በክርስቶስ ማን ነኝ?

በክርስቶስ በሰሚያዊው በረከት ሁሉ የባረከኝ በአብም ቀኝ በክርስቶስ ውስጥ የሰወርከኝ ጌታዬ ተባረክ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም መጻተኛና እንግዳ ነኝ ቤቴ በሰማይ ነው:: አሜን!

ማንነታችንን እንወቅ፤ እኛ ጌታ እንደሚለን ነን::  እራሳችን ነን ካልነው ሰዎችም ከነገሩን ይልቅ ቃሉ የሚለን ነንና ቃሉ በልባችን ይተከል::

በክርስቶስ ማነኝ? በቀን አንድ የእግዚአብሔር ቃልን ይዘን ስለማንነታችን እናስብ::

ይህንን እውነት እናጥና በልባችንም በቀንም በለሊትም እናሰላስለው::

1.   ልጅ ነኝ!!  

ዮሐንስ 1:12፤ ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤

ሮሜ 8:14፤ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና:: 15፤ አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና።

ገላትያ 3:26፤ በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤

ልጅነት በመቀበል የሚገኝ እንጂ ለሰው ሁሉ የሚታደል አይደለም:: ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ማወቅ ከዛም ‘ጌታዬ ነህ’ ብለን በጌትነቱ ስንቀበለው ልጅነትን እናገኛለን::ማወቅ

ልጅነት የተሰጠን በእንስሳት ደም ሳይሆን ኃጥያት የማያውቀው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ዋጋ ከፍሎ ነው!! 

ጸሎት

አባት ሆይ እንዳውቅህ ስለረዳኸኝ አመሰግንሃለሁ:: ከአንተ ተወልጃለሁኝ ይህንን ልጅነት ማንም አይነጥቀኝም:: ተመስገን!

2. ወዳጅ ነኝ!!  

ዮሐንስ 15:15፤ ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።

ወዳጅ አድርጎናል!  ስለዚህም ‘እኔ የእየሱስ ወዳጅ ነኝ’ ብለን አፋችንን ሞልተን ልንናገር እንችላለን::  እራሳችንን አናርቀው::  የሆነ ነገር ስንሆን ደስታም ይሁን ክፉ ቶሎ ብለን ወደ ወዳጃችን እንደሮጣለን:: ታድያ ከእርሱ የሚበልጥ ወዳጅ ማነው?  ይህንን ማንም አይቀይረውም አንድ ጊዜ ተቀብሎናል::

ጸሎት

ሃሌሉያ  ጌታ ኢየሱስ ሆይ ወዳጄ ነህ!

3.  ጨው ነኝ!!  

ማቴዎስ 5:13፤ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።

ይህች ምድር ጠዕሟን አታለች:: የተሰጠን ስራ ጨው መሆንና ለዚች ዓለም ጣዕም መስጠት ነው::  

አለበለዚያ ሰይጣን ሲኦል ነው ሊያደርገው የሚፈልገው ግቡ እግዚአብሔርን መፍራትን ፈጽሞ ሊያጠፋ ነው::  እኛ ግን እያለን ይህ አይሁን!   

ስለዚህ ሳይበላሽ ምግብን ማቆየት የሚችለው የጨው ስራ ይገለጥና እርሱን መፍራት ይመጣል:: ልክ ያልሆነው በእኛ ህይወት ሊወቀስና ሊቆጠቁጥ ይገባል ልክ ጨው ቁስል ላይ እንደማድረግ::  

ግን ማንነታችንን ችላ ብለን ዓለምን ብንመስል አብረን እንበሰብሳለን የሚቀጥለውም መረገጥ ነው ለምንም አንጠቅምምና::

ዮሐንስ 15:6፤ በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል። 

ስራችንን እንስራ እኛ ጨው ነን!  ለዝች ዓለም አስፈልጋለሁኝ ብለን እርግጠኛ እንሁን!!

ጸሎት

አሜን ጌታ ሆይ በእኔ እየተገለጥህ ታይ ጨውነቴን ልቀጥል  ፍሬንም ላፍራ!

4.  ብርሃን ነኝ!!  

ማቴዎስ 5:14፤ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።

ይህች ዓለም ጨለማ ናት ወንጌል ደግሞ ብርሃን ነው::  በጨለማችንን ላይ ብርሃን ይብራ ያለው እርሱ ነው እንደሚል እኛም ጨለማ ነበርን የወንጌል ብርሃን እስኪበራልን::

ለዝች ዓለም በክርስቶስ በማመኔ ብርሃን ተደርጌአለሁ::  ብርሃንን ጨለማ አያሸንፈውም::  ብርሃን ካለ ጨለማ የለም የአንዱ መገኘት ሌላውን እንዳይገኝ ያደርገዋል:: ስለዚህ እኛ ባለንበት ጨለማ ይባራል ወይም በዙሪያችን ያሉት በጨለማ የሚመላለሱ ከብርሃኑ የተነሳ ዙሪያቸውን እንዲያዩ የሚያደርግ ማንነት አለን::  

ለዝች ዓለም አስፈልጋለሁ ምክንያቱም እየሱስ በእኔ ውስጥ ተብለጭልጮ እየታየ ከጨለማ ሌሎችን ይስባል እንጂ እኔ ወደ ጨለማ የምሳብ አይደለሁም::  

ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ ተብለናልና የእኛ ማንነት ነው ብርሃን መሆን በጨለማ የሚደናበሩትን ማሳየት::

ጌታ ይርዳን!

5.  አዲስ ፍጥረት ነኝ

2 ቆሮንቶስ 5:17፤ ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።

አዲስ ፍጥረት ስንሆን አሮጌው ማንነት ሞቶ ቅዱስ እና ህያው ፈጣሪን የሚያኖር ማንነት ተፈጠረ:: ቤተመቅደሱ አደረገኝ!! ይህም አዲስ ማንነት እኛ ጌታን ደስ አስኝተን የምንኖርበት ሳይሆን እርሱ  መቶ የሚኖርበት ነው::  የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ አደረገን ይህ በብሉይ አልነበረም በእነርሱም የእግዚአብሔር መንፈስ ይሰራ ነበር ልዮነቱ በአዲስ ኪዳን ሰርቶ የሚመለስ ሳይሆን በእኛ የሚኖር ነው!! ሃሌሉያ!!  የብሉይ አገልጋዮች በአህዛብ  ላይ መንፈሱ መፍሰሱን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን?!

በጣም የጠለቀ እውነት ነው!  ማንም ከእኛ የማይወስድብን ማንነት የእርሱ ማደርያ መሆን ማንስ ያስወጣዋል እርሱ የእኛ እኛም የእርሱ አንድ ጊዜ ከእርሱ ተወለድን ከስጋና ከደም ፈቃድ አይደለም:: ተቀባይነትን አግኝተናል!! ስሙ ይባረክ!

