መግቢያ
የዚህ መጽሐፍ ዓላማ
- ቃል በገባው መሰረት ለምን ወደ እነርሱ ለመምጣት እንደዘገየ ለማብራራት (16:5-9):: ልዩነታቸውን እስኪያስወግዱ እየጠበቀ እንደነበር ለማሳወቅ (1:23-2:3) እንዲሁም በመካከላቸው ይቅርታን እንዲያደርጉ በተለይ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቼዋለሁ ካለው ሰው ጋር (2:5-11)፤
- ሐዋርያ መሆኑን ረገጥ አድርጎ ሊነግራቸው (3:1-3; 4:1-15; 10:10-14; 11:4-6, 13-15; 13:3) እና
- ተጨማሪ መመሪያ ለእየሩሳሌም ስለሚሰበሰበው መዋጮ ለማስገንዘብ ነው (9:1-11)
ይህ ቤተክርስቲያን የተመሰረተው በሁለተኛው የጳውሎስ የወንጌል ጉዞ ላይ ነው ጉዞው በሐዋ 18:1-18 እና 20:2-3 ተጠቅሷል:: ቤተክርስቲያንዋ ችግር ስለነበረባት በብዙ ይገናኙ ነበር ከጳውሎስ ጋር: ኤፌሶን እያለ የመጀመሪያውን ደብዳቤ ጻፈ ከዛም ወደ እነርሱ መቶ ጎብኝቷቸዋል (2:1-2) ከጉብኝቱ በኃላ ያለውን መረጃ አድርሰውታል:: ለዛ መረጃ ነው ይህንን መጽሐፍ የጻፈው:: በሐዋ 20:1-3 መሰረት ሊጎበኛቸው መቷል::
የመጽሐፉ ጸሐፊው እራሱ ጳውሎስ ነው (1:1; 10:1)
ምዕራፍ 1
2ኛ ቆሮንቶስ 1: 1-2
1፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ 2፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ እንደሆነ የሚነግራቸው የማይቀበሉትና የሚገፉት ሰዎች ስለነበሩ ነው ግን እርሱ ሐዋርያ የሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው:: የጌታ ጸጋና ሰላም ከእኛ ጋር ይሁን::
በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል
2ኛ ቆሮንቶስ 1: 3-6
3 የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 4 እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። 5 የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። 6 ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው።
አምላካችን:-
- ሩህሩህ ነው::
- የሚያጽናና ነው::
- አባት ነው::
- አምላክም ነው:: አሜን!
በቃሉ ውስጥ በብዙ ቦታ ላይ ስለ እግዚአብሔር ርኅራኄ ተነግሯል በሉቃስ 6: 36፤ አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ ይላል:: ወደ ጸጋ ዙፋኑ ቀርበን የሚረዳንን ጸጋ ለመጽናናት እንቀበላለን:: ጌታ እየሱስ በምድር ሲመላለስ ወደ እርሱ መተው የለመኑ ሁሉ እረፍትን እንዳገኙ ዛሬም በስራ ላይ ነው ይሰማል ይራራል ይረዳል:: አሜን!
በመከራ የሚያጽናና እርሱ ነው ሰው እስከተወሰነ መንገድ ብቻ ነው አብሮን ሊጏዝ የሚችለው ጌታ ግን እስከ ዓለም ፍጻሜ:: ሃሌሉያ! ስለመጽናናት የሚያወራ መቼም የተጽናና መሆን አለበት እንደ ጳውሎስ ደግሞ በመከራ ስለወንጌል የከፈለ አላየሁም:: ተደብድቧል ሞተ ብለው ጥለውት እስኪሄዱ: ታስሯል: ከአውሬ ታግሏል: በማዕበል ተንገላቷል; በወንድሞች ተሰዷል; ተርቧል; ተራቁቷል; በአይሁድ ተሳዷል ወዘተ:: በዚህ ሁሉ ያጽናናውና ያቆመው ግን የርኅራኄ አምላክ ነው:: ለዚህ ነው በተጽናናንበት መጽናናት ማጽናናት የምንችለው ካላለፍንበት ግን የጉዳቱ ጥልቀት ስለማይገባን ሰባሪ እንጂ አጽናኝ አንሆንም::
የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። ይህ ማለት ስለ መዳናችን የምንፈጽመው ነገር አለ ለማለት አይደለም እሱንማ ተፈጸመ ብሎ ጨርሶታል:: እዚህ ጋር የሚናገረው ጻድቅ የሆነውን እየሱስን ስለ ሐጥያቱ ሳይሆን ጻድቅ ስለሆነ ነው ያስወገዱት እኛም ዛሬ በጽድቅ ስንኖር ለዓለም አይመቻትም ስለዚህ ወደ ስቃይ ይወስደናል ጌታን በእውነት መከተል ከቤተሰብ ጀምሮ ዋጋ የሚያስከፍል ነው:: እንግዲህ በዓለም ተቀባይነት እንድናገኝ የጌታን ነገር ገታ እናድርግ? አረ ይቅርብኝ ልገፋ እንጂ ጌታን በመምሰል እምላለሳለሁ ከዓለም እራሴን ለጌታ ስለለየሁ በአንዳች አልጎድልም ጠላት እንደሚሰብከው ማለት ነው ‘ምን አለበት?’ ችግር አለብት ነው መልሱ ምን አለበት ታድያ እየሱስም የተወሰነውን ሳይክፍል ቢተውልን? ሙሉ በሙሉ ዋጋዬን ከፍሎ ዋጅቶኛልና እኔ የርሱ ነኝ እርኩስንም አልነካም:: ብገፋ እንኳን ጌታ መጽናናቴ ነው::
መከራ የሚያሳድደው ሌላውን ለመርዳትና ለማገልገል በሚነሳው ላይ ነው:: ለዚህ ነው መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ የሚላቸው:: እኛም ስንጸና ስታዩ እናንተም ትጸናላችሁ ይላል:: መጽናታችን ሌሎችን እንደሚያጸና አውቀን በጽድቅ በመመላለስ ጌታን እያገለገልን እንኑር:: ጸጋው ይብዛልን::
በእግዚአብሔር መታመን
2ኛ ቆሮንቶስ 1: 7-11
7፤ ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና። 8፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ 9፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። 10-11፤ እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።
እዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ እንደማንኛችንም በእስያ በደረሰባቸው ስደት ተስፋ ቆርጦ መጨረሻችን ነው መውጫም የለም ብሎ እንዲያውም የሞትን ፍርድ ሁሉ በውስጣችን ሰምተን ነበር ይላል:: ነገር ግን እግዚአብሔር ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ አሜን! የምንታመነው በእርሱ ካልሆነ በስተቀር አንድቀን የእኛ ነገር ማጠፊያው ያጥራልና ሁልጊዜ በጌታ እንታመን:: መደገፊያችን ክንዳችን ሳይሆን ልክ እንደ እዮሳፍጥ የመጣብንን አንችልም ብለን በፊቱ ስንወድቅ ድብቅ ጦርን ያስነሳል ብቻ ምን አለፋን መፍትሄ አለው::
በዚህ ውስጥ የዝች ቤተክርስቲያን ድርሻ የነበረው መጸለያቸው ነው ለእነጳውሎስ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ ይላቸዋል:: በተሰጣቸው ጸጋ ጸልየዋል መትረፋችንም ለእግዚአብሔር ምስጋናን አምጥቷል እያለ ነው:; ጸሎት ይሰራል ዛሬም ጌታ ይሰማል ይታደጋል:: በጸሎት እንትጋ በፊቱ መገኘት መልካም ነውና::
የጉብኝቱ እቅድ መለወጥ
2ኛ ቆሮንቶስ 1: 12-24
12፤ ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የሕሊናችን ምስክርነት ነው። 13 –
14 ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አንጽፍላችሁምና፤ በጌታችን በኢየሱስ ቀን እናንተ ደግሞ ትምክህታችን እንደምትሆኑ እንዲሁ ትምክህታችሁ እንድንሆን፥ በከፊል ስለ እኛ እንዳስተዋላችሁ ፈጽማችሁ ታስተውሉት ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ። 15 በዚህም ታምኜ፥ ሁለተኛ ጸጋ ታገኙ ዘንድ አስቀድሜ ወደ እናንተ እንድመጣ፥ 16 በእናንተም መካከል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ ደግሞም ከመቄዶንያ ወደ እናንተ መጥቼ ወደ ይሁዳ በጉዞዬ እንድትረዱኝ አሰብሁ። 17 እንግዲህ ይህን ሳስብ ያን ጊዜ ቅሌትን አሳየሁን? ወይስ በእኔ ዘንድ አዎን አዎን አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የማስበው በዓለማዊ ልማድ ነውን? 18 እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም። 19 በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል። 20 እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው። 21 በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ 22 ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው። 23 እኔ ግን ልራራላችሁ ስል እንደ ገና ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣሁ በነፍሴ ላይ እግዚአብሔርን ምስክር እጠራለሁ። 24 ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፥ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና።
ጳውሎስ እመጣለሁ ብሎ ያልመጣበትን እያብራራላቸውና ዝርዝር መረጃንም እየሰጣቸው ነስ በዚህ ስፍራ ላይ:; እነሱ ግን ተአማኒ አይደለም ቃሉን እንኳን አይጠብቅም የሚሉ ተቃዋሚዎች ለሚያወሩት ወርኡ ነው መልስ የሚሰጠው:: ጳውሎስ ማለት የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ እንደምሆኑ እየዋሸ ወይም ማታለል አይደለም የያዘው ሲለውጥ እቅዱን አስቦበት ለክርክር ሳይሆን ለፍቅር መምጣት ስለፈለገ ነው::
ሌላው እናንተንም እኛንም የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው ይላል እንደገናም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው። ሁላችንም የጌታ ነን ማንም ለማንም አይገዛም የሚገዛ በህዝቡም ላይ አለቃ እግዚአብሔር ብቻ ነው:: እኛን ያዳነ በቅዱስ አጠራርም የጠራን ጌታ ነው:: አሜን!
ምዕራፍ 2
በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ፍቅር ይቅደም
2ኛ ቆሮንቶስ 2:1-4
1፤ ነገር ግን ዳግመኛ በኀዘን ወደ እናንተ እንዳልመጣ ስለ እኔ ቆረጥሁ። 2፤ እኔስ ባሳዝናችሁ፥ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? 3፤ ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸውም በመምጣቴ ኀዘን እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍሁላችሁ፥ ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ታምኜአለሁና። 4፤ በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና፤ ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም።
ትልቁ ጳውሎስን በዝች ቤተክርስቲያን ውስጥ ያስወቅሰው ጉዳይ እመጣለሁ ብሎ አለመምጣቱ ነው:: ምክንያቱን እንደሚገልጸው ችላ ብሎ ወይንም ደግሞ ረስቶ ሳይሆን ነገር ግን በኀዘን ወደ እናንተ እንዳልመጣ ስለ እኔ ቆረጥሁ እናም በመምጣቴ ኀዘን እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍሁላችሁ ይላል:: መሸሽ የያዘው እንዳያሳዝናቸው ነው:: ከዚህ በፊት እንዲያስተካክሉ የጻፈላቸውን ነገሮች እንዳልጨረሱ መረጃ ስላለው እንደገና በዛው ጉዳይ መነጋገሩን አልፈለገም:: በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና፤ እንደገና መነጋገር ይቅርብኝ:: ውስጡን አሳዝኖታል በመካከላቸው እየሆነ ያለው ነገር:: ይህንን ሲል ከጥላቻ አልነበረም ነገር ግን እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም:: ነገርን ሁሉ በፍቅር እንያዝ እኛ የፍቅር እንጂ የህግ አገልጋዮች አይደለንም:: እንደጳውሎስ ያለን ለመንጋው እንደዚህ እያለቀሰ የሚጠነቀቅ አገልጋይ ያብዛልን::
ለምንወደው ሰው መልካም ብቻ ሳይሆን ስህተትም ካለ ቢያምም ቢያስለቅስም ማሳወቅና በፍቅር ማቅናትን ተምሬያለሁ::
ይቅርታ፥ ፍቅርና ማጽናናት
2ኛ ቆሮንቶስ 2: 5-11
5፤ ነገር ግን ማንም አሳዝኖ ቢሆን፥ እንዳልከብድባችሁ፥ በክፍል ሁላችሁን እንጂ እኔን ያሳዘነ አይደለም። 6 እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፥ 7 ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። 8 ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤ 9 ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን አውቅ ዘንድ አሳቤ ነበር። 10 እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥ 11 በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።
ጳውሎስ እዚህ ክፍል ላይ ስለ ይቅርታ፥ ፍቅርና ማጽናናት ይሰብካል:: አንድ ሰው ሲበድል የበደለው እራሱን ብቻ ሳይሆን ጉባኤውን ሁሉ ነውና የበዛ ኃዘን እንዳይሆንበት ይቅር በሉት እያላቸው ነው:: ይቅር ማለት ለራስ ነው አለበለዚያ ግን እራስን ማሰር ነው ጸሎታችንም አይሰማም ከወንድምህ ጋር አንዳች ካለህ መስዋዕቱን ተውና ሄደህ በፊት ያንን አስተካክል እንዲሁም ደግሞ ጌታ ባስተማረን ጸሎት ላይ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን ብሎም አይደል ያስተማረን? ይቅር እንባባል!
