1ኛ የዮሐንስ መልእክት

መግቢያ:-

የመጽሐፉ ጸሕፊ: ዮሐንስ ነው

የተጻፈበትም ዓላማ:- በዘመኑ ተነስቶ የነበረውን የኑፋቄ ትምርህት ስህተት ለማሳየትና ቅዱሳንን ለማጽናት ነበረ:: የስህተት ትምህርቱ መንፈስ ሁሉ ቅዱስ ነው፤ ሥጋ ሁሉ እርኩስ ነው የሚል ሲሆን የክርስቶስን ሥጋ መልበስ እንኳን ወደ መጠራጠርና መካድ ያመጣ ትምህርት ነበረ ለዚህም ነው ዮሃንስ እኔ አብሬው ነበርኩኝ ዳስሼዋለሁ አብሬውም ኖሬያለሁ እያለ ትምህርቱን የሚያፈርሰው:: ስለዚህም ትምህርቱ ሥጋችን እርኩስ ስለሆነ መጎሳቆል አለበት ደግሞም ምንም አይነት የሥነ ምግባር ብልሽት ቢኖርብን የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ አይደለም ስለዚህ ችግር የለውም የሚል እስከዛሬም ድረስ በየቦታው ብቅ የሚለ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያስቸገረ የስህተት ትምህርት መልስ የተሰጠበት ክፍል ነው:: ሰይጣን ዛሬም ሙሽራይቱን እየተዋጋ ስህተትን በእውቀት አስመስሎ በመዋጋት ላይ ነውና ቃሉን እንወቅ!

በብዙ የሚያተኩረው:-

  1. የክርስቶስን ሥጋ መልበስ (1:1-4)
  2. ክርስትና ከአብና ከወልድ ጋር ያለ ህብረት መሆኑ (1:5; 2:28)
  3. ክርስትና የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ነው (2:29; 4:6)
  4. ክርስትና የሥነ ምግባርና የክርስቶስን ማንነት የመረዳት ውህደት መሆኑ (4:7; 5:12)
  5. የክርስትያን እርግጠኛ እምነቶች (5:13-21)

ይህ መልእክት የተጻፈው በ85 ዓ.ም እንደሆነ ይገመታል::


ምዕራፍ 1

የሕይወት ቃል

1ኛ ዮሐንስ 1: 1
1፤ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤

ዮሃንስ እኔ ከእርሱ ጋር ነበርኩኝ ብሎ የመሰከረው ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ሐዋ 4: 20፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም፡ አሉአቸው ይላል ቃሉ:: ይህ የህይወት ቃል የሆነው እየሱስ ዛሬም ህይወትን ይሰጠናል:: ህይወት እንዲበዛልን ነው እርሱ የመጣው ሌላው ግን ሊሰርቅ ስለዚህ ከተገለጠልን እውነት ጋር እንጽና:: በክርስቶስ ላሉት ኩነኔ የለባቸውም ይለንና በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። አሜን ህይወት ብለን ስንል ከሞትና ከአባቱም ከሐጥያት ህግ ማምለጣችንን እናስብበእኛ ዘንድ የሚሰራው የህይወት ህግ እንደሆነ አውቀን ህይወትን እንከታተል:: እኛም ምስክሮች ነን ይህንን ህይወት በህይወታችን ተገልጦ አይተናልና:: ይህንን ጌታ እናመስግነው እናወድሰው!


ሕይወት ተገለጠ

1ኛ ዮሐንስ 1:2
2፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤

ህይወት ምን አለ? ተገለጠ! ከዛስ? አየነው! ስለዚህ ያየነውን እንመሰክራለን:: የሚሰማ ይስማ!

ይህ ህይወት (እየሱስ) የት ነበረ? በአብ ዘንድ! እርሱ የነበረና ያለ ዘላለማዊ አምላክ ነው:: ከአብ ዘንድ መቶ ተገለጠ! ስለዚህ ያየነውን እናወራለን ደግሞም እንመሰክራለን:: እየሱስም እንደተናገራቸው በዮሐንስ 15: 27፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ። ስላላቸው ይኸው ዮሐንስ ምስክርነቱን እየሰጠን ነው:: ህይወት ህይወት እንሽተት ምክንያቱም ይህ ህይወት በእኛ ተገልጧልና ለሌሎችም ህይወትን መስጠት ይፈልጋል:. ከሞት ወደ ህይወት ተሻገርን! ህይወትን እንግለጠው! እናብለጭልጨው! እርሱ የሚሰራው ነው ሁልጊዜ ዓላማው ህይወትን መስጠት ነው:: ህይወት እንዲበዛልን እንዲትረፈረፍልን መጣ! አሜን ታላቅ ስሙ ይባረክ!


ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው

1ኛ ዮሐንስ 1:3-4
3፤ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። 4፤ ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።

ክርስትና የሚታይ የሚዳሰስ ነው:: እኛ የዘላለም ህይወት ያለን ሰዎች ነን ይህ ህይወት ኅብረት እንድናደርግ አድርጎናል:: ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው:: በሌላ ስፍራ እንደሚለው ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው። እዚህ ኅብረት ውስጥ ህይወት፤ ደስታና እረፍት አለ:: ይህ የገባንበት ኅብረት የተለየ ነው ለመቀላቀልም የተጠየቅነው በልጁ ማመን ብቻ ምክንያቱም ስራው እግዚአብሔር በፍጥረት መጀመሪያ ቃል እንደገባው ከሴቲቱ የሚወለደው የተባለው ህይወት የሚሰጠው ቃል መቶ ያለውን ስለተፈጸመ በማመን ብቻ ኅብረትን አደረግን:: ከማይጠፋውም ዘር ተወለድን ለዘላለምም የጌታ ወዳጆች ሆንንና ኅብረትን እናደርጋለን:: ስሙ ይባረክ! ጌታ እንዴት ያለ ቸርነት አደረገልን?!

ደስታችሁም እንዲፈጸም ነው ይህን የምጽፈው ነው የሚለን። እንግዲህ በጌታ ደስ ይበለን በተሰጠንም ኅብረት ደስ ይበለን ከእርሱ የሚለየን ይህንን ህይወት ከእኛ የሚወስድ የለምና! እርሱ የሰጠን ጌታ ከሁሉ ይበልጣል:: ለምን ከአብና ከልጁ ጋር ብቻ ሆነ ኅብረታችን? መንፈስ ቅዱስስ? እርሱማ በምድር ከእኛ ጋር አይደለ ያለው? ቃሉን እናስተውል! ጌታ ያለን እኔ ወደ ሰማይ ስሄድ እርሱ ይመጣል አላለንም? ብቻችንን እንዳንሆን አብሮን ያለ የሚያበረታን ቅዱሱ መንፈስ አብሮን ነው በዚህም ደስ ይበለን!


እግዚአብሔር ብርሃን ነው

1ኛ ዮሐንስ 1: 5-6
5፤ ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፡ የምትል ይህች ናት። 6፤ ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤

ዮሐንስ እንደሚለን ከእርሱ የሰማናት መልእክት ነው እያለን ያለው መልክቱም እግዚአብሔር ብርሃን ነው ስለዚህም ጨለማ የለበትም ማለት ነው ምክንያቱም የአንዱ መገኘት የሌላው አለመገኘት እንደሆነ ግልጽ ነውና:: ብርሃን ካለ ጨለማ ተሰናብቷል ወይም ጨለማ ከሆነ ብርሃን የለም ማለት ነው አብረው ተዋህደው መሄድ አይችሉም:: ስለዚህ በብርሃን ውስጥ ከሆንን ጨለማው ከወዴት ይገኛል?! በፍጹም መገኘት አይችልምና በብርሃን እንመላለሳለን::

ቃሉ ለእግራችን መብራት ነው እንደቃሉ ከተመላለስን ብርሃኑን ይዘን ከተጏዝን ጨለማ ባለበት አንገኝም ማለት ነው:: ኅብረታችን ብርሃን ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ነውና በጨለማ አንመላለስ ነገራችን በጽድቅ ተደርጎ እንደሆነ በብርሃን እንፈትሽ:: ከፍጥረትም መጀመሪያ መፍጠር የጀመረው ብርሃንን ነው ጨለማውን ገለል አድርጎ ይሰራል:: ወደ እኛም ህይወት ሲመጣ ጨለማችንን ገፈፈውና ብርሃን ይሁን ብሎ ወደ ራሱ አቀረበን ኅብረትም አደረግን! ሃሌሉያ! የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ተጠራን! እኔ የእግዚአብሔር ብርሃን የበራልኝ ልጁ ነኝ! አሜን!


የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል

1ኛ ዮሐንስ 1: 7-10
7፤ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 
በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 
10 ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል የሚለው ቃል እንዴት ልብን ያሳርፋል ምክንያቱም ሐዋርያት አንድ ወቅት ላይ ታድያ ማን ይድናል? እስኪሉ ድረስ ጽድቅ ርቆ ታይቷቸው ነበር ነገር ግን ጌታ የምኅረት አባት ስለሆነ በልጁ ደም እያነጻ ይቀድሰናል:: ታድያ በደሙ ያጥበናል ብለን በሐጥያት እንመላለስ? በፍጹም! ይህ ለሐጥያት የተሰጠ ፈቃድ አድርጎ የሚወስድ ካለ ከቶም የወንጌል ጥሪ ያልገባው ነው ወንጌል በብርሃን መመላለስ ነው ብርሃን ሁሉንም ፍንትው አድርጎ ያሳያልና እራሳችንን እያየን ቃሉ እንደሚል እራሳችንን እንመርምርና እንፈትሽ ህሊናችን ካልፈረደብን ጥሩ ነው::

ለዚህ ነው ያለፍርሃት በፊቱ በብርሃን የምንመላለሰው አንዳች ጉድፍ ቢታይ ኃጢአት የለብንም ብለን ብንክድ ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። ነገር ግን ኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።  ዓመጽን አንውደድ እየሱስ እራሱን የሰጠው እኛን ከአመጽ ለማንጻት ነውና ደግሞም የታመነ ነው ወደ እርሱ በድፍረት እንቅረብና ራሳችንን መርምረን በደሙ እንታጠብ አለበለዚያ ግን ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

እኔ በነገር ሁሉ ትክክል ነኝ ብለን አንኮፈስ ዝቅ እንበል እራሳችንን በፊቱ እናዋርድ ያን ጊዜ ከፍ ያደርገናል ኅብረታችን ከእግዚአብሔር ጋር የተገመደው በፍቅር ነውና ይህ ብርሃን የሆነ አባት አይተወንም! ስሙ ይባረክ!


ምዕራፍ 2

ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን

1ኛ ዮሐንስ 2: 1
1፤ ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ቃሉ የሚለን ሐጥያትን አታድርጉ ነው እንጂ በመግቢያው ላይ እንዳየነው የስህተት ትምህርት ስጋ እርኩስ ነው ምንም አይነት የሥነ ምግባር ብልሽት ቢኖርብን የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ አይደለም እንደሚለው አይደለም:: ደስ የሚለው ሐጥያትን አታድርጉ ብሎ ብቻ አላቆመም ብታደርጉ ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠበቃችሁ ነው ይለናል::

ይህ ጻድቅ የሆነ ጠበቃ ምን ያደርጋል?

  1. ይማልዳል – የጠበቃ ስራው ስለእኛ መከራከር ነው ማምለጫውን ማሳየት ነው:: ጌታ እኮ ለኛ ነው የሚያደላው እንጂ ሊፈርድብን አይደለም
  2. በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ መካከለኛ ነው
  3. ከሳሾችን በትኖ እኔም አልፈርድብሽ የሚል ነው
  4. የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ስለእኛ ሐጥያት የሆነ ነው
  5. በእርሱ በቀር ወደ አብ መግባት አይቻልም የተባለለት ነው
  6. በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድን የሚችል ነው
  7. ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ሊቀ ካህን ነው
  8. በነገር ሁሉ የተፈተነ ስለሆነ እጅግ የሚራራ ሊቀ ካህን ነው

አሜን እርሱ እንደዚህ ስለእኛ ቆሟል እንዴት የሚያስድስት ጌታና አባት ነው?! እንድንጠቃ የማይፈልግ ሁሌ በድል እንድንመላለስ የሚፈልግ አባት:: ሃሌሉያ! በጠበቃችን ደስ ይበለን! ጠላት ኮርነር እስይዞ መውጫ ሲያሳጣን እናስታውስ ጠበቃችን በስራ ላይ ነው ለአፍታ እንኳን ተዘናግቶ አያውቅምና መሸነፍን እርሱት! እርሱን ይዘን አንሸነፍም! ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይህንን ጠበቃ እንድንረዳውና እንድናውቀው ይርዳን! አሜን!


እየሱስ የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው

1ኛ ዮሐንስ 2:2፤ እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።

እየሱስ የኃጢአታችን ማስተስሪያ እንዲሆን ከአብ ዘንድ መቷል በሌላም ስፍራ የዓለሙን ሁሉ ሐጥያት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ ይለዋል:: ይህ በግ ስለሐጥያታችን ለመታረድ ዝም አለ አፉንም አልከፈተ የነገስታት ንጉስ ወደ ሞት ተነዳ:: የሚገርመው ነገር ለሚገባው ሰው እንደው ምናልባት ዋጋ ይከፈላል ነገር ግን አሳልፎ ለሞት ለሰጠና ለገፋ መሞት?! ምን አይነት ፍቅር ነው? ይደንቃል! እኔና እናንተ ውለታው የበዛብን የማይገባን ነበርን እርሱ ግን የተገባን አድርጎ ቆጠረንና የሚወደውን አንድ ልጁን ሰጠን ልጁም በፈቃዱ ስለእኛ ራሱን ሰጠ:: ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የእግዚአብሔርን ፍቅር እንፈጽም

1ኛ ዮሐንስ 2: 3-6
3፤ ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን። አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። 
ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤ 
በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል። 

ጌታን እንደምናውቀው የምናውቅበት መንገድ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ትእዛዙን ስንጠብቅ ነው:: ትእዛዙን ስንጠብቅ ፍቅሩ በእኛ ተፈጽሟል ማለት ነው:: አለበለዚያ ግን አውቄዋለሁ ብለን ትእዛዙን ባንጠብቅ ውሸተኞች ነን:: እግዚአብሔር ከስስቱ የተነሳ ወስዶ በአብ ቀኝ በልጁ ውስጥ ሸሽጎናል በእርሱ ስንኖር እርሱም በእኛ እየኖረ ነውና እርሱ እንደተመላለሰ እንድንመላለስ ነው የሚፈለገው:: ማንነታችንን ባወቅን ቁጥር ወደ እርሱ እየተጠጋንና እየመሰልነው እንሄዳለን:: ይህ ማለት ግን አድርግ አታድርግ አይደለም በፍቅሩ ተሸንፈን እጃችንን የሰጠን ዓለምንም የናቅን ለክብሩ የምንኖር ልጆቹ ነን:: ቀድሶናልና ልንረክስ አንሄድም የኑሮ ደረጃችን ጽድቅን የሚፈልግና ከፍ ያለ ነው:: ይህንን እውነት እንድናውቅ ለረዳን ጌታ ክብር ይሁንለት:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ጌታ አምላክህን ውደድ

1ኛ ዮሐንስ 2: 7
7፤ ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።

ከመጀመሪያ የነበረችው አሮጌ ትእዛዝ ምንድናት? በማቴዎስ ወንጌል 22: 37፤ ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። 38፤ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ዮሐንስም ስለዚህ አሮጌ ትእዛዝ ነው እየነገረን ያለው ጌታም በምድር ሲመላለስ ያስተማረውን ህግም አድርጎ ለህዝቡ የሰጠውን እንጂ ሌላ አልጽፍም ነው የሚለን:: እኛ የጌታ ነንና:: እርሱን ባለን ማንነት ሁሉ እንውደድ! መውደድ ደግሞ በተግባር የሚገለጥ ስለሆነ ከወደድነው እንታዘዘው በቃሉም እንኑር::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን እንድንወደውና እንደቃሉም እንድንኖር!


በጨለማ አንመላለስ

1ኛ ዮሐንስ 2:8-11
8፤ ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል። በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። 10 ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤  11 ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።

ዮሐንስ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ ይላል እውነት ስለሆነው ነገር:: ይህም ነገር በእርሱ እንዲሁም በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው አልፏል እውነተኛውም ብርሃን አሁን በርቷል ይለናል አሜን ብርሃኑን በእኛ ውስጥ አብርቶ ጨለማውን ላባረረው ጌታ ክብር ይሁን:: እንግዲህ በብርሃን ውስጥ እየተመላለስን ካለን ወንድማችንን መጥላት የለብንም እርሱ የጨለማ ስራ ነውና:: አለበለዚያ በጨለማ ነን ወንድማችንን መጥላት በእኛ ውስጥ ከተገኘ:: ችግሩ መጥላት ውስጣችን ሲገባ መንገዳችንንም በቅጡ አናየውም በጨለማ መደናበር ነውና የሚሆነው:: ከፍቅር በቀር እዳ አይኑርባችሁ የተባልን የእርሱ ደቀመዝሙርት ነን:: ደቀመዝሙርነታችንም የሚረጋገጠ በፍቅራችን ነውና እርሱ እንደወደደ መውደድ እንድንችል የእርሱን የፍቅር ጥልቀት እንዲገልጥልን እንጸልይ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በጌታ ተደግፈናል

1ኛ ዮሐንስ 2: 12-14
12፤ ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ። 13 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። 
14 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ። 

ከሚከተሉት በአንዱ የእድሜ ክልል ውስጥ እንጠቃለላለን ብዬ አስባለሁ እናም ዮሐንስ ሊለን የፈለገው እድሜ የጠገበውም፤ ልጅ የሆነውም እንዲሁም ጎበዝ የሆነውም በእግዚአብሔር ቤት በተለያየ ተግዳሮት ያልፋል ነገር ግን ለሁሉ የሚሆን ጸጋና ብርታት ጌታ ለህዝቡ አለው::

ልጆች ብሎ ሁላችንንም ያጠቃልልና ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋል ይልና እንደገና ደግሞ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ:: የኃጥያት ስርየት በእየሱስ በልጁ ስናገኝ በእርሱ በኩል ደግሞ ወደ አብ ለመግባት ድፍረት እንዳለን ቃሉ ይነግረናል ስለዚህም አብን የማወቅ እድል ተሰጠን! አሜን በሌላ ስፍራ እራሱ ጌታ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል ብሏልና ልጁን ያወቀ አባቱንም ያውቃል::

አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና ይላል ይህ ከመጀመሪያ የሚለውን ሀሳብ መጽሐፉን ሲጀምር ገና ነው ያሰፈረው እርሱም:- ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ስለ ህይወት ቃል ነው የሚያወራው:: ይህ የህይወት ቃል የሆነ እየሱስ ተግልጧል ለእናንተም ማወቅ ተሰቷችኃል ነው የሚለው::

ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እንዲሁም ደግሞ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ:: በመዝሙረ 119: 9፤ ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው እብደሚል ቃሉ ይቀድሳል:: ጎበዞች ዓለም የሚያደንቃቸው ጡንቻና ውበት ማሳያ ጊዜ ላይ ቢሆኑም ወጣትነታችንን ለጌታ ብለው ክፉውን እንዳሸነፉ ይመሰክርላቸዋል::

ስለዚህ ከጌታ የተነሳ አሸንፈናል ስሙ ይባረክ!


የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል

1ኛ ዮሐንስ 2: 15-17
15-16፤ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 17፤ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።

ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ ይላል ዮሐንስ:: ለምን? ምክንያቱም መውደድ ያለብን አምላካችንን ነው ለዛውም በፍጹም ማንነታችን ስለዚህ ሌላውን ለመውደድ ቦታ የሌለን መሆን አለብን:: ማንም ዓለምን ቢወድ ግን የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም!! ጌታ ይርዳን ልዮነቱን እንድናስተውል:: በዓለም ያለው እንየው እስኪ:-

  1. የሥጋ ምኞት:- ሮሜ 8:6፤ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። የስጋ ምኞት የሚያመጣብን ሞት ስለሆነ ስለ መንፈስ እንድናስብና እንድንመኝ ነው በክርስቶስ የተፈጠርነው:: ሰልፍን በራሳችን ላይ አንጋብዝ ለጌታ እንለይ እንደቃሉም ለጥቅማቭን ስንል እንመላለስ::
  1. የዓይን አምሮት:- በሄዋን ላይ ይህ ችግር ምን እንዳስከተለ የሰው ልጅ ሁሉ የተባረረበት መነሻው ችግር ነው:: የሰይጣን መግቢያ በር ነውና እንዝጋው::
  2. ስለ ገንዘብም መመካት:- ጌታ እራሱ አስጠንቅቆናል:- በማቲ 6:24 ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። በሌላም ስፍራ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ስር ነው ይላልና ገንዘብን መውደድ ወደ ጥፋት መውረድ ነው::

ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል ስለሚል ቃሉ የሚያልፈውን ትተን የተጠራልነትን የዘላለሙን ፈቃድ እንከታተል እግዚአብሔር ፈቃድ ሰቶናል የምናደርገውን እንወቅ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የመጨረሻው ሰዓት ነው

1ኛ ዮሐንስ 2:18-19
18፤ ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን። 19፤ ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።

ዮሐንስ የነበረበትን ዘመን የመጨረሻው ሰዓት ነው ብሎ ካለ ዛሬ ምን ሊባል ይሆን? የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል ይላል:: የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል አይቀርም የዓለምን አካሄድ ሁሉ አስተውሎ ለሚያይ ነገሮች በደንብ እየተዘጋጁለት እንዳሉ እናያለን:: ስለዚህ ምን እናድርግ? እንናወጥ? በፍጹም መፍትሄው መሆን ያለበት

  1. በጌታ መጽናት እንዲሁም
  2. የእኛ ኑሮ ሁልጊዜ ጌታን የሚያከብር መሆን አለበት ምክንያቱም ጌታ በየትኛዋ ሰዓት መቶ እንደሚወስደን አናውቅምና
  3. ህይወታችን የተዘጋጀ ይሁን:: የክርስቶስ ተቃዋሚ ሲበዛ ግር አይበለን ሌላው ቀርቶ ከመካከላችንም ሊወጡ ይችላሉና
  4. መዳናችንን በፍርሃት እንፈጽም::

ምሰሉና ተመልከቱ የተባልነው ክርስቶስን እንጂ በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች አይደለም አለበለዚያ እነርሱ ሲስቱ እኛም እንሰናከላለን:: እኛ ከዚህ ዓለም አይደለንም የምንሄድበት ያለን መጻተኞች ነን:: ጌታ ይመጣል ሊወስደን! ማራናታ


ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል

1ኛ ዮሐንስ 2: 20-21
20፤ እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። 21፤ እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም።

እንደቀደሙት ቅዱሳን ሁሉ እኛም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብለናል ይህ ቅባት ተብሎ የተጠቀሰው ማነው? የእግዚአብሔር መንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ ነው:: ይህንን መንፈስ በዳንንና ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት በፈለስን ጊዜ ተቀብለናል ወይም ተቀብተናል:: ጌታ እየሱስ እንዳለን እኔ ብሄድ ይሻላል ምክንያቱም አጽናኙ ይመጣላችኃል ብሎን ነበር:: እርሱም በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኃል ብሎን ነበር:: ይህ ቅዱስ ቅባት በእኛ ውስጥ ስላለ ሁሉንም ታውቃላችሁ ይላል:: ይህ የእርሱ ብቃት ነው የእኛ አይደለም::

እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም። የምጽፈው ላጸናላችሁ ነው እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም ነው የሚለን:: ውሸትን ከእውነት እንለይ ዲያቢሎድ የውሸት አባት እንደሆነ እናውቃለን እና ጥቂት መርዝ በብዙ እውነት ውስጥ ቀይጦ ሲሰጠን እንለይ ምክንያቱም ከሰማነው መንፈስ ቅዱስ ይመራል ደግሞም እንዳንወድቅ ያስተምራል::

ከቅዱሱ ቅባት ተቀብያለሁ እውነትም በእኔ ውስጥ አለና አመሰግንሀለሁ:: መንፈስ ቅዱስ ሆይ አስተምረኝ::

ጌታ ጸጋውን ያብዛልን ያትረፍርፍልን!


አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው

1ኛ ዮሐንስ 2:22-26
22፤ ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 23 ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው። 24 እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።  25 እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።  26፤ ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።

ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? ክርስቶስ ወይም መሲኡ እንደሚመጣ እስራኤሎች ጠንቅቀው ያውቃሉ አሁንም ይመጣል ብለው የመጣውን ጌታ እየጠበቁ ነው:: በብዙ ምስክር ሐዋርያቱ ያዮትን የዳሰሱትን አብረው የኖሩትን ጌታ መስክረው ሲያበቁ ክህደትን ሲያዮ የውሸት አባት ከሀዲው እርሱም ሰይጣን የሰውን ልብ እያደነዘዘ እንጂ ከዚህ በላይ ምን ምስክር ያስፈልጋል? እኛም ዛሬ ምስክሮች ነን የእግዚአብሔር ልጅ ሲያድን አይተናል እርሱ ጌታና አዳኝ የሆነው አምላክ ነው:: ማስረጃ ከውጪ እስከማያስፈልገን ድረስ አይተናል ልክ እንደ ሳምራይቱ ሴት የከተማው ህዝብ ሁሉ ተከትሏት ከመጣ በኃላ ከእየሱስ ጋር ከቆዩ በኃላ አሁን የምናምነው ስለቃልሽ ሳይሆን አይተን ነው እንዳሉት:: አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። መንፈስን ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ በዚህ እንለያለን ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሆኖ እየሱስን አይክድም::

ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም ምክንያቱም ወደ አብ መድረሻው መንገድ እየሱስ ብቻ ነው:: በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው። አሜን! እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።  እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው። ይህንን የዘላለምህይወት ለፍተን አይደለም ያገኘነው በልጁ መስዋዕትነት እንጂ ስለዚህም ከእኛ አይወሰድም ጸንተን እንኑር!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእርሱ ኑሩ

1ኛ ዮሐንስ 2 : 27-29
27፤ እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 28፤ አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ። 29፤ ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።

በእርሱ ኑሩ እያለ ይመክረናል ለምን?

  1. እውነተኛ አስተማሪ ስለሆነ:- የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ
  2. ሲመጣ እንዳናፍር:- በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ

በእርሱ መኖራችን የሰጠን ተስፋ እርሱም የዘላለም ሕይወት ነው። ስለዚህ በእርሱ ውስጥ እንኑር:: እናንተ በእኔ ውስጥ እኔም በእናንተ ስጥ እንደሆንኩኝ ያኔ ታውቃላችሁ ብሎናል::


ምዕራፍ 3

የእግዚአብሔር ልጆች ነን

1ኛ ዮሐንስ 3:1
1፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም።

ይህ ፍቅር የሚገባን ማን እንደሆንንና ምን እንደተደረገልን ሲገባን ብቻ ነው:: እኛ በኃጥያታችን ሙታን ነበርን፤ በበደላችን ምክንያት የሞት ቅጣት የሚጠብቀን ነበርን፤ ከፊቱ የኮበለልን ነበርን፤ እንደወደደ ሰይጣን የሚዘውረን ነበርን እንግዲህ ከዚህ አንስቶ ነው ልጅ ሁኑኝ ያለው ጻድቁና ቅዱሱ ጌታ:: ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ውስጥ የሚኖር ብርሃን የሆነ ጌታ በጨለማ የምንደናበረውን ታግሶ፤ መንፈሱን ሰቶ፤ ጸጋን ጨምሮልን በልጁ መስዋትነት አንጽቶ የእኔ ብሎ ጠራን ታድያ ይህ ምን አይነት ፍቅር ነው? ለማይገባው የተሰጠ ፍቅር?

ዛሬ ግን ያ ሁሉ አልፎ የእግዚአብሔር ልጆች ስንባል ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር እራሱ አባታችን ፈልጎ እንዳገኘን እንጂ አንዳች የምንደገፍበት ጽድቅ የሌለን ሰዎች እንደሆንን እንወቅ:: ይህንን ማወቃችን የሚጠቅመን እንዴት እንደምንኖር ህይወታችንን ያስታውሰናል ትላንትና የሌለን ጽድቅ ዛሬ ከእኛ ውስጥ አይወጣምና ዛሬም በእርሱ ጽድቅ ተደግፈን እንኑር እርሱ ስለእኛ ኃጥያት ሆነ እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ:: እባቡ ዛሬም ይሰራል ጽድቃችንን ሊያስቆጥረን ወይንም ደግሞ ህይወታችንን እንድናወዳድር ሊያደርግ ይመጣል “መቼም የእኔ ህይወት ከእከሌ ይሻላል” እንድንል ይፈልጋል ይህ ነገራችን ጌታን ቅር እንደምናሰኝ ጠላት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው:: ስለዚህ ጽድቄ እየሱስ ነው የቆምኩትም በጸጋው የሚለውን ሁልጊዜ እናስታውስ:: እርሱ ፈልጎን መቷል! ዓለም እንዲያውቀን አንጣር አይፈልገንም እኛ አንመችምና የምንኖረው እርሱን ለማስደሰት ስለሆነ የህይወት መርህዋችን ከማንም ባይገጥም አይድነቀን! የጌታም እንደዛው ነበረና:: በእርሱ ዘንድ ተወደናል ተቀባይነትንም አግኝተናልና በጌታ ደስ ይበለን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን


እርሱን እንድንመስል እናውቃለን

1ኛ ዮሐንስ 3
2፤ ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።

የእግዚአብሔር ልጆች ነን ነገር ግን ገና ምን እንደምንሆን አልተገለጠም:: ቢገለጥ ግን እርሱ በእኛ ውስጥ እንዳለ እናያለን ደግሞም እንድንመስለውም እናውቃለን:: አይገርምም?! ቃሉ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው በሮሜ 8: 29፤ ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ ስለዚህ እርሱን ነው የምንመስለው በሌላም ስፍራ እርሱን እያብለጨለጭን እንደምንኖር ይናገራል:: ምን አይነት መታደል ነው? እርሱ እራሱ በእኛ ውስጥ መኖሩ? ስለዚህ ታቦታችንን እየሱስን ተሸክመን ነው የምንመላለሰው:: በሄድንበት ስፍራ ሁሉ መከበር አለበት ሰዎች ከክብሩ የተነሳ ለሚናገሩት ነገር እንኳን መጠንቀቅ አለባቸው::


ኃጢአትም ዓመፅ ነው

1ኛ ዮሐንስ 3: 3-6
3፤ በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል። ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው።  እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም።  በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም። 

ኃጢአትም ዓመፅ ነው! ሌላው ስሙ የኃጢአት አመጽ ነው ማለት ነው ከመጀመርያው ያመጸው ሰይጣን ነበረ አሁንም ሰውን የሚያሳምጸው እርሱው ነው:: ስለዚህ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ እየሱስ ግን ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም። ፍጹም ንጹና ጻድቅ ነው እየሱስ! በነገር ሁሉ የተፈተነ ነገር ግን ምንም ኃጥያት ያላደረገ ጻድቅ ነው::

በእየሱስ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ለዚህ ነው ከላይ እንዳየነው:- ስለሚያስተምረንና ሲመጣ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ የተባልነው:: በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም ቢያደርግስ?

  1. አላየውም!
  2. አላወቀውምም ነው የሚለን ቃሉ:: አያስፈራም?!

በጌታ መሆናችን ወይም እርሱ ጽድቃችን ነው ማለታችን እንደፈለገን እያመጽን እንድንኖር አይደለም ይህም ለኃጢአት ፈቃድ እንደመስጠት እንዳይመስለን እናስተውል:: ኃጥያት አመጽ ነውና! ነገር ግን በእርሱ ውስጥ ስር እየሰደድን እርሱን እንምሰል ጌታ ሊወስደን ይመጣል ሲመጣ እንዳናፍር!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን እውነትንም በውስጣችን ይግለጽልን!


የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ

1ኛ ዮሐንስ 3: 7-10
7፤ ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። 8፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። 9፤ ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም። 10፤ የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።

እዚህ ክፍል ላይ ዮሐንስ ሁለት አይነት ሰዎችን ያሳየንና እንዴት እንደሚለዩም ይናገራል:: አንዱ የጽድቅ ሲሆን ሌላው የአመጽ (ከላይ እንዳየነው ኃጢአት አመጽ ነው):: የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤

  1. አመጽን የሚያደርግ ከዲያቢሎስ ነው:- በመጀመሪያ አምጾ ያሳመጸው ዲያብሎስ ነው:: ስለዚህም የእግዚአብሔር ልጅ ይህንን የአመጽ ስራ ለማፍረስ ተገለጠ::
  2. ጽድቅን የሚያደርግ ደግሞ ከእግዚአብሔር ተወልዷል ይህም ማለት አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው አመጸኛው ማንነት ተሰናብቷል ተቀብሯል ስለዚህ ከዲያብሎስ ጋር መግጠም ቀርቶ ጠላትነት ነግሷል ለእርሱ ሽንገላ እንቢ የሚል ዘር በውስጣችን ተፈጥሯል::

ለዚህም ነው ቃሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም:: ለምን? ምክንያቱም ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ (ይህ የማይጠፋ ዘር በእኛ ውስጥ አለ ስለዚህም በውስጣችን ከገባው ከእግዚአብሔር ልጅ ማንነት የተነሳ ነው እንቢ ማለት የምንችለው) ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም (አይችልም?!) አዎን!! አይችልም::

ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ወንማችንን እንደራሳችን እንውደድ ደግሞም ትእዛዝ ነው:: እኛ በሙሉ ኃይላችን ጌታን የምንወድ ነንና ስለእርሱ ነው የምናስበው የጠላትን አሳብ የምንዘውር አይደለንም ስለዚህ ለዚህ ለሚጠፋ ዓለም አናጎበድድም መንገደኞች ነንና አይናችን በመንገዳችን ላይ ነው:: ለዚህም ነው ከምታዩትና ከምትሰሙት ተጠንቀቁ የተባልነው ጠላት አሳቡን አቀብሎን ስናቆለጳጵሰው እንዳንገኝ ነው ደግሞም ምን ማሰብ እንዳለብን ቃሉ ይመክረናል መልካም የሆነውን ፍቅር ያለበት እያለ አለበለዚያ ግን አሳብ ጸንሶ ምኞትን ይወልዳል በምኞታችንም ተስበን በኃጢአት ማመጽ ይመጣል:: ስለምናስበው እንጠንቀቅ በአእምሯችንም መታደስ እንለወጥ:: ጌታ አምላካችንን እንውደድ እንዲሁም ወንድሞችን እንውደድ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እርስ በርሳችን እንዋደድ

1ኛ ዮሐንስ 3: 11-12
11፤ ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት፦ እርስ በርሳችን እንዋደድ፡ የምትል ይህች ናትና፤ 12፤ ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።

ጌታ እየሱስ ደግሞ ደግሞ የነገረን በምድርም ሲመላለስ ኖሮም ያሳየን ፍቅርን ነው:: ፊተኛይቱ ትዕዛዝ አምላካችንን መውደድ ስትሆን የምትከተለው ደግሞ እርስ በእርስ መዋደድ የምትለው ነች:: ቃኤል ወንድሙን አቤልን የገደለው በተግባር ነው በአዲስ ኪዳን ግን ወንድማችንን ካልወደድን ወይም ፍቅርን ካልሰጠን ያንን ሰው እንደገደልነው ነው የሚቆጠረው:: ለዚህ ነው ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁ በፍቅር ይታወቅ ያለን:: የማስመሰል ጉዳይ ሳይሆን በእውነት ወንድማማች መዋደድ ልንዋደድ ይገባል ጌታ ልብን ይመረምራልና:: ለምን እንዋደድ ያልን እንደሆነ ሰውን ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ ነው እንድናውቅ የተነገረን እንግዲህ ክርስቶስን አንጠላው?! ስለዚህ ክርስቶስን በሰውን ሁሉ ውስጥ ማየት ስንጀምር ያለማዳላት መውደድ እኛ ውስጥ ይሆናል:: ክርስቶስን እናስብ ሞኝ ቢያስብለንም እንኳን የምናደርገውን እናውቃለንና እንቀጥል:: ጌታን መታዘዝ ይበልጥብናል ለእኛ ምክንያቱም የማይገባንን እኛን ወዶ ሞታችንን ሞቶልናልና:: ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን


እንዋደድ

1ኛ ዮሐንስ 3: 13-15
13፤ ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። 14፤ እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። 15፤ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።

በዚህ ጥያቄ ልጀምር:- ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን በምን እናውቃለን? ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን ይላል ዮሐንስ ሲመልሰው:: እውነት ነው? ወንድሞችን እንወዳለን? ሰው በክርስቶስ ካልሆነ በቀር ጠላቱን መውደድ አይችልም ሁሉ ወንድም ነው የዳኑትን ቅዱሳንን ብቻ እንዳይመስለን ሁሉንም የሰው ልጅ መውደድ ይህ ከጌታ የተጋባብን ነገር ነው:: ይህ ነው መመዘኛው ሁሉን ብናደርግ ፍቅር ግን ከሌለን ከንቱ ነው ሁሉም የምናደርገው::

ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ ምክንያቱም ዓለም ክርስቶስንም ጠልታለችና በዓለም ያሉት ሰዎች ብርሃንን አይወዱም ምክንያቱም ነገራቸውን ስለሚገልጠው አይወዱትም ለዚህ ነው የማይቀበሉን:: እኛ ግን መውደድ አለብን::

ወንድሙን የማይወድ ወይም የሚጠላ

  1. በሞት ይኖራል
  2. ነፍሰ ገዳይ ነው
  3. የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።

በፍቅር እንመላለስ ምሳሌያችን እየሱስ ነውና ክርስቶስ እንደወደደን ሌሎችን እንውደድ:: አለበለዚያ ግን በሞት ውስጥ ነን::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ

1ኛ ዮሐንስ 3: 16-18
16፤ እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። 17፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? 18፤ ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።

ምሳሌያችን እየሱስ ነው እርሱ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። እያንዳንዳችን ብዙ የተተወልን ነንና በብዙ ሌሎችን ይቅር እያልን ልንወድ ይገባል:: ብዙ የተተወለት ብዙ ይወዳልና:: እርሱ ፍቅሩን በተግባር አሳይቶናልና እኛም ፍቅራችንን በተግባር እንግለጽ አንድ ሰው የሚያስፈልገውን ማድረግ እየቻልን አለማድረግ የሚያሳየው ፍቅር እንደሌለን ነው ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ የሚለን። ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ነውና የእግዚአብሔር መንፈፈስ በእኛ ውስጥ እስካለ ድረስ ምንም ሳንጥር አዲሱ ማንነታችን እራሱ መገለጥ ይጀምራል:: ከጌታ ጋር ጊዜ እንውሰድ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል

1ኛ ዮሐንስ 3: 19-21
19-20፤ ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፥ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፥ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል። 21፤ ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፥

ስለ ፍቅር እየነገረን መቶ አሁን ደግሞ ልባችሁን መርምሩ ይለናል ምክንያቱም የህይወት መውጫ ነውና:: ልባችን አይታይም ብለን የአፋችንን እንዳናሳይ ደግሞ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል ብሎ እየነገረን ነው ዮሐንስ:: ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት ንጹ ህሊናና ንጹ ልብ እንያዝ በፊቱም እውነተኞች እንሁን:: ፍቅራችን ያለግብዝነት በተግባር ይሁን::


የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን

1ኛ ዮሐንስ 3: 22-24
22፤ ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። 23፤ ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ። 24፤ ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።

ጌታ እየሱስ እራሱ በዮሐ 15: 7፤ በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል ተብለናል። ስለዚህ ጸሎታችን እንዲሰማ የምንፈልግ ከሆነ ትእዛዙን እንጠብቅ:: ትእዛዛቱ ምንድነው? ትእዛዚቱም ይህች ናት፥

  1. በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥
  2. እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።

እየሱስ ትእዛዜን ጠብቁ ያለበት ሌላው ምክንያት እርሱ በእኛ እኛም በእርሱ ስለምንኖር ነው ይህንንም በመንፈስ ቅዱስ እናውቃለን እርሱ በእኛ ስለሚኖር ማንም የእርሱን መኖር ሊያስረዳን አያስፈልግምና እራሱ ቅዱሱ መንፈስ ልጅ መሆናችንን በመንፈሱ በኩል ለመንፈሳችን ይመሰክርልናል ይመራናል ደግሞም ያጽናናናል:: እንደኛ የተሞላቀቀ አለ? ማንንም ስለማያምን ከፍቅሩ የተነሳ መልአክ ሳይሆን የላከልን እራሱ መቶ በእኛ ውስጥእየኖረ ነው ስሙ ይባረክ:::

በእኛ ውስጥ ያለውን ቅዱሱን መንፈስ እያመሰገንን መዋደዳችንን ከፊት ይልቅ እንጨምር::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 4

መንፈስን ሁሉ አትመኑ

1ኛ ዮሐንስ 4: 1-3
1፤ ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥  ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። 

መቼም ያለንበት ጊዜ እግዚኦ የሚያስብሉ ብዙ ነገሮችን ሰዎች በእግዚአብሔር ስም ሲያደርጉ እያየን ነው:: በእግዚአብሔር ቃል ግን ሐሰተኛ ነብይ ማነው? እንዴትስ ለዮ ይለናል?

  1. መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ መብታችን ነው መጠራጠርና ሚዛን ላይ ማስቀመጥ እግዚአብሔር አይቆጣም እንዲያውም ያበረታታል:: ሰይጣን የብርሃን መልአክ እስከሚመስል እራሱን ይለውጣልና ደግሞም በነሄዋን ላይ ተሳክቶለታል::
  2. መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ
  3. ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና:- አሁንም በዛው ዓለም ላይ ነን ሰዎች በክፉ መናፍስት የሚነዱበት ዘመን አላለቀም እየኖርንበት ነውና በቃሉ ሚዛን ላይ እናስቀምጥ
  4. (በሌላ በኩል) የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ የእየሱስን ስራ ያንኳስሳል? በስጋ መገለጡን ይክዳል? ይሸሻል? ወይስ ያጣጥላል? እንደዛ ከሆነ በዚህ ሰው ውስጥ ያለው መንፈስ ከእግዚአብሔር አይደለም ማለት ነው:: ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤

ጌታ ማስተዋልንና ጸጋውን ይስጠን!


በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነው

1ኛ ዮሐንስ 4: 4-6
4፤ ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። 5፤ እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል። 6፤ እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን።

ከእግዚአብሔር ወገን ነንና ከአሸናፊው ወገን ነን:: እርሱ ስለእኛ አሸንፏል ወደኃላ ሄዶ መሸነፍ የለም ከጌታ ጋር ወደፊት እንራመዳለን:: እኛ ከእግዚአብሔር ስለሆንን አሸንፋችኋቸውማል ተባልን፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእኛ ያለው ታላቅ ነው። ሃሌሉያ! ብንደክም እንኳን ይሸከማል ደግሞም 99ኙን ትቶ አንዱን ፍለጋ ይሄዳል:: የሚገርመው በጣም የደነቀኝ ነገር ቢኖር ከዓለም የሆኑ የዓለም ነገር ነው የሚጥማቸው እኛ ግን ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። ይደንቃል! ከእግዚአብሔር የሆነ ይሰማናል አለበለዚያ ግን አይሰማም::

የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን ይላል ቃሉ። በምን እናውቃለን? እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። ስለዚህ ሐይለኛውን አስረን ነው መበዝበዝ የምንችለው በእኛ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣልና:: ሰው ባይሰማን ቢያሾፍ አይድነቀን የዚህ ዓለም ገዢ አሳውሮት ነው::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እግዚአብሔር ፍቅር ነው

1ኛ ዮሐንስ 4: 7-8
7፤ ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። 8፤ ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።

ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ የሚለው አሳብ በጣም ያስደነግጣል እውነት ነውና:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍቅር ነው:: ደስ የሚለው ነገር እግዚአብሔር ፍቅር አለው አይደለም የሚለው እርሱ እራሱ ፍቅር ነውውውው! አለው ካልን ይጨመራል ይቀነሳል በሁኔታ ይለዋወጣል:: የእኛ ጌታ ግን ከማስተዋል የሚያልፍ ፍቅር ነው! ማንነቱ ፍቅር ነው:: ሃሌሉያ! ለእኛ ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ነው የእግዚአብሔር ባህሪ ነውና ከመንፈሱ ወደ መንፈሳችን ይንቆረቆራል:: የእርሱ ነን ካልን አብረነው ከቆየን ይህ ባህሪው ይጋባብናል የእኛም ማንነት በፍቅር የተናኘ ይሆናል:: ለዚህም ነው ቃሉ:-

  1. ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ እንጂ እኛ ፍቅር ኖሮን አይደለም ከእርሱ ነው ፍቅር የመነጨው::
  2. የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ:- የተወለደ ልጅ ወላጁን ይመስል የለ? እኛም ይህንን የመምሰልና በፍቅር መመላለስ ተሰቶናል::
  3. እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ ካወቅነው እንመስለዋለን ታርጋችንም ወይም መታወቅያችን ሌላ አይሆንም::
  4. እርስ በርሳችን እንዋደድ :- ይህ ሁሉ ተሟልቶ የተሰጠን እንድንዋደድና ደቀ መዝሙር መሆናችን እንዲታወቅ ነው::

ብዙ ነገር ብናደርግ ፍቅር ግን ከሌለን ሁሉን በዜሮ ማባዛት ነው:: ስናገለግልም በፍቅር ይሁን፥ ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል የትኛውም የምድር ህግ አይቃወመውም:: እኛ በፍቅር የምንመላለስ ነን:: ሞኝ ቢያስብልም ለእየሱስ ልሁንለት የማደርገውን አውቃለሁና::

ጸጋው በሙላት ያግኘን!


በሕይወት እንድንኖር እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል

1ኛ ዮሐንስ 4: 9-11
9፤ በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። 10፤ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። 11፤ ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።

እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል:: ለምን ላከው? በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ! ስለዚህም በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ ፍቅሩ በተግባር እንጂ በአፍ ወይም በንግግር ብቻ አይደለም:: አንባቢ ሆይ ዛሬ ላረጋግጥ የምፈልገው እውነት እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር መወደዳችንን ነው:: ወደ ዓለም ሁሉ ላከው እንጂ ወደ አንድ የተለየ ሰው ወይም ወገን ብቻአይደለም የተላከው:: እራሳችንን በአጉል ትህትና አናሳንስ ለሁሉ መጣሁ ሲል ያንኑ እውነት እንቀበል እያንዳንዳችን ዋጋ አለን በፊቱ ለማንም አያዳላም::

ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እንዴት? ብለን እንጠይቅ:-

  1. እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን: – መወደዳችን እውነት የሆነና ለዘላለም የጸና ነው ከላይ እንዳየነው የእግዚአብሔር ፍቅር አይጨምር አይቀንስ እርሱ ራሱ ፍቅር ነው:: ስለመወደዳችን አንጠራጠር::
  2. ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ :- ጻድቁ እየሱስ ስለእኛ ብሎ ሐጥያት ሆነና ንጹውን ደሙን ለማስተሰሪያ አንድ ጊዜ እያንጠባጠበ ወደ ቅድስት ወደ አብ ገብቶ ቀደሰን በእርሱ መስዋዕትነት እኛ ነጻ ተባልን! ምን ይባላል ከማመስገን ሌላ?!
  3. እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም:- እርሱ ነው ወዶን የመጣው ሳንጠይቀው ሳንፈልገው ፈልጎንና ወዶን የመጣው:: ሲመጣም ገፋነው ከሰይጣን ጋር ተባብረን እርሱ ግን ታገሰ: ፍቅር ይታገስ የለ?

ይህንን ሁሉ መንደርደሪያ የሚነግረን ሐዋርያው የሚቀጥለውን የህይወት መመሪያ ሊመክረን ነው:: እንግዲህ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅምና እርስ በእርሳችን እንዋደድ:: አለበለዚያ የምናደርገእ ሁሉ በዜሮ ማጣፋት ነው:: ከሰው ጉድለት ከመፈለግ ይልቅ ክርስቶስን እንየው እርሱ ፍጹም ነው አንሰናከልም::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል

1ኛ ዮሐንስ 4
12፤ እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።

እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እንደዚሁም በዮሐንስ 1: 18፤ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። እንዴት ተረከው? እያከበረው በፍቅር እየተመላለሰ ነበር ያከበረው:: ዛሬ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። ከላይ ጀምሮ ደግሞ ደጋግሞ እየነገረን ያለው ፍቅር ፍቅር እያለ ነው ምን ያህል እንደተወደድን አሳየን ደግሞም ጌታን ካወቅነው እኛም የፍቅር ሰው እንደምንሆን ነገረን ነገር ግን በፍቅር ካልተመላለስን ጌታን አናውቀውም:: ያለ ፍቅር አገልግሎት የለም ቢኖርም ተቀባይነት የለውም! እርስ በእርሳችን ግን ብንዋደድ እርሱ በመካከላችን ይኖራል! አሜን! በእኛ ዘንድ እንዲኖር ከፈለግን እርስ በእርሳችን እንዋደድ ሲገኝ ደግሞ ፍቅሩ ፍጹም ይሆናል!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል

1ኛ ዮሐንስ 4: 13-16
13፤ ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን። 14 እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን። 15 ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።  16 እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 

የእግዚአብሔር አብ የፍቅሩ ጥግ የታየው እኮ ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን ሲልከው ነው ይህንንም ዮሐንስ እንደሚለው እኛም አይተናል አባት ልጁን እንደላከው ደግሞም እንመሰክራለን ይላል። አሜን ስለ ሁላችን እየሱስ መከራ ሊቀበልና ሊታደገን ተላከ! አቤት ፍቅር! ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። የሚገርም መዋሀድ ነው:: ግን በእኛ መኖሩን እንዴት እናውቃለን? ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን። የእግዚአብሔርን መንፈስ ዓለም አያውቀውም አለን እየሱስ እናንተ ግን በውስጣችሁ ስለሚኖር ታውቁታላችሁ እንዳለን እርሱ በእኛ ውስጥ እንዳለ ውጫዊ ማረጋገጫም አንፈልግም እርሱ በእኛ እኛም በእሱ እየኖርን ነው::

እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። ምክንያቱም ስለወደደን ነው ከእኛ ጋር ለዘላለም ሊኖር የመጣው ፍቅሩማ ግልጽ ነው:: እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። በምን የሚኖር እንደሚል እናስተውል:- በ ፍ ቅ ር ! የሚኖር:: እኛ ህይወታችንንም መምራት ያለብን በፍቅር እንደሆነ ልብ እንበል ያኔ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል:: ፍቅርን እንከታተል! ይህንን ከመታወቅ የሚያልፍ ፍቅሩን ለማወቅ እንጸልይ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ፍቅር በፍርድ ቀን ድፍረታችን

1ኛ ዮሐንስ 4: 17
17፤ በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና።

በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል:: ፍቅር በፍርድ ቀን ድፍረታችን ነው? አዎን! ምክንያቱም እዳ እንዲኖርብን የሚፈለገው የፍቅር ብቻ ነው ብዙ ሰተን ያልተመለሰ፤ ከተመለሰልንማ የወደዱንን ነው የወደድነው እርሱንማ ሁሉም ያደርገዋል:: የጠሉንን ስንወድ ግን እዳቸው ለእኛ ነጥብ ሆኖ ይያዛል:: ፍቅር ያሸንፋል ደግሞም የቤት ስራ የለውም:- ማለቴ ጠላት መቶ አንቺን ብሎ ክርስትያን እያለ አያዋክበኝም፤ የሚለውም የለውም ዝም ጭጭ ነው የሚለው፤ ህሊናችንም አይፈርድብንም ከዛም አልፎ ጌታ ደስ ይለዋል መገለጫችን ፍቅር ሲሆን:: በፍቅር እንመላለስ እመኑኝ አንከስርም:: ፍቅር ካለ ጌታ አለ በመካከላችን::

እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና። እርሱን የምናሳይ አምባሳደሮች ነን በዚህ ምድር እርሱ በእኛ ውስጥ እየተመላለሰ እንዳለ እንወቅ ስለዚህ የሚወድ በእኛ አድሮ እርሱ እራሱ ነእ እኛማ ፍቅር ከየት አምጥተን የእርሱ ማንነት ነው ፍቅር! ሁሉን እንውደድ የትናንቱን ለትላንትና እንተው ዛሬ አዲስ ቀን ነውና ዛሬን እንኑር ጠላት በትናንቱ ጠብና ቂም ውስጥ እንዳያጠምቀን እንጠንቀቅ:: በተቻለው መጠን ትላንትና ላይ እንድንኖርና የዛሬውን የእግዚአብሔርን ስራ ቸል እንድንል ነው ፍላጎቱ:: እንንቃ! ዛሬ እኔ በፍቅር እገለጣለሁ እወዳለሁ እንበል እራሳችንን እናሳምን ፍቅር የሌለው እግዚአብሔር አያውቅም ደግሞም አላየውም ነው የሚለው ቃሉ:: አምባሳደሮች ነንና እርሱን በፍቅር እናሳይ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በፍቅር ፍርሃት የለም! ፍርሃት ቅጣት አለው!

1ኛ ዮሐንስ 4:18-19
18፤ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። 19፤ እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።

በፍቅር ውስጥ ፍርሃት የለም:: ለምን? መተማመን ስላለ ነው በአጭሩ መልሱ:: እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። የተሰጠን መንፈስ እራሱ የፍርሃት አይደለም የሀይል ደግሞም የድፍረት ነው እንድንፈራ አያደርገንም በሌላም ስፍራ ላይም አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። ፍርሃት ከባርነት ጋር ነው የሚመጣው ልጅ ውስጥ ግን ይህ የባርነት መንፈስ የለም:: እየሱስ እራሱ ባሪያዎች አልላችሁም ወዳጆች እንጂ ብሎናል:: ፍርሃት ካለ አለመተማመን ነግሷል ማለት ነው:: ስንጸልይ እንኳን ጸሎታችን እራሱ ከፍርሃት መሆን የለበትም:: አሁን ምን ይመጣብኛል ይህና ያ ሊደርስብኝ ነው የምንል መሆን የለብንም እርሱ ወዳጃችን አባታችንም ነውና:: ተማምነን ክፉውን ለበጎ የሚቀይር አባት አለኝ ብለን ልንተማመንበት ይገባል:: ከምስጋና ጋር ነገራችንን በፊቱ እናሳስብ እንጂ በአንዳች አንጨነቅ ከጭንቀት የሚቀጥለው ፍርሃት ነውና:: ፍሩ አላለንም! ተማመኑ እንጂ!

ፍርሃት ግን ቅጣት አለው! ለምን እንፈራለን ሁሉን እኛ መቆጣጠር ስለምንፈልግ አይደል? የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። ልጆችንን ስናይ ወላጅ ወደሚወስዷቸው ቦታ እየቦረቁ ከመሄድ በቀር ከፊቴ ክፉ ሊያደርጉብኝ ነው ወላጆቼ ብለው ሳያስቡ እጃችንን ይዘው ይከተላሉ:: ታድያ እኛ በእግዚአብሔር ላይ አደግንበት? ብልጥ መሆናችን ነው?የምንጠራጠረው ወይም ሁለተኛ አማራጭ የምንይዘው እንደነሃናንያና ሰጲራ ካልተሳካ ነው? አማራጭ?! አረ ጌታን እንተማመነው! እርሱ ስለእኛ ያስባል ልጅ ሆነን ሳለን የባርያ ስነልቦና አንያዝ! በፍቅር ተማምነን ህይወታችንን በእርሱ ላይ ጥለን እንመላለስ:: ማንን እንዳሳፈረ ልናፍር?! የእኛ ጌታ እንደሆነ ፍቅር ነው ማንንም አሳፍሮ አያውቅም እርስ በእርሳችን እንዋደድ ይህ ሲሆን አባት ደስ ይለዋል:: በድፍረት መንፈስ እየደገፈን ነውና በፍቅር እንመላለስ:: ፍርሃትን አውጥተን እንጣል! ፍቅራችንም ፍጹም ይሁን!


እግዚአብሔርን እወዳለሁ፥ እያለ ወንድሙን የሚጠላ፥ ሐሰተኛ ነው

1ኛ ዮሐንስ 4
20፤ ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ፥ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፥ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? 21፤ እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።

እግዚአብሔርን ያየ በፍቅር መሞላቱ የማይቀር ነው ፍቅር ብለን ስንል የማያዳላ፤ ይቅር ባይ፤ የማይቀና፤ የማይቀየም፤ ታጋሽ ፤ ርህሩህ ሌላም ሌላም ያለው ነው:: እንግዲህ እግዚአብሔርን እወዳለሁ ካልን ሰውንም ሁሉ እንወዳለን ማለት ነው:: አንድ ስብእና ነው ሊኖረን የሚገባው እየመረጡ መውደድ ብሎ ነገር የለም ለዚህም ነው ቃሉ ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ፥ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፥ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? የሚለው:: ሐሰተኛ ያሰኛል ፍቅር አለኝ እያሉ ሁሉንም እኩል አለመውደድ:: ፍቅርን የምንተገብርበት ሜዳ ላይ ነንና የክርስቶስ መሆናችንን በዚህ እንግለጥ እርሱ ዓለም በሚባለው ሜዳ ላይ ፈጽሞ አባቱን አክብሮ እንዳለፈ እኛም እናክብረው ፈለጋውን ትቶልን ሄዷል::

እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን። የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ እግዚአብሔርን ውደድ የምትል ስትሆን ሁለተኛይቱ ደግሞ ሌላውን እንደራስህ ውደድ የምትለው ናት:: የመጀሪያው ትእዛዝ ያለው ደግሞ ሁለተኛይቱን መኖር ይችላል:: እናስተውል ትእዛዝ ነው መዋደድ ጌታ ያለንን እናስታውስ ቀንበሬ ቀሊል ነው ብሎን ነበር የእኛን ከባዱን ሐጥያት ወስዶ ፍቅርን ሰጠንና ኑሩበት አለን:: ከፈለግን የምናደርገው ወይም መርጠን የምንሰጠው አይደለም የታዘዝነው ነውና በወንድማማች መዋደድ እንዋደድ:: ወንድሜ ከእኔ ይበልጣል የሚል ልብ እንያዝና ዝቅ ብለን እንውደድ ያለ አድልዖ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል

1ኛ ዮሐንስ 5: 1-5
1፤ ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን። 
ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። 
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 
ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? 

የሚገርመው ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። ወላጃችን ማነው? እግዚአብሔር ነው ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ እኔም አባት እሆናችኃለህር ብሎ አባ አባ የሚልን መንፈስ በውስጣችን ጨመረ:: ሃሌሉያ! እርሱን ከወደድን ልጆቹንም ሁሉ እንድንወድለት ነው የሚፈልገው ልክ እንደማንኛውም ወላጅ:: ልጆቼ የሚለው እነማንን ነው? ክርስቶስ ነው ብለው በኢየሱስ የሚያምኑትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልደዋል ስለዚህ እነዚህን እንውደድለት:: እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን።  ትእዛዛቱ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ነው:: ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። ተዋደዱ ሲለን ጸጋውን ሰቶን ነውና እርስ በእርሳችን እንዋደድ:: አብዝተንም እንፈላለግ!

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ከማሸነፍ በፊት መወለድ ይቀድማል ከዛም በእየሱስ ስራ ላይ ባለው እምነታችን ዓለምን እንድናሸንፍ ተደረግን:: ይህም ከጌታ የተወለደ ዓለምን ማሸነፉ ጥርጥር የለውም ምክንያቱም ዘሩ አለና በእኛ ውስጥ ማንም እንዳይመካ ከስራ አይደለም ማሸነፋችን በእምነት ነው እንጂ! ይህንን ድል ለሰጠን ለጌታችን ክብር ይሁን:: ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? ጥሩ ጥያቄ ምክንያቱም በአንድ ወቅት አሸነፍን ያሉ ሁሉ ተሸንፈዋል ሲፈሩት ኖረው ይዟቸው ሄዷል ሞት! እኛ ግን ሞትንናሲኦልን ድል የነሳ ጌታ በውስጣችን ስላለ ምንም አይነት ኃይል ከድላችን ላይ ንቅንቅ አያደርገንም:: ድሉ ገና ድሮ ላይለወጥ ታትሟል!! የጌታ ስም ይባረክ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም

1ኛ ዮሐንስ 5: 6-12
6፤ በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፡ መንፈስ እውነት ነውና። መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።  የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። 10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።  11 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። 12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። 

መጽሐፉን ስንጀምር እንዳየነው አንዱ ምክንያት ለዚህ ክፍል መጻፍ እየሱስ በአካል አልመጣም የሚል የስህተት ትምህርት ምላሽ ነው:: ስለዚህም የመምጣቱ ምስክርነት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ የጸና እንደሆነና የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፡ መንፈስ እውነት ነውና ነው የሚለን:: አብ ስለ እየሱስ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሎ ከሰማይ መሰከረ፤ መንፈስም መቶ በላዩ ላይ አረፈበት ከዚህ በላይ ምስክር ምን አለ? እየሱስ ውሀም ደምም ፈሶታል እኛን ለማዳን ዋጋ ሲከፍል በእርሱ በቀር ወደ አብ መድረስ የለም::

ሰው ይህንን መስክሯል ግን የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው:- ምስክሩ ማነው ከላይ እንዳየነው ስላሴዎች ይመሰክሩልናል! አለበለዚያ ግን ምስክርነቱን አለመቀበል ቃሉ እንደሚለን በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።  እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ደስ አይልም? እግዚአብሔር የዘላለምን ህይወት ሰጠን! ይህ ህይወት በልጁ ውስጥ ነው ስለዚህ ልጁ ያለው ህይወት አለው ልጁ የሌለው ህይወት የለውም:: ጌታን እያመሰገንን እንዋል ስለሆኑልን መዳን፤ ስለ ዘላለም ህይወት እናም ይህንን በነጻ የተሰጠ ህይወት ለሌሎች እንመስክር:: ዛሬ እግዚአብሔር የሚድኑ ነፍሳትን ወደእኛ ይምራ:: አሜን!


እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል

1ኛ ዮሐንስ 5: 13-15
13፤ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። 14፤ በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። 15፤ የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።

የምስራች! የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። ቀላል አይሁንብን መዳናችን የከበረ ነውና ሁሉን ትቶ እኛን ፍለጋ መቶ ዋጋ በህይወቱ ከፍሎ የራሱ ያደረገንን ጌታን እናመስግን:: ይህ የዘላለም ህይወት እንዲኖረን የእኛ አስተዋጾ በልጁ ማመን ብቻ ነውና ሁሉን ያደረገው እርሱ ነው:: በዚህ ህይወት እርፍ እንበል እኛ ወደ እረፍቱ ገብተናል ገና ለመግባት የምንጥር አይደለንም በመወለድ አግኝተናል እርሱ ነው በመስቀል እኛን ለመውለድ ያማጠው:: ሃሌሉያ!

ታድያ ወደ እረፍቱ የገባ ሰው ጸሎቱ እንዲሰማ ፊቱን መቦጨቅና መንከባለል አይጠበቅበትም:: ገና ልባችንን ወደ እርሱ ስናነሳ እርሱ ከሰማይ ሰምቶናል! ቃሉም እንደሚለን በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። ቅድመ ሁኔታው እንደፈቃዱ ብንለምን ብቻ ነው ይህ ፈቃዱ የሚለው ምንድነው? ፈቃዱማ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ነው ፍቅር ካለ ጸሎታችን ሁሉ ከፍቅር ልብ እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነው የሚሆነው ስለዚህ እንሰማለን:: ስለዚህ የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። ልመናው እንደተሰማለት የሚያምን ማመስገን ይጀምራል:: ሃና ይህንን ነው ያደረገችው በፊቱ አነባች ከዛም በኃላ ሀዘንተኛ ሆና አልታየችም:: የጸሎትዋ መልስ ሳሙኤል ነበረ እሱም ቃሉ ጠብ የማይል የእግዚአብሔር አገልጋይ:: የጸሎት ህይወታችንን እንየው እንደፈቃዱ እንጸልይ ደግሞም እንደተቀበልን እንወቅ እና እናመስግን:: ይሁንልህ ወይም ደግሞ ይቅርብህም መልስ ነውና:: ልመናችሁን ከምስጋና ጋር አድርጉ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ስለሌላው እንማልድ

1ኛ ዮሐንስ 5: 16-17
16፤ ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም። 17፤ ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ።

ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው፤ ምን ሲሆን? ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው እዚህ ላይ ነው እንግዲህ እስከአሁን ድረስ የተነገረን ቃል አገልግሎት ላይ የሚውለው:: እርስ በእርስ ተዋደዱ የሚለው:: እንዴት ብትሉኝ? ኃጢአት ሲያደርግ ወንድማችን ስናይ ለሌላ ሰው ነግረን በእንጸልይለት ሽፋን ሀሜት ውስጥ መግባት የለብንም:: የተባልነው እኛው እንድንጸልይ ነው ካየነው እንጸልይእንጂ አንንቀፍ ጌታ አምኖ የሰውን ጉድለት ሲያሳየን እንሸከም:: ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ እርሱ እንዳለ ሆኖ እርስ በእርሳችን እንድንማልድ ጌታ ሊያስተምረን ፈልጎ ነው ከመማለድ ባለፈ ሰውየው ተመልሶ ከጌታው ጋር አስተካክሎ ሳለ እኛ የማንመለስበት አጋጣሚ ብዙ ነው ጌታ ግን የቱን ኃጥያት ብሎ ከንስሀ በኃላ ረስቶለታል ስለዚህ የጌታን ልብ እንያዝ ጎበዝ! እናም በተግባር የሆነ መዋደድ እንዋደድና እንሸከም ደግሞም ይቅር እንበል የወንድማችንን ገበናን ሸፍነን እንሸከም:: ይህ ወተት ከመጋት ወጥቶ አጥንት መቆርጠም ነው! ጌታም ይህንን ጸሎት ይሰማና ሞት የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል! የሚገርመው ይሰጠዋል ሳይሆን ይሰጥለታል ስለ ጸላዩ ብሎ:: ስንቱን መርዳት እንችል ነበር?!

ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም። ይህ ሞት የሚገባው ኃጥያት ምንድነው? መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ነው ጌታም ነግሮናልና:: ለመንፈስ ቅዱስ እንጠንቀቅ!!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እየሱስ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው

1ኛ ዮሐንስ 5: 18-21
18፤ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን። 19 ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን። 20 የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው። 21 ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ

  1. ኃጢአትን እንዳያደርግ:- ለምን ሐጥያትን አያደርግም? ምክንያቱም ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።
  2. ራሱን እንዲጠብቅ:- ሰው እራሱን እንዴት ይጠብቃል? በአእምሯችን መታደስ እንለወጥ እንጂ ይህንን ዓለም አንምሰል ነው ቃሉ የሚለን:: አእምሯችንም የሚታደሰው በቃሉና በመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ለቃሉ ጊዜ እንስጥ እናመንዥገው አእምሯችን ስራ አይፍታ በቃሉ እንሙላው::
  3. ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን:- ልጅ ነንና እግዚአብሔር ስለሚጠብቀን ክፉ አይነካንም እኛ ለእርሱ ተቀድሰናልና በእኛ እርሱ ይታያል::

የክርስትና እምነታችን በአጭሩ ወይም በአንድ ጥቅስ:-

  1. የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፥
  2. እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤
  3. እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥
  4. እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
  5. እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።

የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ ያወቀ የሚያውቅበትን ልብ የተቀበለው ከጌታ ነው የሚኖረውም እውነት በሆነው በልጁ ውስጥ ነው ዓለም በሞላው በክፉ ቢያዝም እኛ ግን እውነት በሆነው በእየሱስ ውስጥ እየኖርን ነው::

በዚህ 1ዮሐንስ ጥናታችንን ጨርሰናል::
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የማርቆስ ወንጌል

የመጽሐፉ መግቢያ:- ይህ የወንጌል መጽሐፍ ከአራቱ መጽሐፍት አነስ ያሉ ምዕራፎችን የያዘና በተለይም ከአይሁድ ውጪ ያሉ አንባቢዎችንም ታሳቢ ያደረገ መጽሐፍ ነው::  ደራሲው ክፍሉ እንደሚለው ማርቆስ የተባለው በሌላ ስሙም ዮሐንስ የሚባል ነው የፃፈው:: ሐዋ 12:12 ላይ ጼጥሮስ ከእስር እንዳመለጠ ቅዱሳን ተሰብስበው ወደሚፀልዮበት ወደ እርሱ ቤት እንደመጣ ይነግረናል:: ማርቆስ ከጳውሎስም ከጴጥሮስም ጋር ያገለገለ ሰው ነው:: እንዲያውም ይህ መጽሐፍ በጴጥሮስ ስር ሆኖ ነው የፃፈው ይባላል::
ምዕራፍ 1

የማርቆስ ወንጌል 1: 1-8

1፤ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ። 2እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ። የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር። ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል። እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።

ማርቆስ ጌታ እየሱስን የእግዚአብሔር ልጅ ብሎ ይጠራዋል እንደዛውም ነው! አሜን!

በምድረ በዳ ስለሚጮኽ ሰው ድምፅ ይነግረናል ይህም ሰው ከጌታ በፊት የተላከና መንገዱን የሚጠርግ ነበር:: እርሱም ፍፁም ከብሉይ ስርአት ውጪ ነበር የሚሰብክና የማያደርገው:: ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ አይሁድ ለኃጢአት የሚያውቁት መስዋትን ማቅረብ ነበር:: እርሱ ግን ንስሀ ግቡና ተጠመቁ ነበር የሚላቸው ለመቀበል አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳን የዮሐንስን አወላለድና ህይወቱን ስለሚያውቁ ብዙዎች መተው ይጠመቁና ለሚመጣው ጌታ ይዘጋጁ ነበር:: በብሉይ ኪዳን አምልኮ እኮ የሚካሄደው በቤተ መቅደስ ነበር:: የሐጥያትም ስርየት ደም ሳይፈስ ስርየት እንደሌለ እያወቁ ግን ይሰሙትና የሚላቸውን ያደርጉ ነበር:: ዛሬም በህይወታችን ጌታ የላከንን በማድረግ ለተፈጠርንለት ስራ እንትጋ አንታክት:: ዮሐንስ ህይወት ከተለመደው ለየት ያለ ነው የግመል ጠጉር ይለብስና ወገቡንም በጠፍር ይታጠቅ ነበር:: አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር። ምንም አይነት ትስስር የለውም ነበር ከዓለም ጋር ምኑንም ይዘው ሊያስፈራሩት የማይችሉት ነበር:: ስለዚህም ይፈሩት ነበር::

ስለእየሱስም ሲናገር እያጎላ ይናገር ነበር እንጂ በምንም አይነት ክብርን ለራሱ አይወስድም ነበር:: ስለ ኢየሱስ ይል የነበረውም ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል:: እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር። ዛሬ ለዚህ ቃል እኛ ምስክሮች ነን::


ኢየሱስ ተጠመቀ

የማርቆስ ወንጌል 1: 9-13
9፤ በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። 10፤ ወዲያውም ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና፦ 11፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል፡ የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ። 12፤ ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው። 13፤ በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ ከአራዊትም ጋር ነበረ፥ መላእክቱም አገለገሉት። ጌታ ኢየሱስ ሲጠመቅ ሰማያትም ሲቀደዱ ታየ የኢሲይያስም ፀሎት ተመለሰ ኢሳይያስ 64: 1፤ ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! የሚለው:: አብም ስለእርሱ በድምፅ ከሰማያት ተናገረ:- የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል፡ የሚል:: እግዚአብሔር አብ በልጁ ደስ ተሰኝቷል ምክንያቱም የሰውን ልጅ ለመታደግ ታዞ ወደምድር መቷልና:: መንፈስም ወደምድረ በዳ እንደወሰደው እናያለን:: ከፍታ ላይ ነው ኢየሱስ ስለእርሱ አብ መስክሮለት ደስ ብሎት እያለ ፈተና መጣ:: ጠላት ደስታንና ከፍታን ሲያይ ሊጥል ይመጣል የተዘጋጀንና የነቃን በቃሉ የተመሰረትን ልንሆን ይገባል:: በፈተና ውስጥ ሆኖ ከአራዊት ጋር እንጂ ሰው እንኳን አብሮት አልነበረም መላእክት ግን አገለገሉት:: ይህ ሁሉ እኔን ለመታደግ ነው ያደረገው:: ስሙ ይባረክ!


የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች

የማርቆስ ወንጌል 1 : 14-15
14-15፤ ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፦ ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሐ ግቡ፡ በወንጌልም እመኑ፡ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።

ዮሐንስ ተላልፎ ከተሰጠ በኃላ እንደገደሉት እናውቃለን:: አገልግሎቱን ጨርሶ ሄደ እየሱስም አገልግሎቱን ቀጠለ:: እየሱስ ምን ሰበከ ወይም ምን ላይ አተኮረ ብለን ስንል የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከ እንደነበረ እናያለን እኛም በዚህ መሰረት ነው ወንጌልን ማድረስ ያለብን:-

  1. ዘመኑ ተፈጸመ – የዘመኑን መፈፀም ሁሉም ሰው በደንብ ያወቀበት ጊዜ ላይ ነን በዚህ ረገድ ምንም ጥያቄ የለም::
  2. የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች፤ ወደእኛ አምላካችን ከምን ጊዜውም በላይ ቀርቧል ብለን ስንል ልጁን ከመላክ በላይ መቅረብ ምን አለ?
  3. ንስሐ ግቡ፡ ትልቁ መልእክት ንስሀ ግቡ እንታረቅ እያለ ያለው እራሱ የተበደለው እግዚአብሔር መሆኑ ይገርማል
  4. በወንጌልም እመኑ :- በልጁ ሞትና ትንሳኤ እመኑ ብሎ በሩን ከፍቶ እየጠበቀ ነው መምጣቱንም ያዘገየው ሰዎች ሁሉ ይድኑና ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ ነው የታገሰውና መምጣቱን እያዘገየ ያለው::

እየሱስ ዛሬ ይህንን አገልግሎት ለእኛ ሰቶንና ሾሞን ሄዶ መንፈስ ቅዱስን ልኮልናል:: ከዚህ ውጪ ምንም መስበክ የለብንም:: ዘመኑ ተፈፀመ የሚባልበት ዘመን ላይ ነን እናም መንግስቱን እንስበክ:: ማራናታ!


ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ

የማርቆስ ወንጌል 1: 16-20
16፤ በገሊላ ባሕርም አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። 17 ኢየሱስም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው።  18 ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። 19 ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ደግሞ በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አየ። 20 ወዲያውም ጠራቸው አባታቸውንም ዘብዴዎስን ከሞያተኞቹ ጋር በታንኳ ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ። 

ጌታ እየሱስ ደቀመዝሙሮችን ሲጠራ እናያለን የተጠሩትንም አንድ የስራ ኃላፊነት ነበር የሰጣቸው ሰውን አጥማጅ መሆን የሚል:: የተጠሩትም: – ወንድማማቾቹን ስምዖንና እንድርያስን እንዲሁም ሌሎቹ ወንድማማቾች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ:: እነዚህ ሶስቱ መሪዎች የሆኑና ክብሩንም ያሳያቸው ናቸው:: የሚገርመው ሲጠራቸው ብድግ ብለው ሁሉን ትተው ተከተሉት እንጂ ጥያቄ እንኳን አልጠየቁም:: እኛስ ዛሬ ለጌታ ጥሪ ምላሻችን እንዴት ይሆን? እኛም ዛሬ ለክርስቶስ ሰውን የምናጠምድና ከጌታ ጋር ታረቁ ልንልየተጠራን ነን! ከኃላው እንከተለው:: ጌታ ፀጋውን ያብዛልን!