ጸሎት

አሜን እኔ አዲስ ፍጥረት ነኝ ጠላት አሮጌ ነገር እያመጣ አይከሰኝም::  ከወይኑ ግንድ ጋር ተጣብቄያለሁ!!!ክበር ጌታዬ ይህ የከበረ እውነት በውስጤ ይታተም!!  በእኔ ውስጥ ኑሮህን ኑረው  አባ! አሜን

6.  ቅዱስ ነኝ

ሮሜ 1:7፤ በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ፥ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

1 ቆሮንቶስ 1:2፤ በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤

ጳውሎስ ለሁለቱም ቤተክርስትያናት ሲጽፍ ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ ይላል::  እኛ በእግዚአብሔር የተወደድንና ኑሯችንም በቅድስና መመላለስ የሞላበት ነው::  የጠራን ቅዱስ ነውና ቅዱሳን ሁኑ ተብለናል:: 

በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት እንዴት ደስ ይላል የተቀደስነው በእርሱ ስራ ነው::  ስለዚህ ቅዱስ ነኝ ብለን ለማለት የምንደፍረው በእርሱ ነው::  ቅዱስ ነኝ ስል አልፈራም እርሱ ቀድሶ በውስጤ እየኖረ ነውና::

ጸሎት

ቅዱስ ላደረገኝ ስሙ ይባረክ!!!

7.  ለሐጥያት የሞትኩኝ ነኝ!!

ሮሜ 6:2:  ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን?

ሮሜ 6:11፤ እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቈጠሩ።

1 ጴጥሮስ 2:24፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። 

ብዙ ነገር አሳባችንን ለመቆጣጠር ይፈልጋል እኛ ግን ለዓለም ነገር ሞተናል ለክርስቶስ ግን ለእግዚአብሔር ሕያዋን ነን የመንግስቱን ስራ ለመስራት ለዝችም ዓለም ብርሃንና ጨው ለመሆን::  ለብዙ ነገሮች መልሳችን እኔ ለኃጥያት ሞቻለሁ ነው::  ስድብ ቢሆን ባርከን ማለፍን እንማር ለሚደረግብን ክፋት ሁሉ መልካምን መመለስ እናስቀድም:: 

የጌታን ፊት እያየን እናገልግል እርሱን ደስ ይበለው::

እስኪ እንለማመድ አኔ ሞቻለሁ ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እያልን:: እውነታው እርሱ ነው::

ጌታ ጸጋ ያብዛልን!

8.  አሸናፊ ነኝ

ሮሜ 8:37፤ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።

በዚህ ሁሉ ብሎ የጀመረበትን  ምክንያት ከላይ ስናየው ከፍታና ዝቅታ ማንም ከእርሱ አይለየኝም:: ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?  ከዚህ ውጪ  ምን  ይመጣል? ጠላትና ስጋ  በዚህ ነው የሚፈትኑን መሸነፍ አይታሰብም::  እንዲያውም ታሸንፋላችሁ ብቻ ሳይሆን የተባልነው ጭራሽ ከአሸናፊዎች ሁሉ ትበልጣላችሁ ነው

ህይወቱን በሰጠኝ ጌታ ተወድጃለሁ ይህ ጌታ ደግሞ  ማሸነፍን በእርሱ በኩል ተሰጠኝ::  መሸነፍ የለም ማሸነፍ ግን ተሰቶኛል by default. 

በክርስቶስ የማይሸነፍ ምን አለ?! ሁሉ ተሸናፊ ነው::  የከበረው የጥበብ ሁሉ መዝገብ እየሱስ በዚህ ሸክላ ውስጥ እየኖረ ነው::  ሸክላ ተሰባሪ ነው ጌታ ግን እየጠበቀኝ ከውስጤ ሆኖ ድል እየነሳ በድል ጎዳና ያራምደኛል::

ጸሎት

ሰባሪው እግዚአብሔር ከፊቴ ሲወጣ ሊገዳደር የሚቆም ማን ነው? ማንም! ጌታ ሆይ ድልን ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁኝ!  አቤት የኔ ጌታ እንዴት ይደንቃል ስራህ እራስህ ጠርተህ በደምህ አጽድቀህ የምቆምበትን ጸጋ ሰተህ ደግሞም በእኔ ውስጥ እየኖርክ ጉልበትና ብቃት ሆነኸኝ ከአሸናፊዎች እንድበልጥ አደረከኝ::  ተ መ ስ ገ ን!!!!አሁንም በቃልህ ላይ እንድቆም እርዳኝ::

9.  በጌታ ተመርጫለሁ ፍሬንም ለማፍራት ተሾምኩ ነኝ!!  

ዮሐንስ 15:16፤ እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።

እራሱ ጌታ መረጠን እርሱ በጸጋ አዳነን እርሱ በጸጋ ያኖረናል::  የእኛ ነገር የቱ ጋር ነው ያለው ታድያ?!  እርሱ ሁሉን አደረገልን በእኛ የሚኖር ዛሬም እርሱ ነው::  

ፍሬ ለማፍራት የሚያስፈልገንን ሁሉ እንድንጠይቅ አብም በእየሱስ ስም የምንጠይቀውን እንደሚሰጠን ተነግሮናል:: ፍሬ  ልናፈራ ተሹመናል ይህም ፍሬ ለአንድ ጊዜ አፍርተን አስቆጠርን ለማለት ሳይሆን ፍሬያችንም ከእኛ ጋር እንዲኖር ይፈልጋል::  ክርስትና በወቅት መሆን የለበትም አመቱን ሙሉ ማፍራት አለብን::  ፍሬ ፍለጋ ጌታ ይመጣልና ፍሬያችን ሁልጊዜ ይገኝ::  ፍሬ  ብለን ስንል የመንፈስ ፍሬ ነው እርሱም በገላትያ 5:22፤ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፣ 23፤ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።

ይህንን በህይወታችን ማየት ይፈልጋል ፍሬውም የሚፈራው በመንፈስ ነው:: እራሱ መንፈስ ቅዱስ ያፈራዋል መቅደሱ ስለሆንን በእኛ እየኖረ ነው::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን::

10. በእርሱ ሙሉ ነኝ!

ቆላስይስ 2: 9 -10፤ በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።  ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።

አምላክና ፈጣሪ በሆነው በክርስቶስ እየሱስ ከመሞላት በላይ ምን ያስፈልጋል?!  ለአለቅነትና ለስልጣንም ሁሉ ራስ በሆነው በእርሱ ከመሞላት በላይ ምን ይስጠን? በእርሱ ላይ የሚጨመር ነገር የለም – ሙሉ ነን!!  