እዚህ ላይ የምንማረው ነገር የኔ ህይወት ሌላውን ምን አገባው ብሎ ነገር የለም አንዱ ሲነካ ሁሉ ተነክቷል አንዱ ሲያጠፋ ሁሉ ይነካል ምክንያቱም አካል ነን:: ለምሳሌ ኢንፌክሽን ትንሽዋ ጣታችን ላይ ቢፈጠር አጠቃላይ ሰውነታችን በትኩሳት ይነዳል ያንን ኢንፌክሽን ለመከላከል ብሎም ለመፈወስ እኔጋ አይደለም ችግሩ እጣት ላይ ብቻ ነው የሚባል አሰራር የለም ሁሉም አብሮ ይታመማል:: የክርስቶስም ቤት እንደዛው ነው በአንዱ ምክንያት ሽንፈት ይመጣልና የምንኖረው ኑሮ የጌታ ነው የእርሱ አካል ነንና እርሱን እናስከብር በአካሄዳችን ሁሉ::
የበደለንውን ወገን እናንተ መንፈሳውያን የሆናችሁ አቅኑት እንደሚል ቃሉ ወገናችንን እናቅና:: የጣቱን ምሳሌ ልቀጥል:- የሚፈውስ ነገር ለጣታችን እንደምንቀባው፥ ከተጨማሪ ችግር ለመጠበቅ እንደምናሽገው፥ እንደምንከባከብ፥ የአካልም ሁሉ ትኩረቱ በዝች ትንሽ በሆነችው የሰውነት ክፍል ላይ እንደሚሆን እንዲሁ ይህንን ሰው ለመፈወስና ለማቅናት መረባረብ አለብን::
ሁሉን በፍቅር ማሸነፍና ይህንን የክርስቶስን ፍቅር በማሳየት መመላለስ አለብን:: እንደገናም ደግሞ ማጽናናት እና ወደ ቀደመ ማንነቱ መመለስ አለብን የሰይጣን ዓላማው አንድ በአንድ እያለ መጣል ነው ስለዚህ ስራውን አንስተውም ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እየሱስ ግን ሕይወት እንዲሆንልን እንዲበዛልንም መቷል። አሜን!
በእኛ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን
2ኛ ቆሮንቶስ 2: 12-17
12፤ ስለ ክርስቶስም ወንጌል ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ ለጌታ ሥራ በር ምንም ቢከፈትልኝ፥ ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም፥ 13 ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። 14 ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ 15 በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ 16 ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? 17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።
ጳውሎስ ከቲቶ ጋር ስላልተገናኘ በቀጠሮው ሰዓትና ቦታ መንፈሱ ተጨንቆበታል:: ቲቶን እንደዚህ አጥብቆ የፈለገበትም ምክንያት በእርሱ ነበር የመጀመሪያውን መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የላከው እራሱም እንደሚለው በብዙ እንባና ሀዘን የጻፈውን መልእክት የላከውን ከባድ መልእክት እንዴት እንደሆኑ የሚነግረው ቲቶ ነበር::
በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ ይላል ድል የመንሳቱን ነገር አንድ የሮም ጀነራል እንቢልታ እያስመታ እዩልኝ ገድሌን እያለ ከተማዋን ይዞራል በዘመናቸው አሁንም ይህንን ነገር ከእየሱስ ድል ጋር በማያያዝ ነው ያስቀመጠው ድል መንሳቱን አሳውቋል እኛን እንደ ሰራዊቱ ይዞን እያዞረ የተማረከውና ማዕረጉ የተገፈፈው ደግሞ ሰይጣንን ነው ይዞ ያሳየው ድሉን:: ድል ነስቷል እየሱስ! ሃሌሉያ! ስለዚህ እኛ ሁለት አይነት ሽታ ይዘን የምንዞር ነን:- ለሚድኑት የህይወት ሽታ ለሚጠፉት ደግሞ የሞት ሽታ:: ይህን ብሎ ሲያበቃ ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? በሚል ጥያቄ ይደመድማል::
ለዚህ የሚበቃማ ሰው
- ቃሉን የማይሸቃቅጥ እና
- በቅንነት ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆኖ የሚናገር ነው።
ለዚህ ስላበቃን ብቃታችንም እርሱ እንደሆነ የምናውቅ የምንመካበት ከጌታ ሌላ የሌለን የእርሱን ሽታ ለሰው ሁሉ የምናደርስ የራሳችን ያልሆንን ነን:: ይህ በእውነት ያስመካል!
ምዕራፍ 3
ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው መንፈስም ህይወትን ይሰጣል
2ኛ ቆሮንቶስ 3: 1-6
1፤ እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን? 2 ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። 3 እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው። 4 በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። 5 ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤ 6 እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።
ቃሉን የምንሸቃቅጥ አይደለንም ብዬ ማለቴ ምስጋና ወይም እውቅና ፈልጌ ወይም ለጉራ አይደለም ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። ይላቸዋል:: ማስታወስ ያለብን እነዚህን ሰዎች ወደ እውነት ያመጣና ያገለገላቸው ጳውሎስ እንዲሁም አብረውት ያሉት ወንድሞች ናቸው እንግዲህ በምን ሂሳብ ነው ሊኮሩ ወይም ይህንን ስራ ሊክዱ የሚችሉት ወይም በራሳችን ዳንን አይሉ መቼም ጳውሎስን መግፋት የሚገርም ነው:: እርሱ ግን ምንም እውቅና አንፈልግም እናንተ እራሳችሁ በልባችን የተጻፋችሁ መልእክታችን ናችሁ የሚለው:: እውነትን ይዘን ክርስቶስን በእውነት እናገለግላለን ከምድር እውቅናን በመፈለግ ሳይሆን::
በዚህ ሁሉ ውስጥ ፍቅርን ነው የሚያሳያቸው ጳውሎስ እነሱ ለእርሱ ምን ማለት እንደሆኑ ያስረዳቸዋል:-
- ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ።
- እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥
- በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው።
እናንተ ውድ ናችሁ ለእኛ ምክንያቱም በቀለም ሳይሆን የተጻፈው ደራሲው ራሱ ጌታ ነውና በልባችሁ የፃፈው ይህንን እወቁ ነው የሚለው ምንም እንኳን በመካከላቸው ሐዋርያነቱን የማይቀበሉ ቢኖሩም::
ስለዚህ እናንተን ያገለገለ እራሱ ጌታ ነው:: በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። ለእኛ ሳይሆን ምስጋና ለእርሱ ይሁንለት እምነታችን በእርሱ ነውና:: ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም:: አሜን ማንም ብቃት የለውም ጳውሎስ እራሱን አያዋድድም ስራው የተሰራው በጌታ ክብር የሚገባው እሱ ነው እኛ በራሳችን አንዳች አላደረግንም:: ጳውሎስ እንደዚህ አገልግሎ የአዲስ ኪዳንን አብዛኛውን መጽሐፍ ጽፎ ሲያበቃ የበቃን አይደለንም ካለ ማሰብ ነዋ! የምንመካበት አንዳችም የለንም:: እርሱም ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። ህይወት የሚሰጠው እራሱ መንፈሱ ነው ፊደልማ ከመክሰስ ውጪ ምንም አያደርግልንም:: ህያው የሆነው ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ይዋሀድ:: አሜን!
የአዲስና የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ልዩነት
2ኛ ቆሮንቶስ 3: 7-18
7፤ ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ 8 የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? 9 የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ፥ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። 10 ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። 11 ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና። 12 እንግዲህ እንዲህ ያለ ተስፋ ካለን እጅግ ገልጠን እንናገራለን፥ 13 የዚያንም ይሻር የነበረውን መጨረሻ ትኵር ብለው የእስራኤል ልጆች እንዳይመለከቱ፥ በፊቱ መጋረጃ እንዳደረገ እንደ ሙሴ አይደለንም። 14 ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና። 15 ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ 16 ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል። 17 ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። 18 እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።
በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ጳውሎስ አስቀምጦልናል በዚህ ክፍል ላይ ይህ ሊገባን ይገባል እንደ አዲስ ኪዳን አገልጋይ::
የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ከአዲስ ኪዳን የሚለያየው:-
- የፊደል አገልግሎት ነው
- የሞት አገልግሎት ነው
- የኵነኔ አገልግሎት ነው
- የከበረ አገልግሎት ነው
- የሚሻር አገልግሎት ነው
- አሳብ የሚያደነዝዝ አገልግሎት ነው
- በመጋረጃ የተሸፈነ አገልግሎት ነው
በሌላው እንፃር ደግሞ የአዲስኪዳን አገልግሎት:-
- መንፈስን የሚሰጥ አገልግሎት
- ህይወት የሚሰጥ አገልግሎት
- የጽድቅ አገልግሎት
- የላቀ ክብር ያለው አገልግሎት
- ጸንቶ የሚኖር አገልግሎት
- የአርነት አገልግሎት
- መጋረጃው የተገፈፈ – የጌታን ክብር እንደ መስተዋት የማብለጭለጭ አገልግሎት
ልዩነት አለው ሁለቱ አገልግሎት አንደባልቅው በአጠቃላይ የአዲስ ኪዳን አገልግሎት እረፍት የሞላበትና መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር መለወጥ ነው:: የአብ እቅድ ሁሉን በክርስቶስ መጠቅለል አይደል? ለዚህ ህይወት ለሚሰጥ አገልግሎት ያበቃንን ጌታ እያመሰገንን ዛሬም እሱን በማወቅና በመገለጥ መንፈስ ይሙላን:: አሜን! እኛ የአርነት አገልጋዮች ነን:- ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። አሜን! ሃሌሉያ!
