የያዕቆብ መልእክት

የያዕቆብ መልእክት 1: 1-4

2-3፤ ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት  4፤ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።

ክርስትና  ፈተና እንዳለው እየሱስ ቁልጭ አድርጎ ነግሮን ነው የሄደው አልዋሸንም::  የሚፈተነውም እምነታችን ነው!  ሲፈተንም የሚያፈራው ትዕግስትን ነው::  በመከራ መታገስ ምክንያቱም ዓለም ባሰመረችልን መንገድ የምንሄድ አይደለንም እኛ የምንኖርለት የሞተልን ጌታ አለ::  በአጭር መንገድ እየሄድን የማይገባንም እያደረግን ጌታን አናስከብረውም ፈታኙ ይመጣልና ሊነቀንቀንና ሊነቅለን::  በዚህ ውስጥ ዓለማውያን እንደሚያደርጉት እያመቻመችን አንጏዝም እውነትን እንይዛለን::  አልተዋችሁም ያለንንም ጌታ ከምናልፍበት መከራ ይልቅ ልናምነው ይገባል በጌታችን መወራረድ አለብን::  እነሲድራቅ ሚሳቅ እኮ የተጠየቁት መስገድ ነበረ በባእድ አገር ማን እንዳያያቸው ነው?  በሁሉም ላይ የመጣ ነው ብለው አላጎበደዱም ብንጠፋም እንጥፋ እንጂ አንሰግድም ብለው አልጠፉም ያከበሩት ጌታ በእሳት ውስጥ ተገኘ::  በምናልፍበት ነገር ሁሉ ውስጥ መውጫውን ይሰጠናልና በጽድቅ  እንሂድ ምንም ይሁን ምን::  ወንድሞች እንኳን ምናለበት ቢሉን አንስማ::  እምነታችን እየተፈተነ ነውና ያለ እምነት ደግሞ ጌታን ደስ ማሰኘት አይቻልም!! 

ጌታ ሆይ እኔንና ወገኖቼን በምናልፍበት ፈተና ሁሉ የምንጸናበትን ጸጋ ትሰጠን ዘንድ ትግስትም ስራውን  በእኛ ላይ ይፈጽም በአንተ መታመናችን ይታይ!  አሜን!

ይህንን ቃልሳሰላስል ውዬ ውስጤ እያደገ መጣ::  ያዕቆብ  ይህንን መልእክት የጻፈው ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ነው::  የተበተኑት በመከራ ነው እርሱ ግን እንደሙሉ ደስታ ቀጠሩት ይላቸዋል!  እንዴት ይቻላል ያስብላል ግን ይቻላል:::  ደስታ ከውጭ በምናየው አይደለም የሚመጣው እሱማ ይመጣል ይሄዳል ሁኔታ በተቀየረ ቁጥር::  እኛ ደስ ሊለን የሚገባው በጌታ ነው በማንነቱ ብቻ!!!  ዓይናችንን ከሁኔታ ላይ እናንሳና በጌታ ላይ እናድርግ  ያኔ የእኛ ነገር ከፍና ዝቅ አይልም::  በሚያጸናው ጌታ ላይ እንጽና!  የዓለምን ስብከት ወደጎን እናድርገው እሱ ለእኛ አይደለም ዓለም እንደሚያስብ አናስብ በአእምሯችን መታደስ እንለወጥ ከዚህ ዓለም አይደለንምና የምድርን ቀመር አንጠቀምም::  ነፍሳችንን እናንቃት በእግዚአብሔር ታመኚ እንበላት የመጣው መከራ እምነታችንን አጥብቆት ይሄዳል እንጂ አዳክሞን አይሄድም::  ጌታ ማስተዋልን ይስጠን::

እምነት ሲፈተን መታመናችን ይበዛል::  ትላንትናን ያሻገረን ዛሬም አለ ብለን እንታመናለን::  ይህ ትዕግስት ምንም እስከማይጎድለን ድረስ ፍጹምና ምሉዓን እስክንሆን ስራውን ይፈጽም ጌታ ሲሰራ እስከመጨረሻው ነው ምክንያቱም  ስራው ግሩምና ድንቅ ነውና::   እምነታችን እንደወርቅ ነጥሮ ይወጣና ለምስጋናም ይሆናል::  እንመነው ብቻ ጌታን::   ጳውሎስና ሲላስ በምሪት መተው የት ነው የተገኙት እስር ቤት በስቃይ ግን ጌታ መጣ አልመጣም? ከእነርሱጋር ተገኝቶ የነሱን ብቻ ሳይሆን በእስር ቤት ያሉትን ሁሉ ፈታ::  ከእኛ ያለፈ ስራ ሊሰራ ሲል እንፍቀድለት ሙልጭልጭ እያልን አናስቸግር እንደበሰለ  ደቀ መዝሙር እንከተለው እርሱ ወደ እረፍት ውሀ ዘንድ  ይመራናል::  ብቻ እንታመን ብልጣብልጥ አንሁን!!  እናስተውል መከራ የለም አይደለም ያለን አይዟችሁ አሸንፌአለሁ እንጂ!  እንበረታታ የደከሙትንም እናበርታ!  

የያዕቆብ መልእክት 1: 5-8

5፤ ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። 6፤ ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።7-8፤ ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።