ጠላት ሁልጊዜ ጎዶሎ አለ ነው የሚለን ሊያታልለን በዚህ ላይ የሆነ ነገር መጨመር አለበት እያለ::  ጸሎት ቢሆን ማገልገል ቢሆን ምንም ነገር ቢሆን እኛን ለመሙላት አይደለም ስለምንወደው የምናደርገው ነው  ጠላት የሆነ ነገር አድርገን ክፍተትን ለመሙላት እንድነሳ ነው የሚያሳስበን ነገር ግን ሁሉ በክርስቶስ ተሟልቷል እኛም በእርሱ ተሞልተናልና :: ጌታን እናመስግን ለጠላት ሽንገላ መልሳችን ሙሉ ነኝ የምጨምረው የለም ነው::

ጌታ ይባረክ በራሱ ማንነት የሞላን!

ጸሎት

አባት ሆይ ተመስገን ማንነቴ ሙሉ ነው:: በአንተ ተሞልቻለሁ ይህንን ማንም አይሽረውም! አይለውጠውምም!

11. የጸደኩኝ ነኝ!

ሮሜ 5:1፤ እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤

መጽደቃችን እርግጥ ነው::  ቃሉ እንደሚለን የጸደቅነውም በእምነት ነው እንጂ በስራ አይደለም::  ደርሶ በራሳችን የጸደቅን ይመስል ጠላት ይመጣና ውጊያውን በስራችን ላይ አድርጎ ይዋጋናል::  በስራ ወደ ጌታ እንዳልመጣን ሁሉ በስራችን ታምነን አንመላለስም ዛሬም ጽድቃችን ጌታ ነው::  አብርሃም በእምነት እንደጸደቀ እንዲሁ እኛም በእምነት ጸድቀናል::  

መጽደቃችን በእምነት እንደሆነ ከተገነዘብን በክርስቶስ ሰላምን እንያዝ::  ሰላም ይሁንልን! እንረጋጋ::  አእምሮን የሚያልፍ ሰላም የሚሰጥ የሰላም አለቃ ከእኛ ጋር ነውና:: ማንነታችንን አውቀን የሚመጣብንን ፍላጻ ሁሉ በቃሉ ውስጥ እንየው ያኔ ነገሩ ሁሉ ቀላል ይሆናል::  ጌታ እየሱስ የጠላትን ፈተና ያሸነፈው እንደዚህ ተብሎ  ተጽፏል ብሎ ነውና ከእርሱ እንማር::

ጸሎት

ጌታ ሆይ አመሰግንሃለሁ ለመጽደቄ ያደረኩት አስተዋጽኦ ስለሌለ::  አንተው ነህ በመስቀል ላይ ስራዬን  አጠናቀህ ተፈጸመ ብለህ የሰራህልኝ::  ይህንንም እንዳውቅ ልቦናዬን ከፈትክልኝና ያመንኩት::  በዚህም የአንተ ጽድቅ ይኸው ለእኔ ተቆጥሮ ጻድቅ ተባልኩኝ::  አመሰግንሃለሁ!!!!

12. የክርስቶስ አካል ነኝ

1 ቆሮንቶስ 12:27፤ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።

በክርስቶስ ውስጥ ብልት ነኝ:: ይህንንም ያገኘሁት በእርሱ በማመን ነው::  ስራዬን የሰራና የራሱ ያደረገኝ ጌታ የተባረከ ይሁን!  

በአካል ውስጥ ደግሞ የማያስፈልግ  ብልት የለም ሁሉ ብልት ይሰራል::  እኔ አስፈላጊ ነኝ ጠላት አታስፈልጊም ይላል ወይም አንቺ ብትመጪ ብትቀሪ ምንም አታመጪ ብሎ ሊዋጋ ይችላል ነገር ግን አስፈልጋለሁ::  እኔም በአካሉ ውስጥ ስራ አለኝ  እርሱ አውቆኛል በስሜ ጠርቶኛል ጌታዬን እንጂ ጠላትን አልሰማም::  ስራዬን መስራትና በተሰጠኝ መክሊት ማትረፍ አለብኝ:: 

ጸሎት

ጌታ ሆይ በአካልህ ውስጥ ስፍራ ስላለኝ ስለተቀበልከኝ ይህንንም ማንም ስለማይቀይረው  አመሰግንሃለሁ:: እንደሰጠኸኝም ጸጋ አገለግልሃለሁ::

13.  ኩነኔ የሌለብኝ ነኝ! 

ሮሜ 8:1፤ እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። 2፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና።

ከመኮነን ነፃ መሆን ምንኛ ደስ የሚል ነገር ነው? ግን እንደዚሁ አይደለም ነፃ የወጣነው እየሱስ ዋጋ ከፍሎ የሕይወትን መንፈስ ሕግ በእኛ ውስጥ አድርጎ ነው::  ይህ የህይወት መንፈስ ህግ ደግሞ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ጋር እጅ ለእጅ አይሰራም የአንዱ መገኘት የሌላው አለመገኘት ነው::  ኃጢአትና ሞት በእኔ ላይ ስልጣን የላቸውም ተሽረዋል::  ኩነኔ ቢኖርብኝ መብት በነበራቸው  አሁን ግን የእየሱስ ህይወት በእምነት ከእኔ ጋር ስለተዋሃደ  መሰልጠንና እኔን በስራቸው ማድረግ አልቻሉም:: ኃጢአትና ሞት ከእኔ ተሽሯል ክብር ለአዳኜ!!!

በጸጋ ድኛለሁ ከህግ ጋር ተፋትቻለሁ::  በህግ እንደማልድን አውቆ ጌታዬ እንደበግ ስለእኔ ታረደ::  ስለዚህ ጌታ እኔን  አርነት አውጥቶኛል::  ክብርና ምስጋና ይብዛለት!

ጸሎት

አባት ሆይ ኩነኔ ስለሌለብኝ የሕይወት መንፈስ ሕግ  በእኔ ላይ ስላደረክ- ተመስገን::  ህይወት እንዲበዛልኝ እንዲትረፈረፍልኝ ስለመጣህ ተመስገንልኝ!!! አሜን!