ምዕራፍ 4
እውነትን እናገልግል
2ኛ ቆሮንቶስ 4: 1-2
1፤ ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም። 2፤ ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን።
ምዕራፍ 3 ላይ ስለ አዲስ ኪዳን አገልግሎት ካስረዳ በኃላ ነው እንግዲህ እዚህ ጋር ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም የሚለው:: በምሕረቱ ነው ወደ መንግስቱ የመጣነውና የዚህ የከበረ ያለቀለት ወንጌል አገልጋዮች የተባልነው::
ሌላው እዚህ ጋር ከሚጠቅሳቸው አገልጋዮች እንደሚለይ ይናገራል:: እስኪ እንይ:-
- በተንኮል አንመላለስም – የተሰወረ የምናራምደው ነገር ስለሌለን ነገራችን ሁሉ በግልጽ ክርስቶስን ማክበር ነው
- የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም:- እውነትን እንናገራለን
- እውነትን በመግለጥ :- ለራሳችን እንዲመች ብለን ቃሉን አናጣምም ነገር ግን የሚያድነውን መድኅን ጌታ እየሱስን እንሰብካለን::
ከዚህ የምናየው ሰዎች እንዲመቻቸው ቃሉን እንደሚያጣምሙና ወንጌልን እንደሚሸቃቅጡት ነው ስለዚህ የበዛልንን ምኅረት እያየን ሳንታክት እውነትን በመግለጥና ለእእነት በመኖር እንመላለስ:: ጌታም ከነዚህ ሐሰተኞች እንድንጠበቅ ነግሮናል (በማቴ 7: 15፤ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።) እንጠንቀቅ እንግዲህ:
የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን ያብራ
2ኛ ቆሮንቶስ 4: 3-4
3፤ ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። 4፤ ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።
ወንጌል ግልጽና እሰየው ብለን መቀበል ያለብን እረፍት የሞላበት መዳን ነው ብለን እናስባለን ነገር ግን በጣም ተቸግረው ሰዎች የምንላቸው አልገባ ብሏቸው በራሳቸው ጽድቅን ሊያቆሙ ሲፍጨረጨሩ ደግሞ እናያለን:: የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው ጠላት ይተጋል ይህ የሚሆነው ደግሞ በቆላ 2: 3፤ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና እንደሚል እየሱስን የገፉ ናቸው ማንም ይህንን የጥበብና የእውቀት መዝገብ ከገፋ እንዴት ወንጌል ይገባል በተለይ ደግሞ የዚህ ዓለም ገዢ ተግቶ አሳባቸውን እያሳወረ::
የሰይጣንን ስራ አንስተውም እርሱ የውሸትአባት ነው፤ ሰውን የሚፈትን፤ ሰውን የሚከስ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ከሰው ልብ የሚሰርቅ፤ በተቻለው ሁሉ ወንጌል እንዳይሰበክ የሚዋጋ የእግዚአብሔር ቃልና የመንግስቱም ጠላት ነው::
በኤፌሶን 2: 2፤ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ስለዚህ መገንዘብ ያለብን ሰዎቹ ምንም አላጠፉም ያ የእውነት ጠላት ተግቶ እየተዋጋቸው መሆኑን በማወቅ ስልጣናችንን እንጠቀም:- በያዕቆብ 4: 7፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል:: መሸሽ ግድ ይለዋል የተባልነው ይህንን ስልጣን መጠቀም ነው እንጂ እንዴት ይህ እውነት አይገባም ብለን ተስፋ አንቁረጥ:: እንዲያውም እናሳደው! አባረን ኢላማችንን እየሱስን እናውለብልብ:: ጌታ የጠላትን ደጅ ያስወርሰን የምንመሰክርለትንም ሰው ወደእኛ ይላክ የምንመሰክርበትንም ኃይልና ጥበብ ጸጋም ሁሉ ያብዛልንና በአንድ ነፍስ መዳን ሰማይ እልል ይበል! አሜን!
የእግዚአብሔር ብርሀን በራልን
2ኛ ቆሮንቶስ 4:5-6
5፤ ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። 6፤ በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ፡ ያለ እግዚአብሔር ነውና።
ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰንክም:: ጌትነቱንም ያሳየን እራሱ እግዚአብሔር አብ ነው በሰማይ አዋጅን ያወጀው እየሱስ ጌታ እንደሆነ ደግሞም አብ እንዲከብር እየሱስ ጌታ እንደሆነ ምላስ ሁሉ ገና ይመሰክራል፦ ጌታም ስለሆነ ከስም ሁሉ በላይ ስምን ተቀብሏል:: አሜን! በስንቱ መድረክ ላይ ይሆን ታድያ ስለሰው ሳንሰማ የቀረነውና ክርስቶስ ብቻ ገኖ ያየነው? ክብሩ ለጌታ ሊመለስ ይገባል! የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ስናይ ግን አይኖችን ሁሉ ወደ ጌታ ነበር የሚያመለክቱት ለምሳሌ መጥምቁ ዮሐንስ:- እኔ አይደለሁም ከኔ በኃላ በእሳት የሚያጠምቅ ይመጣል ደግሞም በሌላ ስፍራ የዓለምን ሁሉ ሐጥያት የሚያስወግድ በግ እያለ ወደ እርሱ ጠቆመ እንጂ ክብርን ለራሱ አልወሰደም::
በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለው ገና ከመጀመሪያው ፍጥረትን ሲፈጥር ነበር:: አሁንም ደገመው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረትን ዳግመኛ ሲፈጥር እንደገና ብርሀን ይብራ ብሎ ጨለማችንን አስወገደው:: ይህ እልል ካላስባለ ምን ያስብላል አዲስ ፍጥረት አድርጎ የራሱ ሲያደርገን? እልልልልልልልል! አሜን! እርሱ የብርሃን አምላክ ነው:: እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፡ ከጨለማ ጋር ህብረት የለውም፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሀን ውስጥ ይኖራል፤ ብርሃንን እንደ ልብስ ለብሷል፤ ወደ እዚህ ብርሀኑ ጠራን፤ ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው፥ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ። በብርሀኑ ሁሉ ነገር ተነክቷል::
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ይህንን አምነን መልስ የሰጠን ሁላችን ጌታን እየሱስን እንስበክ አካሉንም ዝቅ ብለን እናገልግል! እየሱስን ስናይ አብንም አይተናል ምክንያቱም ህብረታችን ከአብ ጋር ከልጁም ከእየሱስ ጋር ነውና ወደዚህ ወደሚደነቅ ብርሀን ተጠርተናል! አሜን!
የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር ነው
2ኛ ቆሮንቶስ 4: 7-9
7፤ ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 8፤ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ 9፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤
ይህ መዝገብ የሚለው ከላይ እንዳየነው ብርሀን ይብራ ብሎ በውስጣችን ያበራውን የእግዚአብሔርን ብርሀን ነው:: ይህ ብርሀን በምንም ጨለማ የማይዋጥ ነገር ግን አሸንፎ የሚያበራ በእኛ ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር ብርሀን ነው:: ሃሌሉያ! ደግሞም በሌላ ስፍራ የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። አሜን! ይህን ሲያደርግ አምላካችን የሀይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳልሆነ ሊያሳይ ወደደ:: በዚህ ውስጥ ታላቅነቱ ታይቷል እኛን ከሞት ወደ ህይወት ወደዚህም ክብር ለማምጣት እራሱ መምጣት ደግሞም መሞት ነበረበት:: የሞትንም ጣር አጥፍቶ በትንሳኤው ሀይል ተነሳ መበስበስንም አላየም የሲኦልንና የሞትን ቁልፍ ተቀበለ:: በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ነው የተዋጀነው። በትንሳኤውም የሀይሉ ታላቅነት ታየ!
የሚገርመው ግን ይህንን የከበረና ታላቅነቱን እንዲሁም ኃይሉን ያሳየበትን ስራ በሸክላ ውስጥ ማስቀመጡ ነው! አይገርምም?! ውድ የሆነን ነገር መቼም እንደምናውቀው ጥሩ ሊሰበርና ሊሰረቅ በማይችል በብዙ ጥበቃ ውስጥ ይቀመጣል እንጂ በሸክላ ውስጥ እንዴት? በእርግጥ ተስፋ ተሰቶናል ለአሰራሩ እንዲመች ወደፊት አካላችን የእርሱን እስከሚመስል እንደሚቀየር ግን ለምን አሁን አልሆነም ያልን እንደሆነ ምክንያቱ ስራውን በእኛ ውስጥ ሆኖ የሚሰራው እርሱ ስለሆነ እንዲያውም ይህ ሸክላ ውስጡ ባለው እንዲመካ ስለሚፈልግ ነው:: ማንም እንዳይመካ በስራ አይደለም የተባለውም ለዚህ ነው:: ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን! አሜን!
ስለዚህ ይህ የከበረ ጌታ በእኛ ውስጥ ስላለ
በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤
እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤
እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤
እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤
ማጠቃለያዬ አንጨነቅም፤ ተስፋ አንቆርጥም፤ አንጣልም እንዲሁም አንጠፋም ምክንያቱም ብርቱ የሆነው በእኛ ውስጥ ነውና ብቻችንን አይደለንም እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ነግሮናል ደግሞስ ከእኛ ውስጥ ወዴት ይሄዳል አንድ ጊዜ በቀራንዮ መስቀል ላይ ወልዶን ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም አይደል ያለን? ለቃሉ ታማኝ ነው ስለዚህ መሸነፍ አይታሰብም! ሃሌሉያ!
የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን
2ኛ ቆሮንቶስ 4: 10-12
10፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። 11፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና። 12፤ ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል።
ምንድነው ተሸክመን የምንዞረው በስጋችን? መልሱ:- የኢየሱስን ሕይወት ነው:: ምን ማለት ነው ሕይወቱን መሸከም ወይም በሚሞት ሥጋችን ህይወቱ ይገለጥ ዘንድ ማለት? ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ተባብረናል:: የሞተ ሰው ለራሱ አይኖርም እንዲሁ እኛ ሁልጊዜ ሞቱን ተሸክመን እየዞርን ለሞተልን እንኖራለን:: ዓለም ጌታን እንደጠላችው እኛንም ትጠላናለች ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ጌታ የሰጠን ተልዕኮ:- እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ ብሎ አደጋ እንዳለው ተልዕኮው አሳውቆናል፤ ሞትን መሸከም እንግዲህ ይህ ነው፤ መልሶም ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም ብሎም ነግሮናል:: ማለትም እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዱአችኃል:: ስለዚህ ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለን ማለት ነው:: እኔ ዓለምን አሸንፌያለሁና አይዟችሁ ብሎናል እየሱስ:: በሄድንበት ሁሉ የህይወት ወይም የሞት ሽታ መሆን ግድ ይላል::
ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን እንደሚል ጳውሎስ ይህንን ጌታ ስናገለግል ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በምናገልግላቸው ላይ ይሠራል ማለት ነው።
አንታክትም
2ኛ ቆሮንቶስ 4 13-18
13፤ ነገር ግን፦ አመንሁ፡ ስለዚህም ተናገርሁ፡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤ 14፤ ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና። 15፤ በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና።
16፤ ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 17–18፤ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።
እኛ የእምነት ሰዎች ነን እናምናለን ያመነውንም እንናገራለን እንኖረውማለን:: ያመነውም ከሞት የተነሳን ጌታ ነው እኛንም ከሞት ያነሳል ስለዚህ የጊዜው ነገር አሁን ዙሪያችንን ከቦ ለማስጨነቅ ጦር እየጎሰመ ያለውን አንፈራም ምክንያቱም የጊዜው ነው:: እኛን ማጥፋት አይችልም በእጁ መዳፍ የቀረጸን ጌታ አሸንፏልና አንፈራም:: ማስፈራራቱ ግን ይቆማል እንዴ? መልሱ አይቆምም ከእየሱስም እንኳን ለጊዜው ተለየ ነው የሚለው ፈተናው ሁሉ ከከሸፈበት በኃላ ስለዚህ እንበርታ አንታክት::
የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና እንደሚል ጸጋን ተሞልቶ በእኛ ዘንድ ያደረው እየሱስ አትረፍርፎ ጸጋውን ይሰጠናል እንዳንታክት:: በዚህ ጸጋ የውስጡ ሰውነታችን እየታደሰ ይኖራል ምንም እንኳን የውጭው እየደከመ ቢመጣም:: ጳውሎስ ስለውጭው ሰውነት መድከም ሲያወራ በዚህ ዘመን ብዙም የማናየው አይነት መከራ ውስጥ ያልፍ ነበር መደብደቡ መራቡ አረ ስንቱ ግን አልታከተም በትንሳኤ ይህ ሁሉ እንደሚረሳ እርግጠኛ ነበረ::
ስለዚህ የማይታየውን እየተመለከትን እንበርታ የሚታየውን ካየን ድካምን እናጭዳለን አይናችን ግን በማይታየው ላይ ሲሆን ዕለት ዕለት የውስጥ ሰውነታችን ይታደሳል:: አይናችሁን አድርጉ በተባለው ላይ እናድርግ:: የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። ሁልጊዜ አስተሳሰባችንን በዚህ በከበረ ቃል እንሙላው፥ ጌታንም ተስፋ እናድርግ፥ ወገኖችንም እናበርታ፥ ወደፊት እንጂ ወደኃላ ሳናይ መታከትን አስወግደን፥ ጸጋን እየጠየቅን መንገዳችንን እንጠብጥብ::
ምዕራፍ 5
በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት አለን
2ኛ ቆሮንቶስ 5: 1-3
1፤ ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። 2፤ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ 3፤ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም።
ያለፈው ምዕራፍ ሲዘጋ አሳቡ የጊዜውን ከማየት ይልቅ የዘላለሙን ብናይ የጊዜው ነገር ቀላል ነው እያለን ነው ስለዚህም ከዚሁ ጋር አያይዞ የምድሩ ድንኳናችን ቢፈርስ በሰማይ ሌላ አካል እንቀበላለን ይለናል:: ግን ህይወታችንን ለምን ከድንኳን ጋር አመሳሰለው? ምክንያቱም እስራኤላውያን ስለድንኳን በምድረ በዳ ሲጏዙ በነበረ ጊዜ በደንብ ያውቃሉ ድንኳኑን ያቆማሉ ስርአቱን ያደርጋሉ ደግሞ እንሂድ ሲላቸው ደመናው ሲነሳ አፍርሰው ተነስተው ይጏዛሉ ምን ያህል እንደሚቆይ ይህ ድንኳን ከጌታ በስተቀር ማንም አያውቅም እንዲሁም እኛ ምን ያህል እንደምንቆይ አናውቅም:: ህይወታችን እንደዛች ናት ዛሬ ይተከላል ነገ ደግሞ ፈርሶ ይነሳል ለመመካት እንኳን የማይሆን ነው ህይወታችን ፈራሽ ግን ጌታ እራሱ መቶ እየኖረበት ያለ ድንኳን ነው ከእርሱ ጋር ነን በሰማይም ከእርሱ ጋር ነን ለዛውም በተሻለ አንዋዋር:: እርሱን ለመምሰል እንለወጣለን!
