርሱን በመምሰል እንመላለስ:: ሲመጣስ በእኛ ላይ ምን ይሆናል ብለን ስንል ለአሰራሩ እንዲመቸው ይህን ስጋ ክቡር ስጋውን እንዲመስል ይቀይረዋል:: እንዴት? ስንቶቻችንን? ብዙ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል አይደል? ቀመቅጽበት የሁላችንም የተዋረደ፥ ደካማ ስጋ ይለወጣል:: ለዛኛው አገር እንዲሆን ተደርጎ እናም ከዛ በኃላ ድካም፥ ሞት፥ ለቅሶ፥ ሰቆቃ፥ ኃዘን የለም! የለም! የለም!!!! አሜን ለታረደው በግ ክብር ይሁንለት:: ይህንን ለማየት በጣም እናፍቃለሁ፥ እጏጏለሁም:: ይህ ሁሉ በነጻ የተሰጠኝ እድለኛ ሰው ነኝ:: ከእግዚአብሔር ቁጣ ያመለጥኩኝ፥ ልጅነት የተሰጠኝ ነኝና የዓለምን ነገር ንቄው እኖራለሁ ለጌታ ክብር:: ደግሞም ለዚህ ጌታ ስኖርለት አንዳች ጸጋ አይጎድለኝም በሚያስፈልገኝ ሁሉ ይሞላኛል እውስጤም ሆኖ ያበረታኛል ያ ቀን ሲመጣ እኔ በእርሱ ውስጥ እርሱም በእኔ ውስጥ እንዳለ አውቃለሁ::

ከዘላለም እስከ ዘላለም ስሙ ይባረክ:: አሜን


ምዕራፍ 4

ምዕራፍ 4 ንባብ
በጌታ ቁሙ

ወደ ፊልጵስዩስ 4: 1-3
1፤ ስለዚህ፥ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ፥ እንዲሁ በጌታ ቁሙ፥ ወዳጆች ሆይ። 2፤ በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። 3፤ አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎቹ ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና።

ከላይ ሲነግረን እንደመጣው አገራችን በሰማይ ነውና ከዛም የሚመጣ መድኃኒት እንጠባበቃለንና ጸንታችሁ በጌታ ቁሙ ይለናል:: ጸንተን ስለመቆም ከተነገረን መቼም ሊጥለን የሚጋፋ ነገር አለ ማለት ነው:: ጌታም እንደነገረን በዚህ ዓለም ስንኖር አልጋ ባልጋ ነው አልተባልንም የተባልነው አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌያለሁና እረዳችኃለሁ እንጂ:: ስለዚህ ጸንተን በጌታ እንቁም:: ሌላው ጳውሎስ እንዴት እንደሚወዳቸው እዚህ ጋር ማየት ይቻላል:- የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ እያለ ይገልጽላቸዋል ፍቅሩን:: ለታይታ ወይም አንዳች ፈልጎ ሳይሆን ከውስጥ የሆነ መውደዱን ነው የሚያሳውቃቸው እነሱን በማገልገሉ የደረሰበት መከራና ግርፍ ነው እንጂ ድሎት አልነበረም ግን አሁንም ይናፍቃል ሊያያቸው መከራ ቢጠብቀውም እንኳን:: ምን አይነት ፍቅር ነው?! ጌታ እንደዚህ ያለ የወንድማማችን መዋደድ በውስጣችን ያድርግልን::

መቼም ጌታን ስናገለግል በተለያየ አሳብ ላይ አለመግባባት ይኖራል ምክንያቱም ሰው የተለያየ አቋም፥ አስተዳደግ፥ አመልና አመለካከት አለው:: አንድ ሊያደርገን የሚገባው እዚህ ጋር ጳውሎስ የሚመክረው በአንድ አሳብ በጌታ መስማማት ነው:: የመስማማታችን ምክንያት ጌታ መሆን አለበት ይህ እርሱን ደስ ያሰኘዋል ወይ ሊሆን ይገባል የሚያሳስበን:: ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም እንዳለው የክርስቶስን የምንፈልግ ከሆነ በአንድ አሳብ ጌታን ለማክበር አንቸገርም:: የህይወታችን ማዕከል ጌታ ብቻ ሊሆን ይገባል::

አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ ይላል:: አብሮ መጠመድ ምሳሌው ልክ ሁለት በሬዎች ተጠምደው አብረው እንደሚያርሱት ያለ ምሳሌ ነው:: አንዱ ወደግራ ሌላው ወደቀኝ ልሂድ ቢል ስራ አይሰራም ግን ግባቸውን አውቀው በአንድ አሳብ ላይ ቢስማሙና ቢሰሩ ግን ውጤት ይኖረዋል:: በእውነት ጌታን ከሚከተሉና ስማቸው በህይወት መጽሐፍ ከተጻፈው ጋር ህብረት ማድረግና መተጋገዝ ያስፈልጋል::


ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ

ወደ ፊልጵስዩስ 4: 4-5
4፤ ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ:: 5፤ ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ።

ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ ትእዛዝ ነው ምክንያቱም ደስታ የመንፈስ ፍሬ ነው እኛም ውስጥ አለ:: ደስ ይበላችሁ ብሎ ጳውሎስ የሚጽፍልን ከእስር ቤት ነው ይህ የሚያሳየው በውጭው ሁኔታ አይደለም ደስታችን ከውስጥ እንጂ:: ከውስጣችን ይህንን ደስታ መውሰድ የሚችል የለም በእኛ ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ ሞልቶናልና ማን ይወስድብናል? ደስ ይበላችሁ ብሎ በቃሉ ዛሬ ሲናገረን የማይቻል ነገር አድርጉ ብሎ እየፈተነን አይደለም የኛ ጌታ ማንንም በክፉ አይፈትንምና:: ስለዚህ በዙሪያችን ያለው ነገር ደስ ለመሰኘት የማይደግፍ ቢመስልም እንኳን እኛ ግን ዙሪያችንን ሳናይ በጌታ ደስ ይለናል:: አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም ያለን ደግሞም የሚለው ደስ ይበላችሁ በጌታ ነው:: ስለዚህ በየዕለቱ ደስ ሊለን ይገባል በጌታ:: አሜን!

ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ ሲለን ኑሩት የጌታ ባህርይ በእናንተ ይታይ እርሱ ገር እንደነበር እንዲሁ ተመላለሱ አሳዩት ለዓለም እያለን ነው:: በማቴ 5:14-16 (14 እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። 15 መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።  16 መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ) በሰማይ ያለው አባታችን የሚከብረው እኛን በማየት ነው እኛ የሰማይ መንግስት አምባሳደሮች ነን:: የምንወክለውን መንግስት እናሳይ ዛሬ ጌታ በእኛ ውስጥ ሆኖ መስራት ይፈልጋል የሚሰራውም ሰዎችን ማዳንና ለመንግስቱ ማብቃት ነው:: ለዚህ የተቀደሰ አላማ ተጋብዘናልና ጌታን እናሳይ ለሁሉ:: በመምጣቱ ፊት የምናፍር እንዳንሆን ዛሬ ጊዜ ሳለ በየዋህነትና ለሌሎች በማሰብ እንመላለስ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ጌታ ቅርብ ነውና በአንዳች አትጨነቁ

ወደ ፊልጵስዩስ 4:6-7
6፤ ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። 7፤ አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።

ጌታ ቅርብ ነው!! እውነት ነው ቅርብነቱ ያለንን እናስብ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ አላለምን? ደግሞስ መንፈስ ቅዱስ በእኛ እንደሚኖርና እኛው ብቻ ይህንን እንደምናውቅ ዓለም ግን እንደማያውቅ አልነገረንም? ታድያ ከዚህ በላይ ቅርብ መሆን ምንድነው? እርሱ በእኛ ውስጥ ከመኖርና የአብሮነቱን ቃሉ ከመስጠት በላይ? አሁን በዚህ ሰዓት እርሱ ቅርብ መሆኑን ማየትና መለማመድ ይቻላል:: እውነተኛ ስለሆነ:: ቃሉን ዛሬ በውጣችን እንሸሽግ ያሻግረና ምድረበዳ ወደ ህይወታችን ሲመጣ የምንይዝ የምንጨብጠውን የምናጣው ቃሉ ከእኛ ጋር ስላልተዋሀደ አይደለምን? ዛሬ ቀን ሳለ እናሰላስለው እንጸልይበት ቃሉን::

በነገር ሁሉ

  1. በጸሎትና
  2. በምልጃ
  3. ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ
  4. በአንዳች አትጨነቁ