14.  የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነኝ

1 ቆሮንቶስ 6:19-20፤ ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።

ይህ የኔ የምለው ስጋ በዋጋ የተገዛ የኔ ያልሆነ በደሙ የዋጀው ጌታ ያለው ነው:: የኔ ብዬ እለዋለሁ እንጂ የተቀበልኩትም ከእግዚአብሔር ነው:: እሱው ሰቶኝ እሱው እንደገና ዋጅቶት እንዴት የኔ እለዋለሁ?  ኩነኔ የሌለኝ አድርጎ ጻድቅና ቅዱስ አድርጎኝ ይኖርብኛል::  እንዴት ይደንቃል!  ይህ ስጋ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነው ቢባል አይደንቅም ይህ በልቤ ሊታተም ይገባል::

እራሳችሁን የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ አቅርቡ እንደሚል ቃሉ እራሳችንን ዕለት ዕለት ለእርሱ እናቅርብለት::

በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። እንደሚል ነፍስን ከሚዋጋ የስጋ ምኞት እራሳችንን እየጠበቅን እራሳችንን ህያዋን ቤተመቅደስ ሆኖ ለመሰራት በፊቱ እናቅርብ::  በዝች ዓለም መጻተኞች ነንና  በሰማይ አገር አለን::  በሰማይ ስለእኛ የሚያስብ አለ:: 

ይህንን ቃል ለአንድ ሰው አካፍይው እንደዛ ሲሆን ይበዛልሻል በውስጥሽም ይታወጃል::

ፀሎት: – 

አባት ሆይ ሰው በሰራው አላድርም ብለህ እራስህ በሰራኸው ማንነቴ ልታድር ስለወደድክ አመሰግንሃለሁ:: እኔነቴን በፊትህ የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጌ አቀርባለሁኝ::  በአእምሮዬም መታደስ ለውጠኝ ቃልህም ከኔ ጋር በእምነት ይዋሃድ:: አሜን

15.  ከጨለማው ስልጣን የዳንኩ ፤  ይቅር  የተባልኩና ወደ መንግስቱ  የገባሁ ነኝ!

ቆላስይስ 1:13-14፤ እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።

እኔም ጨለማ ሆኜ በጨለማው  አገዛዝ ስር ሆኜ እንደወደደ ያሽከረክረኝ ነበር::  ጌታዬ ግን ብርሃን ይብራ ብሎ በህይወቴ ጨለማውን ገፎ ሐጥያቴን ሁሉ ይቅር ብሎ ወደ መንግስቱ አፈለሰኝ!! አነፃኝና ቀደሰኝ!! 

አቤት ቀላል ነገር ይመስላል መዳን ነገር ግን የከበረ ነው::  ወንጌል ለሰው  ነግራችሁ አልገባው ሲል ሲያሾፍ  አቤት እኔ እንዴት አመለጥኩ ያስብላል ምክንያቱም የጨለማው አለቃ አእምሯቸውን አሳውሮት ይህንን የመዳን ወንጌል ቸል ይላሉና ወደው አይደለም እንዘንላቸው::

በክርስቶስ በሰማያዊዉ በረከት ሁሉ የበረከኝ በአብም ቀኝ በክርስቶስ  ውስጥ የሰወርከኝ ጌታዬ ተባረክ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም መጻተኛና እንግዳ ነኝ ቤቴ በሰማይ ነው::  አሜን!

ጸሎት

አባት ሆይ ወደ መንግስትህ ስላፈለስከኝ የጠላትን ቀንበር ስለሰበርክልኝ ሐጥያቴንም ሁሉ ይቅር ስላልከኝ አመሰግንሃለሁ:: 

16.  ከጌታ ጋር አንድ መንፈስ ነኝ

1 ቆሮንቶስ 6:17፤ ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው።

ይህንን ማሰብ ድፍረት ይመስል ይሆናል ነገር ግን ይህ እውነት ነውና ከእኛ ጋር መዋሃድ አለበት::  ቤተመቅደስ አድርጎኝ እኔ እኖራለሁ በውስጥሽ ካለኝ በዚህ በመንፈሱ ከእርሱ ጋር አንድ ሆኛለሁ::

ይህንን ህብረት ማቋረጥ የሚችል ኃይል የለምና ጌታዬ የተመሰገነ ይሁን::  ከእርሱ ጋር አንድ ነኝ በመንፈስ::

17.  ወደ ጸጋ ዙፋኑ ለመቅረብ መብት ያለኝ ነኝ!

ዕብራውያን 4:14፤ እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። 15፤ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። 16፤ እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።

ይህ ግብዣ ሁሌ ይገርመኛል::  በሰማያት ሊቀ ካህናት ስላለን እርሱ ስለሚማልድልን ኑ ወደ ጸጋ ዙፋኑ እርሱ እንዳዳናችሁ እርሱው ይረዳችኃል ያለ እርሱ አንዳች ማድረግ አትችሉምና::  እርሱ እንደሆነ ይራራልናል እንጂ አይፈርድብንም!  ምንኛ መታደል ነው?!  

ድካም እንዳለብን የታወቀ ነው ነገር ግን ወደ ጸጋ ዙፋኑ በእምነት ማለትም  በሙሉ ልብና በእርግጠኝነት እንደምንቀበል አውቀን ቀርበን ድካማችንን መርታትና ብርታትን መቀበል እንችላለን:: 

ጸሎት

አባ እያልኩኝ  አባት ሆይ ስምህ ይባረክ ስለረዳኸኝ ከፍ በል::  

ካህኔ ሆይ!   ይኸው አሁን ወደ ጸጋ ዙፋንህ  በእምነት ቀርቤ ጸጋ ስጠኝ እላለሁ::  በጎደልኩበት ሁሉ ሙላት ይሁንልኝ::  አሜን!

18.  በስጋው ተቀድሻለሁ

ዕብራውያን 10:10፤ በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል።

የተቀደስኩት በኮርማ ወይም በእንስሳ ደም አይደለም:: በፈጠረኝ ክብሩን ትቶ የባርያን መልክ ይዞ በመጣው በልጁ ነው:: እኔን ለመታደግ የማይገባውን ኑሮ ኖሯል ይህ ጌታ ይገርመኛል ፍቅሩና ትህትናው:: ዛሬም ዓይኑን በእኔ ላይ ማጽናቱ:: በራሴ መቆም አሁንም አልችልም የሚያስችለኝ መንፈስ ቅዱስ ነው:: ሮሜ 8:11፤ ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል:: አሜን

ጸሎት

አባት ሆይ አመሰግንሃለሁ ምንም ማድረግ እለመቻሌን አይተህ ሙሉ በሙሉእዳዬን ከፈልክልኝ:: ተ መ ስ ገ ን!

አሜን

19.  ወራሽ ነኝ!

