1ኛ የዮሐንስ መልእክት

መግቢያ:-

የመጽሐፉ ጸሕፊ: ዮሐንስ ነው

የተጻፈበትም ዓላማ:- በዘመኑ ተነስቶ የነበረውን የኑፋቄ ትምርህት ስህተት ለማሳየትና ቅዱሳንን ለማጽናት ነበረ:: የስህተት ትምህርቱ መንፈስ ሁሉ ቅዱስ ነው፤ ሥጋ ሁሉ እርኩስ ነው የሚል ሲሆን የክርስቶስን ሥጋ መልበስ እንኳን ወደ መጠራጠርና መካድ ያመጣ ትምህርት ነበረ ለዚህም ነው ዮሃንስ እኔ አብሬው ነበርኩኝ ዳስሼዋለሁ አብሬውም ኖሬያለሁ እያለ ትምህርቱን የሚያፈርሰው:: ስለዚህም ትምህርቱ ሥጋችን እርኩስ ስለሆነ መጎሳቆል አለበት ደግሞም ምንም አይነት የሥነ ምግባር ብልሽት ቢኖርብን የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ አይደለም ስለዚህ ችግር የለውም የሚል እስከዛሬም ድረስ በየቦታው ብቅ የሚለ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያስቸገረ የስህተት ትምህርት መልስ የተሰጠበት ክፍል ነው:: ሰይጣን ዛሬም ሙሽራይቱን እየተዋጋ ስህተትን በእውቀት አስመስሎ በመዋጋት ላይ ነውና ቃሉን እንወቅ!

በብዙ የሚያተኩረው:-

  1. የክርስቶስን ሥጋ መልበስ (1:1-4)
  2. ክርስትና ከአብና ከወልድ ጋር ያለ ህብረት መሆኑ (1:5; 2:28)
  3. ክርስትና የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ነው (2:29; 4:6)
  4. ክርስትና የሥነ ምግባርና የክርስቶስን ማንነት የመረዳት ውህደት መሆኑ (4:7; 5:12)
  5. የክርስትያን እርግጠኛ እምነቶች (5:13-21)

ይህ መልእክት የተጻፈው በ85 ዓ.ም እንደሆነ ይገመታል::


ምዕራፍ 1

የሕይወት ቃል

1ኛ ዮሐንስ 1: 1
1፤ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤

ዮሃንስ እኔ ከእርሱ ጋር ነበርኩኝ ብሎ የመሰከረው ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ሐዋ 4: 20፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም፡ አሉአቸው ይላል ቃሉ:: ይህ የህይወት ቃል የሆነው እየሱስ ዛሬም ህይወትን ይሰጠናል:: ህይወት እንዲበዛልን ነው እርሱ የመጣው ሌላው ግን ሊሰርቅ ስለዚህ ከተገለጠልን እውነት ጋር እንጽና:: በክርስቶስ ላሉት ኩነኔ የለባቸውም ይለንና በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። አሜን ህይወት ብለን ስንል ከሞትና ከአባቱም ከሐጥያት ህግ ማምለጣችንን እናስብበእኛ ዘንድ የሚሰራው የህይወት ህግ እንደሆነ አውቀን ህይወትን እንከታተል:: እኛም ምስክሮች ነን ይህንን ህይወት በህይወታችን ተገልጦ አይተናልና:: ይህንን ጌታ እናመስግነው እናወድሰው!


ሕይወት ተገለጠ

1ኛ ዮሐንስ 1:2
2፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤

ህይወት ምን አለ? ተገለጠ! ከዛስ? አየነው! ስለዚህ ያየነውን እንመሰክራለን:: የሚሰማ ይስማ!

ይህ ህይወት (እየሱስ) የት ነበረ? በአብ ዘንድ! እርሱ የነበረና ያለ ዘላለማዊ አምላክ ነው:: ከአብ ዘንድ መቶ ተገለጠ! ስለዚህ ያየነውን እናወራለን ደግሞም እንመሰክራለን:: እየሱስም እንደተናገራቸው በዮሐንስ 15: 27፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ። ስላላቸው ይኸው ዮሐንስ ምስክርነቱን እየሰጠን ነው:: ህይወት ህይወት እንሽተት ምክንያቱም ይህ ህይወት በእኛ ተገልጧልና ለሌሎችም ህይወትን መስጠት ይፈልጋል:. ከሞት ወደ ህይወት ተሻገርን! ህይወትን እንግለጠው! እናብለጭልጨው! እርሱ የሚሰራው ነው ሁልጊዜ ዓላማው ህይወትን መስጠት ነው:: ህይወት እንዲበዛልን እንዲትረፈረፍልን መጣ! አሜን ታላቅ ስሙ ይባረክ!


ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው

1ኛ ዮሐንስ 1:3-4
3፤ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። 4፤ ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።

ክርስትና የሚታይ የሚዳሰስ ነው:: እኛ የዘላለም ህይወት ያለን ሰዎች ነን ይህ ህይወት ኅብረት እንድናደርግ አድርጎናል:: ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው:: በሌላ ስፍራ እንደሚለው ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው። እዚህ ኅብረት ውስጥ ህይወት፤ ደስታና እረፍት አለ:: ይህ የገባንበት ኅብረት የተለየ ነው ለመቀላቀልም የተጠየቅነው በልጁ ማመን ብቻ ምክንያቱም ስራው እግዚአብሔር በፍጥረት መጀመሪያ ቃል እንደገባው ከሴቲቱ የሚወለደው የተባለው ህይወት የሚሰጠው ቃል መቶ ያለውን ስለተፈጸመ በማመን ብቻ ኅብረትን አደረግን:: ከማይጠፋውም ዘር ተወለድን ለዘላለምም የጌታ ወዳጆች ሆንንና ኅብረትን እናደርጋለን:: ስሙ ይባረክ! ጌታ እንዴት ያለ ቸርነት አደረገልን?!

ደስታችሁም እንዲፈጸም ነው ይህን የምጽፈው ነው የሚለን። እንግዲህ በጌታ ደስ ይበለን በተሰጠንም ኅብረት ደስ ይበለን ከእርሱ የሚለየን ይህንን ህይወት ከእኛ የሚወስድ የለምና! እርሱ የሰጠን ጌታ ከሁሉ ይበልጣል:: ለምን ከአብና ከልጁ ጋር ብቻ ሆነ ኅብረታችን? መንፈስ ቅዱስስ? እርሱማ በምድር ከእኛ ጋር አይደለ ያለው? ቃሉን እናስተውል! ጌታ ያለን እኔ ወደ ሰማይ ስሄድ እርሱ ይመጣል አላለንም? ብቻችንን እንዳንሆን አብሮን ያለ የሚያበረታን ቅዱሱ መንፈስ አብሮን ነው በዚህም ደስ ይበለን!


እግዚአብሔር ብርሃን ነው

1ኛ ዮሐንስ 1: 5-6
5፤ ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፡ የምትል ይህች ናት። 6፤ ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤

ዮሐንስ እንደሚለን ከእርሱ የሰማናት መልእክት ነው እያለን ያለው መልክቱም እግዚአብሔር ብርሃን ነው ስለዚህም ጨለማ የለበትም ማለት ነው ምክንያቱም የአንዱ መገኘት የሌላው አለመገኘት እንደሆነ ግልጽ ነውና:: ብርሃን ካለ ጨለማ ተሰናብቷል ወይም ጨለማ ከሆነ ብርሃን የለም ማለት ነው አብረው ተዋህደው መሄድ አይችሉም:: ስለዚህ በብርሃን ውስጥ ከሆንን ጨለማው ከወዴት ይገኛል?! በፍጹም መገኘት አይችልምና በብርሃን እንመላለሳለን::

ቃሉ ለእግራችን መብራት ነው እንደቃሉ ከተመላለስን ብርሃኑን ይዘን ከተጏዝን ጨለማ ባለበት አንገኝም ማለት ነው:: ኅብረታችን ብርሃን ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ነውና በጨለማ አንመላለስ ነገራችን በጽድቅ ተደርጎ እንደሆነ በብርሃን እንፈትሽ:: ከፍጥረትም መጀመሪያ መፍጠር የጀመረው ብርሃንን ነው ጨለማውን ገለል አድርጎ ይሰራል:: ወደ እኛም ህይወት ሲመጣ ጨለማችንን ገፈፈውና ብርሃን ይሁን ብሎ ወደ ራሱ አቀረበን ኅብረትም አደረግን! ሃሌሉያ! የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ተጠራን! እኔ የእግዚአብሔር ብርሃን የበራልኝ ልጁ ነኝ! አሜን!


የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል

1ኛ ዮሐንስ 1: 7-10
7፤ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 
በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 
10 ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል የሚለው ቃል እንዴት ልብን ያሳርፋል ምክንያቱም ሐዋርያት አንድ ወቅት ላይ ታድያ ማን ይድናል? እስኪሉ ድረስ ጽድቅ ርቆ ታይቷቸው ነበር ነገር ግን ጌታ የምኅረት አባት ስለሆነ በልጁ ደም እያነጻ ይቀድሰናል:: ታድያ በደሙ ያጥበናል ብለን በሐጥያት እንመላለስ? በፍጹም! ይህ ለሐጥያት የተሰጠ ፈቃድ አድርጎ የሚወስድ ካለ ከቶም የወንጌል ጥሪ ያልገባው ነው ወንጌል በብርሃን መመላለስ ነው ብርሃን ሁሉንም ፍንትው አድርጎ ያሳያልና እራሳችንን እያየን ቃሉ እንደሚል እራሳችንን እንመርምርና እንፈትሽ ህሊናችን ካልፈረደብን ጥሩ ነው::

ለዚህ ነው ያለፍርሃት በፊቱ በብርሃን የምንመላለሰው አንዳች ጉድፍ ቢታይ ኃጢአት የለብንም ብለን ብንክድ ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። ነገር ግን ኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።  ዓመጽን አንውደድ እየሱስ እራሱን የሰጠው እኛን ከአመጽ ለማንጻት ነውና ደግሞም የታመነ ነው ወደ እርሱ በድፍረት እንቅረብና ራሳችንን መርምረን በደሙ እንታጠብ አለበለዚያ ግን ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

እኔ በነገር ሁሉ ትክክል ነኝ ብለን አንኮፈስ ዝቅ እንበል እራሳችንን በፊቱ እናዋርድ ያን ጊዜ ከፍ ያደርገናል ኅብረታችን ከእግዚአብሔር ጋር የተገመደው በፍቅር ነውና ይህ ብርሃን የሆነ አባት አይተወንም! ስሙ ይባረክ!


ምዕራፍ 2

ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን

1ኛ ዮሐንስ 2: 1
1፤ ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ቃሉ የሚለን ሐጥያትን አታድርጉ ነው እንጂ በመግቢያው ላይ እንዳየነው የስህተት ትምህርት ስጋ እርኩስ ነው ምንም አይነት የሥነ ምግባር ብልሽት ቢኖርብን የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ አይደለም እንደሚለው አይደለም:: ደስ የሚለው ሐጥያትን አታድርጉ ብሎ ብቻ አላቆመም ብታደርጉ ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠበቃችሁ ነው ይለናል::

ይህ ጻድቅ የሆነ ጠበቃ ምን ያደርጋል?

  1. ይማልዳል – የጠበቃ ስራው ስለእኛ መከራከር ነው ማምለጫውን ማሳየት ነው:: ጌታ እኮ ለኛ ነው የሚያደላው እንጂ ሊፈርድብን አይደለም
  2. በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ መካከለኛ ነው
  3. ከሳሾችን በትኖ እኔም አልፈርድብሽ የሚል ነው
  4. የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ስለእኛ ሐጥያት የሆነ ነው
  5. በእርሱ በቀር ወደ አብ መግባት አይቻልም የተባለለት ነው
  6. በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድን የሚችል ነው
  7. ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ሊቀ ካህን ነው
  8. በነገር ሁሉ የተፈተነ ስለሆነ እጅግ የሚራራ ሊቀ ካህን ነው

አሜን እርሱ እንደዚህ ስለእኛ ቆሟል እንዴት የሚያስድስት ጌታና አባት ነው?! እንድንጠቃ የማይፈልግ ሁሌ በድል እንድንመላለስ የሚፈልግ አባት:: ሃሌሉያ! በጠበቃችን ደስ ይበለን! ጠላት ኮርነር እስይዞ መውጫ ሲያሳጣን እናስታውስ ጠበቃችን በስራ ላይ ነው ለአፍታ እንኳን ተዘናግቶ አያውቅምና መሸነፍን እርሱት! እርሱን ይዘን አንሸነፍም! ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይህንን ጠበቃ እንድንረዳውና እንድናውቀው ይርዳን! አሜን!


እየሱስ የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው

1ኛ ዮሐንስ 2:2፤ እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።

እየሱስ የኃጢአታችን ማስተስሪያ እንዲሆን ከአብ ዘንድ መቷል በሌላም ስፍራ የዓለሙን ሁሉ ሐጥያት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ ይለዋል:: ይህ በግ ስለሐጥያታችን ለመታረድ ዝም አለ አፉንም አልከፈተ የነገስታት ንጉስ ወደ ሞት ተነዳ:: የሚገርመው ነገር ለሚገባው ሰው እንደው ምናልባት ዋጋ ይከፈላል ነገር ግን አሳልፎ ለሞት ለሰጠና ለገፋ መሞት?! ምን አይነት ፍቅር ነው? ይደንቃል! እኔና እናንተ ውለታው የበዛብን የማይገባን ነበርን እርሱ ግን የተገባን አድርጎ ቆጠረንና የሚወደውን አንድ ልጁን ሰጠን ልጁም በፈቃዱ ስለእኛ ራሱን ሰጠ:: ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የእግዚአብሔርን ፍቅር እንፈጽም

1ኛ ዮሐንስ 2: 3-6
3፤ ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን። አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። 
ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤ 
በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል። 

ጌታን እንደምናውቀው የምናውቅበት መንገድ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ትእዛዙን ስንጠብቅ ነው:: ትእዛዙን ስንጠብቅ ፍቅሩ በእኛ ተፈጽሟል ማለት ነው:: አለበለዚያ ግን አውቄዋለሁ ብለን ትእዛዙን ባንጠብቅ ውሸተኞች ነን:: እግዚአብሔር ከስስቱ የተነሳ ወስዶ በአብ ቀኝ በልጁ ውስጥ ሸሽጎናል በእርሱ ስንኖር እርሱም በእኛ እየኖረ ነውና እርሱ እንደተመላለሰ እንድንመላለስ ነው የሚፈለገው:: ማንነታችንን ባወቅን ቁጥር ወደ እርሱ እየተጠጋንና እየመሰልነው እንሄዳለን:: ይህ ማለት ግን አድርግ አታድርግ አይደለም በፍቅሩ ተሸንፈን እጃችንን የሰጠን ዓለምንም የናቅን ለክብሩ የምንኖር ልጆቹ ነን:: ቀድሶናልና ልንረክስ አንሄድም የኑሮ ደረጃችን ጽድቅን የሚፈልግና ከፍ ያለ ነው:: ይህንን እውነት እንድናውቅ ለረዳን ጌታ ክብር ይሁንለት:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ጌታ አምላክህን ውደድ

1ኛ ዮሐንስ 2: 7
7፤ ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።

ከመጀመሪያ የነበረችው አሮጌ ትእዛዝ ምንድናት? በማቴዎስ ወንጌል 22: 37፤ ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። 38፤ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ዮሐንስም ስለዚህ አሮጌ ትእዛዝ ነው እየነገረን ያለው ጌታም በምድር ሲመላለስ ያስተማረውን ህግም አድርጎ ለህዝቡ የሰጠውን እንጂ ሌላ አልጽፍም ነው የሚለን:: እኛ የጌታ ነንና:: እርሱን ባለን ማንነት ሁሉ እንውደድ! መውደድ ደግሞ በተግባር የሚገለጥ ስለሆነ ከወደድነው እንታዘዘው በቃሉም እንኑር::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን እንድንወደውና እንደቃሉም እንድንኖር!


በጨለማ አንመላለስ

1ኛ ዮሐንስ 2:8-11
8፤ ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል። በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። 10 ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤  11 ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።

ዮሐንስ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ ይላል እውነት ስለሆነው ነገር:: ይህም ነገር በእርሱ እንዲሁም በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው አልፏል እውነተኛውም ብርሃን አሁን በርቷል ይለናል አሜን ብርሃኑን በእኛ ውስጥ አብርቶ ጨለማውን ላባረረው ጌታ ክብር ይሁን:: እንግዲህ በብርሃን ውስጥ እየተመላለስን ካለን ወንድማችንን መጥላት የለብንም እርሱ የጨለማ ስራ ነውና:: አለበለዚያ በጨለማ ነን ወንድማችንን መጥላት በእኛ ውስጥ ከተገኘ:: ችግሩ መጥላት ውስጣችን ሲገባ መንገዳችንንም በቅጡ አናየውም በጨለማ መደናበር ነውና የሚሆነው:: ከፍቅር በቀር እዳ አይኑርባችሁ የተባልን የእርሱ ደቀመዝሙርት ነን:: ደቀመዝሙርነታችንም የሚረጋገጠ በፍቅራችን ነውና እርሱ እንደወደደ መውደድ እንድንችል የእርሱን የፍቅር ጥልቀት እንዲገልጥልን እንጸልይ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በጌታ ተደግፈናል

1ኛ ዮሐንስ 2: 12-14
12፤ ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ። 13 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። 
14 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ። 