እየሱስ የእግዚአብሔር ቅዱሱ

የማርቆስ ወንጌል 1: 21-28
21፤ ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ። 22 እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ። 23 በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤  24 እርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ። 25 ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። 26 ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ። 27 ሁሉም። ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። 28 ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ። 

ወድያውም ጊዜ ሳያጠድፋ ወደ ምኩራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ የሚያስተምር የነበረውም እንደ ባለ ስልጣን ነበርና ሰሚዎቹ ተገረሙ ይለናል:: እየሱስ በስልጣን ቢያስተምር የማይደንቀው ምክንያት ቃሉን የሰጠው ለሙሴና ለነብያቱ እርሱ ነበረና ነው:: በዛም የነበረ እርኩስ መንፈስ እየሱስን ማን እንደሆንክ አውቃለሁ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ እርሱም አስወጣው:: በዛም የነበሩት ይህ ምንድነው መናፍስት የሚታዘዙለት ብለው አደነቁ:: አላወቁም እንጂ በመካከላቸው የቆመው የጌቶች ጌታና የነገስታት ንጉስ ነው:: የእየሱስ ዝና በየስፍራው ሁሉ ወጣ ይላል በዛ በአንድ ሰው ነፃ መውጣት:: ስለዚህ ዛሬም ይህ ጌታ በእስራት ያሉትን በእኛ ውስጥ ሆኖ ሰርቶ ነፃ ማውጣት ይፈልጋል:: የልጅነት ስልጣን ተሰቶናል እኛም ይህንን ስልጣን ልንለማመድ ይገባል ስሙን ሰቶናል በስሙ ደግሞ አጋንንት ይወጣል:: እየሱስ ከስም ሁሉ በላይ ስም አለው ስሙም በላይ በሰማይ በምድር ከምድር በታች ያሉ ሁሉ ይንበረከካል:: እርሱ ሁሌም ይሰራል:: አባቴ ሁሌ ይሰራል እኔም እሰራለሁ ብሎናልና በእኛም ውስጥ መንፈሱን ልኳል ይሰራል::


ብዙዎችን ፈወሰ አጋንንትንም አወጣ

የማርቆስ ወንጌል 1:29-34
29፤ ወዲያውም ከምኵራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገባ። 30 የስምዖንም አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ነገሩት። 31 ቀርቦም እጅዋን ይዞ አስነሣት ንዳዱም ወዲያው ለቀቃትና አገለገለቻቸው። 32 ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ 33 ከተማይቱም ሁላ በደጅ ተሰብስባ ነበር። 34 በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፥ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፥ አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም። 

የስምዖን አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ለእየሱስ ነገሩት ይላል ክፍሉ ነገሩት የሚለው አሳብ እኮ ዛሬ እኛ ፀሎት የምንለው ነው:: ፀሎት ማለት ደግሞ መናገርና ተማምኖ እንደሰማን አውቀን መጠበቅ ነው:. እነዚህ ሰዎች ነገሩት እሱም ወደ እርስዋ ሄዶ እጅዋን ይዞ አስነሳት ንዳዱም ለቀቃት:: ዛሬ የምንፀልየውን ፀሎት እንደሰማን አምነን ማመስገን እንጂ የማናምን መሆን የለብንም እንደተሰማን ማወቅ አለብን ጌታ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎን የለም እንዴ? የምናምን እንሁን እንጂ የማናምን አማኝ አንሁን::

ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ:: ለምን ብለን ያልን እንደሆነ ሲፈውስና አጋንንትን ሲያወጣ አይተዋል ደግሞም ሰምተዋል:: ለእኛም ያደርግልናል ብለው አምነው በሽተኞችን ይዘው መጡ:: እምነታቸው የመጣው ከመስማትና ከማየት ነው:: ተአምራት ሲደረግ ማየት እንኳን ባንችል ከቃሉ ዛሬ እይኸው እየሰማን ነው እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል እንጂ እምነትን ከየትም አናመጣም ቃሉ ወደ እኛ መጥቶ በእምነት መዋሀድ አለበት:: እርሱም በሽተኞችን ፈወሰ አጋንንትንም አወጣ:: ዛሬም ይሰራል ይህ ጌታ ይፈውሳል አጋንንትንም በእኛ ሆኖ ያወጣል:: ማንንም አንጠብቅ እንጣራ ይሰማል ከሰው ሰው አይለይም ጌታ ቅርብ ነው በነገር ሁሉ ይሰማናል ይረዳናል::


ማለዳም ተነሥቶ ጸለየ

የማርቆስ ወንጌል 1: 35-39
35፤ ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ። 36 ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩትም ገሥግሠው ተከተሉት፥ 37 ባገኙትም ጊዜ። ሁሉ ይፈልጉሃል አሉት። 38 እርሱም። በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና አላቸው። 39 በምኵራባቸውም እየሰበከ አጋንንትንም እያወጣ ወደ ገሊላ ሁሉ መጣ። 

ከእየሱስ የምንማረው ነገር በዚህ ክፍል ላይ ጸሎትን ነው:: ማለዳ ተነስቶ ማንም ወደማይረብሸው ቦታ ሄዶ ይጸልይ ነበር:: ሐዋርያት ግን መተው ሁሉ ይፈልጉሀል አሉት እንጂ ከአንተ ጋር በጸሎት እንትጋ ሲሉ አናይም ብቻ ናና ተአምርን አድርግ እንጂ ነው ጥያቄያቸው ተአምራት የሚሆነው እኛ ከጌታ ጋር ጊዜ ስናሳልፍ ነው ደግሞም ተአምራትን ለማድረግ አይደለም ፊቱን የምንፈልገው ፍቅሩ ግድ ብሎን እንጂ! ሁሉ የፈለጉት ምክንያት ጌትነቱ ገብቷቸው ሊከተሉት ሳይሆን የጎደላቸውን እንዲሞላላቸው ብቻ ነበረ ነገር ግን እኛ ዛሬ የምንፈልገው ለምን ይሆን? የህይወታችን ጌታና ንጉስ መሆኑን አውቀን በፊቱ ልንገዛ መሆን አለበት ወደ እርሱ የምንመጣው:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!!


እየሱስ ለምጻሙን አንፃ

የማርቆስ ወንጌል 1:40-45
40፤ ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ ተንበረከከና፦ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፥ ብሎ ለመነው። 41 ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው። 42 በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀውና ነጻ። 43 በብርቱም ተናግሮ ወዲያው አወጣው፤ 44 ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ አለው። 45 እርሱ ግን ሲወጣ ብዙ ሊሰብክና ነገሩን ሊያወራ ጀመረ፥ ስለዚህም ኢየሱስ ተገልጦ ወደ ከተማ መግባት ወደ ፊት ተሳነው፥ ነገር ግን በውጭ በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ከየስፍራውም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

ይህ ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ መጀመሪያ ያደረገው ነገር መንበርከክና አምልኮን መስጠት ነበር፦ ከዛም ጥያቄውን ማቅረብ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፥ ብሎ እርግጠኛ የሆነበትን ነገር ጠየቀ ብትወድ ችግር የለብህም ትችላለህ በአንተ ዘንድ ጥያቄ የለም ብሎ ለመነው። ጌታ ኢየሱስም አዘነለት ይላል በጣም ይገርማል በዛች ቅፅበት ህይወቱን ሁሉ ማየትና ያለበትን ነገር ተረዳው እናም እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው። ጌታ ያውቀናል ያሳለፍነውንና ያለንበትን ነገር ደግሞም የሚራራ እንጂ የሚጨክን ጌታ አይደለም ጌታችን:: ተናገረው ለምፁም ሰምቶ ለቆ ሄደ እንዴት ድንቅ አምላክ ነው የምናመልከው? ስሙ ይባረክ! ምንም አይነት ህመም ቢሆን ጌታ ይፈውሳል!

ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ የተባለው ሰው ወጥቶ ወሬውን በሰፊው አወራ ውጤቱም እየሱስ ወደ ከተማዋ መግባትም እንዳይችልና በምድረ በዳ እንዲያገለግል አደረገው:: ስውየው የተባለው ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ ነበረ። የተባልነውን ቢገባንም ባይገባንም እናድርግ::


ምዕራፍ 2

እየሱስ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን አለው

የማርቆስ ወንጌል 2: 1-12
1፤ ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ። በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር። አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት። ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ።  ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም። ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል?  ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው አሰቡ።  ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው። በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ? ሽባውን። ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? 10 ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤ 11 ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። 12 ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፥ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና። እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ። 

እየሱስ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው ሲያስተምር እዚህ ክፍል ላይ እናያለን:: ይህንን ሽባ ሰው ያለው ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ነው:: ይህን በማለቱ ግን በዛ ስፍራ የነበሩ ጻፎች በልባቸው ያሰቡትን አውቆ ነበር መልስን የሰጠው በጊዜው የእግዚአብሔር ቤት አገልጋዮች ናቸው ግን እየሱስ ለሚለው ነገር እንግዳ ናቸው ወይ ጠይቀው አልተማሩ ወይ አንብበው ተዘጋጅተው አልጠበቁ:: መጽሐፍት ሁሉ ስለእኔ ይናገራሉ ብሎ ያውቃልና ጌታ:; ዛሬ ስናገለግለው ከሁሉ በላይ የሆነውን ጌታን እንወቅ እርሱንም በቃሉ ውስጥ እናገኘዋለን::

የሚገርመው ግን ሰውየው የተፈወሰው ጣርያውን ነድለው ባወረዱት ወዳጆቹ እምነት ነው:: እየሱስም ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ:: ሃሌሉያ! የጌታ ነገር ሁሉ ያጠነጠነው ሰዎችን ነፃ ማውጣት ላይ ነው:: እኛም ዛሬ የቤተክርስቲያንን ህግ ለመታዘዝ የእግዚአብሔርን ቃል እንዳንጠመዝዝ እንጠንቀቅ የጌታ አይን ባለበት ላይ እርሱም ሰው ላይ ይሁን አይናችን:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!


ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም

የማርቆስ ወንጌል 2: 13-17
13፤ ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። 14 ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው። 15 በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ ይከተሉትም ነበር። 16 ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ። ከቀራ ጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው? አሉ። 17 ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው። 

እዚህ ክፍል ላይ አምስተኛው ደቀ መዝሙር ማቲዎስ በሌላ ስሙ ሌዊ ሲጠራ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ ሲከተለው እናያለን:: እርሱም ቀራጭ ነበረና በቤቱ በመአድ ሲቀመጡ የተሰበሰቡት ሁሉ እርሱን የሚመስሉ ሐጥያተኞች ስለነበሩ ሀይማኖተኞቹን አስቆጣ:: ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።  እንደዛማ ባይሆን የት ነበርን ዛሬ? እያንዳንዳችን ሐጥያተኞችና ሞት የሚገባን ነበርን በቸርነቱ ይቅር ብሎ ቀድሶ የራሱ ባያደርገን ኖሮ:: ስለዚህ ዛሬ ብዙ ይቅር የተባልን ነንና ጌታን በብዙ እንወዳለን ደግሞም ሰዎችን ታግሰን ወደ ጌታ እናመጣለን በማንም አንፈርድም የባስን ስለነበርን::


የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው

የማርቆስ ወንጌል 2: 18-28
18፤ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም፦ የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት። 19 ኢየሱስም አላቸው። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም። 20 ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ። 21 በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። 22 በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ። 23 በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። 24 ፈሪሳውያንም። እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት። 25 እርሱም። ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ 26 ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። 27 ደግሞ። ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ 28 እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።

ሰዎች እየሱስን ስለምን እንደዚህና እንደዚያ ያደርጋሉ ወይም አያደርጉም ተብሎ ስለ ደቀመዝሙርቱ ጥያቄ ሲቀርብለት እናያለን:: አንዱ ጥያቄ አይጾሙም ሲሆን ሌላው ደግሞ ህግን አይጠብቁም በሰንበት እህል ቀጥፈው በሉ ነበር:: ያልገባቸው ጉዳይ እየሱስ ስርነቀል ለውጥ ሊያደርግ መምጣቱን ነው:: እኛም እንኳን የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች ሆነን በአንዳንዱ ጉዳይ ስናነክስ እንታያለን:: በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ ለማድረግ ስንጥር እንታያለን:: እኛ በክርስቶስ አዲስ ነን አዲስ ኪዳንን የተቀበልን እንደሆንን እንወቅ እንጂ ዳግመኛ ወደ ተተወ ኪዳን አናመዝንና በስራ ለመጽደቅ ጽድቃችንንም ለማቆም አንጣር::

ሰንበት ለእኛ እንጂ እኛ ለሰንበት አይደለንምና እኛ ወደ እረፍት የገባን ሰዎች ነን:: የሰውን ህግ ከመጠበቅ ይልቅ ጌታን ለማወቅና እርሱን ለመታዘዝ እንትጋ:: ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው ልንፈራ የሚገባን ጌታን ብቻ ነው::


ምዕራፍ 3

እጁ የሰለለችውንም ሰው ፈወሰ

የማርቆስ ወንጌል 3: 1-6
1፤ ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፥ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ ሊከሱትም፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። 
እጁ የሰለለችውንም ሰው። ተነሥተህ ወደ መካከል ና አለው። በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ። ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፥ ሰውየውንም። እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እጁም ዳነች። ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ከሄሮድስ ወገን ጋር ተማከሩበት። 

ሰንበት ለሰው እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም ብሏችው ነበር ወደ ምኩራብ የገባው ነገር ግን እዛም ምን ሊያደርግ እንደሆነ ይጠባበቁት ነበር :: እርሱም ጠየቃቸው በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ እርሱም የሰውየውን እጅ ፈወሰው:: በፈውሱ በመደሰትና ነፃ ስለወጣው ሰው ስለማመስገን ፋንታ እንዴት እንደሚያጠፉት ነበር የተማከሩት:: ዛሬም ልባችንን ልንጠብቅና ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይለን ዘንድ እናመሰግን ዘንድ ነው የሚገባው:: እየሱስ አይኑ ሁሉ በሰዎች ላይ ነው እኛም ዛሬ ህግና ስርአት ባህልና ዘር ከሚል መጠላለፍ ወተን የጌታን አሳብ እናገልግል እርሱም በአምሳሉ የፈጠረውን ሰውን ነፃ ማእጣት:: ከዚህ ክፍል ላይ ስለእየሱስ ባህሪ የተማርኩት ታጋሽነቱን (ለተቃዋሚዎቹ) ርህራሄውን (ለታመመው ሰው) ነው::


ብዙ ሕዝብ ተሰበሰቡ

የማርቆስ ወንጌል 3: 7-12
7፤ ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገው ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ 10 ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። 11 ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ።  12 እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው። 

እዚህ ክፍል ላይ ከተለያየ ስፍራ ሰዎች ተሰብስበዋል ከአካባቢው አገር ሳይቀር ዝናው ወቶ ነበር:: አብዛኛው የመጣው ችግሩ እንዲፈታለት ሌላው ደግሞ ዝናውን ሰምቶ ለማየት ነው:: እርሱም ሁልጊዜ ሁለት ነገሮችን ያደርጋል በመጀመሪያ ያስተምራል ከዛም ይፈውሳቸዋል:: አጋንንትም ሲያዩት ወድቀው እየሰገዱ ይወጣሉ እርሱም እንዳይገልጡት ያዛቸዋል ምክንያቱም አጋንንት አይደለም እርሱን መግለጥ ያለበት እርሱ በራሱ ጊዜ ለሚፈልጋቸው ይገልጥ ነበርና:: የአጋንንት ምስክርነት አያስፈልገውም:: እዚህ ክፍል ላይ ያየሁት የእየሱስ ባህሪ አለመሰልቸቱን አይቻለሁ ስቃያቸውን አይቶ ችላ አይልም ነበር::


የሐዋርያት ሹመት

የማርቆስ ወንጌል 3: 13-19
13፤ ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። 14 ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ 15 ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤16 ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ 17 የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ 18 እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ 19 አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን። 

ጌታ እየሱስ ወደ ተራራ የሚሄደው ለመጸለይ ጊዜ ከአባቱ ጋር ለማሳለፍ ነው:: እዚህ ጋር ስንመለክት እጸሎት ስፍራው ላይ አገልጋዮችን መርጦ ይዞ ሲሄድ እናያለን:: የተጠሩትን አገልጋዮች የስራ ድርሻቸው እንይ:-

  1. ከእርሱም ጋር እንዲኖሩ – የአገልግሎት መጀመሪያ ከእርሱ ጋር መኖር ነው
  2. ለመስበክ እንዲልካቸው – ከእርሱ ጋር ስንኖር ስለ እርሱና ስለ መንግስቱ መስበክ እንችላለን:: ያየነውንና የሰማነውን እንሰብካለን
  3. ድውዮችንም ሊፈውሱ – ጌታ ሁልጊዜ ለተጨነቁት ሲራራና ሲፈውስ እናያለን ይህም ህዝቡን ነፃ የማውጣት ስራ በቤቱ እንዲሰራና ህዝቡ እረፍትን እንዲያገኝ ይፈልጋል::
  4. አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ – ያለ ስልጣን አጋንንት አይወጣም
  5. አሥራ ሁለት አደረገ – ስንት መሆን እንዳለባቸው ወስኗል

ዛሬም ከእርሱ ጋር ለመኖርና ጊዜያችንን በፀሎት ለማሳለፍ እንነሳሳ ደግሞም እናዘውትር:: ዛሬ በቤተክርስቲያን የሚያገለግሉትን በቁጥር ፀጋን ሞልቶ የሚሰጥ ጌታ እራሱ ነው:: እዚህ ክፍልላይ ያየሁት የጌታ ባህርይ መፀለይን ማዘውተሩን ነው::


በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ አይሰረይለትም

የማርቆስ ወንጌል 3: 20-30
20፤ ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። 21 ዘመዶቹም ሰምተው። አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ። 22 ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም። ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። 23 እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው። ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? 24 መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ 25 ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። 26 ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። 27 ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። 28 እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ 29 በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም። 30 ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና። 

ሐዋርያት እንጀራ መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ይሰበሰብ ነበር ሁሉ እየሱስን ይፈልጉ ነበርና ከመከራቸው ለመላቀቅ:: ዛሬም እየሱስ ይፈለጋል ብዙ ሰው በእንቆቅልሽ ውስጥ ነው ያለው:: ይህንን ሁሉ ድንቅ ሲያደርግ ሲያዩት አዲስ ነገር ነውና በብሉይ ኪዳን በተለይ ሐጥያትን ማስተሰረይ ይህ የሚሆነው በአጋንንት አለቃ ነው ብለው ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ተሳደቡ::

ስለዚህም ጌታ እየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም ብሎ አላቸው:: የሚገርመው ቤተሰቦቹ ሳይቀሩ አብዷል አሉ ምክንያቱም ከኢየሩሳሌም የመጡ ጻፎች ነበሩና በዛ ስፍራ እየሱስ በሚያደርገው ነገር ደስተኞች እንደማይሆኑና ሊያጠፉት እንደሚነሳሱ በደንብ ነቅተዋል:: በእኛም ህብረተሰብ ትልቁን ቅጣት የሚቀጡት የመቀበርያ ስፍራ አታገኝምና ከእድር እናስወጣለን አይደል ትልልቁን ሰው አስሮ የያዘው? እንደዚሁ በእስራኤት ያልተገደለው የትኛው ነብይ ነው? ሁሉንም ገድለዋል አሁን ደግሞ ልጁን:; እነሱ ግን ለእግዚአብሔር የቀኑ ነው የሚመስላቸው ዛሬም በዘመናችን የክርስቶስን ተከታዮች በማሳደድ ላይ ያሉ አሉ ከጥንትም ያለ ደግሞም የሚኖር ነው ይህንን የሚያደርገው የዚህ ዓለም ግዢ እንደሆነ የታወቀ ነው:: ይህንን ገዢ ሐይለኛ ተብሎ የተገለፀውን አስረን የያዘውን ሁሉ መበዝበዝ በስሙ ማለትም በእየሱስ ስም ለእኛ ተሰቶናልና የያዘውን ሁሉ እናስጥላለን:: በስሙ ውስጥ ሐይል አለ:: አሜን!

ዛሬም ጌታን ለማገልገል እንነሳ እኔን ላከኝ እንበለው:: ቅዱሱንም መንፈስ እናክብር::


የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ

የማርቆስ ወንጌል 3: 31-35
31፤ እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። 32 ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና። እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። 33 መልሶም። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። 34 በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና። እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። 35 የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።

ቤተሰቦቹ ልከው ሲያስጠሩት እናያለን እዚህ ክፍል ላይ:: ከላይም ደግሞ እንዳየነው ዘመዶቹ አብዷል ብለው ነበርና ስላልሰማቸው እንደገና እናቱና ወንድሞቹ ደግሞ እየሞከሩ ነው ሊያስቆሙት:: እሱም ያንን ስለሚያውቅ አልወጣም ነገር ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእርሱ ቤተሰብ እንደሆነ መሰከረ:: በሌላ ስፍራም ቃሉ እንደሚለን በማቴ 7: 21፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። እንዲሁም ደግሞ በ1ኛ ዮሐንስ 2: 17፤ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። በአባታችንም ጸሎት ሲያስተምረን ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን የሚል ነው::

ዛሬ የማንንም ፈቃድ ሳይሆን የጌታን ፈቃድ እንፈጽም እርሱንም ደስ እናሰኝ:: ከጌታ የተማርነው ይህንን ነው መከራው እያስፈራው ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ ግን የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን ብሎ እራሱን ስለ እኛ እንደሰጠ እናውቃለንና ፈቃዱን ከመታዘዝ ወደኃላ እንዳላለ እኛም አንልም:: የጌታ ጸጋ ያግዘን!

ያየሁት የጌታ ባህሪይ በዚህ ክፍል ላይ ቆራጥነትን ነው::


መልካም መሬት

የማርቆስ ወንጌል 4: 1-20
1፤ ደግሞም በባሕር ዳር ሊያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በታንኳ ገብቶ በባሕር ላይ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕር ዳር በምድር ላይ ነበሩ። በምሳሌም ብዙ ያስተምራቸው ነበር፥ በትምህርቱም አላቸው። ስሙ። – እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤  ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ። 10 ብቻውንም በሆነ ጊዜ፥ በዙሪያው የነበሩት ከአሥራ ሁለቱ ጋር ስለ ምሳሌው ጠየቁት። 11 12 እንዲህም አላቸው። ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን፥ አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፥ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፥ እንዳይመለሱ ኃጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል። 13 አላቸውም። ይህን ምሳሌ አታውቁምን? እንዴትስ ምሳሌዎቹን ሁሉ ታውቃላችሁ? 14 ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው:: 15 በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል። 16 እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ 17 ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። 18 በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ 19 የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። 20 በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።

ይህ ምሳሌ ስለ ቃል አቀባበላችን በሰፊው የሚነግረን ስፍራ ነው ሰው በህይወቱ እንዴት አደገ ወይም ለምን አላደገም የሚለውን በደንብ ይመልሳል:: አራት አይነት የቃል አቀባበል አለና መንገድ ዳር፥ ጭንጫ፥ በእሾክ መካከልና መልካም መሬት ናቸው:: ቃሉ ነው ህይወታችንን የሚያሳድገእንይ የሚቀይረው እንጂ ሌላ ማጂክየለውም በህይወት ለመለወጥና ለማደግ::

  1. መንገድ ዳር – ህይወቱ በጣም በቀላሉ በጠላት የሚጠቃ ነው ሲጀምር መንገድ ዳር ምን ያደርጋል በጌታ አልረካም ማለት ነው የተሻለ ሌላ አለ ወይም ደግሞ ለዚህ ህይወቴን አላንበረክክም የሚል ማንነት ነው
  2. ጭንጫ – እነዚህ ሰዎች አስመሳዮች ናቸው የጌታንም የዓለምን ይፈልጋሉና
  3. በእሾክ መካከል – ይሞክራሉ ይጥራሉ ግን ይሸነፋሉ:: ምክንያቱም የጌታ ፍቅር አልገባቸውምና በዓለም ፍቅር ተይዘዋል ስለዚህም ድካምን ለመሸፈን ግድ የለም ይህንን ባደርግ ወይም ምን አለበት ይህንን ባደርግ ያበዛሉ:: አንዳንዴም ወገባቸውን ገትረው ብንዘፍን ምን ችግር አለው? ብለው ዓለምን በግልፅ ወደ ቤተክርስቲያን ሊጋብዙ ይጥራሉ:: የክርስቶስ ፍቅር ሲገባን ግን ሁሉን ትተን እንከተላለን::
  4. መልካም መሬት – የሚያፈራ መሬት ነው እድገቱ የተጠበቀ ነው:: ቃሉ ይመጣል ያብባል ፍሬውም በህይወት ይታያል ይህ ህይወት ከትክክለኛ መለወጥ በኃላ የሚመጣ ነው:; ሰው በክርስቶስ ፍቅር ሲሸነፍ ምልክቱ መለወጥ መጀመሩና ያለ ምንም ማስመስል እርሱን ወደ መምሰል መምጣቱ ነው::

አናስመስል ይልቁንስ ወደ ጌታ መተን ይህንን መሬት እመስላለሁና ለውጠኝ ውጤትን ያመጣል ምክንይቱም ጌታ ፀሎትን ይሰማልና:; የጌታ ፀጋ ይርዳን! አሜን!


በብርሃን እንመላለስ

የማርቆስ ወንጌል 4: 21-25
21፤ እንዲህም አላቸው፦ መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? 22 እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም። 23 የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። 24 አላቸውም። ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል። 25 ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 

መብራትን ስናስብ ለራሱ የተፈጠረ አይደለም ለሌላ መጠቀሚያ እንጂ በርቶ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሌላውን እንዲረዳ ካልተቀመጠ ምንም ዋጋ የለውም:: እንደዚሁም የእኛ ህይወት ለዓለም ብርሀን እንደሆነ እናውቃለን:: ቃሉ እንደሚል ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ የተጠራነውም በውስጣችን የበራውን ብርሃን ክርስቶስን ልናብለጨልጭ ነው እንጂ እርሱ ካላበራና ካልታየ የእኛ በምድር መቆየት እምኑ ላይ ነው? ብርሃኑን በእኛ ውስጥ ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና ተነስተን በከፍታ ላይ ማብራት አለንብ:: ህይወታችን የሚኮንን ጨለማን የሚገልጥና የሚያሳይ ከጨለማ ጋር የማይተባበር ወደ ብርሃን የሚጋብዝ ተደርጎ ተፈጥሯል:: እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ እኛ አዲስ ፍጥረት ነን አሮጌው ሁሉ አልፏል:: አሜን ሃሌሉያ!

ዛሬ የምንሰማው ምንድነው? ከየትስ እየሰማን ነው? የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። አለ እየሱስ። ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ ብሎም አክሏል ምክንያቱም በቃሉ ላይ በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ ሌላውን አይሰሙም ይላል መስማት ያለብን ከከበረው ቃሉ መከተልም ያለብን እረኛችንን ነው:: በእኛ ተማምኖ ሌላውን አይሰሙም ይላል እንጠንቀቅ መስማት ያለብንን እንለይ ሁሉንም አግበስብሰን እንዳንቸገር መገኘት በሌለብን ስፍራ አንገኝ መለየት ካለብን ትስስር እንለይ እርሱን ከሚመስሉ ጋር ህብረትን እናድርግ ቃሉን እናጥና በጸሎትም እንትጋ:: ከቅዱሳን ጋር አብዝትን እንተያይ ዘመኑ ሲያልቅ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ ቃሉ ይነግረናልና አብዝተን ህብረትን እንፈልግ በዛ ውስጥ መታነጽ አለና:: ቃሉ በእኛ ዘንድ ሲኖር እየበዛ ይሄዳል አለበለዚያ ያው ያለውም ይለቀምና ይሟጠጣል ሁልጊዜ በቃሉ ካልተሞላን:: ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል። እንበርታ ጌታ መልካም ነውና:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የቃሉ ዘር በራሱ ያድጋል

የማርቆስ ወንጌል 4: 26-29
26፤ እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ 27፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። 28፤ ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። 29፤ ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።

የእግዚአብሔርን መንግስት በገበሬ ይመስለዋል:: ገበሬውም ዘርን ይዘራል ለሊትና ቀን ሳይል ማደግ ይጀምራል:: ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ሲሆን መሬቱ ደግሞ ቤተክርስቲያን ናት:: ሲደርስ ደግሞ የሚያጭዱት መላእክት ናቸው:: የሚገርመው ዘሩ አውቆ ማደጉ ነው:: በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። ይህ የሚሆነው ያለውሀና የፀሓይ ብርሀን እንዳይደለ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን እጅ እናያለን በዚህ ረቂቅ ስራው ውስጥ:: ስለዚህ እዚህ ጋር መጠየቅ የምፈልገው ዘሩም ሆነ ምድሩ የማን ነው ነው? ሁሉም የጌታ ነው ስለዚህ ቤተክርስቲያን አትሸነፍም ታድጋለች ደግሞም ታፈራለች:: አትጠወልግም!አትረግፍም! ጌታ ሁልጊዜ ይሰራል! የቤተክርስቲያን ራስ እየሱስ ነው:: በቃሉ እንሞላ! ቃሉ በእኛ ውስጥ ያድጋል:: ቃሉ ለእኛ የጦር እቃችን ነውና:: ጳውሎስ ተከለ አጵሎስ አጠጣ የሚያሳድግ ግን እግዚአብሔር ነው::


የእግዚአብሔር መንግስት ሰናፍጭ ቅንጣት ናት

የማርቆስ ወንጌል 4: 30-34
30፤ እርሱም አለ፦ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? 31 እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥  32 የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች።  33 መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፥  34 ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር። 

ሰናፍጭ ከዘር ሁሉ ትንሽ ነች ነገርግን ስታድግ ሁሉን ትበልጣለች:: የእግዚአብሔርም መንግስት ሁልጊዜ ሲጀመር ከትንሽ ይሆንና አገሩን ይሞላል:: እየሱስ የመረጠው አስራ ሁለት ሐዋርያትን ነበር ዛሬ ከሁሉም ወገንና ቋንቋ በዓለም ሁሉ ወንጌል እየተዳረስ ይገኛል:: ለዚህም ነው ጅማሬህ ታናሽ ቢሆን ፍጻሜህ ትልቅ ይሆናል ይለናል::


ስንጠፋ አይገድህምን?

የማርቆስ ወንጌል 4: 35-41
35፤ በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ፦ ወደ ማዶ እንሻገር፡ አላቸው። 36 ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። 37 ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር።  38 እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። 39 ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። 40 እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። 41 እጅግም ፈሩና። እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።

ወደ ማዶ እንሻገር ብሎ ተናግሮ የተጀመረው መንገድ እክል አጋጠመው ይኸውም ማዕበል ነበር:: በጌታ ውስጥ ያለው አሳብ እንሻገር ብሏል መሻገር ግድ ነው የሚያቆም ነገር የለም ነው ነገር ግን የሚያጨናግፍ ነገር ተፈጠረ:: ስንጠፋ አይገድህምን? ብለው እስኪሉ ድረስ ጀልባዋ ላይ የገባውን ውሀ በማፍሰስና በመቅዘፍ ላይ ተጠምደው ነበረ:: ዛሬ ምን ላይ አጥምዶን ይሆን ጠላት ከትልቁ ተልእኮ ላይ አይናችንን አስነስቶትስ ይሆን? መጠየቅ ጥሩ ነው ዙሪያችንን እንይ እስኪ እኛ መንፈሳውያን ሰዎች ነንና የጊዜውን ፀልየን መቀበል አለብን:: ጌታ ከተኛበት ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው ይላል:: ሃሌሉያ! ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? ብሎ ነበር ያላቸው:: የተጠየቁትን እናስተውል እምነት የላችሁምን? እንሻገር አይደለም ያልኩት ታድያ ቃሌን የሚያጥፍ ማነው? ባለማመናችሁ እናንተ ናችሁ ያልታዘዛችሁት:: አለመታዘዛችንን ሳናስተውል ሳንታዘዝ ስንቱን አጋጣሚ አልፈነው ይሆን? ዛሬ ስለተፃፈ ምን ነካቸው ሐዋርያት እንል ይሆናል ነገር ግን ዛሬም ጠላት ለማዘናጋት በዙሪያችን እንደሚዞር አውቀን እንንቃበትና ጌታ ያለን ቃል ላይ እንቁም::


ምዕራፍ 5

ሌጌዎን ያለበትን ሰው ፈወሰ

የማርቆስ ወንጌል 5: 1-20
1፤ ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር መጡ። ከታንኳይቱም በወጣ ጊዜ፥ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ከመቃብር ወጥቶ ወዲያው ተገናኘው፤ እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፥ በሰንሰለትም ስንኳ ማንም ሊያስረው በዚያን ጊዜ አይችልም ነበር፤ ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና ዳሩ ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፥ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም፤ ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን በመቃብርና በተራራ ሆኖ ይጮኽ ነበር ሰውነቱንም በድንጋይ ይቧጭር ነበር። ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፥ በታላቅ ድምፅም እየጮኸ። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤ አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ ብሎት ነበርና። ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው አለው፥ 10 ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው። 11 በዚያም በተራራ ጥግ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበርና። 12 ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን ብለው ለመኑት። 13 ኢየሱስም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ገቡ፥ ሁለት ሺህም የሚያህል መንጋ ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና በባሕር ሰጠሙ። ፍ1 ሌጌዎን ማለት ጭፍራ ማለት ነው። 14 እረኞቹም ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩ፤ ነገሩም ምን እንደ ሆነ ለማየት መጡ። 15 ወደ ኢየሱስም መጡ፥ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ። 16 ያዩት ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ እሪያዎቹ ተረኩላቸው። 17 ከአገራቸውም እንዲሄድላቸው ይለምኑት ጀመር። 18 ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው። 19 ኢየሱስም አልፈቀደለትም፥ ነገር ግን። ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው። 20 ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ። 

በብዙ ጉልበትና ኃይል እንኳን ለማሰር ያስቸገረው ሰው እየሱስን ሲያይ በእግሩ ስር ወድቆ አታሰቃየን ብሎ ሲለምን እናያለን:: ሰይጣን ሁልጊዜ ስራው ክፉ ነው ማሰቃየትንም ይወዳል የኛ ጌታ ደግሞ ነፃ ማውጣት ነው ስራው ይህንን ሁሉ ጊዜ የተሰቃየውን ሰው ሊረዳ ነበር ወደ መቃብሩ ስፍራ የመጣው:: በእርሱ ነፃ መውጣት ሰዎች ሲደሰቱ ሳይሆን እንዲያውም ሂድልን ነበር ያሉት:: በዓይናቸው ፊት የማይቻለው ተችሎ እያዩ ግን ማስተዋልን አልቻሉም ነበር:: ለጌታ ግድ የሚለው የሰው ከስቃይ መገላገል ነውና::

አጋንንት የወጣለት ሰው ከጌታ ጋር መሆን ፈልጎ ነበር ጌታ ግን ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው። የጌታ ምህረት ነው ይህንን ሰው ደህና ያደረገው:. ሰውየውም ሄዶ ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ:: ይህ ሰው ወንጌላዊ ነው የሆነው የተደረገለትን በመስበክ:, እኛም የበዛልንን ምህረት እንመስክር ብዙ ተደርጎልናልና::


የደምዋ ምንጭ ደረቀ

የማርቆስ ወንጌል 5: 21-34
21፤ ኢየሱስም ደግሞ በታንኳይቱ ወደ ማዶ ከተሻገረ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ በባሕርም አጠገብ ነበረ። 22 ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና። 
23 ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው። 
24 ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። 
25 ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ 
26 ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ 
27 የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች። 
28 ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና። 
29 ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። 
30 ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ። ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ። 
31 ደቀ መዛሙርቱም። ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ። ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት። 
32 ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። 
33 ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። 
34 እርሱም። ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት።

ብዙ ሕዝብም ተከተሉት እያጋፉትም ወደ ኢያኢሮስ የሚሉት ከምኵራብ አለቆች አንዱ ወደሆነው ሰው ቤት ልጁን ለመፈወስ በጉዞ ላይ ነበረ:: በመንገዱም ላይ አንዲት ሴት የልብሱን ጫፍ ነካች:: እርሱም ቆመ በመነካቱ ሳይሆን ኃይል ከእርሱ እንደወጣ ስላወቀ ነው:: ሐዋርያቱ ግን ማን ነካኝ ትላለህ እንዴ ይህ ሁሉ ህዝብ እያጋፋህ? አልገባቸውም ነበር እርሱ የሚለው ነገር ስለዚህም ልትደበቅ እንዳልተቻላት አውቃ የሚለውም ገብቷት ነበረና በእግሩ ስር ወድቃ የሆነውን ሁሉ ነገረችው::

ገና ስትመጣ ዓላማ ነበራት የልብሱን ጫፍ የነካሁ እንደሆነ እድናለሁኝ እና መንካት አለብኝ ብላ ነው የመጣችው:: ያላትን ሁሉ በጤናዋ ምክንያት ያጣች ግን በህመም የምትሰቃይ ሰው ናትና ወደ እርሱ ስትመጣ ሌላ አማራጯን ሁሉ ጨርሳ ነው:: ስለዚህም እንደምንም ብላ ተንጠራርታ ነካችው ወድያውም መዳንዋን የደምዋንም መቆም አወቀች:: ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል! የሚገርመው ነገር መዳንዋን ያወቀች ብትሆንም እንኳን ጌታ:- ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት ከእርስዋ ጋር ተስማማ:: ሰውን ከስቃይ መገላገል ይወዳልና ጌታ ከስቃይሽ ተፈወሺ አላት:: ያለፈችበትን የሚረዳ ጌታ እርሱ እጅግ የሚምር የሚራራ ነውና:: ስሙ የተባረከ ይሁን! እምነታችንን በጌታ ላይ እናድርግ ሌላው አልተፈወሰምናእኔስ ምን አገኛለሁ አንበል አንዳንዱ ዝም ብሎ የሚያጋፋ ነውና በእምነት ወደ እርሱ እንቅረብ አያሳፍረንም:: ዛሬም ጌታ ይፈውሳል! ዛሬም በስራ ላይ ነው! አሜን!


እመን ብቻ እንጂ አትፍራ

የማርቆስ ወንጌል 5: 35-43
35፤ እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት፦ ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት። 36 ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ። እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። 37 ከጴጥሮስም ከያዕቆብም ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። 38 ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤትም መጥቶ ሰዎች ሲንጫጩና ሲያለቅሱ ዋይታም ሲያበዙ አየ፤ 39 ገብቶም። ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው። 40 በጣምም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናትም ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ። 41 የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። 42 ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ። 43 ይህንም ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አዞአቸው። የምትበላውን ስጡአት አላቸው።

መቼም የእየሱስ ነገር ይገርማል ሰውን ከሞት አስነስቶ እያለ ለማንም አትንገሩ ማለቱ ነው:: ግን ይህንን ለማድረግ ይቻላል? ልጅትዋ እኮ እራስዋ ምልክት ናት ከሞት የተነሳችው ነው ቅፅል ስምዋ የሚሆነው:: እንዴት ከሞት ተነሳሽ ስትባል መናገርዋ አይቀርም::


እየሱስ ወደ ምኩራብ አለቃው ቤት እየሄደ ሳለ አታድክመው ልጅህ አርፋለች የሚል መልእክት ተነገረው:. አይይ አይዞህ እንግዲህ እኔስ ከእእንተ ጋር ልሄድና ልፈውስልህ ነበር ግን ቀድማ ሞተች ብሎ አልተለየውም:: እመን ብቻ እንጂ አትፍራ ነበር ያለው! ግን አሁን ልጅህ ሞታለች ለተባለው ሰው አትፍራ ምን አይነት መልእክት ነው? በትክክል መልክቱን የሰማ አይመስልም እየሱስ ግን አትፍራ የሚለው ቃል ህያው ነውና የኢያኢሮስን ልብ ደግፎ ያዘለት:: ወደ ስፍራውም ሲደርስ ጫጫታና ዋይታ ለቅሶ ነበረ የገጠማቸው ስለዚህም እየሱስ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው። በጣምም ሳቁበት። ዛሬም እየሱስ በእኛ ውስጥ ይሳቅበታል ስንት ጊዜ አይተን የለም? ሲመራን እሺ ብለን ስንመራ ሞኝ ተብለናል ግን ማን ሞኝ እንደሆነ ጊዜ ገልጧል:: የሳቁበትን ሁሉ አስወጥቶ እነዛኑ ክብሩ ሲገለጥ ያዩትን ሐዋርያትና የብላቴናይቱን እናትና አባት ይዞ በሩን ዘጋ:: ምክንያቱም አለማመንን በሙሉ አወጣ ከስፍራው ወላጆችዋ እንደሆነ የፈለገህን በለን ልጃችን እንድትነሳ እናምናለን የሚሉ ናቸውና:: አለማመንን ዛሬ አስወጥተን በራችንን እንዝጋ:: እየሱስም:- የብላቴናይቱን እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ ይላል ቃሉ:: የሳቁት ሱዎች ምን ብለው ይሆን ከእፍረት ሌላ? ጌታ ዛሬም ይሰራል ምንም የሚሳነው ነገር የለም:: ብቻ እንመን ነውጌታ የሚለን:: ስለምንሰማውም ነገር እንጠንቀቅ! እምነት የሚመጣውም ሆነ የሚጣለውም ከመስማት ነውና:: እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል:: እምነት ተሰፍሮ የሚሰጥ ሳይሆን ከቃሉ ውስጥ የሚወለድ ነውና ህያው ቃሉን ዕለት ዕለት እንብላ:: ለሚያምን ሁሉ ይቻላል:: ያለ እምነት እግዚአብሔር ደስ ማሰኘት አይቻልምና የምናምን አማኞች እንሁን:: የጌታ ጸጋ ይሙላብን! አሜን!


ምዕራፍ 6

ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ

የማርቆስ ወንጌል 6: 1-6
1፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና። እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው?  ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። 

እየሱስ ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ ይለናል ቃሉ:: የታዘብኩት ጉዳይ ቢኖር ጌታ እየሱስ ቢነቅፍ ወይም ቢቆጣ ከእምነት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ነው:: ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና::

ወዳደገበት አካባቢ መቶ በሰንበት በምኵራብ ያስተምር ነበር ነገር ግን ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና ስለ ማንነቱ መነጋገር ጀመሩ:: እነሱ የዚህ ቤተሰብ ልጅ አይደለምን ብለው የፈረጁት እየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው! አሜን! ሃሌሉያ! ስለተሰጠችው ጥበብ አድንቀው ሳይጠቀሙበት ተሰናክለው ቀሩ ምክንያቱም ማንነቱን አላወቁምና:: ዛሬም የምናጋፋ እንዳንሆን ጌታን በግላችን እንወቀው፤ ክርስትና የግል ነውና::

ስለዚህም እየሱስ በዚያም ስፍራ በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። ለካስ ጌታንም አላሰራ የሚል ሁኔታ አለ?! እርሱም አለማመን ነው! እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው:: እዚህ ቦታ ግን የሰሙትን ቃል እንዳያምኑት ሌላ ቃል በሰሚዎቹ መካከል ተነገረ ይኸውም እናውቀው የለም እንዴ ይህንን ሰው? ደሞ ከየት አመጣው ብለው ሲሉ የተዘራውን መልካም ዘር ሁሉ ተለቀመ ከሰሚዎቹም አልተዋሀደም:: ስለዚህ ከምንሰማው እንጠበቅ ከማመን ሊያሰናክለን ከሚችል ሁሉ እንራቅና የህይወት እንጀራ የሆነውን ሰው ያለ እርሱ መኖር አይቻለውም የተባለለትን የቃሉን ምግብ እንመኝና ለመንፈሳችን እንመግብ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው

የማርቆስ ወንጌል 6: 7-13
7፤ አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ። 10 በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። 11 ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። 12 ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ 13 ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።

ጌታ እየሱስ በመጀመሪያ ሐዋርያትን ሲጠራቸው ከእርሱ ጋር እንዲኖሩና ወንጌልን እንዲሰብኩ አጋንንትንም እንዲያወጡ ነበር:: አሁንም ጊዜው ደረሰና ወደ እርሻው ብቻቸውን ሁለት ሁለት አድርጎ ሲልካቸው እናያለን:: ሁለት ሁለት የመሆናቸውም ምክንያት እንዲደጋገፉና እንዲበረታቱም ነው:: ሲልካቸውም በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰቶ አስታጥቆ ነው የላካቸው እነሱም ሲመለሱ ያመጡት መረጃ ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ እና ብዙ አጋንንትንም እንዳወጡ ነበር፥ ይህም ብቻ አይደለም ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው ነው የሚለው ቃሉ:: ዛሬም ጌታ አልተለወጠም፥ ይሰራል፥ ሲልከንም ስልጣንን ሰቶ ነው ስራው የእርሱ ነውና በእኛ ላይ የተጠራውን ስሙን ያከብራል:: ማገልገል ብለን ስንል ደግሞ ጌታ ልኮናልና እርሱ የሚያስፈልገንን ሁሉ ያሟላል:: እግዚአብሔር የላከውን መልክተኛ አለመቀበል ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል ነበር ያላቸው:: የእግዚአብሔርን የምህረት ጊዜ ሰዎች እንዲቀበሉት እንምከር:: የእግዚአብሔርን መንግስት እንስበክ ንስሀ ግቡ እያልን በአጋንንት እስራት ውስጥ ያሉትን ነፃ ማውጣትና ህመምተኞችን መፈወስ የእኛ ስራ ነው:: የጌቲ ጸጋ ይብዛልን!


የመጥምቁ የዮሐንስ መገደል

የማርቆስ ወንጌል 6: 14-29
14፤ ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል፡ አለ። 15 ሌሎችም። ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም። ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ። 
16 ሄሮድስ ግን ሰምቶ። እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ።
17 ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ 
18 ዮሐንስ ሄሮድስን። የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና። 
19 ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤ 
20 ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ 
21 በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና 
22 የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን። የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ 
23 የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት። 
24 ወጥታም ለእናትዋ። ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች።
25 ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። 
26 ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። 
27 ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ 
28 ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። 
29 ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት። 

መጥምቁ ዮሐንስን ስንመለከት ከዓለም እራሱን ያራቀና በምንም መንገድ በዓለም ነገር የማይጠላለፍ ሰው ነው:: ኑሮውን በምድረ በዳ ምግቡን የበረሀ አንበጣና ማር ልብሱ የግመል ፀጉር ያደረገነበረ ታድያ ምን ቀርቶት ከዓለም ጋር ህብረት ያድርግ? ስለዚህም የሚያየውን ሐጥያት ሐጥያት ነው ለማለት የጨከነ ሰው ነውና ይኸው ጉዳይ ነበር ከንጉሡ ሄሮድስ ጋር ያጣላው:: ንጉሡ ሄሮድስም ይፈራው ነበር ጻድቅ መሆኑን ስለሚያውቅ ሊያስገድለውም አልፈለገም የተናገረውን ቃሉን ማጠፍ ስለማይችል ብቻ ነበር እንዲገደል ያደረገው:: ይህ ሰው የተገደለው ሐጥያታቸውን ለመሸፈን ሲባል ብቻ ነው::

በዛው በጽድቅ መንፈስ እየሱስ ሲመጣ አልተመቻቸውም ምክንያቱም ይህ የጽድቅ መንፈስ ይወቅሳልና እንጂ ዮሃንስስ አልተነሳም:: የእግዚአብሔር መንፈስ አንዱ ስራው ስለሐጥያት መውቀስ ነውና ሰዎች በሐጥያት ሲመላለሱ ስለሚወቀሱ ቅዱሳንን መሸሽ ይጀምራሉ:: እኛ ግን ታረቁ የምንል ነንና በየዋህነት መንፈስ ሰዎችን እናቅና:: እግዚአብሔር እጅግ የሚምር የሚራራና ማንም እንዲጠፋ የማይፈልግ ጌታ ነውና ብርሃናችን ሁልጊዜ የበራና ለዚህ ጨለማ ዓለም ብርሃን መሆንን እንቀጥል:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው

የማርቆስ ወንጌል 6: 30-44
30፤ ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። 31 እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። 32 በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ። 33 ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ። 34 ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። 35 በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤ 36 የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው አሉት። 37 እርሱ ግን መልሶ። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት። 38 እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ አላቸው። ባወቁም ጊዜ። አምስት፥ ሁለትም ዓሣ አሉት። 39 ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው። 40 መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ። 41 አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ 42 ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ 43 ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ። 44 እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ። 

ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት በዚህ ጊዜ ነው በሉ ወደ ምድረ በዳ እንውረድ የሚላቸው ምክንያቱም እንዲያርፉ:: ግን ምድረ በዳ የእረፍት ቦታ ነው? እስኪ ከየት እንደመጡ እንየው :- ከአገልግሎት ድል በድል ሆነው ትንሽም ብትሆን ልባቸው አበጥ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ እየሱስ አብሯቸው ሳይኖር ትልልቅ ነገሮችን አድርገው ተደንቀው እያሉ ነው የምድረ በዳ ጥሪ የመጣው:: ነገሩ እንዲያርፉ፤ እንዲበሉ፤ እራሳቸውን ተረጋግተው እንዲያዩ ደግሞም ለነገው አገልግሎት አቅም እንዲኖራቸው ብሎ ነው:: ቁጭ ብሎ ድልን ማውራት ለፈተናና ሽንፈት ያጋልጣል::

ወደ ምድረ በዳ ሲሄዱ ሰዎች በዛ ጠበቁዋቸው ድካም ቢኖርም እንኳን ለማረፍ ቢሆንም የሄዱት እየሱስ ማገልገልን ቀጠለ:: አስተምሮ ሲጨርስም የሚበሉትን ስጡአቸው ብሎ እርፍ:: እምድረ በዳ ላይ ምግብ ከወዴት ይመጣል እራሱ አይደል እንዴ እረፍት ያስፈልጋችኃል ብሎ የወሰዳቸው እንደገና ስራና አሳብ ውስጥ ገቡ ህዝቡ ብዙ ነው ለዚህ ሁሉ የሚሆን ምግብ ከየት ደግሞስ በምን ያህል ገዝተን ተሸክመን ልናመጣ ነው? ብዙ ነገር ነው ጭንቅላታቸው ውስጥ የሚመላለሰው:: እየሱስም ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው አጣርተው አምስት እንጀራና ሁለት አሳ ብለው መለሱ:: ከአምስት ሺህ በላይ የሆነ ህዝብ ለመመገብ አስቀመጧቸው ያላቸው ግን አምስት እንጀራና ሁለት አሳ ብቻ ነው:: አመስግኖ ቆራርሶ ሰጣቸው እያንዳንዳቸው ቁራሽ እንጀራና አሳ ደረሳቸው እንጂ የተቆለለ ምግብ ወይም በትሪው ላይ ተቆልሎ መሸከም እቅቷቸው ነበር አይልም:: ስለዚህ የሆነው ነገር የመጀመሪያውን ቁራሽ ሲሰጡ የሚቀጥለው ይመጣል:: እምነታቸው ነው የታየው ኢቺ ቁራሽ ናት ይህንን ሁሉ ህዝብ የምትመግበው ብሎ መቀበል:: ሐዋርያት ከአገልግሎት መተው ብዙ ነገር አወቅን ብለው እያሉ ነው እንግዲህ ከዚህ በፊት አይተውት የማያውቁት ትምህርት ሊያስተምራቸው የፈለገው:: ግን አምነው ቁራሽዋን ይዘው ለማደል ተነሱ:: ተአምራቱ በእጃቸው ላይ በዛ ያ ሁሉ ህዝብ ተመግቦ የተረፈው አስራ ሁለት መሶብ ነበረ:: ተአምር!

በእጃችን ላይ ያለውን ነገር ይዘን እንቅረብና እንመን እርሱ የሚሰራውን ያውቃል ያትረፈርፈዋል::


ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር

የማርቆስ ወንጌል 6: 45-56
45፤ ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። 46 ካሰናበታቸውም በኋላ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 47 በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ። 48 ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር። 49 እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥ 50 ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው። 
51 ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤ 52 ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር። 53 ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ። 54 ከታንኳይቱም ሲወጡ ወዲያው አውቀውት 55 በዚያች አገር ሁሉ ዙሪያ ሮጡና እርሱ እንዳለ ወደ ሰሙበት ስፍራ ሕመምተኞችን በአልጋ ላይ ያመጡ ጀመር። 56 በገባበትም ስፍራ ሁሉ፥ መንደርም ከተማም ገጠርም ቢሆን፥ በገበያ ድውዮችን ያኖሩ ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

ሐዋርያቱን አሰናብቶ እርሱ ግን እንደለመደው ለጸሎት ወደ ተራራ በምሽት ወጣ:: ለምን አብረው እንዳልጸለዩ አይገባኝም ጻድቅ በምቹ ጊዜ ይጸልያል ይላልና ቃሉ:: በእርግጥ እንዲሄዱ ግድ አላቸው እራሱ ጌታ በመሄዳቸው ግን አትርፈዋል ብዬ ለማለት ይከብደኛል ከማዕበል ጋር ነው ሲታገሉ የነበሩትና::

ሲጨነቁ አይቶ በባህሩ ላይ እየተራመደ መጣ ከማዕበሉ የበለጠ ያስፈራቸው ግን ይህ ምትሀት ብለው የጠሩት ነገር ነው ከውሀው ብንተርፍ ይህ ነገር ይገድለንማል ሳይሉ አይቀሩም:: የጌታን ስም መጥራትና መቃወም የሚለው አሳብ ውልም ያለባቸው አይመስሉም ብቻ ባለ በሌለ ኃይላቸው ከማዕበል ጋር መታገል ይዘዋል:: ልክ እንደታሪክ አንብበን ካለፍነው አንማርበትም ነገር ግን ይሄ የብዙዎቻችን ችግር ነው ብዬ አምናለሁ ከነገሮች ጋር መታገል:: ይልቅስ ወደ ዙፋኑ እናምጣው አምላካችን መፍትሄ አለው መንገድ በሌለበት ውስጥ መንገድን ያወጣል:: ጌታም አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸውና ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ::

ለምን እንዲሄዱ ግድ አላቸው? ይህ ችግር እንደሚመጣ ያውቅ የለም እንዴ? ያልን እንደሆነ ከሰአታት በፊት የሆነውን በአእምሯቸውም አልመዘገቡት በቁራሽ እንጀራና አሳ ስንትና ስንት እንደመገቡ ከዛም ስንት መሶብ እንደተነሳ ተአምራት በፊታቸው ተደርጎ ነበር:: መቼም ይህንን ስናይ ምን ነካቸው እነዚህ ሰዎች ብለን እንፈርዳለን የእኛም ታሪክ ዛሬ ቢጻፍ እመኑኝ ከዚህ ላይሻል ይችላል:: ለዚህ ነው መንፈስ ቅዱስ የተሰጠን የተማርነውን እንዲያሳስበን፤ ወደ እውነትም ሊመራን፤ ሊያበረታን፤ ከእኛ ጋር የሚኖር ረዳት፤ ለቤዛነት የታተምንበት ጌታ ዛሬ ኃይላችን ነው:: ማንም እንዳይመካ ሁሉን በእኛ ውስጥ እያደረገ ያለው እርሱ ነውና አሁንም ከመደንንዘዝ ያውጣንና ወደ ማስተዋል ይምራን!

በዚህ ሁሉ ውስጥ መቼም የጌታ ትዕግስት ይደንቃል ልቡን ሰፊ አድርጎ ነው የሚያገለግላቸው:: እኛም ልባችንን አስፍተን እናገልግል:: ወደ ጌታ የመጡትና የዳሰሱት ሁሉ ተፈወሱ:: ጌታ ዛሬም ይፈውሳል::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 7

ወግን ለመጠበቅ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መሻር

የማርቆስ ወንጌል 7: 1-23
1፤ ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡትም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንድ በርኵስ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ። ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፥ ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፥ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ። ፈሪሳውያንም ጻፎችም። ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች። ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። እንዲህም አላቸው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። 10 ሙሴ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና። 11 እናንተ ግን ትላላችሁ። ሰው አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው ቢል፥ 12 ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤ 13 ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። 14 ደግሞም ሕዝቡን ጠርቶ። ሁላችሁ እኔን ስሙ አስተውሉም። 
15 ከሰው የሚወጡት ሰውን የሚያረክሱ ናቸው እንጂ ከሰው ውጭ የሚገባውስ ሊያረክሰው የሚችል ምንም የለም። 16 የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ አላቸው። 17 ከሕዝቡ ዘንድ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ምሳሌውን ጠየቁት። 18 እርሱም። እናንተ ደግሞ እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ሊያረክሰው ምንም እንዳይችል አትመለከቱምን? 19 ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና፤ መብልን ሁሉ እያጠራ አላቸው።20 እርሱም አለ። ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው። 21 ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ 22 ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤ 23 ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል። 

ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። እነማን ናቸው ይህንን ጥያቄ የጠየቁት ስንል? ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና ጻፎች ናቸው:: እንከን ማውጣት ክህሎታቸው ነው ሁልጊዜ በምን እንደሚያጠምዱት ስለሚፈልጉ እግዚአብሔር ትኩረት ያልሰጠውን፤ በነሱ አይን ግን ትልቅ ስፍራ የተሰጠውን የእጅ መታጠብ ስርአት አካብድው ጊዜውን ያጠፉበታል:: ይህንን ሳነብ ጌታ እዚህ ግባ የማይለው ነገር እኔ ግን ሙጭጭ ብዬ የያዝኩት ምን ይሆን ብዬ አሰብኩኝ፤ ዋናውን ጉዳይ ወደጎን እንዳደርግ የሚያደርገኝ ነገር ካለ መንፈስ ቅዱስ ፈትሸኝና ልወቀው ነው ጸሎቴ:: አንባቢም እራሱን ቢያይ አይከፋም::

ለጥያቄያቸው የጌታ መልስ መቼም እሱ ባይልም እንኳን ስለ እዳሪ አታስቡ ይልቅስ ከልባችሁ የሚወጣው እንዳያረክሳችሁ ተጠንቀቁ ልብና ሆድ ከአንድ አይመገቡም ነበር መልሱ:: ጎሽ ጥሩ አደረጋችሁ ወይም የኔዎቹ ልክ አይደሉም ነበር የጠበቁት መልስ እርሱ ግን ትንቢትን በመጥቀስ ከዚህ በፊት ተነገራችሁ አሁንም እዛው ላይ ናችሁ? ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ።  የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። እንዲህም አላቸው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል።  ተብለው በትእዛዝ ሰጪው እየተነገራቸው እያለ እሱን ተወውና እጅ መታጠብ አስፈላጊ ነው ይላሉ:: የህዝቡንም ትኩረት ወደ ተራ ጌታ ወዳልስጠው ነገር በመምራት ደርሶ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ እየመሰላቸው ነው:: ስንቱ ይሆን ሚዛን በማያነሳ ነገር ላይ ጊዜውን የሚፈጅ ዛሬ በእኛ ዘመን? ጌታ ይርዳን!

ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥  ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤  ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል። ህይወታችንን በቃሉ እንጠብና እንቀድስ:: በእኛ ህይወት ውስጥ እንዲመጥን አድርገን ቃሉን አንጠምዝዝ ይልቁንስ ህይወታችንን ወደ ጸጋ ዙፋኑ አቅርበን በሚያስፈልገን ጸጋ ተሞልተን የልቡን አሳብ እናገልግል::


ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት

የማርቆስ ወንጌል 7: 24-30
24፤ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። ወደ ቤትም ገብቶ ማንም እንዳያውቅበት ወደደ ሊሰወርም አልተቻለውም፤ 25 ወዲያው ግን ታናሺቱ ልጅዋ ርኵስ መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ተደፋች 26 ሴቲቱም ግሪክ፥ ትውልድዋም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች፤ ከልጅዋ ጋኔን ያወጣላት ዘንድ ለመነችው። 27 ኢየሱስ ግን። ልጆቹ በፊት ይጠግቡ ዘንድ ተዪ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምና አላት። 28 እርስዋም መልሳ። አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው። 29 እርሱም። ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት። 30 ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። 

ይህች አህዛብ ሴት የጨነቃት እናት ናት ልጅዋን አጋንንት ይዞ ያሰቃየባት ናት:: የትኛውም የምድር አካል ሊረዳት አይችልም ከጌታ በቀር:: ጌታጋርም ስትሄድ ለአንቺ አይደለም የመጣሁት ልጆች ይጥገቡ ዘንድ ተዪ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምና አላት:: አይሰጥሽም የተባለችው ፈውስን በምን መልክ እንደሚጠራው ስናይ እንጀራ ይለዋል:: እንጀራን በአባታችን ቤት መብላት ለእኛ ነው ፈውስም እንጀራችን ነው አንከለከልም:: ቡችላ ብሎ ቢጠራትም ከእንብርክክዋ ሳትነሳ ክብርን እየሰጠችው ጌታ ሆይ፥ ብላ እየጠራችው ቡችሎችም እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው። የሙጥኝ ዛሬ አለቅህም ልጄን ሳትፈውስ ተሰቃይተናል የሚረዳንም የለም እናም ብዙ ብዙ ነገር ነው በውስጥዋ እየተመላለሰ ያለው::

እየሱስም ያለ መልስ እንደማትሄድ ቆርጣ አምና መምጣትዋን አይቶ እምነትን ማለፍ ስለማይችል ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት። ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። ባይፃፍም ቅሉ ምስጋናና እልልታ በዛ ቤት እንደሚበዛ እርግጠኛ ነኝ:: ትልቅ እረፍትን በቤትዋ አደረገ ካመንን ለእርሱ መስራት ቀላል ነው::


ሁሉን ደኅና አድርጎአል

የማርቆስ ወንጌል 7: 31-37
31፤ ደግሞም ከጢሮስ አገር ወጥቶ በሲዶና አልፎ አሥር ከተማ በሚባል አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። 32 ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፥ 33 እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት። ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ 34 ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና። ኤፍታህ አለው፥ እርሱም ተከፈት ማለት ነው። 35 ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ። 36 ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት። 37 ያለ መጠንም ተገረሙና። ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ።

የዚህን ከተማ ስም ማር 5:1-20 ባለው ታሪክ ላይ እናውቀዋለን:: ሌጊዎን ይዘው በመቃብር ስፍራ ሲያሰቃዩት የነበረው ሰው ከተፈወሰ በኃላ የተደረገለትን የሚሰብክበት ስፍራ ነው:: እሱን በፈወሰው ጊዜ ግን እሪያዎቻቸው ስላለቁባቸው ሰዎቹ ወደ ከተማችን አትገባም ብለው ጌታን ከዛው መልሰውት ነበር ዛሬ ግን በሽተኞቻቸውን ወደ እርሱ አመጡ እርሱም ፈወሰላቸው::

ጌታ ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ሲፈውስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም በሌሎችም ወንጌላት ላይ ተፅፏል ሁሉንም አጋንንት ነበር የያዛቸው የዚህኛው ላይ ገስጾ ሲያወጣ አናይም:: ህዝቡም እጁንም ይጭንበት ዘንድ ነበር የለመኑት ነገር ግን ከዛ በላይ ነበር ያስፈለገው:-

  1. ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ መለየት ያስፈልገው ነበር ከተጽእኖና ከማንኛውም ልምምድ
  2. ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ
  3. እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ ማየት የተሳነውንም በዚህ ሁኔታ ፈውሶ ያውቃል
  4. ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና :- ጸሎት ያስፈልጋል ፈውስን ለማግኘት እንጂ እጅ ብቻ ስለተጫነ ላይመጣ ይችላል
  5. ኤፍታህ አለው፥ ቃልን አወጀ ይፈታ ዘንድ::

ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ።  ያለ መጠንም ተገርመው ያሉት አባባል ደስ ይላል:- ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ሃሌሉያ የእኛ ጌታ ሁሉን ደህና ያደርጋል በጥያቄያችን ላይ መልስ አለው:: ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ ዛሬም ያደርጋል ይሄ ጌታ ህያው ነው።

ፈውስን ስናስብ ከጌታ ምሪት የሚያስፈልገው ነው አንድ አይነትን በሽታ በተለያየ መልኩ ሲፈውስ እናያለን ስለዚህ ምሪት እንቀበል እርሱ እንጂ እኛ ፈዋሾች አይደለንም የሚለንን እናድርግ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 8

አዝንላቸዋለሁ አለ እየሱስ

የማርቆስ ወንጌል 8: 1-13
1፤ በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም። በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት። እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው፥ እነርሱም። ሰባት አሉት። ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፥ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ለሕዝቡም አቀረቡ። ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ። በሉም ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ። የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ። 10 አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ። 11 ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር። 12 በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ። 13 ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ። 

ጌታ ለህዝቡ አዝንላቸዋለሁና የሚበሉትን ስጧቸው አለበለዚያ በመንገድ ይደክማሉ ብሎ ለህዝቡ እንደ እረኛ ሲቆረቆር እራሴን በዛ ውስጥ እያሰብኩኝ ደስ አለኝ ጌታዬ ያስብልኛል:: እንደተለመደው ሐዋርያት የትናንቱን ተአምር እንዴት ህዝቡን እንደመገበ ጠፍቷቸው በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት:: ወቸ ጉድ ምድረ በዳ ቢሆንስ በአይን መፍትሄው ባይታይስ ለጌታ ምን ተስኖት? እኛም የያዝነው ይህንኑ ነው የትላንቱን እየረሱ ጥሬ መሆን አቤኔዘር እንበል እንጂ?! እርሱም የመለሱለትን ልክ እንዳልሰማ ምን አለ እጃችሁ ላይ አለ? ሰባት አሳ ጥቂትም አሳ አሉት:: እንደልማዱ በሉ አምጡ ብሎ ባርኮ ሰጣቸው:: ህዝቡም በሉ ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ። የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ። አሰናበታቸውም ይልና ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ ይላል:: አሁንም ረጋ ብለው የሆነውን ነገር ለማገናዘብ ጊዜ አልነበራቸውም አንድ ምዕራፍ ተዘጋ እጃቸውን እያራገፉ ወደሚቀጥለው ሩጫ:: እኛም እዛው ላይ ነን ያለነው ተረጋግተን እንመላለስ ትላንትን ያለፍነው በእርሱ ነው:: የምናልፍበትን የሚያውቅ ነውና እንታመን ያዝንልናልና:: ምድረ በዳውን አይተን ከየት ነው መፍትሄ የሚመጣው ብለን ተስፋ የቆረጥንበት ጊዜ ነበረ ግን ጌታ ደርሶ አሻገረን:: አይጥፋብን የትናንቱ እናመስግን::

ጌታ የሚገርመው እጅግ ታጋሽ መሆኑ እንጂ ሰው ቢሆን እነዚህን መልሶ ሌላ ሐዋርያትን ይመለምል ነበር:: ግን ዛሬን ሳይሆን የነገውን ማንነታችንን እያየ እኛንም ታግሶ በመንፈሱ ያነቃናል:: ሃሌሉያ! እጅግ የሚምርና የሚራራ ጌታና አባት አለን::

ወደ ማዶም ሲሻገር የባሰ ያለማመን ነበር የገጠመው ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር።  ቢያውቁት ግን ባከበሩት ነበረ:: በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ። ትልቁ ምልክት የእግዚአብሔርን ልጅ ከማየት በላይ ምን ሊኖር ይችል ይሆን? መተላለፍ!! ጸጋው ይብዛልን! አሜን!


ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው

የማርቆስ ወንጌል 8: 14-21
14፤ እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። 15 እርሱም። ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው። 16 እርስ በርሳቸውም። እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ። 17 ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? 18 ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? 19 አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም። አሥራ ሁለት አሉት። 20 ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም። ሰባት አሉት። 21 ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው። 

ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው:: የእግዚአብሔር ቃል ስለ ሰጎን በኢዮብ 39: 17፤ እግዚአብሔር ጥበብን ከእርስዋ ከልክሎአልና፥ ማስተዋልንም አልሰጣትምና። ይላል እዚህም ክፍል ላይ የምናየው ሐዋርያት ማስተዋል አተው ፊታቸው የተደረገው ተአምር በአእምሯቸው ሳይመዘግቡት ከእነሱም ሳይዋሀድ ቀርቷልና ሊጠቀሙበት አልቻሉም:: ለዚህም ነው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 2: 14፤ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። ስለዚህ ቃሉን ለመረዳት መንፈሳዊ መሆን አለብን:: ትዝ ይለናል እኮ ምን እንዳደረገ ዘርዝረን መናገር እንችላለን አንዳችም ሳይቀር አምስቱን እንጀራ አምስት ሺህ ተመግበው አሥራ ሁለት መሶብ ቍርስራሽ እንደተነሳ። እንዲሁም  ሰባቱን እንጀራ አራት ሺህ ተመግበው ሰባት መሶብ ቍርስራሽ እንደተነሳ አይጠፋንም መዘንጋት አይደለም ችግሩ ችግሩ መዋሀዱ ላይ ነው። እዚህ ክፍል ላይ አንድ እንጀራ ነበራቸው እኮ ይህ አንድ እንጀራ ለተፈለገው ቁጥር መብዛት ይችል ነበር ግን አላስተዋሉም ልባቸው ደንዝዞ ነበረና:: ታድያ በእምነት ካልተዋሀደ ምንም አይጠቅምምና ምን እናድርግ? አለበለዚያ በቀላሉ ጠላት መቶ ይለቅመውና ስራውን ያቃልላል:: በኢያሱ 1: 8፤ የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ይህ ነው የሚያስፈልገው ደግመን ደጋግመን ማንበብና ለሌሎችም ማካፈል ያኔ በልባችን ላይ ይጻፋል::

ሌላው ተጠንቀቁ፥ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው ይላል ቃሉ:: ከምን? ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ይህም ማለት ከዓለም ነገርና የራስን ጽድቅ ከማቆም መጠንቀቅ እንዳአለብን ነው የሚነግረን:: እኛ ጽድቃችን እየሱስ ነውና በእርሱ የምንመካ ነን ይህ አይጥፋብን:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


አጥርቶም አየ

የማርቆስ ወንጌል 8: 22-26
22፤ ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት። 23 ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፥ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት። አንዳች ታያለህን ብሎ ጠየቀው። 24 አሻቅቦም። ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ። 25 ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየና ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ። 26 ወደ ቤቱም ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው። 

ለየት ያለ ተአምራት ነው በዚህ ስፍራ የተደረገው:: ይኸውም በመጀመሪያ ከከተማ ይዞት ወጣ ሌላው ደግሞ አንዳች ታያለህን ብሎ መጠየቁ:: ስለ ቤተ ሳይዳ በሌላ ስፍራ የተናገረው ካላነበብን ይህንን ታሪክ ለመረዳት ይከብደናል:: በማቴዎስ 11: 21፤ ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ንስሀ አለመግባታቸው ወይም ከጌታ ያለመተባበራቸው ምክንያት አለማመን ነው:: ከተማዋ ሁሉ ባለማመን ተሞልታ ህዝቡም ሁሉ በአለማመኑ ስለፀና ይህንን ሰው እንዴት ይፈውሰው? ምክንያቱም በማርቆስ 6: 5፤ በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። 6፤ ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። ያለ እምነት ፈውስ ሊመጣ አይችልምና:: ሰውየውን ለመርዳት ነው ምን ታያለህ ያለው እንጂ ጸሎቴ ተሰምቶ ይሆን ከሚል ጥርጣሬ አይደለም:: እምነት ማጣት ተአምራትን ስለሚያቆም እንጂ:: ደግሞ ጸለየ ሰውየውም አጥርቶ አየ ከዛም ወደ ቤቱ ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው:: ለምን ይሆን ለማንም አንዳች አትናገር ያለው? እምነቱን ሸርሽረው ፈውሱን እንዳያስጥሉት ነው:: እኛም ከምንሰማው እንጠንቀቅ ደግሞም ድንቅና ተአምራትን አማኞች እንሁን:: ጌታ ዛሬም ይሰራል:: ማስተዋል ይስጠን!


ማን ትሉኛላችሁ?

የማርቆስ ወንጌል 8: 27-33
27፤ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም፦ ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። 28 እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት።29 እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም። አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። 30 ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። 31 የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር። 32 ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። 33 እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለው። 

እየሱስ ሰዎች ማን እንደሆንኩ ይላሉ ብሎ ጠየቃቸው የሚባለውን ነገሩት:: እርሱም እናንተስ? ብሎ ጠየቃቸው:- ጴጥሮስም አንተ ክርስቶስ ነህ አለው:: አሜን! ለእኛስ ይሄ ጌታ ማነው? እዳችንን በመስቀል የከፈለ፤ ሳንወደው የወደደን፤ በደሙ ያጠበን፤ የቀደሰን፤ ለመንግስቱ ካህናት ያደረገን፤ ብሎም ልጆቼ ያለንና በመንፈሱ የሞላን ጌታችን፤ አዳኛችን፤ ንጉሳችን ነው! አሜን!

ትንሽም ቆይቶ የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር:: በዚህ ጊዜ ወንድማችን ጴጥሮስ አይሁንብህ ብሎ ሊመክረው ተነሳ:: ክፉ ከመመኘቱ ሊያወጣውና የወዳጅነቱን ሊነግረው ቢመስልም ቅሉ ነገሩ ግን ወዲህ ነው:: ይህንን አሳብ ወደ ጴጥሮስ የላከው ሰይጣን ስለሆነ ነው ጌታም በጴጥሮስ የተጠቀመውን ጠላት የገሰጸው:: የእርሱን አሳብ አንስተውም እንደሚል ቃሉ እንዳንስት የሚያስፈልገን የቃሉ መነጽር ነውና በቃሉ ውስጥ አሳባችንን እንየው ደግሞም እንፈትሽ:: እዚሁ በዚሁ ከአንድ ጥግ ወደሌላው ሲወነጨፍ የምናየው የሰውን ድክመት በቃሉና በመንፈሱ ማሸነፍ እንችላለን:: ለምን ይመስላችኃል ጠላት ቃሉን የሚለቅመው? እንዳናመልጥበት፤ እንዳንጸናበት፤ የእርሱን ሽንገላ እንዳንመክትበት ብሎ ነው ቃሉ በልባችን ከእኛ ጋር ከተዋሃደ በፍጹም አያታልለንምና:: ጴጥሮስ አይኑን ማድረግ የነበረበት ትንሳኤው ላይ ነበር ሞቼ እቀራለሁ አላለምና:: አይናችንና አትኩሮታችን በእርሱ ላይ ይሁን:: በቃሉና በጸሎት ስር እንስደድ ጌታ ጸጋውን ያብዛልን:: አሜን!


ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ

የማርቆስ ወንጌል 8: 34-38
34፤ ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 35 ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። 36 ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? 37 ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? 38 በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።

ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር፥

  1. ራሱን ይካድ – የመጀመሪያ ነገር በክርስትና ራስን መካድ ነው ምክንያቱን ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።
  2. መስቀሉንም ተሸክሞ – ብዙ ጊዜ የመከራ ምሳሌ ይመስለናል ነገር ግን መቁረጥን ወደኃላ አልማፈግፈግንና ታማኝነትን ያሳያል:: ከጨከንን በጌታ አናፍርም የመጣውን ሁሉ እንቀበላለን እንጂ አናፈገፍግም::
  3. ይከተለኝ – መከተል መቼም የምንከተለውን ሰው አሳብ ብቻ ማስተናገድ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው:: ስለዚህም ነፍሳችንን ልናድን የምንዋትር አይደለንም እርሱን ለማክበርና ለመታዘዝ የምንተጋ እንጂ:: አለበለዚያ ለነፍሳችን ቤዛ የምንሰጠው እራሳችንን ክደን በመከተል ለእሱ ላዳነን ነው::
    የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!

እየሱስ በፊታቸው ተለወጠ

የማርቆስ ወንጌል 9: 1-13
1፤ እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ፡ አላቸው። ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፥ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም። የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። 10 ቃሉንም ይዘው። ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። 11 እነርሱም። ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። 12 እርሱም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናናል፤ ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም። 13 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ደግሞ መጥቶአል፥ ስለ እርሱም እንደ ተጸፈ የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት አላቸው። 

የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ ብሎ ባለው መሰረት ከስድት ቀን በኃላ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው:: ብዙ ጊዜ እነዚህን ሶስት ሐዋርያት ለይቶ ይወስዳል በመጨረሻም መሪ የነበሩት እነዚሁ ናቸው ከፊታቸው ላለው ኃላፊነት እያዘጋጃቸው ነበረ ባይገባቸውም እንኳን:: ጌታ ጊዜን አያባክንም ለመረጠን ስራ እያዘጋጀን ነውና መክሊታችንን እንዳንቀብር እንመንዝረው:: እዚህ ጋር እንደምናየው የመንግስቱ ክብርና ሞገስ ሲገለጥ እንዳልተዘጋጁ ያስታውቃል የሚሉትን አያውቁም ነበረና:: እርሱ ግን ቃሉን ጠብቋል ክብሩን አሳይቷቸዋል:: እኛም እስራው ላይ እንቁም እርሱ እራሱ ይመራናል ያስተምረናል ወደ እርሱ ካልቀረብን ግን የተሰጠንን የመንግስቱን ስራ መስራት አንችልም::

የእግዚአብሔር መንግስት ሲገለጥ

  1. ፍርሃት ይሆናል :- እግዚአብሔርን መፍራት ይወድቃል:: እዮብ ይህንና ያንን እጠይቀዋለሁ ይገለጥ ሲል ከርሞ አንድም ጥያቄ መጠየቅ ትዝ አላለውም::
  2. እራስንም መርሳት ይመጣል:- ለእኛ በዚህ መሆን መልካም ነው ብሎ ሲያበቃ ዳስ እንስራ ብሎ ያለበት ዝርዝር ውስጥ እርሱ የለም:: እርሱን ደስ ለማሰኘት እንጂ እራሳችንን የምንረሳ ነው የምንሆነው::
  3. የእግዚአብሔር ድምጽ መስማት አለ:- እግዚአብሔር አብ ስለ ልጁ ሲመሰክር ሰሙ:: ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም። የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።

ዛሬም እርሱን እንስማ ከቃሉ እናገኘዋለን የሚለንን በጸሎት ወደ ፊቱ እንቅረብ በመገዛትም ወደ አደባባዮቹ እርሱም ህያው ነውና ያበራልናል ደግሞም ይገኝልናል:: አሜን!