በዚህ ድንኳን ውስጥ እንቃትታለን:: ለምን ይሆን? ምክንያቱም አዲስ ፍጥረት ሆነናል አሮጌው አልፏል፤ አዲሱ በአሮጌው ውስጥ ነው የተቀመጠው ሁልጊዜ ትግል አለ ስጋ በመንፈስ ላይ እንዲሁም መንፈስ በስጋ ላይ ይቀዋወማል፤ ውስጣችን የላይኛውን ሲል ስጋችን ደግሞ አይፈልግም ብቻ ምን አለፋችሁ መጏተት ነው የያዝነው ስለዚህም ጳውሎስ በሌላ ስፍራ ላይ በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም ይለናል:: ስለዚህ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለን ይሄ ኑሮ ያኛውን በጣም እንድንናፍቅ ያነሳሳናል መጏተት የሌለበት እረፍት በሰማይ ይጠብቀናልና የጊዜውን አንይ የዘላለሙን እንጂ:: ኑሮ ስላልተመቸን አይደለም ወደ ጌታ በሄድኩኝ የምንለው ግን የሰማዩን እንናፍቅ ዘንድ ነው በዚህ አሮጌ ማደሪያ ውስጥ ያለነው:: በዚህ ምድር ስንኖር በጌታ ባንደገፍ ህይወታችን እርሱን ፈፅሞ ማሳየት የማይችል ነው የሚሆን የነበረው በሸክላ ውስጥ የከበረ ማንነቱን ያስቀመጠ ጌታ ይመስገን::
የመንፈሱን መያዣ ሰጠን
2ኛ ቆሮንቶስ 5: 4-10
4፤ በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። 5 ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን። 6 –7 እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ 8 ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል። 9 ስለዚህ ደግሞ ብናድር ወይም ተለይተን ብንሆን እርሱን ደስ የምናሰኝ ልንሆን እንቀናለን። 10 መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና።
የተለመደው አሰራር ሞት ነው የሚውጥ እዚህ ክፍል ላይ ግን ሞት በህይወት ይዋጣል! አሜን! እየሱስ ሞትን ድል ነስቷል ቁልፉንም ይዟል!የመንፈሱን መያዣ የሰጠን እርሱ እራሱ እግዚአብሔር ነው ለምን? ያልን እንደሆነ በድንኳኑ ውስጥ መኖር ከባድ ስለሆነ ሊያበረታንና የሰጠን የተስፋ ቃል ሁሉ እውነት መሆኑን ለማስረገጥ ነው:: የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። ለዚያውም ይህ ያለንበት ሁኔታ እኮ በጣም የተሻለ ነው ክርስቶስን አውቀናልና የእኛ ህይወት ጌታን ካላወቀው ጋር ሲወዳደር እስከአሁን ድረስ በእግዚአብሔር ቁጣ ስር የመሆናቸው ነገር ያስፈራል እኛ ከዚህ አምልጠናል ምንም እንኳን በምጥ ውስጥ ብንሆንም ቅሉ:: ከዚህም ደግሞ የተሻለ እንዳለ በቃሉና በመንፈሱ ስለተረዳን አሁንም ወደ ተሻለው እንቃትታለን::
ሁልጊዜ ታምነን እንጂ በማየት አንመላለስም እኛ መንፈሳውያን ነን:: በመንፈስ የምንመላለስ ነን: የእምነት ሰዎች ነን በምድር ሳለን ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የሚሰማንና ጌታን የምንናፍቅ መሆን አለብን:: ስደት ላይ ያለ ሰው እኮ ተረጋግቶ እዚህ ነው ማረፊያዬ እንደማይል ሁሉ እንዲሁ እኛም መንገደኞች ነን በዚህም ምድር መጻተኞች መሆናችንን እያሰብን ልባችንን በመንገዳችን ላይ በማድረግ በጌታ ዘንድ ማደርን መናፈቅ አለብን::
በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ግድ ይላል በስጋ የተመላለስንበት ነገራችን ይፈተናል ስለዚህ የምድሩን ነገር ትተን በላይ በሰማይ ያለውን እንሻ ለእርሱም እንኑር::
አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ
2ኛ ቆሮንቶስ 5: 11-14
11፤ እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን ለእግዚአብሔር ግን የተገለጥን ነን፤ በሕሊናችሁም ደግሞ የተገለጥን እንደ ሆንን ተስፋ አደርጋለሁ። 12፤ በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን እንጂ ራሳችንን ደግሞ ለእናንተ የምናመሰግን አይደለንም። 13፤ እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው። 14፤ ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ::
የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን ማለትም ወደ ህይወት ስንመጣ የመንግስተ ሰማያትንና የሲዖልን መኖር በእርግጥ አውቀናልና ይህንን እውቀት ለሰዎች እንናገራለን:: ከእግዚአብሔር ቁጣ በልጁ ዳኑ ብለን እንሰብካለን ምክንያቱም እኛ ለእግዚአብሔር የተገለጥን ነን:: በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች በማየት ይመላለሳሉ በውጫዊ ነገር ነው ሁሉንም የሚለኩት ለእኛ ግን የውስጥ ማንነት ነው ተጽዕኖ ያለው ስለዚህም ነው ጳውሎስ በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን እንጂ ራሳችንን ደግሞ ለእናንተ የምናመሰግን አይደለንም:: ህይወታችን ምስክር ነው እኛ የተለወጥን ክርስቶስን የምንመስል አዲስ ፍጥረት ነን:: ጉራ እንዳይመስልብኝ ብሎ እንዴት ባለ ትህትና ነው እራሱን የሚያሳያቸው ምስጋናንም አልፈልግም ግን እውነታው እኛ ከውስጥ ወደ ውጭ ተቀይረናል እያለ ነው:: ይህንን ሲል ጳውሎስ በሌሎች ዘንድ እብድ እስከመባል የደረሰበትና ያስናቀው ጉዳይ ጌታ ጌታ ማለቱ ነው ግን ይህንን ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ነው ይላል ምክንያቱም እንደማንኛውም ሰው እኔም ኑሮዬን በአንድ ቦታ አርፌተረጋግቼ ልኑር ቢል ይህንን ሁሉ የሚያስደንቅ ህይወትን የሚለውጥ ቃል በእርሱ ባልደረሰን ነበር:: እብድ ብሆን ለጌታ ነው እያለ አገልግሎቱን የቀጠለ ብርቱ የእግዚአብሔር ሰው ነው:: ዛሬ ከፊታችን የቆመ ሰልፍ ምንድነው ጌታ ሰብሮ ያሻግራል ዛሬም እርሱ በስራ ላይ ነው:: አሜን!
እንደዚህም ተባለ እንደዛ ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ:: የሞተ መቼም ለራሱ አይከራከርም ፍቅሩ ግድ ስለሚለን ለሞተልን ለክርስቶስ እንኖራለን ለሚነሳብን ስደት ብዙም ፊት አንሰጠውም ምክንያቱም እኛ የምናየው የዘላለሙን እንጂ የዛሬውን አይደለም:: እኔ ለክርስቶስ እንጂ ለራሴ የማልኖር ሰው ነኝ::
ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው
2ኛ ቆሮንቶስ 5:15-17
15፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 16፤ ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 17፤ ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።
ስለእኛ ሞትዋልና እየሱስ ለእርሱ እንድንኖር ይጠብቃል!! እርሱ ህይወትን ሰጠን የሰጠንን ህይወት ደግሞ እርሱ እንዲኖርበት መልሰን እንሰጠዋለን::
ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም ምክንያቱም ወደ ህይወት ራስ ወደሆነው ወደ እየሱስ ስንመጣ የሆነው ነገር አዲስ መሆንና መንፈሱን መጋራት ነው:: ይህ አዲስ ማንነት በሚገርም ሁኔታ ጌታን በመንፈስ መገናኘት የሚችል ማንነት ነው:: ሁሉም ሰው ከክርስቶስ ሲወለድ ይህንን ብቃት አግኝቷልና ሰዎችን ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ እንዳሉ ተረድተን እንቀበል:: የሁላችንም ብቃት እራሱ ጌታ ነውና አንዱ ብርቱ ሌላው ደካማ ብሎ ነገር የለም እየሱስ በሁሉ ውስጥ ብርቱ አንበሳ ነውና:: ሁሉንም ሰው በአንድ አይን ማየት አለብን አይናችን አለመከፈቱ እንጂ ቢከፈትማ ጌታን ማየት እንችል ነበር በወንድምና በእህቶቻችን ውስጥ:: ስለዚህ ሰውን ሁሉ በስጋ እንዳለ አላውቅም መንፈሳዊ እንደሆነ እንጂ ልንል ይገባል:: ደክመው ብናይ አንበሳው እየሱስ ዛሬ አሁን ድካምን ማንሳት እንደሚችል እንጂ አለቀለት ብለን ሙሾ የምናወርድ አንሁን ከጌታ የተወለደ አይጠፋም ጌታ ሁሌ ይረዳዋል:: በስጋ እየሱስን የሚያውቀው ዮሀንስ እኮ ጌታን ሲያይ እንደሞተ ሰው ነው የሆነው ጌታ አለ በክብሩ::
ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው ሁላችንም ማንም የሚለውን መስፈርት እናሟላለን ስለዚህ በክርስቶስ የሆንን ቀን ከጌታ ጋር ፋይል ተቀያየርን እርሱ ሀጥያታችንን ወስዶ ጽድቁን አለበስንና በመንፈስ አዲስ ማንነትን በእኛ ውስጥ ፈጠረ የድሮው ማንነት ከአሁኑ ጋር አይገናኙም – አዲስ ፍጥረት አድርጏናል!! አሜን! አዲስ ካለ መቼም አሮጌ የሚባልም ይኖራል ጌታ አሮጌውን ነገር አልፎአል፤ ብሎ አወጀ ምክንያቱም እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። በመንፈስ አዲስ ሆነናል ሰው መንፈስ፤ ነፍስ እና ስጋ ነው:: መንፈሳችን እንዳልነው አዲስ ነው ስለዚህ አሁን ቃል ማንበብና መለወጥ ያለባት ደግሞ ነፍሳችን ናት (አስተሳሰባችን፤ አስተዳደጋችን፤ ቤተሰባችን፤ ባህላችን ሁሉ ተጽዕኖ አድርገውባታልና እስዋ ላይ ነው የምንሰራው ያለነው) ስጋችን ወዳሸነፈው ስለሚወግን ብዙም ስራ አያስፈልገውም:: እኛ አዲስ ፍጥረት ነን ለጌታ የተለየን አሮጌ ተራ የዕለት ዕለት ጌታን የምንናፍቅ ልጆቹ ነን:: አሜን!
እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ ነን በክርስቶስ
2ኛ ቆሮንቶስ 5: 18-21
18፤ ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ 19፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 20፤ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። 21፤ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።
ነገር ግን የሆነው ሁሉ ብሎ ነው የሚጀምረው በዚህ ክፍል ላይ ይህም ማለት ከፊት ያለውን ማየት ግድ ይላል:- “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” ይህ አዲስ ፍጥረት የመሆን እቅድ ከእርሱ መጣ እርሱው ደግሞ መቶ ሞተና ፈጸመው:: ምን አለ በዚህ አዲስ የመሆን መርሀ ግብር ውስጥ የሆነልን?