ሮሜ 8:17፤ ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።

ልጅ ከሆንን አብሮ ከልጅነት ጋር መውረስ ይመጣል የማይነጣጠል ጉዳይ ነው::  ምን ያህል ቤተሰብ እንዳደረገን እንመልከትና እናስተውል::  ልጅ አድርጎ ተቀብሎኛል!!! ዛሬ የምንቀበለው ማንኛውም ነገር ጊዜያዊ ነው ሁሉም ነገር ያልፋልና ቃሉን በልባችን እንሸሽግ!!

ጸሎት

አባት ሆይ ልጅ ነኝና ወራሽ ነኝ::  ልጅነትን ስለሰጠኸኝ ተመስገን ንፁ አድርገህ የራስህ አድርገኸኛልና ተባረክ!!  አባት ሆይ እንደአባት እፈራሃለሁ አከብርህማለሁ::  በህይወቴ ክበር!  አሜን!

20.  ከክርስቶስ ጋር የተሰቀልኩ ነኝ!

ገላትያ 2:20፤ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።

ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ የሚለው ሃሳብ በራሱ የቆመ አይደለም ሞቻለሁ በቂ አይደለም ምክንያቱም ህጋዊ ያደርገናል::  ሞተናል የተባለበት ምክንያት:-  እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ በአንድ ህይወት ውስጥ ሁለት ሰው መሆን አይቻልም ወይ እኔ ወይም ደግሞ እርሱ መኖር አለበት::  ከሞትን እርሱ ይኑር!!!

እምነት ከመስማት ነው መስማትም የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚለን ቃሉ ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው የዛሬው ኑሮዬ። 

ጸሎት

አባት ሆይ ቤተመቅደስህ አድርገኸኛልና ሞቻለሁምና በእኔ የምትኖረው እየሱስ ኑሮህን ኑረው::  አሜን!!

21.   ከክርስቶስ ጋር ሕይወት የተሰጠኝ ነኝ!

ኤፌሶን 2:5፤ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥

በህይወት መኖር የተሰጠኝ ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ ነው በእርሱ ተወድጃለሁ::  በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ እግዚአብሔር አሰበን ምንም የሚያስመካንና ለመዳን የሚያበቃን ነገር ሳይኖር  ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን::  ይህንን ህይወት ያገኘነው ጎበዝ ስለሆንም አይደለም የዓለምን ምናምንቴ መርጦ ደህንነትን ገለጠልንና  በጸጋ ዳንን::  ሃሌሉያ!!

የሰው እጅ በሰራው ውስጥ አልኖርም ሲል ሁሉንም አጠናቆ ሰርቶ አንዳችም የምንመካበት የሌለን መሆናችን እያየን ያለ እርሱም አንዳች ማድረግ እንደማንችል አውቀን በእርሱ እንመካ! እንደገፍበት: እንጣልበት በዚህ ድንቅ ጌታ ላይ::  

ጸሎት

አባት ሆይ ክርስቶስን ከሙታን ስታስነሳው እኔንም ከእርሱ ጋር አስነስተህ ህይወትን ስለሰጠኸኝ ተባረክ::  ይህ የተሰጠኝ ህይወት ዘላለማዊ ነው ሞትም አይወስደውም የህይወት ህግ እንጂ የሞት ወይም የሐጥያት ህግ በእኔ አይሰራም!  ህይወት እንዲበዛልንና እንዲትረፈረፍልን አንተ መተሃል::  ጌታዬ ሆይ ተባረክ! አሜን!

22.  ከእግዚአብሔር ጋር የታረኩኝ ነኝ!

2 ቆሮንቶስ 5:18፤ ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤

እግዚአብሔር  እራሱ ታረቀኝ እውነታው ግን የሰው ልጅ ነበር ትዕዛዙን አፍርሶ የተባረረው::  መሆን የነበረበት ሰው እራሱ ነበር እግዚአብሔርን ፈልጎ መምጣትና ይቅርታ መጠየቅ  የነበረበት::  ይህ አለመሆኑ  ሳያንስ እራሱ እዳችንን ከፍሎ ወደቤቱ መለሰን ልያውም በተሻለ ክብር እርሱም ልጅ መሆን::  እንዴት ያለ ፍቅር ነው?! 

ወደቤቱ መመለሱና ከእኛ ጋር መታረቅ ሳያንስ ደግሞ ይህንን የማስታረቅ አገልግሎት ሰጠን::  በእኛ ውስጥ በሚኖረው በመንፈሱ ይህንን ያደርገዋል::  ሰውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እንላለን::

ጸሎት

አባት ሆይ የጠፋሁትን ፈልገህ ስለታረከኝና  በቤትህ ስለተከልከኝ  አመሰግንሃለሁ::  ከኔ የሆነ አንዳንችም የለምና ክበርልኝ::  እኔ ከእግዚአብሔር ጋር የታረኩ ነኝ!  ክበር! ክበር ተመስገን!ሃሌሉያ!

23.  የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ   የተለየ ወገን ነኝ!

1 ጴጥሮስ 2:9፤ እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤

ጨለማችንን አብርቶ ወደ እራሱ የጠራን ጌታ ስሙ ይባረክ!  የጠራንም  የእርሱን በጎነት እንድንናገር ነው የመረጠን::  ተመርጠናል  ወደሚደነቅ ብርሃኑ ተጠርተናል:: የሆነልንን በራሳችን ማድረግ አንችልም!  ሆነልን እራሱ መርጦ ጠርቶ የራሱ አደረገን::

ጸሎት

አባት ሆይ ለዚህ ክብር ያበቃኸኝ አንተ ነህና ክብር ምስጋና ይገባሃል::  ከጨለማ አውጥተህ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህን፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስትህ  የተለየ ወገን ስላደረከኝ ተመስገን:: ዘመኔን ሁሉ እገዛልሃለሁ::

24.  አገር አለኝ በሰማይያለኝ ነኝ!

ፊልጵስዩስ 3:20፤ እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤

አገር  እንዲኖረኝ ያደረገው እራሱ ጌታ ነው::  እኔ የፈለገውን ባደርግ መግባት የማልችልበት ስፍራ በስራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የገባሁበት ነው:: በዚህ ምድር መጻተኛና ስደተኛ ነኝ ተመቻችቼ በዓለም ውጥንቅጥ ሳልጠላለፍ የሚመጣውን ተስፋዬን እየሱስን እጠባበቃለሁ::  እርሱን ስጠባበቅ አንዳችም ጸጋ አይጎድልብኝም ብቃቱን ሰቶኛል::  አሜን ዜግነቴንም በደሙ ታጥቤ በመንፈስ ቅዱስ  ታትሜ አረጋግጫለሁ::

ጸሎት

አባት ሆይ በዚች ምድር ስደተኛ ነኝ ስፍራ ባዘጋጀህበት በዛ ከአንተ ጋር እኖራለሁ:  ተመስገን አገሬ በሰማይ ነው:: ተመስገን እላለሁ እየተደነኩ!