ጥበብ የጎደለንከሆነ ነው ይህንን ጸሎት መጸለይ ያለብን ግን ጥበብ አልጎደለኝም የሚል ይኖር ይሆን?  ያዕቆብ ጥበብን ለምኑ ሲለን ስለተለማመደው ነው በእየሩሳሌም ያለችውን ቤተክርስቲያን ከሚመሩት አንዱ ነበረ::  በዚህ አገልግሎት ውስጥ  ስንቱን በገደሉበት ቦታ ላይ ማገልገል በደንብ ጥበብ የሚያስፈልገው ቦታ ላይ ነው ያለው::  ሌላው ጳውሎስ አእማዕድ ወደሚሆኑት ሄድኩኝ አህዛብ ምን ማድረግ እንዳለባቸስ ህግን ይጨምሩ ወይስ እኔ የማገለግለው ልክ ነው ብሎ ሲመጣ የመጨረሻውን የጥበብ ንግግር ተናግሮ እኛንም ክህግ ነጻ ያደረገን ይህ ሰው ነው::  እኛና መንፈስ ቅዱድ ይህንን ወስነናል ብሎ ለጣኦት ከተሰዋ ከዝሙት እንድንርቅ ያለው እርሱ ነበር::  ጥበብ ስንል የጊዜውን ነገር አውቀን ውሳኔ ማድረግ ነው እንደ ይሳኮር ልጆች ዘመኑን ያውቁ ነበር እንዲሁም ኢሳያስ እንደሚል የተማረ ምላስ ይሰጣል::  የጥበብ መጀምርያውም እግዚአብሔርን ምመፍራት ነው::  በተለይ ውሳኔ መወሰን የሚቸግረን ከሆነ ሳናመነታ ጥበብን እንጠይቅ እርሱም ሳይታዘበን በልግስና ይሰጠናል::  ያለ ጥበብ የየቀኑን ኑሮ መኖር ከባድ ነው ሁሉነገር ውሳኔ ያስፈልገዋል ነገሮች ጥርት ብለው ሊታዩን ይገባል::  እንግዲህ ዛሬ እንጀምር ጥበብን መጠየቅ መወሰን አቅቶን በተንጠለጠሉብን ነገሮች ሁሉ ላይ እርሱም ጥበብን ይሰጠናል::  ስለ ጥበብ ከመማር ይልቅ መለማመድ ይበልጣልና  አምነን እንጠይቅና እንቀበል::  እራሴን ሳይ በብዙ ያስፈልገኛል::  ጌታ ሆይ ጥበብን በእኔም በወገኖቼም ላይ አድርግ ::  በእየሱስ ስም! አሜን!!

የያዕቆብ መልእክት 1: 9-11

9-10፤ የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። 11፤ ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።

መግቢያው ላይ እንደሚናገረው እነዚህ አይሁዶች ተበትነው በስደት ባሉበት ነው ይህ መልክት የተጻፈላቸው::  ባለጠጋ የነበሩ አሁን ደህይተዋል ስለዚህ በምድር ሀብት ላይ በዝቅታቸውም ላይ እንዳይሆን ዓይናቸው እየመከራቸው ነው :: ባለጠጋም ብትሆኑ ያልፋል ደሀም ብትሆኑ ያልፋል ግን ትህትናን ልበሱ ምንም ይሁን ምን የሀብት ደረጃችሁ እንደ እየሱስ ሁኑ እርሱ እኔ በልቤ ትሁት ነኝ አለ ቤት እንኳን አልነበረውም የሰማይና የምድር ፈጣሪ ሆኖ ሳለ::  ከከፍታ ወደዝቅታ ብትወርዱም ሆነ ከዝቅታ ወደ ከፍታ ብትወጡ ይህ በእናንተ ባህሪ ላይ ለውጥ ማምጣት የለበትም ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ ይላል ቃሉ የዋህና ትሁት እንድንሆን ጌታ ይፈልጋል:: የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና ይላል ቃሉ::

የሀብት ደረጃ በእኛ ላይ ተጽኖ ማምጣት የለበትም ሁሉ እንደ ሳር አበባ ያልፋልና ገንዘብ እንዳይገዛን ነገር ህን መገልገያችን እንደሆነ ብቻ አስበን መገዛት ለሚገባን ለንጉሳችን እንገዛ ሁሉም አላፊ ነውና::  ጠላት በተንኮሉ ከዚህ ሀሳብ አያውጣን ምድርን እንናቅ መንገደኞች ነን እኛ::  በምናልፍበት ዝቅታ ሁሉ እምነታችን ተፈትኖ እየዳበረ እንገስግስ ወዳሰበልን መድረሻ::  የአባቴ ብሩካን ተብለን እንድንጠራ የታመሙትን እንጠይቅበት:  የታሰሩትንም እንጎብኝበት ገንዘባችንን በስራ ላይ እናውለው::

የያዕቆብ መልእክት 1: 12-15

12፤ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።  13፤ ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ፡ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።  14፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።

በፈተና መጽናት የህይወት አክሊልን ያሸልማል::  በፈተና የሚፈተነውም ከላይ እንደነገረን እምነታችን ነው::  ስንፈተን ግን እግዚአብሔር እየፈተነኝ ነው የሚል ድምዳሜ ነው ያለን እግዚአብሔር በቃሉናበመንፈሱ ያሳድገንና ይለውጠናል እንጂ እንድንለወጥ ብሎ መከራንና ፈተናን ወደ እኛ አይልክም::  በአእምሯችን መታደስ መለወጥ ያለብን ለዚህ ነው አለበለዚያ ግን የምናስበው ካልተቀደሰና ምኞታችን ካልተለወጠ የሚሆነውን እየነገረን ነው::

ምኞት ፀንሳ  –> ኃጥያትን –> ኃጥያትን አድጎ ሞትን ይወልዳል::

አንዱ ፕሮሰስ ከተጀመረ የተቀረው እየተወለደ ይሄዳል::  ስለዚህ የራሳችንን ምኞት ሳናስገዛ እየተሳብንና እየተታለልን ብንፈተን እግዚአብሔርን እዚህ ውስጥ አንጨምረው::  በፈተና ለሚፀና የህይወት አክሊል ይጠብቀዋል! 

ሲያመንም እግዚአብሔር እያስተማረኝ ነው የምንል አለን ይህ ከቃሉ ጋር አብሮ አይሄድም እርሱ ህመማችንን ተቀበለ እያለን ቃሉ እንደገና ደግሞ ህመምን ሰጠን የሚለው አሳብ አብሮ አይሄድም::  እግዚአብሔር አሳቡን በግብር ይውጣ የሚቀያይር አይደለም እኛ እንኳን ለልጆቻችን የማናደርገውን ያደርጋል ብለን ማሰብ እርሱንና ቃሉን አለማወቅ ነው::  እንደቃሉ እንኑር!  አንድ ነገር እርግጠኛ እንሁን አሁን ያለንበትም ይሁን ወደፊት ያለው ፈተና ከእግዚአብሔር አይደለም እርሱ ግን መውጫውን እንደሚሰጠንና ሊረዳን አብሮን እንዳለ እርግጠኞች እንሁን!! እርሱ ማንንም አይፈትንም!!! ስሙ ይባረክ!