ክብሩን ዛሬ እንጠማ እንፈልግ እንበረታታ የፈለጉት ሁሉ አግኝተውታልና ፊታችን አያፍርም ያለ ክብሩም አንዳች ማድረግ አይቻልም:: ሃሌሉያ! አሜን!
ሶስቱን ሐዋርያት ብቻቸውን እንደወሰዳቸው ከእያንዳንዳችን ጋር ጉዳይ አለውና ፊቱን በመፈለግ እንትጋ::

ከተራራውም ሲወርዱ አንድ ትእዛዝ ሰጣቸው የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ እነሱም ቃሉንም ይዘው ግራ ገብቷቸው ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ከዛም ትዝ ያላቸው ነገር ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት እንግዲህ የምናውቀው ይመጣል የሚባለው ኤልያስ ነው ብለው:: እርሱ ሲያስተምራቸው የከረመውን ረስተውታል እንደሚሞትና እንደሚነሳ አይሁንብህ ሁሉ ብለው ሲያበቁ ውስጣቸው አልተቀመጠምና ምንም አልገባቸውም:: እንገረም ይሆናል በነሱ ነገር እስኪ አንድ ነገር ልጠይቅ ስንት ጊዜ የጌታን እርዳታ አይተን ሌላ ችግር ሲመጣ አዲስ ሆነን አናውቅም? እኛም ያው ነን መንፈስ ቅዱስ ይርዳን እንጂ ቃሉን በቀንም በለሊትም እናመንዥግ አለበለዚያ እውቀት ብቻ እንጂ መገለጥ ሆኖና የህይወት መመሪያ ሆኖ በልባችን አይመዘገብም:: እንደነገሩ አይሁን የጌታን ቃል ስናነብና ስንሰማ ጌታ አጠገባችን ሆኖ እንደሚናገረን አክብረን በልባችን እየተንቀጠቀጥን እንስማ::

ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም ብሎ አለ እየሱስ እርሱ ስለእኛ ነው ክብሩን ትቶ ባዶ ሆኖ የባርያን መልክ ይዞ የመጣው:: ክብር ከዘላለም እስከ ዘላለም ለስሙ ይሁን:: ለዚህ ስለ እኔ ለተናቀውና መከራን ለተቀበለው ጌታ እኖራለሁ አከብረውማለሁ ዘመኔም ይገባሀል አባት ሆይ:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


እየሱስ:- ወደ እኔ አምጡት አለ

የማርቆስ ወንጌል 9: 14-29
14፤ ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ሲከብቡአቸው ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አየ። 15 ወዲያውም ሕዝቡ ሁሉ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፥ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። 16 ጻፎችንም። ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። 17 ከሕዝቡ አንዱ መልሶ። መምህር ሆይ፥ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ 18 በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፥ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፥ አልቻሉምም አለው። 19 እርሱም መልሶ። የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው። 20 ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። 21 አባቱንም። ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ 22 ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው። 23 ኢየሱስም። ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። 24 ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ። አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ። 25 ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና። አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፥ ከእርሱ ውጣ እንግዲህም አትግባበት አለው። 26 ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም። ሞተ እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። 27 ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው ቆመም። 28 ወደ ቤትም ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ። እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው? ብለው ብቻውን ጠየቁት። 29 ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም አላቸው። 

በዚህ ክፍል ላይ የተጨነቀ አባት የታመመ ልጁን አምጥቶ ደቀ መዛሙርቱ ሊረዱት አልቻሉም:: እየሱስ ክብሩን ለተወሰኑት ሐዋርያት አሳይቶ ሲመለስ የጠበቀው ይህ ነበር:: ከቻልክ እርዳን የሚል ተስፋ የቆረጠ ሰው ጥያቄ ትላንትና ልኳቸው አጋንንት በስምህ ተገዛልን ብለው የነገሩት ሐዋርያት ሊረዱዋቸው አልቻሉም ምናልባትም እርሱም ሐዋርያቱም ይፈውሳሉን ሰምቶ የመጣ መሆን አለበት ለዚህም ተስፋ ቢቆርጥ አይደንቅም:: እየሱስ ግን መልሶ ብትችልስ? ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ብሎ አለው:: እርሱማ ይችላል እኔ ነኝ አምኜ መቀበል ያለብኝ:: እየሱስ ሰውን ሲነቅፍ የነበረው እምነት ሲያጡ ነው:: አንዳንዱ ጸሐይ ትቁም ብሎ አምኖ ጸልዮ አቁሞ የለም እንዴ ብዙ ነገርን ሊያዛባ የሚችል ያልገባው በሌላ ስፍራ የሚኖር ይሄኔ ጸሐይ ሳትጠልቅ ቆየች ብሎ ይል ይሆናል ለሌላው ደግሞ ምነው ጠዋቱ ጨለመ ይላል ዓለም ሁሉ የሚያየው ጸሎትና ውጤት እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ ነው እርሱ ይችላል እኛ እንታመን::

የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው። ትልቁ እምነትን የሚሰርቅ ነገር ቢኖር በእኛ ልክ እግዚአብሔርን ማየት ነው:: የተባልነው በራሳችሁ አንዳች ማድረግ አትችሉም ነውና ወደ እኔ አምጡት እንዳላቸው ሁሉን ነገር ወደ እርሱ እናምጣ እንዴት እንደሚሰራ የሚያውቀው እርሱ ነው ብቻ እንመን:: በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ ብሏልና እየሰማን እንታዘዝ እርሱ ሁልጊዜ ይሰራል:: የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ እምነትን በምድር ያገኝ ይሆንን? ብሎ ጌታን ያሳሰበው ጉዳይ ነውና ከጭንቅላታችን ጭላንጭል እውቀት እንውጣና በጌታ ላይ እንታመንና ክብሩን እንይ:: ስንተጋ በጾምና በጸሎት ወደ እርሱ እየቀረብን ነውና እርሱም ወደ እኛ ይቀርባል ታድያ ጨለማ በብርሃን ፊት እንዴት መቆም ይችላል:: ብርሃኑ ግድ ይወርሳል ጨለማችንን ያበራ ጌታ በእኛ ውስጥ ከዚህ ከሸክላ ውስጥ የከበረውን ማንነቱን ያሳያል ታምነን እንሰማራ ምንም አይነት አጋንንት በፊታችን አይቆምም! አይችልማ ሃሌሉያ! ከዛ በኃላ ጻፎች ሲከራከሩ አልታዩም ምክንያቱም ወንጌል በእውነት ከኖርነው የሚታይ ነውና ምን ክርክር ያስፈልጋል በተግባር እየታየ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም

የማርቆስ ወንጌል 9: 30-37
30-31፤ ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ያስተምር ስለ ነበር ማንም ያውቅ ዘንድ አልወደደም፤ ለእነርሱም፦ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ይገድሉትማል፥ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል፡ ይላቸው ነበር። 32 እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም፥ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። 
33 ወደ ቅፍርናሆምም መጣ። በቤትም ሆኖ። በመንገድ እርስ በርሳችሁ ምን ተነጋገራችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። 
34 እነርሱ ግን በመንገድ። ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? ተባብለው ነበርና ዝም አሉ። 
35 ተቀምጦም አሥራ ሁለቱን ጠርቶ። ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው። 
36 ሕፃንም ይዞ በመካከላቸው አቆመው አቅፎም። 
37 እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው።

እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም ዋናውን ነገር ማስተዋል አልቻሉምና ይስቱ ነበረ:: የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ይገድሉትማል፥ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል፡ ይላቸው ነበር። ልብ ብለው ቢሰሙት ጥሩ ነበረ ምክንያቱም እሞታለሁ ብቻ ሳይሆን እነሳለሁ ነበር እያላቸው ያለው:: ኢቺ ብቻ ገብታቸው ቢሆን ኖሮ ሳይበታተኑ እየተጉ በጠበቁት ነበር:: በእርግጥ የሞተ ሲነሳ ያዩት ሶስቱ ሐዋርያት ሙሴን ነበር በክብሩ መገለጥ ጊዜ ኤልያስስ ተወሰደ እንጂ አልሞተም ለነገሩ ብዙም ልብ አላሉትም ከመደንገጣቸው በቀር እናም አሁን ከሙታን መካከል እነሳለሁ ሲል እንደነገሩ ሰምተውታል ግን ሆኖ ስለማያውቅ ችላ ብለውታል ለዚህም ነው ከሞተ በኃላ ሁሉም ወደ ጉዳዩና ህይወቱ የተመለሰው ከትንሳኤው በኃላ አብሯቸው ባይሆን አይጸኑም ነበር:: እጅግ የሚምርና የሚራራ ጌታ ራራላቸውና ወደ አገልግሎታቸው አበርትቶ መለሳቸው:: ዛሬስ እንዴት ባለ ልብ ይሆን ቃሉን የምንሰማው? እናስተውል ጌታ በብዙ መንገድ ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም ነውና የሚለው በማስተዋሉ ይሙላን::

እርሱ ስለሞትና ትንሳኤው ሲያስተምራቸው የእነሱን ልብ የያዘው አሳብ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? ነበር! ስለዚህም ጌታ ትልቅ ለመሆን ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው ይሄ መቼም ለሰው የሚመች አይደለም ግን ዝቅ ማለትን መማር አለብን:: ጌታ እኮ ሁሉን ትቶ ነው የባሪያን መልክ ይዞ የመጣውና ደግሞም የመስቀል ሞት የታዘዘው በዚህም ምክንያት ከልክ በላይ ከፍ ከፍ አደረገው እግዚአብሔር አብ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ሰጠው:: አሜን! ሃሌሉያ! ስለዚህ ዝቅ ብለን ሌሎችን እናገልግል የተወልን ፍለጋው ይህ ነውና::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነው

የማርቆስ ወንጌል 9: 38-41
38፤ ዮሐንስ መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ስለማይከተለንም ከለከልነው፡ አለው። 39 ኢየሱስ ግን አለ። በስሜ ተአምር ሠርቶ በቶሎ በእኔ ላይ ክፉ መናገር የሚችል ማንም የለምና አትከልክሉት፤ 
40 የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነውና። 
41 የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ። 

በክርስቶስ አንድ አካል መሆናችን ካልገባን እንደ ዮሐንስ ህግ አስከባሪ አጋፋሪዎች መሆናችን ነው:: የሚሆኑትን ነገሮች ለክርስቶስ ነው ወይ ከማለት ይልቅ ከቤተክርስቲያናችን ህግ ውጪ ነው የሚል አባባል ሲቀድም ብዙ ታዝበናል መቼም:: መንግስቱን የሚያስፋፋ ከሆነ እንዲያውም በርታ ምን እንርዳህ ነው መባል ያልበት:: በኦርቶዶክስ ተሀድሶ ህብረት ውስጥ እያለሁ እነዚህን በብዙ ሰምቻለሁ ከአስራ ሁለቱ ነገድ ውጪ እንዴት ሆኖ ዘራፍ የሚሉ ብዙ ነበሩ የተወሰኑት ደግሞ ይህ ከእግዚአብሔር ነው ብለው ደግፈውናል:: በእኔ በኩል ሳንሱር አድርጌ ካላሳለፍኩት እንዴት ሆኖ? አንበል በቅድሚያ እንመርምር አለበለዚያ ዝም ማለት ይሻላል:: ከእግዚአብሔር ከሆነ ይዘልቃል ካልሆነ ደግሞ ይከስማል:: ከቻልን እንጸልይ በጉዳዮ::

የጌታ መልስ ግን በስሜ ተአምር ሠርቶ በቶሎ በእኔ ላይ ክፉ መናገር የሚችል ማንም የለምና አትከልክሉት፤  ቃሉ እንደሚል ለውሳኔ አንቸኩል ሁሉን በፍቅር መነጽር እንይ ደግሞም አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል ይላል:: በሌላም ስፍራ ላይ እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። እንጠንቀቅ ለአስተያየታችን:: ስለዚህ የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነውና በህብረት የመንግስቱን ስራ እንስራ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእኔ የሚያምኑትን አታሰናክሉ

የማርቆስ ወንጌል 9: 42-50
42፤ በእኔም ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር። 43 44 እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመሄድ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል። 
45 46 እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመጣል አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። 
47 48 ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነመ እሳት ከመጣል አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል። 
49 ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል። 
50 ጨው መልካም ነው፤ ጨው ግን አልጫ ቢሆን በምን ታጣፍጡታላችሁ? በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።

ጌታ በደሙ ዋጅቶ ወደ ቤቱ ያመጣቸውን ታናናሾች ከማሰናከል እንድንቆጠብ ነው ጌታ የሚያሳስበው:: ማሰናከል በብዙ መንገድ ይገለጣል:- ክርስቶስን የማያከብር ኑሮ፥ በስህተት ትምህርት፥ ቅድስናን ባለመጠበቅ እና ሌላ ብዙ ማሰናከያ ማንሳት ይቻላል መዳናችንን በፍርሃት እንፈጽም:: ይህን የሚያደርግ ሞት ነው የሚገባው እያለ ነው ጌታ ስለዚህ ህይወታችንን እንመርምር እንቅፋት እንዳንሆን በቤቱ:: ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ሰውን የምናሰናክለው ለስጋችን ጥቅም ነው እንጂ መቼም ለጌታ አይደለም ማሰብ ያለብን ሁሉን ጥለን እንሄዳለን ታድያ ለዘላለሙ ህይወት ብንተጋ አይሻልም:: ላለማሰናከል ያለህን ሁሉ ስጥ ነው እያለን ያለው ወደ ሲኦል ከመጣል ሁሉን በቅን ልብ አገልግለን ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባትን ምርጫችን እናድርግ::

ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ እኛ በመንፈስ ቅዱስ እሳት ተሞልተን ለእግዚአብሔር የተለየንና የተቀደስን ነን:: መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል እንደሚል የአፋችን ፍሬ የሆነው መስዋት በጨው የተቀመመና ጌታን ደስ የሚያሰኝ ይሁን:: መቼም በአዲስ ኪዳን የእንስሳ መስዋዕት አናቀርብም የአፋችንን ፍሬ እንጂ:: ስለዚህ ከዚህ አንደበት መውጣት ያለበት ቃል የሚያንጽና የሚያጽናና ከልብ የሆነ እውነተኛ ቃል መሆን አለበት:: ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን ይላል ቃሉ። ስለዚህም ነው በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ የተባልነው፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ እንደሚል ሰው ለራሱ መኖር ካቆመ ጌታን ለማገልገልና ደስ ለማሰኘት የሚያግደን ስለማይኖር ከሌላው ጋር ተስማምተን እንሰራለን::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 10

ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው

የማርቆስ ወንጌል 10: 1-12
1፤ ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ ደግሞም ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ እንደ ልማዱም ደግሞ ያስተምራቸው ነበር። ፈሪሳውያንም ቀርበው። ሰው ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። 
እርሱ ግን መልሶ። ሙሴ ምን አዘዛችሁ? አላቸው። 
እነርሱም። ሙሴስ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ አሉ። 
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ። 
ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ 
ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ 
ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። 
እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። 
10 በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር ጠየቁት። 
11 እርሱም። ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤ 
12 እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።

ሊፈትኑት ፈልገው ነው ስለፍቺ የጠየቁት ህግ ሰጪውን ከማን ጋር እየተነጋገሩ እንዳሉም አያውቁምና:: እነሱ ለእግዚአብሔር የቀኑ መስሏቸው እሱኑ ሊያስደስቱት የሚፈልጉትን ገፉት! ስለፍቺ የሰጣቸው መልስ እርሱ ስለትዳር ያሰበው ገና ከፍጥረት መጀመሪያ እንደሆነ ነገራቸው:-

  1. ከፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ ተሳስቶ የማያውቀው እግዚአብሔር እንደዚህ ፈጥሮናልና ይህ ዘመን አመጣሽ ችግር በዚህ ቃል ይፈታል ወንድ ወንድ ነው ሴትም ሴት ናት አለቀ:: ጠላት ሁሌ እግዚአብሔር አቅዶ ያደረገውን ነገር ለመምታት ይፈልጋል ግን አይሆንም ህብረተሰቡ እንኳን ቢቀበላቸው ሰዎች እራሳቸውን መቀበል ስለማይችሉ እራስን ወደ ማጥፋት ይሄዳሉ ይህም የጠላት ግብ ነው ሰውን መግደል ጌታ ግን ነፃ ሊያወጣን መጣ:: ሃሌሉያ!
  2. በጋብቻ ሲተሳሰሩ ባል አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ለዚህም ነው የባል ቤተሰብ ከትዳር መካከል መውጣት ያለበት እርሱ ነው ቤተሰቡን ትቶ ከሚስቱ ጋር መተባበር ያለበት:: ይህ የብዙ ትዳር መፍረሻ ምክንያት ነው የባል ቤተሰብ ልጃቸው እንደተጎዳ ነው የሚያስቡት አይተው የማያውቁት አይነት መታዘዝና ሚስቱን መስማቱን ሲያዩ የተበደለና እየተጫነችው አለቃ የሆነችበት ስለሚመስላቸው ጣልቃ መግባት ይፈልጋሉ ግን እንደዛ አይደለም ቤተሰብ ከልጆች ትዳር መውጣት አለበት ይህ የእግዚአብሔርም አቋም ነው::
  3. ሁለቱም አንድ ስጋ ይሆናሉ:- ህብረታቸው አንድ የመሆን ነው:: ትዳርን የመሰረተ እራሱ ስለሆነ ነው በመጀመሪያ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ተአምራትን ያደረገው በየትኛውም ትዳር ውስጥ ጌታ አለ ያንን ህብረት የመሰረተው እርሱ ነውና በመካከላቸው ተገኝቶ ቃል ኪዳናቸውን ያከብራል::
  4. ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም:- በእግዚአብሔር ፊት አንድ እንደሆኑ ነው የሚያውቀው:: ልክ አንድ ሰው ተነስቶ ሰውነቴ ለሁለት ይከፈልልኝ ብሎ እንደመጠየቅ ነው:: ይህ እብደት ነው የሚባለው ፍቺም እንደዛው ነው ካለ ዝሙት በቀር::
  5. እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው:- በመካከላቸው ተገኝቶ አጽድቆ አጣምሮ ከሁለት ሰው አንድ ሰርቷልና መለያየት የጌታን ህግ መተላለፍ ነው እንጂ እንደቀላል ተነስተን እነ እከሌ አድርገውታልና ምን ችግር አለው ብሎ ነገር አይሰራም ይህ የልብ እልህ እንደሆነ ቃሉ ይነግረናል ከሞትን ለጌታ ሁሉ ሰላም ይሆናልና እንሙት በፊት::
  6. ትዳሩን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ስለዚህ ትዳራችንን እንንከባከብ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊት ጸድቋልና:: ባል ሚስቱን ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደደ ይውደዳት እንዲሁም ሚስት ለባልዋ ትገዛ እርሱ ራስ ነውና:: በሌላ ስፍራም ላይ ቃሉ የሚለን:- ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንደህፃናት እንሁን

የማርቆስ ወንጌል 10: 13-16
13፤ እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። 14 ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና። ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። 
15 እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው። 
16 አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው። 

የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ ጌታችን:: ህፃናትን ስናስብ ሁሉን ያምናሉ ለምሳሌ:- በኃላ ስመጣ ክንፍ ይዤ እመጣና ትበራለህ ቢባል ችግር የለበትም ልጅ ሲያስብ የሚውለው የት ድረስ እንደሚበር እንጂ ልወድቅ እችላለሁኝ ብሎ እንኳን ለቅጽበት አይጠራጠርም ወላጁን አምኖ በጉጉት ይጠብቃል:: ጥርጣሬ የለም አምኖ ቁጭ ነው የሚለው:: እኛስ?! ብልጥ ነን አይደል እግዚአብሔር ላይ ከመደገፍ ይልቅ የአውሮፕላን ትኬት ብትገዛልኝ በረርኩ ማለት ነው ብለን ቁጭ! ቃሉን ለኛ እንዲመች ቀይረን እንሰማለን ምክንያቱም ለአእምሮ የማይመች ብለን እንፈርጃለን የእግዚአብሔርን ድምጽ:: አይይ ይሄ አስተሳሰባችን በጌታ ቃል ይሞላ እናም ቃሉን ህያው እንደሆነ እንቀበል ምክንያቱም ጌታ ያለን ይህ የምናገረው ቃል ህያው ነው መንፈስም ነው ብሎናልና! እ ን መ ን!!!
ሌላው የልጅ ባህሪ አሁን አጥፍቶ ተቀቶ እያለቀሰ ወደ ስራችን ይገባል የሚቀየምን ልብ የለውም ይቅር ይላል እኛም በይቅርታ ካልተመላለስን ፀሎታችን እንኳን አይሰማም ጉንጭ ማልፋት ብቻ ነው የሚሆነው ከወንድምህ ጋር አንዳች ካለህ መስዋዕቱን አስቀምጥና በፊት ታረቅ ነው የሚለን ቃሉ:: ስለዚህ እንደልጅ በፊቱ እንመላለስ እንመነው የሚለንን ሳንጠራጠር እንቀበል::

አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው:- ሳነበው ገና ደስ አለኝ የጌታ ልጅ ነኝ ዛሬም እቅፍ አድርጎ ይባርከኛል እንደሁልጊዜው ስሙ ይባረክ:: ሁልጊዜ የሚባርክ የሚንከባከብ እረኛ ነእጥሎን ወዴትም አይሄድም እርሱ አስቀድሞ ወደደን እርሱ ወደ መንግስቱ ዋጋችንን ከፍሎ ተቤዠን! ስሙ ይባረክ! ልጆቹን ይወዳል ይባርካል ጌታ! ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል

የማርቆስ ወንጌል 10 17-31
17፤ እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። 18 ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። 
19 ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። 
20 እርሱም መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው። 
21 ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው። 
22 ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ። 
23 ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው። 
24 ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ። ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። 
25 ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው። 
26 እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው። እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ። 
27 ኢየሱስም ተመለከታቸውና። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ። 
28 ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ይለው ጀመር። 
29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ 
30 አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። 
31 ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ። 

ይህ ሰው ለእየሱስ ሰገደና ቸር መምህር ሆይ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀ:: ይህ ሰው በትክክል ከልጅነቱ ጀምሮ ነው ትዕዛዛትን የፈጸመው እናም የጎደለኝ ይኖር ይሆን ወይ ብሎ ነው ጌታን እየጠየቀ ያለው:: ጌታም ወደደውይላል ቃሉ:: ሐብትህን ለደሀ ሰተህ ተከተለኝ ሲለው እርሱን ማድረግ አልቻለም ከበደው ምክንያቱም ገንዘብን ወዷልና:: ገንዘብን መውደድ ደግሞ የሐጥያት ሁሉ ስር ነውና ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻልም አንዱን መተው ለሌላው መገዛት ግድ ነው ከሁሉ ነገር ይልቅ እንደአምላክ የተቆጠረ ገንዘብ ነው:: ጌታም ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው አለ:: ምን በሚሉ? በገንዘብ ለ ሚ ታ መ ኑ! አንታመንበት መታመኛችን ጌታ ብቻ ይሁን! ንስሀ ልንገባ ይገባል ራሳችንን ብንመረምር አይፈረድብንም እንደሚል ቃሉ ፈትሸኝ በደምህም እጠበኝ እንበለው::

ግን እኮ ይህ ሰው የሳተው የትዕዛዝ ሁሉ መጀመሪያ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ የሚለውን ነው:: በአንዱ የወደቀ በሁሉ ወድቋል:: ስለዚህ ምክንያት ነው ጌታ እየሱስ የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ሁሉ ሐጥያት ሊሸከምና ሊቤዠን የመጣው:: ክብር ለስሙ ይሁን ሁሉ ሐጥያትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል የሚለው እውነት ነው ምክንያቱም አንድ የሚችል ቢገኝ ኖሮ እየሱስ ባልመጣ ነበር ሁሉላችንም ከሐጥያት ቀንበር በታች ነበርን ጌታ ባይመጣልን ኖሮ ሌላ መፍትሄ የለንም ነበር::

ማን ሊድን ይችላል ብለው ግራ ሲገባቸው ኢየሱስ ተመለከታቸውና። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ። አሜን እርሱ በጸጋው ይረዳናል በገንዘብ ላይ አለቃው ሆነን እንድንሰለጥንበትና እንድናሰራው እንጂ በራሳችን አንዳክር ለሚረዳው መንፈሱ እራሳችንን እናስገዛ:: ምንም የከሰርነው ነገር የለም ጌታን ተከትለን ዓለምን ንቀን ሁሉ አለን! ጌታም እንዳለን በዚህ ዘመን ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። አሜን መቶ እጥፍ ነው የተሰጠን:: ይህንን ካለን በኃላ ደግሞ ለጥንቃቄ ይሆን ዘንድ ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ አለ ሁልጊዜ አቋማችን አንድ ይሁን ለእርሱ መገዛት ሌላው ሁሉ ይጨመራል::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እየሱስ ስለሞትና ትንሳኤውን ተናገረ

የማርቆስ ወንጌል 10: 32-34
32፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፥ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም አሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር፦ 33፤ እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፥ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፥ 34፤ ይዘብቱበትማል፡ ይተፉበትማል፡ ይገርፉትማል፡ ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፡ አላቸው::

የሞትና የትንሳኤውን ነገር ደግሞ ደጋግሞ ነው የነገራቸው እነርሱ ግን ብዙም አያስተውሉም ነበረ:: ጌታ እየሱስ ስለእኛ የሚሆንበትን ሲናገር እንደሚዘብቱበት፡ እንደሚተፉበት፡ እንደሚገርፉት፡ እንደሚገድሉት፥ ነገር ግን በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ፡ ተናገረ:: አምላክ የሆነው እየሱስ በራዕይ ላይ ዮሃንስ ባየው ጊዜ እንደሞተ ሰው ነበረ የሆነው ትላንትና ደረቱ ጋር ጠጋ ብሎ እንዳላወራው ዛሬ ግን በፊቱ መቆም እንኳን አይቻልም:: ይህንን ጌታ ነው እንግዲህ የዛቱበት የተፉበት የገረፉት የተዘባበቱበት ብሎም የገደሉት:: ትልቅ ሆኖ ሳለ ህይወት ሰጪ ሆኖ ሳለ አሰቃዩት ምን አይነት ፍቅር ነው:: ክብሩን ሁሉ ትቶ ለዚህ አንድ ጉዳይ ወደ ምድር መጣ ህይወቱን ሰጠ በግ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንዲል እርሱም ዝም አለ:: ወደ እየሩሳሌም ለህይወቱ ሳይሰስት ሲያቀና ይገርማል ይህ የሆነው ለእያንዳንዳችን ነውና ክብር ይገባዋል! አሜን!


ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን

የማርቆስ ወንጌል 10: 35-45
35፤ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው፦ መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን፡ አሉት። 36 እርሱም። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው። 
37 እነርሱም። በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት። 
38 ኢየሱስ ግን። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አላቸው። 
39 እነርሱም። እንችላለን አሉት። ኢየሱስም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 
40 በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው። 
41 አሥሩም ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ይቈጡ ጀመር። 
42 ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። 
43 በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ 
44 ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ 
45 እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። 

ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው እየሱስ ለወንድማማቾቹ እነሱም የተለመነውን ሁሉ ሲያደርግስላዮት አሁን ደግሞ ልሞት ነው እያለ ነው ሳንጠይቀው ከምንቀር ብለው ልባቸውን ሞላ አድርገው በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት:: ግን የውስጥ ጥያቄያቸው ምንድነው? ታላቅ መሆን ነው ምክንያቱም በመልሱ ውስጥ ጠቅሶታል ጌታችን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ ነበረ መልሱ:: እየሱስ ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣምና አለ:: እርሱ ዝቅ ብሎ ሊያገለግል ከመጣ ተከታዮቹም ይህንን እንዲያደርጉ እና ያንን ያገልጋይነትን ልብ እንድንይዝ ነው የሚፈልገው:: ዛሬም እኔ ይህንን አደረኩ ያንን አደረኩ ከማለት እርሱ ይህንና ያንን አደረገ ማለትን እንማር:: እርሱን ከፍ እናድርግና እናክብር::

የሚገርመው የምትለምኑትን አታውቁም ነበር የጌታ የመጀመሪያ መልስ። ሲቀጥልም እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አላቸው። ጽዋ? ምን ችግር አለው አሉ:: ጥምቀት? እንዴ ዮሃንስ ሲያጠምቅ አይተን የለም እንዴ? እንችላለን አሉ እርሱ ግን ስቃዩን ጽዋ ሞቱን ደግሞ ጥምቀት እያለ እንደሆነ አላስተዋሉም ነበር:: ለዚህ ነው ጥምቀት ከእርሱ ጋር ሞተን እንደመነሳት የሚታይ ስርዓት የሆነው:: እናም በዚህ ጸሎት መሰረት ያዕቆብ የመጀመሪያው መስዋዕት ሆነ የምንለምነውን እንወቅ:: ጴጥሮስ ግን ተረፈ መትረፍ ከማይችልበት ጥብቅ ጥበቃ ውስጥ ወጥቶ ጌታን አገለገለ:: የሚገርመው ሐዋርያት በአስራ ሁለቱ ነገዶች ላይ የሚፈርዱ ነበሩ እንጂ በቀኝና ወይም በግራ የሚቀመጡ አይደሉም ደግሞም የሚቀመጡት የተዘጋጀላቸው ሰዎች ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው። ቃሉን ስለማያውቁ ወይም ስላላስተዋሉ ይስቱ ነበረ:: ቃሉን እንወቅና እንደቃሉ እንጸልይ ጌታም ይሰማናል::


ኢየሱስም ምን ላደርግልህ ትወዳለህ አለው?

የማርቆስ ወንጌል 10: 46-52
46፤ ወደ ኢያሪኮም መጡ። ከደቀ መዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጣ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስ እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር። 47 የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ። የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ይጮኽ ጀመር። 
48 ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። 
49 ኢየሱስም ቆመና። ጥሩት አለ። ዕውሩንም። አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል ብለው ጠሩት። 
50 እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ። 
51 ኢየሱስም መልሶ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? አለው። ዕውሩም። መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ አለው። 
52 ኢየሱስም። ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው።

ብዙዎች ዝም እንዲል የገሰጹት ማየት የተሳነው በርጤሜዎስ ግን የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። ያለበትን የሚያውቀው እርሱ ነው እንዴት አብዝቶ አይጮህ ጠዋት ማታ እርዳታ የሚጠይቅ ምናልባትም ሰው የሰለቸው ሰው ነው:: ታድያ እንዴት አብዝቶ አይጮህ? እኛም በጉዳዮቻችን ስንጸልይ አብዝተን እንጩህ ይሰማናልና::

ኢየሱስም ቆመና። ጥሩት አለ። ዕውሩንም ዝም በል ብለው የገሰጹት ሁሉ አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል ብለው አሉት:: መጽናት ጥሩ ነው ጸንተን ባለመናወጥ ፊቱን እንፈልግ:: እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ።  ኢየሱስም ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? አለው። እርሱም ምንም ጊዜ ሳይወስድና ሳያቅማማ መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ አለው። ለጌታ የሚሳነው ነገር የለም ስንጸልይ በእኛ ልክ አይሁን የእርሱን ታላቅነት አይተን እንጂ:: ኢየሱስም። ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም:: የመንግስተ ሰማያት መገበያያ እምነት ነው በእምነት ነው የምንቀበለው:: ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው። አይኑን አልነካው አልዳሰሰው ወይም ጭቃ አልቀባው ሄደህ ታጠብ አላለው እምነትህ አዳነህ ሲለው አጥርቶ አየ ደግሞም መጸለይ አላስፈለገውም:: የጌታ አሰራር ግሩም ነው ሁልጊዜ አንድ እንዲሆን አንፈልግ እርሱ ሉአላዊ አምላክ ነውና ብቻ ከእርሱ ጋር እንስማማ የሚለንንም እንስማ ያስደንቀናል ስሙ ይባረክ! ሃሌሉያ! የተፈወሰው ሰው እራሱ ተከተለው ሰው ከእስራቱ ሲፈታ የተደረገለትን ሲያውቅ ጌታውን ይከተላል::

ዛሬ በምን ላይ ነው የጌታን ፊት የምትፈልጉት? ይሰማል በርቱና ጸልዮ ፊታችሁም አያፍርም:: እርሱየታመነ ጌታ ነውና!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 11

ሆሣዕና በአርያም

የማርቆስ ወንጌል 11: 1-11
1፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወዳሉቱ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወዲያውም ወደ እርስዋ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። 
ማንም። ስለ ምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፥ ወዲያውም ደግሞ ወደዚህ ይሰደዋል አላቸው። 
ሄዱም ውርንጫውንም በመንገድ መተላለፊያ በደጅ ውጭ ታስሮ አገኙት፥ ፈቱትም። 
በዚያም ከቆሙት አንዳንዶቹ። ውርንጫውን የምትፈቱት ምን ልታደርጉት ነው አሉአቸው። 
እነርሱም ኢየሱስ እንዳዘዘ አሉአቸው፤ ተዉአቸውም። 
ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡት፥ ልብሳቸውንም በላዩ ጣሉ፥ ተቀመጠበትም። 
ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር። 
የሚቀድሙትም የሚከተሉትም። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ 
10 በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። 
11 ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቅደስ ገባ፤ ዘወር ብሎም ሁሉን ከተመለከተ በኋላ፥ ጊዜው መሽቶ ስለ ነበረ ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። 

ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቅደስ ገባ፤ ዘካርያስ 9: 9፤ አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። እንደተባለው ትንቢት ተፈጸመ እንደገናም በሐጌ 2 ላይ እንዳለው ትንቢት ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምክንያቱም እራሱ ንጉሱ በትህትና በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ገብቷልና ነው:: ሃሌሉያ! እንደዚሁም ደግሞ በመዝሙረ ዳዊት 118: 25፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና። 26፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ። የሚለውን ቃል ሆሳእና እያሉ እያስተጋቡ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ያነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።  በቁጥር 27፤ እግዚአብሔር አምላክ ነው፥ ለእኛም በራልን፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ፡ የበዓሉን መሥዋዕት በገመድ እሰሩት። እንደሚል ይህ የእግዚአብሔር በግ እየሱስ ለእያንዳችን መስዋዕት ይሆን ዘንድ እራሱን አሳልፎ ለመስጠት አዘጋጀ:: ዋዉ ምን አይነት ፍቅር ነው?! እናመሰግንሀለን አባት ሆይ!

የሚገርመው ሌላው ታሪክ የአህያይቱ ውርንጫ ነገር ነው የት እንደሚያገኙአት ነግሮ ላካቸው ሄደው ያላቸው ቦታጋ አገኙአት ባለቤቱም አልከለከለም ፈቀደላቸው:: ጌታ ቀድሞ ተናግሮታል ማለት ነው ሳይከራከር ፈቀደላቸው:: ስንት ጊዜ ይሆን ከእርሱ ዘንድ ሰምተን የተባበርንና የታዘዝነው? እግዚአብሔር በብዙ ጎዳና ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም የሚለው እንዳይፈጸምብን ወደፊቱ እንምጣና በፊቱ እንገኝ ሲሰራም አብረነው ሰራተኞች እንሁን:: የውርጫዋ ባለቤት የዋህ ሆኖ የመጣውን ንጉስ የምታስቀምጥ እንሰሳ አበረከተ:: እኛስ ምን ተጠይቀን ይሆን? ዛሬ ለጌታ የሚያስፈልገውን ወደ ፊቱ እናምጣ::
ሌላው አህያዋ ማንም ተቀምጦባት አያውቅም ይላል መቼም ብዙ ስለ እንሰሳ ባላውቅም ፈረስ እንደሚሰለጥነው መሰልጠን አለበት ብዬ አስባለሁ ነገር ግን ምንም ያልሰለጠነ ውርንጫ ላይ ቢሆንም የተቀመጠው አላስቸገረውም ለዚህ ጌታ ፍጥረት ሁሉ ይታዘዘዋል:: ሊታደገው የመጣለት የአዳም ዘር ግን አልታዘዘም ጌታውንም አላወቀም ስለዚህ በኢሳይያስ 53 እንደሚለው በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ብሎ ጌታ የጠየቀው ተፈጸመ:: ዛሬ ልባችንን እልኸኛ አናድርግ የሚናገረንን እንስማና እንታዘዝ:: ንጉሳችን ጻድቅና አዳኝ ፤ ትሑትም ነው ታድጎናልና ለእርሱ ክብር እንኑር!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!!


በለሲቱን ረገመ

የማርቆስ ወንጌል 11: 12-14
12 በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። 
13 ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 
14 መልሶም። ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ። 

የበለስ ወራት አይደለም ለምን ፍሬ ፈልጎ መጣ? እርሱ አምላክም ነው ፍሬ እንደማይኖረው ሙሉ እውቀት የለውም? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጤ ናጡኝና ምን ይሆን የዚህ ትምህርት ሚስጥር ብዬ ጸለይኩኝ መቼም ለመናገር ያህል አይናገርምና መልክትማ አለው::

የበለስ ዛፉ አላናገረውም ነገር ግን ጌታችን “መልሶም” ይላል ልክ ንግግር ውስጥ እንደነበረ:: ምን እያለ ነበር ዛፉ? የበለስ ወራት ባይሆንም ቅሉ ደርሻለሁ ፍሬ አለኝ የሚል የውሸት መረጃ እያሳየ ነበረ:: እኛም ዛሬ ብዙ የወሸት መረጃ የሚሰጡንን ጉዳዮች ጭራ ይዘን በዙሪያችን እንሸበራለን ስለጤና ቢሆን ስለስራ ቢሆን ስለቤተሰብ ስለአገር ሌላም ሌላም ጉዳይ:: ዓለማትን ሁሉ በቃሉ የፈጠረ በቃሉ ደግሞ ማድረቅም ይችላል እኛም በስሙ እንድናደርቅ ስልጣን ተሰቶናል::

ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም እየሰሙ ነው የተናገረው የመለሰ ወይም የጠየቀም የለም እንደነገሩ አለፉት እንጂ ከዚህ ውስጥ የፈጣሪነቱን አንደምታ እንደሚያዩ አላወቁም:: ስለምንናገረው ነገር ማስተዋል ይስጠን ስንት ጊዜ ይሆን በሀይለ ቃል ሰውን የሚጎዳ የእርግማን ቃል የተናገርነው? እናስተውል ምን ከአንደበታችን እንደሚወጣ:: የአንደበትህን ፍሬ ትበላለህ ይላልና ቃሉ ስለዚህ ትዳራችንን ፤ ልጆቻችንን፤ አካላችንን ፤ ቤተሰባችንን ፤ አብረውን የሚያገለግሉትን ፤ አገራችንን ሁሉ እንባርክ! የምትባርክ ነፍስ ደግሞ ትባረካለች:: ዛፍዋ ደግማ ፍሬ እንዳትሰጥ በተነገራት መሰረት ዝቅ ብለን ስናነብ እንደደረቀች እናያለን::

ይህንን ምሳሌ ወደ ህይወታችን ስናመጣው ደግሞ ጌታ ከህይወታችን ፍሬ ይፈልጋል ወራትን ጠብቆ አይደለም ፍሬ መገኘት ያለበት በህይወታችን ምክንያቱም ፍሬ ልናፈራ ተሹመናልና ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም ፍሬ የማፍራቱ ጉዳይ:: ዕለት ዕለትም እርሱን ወደ መምሰል ማደግ አለብን:: ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ገበሬው አብ ይቆርጠዋል፤ ይደርቃል ወደ እሳትም ይጣላልና ፍሬ ይኑረን በወይኑ ግንድ ላይ ሆነን ማፍራት አለብን:: ጆሮ ያለው ይስማ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች

የማርቆስ ወንጌል 11: 15-19
15፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ወደ መቅደስም ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ 16 ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም። 
17 አስተማራቸውም። ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። 
18 የካህናት አለቆችም ጻፎችም ሰምተው፥ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ይገረሙ ስለ ነበር ይፈሩት ነበርና እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ፈለጉ። 
19 ማታ ማታም ከከተማ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር። 

ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ብሎ ያለበት ምክንያት መስዋዕት ለማቅረብ የሚመጡት ሰዎች የሚገበዩት ከዛው ከቤተመቅደሱ ስለሆነ ከቀን ወደ ቀን ቅልጥ ያለ የገበያ ስፍራ ሆኗልና ነው:: ቤቱ ካለመከበሩም የተነሳ መተላለፊያ ሆኖ ነበር የሲናን ተራራ የረሱ ይመስላል ማንም ወደ ተራራው ቢጠጋ ይሞታል የሚለውን:: እግዚአብሔር በአብዛኛው እስራኤላዊ ዘንድ ችላ የተባለበት ጊዜ ነው ብል ማጋነን አይሆንም:: ይህንን ወደራሳችን እናምጣው እስኪ:- ዛሬ ቤቱ እኔ ነኝ ህንፃው አይደለም በውስጤ ምን አለ? ጸሎት? ምስጋና? ቃሉ? አምልኮ ወይንስ እርሱን ደስ የማያሰኝ ነገር ልቤን ሞልቶት ይሆን? በአእምሯችን መታደስ ልንለወጥ ይገባል ይህንንም የሚያደርገው ህያው የሆነው ቃሉ ነው:: ቃሉን በልባችን እንሸሽግ እናሰላስለው ያን ጊዜ አላስፈላጊውን ቁሻሻ ሁሉ ከእኛ እያስወጣ በሌላ መገለጥ እያስደመመ ወደ ጌታ ያስጠጋናል:: ሃሌሉያ! በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ ነው የሚለን ቃሉ ስለዚህ እዚህ ላይ እናተኩር አስተሳሰባችን መረን ሲለቅ ዝም አንበለው እናግደውና የሚያስበውን እንስጠው አለበለዚያ ግን የጌታ ማደሪያ እንዴት እንሆናለን? ማስተዋል ይስጠን!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእግዚአብሔር እመኑ

የማርቆስ ወንጌል 11: 20-26
20፤ ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት። 21 ጴጥሮስም ትዝ ብሎት። መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው። 
22 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። በእግዚአብሔር እመኑ። 
23 እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። 
24 ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። 
25 ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። 
26 እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። 

ጴጥሮስ ማለዳ ሲያልፉ በአንድ ቀን መድረቋን አስተውሎ ለጌታ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው:: ታድያ ከአፉ ቃል ወቶ ላይተገበር ይችላል? በፍጹም! ጌታም አልደነቀውም ትላንትናም ቆሞ እስክትደርቅ አልጠበቀም ወይም ደግሞ ሲያልፉ አያችሁ እንደደረቀች አላለም የተናገረው እንደሚሆን ያውቃልና:: ይልቁንስ እኛ እናስተውል ለምነን እዛው ቆመን ደረቀ አልደረቀ ቅጠሉ ጠወለገ? እያልን ጸሎታችንን ሲሰራ ለማየት እንሞክራለን ግን አለማመን ነው:: ከለመንን ተሰምተናል ከተናገርንም ቃላችን ይተገበራል ብለን ማመንና ማመስገን አለብን::

በእግዚአብሔር እመኑ አለ ጌታ እንዴት እንመን?

  1. ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን – መቼም ሁላችንም ማንም የሚለው ዝርዝር ውስጥ እንገባለን:: ያለው፥ የፀለየው ወይም የተናገረው እንዲደረግለት ቅድሚያ ሁኔታ አለው እያለን ነው እሱም:-
  2. በልቡ ሳይጠራጠር፥ ለዚህ ነው በእግዚአብሔር እመኑ ያለው ጌታ
  3. ይህን ተራራ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ምንድነው ተራራችን ዛሬ እንዲነቀል በእምነት ያለጥርጣሬ እንጸልይ
  4. የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ማመን ያስፈልጋል ለመጸለይ ብቻ ሳይሆን ከጸለይንም በኃላ ለመቀበልና ፀንተን ለመጠበቅ
  5. ይሆንላችሁማል። አሜን!

ጸሎት የሚከለክል ነገር ጌታ የነገረን በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም ይቅርታን ካላገኘን ደግሞ ጸሎታችን አይሰማም:: ስለዚህ በይቅርታ እንመላለስ:: ለየትኛው ክብራችን ሰስተን ነው ዝቅ ብለን ይቅርታ የማንጠይቀው ወይም ይቅር የማንለው?! እኛ እኮ የራሳችን አይደለንም የጌታ እንጂ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ?

የማርቆስ ወንጌል 11: 27-33
27፤ ደግሞም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እርሱም በመቅደስ ሲመላለስ፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ 28 እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ እነዚህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። 
29 ኢየሱስም። እኔም አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም መልሱልኝ፥ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ። 
30 የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ አላቸው። 
31 እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ነው ብንል። እንግዲያውስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ 
32 ነገር ግን። ከሰው ነው እንበልን? አሉ፤ ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና ሕዝቡን ፈሩ። 
33 ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።

የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? ብለው የሚገርም ጥያቄ ጠየቁት ስልጣን ሰጪውን! ይገርማል! ግን ሊከተሉት እንዳልሆነ እውን ነው የሚከሱበትን ነገር እንዲያገኙ እንጂ! ዮሃንስ ከአወላለዱ ጀምሮ በተአምራት ነበረ ይህ ህፃን ማን ይሆን ብለው እስኪጠይቁ ነበር እዚህ ጋር ግን አገልግሎቱ ከሰማይ ነበረ ወይ ሲባሉ አዎን ለማለትም እንዳልፈለጉ እናያለን:: ከሰማይ ነው ካሉ ደግሞ ዮሃንስ ታድያ ስለእኔ የመሰከረውን ለምን አልተቀበላችሁም ይመጣባቸዋልና መልሳቸው መሀል ላይ ነበር አናውቅም::

እነዚህ ሰዎች ያላስተዋሉት ነገር ቢኖር እየሱስ ፈጣሪ መሆኑንና ደስ ሊያሰኙት የሚፈልጉት ጌታ በትህትና በመካከላቸው መገለጡን ነው:: ለጌታ ቀናን ብለው ስንቶች የእግዚአብሔርን መልክተኞች አደናቅፈው ይሆን? እንጠንቀቅ ካልገባን ዝምታን እንምረጥ እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር ስንጣላ እራሳችንን እንዳናገኝ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 12

ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ

የማርቆስ ወንጌል 12: 1-12
1፤ በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ 
ይዘውም ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። 
ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት አዋርደውም ሰደዱት። 
ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፥ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ አንዳንዱንም ገደሉ። 
የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ። 
እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለው፥ ርስቱም ለኛ ይሆናል ተባባሉ። 
ይዘውም ገደሉት፥ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት። 
እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል ገበሬዎቹንም ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። 
10 
11 ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው። የሚለውን ይህን መጽሐፍ አላነበባችሁምን? 
12 ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ። 

ጌታችን የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ገበሬዎቹ ግን ታማኝ ሆነው አልተገኙም መልክተኞችን ሲልክ ይደበድባሉ ይገድላሉም:; ይህ ምሳሌ ስለእስራኤል ነው ከባርነት አውጥቶ በከንዕን ተከላቸው ምድራቸውን ባረከ ምድረ በዳ ቢሆንም እንኳን ፍሬ እንዲሰጣቸው አደረገ:: ንጉስ አንግስልን ሲሉግም ንጉስ አነገሰላቸው ወደ ጦርነትም ሲወጡ ተዋጋላቸው ከአብርሃም ጋር ስለገባው ቃሉ አብርሀም በሌለበት እንኳን በታማኝነት ፈጸመው:: ይህን ሁሉ ያደረገው በስተመጨረሻ በእነርሱ በኩል መጥቶ ዓለምን ለመዋጀት ነበረ ስሙ ይባረክ:: ልክ ምሳሌው ላይ እንዳለው ያልተደበደበና ያልሞተ መልክተኛ ወይም ነብይ የቱ ነው? ሁሉንም ገደሉ እንዲያውም ልጁ ወራሽ ነውና እንግደለው እንዳሉት ገበሬዎች ይህንኑ ነው ያደረጉበት:: ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ። 

ስለዚህም እናውቃለን ያሉት ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው። አሜን! በእስራኤሎች ተቆጥቶ እስከመቼ እታገሳለሁ? ለሙሴም ይህንን ህዝብ አጠፋለሁ ብሎ ነበር ግን ታገሰና በእነርሱ በኩል ሰው ሆኖ የባርያን መልክ ይዞ መጣልን መጥቶም የሁላችንንም ሐጥያት ለመሸከም እራሱን አቀረበ ይህ የእግዚአብሔር በግ እየሱስ! ስሙ ይባረክ ስለተደረገልን ምን እንላለን ምስጋናን እንሰዋለን እንገዛለትማለን እንጂ!


የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ

የማርቆስ ወንጌል 12: 13-17
13፤ በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ። 14 መጥተውም። መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ? አሉት። 
15 እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ። ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ አላቸው። 
16 እነርሱም አመጡለት። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤ እነርሱም። የቄሣር ናት አሉት። 
17 ኢየሱስም መልሶ። የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በእርሱም ተደነቁ። 

በንግግርም ሊያጠምዱት ስለ ግብር እንዲጠይቁት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ:: ግቡን ልብ ብላሁ አስተውሉ! በንግግርም ሊያጠምዱት ነው የመጡት እነማን ናቸው ያልን እንደሆነ ከሄሮድስ ወገንና እንደገናም ደግሞ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ ሰዎች ናቸው:: አንዳች ምክንያት አግኝተው ሊያስወግዱት ነው የሚፈልጉት::

የሚገርመው የሚናገረውን እየሰሙት አይደለም የላከውን በማንገላታትና በማስወገድ በነሱ ቤት ለእግዚአብሔር መወገናቸው ነው ነገር ግን ጌታ ታግሶ አስተማራቸው የጥበቡን ጥልቀት:: እርሱ እኮ ስለሰው ሊነገረው አይገባም ሁሉን ያውቃል ግን ሊገባቸው አልቻለም:: የቄሳር ምስል ያለበትን ለቄሳር የእግዚአብሔር ምስል ያለበትን ደግሞ ለእግዚአብሔር እያላቸው ነው:: እኛ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረናልና ለፈጠረን ጌታ እንገዛለን:: ሃሌሉያ! ከምናገኘው የተወሰነውን እንደቀረጥ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ለሞተውና ለተነሳው ጌታ እንኖራለን እያንዳንዳችን ይህን እንበል በእኔ የሚኖረው እራሱ እየሱስ ነው እኔ አልኖርም ብለን እንሹመው ሊገዛን ይገባዋልና በዋጋ ተገዝተናል:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም

የማርቆስ ወንጌል 12: 18-27
18፤ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም፡ አሉት፦ 19 መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። 
20 ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤ 
21 ሁለተኛውም አገባት፥ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 
22 ሰባቱም አገቡአት፥ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። 
23 ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች? 
24 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? 
25 ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም። 
26 ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር። እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? 
27 የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ። 

ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም፡ አሉት፦ መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። ደግሞም ሰባቱ አገብዋት ግን ልጅ ሳያስቀሩ ሁሉም ሞቱ በስተመጨረሻ በትንሳኤ ታድያ የማን ሚስት ልትሆን ነው:: ለምን ይህንን ይጠይቃሉ መጀመሪያውኑ የሙታን ትንሳኤ የለም ብለው ካመኑ ወይስ በትንሳኤ እንደዚህ አይነት ታሪክ ያለው ሁሉ ሲጣላ ቀውጢ የሆነ ትንሳኤ ይሆናልና ትንሳኤ ይቅር ብለው ሊያግባቡ? ወይስ እምነታችን ትክክል ነው ብለው ሊያስፈርሙት? ይገርማል የእኛ ጌታ ግን የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር። እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ብሎ ነው እራሱን የሚጠራው:: ሃሌሉያ! በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ከሞት ህግ አርነት ወተን በህይወት እንድንኖር ክርስቶስ እራሱን ቀድሷል:: እንዲሁም በራእይ 1: 17፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ 18፤ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። እኛም ከእርሱ ጋር ተነስተናል!

መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? እጅግ ትስታላችሁ አላቸው ጌታ ስለ ህያውነቱ እያወቁ እንዳላረጀ በዘመናት መካከል እያዩ ቃሉንም ሲመረምሩ እየዋሉ እነሱ ግን ስተዋል:: የሙታን ትንሳኤ ጊዜ ስጋችን ለእርሱ አሰራር እንደሚመቸው አድርጎ ከመቅጽበት ይቀይረዋል የስጋ ምኞት የለም እንደመላእክት በቅድስናው ፊት መኖር ነው የሚጠብቀን:: ላለመሳት የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑር በህይወታችን እናጥና ቃሉን እናሰላስለው ከእኛ ጋር እንዲዋሀድም እናመንዥገው እንጂ የማይጠቅመን እንዳይሆንበጠላት ተለቅሞ:: ጌታ ህያው ነው! ፀሎቴ:- ጌታዬ ሆይ የቃልህን ደጆች ክፈትንል እንድናስተውልም እርዳን ነው:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በፍጹም ልብህ፤ ነፍስህ፤ አሳብህና ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ

የማርቆስ ወንጌል 12: 28-34
28፤ ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ፦ ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው። 29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ 
30 አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። 
31 ሁለተኛይቱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። 
32 ጻፊውም። መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ 
33 በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው። 
34 ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ። አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። 

ለሰዱቃውያን ደህና አድርጎ እንደመለሰ የተመለከተው ይህ ከጻፎችም አንዱ ስለመጀመሪያይቱ ትዕዛዝ ጠየቀው ጠፍቶት ወይም ለማወቅ ፈልጎ እንዳይመስለን እንደተለመደው ለማጥመድ እንጂ:: ህግ ሰጪውም ሲመልስም:- እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም

  1. በፍጹም ልብህ – በልባችን ላይ ጌታን እናንግሰው እርሱ የህይወት መውጫ ነውና በሙሉ ልባችን እንውደደው
  2. በፍጹምም ነፍስህ – ማንነታችን እኔነት እወዳለሁ እጠላለሁ የሚለው ማንነታችን ሊወደው ይገባል
  3. በፍጹምም አሳብህ – የምናወጣውና የምናወርደው በአሳባችን እርሱ መሆን አለበት
  4. በፍጹምም ኃይልህ – በጉልበታችን በገንዘባችን በትምህርታችንና በእውቀታችን ሁሉ ልንወደው ይገባል::

ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። እግዚአብሔር ቀናተኛ ነውና ለማንም እንድንሆን አይፈልግም:: ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት ብሎ አላበቃም የጠየቀው የመጀምሪያይቱን ብቻ ቢሆንም እንኳን ሁለተኛይቱንም ነገረው:: ሁለተኛውም:- ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል ናት:: እየሱስ ደቀመዝሙርቴ እንደሆናችሁ በፍቅራችሁ ታወቁ ነው ያለን ደግሞም ከፍቅር በቀር ሌላ እዳ አይኑርባችሁ ነውና የተባልነው በፍጹም ልብ አሳብ ነፍስና ጉልበት ጌታችንን እንውደድ የሰውንም ልጅ ሁሉ እንደራሳችን እንውደድ::

ሰውየው መልሱን ሰምቶ ልክ ብለሀል መውደድ ከመታዘዝ ይበልጣል ብሎ አለ እንጂ እምነቱን በስራ አልገለጠም ግን እሩቅ አይደለም አለ እየሱስ ልክ እንደዚህ ሰው ያሉ ሰዎች በዙሪያችን አሉና እንጸልይላቸው እምነታቸው በስራ እንዲገለጥና በመገለጥ መረዳት ወደ አምላካቸው እንዲጠጉ ምክንያቱም የአእምሮ እውቀት አያድንም መገለጥ እንጂ::

ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!


እየሱስ መሲህ ነው

የማርቆስ ወንጌል 12: 35-44
35፤ ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ፦ ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው፡ እንዴት ይላሉ? 36 ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። 
37 ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። 
38 39 ሲያስተምርም እንዲህ አለ። ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ 
40 የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ። 
41 ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ 
42 አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። 
43 ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ። እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ 
44 ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው።

ዳዊት በመንፈስ ተረድቶ መሲህ ከእርሱ ዘር የሚመጣ ቢሆንም እንኳን ጌታዬ ብሎ ነው የሚጠራው ደግሞም ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። ስለዚህ ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብሎ ነው የሚጠይቃቸው በሌላ አባባል እኔ መሲህ ነኝ ምንም እንኳን ከዳዊት ዘር ብገኝም እያለ ነው ያስተዋለ የለም እንጂ! መሲሁ ሲመጣ ማድረግ ያለበትን ድንቅና ተአምር ያውቃሉ ለዚህም ነው ዮሃንስ ወደ እርሱ ልኮ ምንም እንኳን የተላከው እርሱ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ ያየ ቢሆንም ግን አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ ብሎ መልእክተኛ ላከበት እየሱስም የምታዩትን ንገሩት ነበር ያለው::

ከዛም ዞር ብሎ ስለመባ መታዘብ ያዘ እንደዛች መበለት ጥቂት የሰጠ የለም እንደእርስዋም የተደነቀ የለም:: ምን ያህል እንደምንሰጥ አይገደውም ግን በደስታና በልግስና ስንሰጥ ጌታ ደስ ይለዋል:: የልግስናና የመታዘዝን መንፈስ ይሙላብን! አሜን!


ምዕራፍ 13

እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል

የማርቆስ ወንጌል 13: 1-13
1፤ እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ፡ አለው። ኢየሱስም መልሶ። እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው። 
በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም። 
ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። 
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። 
ብዙዎች። እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። 
ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። 
ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። 
እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። 
10 አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። 
11 ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። 
12 ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ 
13 በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 

ሐዋርያው ስለቤተ መቅደሱን ውበት ሲያሳየው እየሱስ ግን ይፈርሳል አለው በሚፈርስ ነገር አትደነቅ የፈረሰው ወደ 70 ዖ.ም. አካባቢ ላይ ነበር:: እኛም አይናችንን ማድረግ ያለብን በክብሩ ላይ መሆን አለበት የሚያስገርመን የሚያስደንቀን እርሱ ይሁን:: ደግሞም ዛሬ ቤተመቅደሱ እኛም አይደለን? እኛኑ በመንፈሱ አሳምሮ ይሰራናል:;

ሌላው የጠየቁት ነገር ስለመጨረሻው ዘመን ነበረ መቼ እንደሚሆን:: እርሱ ግን ሲመልስ ቀኑን አልቀጠረም ግን የምጥ መጀመሪያ ምልክቶችን ነገራቸው መቼም ባለንበት ዘመን ሁሉንም አይተናል ብንል ማጋነን አይሆንም:; እየሱስ ግን ትኩረት እንዲያደርጉ የሚፈልገው አንድ ጉዳይ ላይ ነው ይሄውም ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ነው ያለው:: የሚያስት እንደሚመጣ ከተነገረን እንዳንስት ምን እናድርግ? የእግዚአብሔርን ቃልና ኃይሉን አታውቁምና ትስታላችሁ ስለሚል ቃሉን እንወቅ እንዳንስት!

ስለስሙ እንግልት ሲደርስብን እራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው መልስ የሚሰጠው በሐዋርያቱ ህይወት እንዳየነው:: በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ስለዚህ በሙላት እርሱን እያሳየን እንመላለስ በምድር የሚያፍርብኝን በሰማይ ሰራዊትና በአባቴ ፊት አፍርበታለሁ ያለንን እናስብና እንበርታ! እንጽና ያለንበት ጊዜ የመጨረሻ ዘመን ነውና:: ማራናታ!

አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል ስላለን ወገባችንን ታጥቀን ወንጌልን እናድርስ::


የመጨረሻው ዘመን

የማርቆስ ወንጌል 13: 14-27
14፤ ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥ 15 በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥ 
16 በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። 
17 በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። 
18 ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 
19 በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። 
20 ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። 
21 በዚያን ጊዜም ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም። እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ 
22 ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። 
23 እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። 
24 በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ 
25 ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። 
26 በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 
27 በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። 

ያለንበት የመጨረሻ ዘመን መሆኑ አያጠያይቅም ጌታ ሊመጣ በደጅ ያለበት ጊዜ ጠላትም ጊዜ እንደሌለው አውቆ በብዙ ቁጣ ጥፋትን እያደረገ ሰዎችን በብዛት እያጠፋ ያለበት ጊዜ ላይ ነው ያለው:: የመጨረሻው መጨረሻ ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ስታዩ ነው ተብለናል:: ይህም በተቀደሰው ቤተመቅደስ እስራኤሎች በሚያቆሙት ውስጥ መጥቶ እኔ እግዚአብሔር ነኝ አምልኩኝ ሲል ማለት ነው:: እስራኤላውያን ቤተመቅደሱን አዘጋጅተው ጨርሰዋል መትከል ብቻ ነው የሚቀራቸው ያኔ በአይናችን ፊት የመጨረሻውን ለማየት እየታደምን እንደሆነ አውቀን የተመረጡትን እንኳን ለማሳት የሚችል መሆኑ የተነገረለት አሳች ይገለጣልና እንጠንቀቅ:: በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና ስለሚል ለሚጠፉት የሚራራ ልብ ጌታ ይስጠን።  እኛ ግን በዚህ ነገር የምንጨነቅ አይደለንም ምክንያቱም እኛ እስካለን ድረስ ጠላት በግልጽም አይሰራም ደግሞም በእኛ ውስጥ ያለው ይበልጣል:: እኛ ማተኮር ያለብን ሰዎችን ወደ ፍቅሩ መንግስት ማፍለስ ላይ ነው::

በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል! ሃሌሉያ! ማራናታ ጌታ ሆይ ቶሎ ና! በዚያን ጊዜም ጌታ መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።  አሜን! የዝችም ምድር ነገር ሰው እንደዚህ የሚዋደቅላት ያበቃላታል ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ።  አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይኖራል እራሱ በጉ የሚያበራበት! ከአባታችን ጋር ያለ እንባ ያለ ህመም ያለ መከራ በደስታ የምንኖርበት ዘመን ይመጣልናል:, አሜን!


ተኝታችሁ እንዳላገኛችሁ ትጉ

የማርቆስ ወንጌል 13:28-37
28፤ ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ 29 እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። 
30 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 
31 ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። 
32 ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። 
33 ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። 
34 ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። 
35 እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና 
36 ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። 
37 ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።

ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ። ነው ጌታ ያለን ድንገት ስመጣ ተኝታችሁ እንዳላገኛችሁ እያለን ነው:: እኛ የምንፈልገው በዚህ ዓመተ ምኅረት እመጣለሁኝ ብሎ ቀጠሮ ቢሰጠን ደስ ይለናል ጌታ ግን ያለው ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። አብ ብቻ ነው የሚያውቀው ስለዚህ ከእናንተ የሚጠበቀው ነቅቶ መጠበቅ ነው ብሎናል:: ስንጠብቀውም ማድረግ ያለብንንም ነግሮናል:- ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና

  1. ተጠንቀቁ፤
  2. ትጉ፤
  3. ጸልዩ 

አንድ ምልክት የተወልን ቢኖር ስለ በለስ ነው:: ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ አለን በለስ በማን ይመሰላል እዚህ ምሳሌ ላይ? በእስራኤል ነው! መንግስት ከሆነች ይኸው ብዙ አስርት አመታት ተቆጥረዋል ሰሞኑንም ዜና ከሰማን እስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት ላይ ናቸው ብዙ አገር እስራኤልን በመቃወምም ላይ ነው ታድያ ይህ ሁሉ የመምጣቱን ነገር ከመቼውም በላይ እንደቀረበ እያሳየን ነው የጌታን መምጣት የምንለካበት ቴርሞ እስታቱ እስራኤል ናት:: ስለዚህ መምጣቱ በደጅ ነውና አብዝተን እንተያይ በጸሎት እንትጋ እንዲሁም በጸጋው እንታመን::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 14

መልካም ሥራ ሠርታልኛለች

የማርቆስ ወንጌል 14: 1-9
1፤ ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና። 
እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። 
አንዳንዶችም። ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው? 
ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። 
ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። 
ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። 
የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። 
እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል። 

ኢየሱስ እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች አለ ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ሰብራ በራሱ ላይ ስታፈስስ።  ለምን ያልን እንደሆነ  የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው።  ይህ ነበረ ግብዋ መቼም ይሞታል ብላ አይደለም እጅግ ስለወደደችው ያልተለመደ ስጦታ ነው የሰጠችው የትም ቦታ ላይ አናይም እንደዚህ ያለ ስጦታ ምናልባት ሳትሰብር ብትሰጠው እሺ የተለመደ ይሆናል ይህ ግን ለየት ያለ ተግባር ነው እርሱ ግን ያውቅ ነበር ለምን እንደተደረገ:: ከመቀበሩ በፊት ይህን ወግ አያገኝም ነበረና ነው:: ይህች ሴት የተቻላትን አደረገች እንዲሁም መልካም አደረገችልኝ ነው ያለው ጌታ እኛስ ታድያ የተቻለንን ለመንግስቱ እያደረግን ነው? እራሳችንን እንጠይቅ::

የሚገርመው አንዳንዶችም ማለትም ይሁዳ ሌባ ነበረና ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው የሚባክነው ብሎ ነበረ:: ሽቶው ግምቱ ከሦስት መቶ ዲናር የሚበልጥ ዋጋ ያወጣ ስለነበር ለምን ተሽጦ ለድሆች አልተሰጠም ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት ይላል ቃሉ:: ሁልጊዜ ነቀፋ ትክክል ነው ማለት አይደለም ሰው ከራሱ ተነስቶ እንደው ደርሶ ጥሩ መከራከሪያ ጭምብል ለብሶ ሊነቅፍ ይችላል ማሰብ ያለብን ጌታ ምን ይላል ነው ሁልጊዜ በቃሉ እራሳችንን እንፈትሽ እንጂ ወደ እኛ ለተወረወረው ትችት ሁሉ መልስ ለመስጠት ጊዜ አናጥፋ እራሱ ጌታ ይከራከርልን “ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ” ብሎ እንዳለው አሜን! እዚህ ጋር የተማርኩት ሌላው ነገር ጊዜው የሆነና ያልሆነ ነገር አለ የጊዜው ነገር ምንድነው እንድናደርግ ጌታ የሚፈልገው? እርሱ እራሱ ይምራን እኛ እያለን ሌላ ፍለጋ አይሂድ እንታዘዝ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው መከረ

የማርቆስ ወንጌል 14: 10-21
10 ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። 
11 ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። 
12 ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። 
13 ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው። ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ 
14 ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። 
15 እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ 
16 በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። 
17 በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። 
18 ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። 
19 እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም። እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። 
20 እርሱም መልሶ። ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። 
21 የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው። 

እየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ለምን ይሆን የወሰነው በእርሱ ዘንድ መቀመጥ ይቀይራል እንጂ! ይሁዳ ግን ቀስ በቀስ ነው ጠላትን ወደ ህይወቱ የጋበዘው መጀመሪያ መስረቅን ተለማመደ ከዛም ሰለጠነበት በዚሁ ምዕራፍ እንዳየነው ሽንጡን ገትሮ ለድሆች ይሁን ይህ ሽቱ ሲል ነበር በጭንብል ውስጥ ተከልሎ ግን ለድሀ አስቦ አልነበረም ለመስረቅ እንጂ! ታድያ አንድ መስኮት ክፍት ከሆነ ሌባ በዛች መስኮት ገብቶ ሁሉንም ክፍል ማዳረስ እንደሚችል ሁሉ ሌብነትን ያለማመደው አሳልፎ መስጠትም ቀላል እንደሆነ መከረው እርሱም ተነዳ ስለዚህም አሳልፎ ለመስጠት ተደራደረ:: ይህ የሚያስተምረን ህይወታችንን በቀንና በለሊት የሚውጠውን ፈልጎ እንደ አንበሳ በዙሪያችን ያጏራልና ነቅተን፤ ስር ሰደን፤ ጌታን እያከበርንና ጸጋን እየጠየቅን እንመላለስ ምክንያቱም በመንፈስ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም የሚሆነው የእኛ ነገር::

ሌላው ስለዚህ ቤቱን ለመጨረሻው የጌታ እራት በፋሲካ ስላዘጋጀው ሰው እንመለከታለን:: ደቀ መዛሙርቱ መተው መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል አሉት። እርሱም ወድያው በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ አሳያቸው፤ እነርሱም በዚያም አሰናድተው ጠበቁት ጌታም ማምሻው ላይ መጣ። ሰውየው ተዘጋጅቶ ነበረ ጌታ በህልም ይናገረው ወይ በመላእክ ይናገረው ባይገለጥም እንኳን ይህ ሰው ግን ሰምቶ ተዘጋጅቶ ነው የጠበቀው:: እኛም ዛሬ በብዙ መንገድ ጌታ ልመጣ ነው እያለን እየተናገረን ነውና ተዘጋጅተን እንጠብቀው ይመጣል፤ አይዘገይም፤ በእርግጥ ይመጣል! አሜን

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ሥጋውንና ደሙን ባርኮ ሰጣቸው

የማርቆስ ወንጌል 14: 22-26
22፤ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፡ አለ። 23 ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። 
24 እርሱም። ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። 
25 እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው። 
26 መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። 

እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፡ አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ።  እርሱ እራሱ በፈቃዱ ህይወቱን ሰጠን አመስግኖ:: ይህ ማለት ሥጋው ለሥጋችን ደህንነት ደሙ ደግሞ ለሐጥያታችን ስርየት ነው:: ስለዚህ ጉዳይ ጳውሎስ ሲጽፍ ለመታሰቢያው አድርጉት ይለናል:: 1ኛ ቆሮ 11: 24፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም፦ እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡ አለ። 25፤ እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ፦ ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡ አለ።

መታሰቢያ ብለን ስንል ስለሁኔታው እያሰቡ ማመስገን ነው ማለት ነው:: ምን ተፈጠረ በዛ ምሽት የሚለውን በአይነ ህሊናችን እንዳሰው እስኪ የዓለም ሁሉ ፈጣሪ በፍጥረቱ ለመገደል ተላልፎ የሚሰጥበት ቀን! ነፃ ሊያወጣውና ወደክብሩ ሊመልሰው የመጣውን የዋሁን ጌታ ባርያ ካደረገውና በግዞት ካስቀመጠው ጋር ተባብሮ ነፃነት ይቅርብን ብሎ ያወጀበት የመግደል ስርአት! እርሱ ግን ስለበደላችን ደቀቀ ስለ መተላለፋችንም ቆሰለ የደህንነታችንም ተግሳፅ በእርሱ ላይ አረፈ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን:: የሚያደርጉትን አያውቁም እያለ እየማለደልን ስለ እኛ መከራውን በላ ሳያጉረመርም እራሱን ስለእኛ አሳልፎ ሰጠ! ከህያዋንም ምድር ተወገደ! ይህ ሁሉ በፈቃዱ ሆነ ነፍሱንም ስለእኛ አኖረ! ሃሌሉያ! የጌታን እራት ስንወስድ ይህንን እናስብ እርሱ እራሱን ስለእኛ መስጠቱን እያየን በዚህ ውስጥ እያሰብነው ለስጋችን ፈውስን ለሐጥያትም ስርየትን እንዳገኘን እያሰብን ህብረትን እናድርግ ከወደደን ጌታ ጋር! እኛም እራሳችንን እንስጠው:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ

የማርቆስ ወንጌል 14: 27-31
27፤ ኢየሱስም አላቸው፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ፡ የሚል ተጽፎአልና። 28 ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። 
29 ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። 
30 ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። 
31 እርሱም ቃሉን አበርትቶ። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። 

ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ ብሎ ቀጠሮ እየሰጣቸው ነው እነርሱ ግን አላስተዋሉም የሆነውን እናውቃለን:: መነሳቱንም እየነገራቸው ነበር ግን ምንም አልገባቸውም:: የትንቢትን ቃል ጠቅሶ እረኛው ይመታል መንጋውም ይበተናል በኔ ትሰናከላላችሁ እያለ ነበር ግን አልሰሙም:: እኛም እንደዚሁ ነው አንዳንዴ የምንመላለሰው የሚሰማኝ ከመከራ ስጋት ያርፋል ይል የለም ቃሉ? እንስማውና እርፍ እንበል እርሱ ይናገራል ሰው ግን አያስተውልም የሚለእ እንዳይሆንብን እናስተውል:: ቃሉን የምንሰማ ብቻ ሳንሆን እናመንዥገው እስኪዋሀደን ድረስ:: ሰምተውት ቢሆን ኖሮ የኤማኦስ መንገደኞች አይኖሩም ነበር ፤ ፈርተው አይንቀጠቀጡም ነበር፤ ሰውን ማጥመድ ትተው ወደ አሳ ማጥመዳቸው አይመለሱም ነበር፤ ቶማስም ካላየሁ አላምንም አይልም ነበር:: ጌታ እኮ በግልጽ እየተናገረ ነው ስለመነሳቱ ማን ቢሰማ?! ማስተዋልን ጌታ ይስጠን!

ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው እራሱን ከሌሎቹ የተሻለ አድርጎ ነበር ያቀረበው ጌታም የሚሆነውን ነገረው እንዲያውም ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። የሆነውን እናውቃለን:: በጸጋ መቆም ይቻላል በኃይልና በብርታት ግን አይሆንም በመንፈሱ እንጂ! የሚረዳንን ጸጋ ለመቀበል ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ እርሱም በልግስና ይሰጠናል አለበለዚያ ግን በቀላሉ ጠላት ወጥመድ ውስጥ ገብተን እንወድቃለን:: ምን አለፋን የሚረዳ ጸጋ ካለ በእርሱ ላይ እንታመን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩ

የማርቆስ ወንጌል 14: 32-42
32፤ ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ፡ አላቸው። 33 ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና። 
34 ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። 
35 ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና። 
36 አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። 
37 መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? 
38 ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። 
39 ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። 
40 ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም። 
41 ሦስተኛም መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። 
42 ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። 

እንደልማዱ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረ ይላል ቃሉ:: ይህ እኔን ለመውለድ የተጀመረ ምጥ ነው:: ብዙ ነገር አሰብኩኝ ጭንቀቱን ሳየው ምናለ በተደበቀ ወይ አገሩን ጥሎ በሄደ ሁሉ ብዬ በሰውኛ አሰብኩኝ ግን ወግጂ እንደሚለኝ እንደጴጥሮስ አልጠፋኝም ግን ይጨንቃል ያለፈበት ይህ ሁሉ ስለእኔ? ዋው ጌታዬ ሆይ ምን እላለሁ አመሰግናለሁ!! መልሶም አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ብሎ ጸለየና ደግሞ መለስ አድርጎ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። ደግሞም ተመልሶ ይህንኑ ጸሎት ጸለየ:; አቤት ጭንቀቱ?! በዚህ ጭንቅ ውስጥ ፈቃድህ ይሁን ማለት መቻል ትልቅ ነገር ነው::  ይህን ሁሉ ጭንቅ ስላየ ነው የሚራራልን ሊቀ ካህናት አለን የሚለው ሳይፈርድ ይረዳናል::

ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና መለስ ብሎ ሲያያቸው ሐዋርያቱ ግን ተኝተው ነበር:: በምድር ወድቆ ያምጣል፤ ይጨነቃል፤ ቢቻልህ ሰዓቲቱ ትለፍ እያለ ይጸልያል አይዞህ እንኳን ሊሉት አልቻሉም:: ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን?  አለው:: ለምን ብንል እርሱ ነው እስከሞት ድረስ እንኳን ቢሆን እልለይህም ያለው ስለዚህም ቃሉ ፈተና ማምጣቱ እንደማይቀርለት ጌታ አውቆ ነው ትጋ የሚለው ግን እንቅልፍ ላይ ነበረ:: ማንም ሳያጽናናው ብቻውን አምጦ ሰዓቱ ደረስ እንግዲህ እንሂድ አላቸው:: ስለእኔ ይህ ጌታ በሐጥያተኞች እጅ አልፎ ተሰጠ! ጌታዬ ሆይ! ዋጅተኸኛልና እንደዚህ ተሰቃይተህ ስምህ ከዘላለም እስከዘላለም የተባረከ ይሁን! አሜን!

ለአንተ የምኖርበትን ጸጋ ስጠኝ!


እየሱስ ተላልፎ ተሰጠ

የማርቆስ ወንጌል 14:43-52
43፤ ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ። 44 አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 
45 መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤ 
46 እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። 
47 በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ። 
48 ኢየሱስም መልሶ። ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? 
49 በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው። 
50 ሁሉም ትተውት ሸሹ። 
51 ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥ 
52 ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ። 

እየሱስ ተዘጋጅቶ እየጠበቀው ነበር ይሁዳን ልክ እንደው እንደናፈቀ ሰው መምህር ሆይ ብሎ ሲስመውና በዛም ምልክት የተሰጣቸው ጠባቂዎች ሲይዙት እናያለን:: አሁን ደቀ መዛሙርቱ ነቁ ከመንቃትም ባለፈ ለምመምህራቸው ለመዋጋት ተነሱ:: እየሱስ ግን ይህንን አይነት ኃይል አይደለም የፈለገው እርሱ ዝም ብሎ በሸላቾቹ ፊት መሆን እንጂ ቢፈልግማ በአንድ አፍታ አንዱ መልአክ ፀጥ ጭጭ ሊያደርጋቸው ይችላል እርሱ ቢናገር ወደ አፈርነት ሰው ከመቅፅበት አይለወጥም ብላችሁ ነው? ብቻ ጌታ ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ እራሱን ሰጣቸውና ወሰዱት:: መሞት እንኳን ቢሆን ከአንተ ጋር እሞታለሁ ያለ ሁሉ ጥሎት ሸሸ:: በህይወት ላይ ይህ ሊያጋጥም ይችላል ጌታ ህን ታማኝ ነውና የትም ጥሎን አይሄድም በእርሱ እንታመን:: ድሮውንም እግዚአብሔር ልምዱ ቃል ኪዳን ሲያደርግ ብቻውን ነው ከአብርሃም ጋር ያለውን ብናይ አብርሀም እንቅልፍ ላይ ነበረ እግዚአብሔር በመስዋእቱ መካከል ሲያልፍ እንዲሁም እየሱስ የአዲስ ኪዳንን ብቻውን ተወጣ ሰው ሁሉ ፊቱን አዙሮበት:: አቤት ፍቅር!

ሰይፍ የእግዚአብሔርን መንግስት አትሰራም በመንፈስ ነው ስራው የሚሰራው:: ለዚህም ነው ጌታ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ የቀጠለው:: የሆነልን መንፈስ የፍቅር መንፈስ ነው ሁሉን መውደድ ነው የተሰጠን ትዕዛዝ ስለዚህ ምላሳችንንም እንደሰይፍ እንዳንጠቀምበት እንሰብስብ የሰውን ጆሮና ልብ አናቁስልበት ከቻልን በጨው የተቀመመ ንግግር ይኑረን አለበለዚያ ግን ዝም ማለት መልካም ነው ጌታ ይርዳን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ

የማርቆስ ወንጌል 14: 53-72
53፤ ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። 54 ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። 
55 የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤ 
56 ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም። 
57 
58 ሰዎችም ተነሥተው። እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት። 
59 ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። 
60 ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ። አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። 
61 እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። 
62 ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። 
63 ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? 
64 ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ። ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት። 
65 አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። 
66 ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥ 
67 ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና። አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። 
68 እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። 
69 ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት። ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። 
70 እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን። የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት። 
71 እርሱ ግን። ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። 
72 ጴጥሮስንም ኢየሱስ። ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

እየሱስን ብዙዎች በሐሰት ይከሱት ጀመረ ነገር ግን ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። እየሱስም ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ።  ያኔ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ብሎ ሲል ሁሉም በአንድ ድምጽ ይሙት አሉ:: አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።  ይህን ሁሉ የታገሰው እኔን ብሎ ነው:: ሃሌሉያ!

በዚህ ግርግር ውስጥ ቃሉን ለመጠበቅ የሚጥር ጴጥሮስ ነበረ:: በአንዲት አገልጋይ ፊት የምትይውን አላውቅም እያለ ቆየ እርስዋም እየተከታተለች ከእርሱ ወጉን ነው ማለትዋን ቀጠለች ጴጥሮስም መካዱን:: የሚገርመው እየካደ መሆኑን ያስተዋለው ዶሮ ሲጮህ ነው ጌታ እንዳለው ሶስት ጊዜ ካደው ዶሮ ሁለቴ ሳይጮህ:: ደስ የሚለው ግን ተጸጽቶ ማልቀሱ ነው:: ሁልጊዜ ድካሙ ነው የሚታየው ነገር ግን ከእርሱ በስተቀር አስሩ ሐዋርያት በዛም አልነበሩ እርሱ ብቻ ነበር እዛ ድረስ የተከተለው:: ዛሬም ለእያንዳንዳችን የሚያስፈልገን ጸጋ ነው ለመጽናት ስለዚህ ጸጋን እንጠይቅ::

እኛ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ እንዳለ ጌታ የምናይ ነን ጌታ በደመና ከመላእክቱ ጋር ይመጣል ሊወስደን ለሙሽራው ሰርግ ተዘጋጅተን ብርሃናችን በርቶ እንጠብቅ::


ምዕራፍ 15

የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እየሱስን ሰጡት

የማርቆስ ወንጌል 15: 1-15
1፤ ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም። አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። አንተ አልህ ብሎ መለሰለት።
የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም። 
ጲላጦስም ደግሞ። አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል ብሎ ጠየቀው። 
ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም። 
በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር። 
በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። 
ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር። 
ጲላጦስም። የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤ 
10 የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። 
11 የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው። 
12 ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ። እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው። 
13 እነርሱም ዳግመኛ። ስቀለው እያሉ ጮኹ። 
14 ጲላጦስም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን። ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ። 
15 ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። 

በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ግን እየሱስ ከዚህ በፊት በአጠገባቸው ተሰውሮ ሄዶ ያውቃል ጊዜው አልደረሰም ነበረና:: ጊዜው ሲደርስ ግን ለመስቀል ሞት አሳልፎ እራሱን በፈቃዱ ሰጠ:: በጌታ ተወደናልና ጌታን እናመስግን!

የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እየሱስን እንደሰጡት ጲላጦስ ገብቶት ነበር:: ሊፈታው ምን ቢፈልግም ህዝቡን አንድ ጊዜ አሳምጸውት ነበረና የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ።  የመጀመሪያው ነጻ ውጪ በርባን ነበረ:: ወንጀለኛው ተለቆ ጻድቁ በእርሱና በብዙዎች ፈንታ ለሞት ተላልፎ ተሰጠ:: እኛም በርባኖች ነበርን በማንኛውም ጊዜ ለፍርድ በእግዚአብሔር ፊት ብንቀርብ ሞት የሚፈረድብን ነበርን ነገር ግን እግዚአብሔር ፍርዱን ሁሉ በልጁ ላይ አድርጎት እኛ በነፃ ተለቀቅን! እንደቀላል እንዳናየው ከዘላለም ሞትና ስቃይ ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት አፍልሶናልና:: ይህንን የተደረገልንን ለሌሎች ማካፈል የበራልንን ብርሃን ልናበራና መንገድ ነኝ ያለውን እየሱስን ልናሳይ የህይወት አላማ አድርጎ ሰቶናል::

ሌላው እነዚህ የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው ነው የሰጡት:: በገላትያ 5 ላይ እንደምናየው ቅንዓት አንዱ የስጋ ፍሬ ነው እኛ ውስጥም መገኘት የለበትም:: እኛ መንፈሳውያን ሰዎች ነን ጌታ ስለዋጀን የስጋን ምኞት የማንፈፅም ነን:: በቃሉ ላይ እንደሚል ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። ስለዚህ ነው እኛ በመንፈስ ነን የምንለው:: መንፈስ ነን አላልኩም እኛ ስጋ፤ ነፍስና መንፈስ ያለን ፍጥረቶች ነን:: የምንመግበውን እንምረጥ! ስለመንፈሳዊ ነገር እናስብ በላይ መዝገባችን ባለበት ልባችንና አስተሳሰባችን ይሁን:: በማንኛውም ሰዓት አእምሮአችን ያስባል ማሰብ አቁሞ አያውቅም ስለዚህ የሚያስበውን ነገር እንስጠውና እንግራው እንደው እንደፈቀደ እንዳይጋልብ ቃሉን ዕለት ዕለት እንመግበው እምነታችንም ያድጋል ቃሉን ስናውቅ ደግሞ የቃሉን ባለቤት ወደማወቅ ያመጣናል:: አሜን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ወታደሮች ተዘባበቱበት

የማርቆስ ወንጌል 15: 16-20
16፤ ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። 17 ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ 
18 የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ 
19 ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። 
20 ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። 

የሮማ ወታደሮች ጭፍራውን ሁሉ ወይንም በጊቢው ያሉትን ወታደሮች ሁሉ ጠርተው ቀይ ልብስ አለበሱትና ማሾፍ ጀመሩ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ማሾፉም ወደ መምታት ተቀይሮ የከፋውን ነገር አደረጉ ይኼውም ንጉስ ክሆነ አክሊል ያስፈልገዋል ብለው የእሾህ አክሊል ጎንጉነው ደፉበት፤  በዛም አላቆሙም እሾኩ ወደ ጭንቅላቱ ውስጥ እንዲገባ  በመቃ መቱት እርሱም አልበቃም ተፉበትም፥ መትፋቱ ይህ የመጀመሪያ አይደለም ለጌታችን ከዚህ በፊትም የያዙት ተፍተውበታል ግን ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ነው:: በኢሳይያስ 50: 6፤ ጀርባዬን ለገራፊዎች ጕንጬንም ለጠጕር ነጪዎች ሰጠሁ፥ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም። ትንቢቱ ተፈፀመ:: ምንም አይነት የጭንቀት ህመም ይሁን ከራስ ጋር የተያያዘ ህመም እርሱ እራሱ ላይ ቆስሎ ወስዶታልና እኛ መታመም የለብንም በመገረፉ ቁስል ተፈውሰናል:: አሜን!

ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ይህንን ሁሉ የሚያደርገው እኔን ለመታደግ ነው:: እንጂ በመካከላቸው አልፎ መሄድ መሰወር ይችል ነበር ግን ይህንን ሁሉ በዝምታ ተቀበለ:: ኦ ሃሌሉያ! በአምላኬ ተወድጃለሁና ጌታዬን ለዘላለም አመሰግናለሁ:: ለእርሱም ምስክር እሆናለሁ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የእየሱስ መሰቀል

የማርቆስ ወንጌል 15: 21-32
21፤ አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። 22 ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። 
23 ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። 
24 ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። 
25 በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። 
26 የክሱ ጽሕፈትም። የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር። 
27 ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። 
28 መጽሐፍም። ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ። 
29 የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ 
30 ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። 
31 እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ። ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ 
32 አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር። 

የእግዚአብሔር ጊዜ ሆነና እየሱስ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ ቢልም ከእርሱ አላለፈም ነገር ግን ተላልፎ በሐጥያተኞች እጅ ገባ:: ተፉበት፤ ገረፉት፤ ተሳለቁበት፤ ልብሱን በእጣ ተከፋፈሉ፤ የእሾክን አክሊል አደረጉለት ፤ አሾፉበት፤ ሌሎችን ያዳንክ እራስህን አድን፤ ከመስቀል ውረድ አሉት፤ እራሳቸውን እየነቀነቁ አሾፉ፤ ሌላም ሌላም ግን ትንቢትን ሁሉ እየፈጸሙ እንደሆነ አልገባቸውም ያደረጉት ሁሉ ከ700 ዓመት በፊት በኢሳያስ ትንቢት ውስጥ ተጽፎ ይገኝ ነበር:: ከመገረፉና ከመድከሙ የተነሳ መስቀሉን እንኳን መሸከም አልቻለም ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆን የኛ ጌታ ዝም ብሎ ታገሰ የሚሰጡትንም ባህላዊ የህመም ማስታገሻ አልተጠቀመም እንቢ ነው ያለው እያንዳንዷን ህመም ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ ተሰቃየ አፉንም አልከፈተም:: ሃሌሉያ! እንዴት ያለ ፍቅር ነው? እውነትም:- ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለም ነፍሱን ስለሌሎች አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ:: ለዚህ ለዋጀን ለእግዚአብሔር በግ ክብር ይሁን:: አሜን!

እስኪ ዛሬ ይህንን ጌታ እናስበውና ስላደረገልንም ድንቅ የመስቀል ስራ እናወድሰው:: በምስጋና ብቻ እንዋል እርሱ ወዳጅ ነው:: ወዳጅ ደግሞ አብዝቶ አብሮነትን እንደሚፈልግ ሁሉ ዛሬም ጌታ ከእኛ ጋር ማሳለፍን ይወዳልና እድል እንስጠው እናዳምጠው ስሙንም እንቀድስ::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ሰጠ

የማርቆስ ወንጌል 15: 33-41
33፤ ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 34 በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው። 
35 በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ። 
36 አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ። ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው። 
37 ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ። 
38 የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። 
39 በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። 
40 41 ሴቶችም ደግሞ በሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ መግደላዊት ማርያም የታናሹ ያዕቆብና የዮሳም እናት ማርያም ሰሎሜም ነበሩ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የወጡ ሌሎች ብዙዎች ሴቶች ነበሩ። 

ከስድስት ሰዓታት የመስቀል ላይ ስቃይ በኃላ ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ።  በዚህም ሰዓት ፀሐይ ብርሃንዋን ከለከለች ምድርም በጨለማ ተዋጠች:: በዘመኑ የነበረው የሰው ልጅን ያስተውል ይሆን? ያለ ሰዓቱ ጨለማ ሲሆን? እርግጠኛ ነኝ ያስተውላሉ ግን በምን ምክንያት እንደሆነ የሚያውቅ አንድ ሰው እንኳን አለ ለማለት ያስቸግራል በኢሳያስ ላይ እንደሚለው:- በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ማንም አላስተዋለም::

በዛ ሁሉ ስቃይ ውስጥ አልፎ በድብደባ፤ በረሀብ እንዲሁም እንቅልፍ በማጣት ተዳክሞ እያለ በዙሪያው ያሉትን ያስገረመ ነገር ሆነ ይሄውም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? አለ:: እግዚአብሔርም ተወው ፊቱንም አዞረበት የመጣበትን ስራውን እስኪጨርስ ድረስ:: በታላቅ ድምፅ መጮህ አይደለም አይኑንም ማንቀሳቀስ የሚያቅት ከባድ ህመም፤ ስቃይና ድካም ላይ ነው ያሉት ብለው ነው የሚያስቡት ለዚህም ነው ሞታቸውን ለማፍጠን ጭናቸውን የሚሰብሩት:: እነዚህ ወታደሮች ብዙዎችን አይተዋል ሁሉም በሰመመን ውስጥ ገብተው ነው የሚሞቱት እንጂ ይህን ያህል ሀይል እንደማይኖር እርግጠኛ ናቸው:: እርሱ ግን ጮሆ ነፍሱን በፈቃዱ አስረከበ:: ለዚህም ነው በፊቱ ቆሞ የነበረው የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። ሃሌሉያ! የእግዚአብሔር ልጅ ነው! ይህን ሁሉ የሆነው ስለእኔ ነውና ጌታን አመሰግናለሁ::

የቤተመቅደሱን መጋረጃ ምን ነካው? ከስራው ማን አሰናበተው? ከዚህ በኃላ በእኔና በህዝቤ መካከል አትለይም ብሎ ከላይ ወደታች ቀደደው ስለዚህም በእየሱስ ስጋ በኩል ወደፊቱ ለመግባት ድፍረትን አግኝተናል ደሙ ከሐጥያት ሁሉ አንፅቶናል:: በእኛና በእርሱ መካከል የሚለይ ነገር የለም እርሱ በእኛ፤ እኛም በእርሱ ውስጥ ነን:: ሃሌሉያ::


የእየሱስ መቀበር

የማርቆስ ወንጌል 15: 42-47
42፤ አሁንም በመሸ ጊዜ የሰንበት ዋዜማ የሆነ የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ የከበረ አማካሪ የሆነ የአርማትያስ ዮሴፍ መጣ፥ 43 እርሱም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር፤ ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። 
44 ጲላጦስም አሁኑን እንዴት ሞተ ብሎ ተደነቀ፥ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ቆይቶአልን? ብሎ ጠየቀው፤ 
45 ከመቶ አለቃውም ተረድቶ በድኑን ለዮሴፍ ሰጠው። 
46 በፍታም ገዝቶ አውርዶም በበፍታ ከፈነው ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው፥ በመቃብሩ ደጃፍም ድንጋይ አንከባለለ። 
47 መግደላዊትም ማርያም የዮሳም እናት ማርያም ወዴት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።

ከአርማትያስ የሆነው ዮሴፍ የሚባል ሰው የእየሱስን ስጋ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ገብቶ ጠየቀ:: ደፍሮ የምትለውን ቃል እዩልኝ ምክንያቱም ዓለም ሁሉፊቱን ከእየሱስ ባዞረ ጊዜ ዋጋ ቢያስከፍለኝም ያስከፍለኝ የመጣም ይምጣ ብሎ ነው የጠየቀው እናም የተፈቀደለት:: ጲላጦስ ግን በዚህ ፍጥነት እንዴት ሞተ ነበር ያስገረመው ይህ የሚያሳየው በራሱ ነው ነፍሱን የሰጠው ጌታችን:: ማንም ነፍሴን ከኔ አይወስዳትም በፈቃዴ ግን አኖራለሁ ብሎም የለ?

ሌላው ስለዮሴፍ ያየሁት ነገር የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር ይላል ከስራቸውም ጋር አይተባበርም ነበር:: የሚገርም አቋም ነው መንግስቱን መጠበቅ ይህንንም በማድረጉ መቃብሬን ከባለ ጸጎች ጋር አደረግህ የሚለው ትንቢት በእርሱ ተፈፀመ:: ለራሴና ለአንባብያን የምጠይቀው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየተጠባበቅን ነው? ጌታ በደጅ ነው መንግስቱን አገልግለን እንለፍ በእጃችንም ያለውን መክሊት እናትርፍበት::

በዚህ ክፍል ላይ የምናያቸው ሴቶች አሉ:: እነዚህ ሴቶች የጌታ ወዳጆች ናቸው ትጋታቸውም ይገርማል ከማለዳ ጀምሮ እስከመጨረሻዋ እረፍቱ ድረስ ይከተሉና የሚደረገውን ሁሉ ያዩ ነበር:: አንድ እንኳን ሐዋርያ ሊገኝ ባልቻለበት ሁኔታ እነሱ ግን አልተለዩትም:: እነሳለሁ የሚለውን መልእክት ስላላስተዋሉ በዛ እንኳን መጽናናት እስከማይችሉ ድረስ ነው የነበሩት:: የእነሱ ዓላማ ያረፈበትን አይተው ተመልሰው መተው ፍቅራቸን ሽቱና ዘይት በመቀባት ለመግለጽ እንጂ የትንሳኤው የመጀመሪያ ምስክር የመሆን አልነበረም:: ሽቶውንማ መቅደላዊት ማርያም ከአንድ ቀን በፊት አድርጋለች:: ተናግሮም ነበር ለመቃብሬ እያዘጋጀችኝ ነው ብሏቸው ነበር ግን ማን ቢሰማ? ወገኖቼ ጌታ ይናገራል ማስተዋልን ይስጠን ስንቱ ሽው ብሎ ሳንገነዘበው አልፎብን ይሆን?! ጌታ ይርዳን!

ጌታ እየሱስ ስለእኛ ሞትን ቀመሰ ተቀበረ እንዴት ያለ አእምሮን የሚያልፍ ፍቅር ነው:: ታድያ እንደዚህ ከወደደን እንዴት ቅርብ ሆኖ ሊረዳን እንዳለ፤ ፀሎታችንን ሊሰማና ሊመልስ እንደሚችል አይጥፋብን እኛ በጣም የተወደድን ልጆች ነን! ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ብሌናል:: ሃሌሉያ!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 16

ኢየሱስ ተነሥቶአል በዚህ የለም

የማርቆስ ወንጌል 16: 1-6
1፤ ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ። 
እርስ በርሳቸውም። ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር፤ 
ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ።
ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። 
እርሱ ግን። አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። 

የእየሱስን መቃብር እስከ መጨረሻ አይተው የሄዱት ሽቱ አምጥተው ሊቀቡት ነው:: ያሳሰባቸው ግን አንድ ነገር አለ እሱም ድንጋዩ ነበር እየተነጋገሩም የመጡት እሱኑ ነበር:: ነገር ግን ስንት ጊዜ ነው ጌታ እነሳለሁ ብሎ የነገራቸው?! ማስተዋልን ይስጠን! እርሱ በህይወት አለ እነርሱ ግን እንደሞተ ነው የሚያውቁት ገንዘባቸውን ጊዜያቸውን እያባከኑ ነው በእርግጥ ፍቅራቸው በጣም ደስ ይላል:: እርሱ ግን ወደገሊላ እቀድማችኃለሁ እንዳለ ይመጣ ነበር:: ቢሞትም እንኳን ብዙዎች ሲተውት እነሱ በታማኝነት መጡ:: የበለጠን ዜና ተቀበሉ:: ከእውቀት ያለፈ ነው ጌታችን የሚለንን ብቻ እንስማው እናም እንዴት ብለን አንጠይቅ አሜን እንጂ:: ሁላችንም ታሪክ አለን ትላንትን እንዴት እንዳሳለፈን ዛሬም ያው ነው አይጥፋብን ያደረገልን ተአምራት:: ቀና ብለው ሲያዩ ድንጋዩ ተንከባሏል!!! ሃሌሉያ! ያስጨነቀን ነገር ሁሉ ዛሬ በእየሱስ ስም ይንከባለል:: አሜን!

ከዛም ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ።  የእግዚአብሔር መልአክ በዛ እየጠበቃቸው ነበር ኃዘናቸውን የሚያስረሳ ዜና ሊነግራቸውና የመጀመሪያዎቹ የትንሳኤ ምስክሮች ሊሆኑ:: መልአኩም:- አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ።  መቃብሩ ባዶ ነው ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል እርሱ ብቻም አይደለም የተነሳው በእርሱ ያመንን እኛም ተነስተናል!! አሜን! ዮሃንስ እንደጻፈው በራእይ ላይ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። አሜን! የምናመልከው ጌታ ሁሉን የተቆጣጠረ ነው:: ለነሱ እነሳለሁ ብሎ እየደጋገመ ነግሯቸው እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ለእኛ ደግሞ እመጣለሁ እንዳለ ነውና ጌታ ይመጣል እንዘጋጅ!!

ማራናታ!!


የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል በእጃቸው ላከው

የማርቆስ ወንጌል 16: 6-8
እርሱ ግን። አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ።  ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም። ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው።  መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም አንዳች አልነገሩም። እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው። 

የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው:: አሜን! ወንጌል ዘመን ተሻጋሪ ነው ዛሬም አልተለወጠም! ዛሬም ይሰራል አሁንም የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች እንዲድኑና ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት እንዲፈልሱ ነው:: ለዚህ ወንጌልም ባለአደራ ሆነን በእጃችን ተቀብለናል:: ጌታ ይርዳን መድረስ ያለብንን ሰዎች ሁሉ እንድንደርስ::

እነዚህ ሴቶች የመጡት አስክሬን ፍለጋ ነው የጠበቃቸው ባዶ መቃብር ከመላእክ ጋር ታድያ እንዴት አይደነግጡ? ጭራሽ በዚህ የለም ሲላቸው ስንት አሳብ በአእምሯቸው ውስጥ እንደተመላለሰ መገመት ይቻላል የት ወሰዱት? ለምን ያንገላቱታል? ሌላም ሌላም እንጂ ተነስቷል የሚለው አሳብ ውልም አላለላቸውን:: ሲነግራቸው ነበር እንደሚነሳ ግን አላስተዋሉም::

መልአኩም መልክት ላካቸው ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩ ካለ በኃላ ለጴጥሮስም ይላል ጴጥሮስ ደቀመዝሙር ውስጥ አይጠቃለልም እንዴ? ምናልባትም ሶስት ጊዜ ስለካደው በፀፀት ላይ ይሆን? ብቻ ጌታ የሚያውቀው አለና ነው ይህንን ያስገባው:: ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው።  ይህንን ሁሉም ስተውታል ደግሞ ደግሞ የነገራቸው ጉዳይ ነእ ተነስቶ ሲመጣ ቀጠሯቸው በገሊላ ነበር ግን አንዳቸውም ትዝ አላላቸውም ስለዚህ ነው ሌላ መልክተኛ ያስፈለገው:: መቼም እህቶቻችን የመጡት ለምድር ሚሽን ነበር እርሱ ግን የምስራቹ አብሳሪ አድርጎ ሚሽናቸውን ቀየረው ሽቷቸውንም ይዘው ወደ ሚሽናቸው ወጡ::

ነገር ግን የገጠማቸው ያልጠበቁት ስለነበረ አእምሯቸው ማገናዘብም የከበደው ይመስላል በቃሉም እንደሚነግረን መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ እንጂ ሃሌሉያ ጌታ ተነስቷል ብለው አይደለም ከዛ የወጡት:, ጠብቀው ግን ቢሆን ኖሮ እንዴት ያለ የአምልኮ ጊዜ ይሆንላቸው ነበር ብዬ አስባለሁ:: ጌታ ምን ብሎናል? በጣቢያው ላይ ያለንን በልባችን ይዘን እንጠብቀው ጌታ አይዘገይም:: ሄደውም መልክቱን ሲናገሩ በአጭሩ ተናገሩ ነው የሚለው ምናልባትም ልክ እንሆን ያየነው እውነት ነው እያሉ ይሆናል ግን እራሱ ሲመጣ ሌላ ምን ምስክር ያስፈልጋል ያኔ ሁሉም ሞትን ድል ነስቶ መነሳቱን አወቁ::

ጌታ ሊመጣ በደጅ ነውና አይናችንን በእርሱ ላይ እናድርግ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


እየሱስ አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ

የማርቆስ ወንጌል 16: 9-14
9፤ ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ። 10 እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ 
11 እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። 
12 ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤ 
13 እነርሱም ሄደው ለሌሎቹ አወሩ፤ እነዚያንም ደግሞ አላመኑአቸውም። 
14 ኋላም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፥ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። 

እንደው እውነት እንነጋገርና እኛ ብንሆን ከሞት የተነሳነው መጀመሪያ ለማን እንገለጥ ነበር? አልሞትኩም በህይወት አለሁ! እያልኩኝ ለጲላጦስ፤ ለሔሮድስ ወይም ለሊቀ ካህናቱ አይመስላችሁም? እየሱስ ግን የታየው ለተከታዮቹ ብቻ ነበረ ለዛውም ሰባት አጋንንት ላወጣላት በአገልግሎቱ እጅግ በተጠቀመች ሴት ብዙ ስለተተወላት ብዙ ለወደደች ከፍቅርዋም የተነሳ ያልተለመደ የሽቶ ብልቃጥን በመስበር ስጋውን ለመቃብር ላዘጋጀች ምስኪን ሴት:: እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ 
እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። ይገርማል! እነሳለሁ ብሎ ስንቴ አስተምሯል አሁን ደግሞ የመነሳቱ ዜና ሲመጣ ሊያምኑ አልፈለጉም:: ኃዘናቸውን ትተው በደስታ ተሞልተው መጠበቅ ሲገባ አላደረጉትም:: ጠላትና ስጋችን የሚለንን ትተን ቃሉ የሚለንን እንያዝ::

ሁለቱ የኤማኦስም መንገደኞችም ታየን ብለው ነገሩአቸው እነሱንም አላመኑም:: እየሱስ ግን ከተበተኑበት አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ እያደረጋቸው ነው:: በስተመጨረሻም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፥ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። 

ነቀፈ?! እንዴት አይነቅፍ ሲነግራቸው ከርሞ አላስተዋሉም መልእክተኛም ቢልክባቸው አላመኑ ታድያ ይገርማል ቢወቀሱ? እየሱስ የሚወቅሰን በአንድ ነገር ነው እርሱም አለማመንን:: ያለ እምነት እግዚአብሔር ደስ ማሰኘት አይቻልምና እንዲሁም ጻድቅበእምነት በህይወት ይኖራል እንደሚል የምናምን አማኝ እንሁን!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን ማስተዋልንም ይስጠን!


የተሰጠን አደራ

የማርቆስ ወንጌል 16: 15-16
15፤ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፡ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። 16 ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። 

ከትንሳኤው በኃላ ጌታ እየሱስ በመካከላቸው ተገኝቶ አደራን ሰጣቸው:: ይህንን ቃል ለምናምንም ሁሉ ነው ይህ አደራ እንጂ ለሐዋርያቱ ብቻ አይደለም::

  1. ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፡ – እንግዲህ በመጀመሪያ የተሰጠን አገልግሎት እኛ ነን ወደ አልዳኑት የምንሄደው:: የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ባይሄዱ ኖሮ እኛጋር ወንጌል ባልደረሰ ነበር::
  2. ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። የምንሰብከው ለፍጥረት ሁሉ እንጂ ለኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም:: ጌታ ሁሉንም የሰው ልጅ ነው በልጁ መጠቅለል የሚፈልገው:: ሳንመርጥ ለሰው ልጅ ሁሉ ወንጌልን እንንገር:: እግዚአብሔር እንታረቅ በደልንም አላድብም ይላል ብለን መልክቱን እናድርስ::
  3. (በስብከታችሁ) ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። መጠመቅ በአደባባይ በጌታ በእየሱስ አዳኝነት አምኛለሁ ብሎ በአደባባይ ማወጅ ነው እንጂ ጌታ ሲደመር መጠመቅ መዳን ነው ብለን እንዳናስብ መዳን በበጉ በእየሱስ በማመን የሚመጣ ነፃ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው:: ለምሳሌ ቆርኖሊዮስን በሐዋ 11:1-18 ስናይ ሳይጠመቁ በፊት መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረዷልና መዳናቸውን እናውቃለን:: ሌላው ደግሞ ከጌታ ጋር የተሰቀለው ወንበዴ ዛሬ በመንግስትህ አስበኝ ብሎ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ ተብሎ ድኗልና:: ካልተጠመቅን መንግስተ ሰማያት አንገባም አይደለም ምልክት ነውና እንጠመቃለን::

በጸሎት እየተጋን ጌታ የተሰጠንን ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን የመስበክ ተልዕኮ እየተወጣን ሰዎችን ከፍርድ እንታደግ እንዳለንም በመሄድ እናድርስ:: እንደተፈረደባቸው አያውቁም እኛ ግን እናውቃለንና ሙጭጭ ብለን ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት እንዲፈልሱ እንርዳቸው:: ይህ ተልዕኮ የተሰጠ ለሁላችንም ነው እንጂ ለተወሰኑ ሰዎች አይደለም::

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


የአማኝ ምልክቶች

የማርቆስ ወንጌል 16: 17-20
17፤ ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ 18 የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ። 
19 ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። 
20 እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።

ጌታ እየሱስ ሂዱና ወንጌልን ስበኩ ብሎ ሲልከን ባዶ እጃችንን አይደለም:: አብሮን እንደሚሰራ ነግሮን ነው በእኛ ብቃትና ችሎታ የሚሆን ነገር የለም ሁሉ በእርሱ ነው:: እርሱ ደግሞ እውነተኛ ነውና ስናምነው እነዚህ ምልክቶች ይከተሉናል፤

  1. በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በስሙ ነው የሚወጣው ምክንያቱም ስሙ ከስም ሁሉ በላይ ከፍ ያለ እንዲሆን አብ አድርጏልና ሁሉ ይንበረከካል:: ከእኛ ጋር ስሙን የሚያያይዘው ነገር የለም የበር ቁልፍ ቢሰጠን ማን እንደሆንን አይቶ ነው እንዴ በሩ የሚከፈተው? በፍፁም የቁልፉ ትክክለኝነት ብቻ ነው የሚያስፈልገው:: ስሙም እንደዚሁ ነው በራሱ ይሰራል አምነን መሰማራት ብቻ ነው ከእኛ የሚጠበቀው:: አጋንንት ይህንን ስም ስንጠራ ለቆ ይሄዳል::
  2. በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ ይህ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላታችን ልዩ ምልክት ነው:: መንፈስ በማይነገር መቃተት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በእኛ ውስጥ ይጸልያልና አበረታታችኃለሁ ሁልጊዜ በልሳን መጸለይን አዘውትሩ:: በአማርኛ ስንጸልይ ወድያው ጸሎታችን ያልቃል በልሳን ግን ከሆነ ሙሉ ቀን መጸለይ ይቻላል::
  3. እባቦችን ይይዛሉ፥ መቼም እየዞርን እባብን ከነነፍሱ የመያዝ ራዕይ አይደለም ይሄ ነገር ግን ጠላት የሚያመጣውን ውጊያ ሁሉ ማየትና ማሸነፍን ያሳየናል
  4. የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እኔ መርዝ ብጠጣ አልሞትም ብሎ መጠጣት ሳይሆን ሳናውቅ ጠላት ሊያጠቃን ቢመጣ ጥበቃ አለን:: እርሱ ሊሰርቅና ሊገድል አይደል የሚመጣው?
  5. እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ:- እየሱስ ደዌያችንን ተቀብሏል ህመማችንንም ወስዷልና በእምነት እጃችንን ስንጭን የህመም ኃይል ይሰበራል::

ኢየሱስም ይህንን ሁሉ ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።  አሜን ሊቀ ካህናችን እየሱስ በሰማይ አለ:: ሐዋርያትም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር። እነሱ እንደወጡ እኛም ወተን እንስራ ጌታም ከእኛ ጋር አብሮ በመስራት ቃሉን ያጸናልና:: ሃሌሉያ! ጌታ አልተለወጠም!!!

የጌታ ጸጋ ይብዛልን!!
የማርቆስን ጥናት እዚህ ላይ ጨርሰናል::


2ኛ ቆሮንቶስ ሰዎች

መግቢያ

የዚህ መጽሐፍ ዓላማ

  1. ቃል በገባው መሰረት ለምን ወደ እነርሱ ለመምጣት እንደዘገየ ለማብራራት (16:5-9):: ልዩነታቸውን እስኪያስወግዱ እየጠበቀ እንደነበር ለማሳወቅ (1:23-2:3) እንዲሁም በመካከላቸው ይቅርታን እንዲያደርጉ በተለይ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቼዋለሁ ካለው ሰው ጋር (2:5-11)፤
  2. ሐዋርያ መሆኑን ረገጥ አድርጎ ሊነግራቸው (3:1-3; 4:1-15; 10:10-14; 11:4-6, 13-15; 13:3) እና
  3. ተጨማሪ መመሪያ ለእየሩሳሌም ስለሚሰበሰበው መዋጮ ለማስገንዘብ ነው (9:1-11)

ይህ ቤተክርስቲያን የተመሰረተው በሁለተኛው የጳውሎስ የወንጌል ጉዞ ላይ ነው ጉዞው በሐዋ 18:1-18 እና 20:2-3 ተጠቅሷል:: ቤተክርስቲያንዋ ችግር ስለነበረባት በብዙ ይገናኙ ነበር ከጳውሎስ ጋር: ኤፌሶን እያለ የመጀመሪያውን ደብዳቤ ጻፈ ከዛም ወደ እነርሱ መቶ ጎብኝቷቸዋል (2:1-2) ከጉብኝቱ በኃላ ያለውን መረጃ አድርሰውታል:: ለዛ መረጃ ነው ይህንን መጽሐፍ የጻፈው:: በሐዋ 20:1-3 መሰረት ሊጎበኛቸው መቷል::

የመጽሐፉ ጸሐፊው እራሱ ጳውሎስ ነው (1:1; 10:1)

ምዕራፍ 1

ምዕራፍ 1 ንባብ

2ኛ ቆሮንቶስ 1: 1-2

1፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ 2፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ እንደሆነ የሚነግራቸው የማይቀበሉትና የሚገፉት ሰዎች ስለነበሩ ነው ግን እርሱ ሐዋርያ የሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው:: የጌታ ጸጋና ሰላም ከእኛ ጋር ይሁን::


በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል

2ኛ ቆሮንቶስ 1: 3-6
የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።  እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና።  ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው። 

አምላካችን:-

  1. ሩህሩህ ነው::
  2. የሚያጽናና ነው::
  3. አባት ነው::
  4. አምላክም ነው:: አሜን!

በቃሉ ውስጥ በብዙ ቦታ ላይ ስለ እግዚአብሔር ርኅራኄ ተነግሯል በሉቃስ 6: 36፤ አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ ይላል:: ወደ ጸጋ ዙፋኑ ቀርበን የሚረዳንን ጸጋ ለመጽናናት እንቀበላለን:: ጌታ እየሱስ በምድር ሲመላለስ ወደ እርሱ መተው የለመኑ ሁሉ እረፍትን እንዳገኙ ዛሬም በስራ ላይ ነው ይሰማል ይራራል ይረዳል:: አሜን!

በመከራ የሚያጽናና እርሱ ነው ሰው እስከተወሰነ መንገድ ብቻ ነው አብሮን ሊጏዝ የሚችለው ጌታ ግን እስከ ዓለም ፍጻሜ:: ሃሌሉያ! ስለመጽናናት የሚያወራ መቼም የተጽናና መሆን አለበት እንደ ጳውሎስ ደግሞ በመከራ ስለወንጌል የከፈለ አላየሁም:: ተደብድቧል ሞተ ብለው ጥለውት እስኪሄዱ: ታስሯል: ከአውሬ ታግሏል: በማዕበል ተንገላቷል; በወንድሞች ተሰዷል; ተርቧል; ተራቁቷል; በአይሁድ ተሳዷል ወዘተ:: በዚህ ሁሉ ያጽናናውና ያቆመው ግን የርኅራኄ አምላክ ነው:: ለዚህ ነው በተጽናናንበት መጽናናት ማጽናናት የምንችለው ካላለፍንበት ግን የጉዳቱ ጥልቀት ስለማይገባን ሰባሪ እንጂ አጽናኝ አንሆንም::

የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና።  ይህ ማለት ስለ መዳናችን የምንፈጽመው ነገር አለ ለማለት አይደለም እሱንማ ተፈጸመ ብሎ ጨርሶታል:: እዚህ ጋር የሚናገረው ጻድቅ የሆነውን እየሱስን ስለ ሐጥያቱ ሳይሆን ጻድቅ ስለሆነ ነው ያስወገዱት እኛም ዛሬ በጽድቅ ስንኖር ለዓለም አይመቻትም ስለዚህ ወደ ስቃይ ይወስደናል ጌታን በእውነት መከተል ከቤተሰብ ጀምሮ ዋጋ የሚያስከፍል ነው:: እንግዲህ በዓለም ተቀባይነት እንድናገኝ የጌታን ነገር ገታ እናድርግ? አረ ይቅርብኝ ልገፋ እንጂ ጌታን በመምሰል እምላለሳለሁ ከዓለም እራሴን ለጌታ ስለለየሁ በአንዳች አልጎድልም ጠላት እንደሚሰብከው ማለት ነው ‘ምን አለበት?’ ችግር አለብት ነው መልሱ ምን አለበት ታድያ እየሱስም የተወሰነውን ሳይክፍል ቢተውልን? ሙሉ በሙሉ ዋጋዬን ከፍሎ ዋጅቶኛልና እኔ የርሱ ነኝ እርኩስንም አልነካም:: ብገፋ እንኳን ጌታ መጽናናቴ ነው::

መከራ የሚያሳድደው ሌላውን ለመርዳትና ለማገልገል በሚነሳው ላይ ነው:: ለዚህ ነው መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ የሚላቸው:: እኛም ስንጸና ስታዩ እናንተም ትጸናላችሁ ይላል:: መጽናታችን ሌሎችን እንደሚያጸና አውቀን በጽድቅ በመመላለስ ጌታን እያገለገልን እንኑር:: ጸጋው ይብዛልን::


በእግዚአብሔር መታመን

2ኛ ቆሮንቶስ 1: 7-11
7፤ ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና። 8፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ 9፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። 10-11፤ እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።

እዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ እንደማንኛችንም በእስያ በደረሰባቸው ስደት ተስፋ ቆርጦ መጨረሻችን ነው መውጫም የለም ብሎ እንዲያውም የሞትን ፍርድ ሁሉ በውስጣችን ሰምተን ነበር ይላል:: ነገር ግን እግዚአብሔር ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ አሜን! የምንታመነው በእርሱ ካልሆነ በስተቀር አንድቀን የእኛ ነገር ማጠፊያው ያጥራልና ሁልጊዜ በጌታ እንታመን:: መደገፊያችን ክንዳችን ሳይሆን ልክ እንደ እዮሳፍጥ የመጣብንን አንችልም ብለን በፊቱ ስንወድቅ ድብቅ ጦርን ያስነሳል ብቻ ምን አለፋን መፍትሄ አለው::

በዚህ ውስጥ የዝች ቤተክርስቲያን ድርሻ የነበረው መጸለያቸው ነው ለእነጳውሎስ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ ይላቸዋል:: በተሰጣቸው ጸጋ ጸልየዋል መትረፋችንም ለእግዚአብሔር ምስጋናን አምጥቷል እያለ ነው:; ጸሎት ይሰራል ዛሬም ጌታ ይሰማል ይታደጋል:: በጸሎት እንትጋ በፊቱ መገኘት መልካም ነውና::


የጉብኝቱ እቅድ መለወጥ

2ኛ ቆሮንቶስ 1: 12-24
12፤ ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የሕሊናችን ምስክርነት ነው። 13 
14 ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አንጽፍላችሁምና፤ በጌታችን በኢየሱስ ቀን እናንተ ደግሞ ትምክህታችን እንደምትሆኑ እንዲሁ ትምክህታችሁ እንድንሆን፥ በከፊል ስለ እኛ እንዳስተዋላችሁ ፈጽማችሁ ታስተውሉት ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ።  15 በዚህም ታምኜ፥ ሁለተኛ ጸጋ ታገኙ ዘንድ አስቀድሜ ወደ እናንተ እንድመጣ፥  16 በእናንተም መካከል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ ደግሞም ከመቄዶንያ ወደ እናንተ መጥቼ ወደ ይሁዳ በጉዞዬ እንድትረዱኝ አሰብሁ።  17 እንግዲህ ይህን ሳስብ ያን ጊዜ ቅሌትን አሳየሁን? ወይስ በእኔ ዘንድ አዎን አዎን አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የማስበው በዓለማዊ ልማድ ነውን?  18 እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም።  19 በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል።  20 እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው። 21 በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥  22 ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው።  23 እኔ ግን ልራራላችሁ ስል እንደ ገና ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣሁ በነፍሴ ላይ እግዚአብሔርን ምስክር እጠራለሁ።  24 ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፥ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና።

ጳውሎስ እመጣለሁ ብሎ ያልመጣበትን እያብራራላቸውና ዝርዝር መረጃንም እየሰጣቸው ነስ በዚህ ስፍራ ላይ:; እነሱ ግን ተአማኒ አይደለም ቃሉን እንኳን አይጠብቅም የሚሉ ተቃዋሚዎች ለሚያወሩት ወርኡ ነው መልስ የሚሰጠው:: ጳውሎስ ማለት የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ እንደምሆኑ እየዋሸ ወይም ማታለል አይደለም የያዘው ሲለውጥ እቅዱን አስቦበት ለክርክር ሳይሆን ለፍቅር መምጣት ስለፈለገ ነው::

ሌላው እናንተንም እኛንም የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው ይላል እንደገናም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው።  ሁላችንም የጌታ ነን ማንም ለማንም አይገዛም የሚገዛ በህዝቡም ላይ አለቃ እግዚአብሔር ብቻ ነው:: እኛን ያዳነ በቅዱስ አጠራርም የጠራን ጌታ ነው:: አሜን!


ምዕራፍ 2

ምዕራፍ 2 ንባብ
በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ፍቅር ይቅደም

2ኛ ቆሮንቶስ 2:1-4
1፤ ነገር ግን ዳግመኛ በኀዘን ወደ እናንተ እንዳልመጣ ስለ እኔ ቆረጥሁ። 2፤ እኔስ ባሳዝናችሁ፥ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? 3፤ ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸውም በመምጣቴ ኀዘን እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍሁላችሁ፥ ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ታምኜአለሁና። 4፤ በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና፤ ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም።

ትልቁ ጳውሎስን በዝች ቤተክርስቲያን ውስጥ ያስወቅሰው ጉዳይ እመጣለሁ ብሎ አለመምጣቱ ነው:: ምክንያቱን እንደሚገልጸው ችላ ብሎ ወይንም ደግሞ ረስቶ ሳይሆን ነገር ግን በኀዘን ወደ እናንተ እንዳልመጣ ስለ እኔ ቆረጥሁ እናም በመምጣቴ ኀዘን እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍሁላችሁ ይላል:: መሸሽ የያዘው እንዳያሳዝናቸው ነው:: ከዚህ በፊት እንዲያስተካክሉ የጻፈላቸውን ነገሮች እንዳልጨረሱ መረጃ ስላለው እንደገና በዛው ጉዳይ መነጋገሩን አልፈለገም:: በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና፤ እንደገና መነጋገር ይቅርብኝ:: ውስጡን አሳዝኖታል በመካከላቸው እየሆነ ያለው ነገር:: ይህንን ሲል ከጥላቻ አልነበረም ነገር ግን እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም:: ነገርን ሁሉ በፍቅር እንያዝ እኛ የፍቅር እንጂ የህግ አገልጋዮች አይደለንም:: እንደጳውሎስ ያለን ለመንጋው እንደዚህ እያለቀሰ የሚጠነቀቅ አገልጋይ ያብዛልን::

ለምንወደው ሰው መልካም ብቻ ሳይሆን ስህተትም ካለ ቢያምም ቢያስለቅስም ማሳወቅና በፍቅር ማቅናትን ተምሬያለሁ::


ይቅርታ፥ ፍቅርና ማጽናናት

2ኛ ቆሮንቶስ 2: 5-11
5፤ ነገር ግን ማንም አሳዝኖ ቢሆን፥ እንዳልከብድባችሁ፥ በክፍል ሁላችሁን እንጂ እኔን ያሳዘነ አይደለም። እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፥  ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል።  ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን አውቅ ዘንድ አሳቤ ነበር።  10 እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥  11 በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።

ጳውሎስ እዚህ ክፍል ላይ ስለ ይቅርታ፥ ፍቅርና ማጽናናት ይሰብካል:: አንድ ሰው ሲበድል የበደለው እራሱን ብቻ ሳይሆን ጉባኤውን ሁሉ ነውና የበዛ ኃዘን እንዳይሆንበት ይቅር በሉት እያላቸው ነው:: ይቅር ማለት ለራስ ነው አለበለዚያ ግን እራስን ማሰር ነው ጸሎታችንም አይሰማም ከወንድምህ ጋር አንዳች ካለህ መስዋዕቱን ተውና ሄደህ በፊት ያንን አስተካክል እንዲሁም ደግሞ ጌታ ባስተማረን ጸሎት ላይ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን ብሎም አይደል ያስተማረን? ይቅር እንባባል!

እዚህ ላይ የምንማረው ነገር የኔ ህይወት ሌላውን ምን አገባው ብሎ ነገር የለም አንዱ ሲነካ ሁሉ ተነክቷል አንዱ ሲያጠፋ ሁሉ ይነካል ምክንያቱም አካል ነን:: ለምሳሌ ኢንፌክሽን ትንሽዋ ጣታችን ላይ ቢፈጠር አጠቃላይ ሰውነታችን በትኩሳት ይነዳል ያንን ኢንፌክሽን ለመከላከል ብሎም ለመፈወስ እኔጋ አይደለም ችግሩ እጣት ላይ ብቻ ነው የሚባል አሰራር የለም ሁሉም አብሮ ይታመማል:: የክርስቶስም ቤት እንደዛው ነው በአንዱ ምክንያት ሽንፈት ይመጣልና የምንኖረው ኑሮ የጌታ ነው የእርሱ አካል ነንና እርሱን እናስከብር በአካሄዳችን ሁሉ::

የበደለንውን ወገን እናንተ መንፈሳውያን የሆናችሁ አቅኑት እንደሚል ቃሉ ወገናችንን እናቅና:: የጣቱን ምሳሌ ልቀጥል:- የሚፈውስ ነገር ለጣታችን እንደምንቀባው፥ ከተጨማሪ ችግር ለመጠበቅ እንደምናሽገው፥ እንደምንከባከብ፥ የአካልም ሁሉ ትኩረቱ በዝች ትንሽ በሆነችው የሰውነት ክፍል ላይ እንደሚሆን እንዲሁ ይህንን ሰው ለመፈወስና ለማቅናት መረባረብ አለብን::

ሁሉን በፍቅር ማሸነፍና ይህንን የክርስቶስን ፍቅር በማሳየት መመላለስ አለብን:: እንደገናም ደግሞ ማጽናናት እና ወደ ቀደመ ማንነቱ መመለስ አለብን የሰይጣን ዓላማው አንድ በአንድ እያለ መጣል ነው ስለዚህ ስራውን አንስተውም ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እየሱስ ግን ሕይወት እንዲሆንልን እንዲበዛልንም መቷል። አሜን!


በእኛ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን

2ኛ ቆሮንቶስ 2: 12-17
12፤ ስለ ክርስቶስም ወንጌል ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ ለጌታ ሥራ በር ምንም ቢከፈትልኝ፥ ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም፥ 13 ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ።  14 ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ 15 በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤  16 ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? 17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።

ጳውሎስ ከቲቶ ጋር ስላልተገናኘ በቀጠሮው ሰዓትና ቦታ መንፈሱ ተጨንቆበታል:: ቲቶን እንደዚህ አጥብቆ የፈለገበትም ምክንያት በእርሱ ነበር የመጀመሪያውን መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የላከው እራሱም እንደሚለው በብዙ እንባና ሀዘን የጻፈውን መልእክት የላከውን ከባድ መልእክት እንዴት እንደሆኑ የሚነግረው ቲቶ ነበር::

በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ ይላል ድል የመንሳቱን ነገር አንድ የሮም ጀነራል እንቢልታ እያስመታ እዩልኝ ገድሌን እያለ ከተማዋን ይዞራል በዘመናቸው አሁንም ይህንን ነገር ከእየሱስ ድል ጋር በማያያዝ ነው ያስቀመጠው ድል መንሳቱን አሳውቋል እኛን እንደ ሰራዊቱ ይዞን እያዞረ የተማረከውና ማዕረጉ የተገፈፈው ደግሞ ሰይጣንን ነው ይዞ ያሳየው ድሉን:: ድል ነስቷል እየሱስ! ሃሌሉያ! ስለዚህ እኛ ሁለት አይነት ሽታ ይዘን የምንዞር ነን:- ለሚድኑት የህይወት ሽታ ለሚጠፉት ደግሞ የሞት ሽታ:: ይህን ብሎ ሲያበቃ ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? በሚል ጥያቄ ይደመድማል::

ለዚህ የሚበቃማ ሰው

  1. ቃሉን የማይሸቃቅጥ እና
  2. በቅንነት ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆኖ የሚናገር ነው።

ለዚህ ስላበቃን ብቃታችንም እርሱ እንደሆነ የምናውቅ የምንመካበት ከጌታ ሌላ የሌለን የእርሱን ሽታ ለሰው ሁሉ የምናደርስ የራሳችን ያልሆንን ነን:: ይህ በእውነት ያስመካል!


ምዕራፍ 3

ምዕራፍ 3 ንባብ
ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው መንፈስም ህይወትን ይሰጣል

2ኛ ቆሮንቶስ 3: 1-6
1፤ እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን? ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው።  በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን።  ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤  እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። 

ቃሉን የምንሸቃቅጥ አይደለንም ብዬ ማለቴ ምስጋና ወይም እውቅና ፈልጌ ወይም ለጉራ አይደለም ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። ይላቸዋል:: ማስታወስ ያለብን እነዚህን ሰዎች ወደ እውነት ያመጣና ያገለገላቸው ጳውሎስ እንዲሁም አብረውት ያሉት ወንድሞች ናቸው እንግዲህ በምን ሂሳብ ነው ሊኮሩ ወይም ይህንን ስራ ሊክዱ የሚችሉት ወይም በራሳችን ዳንን አይሉ መቼም ጳውሎስን መግፋት የሚገርም ነው:: እርሱ ግን ምንም እውቅና አንፈልግም እናንተ እራሳችሁ በልባችን የተጻፋችሁ መልእክታችን ናችሁ የሚለው:: እውነትን ይዘን ክርስቶስን በእውነት እናገለግላለን ከምድር እውቅናን በመፈለግ ሳይሆን::

በዚህ ሁሉ ውስጥ ፍቅርን ነው የሚያሳያቸው ጳውሎስ እነሱ ለእርሱ ምን ማለት እንደሆኑ ያስረዳቸዋል:-

  1. ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። 
  2. እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥
  3. በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው። 

እናንተ ውድ ናችሁ ለእኛ ምክንያቱም በቀለም ሳይሆን የተጻፈው ደራሲው ራሱ ጌታ ነውና በልባችሁ የፃፈው ይህንን እወቁ ነው የሚለው ምንም እንኳን በመካከላቸው ሐዋርያነቱን የማይቀበሉ ቢኖሩም::

ስለዚህ እናንተን ያገለገለ እራሱ ጌታ ነው:: በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን።  ለእኛ ሳይሆን ምስጋና ለእርሱ ይሁንለት እምነታችን በእርሱ ነውና:: ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም:: አሜን ማንም ብቃት የለውም ጳውሎስ እራሱን አያዋድድም ስራው የተሰራው በጌታ ክብር የሚገባው እሱ ነው እኛ በራሳችን አንዳች አላደረግንም:: ጳውሎስ እንደዚህ አገልግሎ የአዲስ ኪዳንን አብዛኛውን መጽሐፍ ጽፎ ሲያበቃ የበቃን አይደለንም ካለ ማሰብ ነዋ! የምንመካበት አንዳችም የለንም:: እርሱም ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። ህይወት የሚሰጠው እራሱ መንፈሱ ነው ፊደልማ ከመክሰስ ውጪ ምንም አያደርግልንም:: ህያው የሆነው ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ይዋሀድ:: አሜን!


የአዲስና የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ልዩነት

2ኛ ቆሮንቶስ 3: 7-18
7፤ ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ፥ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። 10 ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። 11 ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና። 12 እንግዲህ እንዲህ ያለ ተስፋ ካለን እጅግ ገልጠን እንናገራለን፥  13 የዚያንም ይሻር የነበረውን መጨረሻ ትኵር ብለው የእስራኤል ልጆች እንዳይመለከቱ፥ በፊቱ መጋረጃ እንዳደረገ እንደ ሙሴ አይደለንም።  14 ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና።  15 ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ 16 ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል። 17 ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ።  18 እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።

በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ጳውሎስ አስቀምጦልናል በዚህ ክፍል ላይ ይህ ሊገባን ይገባል እንደ አዲስ ኪዳን አገልጋይ::

የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ከአዲስ ኪዳን የሚለያየው:-

  1. የፊደል አገልግሎት ነው
  2. የሞት አገልግሎት ነው
  3. የኵነኔ አገልግሎት ነው
  4. የከበረ አገልግሎት ነው
  5. የሚሻር አገልግሎት ነው
  6. አሳብ የሚያደነዝዝ አገልግሎት ነው
  7. በመጋረጃ የተሸፈነ አገልግሎት ነው

በሌላው እንፃር ደግሞ የአዲስኪዳን አገልግሎት:-

  1. መንፈስን የሚሰጥ አገልግሎት
  2. ህይወት የሚሰጥ አገልግሎት
  3. የጽድቅ አገልግሎት
  4. የላቀ ክብር ያለው አገልግሎት
  5. ጸንቶ የሚኖር አገልግሎት
  6. የአርነት አገልግሎት
  7. መጋረጃው የተገፈፈ – የጌታን ክብር እንደ መስተዋት የማብለጭለጭ አገልግሎት

ልዩነት አለው ሁለቱ አገልግሎት አንደባልቅው በአጠቃላይ የአዲስ ኪዳን አገልግሎት እረፍት የሞላበትና መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር መለወጥ ነው:: የአብ እቅድ ሁሉን በክርስቶስ መጠቅለል አይደል? ለዚህ ህይወት ለሚሰጥ አገልግሎት ያበቃንን ጌታ እያመሰገንን ዛሬም እሱን በማወቅና በመገለጥ መንፈስ ይሙላን:: አሜን! እኛ የአርነት አገልጋዮች ነን:- ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። አሜን! ሃሌሉያ!


ምዕራፍ 4

ምዕራፍ 4 ንባብ
እውነትን እናገልግል

2ኛ ቆሮንቶስ 4: 1-2
1፤ ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም። 2፤ ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን።

ምዕራፍ 3 ላይ ስለ አዲስ ኪዳን አገልግሎት ካስረዳ በኃላ ነው እንግዲህ እዚህ ጋር ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም የሚለው:: በምሕረቱ ነው ወደ መንግስቱ የመጣነውና የዚህ የከበረ ያለቀለት ወንጌል አገልጋዮች የተባልነው::

ሌላው እዚህ ጋር ከሚጠቅሳቸው አገልጋዮች እንደሚለይ ይናገራል:: እስኪ እንይ:-

  1. በተንኮል አንመላለስም – የተሰወረ የምናራምደው ነገር ስለሌለን ነገራችን ሁሉ በግልጽ ክርስቶስን ማክበር ነው
  2. የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም:- እውነትን እንናገራለን
  3. እውነትን በመግለጥ :- ለራሳችን እንዲመች ብለን ቃሉን አናጣምም ነገር ግን የሚያድነውን መድኅን ጌታ እየሱስን እንሰብካለን::

ከዚህ የምናየው ሰዎች እንዲመቻቸው ቃሉን እንደሚያጣምሙና ወንጌልን እንደሚሸቃቅጡት ነው ስለዚህ የበዛልንን ምኅረት እያየን ሳንታክት እውነትን በመግለጥና ለእእነት በመኖር እንመላለስ:: ጌታም ከነዚህ ሐሰተኞች እንድንጠበቅ ነግሮናል (በማቴ 7: 15፤ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።) እንጠንቀቅ እንግዲህ:


የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን ያብራ

2ኛ ቆሮንቶስ 4: 3-4
3፤ ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። 4፤ ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።

ወንጌል ግልጽና እሰየው ብለን መቀበል ያለብን እረፍት የሞላበት መዳን ነው ብለን እናስባለን ነገር ግን በጣም ተቸግረው ሰዎች የምንላቸው አልገባ ብሏቸው በራሳቸው ጽድቅን ሊያቆሙ ሲፍጨረጨሩ ደግሞ እናያለን:: የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው ጠላት ይተጋል ይህ የሚሆነው ደግሞ በቆላ 2: 3፤ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና እንደሚል እየሱስን የገፉ ናቸው ማንም ይህንን የጥበብና የእውቀት መዝገብ ከገፋ እንዴት ወንጌል ይገባል በተለይ ደግሞ የዚህ ዓለም ገዢ ተግቶ አሳባቸውን እያሳወረ::

የሰይጣንን ስራ አንስተውም እርሱ የውሸትአባት ነው፤ ሰውን የሚፈትን፤ ሰውን የሚከስ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ከሰው ልብ የሚሰርቅ፤ በተቻለው ሁሉ ወንጌል እንዳይሰበክ የሚዋጋ የእግዚአብሔር ቃልና የመንግስቱም ጠላት ነው::

በኤፌሶን 2: 2፤ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ስለዚህ መገንዘብ ያለብን ሰዎቹ ምንም አላጠፉም ያ የእውነት ጠላት ተግቶ እየተዋጋቸው መሆኑን በማወቅ ስልጣናችንን እንጠቀም:- በያዕቆብ 4: 7፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል:: መሸሽ ግድ ይለዋል የተባልነው ይህንን ስልጣን መጠቀም ነው እንጂ እንዴት ይህ እውነት አይገባም ብለን ተስፋ አንቁረጥ:: እንዲያውም እናሳደው! አባረን ኢላማችንን እየሱስን እናውለብልብ:: ጌታ የጠላትን ደጅ ያስወርሰን የምንመሰክርለትንም ሰው ወደእኛ ይላክ የምንመሰክርበትንም ኃይልና ጥበብ ጸጋም ሁሉ ያብዛልንና በአንድ ነፍስ መዳን ሰማይ እልል ይበል! አሜን!


የእግዚአብሔር ብርሀን በራልን

2ኛ ቆሮንቶስ 4:5-6
5፤ ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። 6፤ በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ፡ ያለ እግዚአብሔር ነውና።

ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰንክም:: ጌትነቱንም ያሳየን እራሱ እግዚአብሔር አብ ነው በሰማይ አዋጅን ያወጀው እየሱስ ጌታ እንደሆነ ደግሞም አብ እንዲከብር እየሱስ ጌታ እንደሆነ ምላስ ሁሉ ገና ይመሰክራል፦ ጌታም ስለሆነ ከስም ሁሉ በላይ ስምን ተቀብሏል:: አሜን! በስንቱ መድረክ ላይ ይሆን ታድያ ስለሰው ሳንሰማ የቀረነውና ክርስቶስ ብቻ ገኖ ያየነው? ክብሩ ለጌታ ሊመለስ ይገባል! የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ስናይ ግን አይኖችን ሁሉ ወደ ጌታ ነበር የሚያመለክቱት ለምሳሌ መጥምቁ ዮሐንስ:- እኔ አይደለሁም ከኔ በኃላ በእሳት የሚያጠምቅ ይመጣል ደግሞም በሌላ ስፍራ የዓለምን ሁሉ ሐጥያት የሚያስወግድ በግ እያለ ወደ እርሱ ጠቆመ እንጂ ክብርን ለራሱ አልወሰደም::

በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለው ገና ከመጀመሪያው ፍጥረትን ሲፈጥር ነበር:: አሁንም ደገመው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረትን ዳግመኛ ሲፈጥር እንደገና ብርሀን ይብራ ብሎ ጨለማችንን አስወገደው:: ይህ እልል ካላስባለ ምን ያስብላል አዲስ ፍጥረት አድርጎ የራሱ ሲያደርገን? እልልልልልልልል! አሜን! እርሱ የብርሃን አምላክ ነው:: እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፡ ከጨለማ ጋር ህብረት የለውም፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሀን ውስጥ ይኖራል፤ ብርሃንን እንደ ልብስ ለብሷል፤ ወደ እዚህ ብርሀኑ ጠራን፤ ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው፥ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ። በብርሀኑ ሁሉ ነገር ተነክቷል::

ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ይህንን አምነን መልስ የሰጠን ሁላችን ጌታን እየሱስን እንስበክ አካሉንም ዝቅ ብለን እናገልግል! እየሱስን ስናይ አብንም አይተናል ምክንያቱም ህብረታችን ከአብ ጋር ከልጁም ከእየሱስ ጋር ነውና ወደዚህ ወደሚደነቅ ብርሀን ተጠርተናል! አሜን!


የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር ነው

2ኛ ቆሮንቶስ 4: 7-9
7፤ ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 8፤ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ 9፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤

ይህ መዝገብ የሚለው ከላይ እንዳየነው ብርሀን ይብራ ብሎ በውስጣችን ያበራውን የእግዚአብሔርን ብርሀን ነው:: ይህ ብርሀን በምንም ጨለማ የማይዋጥ ነገር ግን አሸንፎ የሚያበራ በእኛ ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር ብርሀን ነው:: ሃሌሉያ! ደግሞም በሌላ ስፍራ የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። አሜን! ይህን ሲያደርግ አምላካችን የሀይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳልሆነ ሊያሳይ ወደደ:: በዚህ ውስጥ ታላቅነቱ ታይቷል እኛን ከሞት ወደ ህይወት ወደዚህም ክብር ለማምጣት እራሱ መምጣት ደግሞም መሞት ነበረበት:: የሞትንም ጣር አጥፍቶ በትንሳኤው ሀይል ተነሳ መበስበስንም አላየም የሲኦልንና የሞትን ቁልፍ ተቀበለ:: በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ነው የተዋጀነው። በትንሳኤውም የሀይሉ ታላቅነት ታየ!

የሚገርመው ግን ይህንን የከበረና ታላቅነቱን እንዲሁም ኃይሉን ያሳየበትን ስራ በሸክላ ውስጥ ማስቀመጡ ነው! አይገርምም?! ውድ የሆነን ነገር መቼም እንደምናውቀው ጥሩ ሊሰበርና ሊሰረቅ በማይችል በብዙ ጥበቃ ውስጥ ይቀመጣል እንጂ በሸክላ ውስጥ እንዴት? በእርግጥ ተስፋ ተሰቶናል ለአሰራሩ እንዲመች ወደፊት አካላችን የእርሱን እስከሚመስል እንደሚቀየር ግን ለምን አሁን አልሆነም ያልን እንደሆነ ምክንያቱ ስራውን በእኛ ውስጥ ሆኖ የሚሰራው እርሱ ስለሆነ እንዲያውም ይህ ሸክላ ውስጡ ባለው እንዲመካ ስለሚፈልግ ነው:: ማንም እንዳይመካ በስራ አይደለም የተባለውም ለዚህ ነው:: ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን! አሜን!

ስለዚህ ይህ የከበረ ጌታ በእኛ ውስጥ ስላለ

በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤

እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤

እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤

እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤

ማጠቃለያዬ አንጨነቅም፤ ተስፋ አንቆርጥም፤ አንጣልም እንዲሁም አንጠፋም ምክንያቱም ብርቱ የሆነው በእኛ ውስጥ ነውና ብቻችንን አይደለንም እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ነግሮናል ደግሞስ ከእኛ ውስጥ ወዴት ይሄዳል አንድ ጊዜ በቀራንዮ መስቀል ላይ ወልዶን ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም አይደል ያለን? ለቃሉ ታማኝ ነው ስለዚህ መሸነፍ አይታሰብም! ሃሌሉያ!


የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን

2ኛ ቆሮንቶስ 4: 10-12

10፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። 11፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና። 12፤ ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል።

ምንድነው ተሸክመን የምንዞረው በስጋችን? መልሱ:- የኢየሱስን ሕይወት ነው:: ምን ማለት ነው ሕይወቱን መሸከም ወይም በሚሞት ሥጋችን ህይወቱ ይገለጥ ዘንድ ማለት? ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ተባብረናል:: የሞተ ሰው ለራሱ አይኖርም እንዲሁ እኛ ሁልጊዜ ሞቱን ተሸክመን እየዞርን ለሞተልን እንኖራለን:: ዓለም ጌታን እንደጠላችው እኛንም ትጠላናለች ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ጌታ የሰጠን ተልዕኮ:- እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ ብሎ አደጋ እንዳለው ተልዕኮው አሳውቆናል፤ ሞትን መሸከም እንግዲህ ይህ ነው፤ መልሶም ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም ብሎም ነግሮናል:: ማለትም እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዱአችኃል:: ስለዚህ ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለን ማለት ነው:: እኔ ዓለምን አሸንፌያለሁና አይዟችሁ ብሎናል እየሱስ:: በሄድንበት ሁሉ የህይወት ወይም የሞት ሽታ መሆን ግድ ይላል::

ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን እንደሚል ጳውሎስ ይህንን ጌታ ስናገለግል ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በምናገልግላቸው ላይ ይሠራል ማለት ነው።


አንታክትም

2ኛ ቆሮንቶስ 4 13-18
13፤ ነገር ግን፦ አመንሁ፡ ስለዚህም ተናገርሁ፡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤ 14፤ ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና። 15፤ በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና። 
16፤ ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 1718፤ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።

እኛ የእምነት ሰዎች ነን እናምናለን ያመነውንም እንናገራለን እንኖረውማለን:: ያመነውም ከሞት የተነሳን ጌታ ነው እኛንም ከሞት ያነሳል ስለዚህ የጊዜው ነገር አሁን ዙሪያችንን ከቦ ለማስጨነቅ ጦር እየጎሰመ ያለውን አንፈራም ምክንያቱም የጊዜው ነው:: እኛን ማጥፋት አይችልም በእጁ መዳፍ የቀረጸን ጌታ አሸንፏልና አንፈራም:: ማስፈራራቱ ግን ይቆማል እንዴ? መልሱ አይቆምም ከእየሱስም እንኳን ለጊዜው ተለየ ነው የሚለው ፈተናው ሁሉ ከከሸፈበት በኃላ ስለዚህ እንበርታ አንታክት::

የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና እንደሚል ጸጋን ተሞልቶ በእኛ ዘንድ ያደረው እየሱስ አትረፍርፎ ጸጋውን ይሰጠናል እንዳንታክት:: በዚህ ጸጋ የውስጡ ሰውነታችን እየታደሰ ይኖራል ምንም እንኳን የውጭው እየደከመ ቢመጣም:: ጳውሎስ ስለውጭው ሰውነት መድከም ሲያወራ በዚህ ዘመን ብዙም የማናየው አይነት መከራ ውስጥ ያልፍ ነበር መደብደቡ መራቡ አረ ስንቱ ግን አልታከተም በትንሳኤ ይህ ሁሉ እንደሚረሳ እርግጠኛ ነበረ::

ስለዚህ የማይታየውን እየተመለከትን እንበርታ የሚታየውን ካየን ድካምን እናጭዳለን አይናችን ግን በማይታየው ላይ ሲሆን ዕለት ዕለት የውስጥ ሰውነታችን ይታደሳል:: አይናችሁን አድርጉ በተባለው ላይ እናድርግ:: የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። ሁልጊዜ አስተሳሰባችንን በዚህ በከበረ ቃል እንሙላው፥ ጌታንም ተስፋ እናድርግ፥ ወገኖችንም እናበርታ፥ ወደፊት እንጂ ወደኃላ ሳናይ መታከትን አስወግደን፥ ጸጋን እየጠየቅን መንገዳችንን እንጠብጥብ::


ምዕራፍ 5

ምዕራፍ 5 ንባብ
በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት አለን

2ኛ ቆሮንቶስ 5: 1-3
1፤ ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። 2፤ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ 3፤ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም።

ያለፈው ምዕራፍ ሲዘጋ አሳቡ የጊዜውን ከማየት ይልቅ የዘላለሙን ብናይ የጊዜው ነገር ቀላል ነው እያለን ነው ስለዚህም ከዚሁ ጋር አያይዞ የምድሩ ድንኳናችን ቢፈርስ በሰማይ ሌላ አካል እንቀበላለን ይለናል:: ግን ህይወታችንን ለምን ከድንኳን ጋር አመሳሰለው? ምክንያቱም እስራኤላውያን ስለድንኳን በምድረ በዳ ሲጏዙ በነበረ ጊዜ በደንብ ያውቃሉ ድንኳኑን ያቆማሉ ስርአቱን ያደርጋሉ ደግሞ እንሂድ ሲላቸው ደመናው ሲነሳ አፍርሰው ተነስተው ይጏዛሉ ምን ያህል እንደሚቆይ ይህ ድንኳን ከጌታ በስተቀር ማንም አያውቅም እንዲሁም እኛ ምን ያህል እንደምንቆይ አናውቅም:: ህይወታችን እንደዛች ናት ዛሬ ይተከላል ነገ ደግሞ ፈርሶ ይነሳል ለመመካት እንኳን የማይሆን ነው ህይወታችን ፈራሽ ግን ጌታ እራሱ መቶ እየኖረበት ያለ ድንኳን ነው ከእርሱ ጋር ነን በሰማይም ከእርሱ ጋር ነን ለዛውም በተሻለ አንዋዋር:: እርሱን ለመምሰል እንለወጣለን!

በዚህ ድንኳን ውስጥ እንቃትታለን:: ለምን ይሆን? ምክንያቱም አዲስ ፍጥረት ሆነናል አሮጌው አልፏል፤ አዲሱ በአሮጌው ውስጥ ነው የተቀመጠው ሁልጊዜ ትግል አለ ስጋ በመንፈስ ላይ እንዲሁም መንፈስ በስጋ ላይ ይቀዋወማል፤ ውስጣችን የላይኛውን ሲል ስጋችን ደግሞ አይፈልግም ብቻ ምን አለፋችሁ መጏተት ነው የያዝነው ስለዚህም ጳውሎስ በሌላ ስፍራ ላይ በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም ይለናል:: ስለዚህ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለን ይሄ ኑሮ ያኛውን በጣም እንድንናፍቅ ያነሳሳናል መጏተት የሌለበት እረፍት በሰማይ ይጠብቀናልና የጊዜውን አንይ የዘላለሙን እንጂ:: ኑሮ ስላልተመቸን አይደለም ወደ ጌታ በሄድኩኝ የምንለው ግን የሰማዩን እንናፍቅ ዘንድ ነው በዚህ አሮጌ ማደሪያ ውስጥ ያለነው:: በዚህ ምድር ስንኖር በጌታ ባንደገፍ ህይወታችን እርሱን ፈፅሞ ማሳየት የማይችል ነው የሚሆን የነበረው በሸክላ ውስጥ የከበረ ማንነቱን ያስቀመጠ ጌታ ይመስገን::


የመንፈሱን መያዣ ሰጠን

2ኛ ቆሮንቶስ 5: 4-10
4፤ በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።  እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል። ስለዚህ ደግሞ ብናድር ወይም ተለይተን ብንሆን እርሱን ደስ የምናሰኝ ልንሆን እንቀናለን። 10 መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና።

የተለመደው አሰራር ሞት ነው የሚውጥ እዚህ ክፍል ላይ ግን ሞት በህይወት ይዋጣል! አሜን! እየሱስ ሞትን ድል ነስቷል ቁልፉንም ይዟል!የመንፈሱን መያዣ የሰጠን እርሱ እራሱ እግዚአብሔር ነው ለምን? ያልን እንደሆነ በድንኳኑ ውስጥ መኖር ከባድ ስለሆነ ሊያበረታንና የሰጠን የተስፋ ቃል ሁሉ እውነት መሆኑን ለማስረገጥ ነው:: የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። ለዚያውም ይህ ያለንበት ሁኔታ እኮ በጣም የተሻለ ነው ክርስቶስን አውቀናልና የእኛ ህይወት ጌታን ካላወቀው ጋር ሲወዳደር እስከአሁን ድረስ በእግዚአብሔር ቁጣ ስር የመሆናቸው ነገር ያስፈራል እኛ ከዚህ አምልጠናል ምንም እንኳን በምጥ ውስጥ ብንሆንም ቅሉ:: ከዚህም ደግሞ የተሻለ እንዳለ በቃሉና በመንፈሱ ስለተረዳን አሁንም ወደ ተሻለው እንቃትታለን::

ሁልጊዜ ታምነን እንጂ በማየት አንመላለስም እኛ መንፈሳውያን ነን:: በመንፈስ የምንመላለስ ነን: የእምነት ሰዎች ነን በምድር ሳለን ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የሚሰማንና ጌታን የምንናፍቅ መሆን አለብን:: ስደት ላይ ያለ ሰው እኮ ተረጋግቶ እዚህ ነው ማረፊያዬ እንደማይል ሁሉ እንዲሁ እኛም መንገደኞች ነን በዚህም ምድር መጻተኞች መሆናችንን እያሰብን ልባችንን በመንገዳችን ላይ በማድረግ በጌታ ዘንድ ማደርን መናፈቅ አለብን::

በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ግድ ይላል በስጋ የተመላለስንበት ነገራችን ይፈተናል ስለዚህ የምድሩን ነገር ትተን በላይ በሰማይ ያለውን እንሻ ለእርሱም እንኑር::


አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ

2ኛ ቆሮንቶስ 5: 11-14
11፤ እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን ለእግዚአብሔር ግን የተገለጥን ነን፤ በሕሊናችሁም ደግሞ የተገለጥን እንደ ሆንን ተስፋ አደርጋለሁ። 12፤ በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን እንጂ ራሳችንን ደግሞ ለእናንተ የምናመሰግን አይደለንም። 13፤ እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው። 14፤ ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ::

የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን ማለትም ወደ ህይወት ስንመጣ የመንግስተ ሰማያትንና የሲዖልን መኖር በእርግጥ አውቀናልና ይህንን እውቀት ለሰዎች እንናገራለን:: ከእግዚአብሔር ቁጣ በልጁ ዳኑ ብለን እንሰብካለን ምክንያቱም እኛ ለእግዚአብሔር የተገለጥን ነን:: በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች በማየት ይመላለሳሉ በውጫዊ ነገር ነው ሁሉንም የሚለኩት ለእኛ ግን የውስጥ ማንነት ነው ተጽዕኖ ያለው ስለዚህም ነው ጳውሎስ በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን እንጂ ራሳችንን ደግሞ ለእናንተ የምናመሰግን አይደለንም:: ህይወታችን ምስክር ነው እኛ የተለወጥን ክርስቶስን የምንመስል አዲስ ፍጥረት ነን:: ጉራ እንዳይመስልብኝ ብሎ እንዴት ባለ ትህትና ነው እራሱን የሚያሳያቸው ምስጋናንም አልፈልግም ግን እውነታው እኛ ከውስጥ ወደ ውጭ ተቀይረናል እያለ ነው:: ይህንን ሲል ጳውሎስ በሌሎች ዘንድ እብድ እስከመባል የደረሰበትና ያስናቀው ጉዳይ ጌታ ጌታ ማለቱ ነው ግን ይህንን ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ነው ይላል ምክንያቱም እንደማንኛውም ሰው እኔም ኑሮዬን በአንድ ቦታ አርፌተረጋግቼ ልኑር ቢል ይህንን ሁሉ የሚያስደንቅ ህይወትን የሚለውጥ ቃል በእርሱ ባልደረሰን ነበር:: እብድ ብሆን ለጌታ ነው እያለ አገልግሎቱን የቀጠለ ብርቱ የእግዚአብሔር ሰው ነው:: ዛሬ ከፊታችን የቆመ ሰልፍ ምንድነው ጌታ ሰብሮ ያሻግራል ዛሬም እርሱ በስራ ላይ ነው:: አሜን!

እንደዚህም ተባለ እንደዛ ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ:: የሞተ መቼም ለራሱ አይከራከርም ፍቅሩ ግድ ስለሚለን ለሞተልን ለክርስቶስ እንኖራለን ለሚነሳብን ስደት ብዙም ፊት አንሰጠውም ምክንያቱም እኛ የምናየው የዘላለሙን እንጂ የዛሬውን አይደለም:: እኔ ለክርስቶስ እንጂ ለራሴ የማልኖር ሰው ነኝ::


ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው

2ኛ ቆሮንቶስ 5:15-17

15፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 16፤ ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 17፤ ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።

ስለእኛ ሞትዋልና እየሱስ ለእርሱ እንድንኖር ይጠብቃል!! እርሱ ህይወትን ሰጠን የሰጠንን ህይወት ደግሞ እርሱ እንዲኖርበት መልሰን እንሰጠዋለን::

ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም ምክንያቱም ወደ ህይወት ራስ ወደሆነው ወደ እየሱስ ስንመጣ የሆነው ነገር አዲስ መሆንና መንፈሱን መጋራት ነው:: ይህ አዲስ ማንነት በሚገርም ሁኔታ ጌታን በመንፈስ መገናኘት የሚችል ማንነት ነው:: ሁሉም ሰው ከክርስቶስ ሲወለድ ይህንን ብቃት አግኝቷልና ሰዎችን ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ እንዳሉ ተረድተን እንቀበል:: የሁላችንም ብቃት እራሱ ጌታ ነውና አንዱ ብርቱ ሌላው ደካማ ብሎ ነገር የለም እየሱስ በሁሉ ውስጥ ብርቱ አንበሳ ነውና:: ሁሉንም ሰው በአንድ አይን ማየት አለብን አይናችን አለመከፈቱ እንጂ ቢከፈትማ ጌታን ማየት እንችል ነበር በወንድምና በእህቶቻችን ውስጥ:: ስለዚህ ሰውን ሁሉ በስጋ እንዳለ አላውቅም መንፈሳዊ እንደሆነ እንጂ ልንል ይገባል:: ደክመው ብናይ አንበሳው እየሱስ ዛሬ አሁን ድካምን ማንሳት እንደሚችል እንጂ አለቀለት ብለን ሙሾ የምናወርድ አንሁን ከጌታ የተወለደ አይጠፋም ጌታ ሁሌ ይረዳዋል:: በስጋ እየሱስን የሚያውቀው ዮሀንስ እኮ ጌታን ሲያይ እንደሞተ ሰው ነው የሆነው ጌታ አለ በክብሩ::

ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው ሁላችንም ማንም የሚለውን መስፈርት እናሟላለን ስለዚህ በክርስቶስ የሆንን ቀን ከጌታ ጋር ፋይል ተቀያየርን እርሱ ሀጥያታችንን ወስዶ ጽድቁን አለበስንና በመንፈስ አዲስ ማንነትን በእኛ ውስጥ ፈጠረ የድሮው ማንነት ከአሁኑ ጋር አይገናኙም – አዲስ ፍጥረት አድርጏናል!! አሜን! አዲስ ካለ መቼም አሮጌ የሚባልም ይኖራል ጌታ አሮጌውን ነገር አልፎአል፤ ብሎ አወጀ ምክንያቱም እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። በመንፈስ አዲስ ሆነናል ሰው መንፈስ፤ ነፍስ እና ስጋ ነው:: መንፈሳችን እንዳልነው አዲስ ነው ስለዚህ አሁን ቃል ማንበብና መለወጥ ያለባት ደግሞ ነፍሳችን ናት (አስተሳሰባችን፤ አስተዳደጋችን፤ ቤተሰባችን፤ ባህላችን ሁሉ ተጽዕኖ አድርገውባታልና እስዋ ላይ ነው የምንሰራው ያለነው) ስጋችን ወዳሸነፈው ስለሚወግን ብዙም ስራ አያስፈልገውም:: እኛ አዲስ ፍጥረት ነን ለጌታ የተለየን አሮጌ ተራ የዕለት ዕለት ጌታን የምንናፍቅ ልጆቹ ነን:: አሜን!


እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ ነን በክርስቶስ

2ኛ ቆሮንቶስ 5: 18-21
18፤ ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ 19፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 20፤ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። 21፤ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።

ነገር ግን የሆነው ሁሉ ብሎ ነው የሚጀምረው በዚህ ክፍል ላይ ይህም ማለት ከፊት ያለውን ማየት ግድ ይላል:- “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” ይህ አዲስ ፍጥረት የመሆን እቅድ ከእርሱ መጣ እርሱው ደግሞ መቶ ሞተና ፈጸመው:: ምን አለ በዚህ አዲስ የመሆን መርሀ ግብር ውስጥ የሆነልን?

  1. በክርስቶስ ከራሱ ጋር አስታረቀን – ልብ እንበል እርሱ እራሱ ነው መቶ የታረቀን እኛ አጥፍተን ሳለን
  2. የማስታረቅም አገልግሎት ሰጠን – በሉ ሂዱና የሆነላችሁን እየተናገራችሁ ሌላውን ወደ እኔ አምጡ ብሎ ላከን:- እርሱ እራሱ
  3. እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና :- አሁንም እራሱ ነው ዓለምን ወደ እራሱ እየሳበ ያለው
  4. በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር :- ለሰዎች መንገርያለብን እግዚአብሔር እንታረቅ ብሏል ኑ ታረቁ በደላችሁን አይቆጥርም ብለን እንናገር:, ወንጌል ይሄ ነው::
  5. በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ :- ልጁን በእኛ ውስጥ ላከ ይህ ህይወት ያለው ቃል በእኛ አደረ ሌላውን ለማዳን::
  6. እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን :- መልክተኞቼ ሁኑ ብሎ ላከን ግን በእኛ የሚሰራው እራሱ እንደሆነ እንገንዘብ
  7. ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን :- እንለምናለን! ምክንያቱም አይተነዋል ምን ማለት እንደሆነ ይቅር መባልና ከጌታ ጋር ህብረት ማድረግ:: አይገርምም እግዚአብሔር እንታረቅ ብሎ ሲልክ:: ወይ ፍቅር!