25.  ከህያው ድንጋይ የተሰራሁ  መንፈሳዊ ቤት ነኝ!

1 ጴጥሮስ 2:5፤ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።

ለሁለት ምክንያት ነው መንፈሳዊ ቤት ለመሆን የምሰራው::  እርሱም 

1. በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር 

    ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን 

    ታቀርቡ ዘንድ 

2. ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ 

መስዋእት ካለ የሚያቀርበው ካህን እንደሚያስፈልግ ግልፅ ነው::  ስለዚህም በብሉይ መስዋትን ወደ መቅደስ ይወስዱና  ለካህኑ ይሰጡታል እንዲያቀርብላቸው::  በአዲስ ኪዳን ወዴትኛውም መቅደስ አንሄድም አምልኮ በመንፈስና በእውነት እንጂ በስፍራ አይወሰንም:: እኛው ነን መቅደሱ::  መስዋቱም የእኛው አምልኮና ምስጋና ነው::  ካህንም ፍለጋ አንሄድም እኛኑ ካህን አደረገን:: 

ስለዚህ በእየሱስ መንፈሳዊ ቤት ሆነናል ደስ የሚያሰኘውን መስዋት እንሰዋለን መስዋእቱንም እንደካህን እናቀርባለን:: 

ጸሎት

አባት ሆይ አመሰግንሃለሁ  መንፈሳዊ ቤት  አደረከኝ ዕለት ዕለትም እየገነባኸኝ ስለሆነ ተመስገን::  የተወደደና የተቀደሰ አንተንም ደስ የሚያሰኝ መስዋትን በፊትህ የማቀርብ ካህን ስላደረከኝም አመሰግንሃለሁ!! ሃሌሉያ!

26.  መልካሙን ሥራ ለማድረግ የተፈጠርኩኝ ነኝ!

ኤፌሶን 2:10፤ እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።

እኔ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ነኝ አሮጌው አልፏል ሁሉ አዲስ ነው::  የቀደመው ማንነቴ ከጨለማው ነበርና ክፋት የሞላበት ነበረ::  በጌታ እየሱስ  የተፈጠረው ማንነቴ መልካም ማድረግ እንጂ ክፋት የለበትም:: አዲስ ማንነት!

አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ ነው በክርስቶስ ኢየሱስ እኔ የተፈጠርኩት::  ዛሬ አይደለም ጌታ የሚያስበው ምን ታድርግልኝ ብሎ እርሱ ያቀደው  አስቀድሞ የምመላለስበትን ጎዳና አዘጋጅቷል::  ሃሌሉያ!   እርሱ አስቦ ወለደኝ አስቦበትም አባት ሆነኝ:: 

ጸሎት

አባት ሆይ አንተ ፍቅር ነህ!  አደራረግህ ሁሉ ይገርማል አሰራርህም ግሩም ነው::  በእኔ ውስጥ ስለፈጠርከው ማንነት ተመስገን ከእኔ አይደለምና መልካም ማድረግ ከአንተ ነው ተመስገን!  ይህንን ማንነት ማንም መለወጥ አይችልምና ስለታተመው አዲስ ማንነት አከብርሃለሁ::  እኔም እራሴ ብሆን መለወጥ አልችልም::  መልካምነትን ያገኘሁት ከአንተ ነውና ክበር::  አሁንም መልካሙን በእኔ የጀመርከውን ስራ እስከፍፃሜው ስለምትቀጥለው ተመስገን::  ጠላቴ እፈር!  አሜን!

27.  ከኃጢአት አርነት የወጣሁ ነኝ!

ሮሜ 6:17-18፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ የኃጢአት ባሪያዎች ከሆናችሁ፥ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት ዓይነት ከልባችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።

ቀላል ነገር ይመስላል ከኃጢአት አርነት መውጣት ነገር ግን ሁሉን ከስሩ አድርጎ ማን አለብኝ የሚል ነበር::  እየሱስ ግን የእግዚአብሔር በግ ሆኖ መቶ እንደ በግ ታረደና የኃጢአታችንን ዋጋ  ሁሉ ስለከፈለው ነው ዛሬ በነፃነት ከኃጢአት አርነት ወጥቻለሁ ማለት የቻልኩት::

በራሴ  እንዳላደረኩት ማስተዋልና በጌታ ላይ ተደግፌ መራመድ አለብኝ::  ጠላት ይህን አደረግሽ ያንን አደረግሽ እያለ የሚከሰኝ ስራ ሊያሰራኝና ከጌታ ጸጋ  ሊያወጣኝ ነው::  ስራው ተሰርቶ አልቋል ጌታዬ ከፍሎልኛል እኔ የምጨምርበት ምንም የለም ይህ ህይወት በእኔ ያብባል::  በሁኔታዎች የሚለዋወጥ  ማንነት  አይደለም የተቀበልኩት::  ጠላት የማታለሉን ስራ እየሰራ ዘመኔን እንዳይፈጀው መጠንቀቅ አለብኝ::  በአእምሮዬ መታደስ መለወጥ አለብኝ::  ይህ ማንነቴ በውስጤ እየደመቀ መምጣትና ከኔ አሳብ ጋር መዋሃድ አለበት:: 

ጸሎት

አባት ሆይ ከኃጢአት አርነት ስላወጣኸኝ አመሰግንሃለሁ::  ይህ ማንነቴ ነው!! የሚከሰኝና የሚኮንነኝም የለም አዲስ ፍጥረት አድርገኸኛል::  ተመስገን! በዚህ እውነት ውስጥ ስር ልስደድ በአእምሮዬም መታደስ ልለወጥ:: ጠላቴን ኩምሽሽ  ስላደረከው ተመስገን በእኔ ዘንድ አንዳችም የለውም!!  ጸጋህን ስጠኝ::  አሜን!

28.  የሞትኩኝ ነኝ!