የያዕቆብ መልእክት 1: 16-18

16፤ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ። 17፤ በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።

18፤ ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።

ከላይ እንዳየነው እግዚአብሔር አይፈትንም ብለናል ምክንያቱም  

1.  በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥  አምላካችን ፍጥረትን እንኳን ሲፈጥር በዘፍጥረት ላይ ሁሉም መልካም አድርጎ ነው የፈጠረው እንጂ የሚጎዳ ነገር ፈተናንም የሚያመጣ ነገር አላስቀመጠም ስለዚህ እግዚአብሔር ሊፈትነን ባህሪውም አይደለም መልካም ስጦታ ብቻ ነው ያለው::  ይህንን አሳብ አእምሮአችን ውስጥ ማስገባት አለብን አትሳቱ! እንደሚል እንዳንስት::  በምናልፍበት ፈተና ውስጥ እጅህ የለበትምንይ ተመስገን ልትረዳኝ መተሀልና ተመስገን እያልን በምስጋና እንሞላ አምላካችን ለእኛ ነው የሚያደላው::  በጠላት ሽንገላ እንዳንታለልና ጌታን እንዳናማው እርሱ ፍጹም ነው ስሙ ይባረክ::

2.  መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ የሚገርመው አንድ ቀን አሳቡን ቀይሮ ይፈትነናል እንዳንል አምላካችን አይለወጥም::  በጎ ስጦታ ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ነው:: 

3. በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።  አምላካችን በብርሀን ውስጥ ያለ እንጂ ጨለማ ፈጽሞ በእርሱ ዘንድ የለም እኛንም ሲጠራን ወደሚደነቅ ብርሀኑ ጠራን እኛም በብርሀን እንመላለሳለን!!  ጥላ የለውም ጨለማ ሲኖር ነው ጥላ የሚኖረው የእኛ አምላክ ግን ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሀን ውስጥ ይኖራል!!  

ይህ ጌታ ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደ::  እናስተውል በእውነት  ቃል አስቦ ነው የወለደን!!!  ልጅነታችን የማይቀየር ነው ምክንያቱም እርሱ አይቀይርምና አሳቡን ሃሌሉያ!!!! የነገስታት ንጉስ አስቦ ወለደኝ በመስቀል ምጥ ማን ከእርሱ ይለየኛል መከራ ወይስ ስደት ውይስ ምን ይሆን ይህች ዓለም በእኔ ላይ የምትወረውረው ምንም ነገር ከእርሱ አይለየኝም እርሱ በእኔ እኔም በእርሱ ውስጥ እኖራለሁ::  አሜን

የያዕቆብ መልእክት 1: 19-25

19፤ ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ 21፤ ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። 22፤ ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።

እነዚህ ሰዎች ካላቸው ነገር ሁሉ በወንጌል ምክንያት ከስፍራቸው የተነቀሉና በየቦታው የተበተኑ ናቸው::  ስለዚህ ባሉበት የስደት ህይወት ውስጥ ሲያባብላቸው አናይም ያዕቆብ እንዲያውም ቁጣንና መናገሩን ቀንሱ እግዚአብሔር በክፉ እየፈተናችሁ አይደለም መልካም አምላክ ነውና ጆሮአችሁን ለቃሉ ክፈቱና ስሙ እያላቸው ነው::

እንዲሁም የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ማለትም እርሱ የጠራችሁ መልካም ነውና እምነታችሁ ሲፈተን በርቱ የክፋትን ትርፍ እስወግዱመልካምነት ብቻ ይገኝ በእናንተ ዘንድ እያላቸው ነው::  ዛሬ የሚገፋን ትክክል ባልሆነ መንገድ የሚቃወመንን ሁሉ መልካም በማድረግ ነው የምናሸንፈው እንጂ በክፋት አይደለም:: ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ ይላቸዋል::  እዚህ ያደረሳቸው እውነትን ማወቃቸው ነው ስለዚህ ያንን እውነት ያዙት አርነት የወጣችሁበትን ቃል እናም ጽኑ እያላቸው ነው::  ቃሉን የምታደርጉ እንጂ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ ቃሉ የሚለው አምላክህን በሙሉ ኃይልህ ውደድ ባልንጀራህንም ውደድ ስለዚህ ክፋት ቦታ የለውም መልካም የሆነው አምላክ ወደ ቤቱ ጠርቶን እርሱን እንድንመስል ወስኗልና!!  በቃሉ እንኑር ቁጣንና ብዙ ንግግርን አስወግደን ከጌታ ዘንድ ለመስማት የፈጠንን እንሁን ሰምተንም እንታዘዝ!!  የጌታ ጸጋ ይርዳን ጥበቡንም ይጨምርልን!!

የያዕቆብ መልእክት 1: 26-27

26፤ አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። 27፤ ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።

እዚህ ክፍል ላይ እንደምናየው እግዚአብሔር  ምን  አይነት  አምልኮ  እንደሚወድና  የቱን እንደሚጠላ  ቁልጭ  አድርጎ  ይነግረናል  ያዕቆብ:: 

1. የሚጠላው አምልኮ:- 

1. 1. አንደበቱን የማይገታን  ሰው አምልኮ

ጌታ ሰውየውን አይደለም የሚጠላው ነገር ግን እንደፈለገ አፉን ሳይቆጣጠር በዋለበት አንደበት ለእርሱ ደግሞ አምልኮን ዝማሬን ፀሎትን ሲያመጣለት  ነው::  ከአንደበታችን መውጣት  ያለበት  ቃል  በጸጋ  የተቀመመ  የሚያንጽ  መሆን  አለበት:: ጴጥሮስም እንደሚለን ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ይላል::  በአንድ አፍ መልካምም ክፉም መነገር የለበትም::  አንደበት የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለችና አንደበታችንን እንግታ!

1. 2. ልቡን እያሳተ :-  ልብ ለመሳት ቀላል ነው::  ልባችን የሚከተለው አስተሳሰባችንን ነውና ስለዚህ ነው ቃሉ  በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ ይህንን ዓለም አትምሰሉ የሚለን:: ምክንያቱም  በልብ ያለው ሞልቶ በአፍ ይወጣልና  ውስጣችን የሞላው ምንድነው?!  ጌታም እንዳለ ምግብ ወደ እዳሪ ነው ከልብ የሚወጣው ግን እርሱ ሰውን ያረክሳል::  ልባችን የህይወት መውጫ ነውና ተግተን በቃሉ እንሙላውና እንጠብቀው:: ልባችን የእግዚአብሔር እርሻ ነው  የተዘራውን እንመርምር መራራ ስር አድጎ ሩጫችንን እንዳያሰናክልብን ቃሉን በውስጣችን ይሸሽግልን!!