ከሚከተሉት በአንዱ የእድሜ ክልል ውስጥ እንጠቃለላለን ብዬ አስባለሁ እናም ዮሐንስ ሊለን የፈለገው እድሜ የጠገበውም፤ ልጅ የሆነውም እንዲሁም ጎበዝ የሆነውም በእግዚአብሔር ቤት በተለያየ ተግዳሮት ያልፋል ነገር ግን ለሁሉ የሚሆን ጸጋና ብርታት ጌታ ለህዝቡ አለው::

ልጆች ብሎ ሁላችንንም ያጠቃልልና ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋል ይልና እንደገና ደግሞ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ:: የኃጥያት ስርየት በእየሱስ በልጁ ስናገኝ በእርሱ በኩል ደግሞ ወደ አብ ለመግባት ድፍረት እንዳለን ቃሉ ይነግረናል ስለዚህም አብን የማወቅ እድል ተሰጠን! አሜን በሌላ ስፍራ እራሱ ጌታ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል ብሏልና ልጁን ያወቀ አባቱንም ያውቃል::

አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና ይላል ይህ ከመጀመሪያ የሚለውን ሀሳብ መጽሐፉን ሲጀምር ገና ነው ያሰፈረው እርሱም:- ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ስለ ህይወት ቃል ነው የሚያወራው:: ይህ የህይወት ቃል የሆነ እየሱስ ተግልጧል ለእናንተም ማወቅ ተሰቷችኃል ነው የሚለው::

ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እንዲሁም ደግሞ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ:: በመዝሙረ 119: 9፤ ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው እብደሚል ቃሉ ይቀድሳል:: ጎበዞች ዓለም የሚያደንቃቸው ጡንቻና ውበት ማሳያ ጊዜ ላይ ቢሆኑም ወጣትነታችንን ለጌታ ብለው ክፉውን እንዳሸነፉ ይመሰክርላቸዋል::

ስለዚህ ከጌታ የተነሳ አሸንፈናል ስሙ ይባረክ!


የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል

1ኛ ዮሐንስ 2: 15-17
15-16፤ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 17፤ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።

ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ ይላል ዮሐንስ:: ለምን? ምክንያቱም መውደድ ያለብን አምላካችንን ነው ለዛውም በፍጹም ማንነታችን ስለዚህ ሌላውን ለመውደድ ቦታ የሌለን መሆን አለብን:: ማንም ዓለምን ቢወድ ግን የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም!! ጌታ ይርዳን ልዮነቱን እንድናስተውል:: በዓለም ያለው እንየው እስኪ:-

  1. የሥጋ ምኞት:- ሮሜ 8:6፤ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። የስጋ ምኞት የሚያመጣብን ሞት ስለሆነ ስለ መንፈስ እንድናስብና እንድንመኝ ነው በክርስቶስ የተፈጠርነው:: ሰልፍን በራሳችን ላይ አንጋብዝ ለጌታ እንለይ እንደቃሉም ለጥቅማቭን ስንል እንመላለስ::
  1. የዓይን አምሮት:- በሄዋን ላይ ይህ ችግር ምን እንዳስከተለ የሰው ልጅ ሁሉ የተባረረበት መነሻው ችግር ነው:: የሰይጣን መግቢያ በር ነውና እንዝጋው::
  2. ስለ ገንዘብም መመካት:- ጌታ እራሱ አስጠንቅቆናል:- በማቲ 6:24 ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። በሌላም ስፍራ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ስር ነው ይላልና ገንዘብን መውደድ ወደ ጥፋት መውረድ ነው::

ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል ስለሚል ቃሉ የሚያልፈውን ትተን የተጠራልነትን የዘላለሙን ፈቃድ እንከታተል እግዚአብሔር ፈቃድ ሰቶናል የምናደርገውን እንወቅ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የመጨረሻው ሰዓት ነው

1ኛ ዮሐንስ 2:18-19
18፤ ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን። 19፤ ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።

ዮሐንስ የነበረበትን ዘመን የመጨረሻው ሰዓት ነው ብሎ ካለ ዛሬ ምን ሊባል ይሆን? የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል ይላል:: የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል አይቀርም የዓለምን አካሄድ ሁሉ አስተውሎ ለሚያይ ነገሮች በደንብ እየተዘጋጁለት እንዳሉ እናያለን:: ስለዚህ ምን እናድርግ? እንናወጥ? በፍጹም መፍትሄው መሆን ያለበት

  1. በጌታ መጽናት እንዲሁም
  2. የእኛ ኑሮ ሁልጊዜ ጌታን የሚያከብር መሆን አለበት ምክንያቱም ጌታ በየትኛዋ ሰዓት መቶ እንደሚወስደን አናውቅምና
  3. ህይወታችን የተዘጋጀ ይሁን:: የክርስቶስ ተቃዋሚ ሲበዛ ግር አይበለን ሌላው ቀርቶ ከመካከላችንም ሊወጡ ይችላሉና
  4. መዳናችንን በፍርሃት እንፈጽም::

ምሰሉና ተመልከቱ የተባልነው ክርስቶስን እንጂ በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች አይደለም አለበለዚያ እነርሱ ሲስቱ እኛም እንሰናከላለን:: እኛ ከዚህ ዓለም አይደለንም የምንሄድበት ያለን መጻተኞች ነን:: ጌታ ይመጣል ሊወስደን! ማራናታ


ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል

1ኛ ዮሐንስ 2: 20-21
20፤ እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። 21፤ እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም።

እንደቀደሙት ቅዱሳን ሁሉ እኛም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብለናል ይህ ቅባት ተብሎ የተጠቀሰው ማነው? የእግዚአብሔር መንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ ነው:: ይህንን መንፈስ በዳንንና ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት በፈለስን ጊዜ ተቀብለናል ወይም ተቀብተናል:: ጌታ እየሱስ እንዳለን እኔ ብሄድ ይሻላል ምክንያቱም አጽናኙ ይመጣላችኃል ብሎን ነበር:: እርሱም በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኃል ብሎን ነበር:: ይህ ቅዱስ ቅባት በእኛ ውስጥ ስላለ ሁሉንም ታውቃላችሁ ይላል:: ይህ የእርሱ ብቃት ነው የእኛ አይደለም::

እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም። የምጽፈው ላጸናላችሁ ነው እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም ነው የሚለን:: ውሸትን ከእውነት እንለይ ዲያቢሎድ የውሸት አባት እንደሆነ እናውቃለን እና ጥቂት መርዝ በብዙ እውነት ውስጥ ቀይጦ ሲሰጠን እንለይ ምክንያቱም ከሰማነው መንፈስ ቅዱስ ይመራል ደግሞም እንዳንወድቅ ያስተምራል::

ከቅዱሱ ቅባት ተቀብያለሁ እውነትም በእኔ ውስጥ አለና አመሰግንሀለሁ:: መንፈስ ቅዱስ ሆይ አስተምረኝ::

ጌታ ጸጋውን ያብዛልን ያትረፍርፍልን!


አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው

1ኛ ዮሐንስ 2:22-26
22፤ ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 23 ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው። 24 እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።  25 እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።  26፤ ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።

ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? ክርስቶስ ወይም መሲኡ እንደሚመጣ እስራኤሎች ጠንቅቀው ያውቃሉ አሁንም ይመጣል ብለው የመጣውን ጌታ እየጠበቁ ነው:: በብዙ ምስክር ሐዋርያቱ ያዮትን የዳሰሱትን አብረው የኖሩትን ጌታ መስክረው ሲያበቁ ክህደትን ሲያዮ የውሸት አባት ከሀዲው እርሱም ሰይጣን የሰውን ልብ እያደነዘዘ እንጂ ከዚህ በላይ ምን ምስክር ያስፈልጋል? እኛም ዛሬ ምስክሮች ነን የእግዚአብሔር ልጅ ሲያድን አይተናል እርሱ ጌታና አዳኝ የሆነው አምላክ ነው:: ማስረጃ ከውጪ እስከማያስፈልገን ድረስ አይተናል ልክ እንደ ሳምራይቱ ሴት የከተማው ህዝብ ሁሉ ተከትሏት ከመጣ በኃላ ከእየሱስ ጋር ከቆዩ በኃላ አሁን የምናምነው ስለቃልሽ ሳይሆን አይተን ነው እንዳሉት:: አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። መንፈስን ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ በዚህ እንለያለን ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሆኖ እየሱስን አይክድም::

ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም ምክንያቱም ወደ አብ መድረሻው መንገድ እየሱስ ብቻ ነው:: በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው። አሜን! እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።  እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው። ይህንን የዘላለምህይወት ለፍተን አይደለም ያገኘነው በልጁ መስዋዕትነት እንጂ ስለዚህም ከእኛ አይወሰድም ጸንተን እንኑር!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእርሱ ኑሩ

1ኛ ዮሐንስ 2 : 27-29
27፤ እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 28፤ አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ። 29፤ ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።

በእርሱ ኑሩ እያለ ይመክረናል ለምን?