- በክርስቶስ ከራሱ ጋር አስታረቀን – ልብ እንበል እርሱ እራሱ ነው መቶ የታረቀን እኛ አጥፍተን ሳለን
- የማስታረቅም አገልግሎት ሰጠን – በሉ ሂዱና የሆነላችሁን እየተናገራችሁ ሌላውን ወደ እኔ አምጡ ብሎ ላከን:- እርሱ እራሱ
- እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና :- አሁንም እራሱ ነው ዓለምን ወደ እራሱ እየሳበ ያለው
- በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር :- ለሰዎች መንገርያለብን እግዚአብሔር እንታረቅ ብሏል ኑ ታረቁ በደላችሁን አይቆጥርም ብለን እንናገር:, ወንጌል ይሄ ነው::
- በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ :- ልጁን በእኛ ውስጥ ላከ ይህ ህይወት ያለው ቃል በእኛ አደረ ሌላውን ለማዳን::
- እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን :- መልክተኞቼ ሁኑ ብሎ ላከን ግን በእኛ የሚሰራው እራሱ እንደሆነ እንገንዘብ
- ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን :- እንለምናለን! ምክንያቱም አይተነዋል ምን ማለት እንደሆነ ይቅር መባልና ከጌታ ጋር ህብረት ማድረግ:: አይገርምም እግዚአብሔር እንታረቅ ብሎ ሲልክ:: ወይ ፍቅር!
ስለዚህ ቃሉ እንደሚለን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው:: እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ ነን! ይህ ጉራ እንዳይመስለን ወይም ደግሞ እግዚአብሔር መድፈር እንዳይመስለን ቃሉ እንደሚለን ነን! ትህትና እንዳይመስለን ጻድቅ አይደለሁም ማለት ግን እግዚአብሔርን መቃወም እንጂ! እንንቃ በራሳችን ስላላገኘነው ለመመካትም አንበቃም እርሱ በራሱ ሁሉን አድርጏልና እንቁምና ክብርን እንስጠው::
ምዕራፍ 6
በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፡ በመዳንም ቀን ረዳሁህ
2ኛ ቆሮንቶስ 6: 1-2
1፤ አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ 2፤ በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፡ በመዳንም ቀን ረዳሁህ፡ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።
የእግዚአብሔር መልእክተኞች እንደሆንን ከላይ አይተናል መልክተኛ ደግሞ የተላከውን ያደርሳል ከሚልከው ጋር አብሮ ይሰራል ማለት ነው የመልእክቱ ጠንሳሽ ወይንም ተጠያቂ አይደለም:: እንዲሁም በዚህ ስፍራ ላይ እንደምናየው አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን ይላል:: አብሮ ለመስራት ጌታ ጸጋን ሰቶናልና ይዘን ብቻ ቁጭ እንዳንል ይህ ጸጋ የመጣው ሌላውን ሊጠቅም ስለሆነ በከንቱ እንዳናስቀምጠው ጌታ ይርዳን:: አሁንም ማስታወስ ያለብን ነገር የእግዚአብሔር አምባሳደሮች እንደሆንን አብረንም መልካምን ስራ ለመስራት ጌታ እንደፈጠረን እናስብ::
በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፡ በመዳንም ቀን ረዳሁህ፡ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው። የተወደደ ሰዓት አሁን ነው ይላል ቃሉ ዛሬ እድሉን ካገኘን ለሰዎች እንታረቅ ብሎ መልእክት ልኳል እግዚአብሔር በደልንም አላስብም ብሏል ብለን እንናገር የመዳን ቀን ዛሬ ነውና:: ዛሬየመዳን ቀን የተወደደም ቀን ነው:: ነገ የእኛ አይደለምና ዛሬ ላይ ሳለን ለጌታ እንስራ የመዳን ቀን ዛሬ ነው::
አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ
2ኛ ቆሮንቶስ 6: 3-5
3፤ አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። 4፤ ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ 5፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥
አገልግሎት እንዳይነቀፍ ለሌሎችም ማሰናከያ እንዳንሆን መጠንቅቅ አለብን:: በነገር ሁሉ እራሳችንን እየመረመርን የእግዚአብሔርን ስም እንዳናሰድብና ለሌሎችም እንቅፋት እንዳንሆን እንመላለስ:: እዚህ ጋር ጳውሎስ በአገልግሎቱ የገጠመውን ይነግረናል::
- በብዙ መጽናት/ትዕግስት :- በያዕቆብ 1:4፤ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ለአገልግሎት አስፈላጊው አንዱ ትግስት ነው ሰፊ ልብ ይዘን ነው ማገልገል ያለብን::
- በመከራ፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፦ እስራትና መከራ ይቆይሃል፡ ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። በሐዋ 20: 23 ክርስቶስን ስንመስል እንሰደዳለን
- በችግር፥ በጭንቀት:- ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ሮሜ 8: 35
- በመገረፍ፥ በወኅኒ :- በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። የሐዋ 16: 23
- በሁከት፥ በከተሞም ሁከትን አስነስተውበት ያውቃሉ
- በድካም፥ ሌት ከቀን በመጏዝ ነበር ወንጌልን የሚሰብከው በዚህ ውስጥ ያለውን ድካም መገመት አያቅትም
- እንቅልፍ በማጣት፥ በእስርና በድብደባ በመንገላታትም ሁሉ ውስጥ እንቅልፍ ይኖራል ማለት ዘበት ነው::
የሚገርመው በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ቢያልፍም እንኳን ሁልጊዜ አይኑ በጌታ ላይ ነው:: ሀይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ ነው መፈክሩ:: ይህ ሁሉ መከራ ተስፋ አስቆርጦ አልመለሰውም በዚህ ውስጥ ሆኖ የሚያሳስበው ነገር ቁስሉ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ነገር እንደሆነ ይነግረናል:: አይናችንን በጌታ ላይ ስናደርግና ቆርጠን እርሱን ልናገለግል ስንነሳ አልጋ ባልጋ አይሆንም መንገዱ ሁልጊዜ ጠላት መሰናክል ከፊታችን ያመጣል ተስፋ ለማስቆረጥ ግን እንበርታ በጌታ ጸጋና በችሎቱ አንዳች አይታጣም:: ጌታ ከእኛ ጋር ነውና እንበርታ!
ተስፋፉ
2ኛ ቆሮንቶስ 6: 6-13
6፤ በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ 8 በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤
9 ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ 10 ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 11 እናንተ የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፥ አፋችን ለእናንተ ተከፍቶአል ልባችንም ሰፍቶላችኋል፤ 12 በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል፤ 13 ልጆቼ እንደ መሆናችሁ ግን እላችኋለሁ፥ እናንተ ደግሞ ብድራት መልሳችሁልን ተስፋፉ።
በቀደመው ቁጥር ላይ አገልጋይ ሊደርስበት የሚችለውን መከራ አሳይቶናል:: እዚህ ክፍል ላይ ደግሞ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ያቆመውን ሚስጥር እናያለን:: የሚከተሉት የአገልጋይ ህይወት (qualities) እንደዚህ መሆን አለበት:-
- በመጦም፥ በጌታ ፊት በጾምና በፀሎት መትጋት እንዳለብን
- በንጽህና፥ እግዚአብሔርን በመፍራት በፅድቅ እና ቅድስና መመላለስ
- በእውቀት፥ እግዚአብሔርንና ቃሉን በማወቅ
- በትዕግሥት፥ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት በሰፊ ልብ
- በቸርነት፥ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት ጌታ ያለውን ሁሉ እንደሚያካፍል እኛም እንደዛው እናድርግ
- በመንፈስ ቅዱስ፥ በጌታ መንፈስ ላይ በመደገፍ ብቻ ማገልገል እንጂ በራስ አለመታመን
- ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ ያለ ፍቅር ማገልገል አይቻልም ደቀ መዛሙርት መሆናችን ትልቁ ምልክት ይህ ነው::
- በእውነት ቃል፥ ንጹህ የሆነውን ቃል በመስበክ
- በእግዚአብሔር ኃይል፥ በቃል ብቻ ሳይሆን መንፈስን በመግለጥ ማገልገል
- ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ የጽድቅን ጥሩር እንልበስ ቃሉ እንደሚል
ሌላው በዚህ ክፍል ላይ የምናየው ነገር እንዴት ዓለም እኛን እንደሚያየን እና እኛ መያዝ ያለብን አቋም ነው:-
- በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ መካከል እናማጥናለን፤
- አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤
- ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤
- የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤
- የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤
- ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤
- ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤
- አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።
ስለዚህ እንደዚህ ልባችን ሰፍቶላችሁ ህይወታችንን ሁሉ አካፍለናችሁ ነው ያገለገልናችሁ ብሎ የሚነግራቸውና የሚንደረደረው ወደ አንድ ግብ ነው ግቡም ለዚህ ብድራት እንድትከፍሉን የምንፈልገው በመስፋፋት ነው:: ስፉ አገሩን ሁሉ በክርስቶስ ትምህርት ሙሉት ስታገለግሉም እኛን በመምሰል ይሁን ነው የሚለው:: እኛም ዛሬ እነዚህን ምክሮች በማየት የጌታን ነገር እናስፋ::
እኛ የሕያው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን
2ኛ ቆሮንቶስ 6: 14-18
14፤ ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? 15 ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? 16 ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል። በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። 17–18 ስለዚህም ጌታ። ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ። እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።
አንዳንዴ ሰዎች በስጋዬ የማደርገው ነገርና የፈለኩትን ባገባ ወይም ደግሞ ከፈለኩት ጋር ጏደኛ ብሆንስ ምን ችግር አለው ብለው ሲከራከሩ እሰማለሁ:: እዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ በግልጥ አስቀምጦልናል:: ውሃና ዘይት መቼም አይዋሀድም – ሊከብድ ይችላል ግን ይህ እውነት ነው፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅና የሚፈራ ሰው ማግባት እረፍት ነው:: እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን:: ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ብሎ ሲለን የዳነውን ካልዳነው ጋር ሲያነጻጽረው እስኪ እንይ:-
- ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና?
- ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?
- ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ
- የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?
- ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?
እግዚአብሔር ቤተ መቅደሴ ናችሁ ብሎ ሲል ምን ማለቱ ነው? እንዴት ከሌላው የተለየን ነን?
- በእነርሱ እኖራለሁ :- እኛን ከመውደዱ የትነሳ እኔ ብቻ በነሱ እኖራለሁ ለሌላ አይሆኑም እያለ ነው አምላካችን:: እኔ ቀናተኛ ነኝ ይል የለ?
- በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ ልክ ከአዳም ጋር ያደርግ እንደነበረው ጊዜ በእኛ መካከልም ይመላለሳል
- አምላካቸውም እሆናለሁ:- በእኛ ላይ የሚገዛ ሌላ አምላክ ከእርሱ በቀር የለም!
- እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ:- እኛም ለርስቱ የተለየን ወገን ሆነናል
- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ:- መለየት ግድ ይላል ቅድስና ለእግዚአብሔር
- ርኵስንም አትንኩ ይላል:- ከክፉ ርቀን እርሱን ብቻ እንመስላለን
- እኔም እቀበላችኋለሁ:- እርሱም ተቀብሎናል የእግዚአብሔር ወገን ተብለን ተጠርተናል::
- ለእናንተም አባት እሆናለሁ:- አባ አባ የምንልበትን የልጅነት መንፈስ ሞልቶናል::
- እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል :- አንድ ጊዜ ከማይጠፋው ዘር ተወልደናልና ልጅነታችንን የሚክድ የለም እኛ የህያው እግዚአብሔር ልጆች ነን:: አሜን!
እንግዲህ እንደዚህ ናችሁ ለእኔ እያለን እንዴት አድርገን በማይመች አካሄድ ለመሄድ እንነሳለን? እንዴትስ ከአመጽና ከጨለማ ጋር እንተባበራለን? አረ ይቅርብን ለጌታ መሆን ይሻለናል:: ማመቻመች ትተን ለእግዚአብሔር በዘመናችን ሁሉ እንለይለት! የጌታ ፀጋ ማስተዋልን ይስጠን! አሜን!!
በፈቃዴ እንዲሁም ደስ እያለኝ:- እኔ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነኝ ብዬ አዋጅን አውጃለሁ!!!!
ምዕራፍ 7
ተስፋው የጸና ነው
2ኛ ቆሮንቶስ 7: 1
1፤ እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፥ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።
የዚህ ተስፋ ቃል ካለን የሚለው የቱን ተስፋ እንደሆነ እንመልከት:- እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን፥ በእነርሱ እኖራለሁ፥ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፥ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ልጆች ትሆናላችሁ የሚለውን የተስፋ ቃል ነው የሚጠቅሰው ጳውሎስ። ስለዚህ ይህ የተስፋ ቃል ካለን ምን እናድርግ?