ስለዚህ ቃሉ እንደሚለን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው:: እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ ነን! ይህ ጉራ እንዳይመስለን ወይም ደግሞ እግዚአብሔር መድፈር እንዳይመስለን ቃሉ እንደሚለን ነን! ትህትና እንዳይመስለን ጻድቅ አይደለሁም ማለት ግን እግዚአብሔርን መቃወም እንጂ! እንንቃ በራሳችን ስላላገኘነው ለመመካትም አንበቃም እርሱ በራሱ ሁሉን አድርጏልና እንቁምና ክብርን እንስጠው::


ምዕራፍ 6

ምዕራፍ 6 ንባብ
በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፡ በመዳንም ቀን ረዳሁህ

2ኛ ቆሮንቶስ 6: 1-2
1፤ አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ 2፤ በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፡ በመዳንም ቀን ረዳሁህ፡ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።

የእግዚአብሔር መልእክተኞች እንደሆንን ከላይ አይተናል መልክተኛ ደግሞ የተላከውን ያደርሳል ከሚልከው ጋር አብሮ ይሰራል ማለት ነው የመልእክቱ ጠንሳሽ ወይንም ተጠያቂ አይደለም:: እንዲሁም በዚህ ስፍራ ላይ እንደምናየው አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን ይላል:: አብሮ ለመስራት ጌታ ጸጋን ሰቶናልና ይዘን ብቻ ቁጭ እንዳንል ይህ ጸጋ የመጣው ሌላውን ሊጠቅም ስለሆነ በከንቱ እንዳናስቀምጠው ጌታ ይርዳን:: አሁንም ማስታወስ ያለብን ነገር የእግዚአብሔር አምባሳደሮች እንደሆንን አብረንም መልካምን ስራ ለመስራት ጌታ እንደፈጠረን እናስብ::

በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፡ በመዳንም ቀን ረዳሁህ፡ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው። የተወደደ ሰዓት አሁን ነው ይላል ቃሉ ዛሬ እድሉን ካገኘን ለሰዎች እንታረቅ ብሎ መልእክት ልኳል እግዚአብሔር በደልንም አላስብም ብሏል ብለን እንናገር የመዳን ቀን ዛሬ ነውና:: ዛሬየመዳን ቀን የተወደደም ቀን ነው:: ነገ የእኛ አይደለምና ዛሬ ላይ ሳለን ለጌታ እንስራ የመዳን ቀን ዛሬ ነው::


አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ

2ኛ ቆሮንቶስ 6: 3-5
3፤ አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። 4፤ ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ 5፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥

አገልግሎት እንዳይነቀፍ ለሌሎችም ማሰናከያ እንዳንሆን መጠንቅቅ አለብን:: በነገር ሁሉ እራሳችንን እየመረመርን የእግዚአብሔርን ስም እንዳናሰድብና ለሌሎችም እንቅፋት እንዳንሆን እንመላለስ:: እዚህ ጋር ጳውሎስ በአገልግሎቱ የገጠመውን ይነግረናል::

  1. በብዙ መጽናት/ትዕግስት :- በያዕቆብ 1:4፤ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ለአገልግሎት አስፈላጊው አንዱ ትግስት ነው ሰፊ ልብ ይዘን ነው ማገልገል ያለብን::
  2. በመከራ፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፦ እስራትና መከራ ይቆይሃል፡ ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። በሐዋ 20: 23 ክርስቶስን ስንመስል እንሰደዳለን
  3. በችግር፥ በጭንቀት:- ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ሮሜ 8: 35
  4. በመገረፍ፥ በወኅኒ :- በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። የሐዋ 16: 23
  5. በሁከት፥ በከተሞም ሁከትን አስነስተውበት ያውቃሉ
  6. በድካም፥ ሌት ከቀን በመጏዝ ነበር ወንጌልን የሚሰብከው በዚህ ውስጥ ያለውን ድካም መገመት አያቅትም
  7. እንቅልፍ በማጣት፥ በእስርና በድብደባ በመንገላታትም ሁሉ ውስጥ እንቅልፍ ይኖራል ማለት ዘበት ነው::

የሚገርመው በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ቢያልፍም እንኳን ሁልጊዜ አይኑ በጌታ ላይ ነው:: ሀይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ ነው መፈክሩ:: ይህ ሁሉ መከራ ተስፋ አስቆርጦ አልመለሰውም በዚህ ውስጥ ሆኖ የሚያሳስበው ነገር ቁስሉ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ነገር እንደሆነ ይነግረናል:: አይናችንን በጌታ ላይ ስናደርግና ቆርጠን እርሱን ልናገለግል ስንነሳ አልጋ ባልጋ አይሆንም መንገዱ ሁልጊዜ ጠላት መሰናክል ከፊታችን ያመጣል ተስፋ ለማስቆረጥ ግን እንበርታ በጌታ ጸጋና በችሎቱ አንዳች አይታጣም:: ጌታ ከእኛ ጋር ነውና እንበርታ!


ተስፋፉ

2ኛ ቆሮንቶስ 6: 6-13
6፤ በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ 
ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤  10 ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።  11 እናንተ የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፥ አፋችን ለእናንተ ተከፍቶአል ልባችንም ሰፍቶላችኋል፤  12 በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል፤  13 ልጆቼ እንደ መሆናችሁ ግን እላችኋለሁ፥ እናንተ ደግሞ ብድራት መልሳችሁልን ተስፋፉ።

በቀደመው ቁጥር ላይ አገልጋይ ሊደርስበት የሚችለውን መከራ አሳይቶናል:: እዚህ ክፍል ላይ ደግሞ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ያቆመውን ሚስጥር እናያለን:: የሚከተሉት የአገልጋይ ህይወት (qualities) እንደዚህ መሆን አለበት:-

  1. በመጦም፥ በጌታ ፊት በጾምና በፀሎት መትጋት እንዳለብን
  2. በንጽህና፥ እግዚአብሔርን በመፍራት በፅድቅ እና ቅድስና መመላለስ
  3. በእውቀት፥ እግዚአብሔርንና ቃሉን በማወቅ
  4. በትዕግሥት፥ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት በሰፊ ልብ
  5. በቸርነት፥ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት ጌታ ያለውን ሁሉ እንደሚያካፍል እኛም እንደዛው እናድርግ
  6. በመንፈስ ቅዱስ፥ በጌታ መንፈስ ላይ በመደገፍ ብቻ ማገልገል እንጂ በራስ አለመታመን
  7. ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ ያለ ፍቅር ማገልገል አይቻልም ደቀ መዛሙርት መሆናችን ትልቁ ምልክት ይህ ነው::
  8. በእውነት ቃል፥ ንጹህ የሆነውን ቃል በመስበክ
  9. በእግዚአብሔር ኃይል፥ በቃል ብቻ ሳይሆን መንፈስን በመግለጥ ማገልገል
  10. ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ የጽድቅን ጥሩር እንልበስ ቃሉ እንደሚል

ሌላው በዚህ ክፍል ላይ የምናየው ነገር እንዴት ዓለም እኛን እንደሚያየን እና እኛ መያዝ ያለብን አቋም ነው:-

  • በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ መካከል እናማጥናለን፤
  • አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ 
  • ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤
  • የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤
  • የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ 
  • ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤
  • ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤
  • አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።

ስለዚህ እንደዚህ ልባችን ሰፍቶላችሁ ህይወታችንን ሁሉ አካፍለናችሁ ነው ያገለገልናችሁ ብሎ የሚነግራቸውና የሚንደረደረው ወደ አንድ ግብ ነው ግቡም ለዚህ ብድራት እንድትከፍሉን የምንፈልገው በመስፋፋት ነው:: ስፉ አገሩን ሁሉ በክርስቶስ ትምህርት ሙሉት ስታገለግሉም እኛን በመምሰል ይሁን ነው የሚለው:: እኛም ዛሬ እነዚህን ምክሮች በማየት የጌታን ነገር እናስፋ::


እኛ የሕያው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን

2ኛ ቆሮንቶስ 6: 14-18
14፤ ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? 15 ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? 16 ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል። በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።  1718 ስለዚህም ጌታ። ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ። እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።

አንዳንዴ ሰዎች በስጋዬ የማደርገው ነገርና የፈለኩትን ባገባ ወይም ደግሞ ከፈለኩት ጋር ጏደኛ ብሆንስ ምን ችግር አለው ብለው ሲከራከሩ እሰማለሁ:: እዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ በግልጥ አስቀምጦልናል:: ውሃና ዘይት መቼም አይዋሀድም – ሊከብድ ይችላል ግን ይህ እውነት ነው፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅና የሚፈራ ሰው ማግባት እረፍት ነው:: እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን:: ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ብሎ ሲለን የዳነውን ካልዳነው ጋር ሲያነጻጽረው እስኪ እንይ:-

  1. ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና?
  2. ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?
  3. ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ
  4. የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? 
  5. ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?

እግዚአብሔር ቤተ መቅደሴ ናችሁ ብሎ ሲል ምን ማለቱ ነው? እንዴት ከሌላው የተለየን ነን?

  1. በእነርሱ እኖራለሁ :- እኛን ከመውደዱ የትነሳ እኔ ብቻ በነሱ እኖራለሁ ለሌላ አይሆኑም እያለ ነው አምላካችን:: እኔ ቀናተኛ ነኝ ይል የለ?
  2. በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ ልክ ከአዳም ጋር ያደርግ እንደነበረው ጊዜ በእኛ መካከልም ይመላለሳል
  3. አምላካቸውም እሆናለሁ:- በእኛ ላይ የሚገዛ ሌላ አምላክ ከእርሱ በቀር የለም!
  4. እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ:- እኛም ለርስቱ የተለየን ወገን ሆነናል
  5. ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ:- መለየት ግድ ይላል ቅድስና ለእግዚአብሔር
  6. ርኵስንም አትንኩ ይላል:- ከክፉ ርቀን እርሱን ብቻ እንመስላለን
  7. እኔም እቀበላችኋለሁ:- እርሱም ተቀብሎናል የእግዚአብሔር ወገን ተብለን ተጠርተናል::
  8. ለእናንተም አባት እሆናለሁ:- አባ አባ የምንልበትን የልጅነት መንፈስ ሞልቶናል::
  9. እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል :- አንድ ጊዜ ከማይጠፋው ዘር ተወልደናልና ልጅነታችንን የሚክድ የለም እኛ የህያው እግዚአብሔር ልጆች ነን:: አሜን!

እንግዲህ እንደዚህ ናችሁ ለእኔ እያለን እንዴት አድርገን በማይመች አካሄድ ለመሄድ እንነሳለን? እንዴትስ ከአመጽና ከጨለማ ጋር እንተባበራለን? አረ ይቅርብን ለጌታ መሆን ይሻለናል:: ማመቻመች ትተን ለእግዚአብሔር በዘመናችን ሁሉ እንለይለት! የጌታ ፀጋ ማስተዋልን ይስጠን! አሜን!!

በፈቃዴ እንዲሁም ደስ እያለኝ:- እኔ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነኝ ብዬ አዋጅን አውጃለሁ!!!!


ምዕራፍ 7

ተስፋው የጸና ነው

2ኛ ቆሮንቶስ 7: 1
1፤ እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፥ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።

የዚህ ተስፋ ቃል ካለን የሚለው የቱን ተስፋ እንደሆነ እንመልከት:- እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን፥ በእነርሱ እኖራለሁ፥ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፥ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ልጆች ትሆናላችሁ የሚለውን የተስፋ ቃል ነው የሚጠቅሰው ጳውሎስ። ስለዚህ ይህ የተስፋ ቃል ካለን ምን እናድርግ?

  1. በእግዚአብሔር ፍርሃት:- እግዚአብሔር ከመስማቱ የተነሳ ፀሎቱ ተሰማለት እንደሚል እኛም ጌታን እየፈራንና እያከበርን እንመላለስ::
  2. ቅድስናን ፍጹም እያደረግን:- በዚህ ዘመን ችላ የተባለ ነገር ቢኖር ቅድስና ነው:: እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እኛም ቅድስናን እንከታተል::
  3. ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ

ደህንነታችን ስራ እንደማይፈልግ መዳንም በስራ እንዳልሆነና እየሱስ ክርስቶስ ጽዋዉን ሁሉ ስለእኛ በመጨለጥ ሐጥያት የማያውቀው ንጹ ጌታ ሐጥያት ሆነና እኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ እንደተባልን የገባን ህዝቦች ነን:: እዚህ ጋር ጳውሎስ በምድር ስንመላለስ እርሱን እንምሰል ነው እያለን ያለው እንጂ ገና ለገና በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ለማድረግ የምንጥርበት አይደለም ነገር ግን እንደተወደዱ ልጆች ጌታን እየመሰልን እንመላለሳለን ይህንንም ዓለም አንመስልም እራሳችንን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ለጌታ እንለያለን:: ለዚህ ነው ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ የተባልነው:: ምንም አይቀርብንም ጌታን አክብረንና ፈርተን ሰውን ሁሉ ወደን ብንመላለስ አንከስርም እናተርፋለን እንጂ::


የጳውሎስ ደስታ

2ኛ ቆሮንቶስ 7: 2-16
2፤ በልባችሁ ስፍራ አስፉልን፤ ማንንም አልበደልንም፥ ማንንም አላጠፋንም፥ ማንንም አላታለልንም። 3፤ ለኵነኔ አልልም፤ በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን እንዳላችሁ አስቀድሜ ብዬአለሁና። ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፥ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ መጽናናት ሞልቶብኛል፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ከመጠን ይልቅ ይበዛል። ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም፤ በውጭ ጠብ ነበረ፥ በውስጥ ፍርሃት ነበረ። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ በመምጣቱም ብቻ አይደለም ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም ቅንዓታችሁን ሲናገረን በእናንተ ላይ በተጽናናበት መጽናናት ደግሞ ነው፤ ስለዚህም ከፊት ይልቅ ደስ አለን። በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ አያለሁና አሁን ለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤ በምንም ከእኛ የተነሣ እንዳትጎዱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና። 10 እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። 11 እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፥ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል። 12 እንግዲያስ የጻፍሁላችሁ ብሆን እንኳ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋታችሁ ከእናንተ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በዳዩ ወይም ስለ ተበዳዩ አልጻፍሁም። ስለዚህ ተጽናንተናል። 13 በመጽናናታችንም ስለ ቲቶ ደስታ አብልጦ ደስ አለን፥ መንፈሱ በሁላችሁ ዐርፎአልና፤ 14 ለእርሱ በምንም ስለ እናንተ የተመካሁ እንደ ሆነ አላፈርሁምና፥ ነገር ግን ሁሉን ለእናንተ በእውነት እንደ ተናገርን፥ እንደዚህ ደግሞ ትምክህታችን በቲቶ ፊት እውነት ሆነ። 15 ስለዚህም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደተቀበላችሁት፥ የሁላችሁን መታዘዝ እያሰበ ፍቅሩ በእናንተ ላይ እጅግ በዝቶአል። 16 በነገር ሁሉ ተማምኜባችኋለሁና ደስ ይለኛል።

ጳውሎስ እዚህ ክፍል ላይ እግዚአብሔር እንዴት እንዳፅናናው ከነበረበትም ሀዘን እንዴት እንዳወጣው ይናገራል:: የውጭው አካል እየደከመ ቢሄድም እንኳን የውስጡ ማንነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል:: ቲቶን ሲያገኝ የተፅናናውና የተደሰተበት ምክንያት የላከላቸውን መልእክት ተቀብለው የሚገባ ንስሀ ስላደረጉ ነበር እሱ ያሰበው ጎድቻቸው ይሆን ተረድተውኝ ይሆን እያለ ነበር ፍቅራቸውን ሲሰማና በመልእክቱም ትክክለኛውን አቅጣጫ ሲይዙ ተደስቷል:: የሚገርመው ታምኜባችሁ ነበር አላሳፈራችሁኝም ይላቸዋል ግን እኮ በዝች ቤተክርስቲያን ይሰማ የነበረው ሐጥያት የሚዘገንን ነበር:: ግን ሁሉም ነበሩ ያጠፉት? አልነበረም እንዲያውም ከመካከላቸው አስወግደው ቆፍጠን ያለ አቋም ያዙ ለፍሬ የሚሆን ንስሀን ገቡ:: የጌታን ቤት ስናገለግል ሰፊ ልብ ያስፈልጋል የመንጋው ባልቤት እግዚአብሔር እንደሆነም እንወቅ::

ምንም እንኳን መከራ ቢበዛበትም ለውጭው ማንነቱ ብዙም አይገደውም የጌታ ስራ ሲሰራ ተፅናንቶ ሁሉን በጌታው ይረሳል:: እኛም ዛሬ በጌታ ላይ እንመካ የሁሉ ነገራችን ምንጩ እርሱ ይሁን::

ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ምንን አመጣ?

  1. እንዴት ያለ ትጋት፥
  2. እንዴት ያለ መልስ፥
  3. እንዴት ያለ ቁጣ፥
  4. እንዴት ያለ ፍርሃት፥
  5. እንዴት ያለ ናፍቆት፥
  6. እንዴት ያለ ቅንዓት፥
  7. እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል።

የጠፉ ነበር የሚመስለው ነገር ግን ጌታ ተከላቸው ትጋትን ጨመረባቸው በስተመጨረሻም ንፁ መሆንን:: የጌታ ፀጋ ይብዛልን!


ምዕራፍ 8

በልግስና ማካፈል

2ኛ ቆሮንቶስ 8: 1-15

ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር፥ አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም። ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ እንደ ጀመረ እንዲሁ ደግሞ ይህን ቸር ሥራ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ሊፈጽም ለመንን። ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደ ተረፋችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ። ትእዛዝ እንደምሰጥ አልልም፥ ነገር ግን በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ፤ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ። 10 በዚህም ነገር ምክር እሰጣለሁ፤ ከአምና ጀምራችሁ ለማድረግ ብቻ ያይደለ ነገር ግን ለማሰብ ደግሞ አስቀድማችሁ የጀመራችሁት ይህ ይጠቅማችኋልና፤ 11 አሁንም ለማሰብ በጎ ፈቃድ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እንዳላችሁ መጠን መፈጸም ደግሞ ይሆን ዘንድ፥ ማድረጉን ደግሞ ፈጽሙ። 12 በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም። 13 ለሌሎች ዕረፍት ለእናንተም መከራ እንዲሆን አይደለም፥ ትክክል እንዲሆን ነው እንጂ፤ 14 የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። 15 ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም። 

ምዕራፉ ሲጀምር ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን ብሎ ነው:: ይህ ፀጋ እንዴት እንደረዳቸው ነው የምናየው:-

  1. በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል – ሊያጉረመርሙና ሊያማርሩ ሲገባ በተቃራኒው በደስታ ተሞልተው የራሳቸው ችግር ሳይታያቸው ስለወገኖች አስበው አካፈሉ
  2. እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና – ከሚችሉት በላይ ነው የሰጡት
  3. ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር – ስጡ ተብለው ሳይሆን ካልሰጠን ብለው ነው የሰጡት
  4. አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ – ከሙስጠት በፊት መሰጠት ይቀድማል

የእግዚአብሔር ጸጋ መከራንና ድህነትን አስረስቶ በደስታና በልግስና የሚሞላ ነው:: ልግስና የሚመነጨው ከሀብት አይደለም ለጌታ ስንሰጥ መስጠት ባህሪያችን ይሆናል እንጂ መስጠት የሀብት መኖርና አለመኖር ጉዳይ አይደለም:: ቃሉም እንደሚል ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም። 

ይህች ቤተክርስቲያን ለመርዳት ስታስብ ቆይታለች ግን አላደረገችውም ይህንንም እያበረታታቸው ነው ማሰብ ብቻ ማድረግንም አድርጉ ብሎ:: ልግስናን የተማርነው ከጌታ ነውና በልግስና እንታወቅ ማካፈልን አንርሳ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን::


በራስ ተነሳሽነት ማገልገል

2ኛ ቆሮንቶስ 8: 16-24
16፤ ነገር ግን በቲቶ ልብ ስለ እናንተ ያንን ትጋት የሰጠ አምላክ ይመስገን፤ 17 ምክራችንን ተቀብሎአልና፥ ትጋት ግን ስለ በዛበት ወዶ ወደ እናንተ ይወጣል።  18 ከእርሱም ጋር ስለ ወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም እንልካለን፤ 19 ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን የጌታን የራሱን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግለው በዚህ ቸር ሥራ ከእኛ ጋር እንዲጓደድ በአብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ተመረጠ።  20 ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤  21 በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና። 22 ብዙ ጊዜም በብዙ ነገር መርምረን ትጉ እንደ ሆነ ያገኘነውን፥ አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከፊት ይልቅ እጅግ ትጉ የሚሆነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር እንልካለን። 23 ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር ስለ እናንተ አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖርም የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞችና የክርስቶስ ክብር ናቸው።  24 እንግዲህ የፍቅራችሁንና ስለ እናንተ ያለውን የትምክህታችንን መግለጫ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ለእነርሱ ግለጡ።

በምናደርገው ሁሉ ትጋትን የሚሰጥ ጌታ ነው ልክ እዚህ ክፍል ላይ እንደምናየው ለቲቶ እንደተሰጠው ሁሉ ለእኛም ይሰጣል:: ቅዱሳንን ለመርዳት መነሳሳትና ማድረግ እንዳለብን ይህ ክፍል ያስተምረናል:: እዚህ ጋር እንደምናየው ቲቶ በራሱ ተነሳሽነት ነው ይህንን ስጦታ የመሰብሰቡን አገልግሎት ለማገልገል የፈለገው እንጂ ጳውሎስ ወይም ቤተክርስቲያን አላከችውም እናም ቤተክርስቲያን በሰዎች ውስጥ የሚመጣውን ምሪት ተቀብላ ልትረዳና ልታበረታታ ይገባል:: እኛ የእግዚአብሔር ቤት አገልጋዮችና የእግዚአብሔር ክብር ተብለን ተጠርተናል እዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ ስለ ወንድሞች እንዳለው::


ምዕራፍ 9

ቅዱሳንን ማገልገል

2ኛ ቆሮንቶስ 9: 1-5
1፤ ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤ በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም። አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል። ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤ ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን።  እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ። 

ቅዱሳንን ለማገልገል ልባችን ሊነሳሳና በጎ ፈቃድ ሊኖረን ይገባል:: በእርግጥ እዚህ ክፍል ላይ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ማለቱ መዋጯቸውን ነው ለእኛ ደግሞ ጌታን ተዘጋጅተን መጠበቅ አለብን:: ለቅዱሳንም ሆነ ለቤተክርስቲያን ስንሰጥ በስስት ወይም በግዴታ ሳይሆን በልግስና እና በፈቃደኝነት መሆን አለበት::


የምንዘራውን እናጭዳለን

2ኛ ቆሮንቶስ 9: 6-7
6፤ ይህንም እላለሁ፦ በጥቂት የሚዘራ፡ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ፡ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። 7፤ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።

መስጠት ከመዝራት ጋር ይመሳሰላል ዘርን ስንዘራ የሚበቅለው የዘራነው ብቻ ሳይሆን እሱ ሞቶ በብዙ እጥፍ ፍሬው ይበቅላል እንደዚሁም ደግሞ በደስታ ስንሰጥ በብዙ እጥፍ ጌታ ይመለሳል አለን:: ግን የሚመለሰውን ብቻ አስበን ከዘራን ከስረናል ከልባችን ተነክተን በደስታ መስጠት ነው ያለብን:: ለእግዚአብሔር ስንሰጥ

  1. በደስታ
  2. በልባችን እንዳሰብን
  3. በኀዘን ወይም
  4. በግድ ሳይሆን

ጌታ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እንደዚህ እንስጥ:: እርሱ መስጠትን አስተምሮናል የሰጠንም ህይወቱን እንደሆነ እናስብና ለመስጠት ካበቃን በደስታ እንስጥ::


እግዚአብሔር ለበጎ ስራ እንድትበዙ ጸጋን ሊያበዛላችሁ ይችላል

2ኛ ቆሮንቶስ 9: 8-9
8-9፤ በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል፡ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ፡ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።

ክፍሉ ከላይ ጀምሮ ስለመስጠት እያስተማረን መሆኑ ግልጽ ነው ይህም ደግሞ የምናካፍለው መቼም ሲኖረን ነውና:: ስለሆነም ክፍሉ በነገር ሁሉ የሚለው ውስጥ ዋናው ሀሳብ በሀብት ስለመባረክ ነው የሚናገረው:: ጳውሎስ እንደሚናገረው እግዚአብሔር እራሱ ነው ምስኪኖችን ያሰበው እርሱ ለሁሉ አምላክ ነውና:: እኛም ለምስኪን/ለተቸገረ እንሰጥ እና እናስብ ዘንድ ነው ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝተን፡ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድበዛ ነው ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል የሚለን ደግሞም አስተውሉ እዚህ ጋር:- ሊያበዛላችሁ ይችላል ነው እንጂ አብዝቶላችኃል አይልም ስለዚህ ምርጫ ነው ማለት ነው የምንፈልግ ከሆነ ነው እንጂ ለሁሉ በግድ አይሰጥም:: የሰዎች ጭንቀት ያስጨንቀናል? መርዳትስ እንፈልጋለን? መልሳችን አዎ ከሆነ ለእኔ ብቻ የማይል ልብ ካለን ብቃትን እንደዚሁም ጸጋን ይሰጠንና ሀብትን ማፍራት እንችላለን:: ይህንን ስል ብልጽግና ወንጌል የሚባለውን እየሰበኩ አይደለም የእርሱም ዝንባሌ የለኝም አስተምሮቱም ሁሉንም ለእኔ የሚል አቋም ያለው እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ: : በዚህ ውስጥ ለአምላካችን ክብር አይመጣም ቃሉም እንደሚል:- በዘዳግም 8: 17-18፤በልብህም፦ ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ፡ እንዳትል። 18፤ ነገር ግን ዛሬ እንደ ሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ።

ወገኖቼ ጉልበት የሚሰጠን ሀብት ለማከማቸትና ሌሎችንም ለመባረክ እራሱ ጌታ ነውና አንታበይ:: ስለዚህ ሀብት ቢኖረን ጌታ በዛ ቅር የሚሰኝ ወይም የምንበድል አይምሰለን የተሰጠን ግን ሌሎችንም እንድናስብበት መሆኑ ላይ ይሰመርበት:: ስንሰጥም ጌታን እያከበርን ምስጋናም ለስሙ ከምንባርካቸው ሰዎች እንደሚመጣ እንውቅና እንስጥ:: ጌታ ማስተዋልን ይስጠን! ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም ይላል ቃሉ። 


ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን

2ኛ ቆሮንቶስ 9: 10-15
10፤ ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 11 በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ። 12 የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤  13 በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥  14 ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል። 15 ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።

የሚገርመው እግዚአብሔር እራሱ ነው ሁሉንም የሚሰጠን ደግሞም ፍሬያችንንም የሚያሳድገው::

  1. ለዘሪ ዘርን
  2. ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም
  3. የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል
  4. ያበረክትላችሁማል፥
  5. የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል

ልግስናን ማድረግ እንዴት ለእግዚአብሔር ምስጋናን የሚያመጣ እንደሆነ እንወቅ እናም በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ:: በዚህ ሁሉ ውስጥ ሊመሰገን የሚገባው ጌታ ነው ምክንያቱም ሁሉን የሰጠን እርሱ ነውና:: ለመለገስ አንታክት:: ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።


ምዕራፍ 10

የጦር ዕቃችን ምሽግን ለመስበር በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው

2ኛ ቆሮንቶስ 10 :1-6
1፤ እኔም ራሴ ጳውሎስ፥ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ግን ብርቅ የምደፍራችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ፤ በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ፥ በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር እለምንችኋለሁ። በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል። 

ከፊተኛው ምዕራፍ ማለትም ስለመስጠት ከሚያወራበት ወደ አገልግሎቱን ወደማብራራት የዞረበት ነው ይህ ክፍል:: ለምን ያልን እንደሆነ አሁንም በእግዚአብሔር የተጠራ ሐዋርያ መሆኑን ለመግለጥና የሚልክላቸውንም መልእክት እንዲያከብሩና እንዲኖሩበትም ጭምር ነው:: ከእናንተ ጋር ሳለሁ ትሁት አሁን ስርቅ ደግሞ የምደፍራችሁ አይደለሁም የሰማሁትን ስህተት ግን እንድታርሙ ብዬ ነው የፃፍኩላችሁ ደግሞም በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ ነው የሚላቸው::

በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ ምክንያቱም:-

  1. ምንም እንኳ በሰው ልማድ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም :-
  2. የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና- የጦር ዕቃችን ብለን የምንላቸው በኤፌሶን 6: 10-18 ተዘርዝረዋል:: ቃሉን በመንፈሱ የሚያፀና እራሱ ጌታ ነው::
  3. ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው
  4. የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን – ዋናው ጦርነት እኮ በእግዚአብሔር ሀሳብ ላይ መነሳት ነው የሰይጣን ስራ ይህንኑ ነበር ያደረገው በኤደን ገነት እናም ያሳተው:: ስለዚህ ዛሬ ሀሳባችንን እናጢን ጠላት እንዳይፈትነን ሌሎችንም ከተሳሳተ አመለካከት እንመልስ::
  5. ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን – ጦርነቱ የሚካሄደው በአስተሳሰባችን ላይ ነው:: አስተሳሰባችንን ካገኘ ህይወታችንን እንደወደደ ሊቆጣጠር ስለሚችል ሁልጊዜ አእምሮአችንን ለጌታ እናስገዛ:: ለዚህም ነው ቃሉ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህንን አለም አትምሰሉ የተባልነው:: ቃሉ በአእምሯችን በሞላ ቁጥር የጠላትን ሽንገላና ውሸት እንደዚህ ተብሎ ተጽፏል በማለት እናፈርሳለን ልክ ጌታ በጠላት ሲፈተን እንደመለሰው ማለት ነው:: ለዚህ ነው ቃሉን ጊዜ ወስደን የምናጠናው::
  6. መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል – አመጻ በእኛ ዘንድ አይገኝም ማለት ነው በመታዘዝ ውስጥ ፍሬን መብላት አለ::

ጸጋን ጌታ የሰጠው ለማነጽ ነው

2ኛ ቆሮንቶስ 10: 7-18
7፤ በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቁጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛ ደግሞ እንዲሁ ነን። 8፤ ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም። በመልእክቶቼ የማስደነግጣችሁ አይምሰላችሁ። 10 መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። 11 እንዲሁ የሚል ይህን ይቁጠረው፤ በሩቅ ሳለን በመልእክታችን በኩል በቃል እንዳለን፥ በፊቱ ደግሞ ሳለን በሥራ እንዲሁ ነን። 12 ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 13 እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም። 14 ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤ 15 16 በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፥ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር እስክንሰብክ ሥራችንን እየጨመርን፥ በክፍላችን በእናንተ ዘንድ እንድንከብር ተስፋ እናደርጋለን፤ በሌላው ክፍል ስለ ተዘጋጀው ነገር አንመካም። 17 18 የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና።

በዚህ ክፍል ላይ ጳውሎስ የሚናገረው በተለይ እየተቃወሙት ላሉት ወገኖች ነው:: የሚለው ሁሉ እውነት ነው? እግዚአብሔር በእርሱ ይሰራል? እናም ብዙ ሌሎች ጥያቄዎችን እየመለሰ ነው:: በመጀመሪያ ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም ይላል ይህ ጸጋና ስልጣን የሰጠኝ እንዳፈርሳችሁ ሳይሆን ላንጻችሁ ነው ይህ ማለት ሐዋርያነቱ ጥያቄ ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው:: እግዚአብሔር የሚሰጠንን ሁሉ የሚሰጠን ሌላውን ለማነፅ ነው::

ከዚህም አልፈው ስለ ሰውነቱ አቋም እንኳን አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡ አልነበሩም ሰውነቱ ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። ግን ወደ ጌታ የመጡትና ከሞትም የተረፉት በሱ ንግግርና ምስክርነት እንደሆነ ዘንግተዋል:: ለዚህም ነው ከላይ በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሚለው መቼ በሰውነት አቋም ሆነና በውስጡ ሆኖ ከሚሰራው ከእግዚአብሔር እንጂ:: የስጋን ነገር እያዩ ዋናውን የጌታን ነገር እያባከኑት ይገኛሉ::

የእኔ ዓላማ ማገልገል ነእ እናንተን ከደረስን በኃላ ደግሞ ተሻግሮ ወደ ሌሎች መሄድ እንጂ የፉክክር ነገርና እራሴን የማሳየት ነገር የለኝም ነእ የሚለው:: እኛም ሁልጊዜ ይህንን እያሰብን ጌታን ለማክበርና ለማገልገል የተዘጋጀን እንሁን እንጂ ከፊታችን በሚገጥሙን ያልተለወጡ ወገኖች ምክንያት ስፍራን አንልቀቅ:: የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና። እራሳችንን ለማመስገን ከተነሳን ወንጌል አልገባንም ማለት ነው ምክንያቱም ለመዳናችን ምንም አስተዋጽዖ እንዳላደረግን በቀራንዮ እናስብ:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!


ምዕራፍ 11

ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁ

2ኛ ቆሮንቶስ 11: 1-2
1፤ በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ። 2፤ በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤

ይህ ሁሉ የጳውሎስ ጥረቱና ትጋቱ ንፅህት የሆነችን ቤተክርስቲያን ለማጨት ነው እንጂ ሌላ ግብ እንደሌለው እየነገራቸው ነው:: እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ የሌላትን ቤተክርስቲያን እንደሚል ቃሉ በሌላ ስፍራ ላይም እናያለን:: እግዚአብሔር ቀናተኛ ነው በእኛ ላይ ይቀናልና እራሳችንን ለእርሱ እንቀድስ:: የምናገለግለው አገልግሎት ሁሉ ለእርሱ እየቀናን አእምሮን ሁሉ እናስገዛለት:: በቅናት እናገልግል ያለ ነውርና እንከን የሌለው አገልግሎት እናገልግል::


ለክርስቶስ የሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ይኑረን

2ኛ ቆሮንቶስ 11:3-15
3፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።  ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደ ጎደልሁ ራሴን አልቆጥርም። በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል በነገር ሁሉ ተገልጠንላችኋል። ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይሆንን?  እናንተን ለማገልገል ደመወዝ እየተቀበልሁ ሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ። ከእናንተም ጋር ሳለሁ በጎደለኝ ጊዜ፥ በማንም አልከበድሁበትም፤ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ሰጥተዋልና፤ በነገርም ሁሉ እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅሁ እጠነቀቅማለሁ።  10 የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህት በእኔ ዘንድ በአካይያ አገር አይከለከልም።  11 ስለ ምን? ስለማልወዳችሁ ነውን? እግዚአብሔር ያውቃል። 12 ነገር ግን በዚያ በሚመኩበት እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ፥ ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ። 13 እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። 14 ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።  15 እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል። 

የጳውሎስ ፍርሀት ምን ነበር? አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ ይላቸዋል ይህንንም በመጀመሪያ ሔዋን ከሳተችበት ጋር ያመሳስለዋል:: ሰይጣን እኮ ሁሌ አንድ ሽንገላ ነው ያለው እሱም እኛን በቂ አድርጎ አሳይቶ እግዚአብሔር አያስፈልግም የሚል ስብከት:: ስለዚህ ሁልጊዜ አሳባችንን እንዳይበላሽና ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ::

በጳውሎስ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ሰይጣን ዛሬም ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና አገልጋዮቹም እንደዛው:: ስለዚህ እራሳችንን ከቃሉ ጋር እያዋሀድን ጌታን እያከበርን እንመላለስ በውስጣችንም ያሉትን የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችን ከመስማትና ከመከተል እንጠበቅ:: እነዚህ ሰዎች ህዝቡ በጳውሎስ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው እያደረጉ ነበር ይህንንም ከንግግሩ እናያለን እርሱ ግን አይደንቅም ይላል ይሄ ሁሉ ውርጅብኝ እየወረደበት እያለ ወደ ሩጫውና አገልግሎቱ ነው የሚያተኩረው እኛም ዛሬ ጠላት አንዳንዶችን እየነዳ እንደሚጠቀም አውቀን አይናችንን በጌታ ላይ በማድረግ መንገዳችንን እንቀጥል አገልግሎታችንንም እሱን የሚያስከብር እናድርግ::


የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት አሳብ ነው

2ኛ ቆሮንቶስ 11: 16-33
16፤ እንደ ገና እላለሁ፦ ለማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ ያለዚያ ግን እኔ ደግሞ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሞኝ እንኳ ሆኜ ተቀበሉኝ። 17 እንደዚህ ታምኜ ስመካ የምናገረው፥ በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም። 18 ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ። 19 ልባሞች ስለምትሆኑ በደስታ ሞኞችን ትታገሣላችሁና፤ 20 ማንም ባሪያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበላችሁ፥ ማንም ቢቀማችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁና። 21 ደካሞች መስለን እንደ ነበርን በውርደት እላለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍርበታለሁ። 22 ዕብራውያን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የእስራኤል ወገን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? 23 እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ።  24 አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። 25 ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። 26 ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤. 27 በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። 28 የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 29 የሚደክም ማን ነው፥ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፥ እኔም አልናደድምን? 30 ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ። 31 ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል። 32 በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥ 33 በቅጥሩም ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።

ጳውሎስ እዚህ ክፍል ላይ መከራውን ይዘረዝራል ግን ፈልጎ አይደለም ሌሎች አገልግሎቱን በማናናቅና ሐዋርያነቱን ላለመቀበል ስለተነሱበት ነው:: እስር ቤት እንኳን ሆኖ መከራውን አይናገርም ይህ ሰው:: እራሱን ከተቃዋሚዎች ጋር ሲያወዳዱድር ዕብራውያን ነኝ። የእስራኤል ወገን ነኝ። የአብርሃም ዘር ነኝ። የክርስቶስ አገልጋይ መሆኔን እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ ይላል:: ግን በዚህ ሁሉ ይመካል? በፍጹም በድካሜ ነው የምመካው ነው የሚለው ምክንያቱም በድካም ውስጥ የእግዚአብሔር ፀጋ ይገለጣልና::

ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው ይላል ዛሬ ብዙ አይነት ሰዎች በዙሪያችን ቢኖሩም እንኳን ትኩረታችን መሆን ያለበት ስለ አካሉ:ቤተክርስትያን ሊሆን ይገባል:: ንፁ የሆነ ደስ የሚል የተቀደሰ አገልግሎትን ከማገልገል ወደኃላ አንበል:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ምዕራፍ 12

ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማል

2ኛ ቆሮንቶስ 12: 1-10
1፤ ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ። እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ። ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱም። ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 10 ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። 

መንፈሳዊ ነገር የዓለምን እሴት ሁሉ ገልብጦ ነእ የሚያየው ለምሳሌ በዚህ ክፍል ላይ እንደናየው ጳውሎስ እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።  (በድካም መመካት የለም በዓለም መደበቅ እንጂ) ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። በችግር ደስ ይለኛል?! ስደክም ኃይለኛ ነኝ?! የሌለ አቋም አይመስልም ዋጋ የማያሰጥ? ግን በጌታ ነው ብርታታችን እርሱ እየረዳን የምንራመድ የእርሱ ሰራዊት ነን:: በድካማችን ውስጥ ብርታትን የሚጨምር ጌታ ስላለን ብንደክምም እናሳድዳለን ኃይል ከእርሱ ነውና ስሙ ይባረክ!

መቼም እዚህ ክፍል ላይ ብዙዎች ብዙ መላ ይሰጡበታል ስለጳውሎስ የስጋ መውጊያ:: አንድ ነገር ማለት የምንችለው ግን ህመም ቢሆን የመፈወስ ፀጋ አለ ደግሞም እግዚአብሔር የዚህ ሰልፍ አቀናባሪ አይደለም ምክንያቱም እዚህ ጋር እየወጋ ኃይል እሰጥሀለሁ አይልም ጌታም በክፉ አይፈትንም:: አንድ የሚያስማማን ነገር ቢኖር ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ ይደበደባል፤ ይታሰራል፤ ይዋረዳል ስለዚህም በሌላ ስፍራ እግዚአብሔርን እየመሰሉ የሚኖሩ ይሰደዳሉ ይላል:: ስደትን ጌታ አያቆምም ሊከተለኝ የሚፈልግ ቢኖር እራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ብሎናል ደግሞም በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ተብለናል:: እስጢፋኖስ ሲወገር ጌታ ሊቀበለው ተነሳ እንጂ አላስቆመውም ወንጌልን ስናደርስ ባለው ግፍያ ወይም የአፀፋ ምት ከጠላት ሰፈር ስደትን ያስነሳል:: ጳውሎስ መውጊያ የሚለውን አሳቡን የወሰደው ከብሉይ ኪዳን ላይ ነው:- መሳፍ 2:3፤ ኢያሱ 23: 13፤ እግዚአብሔር ሆን ብሎ ሳያጠፋ የተዋቸው አሕዛብ እንዴት እስራኤልን እንደሚያስቸግሩ ይናገራል ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ነገር ይቃወማሉ ስደትንም ያስከትላሉ ይህ የማሆነው ትእዛዙን ካልጠበቁና ከጌታ ጋር ካልተስማሙ ነው:: አሁንም ሰልፍ ሲነሳ ጌታ ፀጋን ሰቶ ያሻግራል እንጂ አያጠፋቸውም ቢያጠፋማ ኖሮ ጳውሎስ እራሱ ሲያሳድድ ሳለ በጠፋ ነበት የጌታ ትዕግስት ሁሉ እንዲድኑ ነው:: የጌታ ፀጋ ይብዛልን!


በደስታ ራስን ሰጥቶ ስለማገልገል

2ኛ ቆሮንቶስ 12: 11-21
11፤ በመመካቴ ሞኝ ሆኜአለሁ፤ እናንተ ግድ አላችሁኝ፤ እናንተ እኔን ልታመሰግኑ ይገባ ነበርና። እኔ ምንም ባልሆን እንኳ፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አልጎድልምና። 12 በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም በሁሉ ትዕግሥት ተደረገ። 13 እኔ ራሴ ካልከበድሁባችሁ ከዚህ በቀር፥ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን ያነሳችሁበት በምን እኮ ነው? ይህን በደሌን ይቅር በሉልኝ። 14 እነሆ፥ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ አልከብድባችሁምም፥ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና። 15 እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ። ከመጠን ይልቅ ብወዳችሁ በዚህ ልክ ፍቅራችሁ የሚያንስ ነውን? 16 ይሁን እንጂ እኔ አልከበድሁባችሁም፤ ነገር ግን ሸንጋይ ሆኜ በተንኰል ያዝኋችሁ። 17 ወደ እናንተ ከላክኋቸው በአንዱ ስንኳ አታለልኋችሁን? 18 ቲቶን መከርሁት ከእርሱም ጋር ወንድሙን ላክሁት፤ ቲቶስ አታለላችሁን? በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? በአንድ ፍለጋስ አልተመላለስንም? 19 ለእናንተ ስለ ራሳችን እንድንመልስ ሁልጊዜ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆች፥ እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን። 20 ስመጣ፥ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፤ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፤  21 እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ።

ጳውሎስ እዚህ ክፍል ላይ እናንተው ግድ አላችሁኝ ስለራሴ እንዳወራ እናንተ እኔን ልታመሰግኑ ይገባ ነበር ይላቸዋል ምክንያቱም፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አልጎድልምና። እናንተ የሰራሁት ካልታያችሁ እንግዲያውስ የተወሰነውን ልጥቀስ:-

  1. በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም ሁሉ ጌታ ሰርቷል
  2. አልከበድኩባችሁም ወንጌልን በነፃ ሰጠኃችሁ:- እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና
  3. ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥
  4. ራሴን እንኳ እከፍላለሁ ከመጠን ይልቅ እወዳችኃለሁ
  5. ወደ እናንተ የላኳቸውም አላተለሏችሁም
  6. ወዳጆች ሆይ፥ እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን

አላማዬ እናንተን እንደ ልጆች እያየሁና እናንተን ማነፅ እንጂ ከእናንተ የማገኘው ነገር አይደለም ትርፌ በፍቅር አገለገልኩ ያለኝንም ሁሉ ሰጠሁ አሁንም እሰጣለሁ ነገር ግን ስመጣ ይስተካከሉ ብዬ ያልኳቸው ነገሮች ካልተለወጡ ያጠፉትም ንስሀ ካልገቡ ልቤ እንዳያዝንና ጊዜያችንን እንዳናባክን እፈራለሁ ይላል:: የስጋ ፍሬን ማለትም (ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም) ሁሉ አስወግደው እንዲጠብቁት አለበለዚያ ግን እኔም በእናንተ እናንተም በእኔ የማትፈልጉት ልታገኙ ትችላላችሁ ብሎ እያስጠነቀቃቸው ነው::

ዛሬ ለእኛ መልእክቱ ምንድነው? በፍቅር ከሰዎች ሳንጠብቅ በታማኝነት ማገልገልንና መሰጠትን ይፈልጋል ጌታ ከእኛ::


ምዕራፍ 13

ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?

2ኛ ቆሮንቶስ 13: 1-14
1፤ ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ሁሉ ነገር በሁለትና በሦስት ምስክር አፍ ይጸናል። – 
ሁለተኛ በእናንተ ዘንድ በነበርሁ ጊዜ እንደ ተናገርሁ አሁንም ደግሞ በሩቅ ስሆን፥ ክርስቶስ በእኔ አድሮ እንዲናገር ማስረጃ ከፈለጋችሁ፥ እንደ ገና ብመጣ እንዳልራራላቸው አስቀድመው ኃጢአት ላደረጉት ለሌሎችም ሁሉ አስቀድሜ ብዬአለሁ፥ አስቀድሜም እላለሁ። ክርስቶስም ስለ እናንተ አይደክምም ነገር ግን በእናንተ ኃይለኛ ነው። በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንደክማለንና፥ ነገር ግን ስለ እናንተ በሆነ በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን። በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? እኛ ግን የማንበቃ እንዳይደለን ልታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ። ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ እኛ የምንበቃ ሆነን እንገለጥ ዘንድ አይደለም ነገር ግን እኛ ምንም እንደማንበቃ ብንሆን፥ እናንተ መልካሙን ታደርጉ ዘንድ ነው። ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና። እኛ ስንደክም እናንተም ኃይለኞች ስትሆኑ ደስ ብሎናልና፤ እናንተ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ ለዚህ ደግሞ እንጸልያለን። 10 ስለዚህ ጌታ ለማፍረስ ያይደለ ለማነጽ እንደ ሰጠኝ ሥልጣን፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በቁርጥ እንዳልሠራ በሩቅ ሆኜ ይህን እጽፋለሁ። 11 በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። 12 በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። 13 ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 14 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

በዚህ የመዝጊያ ክፍል ላይ ጳውሎስ ጌታ ለእኛ ምን እንደሆነልን ያስረዳል:-

  1. ክርስቶስም ስለ እናንተ አይደክምም ነገር ግን በእናንተ ኃይለኛ ነው
  2. በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን።
  3. ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?

ስለዚህ ጳውሎስ የሚሰጠው ምክር

  1. በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤
  2. ራሳችሁን ፈትኑ፤
  3. ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 
  4. ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን
  5. ፍጹማን ሁኑ፥
  6. ምክሬን ስሙ፥
  7. በአንድ ልብ ሁኑ፥
  8. በሰላም ኑሩ፥
  9. የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል

እራሳችንን ስናይ ድካም ይኖራል ነገር ግን እየሱስ ነው ብቃታችን ማንም በራሱ ብቁ አይደለም:: በእግዚአብሔር ኃይል የተጠበቅን እንደሆንም እያሰብን ጌታን እናክብር::


የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች

መግቢያ

የዚህ መጽሐፍ ዓላማ:

ይህ መጽሐፍ ጳውሎስ ከእስር ቤት ሆኖ ከጻፋቸው አራቱ መልእክቶች ውስጥ አንዱ ነው:: (ሌሎቹ መጽሐፍት ኤፌሶን፤ ቆላስያስ እና ፊልሞና ናቸው) ይህ ቤተክርስቲያን በአውሮፓ የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ነው:: በሐዋርያት 15:40-19:22 በጳውሎስ ሁለተኛው የወንጌል ጉዞ ላይ በህልሙ (በሐዋ 16:9) ወደ መቄዶንያ መተህ እርዳን የሚለውን ራዕይ ካየ በኃላ ነው የመጣው:: ፊልጲስዮስ በመቄዶንያ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ወይም በአሁንዋ ሰሜናዊ ግሪክ ውስጥ ያለች ግዛት ናት:: የመጽሐፉ ጸሐፊ እራሱ ጳውሎስ ነው::

በዚህ መልዕክቱ:-

  1. ስለሰጡት ስጦታ ሊያመሰግናቸው (ከነሱ ከተለየ በኃላ ስጦታ በተደጋጋሚ የላኩለት ከዚህ ቤተክርስቲያን ብቻ ነው (2ቆሮ 11:9 እና ፊል 4:10-20)
  2. ሊያበረታታቸው
  3. ሁልጊዜ በጌታ ደስ እንዲላቸው (ምንም እንኳን ከእስር ቤት የጻፈው መልዕክት ቢሆንም 16 ጊዜ ስለደስታ ጽፏል)

ምዕራፍ 1

ምዕራፍ 1 ንባብ
ሰላምታ

ወደ ፊልጵስዩስ 1:1-2
1፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤
2፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ጳውሎስ እራሱንና አብሮት የሚያገለግለውን ጢሞቴዎስን የኢየሱስ ባርያ ብሎ ይጀምራል ጽሁፉን:: እየሱስ ጌታዬ ነው በሰራሁት ስራ ሁሉ ጌታዬን ለማስደሰት ነው እያለ ይህንን እንደመረጃ እየሰጠ ያለውነው::

የተጻፈላቸውም የቤተክርስቲያንዋ አገልጋዮችና እንዲሁም ምዕመኑ በሱ አጠራር ቅዱሳን ብሎ ይጠራቸዋል ዛሬም ለኛ ቢጽፍ እንደዚህ አድርጎ ነው የሚጠርን ደግሞም ቅዱሳን ነን በጌታ ከመዋጀታችን የተነሳ::

የመግቢያው ሰላምታ እንደሰላምታ ብቻ አይደለም ባርኮትም አለበት ከአባታችን እንዲሁም ከእየሱስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን:: አሜን! ማንም በክርስቶስ ካልሆነ በስተቀር ይህንን ሰላም መለማመድ አይቻልምና እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይነት አይደለም አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ ነው:: ዛሬም ሰላሙና ጸጋው ይብዛልን ይትረፍረፍልን::


መልካሙን ስራ ክርስቶስ ይፈጽመዋል

ወደ ፊልጵስዩስ 1: 3-8
3-5፤ ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ።
6፤ በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤
7፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል።
8፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና።

የዝች ቤተክርስቲያን ሰዎች ከጳውሎስ ጋር ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ነው አብረውት የወንጌል ሰራተኛ የሆኑት እርሱም በጣም ነው የሚወዳቸውና ስለእነሱ ሲጸልይም በደስታ አምላኩን ያመሰግናል:: ጳውሎስ ወዳጅነቱን በግልጽ ነው የሚያሳየው ደብዳቤው የግል እንጂ ለቤተክርስቲያን የተጻፈ መልእክት እንኳን አይመስልም:: ባደረጉለት ስጦታ ምክንያት ህይወቱን ይደግፉ ነበርና መቼም ድንኳን በመስፋት ብዙውን ጊዜ ከሚያውል ለማገልገል እንዲችል አስችለውታል ምክንያቱም አብራችሁኝ አገለገላችሁ ብሎ እውቅና እየሰጣቸው ነው:: ጸጋ የተለያየ ነውና በተሰጠን ጸጋ እንገለጥ ያን ጊዜ ወንጌል በኃይል ይሄዳል የግድ ሁሉም ሰው መስበክ የለበትም ልግስናም ጸጋ ነውና ለመንግስቱ ያስፈልጋል:: የተሰጠን ጸጋ ምንድነው? እናገልግልበት::

እግዚአብሔር ታማኝ ነውና በእናንተ የተጀመረው ስራ ይቀጥላል፥ ይሰፋል ምክንያቱም እሱ የታመነ ጌታ ስለሆነ የስራውም ባለቤት እርሱ ስለሆነ ይህ የማይቀር ሀቅ ነው:: በእርግጥ የእኛ መተባበር ያስፈልጋል የእግዚአብሔር ግን መምራትና መርዳት አስፈላጊ ነው እርሱንም ያደርገዋል እያለን ነው ለእኛም::

በእስራቱ ሳያፍሩና ሳይረሱት ስለእርሱ በማሰብ አብረውት ቆመዋል ከዚህ ሁሉ በላይ ግን እንደዚህ ያቆመው ጸጋ እንደሆነ ጳውሎስ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው ለእናንተም ይህ ጸጋ ያቆማችኃል እያላቸው ነው:: ምንም አይነት ነገር ቢመጣ እርሱ በጸጋው ያቆማችኃል እኔ ምስክር ነኝ እያለ ነው:: ዛሬም በምናልፍበት ሁሉ በጸጋው ሊረዳን የታመነ ነው የእኛ ጌታ ከጳውሎስ ጋር እንደነበረ ዛሬም ከእኛ ጋር በስራ ላይ ነው::

ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች ከመውደዱ የተነሳ ሁልጊዜ መቼ ነው የማያቸው በሚል ጉጉት ውስጥ ነበር ግን የወንጌል ስራ ስለበለጠበት ሳያያቸው ቆየ:: ሊያያቸው እንዴት እንደሚናፍቅ ግን እግዚአብሔር ነው ምስክሬ ይላቸዋል እንዲህ ያለ መነፋፈቅንና መተሳሰብን ጌታ በዘመናችን ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥም ያድርግ ይህ ፍቅር ይፍሰስልን:: አሜን!


ፍቅራችን በእውቀትና በማተዋል ይብዛ

ወደ ፊልጵስዩስ 1: 9-11
9-11፤ ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።

1. ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሆን ዘንድ ከክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶብን መገኘት አለብን:: እናስተውል ከእኛ አይደለም የጽድቁ ፍሬ የሚመጣው ከጠራን ከራሱ ነው:: ነገር ግን ገና የራሳችንን ጽድቅ ለማቆም የምንነሳ ከሆነ አስቸጋሪ ነው ወደ እረፍቱ መግባታችን ታድያ ምኑ ላይ ነው? ውላችን እኛ ልንሞት እርሱ በእኛ ሊኖርም አይደል? እንደዛ ካላሰብን የምንፈልገውን መለወጥ አናየውም ጥረት ግረት ሆኖ ይቀራል:: ክርስትና ግን እረፍት ነው ደግሞም ክብርና ምስጋናን ከእኛ ህይወት የተነሳ የምናመጣ ነን:: ደስ አይልም? በተቃራኒውምእንዳለ ልብ እንበል::

2. ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ እኛ የመድኃኒታችንን ከሰማይ መገለጥ የምንጠባበቅ ነን:: ስንጠባበቅ ግን ኑሮ እናቆማለን ማለት አይደለም ነገርን ፈትነን የሚሻለውን ማለትም:- እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ይለናል ቃሉ:: ይህንንም የምናደርገው ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅተን ቅኖችና እለነውር ሆነን እንጠብቅ::

3. ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። ፍቅር በእውቀት እየጨመረ የሚመጣ ነው:: ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ ጌታ ይፈልጋል:: ይህ እንዲበዛ ነው ጳውሎስ እጸልያለሁኝ ያለን እኛም እንጸልይ ይህ ከመታወቅ የሚያልፍ ፍቅር በህይወታችን ውስጥ ይገኝ ዘንድና ማስተዋልም እንዲሆንልን::


በሁሉ ምክንያት ክርስቶስ ይሰበክ

ወደ ፊልጵስዩስ 1:12-20


12፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።
13፤ ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥
14፤ በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ።
15፤ አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤
16፤ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥
17፤ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ:: 18፤ ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።
19፤ ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
20፤ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል።

ወንድማችን ጳውሎስ ወንጌልን ሲሰብክ የደረሰበት ብዙ ድብደባ ብሎም እስራት ነው:: መታሰሩም ወንጀል ሰርቶ ሳይሆን በእምነቱ እንደሆነ ታውቋል:: ይህም ወሬ አሳሪዎቹም ሳይቀሩ አውቀዋል ምናልባትም ወንጌልን ሰምተዋል:: በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በእኔ ላይ የመጣውን መከራ እዩ ሳይሆን እያለ ያለው አይዟችሁ መታሰሬ አያሳዝናችሁ በርቱ ወንጌልን ስበኩ እያለ ነው:: እንዲያውም አንዳንድ ወንድሞች እስራትን ንቀው ከፊት ይልቅ ወንጌልን እየሰሩ ነው ይላል ምክንያቱም እርሱ ስለ እስራቱ ሳይሆን የሚያወራው ስለወንጌል መሰበክ ስለሆነ በወገኖች ላይ ያሳደረው ነገር ወንጌል መሮጥ አለበት የሚልና ብያዝ እንኳን ግፋ ቢል መታሰር ነው እንደእርሱ ሳልያዝ ልስራ የሚል መንፈስ ነው:: ሌሎች ደግሞ በማሾፍ የሞተ ተነሳ ይላል ብለው አንዳንዶችም መከራውን ሊያበዙና ወደፊት ስለዚህ ጌታ ሁለተኛ እንዳይናገር ተስፋ ለማስቆረጥ ስለ እየሱስ ይናገራሉ:: በዚህ ሁሉ ግን ይላል እየሱስ ብቻ ይሰበክ በዚህ ደስ ብሎኛል ይላል::

በህይወት ይሁን በሞት በስጋዬ ጌታ ይክበር ባይ ነው ምክንያቱም አላፍርም በጸሎታችሁና በመንፈሱ ተረድቼ እቆማለሁ ይህ ተስፋዬ ናፍቆቴም ነውና ብሎ ስለ ዘላለም ህይወቱ እንጂ ከስር ስለመፈታቱ አያወራም ሁልጊዜ ወደጌታ ያሳያል ያበረታል:: እኛም ዛሬ አይናችንን በርሱ ላይ አድርገን ወንጌልን እንስበክና እንኑረው::


ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ነው

ወደ ፊልጵስዩስ 1:21
21፤ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።

ዘራፍ!! እያለ ድፍረት ለማግኘት እራሱን እያነቃቃ አይደለም ጳውሎስ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነው ሲለን ውስጡ የሞላውን እውነት ነው የሚነግረን ያለው:: ያስጨነቀው መሞቱ አይደለም ለኔ መሞት ጥቅም ነው ነው ያለው ብኖር እጠቅማችኃለሁ ስለዚህ ስጋዬ በግርፋትና በመከራ ይለፍ እንጂ ነፍሴን መንካት ማንም አይችልም በሚል ልበ ሙሉነት ነው እየተናገረ ያለው:: ለሌላው አካል ወይም እስር ቤት ላስገቡት ቦታም አልሰጣቸው ከእስርም ያስመልጣል ከሞትም ያስነሳል የኔ ጌታ ሁሉ በእጁ ነው እያለ ነው:: ከዚህ በፊት ደብድበው ሞቷል ብለው ጥለውት አልሄዱም? እርሱ ግን ተነስቶ መስበኩን ቀጠለ አይደል? ጌታውን ጠንቅቆ ያውቃል እኛም እንወቀው:: የሚያኖረን ከክርስቶስ የተቀበልነው ጸጋ እንጂ የሰው ቸርነት ወይም የስጋችን ብርታት አይደለም::

ህይወታችን እራሱ ክርስቶስ ነው በእርሱ ውስጥ ነን ካልን እዚህ እንሁን ወይም በሰማይ ምንድነው ለውጡ? በመጀመርያ ግን በእርሱ ውስጥ ነኝ የሚለው ሀሳብ በውስጣችን ሊዘልቅና አይምሯችን በዚህ እውነት ሊሞላ ይገባዋል:: ሞት እኮ መውጊያውን ተነጥቋል ዛሬ መጣሁ እያለ አያስፈራራንም ከሞትም ጋር ህብረትም ወዳጅነትም የለንም:: ለእኛ ሞት ማለት በር ብቻ ነው ወደ ዘለዓለሙ መዝለቂያ እንዲያውም ሊያስፈራን ሳይሆን ስራችንን ስንጨርስ በል አሰናብተኝና ወደቤት ልምጣ የምንልበት ማለፊያ በር ብቻ ነው:: የመጨረሻ የተባለውን ትንፋሽ በዚች ምድር ላይ ስንወስድ ወድያው የመጀመሪያውን በሰማይ እንጀምርና ጌታንም በክብሩ እናየዋለን:: ግን ዛሬ ነፍስና ስጋችንን የሚያላቅቀው ነገር ሞት አይደል?! ዛሬም ጠላት መጣሁብህ እያለ ባዶ እጁን የቀረበትን የሽንፈት መሳሪያውን እንደድል ሲጠቀምበት ዝም አልነው:: ይብቃ እኛ የክርስቶስ ነን!! ማንም ከቶ አያስፈራራንም ብንኖር ለጌታ ብንሞት ለጌታ! ሃሌሉያ!!!


ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ

ወደ ፊልጵስዩስ 1: 22-30

22 ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። 23 በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ 24 ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። 25 -26 ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ። 27 ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። 28 በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ 29 ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤
30 በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።

አሁን እንደው ጳውሎስ ልኑር ወይስ ልሙት የቱን ልምረጥ እያለ ሲቸገር ይገርማል:: ማንም በዚህ ጥያቄ ሲፈተን አይቼ አላውቅም ልኑር ህይወቴን አቅና የሚል እንጂ እኔንም ጨምሮ ሊያውም ከአንዱ የድብደባ መድረክ ወደሌላው የሚሄደው ጳውሎስ የቱን መምረጥ እንዳለበት ሲቸገር ይደንቃል:: ልክ እንደው ሁለት የሚያጉዋጉዋ ነገር በፊቱ ያለ ይመስላል:: አንድም እየተደበደቡ መኖር አልያም መሞት እና ወደ ጌታ መሄድ:: እሱ እንዳስቀመጠው ግን ለኔ መሞቱና ወደ እረፍት መግባቱ ይሻላል ደግሞም በጣም እናፍቃለሁና ከጌታዬ ጋር መኖርን ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ብቆይ ደግሞ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ ብሎ መቆየቱን መርጧል:: ከራሱ ይልቅ ለሌላ ለመኖር ወሰነ እኛስ ምን እንወስን ይሆን? እራሳችንን ስናይ ግን አንዳች ጎደለን ብለን ወይም ይህ ነገር አልተሳካም ብለን ወደ ጌታ በሄድን ወይም እርሱ በመጣ እምንል ነን:: ምን አይነት የወንጌል መልእክት እንደያዝን አይገባኝም ጌታ ይርዳን ለክርስቶስ አካል እንኑር ብለን ለመኖር ከየት እንደምንጀምርም ግራ ይገባል:: ወንጌል ግን ለጌታ መኖር ነው::

ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ ብሎ ይላል እንዴት ነው እንደሚገባ የምንኖረው?

1. በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ – የያዝነው የወንጌል ስራ እንደ አካል በህብረት የሚሰራ ነውና በመዋደድና በመደጋገፍ ልንሰራ ይገባል:: ዮሐንስ 13:35. እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።

2. በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ – 1ኛ ቆሮንቶስ 12
13፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። እናስታውስ ያው አንዱ መንፈስ በሁላችን አለልዩነት አለ::

እንደዚህ ስንመላለስ የጠላት ፉከራና ቀረርቶ አያስፈራንም ምክንያቱም የመዳን ምልክት እንጂ ለእኛ የጥፋት አይደለም:: ክርስቶስን ስንከተል ከወንጌል የተንሳ መከራ ይመጣል ግን አያጠፋንም እናሸንፋለን::


ምዕራፍ 2

ምዕራፍ 1 ንባብ

በክርስቶስ ያለ ምክርን እንፈጽም

ወደ ፊሊጲስዮስ 2: 1-4

1 በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤
2 በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤
3 ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤
4 እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።

I. በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ ምን አይነት ምክር ነው? ጳውሎስ ደስታዬን ፈጽሙልኝ ያሰኘው-

  1. የፍቅር መጽናናት
  2. የመንፈስ ኅብረት
  3. ምሕረትና ርኅራኄ

እነዚህ ፍቅር፤ ኅብረት፤ ምህረትና ርህራሄ በክርስቶስ ውስጥ ያየናቸው ባህሪያት ናቸው ስለዚህ እነዚህ ባህርያት በመንፈስ ቅዱስ በኩል ዛሬ በእኛ ይገለጣሉ:: በፍቅር ተመላለሰ ደግሞም ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም የተባለለትን ትልቅ መስዋዕትነት ከፈል:: ከአባቱም ጋር ህብረት ነበረው ለሊቱን ሁሉ ሲጸልይ ያድራል:: ምህረትና ርኅራሄውም በደንብ ታይቷል:- ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? እኔም አልፈርድብሽም ሂጂ ሲል በሌላ ቦታ ደግሞ እረኛ እንደሌላቸው ተበትነው ሲያይ አዝኖ:: ለታመሙት ራርቶ የሚፈውስ ከሚያለቅሱት ጋር የሚያለቅስ ሩህሩህ ጌታ:: ብዙ ማለት ይቻላል ስለ እየሱስ ይህ በርሱ የተጀመረው ህይወት አሁንም በእኛ ይቀጥል::

II. በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ ምን ብናደርግ ነው በአንድ ሀሳብ ልንስማማ የምችለው?

  1. አንድ ፍቅር – ክርስቶስን ብቻ ማየት እንዴት እንደወደደን
  2. አንድም ልብ – ክርስቶስ እንዲከብር ብቻ ማሰብ
  3. አንድም አሳብ – እርሱን በሀሳባችን ሁሉ መቀደስ ያኔ እርሱን ብቻ ለማክበር እንስማማለን
  4. በትሕትና – ሰውን ሁሉ በክርስቶስ ውስጥ ማወቅና ከኔ ይሻላል ማለት
  5. ለሌላው በማሰብ – በሌላው ውስጥም ጌታ ይሰራል ብሎ መቀበልና መርዳት ወደ ተጠሩበት ነገር እንዲደርሱ

በዚህ ሁሉ ውስጥ ዝቅ ማለትና በትህትና መመላለስ አለብን እኔ አውቃለሁን ትተን ከኔ ይሻላል ወገኔ እንበል:: ያለ ሌላው አገልግሎት እኔ የምሮጠው ሙሉ እንድማይሆን ማወቅ:: እግዚአብሔር ለትሁታን ጸጋን ይሰጣልና::


የክርስቶስ አሳብ በእኛ ይገኝ

ወደ ፊልጵስዩስ 2:5-6
5፤ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። 6፤ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥

በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን:: ምን አሳብ በእኛ ዘንድ ይሁን? የቱ አሳብ ይግዛን? እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ የሚለው አሳብ::

ምን ማለት ፈልጎ ነው ለመሆኑ እንደ መቀማት አልቆጠረውም ሲለን:: እስኪ ትቶ የመጣውን ምንም ያልመሰለውን ክብሩን እንይ::

  • የሰማይ ሰራዊት ሳያቋርጡ ቅዱስ ቅዱስ የሚሉት፥
  • ከፍ ባለና በረጅም ዙፋኑ ላይ የተቀመጠ፥
  • በደመናት ላይ የሚራመድ፤
  • ሰማይና ምድርን በውስጧም ያሉትን ሁሉ በቃሉ ትእዛዝ የፈጠረ፥
  • ሰማይን በስንዝር የሚለካ፥
  • ውሆችን በእጁ የሰፈረ፥
  • የምድርንም አፈር በመስፈርያ ሰብስቦ የያዘ፥
  • አስተማሪና አማካሪ የሌለው፥
  • ምድርን በቃሉ ያጸና፥
  • በሚደነቅ ብርሃን ውስጥ የሚኖር፥
  • የአማልክት አምላክ፥
  • የጌቶችም ጌታ፥
  • ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥
  • በፍርድ የማያደላ፥
  • መማለጃም የማይቀበል፥
  • አይደክምም አይታክትም፥
  • ማስተዋሉም አይመረመርም፥
  • ሰውን ከአፈር በእጁ የሰራ የህወትንም እስትንፋስ የጨመረበት፥
  • ለዘመኑ ቁጥር የሌለው፥
  • እንደ እርሱ አይነት አምላክ የለም:: ሃሌሉያ! አሜን! ብዙ ማለት ይቻላል ስለጌታችን ስሙ ይባረክና ይህን ሁሉ ጥሎ እኔን ብሎ መጣ?!

ታድያ እኔ ምኔን ልጣል? የቱን የሚያጏጏውን ክብሬን፤ ውበቴን፤ ሀብቴን? አረ ምኔን ምን አለኝ ይህን ትቼ ነው የመጣሁት የምለው?! እራቁቴንም አይደል የመጣሁት? ስሄድስ ይህ የእኔ ነው ይዤው ልሂድ የማልል ደካማ ፍጡር:: ምኔ ነው ያስመካኝ? የቱ ነው እንደው ዝቅ እንዳልል ሁሉን ትቼ እንዳልከተለው የሆንኩበት?! ምንም የሌለኝ ደካማ መሆኔን ብቻ ነው ያየሁት እንዲያውም በተቃራኒው ትምክህቴን አስትቶ ሊያሸማቅቀኝ የሚገባው ምንም ልሰጠው አለመቻሌ ነው መሆን ያለበት:: የመሰጠቴን ደረጃ ከፍ አድርጎ እኔ ለአንተ በፈቃዴ የተገዛሁ ባርያ ነኝ ልለው ሲገባ እርሱ ግን ከፍቅሩ የተነሳ ደስ የሚለው የምትሰጭኝ የለም እንዲያውም ከነድካምሽ ነይ ብሎ እጁን ዘርግቶ አንቺ ልጄ ነሽ አለኝ!!!!! እሱ ከሆነልኝ ነገር ጋር ሳስተያየው እኔ የደመደምኩት:- ልከተለው፤ ልገዛለት፤ ባለኝ ሙሉ ኃይል ሁሉ ላከብረው፤ በትህትናም ልመላለስ ይገባል ብዬ እላለሁ::

እዘምራለሁ ለክብሩ ሌላማ ምን አለ?

ምን ይከፈልሀል ጌታ ሆይ ምን ይከፈልሀል

ብቻ ተመስገን እንልሀለን ምስጋና ይገባሀል!!!


ምን አለኝና ምኔን ልክፈልህ
እንደው ዝቅ ብዬ ልዘምርልህ
በህያዋን ጉባኤ መካከል
እንዳንተ ያለ የለም ከፍ በል!!!

ሃሌሉያ! አሜን! አሜን! አሜን! አሜን!


እየሱስ ራሱን ባዶ አድርጎ፥ አዋርዶ የባርያን መልክ ያዘ


ወደ ፊልጵስዩስ 2:7-8
7፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ 8፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።

ለመስቀል ሞት ታዘዘ ብለን እንደተለመደ አባባል እንላለን ምናልባትም ከልጅነት ጀምሮ እየሰማን ስላደግንም ሊሆንም ይችላል ብቻ ብዙ አይደንቀንም:: ከሲኦል አምልጠናል የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል ብለን እመስቀሉ ውጤቶች ላይ ነው የምናተኩረው:: ከላይ (በቁጥር 5 እና 6) እርሱ ትቶ የመጣውን ለማየት ሞክረናል:: ፈጣሪ ሆኖ ሳለ በአንድ ስፍራ በአንድ አካል ውስጥ ተገለጠ:: ይህንንም ሁሉ ያደረገው ስለወደደን ነው:: የመስቀል ሞት ግን ምን ይመስላል? እንዴትስ እራሱን ባዶ አደረገ? ምን ማለት ነው የባርያንስ መልክ መያዝ ማለት?

አማካሪ የማያስፈልገው ጠቢብ:- በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።

ምድርን በቃሉ ብቻ የፈጠረው ጌታ:- ለቤተሰቦቹ መታዘዝና መስራት ነበረበት፥

ምንም ሐጥያት የሌለው ቅዱሱ ሊቀድሰን የመጣው:- በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ::

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከአፈር በእጁ እንዳልተሰራው:- ሰው ግን ጌታውን ሰቀለ (በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?)

ሰማይ ዙፋኔ ምድር የእግሬ መርገጫ ያለ ጌታ:- በምድር ሲኖር ቤት አልነበረውም

ያለማቋረጥ የሰማይ ሰራዊት የሚያመልኩት ንጉስ:- እግር ሊያጥብ ዝቅ አለ

የሲናን ተራራ በመገኘቱ ያጨሰው፤ ማንም ቢቀርብ ተራራውን ሰውም ይሁን እንሰሳ ይሞት እንዳልነበረ:- ተፉበት፤ ማነው የመታህ? እያሉ አሾፉበት

እልፍ አእላፍ መላእክት የሚያገለግሉት ጌታ:- የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም አለ

በአንድ ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ:: ይህ እንዲደገም ማድረግ የሚችለው ጌታ:- ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።

ይሄ ነው እንግዲህ በጥቂቱ የሆነው ታድያ ከዚህ በላይ ባዶ መሆን ምንድነው? የባርያን መልክ መያዝ ከዚስ በላይ አለ? እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። የሰውን ልጅ ነፃ በማውጣት ፍሬውን ዛሬ በእያንዳንዳችን ላይ ለማየት ነው ይህን ሁሉ የታገሰው:: ከኔ ተማሩ ሲለን በህይወቱ ኖሮ አሳይቶናል ጌታችን ስለዚህ መታዘዝንና ትህትናን አስተማረን ይህ በእርሱ ውስጥ ያለው አስተሳሰብ በእኔም ውስጥ ይገዛል:: ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ ብሎናል:: በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር ይላል ቃሉ:: እርሱ ግን ፈጽሞ አባቱን ታዞ ስራችንን ሰርቶ ወደ አባቱ ሄደ:: እንዴት እንመላለስ ታድያ?

የተከፈለብኝ ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው!! የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የወደደኝና እራሱን ባዶ አድርጎ የባርያንም መልክ ይዞ መቶ ወደራሱ ሊመልሰኝ የተንገላታልኝ የጌታዬ ነኝ:: አሜን!!


ከስም ሁሉ በላይ ስምን ተቀበለ

ወደ ፊልጵስዩስ 2: 9-11
9፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፥ 10፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ 11፤ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።

በምን ምክንያት ነው አየሱስ ያለ ልክ ከፍ ከፍ ያለው? እራሱን ባዶ አድርጎና አዋርዶ እንዲሁም የባርያን መልክ ይዞ መጥቶ ለሞት ያውም ለመስቀል ሞት ስለታዘዘ ነው:: ከፍ ከፍ ብሎ ብቻ አልቀረም የከፍታው ልክ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስምን አሰጠው:: ይህ ስም አለ እግዚአብሔር አብ በሰማይ፤ በምድርና ከምድር በታች ያሉ ስም ያለው ሁሉ ለዚህ ስም ይንበርከኩ ብሎ አዋጅን አወጀ:: ይህንን አዋጅ የማይታዘዝ ማን ይሆን? ሁሉ ፍጥረት አይደል? ስለዚህ ሁሉ ይገዛል ለዚህ ህግ:: ስም እስካለው ድረስ ሁሉም ለዚህ ለእየሱስ ስም መንበርከኩ ግድ ነው:: ዛሬ የለም ብለው የሚሉት ሁሉ የማያምኑበትም ወደዱም ጠሉም ይንበረከካሉ ለዚህ የተቀባ ስም::

በዚህ ስም ምን የማድረግ ስልጣን አለው?

  1. እንድንበት ዘንድ:- (ሐዋ 4:12፤ መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።)
  2. ምልክትና ድንቅ ያደርጋል:- (የሐዋ 3:6: ጴጥሮስ ግን፦ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ፡ አለው።)
  3. አጋንንት ይወጣሉ (ማር 16: 17)
  4. በስሙ ስንለምን ይደረጋል (ዮሐ 14:13-14)

በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነው

ወደ ፊልጵስዩስ 2:12-13
12፤ ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ 13፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።

በእናንተ ዘንድ ብሆንም ባልሆንም ታማኝ ሁኑ ይላቸዋል እኛም ዛሬ ሰው አየን አላየን ብለን አንቀያየር ሁልጊዜ ጌታ ያየናልና በታማኝነት እንመላለስ:: መዳን አንድ ጊዜ ተሰቶናል ዕብ ምዕራፍ 4 ላይ እንዳለው የምንኖረው ለመግባት አይደለም ምንም ጥረት ማድረግም አያስፈልገንም ያመንን ጊዜ ያን ጊዜ መዳንን በማግኘት ወደ እረፍቱ ገብተናል ደግሞም አገራችን በሰማይ ነው እንላለን:: ግን መስራት እንዳለብን ደግሞ መዳንን ፈጽሙ ይለናል:: ለምን? ብለን ብንል የኛ አገልግሎት የጌታ አምባሳደር ሆነን የመንግስታችንን አቋም በማንጸባረቅ መኖር ነው ሁሉ ትዕዛዝ ከመምሪያው ይተላለፋል የሚያስፈልገንንም ሁሉ እራሱ መንግስታችን ያሟላል::

እንዴት የራሳችንን መዳን እንፈጽም ታድያ? በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ምክንያቱም ለመዳናችን ያደረግነው አስተዋጾ የለምና ሁሉን ጌታችን እየሱስ በመስቀል ላይ ተንገላቶ ተፈጸመ ብሎ ፈጽሞታልና ልንታበይ ወይም ልንመካ በራሳችን አያስፈልግም::

ከላይ እንዳየነው ደህነታችን ከኛ ስራን አይጠይቅም እየሱስ እንዳደረገው አይተናል:: መኖሩም ቢሆን ስራ አይፈልግም እንዴት? የተባልኩኝ እንደሆነ:- ምክንያቱም ስለ በጎ ፈቃዱ

1, መፈለግንም (ሲለን):- ከላይ ፊሊ 2:1 ላይ እንደተብራራው (የፍቅር መጽናናት፥ የመንፈስ ኅብረት፥ ምሕረትና ርኅራኄ) በክርስቶስ ውስጥ ያለው አሳብ በእኛም እንዲሆን ነው::

2. ማድረግንም (ሲለን):- አንድ ፍቅር – አንድም ልብ – አንድም አሳብ -በትሕትና – ለሌላው በማሰብ በመደረግ ይገለጣል ማለት ነው:: ምክንያቱም:-

በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና!!!!