  1. እውነተኛ አስተማሪ ስለሆነ:- የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ
  2. ሲመጣ እንዳናፍር:- በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ

በእርሱ መኖራችን የሰጠን ተስፋ እርሱም የዘላለም ሕይወት ነው። ስለዚህ በእርሱ ውስጥ እንኑር:: እናንተ በእኔ ውስጥ እኔም በእናንተ ስጥ እንደሆንኩኝ ያኔ ታውቃላችሁ ብሎናል::


ምዕራፍ 3

የእግዚአብሔር ልጆች ነን

1ኛ ዮሐንስ 3:1
1፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም።

ይህ ፍቅር የሚገባን ማን እንደሆንንና ምን እንደተደረገልን ሲገባን ብቻ ነው:: እኛ በኃጥያታችን ሙታን ነበርን፤ በበደላችን ምክንያት የሞት ቅጣት የሚጠብቀን ነበርን፤ ከፊቱ የኮበለልን ነበርን፤ እንደወደደ ሰይጣን የሚዘውረን ነበርን እንግዲህ ከዚህ አንስቶ ነው ልጅ ሁኑኝ ያለው ጻድቁና ቅዱሱ ጌታ:: ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ውስጥ የሚኖር ብርሃን የሆነ ጌታ በጨለማ የምንደናበረውን ታግሶ፤ መንፈሱን ሰቶ፤ ጸጋን ጨምሮልን በልጁ መስዋትነት አንጽቶ የእኔ ብሎ ጠራን ታድያ ይህ ምን አይነት ፍቅር ነው? ለማይገባው የተሰጠ ፍቅር?

ዛሬ ግን ያ ሁሉ አልፎ የእግዚአብሔር ልጆች ስንባል ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር እራሱ አባታችን ፈልጎ እንዳገኘን እንጂ አንዳች የምንደገፍበት ጽድቅ የሌለን ሰዎች እንደሆንን እንወቅ:: ይህንን ማወቃችን የሚጠቅመን እንዴት እንደምንኖር ህይወታችንን ያስታውሰናል ትላንትና የሌለን ጽድቅ ዛሬ ከእኛ ውስጥ አይወጣምና ዛሬም በእርሱ ጽድቅ ተደግፈን እንኑር እርሱ ስለእኛ ኃጥያት ሆነ እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ:: እባቡ ዛሬም ይሰራል ጽድቃችንን ሊያስቆጥረን ወይንም ደግሞ ህይወታችንን እንድናወዳድር ሊያደርግ ይመጣል “መቼም የእኔ ህይወት ከእከሌ ይሻላል” እንድንል ይፈልጋል ይህ ነገራችን ጌታን ቅር እንደምናሰኝ ጠላት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው:: ስለዚህ ጽድቄ እየሱስ ነው የቆምኩትም በጸጋው የሚለውን ሁልጊዜ እናስታውስ:: እርሱ ፈልጎን መቷል! ዓለም እንዲያውቀን አንጣር አይፈልገንም እኛ አንመችምና የምንኖረው እርሱን ለማስደሰት ስለሆነ የህይወት መርህዋችን ከማንም ባይገጥም አይድነቀን! የጌታም እንደዛው ነበረና:: በእርሱ ዘንድ ተወደናል ተቀባይነትንም አግኝተናልና በጌታ ደስ ይበለን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን


እርሱን እንድንመስል እናውቃለን

1ኛ ዮሐንስ 3
2፤ ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።

የእግዚአብሔር ልጆች ነን ነገር ግን ገና ምን እንደምንሆን አልተገለጠም:: ቢገለጥ ግን እርሱ በእኛ ውስጥ እንዳለ እናያለን ደግሞም እንድንመስለውም እናውቃለን:: አይገርምም?! ቃሉ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው በሮሜ 8: 29፤ ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ ስለዚህ እርሱን ነው የምንመስለው በሌላም ስፍራ እርሱን እያብለጨለጭን እንደምንኖር ይናገራል:: ምን አይነት መታደል ነው? እርሱ እራሱ በእኛ ውስጥ መኖሩ? ስለዚህ ታቦታችንን እየሱስን ተሸክመን ነው የምንመላለሰው:: በሄድንበት ስፍራ ሁሉ መከበር አለበት ሰዎች ከክብሩ የተነሳ ለሚናገሩት ነገር እንኳን መጠንቀቅ አለባቸው::


ኃጢአትም ዓመፅ ነው

1ኛ ዮሐንስ 3: 3-6
3፤ በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል። ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው።  እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም።  በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም። 

ኃጢአትም ዓመፅ ነው! ሌላው ስሙ የኃጢአት አመጽ ነው ማለት ነው ከመጀመርያው ያመጸው ሰይጣን ነበረ አሁንም ሰውን የሚያሳምጸው እርሱው ነው:: ስለዚህ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ እየሱስ ግን ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም። ፍጹም ንጹና ጻድቅ ነው እየሱስ! በነገር ሁሉ የተፈተነ ነገር ግን ምንም ኃጥያት ያላደረገ ጻድቅ ነው::

በእየሱስ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ለዚህ ነው ከላይ እንዳየነው:- ስለሚያስተምረንና ሲመጣ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ የተባልነው:: በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም ቢያደርግስ?

  1. አላየውም!
  2. አላወቀውምም ነው የሚለን ቃሉ:: አያስፈራም?!

በጌታ መሆናችን ወይም እርሱ ጽድቃችን ነው ማለታችን እንደፈለገን እያመጽን እንድንኖር አይደለም ይህም ለኃጢአት ፈቃድ እንደመስጠት እንዳይመስለን እናስተውል:: ኃጥያት አመጽ ነውና! ነገር ግን በእርሱ ውስጥ ስር እየሰደድን እርሱን እንምሰል ጌታ ሊወስደን ይመጣል ሲመጣ እንዳናፍር!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን እውነትንም በውስጣችን ይግለጽልን!


የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ

1ኛ ዮሐንስ 3: 7-10
7፤ ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። 8፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። 9፤ ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም። 10፤ የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።

እዚህ ክፍል ላይ ዮሐንስ ሁለት አይነት ሰዎችን ያሳየንና እንዴት እንደሚለዩም ይናገራል:: አንዱ የጽድቅ ሲሆን ሌላው የአመጽ (ከላይ እንዳየነው ኃጢአት አመጽ ነው):: የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤

  1. አመጽን የሚያደርግ ከዲያቢሎስ ነው:- በመጀመሪያ አምጾ ያሳመጸው ዲያብሎስ ነው:: ስለዚህም የእግዚአብሔር ልጅ ይህንን የአመጽ ስራ ለማፍረስ ተገለጠ::
  2. ጽድቅን የሚያደርግ ደግሞ ከእግዚአብሔር ተወልዷል ይህም ማለት አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው አመጸኛው ማንነት ተሰናብቷል ተቀብሯል ስለዚህ ከዲያብሎስ ጋር መግጠም ቀርቶ ጠላትነት ነግሷል ለእርሱ ሽንገላ እንቢ የሚል ዘር በውስጣችን ተፈጥሯል::

ለዚህም ነው ቃሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም:: ለምን? ምክንያቱም ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ (ይህ የማይጠፋ ዘር በእኛ ውስጥ አለ ስለዚህም በውስጣችን ከገባው ከእግዚአብሔር ልጅ ማንነት የተነሳ ነው እንቢ ማለት የምንችለው) ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም (አይችልም?!) አዎን!! አይችልም::

ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ወንማችንን እንደራሳችን እንውደድ ደግሞም ትእዛዝ ነው:: እኛ በሙሉ ኃይላችን ጌታን የምንወድ ነንና ስለእርሱ ነው የምናስበው የጠላትን አሳብ የምንዘውር አይደለንም ስለዚህ ለዚህ ለሚጠፋ ዓለም አናጎበድድም መንገደኞች ነንና አይናችን በመንገዳችን ላይ ነው:: ለዚህም ነው ከምታዩትና ከምትሰሙት ተጠንቀቁ የተባልነው ጠላት አሳቡን አቀብሎን ስናቆለጳጵሰው እንዳንገኝ ነው ደግሞም ምን ማሰብ እንዳለብን ቃሉ ይመክረናል መልካም የሆነውን ፍቅር ያለበት እያለ አለበለዚያ ግን አሳብ ጸንሶ ምኞትን ይወልዳል በምኞታችንም ተስበን በኃጢአት ማመጽ ይመጣል:: ስለምናስበው እንጠንቀቅ በአእምሯችንም መታደስ እንለወጥ:: ጌታ አምላካችንን እንውደድ እንዲሁም ወንድሞችን እንውደድ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እርስ በርሳችን እንዋደድ

1ኛ ዮሐንስ 3: 11-12
11፤ ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት፦ እርስ በርሳችን እንዋደድ፡ የምትል ይህች ናትና፤ 12፤ ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።