2.  የሚወደው አምልኮ (ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ):-

2.1.  ወላጆች የሌላቸውን ልጆች –  ብዙ ጊዜ አምልኮ ሲባል ወደ ልባችን የሚመጣው ዝማሬ ነው ግን በተግባርም ማምለክ አለና ዙሪያ ገባችንን እንይ በህፃናት ላይ አንጨክን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እንርዳ በተለይ ወላጅ ከሌላቸውን::

2.2.  ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥  በእድሜ የገፉትን ለራሳቸው ምንም ማድረግ ያልቻሉትንም እናቶችና አባቶችን እንርዳ::  ለደሀ የሰጠ ለእግዚአብሔር አበደረ እንደሚል ብድራትን እንቀበላለን::  በዙሪያችን ብዙ አሉ እንደው ችላ ብለን ካላለፍን በቀር::

2.3.  በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው። ይህ ግልጽ ነው እራስን መጠበቅ ምክንያቱም እኔ የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ነኝና ዓለምን መውደድ በእኔ ውስጥ ሊገኝ አይገባውም::  እኔነቴን ሰጠሁህ ጌታዬ!

ጌታን እንደሚገባው ማምለክ እንድንችል ተምረናልና ቃሉን በተግባር እንኑረው እንጂ አንብበን ብቻ አንለፈው::  ጸጋ ይብዛልን!

የያዕቆብ መልእክት 2: 1-13

1፤ ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። 3፤ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ፡ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ፡ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን?

ወንጌል ካልገባን በትክክል በደሀና በሀብታም መካከል መለያየት እናሳያለን::  ምክንያቱም ወንጌል ለክርስቶስ መሞት ነውና ያልሞተ በስጋ ዓይኑ እያየ ይለያል የሞተ ግን የስጋን ሳይሆን የመንፈስን እውነት ያያል እርሱም ሁሉ በክርስቶስ  አንድ እንደሆነ::  እኛ የክርስቶስ አካል አባል ነን እንግዲህ ወርቅ ሲለብስ ተለይቶ አንገቱ ላይ ወርቅ አለ አንገቱ ሀብታም ነው ጀርባው ግን ደሀ ነው ይባላል?!  አይባልም አካሉ በሙሉ በአንድ ስም ነው የሚጠራው  ራሱ ለብቻ እግሩ ለብቻ አይጠራም::  እንግዲህ የእኛ ራስ ማነው ክርስቶስ አይደለምን?  ቅዱሳንን ሁሉ በአንድ ዓይን ማየት አለብን ሁሉም ሰው ከኔ ይሻላል የሚለውን እውነት ጠንቅቄ ማወቅ አለብኝ አባባል አይደለምና ወይም አጉል ትህትናም አይደለም እውነት እንጂ::  ዓይኖቼ ከተከፈቱ በሁሉ ውስጥ ክርስቶስን ነውና የማየው ሁሉ ይበልጠኛል ለማለት አልግደረደርም::  

የወንጌል እውነት ከገባን የምናተኩረው የሰው መዳን ላይ እንጂ በስጋ ስላለው ኃብትና ድህነት ላይ አይሆንም የሁሉ ነብስ ለጌታ ዋጋ አለው እራቁታችንን እንደመጣን እንዲሁ ምንም ሳንይዝ ለምንሄደው የዓለም ትርፍ ሰውን አንለያይ::  ልብን የሚመረምር ጌታ ያየናል::  ሁሉን በአንድ ዓይን ማየት ይሁንልን::

የያዕቆብ መልእክት 2: 5፤ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? 

መንግስትን ሊያወርስ ጌታ የመረጠውን ክቡር ሰው እንውደድ ያለ መለያየት::  ፍቅራችን ያለግብዝነት ለሁሉ ይሁን!! ማስተዋልን ጌታ ይስጠን::

የያዕቆብ መልእክት 2: 14-26

14፤ ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?  17፤ እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። 20፤ አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?

ይህንን ክፍል ሙሉውን ስናነብ የሚመስለው፤ መዳን ማለት እምነት ሲደመር ስራ ነው አይደል ግን እንደዛ አይደለም::

መዳን በእየሱስ በማመን ብቻ ነው ማንም እንዳይመካ እያለ እያስጠነቀቀ ጳውሎስ ነግሮናል::

ያዕቆብ የሚለው ግን አንድ ጊዜ ከዳናችሁ በኃላ ያለውን ኑሮ በስራ አሳዩ ነው::  ለምን ክርስቶስን ወደ መምሰል እንለወጣለን ታድያ?!  የመንፈስስ  ፍሬ ጥቅሙ ምን ላይ ነው?!  ፍቅር ፥  ቸርነት ፥  በጎነት ፥  ትዕግስት?  ይህ ሁሉ የሚያስፈልገን እኮ በዓለም ስንኖር ብርሃን ሆነን እንድንመላለስ ነው:: ስለዚህ ስራ ሰርቼ ነው ደህንነቴን የያዝኩት ወይም እየጠበኩት ህይወቴን ያለሁት ብለን ካሰብን ስተናል::  የዳነው በጸጋ ነው እግዚአብሔር አብ አንድ ጊዜ በልጁ ደስ ተስኝቶ እርሱን ስሙት ብሎናል::

መልክቱ የተጻፈላቸው አይሁድ ናቸውና የቱን ህግ ጠብቀው የቱን እንደሚተው፥ እንዴት እንደሚጸልዩ፥  ማኅበራዊ ኑሮአቸው እንዴት መሆን እንዳለበት ነው የሚነግራቸው::  ምክንያቱም ስደት ላይ ችግር ውስጥ ናቸው አንዳንዱ ተርቦ ሌላው ጠግቦ የወንድሙን መራብ እንኳን አያስተውልም ይህንን እንዲያስተካክሉም ነው::  ሀብታሞቹ መተው ቤተክርስቲያንን እንዳይቆጣጠሩ ግን ሰው ሁሉ እኩል እንደሆነ እንዲያውቁ ፥  ወላጆቻቸውን በዚሁ በመከራው ያጡትን ህፃናት እንዳረዱ::  ጧሪ ያጡትንም እንዲያስቡ ጠለቅ ያለ የቀን ከቅን ኑሮአቸውን ነው የሚዳስሰውና እንዲያስተካክሉ የፃፈላቸው::  ይህ ሰው የእየሩሳሌምዋን ቤተክርስቲያን ከሚመሩት መካከል እንደመሆኑ ይህንን ጽፏል::

ዛሬም እኛ በፍቅር እየተመላለስን በዙሪያችን ያለውን መማረክ አለብን ክርስትና የቃል ሽምደዳ ሳይሆን ቃሉን መኖር ነውና እምነታችንን ለሌሎች መግለጥ እንድንችል ጌታ ይርዳን:: 

የያዕቆብ መልእክት 3: 1-12

2፤ ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። 5፤ እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። 6፤ አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል። 9፤ በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤

አንደበት :- 

ትንሽ ብልት ነው

እሳት ነው

ሥጋን ሁሉ ያሳድፋል

የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል በገሃነምም ይቃጠላል

አብን እንባርክበታለን

ሰዎች እንረግማለን?