ቅርብ ወደሆነው ጌታ ተጠግተን ልመናና ጸሎታችንን ካሳወቅን በኃላ በምስጋና መሆንና ጌታ እንደሰማን አውቀን በጉዳዩ አለመጨነቅ ነው ያለብን:: አንድ ምሳሌ ላምጣ:- በጣም የምትወዱት በተለይም የሚወዳችሁና የምትጠይቁትን ነገር ለማድረግ የሚችል ሰው ጋር ስልክ ደውላችሁ ጉዳያችሁን ነግራችሁ እርዳኝ ብትሉና ያ ሰው አረ ምንም ችግር የለም ነገ ጠዋት የመጀመሪያ ነገር እሱን ነው የማደርገው ቢለን ምን ይሰማናል? ደስ ብሎን ፈንድቀን እንቅልፍ ሳናጣ ተኝተን እናድር የለ? ታድያ ማንም እወዳለሁ የሚል ሰው ሊያደርግልን ያልቻለውን የመስቀል ሞት ሞቶ ያሳየንን ወደፊቱ ስንቀርብ ቀድሞ እንደ ወገግታ ተዘጋጅቶ የሚጠብቀንን ጌታን መታመን ጸሎቴ ተሰምቷል ብለን መነሳትና ማመስገን፤ አለመጨነቅ ምነው ከበደን? አጭር ነው መልሱ እርሱን በደንብ ካለማወቅ ነውና የጸለይነው ሁሉ ተሰምቷል ሰው ከሰው እንኳን ይሰማማል እንኳን የኛ ጌታ ተናግረን ይቅርና ሳንናገር ይሰማናል:; አሜን! ስንጸልይ የኔ ፋይል ተረሳ ወደ ስር ሆነ የሚል አስተሳሰብ ነው ያለን ማለት የሚገባን በእጁ ሰጥቼዋለሁኝ አባቴ ሰምቶኛል የሚል ልብ ይዘን ከፀሎት ልንነሳ የሚገባን::

አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል ሲለን እሱ የሚሰጠን ሰላም በምንም አይነት በዙሪያችን የሚፈጠር ነገር አይነቀንቀውም እየተባልን ነው:: ልባችንን የሚጠብቀው በፊቱ ቀርበን ጸልየን የሚያስጨንቀንን ስንሰጠ እርሱ ደግሞ ሰላሙን ይሰጠናል እንጂ ሰላም ስጠኝ ብሎ ጸሎት የለም:: ሰላም ያሳጣንን በፊቱ ይዘን ስንቀርብ እርሱምጸሎታችንን ሰምቶ ከእኛ ሲወስደው ሰላማችን የትም አልሄደምና እናገኘዋለን እኛው ጋር:: ሰላም የመንፈስ ፍሬ ስለሆነ ይገለጣል ከላዩ ላይ ያስቀመጥነውን ጭንቀት ስናነሳና በጌታ ላይ በእምነት ስናስቀምጥ:: ስለዚህ ልባችንን ይጠብቃል ምክንያቱም የህይወት መውጫ ነውና አሳባችንንም ይጠብቃል ምክንያቱም አሳባችን ከተያዘ ሁለንተናችን ይያዛልና:: ቃሉን እንኑረው! ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!


እነዚህን አስቡ

ወደ ፊልጵስዩስ 4: 8-9
8፤ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ:: 9፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።

በቀረውስ፥ እነዚህን አስቡ

  1. እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
  2. ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥
  3. ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
  4. ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
  5. ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥
  6. መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥
  7. በጎነት ቢሆን፥
  8. ምስጋናም ቢሆን፥

ለምን እነዚህን አሳቦች እናስብ? ምክንያቱም ጳውሎስ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን ነውና እያለ ነው:: ከላይ ባሉት ቁጥሮች ስለ ስላም አንስቶ ነበር አእምሮንና ልባችንን እንደሚጠብቅ፥ ይህ የሚሆነው ነገራችንን ሁሉ በእርሱ ላይ አድርገን ሳንጨነቅ ስንቀር ነው:: ስለዚህ እንዚህ 8 አሳቦች አሳባችንን ቢሞሉት ሳንናወጥ፥ ሳንጨነቅ፥ ሰላማችን ተጠብቆ እንመላለሳለን የሰላምም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል::

ክርስትናን ታድያ ከባድ ያደረግነው እኛው አይደለን? የእኔ ሸክም ቀሊል ነው እያለን ጌታ ወይ ክርስትና! የምንል እንዳንሆን ብቻ! ጳውሎስ ያያችሁትንም ኑሩት እንደሚለውስ ህይወታችን ምን ያህል ጌታን ያሳያል? አፋችንን ሞልተን ምሳሌ ልሁናችሁ ማለት እንችል ይሆንን? ጌታ ይርዳን!


ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ

ወደ ፊልጵስዩስ 4: 10-14
10፤ ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። 11፤ ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና።. 12፤ መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። 13፤ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። 14፤ ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ።

በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ ይላቸዋል ማጣት መከራ ነው:: ከዝች ቤተክርስቲያን በስተቀር ጳውሎስ ስለስጦታ የሚጠቅሰው የለም:: ችግር አለብኝ እርዱኝ እናንተን ለማገልገል ነው እንደዚህ የምኖረው ብሎ ስለ ራሱ አያሳይም ስለ ክርስቶስ እንጂ እኔ ሞቻለሁ ነው መፈክሩ:: የሞተ ደግሞ ብዙ አያስቸግርም ይሄ ይሁንልኝ ለምቾቴ አይልም አመለካከቱን ሁሉ በጌታ ላይ ያደረገ ሰው ነውና:: ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ ለማለት መሞት ይጠይቃል:: ኃይል የሚሰጠው ጌታን ለማገልገል ነው እንጂ የፈለግነውን እያደረግን ኃይል ስጠኝ የለም::

እንደ ገና ስለእኔ ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በማለት ከዚህም ቀደም ስጦታን እንደሰጡት ያነሳል:: ግን ይህን ሲል ረሳችሁኝ እንዳልሆነ እንዲረዱለት ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና።. በኑሮዬ ይላል ጳውሎስ ምናልባትም አብዛኛዎቻችንን የሚነካ ነገር ውስጥ አልፏል:: እነዚህም:

መዋረድንም አውቃለሁ

መብዛትንም አውቃለሁ፤

በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና

መራብንም

መብዛትንና

መጉደልን ተምሬአለሁ።

ስለዚህ በዚህ ዝርዝር ውስጥ እንኳን በሌለ ነገር ውስጥ የምናልፍ ብንኖር በእኛ አልተጀመረም መከራና ሰልፍ ከመንገዳችን ዝለን እንዳንደክም ኃይል እየጠየቅን ጌታን እያስከበርን መንገዳችንን እንጏዝ:: የምድርን ነገር እንዳው እያደመቅን አናሳይ ጌታን እንጂ:: በጌታ ወንድሞቻችን የሆኑትን በተለይም አገልጋዮችን መርዳት አስፈላጊ ነው:; ወንድምህ ርቦት እሳት ሙቅ ማለት ስህተት ነው ስለዚህ መርዳት የምንችል ሁሉ ለመርዳት እጃችንን እናንሳ::


የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል

ወደ ፊልጵስዩስ 4:15-23
15፤ የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ 16፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። 17፤ በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። 18 ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። 19 አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። 
20 ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።  21 ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።  22 ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 23 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

በመስጠታችን ሰውን ማስደሰትና የእግዚአብሔርም ስም እንዲመሰገን ምክንያት እንሆናለን:: ጳውሎስ ስለ ስጦታቸው ማመስገን ብቻ ሳይሆን መርካቱንም ይነግራቸዋል ተሞልቼዋለሁ በማለት:: አፍሮዲቱ ምን ያህል እርቀት እንደመጣ ማሰብ ነው ብዙ የመጏጏዣ አማራጭ በሌለበት ዘመን ይህንን ሁሉ እርቀት ለመሄድ መነሳሳት በጣም ይገርማል:: ፍቅር ግን ይህንን እንድናደርግ ብቃት ይሰጣል የእነዚህን ሰዎች ፍቅር አይቻለሁ:: ጳውሎስም አምላኬ እንደባለጸግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኃል ነው የሚላቸው ከስጦታቸው የተነሳ:: ለተቸገረ ስንሰጥ ጌታ ይሰጠኛል በሚል ልብ ሳይሆን በልግስና ስንሰጥ እግዚአብሔርን ያስደስተዋል ለዛም ደግሞ ይባርከናል::

እዚህ ጋር ሰላምታ ያቀርቡላችኃል ከሚላቸው ወገኖች መካከል ከቄሣር ቤት የሆኑ የሚላቸው አሉ:: እነዚህ በመጽሐፉም መግቢያ ላይም የገለጣቸው እስራቴ በንጉሱ ዘበኞችና በሁሉ ዘንድ ስለክርስቶስ እንደ ሆነ ታውቋል ይላል:: እነሱንም ሰብኮ ወደ መንግስት አምጥቷቸው ነበር ማለት ነው:: እስራትም ውስጥ ቢሆን እንኳን የእግዚአብሔር ቃል አልታሰረም ነበር:: ዛሬም ጌታ ይሰራል:: ስሙ ይባረክ የኛ ጌታ!


የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።



Published by Betty & Abera

We’re dedicated to share God’s goodness and mercy through His word!

2 thoughts on “ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች

Leave a reply to Asrat Chinasho Cancel reply