- በእግዚአብሔር ፍርሃት:- እግዚአብሔር ከመስማቱ የተነሳ ፀሎቱ ተሰማለት እንደሚል እኛም ጌታን እየፈራንና እያከበርን እንመላለስ::
- ቅድስናን ፍጹም እያደረግን:- በዚህ ዘመን ችላ የተባለ ነገር ቢኖር ቅድስና ነው:: እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እኛም ቅድስናን እንከታተል::
- ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ
ደህንነታችን ስራ እንደማይፈልግ መዳንም በስራ እንዳልሆነና እየሱስ ክርስቶስ ጽዋዉን ሁሉ ስለእኛ በመጨለጥ ሐጥያት የማያውቀው ንጹ ጌታ ሐጥያት ሆነና እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ እንደተባልን የገባን ህዝቦች ነን:: እዚህ ጋር ጳውሎስ በምድር ስንመላለስ እርሱን እንምሰል ነው እያለን ያለው እንጂ ገና ለገና በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ለማድረግ የምንጥርበት አይደለም ነገር ግን እንደተወደዱ ልጆች ጌታን እየመሰልን እንመላለሳለን ይህንንም ዓለም አንመስልም እራሳችንን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ለጌታ እንለያለን:: ለዚህ ነው ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ የተባልነው:: ምንም አይቀርብንም ጌታን አክብረንና ፈርተን ሰውን ሁሉ ወደን ብንመላለስ አንከስርም እናተርፋለን እንጂ::
የጳውሎስ ደስታ
2ኛ ቆሮንቶስ 7: 2-16
2፤ በልባችሁ ስፍራ አስፉልን፤ ማንንም አልበደልንም፥ ማንንም አላጠፋንም፥ ማንንም አላታለልንም። 3፤ ለኵነኔ አልልም፤ በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን እንዳላችሁ አስቀድሜ ብዬአለሁና። 4 ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፥ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ መጽናናት ሞልቶብኛል፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ከመጠን ይልቅ ይበዛል። 5 ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም፤ በውጭ ጠብ ነበረ፥ በውስጥ ፍርሃት ነበረ። 6 ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ 7 በመምጣቱም ብቻ አይደለም ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም ቅንዓታችሁን ሲናገረን በእናንተ ላይ በተጽናናበት መጽናናት ደግሞ ነው፤ ስለዚህም ከፊት ይልቅ ደስ አለን። 8 በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ አያለሁና አሁን ለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤ 9 በምንም ከእኛ የተነሣ እንዳትጎዱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና። 10 እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። 11 እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፥ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል። 12 እንግዲያስ የጻፍሁላችሁ ብሆን እንኳ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋታችሁ ከእናንተ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በዳዩ ወይም ስለ ተበዳዩ አልጻፍሁም። ስለዚህ ተጽናንተናል። 13 በመጽናናታችንም ስለ ቲቶ ደስታ አብልጦ ደስ አለን፥ መንፈሱ በሁላችሁ ዐርፎአልና፤ 14 ለእርሱ በምንም ስለ እናንተ የተመካሁ እንደ ሆነ አላፈርሁምና፥ ነገር ግን ሁሉን ለእናንተ በእውነት እንደ ተናገርን፥ እንደዚህ ደግሞ ትምክህታችን በቲቶ ፊት እውነት ሆነ። 15 ስለዚህም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደተቀበላችሁት፥ የሁላችሁን መታዘዝ እያሰበ ፍቅሩ በእናንተ ላይ እጅግ በዝቶአል። 16 በነገር ሁሉ ተማምኜባችኋለሁና ደስ ይለኛል።
ጳውሎስ እዚህ ክፍል ላይ እግዚአብሔር እንዴት እንዳፅናናው ከነበረበትም ሀዘን እንዴት እንዳወጣው ይናገራል:: የውጭው አካል እየደከመ ቢሄድም እንኳን የውስጡ ማንነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል:: ቲቶን ሲያገኝ የተፅናናውና የተደሰተበት ምክንያት የላከላቸውን መልእክት ተቀብለው የሚገባ ንስሀ ስላደረጉ ነበር እሱ ያሰበው ጎድቻቸው ይሆን ተረድተውኝ ይሆን እያለ ነበር ፍቅራቸውን ሲሰማና በመልእክቱም ትክክለኛውን አቅጣጫ ሲይዙ ተደስቷል:: የሚገርመው ታምኜባችሁ ነበር አላሳፈራችሁኝም ይላቸዋል ግን እኮ በዝች ቤተክርስቲያን ይሰማ የነበረው ሐጥያት የሚዘገንን ነበር:: ግን ሁሉም ነበሩ ያጠፉት? አልነበረም እንዲያውም ከመካከላቸው አስወግደው ቆፍጠን ያለ አቋም ያዙ ለፍሬ የሚሆን ንስሀን ገቡ:: የጌታን ቤት ስናገለግል ሰፊ ልብ ያስፈልጋል የመንጋው ባልቤት እግዚአብሔር እንደሆነም እንወቅ::
ምንም እንኳን መከራ ቢበዛበትም ለውጭው ማንነቱ ብዙም አይገደውም የጌታ ስራ ሲሰራ ተፅናንቶ ሁሉን በጌታው ይረሳል:: እኛም ዛሬ በጌታ ላይ እንመካ የሁሉ ነገራችን ምንጩ እርሱ ይሁን::
ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ምንን አመጣ?
- እንዴት ያለ ትጋት፥
- እንዴት ያለ መልስ፥
- እንዴት ያለ ቁጣ፥
- እንዴት ያለ ፍርሃት፥
- እንዴት ያለ ናፍቆት፥
- እንዴት ያለ ቅንዓት፥
- እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል።
የጠፉ ነበር የሚመስለው ነገር ግን ጌታ ተከላቸው ትጋትን ጨመረባቸው በስተመጨረሻም ንፁ መሆንን:: የጌታ ፀጋ ይብዛልን!
ምዕራፍ 8
በልግስና ማካፈል
2ኛ ቆሮንቶስ 8: 1-15
ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ 2 በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ 3 እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። 4 ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር፥ 5 አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም። 6 ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ እንደ ጀመረ እንዲሁ ደግሞ ይህን ቸር ሥራ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ሊፈጽም ለመንን። 7 ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደ ተረፋችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ። 8 ትእዛዝ እንደምሰጥ አልልም፥ ነገር ግን በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ፤ 9 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ። 10 በዚህም ነገር ምክር እሰጣለሁ፤ ከአምና ጀምራችሁ ለማድረግ ብቻ ያይደለ ነገር ግን ለማሰብ ደግሞ አስቀድማችሁ የጀመራችሁት ይህ ይጠቅማችኋልና፤ 11 አሁንም ለማሰብ በጎ ፈቃድ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እንዳላችሁ መጠን መፈጸም ደግሞ ይሆን ዘንድ፥ ማድረጉን ደግሞ ፈጽሙ። 12 በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም። 13 ለሌሎች ዕረፍት ለእናንተም መከራ እንዲሆን አይደለም፥ ትክክል እንዲሆን ነው እንጂ፤ 14 የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። 15 ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም።
ምዕራፉ ሲጀምር ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን ብሎ ነው:: ይህ ፀጋ እንዴት እንደረዳቸው ነው የምናየው:-
- በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል – ሊያጉረመርሙና ሊያማርሩ ሲገባ በተቃራኒው በደስታ ተሞልተው የራሳቸው ችግር ሳይታያቸው ስለወገኖች አስበው አካፈሉ
- እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና – ከሚችሉት በላይ ነው የሰጡት
- ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር – ስጡ ተብለው ሳይሆን ካልሰጠን ብለው ነው የሰጡት
- አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ – ከሙስጠት በፊት መሰጠት ይቀድማል
የእግዚአብሔር ጸጋ መከራንና ድህነትን አስረስቶ በደስታና በልግስና የሚሞላ ነው:: ልግስና የሚመነጨው ከሀብት አይደለም ለጌታ ስንሰጥ መስጠት ባህሪያችን ይሆናል እንጂ መስጠት የሀብት መኖርና አለመኖር ጉዳይ አይደለም:: ቃሉም እንደሚል ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም።
ይህች ቤተክርስቲያን ለመርዳት ስታስብ ቆይታለች ግን አላደረገችውም ይህንንም እያበረታታቸው ነው ማሰብ ብቻ ማድረግንም አድርጉ ብሎ:: ልግስናን የተማርነው ከጌታ ነውና በልግስና እንታወቅ ማካፈልን አንርሳ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን::
በራስ ተነሳሽነት ማገልገል
2ኛ ቆሮንቶስ 8: 16-24
16፤ ነገር ግን በቲቶ ልብ ስለ እናንተ ያንን ትጋት የሰጠ አምላክ ይመስገን፤ 17 ምክራችንን ተቀብሎአልና፥ ትጋት ግን ስለ በዛበት ወዶ ወደ እናንተ ይወጣል። 18 ከእርሱም ጋር ስለ ወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም እንልካለን፤ 19 ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን የጌታን የራሱን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግለው በዚህ ቸር ሥራ ከእኛ ጋር እንዲጓደድ በአብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ተመረጠ። 20 ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤ 21 በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና። 22 ብዙ ጊዜም በብዙ ነገር መርምረን ትጉ እንደ ሆነ ያገኘነውን፥ አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከፊት ይልቅ እጅግ ትጉ የሚሆነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር እንልካለን። 23 ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር ስለ እናንተ አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖርም የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞችና የክርስቶስ ክብር ናቸው። 24 እንግዲህ የፍቅራችሁንና ስለ እናንተ ያለውን የትምክህታችንን መግለጫ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ለእነርሱ ግለጡ።
በምናደርገው ሁሉ ትጋትን የሚሰጥ ጌታ ነው ልክ እዚህ ክፍል ላይ እንደምናየው ለቲቶ እንደተሰጠው ሁሉ ለእኛም ይሰጣል:: ቅዱሳንን ለመርዳት መነሳሳትና ማድረግ እንዳለብን ይህ ክፍል ያስተምረናል:: እዚህ ጋር እንደምናየው ቲቶ በራሱ ተነሳሽነት ነው ይህንን ስጦታ የመሰብሰቡን አገልግሎት ለማገልገል የፈለገው እንጂ ጳውሎስ ወይም ቤተክርስቲያን አላከችውም እናም ቤተክርስቲያን በሰዎች ውስጥ የሚመጣውን ምሪት ተቀብላ ልትረዳና ልታበረታታ ይገባል:: እኛ የእግዚአብሔር ቤት አገልጋዮችና የእግዚአብሔር ክብር ተብለን ተጠርተናል እዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ ስለ ወንድሞች እንዳለው::
ምዕራፍ 9
ቅዱሳንን ማገልገል
2ኛ ቆሮንቶስ 9: 1-5
1፤ ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤ 2 በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም። አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል። 3 ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤ 4 ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን። 5 እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ።