የሚገርመው ነገር ይህች ትንሽ የሆነች ብልት እንዴት ማንነታችንን መቆጣጠር እንደምትችል ነው የሚያሳየው::  አንደበት ቀላል ስራ የለውም በህይወታችን ውስጥ::  ቃሉ እንደሚል በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። ፍጹም የሚያስብል ውጤትን የሚያስገኝ ነው አንደበትን መግዛት::  ልክ አንድ የምንጭ ውሀጋር ሄደን የጣፈጠን ውሀ ቀድተን  ነገ ስንመለስ የመረረ እንደማይሆን እንዲሁ አንደበታችን የሚያወጣው የጣፈጠ መሆን አለበት ሁልጊዜ አንድ አይነት::  እሩጫችንን ነው የሚያጠፋው  የለፋነው ሁሉ ከንቱ ይሆንብናልና እንጠብቅ ከአንደበታችን የሚወጣውን::

በዚሁ አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን?!  ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ዓይን እኩል እንደሆነ አንዘንጋ ደሀውን አመናጭቀን ሀብታሙን ተለማምጠን ማናገር የለብንም ይህ ምንጭ አንድ አይነት ውጤት ነው መስጠት ያለበት::

ብዙ ስተን ሊሆን ይችላል ዛሬ ግን ንስሀ እንግባና እንስተካከል ከአንደበታችን መውጣት ያለበት የሚያንጽ በጨው የተቀመመ መሆን አለበት አለበለዚያ ግን አንናገር:: በዚሁ አንደበት ነውና ጌታ ፊት ቀርበን የምንፀልየና የምንባርከው ስለዚህ አናቆሽሸው::  የተቀበልነው መንፈስ ራስን መግዛት የሚያስችል ነው እንጂ ከምንችለው በላይ እንድንዘረጋም አልተጠየቅንም ለጸጋው እራሳችንን አሳልፈን እንስጥ::  በአንደበታችን ያበላሸነውን ያሳዘናቸውን ሰዎች መባረክ እንጀምር የምትባርክ ነፍስ ትባረካለችና::  ጌታ ማስተዋልን ይስጠን::

የያዕቆብ መልእክት 3: 13-18

13፤ ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። 14፤ ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። 17፤ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።

ሁለት አይነት ጥበብ አለ:- 

1.  ላይኛይቱ ጥበብና 

2  የምድር/የስጋ/የአጋንንት ጥበብ

ላይኛይቱ ጥበብ:-  የዋህነት የሞላበት ነው ጌታ እንዳለን እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ ነው ያለን ከማን እንማር ታድያ::  እንዲሁም ይህች ጥበብ 

– ንጽሕት ናት፥ 

–  በኋላም ታራቂ፥ 

–  ገር፥

–  እሺ ባይ 

–  ምሕረት የሞላባት፥ 

–  በጎ ፍሬ የሞላባት፥ 

–  ጥርጥር የሌለባት

–  ግብዝነት የሌለባት ናት

ይህንን እንከተታተል!  የላይኛይቱን ጥበብ እንሞላ ሳይሰስት በልግስና ጸጋን እና ጥበብን ይሰጣልና ወደ ጸጋ ዙፋኑ እንቅረብና እንጠይቅ::  በህይወታችን የጽድቅ ፍሬ እፍርተን ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል። በዚህ ፍሬ ስንመላለስ ዓለም ልታሾፍ ትችላለች ለኛ ለገባን ግን ሰላምን እናገኛለንና ቃሉን እንኑረው::

የምድር/የስጋ/የአጋንንት ጥበብ:-

–  መራራ ቅንዓትና 

–  አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ ውጤቱ 

          –  ሁከትና

          –  ክፉ ስራ ነው።

ስጋዊ ከሆንን ይህንን ነው  የምናሳየው ፍሬ ሰላም ያጣን አንደበታችንን የማንቆጣጠር  ስጋውያን ነው የምንሆነው::

እኛ ግን ሰማያዊ ነን ለራሳችን የሞትን ነን::  ፍቅር አይቀናም ደግሞም ፍቅር ሁሉን ያምናል አድመኛ አይሆንም ለዚህ ነው ደቀመዛሙርቴ መሆናችሁ በዚህ ይታወቅ ያለን ጌታ::  የመንፈስን ፍሬ እያፈራን በሰላምና በፍቅር እንመላለስ::  የዋህና ትሁት እንሁን እንደጌታ!!

የያዕቆብ መልእክት 4: 1-3

1፤ በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? 2፤ ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ 3፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።

አንድ ጥያቄ ወደ ውስጤ መጣ ይኸውም ምኞቴ ምንድነው የሚል::  ጌታን መርምረኝ ብዬ በፊቱ ሆንኩኝ::  ያላስተዋልኩት ነገር ውስጤ ይኖርን?  እኔነት ካልሞተ የማስበውም  የምጸልየውም ሁሉ እኔ እኔ በማለት የተሞላ ብቻ ነው::  ጌታ ከእኔነት አውጥቶ ለክብሩ የምንኖር ያድርገን!