ቆላስይስ 3:3፤ ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና።

ሞትን ከእግዚአብሔር አንፃር ስናስብ መለየት ነው::  አዳምና ሄዋን ሞቱ ሲባል በስጋ አልነበረም ነገር ግን በመንፈስ የሞቱ ሆኑና ከእግዚአብሔር ተለዩ::  አሁንም መሞት ሲባል ከዓለም መለየትና ለጌታ መኖር ነው::

ይህ አባባል ቀልድ ቢመስልም እንኳን መልክቱ ይገርመኛል “የዘንድሮ ክርስትያን ሙት ሲባል ፌንት ያደርጋል” የሚለው::  መሞት ማለት ከአንድ ቦታ መለየትና በሌላ ቦታ መገኘት ነው ስለዚህ ለዓለም ሞተን ከክርስቶስጋር መሰወር ሆኖልናል::

ይህንን እውነት እናስተውል ክርስትና የምንኖረው ነው እንጂ የምንለውጠው ወይም ማሻሻያ ማድረግ የምንችለው አይደለም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ናችሁ ሲለን እሺ ብለን መኖር እንጂ እስኪ ልየው ብለን በማየት አንመላለስም በእምነት ነው::  ደህንነትን ስንቀበል ወደ እግዚአብሔር መንግስት ፈልሰናል ግን የተፈራረምነው ነገር የምናሳየው መረጃ ምንድነው?  የለንም በእምነት ግን እርግጠኞች ነን::  እንደዚሁ መሞቴንና በጌታ ውስጥ የሰወረኝ  ስስት የሚያደርገኝ ልጁ ነኝ ብለን እንመን:: በላይ ያለውን እናስብ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም::

ጸሎት

አባት ሆይ ተመስገን ለዓለም ሞቼ ለአንተ የተለየሁ ስላደረከኝ ተመስገን::  ህይወቴን በክርስቶስ ውስጥ ስለሰወርከው ተመስገን አሁንም አንተው ክበርበት::አሜን!

29.  ፍርሃት የሌለኝ ነኝ

2 ጢሞቴዎስ 1:7፤ እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።

ፍርሃት ሰውን የሚያስር የመንፈስ አሰራር ነው::  ጠላትም የሚጠቀምበት ነው::  ለዚህ ነው እግዚአብሔር እንዳንጠቃበት 

–  የኃይል

–  የፍቅር 

–  ራስንም የመግዛት መንፈስ 

የሰጠን::  የፍርሃት መንፈስ በእርሱ ዘንድ የለም ማንን ይፈራል?  እኛም እንድንፈራ አይፈልም::  የመጨረሻውን ውሳኔ የሚወስን የእኛ አባት ነው::  እንመነው ይህንን ጌታ በሰጠን በመንፈሱ እንጏደድና እርፍ እንበል ወደእኛ የሚመጣውን ጠላት የሚያስፈራራበትን ነገሩን ሁሉ ወደ ጌታ እግር ስር እያመጣን እንጣለው እንጂ እንዳንሸከም::

ጌታ በሰጠን ኃይል እንደገፍ

በሰጠን ፍቅር ሁሉን እንውደድ::  

ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥለዋል::  አብረው አይሄዱም እንደብርሃንና ጨለማ የአንዱ መገኘት የሌላውን አለመኖር ያረጋግጣል::

እንዲሁም ምንም አይመጣምና እራሳችንን እንግዛ::  ተናደን አቅላችንን መሳት የለብንም::  አንድ ቁጫጭ ዛሬ ሳልገልሽ አልመለስም ብላ ብትሳደብ ምን ያህል ያስፈራና ያናድደኛል? በምንም አይነት አያስቆጣኝም ወይም ያስቀኛል::  

ጠላትም የተረታ ከእግራችን በታች የወደቀ መንፈስ ነው የቀረለት ሽንገላ ብቻ::  ዙሪያችንን እንዳበሳ ይዞራል አንበሳው ግን በእኔ ውስጥ ይኖራል::  ሃሌሉያ! 

ጸሎት

አባት ሆይ ተመስገን እንዳልረታብህ መንፈስህን ስለሰጠኸኝ ተባረክ! አሜን!

30.  በግንዱ ላይ የምኖር ብዙ ፍሬ  የማፈራ ቅርንጫፍ ነኝ!

ዮሐንስ 15:5፤ እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።

እየሱስ የወይን ግንድ ለቅርንጫፎች ሁሉ ምግብን የሚሰጥ ነው::  በዚህ ግንድ ላይ ያለ አሳብ ነው ቅርንጫፎች የሚኖሩት አይዘሩም አያጭዱም አይቆፍሩብ ብቻ ይኖራሉ ግንዱን ተማምነው::  ግን ጎደለብኝ ብለን ለመዝራትና ለመቆፈር ብንነሳ ደርቀን በዛው መቅረት ነው::  ይህንን እንድናደርግ ነው ጠላት የሚያዋክበን ተረጋግተን በጌታ እርፍእንበል::  

ስለዚህ በግንዱ ላይ መጣበቅና  ያለእርሱ አንዳች እንደማናደርግ አውቀን መደገፍ አለብን::  ጥረት ግረት የሌለበት እድገትን በእርሱ ላይ በመደገፍ ብቻ እናገኛለን:: እድገት ካለ ፍሬ ማፍራት አለ በእርሱ ደግሞ ብዙ ፍሬ ነው የሚፈራው::

ጸሎት

አባት ሆይ በእየሱስ ላይ እንደቅርንጫፍ ስለተከልከኝ ብዙ እንዳፈራም ስለሰጠኸኝ ተመስገን!  ዛሬም ውሳኔዬ በአንተ ላይ መጣበቅ ነው::  አሜን!

31.  የማስታረቅ አገልግሎት የተሰጠኝ ነኝ!

2 ቆሮንቶስ 5:18፤ ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤  19፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።

ክርስትናን ከሌላው እምነት የሚለየው ትልቁ ነገር የመኖር ዘይቤ አይደለም አምላካችን የሰጠን::  ዋጋውን ከፍሎ እዳችንን አስወግዶ ከእራሱ ጋር አስታርቆ ተቀበለን ልክ ምንም እርም እንደሌለን ጻድቅ አድርጎ::  

መቀበል ብቻ አይደለም ዋጋው ተከፍሏልና ለሰው ልጅ በሙሉ ተናገሩ::  ምን ብለን እንናገር?  እግዚአብሔር እንታረቅ ይላል እርሱ ሁሉን ይቅር ብሎ እየጠበቀ ነው ብለን ማወጅ::  ዛሬም በእኛ ውስጥ እየሱስ የማስታረቁን ስራ ቀጥሏል::

ጸሎት

አባት ሆይ ተመስገን እኔ ከአንት ጋር ታርቄ ታረቁ የሚልን አገልግሎት ስለሰጠኸኝ::  አሁንም አባቴ ሆይ በምደርስበት ስፍራ ሁሉ ከእግዚአብሔር ታረቁ እያልክ እራስህ እንድታውጅና የሰዎችንም ልብ እንደ ሊድያ ልብ እንድትከፍት  መንግስትህ እንዲሰፋ እፀልያለሁ:: አሜን!