ቅዱሳንን ለማገልገል ልባችን ሊነሳሳና በጎ ፈቃድ ሊኖረን ይገባል:: በእርግጥ እዚህ ክፍል ላይ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ማለቱ መዋጯቸውን ነው ለእኛ ደግሞ ጌታን ተዘጋጅተን መጠበቅ አለብን:: ለቅዱሳንም ሆነ ለቤተክርስቲያን ስንሰጥ በስስት ወይም በግዴታ ሳይሆን በልግስና እና በፈቃደኝነት መሆን አለበት::
የምንዘራውን እናጭዳለን
2ኛ ቆሮንቶስ 9: 6-7
6፤ ይህንም እላለሁ፦ በጥቂት የሚዘራ፡ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ፡ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። 7፤ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።
መስጠት ከመዝራት ጋር ይመሳሰላል ዘርን ስንዘራ የሚበቅለው የዘራነው ብቻ ሳይሆን እሱ ሞቶ በብዙ እጥፍ ፍሬው ይበቅላል እንደዚሁም ደግሞ በደስታ ስንሰጥ በብዙ እጥፍ ጌታ ይመለሳል አለን:: ግን የሚመለሰውን ብቻ አስበን ከዘራን ከስረናል ከልባችን ተነክተን በደስታ መስጠት ነው ያለብን:: ለእግዚአብሔር ስንሰጥ
- በደስታ
- በልባችን እንዳሰብን
- በኀዘን ወይም
- በግድ ሳይሆን
ጌታ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እንደዚህ እንስጥ:: እርሱ መስጠትን አስተምሮናል የሰጠንም ህይወቱን እንደሆነ እናስብና ለመስጠት ካበቃን በደስታ እንስጥ::
እግዚአብሔር ለበጎ ስራ እንድትበዙ ጸጋን ሊያበዛላችሁ ይችላል
2ኛ ቆሮንቶስ 9: 8-9
8-9፤ በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል፡ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ፡ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።
ክፍሉ ከላይ ጀምሮ ስለመስጠት እያስተማረን መሆኑ ግልጽ ነው ይህም ደግሞ የምናካፍለው መቼም ሲኖረን ነውና:: ስለሆነም ክፍሉ በነገር ሁሉ የሚለው ውስጥ ዋናው ሀሳብ በሀብት ስለመባረክ ነው የሚናገረው:: ጳውሎስ እንደሚናገረው እግዚአብሔር እራሱ ነው ምስኪኖችን ያሰበው እርሱ ለሁሉ አምላክ ነውና:: እኛም ለምስኪን/ለተቸገረ እንሰጥ እና እናስብ ዘንድ ነው ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝተን፡ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድበዛ ነው ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል የሚለን ደግሞም አስተውሉ እዚህ ጋር:- ሊያበዛላችሁ ይችላል ነው እንጂ አብዝቶላችኃል አይልም ስለዚህ ምርጫ ነው ማለት ነው የምንፈልግ ከሆነ ነው እንጂ ለሁሉ በግድ አይሰጥም:: የሰዎች ጭንቀት ያስጨንቀናል? መርዳትስ እንፈልጋለን? መልሳችን አዎ ከሆነ ለእኔ ብቻ የማይል ልብ ካለን ብቃትን እንደዚሁም ጸጋን ይሰጠንና ሀብትን ማፍራት እንችላለን:: ይህንን ስል ብልጽግና ወንጌል የሚባለውን እየሰበኩ አይደለም የእርሱም ዝንባሌ የለኝም አስተምሮቱም ሁሉንም ለእኔ የሚል አቋም ያለው እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ: : በዚህ ውስጥ ለአምላካችን ክብር አይመጣም ቃሉም እንደሚል:- በዘዳግም 8: 17-18፤በልብህም፦ ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ፡ እንዳትል። 18፤ ነገር ግን ዛሬ እንደ ሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ።
ወገኖቼ ጉልበት የሚሰጠን ሀብት ለማከማቸትና ሌሎችንም ለመባረክ እራሱ ጌታ ነውና አንታበይ:: ስለዚህ ሀብት ቢኖረን ጌታ በዛ ቅር የሚሰኝ ወይም የምንበድል አይምሰለን የተሰጠን ግን ሌሎችንም እንድናስብበት መሆኑ ላይ ይሰመርበት:: ስንሰጥም ጌታን እያከበርን ምስጋናም ለስሙ ከምንባርካቸው ሰዎች እንደሚመጣ እንውቅና እንስጥ:: ጌታ ማስተዋልን ይስጠን! ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም ይላል ቃሉ።
ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን
2ኛ ቆሮንቶስ 9: 10-15
10፤ ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 11 በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ። 12 የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤ 13 በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥ 14 ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል። 15 ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
የሚገርመው እግዚአብሔር እራሱ ነው ሁሉንም የሚሰጠን ደግሞም ፍሬያችንንም የሚያሳድገው::
- ለዘሪ ዘርን
- ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም
- የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል
- ያበረክትላችሁማል፥
- የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል
ልግስናን ማድረግ እንዴት ለእግዚአብሔር ምስጋናን የሚያመጣ እንደሆነ እንወቅ እናም በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ:: በዚህ ሁሉ ውስጥ ሊመሰገን የሚገባው ጌታ ነው ምክንያቱም ሁሉን የሰጠን እርሱ ነውና:: ለመለገስ አንታክት:: ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
ምዕራፍ 10
የጦር ዕቃችን ምሽግን ለመስበር በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው
2ኛ ቆሮንቶስ 10 :1-6
1፤ እኔም ራሴ ጳውሎስ፥ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ግን ብርቅ የምደፍራችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ፤ 2 በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ፥ በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር እለምንችኋለሁ። 3 በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ 4 የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ 5 የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 6 መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።
ከፊተኛው ምዕራፍ ማለትም ስለመስጠት ከሚያወራበት ወደ አገልግሎቱን ወደማብራራት የዞረበት ነው ይህ ክፍል:: ለምን ያልን እንደሆነ አሁንም በእግዚአብሔር የተጠራ ሐዋርያ መሆኑን ለመግለጥና የሚልክላቸውንም መልእክት እንዲያከብሩና እንዲኖሩበትም ጭምር ነው:: ከእናንተ ጋር ሳለሁ ትሁት አሁን ስርቅ ደግሞ የምደፍራችሁ አይደለሁም የሰማሁትን ስህተት ግን እንድታርሙ ብዬ ነው የፃፍኩላችሁ ደግሞም በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ ነው የሚላቸው::
በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ ምክንያቱም:-
- ምንም እንኳ በሰው ልማድ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም :-
- የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና- የጦር ዕቃችን ብለን የምንላቸው በኤፌሶን 6: 10-18 ተዘርዝረዋል:: ቃሉን በመንፈሱ የሚያፀና እራሱ ጌታ ነው::
- ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው
- የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን – ዋናው ጦርነት እኮ በእግዚአብሔር ሀሳብ ላይ መነሳት ነው የሰይጣን ስራ ይህንኑ ነበር ያደረገው በኤደን ገነት እናም ያሳተው:: ስለዚህ ዛሬ ሀሳባችንን እናጢን ጠላት እንዳይፈትነን ሌሎችንም ከተሳሳተ አመለካከት እንመልስ::
- ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን – ጦርነቱ የሚካሄደው በአስተሳሰባችን ላይ ነው:: አስተሳሰባችንን ካገኘ ህይወታችንን እንደወደደ ሊቆጣጠር ስለሚችል ሁልጊዜ አእምሮአችንን ለጌታ እናስገዛ:: ለዚህም ነው ቃሉ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህንን አለም አትምሰሉ የተባልነው:: ቃሉ በአእምሯችን በሞላ ቁጥር የጠላትን ሽንገላና ውሸት እንደዚህ ተብሎ ተጽፏል በማለት እናፈርሳለን ልክ ጌታ በጠላት ሲፈተን እንደመለሰው ማለት ነው:: ለዚህ ነው ቃሉን ጊዜ ወስደን የምናጠናው::
- መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል – አመጻ በእኛ ዘንድ አይገኝም ማለት ነው በመታዘዝ ውስጥ ፍሬን መብላት አለ::
ጸጋን ጌታ የሰጠው ለማነጽ ነው
2ኛ ቆሮንቶስ 10: 7-18
7፤ በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቁጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛ ደግሞ እንዲሁ ነን። 8፤ ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም። 9 በመልእክቶቼ የማስደነግጣችሁ አይምሰላችሁ። 10 መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። 11 እንዲሁ የሚል ይህን ይቁጠረው፤ በሩቅ ሳለን በመልእክታችን በኩል በቃል እንዳለን፥ በፊቱ ደግሞ ሳለን በሥራ እንዲሁ ነን። 12 ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 13 እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም። 14 ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤ 15 –16 በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፥ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር እስክንሰብክ ሥራችንን እየጨመርን፥ በክፍላችን በእናንተ ዘንድ እንድንከብር ተስፋ እናደርጋለን፤ በሌላው ክፍል ስለ ተዘጋጀው ነገር አንመካም። 17 –18 የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና።
በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ የሚናገረው በተለይ እየተቃወሙት ላሉት ወገኖች ነው:: የሚለው ሁሉ እውነት ነው? እግዚአብሔር በእርሱ ይሰራል? እናም ብዙ ሌሎች ጥያቄዎችን እየመለሰ ነው:: በመጀመሪያ ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም ይላል ይህ ጸጋና ስልጣን የሰጠኝ እንዳፈርሳችሁ ሳይሆን ላንጻችሁ ነው ይህ ማለት ሐዋርያነቱ ጥያቄ ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው:: እግዚአብሔር የሚሰጠንን ሁሉ የሚሰጠን ሌላውን ለማነፅ ነው::
ከዚህም አልፈው ስለ ሰውነቱ አቋም እንኳን አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡ አልነበሩም ሰውነቱ ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። ግን ወደ ጌታ የመጡትና ከሞትም የተረፉት በሱ ንግግርና ምስክርነት እንደሆነ ዘንግተዋል:: ለዚህም ነው ከላይ በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሚለው መቼ በሰውነት አቋም ሆነና በውስጡ ሆኖ ከሚሰራው ከእግዚአብሔር እንጂ:: የስጋን ነገር እያዩ ዋናውን የጌታን ነገር እያባከኑት ይገኛሉ::
የእኔ ዓላማ ማገልገል ነእ እናንተን ከደረስን በኃላ ደግሞ ተሻግሮ ወደ ሌሎች መሄድ እንጂ የፉክክር ነገርና እራሴን የማሳየት ነገር የለኝም ነእ የሚለው:: እኛም ሁልጊዜ ይህንን እያሰብን ጌታን ለማክበርና ለማገልገል የተዘጋጀን እንሁን እንጂ ከፊታችን በሚገጥሙን ያልተለወጡ ወገኖች ምክንያት ስፍራን አንልቀቅ:: የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና። እራሳችንን ለማመስገን ከተነሳን ወንጌል አልገባንም ማለት ነው ምክንያቱም ለመዳናችን ምንም አስተዋጽዖ እንዳላደረግን በቀራንዮ እናስብ:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!