እነዚህ ሰዎች ከላይኛይቱ ጥበብ ይልቅ በጠብና ቁጣ የተሞሉ ናቸው::  በእግዚአብሔር ፊት ነገራቸውን በጸሎት ከመፍታት ይልቅ በስጋ ነገሮችን ለማድረግ የሚጣሉ የሚገድሉና መብታቸውን ለማስከበር የሚሟሟቱ ናቸው::  ለዚህ ሁሉ መሰረት የሆነው ምኞታቸው ነው::  ጸሎትን እንኳን ቢጸልዩ የሚጸልዩት በክፉ ልብ ነውና አይሰሙም መልስም የለም ከሰማይ::  

ጸሎታችን ምን አይነት ነው?  የሚያስቸግሩን ሰዎች ይኖራሉ በዙሪያችን ስንጸልይ በቁጣ ንቀላቸው አይከናወንላቸው እኔን እንዳስጨነቁኝ አስጨንቃቸው ነው? አይሰማም በእግዚአብሔር ፊት:;  አስቀድሞ የሚያሳድዷችሁን መርቁ ጸልዩላቸው  ተብለናል::  እንባርካቸው እነዚህን ሰዎች ይከናወኑ የልባቸው አሳብ ይሳካ!  ከዚህ ሁሉ በላይ መዳን ይሁንላቸው!  

ጸሎታችንን እንቃኝ በላይኛይቱ ጥበብ እንሞላ ገር እንሁን ይቅር ባይ እንሁን በጎ ፍሬ የሞላብን እንሁን ያን ጊዜ የጽድቅ ፍሬ የሆነው ሰላም በእኛ ውስጥ ያብባል::  ጌታ እጹብ ድንቅ ቅዱስም አምላክ ነውና በፊቱ ስንቀርብ ክፉ ነገር ይዘን እንቅረብ:

ጌታ ሆይ እርዳን ማስተዋልን ፀጋን ጥበብንም ስጠን!

የያዕቆብ መልእክት 4: 4-5

4፤ አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። 5፤ ወይስ መጽሐፍ፦ በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል፡ ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን?

አመንዝሮች የሚያስብለው ምንድነው? እግዚአብሔርንም ዓለምንም መውደድ ነው ይህንን ስም የሚያሰጠው::  ለሁለቱም መሆን አንችልም ወይ ዓለምን ወይንም ደግሞ ጌታን::

1ኛ ዮሐንስ:- ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።

ዓለምን መውደድ የሚመጣው ከመመኘት ይጀምርና ነው ለዚህ ነው ከላይ በቃሉ እንዳየነው የስጋ ምኞት የዓይን አምሮት እንደሆነ የሚነግረን::  ዓለምን መውደድ ከእግዚአብሔር ጋር ጠብ ነው ደግሞም የአባት ፍቅር በእርሱ  የለም ከዛም አልፎ የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ነው::  ከባድ ነገር ነው ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ  ይጠንቀቅ::  እራሳችንን በጌታ እናስመርምር የተቀበልነው ቅዱሱ መንፈስ ይቀናልና::  አናስቀናው!!! 

በዓለም ያለው ሁሉ ያልፋል እኛና ጌታ ብቻ ነን የምንቀረው ደግሞስ ጌታ ምን አጉድሎብ ን ነው ወደ ዓለም የምንቀላውጠው ይህ ማለት እኮ እረኛችን ያጎደለብን ነገር አለ ማለት ነው::  እርሱ ግን በመልካም መንገድ ሁሉ የሚመራ ቅጥረኛ ያልሆነ ነፍሱን ስለወዳጆቹ አሳልፎ የሰጠ ታማኝ እረኛ ነው:: ሲጸልይልንም በዓለም ሳሉ  ጠብቃቸው ካለ በኃላ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። እርሱ ተማምኖ ከዓለም አይደሉም ብሎን እኛ እዛ ውስጥ እንዳንገኝ::  ይህንን ሁሉ በጸጋው እንድንረታው ይፈልጋልና ወደ ጸጋ ዙፋኑ እንቅረብ:: ቲቶ 2: 12-13፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤

ጸጋ እንለምን!

የያዕቆብ መልእክት 4: 6-10

6፤ ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል፡ ይላል። 7፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤  8፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።

ቃሉ እንደሚናገረን እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥  ለምን ያልን እንደሆነ ሰው ማለት ዛሬ ታይቶ ነገ የሚጠፋ ፍጥረት ሆኖ ሳለ መታበዩ ነው  በእግዚአብሔር ፊት የማይወደደው አሳብ::  

ነገር ግን ለትሑታን ጸጋን ይሰጣል ይላል።  በእምነት ወደ ጸጋ ዙፋኑ እንቅረብና ጸጋን እንጠይቅ  ለምን ያለ ጸጋ እንመላለሳለን ውሰዱ በነፃ እየተባልን የምን መታገል ነው?!   

ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ እርሱም ወደ እኛ ይቀርባል ጌታ ሲቀርብ ደግሞ መሸሽ ያለበት ይሸሻል እርሱም ዲያቢሎስ ነው::  የተሰጠው ትእዛዝ ሽሽ ነው ምንም መታገልም አያስፈልግም የእኛን ማንነት እንዲሁም ከእኛ በላይ ቃሉንም ጥንቅቅ አድርጎ ያውቃልና ጠላት::  ብቻ እንገዛ እራሳችንንም በጌታ ፊት ዝቅ እናድርግ እንጂ ጠላት እድል ፋንታ የለውም የተሸነፈ ነው::  እርሱን በየት ገባ ወጣ ከማለት ይልቅ ወደ ጸጋ ዙፋኑ ቀርበን ከጌታችን ጋር ህብረትን እናድርግና ከመወላወል ወተን ልባችን በጌታ ላይ ይረፍ::  በራሳችንም በጌታም መመካት አይቻልም ይህ መወላወል ነውበእርሱ ላይ ብቻ እንደገፍ:: 

አሜን!

የያዕቆብ መልእክት 4:11-12

11፤ ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። 12፤ ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?

ወንድሞች ሆይ አትተማሙ ይላል ያዕቆብ:- ማማት ምን ማለት ነው መቼም ሀሜት የሚኖረው ስለዚያ ሰው መልካም  የምንናገረው ስለሌለ ነው አይደል የምናማው? ባይሆንማ ወንድማችንን እራሱን ሄደን ወንድሜ ሆይ ይህ ያደረከው መልካም ነው ብለን እንባርከው ነበረ::  አንድ ነገር ማወቅ  ያለብን ሰው ቢደክም ለጌታው ነው ቢበረታም ለጌታው ነው እኛን ፈራጅ ያደረገን ማን አደረገን?!  ሰውየው በሌለበት ስሙን በክፉ አላነሳም የሚል አቋም ይኑረን::