ጌታ እየሱስ ደግሞ ደግሞ የነገረን በምድርም ሲመላለስ ኖሮም ያሳየን ፍቅርን ነው:: ፊተኛይቱ ትዕዛዝ አምላካችንን መውደድ ስትሆን የምትከተለው ደግሞ እርስ በእርስ መዋደድ የምትለው ነች:: ቃኤል ወንድሙን አቤልን የገደለው በተግባር ነው በአዲስ ኪዳን ግን ወንድማችንን ካልወደድን ወይም ፍቅርን ካልሰጠን ያንን ሰው እንደገደልነው ነው የሚቆጠረው:: ለዚህ ነው ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁ በፍቅር ይታወቅ ያለን:: የማስመሰል ጉዳይ ሳይሆን በእውነት ወንድማማች መዋደድ ልንዋደድ ይገባል ጌታ ልብን ይመረምራልና:: ለምን እንዋደድ ያልን እንደሆነ ሰውን ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ ነው እንድናውቅ የተነገረን እንግዲህ ክርስቶስን አንጠላው?! ስለዚህ ክርስቶስን በሰውን ሁሉ ውስጥ ማየት ስንጀምር ያለማዳላት መውደድ እኛ ውስጥ ይሆናል:: ክርስቶስን እናስብ ሞኝ ቢያስብለንም እንኳን የምናደርገውን እናውቃለንና እንቀጥል:: ጌታን መታዘዝ ይበልጥብናል ለእኛ ምክንያቱም የማይገባንን እኛን ወዶ ሞታችንን ሞቶልናልና:: ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን


እንዋደድ

1ኛ ዮሐንስ 3: 13-15
13፤ ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። 14፤ እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። 15፤ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።

በዚህ ጥያቄ ልጀምር:- ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን በምን እናውቃለን? ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን ይላል ዮሐንስ ሲመልሰው:: እውነት ነው? ወንድሞችን እንወዳለን? ሰው በክርስቶስ ካልሆነ በቀር ጠላቱን መውደድ አይችልም ሁሉ ወንድም ነው የዳኑትን ቅዱሳንን ብቻ እንዳይመስለን ሁሉንም የሰው ልጅ መውደድ ይህ ከጌታ የተጋባብን ነገር ነው:: ይህ ነው መመዘኛው ሁሉን ብናደርግ ፍቅር ግን ከሌለን ከንቱ ነው ሁሉም የምናደርገው::

ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ ምክንያቱም ዓለም ክርስቶስንም ጠልታለችና በዓለም ያሉት ሰዎች ብርሃንን አይወዱም ምክንያቱም ነገራቸውን ስለሚገልጠው አይወዱትም ለዚህ ነው የማይቀበሉን:: እኛ ግን መውደድ አለብን::

ወንድሙን የማይወድ ወይም የሚጠላ

  1. በሞት ይኖራል
  2. ነፍሰ ገዳይ ነው
  3. የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።

በፍቅር እንመላለስ ምሳሌያችን እየሱስ ነውና ክርስቶስ እንደወደደን ሌሎችን እንውደድ:: አለበለዚያ ግን በሞት ውስጥ ነን::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ

1ኛ ዮሐንስ 3: 16-18
16፤ እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። 17፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? 18፤ ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።

ምሳሌያችን እየሱስ ነው እርሱ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። እያንዳንዳችን ብዙ የተተወልን ነንና በብዙ ሌሎችን ይቅር እያልን ልንወድ ይገባል:: ብዙ የተተወለት ብዙ ይወዳልና:: እርሱ ፍቅሩን በተግባር አሳይቶናልና እኛም ፍቅራችንን በተግባር እንግለጽ አንድ ሰው የሚያስፈልገውን ማድረግ እየቻልን አለማድረግ የሚያሳየው ፍቅር እንደሌለን ነው ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ የሚለን። ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ነውና የእግዚአብሔር መንፈፈስ በእኛ ውስጥ እስካለ ድረስ ምንም ሳንጥር አዲሱ ማንነታችን እራሱ መገለጥ ይጀምራል:: ከጌታ ጋር ጊዜ እንውሰድ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል

1ኛ ዮሐንስ 3: 19-21
19-20፤ ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፥ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፥ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል። 21፤ ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፥

ስለ ፍቅር እየነገረን መቶ አሁን ደግሞ ልባችሁን መርምሩ ይለናል ምክንያቱም የህይወት መውጫ ነውና:: ልባችን አይታይም ብለን የአፋችንን እንዳናሳይ ደግሞ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል ብሎ እየነገረን ነው ዮሐንስ:: ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት ንጹ ህሊናና ንጹ ልብ እንያዝ በፊቱም እውነተኞች እንሁን:: ፍቅራችን ያለግብዝነት በተግባር ይሁን::


የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን

1ኛ ዮሐንስ 3: 22-24
22፤ ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። 23፤ ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ። 24፤ ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።

ጌታ እየሱስ እራሱ በዮሐ 15: 7፤ በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል ተብለናል። ስለዚህ ጸሎታችን እንዲሰማ የምንፈልግ ከሆነ ትእዛዙን እንጠብቅ:: ትእዛዛቱ ምንድነው? ትእዛዚቱም ይህች ናት፥

  1. በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥
  2. እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።

እየሱስ ትእዛዜን ጠብቁ ያለበት ሌላው ምክንያት እርሱ በእኛ እኛም በእርሱ ስለምንኖር ነው ይህንንም በመንፈስ ቅዱስ እናውቃለን እርሱ በእኛ ስለሚኖር ማንም የእርሱን መኖር ሊያስረዳን አያስፈልግምና እራሱ ቅዱሱ መንፈስ ልጅ መሆናችንን በመንፈሱ በኩል ለመንፈሳችን ይመሰክርልናል ይመራናል ደግሞም ያጽናናናል:: እንደኛ የተሞላቀቀ አለ? ማንንም ስለማያምን ከፍቅሩ የተነሳ መልአክ ሳይሆን የላከልን እራሱ መቶ በእኛ ውስጥእየኖረ ነው ስሙ ይባረክ:::

በእኛ ውስጥ ያለውን ቅዱሱን መንፈስ እያመሰገንን መዋደዳችንን ከፊት ይልቅ እንጨምር::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 4

መንፈስን ሁሉ አትመኑ

1ኛ ዮሐንስ 4: 1-3
1፤ ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥  ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። 

መቼም ያለንበት ጊዜ እግዚኦ የሚያስብሉ ብዙ ነገሮችን ሰዎች በእግዚአብሔር ስም ሲያደርጉ እያየን ነው:: በእግዚአብሔር ቃል ግን ሐሰተኛ ነብይ ማነው? እንዴትስ ለዮ ይለናል?

  1. መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ መብታችን ነው መጠራጠርና ሚዛን ላይ ማስቀመጥ እግዚአብሔር አይቆጣም እንዲያውም ያበረታታል:: ሰይጣን የብርሃን መልአክ እስከሚመስል እራሱን ይለውጣልና ደግሞም በነሄዋን ላይ ተሳክቶለታል::
  2. መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ
  3. ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና:- አሁንም በዛው ዓለም ላይ ነን ሰዎች በክፉ መናፍስት የሚነዱበት ዘመን አላለቀም እየኖርንበት ነውና በቃሉ ሚዛን ላይ እናስቀምጥ
  4. (በሌላ በኩል) የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ የእየሱስን ስራ ያንኳስሳል? በስጋ መገለጡን ይክዳል? ይሸሻል? ወይስ ያጣጥላል? እንደዛ ከሆነ በዚህ ሰው ውስጥ ያለው መንፈስ ከእግዚአብሔር አይደለም ማለት ነው:: ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤

ጌታ ማስተዋልንና ጸጋውን ይስጠን!


በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነው

1ኛ ዮሐንስ 4: 4-6
4፤ ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። 5፤ እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል። 6፤ እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን።

ከእግዚአብሔር ወገን ነንና ከአሸናፊው ወገን ነን:: እርሱ ስለእኛ አሸንፏል ወደኃላ ሄዶ መሸነፍ የለም ከጌታ ጋር ወደፊት እንራመዳለን:: እኛ ከእግዚአብሔር ስለሆንን አሸንፋችኋቸውማል ተባልን፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእኛ ያለው ታላቅ ነው። ሃሌሉያ! ብንደክም እንኳን ይሸከማል ደግሞም 99ኙን ትቶ አንዱን ፍለጋ ይሄዳል:: የሚገርመው በጣም የደነቀኝ ነገር ቢኖር ከዓለም የሆኑ የዓለም ነገር ነው የሚጥማቸው እኛ ግን ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። ይደንቃል! ከእግዚአብሔር የሆነ ይሰማናል አለበለዚያ ግን አይሰማም::

የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን ይላል ቃሉ። በምን እናውቃለን? እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። ስለዚህ ሐይለኛውን አስረን ነው መበዝበዝ የምንችለው በእኛ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣልና:: ሰው ባይሰማን ቢያሾፍ አይድነቀን የዚህ ዓለም ገዢ አሳውሮት ነው::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እግዚአብሔር ፍቅር ነው

1ኛ ዮሐንስ 4: 7-8
7፤ ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። 8፤ ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።

ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ የሚለው አሳብ በጣም ያስደነግጣል እውነት ነውና:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍቅር ነው:: ደስ የሚለው ነገር እግዚአብሔር ፍቅር አለው አይደለም የሚለው እርሱ እራሱ ፍቅር ነውውውው! አለው ካልን ይጨመራል ይቀነሳል በሁኔታ ይለዋወጣል:: የእኛ ጌታ ግን ከማስተዋል የሚያልፍ ፍቅር ነው! ማንነቱ ፍቅር ነው:: ሃሌሉያ! ለእኛ ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ነው የእግዚአብሔር ባህሪ ነውና ከመንፈሱ ወደ መንፈሳችን ይንቆረቆራል:: የእርሱ ነን ካልን አብረነው ከቆየን ይህ ባህሪው ይጋባብናል የእኛም ማንነት በፍቅር የተናኘ ይሆናል:: ለዚህም ነው ቃሉ:-

  1. ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ እንጂ እኛ ፍቅር ኖሮን አይደለም ከእርሱ ነው ፍቅር የመነጨው::
  2. የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ:- የተወለደ ልጅ ወላጁን ይመስል የለ? እኛም ይህንን የመምሰልና በፍቅር መመላለስ ተሰቶናል::
  3. እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ ካወቅነው እንመስለዋለን ታርጋችንም ወይም መታወቅያችን ሌላ አይሆንም::
  4. እርስ በርሳችን እንዋደድ :- ይህ ሁሉ ተሟልቶ የተሰጠን እንድንዋደድና ደቀ መዝሙር መሆናችን እንዲታወቅ ነው::

ብዙ ነገር ብናደርግ ፍቅር ግን ከሌለን ሁሉን በዜሮ ማባዛት ነው:: ስናገለግልም በፍቅር ይሁን፥ ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል የትኛውም የምድር ህግ አይቃወመውም:: እኛ በፍቅር የምንመላለስ ነን:: ሞኝ ቢያስብልም ለእየሱስ ልሁንለት የማደርገውን አውቃለሁና::

ጸጋው በሙላት ያግኘን!


በሕይወት እንድንኖር እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል

1ኛ ዮሐንስ 4: 9-11
9፤ በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። 10፤ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። 11፤ ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።

እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል:: ለምን ላከው? በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ! ስለዚህም በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ ፍቅሩ በተግባር እንጂ በአፍ ወይም በንግግር ብቻ አይደለም:: አንባቢ ሆይ ዛሬ ላረጋግጥ የምፈልገው እውነት እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር መወደዳችንን ነው:: ወደ ዓለም ሁሉ ላከው እንጂ ወደ አንድ የተለየ ሰው ወይም ወገን ብቻአይደለም የተላከው:: እራሳችንን በአጉል ትህትና አናሳንስ ለሁሉ መጣሁ ሲል ያንኑ እውነት እንቀበል እያንዳንዳችን ዋጋ አለን በፊቱ ለማንም አያዳላም::

ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እንዴት? ብለን እንጠይቅ:-

  1. እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን: – መወደዳችን እውነት የሆነና ለዘላለም የጸና ነው ከላይ እንዳየነው የእግዚአብሔር ፍቅር አይጨምር አይቀንስ እርሱ ራሱ ፍቅር ነው:: ስለመወደዳችን አንጠራጠር::
  2. ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ :- ጻድቁ እየሱስ ስለእኛ ብሎ ሐጥያት ሆነና ንጹውን ደሙን ለማስተሰሪያ አንድ ጊዜ እያንጠባጠበ ወደ ቅድስት ወደ አብ ገብቶ ቀደሰን በእርሱ መስዋዕትነት እኛ ነጻ ተባልን! ምን ይባላል ከማመስገን ሌላ?!
  3. እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም:- እርሱ ነው ወዶን የመጣው ሳንጠይቀው ሳንፈልገው ፈልጎንና ወዶን የመጣው:: ሲመጣም ገፋነው ከሰይጣን ጋር ተባብረን እርሱ ግን ታገሰ: ፍቅር ይታገስ የለ?

ይህንን ሁሉ መንደርደሪያ የሚነግረን ሐዋርያው የሚቀጥለውን የህይወት መመሪያ ሊመክረን ነው:: እንግዲህ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅምና እርስ በእርሳችን እንዋደድ:: አለበለዚያ የምናደርገእ ሁሉ በዜሮ ማጣፋት ነው:: ከሰው ጉድለት ከመፈለግ ይልቅ ክርስቶስን እንየው እርሱ ፍጹም ነው አንሰናከልም::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል

1ኛ ዮሐንስ 4
12፤ እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።

እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እንደዚሁም በዮሐንስ 1: 18፤ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። እንዴት ተረከው? እያከበረው በፍቅር እየተመላለሰ ነበር ያከበረው:: ዛሬ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። ከላይ ጀምሮ ደግሞ ደጋግሞ እየነገረን ያለው ፍቅር ፍቅር እያለ ነው ምን ያህል እንደተወደድን አሳየን ደግሞም ጌታን ካወቅነው እኛም የፍቅር ሰው እንደምንሆን ነገረን ነገር ግን በፍቅር ካልተመላለስን ጌታን አናውቀውም:: ያለ ፍቅር አገልግሎት የለም ቢኖርም ተቀባይነት የለውም! እርስ በእርሳችን ግን ብንዋደድ እርሱ በመካከላችን ይኖራል! አሜን! በእኛ ዘንድ እንዲኖር ከፈለግን እርስ በእርሳችን እንዋደድ ሲገኝ ደግሞ ፍቅሩ ፍጹም ይሆናል!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል

1ኛ ዮሐንስ 4: 13-16
13፤ ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን። 14 እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን። 15 ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።  16 እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 

የእግዚአብሔር አብ የፍቅሩ ጥግ የታየው እኮ ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን ሲልከው ነው ይህንንም ዮሐንስ እንደሚለው እኛም አይተናል አባት ልጁን እንደላከው ደግሞም እንመሰክራለን ይላል። አሜን ስለ ሁላችን እየሱስ መከራ ሊቀበልና ሊታደገን ተላከ! አቤት ፍቅር! ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። የሚገርም መዋሀድ ነው:: ግን በእኛ መኖሩን እንዴት እናውቃለን? ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን። የእግዚአብሔርን መንፈስ ዓለም አያውቀውም አለን እየሱስ እናንተ ግን በውስጣችሁ ስለሚኖር ታውቁታላችሁ እንዳለን እርሱ በእኛ ውስጥ እንዳለ ውጫዊ ማረጋገጫም አንፈልግም እርሱ በእኛ እኛም በእሱ እየኖርን ነው::

እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። ምክንያቱም ስለወደደን ነው ከእኛ ጋር ለዘላለም ሊኖር የመጣው ፍቅሩማ ግልጽ ነው:: እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። በምን የሚኖር እንደሚል እናስተውል:- በ ፍ ቅ ር ! የሚኖር:: እኛ ህይወታችንንም መምራት ያለብን በፍቅር እንደሆነ ልብ እንበል ያኔ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል:: ፍቅርን እንከታተል! ይህንን ከመታወቅ የሚያልፍ ፍቅሩን ለማወቅ እንጸልይ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ፍቅር በፍርድ ቀን ድፍረታችን

1ኛ ዮሐንስ 4: 17
17፤ በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና።

በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል:: ፍቅር በፍርድ ቀን ድፍረታችን ነው? አዎን! ምክንያቱም እዳ እንዲኖርብን የሚፈለገው የፍቅር ብቻ ነው ብዙ ሰተን ያልተመለሰ፤ ከተመለሰልንማ የወደዱንን ነው የወደድነው እርሱንማ ሁሉም ያደርገዋል:: የጠሉንን ስንወድ ግን እዳቸው ለእኛ ነጥብ ሆኖ ይያዛል:: ፍቅር ያሸንፋል ደግሞም የቤት ስራ የለውም:- ማለቴ ጠላት መቶ አንቺን ብሎ ክርስትያን እያለ አያዋክበኝም፤ የሚለውም የለውም ዝም ጭጭ ነው የሚለው፤ ህሊናችንም አይፈርድብንም ከዛም አልፎ ጌታ ደስ ይለዋል መገለጫችን ፍቅር ሲሆን:: በፍቅር እንመላለስ እመኑኝ አንከስርም:: ፍቅር ካለ ጌታ አለ በመካከላችን::

እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና። እርሱን የምናሳይ አምባሳደሮች ነን በዚህ ምድር እርሱ በእኛ ውስጥ እየተመላለሰ እንዳለ እንወቅ ስለዚህ የሚወድ በእኛ አድሮ እርሱ እራሱ ነእ እኛማ ፍቅር ከየት አምጥተን የእርሱ ማንነት ነው ፍቅር! ሁሉን እንውደድ የትናንቱን ለትላንትና እንተው ዛሬ አዲስ ቀን ነውና ዛሬን እንኑር ጠላት በትናንቱ ጠብና ቂም ውስጥ እንዳያጠምቀን እንጠንቀቅ:: በተቻለው መጠን ትላንትና ላይ እንድንኖርና የዛሬውን የእግዚአብሔርን ስራ ቸል እንድንል ነው ፍላጎቱ:: እንንቃ! ዛሬ እኔ በፍቅር እገለጣለሁ እወዳለሁ እንበል እራሳችንን እናሳምን ፍቅር የሌለው እግዚአብሔር አያውቅም ደግሞም አላየውም ነው የሚለው ቃሉ:: አምባሳደሮች ነንና እርሱን በፍቅር እናሳይ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በፍቅር ፍርሃት የለም! ፍርሃት ቅጣት አለው!