32.  ክርስቶስ በሚሰጠኝ ኃይል ሁሉን የምችል ነኝ።

ፊልጵስዩስ 4:13፤ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።

እኔ በራሴ አንዳች ማድረግ የማልችል ነኝ::  ለዚህም ነው በወይኑ ግንድ ላይ የተተከልኩኝ ቅርንጫፍ የሆንኩት::  ቅርንጫፍ በራሱ ምንም አያደርግም መድረቅ ነው የሚቀርለት  ከግንዱ ሲለይ::  

እኔም እንደዚሁ ከጌታ በሚሰጠኝ  ኃይል ነው ኑሮዬን የምኖረውና ሁሉንም የምችለው::  ኃይል የሚሰጠኝ  በራሴ ቆሜ (ኢንዲፐንደንት) እንድሆን አይደለም ሁልጊዜም በእርሱ ውስጥ እንድኖር ነው እንጂ::  ኃይል ተሰቶኛል በቃ ልሂድና ኑሮዬን ልኑር  እንድልም አይደለም ነገር ግን ሁልጊዜ በእርሱ ላይ ተደግፌ ዕለት ዕለት ኃይልን እየተቀበልኩ የምቀጥለው ኑሮ ነው::  እስራኤላውያን መናን በየዕለቱ ይለቅሙ እንደነበረው ብዙ ቢለቅሙም ለነገ አይሆንም ነበር::  በእርሱ ላይ መታመንን ሊያስተምራቸውና መሪ ሊሆናቸው ነበር እነርሱ ግን ሰለቸን አሉት::  ለኔ ግን ምን አይነት እድል ተሰጠኝ ወደፊቱ ቀርቤ ድካምን የማሸንፍበት ኃይል መቀበል መቻል?! ክርስትና ዕለት በዕለት የሚኖር ነው::  

ስለዚህ በማልፍበት ጎዳና ሁሉ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። 

ጸሎት

አባት ሆይ ተመስገን ኃይልን ስለሰጠኸኝ::  ምንም ቢመጣ በህይወቴ አያስፈራኝም የሚረታኝም የለም:: ዛሬም ኃይልን ስጠኝ::  ጸጋህንም ሙላኝ!  አሜን!

33.  ድምጹን የምለይና የምሰማ ነኝ!

ዮሐንስ 10:3፤ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል።

ይህ ማንነቴ ነው!  እርሱን ለይቼ መስማት!!  ይህንን ነገር ለማምጣት ምንም የማደርገው ነገር የለም በፊቱ በፀሎት መገኘት ብቻ ነው::  

በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው እንደሚል ቃሉ እኔ እረኛና አባት አለኝ:: ይህ እረኛ በስሜ ይጠራኛል – የሚገርም አይደል?!  ከዚህ ሁሉ ሰራዊት ለይቶ ያውቀኛል::   

ጸሎት

አባት ሆይ ተመስገን አንተን የምሰማበትን ብቃት ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ!  አባት ሆይ እከተልሃለሁ! አንተ የእኔ እረኛ ተባረክ ወደ ለመለመ መስክ ሁሉ ስለምታሰማራኝ አንዳችም ስለማይጎድልብኝ ክበር ተመስገን! አሜን!

34.  ጌታን ብቻ እየሰማሁ የምከተል ነኝ!

ዮሐንስ 10:4፤ የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤

5፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።

ከእየሱስ በቀር አሳቹን አልሰማም ደግሞም አልከተልም::  የእየሱስን ድምጽ የመስማት ብቃት አለኝ ይህንንም ብቃት ከእርሱ በመወለድ አገኘሁኝ::  ጠላት እንዴት እለያለሁ የእግዚአብሔርን ድምፅ እያልኩኝ እንድጨነቅና እንድጠራጠር ይፈልጋል::  ጌታዬ ግን የሚናገረኝ በቃሉ ነው::  አዲስ ነገር አይናገርም አይኮንነኝም ንስሃ እንድገባ ስህተቴን አሳይቶ ወደ ንስህ ያመጣኛል::  ዝም ብሎ የሚተገትግና የሚያዋርድ ግን የጠላት ድምፅ ነው::  ለዚህ ነው በአእምሯችን መታደስ መለወጥ ያለብን::  ቃሉን ባወቅን መጠን የጠላት ሽንገላ እርቃኑን ይቀራል::  ቃሉ ውስጣችንን ይለውጣል ያቀናል በሰላምና ደስታ ይሞላናል::

ጸሎት

ጌታዬ ሆይ አንተን ብቻ የምሰማ ነኝና ተምስገን!  እረኛዬ ክበርልኝ ጠብቀኝ ብዬ ዛሬ አላስታውስህም ልክ እንደአይንህ ብሌን ትጠብቀኛለህ::  ክብር ይብዛልህ!  አሜን!

35.  ለአዲስ ኪዳን አገልጋይ ነኝ!

2 ቆሮንቶስ 3:6፤ እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።

ህይወትን በሚሰጠው በእግዚአብሔር መንፈስ ለዚህ አዲስ ኪዳን ብቁ ሆንኩኝ ከኔ የሚጨመር ምንም የለም::  በቃሉ እንደሚል እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው። በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም::  በእውነትም አይደለንም!

ጸሎት

አባት ሆይ በራስህ አሰራር ልቤን ቀይረህ የአዲስ ኪዳን አገልጋይ ስላደረከኝ አመሰግንሃለሁ::  አሜን!

36.  ለበጉ ሰርግ የተዘጋጀሁ ነኝ!

ራእይ 19:7፤ የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ።

እየሱስ ስፍራ አዘጋጅቶ እርሱ ባለበት እንድንኖር ሊወስደን ይመጣል::  ይህ የሰርግ ግብዣ በጣም በትልቁ ነው አምላካችን እየተዘጋጀበት ያለው የሚፈፀምና የሚሆን ነው::  

እንደነዛ ልባም ቆነጃጅት የተዘጋጀንና በር በሩን የምናይ እንሁን እንጂ ይህንን ዓለም አንምሰል::  ጌታ ሊመጣልን በደጅ ነው::  መምጣቱንም ወንጌልን እየሰበክን እናቻኩል::   በሰማይ አገር አለን ከዛም የሚመጣ ሙሽራና ንጉስ እንጠብቃለን::  እርሱ ሲመጣ ነገር ሁሉ ይለወጣል ትንሽ ጠብቅ ብሎ ዮናይት ኔሽን አያቆመውም ወይም ምንም ኃይል የሚያቆመው የለም::  አባት በፈቀዳት በዛች ጊዜና ሰዓት ላይ ይመጣል መሲሁ::  አሜን!

ጸሎት

ማራናታ!!

Published by Betty & Abera

We’re dedicated to share God’s goodness and mercy through His word!

2 thoughts on “በክርስቶስ ማን ነኝ?

Leave a reply to Anonymous Cancel reply