ብዙ ልናይ እንችላለን በቤተክርስቲያን ውስጥ ከቻልን መጸለይ አለበለዚያ ግን በማያገባን እየፈረድንና እያማን በጌታ ዘንድ ደስ የማያሰኘውን  እያደረግን እንዳንገኝ:: ጌታም እራሱ በማቴዎስ 7: 1-2፤ እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል ብሎናልና አንደበታችንን እንጠብቅ እንደመጣልን ከመግናገርና ከመበየን እንጠበቅ::  ትህትናንና ሰፊ ልብን እንያዝ ሌሎችም ሲያሙ አንፍቀድ:: ይህ የምናማው ሰው ጌታ የሞተለት ነውና እንውደደው እርሱን ነው የተጠየቅነው::

የያዕቆብ መልእክት 4: 11-17

14፤ ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። 15፤ በዚህ ፈንታ፦ ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን፡ ማለት ይገባችኋል። 17፤ እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።

አቤት በራሳችን የምንመካ እንፋሎቶች?!!  እግዚአብሔር ይርዳን እንድናስተውል:::  እራሴን ሳየው ስንቱን እቅዴን ይሆን ጌታ ቢፈቅድና ብኖር ብዬ ያቀድኩት?!  ግን ይህንን እውነት አውቀን አለማድረጉ ሐጥያት ነው እያለን ነው ቃሉ::  በእቅዳችን ሁሉ ጌታን እንሹመው እርሱ ሲፈቅድ ነው የሚሆነው::  ደግሞስ ከእቅዳችን በፊት ጌታ ቢመጣስ?  ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅምና በልማድ ሳይሆን በእውነት ቢፈቅድና ብንኖር ማለትን እንልመድ:: ማቀድ ሐጥያት ነው እያልኩኝ አይደለም አቅደን እንሰራለን ቃሉም የሚለን አንድ ቀን እንደቅረው መዘጋጀት አንድ ሺ ዓመት እንዳለው ደግሞ ማቀድ ነው ያለብን::

በጎ  የሆነውን እያወቅን አለማድረግ ሀጥያት መሆኑን ካወቅን ብዙ መጎብኘት ያለበት አመለካከት አለብዬ አስባለሁ::  እኛ የእግዚአብሔር እርሻ እንደሆንን ቃሉ ይነግረናል ምን ይሆን የተዘራው በልባችን?  ምን እንድናስብ እንኳን የተነገረን ነን ምክንያቱም በአእምሯችን የተለወጥን እንጂ ይህንን ዓለም እንዳንመስል ነው ጌታ የሚፈልገው::  የዚህ ዓለም ቀመር በመስጠትና በመቀበል ዙሪያ ሲያጠነጥን የጌታ ግን በመስጠት ዙሪያ ነው ::  ብዙ የተቀበልን ነንና አሁን የምንሰጥበት ጊዜ ነው::  እግዚአብሔር ማስተዋልን ይስጠን!

የያዕቆብ መልእክት 5: 1-6

2፤ ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። 3፤ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል።

በማቴዎስ 6: 19፤ ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ብሎናል ጌታ ምክንያቱም   ገንዘብ ጌታ ሊሆንብን ስለሚፈልግ አብሮት ብዙ ክፋት ይመጣል::  በምድር ሀብት አይኑራችሁ አልተባልንም ነገር ግን ጌታ እንዳይሆንብን ያስፈልጋል ሀብት መገልገያ ነው መልካምን ስራ እንስራበት::  እነዚህ ሰዎች ለአገልጋዮቻቸው ደሞዝን ያልከፈሉ በሰው ችግር የሚስቁ ልባቸውን ያደለቡ ናቸው::  ሰው ግንዛሬ ታይቶ ነገ እንደሚጠፋ ረስተዋል::  

እነሱን እንተውና እኛ እንዴት ነን ለትምህርታችን ተጽፏልና::  በምድር ላይ ተጣብቀን የጌታ ነገር እንዳይቀልብን  እናስተውል::  ሀብት ቢኖረን ጥሩ የሌላቸውን እናስብ እንርዳቸው ከዚህ ምድር ምንም ይዘን አንሄድምና በሰማይ ግን መዝገባችንን እናከማች ብል የማይበላው ሌባም የማይሰርቀው በዛ ነውና::  የሚያገለግሉንን በሚገባ መክፈልን እንማራለን ከዚህ ቃል ለምን የሬስቶራንት አስተናጋጅ አይሆንም? አገልግሎት የሰጡንን እንባርክ::  በተለይ የቤት ሰራተኛ ካለን መልካም እንሁን ገንዘባቸውንም በጊዜ እንክፈል::  ድሮ አስታውሳለሁ እንዳይሄዱ እየተባለ የተወሰነ ደመወዝ ነበር የሚሰጣቸው ቤተሰቦቻችንም ግፍ አድርገው ከሆነ  ካስታወስን ንስሃ እንግባ:: በእጃችን ግፍ እንዳይገኝ! ጌታ ቸር ነውና ይቅር ይላል:: 

ለጌታ እንገዛ!

የያዕቆብ መልእክት 5: 7-11

7፤ እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። 8፤ እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።

እነዚህ ቅዱሳን በመከራ ውስጥ ያሉናቸው ከስፍራቸው ተፈናቅለው በጥገኝነት ለሀብታሞች እየሰሩና እየተበደሉ ያሉ ናቸው:: በቃሉ የሚመክራቸው እንዲታገሱ ነው እነእዮብን እንዲሁም መከራ የተቀበሉትን ነብያትን እያነሳ ለታገሱ 

ሁሉ ፍሬ እንዳለ ነው የሚነግራቸው::  

መቼም ገጹን እየገለጥን ስናነብ ያሉበት መከራ ብዙም አይገባንም ግን ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሟል እያላቸው ነው መግባት ብቻ ነው የቀረው ታገሱ ይላል::  እንደዚሁም ደግሞ የጌታ መምጣት ደርሷል ይላል እነሱ በነበሩበት ጊዜ ደርሷል መምጫው ከተባለ አሁን እኛ ባለንበት ጊዜማ እንዴት የበለጠ የቀረበ ጊዜ ላይ ነው ያለነው?! ጌታ ይመጣል መብራታችን የበራ ዘይታችንም ሙሉ ይሁን::  ዘይቱ መቼም መንፈስ ቅዱስ ነው ዕለት ዕለት እንሞላና እንታደስ መብራቱ እንዳይበራ የሚያግድ በእኛ ውስጥ  አይገኝ:: በራሳችን የምንኖረው አይደለም ክርስትና በእርሱ ላይ ባለን እምነት እንጂ:: 

በምናልፍበት ነገር ሁሉ እንታገስ ጌታ ከመከራ መውጫ በር አለውና:: ይደርስልናል ሁሉ ጊዜያዊ ነው:: በክርስቶስ  ያገኘነው  ህይወት ግን ለዘላለም ነው::

እንበርታ ጌታ ሊመጣ ነው!!! ማራናታ!