1ኛ ዮሐንስ 4:18-19
18፤ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። 19፤ እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።

በፍቅር ውስጥ ፍርሃት የለም:: ለምን? መተማመን ስላለ ነው በአጭሩ መልሱ:: እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። የተሰጠን መንፈስ እራሱ የፍርሃት አይደለም የሀይል ደግሞም የድፍረት ነው እንድንፈራ አያደርገንም በሌላም ስፍራ ላይም አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። ፍርሃት ከባርነት ጋር ነው የሚመጣው ልጅ ውስጥ ግን ይህ የባርነት መንፈስ የለም:: እየሱስ እራሱ ባሪያዎች አልላችሁም ወዳጆች እንጂ ብሎናል:: ፍርሃት ካለ አለመተማመን ነግሷል ማለት ነው:: ስንጸልይ እንኳን ጸሎታችን እራሱ ከፍርሃት መሆን የለበትም:: አሁን ምን ይመጣብኛል ይህና ያ ሊደርስብኝ ነው የምንል መሆን የለብንም እርሱ ወዳጃችን አባታችንም ነውና:: ተማምነን ክፉውን ለበጎ የሚቀይር አባት አለኝ ብለን ልንተማመንበት ይገባል:: ከምስጋና ጋር ነገራችንን በፊቱ እናሳስብ እንጂ በአንዳች አንጨነቅ ከጭንቀት የሚቀጥለው ፍርሃት ነውና:: ፍሩ አላለንም! ተማመኑ እንጂ!

ፍርሃት ግን ቅጣት አለው! ለምን እንፈራለን ሁሉን እኛ መቆጣጠር ስለምንፈልግ አይደል? የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። ልጆችንን ስናይ ወላጅ ወደሚወስዷቸው ቦታ እየቦረቁ ከመሄድ በቀር ከፊቴ ክፉ ሊያደርጉብኝ ነው ወላጆቼ ብለው ሳያስቡ እጃችንን ይዘው ይከተላሉ:: ታድያ እኛ በእግዚአብሔር ላይ አደግንበት? ብልጥ መሆናችን ነው?የምንጠራጠረው ወይም ሁለተኛ አማራጭ የምንይዘው እንደነሃናንያና ሰጲራ ካልተሳካ ነው? አማራጭ?! አረ ጌታን እንተማመነው! እርሱ ስለእኛ ያስባል ልጅ ሆነን ሳለን የባርያ ስነልቦና አንያዝ! በፍቅር ተማምነን ህይወታችንን በእርሱ ላይ ጥለን እንመላለስ:: ማንን እንዳሳፈረ ልናፍር?! የእኛ ጌታ እንደሆነ ፍቅር ነው ማንንም አሳፍሮ አያውቅም እርስ በእርሳችን እንዋደድ ይህ ሲሆን አባት ደስ ይለዋል:: በድፍረት መንፈስ እየደገፈን ነውና በፍቅር እንመላለስ:: ፍርሃትን አውጥተን እንጣል! ፍቅራችንም ፍጹም ይሁን!


እግዚአብሔርን እወዳለሁ፥ እያለ ወንድሙን የሚጠላ፥ ሐሰተኛ ነው

1ኛ ዮሐንስ 4
20፤ ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ፥ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፥ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? 21፤ እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።

እግዚአብሔርን ያየ በፍቅር መሞላቱ የማይቀር ነው ፍቅር ብለን ስንል የማያዳላ፤ ይቅር ባይ፤ የማይቀና፤ የማይቀየም፤ ታጋሽ ፤ ርህሩህ ሌላም ሌላም ያለው ነው:: እንግዲህ እግዚአብሔርን እወዳለሁ ካልን ሰውንም ሁሉ እንወዳለን ማለት ነው:: አንድ ስብእና ነው ሊኖረን የሚገባው እየመረጡ መውደድ ብሎ ነገር የለም ለዚህም ነው ቃሉ ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ፥ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፥ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? የሚለው:: ሐሰተኛ ያሰኛል ፍቅር አለኝ እያሉ ሁሉንም እኩል አለመውደድ:: ፍቅርን የምንተገብርበት ሜዳ ላይ ነንና የክርስቶስ መሆናችንን በዚህ እንግለጥ እርሱ ዓለም በሚባለው ሜዳ ላይ ፈጽሞ አባቱን አክብሮ እንዳለፈ እኛም እናክብረው ፈለጋውን ትቶልን ሄዷል::

እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን። የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ እግዚአብሔርን ውደድ የምትል ስትሆን ሁለተኛይቱ ደግሞ ሌላውን እንደራስህ ውደድ የምትለው ናት:: የመጀሪያው ትእዛዝ ያለው ደግሞ ሁለተኛይቱን መኖር ይችላል:: እናስተውል ትእዛዝ ነው መዋደድ ጌታ ያለንን እናስታውስ ቀንበሬ ቀሊል ነው ብሎን ነበር የእኛን ከባዱን ሐጥያት ወስዶ ፍቅርን ሰጠንና ኑሩበት አለን:: ከፈለግን የምናደርገው ወይም መርጠን የምንሰጠው አይደለም የታዘዝነው ነውና በወንድማማች መዋደድ እንዋደድ:: ወንድሜ ከእኔ ይበልጣል የሚል ልብ እንያዝና ዝቅ ብለን እንውደድ ያለ አድልዖ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል

1ኛ ዮሐንስ 5: 1-5
1፤ ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን። 
ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። 
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 
ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? 

የሚገርመው ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። ወላጃችን ማነው? እግዚአብሔር ነው ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ እኔም አባት እሆናችኃለህር ብሎ አባ አባ የሚልን መንፈስ በውስጣችን ጨመረ:: ሃሌሉያ! እርሱን ከወደድን ልጆቹንም ሁሉ እንድንወድለት ነው የሚፈልገው ልክ እንደማንኛውም ወላጅ:: ልጆቼ የሚለው እነማንን ነው? ክርስቶስ ነው ብለው በኢየሱስ የሚያምኑትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልደዋል ስለዚህ እነዚህን እንውደድለት:: እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን።  ትእዛዛቱ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ነው:: ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። ተዋደዱ ሲለን ጸጋውን ሰቶን ነውና እርስ በእርሳችን እንዋደድ:: አብዝተንም እንፈላለግ!

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ከማሸነፍ በፊት መወለድ ይቀድማል ከዛም በእየሱስ ስራ ላይ ባለው እምነታችን ዓለምን እንድናሸንፍ ተደረግን:: ይህም ከጌታ የተወለደ ዓለምን ማሸነፉ ጥርጥር የለውም ምክንያቱም ዘሩ አለና በእኛ ውስጥ ማንም እንዳይመካ ከስራ አይደለም ማሸነፋችን በእምነት ነው እንጂ! ይህንን ድል ለሰጠን ለጌታችን ክብር ይሁን:: ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? ጥሩ ጥያቄ ምክንያቱም በአንድ ወቅት አሸነፍን ያሉ ሁሉ ተሸንፈዋል ሲፈሩት ኖረው ይዟቸው ሄዷል ሞት! እኛ ግን ሞትንናሲኦልን ድል የነሳ ጌታ በውስጣችን ስላለ ምንም አይነት ኃይል ከድላችን ላይ ንቅንቅ አያደርገንም:: ድሉ ገና ድሮ ላይለወጥ ታትሟል!! የጌታ ስም ይባረክ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም

1ኛ ዮሐንስ 5: 6-12
6፤ በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፡ መንፈስ እውነት ነውና። መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።  የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። 10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።  11 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። 12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። 

መጽሐፉን ስንጀምር እንዳየነው አንዱ ምክንያት ለዚህ ክፍል መጻፍ እየሱስ በአካል አልመጣም የሚል የስህተት ትምህርት ምላሽ ነው:: ስለዚህም የመምጣቱ ምስክርነት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ የጸና እንደሆነና የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፡ መንፈስ እውነት ነውና ነው የሚለን:: አብ ስለ እየሱስ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሎ ከሰማይ መሰከረ፤ መንፈስም መቶ በላዩ ላይ አረፈበት ከዚህ በላይ ምስክር ምን አለ? እየሱስ ውሀም ደምም ፈሶታል እኛን ለማዳን ዋጋ ሲከፍል በእርሱ በቀር ወደ አብ መድረስ የለም::

ሰው ይህንን መስክሯል ግን የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው:- ምስክሩ ማነው ከላይ እንዳየነው ስላሴዎች ይመሰክሩልናል! አለበለዚያ ግን ምስክርነቱን አለመቀበል ቃሉ እንደሚለን በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።  እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ደስ አይልም? እግዚአብሔር የዘላለምን ህይወት ሰጠን! ይህ ህይወት በልጁ ውስጥ ነው ስለዚህ ልጁ ያለው ህይወት አለው ልጁ የሌለው ህይወት የለውም:: ጌታን እያመሰገንን እንዋል ስለሆኑልን መዳን፤ ስለ ዘላለም ህይወት እናም ይህንን በነጻ የተሰጠ ህይወት ለሌሎች እንመስክር:: ዛሬ እግዚአብሔር የሚድኑ ነፍሳትን ወደእኛ ይምራ:: አሜን!


እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል

1ኛ ዮሐንስ 5: 13-15
13፤ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። 14፤ በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። 15፤ የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።

የምስራች! የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። ቀላል አይሁንብን መዳናችን የከበረ ነውና ሁሉን ትቶ እኛን ፍለጋ መቶ ዋጋ በህይወቱ ከፍሎ የራሱ ያደረገንን ጌታን እናመስግን:: ይህ የዘላለም ህይወት እንዲኖረን የእኛ አስተዋጾ በልጁ ማመን ብቻ ነውና ሁሉን ያደረገው እርሱ ነው:: በዚህ ህይወት እርፍ እንበል እኛ ወደ እረፍቱ ገብተናል ገና ለመግባት የምንጥር አይደለንም በመወለድ አግኝተናል እርሱ ነው በመስቀል እኛን ለመውለድ ያማጠው:: ሃሌሉያ!

ታድያ ወደ እረፍቱ የገባ ሰው ጸሎቱ እንዲሰማ ፊቱን መቦጨቅና መንከባለል አይጠበቅበትም:: ገና ልባችንን ወደ እርሱ ስናነሳ እርሱ ከሰማይ ሰምቶናል! ቃሉም እንደሚለን በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። ቅድመ ሁኔታው እንደፈቃዱ ብንለምን ብቻ ነው ይህ ፈቃዱ የሚለው ምንድነው? ፈቃዱማ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ነው ፍቅር ካለ ጸሎታችን ሁሉ ከፍቅር ልብ እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነው የሚሆነው ስለዚህ እንሰማለን:: ስለዚህ የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። ልመናው እንደተሰማለት የሚያምን ማመስገን ይጀምራል:: ሃና ይህንን ነው ያደረገችው በፊቱ አነባች ከዛም በኃላ ሀዘንተኛ ሆና አልታየችም:: የጸሎትዋ መልስ ሳሙኤል ነበረ እሱም ቃሉ ጠብ የማይል የእግዚአብሔር አገልጋይ:: የጸሎት ህይወታችንን እንየው እንደፈቃዱ እንጸልይ ደግሞም እንደተቀበልን እንወቅ እና እናመስግን:: ይሁንልህ ወይም ደግሞ ይቅርብህም መልስ ነውና:: ልመናችሁን ከምስጋና ጋር አድርጉ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ስለሌላው እንማልድ

1ኛ ዮሐንስ 5: 16-17
16፤ ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም። 17፤ ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ።

ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው፤ ምን ሲሆን? ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው እዚህ ላይ ነው እንግዲህ እስከአሁን ድረስ የተነገረን ቃል አገልግሎት ላይ የሚውለው:: እርስ በእርስ ተዋደዱ የሚለው:: እንዴት ብትሉኝ? ኃጢአት ሲያደርግ ወንድማችን ስናይ ለሌላ ሰው ነግረን በእንጸልይለት ሽፋን ሀሜት ውስጥ መግባት የለብንም:: የተባልነው እኛው እንድንጸልይ ነው ካየነው እንጸልይእንጂ አንንቀፍ ጌታ አምኖ የሰውን ጉድለት ሲያሳየን እንሸከም:: ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ እርሱ እንዳለ ሆኖ እርስ በእርሳችን እንድንማልድ ጌታ ሊያስተምረን ፈልጎ ነው ከመማለድ ባለፈ ሰውየው ተመልሶ ከጌታው ጋር አስተካክሎ ሳለ እኛ የማንመለስበት አጋጣሚ ብዙ ነው ጌታ ግን የቱን ኃጥያት ብሎ ከንስሀ በኃላ ረስቶለታል ስለዚህ የጌታን ልብ እንያዝ ጎበዝ! እናም በተግባር የሆነ መዋደድ እንዋደድና እንሸከም ደግሞም ይቅር እንበል የወንድማችንን ገበናን ሸፍነን እንሸከም:: ይህ ወተት ከመጋት ወጥቶ አጥንት መቆርጠም ነው! ጌታም ይህንን ጸሎት ይሰማና ሞት የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል! የሚገርመው ይሰጠዋል ሳይሆን ይሰጥለታል ስለ ጸላዩ ብሎ:: ስንቱን መርዳት እንችል ነበር?!

ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም። ይህ ሞት የሚገባው ኃጥያት ምንድነው? መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ነው ጌታም ነግሮናልና:: ለመንፈስ ቅዱስ እንጠንቀቅ!!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እየሱስ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው

1ኛ ዮሐንስ 5: 18-21
18፤ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን። 19 ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን። 20 የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው። 21 ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ

  1. ኃጢአትን እንዳያደርግ:- ለምን ሐጥያትን አያደርግም? ምክንያቱም ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።
  2. ራሱን እንዲጠብቅ:- ሰው እራሱን እንዴት ይጠብቃል? በአእምሯችን መታደስ እንለወጥ እንጂ ይህንን ዓለም አንምሰል ነው ቃሉ የሚለን:: አእምሯችንም የሚታደሰው በቃሉና በመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ለቃሉ ጊዜ እንስጥ እናመንዥገው አእምሯችን ስራ አይፍታ በቃሉ እንሙላው::
  3. ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን:- ልጅ ነንና እግዚአብሔር ስለሚጠብቀን ክፉ አይነካንም እኛ ለእርሱ ተቀድሰናልና በእኛ እርሱ ይታያል::

የክርስትና እምነታችን በአጭሩ ወይም በአንድ ጥቅስ:-

  1. የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፥
  2. እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤
  3. እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥
  4. እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
  5. እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።

የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ ያወቀ የሚያውቅበትን ልብ የተቀበለው ከጌታ ነው የሚኖረውም እውነት በሆነው በልጁ ውስጥ ነው ዓለም በሞላው በክፉ ቢያዝም እኛ ግን እውነት በሆነው በእየሱስ ውስጥ እየኖርን ነው::

በዚህ 1ዮሐንስ ጥናታችንን ጨርሰናል::
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


Published by Betty & Abera

We’re dedicated to share God’s goodness and mercy through His word!

7 thoughts on “1ኛ የዮሐንስ መልእክት

  1. ትሪት መሀመድ ዑመር

    የአባታች አይረሰ አባባሎች የጀግናው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ” ጆይን ይበሉ …………..የቁራዓንና ሀድስ ታምራት። ኢስላማዊ ጉሩፕ ………… ትሪት መለስ ወደ የአቶ መለስ ዜናዊ ቀልዶች ” ልጅ ያለው ህይወት አለው ። የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ህይወት የለውም።( 1ኛ ዮሐንስ 5:12) በመቶርጓም ይህ ማለት ደግሞ አድሱ የኢትዮጵያ የፌዴራል የግብርና ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ዓ.ም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 54(3) እንደምጥስና እንድሁም በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ድንጋጌዎች መሰረት አድሱ የኢትዮጵያ የፌዴራል ግብርና ታክስ አስተዳደር አዋጁ ህገ ወጥ መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን ።

    #ትርት-መለስ-ዜናዊ እና #ሰመሀል-መለስ-ዜናዊ

    Like

  2. አድሱ የኢትዮጵያ ፌዴራል የግብርና ታክስ አዋጅ ቁጥር 979/2008 ዓ.ም በአንቀጽ 11 የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንጽ 54(3) የሚጥስ እንደሆነ በመግለፅ በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 9 መሰረት አድሱ የኢትዮጵያ የፌዴራል የግብርና ታክስ አዋጁ 979/2008 ህገ ወጥ መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን ።

    ትሪት-መለስ-ዜናዊ እና ሰመሀል-መለስ-ዜናዊ

    Like

Leave a reply to Joshua Abera Cancel reply