እስኪ ከእኛ ይሁን ከሰው ልጆች እየሱስን አይዞህ እንኳን ያለው አለ? በመስቀል ላይ ሲንገላታ?! ማንም የለም እንዲያው የተሰጠንን ደህንነት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንፈጽም::

ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።


ጌታን በህወታችን እናሳይ

ወደ ፊልጵስዩስ 2 :14-18
14-15፤ በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ 16፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። 17፤ ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ 18፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ::

በዚህ በጨለማ በሆነ በመጥፎና ጠማማ ትውልድ መካከል እንዴት እንመላለስ? እነሱን በመምሰል ወይስ ጌታን በማሳየት? እስኪ እንየው
1. ያለ ነቀፋ – እንዳንነቀፍ ፈጽመን የእግዚአብሔርን ቃል እንኑረው እርሱ አይደለም ለዝች ምድር በቅድስናውም ፊት ያለ ነቀፋ አቅርቦናል እርሱን እንግለጥ

2. የዋሆችም – የዋህነትን የምንማረው ከራሱ ከጌታችን ነው እርሱ እንዳለን እኔ የዋህ ነኝ ከእኔ ተማሩ ብሎናል:: በሌላ ስፍራም ያዕ 3: 13፤ ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። እንደእርግብ የዋህ እንሁን ተልኳችንም ነው::

3. ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ – ነውራችንን ሁሉ አስወግዶ መገለጫችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆኗል ብቃትን ሰቶናል የእርሱ ማንነት በእኛ ውስጥ ነግሷል

4. ሳታንጐራጉሩ – ማንጎራጎር እስራኤልን በምድረበዳ አስቀርቷል እንጠንቀቅ እኛ መሆን ያለብን በሁሉ አመስጋኞች መሆን ነው ቃሉ እንደሚለን::

5. ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ – ይህ አመጸኛ ትውልድ ክፉ ማድረጉ፤ ማስጨነቁ፤ ፍርድ ማጣመሙ የማይቀር ነው እኛ ግን ይህ ሁሉ ቢደርስብንም እንኳ ለክፉ ክፉ በማድረግ ሳይሆን በፍቅር ማሸነፍ ያለብን የፍቅር ልጆች ነን

6. እንደ ብርሀን መታየት – በምትጠፋው ዓለም ላይ እኛ ብርሀንና ጨው እንደሆንን አውቀን ለሌላው እናብራ እንጂ ከጨለማው ጋር አንተባበር:: ህይወታችን መመስከሩ ብቻ አይበቃም ነገር ግን ቃሉን እንስበክ ወደ መንግስቱ ሰዎችን ከጥፋት እንሰብስብለት ለጌታ:: ኑሯችን ጌታን ካሳየ ያኔ ቃላችንን ሰዎች ያከብሩታል:: ለዝች ዓለም በጣም እናስፈልጋታለን ጌታ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነውና የራሳችንን ብርሀን እናብራ በጣም አስፈልጋታለሁ::

አገልግሎት እዚህ ጋር ጳውሎስ እንደሚለው የአክሊል መቀበያ እንዲሁም በጌታ ፊት የምናሳየው ትምክህታችን እንጂ ከዚህ ከምድር ምንም አይነት ወሮታን አንጠብቅ:: በስተመጨረሻ አገልግሎታችን በእሳት ይፈተናል:: በሌላው ደስታ ደስ ይበለን እንጂ ውስጣችን አይቆጣ::


ከራስ ይልቅ የክርስቶስን ማስቀደም

ወደ ፊልጵስዩስ 2 :19-30
19 ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። 
20 እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤ 
21 ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። 
22 ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደ ሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ። 
23 እንግዲህ እንዴት እንደምሆን ባየሁ ጊዜ፥ እርሱን ቶሎ እንድልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ 
24 ራሴ ደግሞ ግን ፈጥኜ እንድመጣ በጌታ ታምኜአለሁ። 
25 ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤ 
26 ሁላችሁን ይናፍቃልና፥ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል። 
27 በእውነት ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፥ ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይጨመርብኝ ለእኔ ደግሞ እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም። 
28 እንግዲህ እንደ ገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በብዙ ፍጥነት እልከዋለሁ። 
29 እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፥ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ 
30 በእኔ ዘንድ ካላችሁ አገልግሎት እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን እንዲፈጽም፥ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና።

ጢሞቴዎስ በጳውሎስ ፊት እንዴት ያለ ተቀባይነት እንዳለው በዚህ ክፍል ላይ እናያለን ምክንያቱ ደግሞ

  1. የራሱን ሳይሆን የክርስቶስን የሚፈልግ ነው ልክ እንደ ጳውሎስ:: በዚህ ሰዓት እስር ቤት እያለ ጢሞቴዎስን መላክ ከባድ ነው በብዙ የሚረዳውን እስር ቤትም የሚያስፈልገውን ሁሉ የሚያቀብለውን በልቡም መልእክት ሲመጣ የሚልከውን መጽናናት ሲያስፈልገ ሁሌ አጠገቡ የሚገኘውን በዚህ ወሳኝ ሰዓት መላክ ምን አይነት መሰጠት ነው? እኔ ይቅርብኝ ሄደህ እነሱን አገልግለሀቸው አይተሀቸው ተመክለስ ብሎ መላክ?!
  2. ስለ ኑሮአቸው በቅንነት የሚጨነቅ ነው:- ይህ ነገር በጳውሎስ ውስጥ ነበረ ወደ ጢሞቴዎስም ተላልፏል:: በቅንነት የጌታን ነገር ለማየት በቅን መጨነቅ አላቸው ሁሉቱም:: እንደ አካልም እንዲህ ልናስብ ይገባል ስለሌላው በቅንነት ልንጨነቅ በተለይ ክርስቶስ በህይወታቸው እስኪሳል::
  3. ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ።  ተፈትኖ ጸንቶ መገኘትን እናያለን በህይወቱ:: ወንጌልን ስናገለግል ከውስጥም ከወንድሞች ከውጭም ካልዳኑት ፈተና አለ ግን መዘጋጀትና ጌታ እንዳለን ተግተን መጸለይ ነው:: በፊቱ ስንሆን ማምለጫውን ከፊታችንም ምን እንደመጣ ይነግረናል ደግሞም ያግዘናል::

ይህ ዘመን ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም የሚለው በግላጭ የታየበት ነው ማለት እንችላለን:: የእግዚአብሔር ጸጋ ይብዛልን::

ጳውሎስ ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤ እርሱ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና።

ሌላው የሚገርም አገልጋይ አፍሮዲጡ ነው:: ሲገልጸውም ወንድም፥ ሠራተኛ ወታደር፥ በነብሱ የሚወራረድ ይለዋል:: እንዴት እንደሚያስፈልገው ቢያውቅም ግድ የለም እናንተም ናፍቃችሁታል እሱም እንደዛው ስለዚህ እልከዋለሁ ሲል ይገርማል:: ይህ ሰው እራሱን መጨረሻ ነው የሚያደርገው ያ በክርስቶስ ውስጥ የነበረው አሳብ ለሌሎች መኖር በሱ ላይ ይታያል:: ተቀበሉት እንዲህ አይነቶቹንም የእግዚአብሔር ባሪያዎችን አክብሩ ይለናል::

እኔም እግዚአብሔር መምሰል እራሴን ማስለመድ እንዳለብኝና ሌሎችን ማስቀደም ስለቅዱሳን ኑሮ ማሰብና መማለድ እንዳለብኝ ተምሬያለሁ:: ደግሞም እግዚአብሔር እንዴት ስለእኛ እንደሚጠነቀቅ አይቻለሁ አፍሮዲጡ ታሞ እንዴት ከሞት እንደተረፈ እናያለን ወንጌልን ስናገለግል የፈተናው ዘርፈ ብዙ ነው ግን እንታገስ ሁሉ ያልፋል ጌታ ብቻ ይክበር:: አሜን!


ምዕራፍ 3


ተጠበቁ! ከምን እንጠበቅ?

ወደ ፊልጵስዩስ 3:1-2
1፤ በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው።. 2፤ ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።

ወንድማችን ጳውሎስ ከእስር ቤት በጌታ ደስ ይበላችሁ ይለናል:: በጌታ ደስ መሰኘት የሚመጣው ከሁኔታ ሳይሆን በውስጣችን ካለው መንፈስ ነው:: ደስታ የመንፈስ ፈሬ ነው ስለዚህ ሁልጊዜ በውስጣችን የሚገኝ በነገሮች ያልተደገፈ የጌታ ስጦታ ነውና በራሱ በጌታ ደስ ይበለን:: ዛሬ በምንም ነገር ውስጥ እያለፍን ቢሆን አሁን ቆም ብለን በዚህ ደስታ ውስጥ ለመሆን እንውስን ደግሞም እንጽና ምን እንዳይመጣ ነው? ሁሉን የሚቆጣጠረው እኮ አባታችን ነው:: ሃሌሉያ! አሜን!

ከዚህ በፊት የነገርኳችሁ ቢሆንም እንኳ ደግሜ ልንገራችሁ ይላል:: የተደገመ ነገር ላይ አትኩሮት ማድረግ ጥሩ ነው:: ሊደግምላቸውም የፈለገው ነገር ስለ መጠበቅ ነው:: ከምንድነው ተጠበቁ የሚላቸው?

  1. ከውሾች ተጠበቁ፥ መቼም ውሻ ሲለን እንስሳውን እንዳልሆነ ግልጽ ነው:: ምሳሌው ከአህዛብ አስተሳሰብ ለማለት ነው:: አህዛብ ሐጥያተኛና ከእግዚአብሔር የራቁ እንደሆኑ የታወቀ ነው ስለዚህም እስራኤላውያን በውሻ መስለው መጥራታቸው ይህንን ያመላክታል:: ጌታችንም በማቴ 15: 26፤ እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም፡ አለ። ስለዚህ መጠበቅ ያለብን ከአህዛብ አስተሳሰብ ነው እኛ ህይወታችንን ለጌታ የሰጠን ነን ለራሳችን አንኖርም ለሞተልን እንጂ እነሱ እንደወደዱ ሲሆኑ ከነርሱ ጋር አብረን እነሱ የሚያደርጉትን ሁሉ አናደርግም ይህ እስራት እንዳይመስለን መቀደስ እንጂ ውስጣችንም እሺ አይለንም:: የተከፈለልን ዋጋ ብዙ ነውና ወስደን አንቀላቅለውም::
  2. ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ በየጊዜው የተለያዩ አገልጋዮች ይነሳሉ እኛ ግን ማየትና መመዘን ያለብን በፍሬያቸውና በአኗኗራቸው መሆን አለበት:: የዋህ ልብ ክርስቶስን የሚመስል ማንነት እንጂ ክፋትን ካየን አለመተባበር እንዳለብን እንወቅ::
  3. ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ:- መገረዝም ሁለት አይነት ነው ማለት ነው:: አንዱ የስጋ ብቻ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንፈስ ነው:: መጀመርያ መገረዝ የተሰጠው አብረሀም ነበር ግን አላጸደቀውም:: የጸደቀው በእምነት እንጂ:: የስጋው መገረዝ በራሱ ምንም አያደርግም በእምነት በክርስቶስ ያገኘነው ግን አዲስ ፍጥረት አድርጎናል:: በገላትያ 5: 6፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።

ማን ነን?

ወደ ፊልጵስዩስ 3: 3
እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና። 
ስለማንነታችን እስኪ ትንሽ እንይ:-

  1. በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ:- የእኛ እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚመለከውም በእውነትና በመንፈስ እንደሆነ ጌታ እየሱስ ነግሮናል::
  2. በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ :- እየተከሰስን ወይም ደግሞ አንዳችን ለውጥ ለማምጣት በጽድቃችን ላይ ለመጨመር አይደለም:: የክርስቶስ ደም ከሞተ ህሊና ሁሉ ታድጎን በእርሱ እየተመካን በሆነልን ነገር ላይ አንዳች እስከማንጨምር ድረስ በተጠናቀቀ ድል ላይ ልባችንን ሞልተን እንደልጅ እንመላለሳለን ይህንን ትምክህት የሰጠን የታረደልን እየሱስ ስሙ ይባረክ! አሜን!
  3. በሥጋም የማንታመን :- የስጋን ትምክህት አሽቀንጥረን የጣልን ነን:: በስጋ በመመላለስ መጽደቅ የሚቻል ቢሆን ኖሮ እየሱስ ለምን ይህንን ሁሉ ዋጋ ከፈለ?
  4. እኛ የተገረዝን ነን:- በቁ 2 ከላይ እንዳየነው ከሀሰተኛ መገረዝ ስለመጠበቅ ይነግረናል:: እውነተኛ አለ ማለት ነው እርሱም እኛ በመንፈስ ተገርዘናል በስጋ ሳይሆን በቆላስይስ 2: 11፤ የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። እኛ በእጅ አይደለም የተገረዝነው በእጅ የተገረዙት ልባቸው ሳይገረዝ ቀረ የእኛ ልብ ግን በጌታ ተገረዘ:: በዚህ ዘመን የመገረዝ ጉዳይ አሳሳቢ አይደለም በመንፈስ የመቀደሱ ጉዳይ ላይ ግን ለመቀበል ችግር አለ:: የተቀደስኩት መቀደስ በቂ አይደለም ልጨምርበት የሚለው ሀሳብ በዛ ዘመን ተገረዙ ከሚሉት አይለዩም ባይ ነኝ:: የክርስቶስ ስራ አልተጠናቀቀም እንጨምርበት እንደሆነ ያስተዋልን አልመሰለኝም እርሱ ተፈጸመ ብሎ ሳለ:: ሁልጊዜ የሆነ ደረጃ ላይ ለመድረስ መጣር ነው የያዝነው የተደረገልን አልበቃ ብሎናል በአንድ ጊዜ መንፈሳችን እንደተለወጠ አኮ አይደለም ነፍሳችን የምትለወጠው እንደተወለደ ልጅ እየተማረች የእግዚአብሔርን እውቀት በማወቅ ታድጋለች:: ማስታወስ ያለብን በአብ ቀኝ ወስዶ ስራ አለቀ ቁጭ በሉ ብሎናል:: ይህ ማለት ግን ለሐጥያት ፈቃድ እንደመስጠት የሚቆጥሩት አሉ አሳቡ እራሱ ከየት መጣ የሞተ ይነሳል እንዴ እኛ ለዓለም ሞተን ለክርስቶስ የምንኖር ነን:: ጸጋ ይብዛልን!

ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ

ወደ ፊልጵስዩስ 3: 4-11
4፤ እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። 
ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። 
– አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤  10 11 እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። 

መመካት ቢኖርብኝ ብዙ የምመካበት ነገር አለኝ ይላል ጳውሎስ ባለው እስታንዳርድ በማሕበረሰቡ ዘንድ ፐ! የተባለ ነበር ጳውሎስ ሁሉንም መስፈርት አሟልቶ የሚኖር ነበር :: በሰው ፊት አልፏል በእግዚአብሔር ፊት ግን ከንቱ ነበር:: እውነት የሆነውን ባየ ጊዜ ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ:: ይህንን ሁሉ ዘመኑን የለፋበትን በማኅበረሰቡም ዘንድ ትልቅ ተቀባይነትንና የከበሬታ ወንበር የሚያሰጠውን ሲተው ሞኝ ያሰኛል:: ለእግዚአብሔር ቀንቶ ሲያሳድዳቸው የነበሩትን ተቀላቅሎ ምን ነካው የሚያስብል ነገር ነው በህይወቱ የሆነው:: ሁሉን ለክርስቶስ ስል ትቼዋለሁ ይላል ስደትና መከራ የሚያመጣበትን መንገድ መረጠ::

በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ለጳውሎስ ይህንን ሁሉ ቢያጣም በምድር ለሱ ቦታ ያለው ጉዳይ ጌታውን ማወቁ ነው:: ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥

ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥

በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ ያንን ሁሉ ዘመን የፈጀሁበት የራሴን ጽድቅ ላቆም ነበር ግን ትክክለኛው በእምነት የሆነው እንጂ እኔ ስጠብቅ የኖርኩት ህግ አይደለም::

በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤  እግዚአብሔር አብ ሊያየን የሚፈልገው በክርስቶስ ውስጥ ነው:: የእርሱ ጽድቅ ተቆጥሮልን የራስን ጽድቅ ማቆም ትተን በእርሱ ውስጥ መገኘት::

እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በሮሜ 6: 5፤ ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤

በመከራውም እንድካፈል፥ ክርስቶስን ተከትለን ጠላት መከራ አያመጣም ማለት ዘበት ነው ቢመጣም ግን እንጸናለን::

ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።  ከፈለጉ ህይወቴን ይውሰዱ እንጂ እኔስ እስከመጨረሻ እርሱን እመስላለሁ የሚል አቋም አለው::

እኛም ዛሬ አንዳችም ጽድቅ ማቆም የማንችል መሆናችንን አውቀን በእርሱ ውስጥ እንዳለን አውቀን መንገዳችንን እርሱን በማሳየት እንኑር::


እንዴት ሩጫችንን እንሩጥ

ወደ ፊልጵስዩስ 3:12-13
12፤ አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። 13፤ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥

አሁን እንደያዝኩት አልቆጥርም የሚለን ደህንነቱን አይደለም ሰው ከእግዚአብሔር አንድ ጊዜ ከተወለደ አይጠፋም አምላኬ አይደለም ብሎ እስካልካደ:: እዚህ ጋር ጳውሎስ የሚለው ስለ አገልግሎቱ አልረካሁም እርሱ ለእኔ ብዙ ዋጋ ከፍሏልና ገና እንደሚገባ አላገለገልኩም ለማለት ነው:: እሱ እንደዚህ ካለ እኛ ምን እንበል? ደህንነት አንድ ጊዜ ተቀብለን የሚቆም አይደለም ጌታን ማገልገልና እምነታችንን እግዚአብሔርን በመምሰል እየኖርን ማሳየት አለብን:: በሌላም ስፍራ ፀንተን ሐይማኖታችንን እንጠብቅ ይለናል::

ጳውሎስ ሩጫውን ሲሮጥ እንዴት እንደሆነ ይነግረናል:- 1. እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ:- ማን እንደኔ እዩ እስኪ የደረስኩትን ቦታና የሰው ብዛት እያለ ጉራውን አይቸበችብም ገና አልያዝኩም እያለ ነው:: ዝቅ ብሎም ሐዋርያት ጋር ሄዶ እንዴት ነው ወንድሞች አገልግሎቴ ብሎ የጠየቀ ሰው ነው እነርሱ ግን መቀበል አቅቷቸው ገፍተውት ነበር መለወጡን ተጠራጥረው:: ስለራሱ ክብር ሳይሆን ስለጌታው ብቻ ነበር የሚታየውና የሚያስበው:: አንድ ብቻ ነው ተልዕኮውና ግቡ እርሱም ጌታን ማገልገል! እኛም በግል ጉዳይ ከመከራከር ወተን ጌታን ብቻ ማክበርና ማገልገል ላይ ልባችንን ማድረግ አለብን::

2. በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ :- በእርሱ ውስጥ የሚሰራው ጌታ እንደሆነ ስለገባው የኃላውን እየረሳ ሁልጊዜ ወደፊት ነው የሚያየው ልዘክርም ቢል ጌታን ብቻ ነው የሚያሳየው:: እኛንም ጌታ ይርዳን!

3. በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ ሁልጊዜ ወደፊት ማሰብ ነገ ጌታ ምን ሰርቶ ያስደንቀኝ ይሆን፥ ማነው የሚድነው፥ የት ነው የሚልከኝ ብለን ወደፊት እንደጳውሎስ እናስብ እንጂ ባለፈው ድል ወይም ደግሞ ሽንፈት ላይ አይሁን አይናችን:: ከሰዎችም ጋር ያለንን ነገር በክርስቶስ ውስጥ እናድርግ ሰዎችን ከክርስቶስ ውጪ አንያቸው::


በደረስንበት በዚያ እንመላለስ

ወደ ፊልጵስዩስ 3: 14-16
14፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። 15፤ እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ 16፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ።

በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ እፈጥናለሁ ይለናል:: እኛ ከፍ ላለ ነገር ተጠርተናል በእግዚአብሔር:: እሩጫ ውስጥ እንዳለ ሰው ነው እራሱን የሚቆጥረው ግን ይህ የሩጫ ውድድር ለየት ያለ ነው ምክንያቱም ከጎናችን ካለው ጋር አይደለም የምንወዳደረው የተነገረን ውድድሩን ጨርሱ ነው:: እኛ ሰውን ኮፒ አናደርግም ነገር ግን በተሰጠን ጸጋ ክርስቶስን ማክበር ነው ጎላችን:: የግድ ዳዊት ጦረኛ ለመምሰል የሳዖልን ልብስ መልበስ የለበትም ጌታ ያለማመደው በወንጭፍ ነውና ድሉም በዛው ነው የሚገኘው:: የተሰጠንን መክሊት እናትርፍበትና ለአክሊል እንብቃ ያልሰጠውን የሚጠብቅ ፍርደ ገምድል ጌታ አይደለም ያለን:: ጳውሎስ በመጨረሻ ሩጫዬን ጨርሻለሁ ብሎ የህይወቱን ምዕራፍ ዘግቷል:: የጀመርነውን ሩጫ ሮጠን እንድንጨርስ ጌታ ይርዳን::

ሌላው የሚገርም አባባል በዚህ ክፍል ላይ:- ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ:: ምን የሆንን?! ፍጹማን! አይገርምም ፍጽምና ተሰቶናል:: ምን እንድናስብ ነው ወንድማችን የሚነግረን? በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል ይለናል:: የጠራን ጌታ ነው የሚያሰማርንም እርሱ ነው ግድ እንደነ እንትና መመላለስ የለብንም:: ስለበጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም እርሱ አይደል በእኛ የሚሰራው? ስለዚህ ሁሉን ከእርሱ ጋር እንጨርስ:: በምንም አይነት ሌላው የሄደበትን አንፈልግ ኦርጅናል የሆነ አሰራር አለው ለእያንዳንዳችን ስለዚህ የራሳችንን መንገድ እንጠብጥብ በሌላው እየገባን እንቅፋት አንሁን ሌሎችም እንቅፋት እንዲሆኑብን አንፍቀድ::


ጌታን ምሰሉ

ወደ ፊልጵስዩስ 3:17-19
17፤ ወንድሞች ሆይ፥ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፥ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ። 18፤ ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። 19፤ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው።

ጳውሎስ ደስ የሚለኝ አንዱ ነገሩ እየሱስን እንደሚመስል እርግጠኛ መሆኑና እኔን ምሰሉ ብሎ በድፍረት ማለቱ ነው:: ማንን እንመስላለን? ልንመስል የተጠራነው እየሱስን እንጂ ቤተክርስቲያናችንን ወይም ክርስቶስን የማይመስሉ መሪዎችን አይደለም ሁልጊዜ አይናችን በጌታ ላይ ይሁን:: እርሱን የሚመስሉትን ተመልከቱ ምሰሉዋቸው ደግሞም ለሌሎች ምሳሌ ሁኑ ነው የሚለን:: ምክንያቱም ብዙዎች ለመስቀሉ ጠላቶች ሆነው ነው የሚመላለሱት::

ለመስቀሉ ጠላት መሆን ምን ማለት ነው? ጳውሎስ እንዲያውም አለቅሳለሁኝ ስለነሱ ምክንያቱም መጨረሻቸው ጥፋት ስለሆነ ይላል:: ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው:: ጠላት መሆን ማለት ይህ ነው! የሚያስቡት ሁሉ ለራሳቸው እንጂ እነ ጳውሎስና ጢሞቲዎስ እንደሚያስቡት ስለክርስቶስና ስለአካሉ አይደለም:: ሁሉን ትቶ እኛን ብሎ የመጣውን ጌታ ነው ማክበር ያለብን:: የመስቀሉ ጠላቶች አሳባቸው ሁሉ ምድራዊ ነው እኛ ግን ከዚህ ምድር አይደለንም ስጋን ከክፉ መሻቱ ጋር ሰቅለናል:: (በሮሜ 8:5-8) እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ:: ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። አለቀ! ጌታን በስጋ ደስ ማሰኘት አይቻልም!

ስለዚህ ዛሬ እንዴት እንመላለስ? ጌታን በመምሰል የምድሩን ሳይሆን የሰማዩን እያሰብን እንመላለስ፥ እርሱን የሚመስሉትን እየደገፍን፥ በታማኝነት እንመላለስ::


እኛ አገራችን በሰማይ ነው

ወደ ፊልጵስዩስ 3: 20-21
20፤ እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ 21፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።

አገራችን በሰማይ ነው ብለን ስንል ጌታ እራሱን ባዶ አድርጎ፥ ተዋርዶ፥ የባርያን መልክ ይዞ የመስቀል ሞት ሞቶ እዳችንን ከፍሎ ነው ወደዚህ ክብር ያመጣን:: ስለዚህ እኛም በትክክል የዚህ አገር ዜጋ መሆናችንን ለማሳወቅ እታች እላይ ማለት የለብንም እኛው እራሳችን ካልገባን በቀር:: ምሳሌ ልስጣችሁ:- ኢትዮጵያዊ ለመሆኔ ማስረጃዬ ምንድነው? አንድ ሰው አይደለሽም ቢለኝ ያዙኝ ልቀቁኝ እላለሁ እንዴ? ተወው ብዬ እሄዳለሁ እንጂ የዛ ሰው ማመንና አለማመን ማንነቴን እንደማይቀይረው ስለማውቅ ዝም ብዬ እሄዳለሁ ምክንያቱም ውስጤ ተዋህዷል፥ እርግጠኛም ነኝ:: ልክ እንደዚሁ ኖርማል መሆን ነው ያለበት ወደዚህ እረፍትና አገር የመግባቴ ጉዳይ እንጂ እወቁልኝ ብዬ የምለፍፈው አይሆንም ከኔ ጋር ሲዋሀድ::

እኛ ተስፋ የሌለን አይደለንም ተስፋችን፥ መድኃኒታችን ጌታ እየሱስ ይመጣል እርሱን የምንጠባበቅ ነን:: ስፍራ ላዘጋችላችሁ እሄዳለሁ ብሎ ቃል ገብቶልናል:: እመጣለሁ ብሎን አሳቤን ቀየርኩኝ የማይል እውነተኛና ታማኝ ጌታ ነው! ሃሌሉያ!

ሲመጣ ተዘጋጅተን እንጠብቅ ይህንን ዓለም በመናቅ እርሱን በመምሰል እንመላለስ:: ሲመጣስ በእኛ ላይ ምን ይሆናል ብለን ስንል ለአሰራሩ እንዲመቸው ይህን ስጋ ክቡር ስጋውን እንዲመስል ይቀይረዋል:: እንዴት? ስንቶቻችንን? ብዙ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል አይደል? ቀመቅጽበት የሁላችንም የተዋረደ፥ ደካማ ስጋ ይለወጣል:: ለዛኛው አገር እንዲሆን ተደርጎ እናም ከዛ በኃላ ድካም፥ ሞት፥ ለቅሶ፥ ሰቆቃ፥ ኃዘን የለም! የለም! የለም!!!! አሜን ለታረደው በግ ክብር ይሁንለት:: ይህንን ለማየት በጣም እናፍቃለሁ፥ እጏጏለሁም:: ይህ ሁሉ በነጻ የተሰጠኝ እድለኛ ሰው ነኝ:: ከእግዚአብሔር ቁጣ ያመለጥኩኝ፥ ልጅነት የተሰጠኝ ነኝና የዓለምን ነገር ንቄው እኖራለሁ ለጌታ ክብር:: ደግሞም ለዚህ ጌታ ስኖርለት አንዳች ጸጋ አይጎድለኝም በሚያስፈልገኝ ሁሉ ይሞላኛል እውስጤም ሆኖ ያበረታኛል ያ ቀን ሲመጣ እኔ በእርሱ ውስጥ እርሱም በእኔ ውስጥ እንዳለ አውቃለሁ::

ከዘላለም እስከ ዘላለም ስሙ ይባረክ:: አሜን


ምዕራፍ 4

ምዕራፍ 4 ንባብ
በጌታ ቁሙ

ወደ ፊልጵስዩስ 4: 1-3
1፤ ስለዚህ፥ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ፥ እንዲሁ በጌታ ቁሙ፥ ወዳጆች ሆይ። 2፤ በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። 3፤ አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎቹ ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና።

ከላይ ሲነግረን እንደመጣው አገራችን በሰማይ ነውና ከዛም የሚመጣ መድኃኒት እንጠባበቃለንና ጸንታችሁ በጌታ ቁሙ ይለናል:: ጸንተን ስለመቆም ከተነገረን መቼም ሊጥለን የሚጋፋ ነገር አለ ማለት ነው:: ጌታም እንደነገረን በዚህ ዓለም ስንኖር አልጋ ባልጋ ነው አልተባልንም የተባልነው አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌያለሁና እረዳችኃለሁ እንጂ:: ስለዚህ ጸንተን በጌታ እንቁም:: ሌላው ጳውሎስ እንዴት እንደሚወዳቸው እዚህ ጋር ማየት ይቻላል:- የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ እያለ ይገልጽላቸዋል ፍቅሩን:: ለታይታ ወይም አንዳች ፈልጎ ሳይሆን ከውስጥ የሆነ መውደዱን ነው የሚያሳውቃቸው እነሱን በማገልገሉ የደረሰበት መከራና ግርፍ ነው እንጂ ድሎት አልነበረም ግን አሁንም ይናፍቃል ሊያያቸው መከራ ቢጠብቀውም እንኳን:: ምን አይነት ፍቅር ነው?! ጌታ እንደዚህ ያለ የወንድማማችን መዋደድ በውስጣችን ያድርግልን::

መቼም ጌታን ስናገለግል በተለያየ አሳብ ላይ አለመግባባት ይኖራል ምክንያቱም ሰው የተለያየ አቋም፥ አስተዳደግ፥ አመልና አመለካከት አለው:: አንድ ሊያደርገን የሚገባው እዚህ ጋር ጳውሎስ የሚመክረው በአንድ አሳብ በጌታ መስማማት ነው:: የመስማማታችን ምክንያት ጌታ መሆን አለበት ይህ እርሱን ደስ ያሰኘዋል ወይ ሊሆን ይገባል የሚያሳስበን:: ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም እንዳለው የክርስቶስን የምንፈልግ ከሆነ በአንድ አሳብ ጌታን ለማክበር አንቸገርም:: የህይወታችን ማዕከል ጌታ ብቻ ሊሆን ይገባል::

አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ ይላል:: አብሮ መጠመድ ምሳሌው ልክ ሁለት በሬዎች ተጠምደው አብረው እንደሚያርሱት ያለ ምሳሌ ነው:: አንዱ ወደግራ ሌላው ወደቀኝ ልሂድ ቢል ስራ አይሰራም ግን ግባቸውን አውቀው በአንድ አሳብ ላይ ቢስማሙና ቢሰሩ ግን ውጤት ይኖረዋል:: በእውነት ጌታን ከሚከተሉና ስማቸው በህይወት መጽሐፍ ከተጻፈው ጋር ህብረት ማድረግና መተጋገዝ ያስፈልጋል::


ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ

ወደ ፊልጵስዩስ 4: 4-5
4፤ ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ:: 5፤ ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ።

ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ ትእዛዝ ነው ምክንያቱም ደስታ የመንፈስ ፍሬ ነው እኛም ውስጥ አለ:: ደስ ይበላችሁ ብሎ ጳውሎስ የሚጽፍልን ከእስር ቤት ነው ይህ የሚያሳየው በውጭው ሁኔታ አይደለም ደስታችን ከውስጥ እንጂ:: ከውስጣችን ይህንን ደስታ መውሰድ የሚችል የለም በእኛ ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ ሞልቶናልና ማን ይወስድብናል? ደስ ይበላችሁ ብሎ በቃሉ ዛሬ ሲናገረን የማይቻል ነገር አድርጉ ብሎ እየፈተነን አይደለም የኛ ጌታ ማንንም በክፉ አይፈትንምና:: ስለዚህ በዙሪያችን ያለው ነገር ደስ ለመሰኘት የማይደግፍ ቢመስልም እንኳን እኛ ግን ዙሪያችንን ሳናይ በጌታ ደስ ይለናል:: አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም ያለን ደግሞም የሚለው ደስ ይበላችሁ በጌታ ነው:: ስለዚህ በየዕለቱ ደስ ሊለን ይገባል በጌታ:: አሜን!

ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ ሲለን ኑሩት የጌታ ባህርይ በእናንተ ይታይ እርሱ ገር እንደነበር እንዲሁ ተመላለሱ አሳዩት ለዓለም እያለን ነው:: በማቴ 5:14-16 (14 እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። 15 መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።  16 መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ) በሰማይ ያለው አባታችን የሚከብረው እኛን በማየት ነው እኛ የሰማይ መንግስት አምባሳደሮች ነን:: የምንወክለውን መንግስት እናሳይ ዛሬ ጌታ በእኛ ውስጥ ሆኖ መስራት ይፈልጋል የሚሰራውም ሰዎችን ማዳንና ለመንግስቱ ማብቃት ነው:: ለዚህ የተቀደሰ አላማ ተጋብዘናልና ጌታን እናሳይ ለሁሉ:: በመምጣቱ ፊት የምናፍር እንዳንሆን ዛሬ ጊዜ ሳለ በየዋህነትና ለሌሎች በማሰብ እንመላለስ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን! አሜን!


ጌታ ቅርብ ነውና በአንዳች አትጨነቁ

ወደ ፊልጵስዩስ 4:6-7
6፤ ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። 7፤ አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።

ጌታ ቅርብ ነው!! እውነት ነው ቅርብነቱ ያለንን እናስብ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ አላለምን? ደግሞስ መንፈስ ቅዱስ በእኛ እንደሚኖርና እኛው ብቻ ይህንን እንደምናውቅ ዓለም ግን እንደማያውቅ አልነገረንም? ታድያ ከዚህ በላይ ቅርብ መሆን ምንድነው? እርሱ በእኛ ውስጥ ከመኖርና የአብሮነቱን ቃሉ ከመስጠት በላይ? አሁን በዚህ ሰዓት እርሱ ቅርብ መሆኑን ማየትና መለማመድ ይቻላል:: እውነተኛ ስለሆነ:: ቃሉን ዛሬ በውጣችን እንሸሽግ ያሻግረና ምድረበዳ ወደ ህይወታችን ሲመጣ የምንይዝ የምንጨብጠውን የምናጣው ቃሉ ከእኛ ጋር ስላልተዋሀደ አይደለምን? ዛሬ ቀን ሳለ እናሰላስለው እንጸልይበት ቃሉን::

በነገር ሁሉ

  1. በጸሎትና
  2. በምልጃ
  3. ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ
  4. በአንዳች አትጨነቁ

ቅርብ ወደሆነው ጌታ ተጠግተን ልመናና ጸሎታችንን ካሳወቅን በኃላ በምስጋና መሆንና ጌታ እንደሰማን አውቀን በጉዳዩ አለመጨነቅ ነው ያለብን:: አንድ ምሳሌ ላምጣ:- በጣም የምትወዱት በተለይም የሚወዳችሁና የምትጠይቁትን ነገር ለማድረግ የሚችል ሰው ጋር ስልክ ደውላችሁ ጉዳያችሁን ነግራችሁ እርዳኝ ብትሉና ያ ሰው አረ ምንም ችግር የለም ነገ ጠዋት የመጀመሪያ ነገር እሱን ነው የማደርገው ቢለን ምን ይሰማናል? ደስ ብሎን ፈንድቀን እንቅልፍ ሳናጣ ተኝተን እናድር የለ? ታድያ ማንም እወዳለሁ የሚል ሰው ሊያደርግልን ያልቻለውን የመስቀል ሞት ሞቶ ያሳየንን ወደፊቱ ስንቀርብ ቀድሞ እንደ ወገግታ ተዘጋጅቶ የሚጠብቀንን ጌታን መታመን ጸሎቴ ተሰምቷል ብለን መነሳትና ማመስገን፤ አለመጨነቅ ምነው ከበደን? አጭር ነው መልሱ እርሱን በደንብ ካለማወቅ ነውና የጸለይነው ሁሉ ተሰምቷል ሰው ከሰው እንኳን ይሰማማል እንኳን የኛ ጌታ ተናግረን ይቅርና ሳንናገር ይሰማናል:; አሜን! ስንጸልይ የኔ ፋይል ተረሳ ወደ ስር ሆነ የሚል አስተሳሰብ ነው ያለን ማለት የሚገባን በእጁ ሰጥቼዋለሁኝ አባቴ ሰምቶኛል የሚል ልብ ይዘን ከፀሎት ልንነሳ የሚገባን::

አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል ሲለን እሱ የሚሰጠን ሰላም በምንም አይነት በዙሪያችን የሚፈጠር ነገር አይነቀንቀውም እየተባልን ነው:: ልባችንን የሚጠብቀው በፊቱ ቀርበን ጸልየን የሚያስጨንቀንን ስንሰጠ እርሱ ደግሞ ሰላሙን ይሰጠናል እንጂ ሰላም ስጠኝ ብሎ ጸሎት የለም:: ሰላም ያሳጣንን በፊቱ ይዘን ስንቀርብ እርሱምጸሎታችንን ሰምቶ ከእኛ ሲወስደው ሰላማችን የትም አልሄደምና እናገኘዋለን እኛው ጋር:: ሰላም የመንፈስ ፍሬ ስለሆነ ይገለጣል ከላዩ ላይ ያስቀመጥነውን ጭንቀት ስናነሳና በጌታ ላይ በእምነት ስናስቀምጥ:: ስለዚህ ልባችንን ይጠብቃል ምክንያቱም የህይወት መውጫ ነውና አሳባችንንም ይጠብቃል ምክንያቱም አሳባችን ከተያዘ ሁለንተናችን ይያዛልና:: ቃሉን እንኑረው! ጌታ ጸጋውን ያብዛልን!


እነዚህን አስቡ

ወደ ፊልጵስዩስ 4: 8-9
8፤ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ:: 9፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።

በቀረውስ፥ እነዚህን አስቡ

  1. እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
  2. ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥
  3. ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
  4. ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥
  5. ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥
  6. መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥
  7. በጎነት ቢሆን፥
  8. ምስጋናም ቢሆን፥

ለምን እነዚህን አሳቦች እናስብ? ምክንያቱም ጳውሎስ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን ነውና እያለ ነው:: ከላይ ባሉት ቁጥሮች ስለ ስላም አንስቶ ነበር አእምሮንና ልባችንን እንደሚጠብቅ፥ ይህ የሚሆነው ነገራችንን ሁሉ በእርሱ ላይ አድርገን ሳንጨነቅ ስንቀር ነው:: ስለዚህ እንዚህ 8 አሳቦች አሳባችንን ቢሞሉት ሳንናወጥ፥ ሳንጨነቅ፥ ሰላማችን ተጠብቆ እንመላለሳለን የሰላምም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል::

ክርስትናን ታድያ ከባድ ያደረግነው እኛው አይደለን? የእኔ ሸክም ቀሊል ነው እያለን ጌታ ወይ ክርስትና! የምንል እንዳንሆን ብቻ! ጳውሎስ ያያችሁትንም ኑሩት እንደሚለውስ ህይወታችን ምን ያህል ጌታን ያሳያል? አፋችንን ሞልተን ምሳሌ ልሁናችሁ ማለት እንችል ይሆንን? ጌታ ይርዳን!


ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ

ወደ ፊልጵስዩስ 4: 10-14
10፤ ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። 11፤ ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና።. 12፤ መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። 13፤ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። 14፤ ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ።

በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ ይላቸዋል ማጣት መከራ ነው:: ከዝች ቤተክርስቲያን በስተቀር ጳውሎስ ስለስጦታ የሚጠቅሰው የለም:: ችግር አለብኝ እርዱኝ እናንተን ለማገልገል ነው እንደዚህ የምኖረው ብሎ ስለ ራሱ አያሳይም ስለ ክርስቶስ እንጂ እኔ ሞቻለሁ ነው መፈክሩ:: የሞተ ደግሞ ብዙ አያስቸግርም ይሄ ይሁንልኝ ለምቾቴ አይልም አመለካከቱን ሁሉ በጌታ ላይ ያደረገ ሰው ነውና:: ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ ለማለት መሞት ይጠይቃል:: ኃይል የሚሰጠው ጌታን ለማገልገል ነው እንጂ የፈለግነውን እያደረግን ኃይል ስጠኝ የለም::

እንደ ገና ስለእኔ ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በማለት ከዚህም ቀደም ስጦታን እንደሰጡት ያነሳል:: ግን ይህን ሲል ረሳችሁኝ እንዳልሆነ እንዲረዱለት ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና።. በኑሮዬ ይላል ጳውሎስ ምናልባትም አብዛኛዎቻችንን የሚነካ ነገር ውስጥ አልፏል:: እነዚህም:

መዋረድንም አውቃለሁ

መብዛትንም አውቃለሁ፤

በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና

መራብንም

መብዛትንና

መጉደልን ተምሬአለሁ።

ስለዚህ በዚህ ዝርዝር ውስጥ እንኳን በሌለ ነገር ውስጥ የምናልፍ ብንኖር በእኛ አልተጀመረም መከራና ሰልፍ ከመንገዳችን ዝለን እንዳንደክም ኃይል እየጠየቅን ጌታን እያስከበርን መንገዳችንን እንጏዝ:: የምድርን ነገር እንዳው እያደመቅን አናሳይ ጌታን እንጂ:: በጌታ ወንድሞቻችን የሆኑትን በተለይም አገልጋዮችን መርዳት አስፈላጊ ነው:; ወንድምህ ርቦት እሳት ሙቅ ማለት ስህተት ነው ስለዚህ መርዳት የምንችል ሁሉ ለመርዳት እጃችንን እናንሳ::


የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል

ወደ ፊልጵስዩስ 4:15-23
15፤ የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ 16፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። 17፤ በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። 18 ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። 19 አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። 
20 ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።  21 ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።  22 ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 23 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

በመስጠታችን ሰውን ማስደሰትና የእግዚአብሔርም ስም እንዲመሰገን ምክንያት እንሆናለን:: ጳውሎስ ስለ ስጦታቸው ማመስገን ብቻ ሳይሆን መርካቱንም ይነግራቸዋል ተሞልቼዋለሁ በማለት:: አፍሮዲቱ ምን ያህል እርቀት እንደመጣ ማሰብ ነው ብዙ የመጏጏዣ አማራጭ በሌለበት ዘመን ይህንን ሁሉ እርቀት ለመሄድ መነሳሳት በጣም ይገርማል:: ፍቅር ግን ይህንን እንድናደርግ ብቃት ይሰጣል የእነዚህን ሰዎች ፍቅር አይቻለሁ:: ጳውሎስም አምላኬ እንደባለጸግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኃል ነው የሚላቸው ከስጦታቸው የተነሳ:: ለተቸገረ ስንሰጥ ጌታ ይሰጠኛል በሚል ልብ ሳይሆን በልግስና ስንሰጥ እግዚአብሔርን ያስደስተዋል ለዛም ደግሞ ይባርከናል::

እዚህ ጋር ሰላምታ ያቀርቡላችኃል ከሚላቸው ወገኖች መካከል ከቄሣር ቤት የሆኑ የሚላቸው አሉ:: እነዚህ በመጽሐፉም መግቢያ ላይም የገለጣቸው እስራቴ በንጉሱ ዘበኞችና በሁሉ ዘንድ ስለክርስቶስ እንደ ሆነ ታውቋል ይላል:: እነሱንም ሰብኮ ወደ መንግስት አምጥቷቸው ነበር ማለት ነው:: እስራትም ውስጥ ቢሆን እንኳን የእግዚአብሔር ቃል አልታሰረም ነበር:: ዛሬም ጌታ ይሰራል:: ስሙ ይባረክ የኛ ጌታ!


የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።



1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች

መግቢያ

የዚህ መጽሐፍ ዓላማ

ጳውሎስ ከዚህ ከተማ ሲያሳዱት ነው ከተማውን ለቆ የወጣው አገልግሎቱም ለሶስት ሳምንት ነበር ሐዋ 17:2:: በጣም አጭር ጊዜ ስለነበረ ያገለገላቸው ያሉበትን ለማወቅ ነበር የጻፈው በሐዋርያት ሥራ 16:40 እስከ 17:10 ማየት ይቻላል:: ጳውሎስ አብረውት ያገለገሉትንም ወንድሞች ስም በደብዳቤው ላይ አስገብቷቸዋል::

ምዕራፍ 1

ምዕራፍ 1 ንባብ

ወንጌላችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንጂ በቃል ብቻ አይደለም

1ኛ ተሰሎንቄ 1:1-5
1፤ ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። 2-3፤ በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥ የእምነታችሁን ስራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤4፤ በእግዚአብሔር የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ተመረጣችሁ አውቀናልና።5፤ ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።

እዚህ ጋር ጳውሎስ እንዴት ስለእነሱ እንደሚያመሰግኑ እየነገራቸው ነው:: በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥

1. የእምነታችሁን ስራ

2. የፍቅራችሁንም ድካም

3. በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤

በእግዚአብሔር የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ተመረጣችሁ አውቀናልና።

ወንጌላችን:-

በኃይልና

በመንፈስ ቅዱስ

በብዙ መረዳትም እንጂ

በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ። እነጳውሎስ ማገልገል የቻሉት ጥቂት ጊዜ ቢሆንም እንኳን በመካከላቸው መንፈስ ቅዱስ መረዳትን ሰቷቸው ነበርና ወንጌልን እንደሚገባ ይዘው ነበር:: ዛሬም እኛ የሚያስፈልገን ከወይኑ ግንድ ጋር መጣበቅና ህያው የሆነውን ወንጌል መኖር ነው:: ወንጌል የሚሰራ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም በድንቅና ተአምራትም የተሞላ ነው:: አሜን!


ጌታን መምሰል

1ኛ ተሰሎንቄ 1:6-10

6፤ ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤7፤ ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው።8፤ ከእናንተ ወጥቶ የጌታ ቃል በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አልተሰማምና፥ ነገር ግን ምንም እንድንናገር እስከማያስፈልግ ድረስ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል።9-10፤ እነርሱ ራሳቸው ወደ እናንተ መግባታችን እንዴት እንደነበረ ስለ እኛ ይናገራሉና፤ ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥ ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።

ወንጌልን በብዙ መከራ እንደገናም ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀበሉት::  የተቀላቀለ ስሜት ያለው ነው የሚመስለው አይደል?  መከራና ደስታ?  የእግዚአብሔር መንፈስ ያስችላል ጸጋንም ይሰጣል::  ዛሬም ይህ መንፈስ በደስታ ይሙላን! አሜን!

ጳውሎስ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ ይላል እዚህጋ እንደምናየው ይመሰክርላቸዋል እኛንና ጌታን መስላችኃል ለሌሎችም ምሳሌ ሆናችኃል ይላቸዋል::  እኛስ ጌታን እንመስል ይሆን?  በስፍራው ሁሉ ምንም መናገር እስከማያስፈልገን ድረስ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል::  በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ እምነታችን ለሰው ሁሉ ይታያልና ለጌታም ክብርን ያመጣልና ጌታን እንምሰል::

ወደ እናንተ የገባነው እንዴት እንደነበረ ታውቃላችሁ ከብዙ እንግልትና ድብደባ ሸሽተው ነበር የመጡት በሌላ አነጋገር ደካማ በሚመስል ጌታ ግን ሲሰራ በድካማቸው የተፈጠረው:-  

1.  ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥ 

2.  ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ 

3.  ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።

እኛም ዛሬ ይህንን ህያው ጌታ እናገለግላለን፥  የእርሱን ከሰማይ መገለጥ እንጠባበቃለን፥ ወደ ጣዖትም አንመለከት እኛ የህያው እግዚአብሔር ልጆች ነን::  አሜን! 


ምዕራፍ 2

ምዕራፍ 2 ንባብ

የወንጌል አደራ

1ኛ ተሰሎንቄ 2:1-9
1፤ ወንድሞች ሆይ፥ ራሳችሁ ወደ እናንተ መግባታችን ከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና።2፤ ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን።3፤ ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኵሰት ወይም ከተንኰል አልነበረምና፤4፤ ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም።5፤ እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም 6፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።7፤ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤8፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።9፤ ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን።

በፊልጲስዮስ መከራ ቢቀበሉም ቢንገላቱም እንኳን ከረጅም የመንገድ ጉዞ በኃላ ወደ ተሰሎንቄ መተው እንደገና ተስፋ ሳይቆርጡ ምን ይመጣብን ይሆን ሳይሉ ቁስላቸውም ሳይደርቅ ወንጌልን ለመስበክ ደፈሩ:: በሚገርም ሁኔታ ፍሬን አፍርተው ከዚህም ስፍራ ተባረሩ::

ተስፋ ባለመቁረጥ ወንጌልን የሚሰብኩበት ምክንያት:-
1. እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ – የሚያጸናንና አብሮን የሚሰራ አለ የታመንን ሆነን እንገኝለታለን በፊቱ::

2. ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም – የእነሱ ግብ ጌታን ደስ ማሰኘት ብቻ ነው ሰውንማ ቢሆን ማስደሰት የሚፈልጉት ቀላል ነበር እኮ አለመስበክ ወይንም መሸቃቀጥ ለሁሉ የሚመች ማድረግ ነበር::

ወንጌልን ማገልገል የሚያካትተው ነገር:-

  • የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ – ያለ ስስት ሁሉን ሰተን ማገልገል ይጠይቃል ጌታ እኮ ዙፋኑን ጥሎየባርያን መልክ ይዞ ነው ያገለገለው::
  • ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና – በፍቅር ነው ሁሉንም መስጠት የሚቻለው

እንዲያውም በማንም እንዳይከብዱ እየሰሩ ራሳቸውንም ይችሉ ነበር::

ከዚህ የምንረዳው ጌታ የታመንን ሆነን ተቆጥረናልና ስናገለግል በፍቅር፥ እኛነታችንን በማካፈልና ባለመታከት መሆን አለበት::


ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ተጠርተናል

1ኛ ተሰሎንቄ 2:10-20


10፤ በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ 11-12፤ ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና። 13፤ ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።14፤ እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና። 15፤ እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥16፤ ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል።17፤ እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤18፤ ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን።19፤ ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? 20፤ እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።

በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ

  • ቅድስናና
  • ጽድቅ
  • ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተም እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ ይላል ጌታን ከአወቅን በብርሃን እንመላለስ እንዲህ ነው መመላለስ ያለብን:: በኑሮ ልንገልጠው ይገባል::

ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና። እኛ እኮ የተጠራነው ወደ መንግስቱና ወደ ክብሩ ነውና እንደሚገባ እንመላለስ::

እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥

በእውነት እንዳለ

በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ

እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ

እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት

እኛስ ዛሬ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚሰራ ቃል ተቀብለን ልንመላለስበት ይገባል::

ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና:: ወንጌል ወደኛ እንዳይደርስ ምን ያህል አይሁዶች እንደተከላከሉና እንዴት ያለ ዋጋ እየተከፈለ እኛጋ እንደደረሰ እናስተውል::

ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና። እኛም ላገለገሉን ክብር ያገለገልናቸው ደግሞ ለኛ ክብራችን ናቸው የምናገኘው ሽልማት በመምጣቱ ፊት ይህ ነው::


ምዕራፍ 3

ምዕራፍ 3 ንባብ

በመከራ ስለመጽናት

1ኛ ተሰሎንቄ 3: 1-4


1፤ ስለዚህ ወደ ፊት እንታገሥ ዘንድ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ።2፤ ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤3፤ በዚህ መከራ ማንም እንዳይናውጥ፥ ለዚህ እንደ ተመረጥን ራሳችሁ ታውቃላችሁና።4፤ በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንቀበል ዘንድ እንዳለን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፥ ይህንም ታውቃላችሁ።

ጳውሎስ ልንታገስ ባልተቻለን ጊዜ የእግዚአብሔርን አገልጋይ ጢሞቲዎስን ላክን:: ያሉበትን የእምነት ይዘት ያውቁ ዘንድ አንድ ሰው ንስሀ ገብቶ ብቻ መለቀቅ የለበትም ክትትል ያስፈልገዋል:: ህፃን ተወልዷል በቃ ብለን ትተነው ብንሄድ ምን እንደሚፈጠር ማሰብ አይከብድም:: እንዲሁ ጳውሎስ ቢችል እራሱ ይጎበኛል አብያተ ክርስትያናን አለዚያም አንዳቸውን ይልካል ያሉበትን አውቆ በርቱ አልያም ይህንን አስተካክሉ ለማለት::

ጢሞቴዎስን የላከው ስለ እምነታቸው:-

  1. እንዲያጸናችሁ – መከራ በዝቶባችኃልና እንደምናስባችሁ እንድታውቁ ደግሞም እኛም እራሳችን በዛው መከራ ውስጥ እንዳለን እንድታውቁ እንጂ በእናንተ ላይ ብቻ የመጣ መአት አድርጋችሁ አትውሰዱ ስለዚህም በርቱ:: ጌታ እየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር አጽናኝ እንደሆነ ይናገራል:: እርሱ እራሱ ህዝቡን ያጽናናል::
  2. እንዲመክራችሁ – መምከር የጌታ ስራ ነው እየሱስ ድንቅ መካር ነውና ደግሞም የምክር መንፈስን ይሰጣል ያጸናን ዘንድ::

በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ብሎ ጌታ እንቅጩን ነግሮናል:: ቃሉ ሲዘራ ምን አይነት መሬት ላይ እንደወደቀ እኮ ይፈተናል በቃሉ ደስ ብሏቸው ለጊዜው ፈተና ግን ሲመጣ የማንጸና መሆን የለብንም:: ስር ሰደን እንመላለስ ምንም አይነት ፈተና ወደ እኛ ቢመጣ እረኛችን አይተወንም! እንበርታ::


ለጌታ መኖር

1ኛ ተሰሎንቄ 3:5-8
5፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ፦ ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል፡ ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ።6፤ አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ የምስራች ብሎ በነገረን ጊዜ፥ እኛም እናያችሁ ዘንድ እንደምንናፍቅ ታዩን ዘንድ እየናፈቃችሁ ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስቡን በነገረን ጊዜ፥7፤ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤8፤ እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና።

እዚህ ጋር ጳውሎስን ያሳሰበው ነገር ከእምነት ተንሸራተው ይሆን ልፋታችንስ ከንቱ ሆኖ ይሆንን? ነበር ስጋቱ ለምን ብለን ብንል እምነትን ሊፈትን ቢሆንለትም ወደኃላ ሊመልስ ፈታኝ ይመጣል ከተሰማው ቃል የተነሳ:: ጠላት እኮ ሌላ ምንም ግብ የለውም ቃሉን ከማስጣል በስተቀር ምክንያቱም ቃሉ ከእኛ ጋር በእምነት ሲዋሀድ ነው የሚሰራው አለበለዚያ ካላሳደገን ቃሉን ተነጥቀናል ማለት ነው:: ፈታኝ ሁልጊዜ ይመጣል ከቃሉ በኃላ ስለዚህ የሙጥኝ ብለን ህያው ቃሉን በልባችንም እናሰላስለው የእግዚአብሔር ቃል የሚሰራ ህይወትም የሆነ መንፈስም ነውና:: እነዚህ ሰዎች በፍቅርና በእምነት ጸንተው ነበረ:: መጽናታቸውም እንዴት ጳውሎስን ደስ እንዳሰኘውና እንዳጽናናው እናያለን:: ምክንያቱም እርሱ ህይወቱን ለጌታ ሰቶ ለራሱ መኖር ያቆመ ሰው ነበር በሚሄድበት ሁሉ ግድ የሚለው የአብያተ ክርስትያናት ጉዳይ ነው:: በህይወት የመኖሬ ትርጉም የጌታ ስራ መሰራቱና እናንተ ስር መስደዳችሁ ነው ይላቸዋል::

ዛሬም እኛ በቃሉ ስር ሰደን በእምነትና በፍቅር እየኖርን ጌታን ደስ እናሰኝ ምርኮንም እንሰብስብለት የሚያሳስበንም ነገር የአካሉ ጉዳይ ሊሆን ይገባል:: ጌታ ጸጋውን ያብዛልን! አሜን


ለጌታ ቀን የተዘጋጀን እንሁን

1ኛ ተሰሎንቄ 3:9-13
9-10፤ ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላበት ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እየጸለይን በአምላካችን ፊት ከእናንተ የተነሣ ስለምንደሰተው ደስታ ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር በእናንተ ምክንያት ምን ያህል ምስጋና እናስረክብ ዘንድ እንችላለን?11፤ አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅና፤12-13፤ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።

ጳውሎስ ሊያያቸው የሚፈልገው ማድረግ ካለብኝ ነገር የጎደለ ይኖር ይሆንን? ነው ሁልጊዜ በጭንቅላቱ የሚመላለሰው ያለውን ሁሉ እናም የሚያውቀውን ሁሉ ሊያሳውቃቸው ነው:: ምን አይነት ትጋት ነው? ጸንተው ቆመዋል ተብሎ ሲሰማ ደግሞ ምስጋናውን ያበዛል ለጌታ::

ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት

  • በቅድስና
  • ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥
  • እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።

ልባችንን የሚያጸናው እርሱ ነውና እርሱን እንታመን እርሱም የታመነ ነው:: ዕለት ዕለት ፍቅራችን ያብዛ ይጨምርም::


ምዕራፍ 4

ምዕራፍ 4 ንባብ

መቀደስ

1ኛ ተሰሎንቄ 4:1-3
1፤ እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን።2፤ በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና።3፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤

እዚህጋ ጳውሎስ ያስተማራቸውን ሲደግምላቸው እናያለን:: እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንዴት እንድትመላለሱ ከፊት ይልቅ አብዙት እንጂ ደርሰናል ይበቃናል አትበሉ:: ይህንን ጨምሩ ወይም አስተካክሉ ሲል አናይም ያስተማራቸውን ትምህርቶች በደንብ ጠንቅቀው እየኖሩበት ነው ግን አሁንም ያስተማርናችሁን ያዙ ብሎ በመደጋገም ይነግራቸዋል:: በዚህ ዘመን ሰው ስህተት የሚገባው እኮ አጭር መንገድ ወይም የተሻለ ትምህርት እያለ ነው እዚህጋ የሚያሳየን ግን የያዛችሁትን እውነት አብዝታችሁ ጠብቁ ነው የሚለው:: ለዚህም ነው በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና አይለወጥም አንድ ጊዜ የሰበኩት እውነት ማሻሻያ የለውም እኔ ከጌታ ተምሬዋለሁና ስለዚህ ማንም የተለየ ወንጌል ቢሰብክ የተረገመ ይሁን የሚለው ቃሉ::

ማደግ ከፈለግን በግልጽ ፈቃዱ ምን እንደሆነ ለእያንዳንዳችን በማያሻማ መልኩ እዚህ ክፍል ላይ ተጠቅሷል:: የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ መቀደስ ስንል ሁለት አይነት ነው:: አንደኛው እየሱስ ክርስቶስን ወደ ህይወታችን በጋበዝን ጊዜ ሁሉን ክደን ለጌታ ተለየን ወይም ተቀደስን:: ይህ ቅድስና የጸና የማይዋዥቅ ነው:: ዕብራውያን 10: 10፤ በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። እንዲሁም ወደ ኤፌሶን 4: 24፤ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።

ሁለተኛው እና ጳውሎስ የሚያነሳው እዚህጋ በስጋችን መቀደስን ያሳያል :: በዚህ ዓለም እስከኖርን ድረስ ልንኖረውና ወደውጪ ወቶ ደግሞ መገለጥና መታየት አለበት:: ይሄኛው ቅድስና የመዋዥቅን ነገር እንዳያሳይ ሁልጊዜ በአእምሯችን መታደስ በመለወጥ ደህንነታችንን ዕለት ዕለት እንኖረዋለን:: 1ኛ ቆሮንቶስ 6: 18፤ ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።

ለጌታ እንቀደስ!


ከዝሙት መራቅ

1ኛ ተሰሎንቄ 4: 4-7
4-5፤ ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤
6፤ አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል። 7፤ ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።

እኛ ከዓለም የተለየን ለእግዚአብሔር የምንኖር ነንና በቅድስና እንጂ እግዚአብሔር እንደማያውቁ መመላለስ የለብንም:: እነርሱ በአምልኮ ስፍራዎቻቸው እንኳን ዝሙትን ለማድረግ አይከለክሉም እንዲያውም ይበረታታሉ እኛ ግን ለጌታ ተቀድሰናልና አንድ ሴት ለአንድ ወንድ እንዲሁም አንድም ወንድ ለአንድ ሴት በትዳር ትስስር ውስጥ ብቻ የሚፈጸም አልጋውም ንጹ ተብሎ የተመሰከረለት በእግዚአብሔር የተመሰረተ ሕብረት ነው:: ዝሙትን እንጥላ ደግሞም እንሽሽ!

ጌታ የማይመቸው አንዱ ነገር ማታለል ነው:: እርሱ እውነት ነውና እውነትን ይወዳል እኛም እውነትን እንከታተል:: ስናታልል እግዚአብሔር ለእውነት ይቆምና ተበዳይን ይክሳል ያጠቃነው ሰው ሲለመልም እናያለን ማለት ነው::

እናስተውል ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። ለክብሩ እንቀደስ:: አሜን!


የጌታን ምክር እንስማ

1ኛ ተሰሎንቄ 4:8-12


8፤ እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ።
9፤ እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤
10-12፤ እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን።

ይህንን ምክር የማይሰማ ጳውሎስን አይደለም የገፋው መንፈስ ቅዱስን እንጂ ስለዚህ ቃሉን በሙሉ ክብሩ ልንወስደው ይገባል::

መዋደድን ከእግዚአብሔር ተምራችኃል ይላቸዋል:: ምን አይነት ፍቅር ነው ከእግዚአብሔር የምንማረው ፍቅር? ሲበደል ይቅር የሚል፥ ሲራብ የሚያበላ እንጂ እሳት ሙቅና ሂድ የማይል፥ ሲረግም የሚመርቅ እንዲህ አይነት ነው ከሱ የምንማረው ፍቅር:: የወደደ ደግሞ በብዙ ይጠነቀቃል ለወገኖች እንጂ አታላይ አይሆንም ለዚህ ነው በመካከላቸው ያለው ፍቅር በተግባርም የተገለጠ የሆነው:: ይህም ፍቅራቸው ደግሞ በሌላ ስፍራ ሁሉ ተሰምቷል:

ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥

በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥

የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን።

ማን ስራ ፈት ሆኖ እራሱንና ቤተሰቡን የማይረዳ መሆን ይፈልጋል? መልሱ ማንም ነው:: ሳንሰራ ስራ ፈት ሆነን ወንጌልን እንስበክ ብንል እንዳንተ መሆን አልፈልግም ነው ሰው የሚለው:: በተቻላችሁ መጠን እራሳችሁን ቻሉ ሌላውን እርዱ ያኔ የሚታይ ፍቅር ሲኖር ወንጌልም ሰሚ ያገኛል እያላቸው ነው:: በውጭ ባሉት ዘንድ በአግባብ እንመላለስ::


በጌታ እንጽናና

1ኛ ተሰሎንቄ 4:13-18


13፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን።
14፤ ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። 15፤ በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ 16፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ 17፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። 18፤ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።

ጌታ ከሙታን ተነስቷልና በእርሱ አምነው ያንቀላፉትም ይነሳሉ:: እኛ ተስፋ የሌለን አይደለንም በእርግጥ ልብን ያሳዝናል የምንወደውን ሰው በሞት መነጠቅ ግን እንደማያምን ለዘላለም እንደማናያቸው አድርገን ማየት የለብንም:: እኔ በራሴ ወደጌታ የሄዱ በጣም የምወዳቸው ሰዎች አሉኝ የምጽናናው ግን ሌላ አገር እንዳሉና አንድ ቀን ሄጄ እንደማያቸው ነው:: እንጽናና በዚህ ቃል! መንፈስ ቅዱስንም አናማርር!


ምዕራፍ 5

ምዕራፍ 5 ንባብ

የብርሃን ልጆች ነን

1ኛ ተሰሎንቄ 5: 1-11


1፤ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ 2፤ የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። 3፤ ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም። 4፤ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥
5፤ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤ 6፤ እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ። 7፤ የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፥ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤ 8፤ እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤ 9፤ እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።. 10፤ የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ።. 11፤ ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው።

ለምን ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም ይላል? ማወቅ የለብንም እንዴ? አያስፈልገንም ምክንያቱም ሁልጊዜ የተዘጋጀን መሆን ስላለብን:: ጳውሎስ ብቻ አይደለም ይህንን ያለው እራሱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስም ብሏል:-

የማቴዎስ ወንጌል 24: 36፤ ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።

የሐዋርያት ሥራ 1: 7፤ እርሱም አለ፦ አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤

ሌላው ምክንያት ማወቅ የማያስፈልገን በብርሃን ውስጥ እየኖርን ነንና ማንም ስራው ትክክል ቢሆን ወደ ብርሃን እንደሚያመጣ ለማስፈተሽ እንዲሁ ኑሯችን በብርሃናት አባት በጌታ ፊት እየኖርን ስለሆነ ነው እንጂ እኛ በጨለማ የምንደናበርና የምንሄድበትን የማናውቅ አይደለንም:: እንደሌባ የሚሆንባቸው አመጣጡ በጨለማ ለሚመላለሱት ነው:: ለእኛ ግን ቀኑንና ወራቱን አወቅን አላወቅን ለውጥ የለውም የምንኖረው እኮ አሁን ከእርሱጋር ነው:: አሜን!

እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን እንዴት እንመላለስ ወይም ሊያሳስበን የሚገባው ነገር ምንድነው?!

  1. በመጠን እየኖርን በዚህ ላይ ደግሞ
    1. የእምነትንና
    2. የፍቅርን ጥሩር
    3. የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንልበስ
  2. እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።. እኛ የምንሸበር አይደለንም ምክንያቱም ቁጣ የለብንም አንድ ጊዜ የራሱ ልጆች አድርጎናል::
  3. የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ።. (ሞተንም ወደ እርሱ ብንሄድ ወይም በህወት እየኖርን ቢመጣና በደመና ብንቀበለው ለእኛ ለውጥ የለውም ከእርሱ ጋር እየኖርን ነውና ስለዚህ በዚህም ሆነ በዛ በዛች ቀን በደስታ እንገኛለን)
  4. ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው። የተሰጠን አገልግሎት መተናነጽ ነው::

እምነት፥ ፍቅር እና ተስፋ ጸንተው ይኖራሉ!

ማራናታ


የቤቱ ስርዓት

1ኛ ተሰሎንቄ 5: 12-14
12-13፤ ወንድሞች ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ።
14፤ ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።

በጌታ ቤት የሚያገለግሉትን አገልጋዮች ማወቅና ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን:: ግን እውነት እንነጋገርና በዚህ ዘመን የቤተክርስቲያን መሪዎች ይከበራሉ? እንደኔ እንደኔ የተመታ አገልግሎት ነው ባይ ነኝ ምክንይቱም ሁሉ ለራሱ መሪ ሆኖ እየተመላለሰ ያለበት ዘመን ነውና የአገልግሎቱንም ውጤት ስናየው እንደዛው የተመታ ሆኗል:: መሪ የሌለው ሰራዊት እንዴት ድል ያደርጋል?! ለጠላት ጥቃት በቀላሉ የተጋለጠ እንጂ ድልን ማሰብ ሞኝነት ይመስለኛል:: በሌላው ጎን ስናየው ደግሞ አንዳንድ መሪዎች ያላቸውን ሁሉ ሰተው ለማገልገል የሚፈሩም ያሉ ይመስለኛል:: ያላቸውን ሁሉ አውጥተው ካገለገሉ ምዕመናቸው አይመለስም አኩርፎ ይቀራል ወይም ሌላ ቤተክርስቲያን ይሄዳል እዛም አይጠቅም ወይ አያሰራ አይነት እንቅፋት ይሆናል:: ይሄንን ለማስተካከል ቀላል ያልሆነ ቁርጠኝነት ይጠይቃል ደግሞም እያንዳንዳችንን ይመለከታል:: ለምን ግን በፍቅር ከመጠን ይልቅ አክብሩዋቸው ተባልን?!

  1. የሚደክሙትን :- እውነተኛ አገልጋይ ጌታን በእኛ ለማየት ይደክማል፥ ያለውንም ሁሉ ሰቶ ያገለግላል፥ በምላሹ ምንም ባለመጠበቅ በነፃ የተሰጠውን በነፃ በመስጠት ይደክማልና::
  2. በጌታም የሚገዙአችሁን:- መሪዎችን ጌታ ይሾማል (በእርግጥ እራሳቸውንም የሚሾሙ ይኖራሉና) ፍሬያቸውን እያየን፥ ለቤቱ የሚያደርጉትን ድካም እያየን እንገዛ ከጌታ ተሹመዋልና::
  3. የሚገሥጹአችሁንም:- እውነትን በፍቅር በመያዝ ለሚገስጹን ጆሮ እንስጥ:: አጥፍተን ለምን ተገሰጽን ብለን አናፈንግጥ ትክክለኛ ተግሳጽ ያቀናልና::

እርስ በእርሳችን እንደ አካል ለመኖር እንዴት እንመላለስ?

  1. ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው:- ከላይ እንዳየነው መገሰጽም የአገልግሎት አካል ነው ግን ለተወሰኑ ሰዎች ግን የተተወ አይደልም የሁላችንም ኃላፊነት ነው:: ስርዓት ከሌለ በቅጡ የቤቱን ስራ በአንድ ወጥ መስራት ያስቸግራልና::
  2. ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው
  3. ለደካሞች ትጉላቸው፤
  4. ሰውን ሁሉ ታገሱ
  5. በሰላም ሁኑ

ጌታ በስራ ላይ እንዳለ እንወቅ፤ እናስተውል፤ እንፍራው፤ አንዳፈር ልክ እንደው እንደወደድን አንመላለስ እርሱን ደስ ለማሰኘት ከሆነ እንግድያስ እንደቃሉ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳናችንን እንፈጽም:: ጌታ ወደቤቱ የጠራው የተለያየ አይነት ሰው ነውና ሁሉንም በፍቅር፤ አንዳች የምማረው አለ በማለት ዝቅ ባለ ልብ እየተቀባበልን ልንመላለስ ይገባል::

የጌታ ጸጋና ማስተዋል ይብዛልን!


ምክር

1ኛ ተሰሎንቄ 5: 15-28


15፤ ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።
16፤ ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤. 17-18፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።
19፤ መንፈስን አታጥፉ፤ 20-21፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤
22፤ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ።
23፤ የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። 24፤ የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል። 25፤ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ። 26፤ ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። 27፤ ይህ መልእክት ለቅዱሳን ወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አምላችኋለሁ። 28፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።

እንደ ክርስቶስ ተከታዮች ጳውሎስ ይህን ይመክረናል:-

  1. ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።በሌላ ስፍራ ላይ በተለይ ለቅዱሳን ይላልና እርስ በእርሳችን እንረዳዳ:: ግራህን ለሚመታህ ቀኝህን ስጠው ብሎ አስተምሮናል ጌታ እየሱስ::
  2. ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ:- ደስታን የምናውቀው ለሆነልን መልካም ነገር የምንገልጽበት ስሜት ነው በሚል ነው እዚህ ክፍል ላይ ግን ትዕዛዝ ነው ምንም ይሁን ምን የከበበን በጌታ ነው ደስታችን መሆን ያለበት በሚያልፍበት ነገርና ሁኔታማ ቢሆን ኖሮ እንጉርጉሮ አውጡ ነበር ማለት የነበረበት ጳውሎስ ግን ደስ ይበላችሁ ይለናን:: መቼ ደስ ይበለን? ሁልጊዜ:: አሜን!
  3. ሳታቋርጡ ጸልዩ:- ጸሎት ለእኛ ስንበረከክ የምናስበው ሳይሆን የኑሮ ዘይቤያችን ነው ልክ እንደመተንፈስ:: ጌታ ሲያገለግል ይውልና ለሊቱን ሲጸልይ ያድራል ከሱ ይህንን ተምረናል::
  4. በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። በሁሉ አመስግኑ? ከባድ አይመስልም? ከባድ ነው ግን ያስጨነቀንንና የፈራነውን እያሰብን ወደ ጌታ ቀና ስንል ከማመስገን ሌላ ምን የሚቀርልን አለ? ሁሉ በእርሱ ፊት ኢምንት ነው:: በምንም ውስጥ እያለፍን እያለን እስኪ ማመስገን እንጀምር የእግዚአብሔር ጸጋ ያስረሳናል ደግሞም ብቃት ይሰጠናል:: እሳቱ አያቃጥልም ውሀውም አያሰጥምም ከጌታ ጋር ስንሆን የሚቀየረው ውሀው ወይም እሳቱ ሳይሆን እኛ ነን:: እሳቱ ሌላውን ሲያቃጥል ለእኛ ደግሞ የአምልኮ ቦታ ይሆናል:: ብናማርርና ብናጉረመርምስ? ነገሩን ጥሩ አድርጎ ጠላት እያጠበቀ ወደባሰ መከራ ነው የምንገባው ብናመሰግን ግን የምንጠቀመው እኛው ነን:: እናመስግን አምላካችን ትልቅ ስለሆነ::
  5. መንፈስን አታጥፉ፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ:- ትንቢትን በእግዚአብሔር ቃል እናበጥር እንጂ ትንቢትን አናርቅ ምክንያቱም እንድንጽናናበትና እንታነጽበት ዘንድ ተሰቶናልና እንጠቀምበት::
  6. ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ። የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። ደስ አይልም እኛን የሚቀድሰው እርሱ እራሱ ነው የኛ ድርሻ ራሳችንን ወደ እርሱ ማቅረብ ነው:: ለዚህም ነው ስለመምጫው ቀን መጨነቅ የሌለብን ቀድሶ እርሱ ያቆመናልና ምክንያቱም የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል ይለናል:: እኛ የብርሃን ልጆች ነን ከክፉ ጋር ህብረት የለንም:: ስለዚህ ሁለንተናችን (መንፈሳችን፤ ነፍሳችንና ስጋችን) ይቀደሳል ማለት ነው በስጋዬ እንደፈለኩኝ ልኑር ብሎ ነገር የለም::
  7. ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ። ጌታ እንደረዳን እርስ በርስ እንሸካከም በተለይም ስለአገልጋዮች እንድንጸልይ ያስፈልጋል እየተጠየቅንም ነውና እንጸልይ::
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።


በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ

ወደ ሮሜ 12
2፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።

መለወጥ ማለት ምን ማለት ነው? ሁላችንም መለወጥና ጌታን ደስ ማሰኘት እንፈልጋለን:: ግን እንዴት?!

የማርቆስ ወንጌል 6
35፤ በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤36፤ የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው፡ አሉት።37፤ እርሱ ግን መልሶ፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው፡ አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት።38፤ እርሱም፦ ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ፡ አላቸው። ባወቁም ጊዜ፦ አምስት፥ ሁለትም ዓሣ፡ አሉት።39፤ ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው።

ታሪኩን እናውቃለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ለአምስት ሺህ ሰዎች ተመግበው አስራ ሁለት መሶብ እንደተረፈ እናውቃለን:: ይህ እንዴት ሆነ? ጌታ እኮ አመስግኖ አምስቱን እንጀራ ለአስራ ሁለት አካፍሎ መሶባቸው ላይ ከግማሽ እንጀራ ያልበለጠ ነው እንዲያድሉ የደረሳቸው ሐዋርያቱ:: እስኪ እዚህጋ ቆም ብለን እናስብ አምስት ሺህ ሰው ለመብላት ቁጭ ብሎ ይጠብቃሉ ሐዋርያቱ እጅ የገባው እንጀራ ደግሞ ቁራሽ ነው:: እናስተውል ጌታ ወደ ሰማይ አይቶ ባርኮ ሲሰጣቸው መሶቡን ሞልቶ ፈሰሰ አይለንም ወይም ደግሞ ከክብደቱ የተነሳ አንገዳገዳቸው ወይም ይህንን የመሰለ ነገር አልተጻፈም ስለዚህ ሐዋርያት እየተያዩ እንግዲህ ፊታችን ላለው ሰው ሰተን እንመለስ ብለው ለማደል ተነሱ::

እኔና እናንተ ምን እናደርግ ይሆን? ከነሱ የተሻለ ምክር አንመክርም ቁራሽ ለማቃመስ እንኳን ከባድ ነው ብዙ ገንዘብም ይጠይቃል ብለን እንደመድም ነበር:: ምክንይቱም አእምሮአችን የለመደው የራሱ የአስተሳሰብ ዘይቤ አለ ህብረተሰቡም በዙሪያችን ያለው የተፈጥሮ እውነት ወደ አንድ አቅጣጫ ነው የሚመሩን ስለዚህ እሱን ብቻ ነው የምንከተለው ከዚህ ወጣ ካለብን ይከብደናል ወይም ስህተት ነው እንላለን::

ጌታ እየሱስ የሚያደርገውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ነበር ፊልጶስን የጠየቀው:: ያንን ቁራሽ እንጀራ እፊት ላለው ግለሰብ ሰተው ተመልሰው ለመቀመጥ ነበር የሄዱት ሐዋርያት ግን ልክ ሰተው ዞር ሲሉ የሚቀጥለው ቁራሽ ይቀመጥ ነበር መሶቡ ላይ:: ታድያ በአስተሳሰባችንን ካልተለወጥንና ጌታ እንደሚያይ ካላየን እመኑኝ ተአምራትን የማየት ተስፋችን የተመናመነ ነው በሌላ አባባል ከባድ ነው የሚሆንብን:: ስለዚህ ነገሮችን ጌታ እንደሚያይ እንይና ቃሉን ስናነብ ከቃሉ ተአምራትን ለማየት ይሁን:: ስንት ነገር ላይ እንድንወጣና እንድናደርግ ጌታ ተናገረን ብለን ቁራሽዋ እንጀራ ስትሰጠን ምን ትሰራለች ኢቺ ብለን የእንጀራ ክምር ለምንጠብቅ ሁሉ ይህ የአእምሮ መለወጥ ካልገባን በስተቀር ችግር ላይ እንደሆንን እንወቅ:: ተአምራትንም ማየት ሆነ ጌታንም በቅጡ ማገልገል ይከብደናል:: አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ካላስቀመጥን በስተቀር ይፈነዳል:: እጅ የምታክለው ደመና ምን አይነት ዝናብ እንደወጣው እናውቃለን እኛም እንደዚሁ ጌታ የሚሰራውን ለማወቅ አስተሳሰባችን መለወጥ አለበት:: ሐዋርያት ይህንን የሚያክል ተአምር ቢያዩም እንኳን በማርቆስ ወንጌል 6: 52 ላይ ቃሉ ‘ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።’ ይላል ስለዚህ የእግዚአብሔር ጉብኝት አይለፈን ልባችንን በመንገዳችን ላይ እናድርግ::

እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!