የያዕቆብ መልእክት 5: 12-13

12፤ ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን። 13፤ ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር።

እከንግዲህ በመሐላ  የምናሳምን ካለን እንተወው::  ምክንያቱም አንዱም ነገር የእኛ አይደለምና ልንምልበት አንችልም::  እግዚአብሔር ለአብርሃም በራሱ ማለለት ይላል በመሐላው አብርሐም አልተካፈለም::  ጌታ በራሱ ማለ እራሱ ሰራ:: ስለዚህመሐላን እናስወግድ::

መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ይላል ቃሉ::  ጌታም ሐዋርያትን ያላቸው በመጨረሻው ሰዓቱ ላይወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዮ ነበር::  መከራ ውስጥ ከገባንም እንዲሁም እንዳንገባም እንጸልይ::  በአባታችን ሆይ ጸሎትም ውስጥ ወደ ፈተና አታግባን ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል::  አትጠይቁምና ለእናንተ  አይሰጥም እንደሚለው እንዳይሆን የመከራውን መውጫ ጌታ እንዲያሳየን በፊቱ እንውደቅ::  ጠላታችን ዲያብሎስ ዙሪያችንን እንደሚዞር አንርሳው::

ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር እንደሚል በፊቱ ደስታችንን በዝማሬ እንግለጽ::  በውስጣችን መንፈሳዊ ቅኔ ይፍለቅለቅ::

የያዕቆብ መልእክት 5: 14-15

14፤ ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። 15፤ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።

ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር:- ማንም የሚለው ላይ ማስመር እፈልጋለሁ::  ማንም እንዲታመም ፈቃዱ አይደለም እግዚአብሔር ስለዚህ በሽታ በአንድ እጁ በሌላ ደግሞ ፈውስ የያዘ አምላክ አይደለም::  ማንም እንዲታመም የማይፈልግ  ስለህመማችን የተገረፈ ጌታ ነው በጠባሳውም ሪሲቱን ይዟል ዋጋ አንድ ጊዜ ነው የሚከፈለው::  አንታመምም አይደለም ግን ብንታመም ፈውስ አለ እያልኩኝ ነው::  ጤንነታችንንና ሰላማችንን የሚፈልግ ጌታ ይባረክ::  

እዚህ  ክፍል ላይ እንደምናየው የቤተክርስቲያን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በጌታ ስም ነው ፈውስ ያለው እንጂ በዘይቱላይ አይደለም ዓይናችን በሞተውና በተነሳው ዋጋ በከፈለው ላይ መሆን አለበት እንጂ በሽማግሌዎቹም ላይ መሆን የለበትም:: የሚፈውስ ጌታ ነው::  ሐዋርያትም ያሉት በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሳና ተመላለስ ነው::  እኛም አትኩሮታችን በዚህ ስም ላይ ይሁን!

የሚያድነውም የእምነት ጸሎት ነው::  ለሚወላውል ከጌታ ዘንድ አንዳች አይቀበልም በእምነት ስንጸልይ ጌታ የታመመውን ያስነሳል::  አስምሩልኝ ጌታነው የሚያስነሳው::  ከሰው ላይ ዓይናችንን እናንሳ! በኃጥያትም የመጣ ከሆነ ይቅር ይባላል እንዴት ያለ መብት ነው የሰጠን ይገርማል::  ግን ይህ ማለት በኃጥያት እየተመላለስን እንኑር ለማለት አይደለም እንዲያውም አብዝተን ወደእርሱ እየተጠጋን ዓለምን መናቅ ይብዛልን::  በዛም ይሁን በዚህ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው  እንጂ ለማጥፋት ወይም ለማሰቃየት አይደለም::  እርሱ እጅግ የሚምር የሚራራ ጌታ ነውና::

የያዕቆብ መልእክት 5: 16-20

16፤ እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። 17፤ ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥  18፤ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች።

ሲጀምር ጸሎቴ ለውጥ ያመጣል ብዬ ማመን አለብኝ እንደሚሰማኝ ማወቅ አለብኝ::  ከሰው ሰው የማይለይ ጌታ እያንዳንዳችንን ይሰማናል!  እንመን!  ኤልያስ እንደኛው ሰው ነበረ በአገር ላይ ነው ሰማዮን የዘጋው ሲከፈትም በአጭር  ጸሎት ነው ::  እንግዲህ እርስ በእርሳችን እውነተኞች መሆን አለብን ኃጥያትን መናዘዝና መተው አለብን::  የጻድቅ ሰው ጸሎት በስራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች ይላል::  የጸሎትን ጥቅም እንወቅ ጸሎት ማለት አውርቶ መነሳት ሳይሆን ከጌታ ጋር ህብረት ማድረግ ከእርሱም ዘንድ መስማት ማለት ነው ይህንንእንለማመድ ያን ጊዜ ጸሎት ተራራ አይሆንብንም::

እርስ በእርሳችን ልንሸካከም ይገባል አንዱ የሌላውን ሸክም ይሸከም ይላልና ቃሉ::  በዙሪያችን ያሉትን እንመልከት ወንድማችን እንዴት ነው እህታችንስ?  ጌታ ማንን ይጠቀም እኛ በአቅራቢያው እያለን ከሌላ ያምጣሰው? እኛው እንታዘዝ ስንቱ በዙሪያችን መጽናናት ያስፈልገዋል? ዓይናችንን ይክፈት::

ከእውነት የሳተም ካለ ለመመለስ እንጂ ለመፍረድና ለማማት እንቸኩል::  ቢመለስ ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ ይላል ቃሉ።ጌታን ማገልገል ቀላል ነው እራስን በፊቱ ማቅረብ ብቻ ነው የሚጠይቀው::

በዚህ የያዕቆብን መልክት አጠናቀናል  ቃሉ ውስጣችንን ይቀይር ማስተዋልንም ጌታ ይስጠን::

Published by Betty & Abera

We’re dedicated to share God’s goodness and mercy through His word!

3 thoughts on “የያዕቆብ መልእክት

Leave a comment