ምዕራፍ 11
ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁ
2ኛ ቆሮንቶስ 11: 1-2
1፤ በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ። 2፤ በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤
ይህ ሁሉ የጳውሎስ ጥረቱና ትጋቱ ንፅህት የሆነችን ቤተክርስቲያን ለማጨት ነው እንጂ ሌላ ግብ እንደሌለው እየነገራቸው ነው:: እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ የሌላትን ቤተክርስቲያን እንደሚል ቃሉ በሌላ ስፍራ ላይም እናያለን:: እግዚአብሔር ቀናተኛ ነው በእኛ ላይ ይቀናልና እራሳችንን ለእርሱ እንቀድስ:: የምናገለግለው አገልግሎት ሁሉ ለእርሱ እየቀናን አእምሮን ሁሉ እናስገዛለት:: በቅናት እናገልግል ያለ ነውርና እንከን የሌለው አገልግሎት እናገልግል::
ለክርስቶስ የሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ይኑረን
2ኛ ቆሮንቶስ 11:3-15
3፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። 5 ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደ ጎደልሁ ራሴን አልቆጥርም። 6 በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል በነገር ሁሉ ተገልጠንላችኋል። 7 ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይሆንን? 8 እናንተን ለማገልገል ደመወዝ እየተቀበልሁ ሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ። 9 ከእናንተም ጋር ሳለሁ በጎደለኝ ጊዜ፥ በማንም አልከበድሁበትም፤ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ሰጥተዋልና፤ በነገርም ሁሉ እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅሁ እጠነቀቅማለሁ። 10 የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህት በእኔ ዘንድ በአካይያ አገር አይከለከልም። 11 ስለ ምን? ስለማልወዳችሁ ነውን? እግዚአብሔር ያውቃል። 12 ነገር ግን በዚያ በሚመኩበት እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ፥ ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ። 13 እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። 14 ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። 15 እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።
የጳውሎስ ፍርሀት ምን ነበር? አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ ይላቸዋል ይህንንም በመጀመሪያ ሔዋን ከሳተችበት ጋር ያመሳስለዋል:: ሰይጣን እኮ ሁሌ አንድ ሽንገላ ነው ያለው እሱም እኛን በቂ አድርጎ አሳይቶ እግዚአብሔር አያስፈልግም የሚል ስብከት:: ስለዚህ ሁልጊዜ አሳባችንን እንዳይበላሽና ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ::
በጳውሎስ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ሰይጣን ዛሬም ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና አገልጋዮቹም እንደዛው:: ስለዚህ እራሳችንን ከቃሉ ጋር እያዋሀድን ጌታን እያከበርን እንመላለስ በውስጣችንም ያሉትን የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችን ከመስማትና ከመከተል እንጠበቅ:: እነዚህ ሰዎች ህዝቡ በጳውሎስ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው እያደረጉ ነበር ይህንንም ከንግግሩ እናያለን እርሱ ግን አይደንቅም ይላል ይሄ ሁሉ ውርጅብኝ እየወረደበት እያለ ወደ ሩጫውና አገልግሎቱ ነው የሚያተኩረው እኛም ዛሬ ጠላት አንዳንዶችን እየነዳ እንደሚጠቀም አውቀን አይናችንን በጌታ ላይ በማድረግ መንገዳችንን እንቀጥል አገልግሎታችንንም እሱን የሚያስከብር እናድርግ::
የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት አሳብ ነው
2ኛ ቆሮንቶስ 11: 16-33
16፤ እንደ ገና እላለሁ፦ ለማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ ያለዚያ ግን እኔ ደግሞ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሞኝ እንኳ ሆኜ ተቀበሉኝ። 17 እንደዚህ ታምኜ ስመካ የምናገረው፥ በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም። 18 ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ። 19 ልባሞች ስለምትሆኑ በደስታ ሞኞችን ትታገሣላችሁና፤ 20 ማንም ባሪያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበላችሁ፥ ማንም ቢቀማችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁና። 21 ደካሞች መስለን እንደ ነበርን በውርደት እላለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍርበታለሁ። 22 ዕብራውያን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የእስራኤል ወገን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? 23 እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። 24 አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። 25 ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። 26 ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤. 27 በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። 28 የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 29 የሚደክም ማን ነው፥ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፥ እኔም አልናደድምን? 30 ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ። 31 ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል። 32 በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥ 33 በቅጥሩም ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።
ጳውሎስ እዚህ ክፍል ላይ መከራውን ይዘረዝራል ግን ፈልጎ አይደለም ሌሎች አገልግሎቱን በማናናቅና ሐዋርያነቱን ላለመቀበል ስለተነሱበት ነው:: እስር ቤት እንኳን ሆኖ መከራውን አይናገርም ይህ ሰው:: እራሱን ከተቃዋሚዎች ጋር ሲያወዳዱድር ዕብራውያን ነኝ። የእስራኤል ወገን ነኝ። የአብርሃም ዘር ነኝ። የክርስቶስ አገልጋይ መሆኔን እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ ይላል:: ግን በዚህ ሁሉ ይመካል? በፍጹም በድካሜ ነው የምመካው ነው የሚለው ምክንያቱም በድካም ውስጥ የእግዚአብሔር ፀጋ ይገለጣልና::
ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው ይላል ዛሬ ብዙ አይነት ሰዎች በዙሪያችን ቢኖሩም እንኳን ትኩረታችን መሆን ያለበት ስለ አካሉ:ቤተክርስትያን ሊሆን ይገባል:: ንፁ የሆነ ደስ የሚል የተቀደሰ አገልግሎትን ከማገልገል ወደኃላ አንበል:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!
ምዕራፍ 12
ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማል
2ኛ ቆሮንቶስ 12: 1-10
1፤ ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። 2 ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። 3 እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ 4 ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ። 5 እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። 6 ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ። 7 ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። 8 ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። 9 እርሱም። ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 10 ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።
መንፈሳዊ ነገር የዓለምን እሴት ሁሉ ገልብጦ ነእ የሚያየው ለምሳሌ በዚህ ክፍል ላይ እንደናየው ጳውሎስ እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። (በድካም መመካት የለም በዓለም መደበቅ እንጂ) ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። በችግር ደስ ይለኛል?! ስደክም ኃይለኛ ነኝ?! የሌለ አቋም አይመስልም ዋጋ የማያሰጥ? ግን በጌታ ነው ብርታታችን እርሱ እየረዳን የምንራመድ የእርሱ ሰራዊት ነን:: በድካማችን ውስጥ ብርታትን የሚጨምር ጌታ ስላለን ብንደክምም እናሳድዳለን ኃይል ከእርሱ ነውና ስሙ ይባረክ!
መቼም እዚህ ክፍል ላይ ብዙዎች ብዙ መላ ይሰጡበታል ስለጳውሎስ የስጋ መውጊያ:: አንድ ነገር ማለት የምንችለው ግን ህመም ቢሆን የመፈወስ ፀጋ አለ ደግሞም እግዚአብሔር የዚህ ሰልፍ አቀናባሪ አይደለም ምክንያቱም እዚህ ጋር እየወጋ ኃይል እሰጥሀለሁ አይልም ጌታም በክፉ አይፈትንም:: አንድ የሚያስማማን ነገር ቢኖር ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ ይደበደባል፤ ይታሰራል፤ ይዋረዳል ስለዚህም በሌላ ስፍራ እግዚአብሔርን እየመሰሉ የሚኖሩ ይሰደዳሉ ይላል:: ስደትን ጌታ አያቆምም ሊከተለኝ የሚፈልግ ቢኖር እራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ብሎናል ደግሞም በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ተብለናል:: እስጢፋኖስ ሲወገር ጌታ ሊቀበለው ተነሳ እንጂ አላስቆመውም ወንጌልን ስናደርስ ባለው ግፍያ ወይም የአፀፋ ምት ከጠላት ሰፈር ስደትን ያስነሳል:: ጳውሎስ መውጊያ የሚለውን አሳቡን የወሰደው ከብሉይ ኪዳን ላይ ነው:- መሳፍ 2:3፤ ኢያሱ 23: 13፤ እግዚአብሔር ሆን ብሎ ሳያጠፋ የተዋቸው አሕዛብ እንዴት እስራኤልን እንደሚያስቸግሩ ይናገራል ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ነገር ይቃወማሉ ስደትንም ያስከትላሉ ይህ የማሆነው ትእዛዙን ካልጠበቁና ከጌታ ጋር ካልተስማሙ ነው:: አሁንም ሰልፍ ሲነሳ ጌታ ፀጋን ሰቶ ያሻግራል እንጂ አያጠፋቸውም ቢያጠፋማ ኖሮ ጳውሎስ እራሱ ሲያሳድድ ሳለ በጠፋ ነበት የጌታ ትዕግስት ሁሉ እንዲድኑ ነው:: የጌታ ፀጋ ይብዛልን!
በደስታ ራስን ሰጥቶ ስለማገልገል
2ኛ ቆሮንቶስ 12: 11-21
11፤ በመመካቴ ሞኝ ሆኜአለሁ፤ እናንተ ግድ አላችሁኝ፤ እናንተ እኔን ልታመሰግኑ ይገባ ነበርና። እኔ ምንም ባልሆን እንኳ፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አልጎድልምና። 12 በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም በሁሉ ትዕግሥት ተደረገ። 13 እኔ ራሴ ካልከበድሁባችሁ ከዚህ በቀር፥ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን ያነሳችሁበት በምን እኮ ነው? ይህን በደሌን ይቅር በሉልኝ። 14 እነሆ፥ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ አልከብድባችሁምም፥ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና። 15 እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ። ከመጠን ይልቅ ብወዳችሁ በዚህ ልክ ፍቅራችሁ የሚያንስ ነውን? 16 ይሁን እንጂ እኔ አልከበድሁባችሁም፤ ነገር ግን ሸንጋይ ሆኜ በተንኰል ያዝኋችሁ። 17 ወደ እናንተ ከላክኋቸው በአንዱ ስንኳ አታለልኋችሁን? 18 ቲቶን መከርሁት ከእርሱም ጋር ወንድሙን ላክሁት፤ ቲቶስ አታለላችሁን? በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? በአንድ ፍለጋስ አልተመላለስንም? 19 ለእናንተ ስለ ራሳችን እንድንመልስ ሁልጊዜ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆች፥ እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን። 20 ስመጣ፥ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፤ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፤ 21 እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ።
ጳውሎስ እዚህ ክፍል ላይ እናንተው ግድ አላችሁኝ ስለራሴ እንዳወራ እናንተ እኔን ልታመሰግኑ ይገባ ነበር ይላቸዋል ምክንያቱም፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አልጎድልምና። እናንተ የሰራሁት ካልታያችሁ እንግዲያውስ የተወሰነውን ልጥቀስ:-
- በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም ሁሉ ጌታ ሰርቷል
- አልከበድኩባችሁም ወንጌልን በነፃ ሰጠኃችሁ:- እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና
- ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥
- ራሴን እንኳ እከፍላለሁ ከመጠን ይልቅ እወዳችኃለሁ
- ወደ እናንተ የላኳቸውም አላተለሏችሁም
- ወዳጆች ሆይ፥ እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን
አላማዬ እናንተን እንደ ልጆች እያየሁና እናንተን ማነፅ እንጂ ከእናንተ የማገኘው ነገር አይደለም ትርፌ በፍቅር አገለገልኩ ያለኝንም ሁሉ ሰጠሁ አሁንም እሰጣለሁ ነገር ግን ስመጣ ይስተካከሉ ብዬ ያልኳቸው ነገሮች ካልተለወጡ ያጠፉትም ንስሀ ካልገቡ ልቤ እንዳያዝንና ጊዜያችንን እንዳናባክን እፈራለሁ ይላል:: የስጋ ፍሬን ማለትም (ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም) ሁሉ አስወግደው እንዲጠብቁት አለበለዚያ ግን እኔም በእናንተ እናንተም በእኔ የማትፈልጉት ልታገኙ ትችላላችሁ ብሎ እያስጠነቀቃቸው ነው::
ዛሬ ለእኛ መልእክቱ ምንድነው? በፍቅር ከሰዎች ሳንጠብቅ በታማኝነት ማገልገልንና መሰጠትን ይፈልጋል ጌታ ከእኛ::
ምዕራፍ 13
ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?
2ኛ ቆሮንቶስ 13: 1-14
1፤ ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ሁሉ ነገር በሁለትና በሦስት ምስክር አፍ ይጸናል። 2 –
3 ሁለተኛ በእናንተ ዘንድ በነበርሁ ጊዜ እንደ ተናገርሁ አሁንም ደግሞ በሩቅ ስሆን፥ ክርስቶስ በእኔ አድሮ እንዲናገር ማስረጃ ከፈለጋችሁ፥ እንደ ገና ብመጣ እንዳልራራላቸው አስቀድመው ኃጢአት ላደረጉት ለሌሎችም ሁሉ አስቀድሜ ብዬአለሁ፥ አስቀድሜም እላለሁ። ክርስቶስም ስለ እናንተ አይደክምም ነገር ግን በእናንተ ኃይለኛ ነው። 4 በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንደክማለንና፥ ነገር ግን ስለ እናንተ በሆነ በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን። 5 በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 6 እኛ ግን የማንበቃ እንዳይደለን ልታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ። 7 ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ እኛ የምንበቃ ሆነን እንገለጥ ዘንድ አይደለም ነገር ግን እኛ ምንም እንደማንበቃ ብንሆን፥ እናንተ መልካሙን ታደርጉ ዘንድ ነው። 8 ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና። 9 እኛ ስንደክም እናንተም ኃይለኞች ስትሆኑ ደስ ብሎናልና፤ እናንተ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ ለዚህ ደግሞ እንጸልያለን። 10 ስለዚህ ጌታ ለማፍረስ ያይደለ ለማነጽ እንደ ሰጠኝ ሥልጣን፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በቁርጥ እንዳልሠራ በሩቅ ሆኜ ይህን እጽፋለሁ። 11 በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። 12 በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። 13 ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 14 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
በዚህ የመዝጊያ ክፍል ላይ ጳውሎስ ጌታ ለእኛ ምን እንደሆነልን ያስረዳል:-
- ክርስቶስም ስለ እናንተ አይደክምም ነገር ግን በእናንተ ኃይለኛ ነው
- በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን።
- ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?
ስለዚህ ጳውሎስ የሚሰጠው ምክር
- በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤
- ራሳችሁን ፈትኑ፤
- ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?
- ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን
- ፍጹማን ሁኑ፥
- ምክሬን ስሙ፥
- በአንድ ልብ ሁኑ፥
- በሰላም ኑሩ፥
- የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል
እራሳችንን ስናይ ድካም ይኖራል ነገር ግን እየሱስ ነው ብቃታችን ማንም በራሱ ብቁ አይደለም:: በእግዚአብሔር ኃይል የተጠበቅን እንደሆንም እያሰብን ጌታን እናክብር::
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

ጌታ እግዚ/ር ዘመናችሁን ይባረክ
LikeLiked by 1 person