2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች

መግቢያ

የዚህ መጽሐፍ ዓላማ

  1. ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ዘመን አስተምሯቸው ነበርና:-
    1. መጨረሻው ዘመን አሁን ነው በማለት ደምድመዋው ነበር ከመከራቸው የተነሳ
    2. ከስራቸው በመልቀቅ ስራ የማይሰሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ
  2. የጻፈውም ጳውሎስ ሲሆን በአገልግሎቱ አብረውት ወደዛ ሄደውም የነበሩትን ስልዋኖስንና ጢሞቴዎስን ይጠቅሳል
  3. ይህች ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው በሐዋርያት ሥራ 17 መሰረት በሁለተኛው የጳውሎስ የወንጌል ጉዞ ላይ ነበር::  ስትመሰረትም ብዙ ተቃዋሚዎች ነበሯት ሌላ ንጉስ አለ ብሎ የሮምን ሕግ ጥሷል በሚል ክስ ተነስቶ ነበር::  የቤተክርስቲያኒቷም ምዕመናን በብዛት አሕዛብ ናቸው::
ምዕራፍ 1 ንባብ

ምዕራፍ 1

ፍቅራችንና እምነታችን ይጨምር

2ኛ ተሰሎንቄ 1:1-4
1፤ ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤2፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን።3፤ ወንድሞች ሆይ፥ እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ ስለሚበዛ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን፤4፤ ስለዚህ በምትታገሱበት በስደታችሁና በመከራችሁ ሁሉ ከመጽናታችሁና ከእምነታችሁ የተነሣ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን።

ትልቁ የዝች ቤተክርስቲያን በመከራ ውስጥ የመጽናትን ሚስጥር ብንመረምር ፍቅራቸው፤ መጽናታቸውና እምነታቸው ነበረ:: እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ ስለሚበዛ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን፤ የሚገርመው ነገር እምነት የሚያድግ ነው ምክንያቱም ትላንትናን በመከራ ያሻገረን ዛሬም ያሻግረናል ብለው በማለት እምነታቸው እያደገ ሄዷል:: ሌላው የርስ በርስ ፍቅራቸው ደግሞ እየበዛ ነው የሄደው::  በመጽናታቸው ምክንያት ምስጋና በዝቷል ለእግዚአብሔር:: ይህም በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን ይላቸዋል::  በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ በመቆማችሁ ተመክተናል ለሌሎችም ምሳሌ ሆናችኃል እያለ ነው::

ዛሬ በህይወታችን ምን የሚታይና የሚያስመሰግን ነገር ይኖር ይሆን?  ዕለት ዕለት ፍቅራችንና እምነታችን እያደገ መሄድ አለበት እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።  ስለዚህ እምነታችን በስራም መገለጥ አለበት ልክ እንደ ተሰሎንቄ ሰዎች እርስ በርሳቸው መዋደዳቸው ሚስጥሩ በስራ የተገለጠ እምነት የመኖሩ ጉዳይ ነው::  ወንድማችን ተቸግሮ ብናይ የሚረዳ ፍቅር ሊኖረን ይገባል::   እንደዚህ እምነታችን ሊያድግ ይገባዋል ማለት ነው:: በምንም ነገር ውስጥ ብናልፍ እንኳን እረኛችን ከእኛ ጋር ነውና እንጽና እርሱ የታመነ ነውና ያሻግረናል::  አሜን!


ብድራትን እንቀበላለን

2ኛ ተሰሎንቄ 1:5-8

5፤ ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቈጠሩ ዘንድ፥ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው።6-7፤ ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።8፤ እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤
መቼም በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ብሎ እንቅጩን ነግሮናል ጌታ ስለዚህ እንደው አንዳች እንደደረሰብን አድርገን እራሳችንን አናስጨንቅ የሚረዳንን ጸጋ እንጠይቅ::  እዚህጋ ጳውሎስ ከአሳዳጅነት ልምዱ ነው የሚነግራቸው እርሱን እየመሰላችሁ ከተከተላችሁት መሰደድ አይቀሬ ነው ምክንያቱም የጸኑትን መንቀል ያልጸኑትንም ይነቅላልና::  እርሱ ሲያሳድድ የነበረው ከመለወጡ በፊት እንደነዚህ አይነት ምስክርነት ያላቸውን ነበርና::  ስለዚህ እዚህጋ እያለ ያለው የህይወት ፍሬ ቢታይባችሁ ነው መከራው የበዛው በርቱ ጌታ ይመጣል::  ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ የሚሆነው:-

1.  መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ 

2.  መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።

3.  እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤


ለእኛ ዕረፍትን ይሰጠናል የአባቴ ብሩካን ወደ እረፍታችሁ ግቡ ብሎ ስለዚህ:- ይህ ቀን በእርግጥ እንዲመጣ አውቀን እንጽና::  መቼም እየደረሰብን ያለው ፈተና እዚህጋ ከምናነበው ለየት ያለ የዘመነ ነው::  እናስተውል ሁሉ ያልፋልና ጸንተን ጌታን እንጠብቅ:: ጌታ በእርግጥ ይመጣል!!የበደሉንም ሆኑ ያልተቀበሉትን ጌታ ይበቀላል ከዚህ ጥፋት ከእግዚአብሔርም ቁጣ አምልጠናልና ጌታን እናመስግን::

ማራናታ!!


ስሙ በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ

2ኛ ተሰሎንቄ 1:9-12

9-10፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።11-12፤ ስለዚህም ደግሞ እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥ አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ የእምነትንም ሥራ በኃይል ይፈጽም ዘንድ ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን።

በመስቀል ላይ ዋጋ እየከፈለ ሳለ አሻግሮ ፍሬውን እኔን/አንተን/አንቺን ያይ ነበር ጊዜው ደርሶ ሊወስደን ሲመጣ ደግሞ ይገረምብናል:: ደስ አይልም ፍሬውን አይቶ ማመን አቅቶት ሲገረም በእኛ? ወይ ያ ቀን ምን አይነት ቀን ነው ጌታ እየተገረመ የሚያስተናግደንና የሚደነቅብን? አረ በደስታ እጠብቀዋለሁ ቅዱሳን ከሚለው ማኅበር የቀላቀለኝን ጌታ:: ዛሬ በዙሪያዬ ያለው ሰልፍ ምንድነው? ከዛ ክብር ጋር ሲወዳደር?! ምንም እንዳልሆነ እንቀዋለሁ::

ዛሬም እላለሁ ማራናታ!

በሌላው በኩል ደግሞ:- እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።
ዛሬ ቀን ሳለ ለዚህ ጥሪ መልስ የማይሰጥ በዘላለም ጥፋት ይቀጣል። ለዘላለም ከጌታ መለየት ጥርስ ማፋጨትና መቆጨት ነው የሚሆነው:: እኛ የክርስቶስ ወንጌል የገባን ወንጌሉን ለማድረስ እንሩጥ:: በምድር የመቆየታችን ትልቁ ዓላማ እንደነዚህ ያሉትን እንድንታደግ ነውና ጸጋው ይረዳናል ወጥተን የጠላትን ደጅ ወርሰን የጌታን አዳኝነት እናውጅ:: ጌታ የሟቹን ሞት አይወድምና ሁሉም እንዲድኑ ይፈልጋል::

እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ (እናስተውል በጸጋው ነው)

  1. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር
  2. እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥
  3. አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ ስለ እናንተ ሁልጊዜ ይህንን እንጸልያለን ይላል:-

እኛም ይህንን ለራሳችንም ለቅዱሳንም ሁሉ እንጸልይ:-

  1. የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ በእኛ እንዲሞላ
  2. የእምነትንም ሥራ በኃይል ይፈጽም ዘንድ – በእኛ መስራት የጀመረውን እንዲፈጽም::

አሜን ይሙላን የጀመረውንም ይፈጽም!!


ምዕራፍ 2

ምዕራፍ 2 ንባብ

እውነትንና ፍቅርን እንከታተል

2ኛ ተሰሎንቄ 2:1-12


1-2፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል፡ ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን።3፤ ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና።4፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው።5፤ ገና ከእናንተ ጋር ሳለሁ፥ ይህን እንዳልኋችሁ ትዝ አይላችሁምን?6፤ በገዛ ራሱ ጊዜም ይገለጥ ዘንድ፥ የሚከለክለውን አሁን ታውቃላችሁ። 7፤ የዓመፅ ምሥጢር አሁን ይሠራልና፤ ብቻ ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ አሁን የሚከለክል አለ።8፤ በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል፤9-10፤ ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው።11-12፤ ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።

እየሱስ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ሁለት ነገሮች መሆን አለባቸው:-

  1. ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና።
  2. እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው።

ስለዚህ እነዚህ ምልክቶች ከመሆናቸው በፊት አይመጣምና አንናወጥ ደግሞም አንዘናጋ:: ብዙ ዓመት በፊታችን እንዳለ እናቅድ አንድ ቀንም እንደቀረው የተዘጋጀን እንሁን:: ጌታችን ሲመጣ በአፉ እስትንፋስ የሚያጠፋው እንደሆነም እንገንዘብ አሁንም እየሰራ ያለ ግን እንደወደደ እንዳይገለጥ እየተከለከለ ነው:: ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት:-

  • በተአምራት ሁሉና
  • በምልክቶች
  • በሐሰተኞች ድንቆችም
  • በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። ውስጣቸው ለክፋት የተከፈተ ነው:: የሚያምኑትንም እንኳን የሚያስት ነውና ስር ሰደን በቃሉ እንኑር:: ማንም እንዲጠፋ እግዚአብሔር አይፈልግም::

ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል። ሰው እውነትን በገፋ መጠን ለስህተት አሰራር በራሱ ሀሳብ ተስቦ ባርያ ይሆናል ስለዚህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ እንደሚል ቃሉ ውስጣችንን በዚህ እንሙላና እውነትንና ፍቅርን እንከታተል::


ጸንታችሁ ቁሙ


2ኛ ተሰሎንቄ 2:13-17


13፤ እኛ ግን፥ በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፥ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤14፤ ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ።15፤ እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ።16-17፤ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የወደደን በጸጋም የዘላለምን መጽናናት በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ።

እነዚህ ሰዎች ምስጋናን ለእግዚአብሔር እንዲበዛ አድርገዋል:: እኛ ግን፥ በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፥ ለምንድነው ለማመስገን ግድ የሚላቸው?

እግዚአብሔር :-
– በመንፈስ መቀደስ
– እውነትንም በማመን
– ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤
– በወንጌልም ጠርቷችኃልና
እናንተም ጸንታችኃልና ስለዚህ እናመሰግናለን ይላቸዋል::

ስለዚህ በዚህ መዳን እንዴት እንኑር:-
እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥

  1. ጸንታችሁ ቁሙ፥ ባለመናወጥ
  2. በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ እንድትጸኑ::

ይህንን ያወቅነውን እውነት ይዘን ለሚደርስብን ስደት ማን ይረዳናል ብለን ብንል:-
ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የወደደን፥ በጸጋም የዘላለምን መጽናናት፥ በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ። አሜን!

በነገር ሁሉ የሚረዳ ጌታ አለን በእርሱ ላይ እንደገፍ ሊረዳን የታመነ ነው:: በውጣ ውረዱ ሁሉ ያጸናናል ይታደገንማል በራሱ አሰራር:: ማጽናትና ማጽናናት ብቻ ሳይሆን በዚህ ዓለም ስንኖር በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ይደግፈናል::


ምዕራፍ 3

ምዕራፍ 3 ንባብ

ጌታ የታመነ ነው

2ኛ ተሰሎንቄ 3:1-5


1-2፤ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጌታ ቃል እንዲሮጥ በእናንተም ዘንድ ደግሞ እንደሚሆን እንዲከበር፥ እምነትም ለሁሉ ስለማይሆን ከዓመፀኞችና ከክፉዎች ሰዎች እንድንድን ስለ እኛ ጸልዩ።3፤ ነገር ግን የሚያጸናችሁ ከክፉውም የሚጠብቃችሁ ጌታ የታመነ ነው።4፤ የምናዛችሁንም አሁን እንድታደርጉ ወደ ፊትም ደግሞ እንድታደርጉ ስለ እናንተ በጌታ ታምነናል።5፤ ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው።

የጸሎት ርዕስ ይሰጣል ጳውሎስ የጌታ ቃል እንዲሮጥ እንዲሁም ደግሞ በእናንተም ዘንድ እንደተከበረው በሌላም ስፍራ እንዲከበር:: የጸሎት ርዕሱ ስለራሱ አይደለም ስለጌታ መንግስት እንጂ ይሄ ነው ጳውሎስን በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ እንዲጸና ያደረገው እራሱን አለማየቱ እንጂ እኮ ተስፋ ቆርጦ በቃኝ ይል ነበር:: ከክፉ ሰዎች ሰይጣንም እየነዳ ከሚያመጣብን እንድንጠበቅ ጸልዮ ይላል:: ጌታም እኮ ይህንን ብሎናል ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ:: አይደል ለራሳችንም ለቅዱሳንም መጠበቅ እንጸልይ::
ጌታ የታመነ ነው

  1. ያጸናናል – እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ እንደሚል ጌታ የታመነ ነው ማንም ያላየውን አይቶ ጣልቃ ይገባል ስለዚህ ሁልጊዜ አይናችን በእርሱ ላይ ይሁን በሚያጸናን ላይ::
  2. ይጠብቀናል– ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። ብሎ ጌታ ስለእኛ ማልዷል:: እርሱ ሊጠብቀን የታመነ ነው::

የተሰሎንቄ ሰዎች ልብ የሚጣልባቸው ነበሩ አሁንም ሆነ ወደፊት የምንላችሁን ትታዘዛላችሁ ይላቸዋል እኛም ዛሬ የምንሰማና የምንታዘዝ እንሁን::

ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና እንደሚል:- ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው። ለሰው ከባድ የሆኑ ነገሮች ቢኖሩ ያለምክንያት መውደድና የበዛ ትዕግስት ናቸው:: እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪልክ ዓለምን ምንኛ እንደወደደ እንገንዘብ:: ክርስቶስ በመስቀል እንዴት እንደታገሰ እናስብ:: እኛ አንችልም ይህ ግን በውስጣችን ያለው የጌታ መንፈስ ፍሬ ነውና እርሱ ራሱ በእኛ ውስጥ ይፈጥረዋል:: አሜን ልባችንን ያቅና::


የእግዚአብሔር ቤት ስርዓት አለው

2ኛ ተሰሎንቄ 3:6-18
6፤ ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።7፤ እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ ራሳችሁ ታውቃላችሁና፤ በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዓት አልሄድንምና፤8፤ ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፥ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም።9፤ ይህም እኛን ልትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁ ዘንድ ነበር እንጂ፥ ያለ ሥልጣን ስለ ሆንን አይደለም:: 10፤ ደግሞ ከእናንተ ጋር ሳለን፦ ሊሠራ የማይወድ አይብላ፡ ብለን አዘናችሁ ነበርና።11፤ ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና።12፤ እንደነዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን እንመክራቸውማለን።13፤ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ።14፤ በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ተመልከቱት፥ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ።15፤ ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት።16፤ የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።17፤ በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው፤ የመልእክቴ ሁሉ ማስረጃ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ።18፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

የእግዚአብሔር ቤት ለሁሉ ነገር ስርዓት አለው እንዴት ህይወታችንን መምራት እንዳለብን ቃሉ ይመክረናል:: ቃሉን ካላወቅን ግን ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል እንደሚለው እንዳይሆንብን ቃሉ በሙላት በእኛ ዘንድ ይገኝ:: ይህንን የእግዚአብሔርን ቤት ስርዓት ከማይከተሉ ጋር እንዴት እንኑር ብለን ያልን እንደሆነ መለየትና አለመተባበር ብቻ ነው የሚያዘን:: መለየትን ወይም ደግሞ አለመተባበርን ስናስብ ጠላትነት ማለት እንዳልሆነ እንገንዘብ:: ስንለይ ይህ ሰው ተምሮና ተስተካክሎ እንዲመለስ ነውና በፍቅርና በየዋህነት ገስጸን እናቅና::

የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። አሜን

ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን!



ወደ ገላትያ ሰዎች

መግቢያ

የዚህ መጽሐፍ ዓላማ

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ጳውሎስ ነው
1. ክርስትናንና አይሁዳዊነትን እየቀላቀሉ ስለነበር
2. ከእምነት በምን አይነት ፍጥንት እንደራቁ ስለተገነዘበ
3. ፀጋን/ጽድቅን ከስራ ጋር በመቀላቀላቸው
4. መዳን በፀጋ መሆኑን ሊያሳያቸው

ምዕራፍ 1

ምዕራፍ 1 ንባብ

እኔን የጠራ ጌታ ነው

ወደ ገላትያ 1: 1-2፤

በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤

እዚህ ጋር ጳውሎስ ሊያሳያቸው የፈለገው ማን እንደላከው ነው::  በእግዚአብሔር ነው ሐዋርያ የሆንኩት እርሱ ነው የጠራና የላከኝ እያላችው ነው::  ለምን ብለን ስንል ባለው ስልጣን መሰረት የሚናገረውን ሁሉ ከዚህ በኃላ ከእግዚአብሔር የተላከ መልእክት አድርገው እንዲወስዱት እንጂ ይህ የጳውሎስ ሀሳብ ነው እንዳይሉ ነው::

እርሱ ብቻም አይደለም አብረውትም የሚያገለግሉ ወንድሞች ሁሉ ያመኑበትን ነገር እየጻፈላቸው እንደሆነ እየነገራቸው ነው::  ስለዚህ ብትቀበሉ ይሻላል መልክታችንን ብሎ ነው የሚላቸው:: 

ከዚህ የማየው ነገር;- እኔን የጠራ ጌታ እንደሆነና ዋጋ የክፈለና የራሱ ያደረገኝን ጌታን አገልግለውና  ለእርሱም  የምገዛ፤  ደስ የማሰኘው ልጅ መሆን ነው የእኔ ድርሻ:: ስሙ ይባረክ::  አሜን!


ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ

ወደ ገላትያ 1:3-5

ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። 
1.  ”ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ”
እኔ እኮ ብዙ አተኩር የነበረው በመዳኔ ላይ ከሲኦል ማምለጤን ነው ለካስ ከዛ በፊት ያመለጥኩት ከዝች ክፉ ዓለምም ነው::  ለዚህም ነው ለካ ዓለምን  መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። የሚለው!  በሌላ ስፍራም በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።  ለዚህ አለቃ ነበር ስታዘዝ የኖርኩት አሁን ግን በእኔ ላይ አይሰለጥንም ከእርሱ አገዛዝ ድኛለሁ አለቃዬ አዳኜ ነው::  አሜን!!

2.  ”እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ”
እየሱስ እንደማን ፈቃድ ነው ራሱን የሰጠው? እንደ አባታችን ፈቃድ እርሱ ነበር ያቀደው መዳናችንን እናም ሳይሳሳ አንድ ልጁን የሰጠኝ::  
ሰጠኝ ብዬ ስል እንደው ቀለል አለብኝ የሰጠኝ እኮ እየሱስ ህይወቱን ነው እርሱም በመስቀል ሞት ለመሞት!  ለመሰቃየት!  ትንሽ ጻድቅነት ቢኖረኝ እንኳን እሺ ግን እልም ያልኩኝ ሐጥያተኛ ለሆንኩት ለእኔ?! ዋዉ!  ቃሉ እኮ በትክክል ቁጭ አድርጎታል  በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ የሚለው!  አዎ ሙታን ነበርኩ ዛሬ ግን ያ ሁሉ ነገር አልፎ አዲስ ፍጥረት ሆኛለሁ በህይወት አለሁ ከወይኑ ግንድ ላይ ተጣብቄ::  ሃሌሉያ!

3.  ”ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” ሌላ ምን ይባላል ውለታው ብዙ ነው::   ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን። አሜን!!


በክርስቶስ ጸጋ ተጠርተናል

ወደ ገላትያ 1: 6፤ 

በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ 
1.  በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ 
በቃሉ እንደሚለው ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።  በሌላም ስፍራ ላይ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥ ክብር የጎደለኝ ነበርኩ በዚህ ጸጋ ግን ተጠራሁኝ፤ ጸደኩኝ ፤  የእግዚአብሔርም ወገን ሆንኩኝ ይህንንም ጸጋ ተቀበልኩኝ::  ይህም ጸጋ ዓለማዊ ምኞትን ሁሉ ገሸሽ አድርጌ የተባረከውን ጌታዬን እንድጠብቅ ያደርገኛል::
2.  ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ 
ይህ ልዩ ወንጌል ምንድነው ከእየሱስ ጸጋ ውጪ የሆነ ነው ማለት ነው::  ይቅርብኝ ልዩ ወንጌል! እኔ የያዝኩት እውነት በአዳም ሐጥያትና ሞት ገባ በእየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ በጸጋ መዳን ወደ ህይወት መሻገር ሆነ አሜን!  በትምህርት ንፋስ አልፍገመገምም፤ እቆማለሁ በህይወት፤ በእውነቱና በመንገዴ በእየሱስ ላይ የምሰራው የለም ለእኔ የሰንበት እረፍት ነው የቀረልኝ ፤  ወደ እረፍቴ ገብቻለሁ እኔ አይደለሁም ለማሸነፍ የምጥረው ድል አድርጎ እራሱ ሰርቶ ሰቶኛል ቆሜ ድሌን አጣጥማለሁ::  ክብር ለጌታዬ ጸጋውን ለሰጠኝ ይሁን ከከፍታዬ አልወርድም::ሃሌሉያ!! አሜን!


ወንጌል አንድ ነው

ወደ ገላትያ 1:7-10

እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። 
ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። 
አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። 
ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። 

የተቀበልነው ወንጌል አንድ ነው እርሱም በጸጋ መዳናችን ነው::  በስራ አይደለም ደግሞም የምንጨምርበት ነገር የለም ተጠናቋል::  ስለተሻገርን መዳን ቀሎ አይታየን አንዳንዴ ለሰዎች ስትመሰክሩ ነው ከባድነቱ የሚታየው ሰው እንዴት ይሄ መዳን አይታየውም አትሉም?  የዚህ ዓለም ገዢ አይምሮን ያሳውራል ያንን ሁሉ አልፈን መተን ደግሞ አሁን መወናበድ የለብንም የዳነው በጸጋ ነው የምንጨምርበት ከእንትና የተሻልኩ ነኝ የምንልበት ምንም ማማሀኛ የለም የማይገባን ነበርን ከትልቅ ምህረቱ የተነሳ ቀድሶ ወደ ራሱ አስጠጋን::

ከዚህ እውነት ውጪ ሰዎችን ለማሳመንም ሆነ ለአስተሳሰባችን እንዲመች አድርገን ቃሉን አናጣምም ቃሉ እዚህ ጋር የሚለው እንደዚህ አይነቱ የተረገመ ይሁን ነው::  

ስለዚህ ከሰው ይልቅ አምላካችንንና አባታችንን ደስ ማሰኘት ይሻላል:: የምወደው ልጄ ይህ ነው በእርሱ ደስ የሚለኝ ብሎ አንድ ጊዜ በልጁ ደስ ተሰኝቷል::  የሐጥያት ዋጋ ሙሉው ተከፍሏል እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ልጁን መልበስ ነው::  እርሱ ውስጥ ወስዶ በአብ ቀኝ የሰወረንም ለዚሁ ነው ስራ አበቃ እዳ ሁሉ ተከፈለ ብሎ ደስ አለው አብ ቤተሰቡ ሁሉ ትሰብስቦ ሲያይ በልጁ ውስጥ አለቀ!  ሌላ ስራ አያስፈልግም አትናወጡ ቅዱሳን!


ወንጌል የሚገለጥ ነው

ወደ ገላትያ 1: 11-12

ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም። 

1.  ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤

እኔ ከሰው ተቀብዬ አይደለም ወንጌልን የሰበኩት ከራሱ ከጠሪው ነው የተማርኩትናም የሰበኩት እያለ ነው::   መለኮታዊ ነው ጥሪዬ ድምጹን ሰምቼ፤ አይኔም ከክብሩ የተነሳ ታውሮ፤ ሰዎችን ያሳደድኩ መስሎኝ ፈጣሪዬን ሳሳድድ የነበርኩትን ራርቶ በህይወት አኖረኝና ይህንን ወንጌል ሰጠኝ እያለን ነው::  ዛሬም ጥሪ አለ፤ ዛሬም መላክ አለ፤ ዛሬም መገለጥ አለ::  ጌታ በስራ ላይ ነው::

2.  ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም::

ይሄ ቃል በጣም ዋጋ አለው ለእኔ ምክንያቱም ጳውሎስ ወንጌልን የተማረው ከራሱ ከእየሱስ ነው::  ወንጌል  ሁልጊዜ አዲስ ነው፤ የሚሰራ ነው በሐዋርያት ብቻ ብሎ ነገር የለም::  ዛሬም ለእኔ ወንጌሉን ያበራልኝ በመንፈሱ ነው::  ጸጋ ቢሆን ዛሬ ይሰጣል፤ ቃሉን መግለጥ ቢሆን ዛሬ ይሰጣል ምክንያቱም እየሱስ በስራ ላይ ነው ሙሽራይቱን ያስውባል፤  አካሉንም አገልጋዮችን ልኮ ይገነባል:: ጳውሎስ እንዴት እንደተጠራ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል በሐዋርያት ስራ ላይ

  ”ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።”
ዛሬም ወንጌል አልተለወጠም ይህንን የከበረ ቃል ይዘን እንወጣለን::  አሜን


ወንጌል በአሳዳጁ ሲሰበክ

ወደ ገላትያ 1: 13-24
ከዚህ በፊት እንዳየነው ጳውሎስ ከጌታ እንደተቀበለና እንደተማረ አይተናል::  እስኪ እንየው የእርሱ ትኩረት የነበረውን ከደማስቆ መንገድ በፊት:-

1.  በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ 
2.  የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ 
3.  ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። 

ከደማስቆ መንገድ በኃላ ደግሞ:-

1.  በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ ለየኝ በጸጋውም ጠራኝ 
2.  እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ 
3.  ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥
4.  ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። 
5.  ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።
6. ነገር ግን፡— ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል፡ ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር። 

ይህን ሁሉ ነገር የሚነግራቸው መግቢያው ላይ ለጠቀሰው ሀሳብ ማጠናከሪያ ነው::  ሐዋርያ መሆኑን በፊት ከተጠሩት ሐዋርያት እንኳን ሁለቱን ብቻ እንዳገኘ እነሱንም ያገኘው ወድያው እንዳልሆንና ለተገለጠለግ እውነት ወድያው ምላሽ ሰቶ እንዳገለገለ ነው የሚያስረግጠው ስለዚህ እኔ የነገርኳችሁ ወይም ያስተማርኳችሁ ወንጌል እውነት ነውና ጽኑ እያለ ለማጠናከሪያ ነው የሚነግራቸው የህይወቱን ታሪክ::

ከዚህ የህይወት ጉዞ ያየሁት:-
1.  በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ እንደለየኝ በጸጋውም እንደጠራኝ 
2.  ከስጋና ደም ጋር ሳልማከር መታዘዝን
3.  ለእግዚአብሔር ስም መመስገን ምክንያት መሆንን እንዳለብኝ አይቻለሁኝ::
ጌታሆይ ተመስገን ስለመረጥከኝ ደግሞም እርዳኝ እንድታዘዝ የመታዘዝን መንፈስ በእኔ ውስጥ አድርግ::  በእርምጃዬም ሁሉ ለአንተ ምስጋና ይምጣ እንጂ ስምህ ከእኔ የተነሳ አይሰደብ::  በእየሱስ ስም! አሜን!


ምዕራፍ 2

ምዕራፍ 2 ንባብ

በሐሰተኞች አለመነዳት

ወደ ገላትያ 2: 1-10

ከዚህ በፊት እንዳየነው ጳውሎስ መልእክቱ ለገላትያ ሰዎች ወንጌል ብቻውን ነው የሚያድነው እንጂ ካልተገረዛችሁና የሙሴን ህግ ካልጠበቃችሁ የሚሉትን  አትስሙ ነው የሚለው እዚህም ክፍል ላይ ምክንያቱን እንይ:: 

ከ14 ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤ (መጀመሪያ ሄዶ የነበረው ከዳነ ከ3 ዓመት በኃላ እንደነበር አይተናል)

እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤ 

ለምን አህዛብ የሆነውን ቲቶን ይዞ ሄደ? ስለመገረዝ አንድ እልባት ለመስጠት ፈልጎ ነው::  ታሪኩን በሐዋርያት ስራ 15 ላይ እናገኘዋለን::  መሪዎቹ አላስገደዱትም እንዲገረዝ::  አትሳቱ አያስፈልግም እያላቸው ነው::

ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ።

ጳውሎስ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር ሾልከው የገቡ ሐሰተኛ ወንድሞች ይህንን እንዳደረጉ::ስለዚህ መሪዎች የሆኑትም እጃቸውን ሰጡኝ ቀጥል ብለው እንጂ አልተቃወሙኝም እያለ ነው::

ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ። 

የሰጡት ትዕዛዝ አንድ ነው የሙሴን ህግ መጠበቅ ወይም መገረዝ ሳይሆን እነዚህ ከውጪ የሚደረጉ ነገሮች ናቸውና የውስጥ የሆነውን የፍቅርን አገልግሎት እሱም ደሆችን ማሰብ:: 

ለእኛም ይህ ነው የጌታ ትዕዛዝ በሄድንበት ሁሉ ደሀን እናስብ እናም አርነታችንን አናስነጥቅ::


ለእውነት እንቁም

ወደ ገላትያ 2: 11-14

ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና። አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን፡— አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት። 

እዚህጋ የምንመለከተው ጴጥሮስ አንጾኪያ ያለችውን ቤተክርስቲያን ሊጎበኝ መቶ እያለ ስለተፈጠረው ነገር ነው የሚነግረን::  ጴጥሮስ ከእየሩሳሌም ወገኖች ሳይመጡ በፊት ከአህዛብ ጋር ይበላ ነበር ሰዎቹ ከመጡ በኃላ ግን ማስመሰል ጀመረ እንደማይበላና የሙሴን ህግ እንደሚጠብቅ::  በዚህ ጊዜ ነበር ጳውሎስ ትናንት ሌላ ዛሬ ሌላ ሲሆንበት በሁሉ ፊት የወቀሰው::  የጥልን ግድግዳ አፍርሷል ብለን ታድያ እንዴት መስበክ ይቻላል?  እየሱስ እኮ ቀርበው ላሉትም ሰላምን ርቀን ላለነውም ሰላምን ነው የሰበከውና አንድ ጊዜ የጥልን ግድግዳ አፍርሶ ሁለቱን አንድ አድርጏል በሰማይና በምድርም ያለውን ከአባቱ ጋር አስታርቋል::  ሊወቀስ ይገባው ነበር ጴጥሮስ እንደመሪ ይህንን ሲያይ እንደዚህ እነዚያን ሲያይ እንደዛ መሆን አልነበረበትም ባይ ነው ጳውሎስ::  እንደዚህ ደግሞ መኖር ከፈለክ አህዛብም እንደራሳቸው ህግ ይኑርዋ የእኛን ህግ አንጫንባቸው ነው የሚለው ይሄ ግን ቤተክርስቲያንን ወጥ የክርስቶስ አካል አያደርጋትም ስለዚህ ወደ አንዱ እንምጣ ሁሉ አንድ ነው መለያየት የለም::

ስለዚህ የተማርኩት ነገር ለገባኝ እውነት በየትኛውም አጋጣሚ ጸንቶ መኖር እናም ህያው የወንጌል ምስክር መሆን አለብኝ::


በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ጸድቀናል

ወደ ገላትያ 2: 15-16

እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤ ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።

1. እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤

የሚገርመው ነገር ከአይሁድ ውጪ ያለውን ሰው ሁሉ አይሁዶች ሐጥያተኛ ብለው ነው የሚጠሩት:: ለዚህም ነው እዚህጋ ጳውሎስ ትምክህት ቢያስፈልግ አለኝ አይሁድ ነኝ እንጂ አህዛብ አይደለሁም ይልና ሲቀጥል ያፈርሰዋል ምንም እንደማይጠቅም::

2. ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥

የምንጸድቀው በአንድና አንድ ነገር በማመን ብቻ ነው እርሱም በክርስቶስ እንጂ የህግንማ ስራ እኛም ትተነዋል የሙሴን ህግማ በመጠበቅ የሚዳን ቢሆንማ እኮ የሚጠብቅ ነበረ ግን ህግ ከመክሰስ ያለፈ የማጽደቅን ስራ አይሰራም:: እየተከታተለ ስራውን ይሰራ ነበር በትጋት እሱም መክሰሱን ያለ ርህራሄ እዚህ ጋር ልለፍ ቀላል ነገር ነው የተሰራውወይም ትላንትና በርትቶ ነበር ብሎ እንኳን ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባው ነገር የለም ስለዚህ እግዚአብሔር እርሱን አሮጌ አድርጎ አዲስን መንገድ ከፈተልን ሁሉን እኩል አድርጎ በጸጋ የሰውን ልጅ ሁሉ አጸደቀ:: አሜን!

3. እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።

ስለዚህ ያመነው በጽድቅ ስራ ሳይሆን በክርስቶድ ነው ያንን መንገድ በደንብ ሄጄበታለሁ አድካሚ ነው የሚሻለው አሁን ያስተዋወኳችሁን እውነት መያዝ ነው እሱም በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ መዳን::

ጌታ ይርዳን በጸጋ ጀምረን የህግ ምሁራን እንዳንሆን አይናችንና ልባችን ሁልጊዜ በጸጋው ላይ ይሁን አንቀላቅል ለዚህ ነው ዕለት ዕለት እራሳችንን መስበክና ማንቃት ያለብን ድንገት እህግ ሰፈር እንዳንገኝ አስተሳሰባችንን ሁሉ እንለውጥ ከተመካንም በእየሱስ ስራ ላይ ብቻ ይሁን::


ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖራለሁ

ወደ ገላትያ 2: 17-19

ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና። እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና።

በክርስቶስ የጸደቅን እኛ በጸጋ ድነናል ብለን ስንል እኮ ሐጥያትን ለማድረግ ላይሰንስ አግኝተናል ለማለት አይደለም:: እንዲያውም የህይወት አኗኗራችን ደረጃው ጨምሯል እያልን ነው:: እኛ የጽድቅ አገልጋዮች ነን:: ቃሉ በሌላ ስፍራም እንደሚል ”ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።” በክርስቶስ ያገኘነው ማንነት ይሄ ነው የጽድቅ ዘር በእኛ አለ::

ስለዚህ ህግ እየተከታተለ አይከሰኝም የእኔ ደረጃ ከፍ ብሏል ከጸጋ እንጂ ከህግ በታች አይደለሁም:: እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ምኞት ሁሉ የምክድበትን ጸጋ በእኔ አስቀምጧልና ብቃት አለኝ ጸጋው በዝቶልኛል የዓለም ነገር ለኔ ሞኝነት እንዲሆን አድርጏል ጸጋው::

ስለዚህ እኔ ህያው ሆኜ ለእግዚአብሔር እኖራለሁ እንጂ ለህግማ ሞቻለሁ:: የሞተ ይነሳል እንዴ?! አረ በፍጹም! ለህግ አልነሳም ያለሁበት ተመችቶኛል ከፍታ በጌታ ጸጋ! አሜን!

ከወጣሁበት ከፍታዬ አልወርድም! የጌታ ስም ይባረክ በእኔ ውስጥ ጽድቅን ጨምሮ ከህግ የበላይ ላደረገኝ!


ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል

ወደ ገላትያ 2:20-21

ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።

እየሱስ አንድ ነገር አለ ዕለት ዕለት መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ ለኔ ሊሆን አይገባውም ሲል እዚህጋ ጳውሎስም ያጠናክረዋል አሁን እየተካሄደ እንዳለ አድርጎ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ ይላል:: መቼ? አሁን ወይም ሁልጊዜ::

መስቀል ማለት የምንገኝበት ሁኔታ/ኮንድሽን ማለት ነው እርሱም ለዓለም፤ ለራሳችንና ለሐጥያት ሞተናል:: ሕያው ሆነን የምንኖረው እኛ ሳንሆን ህይወቱን የለወጠን እየሱስ ነው በእኛ የሚኖረው:: አሜን!

ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እንደሚል ቃሉ መውደድና መስጠት አብረው የሚሄዱ ናቸው ወደደንና እራሱን ስለእኛ ሰጠ:: ስለዚህ ለታደገኝ ጌታ ብኖርለትና ህይወቴን ኑርበት ብዬ ፍቅሬን እኔስ በመስጠት ብገልጠው?! ይገባዋል!

እርሱ ስለእኔ እንደበግ በሸላቾቹ ፊት ዝም ብሏል ሲበዛበት ይህች ጽዋ ትለፍ አለ ግን የእኔ ሳይሆን ያንተ ፈቃድ ይሁን ብሎ ስለእኔ ራሱን ሰጠ መድህኔ:: ታድያ ብኖርለት ምን ይገርማል? እኖራለሁኝ ለእርሱ ክብር ዓለምን፤ ሐጥያትን እራሴንም ክጄዋለሁ እኔ አሁን የምኖረው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ብቻ ነው። አሜን!

የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ እንዲህ ሊታደገኝ ተንገላቶ እያለ እየሱስ እናም ሕግን አላቆመውም ምክንያቱም አልችልም ሕግን ጠብቄ መጽደቅ የከፈለውንም የመስቀል ዋጋ ከንቱ አላደርግም:: ላዳነኝ በድንቅ አሰራሩ ለጠራኝ ጌታ ክብር ይሁን::


ምዕራፍ 3

ምዕራፍ 3 ንባብ

ለእውነት እንታዘዝ

ወደ ገላትያ 3:1-5

የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጸማላችሁን? በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን? እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው?

የገላትያ ሰዎች እየሱስ በፊታቸው እንደተሰቀለ ያህል ነበር ወንጌል የገባቸው የነበረው ሐሰተኛ አስተማሪዎች ገብተው ዓይናቸውን ከመስቀሉ ላይ እስኪያስነሷቸው ድረስ:: ይህ ሲሆን ግን አላስተዋሉም ለእውነት መታዘዝ ማቆማቸውን:: በህግ ሳይሆን በእምነት ነበር የመንፈስ ቅዱስን ስራ ሁሉ ያዩትና የተለማመዱት የነበረው:: ዛሬ ታድያ ምን ተፈጠረ በመንፈስ ጀምራችሁ በስጋ የምትፈጽሙት እያለ ነው አወዳደቃቸውን የሚያሳያቸው::

ወደኛ ስንመለስ ይህ ሁሉ ለትምህርታችን ነውና እንዴት እንገኛለን? በእምነት ወይስ በስጋ አስተሳሰብ? እዚህጋ የህግን ስራ የስጋ ነገር እንደሆነ ጳውሎስ እያቀያየረ ይጠቀምበታል:: ለስጋውያን መንፈሳዊ ነገር ሞኝነት ነው ለእኛ ግን መንፈሳውያን ለሆንን ህይወት ነው:: ስንቶቹን አገልጋዮችን በዚህ ምክንያት አተን ይሆን? መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን የሚሰራው በእምነት እንጂ በስራ አይደለምና እንንቃ:: ስለዚህ የመስቀሉን ስራ በማመንና ዓይናችንን በርሱ ላይ በማድረግ ይበቃናል:: ደህንነታችን አይቅለልብን የእየሱስን ህይወት አስከፍሏልና በእምነት እንጏዝ:: የጌታ ጸጋ ይብዛልን!


በእምነት መጽደቅ

ወደ ገላትያ 3: 6-9

እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።

እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፡— በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ፡ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።

የሚገርመው አብርሐም የብሉይ ኪዳን ሰው ሆኖ ሳለ ወንጌል ደርሶት አምኖ ነበር:: አይገርምም?! እየሱስ እኮ ገና አልመጣም፤ አላየውም፤ አልተጻፈለት እንደኛ ግን በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እኛ ግን ዛሬ በዛ ኪዳን ውስጥ እያለን ሌላ ያስመኘናል እሱም የህግ ባርነት!

አይሁድ እኛ የአብርሃም ልጆች ነን ብለው ሲሉ የነበረው ለእየሱስ ይህን ማለታቸው ነው:: ለማንም አልተገዛንም ብለው የሚመኩት:: ግን የህይወትን ራስ አብርሐም ከሩቅ አይቶ ያመነውን ጌታ ማየት አልቻሉም አጠገባቸው ሲመላለስ አላወቁትም ስለዚህም አሳልፈው ሰጡት::

ለእኛ ግን ለምናምን የአብርሃም በረከት በክርስቶስ ደረሰን እናም ”በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ፡” የተባለው ደረሰንና ዛሬ እየኖርንበት ነው::

ስለዚህ አሁን ቃሉ እንደሚል ”እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። ” ይለናል እኛም አሜን እንላለን!


ጻድቅ በእምነት ይኖራል

ወደ ገላትያ 3:10-12

ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግም ከእምነት አይደለም፡ ነገር ግን፡— የሚያደርገው ይኖርበታል፡ ተብሎአል።

ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ ሲባል አታነክሱ እያለ ነው ጳውሎስ ከእምነት ወይም ከህግ አንዱን ምረጡ እንጂ ሁሉቱንም ይዞ መሄድ አይቻልም ብሎ ሲያበቃ ፍጻሜውንም ያሳየናል:: ህግን ከተከትልን በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ኑሮአችን ከእርግማን በታች መሆን ነው ማለት ነው:: በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ማንም መፈጸም ስላልቻለ አይደል እንዴ ጌታ የመጣው?! ስለዚህ ፊታችንን ወደ እምነት እናዙር ጠላት አብዝቶ ፊታችንን ወደ ሚከለክልበት አቅጣጫ ማለት ነው:: ከእምነት ስንርቅ ለጠላት ቀላል ኢላማው ነን የማያልቅ የቤት ስራ ሲያሰራን ይኖራል ያልበቃን እንደሆንን ሁልጊዜ በማሳየት:: ዛሬም ነገም እየተመላለስን ማሳረም ነው ማለት ነው ስራችን ፈተናው ‘open book’ ሆኖ ሁሉም ይለፍ በክርስቶስ በኩል ተብሎ እያለ እኛ ግን ጊዜና ጉልበት ለማያስፈልግ ነገር እያባከንን እንዳንገኝ ብቻ:: እንንቃ!!!!

ጎበዝ እንንቃ የተባልነው እኮ ጻድቅ በእምነት ይኖራል እንጂ በስራ አይደለም:: መቼም ይህን ብዬ ስል እንደው እንደፈለግን በሐጥያት እንመላለስ ማለቴ እንዳልሆነ ይሰመርበት እንደዛማ ከሆነ ጭርሱን በደህንነት ሰፈርም አላለፍን ማለት ነው ክርስቶስን መምሰል ግድ ይላል:: በአእምሯችን መታደስ እንለወጥ እንጂ የሆነ ነገር achieve ለማድረግ አንጣር እንረጋጋ እዳችን ተሰርዟል ነጻ ነን ማመን ነው የሚጠበቅብን:: እግዚአብሔር መዳንን ቀላል ስላደረገው የዚህ ዓለም ጥበበኞች ከበዳቸው:: እኛ ግን መዳን በእምነት እንደሆነ ገብቶናል:: አናሻሽለውም አሜን እንጂ! እየሱስ ከህግ እርግማን ዋጅቶናል!! አሜን!


ከሕግ እርግማን ክርስቶስ ዋጀን

ወደ ገላትያ 3: 13-14

በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።

ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ እርሱ ራሱን የሰጠው እና የተንገላታው እኛ ከዚህ የሕግ እርግማን ነፃ እንድንሆን ነው:: እርሱ ሐጥያትን የማያውቅ ንፁ ሆኖ ሳለ በእንጨት ላይ በተሰቀለ ጊዜ ግን እርሱም እርግማን ሆኖ ከእኛ ጋር ተካፍሎ ነፃ አወጣን:: ሃሌሉያ! አሜን!

ሕግ የመጣው የእግዚአብሔርን የቅድስና ልክና ከእኛ የሚጠበቀውን ሊያሳየንና አዳኝ እንደሚያስፈልገን ለማሳየት ነው:: ከዚህ በፊት እንዳልኩት ሕግ የተሾመበት ስራው እየተከታተለ ስህተትን ማሳየት ነው እሱንም በትጋት ሰርቷል::

ሕግ የመጣው በሙሴ ነው የመጣውም ለእስራኤላውያን እንጂ ለኔ ለአሕዛብዋ አይደለም:: እኔ ግን እንደአሕዛብ የእግዚአብሔርን የቅድስና ልክ (standard) መድረስ ስላልቻልኩ ከቁጣ በታች ተዘግቶብኝ ነበር:: አብርሐም የኖረው ከሕግ በፊት ነበር:: ስለዚህም አብርሐም ወንጌል ተሰበከለት እርሱም ተቀበለና ጽድቅ ሆኖ የተቆጠረለት:: የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ እኔም ይህንን የመዳን ወንጌል ስቀበል በእምነት የአብርሀም በረከት በእየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ለአሕዛብዋ ደረሰልኝ:: መድረስ ያልቻልኩትን ያንን የቅድስና ከፍታ በእየሱስ በማመን የእርሱ ጽድቅ ለኔ ተቆጥሮ ይህንን ሰማያዊ መንግስት ተቀላቀልኩኝ:: ዛሬ በስራዬ እንደማላስደስተው ያወኩኝ በጸጋው የዳንኩኝ ልጅ ነኝ:: አሜን!


በተስፋ ቃል እግዚአብሔር ርስት ሰጥቶአል

ወደ ገላትያ 3: 15-20

ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፡— ለዘሮቹም፡ አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፡— ለዘርህም፡ ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።  ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም። ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 
ሕግ ምንድር ነው? መልሱ:-
ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ::  ስለዚህ ሕግ መዳረሻ ነው ማለት ነው ዘሩ እስኪመጣ::
ይህ ዘር ማነው?
ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፡— ለዘሮቹም፡ አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፡— ለዘርህም፡ ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።  አሜን ሕግ ስራው ጨርሶ ተሰናብቷል የተጠበቀው ስለመጣ እርሱም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መካከለኛው አምላክ ብቻ ሳይሆን እንደ እኛው ሰው ሆኖ የኖረው::  ስለዚህም ቃሉ እንደሚል መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም ለሰው ብቻ አይደለም ወይም ለእግዚአብሔር ነገር ግን ሁለቱንም ያማከለ መካከለኛ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል አለ፤ ሁለቱን ያስታረቀ፤ የጥልን ግድግዳ ያፈረሰ፤ ዛሬም የሚማልድ ሊቀ ካህን አለን በሰማይ::  አሜን!
ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። 
ስለዚህ ርስታችንን የምንወርሰው በሕግ ሳይሆን በተስፋ ቃል ነው ያም የተስፋ ቃል ለአብርሃም ተስቷል ለእኛም ለምናምን ዛሬ ወደ እኛ በክርስቶስ በዘሩ በኩል ደርሶልናል::


ከሞግዚት በታች አይደለንም

ወደ ገላትያ 3:21-25
እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል። እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር። እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤ እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። 

እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማል? አረ በፍጹም::  የጽድቅ መንገዱ እኔ አይደለሁም ስራዬ መክሰስ ብቻ ነው ይልቁንስ ከሐጥያት በታች ከመዘጋት ማምለጫው መንገድ መቶልናል::
በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤ እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። መሆንም አያስፈልግም ወላጃችን ክርስቶስ መቶልናልና ሞግዚት አያስፈልገንም::


በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ

ወደ ገላትያ 3: 26-29
በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ። 


ማመን ብቻ ነው ከኔ የተጠየቀው ልክ አብረሐም እንዳደረገው አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት::  እኔም በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን ልጅ መሆን ተሰቶኛል::  ስለዚህም የተስፋው ቃል ወራሽ ነኝ:: 

ከላይ እንዳየነው የሕግ ነገር የሚያዋጣ አይደለም ደግሞም የራስ ስራ እዚህ ግባ አይባልም በቅዱሱ በእግዚአብሔር ፊት::  ስለዚህ መፍትሄ ብሎ የሰጠኝን ይህንን በክርስቶስ በማመን ልጁ መሆንን  በሙሉ ልቤ ተቀብዬ ፍሬ እያፈራሁ እኖራለሁ::  ሞግዚት ከእንግዲህ ወዲህ አያስፈልገኝም:  

በሞትና ትንሳኤው አምኛለሁ በመሆኑም እርሱን ለብሻለሁ::  ለዚህ ነው ሰውን ሁሉ በክርስቶስ አውቃለሁ የሚለው ቃሉ ክርስቶስን ገልጠን ከስር ያለውን ማንነት አንይ እራሳችንንም አናሳይ ደግሞስ ምን ለማግኘት ወይም ማንን ደስ ለማሰኘት? ጠላትን ወይስ ጌታን?  የእኛ ማንነት በእርሱ ውስጥ ተሸሽጏል ይህ የሆንው እኮ እኔ በራሴ ማድረግ ስላልቻልኩ አይደል? በክርስቶስ እየሱስ ሁሉ አንድ ነው የሚለን እኮ ይህንን ጻድቅ የሆነ ጌታ ስለለበስነው ነው:: – አይሁዳዊ ወይም የግሪክ –  ባሪያ ወይም ጨዋ –  ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና::  ሰውን ሁሉ በክርስቶስ  ውስጥ  እንወቅ:: ልዩነት ሁሉ ጠፍቷል ሁሉ አንድ ነው::

እንግዲያስ በክርስቶስ ከሆንን የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ ይለናል ቃሉ እኛም አሜን እንላለን::


ምዕራፍ 4

ምዕራፍ 4 ንባብ

የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ባሪያ አይደለሁም

ወደ ገላትያ 4:1-7 

ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥ 2፤ ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። 3፤ እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤ 4፤ ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 5፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። 6፤ ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።  7፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። 


በእኛ ላይ ጠባቂና መጋቢ ሞግዚታችን ሕግ ነበር:: ነገር ግን የሰው ልጅን ለማዳን እግዚአብሔር ቀጠሮን ቀጥሮ ስለነበረ ያም ጊዜ እስኪደርስ ድረስ የሰው ዘር ሁሉ ባሪያ ሆኖ ነበር::  

ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ምን አደረገ?

ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 

ለምን ላከልን?

እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ እና

ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። 
ሕግን አሰናበተው እንዳይገዛን ልጅ ናችሁ ብሎ ሻረው ከእኛ ላይ::
ልጆችስ ከሆንን በኃላ? 

እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።  አሜን! በእኔ ውስጥ አባ አባት ብሎ የሚጮህ መንፈስ ተልኮ በስራ ላይ አለ:: የተላከው መንፈስ ልጅ መሆኔን ይመሰክርልኛል እኔ ውስጥ ሆኖ የማንንም ማረጋገጫ አልፈልግም!
ስለዚህ?!

ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነኝ እንጂ ባሪያ አይደለሁም፤ 
ልጅ መሆኔ የሚሰጠኝ ጥቅም ምንድነው ቢባል:- 

ልጅም ከሆንኩ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነኝ።  አሜን!  ልጅ መሆኔ እውን ነውና መውረስ ደግሞ በመወለድ የሚመጣ ጥቅሜ ነው ::


በእግዚአብሔር ታውቄያለሁ

ወደ ገላትያ 4: 8-9

8፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ 9፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን? 
እውነት ነው የቀደመው ህይወት እርሱን ሳናውቅ ተመላለስን አምላክም ላልሆነው ፍጡር ሁሉ ሰገድን ለዚህም ዓለም ገዢ ተገዛንለት እንደውደደም ባርያ አድርጎን ህይወታችንን መራው:: 
አሁን ግን ያ ባርነት አብቅቶ ከእኛ ላይ ተገርስሶ ወደ ህይወታችን እረኛና ፈጣሪ መተናል እርሱን አውቀንማል ከዚህም ሁሉ በላይ በእርሱ ታውቀናል::  እውነተኛው እረኛ አውቆኝ በስሜ ይጠራኛል መሰማሪያንም ይሰጠኛል::  አሜን!

ታድያ የምን ባርነት?!  

ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት እመለሳለሁ? 

ከነፃነት ወደኃላ ወደ ባርነት? 

አረ ይቅርብኝ ተመችቶኛል ይሄ ነፃነት::  

አልያዝም በባርነት! 

እኔ በእግዚአብሔር ልጅ በእየሱስ መስቀል በዋጋ ተገዝቻለሁ ልጁ እንድሆን ስለዚህ ባርያ መሆንም ከሞግዚትም በታች መተዳደር ይቅርብኝ::


ክርስቶስ በእኛ ሊሳል ይገባል

ወደ ገላትያ 4:10-20
10፤ ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። 11፤ ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ። 12፤ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና፡— እንደ እኔ ሁኑ፡ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም። 13፤ በመጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ፥ 14፤ በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። 15፤ እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ::
16፤ እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን? 17፤ በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ። 18፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው። 19፤ ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል። 20፤ ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ::

የገላትያ ሰዎች ልባቸው መሆን በሚገባው ቦታ ላይ አልነበረም :: ጳውሎስ እንደሚለው ልባቸው ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ መጠበቅ ላይ ነበር:: እያደረጉ የነበረው ሰንበትን ማክበር፤ ወራቶችን እየጠበቁ እንደ ሕጉ መስዋትን ማቅረብና ባዕላትን መጠበቅ ነበር ይህ ሁሉ ግን ሊመጣ ላለው ለእየሱስ ምልክቶችና መዳረሻ እንጂ ዋናው አልነበርም:: ስለዚህም ነው ጳውሎስ የደከመለትንና የሮጠለትን የክርስቶስን ወንጌል እርሱም በፊታቸው ተስሎ የነበረውን ክርስቶስን እንዲያዩና ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ነው አሁንም ክርስቶስ በፊታችሁ ይሳል የሚለው::

በመጀመሪያ ሲቀበሉት የነበራቸው ፍቅር ያላቸውን ሁሉ ያለ ስስት የሚያሰጥና እንደ ክርስቶስ መልእክተኛ ነበር የተቀበሉትና ወንጌል የገባቸው አሁን ግን ዋናውን ቁጭ አድርገው ወደ ሞግዚት መሄድ አማራቸው::

እኛስ እንዴት ነን ምን ላይ ነው ልባችን ያለው? ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷል ደግሞም የሰንበት እረፍት ቀርቶልናል ስለዚህ ልባችንን በክርስቶስ ላይ አድርገን እንደጀመርን እንጨርስ:: ለብ ባለ ህይወት አንመላለስ ልክ መጀመርያ እንደጀመርነው በጋለ ህይወት ጌታን በማመን በእርሱ ጽድቅ ተደግፈን እንመላለስ:: ጸጋን ሁሉ ሊሰጠንና ሊረዳን ከእኛ ጋር ነው አዳኛችን እየሱስ! አሜን!


የተስፋ ቃል ልጆች ነን

ወደ ገላትያ 4:21-31

21፤ እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ። 22፤ አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። 23፤ ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። 24፤ ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። 25፤ ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። 26፤ ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት። 27፤ አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል። 28፤ እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። 30፤ ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። 31፤ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም። 

እንደምሳሌ አድርጎ ጳውሎስ ሊያሳየን የሚፈልገው ቁም ነገር የተስፋ ቃልን ነው::  ይስሐቅ እግዚአብሔር እንደተናገረው የዓለም መድኃኒት የእየሱስ ክርስቶስ መምጫ ግንድ ሆነ::  ዘርህ በእርሱ ይጠራል ብሏልና እንዳለው በይስሐቅ በኩል ይህ ተስፋችን መጣልን:: እኛም ተስፋችንን መጀመሪያ ላይ በዘፍጥረት ከሴቲቱ እንደሚመጣ የነገረንን ፈጸመው::  ስለዚህ እግዚአብሔር የዘገየ ቢመስለንም እንኳን ይመጣል ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም::  


ምዕራፍ 5

ምዕራፍ 5 ንባብ

በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን

ወደ ገላትያ 5:1-5

1፤ በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። 2፤ እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፡— ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። 3፤ ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት፤ ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። 4፤ በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። 5፤ እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። 
ባርነትን እንቢ ብለን ነፃነትን እንምረጥ አለበለዚያ ግን ቃሉ እንደሚለን ሁሉንም ሕግ መጠበቅ ግድ ይላል:: የተወሰነውን ወይም ደግሞ አቅሜ የፈቀደውን ካደረኩኝ በቂ ነው ብሎ ነገር የለም ሕግ ካሉ ሁሉንም አንዷን ማጉደል አይቻልም::  ታድያ የቱ ይሻላል በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት  ያወጣንን መቀበል ወይስ እንደማይሆንልን እያወቅን በሕግ ጎዳና መሄድ?  እኔስ በክርስቶስ ያገኘሁት ነፃነት ይሻለኛል አለመቻሌን ጠንቅቄ አውቂአለሁ:: 
ደግሞም በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። ወየው አረ ወደ ጸጋው እንመለስ? ጸጋው ብቻውን በቂ ነው::ስለዚህ እላለሁ  እኔ ግን በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለሁ።  እርሱ ብቻ ነው ያለኝ ተስፋ::


በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት

ወደ ገላትያ 5:6-8

6፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። 7፤ በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? 8፤ ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። 

በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ እሱ ላይ ተቀጥላ አያስፈልገንም::  መገረዝም አለመገረዝም የስጋ ነገር ነውና ለመንፈሳዊዉ ህይወት አይጠቅምም:: እምነት እምነት ስንል ያለ ፍቅር መሆን የለበትም ስለዚህ እሩጫችንን እንሩጥ በፍቅር እንጂ ለእውነት ባለመታዘዝ አይሁን::  ይህ ማባበል ለጥፋት ነውና ወደ ስጋ ማየቱ አያዋጣም አልተቻለንም በስጋ እሱን ደስ ማሰኘር እናም እውነትን በፍቅር እንያዝ እሱም እኛ በመንፈስ ከእምነት ከሆነ የጽድቅን ተስፋ እየተጠባበቅን በክርስቶስ ኢየሱስ በሚሰራው እምነት በፍቅር እንቆማለን::


አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ

ወደ ገላትያ 5:9-15

9፤ ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። 10፤ የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። 11፤ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። 12፤ የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። 13፤ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። 14፤ ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፡— ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፡ የሚል ነው። 15፤ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። 


የመስቀል እንቅፋት ምንድነው?  ሕጉ ነው እንቅፋት የነበረው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል:: አሜን! እርሾን እናስወግድ አለዚያ ግን እህሉን ሁሉ ነው የሚያቦካው ማለትም መገረዝን ብቻ እንፈጽምና ሌላውን ግን ማድረግ የለብንም የሚባል ነገር የለም አንዱን ስናስገባ ፈጽመን ከጸጋው እንወድቃለን ነገራችን ሁሉ ተበላሸ ማለት ነው:: ስለዚህ አሁን አርነት ወተናል ግን ይሄ አርነት ለሥጋ ምክንያትን እንድንሰጥ አይደለም ወይም ደግሞ ወደኃላ ተመልሰን ሕግን እንድናቆለፓፕስ አይደለም ለጠራን ጌታ በፍቅር ተገዝተን ሰውን ሁሉ ወደን በቅድስና እንድንመላለስ ነው::  አንዱ የሌላውን ሸክም ይሸከም ዘንድ ነው ይህም የሚያሳየን እንደው ደርሶ እንድንኮፈስ ሳይሆን የለየልን ሐጥያተኞች በጸጋ እንጂ በስራ ያልዳንን መሆናችንን ስለምናውቅ ወገኖች ላይ የሚፈርድ ሳይሆን የሚራራና የሚሸከም በፍቅር የሚቀበል ከማንም አልበልጥም የሚል ማንነትን እናጎለብታለን:: ብንነካከስና ብንበላላ የምንጠፋፋው እኛው ነን ይህ ደግሞ የጠላታችን ትልቁ ግብ ነው እኛ የተጠራነው እርስ በርስ ተደጋግፈን እንድንመላለስ ነው::  አካል ማለት ይኸው ነው: :


በመንፈስ ተመላለሱ


ወደ ገላትያ 5:16-18

16፤ ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። 17፤ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። 18፤ በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። 

በመንፈስ ተመላለሱማለት በሌላ አባባል የስጋን ምኞት አትፈጽሙም ማለት ነው:: መመላለስን ስናስብ የሚደጋገም ነገር ማለት ነው ለምሳሌ መተንፈስን ስናይ እስከአሁን ተንፍሻለሁ ይበቃኛል ብንል ምን እንደሚሆን ይታወቃል አይደል ስለዚህ ወደ መተንፈሳችን እንመለሳለን::  ሁልጊዜ አንዱ አንዱን ለማሸነፍ ይጥራል ፥ ይቀዋወማል ስለዚህ በመንፈስ መመላለስ ሁልጊዜ የምንኖርበት ሁኔታ መሆን ነው ያለበት እንጂ ወጣ ካልን ከጸጋው መውደቅ ነውና ዕለት ዕለት በመንፈስ መመራትን እንፈልግ ልጆች ነንና:: 

እንዴት እናሸንፍ ታድያ?  በመንፈስ በመመራት ማሸነፍ እንችላለን ያኔ አድርግ አታድርግ አይሆንም ነገራችን መንፈስ ብቃትን ይሰጠናል አለዚያ ግን በመንፈስ የጀመርነውን ጉዞ በስጋ እንዳንጨርስ ያሰጋል::  የምንወደውን ማድረግ አንችልም እኛ የፍቅር ባሪያ ነን ህይወታችንን ለጌታ የሰጠን ነን::  በመንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው ይላልና ቃሉ:: የጠራን የታመነ ነው! አሜን!


የሥጋ ሥራ


ወደ ገላትያ 5:19-21

19፤ የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥20፤ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥21፤ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።


እውነት ነው ከላይ ያሉትን የሚያደርጉ በመንፈስ የሚመላለሱ አይደሉምና የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም::  በመንፈስ መመላለስ በቃሉ መታነጽን ይጨምራል ምክንያቱም ቃሉ ጌታ እየሱስ እንዳለው መንፈስ ነው፥ ህይወትም ነው::  

ማን ወይም እንዴት ልንወርስ ነው ታድያ የሚል ጥያቄ ውስጥ እንደምንገባ እርግጠኛ ነኝ::  ነገሩ እንደዚህ ነው በራሳችን አንዳች ማድረግ የማንችል ነን እናም ወደ ቃሉ ስንመጣ ቃሉ ይረዳናል በእምነት ከእኛ ጋር ሲዋሀድ::  እነዚህ ሕግን የሚሰብኩ ሰባክያን እራሳችሁን ቀይሩ ለሚሉት ስብከት መልስ ነው እነዚህን ሁሉ ስራዎች በህይወታችን እዚም እዛም እናያቸዋለን::  የምንኖርበት እና የምንታወቅበት ባህሪ መሆን የለበትም ሁልጊዜ ራስ ወደሆነው ወደ እየሱስ ማደግ አለብን::  እናም እራሳችንን ከዚህ ሁሉ ስራ ነፃ ካወጣን በኃላ ነው ስራ ተሰራ ጌታን ደስ አሰኘሁት የምንለውና ራሳችንን የምናታልለው::  ማንም በስጋ ጌታን ደስ ማሰኘት አይችልም::  ይሄንን ማሰብ ማለት መቼም የማንወጣው አዙሪት ውስጥ መግባት ነውና እጃችንን እንስጥና ለሚለውጠን ጌታ እንገዛ::   ደስ የሚለው ይህንን ሁሉ ስትጨርሱና ስትችሉ ኑ አላለንም ይህ ልብን ያሳርፋል ያለን እናንት ሸክማችሁ የከብደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኃለሁ ነው::  ስሙ ይባረክ የኔ ጌታ!


የመንፈስ ፍሬ

 ወደ ገላትያ 5: 22-26
22፤ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፣23፤ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።24፤ የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።25፤ በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።26፤ እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።

እናስተውል እዚህጋ የመንፈስ ፍሬ እንጂ የመንፈስ ፍሬዎች አይልም::  ፍሬውን የሚያፈራውም ፍሬውም አንድ ነው እርሱም በእኛ ውስጥ የሚሰራው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው::  እነዚህ ባህሪያቶቹ ናቸው በእኛ ውስጥ ሲኖር የሚገልጠው::  ለዚህ ነው የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ የሚለው::  እኛ መስቀሉን ተሸክመን የምንከተል ሰዎች ነን ለክፉና ለዚህ ዓለም የሞትንበትን ደረሰኝ ይዘን የምንዞር::  ዓለምንም መውደድ ከእግዚአብሔር ጋር ጥል እንደሆነ የገባን ነን::

ደግሞ ደጋግሞ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ጳውሎስ ይነግረናል:- በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ::  ሚስጥሩ ያለው ከመንፈሱ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ላይ ነው:- በመንፈስ ብንኖር ወይም ብንመላለስ ስጋ  ምኞቱንና መሻቱን አይፈጽምም ማለት ነው::  ደግሞም እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ የምንመካም አንሆንም::  በእኛ ውስጥ የሚታየው የእኛ ያልሆነው የእርሱ ፍሬ ይሆናል ማለት ነው::  እኛማ ይህንን ፍሬ ከየት እናመጣዋለን የእኛ ፍሬማ የስጋ እንጂ የመንፈስ አይደለም ምንም ብንጥር አናመጣውም ብናመጣው እንኳን ጊዜያዊ ነው:: ጎበዝ ጥረት ግረት እኮ ቀረ ስሙ ይባረክ ላሳረፈን ጌታ የእኔ ጽድቅ ለእናንተ ይሁን ብሎ ለቀየረንና የመንፈስ ፍሬ ተካፋይ ላደረገን:: ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን! አሜን!


ምዕራፍ 6

ምዕራፍ 6 ንባብ
አንዱም የአንዱን ሸክም ይሸከም

ወደ ገላትያ 6: 1-2


1፤ ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።2፤ ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።


ከላይ እንዳየነው የመንፈስ ፍሬ በእኛ ውስጥ አለና ይሄ የዋህነትና ፍቅር አገልግሎት ላይ እንድናውላቸው ነው ክፍሉ የሚነግረን::  ምን አይነት አገልግሎት ብለን ካልን በበደል ውስጥ የሚገኝን ሰው ማቅናት::  ማቅናት ብልን ስንል ሀሜትን አስወግደን፥ መፍረድን አስወግደን ፥ እኔም እንዳንተው መሆን የምችል የሀጥያት ብቃት ያለኝ ግን በጸጋ የዳንኩኝ ነኝና ብለን በማሰብ እንጂ እኔ ካንተ እሻላለሁ በሚል አስተሳሰብ መሆን የለበትም::  የእኛ ስራማ የተገለጠ ነው አይደል?  ስለዚህ በዚህ በተቀበልነው ማንነት ሌላውን እንደግፍ::  አካሉን እናንጽ ማፍረስ ቀላል ነው መገንባት ግን ትዕግስትንና ፍቅርን ይጠይቃል::  ሌላውን ስንረዳ እንዳንፈተን ማንነታችንን ጠንቅቀን ማወቅ ነው ብቃታችን እርሱ እንደሆነ መገንዘብ አለብን::


የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ እንደሚል ቃሉ ሕጉ ምንድነው ብለን ስንል የሌላውን ሸክም መሸከም ነው::  እርሱ የእኛን በደል ተሸክሟል ምሳሌያችን እርሱ ነው::  ከፍቅር በቀር እዳ እንዳይኖርባችሁ ተብለናል ለምንሰጠው ፍቅር ምላሹ ጥላቻ ቢሆን እንኳን እንደ የድል እዳ ይቆጠርልናል ማለት ነው::  ለምንሰጠው ፍቅር በምላሹ ፍቅር ላናገኝ የምንችልበት አጋጣሚው ሰፊ ነውና በዚህ ደስ ሊለን እንጂ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም:: አንዳችን የሌላችንን ሸክም እንሸከም እንደአካል ምክንያቱም ብቃትን ይሰጠናልና::  ስሙ ይባረክ ይሄ ጌታ!  አሜን!


እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን

ወደ ገላትያ 6: 3-5

3፤ አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና።4፤ ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤5፤ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።
ስለመንፈስ ፍሬና ስለሚሰጠን ብቃት አይተን ነበር ከዛም በኃላ ደግሞ ሌሎችን በበደል ውስጥ የሚመላለሱትን በየዋህነት ማቅናት እንዳለብን አይተናል::  እንደዚህ ስናደርግ አንዳችን የሌላችንን ሸክም ስንተጋገዝ እንደው ምናልባት በእኛ ውስጥ ለምን ብዬ የሚል ልብ እንዳይገኝ::  ምንም ሳንሆን ምንም የሆንን መስሎን እንዳንታበይ ብቻ እናስታውስ ይህ የምንመካበት ፍሬ የመንፈስ ቅዱስ ነውና ሊያገለግልም ነውና በእኛ ውስጥ ያለው ስለዚህ ሌላውን ለማገልገልና ሸክምን ለመካፈል አንዘግይ ፈጥነን እራሳችንን ያለስስት እናቅርብ::


ይህንንም ስናደርግ የራሳችንን ስራ እንፈትን እንጂ በግብር ውጣ የምንመላለስ መሆን የለብንም::  ሁልጊዜም ሸክምን ለሌላው ብቻ አናምጣ እኛም ውስጥ ብቃት አለና እራሳችንንም እንርዳ ስለዚህ ነው ቃሉ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ የሚለው::  እርስ በእርሳችን ሸክማችንን ካልተሸካከምን እንግዲህ የራሳችንን ሸክም ለብቻችን ልንሸከም ነው ማለት ነው::  ክርስትና ግን የመሸካከም ህይወት ነው በአንድ ወቅት መድከም በሌላ ጊዜ ደግሞ መበርታት አለና የዚህ ዓለም ገዢ ሌት ተቀን እንደሚዋጋን እንወቅ እኛ ካለንበት ነገር ሌላው በቀላል ምክር ሊያወጣን እንደሚችል እንገንዘብ::  ክርስትና የህብረትም የግልም ህይወት ነው::

እርስ በርስ ሸክምን እንሸከም እንረዳዳ የአካል አሰራር እንደዛ ነውና::


የዘራነውን እናጭዳለን

ወደ ገላትያ 6: 6-10

6፤ ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል።7፤ አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤8፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።9፤ ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።10፤ እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።


በብሉይ ኪዳን ለካህናቱ ከሁሉም ነገር ላይ አስራትን ያወጡ ነበር ይህ ግን ለእኛ ለአሕዛብ አዲስ ነገር ነው:: ስለዚህም ነው ጳውሎስ ያንን ስርአት ስለማናውቅ ቃሉን ለሚያገለግሉን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ጋር መልካም ነገር ሁሉ እናካፍል የሚለው::

እግዚአብሔር አይዘበትበትም ሁሉንም ያውቃልና እንደዘራነው እንደዛው እንቀበላለን:: ስለዚህ መልካምን ነገር ሁሉ በማካፈል እንታወቅ::
በሁለት አይነት መንገድ ዘር ይዘራል እርሱም በሥጋ ወይም ደግሞ በመንፈስ የሚገርመው ነገር ሶስተኛ አለመኖሩና ሁለቱም ማጨዳቸው ነው:: የሚታጨደውም በሥጋ ከተዘራ መበስበስ በመንፈስ ከተዘራ ከመንፈስ የዘላለምን ህይወት ያታጨዳል ማለት ነው:: መቼም ማንም ውጤቱን እንደዚህ እያየ የሥጋን ዘር ለመዝራት ይወጣል ብዬ አላምንም:: በመንፈስ ግን እንዴት እንዝራ ብለን መጠየቃችን አይቀርም:: ስለዚህ ዘሩን በሚገባው መሬት ላይ እንዝራ ሥጋዊ ውጤት ለማምጣት ሳይሆን ደስ ያለው በልግስና ይስጥ ስለሚል በልግስና ለወንጌል ስራ እንዝራ::
በተለይም ለቅዱሳን አብዝተን ልንተጋገዝና ልንረዳዳ ይገባል:: ጌታ ሁሉን ሰቶናልና እኛም እየሰጠን መንግስቱን እናገለግላለን::



ከክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ

ወደ ገላትያ 6: 11-14

11፤ እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ።12፤ በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው።13፤ በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም።14፤ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።

እዚህ ጋር የምናየው ሰዎች ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ እና በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ እየወደዱ የመስቀሉን ስራ ያጣምማሉ:: ለሚመጣው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ወይም ባህላቸውን ለማክበር ያህል እንጂ ስለ ህዝቡ ወይም ስለ ወንጌል ግድ ብሏቸው አይደለም እነሱ እራሳቸው የማይፈጽሙትን ሕግ በሰው ላይ ለመጫን የሚነሱት:: ስለዚህ በዙሪያችን ያሉትን የመስቀሉን ስራ የሚያዋድቁትን ሰዎች ከመስማትና ከመሳት ይልቅ ቃሉ ምን ይላል ብለን ወደ ቃሉ መሮጥ ይበልጣል::

ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት
እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። አሜን!
እውነት ግን ሌላ ትምክህት ከየት ይገኛል? ሁሉ ነገር ጊዜያዊና እንከን የሞላበት የማያሻግርም ነው::
ለእኔ ግን ትምክህቴ ሌሎች ገለል የሚያደርጉት እኔግን በስንት ምጥ የተወለድኩበት የጌታዬ መስቀል ነው:: ሃሌሉያ አሜን!


አዲስ ፍጥረት መሆን

ወደ ገላትያ 6:15-18

15፤ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።16፤ በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።17፤ እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ።18፤ ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና::  እውነታው ይሄ ነው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት፤ ለርስቱ የተለየን፤ የንጉስ ካህናት፤ ቅዱስ ህዝብ፤ እርሱን እያብለጨለጭን የምንኖር፤ ልጆች እንጂ ገና በሞግዚት ባርነት ስር ያልሆነ ትውልድ፤ ስጋን ከክፉ መሻቱ ጋር  የሰቀለ ትውልድ፤  በመንፈስ ፍሬ የተሞላ እንዲሁም የራሱን መንገድ የሚጠበጥብ ትውልድ ነን::

አሮጌው ማንነት ተንኮታኩቶ ላይነሳ ወድቋል፤ ዓለምን መውደድ ተጠራርጎ ወቷል በፊቴ የተሳለውን ክርስቶስን እያየሁ ወደፊት መንጎድ ብቻ ከጌታዬ ጋር::  ሃሌሉያ!!!  ይህን ሁሉ የሰጠን በመስቀል ላይ ራሱን ያንገላታው እየሱስ ነው::  ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁንለት! አሜን!!

በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን

በየትኛው ሥርዓት?

አዲስ ፍጥረት በመሆኑ ሥርዓት ውስጥ እግዚአብሔር ሰላምንና ምህረትን ሰቷል::  እርሱ የሰላም አለቃ ነውና አይምሮን ሁሉ የሚያልፍ እንዲሁም ዓለም የማይሰጠውን ሰላም በውስጣችን አፈሰሰው::  እንግዲህ ምን ይባላል? ከማመስገን ሌላ? 
እዚህ ጋር ጳውሎስ በማጠቃለያው እውነቱ ይሄ ነው ትከተሉት እንደሆን ተከተሉት እኔ በእርሱ ሰላምና ምህረት ውስጥ ያለሁኝ ባርያው ነኝ አታድክሙኝ እያላቸው ነው:: 

እኛም የክርስቶን ማህተም ተሸክመናል ማለትም በወዶ ገብ ለዘላለም የእርሱ ሆነናል ማለት ነው::  ለዘላለም እገዛልሀለሁ ጌታዬ::

ወገኖቼ ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።  አሜን!!!




1ኛ ቆሮንቶስ ሰዎች

ምዕራፍ 1

እግዚአብሔር የታመነ ነው

1ኛ የቆሮንቶስ 1: 1-9

ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቅዱሳንን እንዲህ ብሎ ነው የሚጠራቸው:
1.  በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ 

2. የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤
እኛም የዚህ አካል ነን ተቀድሰናል – መቀደስ ማለት አንድ ጊዜ የተሰጠን ነው ክርስቶስ ወደኛ ህይወት ሲገባ እንጂ ሰርተን የምናመጣው አይደለም:: ከእርሱ ተካፍለናልና ይህንን የተቀደሰ የህይወት መንገድ እንጠብጥብ:: እራሳችንን እንቀድስ ብለን ስንጥር የመስቀሉን ስራ ዋጋ እንዳናሳጣው:: ስለዚህም እርኩሰትን እጸየፋለሁ እኔ ተቀድሻለሁኝና ማለትና የዓለምን ከንቱ ነገር ሁሉ እንቃለሁ ብለን ዕለት ዕለትም ይህንን በህይወታችን እየገለጥን እንጉዋዝ::

በክርስቶስ ኢየሱስ ስላመናችሁ በተሰጣችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ሁልጊዜ ስለ እናንተ አምላክን አመሰግናለሁ፤ 
ይህም ማለት:-

1. በነገር ሁሉ 

2. በቃልም ሁሉ 

3. በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና::ይህንን ሁሉ ጸጋ ተቀብለናል ይህንንም ሁሉ ነገር በእኛ ላይ አፍስሶአል::
ስለዚህ በዚህ ሁሉ ባለጠግነት ለምን ተሞላን? ብለን ስንል: የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ የምንጠብቀው ሙሽራ አለን ስለዚህ በዛን ቀን 
የቱ ቀን?!እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል። 

ምን ያደርገናል?
ያጸናችኋል!!!!  አሜን አረ ጎበዝ እጃችንን ዘርግተን እርሱን እንጋብዝ እርሱ እራሱ ያጸናናል::  ስሙ ይባረክ!
ምክንያቱም ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው። 
አሜን!!!!!  ባንታመን እንኩዋን እርሱ ለዘለዓለሙ የታመነ ጌታ ነው::  በጌታችን እንኩራ እራሱን ተማምኖ ጠርቶናልና ብቃታችንም እርሱ እራሱ ነው::  “አልበቃም” የሚልን ዘር እንዴት ቢደፍር ነው ጠላት በእኛ ላይ የሚዘራው???  እርሱ የታመነና ብቁ ነው::  አሜን!! አንድን ነገር እናውጅ እኔ በክርስቶስ ሙሉ ነኝ እንበልና ቃሉን ከራሳችን እናዋህድ::
ቀናችሁ ይባረክ!!

የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን

1ኛ ቆሮንቶስ 1:10-17
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። ይለናል ጳውሎስ: ለምን ብለን ያልን እንደሆነ የሚለያይ መንግስት አይጸናምና:
ስለዚህ ከመካከላችን ክርክር አስወግደን እኔ የክርስቶስ ነኝ ፤  አንተም የክርስቶስ ነህ ፤   አንቺም  የክርስቶስ ነሽ ብለን በአንድ ሀሳብ ተስማምተን ትልቁን የእግዚአብሔርን ስራ እያየን እናገልግል እንጂ ወደፊት የምንለያይ መሆን የለብንም:: የተጠራንለት ጥሪ የከበረ ነው እርሱም:ሞትና ትንሳዔውን መመስከር ነው::
ወንጌልን ልሰብክ እንጂየክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም። 
ወደ ሮሜ 116፤ በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። 
እንበርታ! ይህንን ወንጌል ለሁሉ እናድርስ እዳ አለብንና!
የተባረከ ቀን ይሁንልን!!

የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን

1ኛ ቆሮንቶስ 1: 18 – 31
የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። አሜን የእግዚአብሔር ኃይል ለማወቅ ጥበበኛ መሆን አላስፈለገም እንዲያውም ሞኝ ሆኖ በስብከት ማመን ብቻ ነው የተጠበቀብን::  አይገርምም? 
የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። 
መቼም አውቃለሁ ያለ ጠቢብ ዛሬ በእኛ ሲስቅ አይደንቀንም ምክንይቱም በጥበብ እርሱን ማወቅ አይቻልምና::  ወገኖች ገብቶናል የመጠራታችን ሚስጥርና ጥልቀት? 
ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ::
ዛሬም ጆሮ ለሚሱጠን ሁሉ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው::
ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው።   አሜን!!!!
ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።  ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። ነገር ግን፡— የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ፡ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።   
በክርስቶስ የሆነልን ምንድነው ብለን ብንል:-
1.  ጥበብ – እርሱን እናውቅ ዘንድ

2. ጽድቅ – ተሰጠን በፊቱ መሆን የምንችልበት ወይም ደሞ ጻድቃን ተባልን የእርሱ ለኛ ተቆጥሮ

3.  ቅድስና – እርሱ እራሱ ቀደሰን

4.  ቤዛነት – እርሱ ስለ እኛ ሞተና ከኃጢአትና ከጨለማው አሰራር ዋጀን::


እናስተውል በራሳችን አንዳች ነገር እንዳልሆነ ስለዚህ ቃሉ እንደሚለን ትምክህታችን በርሱ ላይ ብቻ ይሁን::
ትምክህታችን እርሱ እንደሆነ ሲገባን ነገራችንን ሁሉ ወደ ፊቱ እንጥላለን እንጂ በአንዳች አንጨነቅም:: ስለዚህ አሁን የሚያስጨንቀንን ወደ ፊቱ አምጥተን እንጣል ባንጥል ደግሞ ምንም ማድረግ እንደማንችል እንወቅ ለውጥ የለም ደግሞም አይመጣም:: ሊረዳን እጅግ ፈጣን ወደ ሆነው ጌታ እንምጣና እንረፍ በጠላት ሽንገላ ስር አንሁን::
መልካም የተባረከ ቀን!!

ምዕራፍ 2

እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኃይል ይሁን

1ኛ ቆሮንቶስ 2: 1-5
እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። 
1ኛ ቆሮንቶስ 1: 18፤ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። 

1ኛ ጴጥሮስ 1: 3-5፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል። 
ወገኖቼ የዳነው በእግዚአብሔር ኃይል ነው: የምንጠበቀውም በእርሱ ኃይል ነው::  ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል ነው::  ስለዚህ ኃይልን በመግለጥ ማገልገልን እንለማመድ እርሱ ነውና የሚሰራው::
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና።
እኛም ዛሬ እንቁረጥ አልችልምን ትተን በእርሱ እችላለሁ ብለን እንውጣና የጌታን ክብር እንይ ይህ ስራ ለሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ብቻ የተሰጠ አይደለም::  የግማሽ ጊዜ አገልጋይ ብሎ ነገርም የለም ጌታ በግማሽ ስላልሞተ ግማሽ ብሎ ነገር የለም::  ሁላችንም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነንና እንበርታና የተሰጠንን ስራ በእርሱ ኃይል እንስራ:: እርሱም ክርስቶስን መግለጥ ነው::  የምንገልጠውም በጥበብ ቃል ሳይሆን በመንፈስና ኃይልን በመግለጥ መሆን አለበት::  ጌታ ማስተዋልን ይስጠን::  አሜን!
የተባረከ ቀን ይሁንልን::

እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን

1ኛ ቆሮንቶስ 2: 6-17
እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን። አሜን! እንዴት በድፍረት ይህንን ማለት እንደምንችል ላሳያችሁ:
እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።
መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በምኑ በኩል? በመንፈሱ በኩል የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ይገልጥልናል:: የጀመርነው የህይወት ጎዳና መንፈሳዊ ነው:: ስለዚህም
መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።
በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።
ጳውሎስ ደግሞ ደግሞ ስለመንፈስ ነው የሚነግረን ለምን ብለን ስንል?
ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።
ወደፊት ፍጥረታዊ ሰዎች መሆን አይገባንም:: እናስብበት:: ሐዋርያትን ኃይል እስክትቀበሉ ድረስ በእየሩሳሌም ጠብቁ የተባሉበት ምክንያት ይኽው ነው:: ዛሬም ጊዜ ሰቶናልና ኃይልን እንቀበል: ጊዜ በፊቱ እንውሰድ አለበለዚያ ቅጠል ብቻ ሆነን ፍሬ ፈልጎ ሲመጣ እንዳናፍር እንጠንቀቅ:: በእግዚአብሔር መንፈስ ተሞሉ ነፃ ስጦታ ነውና::
የጌታ ፀጋ ይብዛልን!

ምዕራፍ 3

እንደ ሰው ልማድ መመላለስ

1ኛ ቆሮንቶስ 3: 1-3

ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? 
ሥጋውያን ማለት ምን ማለት ነው?1. ቅናት2. ክርክር ያለበት እንደሆነ ጳውሎስ በግልጽ አስቀምጦታል::  ይህ ለምን ይገኝበታል ሥጋዊ ሰው ላይ ያልን እንደሆነ መልሱ ግልጽ ነው አልሞተም!!  በገላትያ 5: 20 ላይ ሁለቱም የስጋ ፍሬ ተብለው ይጠቀሳሉ::  በቅለን ስናበቃ ይህ ፍሬ ከሆነ በእኛ ላይ አንዥርጎ የሚገፕው ምን ይባላል? 
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም።ምን እናድርግ ታድያ?!መንፈሳውያን እንሁን!እንዴት?
1ኛ ጴጥሮስ 21፤ እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ 2-3፤ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ። 
ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ጊዜ እናጥፋ እርሱ እራሱ ያሳድገናል: ጫካውን ይመነጥራል: ይቀድሳል እናም ይለውጠናል እራሳችንን ለመለወጥ መጣር ግን ልክ አትክልትን እንደ መግረዝ ነው አብዝቶ ያፈራል::  ወይም ደግሞ ዱቄት ወንዝ እንደወረደችው ነው እራስዋን ልታቦካ::  እራሳችንን ግን ለሚሰራው ቃል ስንሰጥ እንዴት እንደተቀየርን ሳናውቅ ለውጥ በህይወታችን ይመጣል::  እንጸልይ:ጌታ ሆይ እራሴን መለወጥ አልችልም ቃልህን ሰጥተኸኛል እንዲቀይረኝ እራሴን በፊትህ አመጣለሁ እርዳኝ::  ቃልህ ህያው ነው መንፈስም ነው::  ዕለት ዕለት ቃልህን እንዳነብ ጸጋን ስጠኝ:: አሜን!
የተባረከ ቀን ይሁንልን!

እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር

1ኛ ቆሮንቶስ 3: 4-8
እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም።  የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል።  አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው?  ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ።
የሚያሳድግ እግዚአብሔር ነው!!!! በብዙ አገልጋዮች ተገልግለናል ጌታ እራሱ ግን እረኛችን ነው::  የሚከታተልና ግድ የሚለው ነው እርሱ የተለያዮ አገልጋዮችን ልኮ እርሻው ላይ ያሰራል: እርሻው ግን የጌታ ነው::  በዋጋ ገዝቶ የራሱ አድርጎናልና ቸልታ አይታሰብም አባቴ ይሰራል እኔም እሰራለሁ ያለን ጌታ መንፈስ ነው አይደክምም! አይታክትም! አይኖቹ ሁልጊዜ በእርሻው ላይ ናቸው::  
እንግዲህ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ነው ማለት ነው ጉዳዮ ስለዚህ ወደፊቱ እንቅረብ ሳይፈርድ እየራራ የሚያሳድግ አባት አለን::  ሲደክመን የሚሸከም የሚያባብል ጌታ::  እርሱ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ ከሆነ በእርሱ ደስ ይበለንና እርሱን ወደ መምሰል እንሂድ:: እራሳችንን መቀየር እንደማንችል ግን እንገንዘብ::  እርሱ ድሮ ጥለነው የመጣነው የድካም መንገድ ነው አሁን በመረቀልን በዚህ በአዲስ መንገድ ላይ ነው ያለነው::
የጸሎት ርዕሰጌታ ሆይ እነሆ በፊትህ ነኝ እኔ የአንተ ነኝና ስራኝ: አሳድገኝም እንደቃልህ የምትልከውንም ሰራተኛ ልከህ አስተምረኝ እርሻህንም አሳምር: : በእየሱስ ስም አሜን!
የተባረከ ቀን ይሁንልን!

ማነን?!

1ኛ ቆሮንቶስ 3: 9
የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። 
ሕንፃ ወይም እርሻ በራሱ ምንም አያደርግም ካልተሰራበት::  አይደል?  ስለዚህ ወደ ሕንፃችን ወይም ደግሞ ወደ እርሻችን የጋበዝነው  እየሱስ በስራ ላይ ነው::  ገዝቶን በማሰማመር ላይ ይገኛል ታድያ እንደወደደ አድርጎ እኮ መስራት በዋጋ የገዛው የባለቤቱ ውሳኔ ነው::  አይደለም እንዴ?! ለዚህም ነው ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነን የሚለው ቃሉ::
ሕንፃው ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ብዙ ነገር ሊፈጠር ይችላል ግን ማሰብ ያለብን ሕንፃው እራሱን መቀየር እንደማይችል ነው ስለዚህም መላላጥ ትተን ለተፈጠርንለት አገልግሎት እንዋል::  ለሆስፒታልነት የተገነባን ሕንፃ የገበያ ስፍራ ብናደርገው አስቡት እስኪ የሚባክነውን ሪሶርስ?  ማነን?!  ሲጠራን ገና ምን እንደሚሰራብን ወስኖአል እኮ መጠየቅ እና ማወቅ ያለብን ማነኝ ነው::  
እውነት ማነህ? ማነሽ?
መቼም ጊዜውን የሚያባክን አይደለም የኛ ጌታ እርግጠኛ ነኝ ማንነት አለን ወደ ቤቱ እስከጠራን ድረስ::  ዳር ቆመን የምንታዘብ መሆን የለብንም እንግባ ወደ መሀል የአንተን ስራ ማንም አይሰራልህም ያንቺንም እንደዛው::  ስራችን ቁጭ ብሎ እኛኑ ይጠብቃል:: በጌታ ልብ ሰው እንደመደበ ነው የሚያውቀው ምክንይቱም የመስሪያውን ሪሶርስ ሁሉ በጠየቅን ጊዜ ለማቅረብ ሰማይ እየጠበቀ ነው::  በጸጋ ላይ ጸጋን ደሊቨር ለማድረግ::  የመንግስቱ ስራ የሚሰራው በጸጋ ነው::
የዮሐንስ ወንጌል 1: 16፤ እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና:: 
የጸሎት ርዕሰማንነቴን አሳውቀኝ ምንድነው በእኔስ መስራት የምትፈልገው?
የጌታ ክብር በእያንዳንዳችሁ ሲገለጥ  ለማየት እቸኩላለሁ::  
የጌታ ሰላምና ጸጋ ይብዛልን! አሜን!

የእያንዳንዳችን ሥራ ይገለጣል

1ኛ ቆሮንቶስ 3:10-15
ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል
እግዚአብሔር አይዘበትበትም እርሱ ትልቅ ነው እንጠንቀቅ::  ስራችንን በግብር ይውጣ ወይም ደግሞ ሲመቸን ብቻ አልያም ደግሞ ሲመስለን እንዳንሰራ ብቻ አንድ ቀን:-
በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።በእሳት ውስጥ አልፎ ወይ ያሸልመናል ወይ ደግሞ መዳናችን በጭንቅ ይሆናል
ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል። 
ስለዚህ ወገኖቼ እንዴት በቤቱ ልንመላለስ እንደሚገባን እናስተውል::  
እንዴት እናገልግል?
1.  (በተሰጠን ጸጋ) የእግዚአብሔር ጸጋ       እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ       ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን       መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። 2.  (በጥንቃቄ) እያንዳንዱ ግን በእርሱ       ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። 3.  ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ       መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥       እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 
አልረፈደም ለማገልገል ወደ እርሻው ባለቤት ቀርቦ ስራ ስጠኝ ማለት ነው::  እርሱ ያሰማራናል ወደምናፈራበት እርሻ ይልከናል ስለዚህ እንጸልይ::
የጌታ ጸጋ ይትረፍረፍላችሁ! አሜን! 

የእግዚአብሔር መንፈስ መኖርያ

1ኛ ቆሮንቶስ 3: 16፤ 
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? 
‘ቤት’ ከመሆን ወደ ‘ቤተ መቅደስ’ ወደ መሆን ምን ቀየረን?  እየሱስን የህይወታችን አዳኝና ጌታ ባደረግነው ጊዜ ያን ጊዜ በደሙ ዋጅቶ ቀደሰን እናም አብሮን ይኖር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ መጣ::  እኔ ብሄድ ይሻላል አጽናኙ ይመጣል ብሎ ነግሮን ነበር ለእርሱም መጠንቀቅ አለብን ዓለም ባያውቀው እንኩዋን እኛ በደንብ እናውቀዋለን::  እኔ መንፈስ ቅዱስን አልተሞላሁም ብላችሁ እንዳታስቡ ተሞልታችሁዋል ቃሉ እንደሚል ለቤዛነት እንደታተምን ይነግረናል::
ስለዚህ በዋጋ የገዛን መኖርያዎቹ ያደረገን እርሱ እራሱ ነው:: ቤተ መቅደሱ ነኝ ብለን አፋችንን ሞልተን ለመናገር ያበቃን እርሱ ነው::  የሆነውን ሆነናል የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ::  ይህ ቤተ መቅደስ ደግሞ ቅዱስ ነው የተቀደሰውም በበጉ በእየሱስ ደም ነው::  አሜን! 
በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ መሸጥና መለወጥ አይታሰብም ቤቴ የፀሎት ቤት ይባላል ብሎ የቤቱ ቅናት እንደሚበላው ጌታ አሳይቶናል::  ታድያ ዛሬ ቤቱን በምን ሞልተነዋል?  በጸሎት: በቃል: በዝማሬና በመንፈሳዊ ቅኔ? ወይስ በምን? ኮተቱን ሁሉ ሰብስባችሁ አውጡ::  ጌታን ብቻ እናስብ ወደኛጋ ለመኖር የመጣውን እንግዳ እንከባከብ: እናስተናግደው: አንዝጋው እናውራው እርሱ ይህንን ይወዳልና::  አስቡት እስኪ እንግዳ ቤታችሁ መቶ ባታናግሩት ምን ይሰማዋል ምናልባትም ተነስቶ ይወጣል መንፈስ ቅዱስ ግን ታግሶ እየጠበቀን ነው::  አረ እናስተውል ትልቁ እንግዳ በቤት ነው!!!!!! ግድ መንበርከክ የለብንም ከርሱ ጋር ለማውራት እርሱ አባታችን እኮ ነው::
የጸሎት ርዕሰ1.  ንስሀ እንግባ እንደሚገባ       ባላስተናገድነው2.  ጸጋን እንጠይቅ እርሱን መፈለግ       በልባችን እንዲገኝ3.  ሁልጊዜ እናውጅ መቅደሱ       እንደሆንን
የጌታ ጸጋ ይብዛልን::  አሜን!!

ቅዱስ ነን

1ኛ ቆሮንቶስ 3: 17፤ 

ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ። 
ባለፉት ቁጥሮች ላይ ማነን ብለን ከዛም ደግሞ የእግዚአብሔር ህንፃ ወይም እርሻ እንደሆንን አይተን ነበር:: እንደዚሁም ደግሞ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆንና እርሱ እንደሚኖርብን ተነጋግረናል::  ታድያ እርሱ የሚኖርበትን ቤተ መቅደሱን ማፍረስ ጥሩ ነው? ምን በወጣኝና!እንደምትሉኝ እርግጠኛ ነኝ::  እንደዚህ ነው ጉዳዩ: ሰውን ሁሉ በክርስቶስ እንወቅ ይለናል ጳውሎስ ያን ጊዜ በምናየው ሁሉ ላይ መፍረድን እናቆምና ወደ መማለድ እንሄዳለን::  በነገር ሁሉ ከእኛ አፍ መውጣት ያለበት የሚያንጽና በጨው የተቀመመ መሆን አለበት ምክንያቱም የምናናግረው ሰው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና:: እንዴት ቅዱሳንን ትሪት እንደምናደርግ እናስተውል::
ሌላው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ መሆኑን እናያለን::  ቅዱስ ነኝ ለማለት አፋችን መተሳሰሩና መክበዱን አስተውላችሁታል? የደፈርን ያህል ነው የሚሰማን::  ለምን?!  ይህ የጠላት ሽንገላ ነው ቃሉን አናሻሽለውም ናችሁ ካለ አሜን ነው መልሱ::  የቁጫጭዋ ታሪክ መጣብኝ ድልድዩን ከዝሆን ጋር ስትሻገር ነቀነቅነው አይደል እንዳለችው ነው::  ትሁት ሊያደርገን ነው የሚገባው እንጂ ሊያስታብየን አይደለም::  እርሱ ነው የቀደሰን የእኛ ቅድስናማ ከምን ጋር እንደተወዳደረ እናውቃለን::የምተውላችሁ ነገር 1.  ቅዱሳንን በፍቅር ተቀበሉ: አትሙ:      ከትቻላችሁ ተሸከሙ:: 2.  እኔ ቅዱስ የሆንኩ የእግዚአብሔር መቅደስ ነኝ ብለን እናውጅ::
የተባረከ ቀን ይሁንልን::  አሜን!

ሞኝነት ይመረጣል

1ኛ ቆሮንቶስ 3: 18-19
ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና። 
በስብከት ሞኝነት አምነን ከሞት ወደ ህይወት መጣን  ታድያ አሁን የምን ብልጣ ብልጥ ለመሆን መጣር ነው የያዝነው?  በዛው እኔ አላውቅም አንተ ታውቅልኛለህ ብንል በእርሱ ላይ ብንታመን አይሻለንም?  ቃሉም በእኛ ዘንድ ክቡር መሆን አለበት እንደሚለንም ነን::  የዝችን አለም አስተሳሰብ ሎጅክ የሚሰጥ ነገር ስንፈልግ የሚፈጥረውን: ታሪክ የሚቀይረውን የእግዚአብሔርን ቃል ቸል እንዳንል ያስፈራል::  ጉባኤ እግዚአብሔር ቢጠራና ሕዝቤን እንዴት ላሻግረው ባህሩን ቢለን ምናልባትም ሎጅካሉ አስተሳሰባችን አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ነው ስለለመደ ታናል ስራ ወይም እንደዚህ አድርግ እንደዛ አድርግ እንለው ይሆናል እንጂ መቼም ንፋስን አንፍስ አንለውም ቀይ ባህርን ለመክፈል::  ንፋሱም ሲነፍስ ብናይ አረ ይህንን ውሳኔ አስተካክል እያልን እንቅፋት እንሆንበት ነበር በአስተሳሰባችን ካልተቀየርን በስተቀር ስራውን አናይም::  ልክ የአንድ ስልክ ቻርጀር ለሌላው እንደማይሰራ እኛም ኮባተብል አንሆንም በመንግስቱ ስራ ውስጥ::  አካሄዳችን ሁሉ ሎጅክን የተንተራሰሰ ነው ከዚህ መውጣት አለብን::  
የገባው ደግሞ እነዚህ አጥንቶች በህይወት ይኖራሉ? ሲባል አንተ  ታውቃለህ ብሎ አብሮ ሰራተኛ  ሆኖ ድንቅን ያያል:: ከሎጅክ እንውጣ በእጃችን ያደረገው በትር ባህር ይከፍላል::  በእጅህ ምን አለ? ነው ሁልጊዜ ጥያቄው ጥቂት ዘይትም ቢሆን  እሱ በቂ ነው በጌታ እጅ ሲገባ የሚለንን በሞኝነት ስናደርግ ድንቅ ይሆናል::
ዛሬ የምለምናችሁ ነገር ዘመናችሁን አትፍጁ በመጏተት ስለዚህ ዛሬ እጅ ወደ ላይ: እንማረክና ድንቅ በህይወታችን እንይ::

እናንተም የክርስቶስ ናችሁ

1ኛ ቆሮንቶስ 3: 21-23
ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።
የእግዚአብሔር ሀሳብ ዓለምን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው:: ስለዚህም በክርስቶስ ውስጥ ያለው ሁሉ የእኛ ነው:: እራሳችንን ከመንግስቱ ወይም ከአካሉ ውጪ አንየው:: እኛ በክርስቶስ ውስጥ ነው ያለነው:: ትምክህታችንም መሆን ያለበት ባስጠለለን ጌታ ላይ ነው:: ከእርሱ ውጪ ትምክህት ከእኛ የራቀ ይሁን በጥበባችን አልዳንን ወይም እርሱን ወደማወቅ በምርምር አልደረስን ብሞኝነት አመነው ገባን ትልቁ የእግዚአብሔር ሚስጥር እየሱስ:: ስለዚህ መከፋፈልን ትተን በክርስቶስ አንድ አካል እንደሆንንና አካሉም በህብረት ዝንፍ ሳይል አንዱ አንዱን እየረዳ እንዲሁም ሁሉም የራሱን ሚና እየተጫወተ እንደሚኖር እንዲሁ ይሁንልን::እኛ የክርስቶስ እንጂ የራሳችን አይደለንም እርሱ በእኛ ይኖራል:: አሜን ይኑር: ይክበር: ከፍ ከፍ ይበልና ይታይልን የልቡ ሀሳብ በሰማይ ያለው በእኛም ውስጥ ይሁን::የተባረከ ቀን ይሁንልን:: አሜን!

ምዕራፍ 4

በአንዳች አትፍረዱ

1ኛ ቆሮንቶስ 4:1-5
እኛ የክርስቶስ እንደሆንን በትናንትናው ቃል ተነጋግረናል ታድያ ማን በማን ላይ መፍረድ ይችላል? ቢፈርድስ ምን ሊመጣ ይችላል? ህብረትን ከማፍረስና የጌታን ስራ ከማዘግየት ሌላ::
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ በራሴ ላይ ምንም አላውቅምና፥ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ እኔን የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። እርሱ ሲፈርድ ግን:-
1. በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ 2. የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ 3. በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል።
ይህ ማለት ግን የጌታ ቤት ስራ ሲበደልና ሲጠፋ ዝም ማለት አይደለም በፍቅር ሳንፈርድ ማቅናት አለብን ለአንድ ግብ:: ግቡም የጌታ ስራ እንዲሮጥ:: እንዴት ማድረግ እንችላለን ካልን:-
1. ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ 2. አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። 3. ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ተብለናል!
እንደ አካል ከተቀባበልን በመፍረድ መጠፋፋቱ ይቀርና በንጹ ልብ እንተናነፃለን:: ልናገለግል የተነሳነው ጌታን ነው ተጠሪነታችንም ለእርሱ ነው:: በቅንነት እንሰራለን ምስጋናን ከጌታ በመጨረሻ እንቀበላለን:: ስራው የጌታ እኛም የጌታ!
የጌታ ጸጋ ይብዛልን:: አሜን!

አልታበይ

1ኛ ቆሮንቶስ 4:6-7
ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ፡— ከተጻፈው አትለፍ፡ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ።
መታበይ እመውደቅ አፋፍ ላይ ሲደረስ ያለ ምልክት ነው ስለዚህም አውቀናል ብለን ከተፃፈው አንለፍ:: ድንቅና ተአምራት ቢደረጉ እንኳን ከእኛ እንዳልሆነ ተረድተን ሙሉውን እውቅና ላደረገው እንስጥ:: እንጂ ይህን ለማሳየት ከበሮ አናስመታ:: ማስመታቱ ቢያስፈልግ ኖሮ እንደ ጳውሎስ የሚያስመታ የለም ነበር የሚለን ግን በወንድማችን ላይ አንታበይ በእኛ የሰራው ጌታ ነው እያለን ነው:: የሁሉ አይን ወደ ጌታ እንዲሆን እናድርግ:: ምክንያቱም:-
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?
የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ:: እርሱ ለትሁታን ጸጋን ይሰጣል::ዛሬ ልባችንን በፊቱ እንፈትሽ እንሻላለን የምንላቸውን ነገሮች ሁሉ እንይና ከጌታ በተሰጠን ጸጋ እንዳደረግን አውቀን ጌታን እናክብር ከጸጋው ወድቀን እንዳንገኝ::መልካም ቀን!

እራስን መካድ

1ኛ ቆሮንቶስ 4: 8-21
በዚህ ክፍል ላይ ሐዋርያው በቃን፤ ጠግበናል፤ ነግሰናል፤ ማንም ምንም አያስፈልገንም ላሉት የቆሮንቶስ ሰዎች የእነሱንና የሐዋርያት ህይወት እያነፃፀረ ያሳያቸዋል:: ለምሳሌ:-
እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን እናንተ ግን ኃይለኞች ናችሁ፤ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ እኛ ግን የተዋረድን ነን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።
ወደ ጉዳዩ ሲገባ ዋናው ሊጽፍ ያነሳሳው ነገር ወቅሶ ጉድለታቸውን ብቻ አሳይቶ ሊዘጋው አይደለም:-
እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም።
የመልክቱ ዋና የሚከተለው ነው:-
እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ።
ከላይ በንጽጽር እንዳስቀመጠው ህይወቱ ጌታን በማክበር እንጂ በትእቢት አልነበረም የሚመላለስ የነበረው::
ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን:: እራስን መካድ እዚህጋ ነው ያለው::
እኛም ዛሬ በጉዟችን ዝቅ ብለን ጌታን እየመሰልን እራሳችንን እየካድን ልንመላለስ ይገባል::
ተባረኩ

ምዕራፍ 5

ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና

1ኛ ቆሮንቶስ 5: 1-13

በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። 2፤ እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። 3-4፤ እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ 5፤ መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው። 6፤ መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? I7፤ እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ 8፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም። 9፤ ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ። 10፤ በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን አላልሁም፤ ይህስ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር። 11፤ አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። 12፤ በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? 13፤ በውጭ ባሉቱ ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።

ሐዋርያው የቀደመውን ምዕራፍ ሲዘጋው
1ኛ ቆሮንቶስ 4: 20-21 የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን?
ብሎ ስለሰማው ነገር መውቀስ ይጀምራል በአህዛብ መካከል እንኳን የማይታይ ሐጥያት በእግዚአብሔር ቤት እንዳለ ይጠቅስና ፍርድን እንደፈረደበት ይናገራል::
ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም።
ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ።
ሁላችንም አንድ ቀን በፊቱ እንቀርባለን አገልግሎታችንም በእሳት ውስጥ ያልፋል በውጤቱም መሰረት ሽልማት አለ:: ስለዚህ ፋሲካችንን ክርስቶስን ደስ ለማሰኘት እንኑር::
መልካም ቀን!

ምዕራፍ 6

ወንድም ወንድሙን አይክሰስ

1ኛ ቆሮንቶስ 6: 1-11
የወንድሞች ከሳሽ ተብሎ የተባለው ሰይጣን እያለ እኛ ወንድማችንንልንከስ አይገባም ሲሆን መታገስና በየዋህነት መንፈስ ማቅናት እንጂ::
ማን ነበርን የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ የማንችል ነበርን
አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን?
አሁንስ ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል። 
ታድያ መካሰስን ምን አመጣው?!
በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? 
እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?  እንግዲህ ጉድለታችን ምንድነው?!  አለመሞት ነው: ብንሞት ኖሮ ክርክርና መካሰስ በእኛ ዘንድ አይገኝም ነበር::  በእኛ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም ይሰደባል?!  ይህ እንዳይሆን ያለፈውን የማያስፈልገውን የህይወታችንን ዘመን ረስተን አዲሱን ማንነታችንን እናጎልብት አላውቃችሁም ከምንባል ዛሬ ከጌታ ጋር ጊዜ እናጥፋና (በተለይ በዚህ በኮቪድ 19 ዝግ ላይ) እንቀየር አላውቃችሁም ማለት እኮ እኔን አትመስሉም ማለቱ ነው::  

የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ነን

1ኛ ቆሮንቶስ 6:12-20
ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።
ስጋችን ከርሱ የተቀበልነው እንደሆነ አስተውለናል? የተቀበልነውን እንደገና ደግሞ ዋጀቶ የራሱ አደረገን:: ቤተ መቅደሱ ስለሆንን እንዴት እናክብረው ታድያ በስጋችን?
ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።
ይህ ማለት ደግሞ:-
ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና።
ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። እግዚአብሔርም ጌታንም አስነሣ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል። ስለዚህ ዛሬ እንንቃ ከእርሱ ጋር እንተባበር አንድ መንፈስ ነንና:: ቃሉ እንደሚለን ነን ምንም ማሻሻያ አናድርግ አንድ መንፈስ ነን ብለን ስንል እርሱ በእኛ እየኖረ ነው ማለት ነው::ጌትን በዚህ እናመስግን አንድ መንፈስ ከእርሱ ጋር ያደረገንን::ጌታ መልካም ነውና ከመልካምነቱ ያጥግበን:: አሜን!

ምዕራፍ 7

ጋብቻ

1ኛ ቆሮንቶስ 7: 1 -16
በዚህ ክፍል ላይ የቆሮንቶስ ሰዎች ስለትዳር የጠየቁትን ጥያቄ የሚመልስበት ነው::
የሚዳስሳቸውም ሀሳቦች:-

1.  ለእያንዳንዱ ለራሱ ትዳር ይኑረው
2.  ላላገቡና ለመበለቶች 
3.  ያላመነ ላገቡ
ከላይ ላሉት ሀሳቦች መመሪያን ይሰጣል
በትዳር ላይ ላሉ:-
ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት።
ሀ)  ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ 

ለ)   እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋሐ)  ሚስትም ባልም በገዛ ሥጋቸው ላይ ሥልጣን የላቸውም የርስ በርስ ነው እንጂ  

መ)  ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ 

ሠ)  ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ  አብራችሁ ሁኑ።

ረ)   ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፥ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፥ ባልም ሚስቱን        አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፥ እኔ ግን አላዝም፥ ጌታ እንጂ። 
ላላገቡ
ሀ)  ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፡—  እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤ 

ለ)  ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል  መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ። 
ያላመነ ላገቡ

ሀ)  ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር  ልትቀመጥ ብትስማማ፥ አይተዋት፤ 
ለ) ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር  ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፥     አትተወው። 
ሐ) ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ     ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ     ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው። 
መ) የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ     በሚመስል ነገር አይገዙም፤     እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል። 
ሠ)  አንቺ ሴት፥ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ አንተ ሰው፥ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ? 

በዋጋ ተገዝታችኋል

1ኛ ቆሮንቶስ 7: 17-24
ከዚህ በፊት ባለው ክፍል እንዳየነው ስለ ጋብቻ መክሯል::  አሁን ደግሞ ስለ ቅዱሳን ስራ ይናገራል::  ከመዳንችሁ በፊት በማኽበረሰቡ ውስጥ የነበረውን ባህል ቀጥሉ ይላል ለምሳሌ
1.  ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ 2.  ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ። መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ከንቱ ነው፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ። 3.  ባሪያ ሆነህ ተጠርተህ እንደ ሆነ አይገድህም፤ አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል። 4.  ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ ነው። 
ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር። 
ለእኛ ዛሬ የሚቀርልን ነገር ቢኖር በጌታ የሆነ ሰው በዓለም ያለው ስራው ምንም ሊለያየን አይገባም ሁሉን በፍቅር እና በአክብሮት እንቀበል ምክንያቱም ሁላችንም እኩል ነው ዋጋችን እሱም የከበረው የእየሱስ ክርስቶስ ህይወት ነው ዋጋችን::  ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ነን::  በዋጋ ተገዝታችኋል!!

ምክርን እመክራለሁ

1ኛ ቆሮንቶስ 7: 25-40
ምዕራፉን ስንጀምር እንዳየነው እዚህም ቦታ ላይ ለጥያቄያቸው መልስ እየሰጠ ነው:: እዚህጋ እንደሚናገረው እኔ እመክራለሁ ይለናል::
ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ። እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤
1. ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። 2. በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ 3. በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ። 4. ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር። 5. ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።
6. ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት። እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት::
ይህን የሚመክርበትን ምክንያት: –
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኗል፤ የዚች ዓለም መልክም አላፊ ነውና።
ያገባንም ያላገባንም የጌታን መምጣት እንጠባበቅ:: ማራናታ!

ምዕራፍ 8

ከአንዱ በቀር ማንም አምላክ የለም

1ኛ ቆሮንቶስ 8: 1-13
እንግዲህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 
መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።
ከአምላካችን ሌላ አምላክ የለም ስለዚህ በእኛ ባህል ውስጥ ወርንና ቀናትን እያስታከከ በብዙዎቻችን ቤት ወይም ጎረቤት ሲሰዋና ሲበላ እያየን ወይም እየተካፈልን አድገናል ዛሬ ግን ምን እናድርግ?  እንዴት እንመላለስ ነው ጥያቄው::  ቃሉስ ምን ይላል?
መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም። 
መብላት አለብን ለጣዖት የተሰዋ?
ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። 
አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤት በማዕድ ስትቀመጥ አንድ ሰው ቢያይህ፥ ደካማ ሰው ቢሆን ለጣዖት የተሠዋውን ለመብላት ሕሊናው አይታነጽበትምን? በአንተ እውቀትም ይህ ደካማ ይጠፋል፥ እርሱም ክርስቶስ የሞተለት ወንድም ነው። እንዲህም ወንድሞችን እየበደላችሁ ደካማም የሆነውን ሕሊናቸውን እያቆሰላችሁ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። 
ዳሩ ግን ይህ መብታችሁ ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ። ነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም፤ አንዳንዶች ግን ጣዖትን እስከ አሁን ድረስ ስለ ለመዱ፡— ለጣዖት የተሠዋ ነው፡ ብለው ይበላሉና ሕሊናቸው ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል። 
ስለዚህ ጌታን ከምንበድል ሌላውን በማደናቀፍ ባንበላስ?!
ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ ማንም ግን እግዚአብሔርን ቢወድ እርሱ በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው። 

ምዕራፍ 9

ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ

1ኛ ቆሮንቶስ 9:1-27

ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።
በዚህ ምዕራፍ ላይ ጳውሎስ የሚዳስሰው ስለ እርሱ መጠራትና ሐዋርያ መሆን ነው:: ሐዋርያ ለመሆኑም የሚሰጣቸው ማስረጃ እንደሚከተለው ነው
እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ።
ከቤተክርስቲያን እሱና በርናባስ ነበሩ ጥቅም የማይቀበሉት ግን መብታቸው ሆኖ ሳለ በራሳቸው እየሰሩ ይተዳደሩ ነበር:: ይህም ነገር እርሱ ሐዋርያ ባይሆን ነው ወደሚል ድምዳሜና እኔ የእከሌ እኔ ደግሞ የእከሌ የሚል ክፍፍል ውስጥ ያስገባቸው::
እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና።
ስለዚህ አገልጋዮች መንፈሳዊውን ዘርተው መኖሪያቸውን ከቤተክርስቲያን ማግኘት መብታቸው ነው ማለት ነው::
እኛ መንፈሳዊን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር እኛ ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? ስለዚህ ስለሚያገለግሉን ወገኖች እግዚአብሔር ይመስገን እንባርካቸው ደግሞም እንፀልይላቸው::
በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤
አሜን ነፋስን እንደሚጎሽም አይደለም የእኛ ነገር ስለዚህ እንበርታ ፥ ሩጫችንን እንሩጥ ፥ ነፍሳትን ለጌታ እንማርክና የማይጠፋውን አክሊል እንቀበል::ዛሬም ስለምድራችን እንፀልይ እግዚአብሔር ስለደሀው እንዲነሳ::

ምዕራፍ 10

ከዓለቱ ከክርስቶስ ጠጥተናል

1ኛ ቆሮንቶስ 10:1-12

ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ 
ደመናው ለእስራኤላውያን ምን ነበር የሆነላቸው ብለን ብንል:- 1.  በቀን የደመና አምድ ከፀሐይ      ሊከልላቸው2.  በለሊት የእሳት አምድ ጨለማውን      አብርቶ ሊመራቸው3.  በእስራኤልና በግብጽ መካከል ገብቶ      ሊለይና ሊጠብቃቸውይህ ሁሉ እንክብካቤ ነበረ በዙሪያቸው እነሱ ግን: 
ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ።
የ ቆሮንቶስ ሰዎች ዙሪያቸውን ጣኦትን በሚያመልኩ ወገኖቻቸው መካከል የሚኖሩ ናቸው::  ጣኦት ማምለክ ባህልም ነው አሁን አዲስ ሐይማኖት መጣና እንዴት ያቁሙት? አለማምለክ ከጤነኝነት ከማያስመድብ ማህበረሰብ ውስጥ እየኖሩ ያሉበት ነገር ዋጋ ያስከትላል መነጋገርያም ያደርጋል::  ጳውሎስ ግን የሚላቸው ነገር ለእስራኤልም አልበጀም ጣኦትን ማምለክ ከእያሱና ከካሌብ በስተቀር ሁሉም ምድረበዳ ቀሩ እግዚአብሔርግን ልክ እንደናንተው ተንከባከባቸው ጣኦትን ሲያመልኩ ግን:-
እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና። እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን። 
ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። 
ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።
ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።  እንግዲህ እንደተወደዱ ልጆች እንመላለስ::

ከፈተናው ጋር መውጫውን ያደርግላችኋል

1ኛ ቆሮንቶስ 10: 13፤ 

ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 
ማነው ግን እየፈተነን ያለው?!  ያ ክፉ ነው እንጂ እግዚአብሔርማ አይፈትነንም:
የያዕቆብ  መልእክት 1:13፤ ማንም ሲፈተን፡— በእግዚአብሔር እፈተናለሁ፡ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። 
ለምን አይፈትነንም ብለን ስንል እርሱ እራሱን የሰጠ እውነተኛ እረኛችን ነውና::
ዮሐንስ 10: 14-15፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ። 
ስለዚህ እላችኋለሁ እያንዳንዱ ፈተና መውጫ አለው እንደጠላት ሀሳብማ ቢሆን ባልወጣን ነበር ቃሉ እንደሚል ከምንችለው በላይ እንድንፈተን አይፈቅድም! ሃሌሉያ!! አሜን!
ጸሎታችን መሆን ያለበት መውጫ እንዳደረክልኝ እርግጠኛ ነኝ አሳየኝ መውጫውን መሆን አለበት እንጂ ከጨለማው ዓለም የምንሰማውን የአለቀልህ ዜና አናስተጋባ::  በዚህ ቃል ልባችንን እናጽናና እግዚአብሔር የታመነ ነው::   በአይምሮአችን መታደስ እንለወጥና ቃሉ እንደሚለን እንኑር::  ቃሉን ከራሳችን ጋር እናዋህደው:: 
ታድያ ሁሉ ፈተና መውጫ አለው እያልሽ ነው ብትሉኝ አፌን ሞልቼ አዎን እላለሁ:: 
ስለአገራችን እንፀልይ ሰላምና እረፍት እንዲሆን እንዲሁም እርሱን መፍራት በምድራችን ላይ ይሁን::

ጌታን እናስቀናውን?

1ኛ ቆሮንቶስ 10: 14-22
የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? 
ምዕራፉን ሲጀምር ጀምሮ እስከዚህ ድረስ ደግሞ ደጋግሞ የሚነግራቸው ነገር ስለ ጣዖት አምልኮ ነው::  በተለይ እዚህ ጋር ጠበቅ አድርጎ ሽሹ ነው እያለ ያለው::
ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። 
ለምን ይሸሻል ጣዖትን ማምለክ?  ምክንያቱም የነፍስ ትስስር አለበት ለጣዖት የተሰዋን መብላት በክርስትናው የጌታን እራት እንደመብላት ነው:: በጨለማው ዓለም ምን ኮፒ የማይደረግ አለ?  ኦርጅናል የለው!
ስለዚህ በተቃራኒው ለአጋንንት የተሰዋውን ስንመገብ የአጋንንት ማኅበረተኞች እንሆናለን ማለት ነው 
የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? 
ይሄንን ስጋና ደሙን ስንወስድ ከእኛ ጋር ህብረት እንደሚያደርግ ግልጽ ነው መቼም::  ስለዚህ ከእርሱ ጋር አንድ ስጋ እንሆናለን ቃሉ እንደሚለን::
አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው እላለሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን?  አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። 
ከዚህ በኃላ መቼም ይህንን ነገር በቀላሉ እንደማታዩት አምናለሁ ሌሎችንም ለማቅናት ቃሉን ማወቅ መልካም ነው::ጌታ አይናችንን ይክፈት!  አሜን!

ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉ

1ኛ ቆሮንቶስ 10: 23 – 33
እኛ ግን ጌታን ልናመልክና ደስ ልናሰኝ ከዓለም ተለይተናል::
እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።
እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ፥ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ።
ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም።
1. በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤
2. ከማያምኑ ሰዎች አንዱም ቢጠራችሁ ልትሄዱም ብትወዱ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ።
3. ማንም ግን፡— ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው፡ ቢላችሁ ከዚያ ካስታወቃችሁና ከሕሊና የተነሣ አትብሉ፤
በዚህ ሁሉ ውስጥ ሁሉ የተፈቀደልን ነን ብለን የማያንጽና የማይጠቅም ነገር አናደርግም ነገር ግን የክርስትና መሰረቱ ፍቅር ነውና እውነትን በፍቅር ይዘን እሩጫችንን በትዕግስት እንሩጥ:: ለማንም ማሰናከያ ሳንሆን ሁሉን ደግሞ ለእግዚአብሔር ክብር እያደረግን እንመላለስ:: ዓይናችን በጌታ ላይ ይሁን እሱንም ደስ ለማሰኘት እንኑር::

ምዕራፍ 11

ክርስቶስን እንምሰል

1ኛ ቆሮንቶስ 11: 1

እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ። 
እንዴት ያለ ልበ ሙሉነት ነው?  እኔስ እየመሰልኩት ነው?  እራሴን መጠየቅ አለብኝእስኪ ክርስቶስ እንዴት ተመላለሰ ብዬ ልጀምር:-
1.  ለራሱ አልኖረም2.  የሱ መብል የላከውን ፈቃድ ማድረግ      ነበር3.  ሳይመቸው እንኳን የአንተ ፈቃድ      እንጂ የእኔ አይሁን የሚል ነበር4.  ክብሩን ሁሉ ትቶ ዝቅ አለ5.  የበደሉትን ይቅር አለ6.  ትተውት የሄዱትን ሐዋርያት እንኳን       ሳይወቅስ ሰላም ለእናንተ ይሁን አለከጠቀስኩት በላይ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል ስለ እየሱስ::
እኔ ታድያ እንዲህ እንደ ጳውሎስ ለማለት እችላለሁ?
ከሰማይ የተሰጠኝ ብቃት አለ
እንዴት ቢባል የሚያስፈልገኝ ጸጋ ሁሉ ተሰቶኛል እርሱን ለመምሰል::  በደጅ ሆኖ ማንኩዋኩዋቱን ሰምቼ ወደ ህይወቴ በጋበዝኩት ጊዜ ከእኔ ጋር ለመኖር መቷል::  ስለዚህ እኔ አሁን የምኖረው ኑሮ ለሞተልኝ: ለዋጀኝ ጌታ ነው ብዬ ዕለት ዕለትም መስቀሉን ተሸክሜ እከተለዋለሁ::  ደግሞም ወደ ህይወቴ ሲገባ አዲስ ፍጥረት ሆኛለሁ አሮጌው ሁሉ አልፏል::  ከህግ  እርግማን ተዋጅቻለሁ:  የእዳውም ጽህፈት ከፊቴ ተወግዷል::  የእግዚአብሔር መንፈስ ባለበት በዛ አርነት አለ:: አሜን በነፃነት እመላለሳለሁ ልጅ ነኝና ከሰማይም ልጁን ለመምስእል የሚያስፈልገው ሁሉ የተሰጠኝ ነኝ::  በመጨረሻም:-
1ኛ ዮሐንስ 32፤ ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን። አሜን!!

ምክር

1ኛ ቆሮንቶስ 11: 2-16

ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። 
ያስተማራቸውን ወግ ቤተክርስቲያንዋ በደንብ እንደያዘች ጠቅሶ ያመሰግናቸዋል::  ይህንን የሚለው ከፃፉለት ደብዳቤ ላይ ነው::  እርሱ ወደ ሌላ ስፍራ ለአገልግሎት ሲሄድ ጥያቄ ተነሳ እንዴትም ማድረግ እንዳለባቸው እየጠየቁት ነው በደብዳቤያቸው ላይ::  ጥያቄውም ስለ ባህላቸው ነው::  ሙሉ በሙሉ እንተወው ወይስ ምን እናድርግ የሚል አይነት::  የጳውሎስ መልስ:-

1.  ሴት እንድትሸፋፈን 

2.  ወንድ ደግሞ እንዳይሸፋፈን ይነግራቸዋል::  ለምሳሌ:- አሁን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሰዎች ብንመለከት ሴት ትሸፋፈናለች ገና ለገና ወደ ጌታ መጥቻለሁ ብላ ፀጉሯን ለቃ መሄድ ከማህበረተሰቡ ተጽዕኖ የተነሳ አትችልም እስዋም አይመቻትም እነዚህም የቆሮንቶስ ሰዎች ባህላቸው ይህን ይመስላል::  ይህ ግን በሌላ ስፍራ ህግ እንዳልሆነ ጳውሎስ ይነግረናል::
ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም። 
እኛ ዛሬ ይህ ጥያቄ የለብንም ነገር ግን አንዳንድ ቦታ ላይ ተተግብሮ አይተን ጥያቄ ቢፈጥርብን መልሱ ህግ አይደለም የሚለው ነው::  እውቀትን ከማጣት የተነሳ በማይረባ ክርክር የጌታን ቤት ስራ አናዘግይ::  ሁልጊዜ ልናስብ የሚገባን ጌታን ደስ ስለማሰኘትና መንግስቱን ለማስፋት ይሁን::

የጌታ እራት

1ኛ ቆሮንቶስ 11: 17-34
ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤ 
ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም፡— እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡ አለ። እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ፡— ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት፡ አለ።
የጌታን እራት ለምን እንወስዳለን? 

1.  ለመታሰብያዬ አድርጉት ስላለን

2.  እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እንድንናገር

3. ህብረት እንድናደርግ (ሐዋርያት ስራ 2:42-47)

4.  የሚያስተሳስረን ስለሆነ (1 ቆሮንቶስ 10:15-17)


የሚጎዳንስ እንዴት ነው?
1.  ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም  የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት

2.  ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ 

3.  የረሀብ ማስታገሻ አይደለም – ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ።
ፍርዱስ ምንድነው በአግባቡ ባለመውሰዳችን?
ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል
እንግዲህ እንዴት እንዘጋጅ የጌታን እራት ለመውሰድ?
1.  ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም     ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ 

2. ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ 

3.  ስለዚህ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ
ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን።
ይህ ማለት ፈርተን አንውሰድ ማለት ነው አረ እይደለም ለመውሰድ እንበረታታ ከጌታ እና ከቅዱሳን ጋር ህብረት ማድረግ መልካም ነውና::

ምዕራፍ 12

የመንፈስ ቅዱስ አሰራር

1ኛ ቆሮንቶስ 12: 1-6
ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። 

1.  የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ 

2.  አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ 

3.  አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን  በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 
ለመንግስቱ ስራ ጌታ በተለያየ መንገድ ልጆቹን ይጠቀምብናል::  ከላይ እንደተመለከትነው የጸጋም ስጦታ፤ አገልግሎትና አሰራር የተለያዩ ናቸው ያንን ውበት ያመጣው ጌታ ግን አንድ እግዚአብሔር ነው::  በአካሌ ውስጥ የተለያዩ ብልቶች የተለያየ ስራ ይሰራሉ የሚያገለግሉት ግን እኔን ነው::  እንዲሁ በክርስቶስ አካል ውስጥ የተለያየ አሰራር ቢገለጥ እየተገለገለ ያለው ጌታ እየሱስ ነው እኛ አንድ አካል ነን አንዱ ስራውን በትክክል ካልሰራ ሌላው አካል ሁሉ ይታወካል::  ስለዚህ በእያንዳንዳችን ውስጥ እንደሚሰራው አሰራሩ እንታዘዝ::በአንዱ ውስጥ እንደዚህ በሌላው ደግሞ እንደዛ የሚሰራ ጌታ ነው ካልን ዘንዳ ታድያ ለምን ጸጋን እናወዳድራለን?  በእኔ ላይ ጸጋ የለም ወይንም ብዙ ለውጥ አላመጣምን ምን አመጣው?!  ያ መርዘኛ አስተሳሰባችንን በክሎት እኮ ነው እንጂ ያለ ስራ የሚቀመጥ ስራ ፈት ልጅ ጌታ የለውም!!!!  ወደ እርሱ በመጣን ቀን እንደዚህ በአንተ/በአንቺ እሰራለሁ ብሎ መቷል:: እናስተናግደው!!
ምንም ይሰራ ምን የሚሰራው ጌታ ነው::  ተመኙ ብንባል የምንመኛቸውን አገልግሎቶች መገመት ቀላል ነው ግን ውስጣችን ያለውን ጸጋ አክብሮ መገለጥ ደግሞ ታላቅ ጥበብ ነው::  የማንንም ጸጋ ሳታወዳድሩ እኔን ላከኝ እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ ምክንያቱም ጌታን ከጌታ ጋር ማወዳደር ነውና ጸጋን ከጸጋጋር ማወዳደር:: ጌታ ማስተዋልን ይስጠን! 

መንፈስ ቅዱስን መግለጥ

1ኛ ቆሮንቶስ 12: 7
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። 
እዚህጋ ቃሉ እንደሚለን ለእያንዳንዱ (አስምሩልኝ ለእያንዳንዱ ላይ) መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለጥቅም ይሰጠዋል::  መቼም የሚያስተን ሰው ካልፈለግን በስተቀር በግልጽ ነው የተነገረን እያንዳንዳችን ለጥቅማችን ሲባል የተሰጠን ስጦታ አለ ማለት ነው::  የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ልክ እንደ ክሪስማስ ትሪ ውሰዱት መቶ ያስውባል ስለዚህ ከመንፈስ ፍሬ በጣም ይለያል::  አንዳንዴ ሰዎች ድንቅና ተአምራት እየተሰራባቸው ህይወታቸውን ቀርበን ስናይ ያስበረግጋል ምክንያቱ ፀጋ ለመቀበል መዳን ብቻ ይበቃል ለጥቅማችን መቶ ሊረዳን ማለት ነው:: 
ለመንፈስ ቅዱስ በጣም መጠንቀቅ እንዳለብን ቃሉ ይነግረናል::  እርሱ እያንዳንዳችንን ሊያንፅ መቷል:: መሳሪያ ሳንታጠቅ አይደለም ወደ ውጊያ የገባነው ታጥቀናል ስሙ ይባረክ::  እርሱ እሩቅ ሆኖ የምንጠራው ጌታ ወይም ሌሎች ሲፀልዩልን የሚሰማ ከመሰለን ተሳስተናል እርሱ የቅርብ ጌታ ነው:: በፊቱም ተሰሚነት አለን::  አሜን!
ዛሬ እጆቻችንን ዘርግተን እናመስግነው ወደኛ ሊረዳንና ለጥቅማችን የተሰጠንን ጌታ::

የመንፈስ ቅዱ ስጦታዎች

1ኛ ቆሮንቶስ 12: 8- 11
መንፈስ ቅዱስ ለማነጽና ለጥቅማችን እንደተሰጠንና የጸጋ ስጦታዎችን ማወዳደር ልክ እንዳልሆነ አይተናል::  ሌላው ቀርቶ በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር እየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው ማለት እንኳን አይቻልም::  ከዚህ በታች ስጦታዎቹን እንያቸው:-
1.  ጥበብን መናገር

2.  እውቀትን መናገር

3.  እምነት፥ 

4.  የመፈወስ ስጦታ፥ 

5.  ተአምራትን ማድረግ፥ 

6.  ትንቢትን መናገር፥ 

7.  መናፍስትን መለየት፥ 

8.  በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ 

9.  በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም 
ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። 
ይሄ ሁሉ የተሰጠው የአካሉን ወይም የቤተክርስቲያንን ደህንነት ለመጠበቅ ነው::

የክርስቶስ አካል ናችሁ 

1ኛ ቆሮንቶስ 12: 12-27
እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 
አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። 
አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። 
ስለዚህ አንዱ ብልት ሌላውን አታስፈልገኝም ቢለው ወይም ደግሞ እኔ ይህንን ነኝና የአካል ክፍል አይደለሁም፡ ቢል ይህን በማለት የአካል ክፍል መሆን ይቀራልን? አካል ሁሉ አንድ አይነት  ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ?  አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል።  ስለዚህ ማየት ያለብን አካሉን እንጂ አንድ ብልትን መሆን የለበትም::
ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። ከዚህ ክፍል የሚቀርልን- ከአንዱ መንፈስ ጠጥተናል በአንድም አካል ውስጥ እግዚአብሔር አገጣጥሞናልና ሌላው አያስፈልገኝም ወይም እኔ በቂ ነኝ ብሎ ነገር የለም የሚለውን ነው::  አንዱ የሰውነታችን ክፍል ተለይቶ ቢወጣ የወጣ ጊዜ ሞቷል መበስበስ ነው ውጤቱ እዚህም ጋ የምናየው ይህንኑ ነው::  ክርስትና ከአካሉ ውጪ የለም ለመሞት ካልሆነ በቀር::  ጌታ ማስተዋልን ይስጠን! 

ስጦታዎችን ለቤተክርስቲያን ሰጠ

1ኛ ቆሮንቶስ 12: 28-31
ከዚህ በፊት የተለያዩ ስጦታዎችን እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን እንደሰጠ አይተን ነበር::  የሚከተሉትም ስጦታዎችን በተጨማሪ ተሰተዋል:-
1. ሐዋርያትን፥

2. ነቢያትን፥ 

3.  አስተማሪዎችን፥ 

4.  ተአምራት ማድረግን፥

 5.  የመፈወስን ስጦታ፥ 

6.  እርዳታንም፥ 

7.  አገዛዝንም፥ 

8.  የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል
ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን? ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ። 
ምንም እንኳን መጀመሪያ ይህንን ቀጥሎም ይህንን ስጦታ ሰጠ ቢለንም አንዱን ስጦታ ከሌላው ማወዳደር ልክ እንዳልሆነ አይተን ነበር::  እርሱ እንደወደደ ስጦታን በእኛ ውስጥ ያስቀምጣል መስራት የምንችለውን በጥሩ ሁኔታ የምንወጣውን ስለሚያውቅ የሚሰጠን ስጦታ ቅዱሳንን የሚጠቅም አካሉንም የሚያንጽ ነው:: 
እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ ስለማይለዋወጥ ቤተክርስቲያንም ገና ስላልተነጠቀች ዛሬም እነዚህ ስጦታዎች በሙሉ በስራ ላይ ናቸው::  አካሉን ለማገልገል ተሰተዋል::  ስለዚህ የተሰጠንን ስጦታ ጠንቅቀን እንወቅ ነው ምክሬ::

የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ

1ኛ ቆሮንቶስ 12: 31-13:1-3

ያለፈውን ምዕራፍ ሐዋርያው የዘጋው የሚበልጥ መንገድ ላሳያችሁ ብሎ ነው::  ምንድነው የሚበልጠው መንገድ?
ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ። 
1.  በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር 

2. ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ 

3.  ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ 

4.  ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ 

5.  ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥሰው እነዚህን ካደረገ መቼም የምንለው መልአክ የሆነ ሰው ብለን እንመድባለን::  ልክ ነው ይህ ሁሉ ጥሩ ነው ነገር ግን ፍቅር ከሌለበት ሐዋርያው እንደሚለን  
ፍቅር ግን ከሌለኝ

1.  እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል  ሆኜአለሁ። 

2.  ከንቱ ነኝ።

3.  ምንም አይጠቅመኝም። 
ይሄ ሁሉ ስራ ዜሮ ገባ ማለት ነው::  ጌታም ያለን እኮ ደቀመዝሬ መሆናችሁ የሚታወቀው በፍቅር ነው ብሎናል::  
እግዚአብሔር ፍቅር ነው እንጂ ፍቅር አለው አልተባልንም::  ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው::  የተቀበልነውም መንፈስ የፍቅር መንፈስ ነው::በፍቅር እንመላለስ!  ክፋትን ሁሉ እናስወግድ!

የፍቅር ባህሪያት

1ኛ ቆሮንቶስ 13:4-7
ፍቅር :-

1.  ይታገሣል፥ 

2. ቸርነትንም ያደርጋል፤ 

3.  አይቀናም፤ 

4.  አይመካም፥ 

5.  አይታበይም፤ 

6.  የማይገባውን አያደርግም፥ 

7.  የራሱንም አይፈልግም፥ 

8.  አይበሳጭም፥ 

9.  በደልን አይቆጥርም፤ 

10. ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለዓመፃ ደስ አይለውም፤ 

11. ሁሉን ይታገሣል፥ 

12. ሁሉን ያምናል፥ 

13. ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ 

14. በሁሉ ይጸናል። 
እስኪ ራሳችንን በእነዚህ ባህርያት ውስጥ እንየው::  ካላገኘናቸው ውስጣችን እንጸልይ::  ፍቅር ከሁሉ የሚበልጥ ነውና::  እራስን መካድና መስቀሉን ተሸክሞ መመላለስ ጌታን ብቻ ማሰብ እርሱንም በሙሉ ሀይላችን መውደድ ባልንጀራችንንም እንደራሳችን መውደድ ያስፈልጋል::

ፍቅር አይወድቅም/ይበልጣል

1ኛ ቆሮንቶስ 13: 8-13
ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ የሚበልጠው ፍቅር ነው
ለምን አይወድቅም ለምንስ የሚበልጥ ነው?  ብለን ስንል ፤  ይህ ዓለም ያልፍና ወደ ማያልፈው ሙሉ እውቀት ወዳለበት ወደ ዘላለም ቤታችን መግባት ስላለ በዛኛው ዓለም 
ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። 
ፍጹም ወደሆነው አገር ስንገባ በድንግዝግዝ መኖር ይቀራል::  ሃሌሉያ!  እንዴት የሚናፈቅ አገር ነው የወረስነው?
ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ። 
እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። ፍቅር ይበልጣል ደግሞም አይወድቅም!!  ጌታን መምሰል እራሳችንን እናስለምድ ፤  በፍቅር እንመላለስ ፤  ከፍቅር በቀር እዳ እንዳይኖርባችሁ ተብለናልና::  ይህን ለማድረግ በአእምሯችን መታደስ እንለወጥ ፤  ቃሉ ህይወትም ነው መንፈስም ነው ፤  የሚሰራ ነውና የማይገባን ያስወግዳልና ቃሉን በመንፈስ ከእኛ ጋር ይዋሀድ አለበለዚያ አይጠቅመንም::  በቃሉና በፀሎት እንትጋ::

ምዕራፍ 14

ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ

1ኛ ቆሮንቶስ 14: 1-6

ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ። 
ትንቢትን ልትናገሩ ግን ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ፤ ማኅበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጐም በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል። 
ለምን ያልን እንደሆነ:-
1.  ለማነጽ 

2. ለመምከር 

3.  ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል

4. ማኅበሩን ያንጻል
በልሳን መናገርስ ጥቅሙ ምንድነው?
1.  በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና፥ በመንፈስ ግን ምሥጢርን ይናገራል፤ 
2.  በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል 
ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር፥ አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ? 
ስለዚህ እራሳችንን ለማነጽ በልሳን እንናገር ጉባኤን ለማነጽ ደግሞ ትንቢትን እንናገር::
የጸጋ ስጦታዎችን እንድንጠቀም አበረታታችኅለሁ ለጥቅማችን ተሰጥተውናልና:: እርስ በርሳችን እንተናነጽ፥ እንጽናና ፥ እንበረታታ::
የእየሱስ መንፈስ የትንቢት መንፈስ ነው::  አሜን!

መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ ፈልጉ

1ኛ ቆሮንቶስ 14:12-25
መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ 1.  ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ2. በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ
እዚህጋ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ መተርጎምም እንድትችሉ ጸልዩ እያለ ነው ሐዋርያው የሚነግረን::  
እስኪ በልሳን መፀለይን እንይ

1.  መንፈሴ ይጸልያል 

2.  አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። 

3.  ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ 

4.  እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች      ቢገቡ፡— አብደዋል፡ አይሉምን? 
ትንቢትስ?

1.  ትንቢት ለሚያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለማያምኑ አይደለም።

2.  በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ። 

3.  ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤  በልቡም የተሰወረ ይገለጣል፥ እንዲሁም፡— እግዚአብሔር  በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ  እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። 
እንግዲህ: በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ
እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም። 
ስለዚህ ወገኖቼ የጸጋ ስጦታን በብርቱ እንፈልግ በተለይም ትንቢትን መናገር ምክንያቱም ብዙዎችን ያንጻል ያጽናናልም::  አገልግሎት ግን በፍቅር መሆን እንዳለበት እንወቅ::  ጥያቄው ስንቶችን አጽናናህ ሳይሆን ስንቶችን ወደድክ ነው::  በስምህ አጋንንት አላወጣንም እንደዚህና እንደዚያ አላደረግንም?  የሚሉ በመጨረሻ እንዳሉ ቃሉ ይነግረናል::  ጸጋው ሚዛን አይደፋም በስተመጨረሻ በእሳት የሚያልፈው አገልግሎታችን የመንፈስ ፍሬ ነውና ፍቅርን እንከታተል ትዕግስትን እናክልእራስን መግዛት እና ሌሎችንም የመንፈስን ፍሬ እናፍራ::

መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ ፈልጉ

1ኛ ቆሮንቶስ 14:12-25
መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ 

1.  ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ  እንዲበዛላችሁ ፈልጉ

2. በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ
እዚህጋ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ መተርጎምም እንድትችሉ ጸልዩ እያለ ነው ሐዋርያው የሚነግረን::  
እስኪ በልሳን መፀለይን እንይ

1.  መንፈሴ ይጸልያል 

2.  አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። 

3.  ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ 

4.  እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው  ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና  ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች   ቢገቡ፡— አብደዋል፡ አይሉምን? 
ትንቢትስ?

1.  ትንቢት ለሚያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለማያምኑ አይደለም።

2.  በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ። 

3.  ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤  በልቡም የተሰወረ ይገለጣል፥  እንዲሁም፡— እግዚአብሔር  በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ  እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። 
እንግዲህ: በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ
እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም። 
ስለዚህ ወገኖቼ የጸጋ ስጦታን በብርቱ እንፈልግ በተለይም ትንቢትን መናገር ምክንያቱም ብዙዎችን ያንጻል ያጽናናልም::  ስናገለግልም በፍቅር መሆን እንዳለበት እንወቅ:: 
ስንቶቻችን ግን ትንቢትን መናገር እንለማመዳለን?  ይሄ ጸጋ ሊገለጥ ይገባዋል::  እንጸልይ ጸጋውም ካላቸው ጋር እንማከር ምናልባት በውስጣችን እያለ ለመጠቀም አላወቅንበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ::  

ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን

1ኛ ቆሮንቶስ 14: 26-40
ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን። 
አምላካችን የስርዓት አምላክ ነው ወጥ የሆነ ስራ እንጂ የተዘበራረቀ ነገር የለውም::  ስለዚህ ቤቱ በስርዓት ለማነጽ እንዲሆን ይፈልጋል::
በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። 
ከዚህ የምንረዳው በጉባኤ ስንሰበሰብ ለእያንዳችን (አስምሩልኝ እያንዳንዱ ላይ) የሚሰጥ ነገር አለ ማለት ነው አሰራሩ ሲገለጥ ውበቱ ይታያል::  ተለማምደናል?  ወይስ ችላ ብለናል? እርሱ ታማኝ ነው ሰቶናል ስለዚህ ረጋ ብለን እናስተውልና እንደተሰጠን ጸጋ እንገለጥ::
በልሳን የሚናገር ቢኖር 1. ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው      በተራቸው ይናገሩ 2.  አንዱም ይተርጉም፤ 3.  የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር       መካከል ዝም ይበልና ለራሱና       ለእግዚአብሔር ይናገር። 
ነቢያትም 1. ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ     ሌሎችም ይለዩአቸው፤ 2. በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ      ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም      ይበል3.  ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም      እንዲመከሩ ሁላችሁ      በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ      ትችላላችሁ። 4.  የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት       ይገዛሉ፤ 
እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው። 
ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤ ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ። 
ወገኖቼ አበረታታችኅለሁ የጸጋን ስጦታ እንድትለማመዱ ትርፋማ ያደርጋልና ደግሞም እየበዛ ይሄዳል::

ምዕራፍ 15

የክርስቶስ ወንጌል

1ኛ ቆሮንቶስ 15:1-4
እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን፡ ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፡-
መጽሐፍ እንደሚል፡ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል፡ በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ሃሌሉያ!!!!  ሃሌሉያ!!!!   ሃሌሉያ!!!!አሜን!
በዚህም ምክንያት ይህ የምስራች ወደ እኛ ወንጌል ሆኖ ደረሰልን::  በዚህም ወንጌል የሆነልንን እንይ:-
ወንድሞች ሆይ፥ 1.  የሰበክሁላችሁን 2.  ደግሞም የተቀበላችሁትን 3.  በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን4.  በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን      ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ 
በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። 
ይሄ ወንጌል በሌላ አባባል ሞትና ትንሳኤው:-  ተስበክን፤  ተቀበልነው፤ ቆምንበት እናም ዳንበት::  አሜን!
በወንጌል ተለወጥን፥ ወደ ፍቅሩም መንግስት ፈለስን፥  የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ተጠራን፥ በሰማይም ዕርስት ይጠብቀናል እኛ አገራችን በሰማይ ነው::  ድነናል ይህንን ማንም እንዲያረጋግጥልን እስከማያስፈልግን ድረስ በቃሉ ዛሬ አንበነዋል ስለዚህ ሳትናወጡም ቁሙ!  የዚህ ወንጌል አገልጋይ መሆን እንዴት ትልቅ ክብር ነው::እንግዲህ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?  ማንም! 

የትንሳዔ ምስክሮች

1ኛ ቆሮንቶስ 15: 5-11
የክርስቶስ ትንሳዔ በምስክር የጸና ነው ከዚህ በታች እንደምናየው ከተነሳ በኃላ ለብዙዎች ታይቷል::
1.  ለኬፋም ታየ 

2.  በኃላም ለአሥራ ሁለቱ፤ 

3.  ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ       አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ 

4.  ለያዕቆብ 

5.  ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤

6.  ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። 
እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 
እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ።  አሜን አምነናል!
ሐዋርያው እዚህ ጋር የቀደመውን ህይወቱን ያነሳል ሐዋርያ ልባል የማይገባኝ የቤተክርስቲያን አሳዳጅ ቅዱሳንንም የማስር ነበርኩኝ ይለናል::  ይሄ ሁሉ ግን ወደ ጌታ ለመምጣትና ከሁሉ በላይ ለማገልገል አላገደውም ምክንያቱም አሮጌው ሁሉ አልፏል ሁሉም አዲስ ሆኗል::  ባለፈው ነገራችን እየተወቀስን ያለን ካለን እርሱ አልፏል አሁን ምህረትን ያገኘን ነን::  ይልቁንስ በጠላት ሽንገላ የተሰጠንን ጸጋ እንዳናባክን እንጠንቀቅ::  እኛ ተሻግረናል ሌሎችን የማሻገር አገልግሎት ተሰቶናልና ተነስተን የጠላትን መንደር እናሸብር!!  ሃሌሉያ!
ተነስቷል የሚለውን ዝማሬ እጋብዛችኃለሁ::

ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአል

1ኛ ቆሮንቶስ 15: 12-23
ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን፡ ከእናንተ አንዳንዶቹ፡— ትንሣኤ ሙታን የለም፥ እንዴት ይላሉ? ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ 
1.  ስብከታችን ከንቱ ነው  እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ 

2.  ደግሞም፡— ክርስቶስን አስነሥቶታል፤ ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች      የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ 

3.  ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም። 

4.  ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ 

5.  ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ  ጠፍተዋላ። 

6.  እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። 
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 
አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።  አሜን!

1.  ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ  ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። 

2. ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። 
ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው::ወገኖቼ ተስፋ እንደሌላቸው እንዳንሆን ትንሳኤ የሚጠብቀን ነን::  ክርስቶስ ከሙታን በመነሳቱ እኛንም ያስነሳናል ደግሞም የህያው ጌታ አገልጋዮች ነን::  ትንሳኤንና ድልን እናውጃለን::  አሜን!

አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም ይሽራል

1ኛ ቆሮንቶስ 15:24 – 34
በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።  አሜን! 
ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። 
የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ 
ስለዚህም እንላለን ሞት ሆይ መውጊያህ የታል? 
ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፡— ሁሉ ተገዝቶአል፡ ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። መቼም ሁሉን የሚያስገዛው አይገዛም እርሱም እግዚአብሔር አብ ነው::
ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል። 
እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? 
አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 34፤ በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። 
ሁሉን ከእግሩ በታች ይረግጣል የኛ እረኛ::  እርሱ ከሁሉም በላይ ነው ዛሬ ከበበን ብለን እውይ የምንለው እርሱ ጋር ሲደርስ እንደ እርጥብ ጠፍር የሚወድቅ ነው::  አሜን!

እየሱስ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው

1ኛ ቆሮንቶስ 15: 35-45

ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። 
ይሄንን ጥያቄ በሁለት እንክፈለው::  የመጀመሪያው እራሱ ትንሳኤ እንዴት ይኖራል የሚሉ ሰዎች ጥያቄ ነው ሰው ከሞተ ሞተ የሚሉ ናቸዉ የመለሰላቸውን እንይ::
አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል። 
ሞኝ ብሎ ነው አወቅን የሚሉትን የሚጠራው በአእምሯችን ከተመራን የእግዚአብሔርን ነገር ማወቅ እንደማንችል እኔና እናንተ በደንብ ጠንቅቀን እናውቃለን:: ስለዚህ ፍጥረትን በመመልከት እንኳን ይህን ጥያቄ መመለስ እንደሚቻል ነው ያስቀመጠው::  የእንስት ስጋ እንኳን ይለያያል የዓሳ ከበሬ የበሬው ከበግ እና ለእግዚአብሔር የተለየ አድርጎ ማስነሳት እንዴት ይሳነዋል እያለ ያስረዳል ሐዋርያው::  በሌሎችም በብዙ ማስረጃ:: 
ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ የመጉዋጋት ጥያቄ ነው::  ምን እንደምንመስል ነው:: መልሱ እንይ:-
ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው። የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። 
ስለዚህ ወገኖቼ ይህንን እናስተውል አሁን በድካም እየዘራን ነው በኃይል እንነሳለን::  እንዲሁ ደግሞ፡— ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ፡ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። እየሱስ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ እንደሆነ እናስተውል ከእርሱም ጋር አብረን የምንሰራ እንደሆንም አንዘንጋ::  አሜን 

የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም

1ኛ ቆሮንቶስ 15: 46-58
አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፡— ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። 
የማይበሰብሰውን የምንወርስ እኛ እንደምንለወጥ ቃሉ ይነግረናል ይሄ የለበስነው ስጋ የማይበሰብስ ሆኖ ይለወጣል እንጂ በዚህ ድካም በሞላበት ስጋችን መንግስተ ሰማያትን አንወርስም::  ወይም ደግሞ መለከቱ ሲነፋ በህይወት ከሆንን ከመቅጽበት የማይበሰብሰውን እንለብስና እንለወጣለን::  ሃሌሉያ!!
ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፡— ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ፡ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ 
አሜን ሞት መዋጥ ብቻ ነው የሚያውቀው ያኔ ግን ይዋጣል፥ የሚወጋበት ሕግ ይወሰዳል ሐጥያትም አይኖርም ፥ ስለዚህ ሞት  አይቀማም ፥ አያስጨንቅም ፥ ድልም አይነሳም ፥  ይሸነፋል ደግሞ ላያገግም ለመጨረሻ ጊዜ ይሰናበታል::  ሃሌሉያ!!  አሜን! ያ ቀን እንዴት ያለ ቀን ነው ሞትን የምንቀብርበት?!  እስከዛሬ ወግተሀል በቃህ!! የሚባልበት ኦ ያ ቀን! የማይበሰብሰውን አካል የምንወርስበት ምን አይነት ቀን!  ጌታ ሆይ ተመስገን ፈጽመህ የምትበቀልበት ቀን አለና አመሰግንሀለሁ!  አሜን!

ድል መንሳት ተሰቶናል

1ኛ ቆሮንቶስ 15:57-58
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን!
ያለንን ነገር ጠንቅቀን ማወቅ አለብን እርሱም እዚህጋ እንደተጻፈው ድል መንሳት ነው::   የሰጠን ማነው? እራሱ እግዚአብሄር ነው::  ግን ድል ዝም ብሎ ተነስቶ የሚሰጥ ጉዳይ ነው እንዴ?  አረ አይደለም ድሉ የመጣው ውጊያ ተደርጎ ነው: :  እየሱስ ስሙ ይባረክና እዳችንን ሁሉ በመስቀል ተሸክሞ ሞቶ ከሙታንም ድል ነስቶ ድለተነሳ ነው ይሄ ድል የመጣው::  ይሄስ ድል ለኔ እንደሆነ በምን አውቃለሁ?  ብንል አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ::  አትዮጵያ ጣልያንን ስታሸንፍ ነበርን እንዴ? ዛሬ ግን ለማንም ባርያ አልሆንም እያልን እራሳችንን እዛ ድል ውስጥ አድርገን እንቆጥር የለም እንዴ?  ታድያ እኛ እኮ ዛሬ የሰማያዊዉ መንግስት አካል ነን::  ልንፎክርና እራሳችንን እዛ ውስጥ ማየት ግድ ይላል እርሱአባታችን እኛም ደግሞ ልጆች ነን::እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል እየሰማንአለን አሁን እምነታችንም እየጨመረ ነው::  ስለዚህ አዋጅን እናውጃለን:- 
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን!
ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን 1.  አውቃችኋልና 2.  የምትደላደሉ፥ 3.  የማትነቃነቁም፥ 4.  የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ። 
ምንም ሳንሰራ በማመን ብቻ የተሰጠንን ድል እያጣጣምን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ እንሂድ እያለን ነው::  ስለዚህ ድላችንን አውቀናል፥ እንጸናለን፥ አንነቃነቅም የጌታም ስራ ይበዛልናል::  ጠላት በየጊዜው መቶ መሰረታችንን እንድንቆፍር አያድርገን::  ኢትዮጵያዊ አይደለሽም ብሎ ለሚከራከራችሁ ማስረጃችሁ ምንድነው?  ማስረጃው ከመብዛቱ የተነሳ መሳቅ አይቀናንም ብላችሁ ነው?  እንዲሁ ርግጥ ያለእን ማንነታችንን በክርስቶስ እንያዝ ድላችንንም እናውጅ:: 

ምዕራፍ 16

የመጨረሻ ምክር

1ኛ ቆሮንቶስ 16:1-24
በመዝጊያው በዚህ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚመክረን
1.  ንቁ

2.  በሃይማኖት ቁሙ፥ 

3.  ጎልምሱ 

4.  ጠንክሩ እናም

5.  ሁሉ በፍቅር ይሁን በእናንተ ዘንድ ይለናል:::
ስለዚህ ወገኖች የእኛ ስርና መሰረት በፍቅር የጸና ይሁን በፍቅርም ላይ እንደግ ፥  እንጠንክር::
ሌላው የሚመክረው ነገር ለቅዱሳን ገንዘብን ስለ ማዋጣት፥ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።  
ይህንን እኛም ልንከተለውና ቅዱሳን ችግር ሲገጥማቸው መርዳትን እናብዛ::
በማጠቃለያ እንዲህ ይላል:-
ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። 
ጌታችን ሆይ፥ ና። አሜን ቶሎ ና!  ማራናታ!
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። አሜን!